Telegram Web Link
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

[ † እንኩዋን ለጻድቅ ሰው "ቅዱስ ኢያቄም" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


🕊   † ቅዱስ ኢያቄም  †    🕊

ቅዱስ ሰው ኢያቄም የሰማይና የምድር ንግስት እመቤታችን ድንግል ማርያም አባት ነው:: ቅዱሱ ከቅስራ አባቱ የተወለደ የቅዱስ ዳዊት ዘመድ ሲሆን "ኢያቄም : ሳዶቅ እና ዮናኪር" በሚባሉ ፫ [3] ሰሞቹ ይታወቃል::

ቅዱስ ኢያቄም እንደ ኦሪቱ ሥርዓት አድጎ : ከነገደ ሌዊ የተወለደች : የማጣትና ["ጣ" ጠብቆ ይነበብ] ሔርሜላን ልጅ ሐናን አግብቷል:: ሁለቱም በንጽሕናና በምጽዋት እንደ ሕጉ ቢኖሩም መውለድ የማይችሉ መካኖች ነበሩ::

በዚሕ ምክንያት ከወገኖቻቸው ሽሙጥን ታግሰው በታላቅ ሐዘን ኑረዋል:: ከጊዜ በሁዋላ ግን ስም አጠራሯ የከበረ : ደም ግባቷ ያማረ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር መረጣቸውና ከተባረከ ሰውነታቸው ድንግል ማርያምን ወለዱ::

እርሷ "ወላዲተ አምላክ" ተብላ እነርሱን "የእግዚአብሔር የሥጋ አያቶች" አሰኘቻቸው:: ቅዱስ ኢያቄም እመቤታችንን ቤተ መቅደስ ካስገቡ ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ በመልካም ሽምግልና አርፎ ከቅድስት ሐና ጋር በጌቴሴማኒ ተቀብሯል::

+ ቅዱሱ ሰው ያረፈበት ዓመት ግልጽ ባይሆንም ድንግል እመቤታችን ፰  ዓመት ሲሞላት ፪ ቱም ቅዱሳን ወላጆቿ በሕይወተ ሥጋ እንዳልነበሩ አበው ነግረውናል:: በማረፍ ደግሞ ቅድስት ሐና ትቀድማለች:: መቃብሩ ዛሬ ድረስ አለ:: ያደለው ከቦታው ደርሶ ይሳለመዋል::

አምላካችን ከቅዱስ ኢያቄም በረከት ያሳትፈን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኢያቄም [ የድንግል ማርያም አባት ]
፪. ቅዱስ አጋቦስ ሰማዕት
፫. ቅድስት ቴዎድራ ሰማዕት
፬. ቅዱስ አባ መቅሩፋ ጻድቅ

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [ የባሕታውያን አለቃ ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯. ቅዱስ አግናጥዮስ [ ለአንበሳ የተሰጠ ]

" መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው::
ከያዕቆብ ድንኩዋኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል:: የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው . . . ሰው እናታችን ጽዮን ይላል:: በውስጥዋም ሰው ተወለደ:: እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት::
"
[መዝ.፹፮፥፩-፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ እንኩዋን ለቅዱሳት ደናግል ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ! ]


🕊     ቅዱሳት ደናግል    🕊

ቅዱሳት ደናግሉ አጋሊዝ [አጋሊስ] : ኢራኒና ሱስንያ ይባላሉ:: በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ተሰሎንቄ የምትባል ሃገር ውስጥ ይኖሩ ነበር:: ሦስቱም እጅግ ቆንጆዎችና ከብዙ ወንዶች ዐይን የሚገባ መልክ ቢኖራቸውም የእነርሱ ምርጫ ግን ሰማያዊ ሙሽርነት ነበርና በጾምና በጸሎት ተወሰኑ::

ለብዙ ዓመታትም ደናግሉ በሚኖሩበት ደብር ውስጥ በቅድስና ኑረዋል:: ከቆይታ በሁዋላ ያ የመከራ ዘመን [ ዘመነ ሰማዕታት ] ሲመጣ ለጊዜውም ቢሆን ወደ በርሃ ሸሽተው ተቀመጡ::

ያሉበትን ቦታ የምታውቅ አንዲት ደግ ባልቴት እየሔደች ትጎበኛቸው : በእጃቸው የሚሠሩዋቸውን የተለያዩ እቃወችንም እየሸጠች እኩሉን በስማቸው መጽውታ በተረፈው ለራት የሚሆን ደረቅ ቂጣ ትገዛላቸው ነበር::

አንድ ቀን ግን አንድ አረማዊ ሰው ተከትሏት መጥቶ በማየቱ ፫ ቱንም ደናግል ወደ ከሐዲው ንጉሥ አቀረባቸው:: ንጉሡ ሃይማኖታቸውን ቢክዱ የሐብትና የስልጣን ተስፋ እንዳላቸው ነገራቸው:: ደናግሉ ግን በፍቅረ ክርስቶስ በመጽናታቸው ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በዚሕች ቀን አስገድሏቸዋል::

የጌታችን በጐ ምሕረቱ በሁላችን ትደርብን:: ከደናግሉ በረከትን ያሳትፈን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱሳት ደናግል አጋሊዝ: ኢራኒና ሱስንያ
፪. ፻፶ "150" ቅዱሳን ሰማዕታት [ፋርስ [ኢራን] ውስጥ የተሰየፉ]
፫. አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት

[ †  ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ኪሩቤል [አርባዕቱ እንስሳ]
፫. አባ ብሶይ [ቢሾይ]
፬. አቡነ ኪሮስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ከ፲፪ [12]ቱ ሐዋርያት]

" ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት : ወይስ ስደት : ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት : ወይስ ፍርሃት : ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን:: " [ሮሜ.፰፥፴፭-፴፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ † እንኳን ለብጹዐን ጻድቃን: ቅዱስ ዞሲማስ እና አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊   †   ብጹዐን ጻድቃን  †    🕊

† በዚህ ቀን ብሔረ ብጹዐን ውስጥ የሚኖሩ ጻድቃን ይታሠባሉ:: በሃይማኖት ትምሕርት ፭ [5] ዓለማተ መሬት አሉ:: እነሱም አቀማመጣቸው ቢለያይም ከላይ ወደ ታች ፦

፩. ገነት [ በምሥራቅ ]
፪. ብሔረ ሕያዋን [ በሰሜን ]
፫. ብሔረ ብጹዐን [ ብሔረ - አዛፍ - እረፍት ] {በደቡብ}
፬. የእኛዋ ምድር [ ከመሐል ] እና
፭. ሲዖል [ በምዕራብ ] ናቸው::

† ከእነዚሕ ዓለማት ባንዱ የሚኖሩ የብሔረ ብጹዐን ጻድቃን ፦

- ኃጢአትን የማይሠሩ::
- ለ ፲፻ [1,000] ዓመታት የሚኖሩ::
- ሐዘን የሌለባቸው::
- በዘመናቸው ፫ ልጆችን ወልደው ፪ ወንድና አንድ ሴት] ሁለቱ ለጋብቻ: አንዱን ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት የሚያውሉ ሰዎች ናቸው::

† ቅዱሳኑ ወደዚሕ ቦታ የገቡት በነቢዩ ኤርምያስ እና በቅዱስ እዝራ ዘመን ሲሆን አንዴ የተወሰኑት በዘመነ ሰማዕታት ወጥተው በዚሕ ቀን ተሰይፈዋል::

† በመጨረሻ ግን በሐሳዌ መሲሕ ዘመን ወጥተው ሰማዕትነትን ይቀበላሉ::

† የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረቱና ይቅርታው ለምናምን ሁሉ ይደረግልን:: ከደግነታቸውም በረከትን አይንሳን::

🕊   አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ   🕊

አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አባታቸው መልአከ ምክሩ : እናታቸው ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የተወለዱበት ልዩ ቦታው ወሎ ክፍለ ሀገር ዳውንት ነው፡፡ በተወለዱ ዕለት ተነስተው በእግራቸው ቆመው ሦስት ጊዜ "ስብሐት ለአብ : ስብሐት ለወልድ : ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው አመስግነዋል፡፡

- የስማቸው ትርጓሜ "የአብ : የወልድ : የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ" : አንድም "የክርስቶስ እስትንፋስ" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸውና በመንገዳቸው ሁሉ እየመራቸው ነው ያደጉት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎላቸው በ፭ ዓመታቸው የቅዱሳት መጽሐፍት ቃላትን፣ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ ድርሳናትንም ጠንቅቀው ዐውቀዋል፡

+ በተወለዱ በ፲፬ ዓመታቸው ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ደብረ ሐይቅ ገዳም ሄደው ከባሕር ዳር ቆመው የሙሴን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ባህሩን አሻግሯቸው ወደ ቤተክርስቲያን ገብተዋል፡፡ ለ፫ ዓመትም በኃይቅ ገዳም ለመነኮሳት እንጨት በመልቀምና ውሃን በመቅዳት : ለአባቶች መነኮሳት ምግብ ሊሆናቸው ከባህር ውስጥ አሳን በማውጣት አገልግለዋል፡፡

አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት ከጾሙ በኋላ ምንም እህል ሳይቀምሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለሙሴ በደብረ ሲና እንደሰጠው ለአባታችንም ወደ እርሳቸው መጥቶ ዓሥሩን ቃላተ ኦሪትና ስድስቱን ቃላተ ወንጌል በውስጣቸው የተጻፈባቸው ሁለት ጽላቶችን ሰጥቷቸዋል፡፡

+አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ ዕለቱን ስንዴ ዘርተው፣ ወይን ተክለው፣ ጽድን ወይራንና ግራርን ተክለው በአንዲት ቀን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዕለቱን አድርሰዋል፡፡ስንዴውን ለመስዋዕት ወይኑን ለቁርባን በታምራት አድርሰዋል፡፡

+አባታችን በጸሎት ላይ እንዳሉ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተልኮ መጥቶ አባታችንን በደመና ጭኖ ወስዶ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አቆማቸው፡፡ ጌታንም በቅዱሳኖቹ ሁሉ እንዲባረኩ ካደረጋቸው በኋላ መልአኩን "ወደ ተወለድኩባትና ወደ ኖርኩባት ቦታ ወደ
ኢየሩሳሌም አድርሰው" ብሎት ኢየሩሳሌምን አሳልሞ ሀገራችን መልሶ አምጥቷቸዋል፡፡ ሁሉንም የኢትዮጵያን ቅዱሳት ገዳማትንም ተዘዋውሮ ሲጎበኙ በሕይወተ ሥጋ የሌሉት የየገዳማቱ ቅዱሳን ሁሉ በአካል ይገለጡላቸው ነበር፡፡
+ጎጃም ውስጥ እያስተማሩ፣ እያጠመቁ፣ ! የታመሙትን እየፈወሱ፣ የዕውራንን ዐይን እያበሩና ሙታንን እያስነሱ ብዙ ካገለገሉ በኋላ ለዘጠኝ ዓመታት በባሕር ውስጥ ገብተው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ጸልየው የምሕረት ቃልኪዳን ተቀብለዋል፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ጌታችን መጥቶ "ከመነኮሳት ሁሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ምሬልሃለሁ ከዚህች ባሕር ውጣ" በማለት በሞት የሚያርፉበትን ቦታ ነግሯቸዋል፡፡

+ጻድቁ ወደ ደብረ አስጋጅ በሚሄዱበት ጊዜ ጸሐይ ልትገባ ስትል "በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አውግዤሻለሁ፡፡ ለመስፍን ኢያሱ በገባኦን እንደቆምሽ አሁን ቀጥ ብለሽ ቁሚ" ብለው ገዝተው ፀሐይን አቁመዋል፡፡

+አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ደብረ አስጋጅ ሲደርሱ ፀሐይ አፍ አውጥታ "አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እገባ ዘንድ ፍታኝ" ስትላቸው "እግዚአብሔር ይፍታሽ" ባሏት ጊዜ ጠልቃለች፡፡ ጻድቁ ሌላው በእጅጉ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ቃል ኪዳን አላቸው፡፡
+በአምላክ ፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ፣ በቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ገብርኤል ልቡና የሚገኝ እንደ መልክአ ኢየሱስ ያለች እጅግ አስገራሚ ጸሎት አለቻቸው፤ እርሷን ጸሎት በጸለዩ ጊዜ እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጣሉ፡፡ ጸሎቷም የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎቹ የተቀበሉትን ጸዋትዎ መከራዎች ሁሉ ታዘክራለች፡፡ በእያንዳንዱ ክፍልም የጸሎት ማሳረጊያ አቡነ ዘበሰማያት ይደግማሉ፡፡
+ንስሓ የገባ ኃጢአተኛ ሰው እንኳን ቢሆን ይህችን የአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን ጸሎት በጸለየ ጊዜ ሺህ ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ጌታችን በማይታበል ቃሉ ለአባታችን ነግሯቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የመድኃኔ ዓለምን የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች መከራዎቹን የምታዘክረውን ይህቺን በአምላክ ልቡና ያለች ግሩም የሆነች ጸሎት "ነፍሳትን ከሲኦል አታወጣም" ብሎ የሚጠራጠር ቢኖር ግን መንግስተ ሰማያትን አያያትም፡፡

+ ጻድቁ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ታህሳስ ፱ ቀን ተወልው ሚያዝያ ፱ ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ [ገድለ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ]

አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ሃገራችንን
ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱሳን የብሔረ ብጹዐን ጻድቃን
፪. አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጻድቅ [ኢትዮዽያዊ]
፫. ቅዱስ ዞሲማስ ገዳማዊ [ብሔረ ብጹዐንን ያየ እና ዜናቸውን የጻፈ አባት]
፬. ቅዱስ ኤስድሮስ ሕጻን ሰማዕት [ገና በ፲ ወር ዕድሜው ሰማዕት የሆነ]
፭. አባ ሱንቱዩ ሊቀ ዻዻሳት

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. አባ በርሱማ ሶርያዊ [ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት]
፪. ፫፻፲፰ "318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት [ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ]
፫. አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ [ኢትዮዽያዊ]

" ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኑራችሁ: ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ:: እንደሚታዘዙ ልጆች ባለ ማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ:: ዳሩ ግን 'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ' ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ:: " † [፩ዼጥ.፩፥፲፫-፲፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

[ †  እንኳን ለአባ ይስሐቅ ጻድቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊  †  አባ ይስሐቅ ጻድቅ  †   🕊

† ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩት በ፭ [5] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: በጊዜው ዝነኛ ከነበሩት ከታላቁ አባ ዕብሎ [ቅዱስ ዕብሎይ] ተምረዋል:: መማር ብቻ ሳይሆንም ለ፳፭ [25] ዓመታት ያለ መታከት በተልዕኮ አገልግለዋል::

በእነዚህ ጊዜያትም ትሕርምትን : ተጋድሎን : ትምህርተ ቅድስናንና ሌሎች አስፈላጊ መንፈሳዊ ስንቆችን ሰንቀዋል:: በመታዘዛቸው በምድር አበውን : በሰማይ እግዚአብሔርን አስደስተዋል:: በዚህም ከእግዚአብሔር ጸጋውን : ከአበው ምርቃትን አትርፈዋል::

ጊዜው ደርሶም ታላቁ ዕብሎ ሲያርፉ አባ ይስሐቅ በዓት ለይተው ደንበኛውን ተጋድሎ ጀምረዋል:: አምላካቸውን ለማስደሰትና በቅድስና ለመዝለቅም የአርምሞ ሰው ሁነዋል:: ለሚገባው ነገር ካልሆነ በቀር አያወሩም:: ምላሽም አይሰጡም:: "ለምን?" ሲባሉ
፩. "ለሁሉም ጊዜና ቦታ አለው::"
፪. "ሰው በከንቱ በማውራቱ ከጸጋ እግዚአብሔር ይርቃል" ይሉ ነበር::

አባ ይስሐቅ የክርስቶስ መድኃኒታችንን ሕማማት ለማዘከር ሁሌ ያነቡ [ያለቅሱ] ነበር:: ቅዳሴ ሲያስቀድሱ እጃቸው የሁዋሊት ታስሮ ነበር:: ቅዱሱ ሰው ለአዝማናት እንዲህ ተመላልሰው በመልካም ዕርግና ያረፉት በዚህ ቀን ነው::

† አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው አይለየን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አባ ይስሐቅ ገዳማዊ [የታላቁ ዕብሎይ ደቀ መዝሙር]
፪. አባ ገብርኤል ሊቀ ዻዻሳት

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫. ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
፬. አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፭. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ እልፍዮስ]
፮. ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
፯. ቅዱስ ዕፀ መስቀል

" የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ: ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ:: ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: " ††† [ይሁዳ.፩፥፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

† ስንክሳር ዘወርኀ ሚያዝያ ፲፩ †

🕊  †  ለቅድስት ታኦድራ ገዳማዊት †  🕊

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሚያዝያ ዐሥራ አንድ በዚች ዕለት የከበረችና የነጻች እመሜኔት ታዖድራ አረፈች። ይቺም ቅድስት ከእስክንድርያ አገር ከታላላቆች ባለጸጎች ወገን ናት ወላጆቿም ክርስቲያኖች ናቸው። እነርሱም ዋጋው ብዙ በሆነ በወርቅና በብር ያጌጡ የከበሩ ልብሶችን አሠሩለት ከእርስዋ በቀር ልጅ ስለሌላቸው ሊአጋቡአት እነርሱ ያስባሉና።

እርሷ ግን የምንኲስና ልብስ ለብሳ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ልትጋደል ትወዳለች መከራ መስቀሉንም ልትሸከም ትወድ ነበር የዚህን የኃላፊውን ሠርግ አልፈለገችም። ከዚህም በኃላ የወላጆቿን ዕቃ ገንዘብ ወስዳ ለሚሸጥላት ሰጠችው ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተች በቀረውም ከእስክንድርያ ውጭ በስተምዕራብ አብያተ ክርስቲያናትን አነፀች።

ወደ እስክንድያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስም ሔዳ ራሷን ተላጭታ ከእርሱ ዘንድ መነኰሰች። ከደናግል ገዳማትም ወደ አንዱ ገብታ በገድልም ተጸምዳ ጽነዕ ገድልን ተጋደለች አምላካዊ ራእይንም ታይ ዘንድ ተገባት መላእክትን ታያለችና የሰይጣናትንም ሥራቸውን ለይታ ታውቃለችና ለሠሩ የታሰቡትን የምታውቅበትና የምትፈትንበት እውቀት ተሰጣት።

ቅዱስ አትናቴዎስም በእርሷ ፈጽሞ ደስ ይለው ነበር ወደርሱም ይጠራታል እርሱም ሊጎበኛት ወደርሷ ይሔዳል ኀሳቧንም ትገልጥለታለች እርሱም የጠላት ደያብሎስን ወጥመዱንና ምትሐቱን ያስገነዝባታል። ከመንበረ ሢመቱ ከእስክንድርያ በአሳደዱትም ጊዜ ብዙዎች ድርሳናትን ጽፎ ላከላት።

ይቺም ቅድስት እጅግ እስከአረጀች ድረስ ኖረች በመንፈሳዊ ተጋድሎም የጸናች ናት እርስዋ ከአምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ተምራለችና። እሊህም እለ እስክንድሮስ አትናቴዎስ ጴጥሮስ ጢሞቴዎስና ተዎፍሎስ ናቸው።

እንዲህም ብለው ጠየቋት ሰው ተርታ ነገር ቢናገር ዝም በል ሊሉት ወይም እንዳይሰሙት ጆሮአቸውን መክደን ይገባልን እንዲህም ብላ መለሰች ምንም ምን ሊሉት አይገባም ነገሩ ደስ እንዳላቸው ሆነው ዝም ይበሉ እንጂ ሰው ማዕዱን በፊትህ ቢያኖር በላይዋም በጎ የሆነና ብላሽ የሆነ ምግብ ቢያኖር ይህን ብላሹን ከእኔ ዘንድ አርቀው አልሻውም ልትለው አይቻልህም መጥፎውን ትተህ ከምትፈቅደው ትበላለህ እንጂ ያለ ትሕትና ያለ ጾምና ጸሎት ሰይጣንን ድል የሚነሣው የለም።

መላ ዕድሜዋም መቶ ዓመት ሆኖዋት በሰላም አረፈች ጸሎቷ በረከቷ ከኛ ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን።

በዚህችም ቀን የጋዛ ኤጲስቆጶስ የዮሐንስ መታሰቢያው ነው። ደግሞ የእስክንድርያው የአባ በኪሞስ የስምዖን ዘለምጽና እግዚአብሔርም በጸሎታቸው ለዘላለሙ ይማረን አሜን።

🕊

† ሚያዝያ ፲፩ [ 11 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ታኦድራ ገዳማዊት
፪. አባ በኪሞስ ጻድቅ
፫. ስምኦን ዘለምጽ
፬. ቅዱስ ዮሐንስ ኤዺስ ቆዾስ

[   †  ወርሐዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፬. ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፭. አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

" ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ:: "
[፩ዼጥ.፫፥፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/30 01:25:27
Back to Top
HTML Embed Code: