Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_9_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁵ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?
³⁶ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
³⁷ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
³⁸ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥
³⁹ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²-³ ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት
⁴ ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።
⁵ ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።
⁶ ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።
⁷-⁸ ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።
⁹-¹⁰ የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፥ ባለ ጠጋም በውርደቱ ይመካ፤ እንደ ሣር አበባ ያልፋልና።
¹¹ ፀሐይ ከትኵሳት ጋር ይወጣልና፥ ሣርንም ያጠወልጋልና፥ አበባውም ይረግፋልና፥ የመልኩም ውበት ይጠፋልና፤ እንዲሁ ደግሞ ባለ ጠጋው በመንገዱ ይዝላል።
¹² በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።
¹⁷ ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤
¹⁸-¹⁹ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤
²⁰-²¹ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_9_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ደምፁ ወተሐምገ ማያቲሆሙ። ወአድለቅለቁ አድባር እምኃይሉ። ፈለገ ዘይውኅዝ ያስተፌሥሕ ሀገረ እግዚአብሔር"። መዝ 45፥3-4።
"ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ። የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ"። መዝ 45፥3-4።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_9_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።
²⁵ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
²⁶ ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል።
²⁷ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።
²⁸ ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን
²⁹ እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል የተአምራት በዓል፣ የንጉሥ ቅዱስ ያሳይ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥር በዚች ቀን #ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ፣ የሜራሪ ልጅ #ቅድስት_ዮዲት እረፍቷ ነው፣ የከበረች #ቅድስት_መጥሮንያ በሰማዕትነት አረፈች፣ #ንግስት_ሳባ እረፍቷ፣ #ተቀጸል_ጽጌ #አጼ_መስቀል ይከበራል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጼዴንያ

መስከረም ዐሥር በዚህች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የ ድንግል_ማርያም ተአምር ተገለጠ።

ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው ይባላል። ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት። አምላክን የወለደች እምቤታችን #ድንግል_ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር። በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች።

በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስተሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው። እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከእኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን #ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው። እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት።

ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጎዳናው ተመለሰ። ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገቢያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን #ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት።

በጎዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበዴዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ። ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው።

አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር ባየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም።

ከዚህም በኃላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከቡም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጠላትም እርሷም አላወቀችውም።

በማግሥቱም ተሠውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ። ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል። ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሆነህ ነው አለችው።

ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት። ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች።

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞችም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች። ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኩስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን #ድንግል_ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።

የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳውም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚህም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል።

ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሆኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በ #ድንግል_ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ዮዲት

ዳግመኛም በዚህች ቀን ባሏ ምናሴ ሞቶባት፣ ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም፣ በቀኖና፣ በትኅርምት፣ በኀዘን፣ በጸሎት ተወስና የምትኖር የሜራሪ ልጅ ቅድስት ዮዲት አረፈች።

ቅድስት ዮዲት ከከሀዲው ሆሎፎርኒስ እጅ በጥበቧ እስራኤልን ያዳነቻቸው ጥበበኛ የከበረች፣ በ #እግዚአብሔር ኃይል ራሱን እስከ ቆረጠች ድረስ በልቧ ተራቀቀች ወገኖቿንም ያዳነች ናት።

ነገሩም እንዲህ ነው፦ ለፋርስ ንጉሥ ለናቡከደነፆር የጦር አበጋዝ የነበረው ሆሎፎርኒስ ፈቃድ ተሰጥቶት እስራኤልን ለመውረር ሲመጣ በሠራዊቱ (ዮዲ2፣2-7) የእሥራኤል ልጆችም ሆሎፎርኒስ የአሕዛብን አገር እንዳጠፋና ንብረታቸውን እንደዘረፈ ሰምተው ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስና ሰለ ንዋያተ ቅድሳት መርከሰ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከቤተ መቅደሱ በር ወድቀው አለቀሱ።(ዮዲ4፡2-15) ሆሎፎርኒስ ግን የሚጠጡትን ምንጫቸውን በመያዙ ፣ የእሥራኤል ልጆች በውኃ ጥም ከመቸገርና ከመሞት ይልቅ እጃቸውን ለጠላት ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ዖዝያን የአባቶቻቸው አምላክ መልስ እስኪሰጣቸውና ቸርነቱን እስኪመልስላቸው መከራውን በትዕግሥት እንዲቀበሉ ስለመከራቸው ጸኑ፡፡ ዮዲ 7፥10-32)

በዚህ ጊዜ ዮዲት ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትቢያ ነስንሳ፣ ሱባዔ ገባች! አምላክም ሕዝቡን የሚያድንበትን ዕውቀትና ጥበብ ግብር በገባች በሦስተኛ ቀን ገለጸላት፡፡(ዮዲ8፡2) ከዚያም “ወዴት ትሔጃለሽ አትበሉኝ አምላክ እሥራኤል ይከተልሽ ብሉኝ” ብላ የኀዘን ልብሷን ጣለች፡፡ ሰውነቷን ታጠበችና ሽቱ ተቀባች ባሏ በሕይወት ሳለ የምትለብሰውን የክት ልብሷን ለበሰች፣ የጠላት ሰዎች ሁሉ እስኪወዷት ድረስ ፈጽማ አጊጣ ሄደች፡፡ (ዮዲ.10፥2-3) እነርሱም ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች እያሉ ተሻሙባት፡፡ የንጉሥ ጃንደረባ ጋይ የሚባል ይህችስ ለጌታዬ ትገባለች አለ፣ ለምን እንደመጣች ጠይቀዋት ለመልካም ነገር እንደመጣች ሲረዱ ከጦር አበጋዙ አደረሷት፡፡ (ዮዲ10፥12-22)

በአንዲትም ዕለት ሆሎፎርኒስ የአሽከሮች የምሣ ግብዣ አድርጎ ሲያበላ ሲያጠጣ ያችን ዕብራዊት ጥሩ ብሎ አስጠርቶ ከፊቱ አስቀምጦ ሲበላ አብዝቶ ሲጠጣ ውሎ ሰከረ፡፡(ዮዲ12፥1-20) ከዚያም አሽከሮችን ከሁሉ አስወጥቶ ድንኳኑን ቆልፎ እንደተኛ ከባድ እንቅልፍ ያዘው ዮዲትም ከፀለየች በኋላ ከራስጌው ያለውን ሰይፍ አንስታ የራስ ጠጉሩን ይዛ አንገቱን ቆርጣ በድኑን ከመሬት ጥላ ቸብቸቦውን በአቁማዳ ቋጥራ ለብላቴናዋ አሸክማ ግንዱን በታች ገልብጣ ዙፋኑን በላይ አድርጋ ወደ ሃገሯ ተመለሰች፡፡ (ዮዲ13፥1-10) ሕዝበ እሥራኤል በዚህ ድርጊቷ እጅግ ተደነቁ፣ ጠላታቸውን በእጃቸው የጣለላቸውን #እግዚአብሔር አምላካቸውንም አመሰገኑ፡፡ በኋላም የሆሎፎርኒስን ራስ በተራራው ላይ ሰቅለው መዋጋት ጀመሩ፡፡ እስከ ዮርዳኖስም እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የዚህችን ቅድስት እናት በዓለ እረፍቷን በዚህች ዕለት አክብራ ትውላለች ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መጥሮንያ

በዚችም ቀን የከበረች መጥሮንያ በሰማዕትነት አረፈች። ይቺም የከበረች መጥሮንያ ለአንዲት አይሁዳዊት ሴት አገልጋይዋ ናት ። ይችም አይሁዳዊት እመቤቷ ከክርስትናዋ አፍልሳ ትክክል ወደ አልሆነ ሃይማኖቷ ልታስገባት ትሻ ነበር ስለዚህም ታጉሳቁላታለች በላይዋም የአገልግሎት ሥራን ታከብድባታለች ።

ከዚህም በኃላ በአንዲት ቀን አይሁዳዊት እመቤቷን ተከትላ ወደ አይሁድ ምኩራብ ሔደች ተመልሳም ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን ገብታ ጸለየች። ወደ ቤት በገቡም ጊዜ ወዴት ሒደሽ ነበር ወደእኛ ምኩራብ ለምን አልገባሽም ብላ ጠየቀቻት ቅድስት መጥሮንያም ከእናንተ ምኩራብ #እግዚአብሔር ርቋል እኮን እንዴት ወደርሱ እገባለሁ። በውስጧ ልገባባት የሚገባኝ ቦታዬ ግን ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በከበረ ደሙ የዋጃት ይህች ቤተ ክርስቲያን ናት ብላ መለሰችላት።

እመቤቷም ይህ ነገር በሰማች ጊዜ ተቆጣቻት እጅግም ደብደባ በጨለማ ቤት ውስጥ አሠረቻት ያለ መብልና መጠጥም አራት ቀን ኖረች። ከዚህም በኃላ ከእሥር ቤት አውጥታ በጅራፍ ታላቅ ግርፋትን ገርፋ ሁለተኛ ወደ እሥር ቤት መልሳ አሠረቻት በዚያም አረፈች።

እመቤቷም በድኗን አንሥታ ከቤቷ ደርብ ላይ አውጥታ በውጭ ወደታች ጣለቻት። ወድቃ የሚያዩዋት ሰዎች በገዛ ፈቃድዋ እንደወደቀች አድርገው እንዲናገሩ ብላ ነው ስለ መገደሏ ዳኞች እንዳይመራመርዋት ፈርታለች።

በዚያንም ጊዜ በዚያች አይሁዳዊት ሴት ላይ የ #እግዚአብሔር ቁጣ ወረደ ከደርቧ ላይ ስትወርድም በድንገት ወድቃ ሞተች ወደ ዘላለማዊም እሳት ሔደች ይህች የከበረች መጥሮንያ ግን የሰማዕታትን አክሊል ተቀብላ ወደ ዘላለም ሕይወት ሔደች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መጥሮንያ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ንግሥተ_ሳባ

ንግሥት ሳባ ደግ ኢትዮዽያዊት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት። በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ #እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።

ከዚያውም አምልኮተ #እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች። ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ምኒልክን ወልዳለች። ይህቺ ንግሥት በ #ጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች። (ማቴ. 12:42) በስምም "ሳባ: አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች። ዛሬ ዕለተ ዕረፍቷ ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ተቀጸል_ጽጌ /#አጼ_መስቀል/

'ተቀጸል ጽጌ' ማለት 'መስቀል ሆይ! በአበባ አጊጥ' እንደ ማለት ሲሆን 'አጼ መስቀል' ደግሞ አጼ ገብረ መስቀልን አንድም አፄ ዳዊት ቀዳማዊን ይመለከታል። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦

በሃገራችን ኢትዮዽያ የነገረ መስቀሉ ትምሕርት ከመጣ ጀምሮ መስቀል ይከበራል። በአደበባባይ ግን እንዲከበር ያደረጉት የቅዱስ ካሌብ ልጅ አፄ ገብረ መስቀል ናቸው። በወቅቱ ንጉሡ፣ ሠራዊቱ፣ ዻዻሱና ሕዝቡ በተገኙበት ቅዱስ ያሬድ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምጸር።" "መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው: ከጠላትም ያድነናል።" እያለ ይዘምር ነበር።

የአበባ ጉንጉንም ለመስቀሉና ለንጉሡ ይቀርብ ነበር። ከ800 ዓመታት በሁዋላም አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን ባስመጡ ጊዜ መስከረም ቀን ተተክሎ ታላቅ በዓልም ሆኖ ተከብሯል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_10 ና_ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)
"በስመ #አብ_ወወልደ _ወመንፈስ_ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

          #መስከረም ፲ (10) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ገበያተኛውን ሕዝብ አስተምረው ሲጨርሱ ድንጋዩን ዳቦ እያደረጉ ሕዝቡን ይመግቡ ለነበሩት ለታላቁ አባት #አቡነ_ግርማ_ሥሉስ_ለዕረፍታቸው_በዓል #እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

#አቡነ_ግርማ_ሥሉስ፦ አባታቸው ነገደ ኢየሱስ እናታቸው ትኩና ለጽዮን የሚባሉ ሲሆን ትኩና ለጽዮን የዐፄ ሰይፈ አርእድ ልጅ ናት። ስለዚኸም አቡነ ግርማ ሥሉስ ትውልዳቸው ከመንግሥት ወገን ቢሆንም "በዓለም ነግሦ መኖርን አልፈልግም" በማለት የዓለምን ጣዕም ንቀው ገዳም የገቡ ጻድቅ ናቸው። ክቡር ዐፅማቸው ያረፈው በጎንጅ ደብረ ጥበብ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም ነው። ገዳሙ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ከባሕር ዳር 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከጥንታዊቷ የጎንጅ አነስተኛ የገጠር ከተማ ላይ ይገኛል። በጊዜው አወቃቀር የዞኑ ዋና ከተማ ፍኖተ ሰላም ነው። ምንም እንኳን ጎንጂ ቆላላ ለባሕር ዳርና ለአዴት ቅርብ ቢሆንም በአወቃቀር ደረጃ በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ ተካትቷል።

ጎንጅ ቴዎድሮስ ወይም ጎንጅ ደብረ ጥበብ ገዳም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4518 ዓመተ ዓለም በሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ አማካይነት ተመሠረተ። እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ የኦሪት መሥዋዕት ሲሠዋበት ኖሯል። ደብረ ጥበብ የሚለው ስያሜው ከጠቢቡ ተዋነይ ጠቢብነት ጋር ይያያዛል፤ ይኸውም በአሁኑ አጠራር ጎንጅ ደብረ ጥበብ የተባለበት ምክንያት በገዳሙ ታዋቂ የነበረው የቅኔ ሊቅ ተዋነይ የተባለው ሊቅ መወደስ የተባለውን ቅኔ ከተቀኘ በኋላ በደመና ተጭኖ በተመሳሳይ ሰዓት ጎንደር ከተማ ዕጣነ ሞገር የተባለውን ቅኔ በመቀኘቱ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል።

ሊቁ ተዋነይ ከዚኸ ዋርካ ሥር ተደግፎ ለ20 ዓመታት ግስ ገስሶበታል፣ የቅኔ ቀመር ቀምሮበታል፣ መወድስ ዘርፎበታል፣ ተፈላስፎበታል። የአካባቢው ሕዝብ በእምነት የሚኖር አስገራሚና የዋህ ሕዝብ ነው፣ የሀገሬው ሰው አዲስ ልብስ ገዝቶ ከመልበሱ በፊት እሑድ ቀን ወደ ቤተ ክርስትያን ወስዶ አስባርኮ ነው የሚለብሰው።

በገዳሙ ውስጥ 44 ታቦታት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚኸ ታቦታት ውስጥ አንዱ የቅዱስ ባስልዮስ ታቦተ ነው። የጎንጅ ደብረ ጥበብ ካህናት ከ44ቱ ታቦታት ቀድመው የሚጠቅሱት ታቦተ ቅዱስ ባስልዮስን ነው። ምክንያቱም ታቦተ ቅዱስ ባስልዮስ በሌላ ቦታ ሳይኖር በጎንጅ ደብረ ጥበብ ብቻ መኖሩን ለማመልከት ነው። ከቤተ ክርስቲያኑ 50 ሜትር ያህል ከቅጽሩ ደግሞ 25 ሜትር ፈቀቅ ብሎ ትልቁ የተዋነይ ዋርካ በሰባት አክናፍ እንደዣንጥላ ተዘርግቶ ይገኛል። በወረዳው ከጎንጅ ደብረ ጥበብ የቅኔ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ታዋቂው የቅኔ ትምህርት ቤት ዋሸራ ማርያም በዚኹ ወረዳ ይገኛል።

ጎንጅ ገዳም የሚገኘው ትልቅ ተራራ ሥር ሲሆን ሰይጣን ከተራራው ጫፍ ላይ ወጥቶ ድንጋዩን ገደሉን እየናደ ሲጥለው ድንጋዩ እየተፈነቀለ ሲወርድ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሊያፈርስ ሲል ጻድቁ በቃላቸው ድንጋዩን እንዳትንቀሳቀስ ብለው ገዝተው አቁመውታል። በዚያ ትልቅ ገደል ላይ የድንጋዮቹ አቋቋም ላያቸው እጅግ ያስደንቃሉ።

የገዳሙ አስተዳዳሪ ቄስ መልካም በዜ ስለገዳሙ አመሠራረት በቃለ መጠይቅና በጽሑፍ በሰጡት ማስረጃ መሠረት የደብረ ጥበብ ጎንጅ ቴዎድሮስ ገዳም የኦሪት መሥዋት ሲሠዋበት የኖረ መሆኑ፣ ከዋሸራና ከጽላሎ በፊት በእነ ጠቢቡ ተዋናኝ ቅኔ የተዘረፈበትና አሁንም ያለበት መሆኑ፣ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና ዕድሜ ጠገብ የብራና የመቃ ላይ ሥዕላትና በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት ከመሆኑም በላይ ጻድቁ አቡነ ግርማ ሥሉስ የጸለዩበትና ዐፅማቸው ያረፈበት በመሆኑ ልዩና ታሪካዊ ገዳም ያደርገዋል።

ጻድቁ አቡነ ግርማ ሥሉስ ለ40 ዓመት ያህል እሙይት በተባለው ወንዝ አካባቢ ሲጸልዩ ከኖሩ በኋላ በራእይ ተነግሯቸው ወደ ጎንጅ ደብረ ጥበብ ቴዎድሮስ ገዳም በሚሔዱበት ጊዜ ድንጋዮች ተከትለዋቸው ሔደዋል። ተከትለዋቸው ከሔዱት ድንጋዮች መካከል አንዱ ግዝት ድንጋይ እየተባለ የሚጠራው በአሁኑ ወቅት ከገዳሙ 200 ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ በኩል ይገኛል። ከላይ የተከማቸው ድንጋይ ወደ ገዳሙ ለመውረድ ሲንከባለል ተገዝቶ ቆሞ ላየው ይደንቃል። ድንጋዩ ከከተማው እስከ ገዳሙ ድረስ አልፎ አልፎ ተንጠባጥቦ ይታያል።

ጻድቁ ወንጌልን ሊያስተምሩ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወሩ ዛፎችና ድንጋዮች ሁሉ ይከተሏቸው ነበር። አቡነ ግርማ ሥሉስ ገበያተኛውን ሕዝብ አስተምረው ሲጨርሱ ድንጋዩን ዳቦ እያደረጉ ሕዝቡን ይመግቡ የነበሩ ታላቅ አባት ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በተኣምራት በአካላቸው ላይ ማዕተብ አድርገው፣ በእጃቸው መስቀል ይዘው እና ተገዝረው ነው። ከልጅነታቸው ጀምረው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ከጨረሱ በኋላ አበምኔትና መምህር በመሆን በገዳሙ ለ40 ዘመን በመምህርነት አገልግለዋል።

በተጋድሏቸውም ወቅት እሙይት ከተባለው ባሕር ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ ያድሩ ነበር። በኋላ ከእሙይት ባሕር ወደገዳማቸው ቦታ ሲመለሱ ድንጋዮች "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አቡነ ግርማ ሥሉስ" እያሉ ከእሙይት ባሕር እስከ ጎንጂ ድረስ ተከትለዋቸዋል። በኋላም ወደ ገዳሙ ሊወርዱ ሲሉ አብዛኛው ድንጋይ በጻድቁ ቃለ ግዝት ከአፋፍ በላይ ሲቀር፣ ሦስቱ ድንጋዮች ግን አባታችንን "ከወደቁበት እንወድቃለን" ብለው ተከትለዋቸው ሲወርዱ "አይሆንም ተመለሱ" ብለው አዘዟቸው። ድንጋዮቹም ካለበት ቦታ ላይ ቆመው በመቅረታቸው "ግዝት ድንጋዮች" ተብለው እስከዛሬ ድረስ ይጠራሉ።

ድንጋዮቹ የቆሙበት ቦታ ከታች ቁልቁለታማ ገደል ቢሆንም ምንም ሳይሆኑ በጻድቁ ቃለ ግዝት እንደቆሙ ቀርተዋል። ከአፋፍ በላይ የቀሩት ሌሎቹ ደንጋዮች በአሁኑ ወቅት ከጎንጂ ቆለላ ከተማ ከገበያው መሐል ይገኛሉ። ቦታው ከጊዜ በኋላ ገበያ እንደሚቆምበት የታያቸው አቡነ ግርማ ሥሉስ ከባሕር ውስጥ ወጥተው "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አቡነ ግርማ ሥሉስ" እያሉ የተከተሏቸውን ድንጋዮች ባሉበት ቦታ ላይ እንዲቆሙ ጻድቁ በቃላቸው ሲያዟቸው "ከጊዜ በኋላ ከዚኸ ቦታ ላይ ገበያ ይቆማል፣ የደጋውና የቆላው ወገኔ ለገበያ በሚገናኙበት ጊዜ ማረፊያና የሸቀጣሸቀጡ መቀመጫ ትሆናላችሁ" ብለው ስላሏቸው በአሁኑ ወቅት በቍጥር ከ60 በላይ የሚሆኑ ድንጋዮች በገበያው ቦታ ላይ በየቦታው በመደዳ ተሰድረው ለገበያተኛው ሕዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

አቡነ ግርማ ሥሉስ የትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆን በተወለዱ ጊዜ ብርሃን ከሰማይ ወርዶላቸዋል። አስቀድመን እንደጠቀስነው የዐፄ ሰይፈ አርእድ የልጅ ልጅ ቢሆኑም ንግሥናን ትተው ዓለምን ንቀው ስለመነኑ መጽሐፍ "መናኔ መንግሥት ወብእሲት" ይላቸዋል። በአሁኑ ወቅት ከደብረ ጥበብ ገዳም ከፍ ብሎ በአቡነ ግርማ ሥሉስ ስም የተሰየመ ጠበል ፈልቆ ሕሙማን በየጊዜው እየተፈወሱበት ይገኛሉ። መስከረም 10 ቀን በገዳማቸው በዓለ ዕረፍታቸው በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። ከአባታችን አቡነ ግርማ ሥሉስ #እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው።
² አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው። ታዲያ ምንድር ነው?
³ የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?
⁴ እንዲህ አይሁን፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን።
⁵ ነገር ግን ዓመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያስረዳ ከሆነ ምን እንላለን? ቍጣን የሚያመጣ እግዚአብሔር ዓመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ልማድ እላለሁ።
⁶ እንዲህ አይሁን፤ እንዲህ ቢሆን እግዚአብሔር በዓለም እንዴት ይፈርዳል?
⁷ በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል?
⁸ ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና። የእነርሱም ፍርድ ቅን ነው።
⁹ እንግዲህ ምን ይሁን? ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤
¹⁰ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦
¹¹ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥
¹² በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም።
¹³ ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤
¹⁴ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤
¹⁵ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤
¹⁶ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥
¹⁷-¹⁸ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።
¹⁹ አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤
²⁰ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።
²¹ አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥
²² እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤
²³ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤
²⁴ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።
²⁵ እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥
²⁶ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።
¹⁴ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።
¹⁵ ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤
¹⁶ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።
¹⁷ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
¹⁸ የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
¹³ በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፥ ጴጥሮስና ዮሐንስም፥ ያዕቆብም፥ እንድርያስም፥ ፊልጶስም፥ ቶማስም፥ በርተሎሜዎስም፥ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፥ ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳም።
¹⁴ እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምዒ እዝነኪ"። መዝ 44፥9-10።
"የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ መዝ 44፥9-10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_10_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  ሉቃስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁶ ማርያምም እንዲህ አለች፦
⁴⁷ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
⁴⁸ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
⁴⁹ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።
⁵⁰ ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
⁵¹ በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤
⁵² ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
⁵³ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
⁵⁴-⁵⁵ ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።
⁵⁶ ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች።

#ወይም

ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
² ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
³ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
⁴ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
⁵ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
⁶ እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
⁷ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
⁸ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
⁹ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
¹⁰ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
¹¹ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
¹² እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
¹³ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_ማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የፄዴንያ ማርያም በዓልና የ #መስቀሉ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
#መስከረም_10_ግማደ_መስቀሉ_ወደ_ኢትዮጵያ_የገባበት ቀን፡
የ"ጌታችን ቅዱስ መስቀል" ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ዐፄ ዳዊት ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን 47ኛው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል  በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ መኖር በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በ #እግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡ አጼ ዳዊትም ወታደራቸውን ወደ ግብፅ አዘመቱ፡፡ በወታደሩም ኃይል የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ተነሱ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡

ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም #የክብር_ባለቤት_ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የተሰቀለበትን #መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ መስከረም 10 ቀን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ #መስቀሉ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የ #ጌታችን_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን_መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን "ተቀጸል ጽጌ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

#ተቀጸል_ጽጌ /#አጼ_መስቀል/

'ተቀጸል ጽጌ' ማለት 'መስቀል ሆይ! በአበባ አጊጥ' እንደ ማለት ሲሆን 'አጼ መስቀል' ደግሞ አጼ ገብረ መስቀልን አንድም አፄ ዳዊት ቀዳማዊን ይመለከታል። ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ፦

በሃገራችን ኢትዮዽያ የነገረ መስቀሉ ትምሕርት ከመጣ ጀምሮ #መስቀል ይከበራል። በአደበባባይ ግን እንዲከበር ያደረጉት የቅዱስ ካሌብ ልጅ አፄ ገብረ መስቀል ናቸው። በወቅቱ ንጉሡ፣ ሠራዊቱ፣ ዻዻሱና ሕዝቡ በተገኙበት ቅዱስ ያሬድ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምጸር።" "መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነው: ከጠላትም ያድነናል።" እያለ ይዘምር ነበር።

የአበባ ጉንጉንም ለመስቀሉና ለንጉሡ ይቀርብ ነበር። ከ800 ዓመታት በሁዋላም አፄ ዳዊት ግማደ #መስቀሉን ባስመጡ ጊዜ መስከረም ቀን ተተክሎ ታላቅ በዓልም ሆኖ ተከብሯል።

#መስቀሉ ላዳነን #ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የ #መድኃኒታችን_የመስቀሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
በዐርብ ቀን ደም ለአፈሰሱ ጣቶችህና ለጣቶች ጥፍሮች ሰላምታ ይገባል። የ #አብ የቅድምና ስሙ ስምህ የሆነልህ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ በመለኮታዊ ላብ የታጠበው የ #መስቀልህ ክንፍ እንደ ፊያታዊ ዘየማን በራሴ ላይ ይዘርጋልኝ።

#መልክዐ_ቅዱስ_ዕፀ_መስቀል
#በዓለ_ስዕለ_አድኅኖ

፩- የቅዱሳት ሥዕላት ትርጉም፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት እና ትውፊት ቅዱሳት ሥዕላት ማለት፤ በአብያተ ክርስቲያናት ግድግዳ፡ በሸራ፡ በብራና፡ በወረቀት እና በመስቀሎች ላይ በቀለም ወይም በጭረት ባለ ሁለት ጎን ሆነው የሚሠሩ የልዑል #እግዚአብሔርን#የእመቤታችንን፡ የቅዱሳን መላዕክትን፡ የጻድቃንን እና የሰማዕታትን ማንነት የሚገልጥ መንፈሳዊ ጥበብ ነው። ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ መንፈሳዊ መልዕክት ከሌላቸው ሌሎች ሥዕላት ፈጽመው ስለሚለዩ ቅዱሳን ሥዕላት ይባላሉ።

፪- የቅዱሳት ሥዕላት አመጣጥ፤

፪-፩ በብሉይ ኪዳን

ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለያዘው ቦታ መሠረቱ የሁሉ አስገኝ የሆነው አምላካችን #እግዚአብሔር አስቀድሞ ለነቢዩ ሙሴ ሥዕለ ኪሩብን በሥርየት መክደኛው ታቦት ላይ እንዲያዘጋጅ ማዘዙ ነው። ለዚህም መሠረት በዘጸ. ም. ፳፭፡ቁ ፳፪ “በዚያም ካንተ ጋር እገናኛለሁ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ” ብሎ መናገሩ ነው። #እግዚአብሔርም የተናገረውን የማያስቀር ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴን በሥዕለ ኪሩብ መካከል ሆኖ ድምጹን አሰምቶታል።

፪-፪ በሐዲስ ኪዳን

ከሐዋርያዊ ተልዕኮውና የሕክምና ሞያው በተጨማሪ የሥዕል ጠቢብ የነበረው ቅዱስ ሉቃስም ምስለ ፍቁር ወልዳን (እመቤታችን ከልጇ ከወዳጇ ጋር ሆና) በመሳል ለትውልድ አቆይቶልናል። በተጨማሪም ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ለጢባርዮስ ቄሳር የ #ጌታችንን ሥነ-ስቅለት ሥዕል አዘጋጅቶ ሰጥቶታል።

፫- ቅዱሳት ሥዕላት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ ፊደል፡ ሥነ ጽሁፍ፡ ዜማ፡ ኪነ ህንፃ… ወዘተ እንዳሏት ሁሉ የራሷ የሆነ የሥነ ሥዕል ጥበብም ያላት ስንዱ እመቤት ናት። ከጥንተ ክርስትና የአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቦታ እንደነበረው የአርኪዮሎጂ ግኝቶችና የጥንት አብያተ ክርሰቲያናት ፍርስራሾች ያመለክታሉ። በተለይ በዘመነ አክሱም ተሠርተው በከፊል የፈረሱ እና ከመፍረስ የተረፉ እንደ አብርሃ ወአጽብሐ፡ ውቅሮ ቅዱስ ቂርቆስ፡ ደብረ ዳሞ ገዳም፡ መርጡለ ማርያም፡ ወዘተ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የያዟቸው
ሥዕሎች የዘመኑን የሥዕል ጥበብ አሻራ ያሳያሉ። በተለይ በመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥዕል ጥበብ ያደገበት ዘመን ነበር። በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የምናገኛቸው ሥዕላት በዚህ ዘመን የተሠሩ ናቸው።

፬- የቅዱሳት ሥዕላት ጥቅም፡

፬-፩ ለሥርዓተ አምልኮ

ቅዱሳት ሥዕላት ሰውንና #እግዚአብሔርን የሚያገናኙ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው። በሥዕል ፊት ቆሞ መጸለይ፡ ወይንም መስገድ ሥዕሉን አምላክ ማድረግ አይደለም። ነገር ግን የሥዕሉን ባለቤት በሥዕሉ ፊት ሆኖ በመማጸን በረከቱን ለማግኘት የሚፈጸም ሥርዓት ነው። ሥዕሉ ለባለቤቱ መታሰቢያ ነው። “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ተብሎ እንደተጻፈ” ምሳ. ፲፡፯ የሥዕሉን ባለቤት አቅርቦ ያሳየናል። ገድሉን፣ ተአምራቱንና ቃል ኪዳኑን ያስታውሰናል። በመንፈስም ድልድይ ሆኖ ከሥዕሉ ባለቤት ያገናኘናል።

ሙሴና አሮን ወደ ደብተራ ኦሪት ገብተው በታቦቱና ሥዕለ ኪሩብ ፊት እየሰገዱ ከ #እግዚአብሔር ትዕዛዝ ይቀበሉ ነበር ዘኁ. ፲፮፡፵፭

፬-፪ ለትምህርት

ቅዱሳት ሥዕላት ሲሣሉ የሥዕሉን ባለቤት ዐቢይ ገድልና ተአምራት በሚያጎላ መልኩ ነው። ስለሆነም ማንኛውም ምእመን የሥዕሉን ባለቤት መንፈሳዊ ተጋድሎ በቀላሉ እንዲረዳ ያደርገዋል። ለምሳሌ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል ሲሣል ለ22 ዓመታት 8 ጦሮችን ከግራ ከቀኝ ከፊት ከኋላ አስተክለው ሲጸልዩ አንድ እግራቸው በቁመት ብዛት መቆረጡን እንዲሁም ስለ ቅድስናቸው ከተሰጣቸው ስድስት የብርሃን ክንፎች ጋር ተደርጎ ይሣላል። ክህነታቸውን ለመግለጽም የእርፍ መስቀልና ጽና ይዘው ይሣላል። የሥዕሉ ባለቤት እንዲታወቅም በሥዕሉ ላይ አጭር የጽሑፍ መግለጫ ይቀመጣል። ”ዘከመ ጸለየ አቡነ ተክለሃይማኖት” እንዲል። በዚህ ሥዕል ምእመናን የጻድቁን ተጋድሎ ይማሩበታል፤ አርአያም ያደርጉታል።

እንግዲህ ቅዱሳት ሥዕላት ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡን ከሆነ በጥንቃቄ በመያዝ መገልገል እንደሚገባና ዘወትር በጸሎት ሰዓት ከፊት ለፊታችን በማስቀመጥ ልንጸልይ እንደሚገባ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
❀እንኳን አደረሳችሁ!

#ማርያም እግዝእት (ጼዴንያ)
#መስቀል ዕጸ ሕይወት
#ማክዳ ንግሥት
#ሐና ዕብራዊት
#ዮዲት ቅድስት
#አትናስያ ቡርክት
#መጥሮንያ ሰማዕት
#ማርታ ብጽዕት
#ኢያቄም ወላዴ በረከት
#ግርማሥሉስ ገባሬ መንክራት
2024/09/20 16:15:20
Back to Top
HTML Embed Code: