Telegram Web Link
እንኩዋን ለሐዲስ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ

=>ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር:: በተለይ ተንባላቱ ግብፅና ሶርያን ከያዙ በሁዋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር:: ቅዱስ ጊዮርጊስ (ልብ በሉልኝ ሊቀ ሰማዕታት አይደለም) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር::

+እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር:: ስሙንም መዛሕዝም ይሉታል:: ሕጻኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም:: የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር:: በዚሕ ምክንያት ሳይጠመቅ 7 ዓመት ሞላው::

+እናቱ ግን ሕጻን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር:: ባይጠመቅም ጸበሉን: እመቱን ትቀባው ነበር:: ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር:: አንድ ቀን ግን ሕጻናት ሲቆርቡ አይቶ ካልቆረብኩ ብሎ አለቀሰ:: ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው:: "ጌታየ! ልጄን እርዳው" አለች::

+ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ:: ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት:: "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል" አለችው::
ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር::

+አስቀድሞ ትምሕርተ ክርስትናን ተማረ:: ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ:: ጥቂት ጊዜ ከቆየ በሁዋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት:: "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ" አለችው:: ከግብፅ ተነስቶ ሶርያ ገባ:: አባቶችን አፈላልጎ ተጠመቀ:: ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ::

+ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ" ቢላቸው #መንፈስ_ቅዱስ አናግሯቸው "#ጊዮርጊስ" አሉት:: እሱም ደስ እያለው: ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ:: ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው:: ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብፅ ተመለሰ::

+በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም: ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ:: ዕለቱኑ አሠሩት:: ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው አሉት:- "አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ:: ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር: ለእኛም ሞገስ ነው" ብለውም አጽናኑት:: (እንዲሕ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው!!!)

+ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት: አካሉን ቆራረጡት: ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት:: በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት:: እርሱ ግን #ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ:: ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ" አለው::

+በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት:: ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት:: ወደ ባሕርም ጣሉት:: እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር:: በዚሕች ቀን እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል::

=>ቸሩ አምላክ ከሰማዕቱ ጽናትን: ትእግስትን: ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

=>ሰኔ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ ሰማዕት
2.አባ ብሶይ አኖብ ሰማዕት (በአንበሳ ጀርባ ላይ የተቀመጠ አባት)
3.ቅዱሳን "5ቱ" ጭፍሮች (በብዙ ስቃይ ሰማዕት የሆኑ ባልንጀሮች)
4.አባቶቻችን የደብረ ቁዋዐት ጻድቃን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

=>+"+ ስለዚሕ #ወንድሞቼ_ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና:: +"+ (1ቆሮ. 10:14-18)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Forwarded from Bketa @¥
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
✞✞✞🌹 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ 🌹✞✞✞

🌹 እንኳን አደረሳችሁ 🌹

🌹 ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት🌹

=>ትናንት ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ወረደ:: ፊልዽስዩስ በምትባል ሃገር በዼጥሮስ እጅ
የመጀመሪያዋን ቤተ_ክርስቲያን አነጸ ብለን ነበር:: በዚህች ዕለት ደግሞ አእላፍ
መላዕክትን: ሰማያውያን ቅዱሳንን እና እናቱን ቅድስት
ድንግል
ማርያምን ይዟት ወረደ::

+ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዛው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን
ከቅዳሴው በፊት 2 ነገሮችን አሳየ:-
1.አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ
ሥርዓተ ቤተ ክርረስቲያንን አሳየ::
2.ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ_ዼጥሮስን ከመካከል አቁሞ "አርሳይሮስ" ሲል ሾመው:: ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት
(ፓትርያርክ) ማለት ነው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት
"አክዮስ" እያሉ 3 ጊዜ አሰምተው ጮሁ:: አክዮስ ማለት በግዕዙ
"ይደልዎ": በዐማርኛው ደግሞ "ይገባዋል: ያሥምርለት"
እንደ
ማለት ነው::

+ጌታችን ይሕን ከከወነ በኋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ::
¤አማናዊት ማሕደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ:
¤ቅዱስ ዼጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ:
¤ቅዱስ_እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ሆኖ:
¤ሐዋርያት ድንግልን ከበው:
¤መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቁመው ጌታችን ቀድሶ
ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ::

+በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር
የማይችል ደስታ ተደረገ:: ከቅዳሴ በኋላ ጌታችን
ሐዋርያትን
አዘዛቸው::
"ከዚህ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም
አብያተ ክርስቲያናትን እነጹ:: ይህችን ዕለት የሚያከብራትን
አከብረዋለሁ::" ብሏቸው ከድንግል እናቱ ከመላዕክቱ ጋር
ዐረገ::

+"+ ሰኔ_ጐልጐታ +"+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ
ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ
እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም
ያመኑትን
"ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሸሹ" ብሎ መከራቸው::
+ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ
መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ
መሸተኛዋ ሴት
እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት
ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል
ሰይፍ
አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

+እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ
(መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ
ቶማስ ነገሩን
ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ
ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል
ዝም
አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና
"ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን
ጠብቆ ሊያነሳ
ሲል እጁ ሰለለች::

+ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም
እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ
ግን ሕዝቡ
ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን
አምጡልኝ" አለ:: የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል . . .
የገደልኩሽ
እኔ: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው . . . ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው::

+እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች::
ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

=>ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

=>ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
8.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘምስር (ሰማዕት)
9.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ዻዻሳት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ አበው ጎርጎርዮሳት
2፡ አባ ምዕመነ ድንግል
3፡ አባ ዓምደ ሥላሴ
4፡ አባ አሮን ሶርያዊ
5፡ አባ መርትያኖስ
6፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል

=>+"+ ስለ ጽዮን ዝም አልልም . . .
አሕዛብም ጽድቅሽን: ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ::
የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም
ትጠሪያለሽ::
በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ
የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ:: +"+ (ኢሳ. 62:1-3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

""ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን""::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

[ † እንኳን ለቅዱሱ አባታችን የዋህ ዻውሊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  †  ቅዱስ ዻውሎስ የዋህ  †  🕊

† በ፬ [ 4 ] ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ግብፅ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ቅዱሱ ስሙ ዻውሎስ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚጠራው "የዋህ ዻውሊ" በሚል ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

የዋህ ዻውሊ ከሕጻንነቱ ጀምሮ መጻሕፍትን የተማረ: ግን ደግሞ ትዕቢት: ቁጣና ቂምን የማያውቅ ገራገር ሰው ነው:: እድሜው ለአካለ መጠን ሲደርስ ቤተሰቦቹ ሚስት አግባ አሉት:: እርሱ ባያስብበትም ወገኖቹን ላለማሳዘን አገባ:: እንዳለመታደል ሆኖ ግን ያገባት ሴት በጣም ቆንጆ በዚያም ላይ ክፉ ነበረች:: የዋህ ዻውሊ ክፋቷን ሁሉ ታግሶ ለበርካታ ዓመታት አብሮ ኖረ:: ልጆችንም አፈሩ::

አሁንም ግን እርሷ ከክፋቷ ልትታገስ አልቻለችም:: ይባስ ብሎ ዻውሊ በሌለበት ከሌሎች ወንዶች ጋር ትዘሙት ያዘች:: የዋሁ ሰው ይሕንኑ ያውቃል ግን የእግዚአብሔርን ሥራ ዝም ብሎ በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ለነገሩስ እሱ ያርሳል: ይቆፍራል: ነዳያንን ያበላል: እንግዳ ይቀበላል እንጂ ክፋትን ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም::

አንድ ቀን ግን ለሥራ ወደ በርሃ ወጥቶ አንድ ግሩም ዜና ሰማ:: "አባ እንጦንስ ምንኩስና የሚባል ሕይወተ መላእክትን ጀምሯል: ደቀ መዛሙርትንም ይቀበላል" አሉት:: ግን ሚስትና ልጆች አሉትና ምን ያደርጋል?

የዋህ ዻውሊ ሙሉ ቀን ሢሠራ ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን የጠበቀው ሌላ ነው:: ሚስቱ በራሱ መኝታ ላይ ከአገልጋይ እረኛው ጋር ራቁታቸውን አገኛቸው:: ልብ በሉልኝ በትክሻው ሞፈርና ምሳር: መጥረቢያም ይዟል:: እርሱ ግን ክፉን አላሰበም:: ጥሩ ልብስ አንስቶ ሁለቱንም አለበሳቸው:: እንዲሕም አላቸው:- "ከዚሕ በሁዋላ እኔ አልመለስም:: ሀብት ንብረቴን ውረሱ: በደስታም ኑሩ:: የልጆቼን ነገር ግን አደራ" ብሏቸው ተነሳ::

በእጁ ምንም አልያዘም:: በትከሻው ያለችውን ብጣሽ ጨርቅ ይዞ ወደ በርሀ ተጉዋዘ:: አባ እንጦንስም ተቀብለው አስተምረው አመነኮሱት:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ራስን ዝቅ በማድረግ: በመታዘዝ አገለገለ:: ጾም: ጸሎትና ስግደቱንማ ማን ቆጥሮት::

እያለ እያለ ከብቅዐት ማዕርግ ደረሰ:: ምዕመናንም ሆነ መነኮሳት ሊጠይቁት ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይመለከት ነበርና ስለነሱ ሲያለቅስ ቅንድቡ ተላጠ:: ሰውነቱም አለቀ:: አንድ ቀን ጋኔን የያዘውን ሰው ፈውስ ብለው አመጡለት:: እርሱ ግን በአጋንንት ላይ ሥልጣን እያለው በትሕትና ተጠግቶ ጋኔኑን "አባ እንጦንስን ከምጠራብህ ቀስ ብለህ ውጣ" አለው:: ጋኔኑ ግን የፈራው መስሎት በትዕቢት "እንጦንስ ማነው?" አለው::

ያን ጊዜ የዋህ ዻውሊ እንደ እሳት ከጋለ ድንጋይ ላይ ቁሞ "ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው:: ይሕ ጋኔን ካልወጣ አልወርድም" አለ:: ወዲያው በዘንዶ አምሳል ከሴትዮዋ ወጥቶ እየጮኸ ወደ ቀይ ባሕር ገባ:: ቅዱስ ዻውሊ የዋሕም እንዲሕ በቅድስና ተመላልሶ በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

" የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር: ደስታ: ሰላም: ትእግስት: ቸርነት: በጐነት: እምነት: የውሃት: ራስን መግዛት ነው:: እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም:: የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ::" [ገላ.፭፥፳፪] (5:22)

🕊

[ † ሰኔ ፳፪ [ 22 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ አባ ዻውሊ የዋሕ
፪. ቅዱሳን ወክቡራን ቆዝሞስና ድምያኖስ [ ሰማዕታት ]
፫. ቅድስት ቴዎዳዳ ሰማዕት [ እናታቸው ]
፬. አንቲቆስ: ዮንዲኖስና አብራንዮስ [ ሰማዕታት ]

[ †  ወርኀዊ በዓላት ]

፩. ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
፫. ቅዱስ ደቅስዮስ [ የእመቤታችን ወዳጅ ]
፬. አባ እንጦንዮስ [ አበ መነኮሳት ]

[ † አምላካችን ከቅዱስ ዻውሊ የውሃትን: ትእግስትን : በጐነትን : ጸጋ በረከትን ይክፈለን:: አሜን:: † ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
🕊

✞   የሰኔ ፳፫ [ 23 ]   ✞

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ  ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

🕊 † ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል †  🕊

መፍቀሬ ጥበብ :

¤ ጠቢበ ጠቢባን:
¤ ንጉሠ እሥራኤል:
¤ ነቢየ ጽድቅ:
¤ መስተሣልም [ ሰላማዊ ]  . . . እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትና የቅድስት ቤርሳቤህ [ቤትስባ] ልጅ ነው:: ከ ፫ [3] ሺ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ ፲፪ [12] ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጉዋል::

ቅዱስ ዳዊት ፸ [70] ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም:: እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በ፲፪ [12] ዓመቱ ነገሠ:: ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው::

"ልጄ ሆይ ! ልብህን ስጠኝ:: ፈጣሪህንም አምልክ" አለው::

ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ:: ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን: ልቡናን ለመነ:: በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ: ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት: ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም: አይኖርም" ብሎት ተሠወረ:: ቅዱስ ሰሎሞን ለ፵ [40] ዓመታት በእሥራኤል ላይ ነገሠ::

ግሩም በሆነ ፍትሑ: በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት:: እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ ንግስተ ሳባ /አዜብ/ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን [እብነ መለክን] ጸነሰች:: በኋላም ታቦተ ጽዮንና ሥርዓተ ኦሪት መጣልን:: ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን ድንግል ማርያም ከእነሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር::

ነገር ግን :-

¤ አንደኛ ሰው [ሥጋ ለባሽ] ነውና:
¤ ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ እመ ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር:: ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ
[ከፈርዖን ልጅ] ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው:: እግዚአብሔር እጅግ አዘነ::

በራዕይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም" አለው:: ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ:: ማቅ ለብሶ: አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ:: ንስሃ ገባ:: መፍቀሬ ንስሃ ጌታችንም ንስሃውን ተቀበለው::

የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን ፭ [5] መጻሕፍት ገለጠለት:: ተናገራቸው:: ጻፋቸው:: እሊሕም :-

፩. መጽሐፈ ጥበብ
፪. መጽሐፈ ተግሣጽ
፫. መጽሐፈ መክብብ
፬. መጽሐፈ ምሳሌ
፭. መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው::

ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን ቤተ መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል:: ደጉ ንጉሥ: ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በ፶፪ [52] ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል::

🕊  †   አባ ኖብ    †    🕊

ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ሰማዕት አባ ኖብ አርፏል:: በዚሕ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ቢኖሩም ዋናው ይኼው ቅዱስ ነው::

አባ ኖብ እንደ ገዳማውያን በበርሃ የተጋደለ: እንደ ሊቃውንት መጻሕፍትን ያመሰጠረ: በተለይ ደግሞ በዘመነ ሰማዕታት ጭንቅ ጭንቅ መከራዎችን የተቀበለ አባት ነው:: ስለ ገድሉ ብዛት "ኃያል ሰማዕት": አንገቱን ስላልተቆረጠም "ሰማዕት ዘእንበለ ደም" ይባላል:: ዘመነ ሰማዕታትን ካለፉ ፸፪ [72] ቱ ከዋክብትም አንዱ ነው::

ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን: ከኃያሉ ሰማዕት አባ ኖብ በረከትን አምላካችን ይክፈለን::

🕊

[ †  ሰኔ ፳፫ [ 23 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን [ንጉሠ እሥራኤል]
፪. ቅዱስ አባ ኖብ [ሰማዕት ወጻድቅ]
፫. ቅዱሳን መርቆሬዎስ: ፊልዾስና ቶማስ [ሰማዕታት]

[ †  ወርኃዊ በዓላት ]

፩ ፡ ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ
፪ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
፫ ፡ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
፬ ፡ አባ ሳሙኤል
፭ ፡ አባ ስምዖን
፮ ፡ አባ ገብርኤል
፯ ፡ ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ

" የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ: ፀሐይ: ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ: ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ:: ሰባኪው :- "ከንቱ: ከንቱ: ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል::" [መክ.፲፪፥፩-፱]  (12:1-9)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ባሕራን)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ከዘመነ ጸደይ ወደ ዘመነ ክረምት መሸጋገሪያ ለሆነችው ዕለትና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

=>ስንዱ እመቤት ቤተ ክርስቲያን (ሃገራችን) ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ትጠቀማለች:: እሊሕም ዘመናት መጸው (ጽጌ): ሐጋይ (በጋ): ጸደይ (በልግ)ና ክረምት ናቸው:: ዘመናቱ ወቅቶችን ከመለየትና ማሳወቅ ባሻገር የእኛ ሕይወትም ምሳሌዎች ናቸውና ልብ ልንላቸው ይገባል::

+በተለይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና "ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ" ብሎናልና (ማቴ. 24:20) ልንጸልይ ይገባናል:: በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሣናፈራ ሞት እንዳይመጣ: አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኩዋንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና እንደ ሊቃውንት እንዲህ ብለን እንጸልይ:-

"በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ:
እንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ:
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ::"
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ:
ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን:
አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን)

=>ቸሩ አምላካችን ከዘመነ መጸው በሰላም ያድርሰን:: ተረፈ ዘመኑንም የንስሃ: የፍሬና የበረከት ያድርግልን::

=>በዚሕች ዕለት እነዚህ ቅዱሳን ይከበራሉ:-

+" ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ "+

+በዘመነ ሐዋርያት ይሁዳ ተብለው ይጠሩ ከነበሩት አንዱ የሆነው ቅዱሱ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ ሲሆን እናቱ ማርያም ትባል ነበር:: እናቱ ስትሞትበት ተጎድቶ የነበረ ቢሆንም ገና በልጅነቱ ድንግል ማርያም አግኝታው በፍጹም ጸጋ አሳድጋዋለች:: አስተዳደጉም ከጌታችን ጋር በአንድ ቤት ነበር::
ጌታችን እርሱንና ወንድሞቹን (ያዕቆብና ስምዖንን) ከ72ቱ አርድእት ቆጥሯቸዋል:: ቅዱስ ይሁዳ ወንጌል ላይ ከጌታችን ጋር መነጋገሩን ዮሐንስ ወንጌላዊ መዝግቧል:: (ዮሐ. 14:22)

+ቅዱስ ይሁዳ ከጌታችን እግር 3 ዓመት ተምሮ: መንፈስ ቅዱስንም ተቀብሎ ብዙ አሕጉራትን ዙሯል:: አይሁድንም አረማውያንንም ወደ ክርስቶስ ይመልስ ዘንድ ብዙ ድካምና ስቃይን በአኮቴት ተቀብሏል:: አንዲት አጭር (ባለ አንድ ምዕራፍ) መልእክትም ጽፏል:: አጭር ትምሰል እንጂ ምሥጢሯ እጅግ የሠፋ ነው:: ቅዱስ ይሁዳን በዚህች ቀን አረማውያን ገድለውት በሐዋርያነቱ ላይ የሰማዕትነትን ካባ ደርቧል::

+" ቅዱሳን ዺላጦስና አብሮቅላ "+

=>ብዙዎቻችን መስፍኑን ዺላጦስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌታችን እንዳይሰቀል ከአይሁድ ጋር ሲከራከር እናውቀዋለን:: የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ ነበርና አይሁድ እንቢ ሲሉት የክርስቶስን ንጽሕና መስክሮ: እጁንም ታጥቦ ሰጥቷቸዋል:: የዺላጦስ ታሪክ ግን እዚህ ላይ አያበቃም::

+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በሁዋላ ትንሳኤውን በራዕይ ገልጦለት አይሁድን ተከራክሯቸዋል:: ውሸታም ወታደሮችንም ቀጥቷል:: በመጨረሻ ግን በሮም ቄሳር ተጠርቶ ከእሥራኤል እስከ ሮም ድረስ ሰብኮ በሮም አደባባይ አንገቱ ተሠይፏል::

+ቅድስት እናታችን አብሮቅላም የዺላጦስ ሚስት ስትሆን ቁጥሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ነው:: ጌታችንን ተከትላ: ቤቷን ለሐዋርያት አስረክባ: ቤተ ክርስቲያንንም በዘመኗ አገልግላ ዐርፏለች:: ዛሬ ሁለቱም ቅዱሳን ይታሠባሉ::

=>ጌታችን ከሐዋርያው ይሁዳ: ከዺላጦስና አብሮቅላም ጸጋ በረከትን ያድለን::

=>ሰኔ 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ይሁዳ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
2.ሰማዕቱ ዺላጦስ መስፍን
3.ቅድስት አብሮቅላ (ሚስቱ)
4.አባ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት
5.የጸደይ መውጫ / የክረምትመግቢያ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ /አባ ቡላ/
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

=>+"+ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ:
ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ::
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:1)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
2024/09/29 05:21:07
Back to Top
HTML Embed Code: