Telegram Web Link
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

† ሚያዝያ ፬ †


🕊 ቅዱሳን ፊቅጦር: ዳኬዎስና ኤርሞ [ ሰማዕታት ] 🕊

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሚያዝያ አራት በዚች ቀን የከበሩ ፊቅጦርና ዳኬዎስ ኤርሞ ሌሎችም ብዙዎች ሰዎች ሴቶችና ወንዶች ደናግሎች በሰማዕትነት ሞቱ።

እሊህም ቅዱሳን በታላቁ ቈስጠንጢኖስና በልጁ ዘመነ መንግስት የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰው ጣዖታትንም ሰብረው አቃጥለው በቦታቸውም አብያተ ክርስቲያናትን ሠርተው አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በሌሎችም በብዙዎች ቅዱሳን ስም ታቦቱን ሰይመው ነበር።

ከሀዲ ዮልያኖስም በነገሠ ጊዜ የጣዖትን አምልኮ አቆመ የጣዖቱንም ካህናቶች አከበራቸው ብዙዎች ክርስቲያኖችንም አስገደለ።

የእሊህ ቅዱሳን ዜናቸው አስቀድሞ በጣዖታት ቤቶች ላይ ያደረጉት ጣዖታትን እንደሰበሩ ሁሉ ተሰማ።ይዘውም ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩአቸው ብዙ ቀንም ሲሰቅሏቸውና ሲገርፉአቸው ቆዳቸውንም በሾተል ሲነጥቁ ኑረው በኃላም ቸብቸቧቸውን በሰይፍ ቆረጡ።

በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ በረከታቸው ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

🕊

[ † ሚያዝያ ፬ [ 4 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት ]

፩. እግዚአብሔር የሰው ልጅን ፈጠረ
፪. ቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሐ [ጻድቃን ነገሥት]
፫. ቅዱሳን ፊቅጦር: ዳኬዎስና ኤርሞ [ሰማዕታት]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ [ወንጌላዊው]
፪. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]

" እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ:: በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው:: ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው . . . እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ:: እነሆም እጅግ መልካም ነበረ:: "  [ዘፍ.፩፥፳፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
                           †                           

[ ተዋሕዶ ፍጽምት የቅዱሳን ሃይማኖት ]
▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ ! ]

--------------------------------------------------

" ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ከሰማይ መውረዱን ፤ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋን ነሥቶ ሰው መሆኑን ፤ እግዚአብሔር ቃል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ተወልዶ መገለጡን ፤ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ሆኖ በሰዎች መካከል መመላለሱን አምናለሁ፡፡

አንዱ አምላክ ነው ፥ አንዱ ዕሩቅ ብእሲ ነው አልልም፡፡ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከነሣው ሥጋው ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው እንጂ !

ከእግዚአብሔር የተወለደው ከድንግል የተወለደው ይኸው አንዱ ነው ። አንድ ሲሆንም ይታመማል ፤ አይታመምም፡፡ በሥጋው ይታመማል ፤ ሕማማችንንም ገንዘብ ያደርጋል ፤ በመለኮቱ ሕማማችንን ያርቃል፡፡ በሞቱም ሞታችንን ያጠፋል ፤ ለእኛ ለአገልጋዮቹ ድኅነትን የሰጠን እርሱ ነው፡፡ ለአመኑበትም ትንሣኤን ገለጠላቸው፡፡ የዘለዓለም ሕይወትን በጌትነቱ በሚያወርሳት በመንግሥተ ሰማያት ትሰጥ ዘንድ ያላት ተድላ ነፍስንም ሰጣቸው፡፡"

[     አቡሊዲስ     ]

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፤ ወለወላዲቱ ድንግል ፤ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።

†                       †                         †
💖                    🕊                     💖
                          †                          

💖  [    የትሕርምት ሕይወት !    ]  💖

🕊                      💖                      🕊


[ “ ስለ ሐሜት መጥፎነት በተመለከተ  ! " ]


" የመፍረድ ስልጣን ሳይኖረው በሰው ላይ የሚፈርድ ሰውን በተመለከተ ጌታችን ፦ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋሁ በምትሰፍሩትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋልና” በማለት አስተምሮናል፡፡ [ማቴ.፯፥፩]

እንዲሁ የጌታ ወንድም ያዕቆብ ፦ “ወንድሞች ሆይ ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ:: ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል” [ያዕ.፬፥፲፩] ብሎ ጽፎልናል፡፡

ተወዳጆች ሆይ ! ከጌታ ቃልና ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ ምን ተማራችሁ? ጻድቁ ሎጥ በሰዶም ተቀምጦ ነበር ፤ ነገር ግን  “ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበር ” [፪ጴጥ.፪፥፯] ተብሎ እንደተጻፈልን ራሱን በጽድቅ አስጨንቆ ይኖር ነበር እንጂ በማንም ላይ እጁን አልጠቆመም ነበር፡፡ ሐሜት በሰው ላይ መፍረድ ነውና፡፡

ነገር ግን ሐዋርያው ይህን ከጻፈልን በኋላ “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን ፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” [፪ጴጥ.፪፥፱] በማለት ፍርድን መስጠት የእግዚአብሔር ድርሻ እንደሆነ እርሱም በኃጢአተኞችና በዓመፀኞች ላይ አንደሚፈርድባቸው ጽፎልናል፡፡ ስለዚህ ራስን በመግዛትና በትሕትና መመላለስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ፤ ጊዜውም ዛሬ ነው፡፡"

[  ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ  ]


🕊                       💖                    🕊
🕊

[ † እንኳን አምላካችን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ላረፈባት የመጀመሪያዋ ዕለተ ሰንበትና ለቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† አምላካችን እግዚአብሔር በ፮ [6] ቱ ቀናት ፳፪ [22] ቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ በ፯ [7] ኛዋ ዕለት ደክሞት ያይደለ ለእኛ ያስተምረንና ሰንበትን ይቀድስልን ዘንድ አረፈ::

ዕለተ ሰንበት ማለት አንዳንድ ልባቸውን ያሳወሩ ሰዎች እንደሚያወሩት የሥራ መፍቻ ቀን ሳትሆን :-
፩. ከሥጋዊ ተግባራችን ታቅበን መንፈሳዊ ተግባራትን [፮ [6] ቱ ቃላተ ወንጌልን] የምንፈጽምባት:

፪. ለጊዜውም ቢሆን ጥቂት እርፍ ብለን አማናዊቷን ዕረፍተ መንግስተ ሰማያት የምናስብባት ዕለት ናት::

እንደ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትም ለሰንበተ ክርስቲያን ቀዳሚውን ቦታ ሰጥተን ቀዳሚት ሰንበትንም እንደሚገባ ልንጠቀምባት ይገባል::

† የሰንበት ጌታዋ: የምሕረትም አባቷ ጌታችን እግዚአብሔር ለዕረፍተ መንግስቱ የተዘጋጀን ያድርገን::

🕊 † ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ †  🕊

† ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል የነበረው ቅ/ል/ክርስቶስ በ፭፻ [500] ዓመት አካባቢ ሲሆን የጼዋዌ [ምርኮ] አባልም ነበር:: እሥራኤልና ይሁዳ ወደ ባቢሎን በምርኮ ሲወርዱ አብሮ ወርዷል:: ቅዱሱ ከ፬ [4]ቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ሐረገ ትንቢቱም በ፵፰ [48] ምዕራፎች የተዋቀረ ነው::

በዘመኑ ሁሉ ቅድስናን ያዘወተረው ቅዱሱ ከደግነቱ የተነሳ በጸጋማይ [ግራ] ጐኑ ተኝቶ ቢጸልይ ፮፻ [600] ሙታንን አስነስቷል:: ወገኖቹ እሥራኤልንም ያለ መታከት አስተምሯል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት ታላቁን ራዕይ እንዳየ ታስተምራለች:: ነቢዩ በፈለገ ኮቦር ካያቸው ምሥጢራት እነዚህን ያነሷል :-

፩. እግዚአብሔርን በዘባነ ኪሩብ ተቀምጦ ሲሠለስና ሲቀደስ አይቶታል:: የኪሩቤልንም ገጸ መልክእ በጉልህ ተመልክቷል:: [ሕዝ.፩፥፩]

፪. በመጨረሻው ቀን ትንሳኤ ሙታን : ትንሳኤ ዘጉባኤ እንደሚደረግም ተመልክቷል:: [ሕዝ.፴፩፥፩]

፫. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ኆኅት ኅትምት/ኆኅተ ምሥራቅ [የምሥራቅ ደጅ] ሁና አይቷታል::

ይሕ የምሥራቅ ደጅ [በር] ለዘለዓለም እንደታተመ ይኖራል:: የኃያላን ጌታ ሳይከፍት ገብቶ: ሳይከፍት ወጥቷልና:: [ሕዝ.፵፬፥፩] በመጨረሻ ሕይወቱ እሥራኤል ለክፋት አይቦዝኑምና ነቢዩን አሰቃይተው ገድለውታል::

† ከነቢዩ በረከት አምላኩ ያድለን::

🕊

[ † ሚያዝያ ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት ]

፩. እግዚአብሔር ሰንበትን ቀደሰ
፪. ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ
፫. ቅዱስ ዲዮስቆሮስ [ክፉ ላለመናገር ድንጋይ ጐርሶ የኖረ አባት]
፬. ቅድስት ታኦድራ
፭. ቅዱስ አርሳኒ
፮. ቅዱስ ያሬድ ካህን [ልደቱ]

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ
፫. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ [አባ ገብረ ሕይወት]
፬. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
፭. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ

" እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ: ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ: ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና :- በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ:: የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ:: " † [ኢሳ.፶፮፥፬-፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
“እስመ አንተ ትፈድዮ ለኵሉ በከመ ምግባሩ-አንተ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህና"

መዝ 61፥12
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

እንኳን አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።

† ሚያዝያ ፮ [ 6 ] †

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት እነዚህን ታላላቅ ቅዱሳን ታስባለች:-

† 🕊 ቅድስት ማርያም ግብፃዊት 🕊 †

† በዚች ቀን በበረሀ የምትኖር ግብፃዊት ማርያም አረፈች። ይቺም ቅድስት ከእስክንድርያ አገር ሁና ወላጆቿ ክርስቲያን ናቸው። እድሜዋ አስራ ሁለት አመት በሆናት ጊዜ የመልካም ስራና የሰው ሁሉ ጠላት ሸንግሎ አሳታት በእርሷም የማይቆጠሩ የብዙዎችን ነፍስ አጠመደ እርሱ ሰይጣን ስለ ዝሙት ፍቅር ያለ ዋጋ ስጋዋን እስከ መስጠት አድርሷታልና ።

በዚህም በረከሰ ስራ ውስጥ ኖረች በየእለቱም የኃጢአት ፍቅር በላይዋ ይጨመርባት ነበር። ሰውን የሚወድ የእግዚአብሄርም ቸርነት ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ሊባረኩ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚሹ ሰዎችን ገለጠላት።

ከእሳቸውም ጋራ ትሄድ ዘንድ ልቧ ተነሳሳ ከብዙ ሰዎችም ጋራ በመርከብ ተሳፈረች። ባለ መርከቦችም የመርከብ ዋጋ በጠየቋት ጊዜ ስለ መርከብ ዋጋ ያመነዝሩባት ዘንድ ሰውነቷን ሰጠቻቸው ኢየሩሳሌምም እስከ ደረሰች ይህን ስራ አልተወችም።

የክብረ ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ወደ አለች ቤተ ክርስቲያን ትገባ ዘንድ በወደደች ጊዜ መለኮታዊት ኃይል መግባትን ከለከለቻት። እርሷም ከሚገቡ ሰዎች ጋራ ትገባ ዘንድ ብዙ ጊዜ ደከመች ነገር ግን ከለከላት እንጂ የጌታ ኃይል አልተዋትም።

ከዚህም በኃላ ስለ ረከሰ ስራዋ አሰበች በልቧም እያዘነችና እየተከዘች ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር አይኖቿን አቀናች በማንጋጠጥዋም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስእል አየች።

በፊቷም አለቀሰች ፍጥረቶችን ሁሉ የምትረጅአቸው አምላክን የወለደሽ እመቤቴ ተዋሽኝ ከሁሉ ሰዎች ጋራ ገብቼ የመጣሁበትን ስራዬን የፈፀምኩ እንደሆነ ያዘዝሽኝን ሁሉ እኔ አደርጋለሁ ብላ በማመን ለመነቻት።

ቤተ ክርስቲያን ፈጥና ገባች በገባችም ጊዜ የበአሉን ስራ ፈፀመች። ከዚህም በኃላ አምላክን ወደ ወለደች ወደ እመቤታችን ወደ ከበረች ድንግል ማርያም ስእል ተመልሳ ወደ እርሷ መሪር ልቅሶ እያለቀሰች ረጅም ፀሎትን ፀለየች ነፍሰዋን ለማዳን እርስዋ ወደ ወደደችው ትመራት ዘንድ አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ስእል ከዮርዳኖስ በረሀ ብትገቢ አንቺ እረፍትንና ድኀነትን ታገኚ አለሽ የሚል ቃል ወጣ።

ከእመቤታችን አምላክን ከወለደች ከቅድስት ድንግል ማርያም ስእል ይህን ቃል ተቀብላ ወድያውኑ ወጣች። በውጪም አንድ ሰው አግኝታ ሁለት ግርሽ ሰጣትና አምባሻ ገዛችሸት።

ከዚያም በኃላ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራ ፅኑእ ተጋድሎ እየተጋደለች በበረሀው ውስጥ አርባ ሰባት አመት ኖረች ሰይጣንም አስቀድማ በነበረችበት በዝሙት ጦር ይዋጋት ነበር።

እርሷ ግን በተጋድሎ ፀናች ከዚያም ከገዛችው አምባሻ ብዙ ቀን ተመገበች። ሁለት ሁለት ቀን ሶስት ሶስት ቀን ፁማ ከዚያ አምባሻ ጥቂት ትቀምስ ነበር በአለቀም ጊዜ የዱር ሳር ተመገበች።

በዚያችም በዮርዳኖስ በረሀ እየተዘዋወረች አርባ አባት አመት ሲፈፀምላት እንደ ገዳሙ ልማድ የከበረች አርባ ፆምን ሊፈፅም ቅዱስ ዘሲማስ ወደዚያች በረሀ መጣ። በሱ ደብር ላሉ መነኲሳት ልማዳቸው ስለሆነ በየአመቱ ወደ በረሀ ወጥተው የከበረች የአርባ ቀን ፆም እስከ ምትፈፀም በፆምና በፀሎት ተፀምደው በገድል ይቆያሉ ።

ስለዚህም ዘሲማስ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ በወጣ ጊዜ የሚፅናናበትን ያሳየው ዘንድ እግዚአብሄርን ለመነው። በበረሀውም ውስጥ ሲዘዋወር ይቺን ቅድስት ሴት ከሩቅ አያት የሰይጣን  ምትሀት መሰለችው በፀለየም ጊዜ ከሰው ወገን እንደሆነች ተገለጠለችለት።

ወደርሷም ሄደ እርሷ ግን ከእርሱ ሸሸች ወደርሷም ይደርስ ዘንድ ከኃላዋ በመሮጥ ተከተሉት። ከዚህም በኃላ ዘሲማስ ሆይ ከእኔ ጋራ መነጋገር ከፈለግህ ጨርቅን በምድር ላይ ጣልልኝ እከለልበት ዘንድ ብላ በስሙ ጠራችው።

በስሙ በጠራችውም ጊዜ እጅግ አድንቆ ጨርቁን ጣለላት ያን ጊዜም ለብሳ ሰገደችለት እርሱም ሰገደላት እርስበርሳቸውም ሰላምታ ተሰጣጥተው በላዩዋ ይፀልይላት ዘንድ ለመነችው እርሱ ካህን ነውና ካህን ሰለሆነ።

ከዚህም በኃላ ገድሏን ታስረዳው ዘንድ ቅዱስ ዘሲማስ ለመናት ከእርሷ የሆነውን ሁሉ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ነገረቸው። እርሷም በሚመጣው አመት የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋውንና ደሙን ከእርሱ ጋራ ያመጣላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እሺ አላት።

አመትም በሆነ ጊዜ ስጋውንና ደሙን በፅዋ ውስጥ ያዘ ደግሞ በለስ ተምርንና በውኃ የራሰ ምስርን ይዞ ወደርሷ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ መጣ ቅድስት ማርያምን በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ስትሄድ አያት ወደርሱም ደርሳ እርስበርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ በአንድነትም ፀለዩ ከዚህም በኃላ ስጋውንና ደሙን አቀበላት።

በለሱን ተምሩንና ምስሩንም አቀረበላትና ትመገብለት ዘንድ ለመናት ስለ በረከት ከምስሩ በእጇ ጥቂት ወሰደች። ደግሞም በሁለተኛው አመት ወደእርሷ ይመለስ ዘንድ ለመነችው ።ሁለተኛ አመትም በሆነ ጊዜ ወደዚያ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ መጣ ያቺ ቅድስት ሴት ሙታ አገኛት በራስጌዋም ድኀዪቱን ግብፃዊት ማርያምን ከተፈጠረችበት አፈር ውስጥ ቅበራት የሚል ፅሁፍ አገኘ።ከፅሁፉ ቃልም የተነሳ አደነቀ።

ያን ጊዜም ከግርጌዋ አንበሳን ሲጠብቃት አየ እርሱ መቃብርዋን በምን እቆፍራለሁ ብሎ ያስብ ነበር በዚያም ጊዜ ያ አንበሳ በጥፍሮቹ ምድሩን ቆፈረ የከበረ ዘሲማስም በላይዋ ፀሎት አድርጎ ቀበራት ።

ወደ ገዳሙም ተመልሶ ለመነኮሳቱ የዚችን የከበረች ግብፃዊት ማርያምን ገድሏን እንዳስረዳችው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ነገራቸው እጅግም አደነቁ ምስጉን ልኡል እግዚአብሄርንም አመስገኑት። መላው እድሜዋም ሰማንያ አምስት ሆኗታል።

🕊 ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ 🕊

በዚች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ሳምንት ለሀዋርያው ቶማስ ተገለጠለት በእጆቹና በእግሮቹ ውስጥ የችንካሮቹን ምልክትም አሳየው የቶማስንም እጅ ይዞ በመለኮታዊ ጉኑ ውስጥ አኖረውና በጦር የተወጋበትን ቦታ አሳየው ቶማስም  ጌታዬና ፈጣሪዬ መነሳትህን አመንኩ አለ።

ጌታችንም ብታየኝ አመንከኝ የሚመሰገንስ ሳያየኝ የሚአምንብኝ ነው ብሎ መለሰለት። በትርጓሜ ወንጌልም እንዲህ ይላል ቶማስ በመድኀኒታችን ጐን ውስጥ እጁን በአስገባ ጊዜ እጁ በመለኮት እሳት ተቃጠለ ፣በመለኮቱም ደግሞ በታመነ ጊዜ እጁ ከመቃጠል ዳነች ።

†   🕊  " አባታችን አዳም "  🕊  †

አባታችን አዳም የመጀመሪያው ፍጥረት [በኩረ ፍጥረት] ነው:: አባታችን አዳም :-

- በኩረ ነቢያት
- በኩረ ካኅናት
- በኩረ ነገሥትም ነው::
- በርሱ ስሕተት ዓለም ወደ መከራ ቢገባም ወልድን ከዙፋኑ የሳበው የአዳም ንስሃና ፍቅር ነው::

አባታችን ለ፻ [100] ዓመታት የንስሃ ለቅሶን አልቅሷል:: ስለዚህ አባታችን አዳም ቅዱስ ነው:: ከሌሎቹ ቅዱሳን ቢበልጥ እንጂ አያንስም::

ለአባታችን አዳም የተናገርነው ሁሉ ለእናታችን ሔዋንም ገንዘቧ ነው:: ዛሬ የሁለቱም የዕረፍታቸው መታሠቢያ ነው::

አባታችን ቅዱስ ኖሕም ከላሜሕ የተወለደው በዚሁ ቀን ነው::

አምላካችን እግዚአብሔር ለሰማይ ለምድሩ በቅድስናቸው ከከበዱ ወዳጆቹ በረከትን ያድለን::
[  † ሚያዝያ ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን አዳምና ሔዋን [ የዕረፍታቸው መታሠቢያ ]
፪. ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት [ ልደቱ ]
፫. አባታችን ቅዱስ ኖኅ [ ልደቱ ]
፬. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ [ የጌታችንን ጐኑን የዳሰሰበት ]
፭. ቅድስት ማርያም ግብፃዊት [ ከኃጢአት ሕይወት ተመልሳ በፍፁም ቅድስናዋ የተመሠከረላት እናት ]

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. እናታችን ሐይከል
፫. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፬. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፭. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፮. ቅድስት ሰሎሜ
፯. አባ አርከ ሥሉስ
፰. አባ ጽጌ ድንግል
፱. ቅድስት አርሴማ ድንግል

" እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና::

እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅን አደረጉ:: የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ:: የአንበሶችን አፍ ዘጉ:: የእሳትን ኃይል አጠፉ:: ከሰይፍ ስለት አመለጡ:: ከድካማቸው በረቱ:: በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ:: የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ::
"
[ ዕብ. ፲፩፥፴፪-፴፭ ] (11:32-35 )

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/30 07:25:17
Back to Top
HTML Embed Code: