Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

🌷 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ 🌷

[    ❖  ነሐሴ ፲፮  ❖    ]

[ ✞  🕊  እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የትንሳኤና የዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  🕊  ✞ ]

[ 🕊 🌷ዕርገተ ድንግል ማርያም🌷 🕊 ]

◉  ይሕች ዕለት እጅጉን ታላቅና ክብርት ናት:: ምክንያቱም የድንግል ማርያም ሥጋዋ ተነስቶ ዐርጐባታልና:: ድንግል እመቤታችን ተነሳች : ዐረገች ስንል እንደ እንግዳ ደርሶ : እንደ ውሃ ፈሶ: ወይም በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም:: ጥንቱን በአምላክ ልቡና ታስቦ: ሁዋላም ትንቢት ተነግሮለት ነው::

◉ ታሪኩ: ነገሩ: ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :- እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::

◉  ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ፭ [5] ቀን ተኩል ፭ ሺህ ፭ መቶ [5500] ዘመናት] በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::

◉ ከአዳም አንስቶ ለ፭ ሺህ ፭ መቶ [5500] ዓመታት አበው: ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት::
"እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::

🕊 የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ 🕊

◉ ከአዳም በሴት
◉ ከያሬድ በሔኖክ
◉ ከኖኅ በሴም
◉ ከአብርሃም በይስሐቅ
◉ ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
◉ ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::

◉ ከሌዊ ደግሞ በአሮን: አልዓዛር: ፊንሐስ:
ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::

◉ አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ፭ ሺህ ፬ መቶ ፹፭ [5,485] ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች:: [ኢሳ.፩፥፱ (1:9) , መኃ.፬፥፯ (4:7) ]
"ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ::
[ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ]

◉ ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ፫ [3] ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ፲፪ [12] ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ: ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች:: ፲፭ [15] ዓመት በሞላት ጊዜ ጻድቅ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::

◉ በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው:: ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር:
ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ::
[ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ]

◉ ወልደ እግዚአብሔርን ለ፱ [9] ወራት ከ፭ [5] ቀናት ጸንሳ: እንበለ ተፈትሆ [በድንግልና] ወለደችው:: [ኢሳ.፯፥፲፬] (7:14) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በናዝሬት ገሊላ ለ፪ [2] ዓመታት ቆዩ::

◉ አርዌ ሔሮድስ "እገድላለሁ" ብሎ በተሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም: በዕንባና በኃዘን ለ፫ [3] ዓመታት ከ፮ [6] ወራት ከገሊላ እስከ ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን ፭ [5] ዓመት ከ፮ [6] ወር ሲሆነው: ለርሷ ለድንግል ደግሞ ፳፩ [21] ዓመት ከ፫ [3] ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::

◉ በናዝሬትም ለ፳፬ [24] ዓመታት ከ፮ [6] ወራት ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች::

እርሷ ፵፭ [45] ዓመት: ልጇ ፴ [30] ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ፫ [3] ዓመታት ከ፫ [3] ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::

◉ የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: [ሉቃ.፪፥፴፭] (2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች:: ለ፵ [40] ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::

◉ ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮን ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ፲፭ [15] ዓመታት ኖረች:: በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ: ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና: ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::

◉ ዕድሜዋ ፷፬ [64] በደረሰ ጊዜ ጥር ፳፩ [21] ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ: ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ:
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ" እንዲል::

◉ ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት :-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ:
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ:
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::

◉ በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል [ጠባቂ መልአክ ነው] እነርሱን ቀጥቶ እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል::

በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ፪፻፭ [205] ቀናት ቆይታለች::

◉ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ ፩ [1] ሱባኤ ጀመሩ:: ፪ [2] ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም በጌሴማኒ ቀብረዋታል::

◉ በ፫ [3] ኛው ቀን [ነሐሴ ፲፮ [16] እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ ፩
[1] ቀን ሱባኤ ገቡ::

◉ ለ፪ [2] ሳምንታት ቆይተው: በዚህች ቀንም ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል::

ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን : ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን : ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::

🕊  🌷 ቅዱስ ጊጋር ሶርያዊ 🌷  🕊

ይሕ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን የሶርያ መስፍን የነበረ ሲሆን ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰምቷል:: እመ ብርሃን ለስደት ስትወጣ በመጀመሪያ የሔደችው ወደ ሊባኖስ ተራሮች ነው:: መስፍኑ ጊጋር ነበርና እርሱም የአምላክ እናትነቷን አምኖ አክብሮ አስተናግዷታል::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
ሔሮድስም ይሕንን ሲሰማ ጦር አስከትቶ ወደ ጊጋር ሔደ:: መስፍኑ ጊጋር ሔሮድስን እንደማይችለው ሲረዳ ድንግል ማርያምን ወደ ግብጽ ሸሽጐ አሸሻት:: ሔሮድስንም ፊት ለፊት ተገናኘው:: ከአቅሙ በላይ ስለነበረም በወታደሮች ተማርኮ ወደ ሔሮድስ ቀረበ:: እመቤታችንንና ልጇን "አምጣ" ቢለው "አልናገርም" አለው:: በዚህ ምክንያት አካሉን ከብዙ ቆራርጦ ገድሎታል:: በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ስለ እመ አምላክ ፍቅር የተሰዋ የመጀመሪያው ሰው ተብሎ ይታወቃል:: ጌታም ስለ ሃይማኖቱ: ፍቅሩና ሰማዕትነቱ ፫ [3] አክሊላትን ሰጥቶታል::

አምላከ ቅዱሳን ከድንግል እመ ብርሃን ፍቅር:
ከጣዕሟ: ከረድኤቷ ያድለን:: የወዳጆቿን [ጊጋርና
ጊዮርጊስን] በረከትም ያብዛልን::

[  † ነሐሴ ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም [ፍልሠቷ:
ትንሳኤዋና ዕርገቷ]
፪. ቅዱሳን ሐዋርያት
፫. ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት [ፍልሠቱ]
፬. ቅዱስ ጊጋር ሶርያዊ [ሰማዕት]

[  † ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ኪዳነ ምሕረት [የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም]
፪. ቅድስት ኤልሳቤጥ [የመጥምቁ ዮሐንስ እናት]
፫. ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ [የቅ/ ላሊበላ ወንድም]
፬. ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፭. አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፮. አባ ዳንኤል ጻድቅ
፯. ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ [ወንጌሉ ዘወርቅ]

" ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን:: እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን:: አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ:: አንተና የመቅደስህ ታቦት:: ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ:: ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው:: ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት . . ."  [መዝ.፻፴፩፥፯] (131:7)

" ወዳጄ ሆይ ! ተነሺ:: ውበቴ ሆይ ! ነዪ:: በዓለት: በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ ! ቃልሽ መልካም: ውበትሽም ያማረ ነውና : መልክሽን አሳዪኝ:: ድምጽሽንም አሰሚኝ::" [መኃ.፪፥፲፫] (2:13)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[  † እንኳን ለሰማዕታት ቅዱስ እንጣዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ † 🕊 ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ 🕊 † ]

† ይሕ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን የሚጠላ አስቸጋሪ አረማዊ ነበር:: ሃገሩ ሶርያ [ደማስቆ] ሲሆን ግብሩ ጣዖት ማምለክና መስረቅ ነበር:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በምዕመናን ላይም ግፍን ፈጽሟል:: በሥጋዊ ጉልበቱ ኃይለኛ ስለ ነበር የተፈራ ነው::

ሁልጊዜ በጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል:: የሚሔደው ግን ንዋያተ ቅድሳትን ለመዝረፍ: አንድም ካህናትን ለመደብደብ ነበር:: የሚገርመው ግን የወቅቱ ምዕመናንና ካህናት ይህን ሁሉ እያደረገባቸው አይጠሉትም:: ይልቁኑ ይጸልዩለት ነበር እንጂ:: ምክንያቱም ክርስትና ማለት ጠላትን መውደድ ነውና:: [ማቴ.፯] (7)

የእግዚአብሔር ትዕግስትና የምዕመናን ጸሎት ተደምሮው አንድ ቀን ፍሬ አፈራ:: እንጣዎስ እንደ ለመደው ለክፉ ሥራ ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል:: ከዚያም እንደ ደረሰ ወደ ውስጥ ገብቶ: የሚማታውን ተማቶ: የሚዘርፈውንም ዘርፎ: የተረፉትን ንዋያተ ቅድሳት በእሳት አቃጠላቸው::

እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ታጋሽ ነውና አላጠፋውም:: "ዘኢይፈቅድ ለኃጥእ ሞቶ" እንዲል የኃጢአተኛውን መመለስ እንጂ መሞቱን አይፈልግም:: ለዚያም ነው ዛሬ ይሔ ሁሉ ግፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተሠራ እግዚአብሔር እንደማያይ ዝም የሚለው:: ለሁሉም ቀን አለውና በፈረደ ቀን ግን በፊቱ የሚቆም አይኖርም::

እንጣዎስ ግን የሠራውን ሠርቶ እወጣለሁ ሲል አልተሳካለትም:: ከበሩ አካባቢ ሲደርስ: ከወደ ሰማይ አካባቢ ድምጽ ሰምቶ ቀና ሲል መላእክት እንደሱ ዓይነት ኃጢአተኞችን አሰልፈው በጦርና በቀስት ሲወጉአቸው ተመለከተ::

ድንገት ግን ከመላእክቱ አንዱ ዘወር ብሎ አንድ ቀስት ወደ እንጣዎስ ወረወረ [ተኮሰ]:: ቀስቷ አካሉ ውስጥ ገብታለችና እንጣዎስ መሬት ላይ ወድቆ ለሞት ደረሰ:: ላበቱ በግንባሩ ላይ በጭንቅ እየፈሰሰ ጮኸ::

"ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ! ማረኝ? ራራልኝ? ይቅር በለኝ? በድፍረት ባለ ማወቅም በድየሃለሁ:: ይቅር በለኝና ላምልክህ: ስምህንም ልሸከም" ሲል በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አሰምቶ ጸለየ:: በዚያ የነበሩ ምዕመናን ማን: በምን እንደ ወጋው ባያውቁም ባዩት ነገር ግን እጅግ ደስ አላቸው:: እነርሱም የፈለጉትና የጸለዩለት ነገር ይሔው ነበርና::

ወዲያው ግን እንጣዎስ ከሞት ጫፍ ተመልሶ ተነሳ:: መጀመሪያ በቦታው የነበሩ ካህናትና ምዕመናንን "ይቅር በሉኝ?" አለ:: ቀጥሎም ወደ ዻዻስ ዘንድ ሔዶ "አጥምቀኝ" ሲል ጠየቀ:: እርሱ በሚጠመቅበት ቀን ብዙ አሕዛብና ክርስቲያኖች ተሰብስበው ነበር::

እርሱ በከተማዋ ዝነኛ ነበር:: ሥርዓቱ ሁሉ ተደርሶ ቅዱሱ ወደ ውሃ ገንዳው ሲገባ ሁሉ እያዩ የብርሃን ምሰሶ ከሰማይ ወረደ:: ይህንን በገሃድ የተመለከቱ ከ፲ ሺህ [10,000] በላይ አሕዛብ ወዲያውኑ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተጠምቀዋል::

ቅዱስ እንጣዎስ ከዚህ በሁዋላ ምስጉን ክርስቲያን ሆነ:: ስለ ቀደመ ሕይወቱ ፈንታ ጾምን: ጸሎትን: ፍቅርን: ምጽዋትን ገንዘብ አደረገ:: ሕይወቱም ለብዙ ሰዎች መስታውት ሆነ:: እመቤታችን ድንግል ማርያምንም ይወዳት ነበርና ወደ ቅዱሳን ማሕበር [ኢየሩሳሌም] ወስዳው በሥጋዊ አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይቻል ምሥጢርን ገልጣለታለች::

እነዚህን የቅድስና ጊዜያት በስኬት ያሳለፈው ቅዱስ እንጣዎስ መጨረሻው ሰማዕትነት ሆነ::
አረማውያን ወገኖቹና ቀድሞ የሚያውቁት ወደ ቀደመ ክፋትና ክህደት እንዲመለስ ጠየቁት:: "አይሆንም" አላቸው:: በአደባባይ ለፍርድ አቅርበው ደሙ እስኪፈስ ገረፉት::

ጥርሶቹን በሙሉ በድንጋይ አረገፏቸው:: ደሙና ጥርሶቹ መሬት ላይ ተዘሩ:: ነገር ግን ይሕ ስቃይ ቅዱሱን ከፍቅረ ክርስቶስ ሊለየው አልቻለም:: አሕዛብም ተስፋ ቆርጠው በዚህች ቀን ገድለውታል:: ቅዱስ እንጣዎስም ከሁዋለኛው ዘመን ሰማዕታት እንደ አንዱ ተቆጥሯል::

[ † 🕊 ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ  🕊 † ]

† ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶ ያደገው መኑፍ [ግብጽ] ውስጥ ሲሆን ዘመኑም ፫ [3]ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ የተባረኩ ናቸውና እርሱ ሳይወለድ የነበሯቸውን ፫ [3] ሴቶች ልጆች "ተማሩ" ብለው ወደ ገዳም ቢያስገቧቸው በዚያው መንነው ቀሩባቸው::

በዚህ ሲያዝኑ ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶላቸዋል:: እነርሱም በቃለ እግዚአብሔርና በጥበብ አሳድገውታል:: ትንሽ ከፍ ሲል በአካባቢው ከነበረ አንድ ቅዱስ ሽማግሌ ጋር ተደብቀው ገድልን ይሠሩ ነበር:: ሁሌም መልካም ምግባራትን ከመፈጸም ባለፈ ሙሉውን ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ይጸልዩ ነበር::

ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም ፪ [2]ቱ ተመካክረው ስመ ክርስቶስን በገሃድ ሰብከዋል:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱን ሽማግሌ ወዲያው ሲገድሉት ቅዱስ ያዕቆብን ግን ብዙ አሰቃይተውታል:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀብሏል::

† አምላከ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

🕊

[   † ነሐሴ ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል
፪. ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ [ሰማዕት]
፫. ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ [ሰማዕት]
፬. ቅዱስ አክራጥስ ሰማዕት
፭. አባ እለእስክንድሮስ ዘቁስጥንጥንያ

[     † ወርኀዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት [ቀዳሜ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ ዘብዴዎስ]
፫. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬. አባ ገሪማ ዘመደራ
፭. አባ ዸላሞን ፈላሢ
፮. አባ ለትጹን የዋህ
፯. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ [ዘደሴተ ቆዽሮስ]

† " ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" † [፩ጢሞ.፩፥፲፭] (1:15)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡  †

[ ❖  ነሐሴ ፲፰  ❖ ]

† እንኩዋን ለሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †

[ † 🕊 ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ 🕊 † ]

ቅዱሱ ታላቅ የሃይማኖት ጠበቃ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ [የተወለደባት] ግብጽ ናት:: የተወለደው በ፫ [3]ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን በምግባሩ: በትምሕርቱ ለምዕመናን ጥቅም ሆኗቸዋል:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ገና ልጅ ሳለ ምሥጢረ ክርስትናን ይማር ዘንድ ወደ ቅዱስዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት ሔዷል::

ቅዱስ ዼጥሮስ የግብጽ ፲፯ [17]ኛ ፓትርያርክና ሊቅ ሲሆን በታሪክ የዘመነ ሰማዕታት መጨረሻ ተብሎ ይታወቃል:: ከዚህ ሰማዕት ሥር የሚማሩ ብዙ አርድእት ቢኖሩም ፫ [3]ቱ ግን ተጠቃሽ ነበሩ::

፩. ቅዱስ እለእስክንድሮስ [ ደጉ ]
፪. አኪላስ [ ውዳሴ ከንቱ ወዳጅ ]
፫. አርዮስ [ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ]

ከእነዚህም አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲታትር ነበር:: አኪላስ ደግሞ ሆዱ ዘመዱ: ስለ ምንም የማይጨንቀው ሰው ነበር:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ግን በጾምና በጸሎት እየተጋ መምሕሩን ቅዱስ ዼጥሮስን ለመተካት [ለመምሰል] ይጥር ነበር::

ወቅቱ ዘመነ ሰማዕታት እንደ መሆኑ ቅዱሱ ከመምሕሩ ጋር ብዙ ነገሮችን አሳልፏል:: አርዮስ ክዶ: ቅዱስ ዼጥሮስ ካወገዘው በሁዋላ እንደ ባልንጀራ ገስጾ ሊመልሰውም ሞክሮ ነበር:: ነገር ግን የአርዮስን ክፋት ከጌታ ዘንድ የተረዳው ቅዱስ ዼጥሮስ ደቀ መዝሙሩን እለእስክንድሮስን ጠርቶ መከረው::

"እኔ ከሞትኩ በሁዋላ አኪላስ ይተካል:: ከአርዮስ ጋር ስለሚወዳጅ በ፮ [6] ወሩ ይቀሠፋል:: አንተ ግን ከአርዮስ መርዝ ተጠበቅ" አለው:: ይህንን ካለው በሁዋላ ወታደሮች የቅዱስ ዼጥሮስን አንገት ቆረጡ:: ይህ የተደረገውም እ.ኤ.አ በ፫፻፲፩ [311] ዓ/ም ነው::

ወዲያውም አኪላስ ተሾመ:: እንደ ተባለውም ከአርዮስ ጋር ስለተወዳጀ በ፮ [6] ወሩ ተቀሰፈ:: በዚያው ዓመትም ቅዱስ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ [ግብጽ] ፲፱ [19]ኛ ፓትርያርክ [ሊቀ ዻዻሳት] ሆኖ ተሾመ::

ሊቁ ሲሾም መልካም አጋጣሚ የነበረው ያ የመከራ ዘመን ማለፉ ሲሆን በጣም ከባዱ ግን የአርዮስ ተከታዮች ከተገመተው በላይ መበብዛታቸው ነው:: ቅዱሱ ሊቅ በዽዽስና መንበሩ ለ፲፯ [17] ዓመታት ሲቆይ ዕንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አልነበረውም::

በዚህ እየጾመ: እየጸለየ: ሥጋውን እየጐሰመ ለፈጣሪው ይገዛል:: በዚያ ደግሞ ሕዝቡን ነጋ መሸ ሳይል ያስተምራል:: ምዕመናንን ከአርዮስ የኑፋቄ መርዝ ለመታደግ ባፍም: በመጣፍም [በደብዳቤ] አስተማረ::

ብርሃን የሆነ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ አትናቴዎስ እያገዘው: አርዮስን ከነአበጋዞቹ አሳፈሩት:: ለእያንዳንዷ የኑፋቄ ጥያቄ ተገቢውን መንፈሳዊ ምላሽ ከመስጠቱ ባለፈ አርዮስን ከአንዴም ፪ : ፫ቴ [2: 3ቴ] በጉባኤ አውግዞታል::

ነገሩ ግን በዚህ መቁዋጨት ባለመቻሉ ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ:: እ.ኤ.አ በ325 ዓ/ም [በእኛ በ፫፻፲፰ [318] ዓ/ም] ከመላው ዓለም ለጉዳዩ ፪ ሺህ ፫ መቶ ፵፰ [2,348] የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ:: ከእነዚህ መካከል ፫፻፲፰ [318]ቱ ሊቅነትን ከቅድስና የደረቡ: ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ያሳለፉ ነበሩ::

ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲመራ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ እለአእስክንድሮስን መረጠ:: ሊቁም አበው ቅዱሳንን አስተባብሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉትን አርዮስን ተከራክሮ ረታው::

በጉባኤው መጨረሻ አርዮስ "አልመለስም" በማለቱ እርሱን አውግዘው: ጸሎተ ሃይማኖትን ሠርተው: ፳ [20] ቀኖናወችን አውጥተው: መጽሐፈ ቅዳሴ ደርሰው: አሥራው መጻሕፍትን ወስነው: ቤተ ክርስቲያንን በዓለት ላይ አጽንተው ተለያይተዋል:: የዚህ ሁሉ ፍሬ አበጋዙ ደግሞ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ነው::

እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን "ወልድ ዋሕድ: አምላክ: ወልደ አምላክ: የባሕርይ አምላክ" መሆኑን መስክሮ ክብርን አግኝቷል:: የእምነታችንም መሠረቱ ይሔው ነው:: ክርስቶስን "ፈጣሬ ሰማያት ወምድር: የባሕርይ አምላክ: ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ [ከአባቱ ጋር በመለኮቱ የሚተካከል]" ብለው ካላመኑ እንኩዋን ድኅነት ክርስትናም አይኖርም::

ከጉባኤ ኒቅያ በሁዋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመልካሙ ጐዳና ሲጋደል: ምዕመናንንም ሲያጸና ኑሯል:: ዘወትር ወንጌልን በፍቅር ያነብ ነበርና ሲጸልይ የብርሃን ምሰሶ ይወርድለት ነበር::

ስለ ውለታውም ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ካበሩ ፭ [5]ቱ ከዋክብት ሊቃውንት እንደ አንዱ ታከብረዋለች:: ቅዱሱ ሊቅ በ፫፻፳፰ [328] ዓ/ም [በእኛ በ፫፻፳ [320] ዓ/ም] በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::

ቸር አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላ ይጠብቅልን:: ከቅዱሱ ሊቅም በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  †  ነሐሴ ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል [ ፫ኛ ቀን ]
፪. ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
፫. ቅዱስ እንድራኒቆስ ዲያቆን
፬. አባ ዘክርስቶስ ዘወሎ [ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ ]

[   †  ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት [ ረባን ]
፫. አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬. ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
፭. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ከ፸፪ [72]ቱ አርድእት]

" . . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩአችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ::" [ይሁዳ.፩፥፫] (1:3)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለቅዱሳን አበው አባ መቃርስ: ቅዱስ አብርሃም እና ቅዱስ ፊንሐስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

[ † 🕊 ታላቁ ቅዱስ መቃርስ 🕊 † ]

† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ [መቃሬ] "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ ከ፹ ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ በግብፅ ትልቁን ገዳም [አስቄጥስን] የመሠረተ ከ፶ ሺህ በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::

በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ፪ ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል::

በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ [ስም አጠራሩ ይክበርና] እመቤታችንን ቅዱሳን ሐዋርያትን አዕላፍ መላእክትን በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን ማርቆስን ዼጥሮስን: ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

ታላቁ ቅዱስ መቃርስና መቃርዮስ ከ፪ ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት በዚችው ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ፶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::

ይህች ዕለት ለአባታችን መቃሬ በዓለ ፍልሠቱ ናት:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ [የሳስዊር] ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ [አብርሃምና ሣራ] የኖሩባት ቦታ ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::

በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት አደረጉት::

ወደ ሳስዊርም ወስደው ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ፯ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት [እስላሞች] መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::

በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ::

ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::

መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::

ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል:: ይህ የተደረገው በዚህች ዕለት ነው::

[ † 🕊 አባታችን ቅዱስ አብርሃም 🕊 † ]

የሃይማኖት-የደግነት-የምጽዋት-የፍቅር አባት የሆነው አብርሃም ደጉ በዚህች ቀን ይታሠባል:: በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር:: ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር::

በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር:: አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ:: "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ:: መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው::

"እርቦኛል አብላኝ" አለው:: መልስ የለም:: "እሺ አጠጣኝ" አለው:: አሁንም ያው ነው:: "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው:: ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር:: ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር::

ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል:: ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ:: "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው::

ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው:: ይህ የተደረገው ከ፪ ሺህ ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው:: የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ በነፋስ በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል::

[ † 🕊 ቅዱስ ፊንሐስ ካህን 🕊 † ]

ካህኑ ፊንሐስ የብሉይ ኪዳን ዘመን አገልጋይ ከነገደ ሌዊ የሊቀ ካህናቱ የአሮን የልጅ ልጅ ነው:: አባቱም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛር ነው:: ፊንሐስ እሥራኤል ከግብጽ ሲወጡ ሕጻን የነበረ ሲሆን አድጐ በመጀመሪያ ካህን አባቱ አልዓዛርና አያቱ አሮን ሲያርፉ ደግሞ ሊቀ ካህንነትን ተሹሟል::

አንድ ቀን በጠንቅ-ዋዩ በበለዓም ክፉ ምክር እሥራኤላውያን ከሞዐብ ሴቶች ጋር በኃጢአት በመሳተፋቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶ ነበር:: ያጠፋቸው ዘንድም መቅሰፍት ተጀምሮ ሳለ ፊንሐስ ወንድና ሴት በደብተራ ኦሪቱ አንጻር የማይገባውን ሲሠሩ አያቸው::

ለፈጣሪው ቀንቶ በአንድ ጦር ሁለቱንም በአንድ ላይ ጥሏቸዋል:: ያን ጊዜ ጌታ "አስተንፈስካ ለነፍስየ" ብሎታል:: መቅሰፍቱም ተከልክሏል:: በዚህም ምክንያት ካህኑ ፊንሐስ የ፫ መቶ ዓመት ዕድሜ ተጨምሮለት እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል:: [ዘኁ.፳፭፥፯] , መዝ.፻፭፥፴]

ለአበው ቅዱሳን የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን:: ክብራቸውንም በእኛ ላይ ይሳልብን::

[ ነሐሴ ፲፱ [ 19 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል [፬ኛ ቀን]
፪. ታላቁ ቅዱስ መቃርስ [ፍልሠቱ]
፫. አባታችን ቅዱስ አብርሃም [ጣዖቱን የሰበረበት]
፬. ቅዱስ ፊንሐስ ካህን [ወልደ አልዓዛር]

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
፫. አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
፬. አቡነ ስነ ኢየሱስ
፭. አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

"እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:- 'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ' ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ:: እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ::" [ዕብ.፮፥፲፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

        †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለቅዱሳን ፯ቱ ደቂቅ እና ለአቡነ ሰላማ ካልዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

[ † 🕊 ቅዱሳን ፯ ቱ ደቂቅ 🕊 † ]

† እነዚህ ፯ ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: ፯ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ፪ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::

በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::

ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ ለጣዖትም ያልሰገደ ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ እጅ እግሩ ለእስር ደረቱ ለጦር አንገቱ ለሰይፍ ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::

የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ ፯ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::

ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ወጣ::

ከመውጣቱ በፊት ግን ፯ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::

ዓለምን ንቀው ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር [በጐች አሉት] ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::

አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ፯ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::

ያ የበጐች ባለቤት [ወታደር] ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::

ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ፫፻፸፪ ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::

በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን ፬፻ ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::

በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት: ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል:: ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህቺ ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው:: እርሱም "አዎ ናት" ብሎት አለፈ::

ችግሩ ግን "ራት ልግዛ" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ: እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር:: በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ዘንድ ቀረበ:: [ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው:: የነገሠውም በ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው]

በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም ሊቀ ዻዻሱም [አባ ቴዎድሮስ ይባላል] ተገረሙ:: አብረው ከከተማ ወጥተው ሔደው ፯ቱንም ሲጸልዩ አገኟቸው:: ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር:: ፯ቱም ለ፯ ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ::

ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሳኤ ሙታን የለም" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነሱ ምሥክር ሊሆንባቸው ነው:: በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃየማኖት ተመልሰዋል:: ፯ቱ ቅዱሳን ግን በ፯ኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል:: ንጉሡ በ፯ የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል::

[ † 🕊 አቡነ ሰላማ ካልዕ  🕊 † ]

እኒህ ታላቅ ደግ ሰው የነበሩት በሃገራችን ኢትዮዽያ ከ፲፻፫፻፵ እስከ ፲፻፫፻፹ ዓ/ም ነው:: በትውልድ ግብጻዊ ቢሆኑም ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ውለታን ውለዋል:: በዘመኑ ዻዻስ ሁነው ቢመጡም እንደ ሌሎቹ ዻዻሳት በቤተ መንግስት አካባቢ ሥራ ፈትተው መቀመጥን አልፈለጉም::

ወዲያው እንደ መጡ የግዕዝ ልሳንን ልቅም አድርገው ተማሩ:: ቀጥለው ኢትዮዽያውያን ሊቃውንትን ሰብስበው ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተረጉሙ ገቡ:: አሥራው መጻሕፍትን [፹፩ ዱን] ጨምሮ ብዙ መሠረታዊ መጻሕፍትን መተርጐም ችለዋል::

ይህም ሥራ አድካሚ በመሆኑ ከ፴ ዓመታት በላይ ጊዜን ወስዷል:: ከተረጐሟቸው መጻሕፍትም :-

◉  ስንክሳር
◉  ግብረ-ሕማማት
◉  ላሃ-ማርያም
◉  ፊልክስዩስ [መጽሐፈ መነኮሳት]
◉  መጽሐፈ-ግንዘት
◉  ድርሳን ዘቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ. . . ይጠቀሳሉ::

አቡነ ሰላማ በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸውና በገዳማዊ ሕይወታቸው ይታወቁ ነበር:: በተጨማሪም በየቦታው እየዞሩ ይናዝዙ ያጠምቁም ነበር:: በወቅቱ ልክ እንደ ስማቸው ሰላም እንዲሰፍን ይተጉ ነበር:: መሣፍንቱን ነገሥታቱን እያስታረቁ ለቤተ ክርስቲያን በአንድነት እንዲቆሙ አድርገዋል::

ጻድቁ አቡነ ፊልዾስን ጨምሮ ቅዱሳንን ገንዘውም ቀብረዋል:: በቀደመ ስማቸው አባ-ፊቅጦር የሚባሉት ካልዕ [፪ኛው] ሰላማ በ፩ ሺህ ፫፻፹ ዓ/ም ከ፵ ዓመታት ትጋት በሁዋላ ዐርፈዋል:: ሲጠሩም :-
◉  መተርጉም [መጻሕፍትን የተረጐሙ]
◉  ብርሃነ አዜብ [የኢትዮዽያ ብርሃን]
◉  መጋቤ ሃይማኖት ተብለው ነው::

† አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን እንዳጸናቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

[ † ነሐሴ ፳ [ 20 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል [፭ኛ ቀን]
፪. ቅዱሳን ፯ቱ ደቂቅ
፫. አቡነ ሰላማ ካልዕ [መተርጉም]
፬. ቅድስት ሔዛዊ

[ †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
፪. ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
፫. ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮዽያ]
፬. አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
፭. ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
፮. ቅዱስ ወክቡር ማር ቴዎድሮስ ሰማዕት

† "በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ:: ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል:: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን::" † [፪ቆሮ.፲፫፥፲፪]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2024/09/28 04:23:20
Back to Top
HTML Embed Code: