Telegram Web Link
††† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን †††

††† ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብፅ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ "አውሴ" ይባላል:: ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ215 ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ 80 ዓመቱ : ኢያሱ ደግሞ 40 ዓመቱ ነበር::

ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለ40 ቀን የታሠበላቸውን መንገድ 40 ዓመት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምሕሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም::

አውሴን "ኢያሱ" ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው:: ኢያሱ ማለት "መድኃኒት" ማለት ነው::
ለዚሕም ምክንያቶች አሉት:- ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል:: ምድረ ርስትን አውርሷል::
ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) እንዲሆን ነው::

ቅዱስ ኢያሱ በበርሃ ለ40 ዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል:: ሊቀ ነቢያትን ታዝዞታል (አገልግሎታል):: እሥራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል::

በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል:: ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን : ካሕናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: ይህን ጊዜ ዕድሜው 80 እየሆነ ነበር::

††† እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን (አስተዳዳሪ) እንዲሆን ሾመው:: ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ:
¤ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ
¤ሕዝቡን አሻግሮ
¤የኢያሪኮን ቅጥር 7 ጊዜ ዙሮ
¤በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ
¤የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ::

የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ:: እነዚያን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል : በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ:: በዚያች ዕለትም ለ12ቱ ነገደ እሥራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን: ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም (በኤሎም ሸለቆ) አቆመ::

ሰባት አሕጉራተ ምስካይ (የመማጸኛ ከተሞችን) ለየ:: ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለ40 ዓመታት አገለገለ:: በመጨረሻም ለሕዝቡ አላቸው:-
"እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን:: (ኢያ. 24) እናንተስ?" አላቸው:: እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን" አሉት:: ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ 3 ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ::

ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት:: ሐውልቷ 3 ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በ3 ወገን (በነፍስ: በሥጋ: በልቡና) ድንግል ናት:: አንድም በ3 ወገን (ከኃልዮ: ከነቢብ: ከገቢር ኃጢአት) ንጽሕት ናት:: ለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" (የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ) ሲል ያመሰገናት::

ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በ80 ዓመት: በተወለደ በ120 ዓመቱ (ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በ110 ዓመቱ ይላል) በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለ30 ቀናት አለቀሱለት::

††† በወዳጁ በኢያሱ እጅ የአሕዛብን ቅጥር ያፈረሰ እግዚአብሔር የእኛንም የኃጢአታችንን ግንብ በወዳጆቹ ምልጃ ያፍርስልን:: ከቅዱሱ ነቢይም በረከትን ያሳትፈን::

††† ሰኔ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን
2.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (ቅዳሴ ቤቱ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ:: በእውነተኛም ልብ አምልኩት . . . እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ . . . የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ: የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ:: እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን::" †††
(ኢያሱ. 24:14)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ † እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያ እና ለሰማዕቱ ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

🕊 † ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ † 🕊

† ሐናንያ ቁጥሩ ከ፸፪ ቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው:: ከነገደ እሥራኤል ተወልዶ : በሕገ ኦሪት አድጐ : ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው:: እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከ፸፪ ቱ አርድእት ደመረው::

ለ፫ ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ : ከዕለተ ስቅለት በፊት ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር:: ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን" ማለታቸውን አስቀምጦልናል:: [ሉቃ.፲፥፲፯] ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በ፶ ኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር:: በሁዋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ዻዻስ አድርገው ሹመውታል:: ጌታ ባረገ በ፰ ኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል [የሁዋላው ቅዱስ ዻውሎስ] ወደ ደማስቆ የተጉዋዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር::

ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዐይኑን አጠፋው:: ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነገረው:: ከ፫ ቀናት በሁዋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል::

ሳውል [ዻውሎስ] ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር:: ፪ ቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው : ፈወሰው : አጠመቀው : በጐ መንገድንም መራው:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ዻውሎስ የንስሃ አባቱ ይሰኛል:: [ሐዋ.፱፥፩-፲፱]

ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ:: መከራንም ተቀበለ:: በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል::

🕊 † ቅዱስ ቶማስ ዘሰንደላት † 🕊

† በ፫ ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ሰማዕታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ ሰማዕትነት ሕይወት የገባው በ፲፩ ዓመቱ በመላእክት መሪነት ነው:: ገና ወደ ምስክርነት አደባባይ እንደ ቀረበ መኮንኑ "ክርስቶስን ካድና ልሹምህ" ቢለው ሕጻኑ ቅዱስ ቶማስ ተቆጥቶ : "አንተ ሰነፍ መኮንን" ብሎ ገስጾ : በጐችን ይመልስባት በነበረችው ጅራፍ ገርፎታል:: ይሔም በዘመኑ የመጨረሻው የድፍረት ደረጃ ነበር::

† በዚህም ምክንያት በሕጻን ገላው ላይ የተቀበለው መከራ ሊናገሩት ይከብዳል::

¤ ግርፋት
¤ እሳት
¤ አራዊት በእርሱ ላይ አልፈዋል::

አካሉ ተቆራርጧል:: አንድ ጊዜም "ለጣዖታችሁ እንድሰግድ አምጡት" ብሏቸው ልክ ከፊቱ ሲደርሱ ወደ ጌታ ቢጸልይ መሬት ተከፍታ ውጣቸዋለች:: እሱን ያሰቃየው የነበረውን መኮንንም ከደዌው አድኖ ከነ ሠራዊቱ አሳምኖታል:: ሕጻኑን ቅዱስ ቶማስን ግን ያላመኑ አረማውያን በዚህች ቀን አንገቱን ሰይፈውት በሰማዕትነት ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔዷል::

† አምላከ ቅዱሳን ከሐዋርያው በረከት : ከሰማዕቱም ምልጃ አይለየን::

🕊 † ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ  †  🕊

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው: በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::

ሊቁ የተወለደው መጋቢት ፳፯ ቀን በ፬፻፴፫ ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::

አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት ገና በ፫ ዓመቱ እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ-እኔስ ፫ ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም :-

፩. ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ
፪. ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ
፫. ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "እግዚአብሔር በዚሕ ሕጻን አድሮ ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::

ቅዱስ ያዕቆብ ፯ ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ፭ ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ፲፪ ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::

"እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል:: ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በሁዋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን: ዕጸበ ገዳምን: ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ: ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ [በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት] ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል:: በዘመኑም:-

፩. የ፬፻፶፩ ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል
፪. ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል
፫. በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል
፬. ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በሁዋላ በተወለደ በ፸፪ ዓመቱ በ፭፻፭ ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ ፳፯ ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ::  ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::

አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † ሰኔ ፳፯ [ 27 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ [ከ፸፪  ቱ አርድእት]
፪. ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት [ዘሰንደላት]
፫. ቅዱስ አልዓዛር ነዳይ [በነዌ ደጅ የወደቀ : ቀጥሎ ደግሞ በአብርሃም እቅፍ ውስጥ የተገኘ ጻድቅ - ሉቃ.፲፮፥፲፱]
፬. ቅዱስ ማማስ

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
፪. አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
፫. ቅዱስ መቃርስ [የመነኮሳት ሁሉ አለቃ]
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
፭. ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
፮. ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
፯. ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

" በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ:: ጌታም በራዕይ :- "ሐናንያ ሆይ!" አለው:: እርሱም "ጌታ ሆይ! እነሆኝ" አለ:: ጌታም :- ተነስተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሒድ:: በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ:: እነሆ እርሱ ይጸልያልና:: ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቷል" አለው::" † [ሐዋ.፱፥፲-፲፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር
† ወለወላዲቱ ድንግል
† ወለመስቀሉ ክቡር

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †            †            †
▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬
💖               🕊                  💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
†† "በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ:: ጌታም በራዕይ:- "ሐናንያ ሆይ!" አለው:: እርሱም "ጌታ ሆይ! እነሆኝ" አለ:: ጌታም:- ተነስተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሒድ:: በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ:: እነሆ እርሱ ይጸልያልና:: ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቷል" አለው::" †††
(ሐዋ. 9:10-18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                           †                           

   [   ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል  !  ]
▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

" ታመመ ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ ፣ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም ፣ አይጠማም ፣ አይደክምም ፣ አያንቀላፋም ፣ አይታመምም ፣ አይሞትም ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፡፡"

[ ቅዱስ ቄርሎስ ]

"ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ"  [ ኃይሌና መጠጊያዬ እርሱ ጌታዬ ነው ! ]

🕊


†                       †                         †
💖                    🕊                     💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
                         †                        

  [      🕊  ፍኖተ ቅዱሳን   🕊      ]

[  የቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስናና የተጋድሎ ሕይወት ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[        በሌላ ላይ አለ መፍረድ !        ]

🕊

" እኛ ያየነው ኃጠአታቸውን ነው .... ! "
........

በአንጾኪያ የሚኖር አንድ አረጋዊ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ሲያይ በጣም የሚናደድና የሚበሳጭ ረድእ ነበረው፡፡

አረጋዊው ግን እንዲህ እያለ ይመክረውና ይገሥፀው ነበር ፦ " ነፍስህን በሚያጠፋ በከባድ ፍርድና ጥፋት ውስጥ እንዳለህ በእውነት እነግርሃለሁ ፣ የሰውን እውነተኛ ሥራና ማንነት ከራሱ በስተቀር ሌላ ማንም የሚያውቅ የለምና። በሰዎች ፊት ብዙ ኃጢአትን የሠሩ ፣ ነገር ግን በኅቡዕ ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር የተመለሱና የተቀበላቸው ብዙዎች አሉና።

እኛ ያየነው ኃጠአታቸውን ነው ፣ ደግነታቸውንና ትክክለኛ ማንነታቸውን የሚያየውና የሚያውቀው ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው:: ዘመናቸውን በኃጢአት አሳልፈው ወደ ሞት ሲቃረቡ ንስሐ ገብተው የዳኑ ብዙዎች አሉ ፣ በቅዱሳን ጸሎት የዳኑ ብዙ ኃጥአንም አሉ፡፡

ስለዚህ ማንም ሰው ሌላውን ሰው ኃጢአት ሲሠራ በዓይኑ ቢያየው እንኳ ይፈርድ ዘንድ አይገባውም ፤ ፈራጅ አንድ ወልደ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። የሚፈርድ ሰው ግን ፈራጅ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን መቃወሙ ነው፡፡ "

የአባቶቻችን ጸሎትና በረከት ይደርብን፡፡


†                       †                         †
💖                    🕊                     💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ †  እንኩዋን ለስደተኛው ሊቀ ዻዻሳት "አባ ቴዎዶስዮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  † ]

🕊   †  አባ ቴዎዶስዮስ   †   🕊

ጻድቁ ሊቀ ዻዻሳት ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ከልጅነቱ መጻሕፍትን ተምሮ በመንኖ ጥሪት የሚኖር ደግ ሰው ነበር:: ያ ዘመን መለካውያንና ልዮናውያን [ክርስቶስን ፪ [2] ባሕርይ የሚሉ] የሰለጠኑበት ዘመን ነበር:: በአንጻሩ ደግሞ ተዋሕዶን የሚያምኑ ሊቃውንትና ምዕመናን ቁጥራቸው የተመናመነ ነበር::

ችግሩ ግን ይህ ብቻ አልነበረም:: በጊዜው ተዋሕዶን አምኖ መገኘት እስከ ሞት የሚደርስ ዋጋንም ያስከፍል ነበር:: ለዚሕም ነው ሮማውያን ሃይማኖትን በግድ ለማስለወጥ ከነገሥታቱ ጋር የተቆራኙት:: ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጋግራ ደሴት ውስጥ ከተገደለ በሁዋላ በግብፅ የተሾሙ ሊቃነ ዻዻሳት አብዛኞቹ መከራና ስደትን ቀምሰዋል:: ትልቁን ቦታ ግን አባ ቴዎዶስዮስ ይወስዳል::

አባ ቴዎዶስዮስ ለእስክንድርያ [ግብፅ] ፴፫ [33] ኛ ፓትርያርክ ነው:: እረኝነት [ዽዽስና] እንዳሁኑ ዘመን ሠርግና ምላሽ አይደለምና ገና እንደ ተሾመ የቀረበለት ጥያቄ አንድ ነበር:: "ተዋሕዶን ትተህ መለካዊ ትሆናለህ ወይስ የሚከተልብህን ፍርድ ትቀበላለህ?" አሉት:: ይህንን ያሉት ከንጉሡ ዮስጢያኖስ የመጡ መልእክተኞች ነበሩ:: መልሱ ፈጣን ሆነባቸው:: "እኔንም ሆነ ሕዝቤን ከቀናችው እምነታችን በምንም ልትለዩን አትችሉም" አላቸው::

በዚህ ምክንያት በቀጥታ ግዞት [ስደት] ተፈረደበት:: ወደ በርሃ ሲያግዙት ካህናት : መምሕራንንና ምዕመናንን አደራ ብሏቸው ነው የሔደው:: መናፍቃኑ እሱን ካሰደዱ በሁዋላ ሕዝቡን ለመቀየር ብዙ ደክመዋል:: ግን ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም አደርነትን የማይረሱ ደጋግ መምሕራን ነበሩና ነው::

በዚያ ላይ አባ ቴዎዶስዮስ ጦማር [መልእክት] በየጊዜው ይጽፍላቸው ነበር:: እጅግ ብዙ ከሆኑት መልእክቶቹ የተወሰኑት ዛሬም ድረስ ሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ::

በዚሕ አስቸጋሪ ዘመን መልካም ነገሮችም ነበሩ:: ቀዳሚው ማሕቶተ ተዋሕዶ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ ሲሆን ፪ [2] ኛው ደግሞ የንጉሡ ሚስት የተባረከችው ታኦድራ ናት::

አባ ቴዎዶስዮስ በግዞትና በስደት ሳለ ንግሥቲቱ ትራዳው : ምዕመናንንም ትንከባከብ ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ከሊቀ ዻዻሱ ዘንድ ክህነትን ተቀብሎ ከሶርያ እስከ ምድረ ግብጽ ስለ ተዋሕዶ ሕልውና ተጋድሏል:: ምናልባትም ከሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ በሁዋላ በፈሊጥ ክርስትናን በማስፋፋት ቀዳሚ አባት ነው:: [በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕተብ ማሰርን ያስተማረ አባትም ነው]

፪ [2] ቱ [አባ ቴዎዶስዮስና ቅዱስ ያዕቆብ] ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ስለ ደከሙ የዘመኑ ምዕመናን በስማቸው "ያዕቆባውያን እና ቴዎዶስዮሳውያን" ተብለው ተጠርተዋል:: አባ ቴዎዶስዮስ ግን ሲታሠር ሲፈታ : ሲሰደድ ሲመለስ ብዙ ተሰቃየ::

ሕዝቡን ግን በመልካም እረኝነት ጠብቆ : ከተኩላ አፍ ታደገ:: በዚህች ቀንም ዐርፎ ተቀብሯል:: በፓትርያርክነት ያገለገለባቸው ዘመናት ፴፪ [32] ዓመታት ሲሆኑ ከእነዚህ ዓመታት ፳፰ [28] ቱ ያለቁት በስደትና በመከራ ነው::

እግዚአብሔር የአባቶቻችን ስደት አስቦ ከነፍስ ስደት ይሰውረን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

🕊

[ † ሰኔ ፳፰ [ 28 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ዻዻሳት
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ
፫. ቅዱስ ባስልዮስ
፬. ቅዱስ ባሊዲስ

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. አማኑኤል ቸር አምላካችን
፪. ቅዱሳን አበው [አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ]
፫. ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
፬. ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
፭. ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ [ሰማዕት]

" ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና:: " [ማቴ.፭፥፲] (5:10)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
2024/09/29 07:18:55
Back to Top
HTML Embed Code: