Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

             #ሐምሌ ፳፯ (27) ቀን።

እንኳን #ለነቢዩ_ቅዱስ_ሕዝቅኤል_ለራእዩ_መታሰቢያ ቀን በዐል፣ #ለአዳም_ልጅ_ለቅዱስ_ሴት_ለዕረፍት በዐል፣ #ለወንጌላዊው_ለቅዱስ_ዮሐንስ በእስክንድርያ #ቤተ_ክርስቲያኑ_ለከበረችበት_በዐልና ተርኑጥ ከሚባል አገር ሰው ለሆነ #ለቅዱስ_አሞን_ሰማዕትነት_ለቀበለበት_ለዕረፍቱ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከሰማዕቱ #ቅዱስ_አሞን ጋር ሰማትነት ከተቀበለች ከድንግል #ቅድስት_ትዮጲላ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትን በረከትን ያሳትፈን።

                         

                          
#የአዳም_ልጅ_ቅዱስ_ሴት፦ ሴትም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ ሔኖስንም ወለደው። ሔኖስንም ከወለደ በኋላ ሰባት መቶ ዓመት ኖረ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ። መላ እድሜውም ዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሁለት ሆነ በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

                             
#ሰማዕቱ_ቅዱስ_አሞን፦ ይህም ቅዱስ ተርኑጥ ከሚባል አገር ሰው የሆነ ነው። ወደ ላይኛው ግብጽ በሔደ ጊዜ የቅዱሳን ሰማዕታት ግፍ ተመለከተ ወደ እንዴናው ገዥ ወደ አርያኖስም ቀርቦ ክብር ይግባውና በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ታላቅ ስቃይ አሠቃየው ሥጋውን ሁሉ ሠነጣጠቀው እረጃጅም በሆኑ በተሳሉ በብረት ችንካሮች ቸነከሩት ጌታችንም ያጸናውና ያስታግሠው ያለ ጉዳትም በጤና ያስነሣው ነበር።

ከዚህም በኋላ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ ወደ እስክንድርያ ከተማ ሰደደው ክብር ይግባውና ጌታችንም ለእርሱ ተገልጦ መታሰቢያው ለሚያደርግ፣ ገድሉንም ለሚጽፍ ስሙንም በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃል ኪዳን ሰጠው። ይህን ቃል ኪዳን ከሰጠው በኋላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ዐረገ አባ አሞንም ፈጽሞ ደስ አለው።

ከዚህም በኋላ በዚያ ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሥቃዩ ሁሉ አዳነው ይህንንም ባዩ ጊዜ ብዙ ሕዝቦች ስለ ርሱ በጌታ አመነው በሰማዕትነት ሞቱ። ከውስጣቸው ቲዮጲላ የምትባል ድንግል ነበረች ወደ መኰንኑ ቀርባ ርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመች ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነች። በእሳት ውስጥ እንዲጥሏት አዘዘ እሳቱም አላቃጠላትም ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ የሰማዕትነት አክሊል ተቀበለች።

ቅዱስ አሞንንም ብዙ ከአሠቃዩት አባላዘሩንም ቆረጡ ከዚያም እራሱን በሠይፍ ይቆርጡ ዘንድ መኰንኑ አዝዞ ቆረጡት ተጋድሎውንም ፈጽሞ የሰማዕትነት አክሊልን ፈጸመ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ አሞን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 27 ስንክሳር።

                            
"#ሰላም_ለአሞን_አባላቲሁ_ዘቊስላ። በቅንዋተ ኅፂን ዲቤሁ እለ ተተክላ። እስከ አስፈዎ አምላክ ኪዳነ መሐላ። ወሰላም ዓዲ ለድንግል ቲዮጲላ። እንተ ምስሌሁ በሠይፍ መኰንን አቅተላ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_27

                           
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም። ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር። አንተ አጽናዕካ ለባሕር በኃይልከ"። መዝ 73፥12-13። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 18፥20-ፍ.ም።

                             
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወቅዱሰ እስራኤል ንጉሥነ። ውእቱ አሚረ ተናገርኮሙ በራእይ ለደቂቅከ። ወትቤ እሬሲ ረድኤተ በላዕለ ኃይል"። መዝ 88፥18-19። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 5፥7-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 5፥17-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 4፥10-19። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ10፥30-43። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅድስት መስቀል ክብራ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።


@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለአበው ቅዱሳን ሴት : ሕዝቅኤል ነቢይ እና ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !


🕊  †  ቅዱስ ሴት ነቢይ  †  🕊

† አባታችን ሴት የመጀመሪያዎቹ ፍጥረቶች የአዳምና ሔዋን የተባረከ ልጅ ነው:: ቀደምተ ፍጥረት አዳም እና ሔዋን በዕጸ በለስ ምክንያት ከገነት ከተባረሩ በኋላ በመጀመሪያ ቃየን እና አቤልን ከነ መንትያዎቻቸው ወልደው ነበር::

ነገር ግን የልጅ ደስታቸው ቀጣይ ሊሆን አልቻለም:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቃየን ሲሆን ወንድሙን አቤልን በጾታዊ ፍላጐት ምክንያት በመግደሉ ነበር:: የአቤል ሞት ለአባታችን አዳም መራር ዜና ነበር:: ወላጅ እንኳን ደጉን ይቅርና ክፉ ልጁም እንዲለየው አይፈልግምና::

ቅዱስ አዳም ቅዱስ አቤልን ቀብሮ: ፈጽሞ አለቀሰ:: ልቅሶውም እንዲሁ የወርና የሁለት ወር አልነበረም:: አራት ኢዮቤልዩ [ሃያ ስምንት ዓመታት] ነበር እንጂ:: ይህንን ሐዘንና ልቅሶ የተመለከተ እግዚአብሔር ደግሞ ደግ ፍሬን በሔዋን ማኅጸን ውስጥ አሳደረ::

ይሕ ሕፃን በተወለደ ጊዜ "ሴት" ብለው ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "የአቤል ምትክ" እንደ ማለት ነው:: ሴት ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በብዙ ነገሩ አዳምን የሚመስል ነበረ:: ደም ግባቱ: ቅንነቱ: ታዛዥነቱ: ደግነቱ ሁሉ ልዩ ነበር:: በዚህም አዳምና ሔዋን ተጸናንተዋል::

ትልቁ ነገር ደግሞ ዓለም የሚድንባት እመቤት ድንግል ማርያም ከስልሳ በላይ የአዳም ልጆች ተመርጣ ለቅዱስ ሴት መሰጠቷ ነው:: ይሕንን ምሥጢርና የሴትን ማንነት ያስተዋለው ሊቁ አባ ሕርያቆስ እመ ብርሃንን እንዲህ ሲልም አመስግኗታል::
"ሒሩቱ ለሴት - የሴት ደግነቱ: በጐነቱ: ቅንነቱ አንቺ ነሽ" [ቅዳሴ ማርያም]

አባታችን ሴት በሚገባው ትዳር ተወስኖ ቅዱስ ሔኖስንና ሌሎች ብዙ ልጆችን ወልዷል::

አባታችን አዳም ባረፈ ጊዜ የዚህን ዓለም እረኝነት [በደብር ቅዱስ ላሉት] ተረክቧል:: አዳምም ልጆቹንና ወርቅ እጣን ከርቤውን አስረክቦታል:: ሴት እንባው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አስቀድሞ አዳምን: አስከትሎም ሔዋንን ገንዞ በክብር ቀብሯቸዋል::

ወርቅ: እጣን: ከርቤውን ከሥጋቸው ጋራ በቤተ መዛግብት [በተቀደሰው ዋሻ] ውስጥ አኑሮታል:: የአገልግሎት ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ ደጉ ሴት ኃላፊነቱን ለልጁ ሔኖስ ሰጥቶ በዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመቱ ዐርፏል:: እርሱም ከወላጆቹ አዳምና ሔዋን ጋር ተቀላቅሏል::


🕊  † ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ †  🕊

† ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል የነበረው ቅ/ል/ክርስቶስ በ፭፻ ዓመት አካባቢ ሲሆን የጼዋዌ [ምርኮ] አባልም ነበር:: እሥራኤልና ይሁዳ ወደ ባቢሎን በምርኮ ሲወርዱ አብሮ ወርዷል:: ቅዱሱ ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ሐረገ ትንቢቱም በአርባ ስምንት ምዕራፎች የተዋቀረ ነው::

በዘመኑ ሁሉ ቅድስናን ያዘወተረው ቅዱሱ ከደግነቱ የተነሳ በጸጋማይ [ግራ] ጐኑ ተኝቶ ቢጸልይ ስድስት መቶ ሙታንን አስነስቷል:: ወገኖቹ እሥራኤልንም ያለ መታከት አስተምሯል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት ታላቁን ራዕይ እንዳየ ታስተምራለች:: ነቢዩ በፈለገ ኮቦር ካያቸው ምሥጢራት እነዚህን ያነሷል :-

፩. እግዚአብሔርን በዘባነ ኪሩብ ተቀምጦ ሲሠለስና ሲቀደስ አይቶታል:: የኪሩቤልንም ገጸ መልክእ በጉልህ ተመልክቷል:: [ሕዝ.፩፥፩]

፫. በመጨረሻው ቀን ትንሣኤ ሙታን : ትንሣኤ ዘጉባኤ እንደሚደረግም ተመልክቷል:: [ሕዝ.፴፩፥፩]

፫. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ኆኅት ኅትምት/ኆኅተ ምሥራቅ [የምሥራቅ ደጅ] ሁና አይቷታል::

ይሕ የምሥራቅ ደጅ [በር] ለዘላለም እንደታተመ ይኖራል:: የኃያላን ጌታ ሳይከፍት ገብቶ: ሳይከፍት ወጥቷልና:: [ሕዝ.፵፬፥፩]
በመጨረሻ ሕይወቱ እሥራኤል ለክፋት አይቦዝኑምና ነቢዩን አሰቃይተው ገድለውታል::


🕊  † ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ † 🕊

† አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስ እና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ : በገሊላ አካባቢ አድጐ : ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕፃን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው::

ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል:: ከእርሷ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኳን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላእክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

በዚህ ቀንም ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል:: ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ለሰባ ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም : በመጽሐፍም ደክሟል::

ሦስት መልዕክታት : ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት : እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጓቸዋል:: ዳግመኛ ይሕች ዕለት ለሐዋርያው ቅዳሴ ቤቱ ናት::

† እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው :-

¤ ወንጌላዊ
¤ ሐዋርያ
¤ ሰማዕት ዘእንበለ ደም
¤ አቡቀለምሲስ [ምሥጢራትን ያየ]
¤ ታኦሎጐስ [ነባቤ መለኮት]
¤ ወልደ ነጐድጓድ
¤ ደቀ መለኮት ወምሥጢር
¤ ፍቁረ እግዚእ
¤ ርዕሰ ደናግል [የደናግል አለቃ]
¤ ቁጹረ ገጽ
¤ ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ [ከጌታ ጎን የሚቀመጥ]
¤ ንስር ሠራሪ
¤ ልዑለ ስብከት
¤ ምድራዊው መልዐክ
¤ ዓምደ ብርሐን
¤ ሐዋርያ ትንቢት
¤ ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
¤ ኮከበ ከዋክብት

† በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር:: የሴት ደግነቱ : የሕዝቅኤልም በረከቱ ይደርብን::

🕊

[ † ሐምሌ ፳፯ [ 27 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሴት ነቢይ [ወልደ አዳም]
፪. ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ
፫. ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ [ቅዳሴ ቤቱ]
፬. ቅዱስ አሞን ሰማዕት

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪. አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
፫. ቅዱስ መቃርስ [የመነኮሳት ሁሉ አለቃ]
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት [ንጉሠ ኢትዮጵያ]
፮. ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯. ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

† "እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም" ይላል ጌታ እግዚአብሔር:: "የእሥራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ:: ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ:: ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?" በላቸው::" † [ሕዝ. ፴፫፥፲፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

#ሐምሌ ፳፰ (28) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ለደብረ ሊባኖስ ሦስተኛ አበምኔት (እጨጌ) #ለአቡነ_ፊሊጶስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን።



#የደብረ_ሊባኖሱ_እጨጌ_አቡነ_ፊሊጶስ፡- በተወለዱ በ15 ዓመታቸው በምናኔ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከብዙ ጊዜ አገልግሎትም በኋላ በአቡነ ተክለሃይማኖት እጅ መንኲሰው ከእርሳቸውም ዕረፍት በኋላ ሦስተኛ አበምኔት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተወለዱት የመጀመሪያ ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡ አባታቸው ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈቀ ኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ነበር፡፡

በመጀመሪያ የአቡነ ፊሊጶስን የጽድቅ ሕይወትና ሹመታቸውን በተመለከተ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድልና በራሳቸው በአቡነ ፊሊጶስ ገድል ላይ የተጻፈውን እንመልከት፡- "ክቡር አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ከዚህ ዓለም ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ "ከአንተ በኋላ አንተን ተክቶ በዙፋንህ የሚቀመጥ ማነው?" አሉት፡፡ እርሱም "ብዙ ዘመን አይኖርም እንጂ ኤልሳዕ በእኔ ተተክቶ ይቀመጥ" አለ፡፡ ስለ ፊሊጶስ ግን አላነሳም፣ ኤልሳዕ ካረፈ በኋላ በእርሱ ተተክቶ አባት ይሆን ዘንድ ጌታችን የተሸለመ ፊሊጶስን እንደመረጠው ስም አጠራሩ ለልጅ ልጅ ዘመን እንደሚጸና ያውቅ ነበርና ስለዚህ "አልሳዕ በእኔ ተተክቶ አባት ይሁናችሁ" አለ፡፡ ክቡር አባታችንም በታላቅ ክብር ዐረፈ፡፡

አንድ ቀን አንድ ዲያቆን ዐረፈና ሬሳውን ገንዘው አጠቡት፣ ይቀብሩትም ዘንድ አስክሬኑን ይዘው ሲሄዱ በአልጋ ላይ ሳለ አስክሬኑ ተንቀሳቀሰ፡፡ የተሸከሙትም ደንግጠው መሬት ላይ አስቀመጡትና ከመግነዙ ፈቱት፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሦስት ጊዜ ተነፈሰ፡፡ ወንድሞችም "ምን እያልክ ነው?፣ ወዴትስ ነበርክ?" አሉት፡፡ ያ የከበረና የተመረጠ ዲያቆንም "ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት "ኤልሳዕ ወደኔ ይምጣ፣ ፊሊጶስ ስለ እኔ ተሹሞ በወንበሬ ይቀመጥ እርሱ ለብዙዎች አሕዛብ አባት ይሆናልና የክርስቶስንም መንጋ በጽድቅና በቅን ይጠብቃል ብሎኛል" ብሎ ይህን ተናግሮ ተመልሶ ዐረፈ፡፡ ወንድሞችም ኤልሳዕ እንደልማዱ ጎኑን ሳያሳርፍ በወንበር ላይ እንደተደገፈ በሞት ማረፉን አላወቁም ነበር"፡፡

ወደ ጻድቁ የልጅነት ገድላቸው እንመለስና አቡነ ፊሊጶስ በእግዚአብሔር ተመርጠው የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያ ሆነዋልና ገና በሕፃንነታቸው በተወለዱባት ሰላሌ ክፍለ ሀገር ዝማ በምትባል ልዩ ቦታ ውስጥ ሰይጣን በጠንቋይ ላይ አድሮ በነደደ በእሳት ውስጥ በመግባትና የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ በአካባቢው ራሱን ያስመልክ የነበረን ሰይጣን በእሳት ውስጥ እንዳለ በስመ ሥላሴ አማትበውበት አመድ አድርገውታል፡፡ በዚህ በአቡነ ፊሊጶስ ድንቅ ተአምር የጠንቋዩ ቤተሰቦችና የአካባቢው ሰዎችም አምነው ሊጠመቁ ችለዋል፡፡ ይህንንም ያደረገው ገና ሕፃን ሳለ ነው፡፡

መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት የትውልድ መንደሩን ትቶ ወደ ግራርያ ሀገር ደብረ አስቦ ሄዶ ቅዱስ ተክለሃይማኖትን እንዲያገኝ በነገረው መሠረት አንድ ቀን ያህል ተጉዞ ተክለሃይማኖትን አገኛቸውና ባርከውት ከመነኰሳት ጋር እንዲያርፍ አደረጉት፡፡ ሦስት ዓመት እነርሱን በመልካም ሥራ ፍጹም ሆኖ ሲያገለግላቸው ከቆየ በኋላ "ሁሉም በአንድነት አሁን ልብሰ ምንኵስና ይገባዋል" አሉ፡፡ ቅዱስ አባታችን ተክለሃይማኖትም የምንኵስናን ሥራ የሚያሠራ ቅድስናን ሰጠው፡፡ በሌላም ጊዜ ቅስናን ይቀበል ዘንድ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ላኩት፡፡ አቡነ ፊሊጶስ በንጉሥ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ ሲገረፉ ደማቸው እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያሳደደ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡

ንጉሥ አምደ ጽዮን በክፉ ጠንቋዮች ምክር ተታሎ "ያልወለደችህን የአባትህን ሚስት ብታገባ መንግሥትህ ትፀናለች" ብለው ክፉ ምክርን መክረውት የእንጀራ እናቱን አገባትና ንግሥት አደረጋት፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ይህን ሲሰሙ ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡ አክአብንና አልዛቤልን በድፍረት እንደገሠጻቸው እርሳቸውም በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ዘልፈው ገሠጹት፡፡ ወደ ንጉሡም ከመሄዳቸውም በፊት በዚህ ምክንያት ሰማዕት እንደሚሆኑ አውቀውት ነበርና ልጆቻቸውን ተሰናብተውና የሚተካቸውን ሰው ነግረዋቸው ነው የሄዱት፡፡ ንጉሡ አምደ ጽዮንም አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ አስገረፋቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም መሬት ላይ እየተቆረሰ የወደቀውን ሥጋቸውን እያነሱ ለበረከት ወሰዱት፡፡ ደማቸውም እንደ እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያቃጥላቸው ነበር፡፡ 300 እንስራ ውኃ አምጥተው ከደሙ በወጣው እሳት ላይ ቢያፈሱትም የውኃው ብዛት እሳቱን ማጥፋት አልቻለም፡፡ ንጉሡም በፍርሃት ከዙፋኑ ላይ ወርዶ ሸሸ፡፡

የንጉሡ ጭፍሮች ግን በጋለ ማረሻ ጀርባና ግንባራቸውን ደረታቸውንም ተኮሷቸው፡፡ ኃፍረታቸውንም እንዳይሸፍኑ እጆቻቸውን ወደ ኋላ አስረው ራቁታቸውንም በከተማው ሁሉ ሲያዞሯቸው ዋሉ፡፡ ማታም ንጉሡ "ታስረው ለኖሩ ኃይለኛ ውሾች ስጡት" ብሎ በማዘዝ ውሾቹ እንዲቦጫጭቋቸው ቢያደርጉም ውሾቹ ግን ከእግራቸው ስር ሰግደዋል፣ እርሳቸውም በእግራቸው ባረኳቸው፡፡ አማካሪዎቹም ንጉሡን "ከዚህ መነኩሴ ጋር ምን አጨቃጨቀህ በግዞት አርቀህ ስደደው ብለው" ብለው መክረውት "እስከ ቆርቆራ አገር አውጥታችሁ ወደ ትግሬ አገር ውሰዱት" ብሎ አዘዘ፡፡ እርሳቸውም ንጉሡን ከ3 ዓመት በኋላ ትሞታለህ ብለው ትንቢት ነገረውት በወታደሮች ተወሰዱ፡፡ በግርፋት ብዛት የተቆረሰ ሥጋቸው ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ደማቸውም አስረው የሚወስዷቸውን የአንዱን ወታደር አንድ ስውር ዐይኑን ፈወሰለትና ወታደሮቹም አምነው ከእርሳቸው ጋር በዚያው ተሰደው መከራን ተቀብለዋል፡፡ እሳቸው በትግራይ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ ሲያስተምሩ በትንቢታቸው መሠረትም ንጉሡ ከሦስት ዓመት በኋላ ሞተና ልጁ ነገሠ፡፡ ልጁም አባታችንን ከስደት መለሳቸውና ከተክለሃይማኖት መቃብር ደብረ አስቦ ገቡ፡፡

የነገሠውንም ልጅ አንድ ክፉ ሰው "ከአንድ በላይ ማግባት ትችላለህ፣ በገና ወቅትም ረቡዕና አርብን መጾም ተገቢ አይደለም" ብሎ ስለመከረው ጳጳሱን ወደ ሀገራቸው ግብፅ እንዲሰደዱ ሲያደርግ አቡነ ፊሊጶስን ደግሞ "ረቡዕና አርብን በጠዋት ካልቀደስክ" ብሎ ወደ ደራ ተሰደው እንዲሄዱ አደረገ፡፡ አባታችን በአጠቃላይ አምስት ጊዜ ተሰደው በትግራይ፣ በደራ፣ በዝዋይ ባሕረ ደሴት፣ በዳሞት ገማስቄ እና በወለቃ በስደት ቆይተዋል፡፡ ጳጳሱን አባ ሰላማን በአቃሊት ቅበረኝ ብለዋቸው በቃሬዛ አድርጎ ከጌርጌሳ ወደ አቃሊት ወሰዷቸው፤ እዚያም ሐምሌ 28 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ አጽማቸውም ከተቀበረ ከ140 ዓመት በኋላ በመጋቢት 23 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር መጥቶ ዐርፏል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰባት አክሊላት አቀዳጅቷቸዋል፡፡

ስለ አሁኑ ዘመን የአቡነ ፊሊጶስ ትንቢት!፡- በወቅቱ የነበሩት ጳጳስ አባ ያዕቆብ በብዙ ልመናና ምክር አቡነ ፊሊጶስን ጳጳሱ ራሱ የሚለብሰውን የክብር ልብስ አልብሶ በሸዋ አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው፡፡ ከተሾሙም በኋላ አቡነ ፊሊጶስን "ሌሎችን ሹምልን" የሚሉ በርካቶች ሲያስቸግሯቸው እሳቸው የሰጡት ምላሽ "በሥልጣን ፍለጋ ምክንያት ይህችን የትርህምትና የፅሙናን ቦታ (ደብረ ሊባኖስን) የጨዋታ የተድላ ቦታ እናደርጋታለን" በማለት በወቅቱ ማንንም አልሾምም ብለው ነበር፡፡
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
አያይዘውም በዚሁ በሹመት ሽኩቻ ምክንያት ወደፊት የሚፈጠረውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ መነፅርነት አይተውት የሚከተለውን ትንቢት ተናግረዋል፡- "እውነት እላችኋለሁ በመጨረሻው ዘመን ደጋጎች ሰዎችን ክፉዎችና ተሳዳቢዎች የሚያደርጉ፣ ሐሰተኞችና ዋዛ ፈዛዛ የሚወዱትን ደጋጎች የሚያደርጉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ በመጨረሻው ዘመን ኃጥአን በጻድቃን ይመሰላሉ፣ ጻድቃንን ኃጢአተኞች ያደርጓቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን እውነተኛዎቹ መምህራን አይሾሙም፣ ኃጢአተኞች መማለጃ ሰጥተው ወሬ እያቀበሉ ይሾማሉ፣ እንደ እባብ ክፉ ነገርን ለማድረግ ፍላፃቸውን ያሾሉ ደጋግ ሰዎችን በነገር ያጠፏቸው ዘንድ በእውነት ንጹሕ የሆኑትን ሰዎች አመፅን በተመላ አንደበታቸው ሹመትን ከመውደድ የተነሣ በቅናት ያጠፏቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን መጻሕፍትን የሚያውቁ አይሾሙም፣ ነገርን የሚያመላልሱና የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቁ ከመኳንንትና ከነገሥታት ዘንድ ሔደው ነገርን የሚሠሩ ሰውን የሚያጣሉ በአመፅ ሹመትን የሚያገኙ ብቻቸውን ይሾማሉ እንጂ ደጋጎች አይሾሙም፡፡ በሚመረጡበትም ጊዜ ከአባታቸው ከሰይጣን ጋር ሆነው "እገሌ መጻሕፍትን ያውቃል፣ የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቅ ይሾም" ይላሉ፡፡ ያንጊዜም አመፅ ይበዛል፣ ፍቅርም ትጎድላለች፡፡ ከእኔ በኋላ የሚሆነውን እነሆ ነገርኳችሁ ይህንንም አውቃችሁ በልቡናችሁ ያዙ"፡፡

ጌታችን ለአቡነ ፊሊጶስ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- "ገድልህንና ስለ እኔ የታገስከካቸውን መከራዎችህን የጻፈውን ከሁላቸው ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በወርቀ ቀለም ለዘለዓለሙ ስሙን እጽፍልሃለሁ፡፡ ሥጋህ ከተቀበረበት ቦታ ይቅርታዬንና ቸርነቴን አደርጋለሁ፡፡ መቃብርህ የበረከት ቦታ ትሆናለች"። ከአባታችን ከአቡነ ፊሊጶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን!፡፡ ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ።

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ሐምሌ ፳፰ (28) ቀን።

እንኳን ክርስቶስ ለሚወዱ #ለቅዱስ_እንድራኒቆስና #ሚስቱ_ቅድስት_አትናስያ_ለመታሰቢያ_በዐላቸው በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከቅዱሳን አባቶቻችን #አብርሃም_ከይስሐቅና_ከያዕቆብ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                           
#ቅዱስ_እንድራኒቆስና_ሚስቱ_ቅድስት_አትናስያ፦ እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር። 

ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዱራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ። 

ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ "ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የእግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን"። እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ "በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው" እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው። 

ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት። 

ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኋላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በመድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም። 

ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በመንፈስ ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን "ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና" አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም። 

አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ "አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ" አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው "ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና"። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም "ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ" አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኋላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ ያወራቻቸውን ምልክቶች አገኙ። 

እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ። ከጥቂት ቀን በኋላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ እንድራኒቆስ በሚስቱ አትናስያ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 28 ስንክሳር።

                         
"#ሰአሉ_ለነ_አብርሃም_ይስሐቅ_ወያዕቆብ አበወ ሕዝብ ወአሕዛብ ወዘመሐይምናን መክብብ ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ"። ትርጉም፦ የምዕመናን ሹሞች የአሕዛብና የሕዝብ አባቶች #አብርሃም_ይስሐቅ_ያዕቆብ ፈጽማችሁ ለምኑልን፡፡ #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በሰዓታት_ላይ፡፡

                                                 
"#ሰላም_ለእንድራኒቆስ_ለምኔተ_አስቄጥስ ዘሐወጻ። እንዘ ይዘሩ ብዕሎ ዘኢኮነ ብዕለ ዐመፃ። #ወለአትናስያ_ሰላም ለነቢር ዘተባየፃ። ከመ ይእቲ ብእሲቱ እንበለ ይጠይቅ ገጻ። እስመ አዕፅምቲሃ በጽምእ ከመ ሣዕር ነቅጻ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_28

                          
@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
     
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

እንኳን #ለዘመነ_ክረምት_አምስተኛ_ሳምንት ዕለተ እሑድ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                          
#በዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፫ "#በሰንበት ቦአ ኢየሱስ ምኵራቦሙ ለአይሁድ ምህሮሙ ወይቤሎሙ አክብሩ ሰንበትየ፤ አዝ፣(በሰንበት) በሰንበት አጋንንተ አውጽአ ወበቃሉ እለ ለምጽ አንጽሐ፤ አዝ፣ በሰንበት ወረቀ ምድረ ወገብረ ፅቡረ ፅቡረ ወበምራቁ አሕየወ ዕውረ፤ አዝ፣ (በሰንበት) #ዘይኤዝዞሙ #ለደመናት_ያውርዱ_ዝናመ ውስተ ኵሉ ምድር፤ አዝ፣ ውስተ ኀበ ዘይፈቀድ መካን፤ አዝ፣ ኅቡረ ይትፈሣሕ ዘይዘርእ ወየዐርር፤ አዝ፣ ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ"። ትርጉም፦ #ኢየሱስ_በሰንበት ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ አስተማራቸው ሰንበቴን አክብሩ አላቸው በሰንበት አጋንንትን በቃሉ አወጣ፤ ለምጻሞችን አነጻ፤ በሰንበት ምራቁን ወደ ምድር እንትፍ ብሎ ጭቃ አደረገ፤ በምራቁም የዕውርን ዐይን አበራ፤ ወደ ምድር #ዝናምን_ያወርዱ_ዘንድ_ደመናት የሚያዛቸው ወደሚፈለገው ቦታ የሚመራቸው እርሱ ነው፤ የሚዘራውም የሚያጭደውም በአንድነት ይደሰታል፤ ምድርም አየችው አመሰገነችው ባሕርም ሰገደችለት። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ


                           
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "ሐወጽካ ለምድር ወአርወይካ። ወአብዛኅኮ ለብዕላ። ፈለገ እግዚአብሔር ምሉእ ማያተ"። መዝ ። የሚነበቡት መልዕክታት። 2ኛ ቆሮ 10፥1-ፍ.ም፣ ያዕ 3፥1-9 እና የሐዋ ሥራ 28፥17-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 8፥1-ፍ.ም። መልካም በዓል የአቡነ ፊሊጶስ የዕረፍት በዓልና ዕለተ ሰንበት። ለሁላችንም ይሁንልን።

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

[ 🕊 ✞ እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን "እንድራኒቆስ ወአትናስያ" እና ለአቡነ "ፊልዾስ ዘደብረ ሊባኖስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞  🕊 ]


🕊 † ጻድቃን እንድራኒቆስ ወአትናስያ  †  🕊

ሁለቱ ቅዱሳን ባል እና ሚስት [ባለትዳር] ናቸው:: የነበረበት ዘመን ፬ [4] ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እስኪ እግዚአብሔር የቀደሰው ጋብቻ ምን እንደሚመስል እንመልከት::

እንድራኒቆስና አትናስያ በዘመናቸው ከልጅነት ጀምረው ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰሙ : ለወላጆቻቸው የሚታዘዙ ነበሩ:: ዘመኑ ደርሶ በሚገባው የተክሊል ሥርዓት ጋብቻቸውን ፈጸሙ:: ፵ [40] ቀን ከተፈጸመ በሁዋላ ከምንም ነገር በፊት ፪ [2] ቱ ቁጭ ብለው ተወያዩ::

የውይይታቸው ርዕስ ደግሞ "ፈጣሪያችን በምን እናስደስተው" የሚል ነበር:: ውይይታቸው የጠናቀቀው በእነዚህ ውሳኔዎች ነው::

፩. ሁልጊዜም እንግዳ መቀበል አለብን::

፪. ነዳያን ከቤታችን ሊጠፉ አይገባም::

፫. ጸሎት : ጾምና ስግደት በቤት ውስጥ አይቁዋረጥም::

፬. አብሮ ለመተኛት መቸኮል የለብንም::

እነርሱ መልካምን አስበዋልና አምላክ የሰጣቸውን ሃብት ሲመጸውቱ ኖሩ:: ከዘመናት የቅድስና ጉዞ በሁዋላ በፈቃደ እግዚአብሔር ፪ [2] ልጆችን አከታትለው ወለዱ:: ወንዱን "ዮሐንስ" : ሴቷን ደግሞ "ማርያም" አሏት::

እነርሱን ከወለዱ በሁዋላ እንደ ገና ሌላ ውሳኔ አሳለፉ:: "ይህንን ላደረገልን ጌታ ከዚህ በሁዋላ አልጋ እንለያለን" ብለው ለ፲፪ [12] ዓመታት በጾምና በጸሎት ተወሰኑ::

ሕጻናቱ ዮሐንስና ማርያም በቅንነት አድገው እድሜአቸው ፲፪ [12] ሲሆን ፪ [2] ቱም በአንድ ቀን ታመው ሞቱ:: ይህ ለአንድ ወላጅ የመጨረሻው አሰቃቂ ፈተና ነው:: ሁሉቱም [እንድራኒቆስና ሚስቱ አትናስያ] ልጆቻቸውን ታቅፈው ወስደው ቀበሩ::

እንድራኒቆስ ከቀብር በሁዋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ምርር ብሎ አለቀሰ:: ግን እንዲህ አለ :-
"አምላከ ኢዮብ! አንተ ሰጠኸኝ:: አንተም ነሳኸኝ:: ስምህ ለዘለዓለም ይባረክ" ብሎ ሔደ:: እናት አትናስያ ግን ከሐዘን ብዛት ልቡናዋ ሊሠወር ጥቂት ቀረው::

የልጆቿ መቃብር ላይ ተደፍታ ስታለቅስ ቅዱስ መልአክ ልቡናዋን ወደ ሰማይ አሳረገው:: ልጆቿ ዮሐንስና ማርያም በገነት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ሐሴትን ሲያደርጉም ተመለከተች:: ወዲያው ወደ ቤት ተመልሳ ለባሏ እንድራኒቆስ ያየችውን ነገረችውና ደስ አላቸው::

እዛው ላይ "ለዚህ ውለታው ከነፍሳችን ውጪ የምንሰጠው የለም" ብለው ሊመንኑ ተስማሙ:: እጅግ ሃብታሞች ነበሩና ነዳያንን ሰብስበው : ሃብት ንብረታቸውን : ቤት ርስታቸውን አካፍለው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዱ::

እርሷ ከሴቶች ገዳም : እርሱ ደግሞ ከወንዶቹ ገቡ:: ለ፲፪ [12] ዓመታት በፍጹም ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ተገዙ:: በእነዚህ ዘመናት ተያይተው : አንዱ ስለ ሌላው ሰምቶ አያውቅም:: በጸሎት ግን ያለማቁዋረጥ ይተሣሠቡ ነበር::

ከ፲፪ [12] ዓመታት በሁዋላ የፍቅር አምላክ በሁለቱም ልቡና በተመሳሳይ ሰዓት : ተመሳሳይ ሐሳብን አመጣ:: እርሱ ከአበ ምኔቱ [ታላቁ_አባ_ዳንኤል] : እርሷም ከእመ ምኔቷ አስፈቅደው ወደ ኢየሩሳሌም ከቅዱሳት መካናት ለመባረክ ጉዞ ጀመሩ:: በየፊናቸው ጥቂት እንደተጉዋዙ እርስ በርስ ተያዩ::

እርሷ ለየችው:: እርሱ ግን ጭራሽ ሊለያት አልቻለም:: ይህም ጥበበ እግዚአብሔር ነው:: ፪ [2] ቱም እየተጫወቱ : እየጸለዩ በሰላም ተባርከው ወደ ግብጽ ተመለሱ:: በእነዚህ ጊዜያት ቅድስት አትናስያን የሚለያት አልነበረም:: አካሏ በገድል ከመለወጡ ባሻገር የለበሰችው እንደ ወንድ መነኮሳት ነበር::

ወደ ገዳመ_አስቄጥስ ሲደርሱ ጸጋው ተሰጥቶታልና አባ_ዳንኤል ባልና ሚስት መሆናቸውን አወቀ:: "ለምን አብራችሁ አትኖሩም?" አላቸው:: "እኛ ደስ ይለናል" አሉት:: ከዚያ እርሷ እያወቀችው: እርሱ ሳያውቃት ለ፲፪ [12] ዓመታት አብረው በቅድስና ኖሩ::

ከእነዚህ ዘመናት በሁዋላ ግን ሐምሌ ፳፰ [28] ቀን ቅድስት አትናስያ ታመመች:: አባ ዳንኤል ሥጋውን ደሙን አቀብሏትም ዐረፈች:: ሊገንዟት ሲቀርቡ ቅዱስ እንድራኒቆስ መልኩዋን ልብ ቢለው ሚስቱ ናት::

በአንድ ጊዜ ሚስቱንና የሚወደውን ባልንጀራ በማጣቱ አለቀሰ:: እርሷን ቀብረው ወደ በዓቱ ተመልሶ "ጌታ ሆይ! ውሰደኝ?" አለ:: እርሱም ተከትሏት ዐረፈ:: አባ ዳንኤል እርሱንም ቀብሮ ጥዑም ዜናቸውን ጻፈ::


🕊  †  አባ ፊልዾስ ዘደብረ ሊባኖስ †  🕊 

ታላቁ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ: ሐዋርያና ሰማዕት አቡነ_ፊልዾስ የጻድቁ አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆኑ የተወለዱት በምድረ ሽዋ በ፩ ሺህ ፪መቶ ፷፮ [1266] ዓ/ም ነው:: ከልጅነታቸው ጀምረው ምሥጢር ተመራማሪና መጻሕፍትን መርማሪ የነበሩት ጻድቁ የመነኑት ገና በ፲፭ [15] ዓመታቸው ነበር::

+በደብረ_ሊባኖስ በአሞክሮ ለ፫ [3] ዓመታት ቆይተው መንኩሰዋል:: ለ፳፪ [22] ዓመታትም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው አገልግለዋል:: አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፻፫፻፮ [1306] ዓ/ም ነሐሴ ፳፬ [24] ቀን ሲያርፉ የተተኩት አባ ኤልሳዕ ቢሆኑም ለ፫ [3] ወራት ቆይተው ዐርፈዋል::

በ1307 ዓ/ም አቡነ ፊልዾስ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት [እጨጌ] ሁነዋል:: ገዳሙንም ለ፳፰ [28] ዓመታት መርተዋል:: ከዚያም በዘመነ አፄ ዓምደ ጽዮንና በአፄ ሰይፈ አርዕድ ብዙ ስደት: መከራ: እሥራትና ግርፋት ደርሶባቸዋል:: ምክንያቱ ደግሞ እውነትን መናገራቸውና ነገሥታቱን መገሰጻቸው ነበር:: በስደትም ለ፮ [6] ዓመታት ከ፱ [9] ወራት ቆይተዋል::

ሃገሪቱን በስብከተ ወንጌል ካበሩ ፲፪ [12] ቱ_ንቡራነ_እድ አንዱ የሆኑት እጨጌ አባ ፊልዾስ በተወለዱ በ፸፬ [74] ዓመት ከ፱ [9] ወራቸው በ፲፻፫፻፵፩ [1341] ዓ/ም ዐርፈዋል:: የተቀበሩት በደብረ_ዕንቁ ሲሆን ካረፉ በ፻፵ [140] ዓመት አቡነ_መርሐ_ክርስቶስ ዐጽማቸውን አፍልሰዋል::

ከቅዱሳኑ እንድራኒቆስ ወአትናስያ እና ከጻድቁ አቡነ ፊልዾስ በረከትን ይክፈለን::

🕊

[  †  ሐምሌ ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱሳን ጻድቃን እንድራኒቆስና አትናስያ
፪. አቡነ ፊልዾስ ጻድቅ [ዘደብረ ሊባኖስ]

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪. ቅዱሳን አበው [አብርሃም : ይስሐቅና ያዕቆብ]
፫. ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
፬. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ [ሰማዕት]

" ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል:: ከሚስቱም ጋር ይተባበራል:: ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ:: ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው:: እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርትስቲያን እላለሁ:: ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጐ ይውደዳት:: ሚስቱም ባሏን ትፍራ:: " [ኤፌ.፭፥፴፩] (5:31)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
2024/11/05 19:14:50
Back to Top
HTML Embed Code: