Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት ቅዱስ አልዓዛር እና ለቅዱሳን ቤተሰቡ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

†  🕊  ቅዱስ አልዓዛር ካህን   🕊  †

† ይህ ቅዱስ የብሉይ ኪዳን ሰማዕታት ተብለው ከሚታወቁት ዋነኛው ነው:: የነበረበት ዘመንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን "ዓመተ መቃብያን/ ዘመነ ካህናት" ይባላል::

በወቅቱ ሰሎሜ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ይኖር የነበረው ቅዱስ አልዓዛር በኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነበር:: ሐረገ ትውልዱ ከአሮን ወገን ነውና በክህነቱ ተግቶ ያገለግል ነበር:: በዚያ ላይ ሊቀ ካህንነትን በመመረጡ ሕዝቡን ይሠራ: ያስተምር: ያስተዳድር ነበር::

ቅዱስ አልዓዛር ከተባረከች ሚስቱ ሰሎሜ ፯ [7] ወንዶች ልጆችን አፍርቷል:: እነርሱንም በሥርዓት አሳድጐ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጐ ነበር:: በዚያው ዘመን በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ ፫ [3] እኩያን [ክፉ] ካህናት ነበሩ::

እነዚሁም ሕዝቡን ከማስቸገር: ፈጣሪን ከማሳዘን ቦዝነው አያውቁም ነበር:: የክፋታቸው መጨረሻ ግን የገዛ ሃገራቸውን ማጥፋት ሆነ:: ነገሩ እንዲህ ነው:- ፫ [3] ቱም ተመካክረው የአልዓዛርን የሊቀ ካህንነት ቦታ ሊቀሙ ወስነው ወደ እርሱ ሔዱና እንዲህ አሉት::

"ሹመት በተርታ: ሥጋ በገበታ" ሲሆን ያምራልና እኛ በተራችን በወንበሩ ላይ እንቀመጥ::"
እርሱ ግን "ሕዝቡን ጠይቃችሁ ተሾሙ" አላቸው:: እነርሱም ሕዝቡን ጠርተው "ሹመት ይገባናል" ቢሏቸው ሕዝቡ መልሶ "አልዓዛርን የሾመው እግዚአብሔር ነውና እናንተም ከፈጣሪ ጠይቃችሁ ተሾሙ" አሏቸው::

በዚህ ጊዜ ፫ [3]ቱ እኩያን ተቆጡ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ማይሰጣቸው ያውቃሉና:: ወዲያው ግን ፫ [3]ቱም ከአካባቢው ጠፉ:: ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ጨካኙ የግሪክ ንጉሥ አንጥያኮስ ሔዱ::

አንጥያኮስ ማለት "ቀኝ ዐይናችሁን ገብሩልኝ" የሚል ንጉሥ ነው:: እርሱን " ኢየሩሳሌም ባለቤት የላትምና ሒደህ ውረራት" አሉት:: "አጥሩ ጥብቅ ነው:: በምን እገባለሁ?" ቢላቸው "እኛ በመላ እናስገባሃለን" አሉት:: እርሱም ፪ መቶ ፵ ሺህ [240,000] ሠራዊት አስከትቶ ወረደ::

እነርሱ ቀድመው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ያስወሩ ጀመር:: "እናንተ ሹመት ብትነሱንም እኛ ግን አንጥያኮስን ያህል ንጉሥ በእሥራኤል አምላክ አሳምነን መጣን" እያሉ ይሰብኩ ገቡ:: ቅዱስ አልዓዛር "አትስሟቸው:: በዚያም ላይ አሕዛብ የተቀደሰውን ምድር መርገጥ የለባቸውም" ብሎ ነበር::

ነገር ግን አንዳንድ ችኩሎች አይጠፉምና ፈጥነው የከተማዋን በር ከፈቱት:: ሠራዊቱን ደብቆ ትንሽ ራሱን የቆመ የመሰለው አንጥያኮስ በምክንያት: በክፋትና በመላ ሁሉን ሠራዊቱን አስገባ:: የሚገርመው በጊዜው የከተማዋ ሕዝብ ፲፪ [12] እልፍ ፻፳ ሺህ [120,000] ሲሆን ንጉሡ ያስገባው ሠራዊት ግን ፳፬ [24] እልፍ ፪ መቶ ፵ ሺህ [240,000] ሆኖ ተገኘ::

ወዲያው አንጥያኮስ ሕዝቡን ሰበሰበና አልዓዛርን ለብቻው ጠርቶ ተናገረው:: "አንተ አምላክህን እንደምትወድ ሰምቻለሁ:: አንተ የበጉን መስዋዕት በልተህ: ለስዕለ ኪሩብ ሰግደህ: ሕዝቡን ግን እሪያ [አሳማ] እንዲበላና ለጸፀሐይ እንዲሰግድ አድርግልኝ" አለው::

ቅዱስ አልዓዛር መለሰለት :- "እግዚአብሔር የሾመኝኮ በጐ ሃይማኖትን ላስተምር እንጂ ለክፋት አይደለም:: ለሕዝቤ የክፋት አብነት ፈጽሞ አልሆንም" አለው:: ያን ጊዜ ንጉሡ በቅዱሱ ላይ ተቆጣ:: "የምልህን ካላደረግህ ብዙ ግፍ ይደርስብሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የፈለግኸውን አድርግ" አለው::

በዚያን ጊዜ ንጉሡ የቅዱሱን ሚስትና ፯ [7] ልጆች እንዲያመጡለት አዘዘ:: ቅዱሱ እያየ ከፊቱ ላይ ፯ [7] ቱንም ልጆቹን በሰይፍ አስመታቸውና 7ቱም ወደቁ:: ለአንድ አባት ይህ የመጨረሻው መራራ ፈተና ነው:: አልዓዛር ግን ምን አንጀቱ በኀዘን ቢቃጠልም ከልጆቹ ለእግዚአብሔር አድልቷልና ቻለው ታገሠው::

በዚህ ለውጥ እንዳልመጣ ያየው ንጉሡ ሌላ ፍርድ ተናገረ:: ቅዱሱንና ሚስቱን [ሰሎሜን] በፈትል ጠቅልለው በሠም ነከሯቸው:: [ጧፍ እንደሚሠራበት መንገድ ማለት ነው::]

አሁንም ግን ከአምልኮታቸው ፈቀቅ ባለማለታቸው ትልቅ ብረት ምጣድ ተጥዶ: ፪ [2] ቱም ከነነፍሳቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ:: ቀጥሎም ሕዝቡን እንዲፈጁ አዋጅ ወጣ:: በከተማዋ ከነበረው ሕዝብ ፵ ሺህ [40,000] ያህሉ ተገደሉ::

፵ ሺህ [40,000] ያህሉ ሲማረኩ ፵ ሺህ [40,000] ያህሉን ደግሞ ይሁዳ የሚባል አርበኛ በር ሰብሮ ይዟቸው ሸሸ:: "እንሾማለን: እንሸለማለን" ብለው ሕዝባቸውን ያስፈጁ እነዚያ ካህናትም እግዚአብሔር ፈርዶባቸው እነርሱም ተገደሉ:: ቅዱሱ የአልዓዛር ቤተሰብ ግን የክብርን አክሊል አግኝተዋል::

† የእሥራኤል አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲህ ካለው መከራ በኪነ ጥበቡ ይሰውረን:: ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን::

[  † ነሐሴ ፰ [ 8 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ አልዓዛር ካህን [ ሰማዕት ]
፪. ቅድስት ሰሎሜ ሰማዕት [ ሚስቱ ]
፫. ፯ "7ቱ" ቅዱሳን ሰማዕታት [ ልጆቹ ]
፬. ቅዱስ አሞን ሰማዕት

[   † ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
፪. ኪሩቤል [ አርባዕቱ እንስሳ ]
፫. አባ ብሶይ [ ቢሾይ ]
፬. አቡነ ኪሮስ
፭. አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
፮. ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ [ ከ፲፪ [12] ቱ ሐዋርያት]

† " አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ:: የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ:: ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት:: የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ:: የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት:: ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውሃ አፈሰሱ:: የሚቀብራቸውም አጡ::" † [መዝ.፹፰፥፩] (78:1)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

              #ነሐሴ ፰ (8) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ከሰባቱ ከዋክብትን አንዱ ለሆኑት ሁለት ድንጋዮችን በተረአምራት እንደ ታንኳ አድርገው በመጠቀም ጣና ባሕሩን በበትረ መስቀላቸው እየቀዘፉ በመሔድ ታላቁ ገዳም ደጋ እስጢፋኖስን ለመሠረቱት ለታላቁ አባት #አቡነ_ኂሩተ_አምላክ ዕረፍታቸው በዐል በሰላም አደረሰን።

                            
#አቡነ_ኂሩተ_አምላክ_ዘጣና፡- ሰባቱ ከዋክብት ከተባሉት ቅዱሳን አንዱ አቡነ ኂሩተ አምላክ ሲሆኑ እሳቸውም ታላቁን ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስን የመሠረቱት ናቸው፡፡ እርሳቸውም የዐፄ ይኩኖ አምላክ የወንድም ልጅ ናቸው፡፡ ከደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለሃይማኖት ጋር ሆነው በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከአባ ኢየሱስ ሞዐ ሥርዓተ ምንኵስናን ተምረዋል፡፡ ንጉሡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ለመላዋ ኢትዮጵያ ሊቀ ካህናት፣ አቡነ ኂሩተ አምላክን ደግሞ ዓቃቤ ሰዓት አድርገው ሾሟቸው፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክም በዓቃቤ ሰዓትነት ለጥቂት ጊዜ ካገለገሉ በኋላ በዓለም በመንግሥት ተቀምጦ ከማገልገል ይልቅ ከከተማ ወጥቶ ከሰው ተለይቶ እግዚአብሔርን ማገልግል ይበልጣል በማለት የተቀበሉትን መዓርገ ሢመት ንቀው በመተው አልባሌ መስለው ታቦተ እስጢፋኖስን ከሐይቅ ይዘው መልአክ እየመራቸው ወደ ጣና ባሕር ዳርቻ ደረሱ፡፡ ሁለት ድንጋዮችንም በተረአምራት እንደ ታንኳ አድርገው በመጠቀም ባሕሩን በበትረ መስቀላቸው እየቀዘፉ ዳጋ ወደተባለው ደሴት ገብተው ጥቂት ዕረፍትን አድርገዋል፡፡ እሳቸው ያን ጊዜ ያረፉበት ቦታ ዛሬም ድረስ "ዓቃቤ ሰዓት" እየተባለ በመዓርግ ስማቸው ይጠራል፡፡ የጣናን ባሕር እንደ ታንኳ ተጠቅመው የተሻገሩባቸው እነዚያ ሁለት ትላልቅ ድንጋዮችም ዛሬ በገዳሙ ውስጥ የጻድቃን ማረፊያ (ምዕራፈ ጻድቃን) ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ በክብር ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክ በቦታው ላይ ሥርዓቱን አጽንተው ተጋድሎአቸውን ጨርሰው ነሐሴ 8 ቀን በክብር ዐርፈዋል፡፡

ዳጋ እስጢፋስ ገዳምን ከዐፄ ዳዊት ጀምሮ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ የተነሡት ነገሥታት እየተሳለሙት የከበሩ ቅርሶችንና የወርቅ ዘውዳቸውን በስጦታ አበረክተውላታል፡፡ 900 ዓመት ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትና ሌሎች አስደናቂ ቅርሶች የሚገኙበት ገዳም ነው፡፡ የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ የዐፄ ፋሲልና የሌሎቹም ቅዱሳን ነገሥታት ዐፅም በዚህ ገዳም በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ የዐፄ ሱስንዮስም ዐፅም በዚሁ በታላቁ ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ ከብዙ ቅዱሳን ነገስታት ዐፅም ጋር ይገኛል፡፡

ዐፄ ሱስንዮስ የፖርቱጋልን እርዳታ ለማግኘት ሲሉ የካቶሊክን የክህደት እምነት አምነው በሀገራችንም ላይ አውጀው ከ8 ሺህ በላይ ካህናት ምእመናንን ካስገደሉ በኋላ ምላሳቸው ተጎልጉሎ በክፉ አሟሟት ሊሞቱ ሲሉ ልጃቸው ፋሲል ቅዱሳን አባቶችን በመለመን በጸሎታቸው እንዲፈወሱ አድርጓቸዋል፡፡ እነ አቡነ ምእመነ ድንግል እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ጋር በጸሎታቸው የንጉሡን የተጎለጎለ ምላሳቸውን መልሰውላቸው ከሕመማቸውም ፈውሰዋቸዋል፡፡ "ፋሲል ይንገስ ካቶሊክ ይፍለስ…ተዋሕዶ ይመለስ…የዐፄ ሱስንዮስ ምላስ ይመለስ…እግዚአብሔር ይፍታ" ሲል ተጎልግሉ የነበረው ምላሳቸው ተመልሰ፡፡ በዚያን ጊዜ ዐፄ ሱስንዮስ "ብቆይ ዓመት ብበላ ገአት (ገንፎ)" ብለው በመናገር ምላሳቸው እንደቀድሞው ሆነላቸው። ለንስሐ ሞት በቅተው መንግስታቸውን ለልጃቸው አውርሰው በክብር አርፈዋል፡፡ ለዚህም ነው የዐፄ ሱስንዮስ ዐፅም በታላቁ ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ ከብዙ ቅዱሳን ነገስታት ዐፅም ጋር አብሮ መገኘቱ፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክ የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ወደ ሀገራችን ለማምጣት ብዙ የደከሙ አባት ናቸው፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት በዘመናቸው ርሀብ ስለነተሳ የዘደብረ ቢዘኑን ታላቁን ጻድቅ አቡነ ፊሊጶስን ከገዳማቸው አስጠርተው "ምን ባደርግ ይሻለኛል?" ብለው አማከሯቸው፡፡ እኚህም የዘደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን መወለድ በትንቢት የተናገሩ ናቸው፡፡ ንግሥቲቱ የዐፄ ዳዊት ሚስት የአቡነ ፊሊጶስን እግራቸውን አጥባቸው ስትጨርስ የእግራቸውን እጣቢ በእምነት ጠጣችው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ፊሊጶስ ንግሥቲቱን "ከማኅፀንሽ ፍሬ ታላቅ ጻድቅ ልጅ ይወጣል" ብለው ትንቢት ከነገሯት በኋላ በትንቢታቸው መሠረት ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ተወልደዋል፡፡

ዐፄ ዳዊትም በዘመናቸው ስለተነሣው ርሀብ አቡነ ፊሊጶስን ሲያማክሯቸው ጻድቁ ሱባዔ ገብተው በጸሎት ከጠየቁ በኋላ "የጌታችንን መስቀል ያስመጡ" ብለው ንጉሡን መከሯቸው፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም ከኢየሩሳሌም፣ ከቁስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዓሥሩን ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል፡፡

ቅዱስ መስቀሉን ካመጡት ዓሥሩ ታላላቅ ቅዱሳን ውስጥም አንዱ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ ናቸው፡፡ የተቀሩት ዘጠኙ ደግሞ የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክ ወደ ግብፅ ሄደው ግማደ መስቀሉን ይዘው ከግብፅ ስለመጡ አንዳንድ ሰዎች ግብፃዊ ናቸው ይሏቸዋል ነገር ግን ለሀገራቸው ለቅድስት ኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ የዋሉ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ የትውልድ ሀገራቸውም ወሎ ልዩ ቦታው መርጦ እንደሆነ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ከአቡነ ኂሩተ አምላክ ረድኤት በረከትን እግዚአብሔር አምላክ ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን!፡፡ ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

          #ነሐሴ ፰ (8) ቀን።

እንኳን #ለካህኑ_ቅዱስ_አልዓዛርና_ለሚስቱ #ቅድስት_ለሰሎሜ ለሰባቱ ልጆቻቸው #አንኤም#አንጦኒኃስ_ዖዝያ_አልዓዛር_አስዮና_ስሙና #መርካሎት ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዐል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚችን ከሚታሰበው፦ #ከሰማዕቱ_ከቅዱስ_አሞን ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                             
#ካህኑ_ቅዱስ_አልዓዛርና_ሚስቱ_ሰሎሜ ሰባቱ ልጆቻቸው #አንኤም_አንጦኒኃስ_ዖዝያ_አልዓዛር#አስዮና_ስሙና_መርካሎስ፦ ይህም አረጋዊ አልዓዛር ከመምህራነ ኦሪት አንዱ ነው እርሱም ለሕዝቡ አለቃና ሊቀ ካህናትም ነው በፈሪሀ እግዚአብሔርም ሁኖ ያስተዳድራቸው ነበር። ከዚህም በኋላ ዳታንና አቤሮን በሙሴና አሮን ላይ እንደተነሡባቸው ከዘመዶቹ ወገን ሦስት ካህናት በእርሱ ላይ ቀንተው ተነሡበት።

የእሊህም ስማቸው ስምዖን አልፍሞስ መባልስ ይባላል ሹመቱንም እንዲለቅላቸው ፈለጉ ሕዝቡ ግን የአልዓዛር ሹመቱ ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አይደለም ብለው ከለከሉአቸው። ስለዚህም ነገር ወደ ግሪክ አገር ወርደው ንጉሥ አንጥያኮስን አነሳሡት መጥቶም የእስራኤልን መንግሥት እንዲወስድ ቀሰቀሱት። በመጣ ጊዜም ወደ ከተማቸው በተንኰል እንዲገባ አደረጉት።

በገባ ጊዜም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛርን ይዞ የእሪያ መሥዋዕትን ለሕዝቡ እንዲሠዋ አዘዘው እምቢ ባለውም ጊዜ ሰባቱን ልጆቹን ገደላቸው። እርሱንና ሚስቱን በእሳት በአጋሉት ብረት ምጣድ ላይ አስተኙአቸው እንዲህም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የእሊም ቅዱሳንም በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                             
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወድቀት እሳት ወኢርኢክዋ ለፀሐይ። ዘእንበለ ይትዐወቅ ሦክክሙ ሕለተ ኮነ። ከመ ሕያዋን በመዓቱ ይውኅጠክሙ"። መዝ 57፥8-9። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 9፥24-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 4፥12-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 16፥35-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 7፥12-26። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw

                       
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት አባ ኦሪ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

†  🕊  ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ  🕊  †

† ይህ ቅዱስ አባት የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ነው:: በዘመኑ [በ፫ [3]ኛው መቶ ክ/ዘመን] ክርስቲያን መሆን ብቻውን ለሞት እንደሚያበቃ ወንጀል ይቆጠር ነበር:: በጊዜው ክርስቲያን ከመሆን በባሰ መንገድ እረኛ ካህን ሆኖ መገኘት በጣም ከባድ ነበር::

ከመነሻውም ያን ጊዜ ክህነት የሚሰጠው በሕዝቡና በሊቀ ጳጳሱ ምርጫ ነበር እንጂ እንደ ዘንድሮ "እኔን ሹሙኝ" ማለት ልማድ አልነበረም:: ምዕመናንም እረኛቸውን ሲመርጡ በጉቦ: በዝምድና አይደለም:: በርትቶ የሚያበረታቸውን: ለመንጋው ራሱን አሳልፎ የሚሰጠውን ይመርጣሉ እንጂ::

ያልሆነ ሰው ለክህነት ቢመረጥ አንድም ክዶ ያስክዳል: ሲቀጥልም ለሕዝቡ መሰናክል መሆኑ አይቀርም:: በጊዜው [በዘመነ ሰማዕታት] የነበሩ ካህናት የቤት ሥራቸውም ማስተማር ብቻ አልነበረም:: በድፍረት በምዕመናን ፊት አንገታቸውን ለሰይፍ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር እንጂ::

ይህንን በገሃድ መፈጸም ከቻሉ አበው አንዱ ደግሞ አባ ኦሪ ቀሲስ ናቸው:: ቅዱሱ ተወልደው ባደጉባት ሃገረ ስጥኑፍ [የግብፅ አውራጃ ናት] መጻሕፍትን የተማሩ: ተወዳጅ እና ደግ ሰው ነበሩ::

አባ ኦሪ ገና ከወጣትነት ቀዳሚ ግብራቸው መንኖ ጥሪት [ምናኔ] ነበር:: በንጽሕናቸው ደስ የተሰኙ ምዕመናንም "ቅስና ተሹመህ ምራን: አስተምረን::" ቢሏቸው አበው ውዳሴ ከንቱን አይፈልጉምና "አይሆንም" አሉ::

ነገሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረና አባ ኦሪ ቅስናን ተሹመው ያገለግሉ ገቡ:: ሕዝቡን በማስተማር: በመምከር: ደካማውን በማጽናት ብዙ ደክመዋል::
ከቅድስናቸው የተነሳ ቅዳሴ ሊቀድሱ ሲገቡ ጌታችን በገሃድ ይገለጥላቸው ነበር:: ሠራዊተ መላእክትም ከበው ይነጋገሯቸው ነበር::

ሥጋውን ደሙን በማቀበልም ተግተው ዘመናት አለፉ:: ቆይቶ ግን ያ በዜና ይሰሙት የነበረ መከራ [ሰማዕትነት] በደጃቸው ደረሰ:: በጊዜው ብዙ ሰው በሰማዕትነት አለፈ:: አባ ኦሪም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ገብተው ስለ ራሳቸውና ሕዝቡ ጽናትን: ደኅንነትን ለመኑና ከቤተ ክርስቲያን ወጡ::

በቀጥታ የሔዱትም ወደ ዐውደ ስምዕ [የምሥክርነት አደባባይ] ነበር:: በመኮንኑ ፊት ቀርበው "ክርስቶስ አምላክ: ፈጣሪ: የሁሉ ጌታ ነው:: የእናንተ ጣዖት ግን ጠፊ: ረጋፊ: ወርቅ: ብር: እንጨትና ድንጋይ ነው::" ሲሉ በድፍረት ተናገሩ::

መኮንኑም ከአነጋገራቸው የተነሳ ተቆጥቶ ሥቃይን አዘዘባቸው:: ወታደሮቹ ይሆናል ያሉትን ማሰቃያ ሁሉ አባ ኦሪ ላይ ሞከሩ:: በኋላም ወደ ጨለማ እሥር ቤት ወስደው ጣሏቸው:: በእሥር ቤት ውስጥም ድውያንን ፈወሱ: ተአምራትን ሠሩ::

ይሕንን ዜና የሰሙ አሕዛብ ብዙ ድውያንን ሰብስበው መጡ:: ቅዱሱም ሁሉን በጸሎታቸው ፈወሱ:: በዚህ ምክንያትም ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና መጥተዋል:: በክርስቶስ አምነውም ለክብር በቅተዋል::

ቅዱሱንም ከእሥር ቤት አውጥተው ብዙ ካሰቃዩዋቸው በኋላ በዚህች ቀን ገድለዋቸው ሰማዕትነትን አግኝተዋል:: በአክሊለ ጽድቅ ላይ አክሊለ ካህናትን: በአክሊለ ካህናትም ላይ አክሊለ ሰማዕታትን ደርበዋል::

† አምላከ ቅዱሳን በአባቶቻችን ጽናት ያጽናን:: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን::

🕊

[  † ነሐሴ ፱ [ 9 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ [ሰማዕት]
፪. አባ ጲላጦስ ሊቀ ጳጳሳት

[  † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. አባ በርሱማ ሶርያዊ [ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት]
፪. አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ [ኢትዮጵያዊ]
፫. ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት [ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ]
፬. የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
፭. አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ [ኢትዮጵያዊ]
፮. ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ [ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት]

† "ስለዚሕ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና::" † [ ፩ቆሮ. ፲፥፲፬-፲፰ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ነሐሴ ፱ (9) ቀን።

እንኳን #ለአባታች_ለአቡነ_እስትንፋሰ_ክርስቶስ ለወራዊ መታሰቢያ በዓል (በዚች ቀን አባታችን እስትፋሰ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደውን የቊርባን ኅብስት ተቀብለው ያቀበሉበት ነው ብሎ ገድላቸው ይናገራል)ና ስጥኑፍ ከሚባል አገር ለሆኑ ለሰማዕቱ ለካህኑ #አባ_ኦር ለዕረፍት በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በፍቅር አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ሚታሰቡ፦ #ከሊቀ_ጳጳስ_አባ_ጲላጦስ ከመታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                          
ስጥኑፍ ከሚባል አገር የሆነ የከበረ #ቄስ_አባ_ኦሪ፦ ይህ ቅዱስ ብዙ ርኅራኄ ያለው በሥጋው በነፍሱም ንጹሕ የሆነ ነው ብዙ ጊዜም አምላካዊ ራእይን ያያል። ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠዊያው ላይ ታይቶ ብዙ ምሥጢራትን ገለጠለት።

ከዚህም በኋላ የአባ ኦሪ ዜናው በኒቅዮስ አገር መኰንን ዘንድ ተሰማ ወደርሱም አስቀርቦ "ለአማልክት ዕጣን አቅርብ" አለው እርሱም "ለረከሱና ለተሠሩ አማልክት አልሠዋም" ብሎ እምቢ አለው። መኰንኑም ተቆጥቶ በብዙ ሥራ አስፈራራው ቅዱስ ኦሪም ሥቃዩን ምንም ምን አልፈራውም ጹኑ ሥቃይንም አሠቃየው።

ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ አገር ላከው በዚያም ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን አሠቃይተው በወህኒ ቤት ጣሉት። በዚያም ድንቆች ተአምራቶችን በማድረግ በሽተኞችን ፈወሳቸው ። ዜናውም በተሰማ ጊዜ ደዌ ያለባቸው ሁሉ ከየአገሩ ብዙዎች ሰዎች ወደርሱ መጥተው አዳናቸው። ይህንንም መኰንኑ ሰምቶ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግስተ ሰማያትም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ የከበረ ዮልዮስ ሥጋውን አንሥቶ ገንዘው ወደ ሀገሩ ስጥኑፍም ላከው። የመከራውም ወራት ካለፈ በኋላ ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከሥጋውም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። በማመንም ለሚመጡ በሽተኞች ሁሉ ታላቅ ፈውስ ሆነ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ ኦሪ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 9 ስንክሳር።

                          
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ 44፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ፊሊ 1፥12-24፣ 2ኛ ዮሐ 1፥6-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 15፥19-25። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 10፥1-22። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊 ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ 🕊

† አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ፲፬ [14]ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን [መረታ] ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ:: አጥምቀው "ዓቢየ እግዚእ" ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ጳጳስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው:: ትርጉሙም 'በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው' ማለት ነው::

ዓቢየ እግዚእ በሕፃንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ [ደብረ በንኮል] ሔደው መንኩሰዋል::

በገዳሙ በጾም: በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል:: በጊዜው በአርባ ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር::

ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል:: ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ:: ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው::

አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ:: ቀኑ ነሐሴ ፲ [10] ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለሦስት ቀናት ባለመጉደሉ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ:: ጻድቁ በአካባቢው የነበሩት ኢ-አማንያን [አሕዛብ] ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ::

ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ:: ይሕን ድንቅ ያዩ ከዘጠኝ መቶ አርባ በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል:: ይሕም ዘወትር ነሐሴ ፲ [10] ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው [ጐንደር] ይከበራል::

ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ:: ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች:: ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር::

በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ: እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት:: ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ:: በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ: በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም:: በሰማይም እሳትን አያዩም:: ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም::" ብሏቸው አርጓል::

ጻድቁም የወንጌል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተንቤን ተመልሰዋል:: ይሔው እኛ ምን ብንከፋ: ጻድቁንም ብንረሳቸው እግዚአብሔር ግን ዛሬም በጻድቁ ምልጃ ከተማዋን ጠብቆ ይኖራል:: ነገን ደግሞ እርሱ ያውቃል:: ዛሬ ቤተ ክርስቲያኑ የታነጸበት ቦታ [ጎንደር ቀበሌ ፱ [09] ኪዳነ ምሕረት] ጻድቁ የጸለዩበት ቦታ ነው:: እንኳን በወርኀዊ በዓላቸው [በ፲፱ [19] ይቅርና በዓመታዊ በዓላቸው [ግንቦት ፲፱ [19], ነሐሴ ፲ [10] እንኳ ለንግስ የሚመጣው ሰው ቁጥር ያስተዛዝባል::

አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው: ሦስት ሙታንን አስነስተው: ብዙ ድውያንን ፈውሰው: ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው: የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው: በመቶ አርባ ዓመታቸው ግንቦት ፲፱ [19] ቀን አርፈዋል:: የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው::

ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት: አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው: ጐንደር ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል::

በረከታቸው ይደርብን::

†  🕊 ቅዱስ መጥራ ሰማዕት 🕊  †

† ቅዱሱ በዘመነ ሰማዕታት በድፍረቱ ይታወቅ ነበር:: "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" እያሉ ሲያስቸግሯቸው በሌሊት ወደ ቤተ ጣዖቱ ገብቶ የአጵሎንን [የጣዖት ስም ነው] ቀኝ እጁን ገንጥሎ: [ወርቅ ነውና] ለነዳያን መጽውቶታል:: አሕዛብ በዚህ ተበሳጭተው በብዙ ስቃይ ገድለውታል::

†  🕊 ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ ሰማዕት 🕊

† በወጣትነቱ መከራን ሲቀበል አሕዛብ ሊያስቱት ሁለት ዘማ ሴቶችን ላኩበት:: እርሱ ግን አስተምሮ ክርስቲያን አደረጋቸው:: ለሰማዕትነትም በቁ:: በየጊዜው ሲያሰቃዩት ብዙ ተአምራትን ይሠራ ነበርና ከሰላሳ ሺ በላይ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል::

† አምላካችን በወዳጆቹ ምልጃ ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይሠውርልን::
አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ፍቅርና በረከት ያብዛልን::

[  † ነሐሴ ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አባ ዓቢየ እግዚእ ኢትዮጵያዊ [ተአምራትን ያደረጉበት]
፪. ቅዱስ መጥራ ሰማዕት
፫. ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ ሰማዕት
፬. ሰላሳ ሺ ሰማዕታት [የሐርስጥፎሮስ ማኅበር]
፭. ቅዱሳን ቢካቦስና ዮሐንስ [ሰማዕታት]

[   † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫. አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ እልፍዮስ]
፭. ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት
፮. ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፯. ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

" ኑ የእግዚአብሔርንም ድንቅ ሥራ እዩ:: ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው:: ባሕርን የብስ አደረጋት:: ወንዙንም በእግር ተሻገሩ:: በዚያ በእርሱ ደስ ይለናል:: በኃይሉ ለዘለዓለም ይገዛል::" † [መዝ. ፷፭፥፭]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/16 11:04:08
Back to Top
HTML Embed Code: