Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† መስከረም ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት †

[  † እንኳን ለጻድቁ አባ ሙሴ እና አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]


† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊   አባ ሙሴ ዘሲሐት  🕊   †

† ገዳመ ሲሐት የሚባሉ ብዙ ቦታዎች አሉ:: ቅድሚያውን የሚይዘው ግን የግብጹ ነውና ዛሬ የዚህን ገዳም አንድ ቅዱስ እናስባለን:: ሕይወታቸውም በእጅጉ አስተማሪ ነው:: ቅዱሱ አባ ሙሴ ይባላሉ:: የ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ናቸው::

እኒህ ጻድቅ አንድ ነገር ከሌሎች ቅዱሳን ይለያቸዋል:: ከምግባርና ትሩፋት በቀር አንድም የእግዚአብሔር ቃል አያውቁም:: ዝም ብለው በየዋሕነት ይኖሩ ነበር እንጂ:: ተወልደው ባደጉበት በምድረ ግብጽ በቅን ሕይወት ኑረው: በወጣትነታቸው ወደ ደብረ ሲሐት ገቡ::

በዚያም በብሕትውና ዘግተው በጾምና ጸሎት ተወስነው ለ፵፭ [45] ዓመታት ኖሩ:: እጅግ የዋሕ ሰው ናቸውና ከጸጋ [ከብቃት] ደረሱ:: ሰው በአካባቢው አልነበረምና አብረው የሚውሉት ከግሩማን አራዊት ጋር ነበር:: አራዊቱም ጻድቁን ያጫውቷቸው: ይታዘዙላቸውም ነበር:: በፈንታው ደግሞ አባ ሙሴ በተአምራት ዝናብ ያዘንቡላቸው: ምግብም ይሰጧቸው ነበር::

አባ ሙሴ ልብስ አልነበራቸውምና በቅጠል ይሸፈኑ ነበር:: የምግባቸው ነገርማ "በመጠነ ኦፍ" ይላል . . . ትንሽ ድንቢጥ የምትበላውን ያህል ቀምሰው: ጥርኝ ውሃም ተጐንጭተው ነበር የሚኖሩት:: በሁዋላ ግን እጅግ ከመብቃታቸው የተነሳ ዐይናቸውን ሲገልጡ 'ገነት' [የአትክልት ሥፍራ] ይታያቸው ነበር:: ከዚያም ለበረከት ቆርጠው ይበሉ ነበር::

ሰይጣን እርሳቸውን ይጥል ዘንድ እጅግ ቢጥርም አልተሳካለትም:: በስተ መጨረሻ ግን የሚጥልበት መንገድ ተከሰተለት:: ምንም ባለ መማራቸው ሊፈትናቸውም ተነሳ:: አንድ ቀን ከበአታቸው በር ላይ ከአራዊት ጋር ተቀምጠው ሳለ ሰይጣን ሽማግሌ መነኩሴ መስሎ እየተንገዳገደ መጣ::

አራዊቱ ደንግጠው ሲሸሹ እርሳቸው ግን ሳያማትቡ ሮጥ ብለው ደገፉት:: ወደ በዓታቸውም አስገቡት:: ማታ ላይ ሲጨዋወቱ "ማንነትዎን ይንገሩኝ" አላቸው:: ለአባ ሙሴ ሰይጣኑ የበቃ አባት መስሏቸዋልና የ፵፭ [45] ዓመታት ድንግልናዊ የተባሕትዎ ሕይወታቸውን ነገሩት::

እርሱም በፈንታው ሐሰቱን ቀጠለ:: "እኔ ግፍ እየሠራሁ በዓለም እኖር የነበርኩ ሰው ነኝ:: ነገር ግን ዓለምን ትቼ ላለፉት ፵ [40] ዓመታት በበርሃ በንስሃ ኑሬአለሁ:: ያም ሆኖ አንዲት ሴት ልጅ አለችኝና 'ማን ያገባታል' ብየ ስጨነቅ አንተ እንደምታገባት ተገለጠልኝ" አላቸው::

አባ ሙሴ ደንግጠው "እንዴት ድንግልናየንና ሕይወቴን ትቼ አገባለሁ?" ሲሉም ጠየቁ:: ሰይጣን ግን ቃለ እግዚአብሔር እንደማያውቁ ተረድቷልና "አንተ ከአብርሃም: ከያዕቆብ: ከዳዊት ትበልጣለህ? እነሱ አግብተው የለ!" ብሎ ቢገስጻቸው አንዳንዴ አለ መማር ክፉ ነውና አባ ሙሴ ሸብረክ አሉ: ተረቱ::

ከዚያም ተያይዘው ጉዞ ወደ ዓለም ሆነ:: መንገድ ላይ ግን መነኩሴ ነኝ ያለው ሰይጣን ወደቀና የሞተ መሰለ:: አባ ሙሴ በእንባ ቀብረውት ሲሔዱ ተኖ ጠፋ:: አባ ሙሴ ቀና ሲሉ ሰይጣን በምትሐት የሠራውን ያማረ ግቢና ቆንጆ ሴት አዩ:: ወደ እሷ እቀርባለሁ ሲሉ አውሎ ንፋስ ማጅራታቸውን መትቶ ጣላቸው::

አባ ሙሴ ከወደቁበት ሲነሱ ያዩት ነገር ሁሉ ሰይጣናዊ ምትሐት መሆኑን አወቁ:: ወደ በአታቸው መጥተው ከገነት ፍሬ ቢቀምሱ ጸጋ እግዚአብሔር ተለይቷቸዋልና መራራ ሆነባቸው:: እያለቀሱ ከበዓታቸው ወጡ::

መንገድ ላይ ያው ሰይጣን ነጋዴ መስሎ: "መንገድ ልምራዎት" ብሎ ምንም ከሌለበት በርሃ ላይ ጥሏቸው ተሰወረ:: የሚያደርጉት ጠፋባቸው:: ረሃቡ: ጥሙ: ከፈጣሪ ጸጋ መለየቱ አቃጠላቸው:: አሁንም አንዲት ሴት መነኩሴ ድንገት መጥታ ወደ በዓቷ አስገባቻቸው::

የማይገባውን ድርጊት እናድርግ ብላ አባበለቻቸው:: ይባስ ብላ ወደ አይሁድ እምነት እንዲገቡ አሳመነቻቸው:: ወዲያውም ወደ ሌላ በርሃ ወስዳ "አወቅኸኝ?" አለቻቸው:: "የለም" አሏት:: እዚያው ላይ ተቀይራ ጋኔን መሆኗን አሳይታቸው ተሠወረች::

አባ ሙሴ በዚያው ሥፍራ በአንድ ጊዜ ሁሉንም አጡ:: አለቀሱ: ተንከባለሉ:: እንባቸው እንደ ዥረት ፈሰሰ:: ልቡናቸው ሊጠፋ ደረሰ:: ወደ ፊታቸው አፈር እየረጩ: "ወየው" እያሉ ሲያለቅሱ ጌታችን መልአኩን ላከላቸው::

እንደ ቀድሞውም ፊት ለፊት ታይቶ አጽናናቸው:: "አይዞህ! ፈጣሪ እንባህንና ንስሃህን ተቀብሏል" ብሎ ወደ ስውራን ከተማ ወሰዳቸው:: በዚያም ለ፯ [7] ቀናት ቆይተው በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: አባ ሳሙኤልም ቀብሯቸዋል::


†  🕊  አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ  🕊   †

† ጻድቁ የነበሩት በ፲፫ [13] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን የተወለዱት ትግራይ ውስጥ ነው:: ዛሬም ድረስ የብዙ ስውራን ቤት እንደ ሆነ የሚታወቀውን ደብረ_ሐዘሎንም እርሳቸው እንደ መሠረቱት ይነገራል:: አባ አንበስ ከገዳማዊ ትሩፋታቸው ባሻገር በአንበሶቻቸው ይታወቁ ነበር::

የትም ቦታ ሲሔዱ በአንበሳ ጀርባ ላይ ነበር:: በእርግጥ አባቶቻችን ከዚህም በላይ ብዙ ድንቆችን ማድረግ ይችላሉ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነውና:: ጻድቁ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ: የሳሙኤል ዘዋልድባና የአባ ብንያሚን ባልንጀራ ናቸው:: ዛሬ ደግሞ ዕረፍታቸው ነው::

† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፈተና አስቦ እኛን ከመከራ ይሰውረን:: በቃል ኪዳናቸው ይጠብቀን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

🕊

[  † መስከረም ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. አባ ሙሴ ዘደብረ ሲሐት
፪. አባ አንበስ ኢትዮዽያዊ
፫. አበው ኤዺስ ቆዾሳት
፬. አባ ዲዮናስዮስ
፭. አባ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ በትንከል ዲያቆን

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫. ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው [ዘካርያስና ስምዖን]
፬. አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
፭. አቡነ ዜና ማርቆስ
፮. አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል
፯. ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ [ዓምደ ሃይማኖት]

† " በመጠን ኑሩ: ንቁም:: ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና:: በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት::" † [፩ዼጥ.፭፥፰] (5:8)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  🌼  መስከረም [ ፬ ] 4 ቀን የሚከበሩ የቅዱሳን በዓላት 🌼  †

[ †  🕊  እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ እና ለቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።  🕊 †  ]


† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊 ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን  🕊  †

† ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብፅ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ አውሴ ይባላል:: ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ፪፻፲፭ [215] ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያትሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ ፹ [80] ዓመቱ: ኢያሱ ደግሞ ፵ [40] ዓመቱ ነበር::

ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለ40 ቀን የታሠበላቸውን መንገድ [፵] 40 ዓመት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምሕሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም:: አውሴን ኢያሱ ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው::

ኢያሱ ማለት " መድኃኒት" ማለት ነው:: ለዚሕም ምክንያቶች አሉት :-

፩. ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል: ምድረ ርስትን አውርሷል::
፪. ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ [ጥላ] እንዲሆን ነው::

ቅዱስ ኢያሱ በበርሃው ለዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል:: ሊቀ ነቢያትን ታዞታል [አገልግሎታል] : እሥራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል:: በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል:: ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን: ካሕናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: ይህን ጊዜ ዕድሜው [፹] 80 እየሆነ ነበር::

† እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን [አስተዳዳሪ] እንዲሆን ሾመው:: ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ:

¤ ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ:
¤ ሕዝቡን አሻግሮ:
¤ የኢያሪኮን ቅጥር [፯] 7 ጊዜ ዙሮ:
¤ በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ:
¤ የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ:
¤ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ::

የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ:: እነዛን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል: በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ:: በዚሕች ዕለትም ለ፲፪ [12] ቱ ነገደ እሥራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን: ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም [በኤሎም ሸለቆ] አቆመ::

ሰባት አሕጉራተ ምስካይ [የመማጸኛ ከተሞችን] ለየ:: ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለ፵ [40] ዓመታት አገለገለ:: በመጨረሻም ለሕዝቡ :- "እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን:: [ኢያ.፳፬] (24) እናንተስ?" አላቸው:: እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን" አሉት:: ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ 3 ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ::

ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት:: ሐውልቷ ፫ [3] ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በ፫ [3] ወገን [በነፍስ: በሥጋ: በልቡና] ድንግል ናት:: አንድም በ፫ [3] ወገን [ከኃልዮ: ከነቢብ: ከገቢር ኃጢአት] ንጽሕት ናት:: ለዚህም ነው አባሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" [የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ] ሲል ያመሰገናት::

ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በ፹ [80] ዓመት: በተወለደ በ፻፳ [120] ዓመቱ [ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በ፻፲ [110] ዓመቱ ይላል] በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለ፴ [30] ቀናት አለቀሱለት::


†  🕊  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  🕊  †

† አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው::

ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል:: ከእርሷ ጋር ለ፲፭ [15] ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኩዋን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላዕክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በሁዋላ ለ፸ [70] ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል::

ሶስት መልዕክታት: ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት: እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጉዋቸዋል::

† እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው :-

¤ ወንጌላዊ
¤ ሐዋርያ
¤ ሰማዕት ዘእንበለ ደም
¤ አቡቀለምሲስ [ምሥጢራትን ያየ]
¤ ታኦሎጐስ [ነባቤ መለኮት]
¤ ወልደ ነጐድጉዋድ
¤ ደቀ መለኮት ወምሥጢር
¤ ፍቁረ እግዚእ
¤ ርዕሰ ደናግል [የደናግል አለቃ]
¤ ቁጹረ ገጽ
¤ ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ [ከጌታ ጎን የሚቀመጥ]
¤ ንስር ሠራሪ
¤ ልዑለ ስብከት
¤ ምድራዊው መልዐክ
¤ ዓምደ ብርሃን
¤ ሐዋርያ ትንቢት
¤ ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
¤ ኮከበ ከዋክብት

† በዚህች ዕለት ቅዱሱ ሐዋርያ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ: ከአባቱ ዘብዴዎስ መወለዱን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች::


†   🕊   አባ ሙሴ ዻዻስ   🕊  †

እሥራኤላዊ ሲሆኑ ከአቡነ ሰላማ ቀጥለው የመጡ የሃገራችን ዻዻስ ናቸው:: ፍጹም ገዳማዊና ትጉህ: ባለ ረዥም ዕድሜ ጻድቅም ናቸው::

ገዳማቸው ወሎ ውስጥ ቢገኝም አስታዋሽ ያጣ ይመስላል:: መናንያኑ ለዕለት እንኩዋ የሚቀምሱት አጥተው ሲቸገሩ መመልከቱ እጅግ ያማል::

† በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር:: ቸሩ ጌታ ስም አጠራራቸው ካማረና ከከበረ ወዳጆቹ በረከትን ያሳትፈን::

🕊

[  † መስከረም [ ፬ ] 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  🌼  ]

፩. ቅዱስ ኢያሱ ወልደ ነዌ [ነቢይና መስፍን]
፪. ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ [ልደቱ]
፫. ቅዱሳን ዘብዴዎስና ማርያም ባውፍልያ
፬. አባ መቃርስ ሊቀ ዻዻሳት
፭. አባ ሙሴ ዻዻስ

[  † ወርኀዊ በዓላት  🌼   ]

፩. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፪. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]

† " አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ:: በእውነተኛም ልብ አምልኩት . . . እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ . . . የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ: የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ:: እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን::" † [ኢያሱ.፳፬፥፲፬] (24:14)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊                    💖                   🕊

[ 🌼  ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  🌼 ]

                        🕊                       

🕊                   

እንኳን ለቅዱስ እና ታማኝ ሐዋርያ ዮሐንስ ወንጌላዊ የልደቱ መታሰቢያ አደረሳችሁ።

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

[ መስከረም ፬ [ 4 ] ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ልደቱ ]

ካህናቱ በሰዓታት ምስጋናቸው የአምደ ሃይማኖት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ቃል አንደበታቸው በማድረግ እንዲህ ያመሰግኑታል።

🕯

[ ዮሐንስ እንደ መላእክት ንጹሕ ነው ፤ ድንግል ዮሐንስ የቅዱሳን መመኪያ ነው ፤ ዮሐንስ በብርሃን መጎናጸፊያ ሐር የተጌጠ ነው ፤ ዮሐንስ የቤተክርስቲያን አርጋኖን ነው በኤፌሶን የአዋጅ ነጋሪ ዮሐንስ ኃጥአን ለምንሆን ለእኛ ይቅርታን ይለምንልን።]

[ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ደሙ በፈሰሰ ጊዜ ዮሐንስ ፍቅሩን አላጎደለም። ]

[ በወዳጁህ በዮሐንስ ድንግልና በንጽሐ ሥጋውም አቤቱ ይቅር በለን።]

🕊

† በዚህች ዕለት ቅዱሱ ሐዋርያ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ: ከአባቱ ዘብዴዎስ መወለዱን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች::

የግፍና የመከራ ጽዋዕ በመላባት ዓለማችን… ትዕግሥቱ ፤ ጥላቻና መገፋፋት በነገሠባት ምድራችን… ፍቅሩ ፤ ኃጢአትና መተላለፍ በሠለጠነባት ሕይወታችን… በረከቱ ፤ እርሱ በተወለደባት በዚህች ዕለት በእኛም ልቡና ይወለድ ዘንድ ምልጃው አይለየን።

†                       †                        †
🌼                    🍒                     🌼
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
በታመምህ ጊዜ ድካም ይሰማሃል፤ ብርታት ያንስሃል፤ ፊትህም ይገረጣል፡፡ የዕለት ተዕለት ሥራዎችህን በአግባቡ ማከናወን ይሳንሃል፡፡ በዚህ ጊዜም ሕመምህ ምን ያህል እንደበረታ ሰዎች ያስተውላሉ፤ መታከም እንደሚገባህም ይነግሩሃል፡፡ ስለዚህ ወደ ሐኪም ትኼዳለህ፡፡ ወደ ሐኪም የምትኼደው ግን ሐኪሙ ምን እንዲያደርግልህ ነው? አሁን ለሚሰሙህ ስሜቶች የሚሽሩ መድኃኒቶችን እንዲሰጥህ ነው፡፡ ኾኖም ይሰሙህ የነበሩ ስሜቶች ቢሻሉህም ሰውነትህ አሁንም እንደ ደከመ፣ ፊትህ እንደ ገረጣ ከቀረ፣ የዕለት ተዕለት ሥራዎችህንም በአግባቡ ማከናወን ከተሳነህ፥ በተሰጠህ ሕክምና ደስተኛ ትኾናለህን? አትኾንም!

እውነታው ምንድን ነው?” ስንል ወደ ሐኪሙ የኼድከው የበሽታህን ምንጭ ለመታከም ሳይኾን የበሽታህን ምልክቶች ለማስታገሥ ስለ ኾነ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የበሽታህ መንሥኤ እስካልታከመ ድረስ የበሽታህ ምልክቶች ለጊዜው ቢታገሡም ቅሉ፥ ፈጽመው ሊወገዱ እንደማይችሉ ሐኪሙ በደንብ ያውቃል፡፡

በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ውሉድ፣ በመንፈስ ቅዱስም መንፈሳውያን የተባልን እኛም እግዚአብሔር መንፈሳዊ በሽታችንን እንዲያስወግድልን እንሻለን፡፡ እንደ እውነታው ግን ብዙዎቻችን ወደ እግዚአብሔር ቀርበን እንዲያስወግድልን የምንሻው ምልክቶቹን ነው፡፡ ለምሳሌ ችግርን፣ ኀዘንን፣ ቀቢጸ ተስፋንና የመሳሰሉትን እንዲያርቅልን እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የእነዚህ ምክንያት የኾነውንና ሥር የሰደደውን፣ ዋና ምክንያትም የኾነውን መንፈሳዊ በሽታችንን ሳይሽር እነዚህን ምልክቶች ሊያርቅልን አይፈልግም፡፡ ችግር የሚኾነውም ይህን ጊዜ ነው፡፡ ምልክቶቹን እንዲያርቅልን ስንደክም፥ ወደ ውሳጤያችን ገብቶ የችግሩን ምንጭ ሊያርቅልን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ (ኃይልን) አጥብቀን እንቃወማለንና፡፡ በውሳጤያችን የተሸሸገውን በሽታ ማስወገድ አንፈልግም፡፡ አመለካከታችን እንዲለወጥ አንፈቅድም፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣውና አማን በአማን የምንታከመው ግን የልባችንን ውሳጤ ለእግዚአብሔር ስንከፍትለትና እርሱም በዚያ በመረቀዘው ቁስላችን ላይ ጽኑ መድኃኒት ሲያስርልን ነው፡፡ እንዲለወጡ የምንፈልጋቸው ምልክቶች በእርግጥም የሚለወጡት ይህ በልባችን ውስጥ የተደበቀው መንፈሳዊ በሽታችን ሲጠፋ ነው፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †


[  †  መስከረም [ ፭ ] 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  †  ]

†  🕊   " ቅድስት ሐጊያ ሶፍያ "   🕊  †

ዘመነ ሰማዕታት በሚል በሚታወቀው ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ብዙ ቅዱሳት እናቶቻችን ስለ ፍቅረ ክርስቶስ አንገታቸውን ሰጥተዋል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ሕይወታቸው እጅግ የሚያምር ነበር:: ከእነዚህ ቅዱሳት እናቶቻችን አንዷ ዛሬ የምናከብራት ሐጊያ ሶፊያ ናት::

በዚህ ስም ከሚጠሩት አንዷ ስትሆን በቀደመ ሕይወቷ ክርስቶስን አታውቅም ነበር:: ጣዖትን የሚያመልኩ ወላጆቿ አሳድገው አጋቧት:: ከትዳሯም ፪ [2] ቡሩካት ሴቶች ልጆች ወልዳለች:: ስማቸውም አክሶስናና በርናባ ይባላል:: ልጆቿ ልብ እያገኙ በሔዱ ጊዜ ቅድስት ሶፍያ ስለ እውነተኛው አምላክ ትመራመር ገባች::

በወቅቱ የነበሩ ብዙ ሃይማኖቶችን መዘነች:: ከክርስትና በቀር ግን ሌሎቹ ሚዛን እንደማይመቱም አስተዋለች:: "እውነኘተኛው አምላክ ሆይ! ምራኝ: እርዳኝም" ስትል ጸለየች:: መድኃኔ ዓለም ለጠሩት አያሳፍርምና ፈጥኖ በጐውን ጐዳና አሳያት::

ድኅነት ለልጆቿም ይሆን ዘንድ ሁለቱንም ጠርታ ስለ ክርስትና አማከረቻቸው:: ደስ ብሏቸው ተቀበሏት:: እርሷም ጊዜ ሳታጠፋ ወደ ዻዻስ ሒዳ ማሕተመ ክርስትና: ሃብተ ውልድናን ትቀበል ዘንድ ከልጆቿ ጋር ተጠመቀች:: በቅድስናና ደስ በሚያሰኝ አኗኗርም እስከ መከራ ቀን ቆየች::

የመከራ ጊዜ ሲደርስም ልጆቿን ጠርታ "ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንሙት" አለቻቸው:: ቡሩካቱ አክሶስናና በርናባም ደስ እያላቸው "እሺ" አሏት:: ወዲያውም በመኮንኑ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ከመካድና ከስቃይ ሞት የትኛውን እንደሚመርጡ ቢጠየቁ እነርሱ መሞትን መረጡ:: ወደ እሥር ቤትም ከተቷቸው::

ቅድስት ሶፍያ [፪] 2 ልጆቿ ይጸኑላት ዘንድ አዘውትራ ገድለ ሰማዕታትን እና ክብራቸውን ትተርክላቸው ነበር:: በተለይ የታላቁዋን አንጌቤናይት [እመቤት] ሶፍያንና የ፫ [3] ልጆቿን [ዺስጢስ: አላዺስና አጋዺስ] ተጋድሎ እየነገረች ታጸናቸው ነበር::

ከእሥር በኋላ ግርፋት ታዞባቸው እናት ራቁቷን ስትገረፍ መልአክ ወርዶ ሲጋርዳት ልጆች በማየታቸው ደስ አላቸው:: ቅድስት ሐጊያ ሶፍያና ፪ [2] ልጆቿ እጅግ የበዛ ስቃይን ስለ ቀናች እምነት ተቀበሉ:: ምላስ እስከ መቆረጥም ደረሱ:: በመጨረሻ ግን በዚህች ቀን ተገድለው አክሊለ ሰማዕታትን ገንዘብ አደረጉ::

የመከራ ዘመን ካለፈ በኋላ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ የሁሉን ቅዱሳን ቤት ሠርቶ የእርሷን በመዘንጋቱ ለራሱ ባሰራው ቤተ መንግስት ላይ ተአምር ታይቷል:: ለ፫ ያህል ጊዜ ስሙን ሲያስቀርጽ መልአክ እየወረደ ይፍቀው: የሶፍያንም ስም ይጽፈው ነበር::

በመጨረሻም ንጉሡ ልጁን እስከ መገበር ደርሶ ቤተ መንግስቱ የቅድስት ሶፍያና የ፪ ልጆቿ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል:: ምንም ለ፫ ጊዜያት ያህል ሙሉ እድሳት ቢደረግለትም ዛሬ አሕዛብ የያዙትን ይህንን ቅርስ ንጉሡ የሠራው ከ፲፻፯፻ [1700] ዓመታት በፊት ነው::


†  🕊 ቅዱስ ማማስ ሰማዕት  🕊

የሰማዕቱ ወላጆች ቴዎዶስዮስና ታውፍና ሲባሉ ማማስ የሚለው የስሙ ትርጉም 'ዕጉዋለ ማውታ - እናት አባቱ የሞቱበት' ማለት ነው:: ለምን እንደዚህ ተባለ ቢሉ :- በዘመነ ሰማዕታት ስደት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይዘውት ተሰደው ነበር:: ማምለጥ ባይችሉ ይዘው አሠሯቸው::

በእሥር ቤትም ከስቃዩ ብዛት ፪ [2] ቱም ልጃቸውን ማማስን እንዳቀፉት ሕይወታቸው አለፈች:: ሕጻኑ ሲያለቅስ የተመለከተች አንዲት ሴትም ራርታ እነርሱን አስቀብራ: እርሱን አሳድጋዋለች:: ስሙንም 'ማማስ' ብላዋለች::

ቅዱሱ ባደገ ጊዜ የወላጆቹን ጐዳና በመከተሉ ተይዞ ለፍርድ ቀረበ:: ክርስቶስን አልክድም በማለቱም ብዙ ስቃይን አሳልፎ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል:: ቅዱስ ማማስ ከዐበይት ሰማዕታት አንዱ ሲሆን በአንበሳ ጀርባ ላይም ይቀመጥ ነበር::


🕊  አቡነ አሮን መንክራዊ  🕊

ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ አሮን በ፲፬ [14] ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ኢትዮዽያዊ ሲሆኑ በገዳማዊ ሕይወታቸው: በሐዋርያዊ አገልግሎታቸውና ነገሥታቱን ሳይፈሩ በመገሰጻቸው ይታወቃሉ:: በተለይም ሕይወታቸው በተአምር የተሞላ ስለነበር 'አሮን መንክራዊ' [ድንቅ አባት] ተብለው ይጠራሉ::

አንዳንድ ጊዜም 'አሮን ዘመቄት /ዘደብረ ዳሬት/' በሚልም ይጠራሉ:: የአቡነ አሮን ወላጆች ገብረ መስቀልና ዓመተ ማርያም የሚባሉ ሲሆን ከልጅነታቸው ጀምረው በቅዱስ ቃሉ የታነጹ ነበሩ:: ምናኔን በደብረ ጐል: ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጀምረው ብዙ ገዳማትን መሥርተዋል:: በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፍርተዋል::

ለወንጌል አገልግሎት በወጡበት ጸሐይን አቁመው: ሕዝቡን ድንቅ አሰኝተዋል:: እንኳን ሰዉ ይቅርና አጋንንትም ያደንቁዋቸው ነበር:: ነገሥታቱንም ስለ ኃጢአታቸው በገሰጹ ጊዜ ራቁትነት: እሥራት: ግርፋትና ስደት ደርሶባቸዋል::

ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ወሎ መቄት ውስጥ በሚገኘው ገዳማቸው ዐርፈው ተቀብረዋል:: ገዳሙ እስካሁን ያለ ሲሆን ድንቅ ጥበበ እግዚአብሔር የሚታይበት ነው:: ጣራው ክፍት ሲሆን ዝናብ አያስገባም::

†  🕊  አፄ ልብነ ድንግል  🕊  † 

እኒህ ንጉሥ ኢትዮዽያን ለዓመታት (ከ፲፻፭፻ [1500] እስከ ፲፻፭፻፴፪ [1532] ዓ/ም) ቢያስተዳድሩም ፲፭ ቱ ዓመት ያለቀው በስደት ነው:: ከደጋጉ አፄ ናዖድና ንግሥት ወለተ ማርያም ተወልደው: በሥርዓቱ አድገው ቢነግሡም: በክፉ መካሪዎች ጠንቅዋይ ወደ ቤታቸው ገብቶ ሃገሪቱን ለመከራ ዳርጉዋታል::

ዛሬም ድረስ ጠባሳው ያለቀቀው የግራኝ ወረራ ለ፲፭ ዓመታት ሃገሪቱን ያለ ካህንና ቤተ ክርስቲያን አስቀርቷት ነበር:: ብዙ ክርስቲያኖችም ሰልመው ቀርተዋል:: አፄ ልብነ ድንግል ግን ደብረ ዳሞ ገዳም ውስጥ ገብተው ንስሃ ጀመሩ: አለቀሱ: ተማለሉ::

እመቤታችን ተገልጣም "ይቅርታን በነፍስህ እንጂ በሥጋህ አታገኝም" አለቻቸው:: እርሳቸውም ሱባኤውን ቀጥለው: 'ስብሐተ ፍቁርን': 'መልክአ ኤዶምን' የመሰሉ መጻሕፍትን ደርሰው በዚህች ቀን በ ዓ/ም ዐርፈዋል:: እኛ ክርስቲያኖችም እናከብራቸዋለን::

የቅዱሳኑ አምላክ የወዳጆቹን ፈተና አስቦ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቡንም ከስደት ይሰውርልን:: ከበረከታቸውም አይለየን::

🕊

[  † መስከረም ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፪. ቅዱሳት አክሶስናና በርናባ
፫. ቅዱስ ማማስ ሰማዕት
፬. ቅዱሳን ቴዎዶስዮስና ታውፍና
፭. አቡነ አሮን መንክራዊ
፮. አፄ ልብነ ድንግል

[  †  ወርኀዊ የቅዱሳን  በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
፬. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
፭. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፮. ቅድስት አውጋንያ [ሰማዕትና ጻድቅ]

" ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን: ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን:: ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን::" [ሮሜ.፮፥፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

        †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                  🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን  †


[  † መስከረም [ ፮ ] 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  †   ]

†   🕊  ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ  🕊  †

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢሳይያስን ያህል ትንቢት የተናገረ ነቢይ አይገኝም:: ከትንቢቱ ብዛትና ከምስጢሩ ጉልህነት የተነሳ: አንድም ደፋር ስለ ነበር 'ልዑለ ቃል' ተብሎ ተጠርቷል:: ቅዱስ ኢሳይያስ የተወለደው ከክርስቶስ ልደት ፰፻ [800] ዓመታት በፊት ሲሆን ለነቢይነት የተመረጠው ገና በወጣትነቱ ነበር::

ወላጆቹ  'ኢሳይያስ' [መድኃኒት] ያሉት በትምሕርቱ: በትንቢቱ የጸጋ መድኃኒትነት ስላለው ነው:: እርሱ በነቢይነት በተሾመበት ወራት ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ: ንጉሡ ደግሞ ዖዝያን ይባሉ ነበር:: በሊቀ ካህናቱና በንጉሡ መካከል በተነሳ ጠብ ንጉሡ የበላይነቱን ለማሳየት ሃብተ ክህነት ሳይኖረው ሊያጥን ወደ ቤተ መቅደስ ገባ::

ይህንን የተመለከተው ኢሳይያስ ሊገስጸው ሲገባ 'ወዳጄ ነው' በሚል ዝም አለው:: ፈታሒ እግዚአብሔር ግን ዖዝያንን በለምጽ መታው:: የግንባሩን ለምጽ በሻሽ ቢሸፍነው ከሻሹ ላይ ወጣበት:: በእሥራኤል ለምጽ ያለበት እንኩዋን በዙፋን ከተማ ውስጥም መቀመጥ አይችልምና አስወጡት:: በእርሱ ፈንታም ኢዮአታም ነግሷል::

ኢሳይያስ ደግሞ እግዚአብሔር በሰጠው አንደበት ሙያ አልሠራበትምና ከንፈሩ ላይ ለምጽ ወጣበት:: እርሱንም ወስደው ጨለማ ቤት ዘጉበት:: ሃብተ ትንቢቱንም ተቀማ:: ቅዱሳን ትልቁ ሃብታቸው ንስሃቸው ነውና በዚያው ሆኖ ንስሃ ገባ: ተማለለ: ጾመ: ጸለየ::

እግዚአብሔርም ንስሃውን ተመለከተለት:: ከዚያም ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ኢሳይያስ እግዚአብሔርን በረዥም [ልዑል] ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ: ኪሩቤል ተሸክመውት: ሱራፌል [፳፬ [24] ቱ ካህናተ ሰማይ] "ቅዱስ: ቅዱስ: ቅዱስ" እያሉ ሲያመሰግኑት ተመለከተ:: [ኢሳ.፮፥፩] (6:1)

አበው ሲተረጉሙ "አንተ ያፈርከው ዖዝያን እነሆ ሞተ:: እኔ ግን መንግስቴ የዘለዓለም ነው" ሲለው ነው ይላሉ:: ያን ጊዜ እግዚአብሔር "ወደ ሕዝቤ ማንን እልካለሁ?" አለ:: ኢሳይያስም "ጌታየ! እኔ ከንፈሮቼ የረከሱ አለሁ" አለው:: እግዚአብሔርም ሱራፊን ላከለት:: መልአኩም ፍሕም [እሳት] በጉጠት አምጥቶ ከንፈሩን ቢዳስሰው ነጻ:: ሃብተ ትንቢቱም ተመለሰለት:: ይኸውም የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ነው::

ከዚህች ቀን በኋላ ግን ኢሳይያስ የተለየ ሰው ሆነ:: ማንንም የማይፈራ እውነተኛ የልዑል ወታደር ሆነ:: ከኦዝያን በሁዋላ በየዘመናቸው 4ቱንም ነገሥታት ገሰጸ:: እነዚህም ኢዮአታም: አካዝ: ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው::

ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ፲፬ [14] ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከ ፻፹፭ ሺህ [185,000] በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ: ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት ፻፹፭ ሺህ [185] ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: [፩ነገ.፲፰፥፲፫] (18:13) , [፲፱፥፩]

ታላቁ ነቢይ ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ሐረገ ትንቢትን ያፈስ ነበርና ከተናገራቸው ትንቢቶችም አንዱ "ድንግል ትጸንሳለች: ወንድ ልጅም ትወልዳለች" የሚል ነበር:: [ኢሳ.፯፥፲፬]

በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ክፉ መካሪዎች ቀርበው ንጉሡን በውዳሴ ከንቱ ጠለፉት:: "ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥ:: እንዳንተ ያለ ማንም የለም:: ነቢዩ የተናገረው ትንቢትም እኮ ላንተ ነው:: 'ድንግል' የተባለች ኢየሩሳሌም ስትሆን 'ወልድ-ወንድ ልጅ' የተባልክ ደግሞ አንተ ነህ" አሉት::

ይሕንን ጠማማ ትርጉም እህ ብሎ የሰማቸው ቅዱስ ሕዝቅያስ አልወቀሳቸውም:: በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ኢሳይያስን ላከው:: ነቢዩም መጥቶ ንጉሡን አለው :- "ትሞታለህ እንጂ አትተርፍምና ቤትህን ሥራ::"

ወዲያውኑ ሕዝቅያስ ታመመ: ደከመ:: ንጉሡ ወደ ፈጣሪ :- "ጌታ ሆይ! እንደ ቸርነትሕ በፊትህ በቅን መንገድ መሔዴን አስብና ይቅር በለኝ" ሲል ተማጸነ:: ይህ ሲሆን ቅዱስ ኢሳይያስ ገና ከንጉሡ አካባቢ አልራቀም ነበርና የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ::

ሕዝቅያስን በለው :- "ጸሎትህን ሰምቼ: ስለ ባለሟሌ ስለ ዳዊት ብየ ምሬሐለሁ:: በዘመንህም ላይ ፲፭ [15] ዓመታትን ጨምሬልሃለሁ በለው" አለው:: ነቢዩም ወደ ንጉሡ ተመልሶ ይሕንኑ ነግሮ "እስከ ፫ ቀን ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ድነህ ትመለሳለህ" አለው::

ቅዱስ ሕዝቅያስ "ይሕ እንደሚደረግ በምን አውቃለሁ?" አለው:: ኢሳይያስም ፀሐይን ዓለም እያየ ፲ [10] መዓርጋትን ወደ ሁዋላ መለሳት::

ልዑለ ቃል ቅዱስ ኢሳይያስ ለ ፸ [70] ዘመናት ሕዝቡን አስተምሮ: ነገሥታቱን ገስጾ: ፷፰ [68] ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ጽፎ አረጀ:: በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ምናሴ ግን ይባስ ብሎ ጣዖትን አቆመ: ለጣዖትም ሰገደ:: ቅዱሱ ይህንን ሲያደርግ ዝም አላለውም:: በአደባባይ ገሰጸው እንጂ::

በዚህ የተበሳጨ ምናሴም ሽማግሌውን ነቢይ በእንጨት መጋዝ ለሁለት አሰነጠቀው:: ቅዱስ ኢሳይያስ በዚህ ዓይነት ሞት በጐ ሕይወቱንና ሩጫውን ፈጸመ:: የተናገራቸው ትንቢቶች ግልጽ ስለ ሆኑ 'ደረቅ ሐዲስ' በመባል ይታወቃሉ::

ቸሩ አምላክ 'ደሃ ተበደለ: ፍርድ ተጉዋደለ' የሚሉ መምሕራን አባቶችን አይንሳን:: ከነቢዩም በረከቱን ይክፈለን::

[  † መስከረም ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ኢሳይያስ ነቢይ [ልዑለ ቃል]
፪. ቅድስት ሰብልትንያ ሰማዕት
፫. አባ ያዕቆብ ገዳማዊ
፬. ቅዱስ አናቲሞስ ኤዺስ ቆዾስ

[  †  ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል


" ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር:: ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች:: እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች:: እሺ ብትሉ: ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ:: እንቢ ብትሉ ግን: ብታምጹም ሰይፍ ይበላቹሃል:: የእግዚአብሔር አፍ ይህንን ተናግሯልና:: " [ኢሳ.፲፥፲፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/16 07:28:55
Back to Top
HTML Embed Code: