Telegram Web Link
🌹እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን🌹

‹‹ #በእንተ_አቡነ_አቢብ !››

እነሆ ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ምእመናን በሚቀምሱት የዕለት ምግብ አማካኝነት በነፍስም በሥጋም እንዲድኑ አስገራሚ የምሕረት ቃልኪዳን እንደተቀበሉ የሚናገር የገድል ተአምራታቸው ይህ ነው፡- ብዙዎች ስማቸውን ጠርተው በሚቀምሱት ምግብ አማካኝነት ከተለያዩ በሽታዎች የተፈወሱ አሉ፡፡ ይህ ቃልኪዳናቸው ለኹላችን ይደረግን ዘንድ ከመመገባችን አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም እንጥራ (አቡነ ዘበሰማያትን ማለቱ ነው፡፡) ከተመገብን በኋላም የዕለት ምግባችንን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እናመስግን፡፡ ዘወትር ከተመገብን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹ስለ ወዳጅህ ስለ አቡነ አቢብ›› እያልን ሦስት ጊዜ እንቅመስ፡፡ አስቀድሞ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ አቢብ ተገልጦላቸው ‹‹…ወዳጄ አቢብ ሆይ! የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበልኩትን ሕማማተ መስቀል እያሰብህ ይህንን ሁሉ ገድል ፈጽመሃልና ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ ንዑድ ክቡር ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብም ‹‹ጌታዬ አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መቼም ሰው ሁሉ ሳይመገብ አይውልም አያድርምና በተመገበ ጊዜ ስሜን ጠርቶ የተማጸነውን ማርልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አባታችን አቡነ አቢብ ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅር ካደነቀ በኋላ ‹‹…ከማዕድ በኋላ ስብሃት ተብሎ የተረፈውን ‹በእንተ አቢብ› ብሎ ሦስት ጊዜ የተመሰገበውን ሰው ሁሉ እምርልሃለሁ›› በማለት ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ያልተጠመቀ አረማዊ አሕዛብም እንኳን ቢሆኖ "ስለ አቡነ አቢብ" ብሎ ከተማጸነ ጌታችንን ያንን ሰው ወደቀናች የእምነት መንገድ ሳይመራወና በንስሓ ሳይጠራው በሞት እንደማይወስደው ለአባታችን ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ለማዳን ትንሽ ምክንያትን የሚፈልግ ያለ ምክንያትም የማያድን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ እስከዘላለም ድረስ ይክበር ይመስገን!
ሰው ተመግቦ እንኳን መዳን እንዲችል ይህን ድንቅ ቃልኪዳን ለአባታችን ሰጥቷቸዋልና በየቀኑ በዚህ ቃልኪዳን እንጠቀምበት፡፡ ተመግበን ከጨረስንና ስብሃት ካልን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹በእንተ አቡነ አቢብ›› ብለን እንቅመስ፡፡

በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 25 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው የሚውሉት ጻድቁና ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ከቃልኪዳናቸው ረድኤት በረከት ይክፈሉን!

‹‹ #በእንተ_አቡነ_አቢብ !››

(ደብረ ሰላም ቃጭልቃ አቡነ አቢብ ገዳም ያሳተመው ገድለ አቡነ አቢብ፣ ገጽ 105)
የሮም ሊቀ ጳጳሳት ሰለባስትርዮስ ስለ #ጌታችን ስለ #መድኃኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ስለ ሕማሙ ከአይሁድ ጋር ካደረገው ክርክር።

ሰለባስትርዮስ ዛፍ ቢኖር ብርሀነ ፀሐይ በቀትር ጊዜ ወድቆበት ሳለ በምሳር እንቆርጣለን ቢሉ ዛፉን በምሳር በመቱት ጊዜ ፀሐይ ወድቆበት ሳለ የብረቱ ኃይል በግንዱ ላይ የሚወድቅ አደለም አለ፤ አይሁዳዊው ኖኅም እውነት ነው አለ።

ሰለባስትርዮስም ፀሐይ በምሳሩና በዛፉ ላይ ወድቆባቸው ሳለ ምሳር ፀሐይን ይቆርጠው ወይም ክርክራት ፍልቃት ያደርግበት ይቻለዋልን አለው፤ ኖኅም አይቻልም አለ።

ሰለባስትርዮስም ስለ " #ክርስቶስ " ሕማም ሞት የምንናገረው እንደዚህ ነው፤ ሥጋው በዛፉ፤ ሕማሙ በምሳር፤ መለኮትም በፀሐይ ይመሰላል፤ ጌታችን "#ኢየሱስ ክርስቶስ" መለኮቱን ከሕማም ወገን ምንም ሳያገኘው እንዲሁ በሥጋ ታመመ አለው።

✍️ሐይማኖተ_አበው_ዘቅዱስ_ሰለባስትርዮስ። #በጌታችን_በአምላካችን_በመድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስና በእመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም ትዕዛዝ ጻድቁ አባታችን #አቡነ_አቢብን(አባ ቡላን) ያጠመቁ አባት ናቸው #ቅዱስ_ሰለባስትርዮስ
#ጥቅምት_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ስድስት በዚህች ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ #ሐዋርያ_ቅዱስ_ጢሞና በሰማዕትነት አረፈ፣ የጌታ ወንድም የተባለው #ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሐዋርያ_ጢሞና

ጥቅምት ሃያ ስድስት በዚህች ቀን #ጌታችን ከመረጣቸውና በሽተኞችን ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ አጋንንትንም ያወጡ ዘንድ ሥልጣንን ከሰጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ቅዱስ ሐዋርያ ጢሞና በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ ጢሞና ሰማያዊ ሀብትን መለኮታዊ ኃይልን ገንዘብ አድርጎ በሽተኞችን ፈወሳቸው አጋንንትም ተገዙለት ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ _ክርስቶስ በሥጋ በምድር ሳለ አገለገለው። ወደ ሰማይም ከዐረገ በኋላ ሐዋርያትን አገለገላቸው በሃምሳኛው ቀንም ጰራቅሊጦስ በወረደ ጊዜ የአጽናኝ #መንፈስ_ቅዱስን ጸጋ ከእርሳቸው ጋር ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ሰባት ሁነው ከተቆጠሩት ዲያቆናት ጋር ሐዋርያት ሾሙት እነርሱ #መንፈስ_ቅዱስን ዕውቀትንም የተመሉ እንደሆኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምስክር ሁኖአል።

በዲቁና አገልግሎትም ጥቂት ከአገለገለ በኋላ ብልቃ ከሚባል አገር በስተምዕራብ በሆነ ስብራ በሚባል አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሙት በውስጧም ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ሃይማኖት አስተማረ ከዮናናውያንና ከአይሁድም ብዙዎችን አጠመቃቸው።

የዚያች አገር ገዥም ይህን በሰማ ጊዜ ቅዱስ ጢሞናን ይዞ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃይቶ በእሳት አቃጠለው በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዮሴፍ መታሰቢያ ነው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ የ #ጌታችን ወንድም የተባለውና የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የነበረው ነው፡፡

እርሱም የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ ሲሆን ከልጆቹ ሁሉ ትንሹ ነው፡፡ ድንግልና ንጹሕ ሆኖ ከ #ጌታችን ጋር እየተጫወተ አብሮ አድጓል፡፡ የያዕቆብ ወላጅ እናቱ በልጅነቱ ስለሞተችበትና የብርሃን እናቱ የሆነች ወላዲተ አምላክ #ድንግል_ማርያምን ዮሴፍ አረጋዊ በ83 ዓመቱ ጠባቂ ይሆናት ዘንድ ወደቤቱ ሲወስዳት #ድንግል_ማርያም ያዕቆብን የሙት ልጅ ሆኖ አግኝታው ከወለደችው ከ #መድኃኔዓለም_ክርስቶስ ጋር አብራ ተንከባክባ አሳድጋዋለች፡፡

ቅዱስ ያዕቆብ ከ #ጌታችን ጋር አብሮ እየተጫወተ እያለ አንድ ቀን ትግል ይገጥማሉ፡፡ ያዕቆብም #ጌታችንን አንስቶ ጣለው፡፡ ድጋሚ ተያያዙና አሁንም ያዕቆብ #ጌታችንን ጣለው፡፡ ሦስተኛ ጊዜም እንዲሁ ሆነና ያዕቆብ የልብ ልብ ተሰማው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ድጋሚ ትግል ሲያያዙ ግን #ጌታችን ያዕቆብን ወደ ሰማይ ወርውሮ መሬት ላይ በኃይል ጣለው፡፡ ያዕቆብም እጅግ ደንግጦ "ኃይልህን ደብቀህ ቆይተህ አሁን ምነው እንዲህ ታደርገኛለህ?" ሲለው #ጌታችንም "እኔኮ ካልጣሉኝ አልጥልም" አለው፡፡

#ጌታችን ዕርገት በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾመውታል፡፡ ብዙዎችንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሷቸዋል፡፡ ሕዝቡም የታመሙትን ድውያንን ሁሉ እያመጡለት ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ከኢየሩሳሌምም ውጭ እየሄደ ያላመኑትንም አስተምሮ እያጠመቀ ቤተ ክርስቲያን ይሠራላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በጾም በጸሎት ሆኖ በመቆም ብዛት እግሮቹ አብጠው ነበር፡፡

አንድ ቀን አይሁድ ተሰብስበው መጥተው #ጌታችን የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ወደ ያዕቆብ መጡ፡፡ እነርሱም ወደ ያዕቆብ የመጡት #ጌታችን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነና የእርሱም የሥጋ ወንድም እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ካለው ከሦስተኛው መደብ ላይ ወጥቶ #ጌታችን የራሱ የያዕቆብና የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን መሰከረባቸው፡፡ ዳግመኛም #ጌታችን ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የ #እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ከ #አብም ጋር ትክክል እንደሆነ መሰከረባቸው፡፡ ይህንንም በሰሙ ጊዜ አይሁድ እጅግ ተናደው በጽኑ ግርፋት ካሠቃዩት በኋላ ራሱን ቀጥቅጠው ገደሉት ሰማዕትነቱን ሐምሌ 18 ቀን በድል ፈጽሟል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_26)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_26_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ገላትያ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁵-¹⁶ ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥
¹⁷ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።
¹⁸ ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤
¹⁹ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም።
²⁰ ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።
²¹ ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ።
²² በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤
²³ ነገር ግን፦ ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤
²⁴ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።
¹⁹ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።
²⁰ እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።
²¹ እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።
²² ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።
²³ ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።
²⁴ እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።
²⁵ እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።
²⁶ ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።
²⁷ እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።
²⁸ አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።
²⁹ ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና።
² አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፦ የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም።
³ ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤
⁴ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።
⁵ ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ።
⁶ በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው።
⁷ የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_26_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "ይዌስክ እግዚአብሔር ላዕሌክሙ። ላዕሌክሙ ወላዕለ ውሉድክሙ። ቡሩካኑ አንትሙ ለእግዚአብሔር"። መዝ 113፥22-23።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_26_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው።
² አላቸውም፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።
³ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ።
⁴ ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ።
⁵ ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ።
⁶ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።
⁷ በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ።
⁸ ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤
⁹ በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው።
¹⁰ ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ፦
¹¹ ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
 የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን #የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ጢሞና የዕረፍት በዓል፣ የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ የመታሰቢያ በዓልና የጽጌ ጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት #የአምላካችን_የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፣ #የጻድቁ_አባ_መብዓ_ጽዮን የቃልኪዳን ቀን፣ የማህሌተ ጽጌ ደራሲው #አባ_ጽጌ_ድንግል_ዘወለቃ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው፣ ቅዱስ አባት የሀገረ ቃው #ኤጲስቆጶስ_አባ_መቃርስ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#መድኃኔዓለም (በዓለ ስቅለት)

ጥቅምት ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት የአምላካችን የ #መድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው።

#መድኃኒታችን ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቸርነቱ ስለኹላችን ድኅነት ሲል ራሱን ወድዶ ፈቅዶ ለሞት አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን አሳይቶናል። በቅዱስ ወንጌልም እርሱም #መድኃኒታችን " ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም" ብሎ ነግሮናል። እውነት ነው፣ ራስን ነፍስን ስለጠላት ነፍስ አሳልፎ ከመስጠት በላይ ምን ድንቅ ነገርና ምን ድንቅ ፍቅር አለ?

ቸሩ አምላካችንን የአስቆሮቱ ይሁዳ ሊያስይዘው የሊቃነ ካህናቱን አገልጋዮች እየመራ አመጣቸው። እነርሱንም ማንን ትፈልጋላችሁ ሲላቸው የናዝሬቱ #ኢየሱስን አሉት፣ እኔ ነኝ ቢላቸው የቸሩን አምላክ ድምጽ ሰምቶ አይደለም መቆም በሕይወት መጽናት የሚቻለው የለምና ወደ ኋላቸው ተስፈንጥረው ወደቁ። ደጋግሞም እንዲህ ኾነ። በኋላ ግን እኔ ነኝ ብሎ በፈቃዱ ይሁዳ ስሞ አሳልፎ ሰጣቸው።

ከያዙት በኋላ እያዳፉና እየጎተቱ በሰንሰለት አስረው ወደ ቀያፋና ሐና ግቢ ወሰዱት፣ እስከ ሦስት ሰዓትም አላሳረፉትም ሲያሰቃዩት አድረዋል፣ በራሱም ላይ ሰባ ሦስት ስቊረት ያለው ወደ ሦስት መቶ እሾኾችን የያዘ የእሾህ አክሊል ጎንጉነው ቢያደርጉበት የራስ ቅሉን ቀዶ ገብቶ እስከ ልቡ ዘልቋል። እንደምን ጭንቅ ነው? እንዲህም አድርገው ደግሞ እያፌዙ ርኲስ ምራቃቸውን ይተፉበትና በዘንግም ደጋግመው ይመቱት ነበር። እየተፈራረቁ ያለ ምንም ርኅራኄ ቸሩን አምላክ ሥጋው እየተቆረጠ እስኪወድቅ ድረስ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጽኑዕ ግርፋትን ገርፈውታል። የገረፉበትም ጅራፍ በላዩ ላይ ሥጋን እየጎመደ የሚጥል፣ ሕመሙ አንጀት ሰርሥሮ የሚገባ በስለት የተያያዘበት ነበር።

በኋላም አላሳረፉትም እንዲህ አድርገውትም በሊቶስጥራ አደባባይ ያንን ዕርጥብ #መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። እርሱ ግን ይህን ኹሉ ግፍ ሲያደርሱበት አንድም አልተናገረም ነበር። በቀራንዮም በአምስት ጽኑዕ ቅንዋት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ) ቸንክረው ዕርቃኑን ሰቀሉት።

በዚህች ቀን ድንግል #ማርያም ልቧ በሐዘን ተሰበረ መጽናናትንም አልፈለገች ነበር፤ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ እናቱንም እናት ትሆነው ዘንድ በእግረ #መስቀሉ አደራን ተቀበለ። ቅዱሳት አንስት በፍጹም ሀዘንና በዋይታ ዋሉ። በስልጣኑም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። ሰባት ድንቅ የኾኑ ተአምራትንም አድርጎ አምላክ መኾኑን ገለጠ። ይህም ጽኑዕ የኾነ ለሰማይ ለምድር የከበደ ነገር ሲከሰት ፀሐይ አምላኬን ዕርቃኑ እንዴት አያለሁ ብላ ጨለመች። ጨረቃ ደም ኾነች፣ ከዋክብቱም ረገፉ፣ ንዑዳን ክቡራን ንጹሐን መላእክትም ትዕግስቱን እያደነቁ በጽኑዕ ሐዘንና መደነቅ ከቅዱስ ዕፀ #መስቀሉ ፊት እንደሻሽ ተነጠፉ።

አስራ አንድ ሰዓት በሆነም ጊዜ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር ቅድስት ሥጋውን ከ #መስቀሉ አውርደው በክብር ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በሦስተኛውም ቀን እንደተናገረ ተነሳ።

በዛሬዋ ቀን ቤተ ክርስቲያን የ #መድኃኔለምን የስቅለት በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፡፡ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው መጋቢት 27 ቀን ነው፤ ይህ በዓል ግን በዐቢይ ጾም ስለሚውል በዐቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለና በዓል ማክበር ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ሰርታልናለች፡፡

እርሱ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ ያለ ልዑለ ባሕርይ ከ #አብ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር በጌትነቱ ዙፋን ተቀምጦ ያለ ለእርሱም ምስጋና የክብር ክብር ገንዘቡ የሆነ ራሱን ሰውቶ ያዳነን የመንግሥቱን ደጆች በፈሳሽ ደሙ የከፈተልን ለእርሱ ስግደትአምልኮት ይገባዋል ለዘላለሙ የ #መስቀሉም በረከት በላያችን ይደር አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_መብዓ_ጽዮን

አባ መብዓ ጽዮን በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታቸው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ከሚለምኑ ባልና ሚስት ተወለዱ። የንቡረ እድ ሳሙኤል ረባን የሆነው መብዓ ጽዮን አባቱ እስከ ዳዊት ያለውን ትምህርት አስተማረውና ዲቁናን ተቀበለ። ልጁ የትምህርት ዝንባሌ እንዳለው አባቱ ተረድቶ ቤተ ማርያም ከሚባለው ደብር ወስዶ ተክለ አማኅጸኖ ከሚባል የቅኔ መምህር ዘንድ አስገባው። በዚያም ቅኔና እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን እውቀቶችን ገበየ። ከዚህም በተጨማሪ ሥዕል መሳልና ጽሕፈት መጻፍ ተማረ።

መብዓ ጽዮን የልጅነቱን ዘመን ሲፈጽም ‹‹ለነፍሳቸው ድኅነት ዋጋ ያገኙ ቅዱሳን ብዙ ናቸው።በመጾም ያገኙ አሉ፤ በትምህርት ያገኙ አሉ፤ በድካም ያገኙ አሉ፤ በጸሎት በትጋት ያገኙ አሉ፤ እኔ ግን የ #ጌታዬን_የኢየሱስ_ክርስቶስን የሞቱን መታሰቢያ ማድረግ ይገባኛል። በዚህም ፊቱን አያለሁ፤ እርሱ #ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ "የትንሣኤዬን መታሰቢያ ብታደርጉ የሞቴን መታሰቢያ አድርጉ ብሏልና" በማለት ፍላጎቱ በምንኩስና በመኖር ፈጣሪን ማገልገል መሆኑን ለወላጆቹ ገለጸላቸው።

አባትና እናቱም "ፈጣሪህን ለማገልገል ኅሊናህ ከአሰበ እሺ፤ በጀ ደስተኛ ነን" ብለው ፈቀዱለት። ከዚያም መብዓ ጽዮን ዳሞት አባ ገብረ ክርስቶስ ወደሚባል መነኩሴ በመሄድ መነኮሰ። አባ መብዓ ጽዮን አባ ገብረ ክርስቶስ ጋር በመቀመጥ ሥርዓተ ምንኩስናን ካጠኑ በኋላ ከአባ ገብርኤል ዘንድ ሄደው የቅስናን ማእረግ ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ በአበው ሕግ በምንኩስና ተወስነው፤ በበአታቸው ሆነው ‹‹ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ_ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፤ ስለራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ብለው በጸልዩ ጊዜ ‹‹መከራ #መስቀሉን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም ‹‹አዎ አይ ዘንድ እወዳለሁ›› ሲሉ ለ #ጌታቸው መለሱለት። ያን ጊዜም የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስ ዕፀ #መስቀል ተተከለ። በ #መስቀሉ ላይም እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረውና ተዘርግተው ታዩ ፤በራሱ ላይም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር።

እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው #ጌታችን ለአባ መብዓ ጽዮንም ታያቸው። ከዚህም በኋላ አባ መብዓ ጽዮን የ #ጌታችን_የመድኃኔዓለምን ሕማሙን፣ መከራውን፣ ግርፋቱን፣ እስራቱን በጠቅላላ ፲፫ቱን ሕማማተ #መስቀል በማሰብ ጀርባቸውን በአለንጋ ይገርፉ ፤ራሳቸውንም በዘንግ ይመቱ ነበር። የጌታን መከራ #መስቀል እያሰቡ ዐይኖቻቸው አስከሚጠፉ ድረስ ያለቅሱ ነበር ። #ጌታችን ግንደ መስቀሉን (የመስቀሉን ግንድ) አንደተሸከመ በማሰብ ትልቅ ድንግያ ተሸክመው ይሰግዱ ነበር። መራራ ሐሞት መጠጣቱን በማሰብ ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። የ #ጌታ ደቀመዝሙር ዮሐንስ ወንጌላዊ #ጌታ በተሰቀለ ጊዜ አብሮ ስለነበርና ዐይን በዐይን ስለተመለከተ የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን መከራ #መስቀል እያሰበ ፸ ዘመን ፊቱን በሐዘን ቋጥሮ እንደኖረ ሁሉ ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ የ #ጌታችንን መከራ #መስቀል እያሰቡ ከዓለም ተድላና ደስታ ተለይተው በትምህርት ፣ በትሩፋት ፣
በገድል ጸንተው ኖረዋል። ጻድቁ መብዓ ጽዮን በሕይወተ ሥጋ ዘመናቸው የላመ የጣመ እንዳልተመገቡ፤ በፈረስ በበቅሎ እንዳልሄዱ፤ አልጋ ላይ እንዳልተኙ፤ ገድላቸው ያስረዳል። የክርስትናን ትምህርት ለጋፋት ሰዎች እንዲስፋፋ ያደረጉት አባ መብዓ ጽዮን የ #ጌታን ሕማማተ #መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያነቡ ዐይኖቻችው ጠፍተው ነበር። ነገር ግን እመ ብዙኃን የሆነችው ቅድስት #ድንግል_ማርያም ወደኚህ ጻድቅ አባት በአት የብርሃን ጽዋ ይዛ መጥታ ዐይኖቻቸውን ቀብታ አድናቸዋለች። ከዚህ የተነሳ በትረ ማርያም እየተባሉ ይጠሩ አንደነበር ገድላቸው ያስረዳል።

የጻድቁ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ከ #መድኃኔዓለም የስቅለት በዓል ጋር ይከበራል። ጥቅምት ፳፯ ቀን ለወዳጆቹ እውነተኛውን ዋጋ የሚከፍል #መድኃኔዓለም_ክርስቶስ ለጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን ብዙ ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው።

የአቡነ መብዓ ጽዮን ረድኤታቸው፣ በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፤ አሜን!!!

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጽጌ_ድንግል_ዘወለቃ

በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ሊቅ ሲኾን፤ አባ ጽጌ ድንግል (ጽጌ ብርሃን) ሀገሩ ይፋት ሃይማኖቱ ኦሪት ነበረ፡፡ በንጉሥ ሰሎሞን ፈቃድና በካህኑ አዛርያስ መሪነት የብሉያት መጻሕፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ ተርጕመው ሊያስተምሩ፣ ታቦተ ጽዮንን ከኢየሩሳሌም ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና የብሉያት መጻሕፍት ሊቃውንት ከነበሩት ከ318 ሌዋውያን (ከቤተ እስራኤላውያን) ነገድ ነው፡፡ የተወለደውም በሰሜን ሸዋ በይፋት አውራጃ ውስጥ ሲሆን፤ መጀመርያ ኢእማኒ (ያላመነና ያልተጠመቀ) ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ሰው፤ በወጣትነት ዕድሜው አውሬ ለማድን ወደ ጫካ ሄደ፣ ጫካዋም በዚያው በይፋት አውራጃ የምትገኝና ልዩ ስሟ ደንስ (ገዳመ ደንስ) ትባላለች፣ በጫካዋ ውስጥም ፊቷ በጽጌረዳ አበባ የተከበበና ያጌጠ፣ እጅግም ደስ የምታሰኝ የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያምን ሥዕል አይቶ በሥዕሏ ውበት እየተደነቀ ሥዕሏን ሲመለከት እንደ እርሱ ያልተጠመቀ ጓደኛው መጥቶ፣ "ምን እየፈለግህ ነው? የክርስቲኖችን ሥዕል ነውን?" ብሎ ለ #ድንግል_ማርያም ምስጋና ይግባትና በያዘው በትር ሥዕሏን ሲመታት ወዲያው ተቀሥፎ ሞተ። ከዚህ በኋላ ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ የመሰለ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በነጭ ወፍ ተመስሎ ወደ እርሱ መጥቶ አንድ ቀይ መነኩሴ እሰኪመጣ ድረስ፣ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ነግሮት ተሠወረ።

የአቡነ ዜና ማርቆስ የገድል መጽሐፍ፣ እንደሚናገረው ካህን ከነበረው ከአባቱ ከዘርዐ ዮሐንስ እና ከእናቱ ማርያም ዘመዳ በ1262 ዓ.ም. ኅዳር 24 ቀን በሰሜን ሸዋ ግዛት በሚገኘውና ልዩ ስሙ እቲሳ ቅዱስ ሚካኤል በሚባለው አጥቢያ የተወለደው አቡነ ዜና ማርቆስ ደብረ ብስራት ከሚባለው ገዳሙ ወደ ይፋት መጥቶ ከነብዩ ኢሳይያስ ትንቢት ከምዕ. 11፥1 ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ እያለ በግእዝ ቋንቋ ሲያነብ አባ ጽጌ ድንግል በሰማ ጊዜ አባቶቼ አይሁድ የነቢያትን ትንቢት ንባቡን አስተምረውኛል አውቀዋለሁ፤ ትርጕሙን ግን አላውቀውምና ተርጕምልኝ አለው፡፡

አቡነ ዜና ማርቆስም ሲተረጕምለት እንዲህ አለ፤ ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ የሚለው ንባብ ከእሴይ ነገድ የሕይወት በትር የኾነች እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ትወለዳለች ማለት ነው፡፡ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ የሚለው ንባብ ደግሞ፤ #እመቤታችን ተወልዳ፣ ከእርሷም #ጌታ በድንግልና ይወለዳል፣ ከ #ጌታም ክብር ይገኛል ማለት ነው፣ ይህም #ጌታ ተወልዶ ትንቢቱ በእውነት ተፈጽሟል ብሎ ተረጐመለት፡፡ ኢሳ 7፥14፣ ማቴ18፥24፡፡

ይህ ሰውም (አባ ጽጌ ድንግልም) በዚህ ትርጕም ደስ ተሰኝቶ አባት ሆይ የኢሳይያስን ትንቢት በመልካም ሁኔታ ተረጐምከው፣ መልካም ነገርንም ተናገርክ አለውና፣ ሥዕሏ ወዳለችበት ቦታ ወስዶ ታሪኩ ከላይ እንደተገለጸው፣ በጫካ ውስጥ ያያትን ሥዕል ጓደኛው በያዘው ብትር ሲመታት ወዲያውኑ እንደተቀሠፈና ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ፣ "አንድ ነጭ ወፍ /ቅዱስ ሩፋኤል/" ወደ እርሱ መጥቶ ቀይ መነኵሴ እስኪመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ያነጋገረውን ሁሉ ነገረው፣ አቡነ ዜና ማርቆስም ከሥዕሏ የተደረገውን ተአምር ሰምቶ፣ እጅግ ደስ አለውና በል መጀመሪያ #እመቤታችን በድንግልና በወለደችው በፈጣሪ ልጇ በ #ኢየሱስ_ክርስቶስ እመን ይህችን ሥዕል ያስገኘ፣ ሰማይና ምድርን፣ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፣ እርሱ እንደኾነ እውቅ አለውና በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም አጥምቆ ጽጌ ብርሃን ብሎ ሰየመው፡፡

ከዚህ በኋላ ሥዕሏን በገዳመ ደንስ ደብረ ብሥራት ወደሚባለው ገዳም ወስዶ በዘመነ ጽጌ ጥቅምት አንድ ቀን በክብር አስቀመጣት የምትከብርትንም ቀን ጥቅምት 3 እና ሰኔ 8 ቀን አደረገ፡፡

አቡነ ዜና ማርቆስም ጽጌ ብርሃንን ለመዓርገ ምንኵስና አበቃው፤ የአባ ጽጌ ብርሃንም ጽጌ ድንግል የሚል ቅጽል ስም አለው፣ በማኅሌት አገልግሎት ጊዜም ታላቁ ጻድቅ አቡነ ዜና ማርቆስ ቤተ ክርስቲያኒቱንና ሥዕሏን እየዞረ ሲያጥን፣ #እመቤታችን የካህናቱን አገልግሎት እንደምትባርክ፣ ካህናቱ በግልጽ ይረዱ ነበር፣ አባ ጽጌ ብርሃንም ከመጠመቁ በፊት በአባቶቹ በአይሁድ ሥርዓት እያለ የብሉያት መጻሕፍትን የተማረ ነበር፣ የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜን ግን ከአቡነ ዜና ማርቆስ ተማረ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ላሉ አሕዛብ ሁሉ የድኅነት ምክንያት ትሆኑ ዘንድ ብርሃናቸው፣ መምህራቸው አደረግኋችሁ ብሉ #ጌታ ነቢዩ ኢሳይያስንና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን እንደመረጣቸው፣ ኢሳ 49፥6.፣ የሐ.ሥራ13፥47 ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዜና ማርቆስ ስብከተ ወንጌልን እንደ ዕለት ጉርስና እንደ ዓመት ልብስ አድርጎ፣ መላ ኢትዮጵያን ዞሮ፣ አስተምሮና ባርኮ የዕድሜ ባለጸጋም ሆኖ በተወለደ በ140 ዓመት በ1402 ዓ.ም ታኅሣሥ 3 ቀን ፣ ዐርብ ጠዋት ዐረፈ፡፡

አባ ጽጌ ብርሃንም በወሎ ክፍለ ሀገር በወራይሉ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ ለሚባለው ገዳም የሕግ መምህር ሆኖ ከተሸመውና ከጓደኛው ከአባ ገብረ ማርያም ጋር እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን፣ #እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ማኅሌተ ጽጌ የተባለውን ድርሰት፣ በአባቷ በዳዊት መዝሙር መጠን 150 አድርጎ ደረሰ፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ኹሉ በማኅሌተ ጽጌ #እመቤታችንን በአበባ፥ #ጌታችን በፍሬ፤ ወይም #እመቤታችንን በፍሬ፥ #ጌታችን በአበባ እየተመሰሉ የሚመሰገኑበት ምስጋና ነው። ሰቈቃወ ድንግል ማለት #እመቤታችን ከልጇ ከ #መድኀኔዓለም፣ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በስደቷ ወቅት ያየችውን መከራ፥ ልቅሶ ዋይታ የሚዘከርበት የማኅሌተ ጽጌ አርኬ ነው፡፡

(የሰቈቃወ ድንግልን ደራሲ በተመለከተ አባ ጽጌ ድንግል ደረሱት የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አባ ገብረ ኢየሱስ ዘገዳመ መጕና /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/ ወይም /አባ አርኬላዎስ/ ነው የደረሱት የሚሉም አሉ፡፡)
ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ የማያደርግ የሕግ ፍጻሜ ነውና፤ ሮሜ 13፥10-11፣ አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያምም የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር (በአንድነት) አገልግለዋል፣ ማለትም አንድ ዓመት አባ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25፣ ቀን ከደብረ ሐንታ መጥቶ ገዳመ ጽጌ (ደብረ ብሥራት) ገብቶ ከመስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን አገልግሎትን ከአባ ጽጌ ብርሃን ጋር ፈጽሞ ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብረ ሐንታ ይመለሳል፤ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አባ ጽጌ ብርሃን ከገዳመ ጽጌ (ከደብረ ብሥራት) ወደ ደብረ ሐንታ ሄዶ እንደዚሁ እንደ አባ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አገልግሎ ይመለሳል፣ እኒህ ሁለቱ ቅዱሳን ሊቃውንትም ታሪኩ ከላይ እንደተገለጸው እንዲህ እያደረጉ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍቅርና በትሕትና ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አበው ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_መቃርስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት የሀገረ ቃው ኤጲስቆጶስ አባ መቃርስ አረፈ።

ለዚህም ቅዱስ የዝንጉዎችን ምክር ተከትሎ ያልሔደ፣ በኃጢአተኞችም ጎዳና ያልተጓዘ፣ በዘባቾችም መቀመጫ ያልተቀመጠ፣ የ #እግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ ፈቃዱ የሆነ እንጂ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያነብ የሚያስተምር ብፁዕ ነው የሚለው የነቢይ ዳዊት ቃል ተፈጽሞለታል።

ይህ አባ መቃርስ የ #እግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ በመክሊት ነግዶ ዕጥፍ አድርጎ አትርፎአልና #እግዚአብሔርም በእጆቹ ያደረጋቸውን ታላላቆች ድንቆች ተአምራት ስንቱን እንናገራለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ በሀገረ ቃው ተሾሞ በወንበር ተቀምጦ ሕዝብን በሚያስተምራቸው ጊዜ ዘወትር ያለቅሳል ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ እጅግ የሚወደው አማለውና አባቴ ሆይ ሁል ጊዜ ለምን ታለቅሳለህ ንገረኝ አለው እርሱም ስለ መሐላው ፈርቶ ዘይት በብርሌ ውስጥ እንደሚታይ የወገኖቼን ኃጢአታቸውን የከፋች ሥራቸውንም በማይና በምመለከት ጊዜ አለቅሳለሁ ብሎ መለሰለት።

ሁለተኛ ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ የየአንዳንዱን የሰውን ሥራ መላእክት ሲያቀርቡለት አየው በዚያንም ጊዜ እንዲህ የሚል ቃል ሰማ ኤጲስቆጶስ ሆይ ለምን ቸለል ትላለህ ሕዝቡን አትገሥጻቸውምን አታስተምራቸውምን እርሱም አቤቱ እነርሱ ትምርቴን አይቀበሉም ብሎ መለሰ። ሁለተኛም እንዲህ አለው ለኤጲስቆጶስ ሕዝቡን ማስተማር ይገባዋል ትምርቱን ካልተቀበሉ ግን ደማቸው በራሳቸው ይሆናል።

ከዚህም በኋላ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያኖስ ወደ ሰበሰበው ጉባኤ ከሊቀ ጳጳሳቱ ዲዮስቆሮስ ጋር ይሔድ ዘንድ ጠሩት የተሰበሰቡትም አንዱን #ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ የሚሉ ናቸው በደረሰም ጊዜ ስለ ልብሱ አዳፋነት ወደ ንጉሥ አዳራሽ መግባትን ከለከሉት አባ ዲዮስቆሮስም ከእርሱ ጋር እንዲአስገቡት ጳጳስ መሆኑን ነገራቸው።

በገቡም ጊዜ አንዱን #ክርስቶስን ሁለት ባሕርይ አድርገው ትስብእቱን ከመለኮቱ እንደለዩት እምነታቸውን ሰሙ ስለዚህም ንጉሡንና ጉባኤውን አወገዙአቸው እሊህ አባቶቻችን አባ ዲዮስቆሮስና አባ መቃርስ ስለ ቀናች ሃይማኖታቸው ነፍሳቸውን ለሞት አሳልፎ ለመስጠት ቆርጠዋልና ንጉሡም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዛቸው።

ከዚያም ከምእመን ነጋዴ ጋር ወደ እስክንድርያ አባ ዲዮስቆሮስን ሰደደው እርሱ ለአባ መቃርስ ትንቢት ተናግሮለት ነበርና እንዲህ ብሎ አንተ ግን በእስክንድርያ አገር የሰማዕትነት አክሊል ትቀበል ዘንድ አለህ።

አባ መቃርስም ወደ እስክንድርያ ሲደርስ በዚያን ጊዜ የመናፍቁ የንጉሥ መርቅያን በውስጡ የከፋች ሃይማኖቱ የተጻፈበት የመልእክት ደብዳቤ ደረሰ መልእክተኛውንም እንዲህ ብሎ አዞታል በእኛ ሃይማኖት አምኖ በዚህ መዝገብ ውስጥ መጀመሪያ የጻፈ በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ይሁን የሚል ነው አብሮታራ የሚባል አንድ ሰው ተቀዳድሞ በውስጡ ሊጽፍ ያንን መጽሐፍ ተቀበለ ቅዱስ አባ መቃርስም እንዲህ አለው ከእስክንድርያ አገር በሔደ ጊዜ ከእኔ በኋላ አንተ በቤተ ክርስቲያን የሠለጠንክ ትሆናለህ ብሎ የነገረህን የአባ ዲዮስቆሮስን ቃሉን አስብ ያን ጊዜ አብሮታራ ያንን ቃል አስታውሶ በዚያ በረከሰ መጽሐፍ ላይ ሳይጽፍ ቀረ።

የንጉሡም መልክተኛ አባ መቃርስ በንጉሥ ሃይማኖት እንደማያምን በአወቀ ጊዜ ተቆጥቶ ከኵላሊቱ ላይ ረገጠው ያን ጊዜም ሙቶ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ሥጋውንም ምእመናን ወስደው ከነቢይ ኤልሳዕና ከመጥምቁ ዮሐንስ ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት ወደ ወደደው ክርስቶስም የመንግሥት ዘውድን ተቀዳጅቶ ሔደ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_27#የማሕሌተ_ጽጌ_ትርጕምና_ታሪክ#ገድለ_አቡነ_መብዓ_ጽዮን እና #ከገድላት_አንደበት)
#እመቤታችንን የተዘጋች የውሃ ጉድጓድ የታጠረች ተክል ብሎ የተናገረላት #ቅዱስ
Anonymous Quiz
30%
ቅዱስ ሰሎሞን ( ጠቢቡ)
55%
ቅዱስ ሕዝቅኤል
5%
ቅዱስ ቶማስ ( ሐዋርያ )
10%
መልሱ የለም
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው።
²¹ ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም።
²² ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤
²³ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤
²⁴-²⁵ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው።
²⁶ አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።
²⁷ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።
²⁸ እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል።
²¹ የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።
²² እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤
²³ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤
²⁴ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ።
²⁵ እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ።
¹³ ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥
¹⁴ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።
¹⁵ ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።
¹⁶ ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "ተሣሃለኒ እግዚኦ እስመ ኬደኒ ሰብእ። ወኵሎ አሚረ አሥርሐኒ ቀትል። ወኬዱኒ ፀርየ ኵሎ አሚረ በኑኀ ዕለት። መዝ. 55፥1-2
"አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፤ ሁልጊዜም በሰልፍ አስጨንቆኛል። የሚዋጉኝ በዝተዋልና ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ። መዝ. 55፥1-2
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_27_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።
¹² ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?
¹³ ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።
¹⁴-¹⁵ ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል።
¹⁶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።
¹⁷ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
¹⁸ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።
¹⁹ ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።
²⁰ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤
²¹ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።
²² ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።
²³ ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥
²⁴ እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️  🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ #የቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ቅዳሴ ነው። መልካም የ #መድኃኔዓለም_የስቅለቱ መታሰቢያ በዓል፣ የአባ ጽጌ ድንግል፣ የአቡነ መብዓ ጽዮን፣ የሀገረ ቃው የአባ መቃርስ የዕረፍታቸው በዓልና የጽጌ ጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/11/05 23:23:55
Back to Top
HTML Embed Code: