Telegram Web Link
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† መስከረም ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት †

[  † እንኳን ለጻድቁ አባ ሙሴ እና አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]


† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊   አባ ሙሴ ዘሲሐት  🕊   †

† ገዳመ ሲሐት የሚባሉ ብዙ ቦታዎች አሉ:: ቅድሚያውን የሚይዘው ግን የግብጹ ነውና ዛሬ የዚህን ገዳም አንድ ቅዱስ እናስባለን:: ሕይወታቸውም በእጅጉ አስተማሪ ነው:: ቅዱሱ አባ ሙሴ ይባላሉ:: የ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ናቸው::

እኒህ ጻድቅ አንድ ነገር ከሌሎች ቅዱሳን ይለያቸዋል:: ከምግባርና ትሩፋት በቀር አንድም የእግዚአብሔር ቃል አያውቁም:: ዝም ብለው በየዋሕነት ይኖሩ ነበር እንጂ:: ተወልደው ባደጉበት በምድረ ግብጽ በቅን ሕይወት ኑረው: በወጣትነታቸው ወደ ደብረ ሲሐት ገቡ::

በዚያም በብሕትውና ዘግተው በጾምና ጸሎት ተወስነው ለ፵፭ [45] ዓመታት ኖሩ:: እጅግ የዋሕ ሰው ናቸውና ከጸጋ [ከብቃት] ደረሱ:: ሰው በአካባቢው አልነበረምና አብረው የሚውሉት ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር:: አራዊቱም ጻድቁን ያጫውቷቸው: ይታዘዙላቸውም ነበር:: በፈንታው ደግሞ አባ ሙሴ በተአምራት ዝናብ ያዘንቡላቸው: ምግብም ይሰጧቸው ነበር::

አባ ሙሴ ልብስ አልነበራቸውምና በቅጠል ይሸፈኑ ነበር:: የምግባቸው ነገርማ "በመጠነ ኦፍ" ይላል . . . ትንሽ ድንቢጥ የምትበላውን ያህል ቀምሰው: ጥርኝ ውሃም ተጐንጭተው ነበር የሚኖሩት:: በሁዋላ ግን እጅግ ከመብቃታቸው የተነሳ ዐይናቸውን ሲገልጡ 'ገነት' [የአትክልት ሥፍራ] ይታያቸው ነበር:: ከዚያም ለበረከት ቆርጠው ይበሉ ነበር::

ሰይጣን እርሳቸውን ይጥል ዘንድ እጅግ ቢጥርም አልተሳካለትም:: በስተ መጨረሻ ግን የሚጥልበት መንገድ ተከሰተለት:: ምንም ባለ መማራቸው ሊፈትናቸውም ተነሳ:: አንድ ቀን ከበአታቸው በር ላይ ከአራዊት ጋር ተቀምጠው ሳለ ሰይጣን ሽማግሌ መነኩሴ መስሎ እየተንገዳገደ መጣ::

አራዊቱ ደንግጠው ሲሸሹ እርሳቸው ግን ሳያማትቡ ሮጥ ብለው ደገፉት:: ወደ በዓታቸውም አስገቡት:: ማታ ላይ ሲጨዋወቱ "ማንነትዎን ይንገሩኝ" አላቸው:: ለአባ ሙሴ ሰይጣኑ የበቃ አባት መስሏቸዋልና የ፵፭ [45] ዓመታት ድንግልናዊ የተባሕትዎ ሕይወታቸውን ነገሩት::

እርሱም በፈንታው ሐሰቱን ቀጠለ:: "እኔ ግፍ እየሠራሁ በዓለም እኖር የነበርኩ ሰው ነኝ:: ነገር ግን ዓለምን ትቼ ላለፉት ፵ [40] ዓመታት በበርሃ በንስሃ ኑሬአለሁ:: ያም ሆኖ አንዲት ሴት ልጅ አለችኝና 'ማን ያገባታል' ብየ ስጨነቅ አንተ እንደምታገባት ተገለጠልኝ" አላቸው::

አባ ሙሴ ደንግጠው "እንዴት ድንግልናየንና ሕይወቴን ትቼ አገባለሁ?" ሲሉም ጠየቁ:: ሰይጣን ግን ቃለ እግዚአብሔር እንደማያውቁ ተረድቷልና "አንተ ከአብርሃም: ከያዕቆብ: ከዳዊት ትበልጣለህ? እነሱ አግብተው የለ!" ብሎ ቢገስጻቸው አንዳንዴ አለ መማር ክፉ ነውና አባ ሙሴ ሸብረክ አሉ: ተረቱ::

ከዚያም ተያይዘው ጉዞ ወደ ዓለም ሆነ:: መንገድ ላይ ግን መነኩሴ ነኝ ያለው ሰይጣን ወደቀና የሞተ መሰለ:: አባ ሙሴ በእንባ ቀብረውት ሲሔዱ ተኖ ጠፋ:: አባ ሙሴ ቀና ሲሉ ሰይጣን በምትሐት የሠራውን ያማረ ግቢና ቆንጆ ሴት አዩ:: ወደ እሷ እቀርባለሁ ሲሉ አውሎ ንፋስ ማጅራታቸውን መትቶ ጣላቸው::

አባ ሙሴ ከወደቁበት ሲነሱ ያዩት ነገር ሁሉ ሰይጣናዊ ምትሐት መሆኑን አወቁ:: ወደ በአታቸው መጥተው ከገነት ፍሬ ቢቀምሱ ጸጋ እግዚአብሔር ተለይቷቸዋልና መራራ ሆነባቸው:: እያለቀሱ ከበዓታቸው ወጡ::

መንገድ ላይ ያው ሰይጣን ነጋዴ መስሎ: "መንገድ ልምራዎት" ብሎ ምንም ከሌለበት በርሃ ላይ ጥሏቸው ተሰወረ:: የሚያደርጉት ጠፋባቸው:: ረሃቡ: ጥሙ: ከፈጣሪ ጸጋ መለየቱ አቃጠላቸው:: አሁንም አንዲት ሴት መነኩሴ ድንገት መጥታ ወደ በዓቷ አስገባቻቸው::

የማይገባውን ድርጊት እናድርግ ብላ አባበለቻቸው:: ይባስ ብላ ወደ አይሁድ እምነት እንዲገቡ አሳመነቻቸው:: ወዲያውም ወደ ሌላ በርሃ ወስዳ "አወቅኸኝ?" አለቻቸው:: "የለም" አሏት:: እዚያው ላይ ተቀይራ ጋኔን መሆኗን አሳይታቸው ተሠወረች::

አባ ሙሴ በዚያው ሥፍራ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አጡ:: አለቀሱ: ተንከባለሉ:: እንባቸው እንደ ዥረት ፈሰሰ:: ልቡናቸው ሊጠፋ ደረሰ:: ወደ ፊታቸው አፈር እየረጩ: "ወየው" እያሉ ሲያለቅሱ ጌታችን መልአኩን ላከላቸው::

እንደ ቀድሞውም ፊት ለፊት ታይቶ አጽናናቸው:: "አይዞህ! ፈጣሪ እንባህንና ንስሃህን ተቀብሏል" ብሎ ወደ ስውራን ከተማ ወሰዳቸው:: በዚያም ለ፯ [7] ቀናት ቆይተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: አባ ሳሙኤልም ቀብሯቸዋል::


†  🕊  አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ  🕊   †

† ጻድቁ የነበሩት በ፲፫ [13] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የተወለዱት ትግራይ ውስጥ ነው:: ዛሬም ድረስ የብዙ ስውራን ቤት እንደ ሆነ የሚታወቀውን ደብረ_ሐዘሎንም እርሳቸው እንደ መሠረቱት ይነገራል:: አባ አንበስ ከገዳማዊ ትሩፋታቸው ባሻገር በአንበሶቻቸው ይታወቁ ነበር::

የትም ቦታ ሲሔዱ በአንበሳ ጀርባ ላይ ነበር:: በእርግጥ አባቶቻችን ከዚህም በላይ ብዙ ድንቆችን ማድረግ ይችላሉ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነውና:: ጻድቁ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ: የሳሙኤል ዘዋልድባና የአባ ብንያሚን ባልንጀራ ናቸው:: ዛሬ ደግሞ ዕረፍታቸው ነው::

† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፈተና አስቦ እኛን ከመከራ ይሰውረን:: በቃል ኪዳናቸው ይጠብቀን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

🕊

[  † መስከረም ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አባ ሙሴ ዘደብረ ሲሐት
፪. አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ
፫. አበው ኤዺስ ቆዾሳት
፬. አባ ዲዮናስዮስ
፭. አባ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ በትንከል ዲያቆን

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው [ዘካርያስና ስምዖን]
፬. አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭. አቡነ ዜና ማርቆስ
፮. አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
፯. ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ [ዓምደ ሃይማኖት]

† " በመጠን ኑሩ: ንቁም:: ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና:: በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት::" † [፩ዼጥ.፭፥፰] (5:8)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
#በቸርነትህ_ዓመታትን_ታቀዳጃለህ
መዝ 65፥11

ስለሁሉ እግዚአብሔር ይመስገን እንደ ኃጥአታችን ያይደለ እንደቸርነቱ የንስሃ ጊዜ የፍሬ ጊዜ ሰጥቶናልና እናመሰግነው ዘንድ ይገባናል፡፡ ምስጋናችንም ይህን የተወዳጅ ሐዋርያ የቅዱስ ጳውሎስን ቃል በመተግበር እንግለፅ፡፡

“ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” ኤፌ 4፥22


🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
🌼 #መልካም_አዲስ_አመት🙏 🌼
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
                          †                          

🌼 [ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ! ] 🌼

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊
       
" ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን መውቀስ ... "
.........

" ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን መውቀስም አለ፡፡ ከእናንተ መካከል ፦ " እንዴት ሆኖ ?  እርግጥ ነው ብዙውን ጊዜ ሠራተኞቻችንን እንወቅሳለን ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ መውቀስስ እንደምን ያለ ነው ? " የሚል ሊኖር ይችላል፡፡

አዎ ! የሚሰክር ወይም የሚሰርቅ ሠራተኛ ወይም ጓደኛ ብንመለከት ወይም ከዘመዳችን አንዱ ወደ ተውኔት ቤት ፣ ወይም ለነፍሱ ምንም ረብሕ [ ጥቅም ] ወደማያገኝበት ሥፍራ ሲሮጥ ፣ በከንቱ ሲምል ፣ የሐሰት ምስክርነትን ሲሰጥ ፣ ወይም ሲዋሽ ፣ ወይም ሲቆጣ ብናየው ጀርባችንን ብንሰጠውና ብንገስፀው ወቀሳችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡

ዳግመኛም አንድ ሰው ቢበድለን ፣ እርሱ ራሱ የሠራውን ጥፋት በእኛ ቢያመካኝ ስለ እግዚአብሔር ብለን ይቅር ልንለው ይገባል፡፡ ብዙዎቻችን ግን ለጓደኞቻችን ፣ ለሰራተኞቻችን የዚህ ተቃራኒውን ነው የምናደርገው፡፡

ጓደኞቻችን ወይም ሠራተኞቻችን ቢበድሉን እናንባርቃለን ፤ ይቅርታ የሌለው ፍርድም እንፈርድባቸዋለን፡፡ እኛው ራሳችን እግዚአብሔርን በገቢር ስናስቀይም አንድም ስናሰድብ ወይም ነፍሳችንን ስንጎዳ ግን እንደበደልን አንቆጥረውም፡፡

ይህ ግን በአዲሱ ዓመት ልናስተካክለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ዕለት ዕለትም ልንለማመደው የሚገባ ነገር ነው፡፡ "

🕊

[ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ]


†                       †                        †
🌼                    🍒                     🌼
Forwarded from አብሰራ ገብርኤል ለማርያም (♱ ባሕራን ♱)
🕊                    💖                   🕊

[ 🌼  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  🌼 ]

                        🕊                       

🕊                   

እንኳን ለቅዱስ እና ታማኝ ሐዋርያ ዮሐንስ ወንጌላዊ የልደቱ መታሰቢያ አደረሳችሁ።

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

[ መስከረም ፬ [ 4 ] ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ልደቱ ]

ካህናቱ በሰዓታት ምስጋናቸው የአምደ ሃይማኖት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ቃል አንደበታቸው በማድረግ እንዲህ ያመሰግኑታል።

🕯

[ ዮሐንስ እንደ መላእክት ንጹሕ ነው ፤ ድንግል ዮሐንስ የቅዱሳን መመኪያ ነው ፤ ዮሐንስ በብርሃን መጎናጸፊያ ሐር የተጌጠ ነው ፤ ዮሐንስ የቤተክርስቲያን አርጋኖን ነው በኤፌሶን የአዋጅ ነጋሪ ዮሐንስ ኃጥአን ለምንሆን ለእኛ ይቅርታን ይለምንልን።]

[ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ደሙ በፈሰሰ ጊዜ ዮሐንስ ፍቅሩን አላጎደለም። ]

[ በወዳጁህ በዮሐንስ ድንግልና በንጽሐ ሥጋውም አቤቱ ይቅር በለን።]

🕊

† በዚህች ዕለት ቅዱሱ ሐዋርያ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ: ከአባቱ ዘብዴዎስ መወለዱን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች::

የግፍና የመከራ ጽዋዕ በመላባት ዓለማችን… ትዕግሥቱ ፤ ጥላቻና መገፋፋት በነገሠባት ምድራችን… ፍቅሩ ፤ ኃጢአትና መተላለፍ በሠለጠነባት ሕይወታችን… በረከቱ ፤ እርሱ በተወለደባት በዚህች ዕለት በእኛም ልቡና ይወለድ ዘንድ ምልጃው አይለየን።

†                       †                        †
🌼                    🍒                     🌼
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ 

[  ✞  🌼  እንኩዋን ለብርሃነ መስቀሉ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  🌼 ✞  ]


🕊  ✞ ቅዱስ ዕፀ መስቀል ✞  🕊

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ:
¤ ከግራ ቁመት:
¤ ከገሃነመ እሳት:
¤ ከሰይጣን ባርነት:
¤ ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል::

" እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ " እንዳለ ሊቁ::

ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት::

እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት [ዘፍ.፬፥፲፭]  ጀምሮ

¤ ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት [ዘፍ.፳፪፥፮]
¤ ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል [ዘፍ.፳፰፥፲፪]
¤ ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ [ዘፍ.፵፰፥፲፬]
¤ ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ_በትር [ዘጸ.፲፬፥፲፭]
¤ የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት [ዘኁ.፳፩፥፰]  ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል::

ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: [መዝ.፶፱፥፬]

በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም "መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም: መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

ቅዱስ_ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል:: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: [፩ቆሮ.፩፥፲፰  ገላ.፮፥፲፬]

አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::


†  🕊   በዓለ መስቀል  🕊  †

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም::

መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ፪፻፸ ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እናታችን ቅድስት እሌኒ [ሔለና] በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች::

መስከረም ፲፯ ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት ፲ ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ፲ ዓመት በሁዋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም ፲፯ ቀን ተቀድሷል::

ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ [ግሸን ማርያም] ተለብጦ ተቀምጧል::


†  🕊 ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ  🕊 † 

ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ [ሰማርያዊ] ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ ጐልጐታ ነን" አሉት::

እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::


†  🕊  ቅድስት ታኦግንስጣ  🕊   †

በ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

🕊

[  †  መስከረም ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፪. ቅድስት እሌኒ ንግስት
፫. ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ
፬. ቅዱስ መቃርስ ሊቀ ዻዻስ
፭. ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ
፮. ብጽዕት ታኦግንስጣ ሮማዊት
፯. ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት [ቀዳሜ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ ዘብዴዎስ]
፫. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬. አባ ገሪማ ዘመደራ
፭. አባ ዸላሞን ፈላሢ
፮. አባ ለትጹን የዋህ
፯. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ [ዘደሴተ ቆዽሮስ]

" የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና . . . መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ:: የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ:: እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን:: " [፩ቆሮ.፩፥፲፰-፳፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/11/17 11:39:49
Back to Top
HTML Embed Code: