Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

❇️አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) መደራ❇️

=>አቡነ ገሪማ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሮም
ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸው መስፍንያኖስና ሰፍንግያ
እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት
ነበሩ:: ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ፡፡

+እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን ይስሐቅ
ብለው አሳደጉት:: ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ
ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ:: ለ7 ዓመታት ሕዝቡን
በፍትሕ
እያስተዳደረ: መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል::

+አንድ ቀን ግን ከግብፅ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው::
ላኪው አባ_ዸንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ
ንግሥና ምን ያደርግልሃል?
ይልቁኑስ በሰማይ ለዘለዓለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና"
የሚል ነበር::

+ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው
ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ:: ድንገት
ግን ቅዱስ_ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብፅ አባ
ዸንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው::

+እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው
አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮዽያ
መጡ:: ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና
ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው:: ሰውነታቸውን በገድል
ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር::

+አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው
አባ ዸንጠሌዎን አዘኑ:: ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ
የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ" አሉ:: አባ ይስሐቅ ግን
"ሰዎች ብቻ አይደሉም: ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል"
ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (800 ሜትር)
ተጠራርጎ ሸሸ::

+ይሕንን የተመለከቱት አባ ዸንጠሌዎን
"ወልድየ_ይስሐቅ_ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)
አሏቸው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮም
"አቡነ_ገሪማ" ተብለው ቀሩ፡፡

+አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና
ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም
ግሩም ነህ" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል::

+ጻድቁ ወንጌልን: ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ
ተአምራትን ሰርተዋል:-

1.ስንዴ ጠዋት ዘርተውት በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር "በጽባሕ
ይዘርዕ: ወበሠርክ የአርር" እንዲል::
2.ጧት የተከሉት ወይን በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር::
3.አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጸበል ሆኖ ዛሬም አለ::
4.ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች::
5.አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን
አቁመዋታል::

+ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን
ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው::
"ስምሕን የጠራ: መታሰቢያህን ያደረገ: እስከ 12 ትውልድ
እምርልሃለሁ:: አንተ ግን ሞትን አትቀምስም" ብሏቸው
ተሰወረ:: ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ
ብሔረ_ሕያዋን አድርሰዋቸዋል፡፡

✞ አባ ለትጹን የዋህ ✞

=>ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን
በግብጽ የተወለዱ:
¤በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ:
¤ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ:
¤አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ:
¤ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ:
¤በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን
የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው::

+ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው
ንስሃ ይገቡ ነበር:: አንዴ ግን እናቱን 10 ጊዜ በዝሙት
ያረከሰ: ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማሕጸኗ
የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል
ደረሱ::

+አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ:: ኃጢአቱ
ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሃ ሊቀበሉ ጀመሩ: ከንስሃቸው
ጽናት
የተነሳ ሞቱ:: ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ:
አልምረውም" አላቸው::

+ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ:: ለ2ኛ ጊዜ ሞቱ::
አሁንም ቀጠሉ: 3ኛ: 4ኛ: 5ኛ ጊዜም ሞቱ:: በ6ኛው ግን
መፍትሔ መጣ:: ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ:
ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ:: "ፍርዴ አይታጠፍምና
ወደ ገነት
አላስገባትም:: ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል
አልጥላትም:: ስለዚሕም እንዳልተፈጠረች ትሁን" ብሎ
እፍ
አለባት:: ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች::

+ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ:: ከብዙ
ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ::

✞ አባ_ዸላሞን_ፈላሲ ✞

=>ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ
አባ ዸላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር:: ይሕ ቅዱስ
ከአጋንንት
ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል:: ከ60
ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው
አላየም::

+በነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል::
በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል::
እርሱ ግን
በእግዚአብሔር ቸርነት: በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና
በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል::

=>ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት
ይክፈለን:: በምልጃቸውም ይቅር ይበለን::

=>ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
2.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
3.አባ ዸላሞን ፈላሲ
4.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
5.ሰማዕታት እለ አኮራን
6፡ ፯፼ ፹፻ ሰማዕታት ማኅበረ ቅዱስ ተክለሃ ይማኖት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት
2፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
3፡ ቅዱሳን መክሲሞስ ወደማቴዎስ
4፡ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::ቅዱሳኑንም
አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . . ጻድቃን ምድርን
ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::የጻድቅ አፍ ጥበብን
ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::የአምላኩ ሕግ በልቡ
ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                          †                           

🕊        †      የጽድቅ በር     †        🕊

💛

[   እንደሚወጣ ጭስ ሆኖ አየው .... ! ]

..............................

❝ የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፡ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ ፡ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡

የነፍስን ፆር [ ከዲያብሎስ የሚከፈትን ውጊያና የስጋ ፈቃድን ] ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡ ❞

[  ቅዱስ ዮሐንስ ሃፂር  ]

†   🕊              †                🕊   †

አንድ ወንድም ገና በጧቱ ራበውና ከሦስት ሰዓት በፊት ላለመብላት ከፍላጎቱ ጋር ታገለ፡፡ ሦስት ሰዓት ሲሆን ደግሞ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ልቆይ ብሎ ራሱን አስገደደ፡፡ ስድስት ሰዓት ሲሆን ዳቦውን ቆርሶ ሊበላ ተቀመጠ ፤ ሆኖም "አይ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ልቆይ" አለና እንደገና ተነሣ፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጸሎት ሲያደርስ የዲያብሎስን ኃይል ከእጁ ሥራ ላይ [ ይሠራ ከነበረው ነገር ላይ ] እንደሚወጣ ጭስ ሆኖ አየው ፣ ረሃቡም ጠፋ፡፡"

[ ከበረሐውያን ሕይወትና አንደበት   ]


         †              †               †
▬▬▬▬ ▬▬▬▬▬ ▬▬▬▬
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
💛
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊     ጾ መ ሐ ዋ ር ያ ት     🕊

▷  ❝  በዚያ ጊዜም ይጦማሉ ❞

[   " በመ/ር አምኃ በላይ ... ! "   ]

[                       🕊                       ]
-----------------------------------------------

❝ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን ? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል ፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።

በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም ፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና ፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።

በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም ፤ ቢደረግ ግን ፥ አቁማዳው ይፈነዳል ፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል ፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ❞

[ ማቴ . ፱ ፥ ፲፭ ]


🕊                        💖                     🕊
                             👇
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
††† እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድምያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ድምያኖስ †††

††† አባ ድምያኖስ ተወልደው ያደጉት ግብጽ ውስጥ ነው:: ቤተሰቦቻቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ቅዱሳት መጻሕፍትንና በጐ ምግባራትን ተምረዋል:: ዕድሜአቸው ወደ ወጣትነቱ ሲጠጋ ሥርዓተ መነኮሳትን ለማጥናት ወደ ገዳመ አባ ዮሐንስ ሔዱ:: በዘመኑ ማንኛውም ሰው ተገቢውን ፈተና ሳያልፍ እንዲመነኩስ አይፈቀድለትም ነበር::

አንድ ሰው ሊመነኩስ ካሰበ በትክክል መናኝ መሆኑ ቢያንስ ለሦስት ቢበዛ ደግሞ ለአሥራ ሁለት ዓመታት እንዲፈተን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታዝዛለች:: ይኸውም "ሥርዓተ አመክሮ" ይባላል:: ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ መቆየት ከፈለገ ግን ይፈቀድለታል::

በዚህም መሠረት አባ ድምያኖስ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በአጭር ታጥቀው ገዳሙን አገልግለዋል:: ገዳሙም ይገባሃል በሚል ዲቁና እንዲሾሙ አድርጓል:: ከዚህ በኋላ ከአባቶች ተባርከው: ገዳሙንም ተሰናብተው ወጡ:: ነገር ግን የወጡት ወደ ዓለም ሳይሆን ራቅ ወዳለ ገዳም ነው::

የረድዕነት ዘመናቸውን ጨርሰዋልና አዲስ በሔዱበት ገዳም ወደ መደበኛው ገድል ተሸጋገሩ:: ያም ማለት በጾም: በጸሎት: በስግደት: በትሕርምት: በትሕትናና በፍቅር ሙሉ ጊዜአቸውን ማሳለፍ ጀመሩ:: በእንዲሕ ያለ ግብርም ዘመናት አለፉ::

የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ አባ ጴጥሮስ በእረኝነት ሥራ የሚያግዛቸው ሰው እንዲፈለግላቸው በጠየቁት መሠረት ትምሕርትም: ጽሕፈትም: በጐ ምግባራትም የተሟላለት ሰው እንደ አባ ድምያኖስ አልተገኘምና ያለፈቃዳቸው ወደ እስክንድርያ ተወስደው የፓትርያርኩ ረዳት ሆነው ተሾሙ:: በረዳትነት በቆዩበት ጊዜ በወንጌል አገልግሎትና በመንኖ ጥሪት ሕዝቡንና ሊቀ ጳጳሳቱን አስደስተዋል::

ልክ አባ ጴጥሮስ ሲያርፉ ሕዝቡና ሊቃውንቱ በአንድ ድምጽ አባ ድምያኖስን ለፓትርያርክነት መርጧቸዋል::

ጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት በዘመነ ፕትርክናቸው ከግል የቅድስና ሕይወታቸው ባለፈ እነዚህን ፈተናዎች በመወጣታቸው ይመሰገናሉ::
1.ሕዝቡ ከሃይማኖታቸው እንዳይወጡና በምግባር እንዳይዝሉ ተግተው አስተምረዋል::

2.በአካል ያልደረሱባቸውን በጦማር (በመልዕክት) አስተምረዋል::

3.በዘመናቸው የተነሱትን መናፍቃን ተከራክረው : የተመለሰውን ተቀብለው : እንቢ ያሉትን አውግዘዋል::

4.ከአንጾኪያ ፓትርያርክ የመጣውን የኑፋቄ ጦማር (መልዕክት) በይፋ ተቃውመው አውግዘዋል::

ለአርባ ሦስት ዓመታት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው ያገለገሉት አባ ድምያኖስ ከብዙ ትጋት በኋላ በመልካም ሽምግልና በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: ከግብጽ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ዝርዝር ውስጥም አርባ አምስተኛ ሆነው ተመዝግበዋል::

††† ልመናቸው : ክብራቸው : ጸጋ ረድኤታቸው አይለየን::

††† ሰኔ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ድምያኖስ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት : ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. ፳፥፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from M.A
አንድ በጣም ትልቅ ቆሻሻ የጫነ ጋሪ የሚገፋ ሰው ወደ ቤትህ መጥቶ "እባክህ በርህን ክፈትልኝና ይህን ቆሻሻ አንተ ቤት ላራግፈው?" ቢልህ፣ "ውይ የሚጥልበት ቢያጣ ነው። ባይቸገር ወደ እኔ አይመጣም ነበር" ብለህ ደጅህን ከፍተህ ታስገባዋለህ? በፍጹም፤ እንደውም "እንዴት ብታስበኝ ነው? ምነው ስታየው ቤት አልመሰለህም? እንዴት ሰው በሚኖርበት ቤት ቆሻሻ ካልደፋሁ ትላለህ? ስትል ለጠብ ትጋበዛለህ። መደፈርህ እያንገበገበህ  "እምቢ!" ብለህ ትቆጣለህ። በእርግጥም ያስቆጣል።

ግን ሌላ የሚከፋ ሽታ ያለው ቆሻሻን ጭኖ ለመጣ ባላጋራ እኮ በፈቃድህ የከፈትከው ቤት አለ። "የምን ቤት?" ብለህ ብትጠይቀኝ "ልብህ ነዋ" ብዬ እመልስልሃለሁ፤ "ማን ይኖርበታል?" ካልኸኝም "እግዚአብሔር ነዋ" እልሃለሁ።

አንተ ለመኖሪያ ቤትህ ጽዳት የምትጠነቀቀውን ያህል የያዕቆብ አምላክ ለሚያርፍበት ኅሊናህ ተጠንቅቀህ ታውቃለህ? ሰይጣን ጭኖ የሚያመጣውን የኃጢአት ቆሻሻ ሁሉ እሺ ብለህ ወደ ልብህ በማስገባት የፈጣሪህን መቅደስ ለምን ታቆሽሻለህ? ንጹሑ እግዚአብሔር የሚያድርበትን ቤት ሊያቆሽሽ በመጣ ሰይጣን ላይ እንዴት አልተቆጣህም? ድፍረቱ ለምን አላብከነከነህም?

እግዚአብሔር አንተ ልትኖርበት ከምትፈልገው ንጹሕ ቤት የበለጠ ጽዱ መቅደስ የማይፈልግ ይመስልሃል?

(Dn Abel Kassahun Mekuria )

ምንጭ ፦ ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
እንኩዋን ለሐዲስ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ

=>ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር:: በተለይ ተንባላቱ ግብፅና ሶርያን ከያዙ በሁዋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር:: ቅዱስ ጊዮርጊስ (ልብ በሉልኝ ሊቀ ሰማዕታት አይደለም) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር::

+እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር:: ስሙንም መዛሕዝም ይሉታል:: ሕጻኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም:: የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር:: በዚሕ ምክንያት ሳይጠመቅ 7 ዓመት ሞላው::

+እናቱ ግን ሕጻን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር:: ባይጠመቅም ጸበሉን: እመቱን ትቀባው ነበር:: ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር:: አንድ ቀን ግን ሕጻናት ሲቆርቡ አይቶ ካልቆረብኩ ብሎ አለቀሰ:: ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው:: "ጌታየ! ልጄን እርዳው" አለች::

+ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ:: ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት:: "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል" አለችው::
ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር::

+አስቀድሞ ትምሕርተ ክርስትናን ተማረ:: ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ:: ጥቂት ጊዜ ከቆየ በሁዋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት:: "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ" አለችው:: ከግብፅ ተነስቶ ሶርያ ገባ:: አባቶችን አፈላልጎ ተጠመቀ:: ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ::

+ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ" ቢላቸው #መንፈስ_ቅዱስ አናግሯቸው "#ጊዮርጊስ" አሉት:: እሱም ደስ እያለው: ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ:: ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው:: ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብፅ ተመለሰ::

+በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም: ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ:: ዕለቱኑ አሠሩት:: ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው አሉት:- "አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ:: ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር: ለእኛም ሞገስ ነው" ብለውም አጽናኑት:: (እንዲሕ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው!!!)

+ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት: አካሉን ቆራረጡት: ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት:: በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት:: እርሱ ግን #ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ:: ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ" አለው::

+በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት:: ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት:: ወደ ባሕርም ጣሉት:: እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር:: በዚሕች ቀን እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል::

=>ቸሩ አምላክ ከሰማዕቱ ጽናትን: ትእግስትን: ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

=>ሰኔ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ ሰማዕት
2.አባ ብሶይ አኖብ ሰማዕት (በአንበሳ ጀርባ ላይ የተቀመጠ አባት)
3.ቅዱሳን "5ቱ" ጭፍሮች (በብዙ ስቃይ ሰማዕት የሆኑ ባልንጀሮች)
4.አባቶቻችን የደብረ ቁዋዐት ጻድቃን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

=>+"+ ስለዚሕ #ወንድሞቼ_ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና:: +"+ (1ቆሮ. 10:14-18)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Forwarded from Bketa @¥
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
✞✞✞🌹 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ 🌹✞✞✞

🌹 እንኳን አደረሳችሁ 🌹

🌹 ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት🌹

=>ትናንት ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ወረደ:: ፊልዽስዩስ በምትባል ሃገር በዼጥሮስ እጅ
የመጀመሪያዋን ቤተ_ክርስቲያን አነጸ ብለን ነበር:: በዚህች ዕለት ደግሞ አእላፍ
መላዕክትን: ሰማያውያን ቅዱሳንን እና እናቱን ቅድስት
ድንግል
ማርያምን ይዟት ወረደ::

+ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዛው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን
ከቅዳሴው በፊት 2 ነገሮችን አሳየ:-
1.አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ
ሥርዓተ ቤተ ክርረስቲያንን አሳየ::
2.ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ_ዼጥሮስን ከመካከል አቁሞ "አርሳይሮስ" ሲል ሾመው:: ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት
(ፓትርያርክ) ማለት ነው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት
"አክዮስ" እያሉ 3 ጊዜ አሰምተው ጮሁ:: አክዮስ ማለት በግዕዙ
"ይደልዎ": በዐማርኛው ደግሞ "ይገባዋል: ያሥምርለት"
እንደ
ማለት ነው::

+ጌታችን ይሕን ከከወነ በኋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ::
¤አማናዊት ማሕደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ:
¤ቅዱስ ዼጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ:
¤ቅዱስ_እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ሆኖ:
¤ሐዋርያት ድንግልን ከበው:
¤መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቁመው ጌታችን ቀድሶ
ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ::

+በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር
የማይችል ደስታ ተደረገ:: ከቅዳሴ በኋላ ጌታችን
ሐዋርያትን
አዘዛቸው::
"ከዚህ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም
አብያተ ክርስቲያናትን እነጹ:: ይህችን ዕለት የሚያከብራትን
አከብረዋለሁ::" ብሏቸው ከድንግል እናቱ ከመላዕክቱ ጋር
ዐረገ::

+"+ ሰኔ_ጐልጐታ +"+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ
ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ
እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም
ያመኑትን
"ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሸሹ" ብሎ መከራቸው::
+ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ
መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ
መሸተኛዋ ሴት
እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት
ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል
ሰይፍ
አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

+እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ
(መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ
ቶማስ ነገሩን
ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ
ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል
ዝም
አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና
"ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን
ጠብቆ ሊያነሳ
ሲል እጁ ሰለለች::

+ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም
እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ
ግን ሕዝቡ
ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን
አምጡልኝ" አለ:: የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል . . .
የገደልኩሽ
እኔ: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው . . . ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው::

+እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች::
ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

=>ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

=>ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
8.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘምስር (ሰማዕት)
9.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ዻዻሳት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ አበው ጎርጎርዮሳት
2፡ አባ ምዕመነ ድንግል
3፡ አባ ዓምደ ሥላሴ
4፡ አባ አሮን ሶርያዊ
5፡ አባ መርትያኖስ
6፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል

=>+"+ ስለ ጽዮን ዝም አልልም . . .
አሕዛብም ጽድቅሽን: ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ::
የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም
ትጠሪያለሽ::
በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ
የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ:: +"+ (ኢሳ. 62:1-3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

""ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን""::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
2024/06/28 19:29:22
Back to Top
HTML Embed Code: