Telegram Web Link
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለኃያል ሰማዕት "ማር ቴዎድሮስ" እና "ቅዱስ አንያኖስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ ቅዱስ ቴዎድሮስ ማር ሰማዕት +"+

=>በቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት አለቅነት ከተሰጣቸው ሰማዕታት አንዱ የሆነው ማር ቴዎድሮስ የተወለደው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) በ3ኛው መቶ ክ/ዘ ነው:: አባቱ ዮሐንስ በትውልድ ግብጻዊ የሆነ ክርስቲያን ነው:: እናቱ ግን አስቸጋሪና ጣዖት አምላኪ ሶርያዊት ነበረች::

+ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት ባሏ ክርስቲያን መሆኑን አታውቅም ነበር:: ቴዎድሮስ (የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው) በተወለደ ጊዜ ግን ጠብ ተነሳ:: እሱ ክርስትና ለማስነሳት: ሚስት ደግሞ ወደ ጣዖት ቤት ለመውሰድ ተጋጩ:: ሚስት ወገኖቿ ባለስልጣኖች ናቸውና ልጁን ቀምታ ባሏን ዮሐንስን ወደ ግብፅ አሳደደችው::

+ዮሐንስ በስደት ባለበት ሃገር ስለ ልጁ ፈጽሞ ይጸልይ: ያለቅስም ገባ:: እግዚአብሔር ደግሞ ልመናውን ሰማ:: ማር ቴዎድሮስ ወጣት በሆነ ጊዜ ማንም ሳይጠራው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዶ ተማረ: ተጠመቀ:: ዕለት ዕለትም ጾምና ጸሎትን ከምጽዋት ጋር ያበዛ: ድንግልናውን ለመጠበቅ ይተጋ ነበር::

+በዛው ልክ ደግሞ ገና በ20 ዓመቱ በጉልበቱ ኃያል: በውበቱም ደመ ግቡ: በጠባዩም ገራገር ነበርና ተወዳጅ ነበር:: ነገሥታቱም የአንጾኪያ የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ሾሙት:: እነሆ እስከ ዛሬ "የሠራዊት አለቃ" ተብሎ ይጠራል::

+ማር ቴዎድሮስ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም:: ይልቁኑ የነገሥታቱን (የጠላት) ልጆች በመማረክ ነው የሚታወቀው:: እንዲያውም አንድ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በተደረገ ጦርነት ብቻውን አሸንፏቸዋል::

+የፋርስ ሰዎች ሊዋጉ ሲመጡ መልአክ ከሰማይ ወርዶ ሰይፍ ሰጠው:: ፋርሶችን "በከንቱ ከምትጠፉ ወደ ሃገራችሁ ተመለሱ" አላቸው:: እነርሱ ግን ተሳለቁበት:: ከፈረሱ ወርዶ ወደ ምስራቅ ዙሮ ጸልዮ በመስቀል አማተበ:: በመካከላቸው ገብቶም በመልአኩ ሰይፍ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀር አጠፋቸው::

+አንድ ቀን ወደ አንድ ከተማ ቢገባ ዘንዶ ሲመለክ አገኘ:: ይባስ ብሎ የአንዲት ክርስቲያን ልጆችን ለመስዋዕትነት ሲያቀርበቧቸው ተመለከተ:: በስመ ሥላሴ አማትቦ: በፈረሱ ላይም ተቀምጦ ዘንዶውን በጦር ገደለው:: የዘንዶውም ርዝመት 24 ክንድ ነበር::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ስለ አባቱ ወሬ ሰምቶ: ካለበት ሥፍራ አፈላልጎ አግኝቶ ደስ አሰኘው:: እስኪያርፍ አብሮት ቆይቶ: ቀብሮት ወደ አንጾኪያ ሲመለስ ግን የሚያሳዝን ነገር ጠበቀው::

+ክርስቶስ ተክዶ: ጣዖት ቁሞ: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው: የክርስቲያኖች ደም ፈሶ: ከተማዋ በግፍ ተሞልታ ተመለከተ:: እርሱም በዚያች ሰዓት መወሰን ነበረበትና አደረገው:: የሁሉ ሠራዊት አለቃ ቢሆንም የክብር ልብሱን አውልቆ: ባጭር ታጥቆ በንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ፊት ቆመ::

+ማር ቴዎድሮስ በአደባባይ እንዲህ ተናገረ:- "አንሰ አመልኮ ለክርስቶስ ንጉሠ ስብሐት በኩሉ ልብየ: ወእሠውዕ ሎቱ - እኔስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በፍጹም ልቤ አመልከዋለሁ: ለእርሱም ብቻ እሠዋለሁ::" ንጉሡ በቁጣ መሬት ላይ ጥለው እንዲደበድቡት አዘዘ:: ወታደሮቹ ደሙ እስኪንጠፈጠፍ ገረፉት::

+በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃይተው በእሳት አቃጠሉት:: እርሱ ግን በጸሎቱ እሳቱን ውሃ አደረገው:: ወታደሮቹ እርሱን በብዙ አሰቃዩ:: እርሱ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ጸና: ታገሠ::

+በመጨረሻም ጌታችን በግርማ ወርዶ "ወዳጄ ቴዎድሮስ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ገድልህን (ዜናህን) የጻፈ: ያጻፈ: ያነበበ: ገዝቶ በቤቱ ውስጥ ያኖረውን ሁሉ
እምርልሃለሁ" አለው::

+በስሙም ረድኤት እንደሚደረግ ነግሮት ዐረገ:: ወታደሮቹም በዚህ ቀን አንገቱን ሰይፈው የክብር አክሊልን ተቀብሏል:: እጅግ ብዙ ሺህ ሰዎችም አብረውት ተሰይፈዋል::

+"+ ቅዱስ አንያኖስ ዘግብጽ +"+

=>ይህ ቅዱስ አባት ውለታው ከፍ ያለ ነውና በምድረ ግብጽ እጅግ ይከበራል:: በተለይ ክርስትናን ከሐዋርያት ተቀብሎ ለምዕመናን ያስረከበ አባት በመሆኑ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ወንጌላዊው ሐዋርያ ቅዱስ ማርቆስ በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ተመድቦ: በፈቃደ እግዚአብሔር ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ በ50ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ወደ ምድረ ግብጽ ወረደ::

+እስክንድርያ ከተማ በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ እንደ መኖሯም መጀመሪያ ወደ እርሷ ደረሰ:: ልክ ወደ ከተማ ሲገባ ገና አንደበቱ ለወንጌል ሳይከፈት እንቅፋት መትቶት ጫማው ተበጠሰ:: ያን ሁሉ በርሃ የቻለች ጫማ በእንቅፋት በመበጠሷ እያዘነ ወደ ጫማ ሰፊ ዘንድ ደርሶ "ሥራልኝ?" ይለዋል::

+ይህ ጫማ ሰፊ አንያኖስ (አንያኑ) ይባላል:: ጣዖት አምላኪ: ግን ደግሞ ቅንና ገር የሆነ ሰው ነበር:: "እሺ" ብሎ ሲሰፋለት መሳፈቻው (መስፊያው) ስቶ መሐል እጣቱን ስለ ወጋው "ኢታስታኦስ (አታኦስ)" ብሎ ጮኸ:: ትርጉሙም "አንድ አምላክ" ማለት ነበር::

+ይህንን የሰማው ቅዱስ ማርቆስ ቀና ብሎ "ጌታየ ሆይ! ጐዳናየን ስላቀናህልኝ አመሰግንሃለሁ!" ብሎ: ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ የአንያኖስን እጅ ቀባው::

+ወዲያውም ደሙ ቁሞ: ቁስሉም ድኖ እንደ ነበረው ሆነ:: በዚህ ተአምር ድንጋጤም: ደስታም ቢሰማው "ማነህ አንተ?" ሲል ቅዱሱን ጠየቀው:: ወንጌላዊውም መልሶ "እኔ የክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ" አለው::

+አንያኖስም "እባክህ ወደ ቤቴ እንሒድ" ብሎ ሐዋርያውን ጋበዘው::
እቤት ሲደርሱም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር አስተናግደውት የሕይወትን ቃል ለመኑት:: ቅዱስ ማርቆስም ከስነ ፍጥረት እስከ ጌታችን የማዳን ሥራ አስተምሯቸው አመኑ:: አጥምቆ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው::

+ይህቺው የቅዱስ አንያኖስ ቤትም በምድረ ግብጽ የመጀመሪያዋ ጉባኤ ቤትና ቤተ ክርስቲያን ሆነች:: ቅዱሱ ሐዋርያ በ60 ዓ/ም አካባቢ በቅዱስ አንያኑ ቤት ሆኖ በርካቶችን አሳመነ:: በሰማዕትነት ከማረፉ በፊትም ቅዱስ አንያኖስን የምድረ ግብጽ ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት (ፓትርያርክ) አድርጐ ሾመው::

+ቅዱስ አንያኖስም ለ12 ዓመታት የክርስቶስን መንጋ እያበዛ ተጋደለ:: ከሐዋርያው የተቀበለውን ንጹሕ ዘር ዘራ:: የድኅነት የምሥራቹንም አዳረሰ:: ይሔው ይህ መልካም ተክል ዛሬም ድረስ ሳይጠወልግ አለ::

+የአሁኑ ፓትርያርክ አቡነ ታውድሮስም ከቅዱስ ማርቆስ 118ኛ ሲሆኑ ከቅዱስ አንያኖስ 117ኛ ናቸው:: ቅዱሱ ለእኛ ኢትዮዽያውያንም የክህነት አባታችን ነው:: ይህች ቀንም ዕለተ ዕረፍቱ ናት::

=>አምላከ ቅዱሳን ክፉውን አርቆ ከበጐው ዘመን ያድርሰን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

=>ኅዳር 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ማር ቴዎድሮስ ኃያል ሰማዕት
2.ቅዱስ አንያኖስ (አንያኑ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1..ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

=>+"+ በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኩዋ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: +"+ (1ዼጥ. 3:13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Encoderbot file id2583639 16k
ስንክሳር ዘወርሃ ህዳር ሃያ (፳)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Forwarded from Adanech
Forwarded from Sintu.D
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን።

ኀዳር ጽዮን የእመቤታችን ዓመታዊ ክብረ በዓል ነዉ ብለን በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት ታቦተ ጽዮን በምርኮ ከሀገረ ፍልስጤም ዳጎን የተባለ የአሕዛብ ጣዖትን አድቅቃ በድል የተመለሰችበት እለት በማሰብ
እንዲሁም ታቦተ ጽዮን ንጉሡ ሰለሞን ወደ ሰራላት ቤተ መቅደስ በክብር የገባችበትን እለት በማሰብ ነዉ ።
...
ቀዳማዊ ሚኒሊክ ከአስራሁለቱ ነገደ እስራኤል የበኩር ልጅ ጋር  ሊቀ ካህናቱን አዛርያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበትን እለት በማሰብ የምናከብረዉ ታላቅ በዓል ነው
እንኳን አደረሰን መልካም በዓል 💚💛
✞✞✞ እንኩዋን ለጽዮን "ማርያም ማሕደረ አምላክ" እና ለቅዱሳኑ "ጐርጐርዮስ ወዮሐንስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*"+ ጽዮን ማርያም +"*+

=>"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው:: አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው:: ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም: ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል::

+እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በሁዋላ በጊዜው ለእሥራኤላውያን ክብር: ሞገስ: አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል:: (ዘጸ. 31:18) ከዚያም ለ500 ዓመታት ከእነሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች::

+ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ: በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ-እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮዽያ መጥታለች:: እነሆ በሃገራችን የ3ሺ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው:: ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን::

+ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን:: ግን አንጨነቅም:: ምክንያቱም የመጣችውም: የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም:: በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም:: ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም::

+ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን: ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች:: "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው:: "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው::

+"ታቦት" ማለት "ማሕደር-ማደሪያ" እንደ ማለት ነው:: ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል:: ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው:: በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም 2 ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን:: (2ቆሮ. 6:16, ራዕይ. 11:19)

+በመጨረሻም ኅዳር 21 ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን:: በዚህች ቀን:-

1.ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን:: ይሕ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ 40 መዓልት: 40 ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው:: (ዘጸ. 31:18, ዘዳ. 9:19)

2.በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኩዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች:: ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች:: (1ሳሙ. 5:1)

3.በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና: ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ: አገለገለ:: ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት:: በዚህም ሜልኮል ንቃው ማሕጸኗ ተዘግቷል:: (1ዜና. 15:25) ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል" ብለውናል::

"ሰላም ለኪ ማርያም እምነ::
ዘሰመይናኪ ጸወነ::
ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ::
ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ::
ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ::" እንዲል:: (አርኬ ዘኅዳር 21)

4.በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል:: (2ዜና. 5:1, 1ነገ. 8:1)

5.በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮዽያ ገብቷል::

6.በዘመነ አፄ ባዜን (በ4 ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች:: በዚህ ጊዜም 2ቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል::

7.በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ 12 መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚሁ ቀን በጌታችን ተቀድሷል::

8.በተጨማሪም በየጊዜው: ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር:: ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር 21 ቀን ነው:: በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው::

+*" አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን "*+

=>"ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል:: እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት እምቡሩካን: ኅሪት እምኅሩያን" ናትና::

+ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች:: እርሷ እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ ናትና::

+እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት: ልዩ" ማለታችን ነው::

1."ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ: ከገቢር: ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው: ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ ማርያም)

2."ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በሁዋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::

¤"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ ያሬድ)
¤ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-ማርያም ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

3.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው:: እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

4.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና::

+"+ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘሮም +"+

=>በቤተ ክርስቲያን እጅግ ስመ ጥር ከሆኑት ሊቃውንት አንዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚታወቀው "ገባሬ መንክራት" በሚለው ስሙ ነው:: ገባሬ መንክራት የተባለውም እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በመሥራቱ ነው::

+በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ሥር ተወልዶ ያደገው ቅዱስ ጐርጐርዮስ ከመመነኑ በፊት ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: እርሱ በበርሃ እያለም ከሮም ዻዻሳት የአንዱ በማረፉ ተሿሚ ፍለጋ አበው ሱባኤ ገቡ:: እግዚአብሔርም "የበረሃውን ጐርጐርዮስን ፈልጉት" አላቸው::

+"እሺ!" ብለው ፍለጋ በርሃ ቢሔዱ ውዳሴ ከንቱን ይጠላልና ተሰወረባቸው:: እነርሱም እያዘኑ ተመልሰው በመንበረ ዽዽስናው ላይ ወንጌልን አኖሩና ተለያዩ:: በዚህ ጊዜ ቅዱስ መልአክ ወርዶ "ጐርጐርዮስ ሆይ! ልትሔድ ይገባሃል" አለው::
+እርሱም ወደ ከተማ ወርዶ ታላቁ ሊቅ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ባለበት በዓለ ሲመቱ ተከብሯል:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ በዘመኑ ብዙ መጻሕፍትን ደርሶ: የክርስቶስን መንጋም ጠብቆ: ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከተአምራቱም:-+ወንድማማቾች ከአባታቸው በወረሷት አንዲት ሐይቅ እየተጣሉ ሲያስቸግሩ በጸሎቱ ሐይቁን የብስ አድርጐ አስታርቁዋቸዋል::

+"+ ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስዩጥ +"+

=>በ4ኛውና በ5ኛው መቶ ክ/ዘመናት ከተነሱ ከዋክብት ጻድቃን አንዱ ነው:: እድሜው በጣም ረዥም በመሆኑ የብዙ ቅዱሳን ባልንጀራም ነበር:: በገድል አካሉን ቀጥቅጦ: በስብከትም የአስዩጥን (አሲዩትን) ምዕመናን አንጾ: ብዙ ተአምራትንም ሠርቶ በተወለደ በ125 ዓመቱ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::

=>አምላከ ቅዱሳን የአማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያምን ጣዕሟን ፍቅሯን: ጸጋ በረከቷን ያሳድርብን:: ከአበው በረከትም አይለየን::

=>ኅዳር 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ጽዮን ድንግል ማርያም
2.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘሮሜ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስዩጥ
4.ቅዱስ ቆዝሞስ ሊቀ ዻዻሳት
5.ቅድስት ዲቦራ ዘድልበት
6.ቅዱስ ዘኬዎስ ሐጺር

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ
4.አባ አሮን ሶርያዊ
5.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

=>++"++ ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግስት ይጠፋል:: እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ . . . የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ:: የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ:: የእግዚአብሔርም ከተማ: የእሥራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል:: ++"++ (ኢሳ. 60:12)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
5•­3- ØÈ- ó- ë  •õ---- 16k
ASR by NLL APPS
ስንክሳር ዘወርሃ ህዳር ሃያ አንድ(፳፩)
https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
Daniel:
††† እንኳን ለቅዱሳን ሰማዕታት ቆዝሞስና ድምያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱሳን ቆዝሞስ ወድምያኖስ †††

††† እስኪ ዛሬ ስለ ክርስትናና ወጣትነት እነዚህን ቡሩካን ወንድማማች ክርስቲያኖች መሠረት አድርገን ጥቂት እንመልከት:: ከዚህ በፊት የበርካታ ወጣት ሰማዕታትን ዜና ሰምተናል:: መጽሐፍ እንደሚል "ወኩሉ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ተጽሕፈ" - "የተጻፈው ሁሉ እኛ ልንማርበት: ልንገሠጽበት ነውና" (ሮሜ. 15:4) ልናስተውል ይገባናል::

††† ዜና ቅዱሳን የሚነገረን እንደ ታሪክ እንዲሁ ሰምተን እንድናልፈው አይደለም::

1.ከልቡ ለሚሰማው (ለሚያነበው) በረከት አለው::

2.ከቅዱሱ (ቅድስቷ) ቃል ኪዳን በእምነት ተካፋይ መሆን ይቻላል::

3.ቅዱሳኑ ክርስትናቸውን ያጸኑበት: የጠበቁበትና ለሰማያዊ ክብር የበቁበትን መንገድ እንማርበታለን:: ትልቁም ጥቅማችን ይሔው ነው::

ቁጥራችን ቀላል የማይባል የተዋሕዶ ልጆች ሕይወተ ቅዱሳንን እንደ ተራ ታሪክ ወይ ጀምረን እንተወዋለን:: ምናልባትም በግዴለሽነት እናነበዋለን:: ደስ ሲለንም ምስሉ ላይ 'like' የምትለውን ተጭነን እናልፈዋለን::

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በደንብ አንብበን "ወይ መታደል!" ብለን አድንቀን እናልፋለን:: ማድነቃችንስ ጥሩ ነበር:: ግንኮ ቅዱሳኑ ለዚህ የበቁት የታደሉ ስለ ሆኑ ብቻ አይደለም:: ከእነርሱ የሚጠበቀውንም በሚገባ ሥለ ሠሩ እንጂ::

እግዚአብሔር የሚያዳላ አምላክ አይደለም:: "ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ-እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" (ዘሌ. 19:2, 1ጴጥ. 1:15) ብሎ የተናገረው ለጥቂት ወይም ለተለዩ ሰዎች አይደለም:: በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ ነው እንጂ::

ስለሆነም እኛ ክርስቲያኖች: በተለይም ወጣቶች ከቀደምቶቻችን ተገቢውን ትምሕርት ወስደን ልንጸና: ልንበረታ: ለቤተ ክርስቲያናችንም "አለሁልሽ" ልንላት ይገባል:: ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያን በተለይ በከተሞች የወላድ መካን እየሆነች ነው::

"ይህን ያህል ሚሊየን ሰንበት ተማሪና ወጣት አላት" ይባላል:: ሲፈተሽ ግን በትክክለኛ ቦታው የሚገኘው ከመቶው ስንቱ እንደ ሆነ ለመናገርም ያሳፍራል:: የሆነውስ ሆነ: መፍትሔው ምንድነው ብንል:- እባካችሁ ከቅዱሳን ቀደምት ክርስቲያኖች መሥራት ያለብንን ቀስመን: ከዘመኑ ጋር አዋሕደን (ዘመኑን ዋጅተን) ራሳችንን: ቤተ ክርስቲያንንና ሃገራችንን እንደግፍ:: ካለንበት ያለማስተዋል አዘቅትም እንውጣ::
ለዚህም ቁርጥ ልቡና እንዲኖረን አምላካችን ይርዳን ብለን ወደ ቅዱሳኑ ዜና ሕይወት እንለፍ::

ቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ በምድረ ሶርያ ተወልደው ያደጉ የዘመኑ ክርስቲያኖች ናቸው:: አባታቸው በልጅነታቸው በማረፉ 5 ወንድ ልጆችን የማሳደግ ሃላፊነት በእናታቸው ትክሻ ላይ ወደቀ:: እናታቸው ቅድስት ቴዎዳዳ ትባላለች::

እጅግ የምትገርም: ቡርክት እናት ናት:: አምስቱ ልጆቿ "ቆዝሞስ: ድምያኖስ: አንቲቆስ: አብራንዮስና ዮንዲኖስ" ይባላሉ:: በእርግጥ ለአንዲት እናት የመጀመሪያ ጭንቀቷ "ልጆቼ ምን ይብሉ" ነው:: ለቅድስት ቴዎዳዳ ዋናው ጉዳይ ይሔ አልነበረም::

ጌታችን እንዳስተማረን "ኢትበሉ ምንተ ንበልእ: ወምንተ ንሰቲ: ወምንተ ንትከደን - ምን እንበላለን: ምን እንጠጣለን: ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጠጨነቁ" ብሏልና ዘወትር የምትጨነቀው ስለ ልጆቿ ሰማያዊ ዜግነት ነበር:: (ማቴ. 6:31)

በዚህም ምክንያት አምስቱም ልጆቿን ዕለት ዕለት ወደ ቤተ እግዚአብሔር ትወስዳቸው: ከቅዱስ ቃሉ ታሰማቸው: መንፈሳዊ ሕይወትን ታለማምዳቸው ነበር:: አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በጐ ፈቃዳችንንና በቅንነት የሆነች ትንሽ ጥረታችንን ነውና ቅድስት ቴዎዳዳ ተሳካላት:: ልጆቿ በአካልም: በመንፈሳዊ ሕይወትም አደጉላት::

ዘመኑ እንደ ዛሬ ተድላ ሥጋ የበዛበት ሳይሆን ክርስቲያን መሆን ለሞት የሚያበቃበት ነበር:: ከዚህ በፊት እንደ ተመለከትነው ከክርስቶስ ልደት 275 ዓመታት በኋላ በሶርያና በሮም የነገሡት ሁለቱ አራዊት (ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስ) ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድሩ: ካደሩበትም አላውሉ አሉ::

ቀዳሚ ፈተናዋን በሚገባ የተወጣችው ቅድስት ቴዎዳዳ ይህኛውንም ትጋፈጠው ዘንድ አልፈራችም:: ግን ከልጆቿ ጋር መመካከር ነበረባትና ለውይይት ተቀመጡ:: ሦስቱ ልጆቿ ከልጅነታቸው ጀምረው ሲሹት የነበረውን ምናኔ መረጡ::

ቅድስቷ እናት በምርጫቸው መሠረት ቅዱሳን አንቲቆስ: ዮንዲኖስና አብራንዮስን መርቃ ወደ በርሃ ሸኘች:: እርሷም ከሁለቱ ቅዱሳን ልጆቿ ቆዝሞስና ድምያኖስ ጋር ቀረች::

እነዚህ ቅዱሳን በከተማ የቀሩት ግን ዓለም ናፍቃቸው አይደለም:: በእሥራት መከራን የሚቀበሉ የእግዚአብሔርን ቅዱሳን ያገለግሉ ዘንድ ነው እንጂ::

ቅድስት ቴዎዳዳ በቤቷ ነዳያንን ስትቀበልና ስታበላ ሁለቱ ቅዱሳን ልጆቿ ቀኑን ሙሉ እየዞሩ እሥረኞችን (ስለ ክርስቶስ የታሠሩትን) ሲጠይቁ: ሲያጽናኑ: ቁስላቸውን ሲያጥቡ አንጀታቸውንም በምግብ ሲደግፉ ይውሉ ነበር::

ይሕ መልካም ሥራቸው ለፈጣሪ ደስ ቢያሰኝም አውሬው ዲዮቅልጢያኖስን ግን ከመጠን በላይ አበሳጨው:: ወዲያውኑ ተይዘው እንዲቀርቡለት አዘዘ:: በትዕዛዙ መሠረትም ቆዝሞስና ድምያኖስ ታሥረው ቀረቡ::

"እንዴት ብትደፍሩ ትዕዛዜን ትሽራላችሁ! አሁንም ከስቃይ ሞትና ለእኔ ከመታዘዝ አንዱን ምረጡ" አላቸው:: ቅዱሳኑ ምርጫቸው ግልጽ ነበር:: ከክርስቶስ ፍቅር ከቶውኑ ሊለያቸው የሚችል ኃይል አልነበረምና:: (ሮሜ. 8:36)

ንጉሡም "ግረፏቸው" አለ:: ልብሳቸውን ገፈው: ዘቅዝቀው አሥረው: በብረትና በእንጨት ዘንግ ደበደቧቸው:: ደማቸውም መሬት ላይ ተንጠፈጠፈ:: እነርሱ ግን ፈጣሪን ይቀድሱት ነበር::

ይህ ዜና ፈጥኖ ወደ እናታቸው ደርሶ ነበርና ቅድስት ቴዎዳዳ እየባከነች ወደ ሰማዕታት አደባባይ ሮጠች:: አንዲት እናት ልጆቿ በአደባባይ ተሰቅለው ደማቸው ሲንጠፈጠፍ ስታይ ምን ሊሰማት እንደሚችል የሚያውቅ የደረሰበት ብቻ ነው::

ግን ክብራቸውን አስባ ተጽናናች:: ፈጥናም በሕዝቡ መካከል ስለ ሰነፍነቱ ከሀዲውን በድፍረት ዘለፈችው:: ንጉሡም በቁጣ አንገቷን በሰይፍ አስመታት:: ሁለቱ ቅዱሳን ይህንን በዓይናቸው አዩ:: አንዲት ነገርንም ተመኙ:: የእናታቸውን አካል የሚቀብር ሰው::

ግን ደግሞ ሁሉ ስለ ፈራ የቅድስቷ አካል መሬት ላይ ወድቆ ዋለ:: ያን ጊዜ ተዘቅዝቆ ሳለ ቅዱስ ቆዝሞስ አሰምቶ ጮኸ:: "ከእናንተ መካከል ለዚህች ሽማግሌ ጥቂት ርሕራሔ ያለው ሰው የለም?" ሲልም አዘነ:: ድንገት ግን ኃያሉ የጦር መሪ ቅዱስ ፊቅጦር ደረሰ::

ሰይፉን ታጥቆ: በመካከል ገብቶ የቅድስቷን አካል አነሳ:: በክብር ተሸክሞም ወስዶ ቀበራት:: በመጨረሸ ግን የሦስቱ ወንድሞቻቸው ዜና በመሰማቱ ከበርሃ በወታደሮች ተይዘው መጡ:: ከዚያም በብዙ መከራ አሰቃይተው በዚህች ቀን አምስቱንም አሰልፈው ገደሏቸው:: የክብር ክብርንም ከእናታቸው ጋር ወረሱ::

††† አምላከ ሰማዕታት ከትእግስታቸው: ከጽናታቸውና ከበረከታቸው ያሳትፈን::
††† ኅዳር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ቆዝሞስ ወድምያኖስ (ሰማዕታት)
2.ቅድስት ቴዎዳዳ (እናታቸው)
3.ቅዱሳን አንቲቆስ: ዮንዲኖስና አብራንዮስ (ወንድሞቻቸው)
4."311" ሰማዕታት (የነ ቆዝሞስ ማኅበር)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
3.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
4.አባ ጳውሊ የዋህ
5.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት
6.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ሐዋርያ

††† "ልጆች ሆይ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ:: አሸንፋችሁአቸውማል:: በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና:: እነርሱ ከዓለም ናቸው:: ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ:: ዓለሙም ይሰማቸዋል:: እኛ ከእግዚአብሔር ነን:: እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል:: ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም::" †††
(፩ዮሐ. ፬፥፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/10/01 09:33:47
Back to Top
HTML Embed Code: