Telegram Web Link
''ብሣና ላክልኝ''
-------------
ገላዋ ካደረ…
ወታደር ይመስል ፥ እርቆ ከደጇ
አንተን ከከጀለች
ከሰንበቱ ሎሌ ፣ …ከኔ ከወዳጇ
ከሆድህ መስክ ላይ
ጣናን ከሚተካ ፥ ቶራ ሜዳን አካይ
ከሰፊው ውድማ ፥ ከደረትህ ጥርጊያ
ካማራት ኩትኳቶ ፥ ተዘጭቶ ውጊያ
መጫን ነው አጥብቆ
ገፍታ እንደመጣች ፥ …የህዳር አህያ
እንግዲ ለኪዳን
ለሸንጎ ላይ ሙግት ፥ ላንተም መፋረጃ
ለኔም እንዲሆነኝ ፥ የልዩነት ቀንጃ
ብሣና ላክልኝ ፥ ....…አሲዘህ በእጇ
.
« ሚኪ እንዳለ »
@mebacha ጓኞቻችሁን ADD በማድረግ የዚህ ቻናል ተከታይ ያድርጉ
አብረን እያነበብን አብረን እንደግ
ለአስተያየት👉@MMiku ይጠቀሙ
ጠብቆ በሊታ
——————
እረኛውን አምኖ፣ ተኩላን መስጋቱ
ያደርገዋል የዋህ፣ በግን በሕይወቱ
የዋህነት አድጎ…
እንደ ሻማ እንባ ፥ ካለፈም ከደርዙ
እራስን የማቅለጥ
ጅልነት ይሆናል ፥ መዳረሻ ጠርዙ
፡፡፡፡፡፡፡፡፡
ጠላታችን ብለን
በህሊና ምናብ ፥ ከእሩቅ የተየብነው
በቅርብ ተተክቶ ፥ ወዳጃችን ባልነው
በራስ ጥቅም ሚዛን
በማሸት ውሃ ልክ ፥ አንጥረን ካየነው
ለበጉም አይደለ…
እንቅልፉን እያጣ ፥ ሚጠብቅ እረኛው
፡፡፡፡፡፡፡፡፡
ይብኝልኝና…
እንኳንስ ጀርባውን…
በጉ መቼ አውቆት ፥ ከጎኑ ያለውን
ሲተሻሽ ይውላል ፥ ገፎ ሚያበላውን
ቀና ማለት ትቶ
ጅራፍ ያክል ሰርዶ፥ የጉንብስ ይግጣል
ከበዪም ለመዳን ፥ በ'በይ ይጠበቃል
ጠላትን ፍራቻም ፣ ከጠላት ይውላል
፡፡፡፡፡
ግና ምን ያደርጋል...
እንደ በላው መጠን፣ ሰውነቱ ያድጋል
እንደ በ'ራ ቁልቋል ፥ አካሉም ይሰባል
የኋላ ኋላውን…
የእውነታ ነገር ፥ ግልንቢጥ ይሆናል
በተኩላው ሳይሆን...
ዘላለም ባመነው ፥ በ'ረኛው ይበላል
.
( ሚኪ እንዳለ )
እንከን ላጣሽብኝ
----------------

በሰፌድ ላይ ቀመር
በ.....…ላሜዳ* ባየር
ግብሬን አበጥሮ ፥ ልብሽ እንዲቀጥረኝ
ሙያዬን መዝኖ ፥ አይንሽም እንዲያየኝ
ሽርጥ አገልድሜ ፥ እጅጉን ብለፋ
ጋገርራ ገብቼ ፥ ...ቡኮ ሊጥ ባሰፋ
እስቲበስል ብዬ
በትዝታ ቅርቃር ፥ አንገቴን ብደፋ
ተኝቶ ነው ብለሽ
የምጣዴን ክዳን ፥ ያለጊዜው ከፍተሽ
አይኑ የፈዘዘ ፥ …አፍለኛን አውጥተሽ
እኔን ለማባረር…
ምህኛት ብታጪ፥የእንጀራ'ይን ቆጠርሽ
ይሁና ከበጀሽ…
በማይመስል ህጸፅ ፥ መንገድ ከከጀለሽ
ከማይሳሳቱ
መላእክት ሰባእቱ
...ምስለ አሐዱን ከሆንሽ
እንግዲስ እኔው ነኝ…
እንደ ቀትር ጋኔል ፥ አንቺን ሳይ የምሸሽ
ይብላኝልኝና እኔ ምን ተዳዬ
የነጣ ነውና ፥ የራስ ቅል ጓዳዬ
የወጣ እንዳይገባ…
በአሚን መቀነት ፥ ታስሯል ህሊናዬ
፡፡፡፡፡፡፡
ካንቺ ዘንድ ከዋለው
ጅል መስሎ ጥበብን ፥ ከጉያሽ ካለበው
ውስጡ ሳይታወቅ ፥ ብክር ከተናቀው
ከጭምቱ ራሴ ፥ ከሰላው ሀሳቤ
ከ'ሊናዬ እልፍኝ ፥ በትረ ሙሴን ስቤ
እንደ ቀዩ ባህር…
እከፍልበታለው ፥ ..…ልብሽን ከልቤ
እንግዲስ ዳግማይ ፥ እጉያሽ መጥቼ
የተከለከለ እርምሽን ነክቼ
እንደ ብሉይ አካን፥እንዳይመታኝ ቅስፈት
ልቤን አስሪያለው
ኢያሱን ባስነባች ፥ ....በያሪኮ ግዝት
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
አሁን አቦልሽን
ቶና በረካሽን
ጨርሼ አከተምኩት
አዝመራው ሀሳቤን ፥ ውድማ በተንኩት
የሰላውን ማጭድ ፥ ከሰገባ ሳብኩት
እንደ ቅጠል በጣሽ…
ከልብሽ ቅርንጫፍ፥ተስፋዬን ቆረጥኩት
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
ቢሆንም ቢሆንም...
ሆነሽኛልና ቆንጥጦ መካሪ
ላመስግንሽ እቱ ፥ እልፍ አመትን ኑሪ
ዮናስን በሆዱ…
ሦስት ቀን እንዳቆየ ፥ የተርሴስ አ'ንበሪ
አ'ርገሽዋልና…
ልቤን እንደልብሽ ፥ ተፍቶ አስተማሪ
.
« ሚኪ እንዳለው »


ግጥም ወዳድ የሆኑ ጓደኞቻችሁን ወደዚህ ገጽ በማስገባት እንድታበረታቱኝ በአክብሮት እጠይቃለው፡፡ @mebache
የበረካ ሱስ
—————

የተገኘን ሁላ
እንደ አይጥ መላስ ፥ የለመደ አፋችን
ይደባልቅ ጀመር
መናኛውን ጠላ ፥ ..…ከገሊላ ወይን
ድሮም ጽልመት ወዳጅ፥ ቅይጥን ያበዛል
ከመሐል ለመስፈር…
ነጭ እያጠቆረ ፥ .....…ማካያቶ ያዛል
ድንቅ በሌለበት…
እያጨበጨበም ፥ ኑሮውን ይገፋል
☀️☀️☀️
አወየው ነፈዞ...
በዘመኑ ነፋስ ፥ አይምሮው ቀዝቅዞ
ከእደ ስል'ጡናን ፣ በልመና ናውዞ
አበላል ያደንቃል ፣ በ’ጁ ጉርሻ ይዞ
የብብት ይጥላል ፥ እቆጡ ላይ ፈዞ
☀️☀️☀️
በትንቢት ቀጠሮ ፥ ይትበኃል በአበው
በጥንቲቷ ክታብ፥ ትውልዴን ብመክረው
ይለኛል አፍጥጦ ፥ መስሚያዬ የጥጥ ነው
☀️☀️☀️
ወትሮም ወራጅ ትውልድ
እንደ እንቁራሪት ፥ ከውሃ ይውላል
የነጩ ከራማ ፣ ከዳሚን ይመስላል
አቦል እየደፋ…
የቶናን ቅራሪ ፣ .… ... …በረካን ይጋታል

«ሚኪ እንዳለ»
@mebacha
ለአስተያየት👉 @MMIKU
የቀጩ መዳኒት
🌸🌸🌸🌸🌸
እንደ መሬት ጅና ፥ እንደ ደቡብ ዋልታ
ባራቱ ነፋሳት ፥ .....ብቻነት ተረድታ
አልጋዬ ላይ በረድ ፣ ግግሯን አምርታ
እንደ መንዝ ጠባሴ፥እንደ ጣርማ ምድር
እንደ ሰላ'ድንጋይ፥ እንደ ሞስካብ ድንበር
ከራሴ አንስቶ ፥ እስከ'ግር ጥፍሬ
ብታርከፈክፈው ፥ የሐምሌውን ኩሬ
የለት ጽንስ ይመስል...
ኩርማን አከልኩልሽ ፥ ...መናኛ ሻድሬ*
🌸🌸🌸🌸🌸
እንደው ከወደድሺኝ
ገላዬ በላቦት ፥ ወይባ እንዲመስለኝ
ቆርጣማው አጥንቴ፥ሰላሙን እንዲያገኝ
የቤቴም ምሰሶ ፥ እንዲሞቅ ማገሬ
መጠጥ እንዲልልኝ ፥ ያ ጤዛው አዳሬ
እባክሽ ነይና…
የቀጩን መዳኒት ፥ ...ስጪኝ ለከንፈሬ
🌸🌸🌸🌸🌸

« ሚኪ እንዳለ »

ማንጸሪያ ፦ ሻድሬ* ማለት ከጥጥና ከጭረት የተሠራ ሽድሬ፣ሳዱሬ፣ሻቡሬ ተብሎ የሚጠራ በቀላል ዋጋ የሚሸጥ ልብስ ማለት ነው፡፡

የዚህ ግጥም የመጨረሻዋ የስንኝ ዘርፍ ብቻ ከጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ጋር ትመሳሰላለች፡፡ የሃሳቤ መነሻም እሷ ስለሆነች ከግምት ውስጥ አስገቧት፡፡

@mebacha
@mebacha
@mebacha

ለአስተያየት👉👉👉@mmiku
''ውሻ…በግ…አህያ'' የክብሬ ማሳያ
-------------//-----------------

እንደ'ሰባ ኮርማ
ፍቅር እንደያዘው ፥ ወዶ መሲና ላም
አይኖቼን ተክዬ ፥ ከበሯ ብከትም
ዳስ ጠለል ወጥሬ ፣ እደጇ ብከርም

ከሰናፍጭ ቅንጣ ፥ ሶስት እጥፍ ቀልዬ
ስሯ ብጠቀለል ፥ …ማሰሻን አክዬ
ካረንዳዋ ባንስ ፥ እራሴን አቅልዬ !

እንደ ዳስ መጫሚያ
ከመሬት አጣብቆ ፥ ኩማዋ* ቢረግጠኝ
እንደ ጥጥ ልቃቂት ፥ ፍቅሯ ቢያባዝተኝ
ከክብሬ ዘጭታ
በሰላ ጠገራ ፥..... ጀመረች ትፈልጠኝ
ዝግባ ዛፍ ይመስል ፥ ወድቄላት ብገኝ

ለዚህ እኔነቴ
እንደ ሮሃ አለት ፥ ለጸናው ትግስቴ

ለርብቃ እንደለፋ…
እንደ ቅዱስ ያቆብ ፥ ስባሔ ሲገባኝ
ላገኘችው ሁላ…
ከምስጋና ቢሳን ፥ ውሻ ነው አለቺኝ
ተሳደብኩህ ብላ...
ከስሯ እማልጠፋ ፥ .…ታማኝ አረገቺኝ

ለጥቃስ መች አርፋ
የገመስ መግደያ ፥ ድርጎዬን መንትፋ
ስታጎርስ ጉብሏን ፥ ...ከፊቴ አሰልፋ
ብክር አይኔ ቢያየው
ነገሬን ላይከተው
መርጬ ለመተው
ካልቦ መቀነቴ ፥ ብሰጣት ካለቺኝ
ሰዎችን ሰብስባ ፥ በግ ብላ አማቺኝ
አላውቃም ለሰው ሟች፥ የዋህ እንዳለቺኝ

አሁን የባስ ብላ
ማዕረጌን ሰቅላ
የህዳር አህያ ፥ .......ብላም አላኮረፍኩ
መሰከረች እንጂ…
ፍቅሯን በጫንቃዬ ፥ስሸከም እንደኖርኩ

በስተማካተቻ…
…እሷም ሳይሰለቻት
እኔም ደስ እንዲለኝ ፥ በርግማኗ ብዛት
ያላንዳች ኩነኔ ፥ ሺ ዘመን ያዝልቃት
ካሁን ሰው በላቁ ፥ የዋሃን እንስሶች
ውሻ በግ አህያ ፥ ጥገት ላም እያለች
ስትመርቀኝ ትኑር ፥ መስሏት የሰደበች

«ሚኪ እንዳለ»

@mebacha

ለአስተያየት👉@mmiku
ያ'ዲስ ዘመን ጭዳ
———//————

ጥንት ያሌ ለታ
በእርካብ ምስረታ
ባለሁ አለሁ ስሜት፥ በሃሳብ ወለምታ
እንደ ብርሌ ሆድ ፥ ......ሰማርያ ነቅታ

ባንድ ጆሮ ብቻ ፥ እንዳች ግንጥል ጌጥ
ከግንዱ ተፍቃ ፥ ለብቻ ብትላጥ
ከማጀቱ ወስዶ…
አሦር በማድጋ ፥ አቦካት እንደ ሊጥ

ይህንንም ሰምታ
ይሁዳ በደስታ
ዘለለች በሐሴት ፥ ደለቀች አታሞ
መስሏት ነበርና…
በጤና ም' ታድር ፥ ሰማርያ ታሞ

የኋላ ኋላው…
ደስታዋን አካታ ፥ ስቃ ሳትቋጫት
ዝላይን የሚያሽር ፥ ኮሶን አዘዘላት
ናቡከደነጾር
በገፍ እየነዳ ፥ ከባቢሎን ዶላት

አሁን ተዚያ ቆመህ
ጊዜ የሰጠህን ፥ ተራህን አንግበህ
ያንዲቷን ምሰሶ ፥ መገዝገዝ ካማረህ
በፅልመት ጎዳና…
በበርባሮስ ሽንቁር ፥ መንገድ ከከጀለህ
ትቆማለህ ያኔ…
በማእዘን እራስ ፥ .…ሲፈረከስ ቅልህ

በዝንጋሄ ህሊና ፥ በሙት ልብ አ'ይምሮ
እረስታ የነገን ፥ የስለት ቀጠሮ
አስራ ሰባቱን ቀን ፥ ቆጥራው እንደ ኑሮ
ትስቅ ነበር አሉ ፥ የመስቀሏ ዶሮ
የ'ንቁጣጣሹ በግ…
ከጎኗ ተውስዶ ፥ ..ሲታረድ ተጓሮ

በዛች የሞት ጀጃፍ
በፍርድ ቀን አፋፍ
ደም ከሚፈስበት ፥ እንደ ማይ በሽሎ
በስለት መባቻ ፥ ባ'ውዳመቱ ውሎ
'ባዲስ ዘመን ጭዳ ፥ በበጉ ደበሎ
መዘበት ይቻላል…
ካራው እስኪወጣ ፥ ለመስቀል ተስሎ
.
«ሚኪ እንዳለ»
የጋጋሪ ያለህ !
——————

ድር'ጓችንስ ነበር ፥ ሙሉ ከማጀቱ
እስከ አፍ ገደፉ ፥ ወተት ከወጭቱ
ካልጠበበች ሃገር
ካላረጠች ምድር
ከጠበብቱ አለም ፥ ከማይነጥፈው ፀጋ
ፍጩ ካልጠፋበት ፥ ከአበው ማድጋ
እንጎቻን ወቶልን
እህሉ በስሎልን
ከናታችን ድቁስ ፥ እንዳንጎርስ አጥቅሰን
'ሚያቦካ ብቻ እንጂ፥ ሚጋግር እጅ አጣን

« ሚኪ እንዳለ »

@mebacha
@mebacha
@mebacha

@mmiku
በድፍን አለቅን
------//-------

የደጉን ቀን ኑሮ ...
አያቴ ሲነግረኝ ፥ አምጥቶ ከድሮ
ፍሪምባ እንደበላ ፥ ስሙኒ መንዝሮ
በመልሱ ከሻኛ ፥ ከዳቢት ነብሮ
ለቤቱ እንዳስገባ ፥ በቅንባ ከምሮ
መስሎኝ ነበር እኔስ
የዲጃቩ* ተረት ፥ ምሰማ በአንክሮ

ምነው ታዲያ ዛሬ
የኔስ ዘመን ኑሮ ፥ ደርሶ ቀነበረ
እንደ ኦሪት በግዕ ፥ ቀንዱ ከረከረ
በክፋት እርግብግብ…
እንደ ሙዝ አሙካ ፥ ሳይጣድ አረረ

አሁን ሳይጎልብን...
እንደ ጥንቱ ልማድ ፥ እንዳባቶቻችን
በ'ለተ ምርያ* ፥ ...በሰላም አድርሶን
እግዜር ያለወጪ ፥ አመታት ቢሰጠን
እንኳንስ ልንበላ
እንኳንስ ልንጠጣ
..…መልሱን ተቀብለን
ሀገር ሰላም አታ ፥ በድፍን አለቅን
.
« ሚኪ እንዳለ »

@mebacha
@mebacha
@ETHIO_ART
@ETHIO_ART
''ለማያውቅሽ ታጠኚ''
————//————
.
አወይ እንዴት ያምራል አቋምሽ አለሜ
እንደ ጣና ደንገል
ተክነሽው የለ ፥ .....የተክሌን ዝማሜ
.
ከነገስታት እልፍኝ ፥ ከማጀትሽ ጓዳ
ሙገሳሽ ከአፄው ፥ ባንኳላ ቢቀዳ
ለማያቅሽ ጉብል…
ልዩ ነው ዘረፋሽ ፥ ቅኔሽም አንግዳ
.
እልፍ እያሰለፈ
....…እየደጋገፈ
ያ ወርቁ መቋሚያ ፥ የንጉሥ ግድግዳ
አስቸገረን እንጂ…
ላንቺ ምርኩዝ ሆኖ ፥ …እኛን እየከዳ
.
አንቺ እንደልቡ
የከፍታሽ ነገር ፥ የዙፋንሽ ደርቡ
የለበጥሽው መዳብ ወርቅ አርገሽ በዕቡ'
የጉባዬ ቃናው ፥ ..የቅኔሽ ድባቡ
ገመገም ነውና…
ፈቺ ስላልጠፋ ፥ ገብቶናል ሀሳቡ
.
እንደ ተ'ኩላት ጥሎሽ
እንደ ሰማይ ጭሬ ፥ ያየር ምልልስሽ
ጠቦት በበዛበት ፥ የማንጃበብ ውልሽ
ሥጋ ለማጋዝ ነው…
በክሽን አጀንዳ ፥ በመልካም ወጣትሽ
.
ስራሽንም አውቆ
ፊደልን ጠንቅቆ
ስውር ስፍ ሙያሽን ፥ ለጠየቀ ርቆ
በነብዩ አፍሽ ፥ ተጠቅመሽ ላመሉ
የቅናት መንፈስ ነው ፥ ትይኛለሽ አሉ
.
አሁን ለሸመታ
እንዳዘነ ኩታ
ላላወቀ ታጥነሽ ፥ ድርቡን ለብሰሽው
በጆንያ ፊልተር ፥ ..ጅሉን አስክረሽው
ሚስጥር ሳታወርጂ ፥ እንዳሻ ፈተሽው
ሰሙን በመናገር…
ታግዢያለሽ አሉ ፥ ወርቁን ደብቀሽው
.
«ሚኪ እንዳለ»

@mebach
@mebacha
@mebacha
ድምጹ ከሚሰማ፥ ዘረጥ ከሚለው
እኛን የገደለን፥ ወትሮም የቱስ ነው
.
« ሚኪ እንዳለ»

@getem
@getem
@mmiku
እረክተን ሳንጠጣ ፥ አለቀ ተደፍቶ
በቅጡ ሳይፈላ ፥ ሚገነፍል በዝቶ
.
« ሚኪ እንዳለ»

@mebacha
@mebacha
@mebacha
ለመዳኒት ብለን ፥. . ከንብ የቆረጥነው
ኮሶን አፈራብን ፥ ማር ብለን የዋጥነው

« ሚኪ እንዳለ »

@MEBACHA
@MEBACHA
@MEBACHA
እንደ ሰላ ማጭድ ፥ እንደ ተሞረደው
ፊደል ካራ ሆኖ ፥ ገንጥሎ ሳይለየው
ሳይከፈል ያ…ኔ የሰው ልጅ በቋንቋው
በለቅሶ ነበረ ፤ ....…አፉን የሚፈታው

(ሚካኤል እንዳለ)

የትመጣ
-----

ሊቅ አያሳጣንና ፤ በአንድ ወቅት ታላቁ ሊቅ ነፍስ ሔር አለቃ አያሌው ታምሩ የሰው ልጅ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ምንድነው ተብለው በተጠየቁ ጊዜ ''የሰው ልጅ የአፍ መፍቻ ቋንቋው ለቅሶ ነው'' ብለው ነበር የመለሱት፡፡ እውነት ብለዋል፡፡ ውሉ ተረስቶ እንጂ ፤ ዛሬ ህዝብ በቋንቋው ሳይከፈል ፤ የዚህ ቋንቋ ባለቤት እኔ ነኝ ከማለቱ አስቀድሞ ፤ ሰው የሆነ ፍጥረት ሁሉ ከእናቱ ማህጸን እንደወጣ አፉን የከፈተበት ቋንቋ ቢኖር ለቅሶ ነበር፡፡እንደተወለደ አፉን ፊደል ባለው ቋንቋ የከፈተ ሰው በአለም ላይ የለም፡፡ 
.
ሰው ቋንቋዬ ከሚለው መግባቢያ አስቀድሞ ከእናቱ ጋር ይግባባ የነበረው በዚሁ አፍ መፍቻ ቋንቋው በለቅሶ ብቻ ነበር፡፡ ሽንቱ ሲመጣ ያለቅሳል፤ ሲርበው ያለቅሳል ፤ ሲያመው ያለቅሳል ፤ እቃቃ ሲፈልግ ያለቅሳል፤ መጫወት ሲፈልግ ፤ ሲፈራ ፤ እንቅልፉ ሲመጣ ያለቅሳል፡፡ በዚህም ከናቱ ጋር ይገባባል፡፡ ይህ ነው ለሰው ዘር በሙሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ፡፡ በዚች ምድር ላይ በዓለም የነበረ ሰው በሙሉ ፤ ቢያንስ ምንም ቋንቋ ሳይናገር ለሁለት አመታት ኖሯል ፡፡ ይህም ቢሆን በሁለት አመታቸው መናገር ለሚጀምሩ ፈጣን ልጆች ነው፡፡ አንዳንዶቻችን ደሞ አድገን አፋችን በቋንቋ እስቂጠመቅ ድረስ ሦስት አመትም ላይመልሰን ይችላል፡፡ በዚህ አንጻር(analogy) ካየነው ለሁለት እና ለሶስት አመታት የአለም ህዝብ በአንድ ቋንቋ በለቅሶ ነበር የሚግባባው ማለት ነው፡፡
.
ቋንቋ መግባቢያ ነው የምትለኝ ካለህ ተሳስተሃል !! ምክንያቱም ቋንቋ የሌላቸው እንስሳት ከሰዎች በላይ ሲግባቡ ስታይ ሰው በመሆንህ ታፍራለህ፡፡ቋንቋ መግባቢያ ቢሆን ኖሮ ምነው ዛሬ የሰው ልጆች መግባባት አቃታን ? ሰው እጅግ ሲበዛ ውስብስብ ፍጡር ነው፡፡ ባንድ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሰዎችም'ኳ ቢሆኑ እንደ ሀገር መግባባት አቅቷቸው የፉድድ ሲጓዙ እያየን ነው፡፡ ታዲያ የቋንቋ መግባቢያነት ምኑ ላይ ነው ? ከማግባባት ይልቅ ካባላን ፤ ከማስማማት ይልቅ ከነጣጠለን ፤ አንድ ከማድረግ ይልቅ ከለያየን ፤ ከመደማመጥ ይልቅ ካደናቆረን ፤ ከመተዛዘን ይልቅ ካጨካከነን ፤ ከማፋቀር ይልቅ ካጣላን ፤ የቋንቋ መግባቢያነት ታዲያ ምኑ ለይ ነው? መግባቢያ ነው ብለህ አትፎግር ቋንቋ ዘንድሮ መለያያ ሆኗልና፡፡
.
ተፈጥሮ ባንድም በሌላም መንገድ ታስተምረናለች፡፡ ፍየል፤በግ፤ ፈረስ አህያ፤ላም በአንድ በረት ውስጥ ያለምንም ችግር ማደር ይችላሉ፡፡ ግን ሁሉም በባህሪ አንድ አይደሉም ፡፡ በተፈጥሮ ፤ በይዘት ፤ በአኗኗር ዘይቤም እጅጉን የተለያዩ ናቸው፡፡ በድምፅ'ኳ የላም እምቧ…የበግ በ…የፍየልም ሌላ ፤ የፈረስም ሌላ ነው፡፡ ግን ይህው የቤት እንስሳ ተብለው በአንድ ምድብ ባንድ በረት ይኖራሉ፡፡ ምናልባት እነዚህ እንስሶች ቋንቋ ቢኖረቸው ኖሮ ሰው በሆኑና ፤ ኦሮምኛ ፤ አማርኛ ፤ ትግርኛ ፤ ጉራግኛ ፤ አኟክኛ ወዘተ…ተናጋሪ በመባልል እራሳቸውን ባደራጁ ነበር፡፡ 
ሰው ከተባለው በልዓም ይልቅ አህያው ከሱ ተሽላ እብደቱን ያገደችበት ታሪክ አለ ፡፡ ሰው ሲደነቁር እንዲህ ከአህያም የሚያንስበት ጊዜ ይኖራል፡፡
''በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም ፥ ሕዝቤም አላስተዋለም''፡፡ የተባለው በኛ ዘመን ተፈፀመ ፡፡ ቋንቋ ኖሮን ከምንጣላ እንደእንስሳቱ በ እምቧ ተግባብተን ብንፋቀር ይሻላል ነበር፡፡
.
በስምንተኛው ሺ መባቻ ሰው መሆን እጅጉን የሚያስፈራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡በአንድ ወቅት ታላቁ ባልቅኔ ክቡር ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን...

እኔስ ኖሬዋለው ፥ ሲከፋኝ ሲደላኝ ከእንግዲህ ተወልዶ፥ሰው ለሚሆን ይብላኝ 

ብለው ትንቢታዊነት የተላበሰች አጭር ስንኝ አስቀምጠውልን ነበር ፡፡ የዚችም ስንኝ እውነታነት በዘመናችን እንደ ዶሮ አይን ቁልጭ ብሎ እየታየ ይመስላል፡፡ እውነትም በሚያስብል ደረጃ በዚህ ዘመን ሰው ለሆነው ለኛ ማዘን ነው፡፡ አለያ እንደ አጼ ናኦድ ከስምንተኛው ሺ ዘመን ስርቻ ሰውረን ብለን መፀለይ ይገባናል፡፡ እሳቸውስ ጸሎታቸው ተሰምቶ በ 1499 ዓ.ም ሐምሌ ላይ አንቀላፉ፡፡ ከስምተኛው ሺ መባቻ ተሰወሩ፡፡ እኛስ አንደኛውን ተዘፍቀንበታል፡፡ ቢሆንስ ደሞ በየትኛው ሱባዬአችን እርሳቸው ብቃት ዘንድ እንደርስና? ፡፡እንደው እንደቸርነቱ ይሰውረን እንጂ፡፡''በከመ ምህረትከ አምላክነ ፤ ወአኮ በከመ አበሳነ'' እንዲል፡፡
.
አሁን አሁንማ ከቋንቋም ታልፎ ፊቱ የነእገሌን ይመስላ እከመባል ተደርሷል፡፡ ይህን የመሰለው የሰው ልጅ ክፋት ሲታይ ፤ በግ እና ፍየል ሆኖ ባንድ በረት በሰላም መኖርን የሚያስመኝ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ''ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ። የተባለው እዚህ ጋር ልብ ይሏል፡፡ መዝ 49፥12 ፡፡
.
ዛሬ የዚች ሀገር ክብር ተድሶ ፤ ክብረንጽህናዋ ተገሶ ፤ ኅቡእ ሚስጥሯን መረዳት ያቃታቸው የአንድነት ጠላት የሆኑ እንጭጭ ፓለቲከኞች ቅርሻታቸውን ሲተፋባት ይውላሉ፡፡ ሊቆርሷት ፤ ሊከፍሏት ፤ እንደ ደጉ ይስሐቅ በጀርባዋ አጋድመው ሊባርኳት ይከጅላሉ፡፡ ግን አምላኳ በእጸ ሳቤቅ የታሰረ በግ አያሳጣትምና አንድ ሰው ያድናት ዘንድ ያስነሳል ''ኢየሐድጋ ለሀገር ዘእንበለ አሐዱ ሔር'' ተብለናልና፡፡ መቼም ኢትዮጵያ እንደሰዶም አስር ጻድቅ አጥታ ትጠፋለች የሚል እምነት የለኝም፡፡
.
የዚችን ሀገር ክፋት ቀርቶ ክብሯን'ኳ ለመናገር የሚመጥን ቃል በአለም ላይ የለም፡፡ ያክሱም እና የሮሃን ስልጣኔ ብንተው እንኳ ፤ በከርሰ ምድሯ ተቀብሮ ያለውን የጥበብ ፅንስ መረዳት ቀርቶ ግብኑን መቅመስ እራሱ ተስኖናል፡፡ ነጮች ታይቶ ከሚዳሰሰው ስልጣኔዋ አልፈው ልማት እና ኢንቨስትመንት ፤ ቱሪዝም እና ጥናት እያሉ ሆድቃዋን የሚበረቅሱበት ምክንያት የገባህ ለት ሀገርህ ያረገዘቸውን አስኳል ሰብረህ ለማፍሰስ አችቸኩልም ነበር፡፡ 'ዘቦ እዝን ሰሚዓ ለይስማዕ''፡፡መስማትንስ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡
.
(ሚካኤል እንዳለ)

@mebacha
የቡና ቁርስ
-------

በእልፍኝሽ ደጃፍ ፥ እንዳገሬው ባሕል
አፍን ለማቦዘን ፥... ስትዘረጊ ፍንጃል
እንደ ጥንቱ ጊዜ...
ጥሞኝ እንድበላ ፥ እንደተለመደው
የቡና ቁርስሽን ፥ ዳቦ 'ካደረግሽው
እመጣለው እቱ…
ጀበናውን ጥደሽ ፥ አቦሉን አድርሽው
.
ሚኪ እንዳለ

@mebacha
''በዝሆኖች ልፊያ ፤ ሳሩ ይጠቀማል?
ወይስ ይጎዳል ? በጥበብ እልፍኝ ''
----------//------------
.
(ሚካኤል እንዳለ)
.
በአንድ ወቅት እሳቱ ተሰማ የተባለ ባል ቅኔ በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድን ብዕር ላይ እርግማኑን እንደ ሰዶም እሳት አወረደ፡፡ የጸጋዬ የብዕር ምት ይሙት ፤ ምሰለኝ እንጂ አልመስልህም ፤ በሚሉ እርግማኖች ታላቁን ሊቅ ጋሽ ጸጋዬን አከናነበው፡፡ ቆይቶ ግን የማይሰደብ ሰው መስደቡ፤ የማይረገም ሰው መርገሙ ፤ የማይጣል ሰው ማጣጣሉ ሆዱን በላው፡፡ በእሳት ወይስ አበባ ተማረከ ፤ በጸጋዬ ብዕር ላይ ባወረደው እርግማን ተጸጸተ ፡፡ተጸጽቶም አልቀረ፡፡ እንጅ መንሻ ፤ ሸማ መጣያ ፤ እርቅ መሳቢያ ይሆነው ዘንድ ፤ እርግማኔን መልስልኝ በሚል ርዕስ ድንቅ ግጥም ይዞ ብቅ አለ፡፡ መቼም ዝሆን እና ዝሆን ሲራገጥ የሚጎዳው ሳሩ ነው ''የሚለው ነባር ብሂል በጥበብ እልፍኝ አይሰራም፡፡ በጥበብ ግጥሚያ ውስጥ ዝሆኖች ሲራገጡ ሳሩ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም፡፡ እነዚህ በጥበብ የገዘፉ ሁለት ዝሆኖች በመላፋታቸው እኛ ሳሮቹ ''እርግማኔን መልስልኝ'' እና ''ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ'' የሚባሉ ማለፊያ ቅኔዋችን አተረፍን፡፡
.
ከዚህ ቀደም በነ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ እና በነ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶልሳ አክለውም መሪያስ አማን በላይ ፤ በቅርቡ በዳኒኤል ክብረት እና በበእውቀቱ ስዩም አክሎም በተፋዬ ገብረአብ ፤ በዚሁ በመንደራችን ፌስ ቡክም በፍልስፍናው መምህር ብሩህ አለምነህ እና በሃይማኖተኛው በአማን ነጸረ የነፍስ አለም ውጊያ ብዙ እጅግ ብዙ አትርፈናል፡፡ ሃገር እንድታድግ የሃሳብ ልዕልና እንዲነግስ ጥበበኞችን ያጋጭልን፡፡ ምክንያቱም እንደ ክርክር (argument) ያለ እውቀት ገንቢ መሃንዲስ በአለም ላይ ስለሌለ፡፡ በቂ ማስረጃን ማቅረብን ግን ልብ ይሏል፡፡

የግሪክ ፍልስፍና የአለም ቁንጮ ያደረገው ቅሉ በክርክር ላይ መሰረቱን መጣሉ ነበር፡፡ሰው ጥበባዊ እውቀቱን ለማሳደግ ከፈለገ ፤ የምሁራንን ማስረጃ ጠገብ ክርክሮች እያነፈነፈ መላስ አለበት፡፡ የሃሳብ ግጭት ፤የሃሳብ ፍጭት በቀፎን አለም ውስጥ በብርድ ለተቀሰፈ አዕምሮ የእውቀት ሙቀትን ይለግሳል፡፡ ዘንድሮ ግን ነገሮች የግልንቢጥ ሆነዋል፡፡ በክርክር፤በሃሳብና በሙግት የሚያምን የአብሪ ትልን ያክል መስዋትነት ይከፍላል፡፡ አወራህ አበራህ ተብሎ ይዳጣል፡፡ በሃሳብ ከበለጥካቸው በጉልበት ያሳንሱሃል፡፡ በክርክር ስትረታቸው በሽሙጥ እና በደቦ ፍርድ ይረቱሃል፤ በብዕር አንገት ያስደፉሃቸው እንደሁ በዱላ አንገትህን ያስደፏል፡፡አንብቦ ታሪክን አውቆ ጥበብን በጥበብ ከመርታት ይልቅ ይዝቱብሃል ፤ ያስፈራሩሃል ፤ ኑሮህን የስጋት ፤ እንቅልፍህን የጎን ውጋት ያደርጉብሃል፡፡ያንተን ያክል ሀሳብ ማመንጨት ካቃታቸው እንደ ሶቅራጥስ መርዝ ግተው ይገሉሃል፡፡

ጥንት ግን እንዲ አልነበረም ፤ አባቶች ፍልሚያ የሚወጡት ቅኔን አንግበው ነበር፤ በቅኔ ተፋልመው እውቀት አደላድለው ፤ ራስን አስከብረው ይመለሱ ነበር፡፡ ሊቅ እከሌ እኮ ይህን ያህል ቅኔ ተቀኘ ይባልለታል፡፡ ለእውቀት ሸመታም ተማሪዋችይጎርፉለታል፡፡ በዚህም ሂደት እስከዛሬ አለምን በምስጢራቸው ጉድ ያስባሉ እልቆ መሳፍርት ቅኔዋችን አትርፈውልን አልፈዋል፡፡ ግን ምን ያደርጋል ዛሬ ቅኔ እቀኛለው ብትል ፤ ከተቀኘህው ቅኔ ሃሳብ ይልቅ የተቀኘህበት ቋንቋ ታይቶ ሃሳብህ ምንም ሃገርን የመለወጥ አቅም ቢኖረው'ኳ አዛባ ተቀብቶ የእሪያዋች መፈንጫ ይሆናል፡፡ ወደ ክበባችን እንመለስና በስተማካተቻ ዛሬም ሁሌም በጥበብ ዘርፍ ያሉ ዝሆኖችን ያራግጥልን እያልኩ ድንቅ የሆነውን የእሳቱ ተሰማ የጸጸት ቅኔ ልጋብዛቹ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

“እርግማኔን መልስልኝ”
-------//--------

ከአቻምና በፊት አቻምና …
የዛሬን አያድርገውና፤
ያኔ በልጅነቴ …
በአፍላ ደሜ፣ በፍላቴ፤
አለድግ አለመቀነት… እየሮጥኩ የታጠቁት፣
ይጠልፍና ይጥለኛል …
አለልክ አለስፍሮቴ … እያወጋሁ የጎረስኩት፣
ማንቁርቴ ላይ ይጣበቃል …
… ብዬ በማልሸበር በማልዳዳበት ሰዓት፣
በየካቲት ዋናተኞች … በዘራፊዎቹ …
ተከብቤ በነበር ወቅት፤
ሳላቅማማ ሳልገደር፣
ጸጋዬ ብዕርህ “ይሙት” … ብዬ ረግሜህ ነበር፣
… ወይ ጣጣዬ … የእኔ ነገር!
ጸጋዬ በሥነ-ጥበብ፣ በሥነ-ግጥም ዓለም፤
ምሰለኝ እንጂ … አልመስልህም
እወቀኝ እንጂ … አላውቅህም …
ይሄ ይውደም፣ ያ ይለምልም …
… ብሎ ፈሊጥ ነውር አይደለም?
አሳምረህ ታውቀዋለህ
ይቅር በለኝ፣ አልነግርህም፡፡
“… የቃለ ልሣን ቅመሙ
የባለቅኔ ቀለሙ
ነጠበ እንጂ ፈሰሰ አንበል፣ ቢዘነበል እንኳ ደሙ
ሰከነ እንጂ ከሰለ አንበል፣ ቢከሰከስ እንኳን አፅሙ…
… የቃለ እሳት ነበልባሉ
የድምፀ ብርሃን ፀዳሉ
የኅብረ ቀለማት ኃይሉ
አልባከነምና ውሉ
የዘር ንድፉ የፊደሉ
ቢሞት እንኳ ሞተ አትበሉ”
ከሰው በፊት ያልከው አንተ፣
አቦ ተወኝ! … ተለመነኝ፤
አይን ለአይን አንተያይ፣ እርግማኔን መልስልኝ …
ለሀ…ሁህ፣
ለአቦጊዳህ …
ለአዋሽ-ሰገዱ ዱታህ፤
ምሰለኝህን እምቢ ብል፣ ብከፋብህ… ባመርብህ፣
በበልግህ…
በእሾህ አክሊልህ…
በኦቴሎህ… በማክቤዝህ፣
ጸጋዬ በአበባ እሳትህ…
የለም፣ በእሳት አበባህ…
… እማረክ እማለላለሁ፤
በሥነ-ግጥም ጥማቴ…
የጸጋዬ ቤት ቤቴ፣… በሆነ እያልኩ እመኛለሁ!
ብዕርህን ላይ ነው እምጓጓው፤
ልጠጋህ ነው እምንፏቀቀው፤
የቃላት ኅብረ ቀለምህን
የሕይወት ስንክሳርህን … ጸጋዬ፣ የጸጋ ዳስክን
ፊደል አጣጣልህን
ድምፅ አወራረድህን
የቲያትር የምርምር የፈጠራ ተውህቦህን
እንደ ማክማክሳ ሙርቲ፣
እንደ አምባሰል… እንደ ባቲ..
እንደ በገና እሮሮ
እንደ ሙሾ እንጉርጉሮ …
… እንደ ሰንጎ መገን ጉም
እንደ የወል ቤት እመም …
… እንደ ዳዊት ቀያይ ቤቶች
እንደ ያሬድ ዝማሬዎች…
ወርሰን የምናወርሰው
ዘግነን እምንለግሰው…
የጸጋዬ የብዕር ልጅ፣ የጸጋዬ የግጥም ምት፤
ይደግ ይመንደግ እንጂ፣ እንዴት ይባላል ይሙት?!
ምን ቆርጦኝ ነው እንዲያ ያልኩት?
ወንድሜ… ነውሬን ተውልኝ፤
እባክህ ተባረክልኝ …
እግዜር ይስጤን ውሰድና…
እርግማኔን መልስልኝ፡፡
ከእንግዲህ እኔ በምንም…
ምሰለኝ እንጂ… አልመስልህም
እወቀኝ እንጂ… አላውቅህም…
ምንም ቢሆን፣ አልልህም፡፡
ጽጌሬዳ ቀለሟ ቀይ፣ ብቻ ነው ብሎ ዘበት
ያንተ ጎዳና ወደ ሲኦል፣ የእኔይቱ ወደ ገነት፤ …
… ብሎ ፍጥም፣ ዝግት ግርግም፣
ፍካሬ-እቡይ ዛሬ የለም፡፡ …
ጠብ ያለሽ በዳቦን አልፈን
ተቸንፈን… አሸንፈን፤ አቸንፈን… ተሸንፈን …
አቦ ተወኝ! እባክህን፤…
ባንኳኳን ልንኳኳን መከራ ነው የመከረን
.
(ባላቅኔ እሳቱ ተሰማ)
ድመት እንዳመሉ ፥ …...አይጥን ቢጠላም
ቢያጫውታት እንጂ ፥ ቶም ጄሪን አይበላም
እነሱ ተኳርፈው ፥ ተጣልተው ላይዘልቁ
እናንተ በጭቀት ፥ ......በሞት አትለቁ

( ሚኪ እንዳለ )
አራባ'ና ቆቦ
--------

አንቺ ተናጋሪ ፥ እኔ ከንፈር ወዳጅ
እስከ መቼ ይሆን…
አፍሽን እያየው ፥ በሰቀቀን ምባጅ
፡፡፡፡፡
ያሰርሽው ቃልኪዳን ፥ ደርሶ ከአመቱ
ሺ ልቦች በስጋት ፥ የቁም እየመቱ
ምነው እንደ አርያም…
ከ'ግዜሩ በለጠ ፥ ...የሆድሽ ስፋቱ
፡፡፡፡፡
እሳት እንዳመሉ ፥ በ'ፍታ ይነዳል
. . . . . . . . . .በ'ፍታም ይጠፋል
ብለን በመጽናናት ፥ ተቀምጠን ሳለ
በደረቅ አበሳ…
ምንም ማያገባው ፥ እርጥብ ተቃጠለ
፡፡፡፡፡፡
ዛሬ ምንጩ ነጥፎ
የሚዛንሽ አውታር ፥ ወደራስሽ ዘንፎ
የከንፈርሽ ንዝረት ፥ ከተግባርሽ ገዝፎ
እንደ ዘብር ጭጋግ ፥ ዙሪያችንን ከቦ
እንደነ ተዋናይ የጎንጅ ደመና ፥ ላይያዝ ረቦ
ሆነና ቸገረን ልብሽ ከአራባ ፥ ምላስሽ ከቆቦ

«ሚካኤል እንዳለ»

በቴሌግራም 👉 www.tg-me.com/mebacha ከጥበብ እልፍኝ ይቋደሱ

@mebacha
2024/06/29 01:36:47
Back to Top
HTML Embed Code: