Telegram Web Link
#አንቺ_ሴት_ከአንቺ_ጋር_ምን_አለኝ?

Deacon Henok Haile

ልጅ እናቱን ‹አንቺ ሴት› ብሎ መጥራት በእኛ ሀገር ባሕልና በብዙ ቋንቋዎች ባሕል ፈጽሞ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ በተለይ በአደባባይ ሲሆን ይከብዳል:: ጌታ እናቱን ካልጠፋ ስም ለምን እንዲህ ብሎ ጠራት?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚዳኘው በተጻፈበት ቋንቋ (Source language) እንጂ በተተረጎመበት ቋንቋ ባሕል አይደለም፡፡ ይህ አነጋገር በአይሁድ ዘንድ እና የዮሐንስ ወንጌል ላይ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ የሚሠጠው ትርጉም በእኛ ዘንድ ካለው ትርጉም የተለየ ነው፡፡

በግሪኩ ‹‹አንቺ ሴት›› (gune = woman") ተብሎ የሚጻፍ ሲሆን ጌታችን እመቤታችንን ‹‹አንቺ ሴት›› ብሎ በጠራበት ሥፍራ ግን በግሪኩ ‹አንቺ ሴት› የሚለው ንባብ የተጻፈው ‹አንቺ ሴት ሆይ› (gynai "Dear woman") በሚል የአክብሮት አጻጻፍ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገር ደግሞ ነገሥታት ለንግሥቶቻቸው በሚጽፉአቸው ደብዳቤዎችም ላይ ጭምር ይጻፍ የነበረ እንደሆነ የቋንቋው ባለቤቶች የሆኑት ግሪካውያን አገናዝበው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ አውግስጦስ የተባለው ንጉሥ ለግብፃዊቷ ንግሥት ለክሊዮፓትራ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመው ቃል የግሪኩን ‹gynai› /ጋይናይ /አንቺ ሴት ሆይ/ የሚለውን የአክብሮት አጠራር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ጌታችን በቃና ሰርግ ቤት ‹አንቺ ሴት› ብሎ የተናገረው ንግግር የቁጣ አነጋገር ነው የሚሉ ሰዎችን ሃሳብ እንዳንቀበል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር ለእናቱ የተናገረው በቃና ሰርግ ቤት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር ቆማ መከራውን እያየች በጽኑ ኀዘን ላይ እያለች ‹‹አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ›› በማለት ዮሐንስን ለእርስዋ እርስዋን ለዮሐንስ ሠጥቷል፡፡

በልጅና በእናት መካከል ባለው ሥነ ልቡናዊ ትስስር ምክንያት ለእናት የልጅዋን ስቃይ ቆሞ መመልከት እጅግ ከባድ ስቃይን ያስከትልባታል፡፡ እመቤታችን እያንዳንዱ ችንካር በተወደደ ልጅዋ እጅ ውስጥ ሲቸነከር ልብዋ በኀዘን ይቸነከር ነበር፡፡ ታዲያ ‹አንቺ ሴት› የሚለው አነጋገር የቁጣ አነጋገር ከሆነ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ‹በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ እያለፈባት› ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል?

በሰርግ ቤት ውስጥስ ስለጠየቀችው ተቆጣ ይባል ፤ በመስቀል ሥር የልጅዋን ስቃይ በዝምታ ስትመለከት የነበረችን እናት ልጅዋ በስቃዩ መካከል ትንፋሹን ሰብስቦ ‹‹ተቆጣት›› ብሎ ሊነገር እንዴት ይችላል? በስተግራው የተሰቀለው ወንበዴ ‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህም› ብሎ ሲሰድበው መልስ ያልሠጠ ‹ከቁጣ የራቀ› አምላክ በእርሱ ስቃይ እየተሰቃየች ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል? (ሉቃ. ፳፫፥፴፱) ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ከእናቱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ‹እናቴ› ብሎ በመጥራት ወይም ‹ማርያም› በማለት ፈንታ ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር መጠቀሙ እመቤታችን በኦሪት ዘፍጥረት በተጠራችበት ስም ለመጥራት እና እርስዋ ትንቢት የተነገረላት ዳግሚት ሔዋን ፣ ጌታችንም የዕባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘርዋ መሆኑን የሚያስረዳን ነው፡፡

በሊቃውንት ዘንድ የወንጌል መቅድም (Protevangelium / Protogospel) ወይም ‹የመጀመሪያው የነገረ ሥጋዌ ትንቢት› በመባል የሚታወቀው ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።›› የሚለው ትንቢት በእርስዋ መፈጸሙን ከምንረዳበት መንገድ አንዱ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› ብሎ በመጥራቱ ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፭)

በዕለተ አርብ በዕባብ የተመሰለው ዲያቢሎስ የጌታችንን ‹ሰኮና› በአይሁድ አድሮ ሲቀጠቅጥ ዋለ፡፡ ‹ዘርዋ› የተባለው ጌታም የዕባቡን ራስ እንዲሁ በመስቀሉ ቀጠቀጠው፡፡ በዚህ ወቅት እናቱን ደግሞ ‹አንቺ ሴት› ብሎ ጠራትና በትንቢቱ ላይ ያለችው ‹ሴቲቱ› እርስዋ መሆንዋን አስረዳን፡፡
የጻፈውን መተርጎም ልማዱ የሆነው ዮሐንስም ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ በሚያደርግ ሁኔታ የሴቲቱን ፣ የልጅዋን እና የቀደመውን ዕባብ ማንነት በአንድ ምእራፍ ላይ አብራርቶ በራእዩ ጽፎልናል፡፡ ‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። ... ዘንዶውም (እርሱም የቀደመው ዕባብ) በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ›› በማለት የዘፍጥረቱን ትንቢት በመተርጎም ሴቲቱ በእርግጥም ‹አሕዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ የወለደችው› እመቤታችን መሆንዋን አስረድቶአል፡፡ (መዝ. ፪፥፱) ስለዚህ ጌታ ‹አንቺ ሴት› ማለቱ ጾታን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን እመቤታችን የትንቢቱ ፍጻሜ መሆንዋን የሚያስረዳ የክብር አነጋገር ነው፡፡ (ራእ. ፲፪፥፩-፲፰)

እንዲሁም ለአዳም ሔዋን በተሠጠችው ጊዜ ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።›› ማለቱ (ዘፍ. ፪፥፳፫) ሴት የሚለውን ቃል ትርጉም ጾታን ከመግለጽ በላይ ‹ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽም ከአጥንቴ› የሚል የእኔነት ትርጉም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ የመጀመሪያው አዳም ከጎኑ ሔዋንን ያስገኘ ሲሆን ሁለተኛው አዳም ግን ከሁለተኛዋ ሔዋን የተገኘ ነው፡፡ ሆኖም ሁለተኛው አዳምም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ የሁላችንን እናት ጥምቀትን (ቤተ ክርስቲያንን) አስገኝቷል፡፡

- ከአንቺ ጋር ምን አለኝ

‹‹ከአንተ / ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ስድስት ቦታ ፣ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በአምስት ቦታዎች ተጽፎ የምናገኘው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ዐረፍተ ነገር በየተጻፈባቸው አገባቦች (contexts) ሁለት ዓይነት ትርጉም የሚሠጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው አገባብ አለመግባባትን የሚገልጽ አነጋገር ሲሆን ፤ ሁለተኛው አገባብ ደግሞ አክብሮትን ወይም ሰላም ጠያቂነትን የሚያሳይ አነጋገር ነው፡፡

አለመስማማትን የሚያሳይ የተግሣጽ ንግግር ሆኖ የምናገኘው በነቢዩ ኤልሳዕ ታሪክ ነው፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መፍትሔ ለመጠየቅ መጥቶ ነበር፡፡ ኢዮራም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አድርጎ ስለነበር ኤልሳዕ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ›› ብሎ መልሶለት ነበር፡፡ ኢዮራም ኤልሳዕን ለማነጋገር ሲሞክርም ኤልሳዕ በቁጣው ጸንቶ ‹‹አብሮህ ያለውን የይሁዳን ንጉሥ ባላፍር ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር፡፡›› ብሎታል፡፡ (፪ነገሥ. ፫፥፲፫)

በዚህ ታሪክ ውስጥ በግልጽ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል ‹ከአንተ ጋር ምን ኅብረት አለኝ?› በሚል አገባብ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይም እግዚአብሔር የጢሮስ ፣ የሲዶናና የፍልስጤም ግዛትን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ስላደረሱት በደል እንደሚፋረዳቸው በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ፈጥኜ ብድራታችሁን በእናንተው ላይ እመልሳለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህም ስፍራ እንዲሁ ይህ አነጋገር ከቁጣ ጋር ተነግሮ ይገኛል፡፡ (ኢዮ. ፫፥፬)
ሁለተኛው አገባብ ደግሞ ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ትርጉም የሚሠጠው አገባብ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ለእርሱ የተቆረቆሩ የጽሩያ ልጆች የሰደበውን ሳሚን ‹እንምታው ፣ እንግደለው› ሲሉ ‹‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?›› ብሎ ከልክሎአቸዋል፡፡ (፪ሳሙ. ፲፮፥፲) ተሳዳቢው ሳሚ መጥቶ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቅም ዳግመኛ ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት ይገባዋል›› አሉ፡፡

ይህን ጊዜ ዳዊት ‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን?›› (፪ሳሙ. ፲፱፥፳፪)
በእነዚህ የንጉሡ ንግግሮች ውስጥ ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል በአክብሮት የተነገረ ባይሆንም መልእክቱ ግን ‹ምን ጠብ አለኝ› ማለት መሆኑን ከአገባቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ምናልባት የመጨረሻው አገባብ ቁጣ ያዘለ ቢመስልም እንኳን እየተናገረ ያለው ለእርሱ ከእርሱ በላይ ለተቆረቆሩት ታማኝ ወታደሮቹ ጋር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ እርሱም ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› ያለውን ‹ለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ?› ብሎ በማብራራት የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ ‹ከእናንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› እንደሆነ አሳይቶአል፡፡

ሌላው ማሳያ ደግሞ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ ንግግር ነው፡፡ ኒካዑ ካልተዋጋሁህ ብሎ ለመጣበት ለኢዮስያስ ፡- ‹‹የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት።›› (፪ዜና ፴፭፥፳፩) ይህ አነጋገር በትሕትና እና ‹ሆይ› በሚል የአክብሮት አጠራር የቀረበ ነው፡፡ በግልጽ ‹ልዋጋ የተነሣሁት ከሌላ ጋር ነው ፤ ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝና ነው የምዋጋው!› ነው ያለው፡፡ በእውነቱ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ማለት ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ማለት መሆኑን ለማስረዳት ከዚህም የተሻለና ግልጽ ታሪክ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢዮስያስ የተነሣው ለጠብ ነው፡፡ ኒካዑም በአክብሮት የነገረው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ብሎ ነው፡፡

እንደተጨማሪ ማሳያ የምናገኘው ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስን በቤትዋ የተቀበለችው የሰራፕታዋ መበለት የተናገረችው ነው፡፡ ይህች ሴት ኤልያስ በቤትዋ በመገኘቱ በቤትዋ ያለው ምግብ ተባርኮ በረሃብ ዘመን እየተመገቡ ከከረሙ በኋላ ልጅዋ በጠና ታመመ፡፡ ይህን ጊዜ ሴቲቱ ወደ ኤልያስ ቀርባ ፡-

‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።›› (፩ነገሥ.፲፯፥፲፰)
ይህች ሴት ለነቢዩ በአክብሮት ያለችው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ነው፡፡ የቁጣና የተግሣፅ ንግግር ነው እንዳይባል መቼም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ...›› ብሎ የሚጀምር ቁጣ የለም፡፡ እንዲያውም በአንድ ሰው ስንቆጣ ማዕረጉን ትተን እንናገራለን እንጂ ማዕረግ ጠብቆ ቁጣ የለም፡፡

ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለውን ቃል የተናገሩት ዛሬ በወዳጆቻቸው አድረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ማለት ስድብ ነው› እያሉ የሚበጠብጡን አጋንንት ናቸው፡፡ ከአዋቂ ጋር እንደ አዋቂ ፤ ካላዋቂ ጋር እንደ አላዋቂ ሆኖ ማደናቆር የአጋንንት ልማድ ነውና እነሱ በሚገባ ትርጉሙን ተረድተው እየተንቀጠቀጡ ለጌታ የተናገሩትን የአክብሮት አነጋገር ለእመቤታችን ሲሆን ትርጉሙ ሌላ ነው እያሉ ያውካሉ፡፡

‹‹እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።›› (ማቴ. ፰፥፳፱)

‹‹እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።›› (ማር. ፩፥፳፬)

‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤›› (ማር. ፭፥፯)

‹‹ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ።›› (ሉቃ. ፬፥፴፬)

‹‹ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ›› (ሉቃ. ፰፥፳፰)

ምንም እንኳን አጋንንትን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ክብር ባንሠጣቸውም ‹የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው› እንዲል (ትምህርተ ኅቡዓት/ትር.) የአጋንንቱ ንግግር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ› የሚለው ቃል በአክብሮት ሊነገር የሚችል ‹ምን ጠብ አለኝ› የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡

ምክንያቱም ‹ከአንተ ጋር ምን አለን› ከማለታቸው ጋር ‹ኢየሱስ ሆይ ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሱ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ‹እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ› የሚል ልመና ተከተለ፡፡ ልመናውም ከእግሩ ሥር እስከ መደፋት ድረስ የደረሰ ነበር፡፡ መቼም ከእግር ሥር ተደፍቶ የቁጣ ንግግር መናገር የማይታሰብ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ባየነው የአገባብ ዝርዝር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ለሚለው ንግግር የሚያመዝነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል ነው፡፡ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ጌታችን ለእናቱ የተናገረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገርም ከአገባቡ እንደምንረዳው ሌሎች ስለ እርሱ በፍርሃት የተናገሩትን የአክብሮት የተነገረ ሲሆን ትርጉሙም ‹የጠየቅሽኝን እንዳላደርግልሽ የሚከለከለኝ ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳን መልሱ የእምቢታ ቢሆን ኖሮ አንደኛ እመቤታችን ልመናዋን ቀጥላ ‹እባክህን ልጄ ሆይ› ብላ ለማሳመን ትሞክር ይሆናል እንጂ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ ለአገልጋዮቹ በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝነት ትእዛዝ ልትሠጥ አትችልም ነበር፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ጌታችን ከዚያ በኋላ ጋኖቹን ሙሉ ብሎ ተአምራቱን አያደርግም ነበር፡፡ እንዲያውም ጌታችን ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም› ያላት በቁጣና በእንቢታ ከሆነ ለአገልጋዮቹ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ መናገርዋ የበለጠ ቁጣውን የሚያነድ ነበር የሚሆነው፡፡ ለእርስዋ እንቢ እያላት ቁጣውን ከምንም ሳትቆጥር ሌሎች ሰዎችን ማዘዝዋ የበለጠ አያስቆጣም ወይ ሊባል ይችላል? ይህ ሁሉ የሚያሳየን ጌታችን አንዳች የቁጣ ንግግር አለመናገሩን ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስም የጌታችን መልስ የጠብ ሳይሆን እንዲያውም የጥልቅ ፍቅር መሆኑን ሲገልጽ ‹‹በልቡ ውስጥ ለተከማቸ ፍቅሯ በሚሻል /በሚመጥን/ ነገር መለሰላት›› ‹‹ወአውስኣ ዘከመ ይኄይስ ለዘዝጉብ ፍቅረ ዚኣሃ ውስተ ልቡ›› ብሏል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር) ስለዚህ ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ› የሚለውን ንግግር የቁጣ ንግግር አድርጎ መተርጎም ጥቅሱን ከአገባቡ የወጣ ጥቅስ (Text out of context) ያደርገዋል፡

+ ጌታችን እናቱን ተቆጥቷት ይሆንን? +
የቃና ሰርግ ቤት ታሪክ ለጊዜው እናቆየውና አንድ ልጅ በአደባባይ በሰዎች ፊት እናቱን በምንም ምክንያት ቢቆጣ እንኳን ከሃይማኖት አንጻር ከሥነ ምግባርም አንጻር የሚደገፍ ሥራ አይደለም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ‹እናቱን በቁጣ ተናገራት› የሚለው አስተሳሰብም እንዲሁ ብዙ የሚያመጣው ጣጣ አለ፡፡

‹‹እናትና አባትህን አክብር›› ‹‹እናቱን የሰደበ ይሙት›› የሚለውን ሕግ የሠራ አምላክ ‹እኔን ምሰሉ› እያለ ለሰው ልጆች አርኣያ ሊሆን በመጣበት በዚህ ዓለም ራሱ እናቱን በአደባባይ በሰው ፊት ያቃልላታል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድና ለብዙ ሰዎች የኃጢአትን በር ወለል አድርጎ ከፍቶ መረን የሚለቅ ነው፡፡ (ዘጸ. ፳፥፲፪ ፣ ፳፩፥ )
እመቤታችንን የጎዱ መስሏቸው ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለው የሚሰብኩ ሰዎችም ሳያውቁት እየተናገሩ ያሉት በእመቤታችን ላይ ሳይሆን በራሱ በጌታችን ላይ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?›› ብሎ የተናገረ ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፮) ‹የሚጤስን የጧፍ ክር የማያጠፋ ፣ የተቀጠቀጠ ሸንበቆን የማይሰብር› በአነጋገሩ ጭምት ነው፡፡ ስንክሳሩም ‹‹ወንድሜ ምእመን ሆይ ጌታችን ለንጽሕት እናቱ ለድንግል ማርያም ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለቱ የክብርት እናቱን ቃል እንዳቃለለ አታስብ›› ይላል፡፡ (ስንክ. ጥር ፲፪ ቁ. ፵)
በማስከተልም ‹‹ጌታችን የሰማያዊውና የመለኮታዊ አባቱን ክብር እንደጠበቀ ይታወቅ ዘንድ እንዲሁ ከእርስዋ ፍጹም ሥጋንና ፍጽምት ነፍስን ነሥቶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደውን የእናቱን ክብር ጠበቀ፡፡ በወንጌል ይታዘዛትና ይላላካት ነበር ተብሎ እንደተጻፈ›› ይላል፡፡ (ስንክ.ጥር ፲፪ ቁ. ፵፪)

በእርግጥም ጌታችን የባሕርይ አባቱን አብን ክብር እንደጠበቀ በራሱ አንደበት ‹‹አባቴን አከብራለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፱) ለእመቤታችንና ለአሳዳጊው ዮሴፍም እንዲሁ ‹‹ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩) እመቤታችን በቃና ዘገሊላ ስለ ወይኑ የነገረችውም የልጅዋን መታዘዝ በልብዋ ትጠብቀው ስለነበር እና እንደሚታዘዛት ታስብ ስለነበር ነው፡፡

እስቲ ነገሩን ሌሎች ከሚያዩበት ማዕዘን ለመመልከት እንሞክር፡፡ እውነት ግን ጌታችን እናቱን ሊቆጣ የሚችልበት ምን ምክንያት ነበረው? ከላይ እንደተመለከትነው የለመነችው ስለ ራስዋ ጥቅም አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ልመናዋ ከሚያስፈልግ ነገር ውጪ ይደረግ የተባለ አላስፈላጊ የቅንጦት ልመና አይደለም፡፡ በሰርግ ቤት ሙሽሮችን ለዕድሜ ልክ ውርደት ሊዳርግ የሚችል የወይን ጠጅ እጥረት በተከሰተበት ሰዓት ‹ወይን እኮ የላቸውም› ብሎ ማመልከት እንኳን በሩኅሩኁ አምላክ ፊት ይቅርና በእኛ በጨካኞቹ የሰው ልጆች ፊት እንኳን ሊያስቆጣ የሚችል ነገር አይደለም፡፡
የለመነችው እንደ አይሁድ ምልክት ለማየት ጓጉታ አይደለም፡፡ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃውያን ‹አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ትሠራለህ?› ‹ከሰማይ ምልክት ልናይ እንወዳለን› የሚል የፈተና ጥያቄ አልጠየቀችም፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፩ ፤ዮሐ. ፮፥፳) ተአምር የማየት ምኞት አድሮበት እንደጠየቀው እንደ ሄሮድስም በአጋጣሚው ልጠቀምና ተአምር ልይ ብላም አይደለም፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፰) ደግሞስ ያለ ወንድ ዘር በማኅጸንዋ አድሮ በታተመ ድንግልና ሲወለድ ያየች እናት ሌላ ምን ተአምር ሊያስደንቃት ይችላል?

የሰርጋቸው ቀን የኀዘናቸው ቀን ሊሆን ስለተቃረበ ሙሽሮች ተጨንቃ መለመንዋ እንዴት የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል? ያለጊዜው ስለለመነችውና ስለቸኮለች ተቆጣት እንዳንል ልመናዋን ትንሽ ብታዘገየው ኖሮ ነገሩ ይፋ እየሆነ ፣ ሙሽሮቹ መዋረዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ የደረሰችው በሰዓቱ ነው፡፡

የጌታችን አሠራር እንዲህ አልነበረም፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ አማት በንዳድ በታመመች ጊዜ እንዲፈውሳት ሲለምኑት እሺ ብሎ ንዳዱን ገሥፆ አላቀቃት፡፡ (ሉቃ.፬፥፴፱) የአንድ መቶ አለቃ ልጅ በታመመ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎች ሊያማልዱ በመቶ አለቃው ተልከው መጡ፡፡ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑን በማሰብም ‹‹ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።›› የመቶ አለቃውንም ልጅ በመጨረሻ ፈወሰው፡፡ (ሉቃ. ፯፥፪-፮) እነዚህ ሰዎች ተአምር እንዲያደርግ ሲጠይቁት እሺ ያለ ጌታ እናቱ ስትለምነው ይቆጣል ብለን እንዴት እንቀበል? የአይሁድን ሽማግሌዎች እንኳን ያልተቆጣውን ጌታ በምን አንደበታችን እናቱን ተቆጣ ልንለው ይቻለናል?
ከሁሉ በላይ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን›› እንዳለው በረከሰ አንደበታችን ፣ በሚወላውል ልባችን ፣ በሚባክን ሃሳባችን ወደ እርሱ የምንጸልየውን የእኛን የኃጢአተኞቹን ጸሎት ለምን ጸለያችሁ ብሎ ያልከለከለ አምላክ ንጽሕት እናቱ በፍጹም ትሕትና ለለመነችው ልመና የቁጣ ምላሽ ሠጠ ማለት እንዴት እንደፍራለን? ዳዊት ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ›› ብሏል፡፡ እርሱ በልቡ በደል ስለሌለ ጌታ ከሰማው በሃሳብዋ ድንግል የሆነች እናቱን እንዴት አልሰማትም እንላለን? (መዝ. ፷፮፥፲፱-፳)

እመቤታችን የጠየቀችው ይህን ያህል የማይጠየቅ ነገር ነው እንዴ? የመንግሥትህን እኩሌታ ፣ የሥልጣንህን ፈንታ ሥጠኝ አላለችውም፡፡ የጠየቀችው ስለ ድሆቹ ሙሽሮች ነው፡፡ እኛ በረባ ባልረባው ስንዘበዝበው የምንውለውና የምናድረው ታጋሽ አምላክ ለእናቱ ለእኛ የሠጠውን ነገር ይነሣል ማለት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ‹አብን አሳየንና ይበቃናል› ፤ ‹እሳት ከሰማይ ወርዶ ሕዝቡን ያጥፋቸው› ፤ ‹በግራ ቀኝህ አስቀምጠን› የሚሉ ደቀ መዛሙርትን ታግሶ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ያስከተለ ጌታ ቅድስት እናቱ ተገቢ ልመና በተገቢ ሰዓት ስትለምነው ሊቆጣ አይችልም፡፡

እንደ ወንጌሉ ብቻ ከሔድን ደግሞ እመቤታችን ከዚህ በፊትና በኋላ ምንም ነገር ስትለምነው አልተጻፈም፡፡ በወንጌል ለተጻፈው ለዚህ ብቸኛ ልመናዋም መልሱ ቁጣ ነው ብለን አምነን መቀመጥ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ፈጽሞ የሚዋጥልን ሃሳብ አይደለም፡፡ በልጅነትዋ ወልዳው ለተሰደደችው ፣ በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ ላለፈባት እናቱ አንዴ ብትለምነው ተቆጣ ብለን እንዴት እንናገራለን?

ጌታችን በዚህ ሰርግ ቤት እንኳንስ እንዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚተረጉመው ‹ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግሮ ቀርቶ ፤ ለእናቱ የተናገረው በቀጥታና በግልፅ የቁጣ ንግግር ቢሆን ኖሮ እንኳን ጾመን ጸልየን ፣ ወድቀን ተነሥተን ምሥጢራዊ ትርጉሙን እንፈልጋለን እንጂ ሰማይና ምድር ቢነዋወጥ ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለን አናምንም!!!

ከዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ፌስቡክ ወሰድኩት
(ከቃና ዘገሊላ መጽሐፍ)
ጥር 2013 ዓ ም
"የክርስቶስን አካል ልታከብሩት ትወዳላችሁን? መልሳችሁ አዎ ከሆነ ራቁቱን ሆኖ እያያችሁት አትለፉት፣ በየመንገዱ ራቁቱን ሆኖ በብርድ እየተሰቃየ አለና፤ ራቁቱን ሆኖ በብርድ እየተሰቃየ አልፋችሁት መጥታችሁ እዚህ ከቤተ መቅደስ በብርና በወርቅ ላስጊጥህ አትበሉት፡፡ "ይህ ሥጋዬ ነው" ብሎ የተናገረው ክርስቶስ ራሱ "ተርቤ አይታችሁኝ አላበላችሁኝም" ያለው እንዲሁም "ከእነዚህ ከታናናሾች ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችት ለእኔ አደረጋችሁት" ያለውም ያው እርሱ ራሱ ነውና፡፡ ወንድምህ በረሃብ እየተሰቃየና እየሞተ ቅዱስ ደሙ የሚቀዳበት ጽዋ በወርቅ ቢለበጥና ቢንቆጠቆጥ ጥቅሙ ምን ላይ ነው? አስቀድመህ የወንድምህን ረሃብ በማጥገብና ጥሙን በማርካት ጀመር፤ ከዚያ በኋላ በተረፈህ ገንዘብ ቤተ መቅደሱንና ንዋያተ ቅድሳትን እንዲህ ማስጌጥ ትችላለህ፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
እንኩዋን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ ዘርዓ ቡሩክ እና 7ቱ ደቂቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

አቡነ ዘርዓ ቡሩክ

=>ሃገራችን ኢትዮዽያ:-
*ብሉይ ከሐዲስ ያልጐደለባት
*በክርስቶስና በድንግል እናቱ ኪደተ እግር የተቀደሰች
*የቅዱሳን መጠጊያ እና
*ብዙ ቅዱሳንን ከእቅፏ ያፈራች ስለ ሆነች የተባረከች ሃገር ትባላለች::

+ሁሉም የሃገራችን ክፍሎች ቅዱሳንን አፍርተዋል:: በምሥራቅም: በምዕራብም: በሰሜንም: በደቡብም ያሉ አካባቢዎች ሁሉ የቅዱሳን ቤቶች ናቸው:: ቅዱሳንን በብዛት ካፈሩ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ምድረ ጐጃም ነው::

+በጐጃም አካባቢ ከተነሱ ቅዱሳን ደግሞ አንዱና ስመ ጥሩ ጻድቅ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ናቸው:: አቡነ ዘርዓ ቡሩክ በብዙ ጐዳና የተለዩ አባት ናቸው:: ለመጥቀስ ያህል እንኩዋ:-

1.በታሪክ ዓለምን ከበው የያዙ 2ቱ ግሩማን አራዊት (ብሔሞትና ሌዋታንን) ጥርስ ቆጥረው: ብዙ ምሥጢራትንም ተመልክተው ተመልሰዋል:: (በነገራችሁ ላይ ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳይንሱ በብዙ ድካም ያልደረሰበት ነው)
2.ጻድቁ በልደታቸው ጊዜ ዓይነ ስውራንን አብርተዋል:: ለራሳቸው ግን ይህን የግፍ ዓለም ላለማየት ጸልየው ዓይናቸው እንዲጠፋ አድርገዋል::
3.መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ቅዱስ ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቁሟል:: ዘርዓ ቡሩክ ግን በጥበበ እግዚአብሔር ፀሐይን ለ5 ዓመት አቁመዋል::
4.ጻድቁ ከንጽሕናቸው ብዛት 12 ክንፍ (መንፈሳዊ ክንፍ) ተሰጥቷቸው ነበር:: ከዚህ በተረፈም በጾም: በጸሎት: በትርምትና በስብከተ ወንጌል ፍጹም ጽሙድ ነበሩ::

+ጻድቁ የተወለዱት በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን እዚያው ጐጃም ውስጥ ሲሆን አባታቸው ደመ ክርስቶስ: እናታቸው ደግሞ ማርያም ሞገሳ ይባላሉ:: ወላጆች በልጅ እጦት ተማለው ይህን የተቀደሰ ፍሬ አገኙ:: "ጸጋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ከኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷቸዋልና::

+ቀጥሎ የወለዱትንም "ተስፋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ይህም የጻድቁ ታናሽ ወንድም ነው:: በሒደት ግን የጸጋ ኢየሱስ ስም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ዘርዓ ቡሩክነት ተቀይሯል:: ጻድቁን ስመ ጥር ካደረጉዋቸው ሥራዎቻቸው መካከል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የሠሩት ቅድሚያውን ይወስዳል::

+ነገሩ እንዲህ ነው:: በ1598 ዓ/ም በኢትዮዽያ ላይ የነገሡት አፄ ሱስንዮስ ዼጥሮስ ፓኤዝ (ፔድሮ ፓኤዝ) ከሚባል ፈረንጅ መናፍቅ ጋር በፈጠሩት ወዳጅነት ሃይማኖታቸውን ለወጡ:: ካቶሊክ (ሮማዊ)ም ሆኑ::

+በሁዋላም አልፎንሱ ሜንዴዝ የሚሉት እሾህ መጥቶ ሁሉም የኢትዮዽያ ሕዝብ መናፍቅ እንዲሆን ከንጉሡ ጋር መከረ:: ለጊዜው በቤተ መንግስቱ አካባቢ የነበሩ መሣፍንት ተቀላቀሉ:: እየቆየ ግን ዜናው በመላ ሃገሪቱ ተሰማ::

+በተለይ በ1611 በተዋሕዶ አማኞችና በመናፍቁ ንጉሥ መካከል ነገሩ ተካሮ ዻዻሱ አቡነ ስምዖን ጠዳ ላይ መገደላቸው ተሰማ:: በዚህ ጊዜ ገበሬው ከእርሻው: ሴቷ ከማዕድ ቤት: ካህኑ ከመቅደሱ: ነጋዴው ከገበያው እየወጡ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ደማቸውን አፈሰሱ::

+በበዓት የተወሰኑ በሺህ የሚቆጠሩ ቅዱሳንም ወጥተው ተሰየፉ:: በዚህ ጊዜም የግሺው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዳዊታቸውን አንግበው ለሰማዕትነት ሔዱ:: ዓባይ ወንዝ ላይ ሲደርሱ ዳዊታቸውን ወደ ወንዙ ውስጥ ጣሉት::

+ተሻግረውም ከንጉሡ አደባባይ ደንቀዝ ደረሱ:: በጊዜውም ልክ እንደነ ፍቅርተ ክርስቶስና ወለተ ዼጥሮስ እርሳቸውም መከራ ደረሰባቸው:: ንጉሡም ሳይገደሉ እንዲታሠሩ አደረገ:: በጨለማ እስር ቤትም 5 ዓመታትን ሲያሳልፉ ትኩስ ምግብን ያመጡላቸው ነበር::

+እርሳቸው ግን ምግባቸው ሰማያዊ ነበርና አልነኩትም:: ከ5 ዓመት በሁዋላም ያ ሁሉ ምግብ በተአምራት በትኩስነቱ እየጨሰ ተገኝቷል:: ዘርዓ ቡሩክም ከእሥር ተፈትተዋል::
+እግዚአብሔርም በከሐዲው ንጉሥ ላይ ፈርዶ ፋሲል ነግሷል: ሃይማኖት ተመልሷል:: ጻድቁም በዓባይ ወንዝ ላይ የጣሉት ዳዊታቸውን ሳይርስ አግኝተውታል::

+ጐጃም ሲደርሱም ሰይጣን እርሳቸውን መስሎ ሲያስት ስላገኙት ወደ ጥልቁ አስጥመውታል:: በተረፈ ዘመናቸው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ብዙ ተጋድለው ጥር 13 ቀን ዐርፈዋል:: ታኅሳስ 13 ቀን ልደታቸው ነው::

<< ድንቅ ሠሪ አባት ናቸውና ዛሬም በግሺ ብዙ ተአምራት ይደረጋሉ >>

+" ቅዱሳን 7ቱ ደቂቅ "+

=>እነዚህ 7 ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: 7ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::

+በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም: ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር: በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::

+ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ: ለጣዖትም ያልሰገደ: ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ: እጅ እግሩ ለእስር: ደረቱ ለጦር: አንገቱ ለሰይፍ: ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::

+የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ 7ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::

+ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ዳኬዎስ ወጣ::

+ከመውጣቱ በፊት ግን 7ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::

+ዓለምን ንቀው: ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው: ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር (በጐች አሉት) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::

+አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ 7ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::

+ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::

+ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ372 ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::
+በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን 400 ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::+በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት: ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል:: ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህቺ ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው:: እርሱም "አዎ ናት" ብሎት አለፈ::

+ችግሩ ግን "ራት ልግዛ" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ: እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር:: በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ዘንድ ቀረበ:: (ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው:: የነገሠውም በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው)

+በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም: ሊቀ ዻዻሱም (አባ ቴዎድሮስ ይባላል) ተገረሙ:: አብረው ከከተማ ወጥተው ሔደው: 7ቱንም ሲጸልዩ አገኟቸው:: ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር:: 7ቱም ለ7 ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ: ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ::

+ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሳኤ ሙታን የለም" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነሱ ምሥክር ሊሆንባቸው ነው:: በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃየማኖት ተመልሰዋል:: 7ቱ ቅዱሳን ግን በ7ኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል:: ንጉሡ 7 የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል::

=>አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::
ጥር 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮዽያዊ (እረፍታቸው)
2.ሰባቱ ደቂቅ ቅዱሳን (ከኤፌሶን)
3.ቅዱስ አባ ነካሮ
4.ቅዱስ ቃሮስ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
3.ቅዱስ አስከናፍር
4."13 ግኁሳን ጻድቃን"
5.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ
6.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት

=>+"+ በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ:: ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል:: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር: የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+ (2ቆሮ. 13:12)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Audio
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር አሥራ ሦስት(፲፫)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
õ-3 Eñ5 )K¤ ØÈ- %-
ASR by NLL APPS
ድርሳን ዘቅዱስ ሩፋኤል ዘወርሃ ጥር https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
††† እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ †††

††† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:-
1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ:
2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
3.ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች:: አቡነ አረጋዊና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::

*ዸንጠሌዎን በጾማዕት:
*ገሪማ በመደራ:
*ሊቃኖስ በቆናጽል:
*አባ ይምዓታ በገርዓልታ:
*ጽሕማ በጸድያ:
*ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
*አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ (እዛው ትግራይ) ሆነ::

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው:: ጻድቁ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ:: የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው::

ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው:: ወላጆቻቸው "ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል:: በኢትዮዽያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ::

በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል:: ከመነኮሱ ከዓመታት በሁዋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር 7 ያህል የቤተ መንግስት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል::

"የት ልሒድ" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮዽያን አሳያቸው:: ተመልሰውም ለ8 ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየሁዋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር" ብለው ከ8ቱ ጋር ወደ ኢትዮዽያ መጡ::

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ:: ወደ ሃገራችን የመጡ በ470ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል:: በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ: ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል::

ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል:: በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን (ደብረ ሃሌ ሉያን) አይተው ወደዷት:: የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ 60 ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል::

እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ: ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል:: በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች:: ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በሁዋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው 6ሺ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል::

ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮዽያ - የኢትዮዽያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል::

ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ:: በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግስት እድና ሁናለች::

ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል:: ጌታም 15 ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው::

††† አባ አርከሌድስ †††

††† በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን በግብጽም በሃገራችንም አሉ:: ዋናውና በብዙ መጻሕፍት ዜናቸው የተጻፈላቸው ግን ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: አባ አርከሌድስ የነበሩት በዘመነ ጻድቃን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ናት::

ወላጆቻቸው ክርስቲያን: በዚያውም ላይ ባለ ጠጐች ነበሩ:: አባታቸው ደግሞ መስፍነ ሃገር ነበር:: ቅዱሱን ወልደው: በሕግ በሥርዓት አሳድገዋል:: ለአካለ መጠን አባ አርከሌድስ ሲደርሱ ግን አባታቸው ሞተ::

መዋዕለ ሐዘናቸው ከተፈጸመ በሁዋላም እናት አባ አርከሌድስን ጠርታ:- "ልጄ! ሒድና የአባትህን ሹመት እጅ አድርግ" አለችው:: ለመንገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሰናድታ: አገልጋዮችንና ብዙ ወርቅ (ለሿሚው አካል የሚሰጥ) ጨምራም ልጇን ሸኘች::

ቅዱስ አርከሌድስም ከእናታቸው ተለይተው በአገልጋዮች ተከበው ወደ መርከብ ገቡ:: በባሕር መካከል ሳሉ ግን ታላቅ ማዕበል ተነስቶ መርከቡን በታተነው:: በመርከቡ የነበረው ሰው ሁሉ ሲያልቅ አባ አርከሌድስ ግን በስባሪ ላይ ተንጠልጥለው ተረፉ::
ዋኝተው ወጥተው ወደ ዳርቻ ሲደርሱም ማዕበል የተፋው አንድ በድን ወድቆ ተመልክተው ፈጸመው አለቀሱ:: ወዲያውም በልባቸው የዚህን ዓለም ኃላፊነት አሰቡ:: ሹመት ፍለጋ መሔዳቸውን ትተው ወደ ገዳም ሔዱ::ወደ ምድረ ሶርያ ደርሰው በታላቁ ደብረ ሮማኖስ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበሉ:: በእጃቸው የነበረውን 200 ዲናር ወርቅም ለገዳሙ አበረከቱ:: ለጥቂት ጊዜ በገዳሙ ካገለገሉ በሁዋላም ጾማዕት (በዓት) ተሰጣቸው::

በዚህ ጊዜም "እንግዲህ ወደ ዓለም አልወጣም:: የሴቶችን መልክም አልመለከትም" ሲሉ ቃል ገቡ:: በተጋድሏቸውም በጾምና በጸሎት: በትጋሃ ሌሊት ለ12 ዓመታት ቀጠሉ:: ጾማቸውም 7 ቀን ነበር:: አምላክ ጸጋውን ስላበዛላቸውም ብዙ ድውያንን ፈወሱ::

ዜናቸውም እስከ ምድረ ሮሜ ተሰማ:: እናታቸው (ሰንደሊቃ) የመርከቡን ዜና ከሰማች በሁዋላ የሞቱ መስሏት አልቅሳ ቤቷን የእንግዳ ቤት አድርጋ: በበጎ ምግባር ትኖር ነበርና አንድ ቀን የልጇን ዜና ሕይወት ሰማች::

ከደስታዋ የተነሳ ፈጥና ወደ ደብረ ሮማኖስ ደርሳ "ልጄን ልይ" አለች:: ግን "ሴትን አላይም" ብለው አባ አርከሌድስ ቃል ገብተዋልና ምን ይሁን! ሰንደሊቃም "አራዊት ይብሉኝ እንጂ ልጄን ሳላይ አልሔድም" አለች:: ወዲያው ግን "አባ አርከሌድስ ፈቅደዋልና ግቢ" የሚል መልእክት መጥቶላት ገባች::

ግን ያገኘችው የጻድቁን ልጇን ሥጋ ነበር:: ምክንያቱም የፈጣሪንም: የእናታቸውንም ልብ ላለማሳዘን እንዲወስዳቸው ለምነውት ዐርፈው ነበር:: እናትም በልጇ ሥጋ ላይ እያለቀሰች እዚያው ዐረፈች:: "አብራችሁ ቅበሩን" የሚል ቃል ከቅዱሱ ሥጋ ስለ ተሰማም አብረው ቀብረዋቸዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን ለእነርሱ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

††† ጥር 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ አባ መክሲሞስ
3.ቅዱስ አባ አርከሌድስ
4.ቅድስት እምራይስ
5.ቅድስት ምሕራኤል
6."4034"ሰማዕታት (ማሕበራነ ቅዱስ ቂርቆስ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ስምዖን
2.አባ ዮሐንስ
3.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ (ሙሽራው)
4.ቅዱስ ሙሴ
5.ቅዱስ ፊልዾስ (ከ72 አርድዕት)
6.ቅድስት ነሣሒት

††† "እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. 36:28)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Encoderbot file id3171102 16k
ስንክሳር ዘወርሃ ጥር አሥራ አራት(፲፬)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
          አሜን
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


📌 ስንክሳር ዘወርኀ ጥር ፲፭

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር ዐሥራ አምስት በዚች ቀን ዕውነተኛ ነብይ አብድዩ አረፈ።
       
❖ ይህም ነብይ የሐናንያ ልጅ ነው፤ በንጉሥ ኢዮሳፍጥም ዘመን ትንቢት ተናገረ እግዚአብሔርም ስለ ትንሣኤና ስለ ፍርድ ቀን በቃሉ ነገረው።
❖ ይህም ንጉሥ አካዝያስ ይጠሩት ዘንድ ወደ ኤልያስ ከላካቸው ሦስተኛ መስፍን ነው፤ ከእርሱ አስቀድመው የመጡ እነዚያን ሁለት መስፍኖች በኤልያስ ቃል እሳት ከሰማይ ወርዳ ከእነርሳቸው ጋር ካሉ ወታደሮች ጋር በላቻቸው።
❖ ይህ ግን ወደ ኤልያስ በመጣ ጊዜ በፊቱ ተንበርክኮ ሰግዶ ተገዛለት እንዲህም አለው የእግዚአብሔር ሰው ተገዛሁልህ የእሊህ የባሮችህ ሰውነትና የኔ ሰውነት በፊትህ ትክበር በእግዚአብሔር ነቢይ ላይ ፈጽሞ አልታበየምና ነቢዩ ኤልያስም ራራለት ወርዶም ከርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ሔደ።
❖ ይህም አብድዩ ከምድራዊ ንጉሥ አገልግሎት የኤልያስ አገልገሎት እንደምትበልጥ የኤልያስም አገልገሎት ለሰማያዊ ንጉሥ አገልገሎት ታደርሳለችና ይህን በልቡ ዐወቀ ስለዚህ ምድራውያን ነገሥታትን ማገልገል ትቶ ነቢይ ኤልያስን ተከተሎ አገለገለው በላዩም ከእግዚአብሔር ሀብተ ትንቢት አደረበትና ትንቢትን የሚናገር ሆነ የትንቢቱም ወራት ሃያ ዓመት ነው ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በዘጠኝ መቶ ዓመት በሰላም በፍቅር አንድነትም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ነቢያት ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✍️ በዚችም ቀን ዳግመኛ በሶርያ አገር ያሉ የክርስቲያን ወገኖች የቅዱስ ጎርጎርዮስን የዕረፍቱን መታሰቢያ በዓል ያከብራሉ፤ ይህም አባት በነፍስ በሥጋ በበጎ ሥራ ሁሉ ከወላጆቹ ጋር ፍጹም ነው።
❖ እርሱ እግዚአብሔርን መፍራትንና ትምህርቶችን ተምሮ ዐውቋልና የቋንቋም ትምህርት እጅግ የሚያውቅ የዮናናውያንንም ቋንቋ የሚያነብና የሚተረጒም ለቀና ሃይማኖትም የሚቀና ሆነ በውስጡም በጎ ሥራ በጎ ጠባይ ተፈጸመለት ኑሲስ በምትባል አገርም ላይ ሳይወድ በግድ መርጠው ኤጲስቆጶስነት ሾሙት እርሷም ደሴት ናት የእግዚአብሔርንም መንጋዎች ጠበቀ በትምህርቱና በድርሰቶቹም ልቡናቸውን ብሩህ አደረገ የብሉያትንና የሐዲሳትንም መጻሕፍት ተረጐመ።
❖ ጳጳስ ሁኖ ስለነበረው ስለ ከሀዲው መቅዶንዮስ በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን በቊስጥንጥንያ ከተማ የመቶ ሃምሳ ኤጲስቆጶሳት የአንድነት ስብሰባ በሆነ ጊዜ ይህ ጎርጎርዮስ ከአባቶች ኤጲስቆጶሳት ጋር ሁኖ የሰባልዮስን ወገኖች መቅዶንዮስንና አቡሊናርዮስን ተከራከራቸው መልስ አሳጥቶም አሳፈራቸው ስሕተታቸውንም ገለጠ።
❖ ይህም የካቲት አንድ ቀን ተጽፎአል የእነዚህንም ክህደት አስወገደ በቃሉ ሰይፍነትም የንባባቸውን የስሕተት ሐረግ ቆራርጦ አጠፋ ከተሰበሰቡትም ጋር በሰላም ተመለሰ እነርሱ በድል አድራጊነት እነዚያም ከሀድያን በኀፍረት ሁነው ተመለሱ ።
❖ ወደ መልካም እርጅና ደርሶ እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ አገልገሎ በሰላም አረፈ እነሆ በዚህ ወር ጥር ሃያ አንድ ቀን ከገድሉ ጥቂት ጽፈናል ይኸውም በግብጻውያን ዕረፍቱ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 ዳግመኛም በዚህች ዕለት የከበረ ሕፃን የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበርተኞች የሆኑ አራት ሺህ ሠላሳ አራት ሰዎች በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ ዜና ገድላቸው ከአባታቸው ከሕፃኑ ከቅዱስ ቂርቆስ ዕረፍት ጋር ጥር 15 እንጽፈዋለን፡፡
❖ የእጅግ የከበረ የቅዱስ ዱማቴዎስ ወንድም ቅዱስ መክሲሞስም ዕረፍቱ በዚሁ ዕለት ነው ነገር ግን ገድሉን በዚሁ ወር በ17 ከወንድሙ ታሪክ ጋር እንጽፈዋለን፡፡

📌 ጥር 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
2.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
3.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
4.ቅድስት ሶፍያ
5.ቅድስት አድምራ
6."11,004" ሰማዕታት (ከቅ/ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ)

📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
2.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
3.ቅድስት ክርስጢና
4.ቅድስት እንባ መሪና
ክርስቶስ ማን ነው?
  √ ቅድመ ዓለም የነበረ የአብ ልጅ ነው።
  √ ከድንግል ማርያም የተወለደ ፍጹም ሰው ነው።
  √ ፍጹም አምላክ ነው
  √ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ነው።
  √ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው።
  √ አዳምን ለማዳን ሥጋን የተዋሐደ ነው።
  √ ቤዛችን፣ መድኃኒታችን፣ ጌታችን ነው።
  √ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው።
  √ ክርስቶስ ንጉሠ ነገሥት፣ አምላክ ነው
  √ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነ ነው። ሰው የሆነ አምላክ፣ አምላክ የሆነ ሰው ነው። አምላክም ሰውም ነው።

በቅዱሳት መጻሕፍት ራሱ ስለራሱ የነገረን ይህንና የመሳሰለውን ነው። ሁልጊዜም እኛን ለማዳን ስለኛ ቤዛ ሆኖ በመስቀል የተሰቀለልንን ጌታ እናስበዋለን። መመኪያችን፣ ደስታችን፣ ሕይወታችን እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

(መምህር በትረማርያም አበባው)
2024/09/30 20:31:35
Back to Top
HTML Embed Code: