Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞ 

[  ✞  🌼  እንኩዋን ለብርሃነ መስቀሉ እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  🌼 ✞  ]


🕊  ✞ ቅዱስ ዕፀ መስቀል ✞  🕊

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ:
¤ ከግራ ቁመት:
¤ ከገሃነመ እሳት:
¤ ከሰይጣን ባርነት:
¤ ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል::

" እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ " እንዳለ ሊቁ::

ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት::

እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት [ዘፍ.፬፥፲፭]  ጀምሮ

¤ ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት [ዘፍ.፳፪፥፮]
¤ ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል [ዘፍ.፳፰፥፲፪]
¤ ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ [ዘፍ.፵፰፥፲፬]
¤ ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ_በትር [ዘጸ.፲፬፥፲፭]
¤ የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት [ዘኁ.፳፩፥፰]  ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል::

ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: [መዝ.፶፱፥፬]

በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም "መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም: መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

ቅዱስ_ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል:: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: [፩ቆሮ.፩፥፲፰  ገላ.፮፥፲፬]

አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::


†  🕊   በዓለ መስቀል  🕊  †

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም::

መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ፪፻፸ ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እናታችን ቅድስት እሌኒ [ሔለና] በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች::

መስከረም ፲፯ ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት ፲ ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ፲ ዓመት በሁዋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም ፲፯ ቀን ተቀድሷል::

ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ [ግሸን ማርያም] ተለብጦ ተቀምጧል::


†  🕊 ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ  🕊 † 

ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ [ሰማርያዊ] ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ ጐልጐታ ነን" አሉት::

እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::


†  🕊  ቅድስት ታኦግንስጣ  🕊   †

በ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

🕊

[  †  መስከረም ፲፯ [ 17 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፪. ቅድስት እሌኒ ንግስት
፫. ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ
፬. ቅዱስ መቃርስ ሊቀ ዻዻስ
፭. ቅዱስ አውዶኪስ ቀሲስ
፮. ብጽዕት ታኦግንስጣ ሮማዊት
፯. ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሊቀ ዻዻሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት [ቀዳሜ ሰማዕት]
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ ዘብዴዎስ]
፫. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
፬. አባ ገሪማ ዘመደራ
፭. አባ ዸላሞን ፈላሢ
፮. አባ ለትጹን የዋህ
፯. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ [ዘደሴተ ቆዽሮስ]

" የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና . . . መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ:: የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ:: እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን:: " [፩ቆሮ.፩፥፲፰-፳፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from M.A
ንግሥት እሌኒን እናወድሳት ዘንድ ይገባል፡፡ ክብር የሚገባውን የአምላካችንን የጌታችንን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኝ እንደሆነ ብላ በእምነት ለመፈለግ ተግታለችና፡፡

የጌታችን መስቀል ቅዱስ ስጋው የተቆረሰበት ክቡር ደሙ የፈሰሰበት ከሁሉ የተለየ ከሁሉ የተቀደሰ ሁሉንም የሚቀድስ እንደሆነ አስቀድማ ተገንዝባለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል፡፡

ንግሥትነቷን በዓለማዊ ቅምጥልናና ምቾት ታሳልፈው ዘንድ አልወደደችም፤ ይልቁንስ የተወደደውን መስቀል ትፈልግ ዘንድ በመንፈስ ብርቱ ሆና በስጋ ደከማለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል።

እጅግ የከበረውን መስቀል ትፈልግ ዘንድ ስትጀምር በራሷ መታመን አልታበየችም ይልቁንስ ሁሉን ስለክርስቶስ ትቶ የወጣ ባህታዊ ኪራኮስን ታማክር ዘንድ ወዳለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል።

በተዋህዶ የከበረ የአብ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ይዞ እንዳላስቀረው ሞትንም ድል አድርጎ እንደተነሳ ሁሉ ክቡር መስቀሉም ተቀብሮ ለዘላለም እንደማይኖርና ከተቀበረበትም እንደሚወጣ አምናለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል።

ከጌታችን መስቀል ጋር የተቀበሩት መስቀሎች ብዙ ናቸው የጌታየን እንዴት እለየዋለሁ? ብላ ሳትጨነቅ የክርስቶስ መስቀል ክብሩን ራሱ እንደሚገልፅ በልቧ ተማምና እስክታገኝው ደክማለችና በእውነት ምስጋና ይገባታል፡፡
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን፡፡ †

[ † እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን ኤዎስጣቴዎስ አኖሬዎስና ማር ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]


† 🕊 አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን 🕊 †

ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ [ኤርትራዊ] ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

ጻድቁ በ፲፻፪፻፷፭  ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው ክርስቶስ ሞዐ እና ስነ ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም ማዕቀበ እግዚእ ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው::

ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምሕር ዘንድ ገብተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ በመሆናቸውም የዘመኑ አበው 'ዳግማዊ እስጢፋኖስ' እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::

በዘባነ ኪሩብ በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: 'ዘኪያከ ሰምዐ ኪያየ ሰምዐ.. አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ" ብሏቸው ባርኩዋቸው ዐረገ::

ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::

አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል አፍርተዋል::

አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት ቀዳሚት ሰንበት እንዳትናቅ [እንድትከበር] ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን ፪ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ፪ ጊዜ በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

በመንገድም ወደ ባሕረ ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት:: ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: ሚካኤል በቀኝ ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው ይተረጉሙላቸው ገቡ::

በመካከል ግን አንዱ [የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት] በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው በ፲፻፫፻፵፭ ዓ/ም በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ መርምሕናም ተቀብረዋል:: ዛሬ በኢትዮዽያ ኤርትራ ግብጽና አርማንያ ይከብራሉ::


🕊 አቡነ አኖሬዎስ ጻድቅ 🕊

እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ 'ታላቁ አኖሬዎስ' ይባላሉ:: በዚህ ስም ከሚጠሩ አባቶች ዋነኛው እኒህ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት ሙገር አካባቢ ሲሆን ዘመኑም ፲፬ ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቻቸውም ሰላማ እና ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ::

ጻድቁ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት አንዱ ናቸው:: በወንጌል ትምሕርት ከመሞላታቸው ባሻገር ፍጹም መናኝ ስለ ነበሩ እጅግ ደፋር ነበሩ:: የትኛውንም ስሕተት ፊት ለፊት ይናገሩም ነበር::

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲያርፉ ጌታ "በአንተ ፈንታ አኖሬዎስ ቀሪ ጣዖት አምልኮን ያጠፋል" ብሎ ነግሯቸው ነበር:: ይኸውም አልቀረ ጻድቁ ከ፲፪ ቱ ንቡራነ እድ እንደ አንዱ በተመረጡ ጊዜ በደበቡ የሃገራችን አካባቢ ክርስትናን አስፋፍተዋል::

ደብረ ጽጋጋ ገዳምንም የመሠረቱ እርሳቸው ናቸው:: ዛሬ 'ኑራ ሑሴን' እየተባለ ታሪኩ ጠልሽቶ የሚነገርለት ዋሻ የጻድቁ በዓት ነው:: አቡነ አኖሬዎስ ፪ ቱን ነገሥታት [ዓምደ ጽዮንንና ሰይፈ አርእድን] በመገሰጻቸው ብዙ ፈተና ደርሶባቸዋል:: ጻድቁ ብዙ ፍሬ አፍርተው በዚህ ቀን ዐርፈዋል::


🕊 ማር ያዕቆብ ግብጻዊ  🕊

በግብጽ ገዳማት ውስጥ በ፬ ኛው መቶ ክ/ዘመን ተነስተው ካበሩ ቅዱሳን አንዱ ማር ያዕቆብ ነው:: ቅዱሱ ከተባረከ ቤተሰብ ተወልዶ በሥርዓቱ አድጐ ገና በልጅነቱ ከመምሕሩ ጋር መንኗል:: ከገድሉ ጽናት የተነሳ ሰይጣን በግልጽ ይፈታተነው ነበር:: በተለይ ለ፯ ዓመታት ያህል ይደበድበው መሬት ላይ ይጐትተው በጥፊ ይመታው ነበር:: እርሱ ግን በጸሎቱ መብረቅ አውርዶ አባርሮታል:: በበርሃው ምንም የሚበላ ነገር ባለ መኖሩ የዱር እንስሳትን ወተት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይጠጣ ነበር::

ቅዱሱ ሰማዕት ለመሆን ሞክሮም ነበር:: ማር ያዕቆብ ገድሉና ተአምራቱ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ ስሙ ከፍ ከፍ ብሏል:: እስኪ ጊዜውና እድሉ ካለዎት መጽሐፈ ስንክሳር ላይ የተጻፈውን ገድሉን እንዲያነቡ ልጋብዝዎት:: ጻድቁ ያረፈው በዚሁ ዕለት ነው::
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹ ካሉበት ጉባኤ እንደ ምሕረቱ ታላቀነት ያድርሰን:: በረከታቸውንም ይሙላልን::

🕊

[ † መስከረም ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
፪. አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
፫. ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
፬. ቅዱስ ዕፀ መስቀል
፭. ቅድስት እሌኒ ንግሠት
፮. ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፯. ቅዱስ መርቆሬዎስ ካልዕ [ሰማዕት]
፰. ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት
፱. ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕት
፲. አባ ፊልሞስ
፲፩. ቅዱስ ሰልሖን ሰማዕት
፲፪. ቅዱስ አክሳኤልስ ሰማዕት
፲፫. ቅዱስ ይስሐቅ ሰማዕት
፲፬. ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀሲስ
፲፭. ቅዱስ ነኪጣ ሰማዕት
፲፮. አባ ፊላታውዎስ መንክራዊ
፲፯. አባ ኖብ ባሕታዊ
፲፰. አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
፲፱. ፷ ሰማዕታት [ማሕበረ ቅዱስ አቦሊ]

[ † ወርሐዊ በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፪. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ከ፸፪ቱ አርድእት]

" እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ::" [ማቴ.፭፥፲፫-፲፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from M.A
«ግሸን ደብረ ከርቤ»

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ ከደሴ ከተማ 82 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ወሎ ዞን በአንባሰል ወረዳ ውስጥ በሃይቅ እና በመቅደላ በደላንታና በየጁ መካከል በበሽሎ ወንዝ አዋሳኝ ከፍተኛ በሆነ ተራራ ላይ የምትገኝ ገዳም ናት፡፡ የበሸሎን ወንዝ ተሻግረን ሰማይ ጥግ የደረሱ የሚመስሉትን ተራሮች ወጥተን በስተመጨረሻ መግቢያ አንድ በር የሆነ እና ከተራራው አናት ላይ በሚገኝ ስፋራ ላይ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም የታነጸ እና ግማደ መስቀሉ የሚገኝበት የእግዚአብሔር አብ አብያተ ክርስቲያናት እና ፈዋሽ ጸበል ይገኛሉ፡፡ በ1942 ዓ.ም አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘጎንደር ከዚህም ጋር ''መንፈሳዊ መናኝ'' በመባል የሚታወቁት ደገኛ አባት ያሰሩት ቤተ ክርስቲያንም ይገኛል፡፡

ግሸን ይህን የአሁኑን መጠሪያ ስም ከማግኘትዋ በፊት በተለያየ መጠሪያ ስሞች ትታወቅ ነበር:: በመጀመሪያ በአጼ ድልነአድ ዘመነ መንግስት በ896 ዓ.ም ሃይቅ ደብረ እስጢፋኖስ ሲመሰረት ''ሐይቅ ደብረ ነጎድጓድ'' ተብሎ ሲሰየም ግሸንም በሃይቅ ግዛት ውስጥ ስለሆነች ስምዋ ''ደበረ - ነጎድጓድ'' ተባለች፡፡ ይህን መጠሪያ ስም እንደያዘች እስከ 11ኛው ክ/ዘመን ድረስ ቆየች፡፡ በ11ኛው ክ/ዘ በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው ጻድቁ ንጉስ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍሎ የሰራው ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ይጠራ ስለነበር ግሸንም ''ደብረ እግዚአብሔር'' ተብላ መጠራት ጀመረች፡፡ ነገር ግን በዚህ ስም በመጠራት ብዙም ሳይቆይ ስሟ ተለውጦ ''ደብረ ነገሥት'' ተባለች፡፡ ደብረ ነገስት የተባለችውም ነገስታቱ ይማጸኑባት የክብርና የማእረግ እቃዎች የሚያሰቀምጡባትና የነገስታቱ የመሳፍንቱ ልጆችም የቤተ መንግስት አስተዳደር የሚማሩባት ስፍራ ስለነበረች ነው፡፡ እንደገና ደግሞ በ1446 ዓ.ም ኢትዪጵያዊው ፈላስፋ እየተባሉ በሚጠሩት በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት ግማደ መስቀሉ መጥቶ በዚህ ቅዱስ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ- ነገሥት መባልዋ ቀርቶ ''ደብረ- ከርቤ'' ተባለች፡፡

የግሸኗ እመቤት ወላዲተ አምላክ ከደጇ በረከት ታሳትፈን።
Forwarded from M.A
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን።  †

[  ✞ መስከረም ፲፱ [ 19 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞  ]


🕊 † ቅዱስጐርጐርዮስ ዘአርማንያ † 🕊

✞ ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከሊቃውንትና ከዻዻሳት ዝርዝር ውስጥ ይገኛል:: በቤተ ክርስቲያንም ዓበይት ተጽፎ ከሚባሉ አበው አንዱ ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት [በ፫ ኛው መቶ ክ/ዘመን] ነው::

አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት  እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት :-

፩. ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት
፪. ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት
፫. የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::

ቅዱሱ ፫ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከበመልኩዋ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::

ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በኋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ  ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስበጸሎት ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::

በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና ለጥቂት ጊዜ ቆዩ: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::

በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግንእኔ አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::

ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::

አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::

ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው  እስኪያልቅ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: በብዙሽማግሌ ስቃይም አሰቃዩት::

በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት:: ወደ መጸዳጃ ቤት ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት:: ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት:: አንዲት  ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለ፲፭ ዓመታት ተቀብሮ ኖረ::

አካሉና አፈሩ ተጣበቀ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ:: ከነገርየንጉሡ ሁሉ በኋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት [እሪያነት] ቀየራቸው::

የንጉሡ እንስሳ /አውሬ መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ::  እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት ቆፍረው አወጡት::

አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት:: ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ፲፭ ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::

ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ:: የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል:: በመጨረሻም ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን ደረሰ:: ከ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ:: ዕረፍቱ ታሕሳስ ፲፭ ቀን ሲሆን ዛሬ ከተቀበረበት የወጣበት ነው::


🕊  †  ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ  †  🕊

ቅዱሱ የ፮ኛው መቶ ክ/ዘመን ጻድቅ ሲሆን በዓለም ከመናፍቃን: በገዳም ደግሞ ከአጋንንት ብዙ መከራን ተቀብሏል:: በወቅቱ መለካውያን [የአሁኖቹ ካቶሊኮችና ምስራቅ ኦርቶዶክሶች) አባቶችን ያሳድዱ ነበር:: ልክ ፱ኙ ቅዱሳን በዚህ ምክንያት ወደ ኢትዮዽያ እንደመጡት ቅዱስ ቂርቆስም ወደ ግብጽ በርሃ ከእርሷ ተሰደደ::

በበርሃው ውሃም ሆነ ዛፍ ባለመኖሩ በረሃብና በጥም በመሰቃየቱ ወደ ፈጣሪ ለመነ:: ጌታም አንዲት አጋዘን ልኮለት  ወተትን አልቦ ጠጣ:: እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም ምግቡ ይሔው የአጋዘን ወተት ነበር:: በዚህ ምክንያት ይሔው ዛሬም ድረስ " ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ ዘሲሳዩ ሐሊበ ቶራ" እየተባለ ይጠራል::

በበርሃው ውስጥ በኖረባቸው ዘመናትም አንድም ሰው አይቶ ካለማወቁ ስትሆን ባለፈ አጋንንት በገሃድ እየመጡ ያሰቃዩት ነበር:: ቅዱሱ ግን በትእግስት ኑሮ በዚህች ቀን ሲያርፍ ብዙ ተአምራት በበዓቱ ውስጥ ተገልጠዋል:: ይህንን ያዩት ደግሞ ከዻዻሱ ዘንድ ተልከው የቀበሩት አበው ናቸው::


🕊  †   ቅድስት ሮማነ ወርቅ  †   🕊

ይህቺ ቅድስት እናት ደግሞ ኢትዮዽያዊት ናት:: የነገሥታቱ ልጅ አባቷ አፄ ናዖድ: እናቷ ደግሞ እሌኒ /ወለተ ማርያም ይባላሉ:: ወንድሟ ደግሞ አፄ ልብነ ድንግል ይባላሉ::

በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም መንፈሳዊነቷ የገዳም ያህል ነበር:: ከተባረከ ትዳሯም ቅዱስ ላዕከ ማርያምን አፍርታለች:: አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ባለፈ የነዳያን እናትም ነበረች:: በክርስትናዋ ፈጣሪዋን ደስ አሰኝታ በዚህ ቀን ዐርፋለች::

✞ አምላከ ቅዱሳን ጸጋውን: ክብሩን አይንሳን:: ከወዳጆቹ በረከትም እንደ ቸርነቱ ያድለን::

🕊

✞ መስከረም ፲፱ [ 19 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማርያ
፪. ቅዱስ ቂርቆስ ገዳማዊ
፫. ቅድስት ሮማነ ወርቅ
፬. ቅዱስ ዕጸ መስቀል

" ጻድቃን ጮሁ: እግዚአብሔርም ሰማቸው:: ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው:: እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው:: መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል:: የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው:: እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል:: እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል:: " [መዝ.፴፫፥፲፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
2024/09/30 16:21:25
Back to Top
HTML Embed Code: