Telegram Web Link
🕊

[  † እንኳን ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዘዮሐንስ እና ለሰማዕቱ አባ ኖብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። †   ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  †  አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ  †  🕊

† ኢትዮጵያዊው ጻድቅ የተወለዱት በ፲፫ [13] ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሸዋ [መርሃ ቤቴ] ነው:: ወላጆቻቸው ዘካርያስ እና ሶፍያ እግዚአብሔርን የሚፈሩ : እመ ብርሃንን የሚወዱና ለነዳያን የሚራሩ ነበሩ::

ደጉ ዘካርያስ መስፍን ሲሆን እርሱ በሌለበት የሸዋ ገዢ ሊያገባት በመሞከሩ ቅዱስ ገብርኤል ቀስፎታል:: ሕዝቡ ገዢነቱን ለዘካርያስ ሰጥተውታል:: ከቆይታ በኋላም ድንግል ማርያም የተባረከ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን "ዮሐንስ" አሉት:: በሒደት ግን ዘዮሐንስ [የዮሐንስ] ተብሏል::

ቅዱሱ ዘዮሐንስ እስከ ሰባት ዓመቱ ድረስ በእናቱ እቅፍ ቆይቶ ወደ ትምሕርት ገብቷል:: ጸጋ እግዚአብሔር ጠርቶታልና በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አደን ይወድ ነበርና ሊያድን ሲወጣ 'ብርሕት ደመና' ድንገት ነጥቃ ከኢትዮጵያ [ሽዋ] ወደ ኢየሩሳሌም [ጐልጐታ] አደረሰችው::

ደስ ብሎት ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ደመናዋ ወደ ሃገሩ መለሰችው:: ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከሰማይ ነቢዩ ኤልያስና መጥምቁ ወርደው ባረኩትና "ክፍልህ ከእኛ ጋር እንዲሆን መንን" አሉት::

ዘዮሐንስ ወላጆቹንና ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ [ዲቁና ነበረውና] ሃያ አምስት ዓመት ሞላው:: ያን ጊዜ ወላጆቹ "እንዳርህ" ቢሉት "የለም! አይሆንም" አላቸው:: አርጅተው ነበርና ስለእነርሱ ዕረፍት ጸለየ:: ፈጣሪም ሰምቶታልና ሁለቱም በክብር ተከታትለው ዐረፉ::

ሕዝቡ በወላጆቹ ፈንታ "እንሹምሕ" ቢሉት "እንቢ" ብሎ ወርቁን : ብሩን : ርስቱን : ቤቱን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ::ጊዜው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ባረፉ በሃምሳ ዓመት አካባቢ ሲሆን አባ ሕዝቅያስ አበ ምኔት ነበሩ::
[ከዚህ በኋላ አንቱ እያልን እንቀጥል]

አባ ዘዮሐንስ ለሰባት ዓመታት ገዳሙን ረድተው መነኮሱ:: እንደ ልማዱ ደመና ነጥቆ ወስዷቸው ከኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ቅስና ተቀብለዋልና በደብረ ሊባኖስ ለሃያ አምስት ዓመታት አገለገሉ:: ቤተ መቅደሱን በመዓልት ሰባት ጊዜ በሌሊት ሰባት ጊዜ ያጥኑ : እልፍ እልፍ ይሰግዱ : ተግተው ይጸልዩ : ይታዘዙም ነበር::

ከዚያም በፈጣሪ ትዕዛዝ በትግራይና በሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ወንጌልን ሰብከዋል:: እድሜአቸው ሰባ በሆነ ጊዜ ወደ ጌታ መቃብር [ጐልጐታ] ሔደው ተሳልመው በእርሱ [በጌታ] ትዕዛዝ ወደ ደራ [ጣና ዳር] ተመለሱ::

በአካባቢውም ገብርኤልና መስቀል ክብራ የሚባሉ ደጋግ ባለ ትዳሮች ነበሩና በእንግድነት ከቤታቸው አደሩ:: ቤቱ በቅጽበት በበረከት ሞላ:: እነርሱም የጻድቁን አምላክ አመሰገኑ::

ቀጥሎም በመስቀል ክብራ መሪነት ጻድቁ ዘዮሐንስ ወደ ክብራን ገብርኤል ደሴት ገቡ:: [በነገራችን ላይ ደሴቱ ክብራን የተባለ መስቀል ክብራ በምትሰኘው ደግ ሴት ስም ነው:: እርሷና ባሏ ገብርኤል የተቀደሱ ሰዎች ነበሩና::]

ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ ወደ ደሴቶቹ [ክብራንና እንጦንስ ኢየሱስ] እንደ ገቡ ደሴቶቹ በግማሹ የስውራን ቤት : እኩሉ ደግሞ የጣዖት [ዘንዶ] አምላኪዎች መኖሪያ ነበር:: ጻድቁ ክብራን ገብርኤልንና እንጦንስ ኢየሱስን የመሠረቱት በ1315 ዓ/ም አካባቢ በዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመን ነው:: በአካባቢው ዘንዶ ይመለክ ነበርና ያንን በጸሎታቸው አጥፍተው ሕዝቡን አጥምቀዋል::

በዚያም ገዳሙን የወንድና የሴት ብለው ከፈሉ:: የወንዶች ክብራን ሲሆን ሴት አይገባበትም:: አበ ምኔቱም ራሳቸው ጻድቁ ነበሩ:: የሴቶች እንጦንስ ኢየሱስ ከካህናት በቀር ወንድ አይገባበትም:: እመ ምኔቷም እናታችን ቅድስት ክብራ [መስቀል ክብራ] ሆነች::

ጻድቁ አቡነ ዘዮሐንስ በክብራን ለሰላሳ አምስት ዓመታት ተጋድለዋል:: ለጸሎት ከመቆማቸው ብዛት እግራቸው አብጦ : ቆሳስሎ ነበር:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ይገለጽላቸው : ያነጋግራቸውም ነበር::

እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርተው: ለወንጌል እንደሚገባ ኑረው: በተወለዱ በመቶ አምስት ዓመታቸው በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: ጌታችንም በስማቸው ለተማጸነና ገዳማቸውን ለሳመ የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል:: ልደታቸው ደግሞ ኅዳር ፲፫ [13] ቀን ይከበራል:: ገዳማቸው [ክብራን ገብርኤልና እንጦንስ ኢየሱስ] ድንቅ ነውና እንድታዩት ተጋብዛቹሃል::


🕊  †  ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት  †  🕊

† በምድረ ግብጽ ከታዩ ታላላቅ ከዋክብት አንዱ ቅዱስ ኖብ በሃገረ ንሒሳ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ዘመኑም ዘመነ ሰማዕታት [፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን] ነው:: ወላጆቹ በልጅነቱ ብዙ ሃብት ትተውለት ያርፋሉ:: ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ካህኑ ስለ ምናኔና ሰማዕትነት ሲሰብክ ይሰማዋል::

ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ በቤቱ የነበረውን ሁሉ ለነዳያን አካፍሎ መስቀለ ክርስቶስን ሊሸከም ወደ ዐውደ ስምዕ [የምስክርነት አደባባይ -የክርስቲያኖች መገደያ ቦታ] ተጓዘ:: በዚያም በጉባዔ መካከል ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ ምክንያት በሰብዓዊ አካል ሊሸከሙት የማይችሉትን መከራ በልጅ ገላው ተቀብሏል::

በዚያው ልክም ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: በተአምራቱና በጣዕመ ስብከቱም ከመቶ ዘጠና ሺህ በላይ አሕዛብን ወደ ክርስትና መልሶ ሁሉም ተሰይፈዋል:: በእሳት: በስለት: በሰይፍ: በባሕርና በየብስ መከራን ከተቀበለ በኋላ በዚህች ቀን አክሊለ ክብርን ይቀበል ዘንድ አንገቱን ተከልሏል::

ጌታችን የገባለት ቃል ኪዳኑ ግሩም ነውና ዛሬ በግብጽ በድምቀት ይከበራል:: ምንም በእድሜ ልጅ ቢሆን ቤተ ክርስቲያን አባ [አባታችን] ኖብ ትለዋለች::

† ቸር ጌታ መድኃኔ ዓለም በጻድቁና በሰማዕቱ ጸሎት ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[  † ሐምሌ ፳፬ [ 24 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን [ኢትዮጵያዊ]
፪. ቅዱስ አባ ኖብ ሰማዕት
፫. መቶ ዘጠና ሺህ ሰማዕታት [የአባ ኖብ ማኅበር]
፬. አባ ተክለ አዶናይ ዘደብረ ሊባኖስ
፭. አቡነ ተወልደ መድኅን [ኢትዮጵያዊ]
፮. አባ ስምዖን ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
፯. ቅድስት ክብራ [መስቀል ክብራ] ዘእንጦንስ ኢየሱስ

[    † ወርኀዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅዱስ አጋቢጦስ [ጻድቅ ኤጲስቆጶስ]
፫. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፬. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
፭. ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
፮. ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ [ሱራፌል]
፯. ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም [ኢትዮጵያዊ]

† "ስለዚህ እኔ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ስለሚሆን በጌታ በኢየሱስ ስለማመንና ለቅዱሳን ሁሉ ስለሚሆን መውደድ ሰምቼ ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም::" † [ኤፌ. ፩፥፲፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን : ለአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ እና አባ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊 † አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን †  🕊

† ቅዱሱ በትውልዳቸው ግሪካዊ ቢሆኑም ሶርያ አካባቢ እንዳደጉ ይታመናል:: በቀደመ ስማቸው ፍሬምናጦስ የሚባሉት አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮዽያ የመጡት በአደጋ ምክንያት [በድንገት] ቢመስልም ውስጡ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረበት::

በድንበር ጠባቂዎች [በአደጋ ጣዮች] ከባልንጀራቸው ኤዴስዮስ ጋር ተይዘው ወደ አክሱም የመጡት በንጉሥ ታዜር [አይዛና] እና በሚስቱ ሶፍያ [አሕየዋ] ዘመን ነው:: ጊዜው በውል ባይታወቅም በ፬ [4] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው::

ፍሬምናጦስ ምንም የመጡበት ዓላማ ስብከተ ወንጌል ባይሆንም በአክሱም ቤተ መንግስት አካባቢ ይሰበኩ ነበር:: ያን ጊዜ በጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ የተቀጣጠለው የክርስትና ችቦ ውስጥ ውስጡን በሃገሪቱ ነበረና ፍሬምናጦስ አልተቸገሩም:: በተለይ ሕጻናቱን [ኢዛናና ሳይዛናን] ገና ከልጅነት ስላስተማሯቸው ነገሮች የተሳኩ ሆኑ::

ልክ ንጉሥ ታዜር እንደ ሞተ ሁለቱ ሕጻናት በመንበሩ ተቀመጡ:: ፍሬምናጦስንም ወደ ግብፅ ዻዻስና ጥምቀት ከመጻሕፍት ጋር እንዲመጣላቸው ላኩ:: ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "ሰላማ" ብሎ ሰይሞ : በዽዽስና : በንዋየ ቅድሳትና በመጻሕፍት ሸልሞ መለሳቸው::

አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮዽያ እንደተመለሱ ከነገሥታቱ ጀምረው ለሕዝቡ ጥምቀትን አደሉ:: ኢዛናና ሳይዛናም አብርሃ [አበራ] እና አጽብሃ [አነጋ] ተብለው ስማቸው ተደነገለ:: ከዚያ በሁዋላ ድንቅ በሚሆን አገልግሎት ነገሥታቱ : ዻዻሱ ሰላማና ሊቀ ካህናቱ እንበረም ለክርስትና መስፋፋት በጋራ ሠርተዋል::

†  የአቡነ ሰላማ ትሩፋቶች :-

፩. ዽዽስናና ክህነትን ከእውነተኛ ምንጭ አምተዋል::
፪. ክርስትናና ጥምቀትን በሃገራችን አስፋፍተዋል::
፫. ቅዱሳት መጻሕፍትን ከውጭ ልሳኖች ተርጉመዋል::
፬. ገዳማዊ ሕይወትን ጀምረዋል::
፭. አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል::
፮. ግዕዝ ቋንቋን አሻሽለዋል::
ሀ. ከግራ ወደ ቀኝ እንዲፃፍ
ለ. እርባታ እንዲኖረው
ሐ. ከ"አበገደ" ወደ "ሀለሐመ" ቀይረዋል::

ባላቸው ንጹሕ የቅድስና ሕይወት ለሕዝቡ ምሳሌ ሆነዋ:: "ወበእንተዝ ተሰይመ ከሳቴ ብርሃን" እንዲል ገድላቸው በነዚህ ምክንያቶች "ከሣቴ ብርሃን" [ብርሃንን የገለጠ] ሲባሉ ይኖራሉ:: በመጨረሻም ከመልካሙ ገድል በሁዋላ በ፫፻፶፪ [352] ዓ/ም ዐርፈው ተቀብረዋል::


🕊  †  ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ  †   🕊

† በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ አካባቢ ስም አጠራራቸው ከከበረ ደጋግ እሥራኤላውያን አንዱ የእመቤታችን ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ ነው:: ትውልዱ ከነገደ ይሁዳ ሲሆን አባቱ ያዕቆብ ይሰኛል::

በጉብዝናው ወራት የእመቤታችንን አክስት ማርያምን አግብቶ ብዙ ልጆችን ወልዶ አርጅቷል:: ከልጆቹም ዮሳ: ያዕቆብ: ይሁዳ: ስምዖን እና ሰሎሜ በቅዱስ መጽሐፍ ተዘክረዋል:: ቅዱስ ዮሴፍ እድሜው ፸፭ [75] ሲሆን ሚስቱ ማርያም ሞተችበት::

ከጥቂት ወራት በሁዋላም በመንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን ሊያገለግል ተመረጠ:: "እጮኛ" የሚለውም ለዛ ነው:: [ለአገልግሎት ነው የታጨው] እመቤታችን ለአረጋዊ ዮሴፍ በ፪ [2] ወገን ልጁ [ዘመዱ] ናት::

፩. የሚስቱ ማርያም የእህት [የሐና] ልጅ ናት::
፪. የቅድመ አያቱ የአልዓዛር የልጅ ልጅ ናት::

ደጉ ሽማግሌ ቅዱስ ዮሴፍ ምን ቢያረጅ እመቤታችንን ለማገልገል አልደከመውም:: አብሯት ተሰደደ:: ረሃብ ጥማቷን: ጭንቅና መከራዋን: ሐዘንና ችግሯን ተካፍሏል:: ከእመ ብርሃንና አምላክ ልጇ ጋር ለ፲፮ [16] ዓመታት ኑሯል::

ከእነዚህ ዘመናት በሁዋላም በ፲፮ [16] ዓ/ም : በተወለደ በ፺፩ [91] ዓመቱ ሲያርፍ ጌታችን "ሥጋሕ አይፈርስም" ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶለታል::
"ኢየሱስ ክርስቶስ በከመ አሠፈዎ ኪዳነ::
ኢበልየ በመቃብር ወኢሂ ማሰነ::
እስከ ዮም በድኑ ሐለወ ድኁነ::" እንዳለ መጽሐፈ ስንክሳር::


🕊 † ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት † 🕊

† ይህ ቅዱስ አባት በ፬ [4] ኛው መቶ ክ/ዘመን የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረ አባት ነው:: ዘመነ ሲመቱም ከ፫፻፸፯ [377] እስከ ፫፻፹፯ [387] ድረስ ለ፲ [10] ዓመታት ነው:: በእነዚህ ዘመናቱ "ዘአልቦ ጥሪት" [ገንዘብ የሌለው / ነዳዩ አባት] ነበር የሚባለው:: ገንዘብንና ዓለምን የናቀ አባት ነበር::

ቅዱስ ጢሞቴዎስ የቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ደቀ መዝሙር እንደ መሆኑ ከመንፈሳዊ አባቱ መልካም ሕይወትን ወርሷል:: ምሥጢራትንም አጥንቷል:: በዘመኑ የአርዮስ ውላጆች ቤተ ክርስቲያንን ያስቸግሩ ነበርና ከእነርሱ ጋር ተዋግቷል:: ምዕመኑንም ከተኩላዎች ይጠብቅ ዘንድ ተግቷል::

በ፫፻፹፩ [381] ዓ/ም በቁስጥንጥንያ ጉባዔ በተደረገ ጊዜ ማሕበሩን በሊቀ መንበርነት መርቷል:: ለመቅዶንዮስ : ለሰባልዮስና ለአቡሊናርዮስ ኑፋቄዎችም ተገቢውን ምላሽ ሰጥቶ አውግዟል:: ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘአልቦ ጥሪት በቅድስና ተመላልሶ በ፫፻፹፯ [387] ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፏል::

† ፈጣሪ ከአቡነ ሰላማ : ከአረጋዊ ዮሴፍና ከቅዱስ ጢሞቴዎስ በረከትን ያሳትፈን::

🕊

[  † ሐምሌ ፳፮ [ 26 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
፪. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ [የድንግል ማርያም ጠባቂ]
፫. ቅዱስ አባ ጢሞቴዎስ [ዘአልቦ ጥሪት]
፬. አባ ሮዲስ

[   †  ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
፫. አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፬. ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን

† " እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ::" † [ማቴ.፭፥፲፫] (5:13-16)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
ሐምሌ 26 በዚህች ዕለት መልካም ሽምግልና የነበረው የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆኑ የተገባው #ጻድቁ_ዮሴፍ አረፈ። በአረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደ እርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ላይ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃብር አኖሩት።

       
         #ሰናይ__ቀን🙏

ለመቀላቀል 👇👇👇👇
@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
🕊

† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊 ቁጽረታ [ጽንሰታ] ለማርያም 🕊

ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::
ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::"
[መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ.፩፥፱ ፣ መኃ.፬]

ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ [አሮን] የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ :- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

በሰባተኛው ቀን [ማለትም ነሐሴ ፯] መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::
[ቅዳሴ ማርያም]

🕊 ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት 🕊

ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ ናት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በዚህች ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ይዟቸው ሔደ:: በዚያም ጌታ ከእነሱ ራቅ ብሎ ተቀምጦ ነበርና የማይሰማቸው መስሏቸው እርስ በእርስ ይከራከሩ ገቡ::

የክርክራቸው መነሻ ደግሞ ጌታችን ነበር:: የዋሃን [ገና ምሥጢርን ያልተረዱ] ነበሩና አንዱ ተነስቶ "ኤልያስ ነው": ሌላኛው "ሙሴ": ሦስተኛው "ኤርምያስ ነው" በሚል ተከራከሩ:: ቅዱስ ጴጥሮስ ለብቻው ቆሞ ነበርና ጠርተው "ሃሳባችንን አስታርቅልን:: ለአንተስ ማን ይመስልሃል?" አሉት::

አረጋዊው ሐዋርያም ተቆጣቸው:: "እናንተ እንደምታስቡት እርሱ ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "እግዚአ ነቢያት-የነቢያት ፈጣሪ ነው" አላቸው:: ወዲያውም ጌታ ጠርቷቸው ወደ እርሱ ቀረቡ::

ቸር አምላክ "ለምን ተጠራጠራችሁኝ" ብሎ መገሰጽ ሲችል እንዳይደነግጡ ጥያቄውን በፈሊጥ አደረገ:: "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" አላቸው:: እነርሱም በልባቸው ያለውን የሌላ አስመስለው ተናገሩ::

ጌታችን "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ጸጥ አሉ:: ገና ሃይማኖታቸው አልጸናም ነበርና:: በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ "አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው-አንተ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ነህ" አለው:: [ማቴ.፲፮፥፲፮]

ይህች ቃል የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ናትና ጌታችን "አንተ ዓለት ነህ" ብሎ የቤተ ክርስቲያንን በዚህ እምነት ላይ መመስረት ተናገረ:: ለቅዱስ ጴጥሮስም "መራሑተ መንግስት-የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ [ሥልጣን]" ተሰጠው::

ሊቀ ሐዋርያትነትንም ደረበ:: ዛሬ ለበርካቶቹ የጸነነባቸው ይሔው እምነት ነው::
ኢየሱስ ክርስቶስን "አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ ማርያም:
አካላዊ ቃል:
ሥግው ቃል:
ገባሬ ኩሉ:
የሁሉ ፈጣሪ"ብለው ካላመኑ እንኳን ጽድቅ ክርስትናም የለም::

🕊 አፄ ናዖድ ጻድቅ 🕊

ሃገራችን ኢትዮጵያ ምስፍና ከክህነት: ንግሥናን ከጽድቅ ያጣመሩ ብዙ መሪዎች ነበሯት:: ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አፄ ናዖድ ናቸው:: ጻድቁ ንጉሥ የነገሡት ከ1487 እስከ 1499 ዓ/ም ሲሆን ለእመቤታችን በነበራቸው ልዩ ፍቅር ይታወቃሉ:: ካህን እንደ ነበሩም ይነገራል::

ዛሬ ሁላችን የምንወዳትን ጸሎት [ሰላም ለኪ: እንዘ ንሰግድ ንብለኪ . . .] የደረሷት እርሳቸው ናቸው:: ትልቁን መልክአ ማርያምም ደርሰዋል:: ይህ መልክእ ጣዕሙ ልዩ ነው::

የጻድቁ ንጉሥ ሚስት [ማርያም ክብራ] : ልጆቻቸው [አፄ ልብነ ድንግልና ቡርክት ሮማነ ወርቅ] እጅግ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ:: ንጉሡ አፄ ናዖድ ከባለሟልነት የተነሳ ድንግል ማርያምን "እመቤቴ ስምንተኛው ሺ መቼ ይገባል? ጊዜውስ እንዴት ያለ ነው?" አሏት::

እመ ብርሃንም በአካል ተገልጻ የዘመኑንና የሰውን ክፋት ነገረቻቸው:: ንጉሡም አዝነው "እመቤቴ! ከዛ ዘመን አታድርሺኝ" አሏት:: በዚህ ምክንያት የስምንተኛው ሺህ ዘመን መስከረም 1 በ1500 ዓ/ም ሊገባ እርሳቸው ነሐሴ 7 ቀን በ1499 ዓ/ም ዐርፈዋል::

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የድንግል እናቱን ጣዕም: ፍቅር: የቅዱስ ጴጥሮስን ሃይማኖትና የአፄ ናዖድን በረከት ያሳድርብን::

🕊 

† ነሐሴ ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

፩.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፭.አፄ ናዖድ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮጵያ]
፮.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ
፯.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት

† ወርኀዊ በዓላት

፩.ሥሉስ ቅዱስ
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ [የባሕታውያን አለቃ]
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ

"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው:: ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል:: የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . . ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::" † [መዝ.፹፮፥፩-፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
እንኳን ለእናታችን ድንግል ማርያም በዓለ ጽንሰት
አደረሳቹ
የዐቢ ክብራ ለማርያም እምኩሎም ቅዱሳን

ከቅዱሳን ክብር የእመቤታችን ክብር ይበልጣል፡፡ አካላዊ ቃልን ለመቀበል በቅታ ተገኝታለችና፡፡ መላእከት የሚፈሩትን፣ ትጉሃን በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ቻለችው፡፡ እንዲህም ከኾነ ከመላእክት ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትበልጣለች፤ ከሦስቱ አካል ላንዱ ማደሪያ ኾኖለችና፡፡ ኢትዮጲያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይህን በኆኅተ ብርሃን መጽሐፉ ላይ ሲገልጽ

"ከኪሩቤል ይልቅ አንቺ ትበልጫለሽ፤ ከሱራፌልም ይልቅ አንቺ ትልቂያለሽ፤ ኪሩቤልና ሱራፌል በእሳት ሠረገላ ተሸክመውታልና፤ አንቺ ግን በማኅፀንሽ ወሰንሺው፤ በዠርባሽም አዘልሺው፤ በጉልበቶችሽም ዐቀፍሽው፤ ጉልበቶችሽም እንደ እሳት ሠረገላ ኾኑ፤ እጆችሽም እንደ እሳት አዕማድ ኾኑ” በማለት የተሰጣት ክብር ከኪሩቤል ከሱራፌል የበለጠ መኾኑን አስተምሯል፡፡

ቃል ከሥጋ ጋር ቢዋሐድ ጥንት የሌለው መለኮት ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ዘመን ተቀድሞት ወደ ኋላ ተገኘ፡፡ ቅድምና የሌለውም ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ተባለ፡፡ አንድም ጥንት (ቅድምና) የሌለው ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ተባለ፡፡

ዘመን የማይቆጠርለትም መለኮት ፲፪ ዓመት ኾነው /ሉቃ.፪፡፵፪/፤ ፴ ዓመት ሞላው ተብሎ ዘመን ተቆጠረለት /ሉቃ.፫፡፳፫/፡፡ አንድም አካላዊ ቃል በጎላ በተረዳ ሰው ኹኗልና በኵር ያልነበረ መለኮት በኵር ተባለ /ማቴ.፩፡፳፭/

ክብር የሌለውም ሥጋ ክቡር አምላክ ተባለ፡፡  በገዥነት የማይታወቅ ሥጋ በገዥነት ታወቀ፤ በተገዢ ሥጋ ታይቶ የማይታወቅ መለኮትም በተገዢ ሥጋ ታየ፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረው፣ በማዕከለ ዓለም ያለው፣ መቼም መች የሚኖረው ኢየሱስ ከርስቶስ እንሰግድለትና እናመሰግነው ዘንድ ከአብ ከባሐርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ አንድ ባሕርይ ነው፡፡

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንደይነሣን ለምኚልን፡፡
2024/09/29 11:19:11
Back to Top
HTML Embed Code: