Telegram Web Link
=>+"+ አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ልጆች ሆይ! አብን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ብርቱ ስለ ሆናችሁ: የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር: ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላቹሃለሁ:: +"+ (1ዮሐ. 2:13)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
እንኩዋን ለአጋእዝተ ዓለም "ሥላሴ" እና "ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ሥሉስ ቅዱስ "*+

=>ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::

+እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም: በአካል: በግብር ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::

+ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በሁዋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::

+ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርሕ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት: ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::

+እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ያውቃል::

=>በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው:: አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም:: የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን : በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ: መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ: ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::

=>በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ 2 ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::

+*" ሕንጻ ሰናዖር "*+

=>ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::

+ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::

+ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::

+መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::

+ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::

+ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::

+" ቅዳሴ ቤት "+

=>ልክ የዛሬ 324 ዓመት: አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት: (በ1684 ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::

+ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ ንጉሥ ነውና::

+ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ/ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::

+*" ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ "*+

=>የሊብያው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: 2348 ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::

+ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::

+እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::

+እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና መገለጫ እንመልከት::

1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለ22 ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው)

2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለ50 ዓመታት የተጋደለና ለ15 ዓመታት በስደት የኖረ ነው)

3.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው)

4.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው)

5.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጉዋድ ውስጥ ለ15 ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው)

6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕጻንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው)

7.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው)

8.ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ: ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው)

9.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው)
+እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::
+ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ:-
(ኢሳ. 9:6, መዝ. 46:5, 77:65, ዘካ. 14:4, ዮሐ. 1:1, 10:30, ራዕይ. 1:8, ሮሜ. 9:5 . . .)
አርዮስና የዛሬ መሰሎቹአንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::

+በወቅቱም በመወገዙ አርዮስ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውንት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::

+በ325 ዓ/ም (በኛው በ318 ዓ/ም) ለ40 ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በ4ቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ: ሶል ዼጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::

+በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት::

+በጉባኤው መጨረሻም አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ:: አባቶችም ሥራቸውን ከጨረሱ በሁዋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል::

+ቅዱስ ሶል ዼጥሮስም ከጉባዔው ከተመለሰ በሁዋላ በጐ ጐዳናውን አቅንቶ ቀጥሏል:: ብዙ ድርሳናትን ደርሶ: በድካም ሰብኮ ኢአማንያንን መልሷል:: ፈላስፎችንም ድል ነስቶ አሳምኗል:: መናፍቃን ደግሞ ፈጽመው ይፈሩት ነበር:: ሊቀ ዽዽስናን በተሾመ በ11 ዓመቱም በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁንና ጥር 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.በዓለ ሥሉስ ቅዱስ
2.ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ
3.ቅዱስ ኤፍሬም
4.ቅዱስ ሰሎሞን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
2.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
3.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
4.አባ ባውላ ገዳማዊ
5.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
6.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

=>+"+ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር: የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+ (ቆሮ. 13:14)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን:: †††

=>+"+ እንኩዋን ለቅዱሳን አበው "አባ መቃርስ" እና "ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ታላቁ ቅዱስ መቃርስ "*+

=>ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::

+በ4ኛው መቶ ክ/ዘ አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነ ንጉሳቸው አጥምቀዋል::

+በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን: ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

+ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::

=>ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ) የኖሩባት ቦታ ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::

+በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት አደረጉት::

+ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::

+በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ::

+ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::

+መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::

+ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል::

=>ይህቺ ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ስትሆን የተቀደሰችውም በ7ኛው መቶ ክ/ዘ በአባ ብንያሚን እጀ ነው::

+*" ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ "*+

=>ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

+ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27)

+ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ:: ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር:: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

+ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

+ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

+ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት 15ቱ አበው ነቢያት: 4ቱ ዐበይት ነቢያት: 12ቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

=>"15ቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ

*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

=>"4ቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

=>"12ቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

=>"ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::

=>ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና

*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ:: በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)

*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
+ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
+ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ 1 ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::+ሚክያስ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ-እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::

+ቅዱሱ ነቢይ ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በ3ቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::

+አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ::"
(አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ካንቺ ዘንድ ይወጣልና) አለ::

+ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በሁዋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::

+ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: 7 ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹም ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::

=>አምላከ አበው ቅዱሳን ለተፋቅሮ ይበለን: ከበረከታቸውም ይክፈለንና

ጥር 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ
2.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ
3.አባ እንድራኒቆስ ሊቀ ዻዻሳት
4.አባ ብንያሚን ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>+"+ ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን? +"+ (ሚክ. 6:6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

=>+"+ እንኩዋን ለአበው "ቅዱሳን አባ አብርሃም ወአባ ገዐርጊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ቅዱሳን አብርሃም ወገዐርጊ "*+

+*" ተጋድሎተ ቅዱሳን "*+

=>ቅዱሳኑን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ በግእዙ:: ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው:: መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው::

+ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ:: ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ:: የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከ2 አካላት ጋር ነው:: በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖቸታችሁን ካዱ: ለጣዖትም ስገዱ" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው::

+በተለይ 2ኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል:: የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ::

+ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ:: ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ:: ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው: ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል::

+ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል:: ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው:: ፍቅረ መስቀሉን: የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው: የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም::

+ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው:: ጌታችን "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16:18) እንዳለው ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን::

+*" ገዳማዊ ሕይወት "*+

=>ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::

+አባ እንጦንስ አባ መቃርስን: አባ መቃርስ አባ ዮሐንስን ወልደዋል:: አባ ዮሐንስም የታላቁ ገዳመ አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በጸጋ አገልግለዋል:: አስቄጥስ በምድረ ግብጽ የሚገኝ: በስፋቱና ብዙ ቅዱሳንን በማፍራቱ ተወዳዳሪ የሌለው የዓለማችን ቁጥር አንድ ገዳም ነው::

+ሕይወተ ምንኩሰናም ወደ መላው ዓለም የተስፋፋ በዚህ ገዳም መናንያን አማካኝነት ነው:: በዚህ ገዳም ላይ የሚሾሙ አበው ደግሞ በብዛት መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸውና አባታቸውን ቅዱስ መቃርስ ታላቁን የመሰሉ ናቸውና ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ነው::

+በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ተወልደው ያደጉት አባ ዮሐንስ ከመነኑባት ዕለት ጀምረው በፍጹም ተጸምዶና ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ስለ ተገዙ የታላቁ ገዳም አበ ምኔት ሊሆኑ ተገባቸው::

+በአበ ምኔትነት ዘመናቸውም መንጋውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ደከሙ:: በተለይ ቅዱስ ቃሉን ያስተምሩ ዘንድ ተጉ:: ሕይወተ መላእክትንም ያሳዩ ዘንድ በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር ሆነው : ከመንፈሳዊ አብራካቸው ብዙ ቅዱሳንን ወለዱ::

+ከዋክብቱ አባ ገዐርጊ: አባ አብርሃም: አባ ሚናስ: አባ ዘካርያስ . . . የአባ ዮሐንስ ፍሬዎች ናቸውና:: ጻድቁ በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: ከዕረፍታቸው በሁዋላ እንኩዋ መግነዛቸውና የልብሳቸው እራፊ ብዙ ድውያንን ፈውሷል::

+*" ቅዱሳን አብርሃም ወገዐርጊ "*+

=>እነዚህ 2 ቅዱሳን በግብጽ በርሃ ያበሩ የቅዱሱ አባ ዮሐንስ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቹ ናቸው:: አስቀድሞ ወደ በርሃ የወጣ አባ አብርሃም ሲሆን እርሱም በምድረ ግብጽ የተባረኩ ሰዎች ልጅ ነው::

+ወላጆቹ በፈቃደ እግዚአብሔር እርሱን ከወለዱ በሁዋላ ብዙ በጐነትን አሳይተዋል:: ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የችግርና የረሃብ ጊዜ) ነበርና ሃብታቸውን በምጽዋት ጨርሰዋል:: የሚገርመው የቅዱሱ አባት "ነዳያን እየተራቡ ዝም አልልም" ብሎ እየተበደረ ያበላቸው ነበር::

+እርሱ ባረፈ ጊዜም የተባረከች ሚስቱ መልካምን እየሠራች ብዙ ተፈትናለች:: ለባርነት ተማርካ እስክትሔድ ድረስም ታግሣለች:: ቅዱሱን ልጇን አብርሃምንም እንደሚገባ አሳድጋ "ሚስት ላጋባህ" አለችው::

+እርሱ ግን "እናቴ ሆይ! እኔ ይህንን ዓለም አልፈልገውም" ሲል መለሰላት:: ይህንን ስትሰማም ሐሴትን አድርጋ አብርሃምን ወደ በርሃ ሸኘችው:: አባ አብርሃምም ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዶ በደብረ አባ መቃርስ መነኮሰ:: ተጋድሎንም በዚያው ጀመረ::

+ሲጾም: ሲጸልይ: ሲጋደልም ዘመናት አለፉ:: በዚህ ጊዜም ታላቁ አባ ገዓርጊ ከዓለም ወደ በርሃ መጥቶ መነኮሰ:: የአባ ዮሐንስ የመንፈስ ልጆች ውስጥም እንደ አንዱ ተቆጠረ:: አባ ገዐርጊን የተመለከተው አባ አብርሃምም ስለ ወደደው አብረው መኖር ጀመሩ::

+2ቱ ቅዱሳንም "በግቢግ" በምትባል በዓታቸው በፍቅር ለፈጣሪያቸው ሲገዙ ዘመናት አለፉ:: በነዚህ ዘመናትም በርካታ ቅዱሳን ከመንፈሳዊ አብራካቸው አፈሩ ከቅድስናቸው ብዛትም ከሰንበት በቀር እህልን አይቀምሱም ነበር::

+የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ቀን ከዓለት በተወቀረች በዓታቸው ውስጥ በጸሎት ላይ ሳሉ ወረደላቸው:: የበዓታቸውን ዓለት ሰንጥቆ ሲገባ ታላቅ ግርማና ብርሃን አካባቢውን ዋጠው:: ቅዱሳኑም ለመድኃኒታችን ተደፍተው ሰገዱ::

+እርሱ አነጋግሯቸው: ባርኩዋቸው ዐርጉዋል:: ለምልክትም በዓታቸው እንደ ተሰነጠቀ ቀርቷል:: ዘወትርም በዕለተ ሰንበት ይገለጥላቸው ነበር:: ቅዱሳን አባ ገዐርጊና አባ አብርሃም በርካታ ተአምራትን ሲሠሩ ኑረዋል::
+አባ አብርሃም ጥር 9 ቀን ሲያርፉ አባ ገዐርጊ ግንቦት 18 ቀን ዐርፎ ተቀብሯል:: በዓታቸው በግቢግም ዛሬ ድረስ በምድረ ግብጽ አለች::

=>አምላከ ቅዱሳን አበው በፍቅሩ ይገለጥልን:: ከአባቶቻች ጸጋ በረከትም አይለየን::

=>ጥር 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ አብርሃም ገዳማዊ
2.አባ ገዐርጊ ጻድቅ
3.ቅዱስ ዲዮስቅርስ ዘሮሜ
4.አባ ኪናፎርያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት
2.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
3.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

እንኩዋን "ለጾመ ገሃድ" እና "አባ ታውብንስጦስ" ዓመታዊ የእረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ጾመ ገሃድ "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው 7 አጽዋማት አሏት:: "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው:: የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል::

+"7ቱ" አጽዋማት:-
1.ዓቢይ ጾም
2.ጾመ ፍልሠታ
3.ጾመ ሐዋርያት
4.ጾመ ነቢያት
5.ጾመ ድኅነት
6.ጾመ ነነዌ እና
7.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ::

+በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ 9 ሰዓት ድረስ መጾም ይገባል:: ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት አለውና ይቆየን:: ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ አስፈላጊነቱ ነው:: "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ መጠየቁ ይቀላል::

+ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን መቃወም ነውና:: እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ አለች:: የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል እንከራከራለን::

+ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች በጣም ይገርሙኛል:: ኃጢአትን ለመሥራት: ጾምንም ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም:: እኛ ግን ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. 4:2) አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. 9:19, ነገ. 19:8, ሐዋ. 13:3, ቆሮ. 4:11) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን እንጾማለን::

=>"ገሃድ" የሚለው ቃል በቁሙ "መገለጥን : መታየትን : ይፋ መሆንን" የሚያመለክት ሲሆን በምሥጢሩ ግን "የማይታይ አምላክ መታየቱን : የማይዳሰሰው መዳሰሱን" ያመለክታል::

+ወይም በሌላ ልሳን ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም በተዋሕዶ ሰው ከሆነ በሁዋላ ለ30 ዓመታት ራሱን ሳይገልጥ ቆይቶ ነበርና በ30 ዓመቱ ራሱን ለእሥራኤል በዚህ ሰሞን መግለጡን ልብ የምንልበት በዓል ነው::

+መድኃኒታችን ሁሉን ነገር የሚሠራው በጊዜው ነውና ከሥጋዌው በሁዋላ ለ30 ዓመታት: ከስደት መልስ ደግሞ ለ25 ዓመታት የሰውነቱን ምሥጢር በይፋ ሳይገልጥ ቆይቷል:: ያም ሆኖ የሰውነቱን ምሥጢር እርሱ: የባሕርይ አባቱና ቅዱስ መንፈሱ ለድንግል ማርያም ገልጠውላት ታውቀው ነበር:: እርሷ ግን መዝገበ ምሥጢር ናትና ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር:: (ሉቃ. 2:52)

+መድኃኒታችን ከሥጋዌው (ሰው ከሆነባት) ደቂቃ ጀምሮ መግቦቱን አላቁዋረጠም:: ምንም በግዕዘ ሕጻናት ቢኖርም እርሱ በዘባነ ኪሩብ የሚሠለስ ቸር ጌታ ነውና መግቦናል::

+እንደ እሥራኤል ባህል 30 ዓመት በሞላው ጊዜ ግን ሥግው አምላክ መሆኑን ገለጠ:: የተገለጠውም በጥምቀቱ ሲሆን በዕለቱ ከአብ: ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን አስመስክሯል:: በባሪያው በዮሐንስ እጅም ተጠምቆ ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶልናል::

+የእዳ ደብዳቤአችን ቀዶ ልጅነታችንን መልሶልናል:: ይህ ሁሉ የተደረገ ለእኛ ነውና በዓለ ኤዺፋንያን (እለተ አስተርእዮቱን) በድምቀት እናከብራለን::

+ነገር ግን ልክ በቅርብ ጊዜ እያየነው እንደሚገኘው በዘፈንና ከአምልኮ ባፈነገጠ መንገድ እንዳይሆን ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች:: የመድኃኒታችንን የማዳን ሥራ ከማዘከርና ለእርሱ ከመገዛት ይልቅ ራስን ዘፈን በሚመስል መዝሙር መቃኘቱና ለልብስ ፋሽን መጨነቁ የሚጠቅም አይደለም::

+በዓላት በሚዲያ ታዩ: ተመዘገቡ ብለን ከመዝናናት ትውፊታችንን እያጠፉ ያሉ ድርጊቶቻችን ብንታዘባቸውና ብናርማቸው ይመረጣል:: ስኬታችን ሁሉም ክርስቲያን ለእግዚአብሔር መንግስት መብቃቱ እንጂ በዓል አከባበራችን ዝነኛ መሆኑ አይደለም::

+ጉዳዩ መለኮታዊ እንጂ ፓለቲካዊ አይደለምና ጥንቃቄን ይሻል:: ዛሬ ለታቦተ እግዚአብሔር ክብርን የማይሰጥና ተጋፊ ትውልድን እየፈጠርን ነው:: ካህናትን አለመስማትና ታቦታትን አግቶ አላስገባም ማለት በክርስትና ትርጉሙ ከሰይጣን መወዳጀት ነው:: ስለዚህም በዓል አከከባበራችንን እንታዘብ:: ደግሞም እናርመው::

+*" ጾመ ገሃድ "*+

=>ቤተ ክርስቲያን ጾመ ገሃድን የደነገገች ለ3 ምክንያት ነው:-

1.የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጥሙና እያሰብን በጾም እንድናመልከው::
2.በዓል አከባበራችን እንደ አሕዛብ በተድላ ሥጋ: በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳይሆንና ሰውነታችንን በጾም እንድንገራው::
3.ልደትና ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ሲውሉ እህል በነግህ (በጧት) መቀመስ ስላለበት የእርሱ ቅያሪ (ተውላጥ) እንዲሆን ነው::

+ጾመ ገሃድን የሠሩት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ ያጸኑት ደግሞ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው:: አጿጿሙም ጥምቀት ከማክሰኞ እስከ ቅዳሜ ከዋለ በዋዜማው "እስከ ይሠርቅ ኮከብ" እንዲሉ አበው እስከ ምሽት 1 ሰዓት ድረስ ይጾማል::

+በዓለ ጥምቀት እሑድ ሲሆን ዐርብን አዘክሮ: በዕለተ ቅዳሜ ደግሞ ከጥሉላት ተከልክሎ መዋል ይገባል:: በመሳሳይ ሰኞ ቢውል ዐርብን አዘክሮ: ቅዳሜና እሑድን ከጥሉላት (ከሚያገድፉ ምግቦች) ሁሉ ተከልክሎ መዋል ይገባል::

+ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ ነውና የተለየ ግለሰባዊ ችግር እስከሌለ ድረስ ሊጾም ግድ ይላል:: ችግር ካለ ደግሞ ከንስሃ አባት ጋር ሊመክሩ ይገባል::

+*" አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት "*+

=>በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም የተነሳ
+ከልጅነቱ መጻሕፍትን የተማረ:
+በክህነት አገልግሎቱ ለብዙዎች አባት የሆነ:
+በምናኔ ወደ ግብጽ የወረደ:

+በእስክንድርያ አካባቢ አበ ምኔት ሆኖ ብዙ መነኮሳትን የመራ::
+በዘመነ ሰማዕታት የተሰደደ:
+ብዙ አሕጉራትን ዞሮ ያስተማረ:

+በትምሕርተ ክርስቶስ ያላመኑትን አሳምኖ : ያመኑትን ያጸና:
+ሽፍቶችን እየገሠጸ ለንስሃ ያበቃ የነበረ ታላቅ አባት ነው::

+በዘመነ ሰማዕታት ስደትን ታግሦ: በሁዋላም በደብረ ሲሐት ተወስኖ ኑሯል:: በዚህች ቀንም በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::
=>አምላከ ቅዱሳን ፍቅሩን: ምሥጢሩን ይግለጥልን:: ከጾመ ገሃድ በረከትም አይለየን::

=>ጥር 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ጾመ ገሃድ
2.አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት
3.ቅዱስ ኪናርያ
4.ቅድስት ጠምያኒ

=>ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
7.ቅዱስ እፀ መስቀል

=>+"+ እነርሱ እሥራኤላውያን ናቸውና:: ልጅነትና ክብር: ኪዳንም: የሕግም መሰጠት: የመቅደስም ሥርዓት: የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና:: አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና:: ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ:: እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው:: አሜን:: +"+ (ሮሜ. 9:4)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
....✣...✣.....ከተራ .....✣....✣... ከተራራ ማለት ከተረ ከተረ ከበበ  አጠረ አገደ አቆመ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን  ከተራራ ማለት ማገድ ማቆም መክብብ ማጠር ማለት ነው ።
.......✣........✣......✣......

@@✣@@@✣@@@✣@@@@✣@@✣@@@@✣@@
.......✣.........✣........✣.....
ከተራ ስንል ሁለት ነገሮችን ለማሳታዎስ ነው

@@✣@@@✣@@@@✣@@✣@@@✣@@@@✣@@
..........✣........✣......✣.......
አንደኛ በክርስቶስ ጥምቀት ጊዜ የተደረገውን የታሪክ ክንዋኔ ለማስታወስ ነው ።

ክርስቶስ ሲጠመቅ  ነቢዩ ዳዊት " ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአት ድኅሬሁ፦ባሕርይ አይታህ ሸሸች ዮርዳኖስስም ወደኋላ ተመለሰ " ብሎ እንደተናገረ መዝ ፻፲፫
ዮርዳኖስ ከሁለት ተከፍሎ ቁሞ ነበርና የዮርዳኖስ ውሃ መቆሙን ለማስታወስ  "ከተራ" ክርስቶስ ሲጠምቅ ሰማያውያን መላእክት  ምድራውያን ዓሣ አንበሬዎች አዞት ጉማሬዎች ለማመስገን ለምስጋና ከበውት ቁመው ነበር ዮርዳኖስ ከዚህ በፊት የበጎች መኛ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ውቅያኖስን የፈጠረው አምላክ ሲጠመቅ ዮርዳኖስ በብርሃን ተከባ ስለነበር"ከተራ" እንለዋለን ።


@@✣@@✣@@@@✣@@@✣@@✣@@@@@✣@@
........✣......✣..............✣....
ሁለተኛ ለጥር ዓሥራ አንድ ቀን  የበረከተ ጥምቀት መጠመቂያ ውሃ
በገጠር ያሉ ክርስቲያኖች ወራጁን ውሃ ገድበው፥ አቁመው ፥ከትረው
በከተማ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደ ጃንሜዳ እንደ ጎንደር በሰው ሠራሺ ገንዳዎች ውሃ አቁረው የሚያመሹበት ቀን ስለሆነ ከተራ በማለት እናስታውሳለን ።

@@✣@@@✣@@@✣@@@@✣@@✣@@@@✣@@
.......✣.......✣........✣........
ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ  መሄዳቸው " አሚሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ፦ያን ጊዜ ክርስቶስ ከዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ"ብሎ እንደተናገረ  ማቴ ፫÷፲፫ 

@@✣@@@✣@@@@✣@@@✣@@✣@@@✣@@@
........✣.....✣......✣............
ታቦታቱ ከቤተክርስቲያን ተነሥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት መሄዳቸው ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው ።

@✣@@✣@@@@✣@@@
@@✣@@@@✣@@@✣@
..........✣......✣..........✣......
ታቦታቱ የክርስቶስ ምሳሌዎች ናቸው። ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት የዮሐንስ መጥምቅ ምሳሌዎች ናቸው ።



@@✣@@@@✣@@@✣@@@@@@✣@@@@✣@✣
........✣..............✣.............✣
ታቦቱን አክብረው የሚሄዱ ካህናት የዮሐንስ መጥምቅ ደቀመዛሙርት ምሳሌዎች ናቸው ምእመናንን ከዮሐንስ ለመጠመቅ ሲሄዱ የነበሩ ምእመናን ምሳሌ ናቸው በዋዜማው መውረዳችን ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ የሄደው በዋዜማው ነበርና የዚያ ምሳሌ ነው።
ድንኳን ጥለን ማደራችን ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚመጡት ምእመናንን ድንኳን ጥለው አጎበር ተከለው በዮርዳኖስ ዙሪያ ያድሩ ነበርና የዚያ ምሳሌ ሲሆን ከድንኳኑ ውጭ ሲጸልዩ እና ውርጩን ታግሰሠው ሲዘምሩ የሚያድሩ ምእመናን ክርስቶስ ተራው እስኪደርስ ድረስ እየጠበቀ  እርሱ ሲጠመቅ የነበረውን የክረምት ብርድና ቅዝቃዜውን ታሦ የማደሩ ምሳሌ ነው ።
......................................
እንኳን ለ፳፻፲፮ ለከተራ በዓል በሰላም አደረሳችሁ !!!
............................................
መምህር ናትናኤል ባየ የብሉይ እና የሐዲስ መምህር የሊቅ ደቀመዝሙር
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
2024/09/25 21:22:17
Back to Top
HTML Embed Code: