Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
                          †                          

🕊

እንኳን ለቅዱስ ሩፋኤል አመታዊ በአል በሰላም አደረሳችሁ !

🌼   🕊 ጳጉሜ ፫ ቅዱስ ሩፋኤል  🕊  🌼

                              
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬


" ከከበሩት ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ" እንዳለ:: [ጦቢት ፲፪፥፲፫]
                           
💖

ከባህሪው ቅድስና ፍጥረቱን በጸጋ ቅድስና መርጦ የሚለይ እግዚአብሔር አክብሮ እንዲህ ያለ ሰማያዊ ፀጋ ከሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት መካከል በስልጣኑ ሊቀ መናብርት [ የመናብርት አለቃ ] የሆነ ፣ በሹመት ፈታሔ ማኅጸን [ ማሕጸን የሚፈታ ] ፣ ከሳቴ እውራን [ የእውራንን ዓይን የሚያበራ ] ፣ ሰዳዴ አጋንንት [ አጋንንትን የሚያባርር ] ፣ ፈዋሴ ድውያን (ድውያንን የሚፈውስ) ፣ አቃቤ ኆኅት [ የምህረትን ደጁ የሚጠብቅ ] ተብሎ የተገለጠ ከሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ተከትሎ የሚነሳ መልአክ ራሱን እንዲህ በማለት ገለጠ "የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነት ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ" [ጦቢ.፲፪፥፲፭]

ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ስሙ ሩፋኤል የሚለው ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ የሚለውን ይተካል " በሰው ቁስል የተሾመ ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው።" [ሄኖ.፮÷፫]
ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል [ዳን.፬÷፲፫ ዘጸ.፳፫÷፳ መዝ. ፺÷፲፩] ያማልዳል ፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡ [ዘካ.፩÷፲፪] በፈሪሐ እግዚአቤሔር እና በአክብሮተ መላእክት ያሉትን ምዕመናን ያድናቸዋል [ዘፍ.፵፱÷፲፭ መዝ.፫÷፴፯]

"እግዚአብሔር ሃይሉን የሚገልጥበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ መርጦ በወደዳቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የይቅርታ መላእክትን ያመጣል" [ሮሜ.፱÷፳፪]

የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ አዋላጅ ብትኖርም ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም፡፡ በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው "ማርያም ማርያም" ይላሉ ማየ ጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ "ሩፋኤል" እያሉ ደጅ ጠንተው ይማጸኑታል፡፡

ዜና ግብሩን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረለት በመነሳት በቅዱሳን ላይ ድንቅ የሆነ እግዚአብሔር በመልአኩ አድሮ ያደረጋቸውን ተግባራት አበው የበረከት ምንጭ በሆነ ድርሳኑ ላይ አኑረው የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን ሰጥተውናል፡፡ በጉልህ ሠፍረው ከምናገኛቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች መሀል ጥቂቶቹን እነሆ፦

በሥነ-ስዕሉ የተማጸኑ ፣ በምልጃው ታምነው የጸኑ ቴዎዶስዮስንና ዲዮናስዮስን በገሃድ ተገልጾ ለንግስናና ለጵጵስና ክብር አብቅቷቸዋል፡፡

የንጉስ ቴዎዶስዮስ ልጅም ጻድቁ አኖሬዋስም በፈጣሪው ህግ እየተመራ የሊቀ መናብርቱን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ አሳንጾ ሲያስመርቅ ለበለጠ ክብር ልቡን አነቃቅቶ ለታናሽ ወንድሙ ለአርቃዴዋስ የነጋሢነት ስልጣኑን ትቶ መንኖ በስውርና በጽሙና እዲኖር ረድቶታል፡፡

በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀ መናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ሳለች ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፉ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ወደ ሊቀ መናብርቱ ተማጽነው እርዳን ቢሉ ፈጥኖ ደርሶ በበትረ መስቀሉ [ዘንጉ] ገሥጾ ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡

በቅዱስ መጽሐፍም እንደተገለጠው ሣራ ወለተ ራጉኤልን አስማንድዮስ ከተባለው የጭን ጋንኤን ሲታደጋት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን አበራለት [መጽሐፍ ጦቢት]፡፡ ከዚህም አልፎ የይስሐቅን እናት ሣራን ፣ የሶምሶንን እናት [እንትኩይን] ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔ ማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡

" ሩፋኤል ሆይ ከላይ ከሰማይ ወርደህ የጻድቃንና የሰማዕታትን ጸሎት የምታሣርግላቸው አንተ ነህ ፡ ሩፉኤል ሆይ የድኩማን ኃይላቸው አንተ ነህና፡፡ ምስጋናዬን ጸሎቴን ወደላይ ታሣርግልኝ ዘንድ በእግዚአብሔር ወልድና በእናቱ በድንግል ማርያም ስም እማልድሃለሁ፡፡"

[  መልክአ ሩፋኤል  ]
                         
🕊
                            
የመልአኩ ጥበቃና የክንፎቹ መጋረድ ከተዋህዶ ምእመናን ጋር ይኑር አሜን።


†                       †                        †
🌼                    🍒                     🌼
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለርኅወተ ሰማይ: ለቅዱስ ሩፋኤል: መልከ ጼዴቅ: ዘርዓ ያዕቆብና ሰራጵዮን ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†  🕊    ርኅወተ ሰማይ    🕊   †

† ይህች ዕለት የሰዎች ሁሉ ጸሎት የሚያርግባት: አራተኛው መጋቢ ኮከብ የሚያልፍባት: ለሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጸጋ በረከት የሚሰጥባት ዕለት ስለሆነች "ርኅወተ ሰማይ-ሰማይ የሚከፈትባት ቀን::" ትባላለች::

አሁን በሰማይ መዘጋት መከፈት ኑሮበት አይደለም:: የሰው ልጆችን ልመና ቅዱሳን መላእክት ያለ ከልካይ የሚያሳርጉበት: አንድም ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገብ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ እንዲህ ተባለ እንጂ::

እመቤታችን ድንግል ማርያም ለአጼ ናዖድ እንደ ነገረቻቸው በዚህች ዕለት ሁሉም ቅዱሳን ስለሚታሰቡ: የእግዚአብሔር የምሕረት መዝገቡ ስለሚከፈት: ዕለቷን ክብርት ያሰኛታል:: በቅዱስ ሩፋኤል አበጋዝነት [መሪነት] በዚህች ዕለት ለዓመት የሚበቃ ምሕረት ይገኛል::

ስለዚህም አባቶቻችን በዚህች ሌሊት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት አቡነ ዘበሰማያትን ሲጸልዩ ያድራሉ:: በሌላ ወገን ደግሞ የጌታ ዳግም ምጽዓቱ መታሰቢያ እንደ መሆኗ ትልቅ ትኩረትም ይሰጣታል::
ቸሩ ጌታችን ከተከፈተች ገነት ከተነጠፈች ዕረፍት ሁላችንንም ያድርሰን::


†  🕊  ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት  🕊  † 

† ቅዱስ ሩፋኤል በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት በደረጃው ሦስተኛ ነው:: በመጀመሪያዋ ዕለተ ፍጥረት እግዚአብሔር መቶ ነገደ መላእክትን ፈጥሮ በአሥር ከተማ ሲያኖራቸው የቅዱስ ሩፋኤል ዕድል ፈንታው ራማ ሆነች::

በዚያም "መናብርት" ተብለው ለሚጠሩ አሥሩ ነገድ አለቃ [መሪ] ሆኖ በፈጣሪው ተሹሟል:: በኋላም "መጋብያን" በሚባሉ በሃያ ሦስቱ ነገድ ላይ ሹሞታል:: ይህች ዕለትም በዓለ ሲመቱ ናት::

አንድ ቀን ጌታችን ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ሐዋርያቱ ቅዱስ ሩፋኤልን እንዲያስተዋውቃቸው ለመኑት:: ጌታም ሦስቱን ሊቃናት [ሚካኤል: ገብርኤል እና ሩፋኤል] ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው::

ቀጥሎም ቅዱስ ሩፋኤልን "ክብርህን ንገራቸው::" አለው:: እርሱም ለጌታ ሰግዶ ለሐዋርያት ብዙ ምሥጢር ነገራቸው:: በተለይ ስሙን ለሚጠሩ: መታሰቢያውን ለሚያከብሩ የሚደረገውን ጸጋ አብራርቶላቸው ዐረገ::

በመጽሐፈ ጦቢት ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ቅዱሱ መልአክ ሰው [አዛርያን] መስሎ: ጦብያን ለትዳር አብቅቶ: ሣራን አስማንድዮስ ከሚባል ሰይጣን አድኖ: የጦቢትን ዓይን አብርቷል:: በገድላተ ቅዱሳን እንደምናየውም ለብዙ ቅዱሳን ረዳታቸው ሆኖ ገድላቸውን አስፈጽሟል::

ታሪክ እንደሚለው ይህች ቀን ለቅዱስ ሩፋኤል ቅዳሴ ቤቱም ናት:: በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በቅዱስ ቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ አማካኝነት ቤቱ ታንጿል:: የሚገርመው ደግሞ የታነጸው በዓሣ አንበሪ ጀርባ: ደሴት ላይ ነው:: በመልአኩ አጋዥነትም ለሦስት መቶ ዓመታት አገልግሏል::


† ቅዱስ ሩፋኤል

¤ መስተፍስሒ [ ልቡናን ደስ የሚያሰኝ ]
¤ አቃቤ ሥራይ [ ባለ መድኃኒት ፈዋሽ ]
¤ መዝገበ ጸሎት [ የጸሎት መዝገብ መክፈቻ የተሰጠው ]
¤ ሊቀ መናብርት [ በዙፋን ላይ በክብር የሚቀመጡ መላእክት መሪ ]
¤ ፈታሔ ማኅጸን [ የሰውንም ሆነ የእንስሳትን ማኅጸን የሚፈታ ]
¤ መወልድ [ አዋላጅ: ምጥን የሚያቀል ] ይባላል::
"ለሰብእ ወለእንስሳ ፈታሔ ማኅጸኖሙ አንተ" እንዲል::


†   🕊   ቅዱስ መልከ ጼዴቅ  🕊   †

† ካህኑ መልከ ጼዴቅን ቅዱስ ጳውሎስ "የትውልድ ቁጥር የለውም: ለዘመኑም ጥንትና ፍጻሜ የለውም::" ይለዋል:: [ዕብ.፯፥፫] ሐዋርያው ይህንን ያለው ለወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሲያደርገው እንጂ ትውልዱ ከነገደ ካም ነው:: ወላጆቹም "ሚልኪ እና ሰሊማ" ይባላሉ::

ገና ከእናቱ ማኅጸን የተመረጠው ቅዱሱ "ካህነ ዓለም: ንጉሠ ሳሌም" ይባላል:: የዛሬ አምስት ሺ አምስት መቶ ዓመት አካባቢ ሴም ባኖረበት ቦታ [በደብረ ቀራንዮ] ለዘላለም ይኖራል:: ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከሰው ወገን እጅግ ክቡርም ነው::


†  🕊   አፄ ዘርዓ ያዕቆብ   🕊  † 

† ሃይማኖቱ የቀና ኢትዮጵያዊው ንጉሥ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በኢትዮጵያ በነገሠባቸው ሠላሳ አራት ዓመታት [ከ1426 እስከ 1460 ዓ/ም] ብዙ በጐ ነገሮችን ሠርቷል:: ላለፉት ሰባ ዓመታት ግን አንዳንድ ጥቃቅን ሰብአዊ ስህተቶችን እየነቀሱ ተሐድሶዎቹ ስሙን ሲያጠፉት ኑረዋል::

ዛሬ ዛሬ ደግሞ የእኛ ቤት ሰዎችም ተቀላቅለዋቸዋል::
እነርሱ ያሉትን ይበሉ እንጂ ለእኛ ግን ዘርዓ ያዕቆብ ማለት :-

፩. ጣዖት አምልኮን ከሃገራችን ለማጥፋት ብዙ ሺህ ካህናትን አሰልጥኖ አሰማርቷል::
፪. የኑፋቄ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉባኤያትን አዘጋጅቷል::
፫. ከአሥራ አንድ ያላነሱ መጻሕፍትን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ደርሶ ለአገልግሎት አብቅቷል::
፬. ብዙ መጻሕፍትን ከውጪ አስመጥቶ አስተርጉሟል [በተለይ ተአምረ ማርያምን]
፭. ሰው ሁሉ ለእመ ብርሃንና ለመስቀሉ ፍቅር እንዲገዛ ጥረት አድርጓል
፮. እመቤታችንን በፍጹም ልቡ ከመውደዱ የተነሳ ዛሬ ድረስ በሃገራችን ድንግል ማርያም "የዘርዓ ያዕቆብ እመቤት" እየተባለች ትጠራለች::
፯. ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አንጾ: ብዙ ሥርዓቶችም በሊቃውንት እንዲሠሩ አድርጐ: ሌሎች ብዙ በጐ ተግባራትንም ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::
ቤተ ክርስቲያን ስለውለታቸው ዘርዓ ያዕቆብን: እናታቸው ጽዮን ሞገሳን እና አባታቸው ዳዊትን በክብር ታስባለች::


†  🕊  ቅዱስ ሰራጵዮን ዘሰንዱን  🕊  †

† ይህ ቅዱስ እጅግ የበዛ ሃብቱን ለነዳያን አካፍሎ: ወደ ሌላ ሃገር ሔዶ ለባርነት ተሽጧል:: በተሸጠበት ሃገርም በጸሎት ተግቶ ከክህደት ወደ ሃይማኖት መልሷቸዋል:: ክብሩን ሲያውቁበትም በተመሳሳይ ወደ ሌላ ሃገር ሒዶ አሕዛብን አድኗል:: በፍጻሜው ወደ በርሃ ገብቶ በተጋድሎ ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::

† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ሁሉ በረከትና ጸጋ ያብዛልን:: ለዓለምም ሰላሙን ይዘዝልን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፫ [ 3 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩ . ርኅወተ ሰማይ [የሰማይ መከፈት]
፪ . ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫ . ቅዱስ መልከ ጼዴቅ ካህን
፬ . አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ንጉሥ [የእመቤታችን ወዳጅ]
፭ . ቅዱስ ሰራጵዮን ዘሰንዱን
፮ . ቅዱስ አኖሬዎስ
፯ . ቅዱስ ቴዎፍሎስ
፰ . አባ ዮሐንስ
፱ . ቅዱስ ጦቢት
፲ . ቅዱሳን ጦብያና ሣራ

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

-  የለም

† " እውነት እውነት እላችኋለሁ:: ሰማይ ሲከፈት: የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ::" † [ዮሐ. ፩፥፶፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለቅዱስ አባ ባይሞን እና ለቅዱስ ሊባርዮስ ሊቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


 †  🕊  አባ ባይሞን [ ጴሜን ]  🕊

† ይህ ቅዱስ አባት የ፬ [4]ኛው መቶ ክ/ዘ የቤተ ክርስቲያን ፍሬ ሲሆን ተሰምተው በማይጠገቡ መንፈሳዊ ቃላቱ [ምክሮቹ]ና በቅድስና ሕይወቱ ይታወቃል::

ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

በተጠቀሰው ዘመን በምድረ ግብጽ የምትኖር አንዲት ደግ ሴት ነበረች:: አምላክ በፈቀደው ጋብቻ ውስጥ ገብታ ሰባት ወንዶች ልጆችን አፈራች:: ሰባቱም ወንድማማቾች ገና ሕፃን እያሉ አባት በመሞቱ እናት ፈተና ውስጥ ገባች::

ነገር ግን ብርቱ ሴት ነበረችና በወዟ ደክማ አሳደገቻቸው:: ሥጋዊ ማሳደጉስ ብዙም አይደንቅም:: ምክንያቱም ሁሉም እናቶች ይህንን ያደርጉታል ተብሎ ይታመናልና:: የዚህች እናት የሚገርመው ግን ሁሉንም ንጹሐን: የተባረኩ: የክርስቶስ ወዳጆች: የቤተ ክርስቲያንም አለኝታዎች እንዲሆኑ አድርጋ ማሳደጓ ነው::

እነዚህ ሰባቱ ወንድማማቾች :-

፩. አብርሃም
፪. ያዕቆብ
፫. ዮሴፍ
፬. ኢዮብ
፭. ዮሐንስ
፮. ላስልዮስ እና
፯. ባይሞን [ጴሜን] ይባላሉ:: ለእነዚህም ዮሐንስ በኩር ሲሆን ባይሞን መቁረጫ ነው::

ሰባቱም ወጣት በሆኑ ጊዜ ወገባቸውን ታጥቀው እናታቸውን ያገለግሉ: ለፈጣሪያቸው ይገዙ ያዙ:: ያየ ሁሉ "ከዓይን ያውጣችሁ::" የሚላቸው: ቡሩካንም ሆኑ:: አንድ ቀን ግን መንፈስ ቅዱስ በሰባቱ ልብ ውስጥ አንድ ቅን ሃሳብን አመጣ:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ምናኔ አወሱ::

ይህንን ዓለም ከነ ኮተቱ ይተውት ዘንድ መርጠዋልና ወደ በርሃ ለመሔድ ተስማሙ:: እናታቸው ምን መንፈሳዊ ብትሆን የትኛዋም እናት ሁሉን ልጆቿን በአንዴ ማጣትን አትፈልግምና አላማከሯትም:: ይልቁኑ እነርሱ ከሔዱ በኋላ እንዳትቸገር የምትታገዝበትን መንገድ አዘጋጅተውላት ተሰወሩ::

ሰባት ልጆቿን በአንዴ ያጣችው እናት ብቻ አይደለችም: ሁሉም አዘነ:: ተፈለጉ: ግን አየኋቸው የሚል ሰው አልተገኘም:: ሰባቱም ቅዱሳን ከቤታቸው እንደ ወጡ ወደ ገዳም ሔደው አንዲት በዓት ተቀበሉ:: ሰባቱም የሚጸልዩ በጋራ: የሚሠሩ: የሚመገቡ: የሚውሉ: የሚተኙም በጋራ ነው::

በአገልግሎታቸውም ሆነ በፍቅራቸው አበውን ደስ አሰኙ:: "እምኩሉ የዓቢ ተፋቅሮ - እርስ በእርስ መዋደድ ከሁሉ ይበልጣል::" እንዲሉ አበው:: ከዘመናት ተጋድሎ በኋላ ግን ዝናቸው ከገዳሙ አልፎ በከተሞች ተሰማ:: ይህንን የሰማችው እናታቸው የእርሷ ልጆች መሆናቸውን በማወቋ ፈጥና ወደ ገዳሙ ገሰገሰች::

"ልያችሁ ልጆቼ?" ስትልም ላከችባቸው:: እነሱ ግን "እናታችን በመንግስተ ሰማያት እንድታይን በዚህ ይቅርብሽ::" አሏት:: ምክንያቱም ሰባቱም የሴትን ፊት ላያዩ ቃል ገብተው ነበርና:: ይህ ለአንድ እናት ከባድ ቢሆንም እርሷ ግን ተረዳቻቸው:: ፈጥናም ወደ ቤቷ ተመለሰች::

ከኮከብ ኮከብ ይበልጣልና [፩ቆሮ.፲፭፥፵፩] (15:41) ከሰባቱ ቅዱሳን ደግሞ ትንሹ አባ ባይሞን የተለየ አባት ሆነ:: ከንጽሕናው: ቅድስናና ትጋቱ ባሻገር ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላት ሕይወትነት ያላቸው ሆኑ:: በዘመኑም ከሕፃን እስከ አዋቂ ድረስ ብዙዎች ከመንፈሳዊ ቃላቱ ተጠቅመዋል::

እነዚህ ምክሮቹ ዛሬ ድረስ ለምዕመናንም ሆነ ለመነኮሳት ጣፋጮች ናቸው::
እልፍ አእላፍ ከሆኑ ምክሮቹ እስኪ አንድ አምስቱን እንጥቀስ :-

፩. "ባልንጀራህ በወደቀ ጊዜ በፍጹም ተስፋ አትቁረጥበት:: ይልቅስ አንቃው: አበረታታው: ሸክሙንም አቅልለት እንጂ::"

፪. "ለጥሩ ባልንጀራህ የምታደርገውን ደግነት ለክፉው በእጥፍ አድርግለት:: መድኃኒትን የሚሻ የታመመ ነውና:: አልያ ግን ለበጐው ያደረከው ከንቱ ነው::"

፫. "ባልንጀራህ በበደለ ጊዜ አትናቀው:: ያንተ ተራ በደረሰ ጊዜ ጌታህ ይንቅሃልና::"

፬. "የማንንም ኃጢአት አትግለጥ [አታውራ]:: ካላረፍክ ጌታ ያንተኑ ይገልጥብሃልና::"

፭. "አንደበትህ የተናገረውን ሁሉ ለመሥራት ታገል:: አልያ ውሸታም ትሆናለህ::"

ሰባቱ ቅዱሳን ወንድማማቾች ለብዙ ዓመታት በፍቅርና በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::


†  🕊   ቅዱስ ሊባርዮስ ሊቅ   🕊  †

† ሊቁ ተወልዶ ያደገው በአውሮጳ ሮም ውስጥ ሲሆን የታላቁ ሊቅ ቅዱስ አትናቴዎስ ባልንጀራም ነበር:: በቀደመ ሕይወቱ ምሑርና ገዳማዊ በመሆኑ ሊቃውንት የሮም ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: ዘመኑ አርዮሳውያን የሰለጠኑበት በመሆኑ ምዕመናንን ከተኩላ ለመጠበቅ እንቅልፍን አልተኛም::

የወቅቱ ንጉሥ ታናሹ ቆስጠንጢኖስ እምነቱ አርዮሳዊ በመሆኑ ቅዱሱን ያሰቃየው: ያሳድደውም ነበር:: ለበርካታ ዓመታትም ከመናፍቃንና ከአጋዥ ነገሥታት ጋር ስለ ሃይማኖቱ ተዋግቶ በዚህች ዕለት ዐርፏል::

† የአባቶቻችን አምላክ መፋቀራቸውንና ማስተዋላቸውን ያድለን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፬ [ 4 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አባ ባይሞን [ ጴሜን ]
፪. ስድስቱ ወንድሞቹ [ አብርሃም: ያዕቆብ: ዮሴፍ: ኢዮብ: ላስልዮስና ዮሐንስ ]
፫. ቅዱስ ሊባርዮስ ሊቅ

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

- የለም

† " ለእውነት እየታዘዛችሁ: ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በእርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ:: ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም:: በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል: ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ::" † [፩ጴጥ. ፩፥፳፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለታላቁ አባ በርሶማ እና ለቅዱስ አሞጽ ነቢይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


†   🕊   ታላቁ አባ በርሶማ   🕊   †

† ታላቁ ገዳማዊ ሰው ቅዱስ በርሶማ ከኋለኛው ዘመን ጻድቃን አንዱ ሲሆን ተወልዶ ያደገውም በግብጽ ምስር(ካይሮ) ውስጥ ነው:: ዘመኑ በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: የታላቁ በርሶማ ወላጆች ክርስቲያኖች ነበሩና ያሳደጉት በሃይማኖትና በምግባር እየኮተኮቱ ነው::

ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንዲማር አድርገውት ወጣት በሆነ ጊዜ አንድ ሰሞን ተከታትለው ዐረፉ:: በወቅቱም ስለ ሃብት ክፍፍል ዘመዶቹ ተናገሩት:: ነገር ግን አንድ ጉልበተኛ አጐት ነበረውና ንብረቱን ሁሉ ቀማው:: ቅዱስ በርሶማ በልቡ አሰበ:- "እንዴት ነገ ለሚጠፋ ገንዘብ ፍርድ ቤት እሔዳለሁ?" አለ::

ቀጥሎም ይህችን ዓለም ይተዋት ዘንድ ወሰነ:: ከቤቱም እየዘመረ ወደ በረሃ ገሰገሰ:: "ምንት ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኩሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ኃጉለ - ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ካጐደለ ምን ይረባዋል::" [ማቴ.፲፮፥፳፮] (16:26) እያለም ጉዞውን ቀጠለ:: ልብሱን በመንገድ ለኔ ቢጤዎች ሰጥቶ ራቁቱን በአምስት ኮረብታዎች ውስጥ ተቀመጠ::

በዚያም የቀኑ ሐሩር: የሌሊቱ ቁር [ብርድ] ሲፈራረቅበት ለብዙ ዓመታት ኖረ:: እርሱ ግን ያ ሁሉ መከራ እያለፈበት ደስተኛ ነበር:: ዘወትር የዳዊትን መዝሙር ያለ ማቋረጥ ይዘምራል:: ገድላተ ቅዱሳንን እያነበበ መንፈሳዊ ቅናትን ይቀናል:: ያነበባትንም ነገር በተግባር ይፈጽማል::

ይህ ቅዱስ ስለ ራቁትነቱ እንዳይከፋው ዘወትር ራሱን "በርሶማ ሆይ! ከእውነተኛው ዳኛ ፊት ራቁትህን መቆምህ አይቀርምና የዛሬውን ጊዜአዊ ራቁትነትህን ታገስ" እያለ ይገስጽ ነበር:: እርሱ ለጸሎት ከቆመ የሚቀመጠው ከቀናት በኋላ ነው:: ያለ ዕለተ ሰንበት እህልን አይቀምስም::

ምግቡም የሻገተ እንጀራና ክፍቱን ያደረ ውኃ ነበር:: በእንዲህ ያለ ተጋድሎ እያለ ውዳሴ ከንቱ ስለ በዛበት ሸሽቶ ወደ ምሥር ሔዶ በቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አደረ:: በዚያም እንዳስለመደ ለሠላሳ ዓመታት ተጋደለ::

በቦታው የጉድጓድ ውኃ ነበርና ሁሌ ሌሊት ወደ ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ ነበር:: እንደ ስለት የሚቆራርጠውን ውርጭም ይታገሥ ነበር:: በዚያ አካባቢ ብዙ ሰውና እንስሳትን የፈጀ አንድ ዘንዶ ነበርና በአካባቢው ሰው አያልፍም ነበር::

ታላቁ በርሶማ ግን ወደ ዘንዶው ዋሻ ሔደና ጸለየ:: "ጌታ ሆይ! በስምህ ለሚያምኑ የሰጠሃቸውን ሥልጣን አትንሳኝ?" ብሎ (ማር. 16:18) "በአንበሳና በዘንዶ ላይ ትጫናለህ::" የሚለውን መዝሙር ዘመረ:: [መዝ.፺፥፲፫] (90:13)

ዘንዶውንም "ና ውጣ::" ብሎ አዘዘው:: ወዲያው ወጥቶ ሰገደለት:: የጻድቁ ሰው አገልጋይም ሆነ:: የአካባቢው ሰውም እጅግ ደስ አላቸው:: ብዙ ጊዜም አገልግሏቸዋል:: [በሥዕሉ ላይ የምታዩት እርሱው ነው::]

ታላቁ አባ በርሶማ የሚያርፍበት ቀን በደረሰ ጊዜ ደቀ መዝሙሩን "እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ 'የብርቱ [የእግዚአብሔር] ልጅ' ብሎ ለሚጠራኝ በረድኤት እመጣለታለሁ::" ብሎ: ምላሱን በምላጭ ቆርጦ ጣለውና አሰምቶ ዘመረ::

"እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ . . . እግዚአብሔር ያበራልኛል: ያድነኛልም:: ምን ያስፈራኛል::" አለ:: [መዝ.፳፮፥፩] (26:1) ልብ በሉልኝ! የሰው ልጅ ምላስ ከሌለው መዘመርም: መናገርም አይችልም:: ቅዱሳን ግን ሲበቁ ልሳን መንፈሳዊ ይሰጣቸዋል:: ከዚህ በኋላ በትእምርተ መስቀል አማትቦ ዐረፈ::

ፓትርያርኩን አባ ዮሐንስን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳትና የምስር ሹማምንት ገንዘውት ከበረከቱ ተካፈሉ:: ገድሉ እንዳስቀመጠው በዘመኑ ሁሉ ምንጣፍ ላይ ተኝቶ አያውቅም:: "ማዕከለ ሥጋሁ ወምድር ኢገብረ መንጸፈ" እንዲል:: ያረፈውም በ1340 ዓ/ም ነው::


†  🕊   ቅዱስ አሞጽ ነቢይ   🕊  †

† አሞጽ ማለት "እግዚአብሔር ጽኑዓ ባሕርይ ነው: አንድም እግዚአብሔር ያጸናል::" ማለት ነው:: "ተወዳጅ ሰው" ተብሎም ይተረጐማል:: የነበረው ቅ.ል.ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት ሲሆን አባቱ ቴና እናቱ ሜስታ ይባላሉ:: ትውልዱም ከነገደ ስምዖን ነው::

በትውፊት ይህ ቅዱስ ነቢይ የነቢዩ ኢሳይያስ አባት ነው የሚሉ ቢኖሩም ሁለቱ አሞጾች የተለያዩ መሆናቸውን ሊቃውንት ይናገራሉ:: ቅዱስ አሞጽ ዘጠኝ ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ስለ ነገረ ድኅነት ብዙ ትንቢቶችን ተናግሯል::

ስለ ሃገራችን ኢትዮጵያም እንዲህ ብሏል :-
"የእሥራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር::"
ቅዱሱ ነቢይ ወገኖቹን አብዝቶ ይገስጻቸው ስለ ነበር ተቆጥተው በዚህች ቀን ገድለውታል::

† የቅዱሳን አምላክ አዲሱን ዘመን ቅዱሳኑን አብዝተን የምናስብበት ያድርግልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[  † ጳጉሜን ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ታላቁ አባ በርሶማ
፪. ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
፫. ቅዱስ ያዕቆብ ዘምስር
፬. አባ መግደር [እግዚአብሔር በጸሎቱ ይማረን]

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

- የለም

† " መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይህንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል:: ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም::" † [፪ጢሞ. ፬፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ዘመን ማን ነው? ዘመን ማለት እኛ ነን..ስንከፋ የሚከፋ ደግ ስንሆን ደግ የሚሆን የእኛው ነጸብራቅ ነው ዘመን። ለዚህ ነው አበው በአንጋረ ፈላስፋ "ዘመን ማለት አንተ ነህ፡፡ አንተ ሰላማዊ ስትሆን ሰላማዊ ትሆናለች፡፡ አንተ የከፋህ እንደሆነ ትከፋለች፡፡" በማለት የተናገሩት።

እናም ዘመን እኛ እኛም ዘመን ነንና ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው በዕሜያችን ስንት ጊዜ እያለፈ እንደ ኾነ እያሰብን ራሳችንን እንዲህ ብልን እንጠይቅ፡- “ቀናት እየሮጡ ነው፣ ዓመታቱም እየነጐዱ ነው፣ የዕድሜዬ መንገድም እየተጋመሰ ነው፤ ታዲያ ምን በጎ ምግባር ያዝኩ? ከዚህ ምድር የማልፍበት ቀን እየቀረበ ነው፤ ታዲያ ምን የጽድቅ ሥራ ሠራሁ? በዚህ ዕድሜዬ (ዘመኔ) መሥራት የነበረብኝ ምግባር ትሩፋት ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ አልችልም፤ ታዲያ ዕድሜዬ (ዘመኔ) ሲገፋ ማድረግ የማልችላቸውን የጽድቅ ሥራዎች (ፆም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ አገልግሎት፣… ዕድሜ ሲገፋ ይከብዳሉና) እንደ አቅሜ እያደረግኩ ነውን?” በማለት ልቡናችንን እንጠይቅ።"

“አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።” ሰቆ.ኤር 5፥21
🌼🌼"በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። 🌼የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ 🌼ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። 🌼ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።>  መዝሙረ ዳዊት 65፥9
እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ አሸጋገርዎት🌼
መልካም በዓል ይሁንላችሁ ውድ የኢትዮጵያ ቻናል ቤተሰቦች
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

🌼    እንኳን አደረሳችሁ !    🌼


[  †  መስከረም ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]  🌼


†  🕊  ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ 🕊

ወንጌል ላይ እንደ ተጠቀሰው ከ፲፪ [12] ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ ቅዱስ በርተሎሜዎስ ነው:: [ማቴ.፲፥፫] (10:3) ነገር ግን ዜና ሕይወቱ በስፋት ሲተረክ አንሰማም:: ቅዱሱ ሐዋርያ እንደ ሌሎቹ ወንድሞቹ ዓለምን በወንጌል ትምሕርት አብርቷል:: በትውፊት ትምሕርት መሠረት 'በርተሎሜዎስ' የሚለውን ስም ያወጣለት ጌታችን ሲሆን ትርጉሙም 'ተክሎችን የሚያጠጣ' ማለት ነው::

ከሐዋርያትም ጌታ አስቀድሞ የስም ቅያሪ ያደረገለት ለእርሱ እንደ ሆነ ይታመናል:: በርተሎሜዎስ የግብርና ሥራውን ትቶ: የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ: ከዋለበት እየዋለ: ካደረበትም እያደረ ምሥጢረ ወንጌልን ተምሯል::

ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላም ከሐዋርያት ጋር ዓለምን በዕጣ ተካፍሏል:: ሃገረ ስብከቱም 'እልዋህ' እና 'አርማንያ' ናቸው:: የአርማንያ መንበርም የእርሱ ነው:: ቅዱሱ ገድሉ እንደሚለው አሕዛብን በስብከቱና በሚያስደነግጡ ተአምራቱ አሳምኗል::

ከቅዱስ ዼጥሮስ: ከቅዱስ እንድርያስ: ከክርስቶፎሮስና ከሌሎቹም ሰባክያን ጋር ዓለምን ዙሯል:: ሙታንን አስነስቶ: ድውያንን ፈውሶ: አጋንንትን አውጥቶ: ብዙወችን ወደ ሕይወት መልሷል:: የደረቁ እንጨቶችም በእጁ ላይ እንዳሉ ለምልመው: አብበው ያፈሩ ነበር::

ቅዱስ በርተሎሜዎስ እያስተማረ ወደ ኢትዮዽያም ደርሶ እንደ ነበር ይነገራል:: በመጨረሻም 'ለሚስቶቻችን ንጽሕናን አስተምረሃል' በሚል ተከሶ: ንጉሥ አግሪዻ በሰቅ [ጸጉር] ጠቅልሎ: አሸዋ ሞልቶ: ባሕር ውስጥ ጥሎታል:: በዚያውም ዐርፏል::


†  🕊  ቅዱስ ሚልኪ ቁልዝማዊ  🕊  †

ይህቺ ሃገረ ቁልዝም ግብጽ ውስጥ የምትገኝ ስትሆን ብዙ ቅዱሳንን አፍርታለች:: በተለይ የአባ እንጦንስና የልጆቹ ማረፊያ ከመሆኗ ባሻገር ቅዱስ አባ ሚልኪም ወጥቶባታል:: ቅዱሱ የዘመነ ጻድቃን ፍሬ: የስለት ልጅም ነው:: ጥሩ ክርስቲያኖች የነበሩት ወላጆቹ እጅግ ባለጸጐችም ነበሩ::

በስለት መንታ ልጆችን [ሚልኪና ስፍናን] ወልደው: በሥርዓት አሳድገዋል:: ቅዱስ ሚልኪ በሕጻንነት ወራቱ ስቆና ከሕጻናት ጋር ተጫውቶ አያውቅም:: ብሉያትና ሐዲሳትን ጠንቆቆ ካጠና በኋላ እድሜው ፲፱ [19] ሲደርስ ወላጆቹ "እንዳርህ" አሉት:: የልቡን እያወቀ "እሺ" አላቸው::

ቀጥሎም "ባልንጀሮቼን ልጋብዝበት" ብሎ: ፲፻ [1,000] ወቄት ወርቅ ተቀብሎ: በፈረስ ተቀምጦ ሔደ:: መንገድ ላይ መቶውን ለተከተሉት: ፱ [9] መቶውን ወቄት ለነዳያን: ፈረሱን ደግሞ ለአንድ ደሃ ሰጥቶ: ጡር [ጢር] ወደ ሚባል በርሃ ገሰገሰ::

መጥፋቱ በቤተሰብ ሲሰማ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: እናቱም ዐይኗ ተሰወረ:: እርሱ ግን አባ አውጊን ከሚባል ባሕታዊ ሒዶ ደቀ መዝሙሩ ሆነ:: ለ፫ [3] ዓመታትም ተፈትኖ መነኮሰ::

*ከዚያም በጠባቡ ጐዳና ገብቶ በጾም: በጸሎት: በትሩፋት ከፍ ከፍ አለ:: ከቅድስናው ብዛት የተነሳ አጋንንት ገና ከርቀት ሲያዩት ይሸሹት ነበር:: የነካቸውም ሁሉ ይፈወሱለት ነበር:: በእርሱ ጸሎትም በፋርስና በሮም ሰላም ሆነ::

አንድ ቀን የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ሲሔድ የአገረ ገዥውን ልጅ ዘንዶ በልቶት ሲለቀስ ደረሰ:: ጸሎት አድርጐ ዘንዶውን ጠራውና "እንደ ነበረ አድርገህ ትፋው" ሲል አዘዘው:: ዘንዶውም ተፋው: ሰይጣኑም ሸሽቶ አመለጠ::

ሃገረ ገዥው ደስ ቢለው ፫፻ [300] ቤቶች ያሉት ገዳም ለማር ቅዱስ ሚልኪ አነጸለት:: በዚያም ፫፻ [300] መነኮሳት ተሰብስበው ትልቅ ገዳም ሆነ:: ማር ሚልኪ ሁሉን ካሰናዳ በኋላ "ከዚህ አልወጣም" ብሎ በዓቱን ዘጋ:: ሰይጣን ግን "አስወጣሃለሁ" ብሎ ፎክሮ ሒዶ በንጉሡ ልጅ አደረባትና አሳበዳት::

"ከሚልኪ በቀር የሚያሰወጣኝ የለም" አለ:: ንጉሡ ወታደሮቹን ጠርቶ "ሒዳችሁ: አባ ሚልኪን ይዛችሁ ብትመጡ ሽልማት: ካልሆነ ግን ሞት ይጠብቃችሁአል" አላቸው:: እነርሱም በጭንቅ አግኝተው "እንሒድ" አሉት:: "በሮም ከተማ በር ላይ እንገናኝ" አላቸው::

ልክ በዓመቱ እነርሱ ሮም ሲደርሱ ማር ሚልኪ ደመና ጠቅሶ ከተፍ አለ:: ልጅቱንም አቅርቦ ሰይጣንን "እየታየህ ውጣ" አለው:: ወደል ጐረምሳ ሆኖ ወጣ:: ወስዶም አሰረው:: ከቀናት በኋላ ሕዝቡና ንጉሡ እያዩ ማር ሚልኪ ደመና ላይ ተቀምጦ: ሰይጣኑን የድንጋይ ገንዳ አሸክሞ እየነዳ ወሰደው::

ሕዝቡም ደስ ብሏቸው በታላቅ ዝማሬና እልልታ ሸኙት:: ሰይጣኑንም ለዘለዓለም አሰረው:: ቅዱስ ሚልኪ በገዳሙ ለዓመታት ከተጋደለ በኋላ በዚህች ቀን ቅዱሳን አባ እንጦንስ: መቃርስ: ሲኖዳና ሌሎችም መጥተው: በክብር ተቀብለውት ዐርፏል:: አበው 'ትሩፈ ምግባር' ይሉታል::


†  🕊 ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት 🕊

ከዘጠኙ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በብርሃናት ላይ ተሹሟል:: ለሃገራችን ልዩ ፍቅር ያለው መልአኩ ከሔኖክ ጀምሮ የብዙ ቅዱሳን ረዳት ነው:: ዛሬ በዓለ ሲመቱ ነው::


†   🕊  ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ   🕊  †

ታላቁ ጻድቅ: የትእግስትም አባቷ ቅዱስ ኢዮብ በጭንቅ ደዌ ለብዙ ዘመናት በመከራ ከኖረ በኋላ በዚህች ቀን በፈሳሽ ውሃ (በዮርዳኖስ) ታጥቦ ሰውነቱ ታድሷል:: ክብርም ተመልሶለታል:: በፈሳሽ ውሃ የምንጠመቅበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

የበርተሎሜዎስ አምላክ ፍቅሩን: የሚልኪ አምላክ ትሩፋቱን: የራጉኤል አምላክ ረድኤቱን: የኢዮብ አምላክ ትእግስቱን ያሳድርብን::

🕊

[  † መስከረም ፩ [ 1 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ] 🌼

፩. ርዕሰ ዓውደ ዓመት
፪. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፫. ቅዱስ /ማር/ ሚልኪ [ትሩፈ ምግባር]
፬. ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
፭. ቅዱስ ኢዮብ ተአጋሲ
፮. ሜልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ] 🌼

፩. ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
፪. ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

" የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት:: መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ :- የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው:: ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና:: ለታሠሩትም መፈታትን: ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ: የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ: የተወደደቺውንም የጌታ ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል::' ተብሎ የተጻፈበትን ሥፍራ አገኘ::" [ሉቃ.፬፥፲፯] (4:17)


† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🌻 እንኩዋን ለታላቁ #ነቢይና_ሰማዕት_ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ 🌻

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

=>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ሚያዚያ 15 ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

=>መስከረም 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)
2.ቅዱስ ዳስያ ሰማዕት
3.ቅዱስ ዲዲሞስ ሰማዕት
4.ቅድስት መሪና

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
5.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
6.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

=>+"+ #ጌታ_ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ #ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው #ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
2024/11/16 10:09:21
Back to Top
HTML Embed Code: