Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

              #ነሐሴ ፮ (6) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ሶሀባ በሚባለው ቦታ ቆመው በጸለዩበት ወንዝ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዓሣ ከሰማይ ለሚዘንብላቸው ለመናኔ መንግሥት #አቡነ_ኢዮስያስ_ለዕረፍታቸው_በዐል በሰላም አደረሰን።

                          
#መናኔ_መንግሥት_አቡነ_ኢዮስያስ፡- ትውልዳቸው ሸዋ ሲሆን የንጉሥ ዓምደ ጽዮን ልጅ ናቸው፡፡ ጥር 6 ቀን ሲወለዱ ቅዱሳን መላእክት ከበዋቸው ታይተዋል፡፡የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በዓለም ነግሠው መኖርን ንቀው በመመነን በመጀመሪያ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ገቡ፡፡ አቡነ ኢዮስያስ በሐይቅ ገዳም ለ14 ዓመታት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ በዚያም ብሉይንና ሐዲስን፣ መጽሐፈ መነኰሳትንና መጽሐፈ ሊቃውንትን አጠናቀው ተምረዋል፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ትግራይ ደብረ በንኰል ገዳም ሄዱ፡፡ በደብረ በንኰልም በታላቅ ተጋድሎ ኖረው በታላቁ አባት በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ መነኰሱ፡፡ ቆብ የተቀበሉት ግን ከአቡነ ተክለሃይማኖት ነው፡፡

አቡነ መድኃኒነ እግዚእም ሰባት ዓመት ከእሳቸው ጋር ካቆዩአቸው በኋላ አቡነ ኢዮስያስን ወንጌልን ዞረው እንዲሰብኩና ገዳም እንዲገድሙ በማዘዝ መርቀው ሸኝተዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢዮስያስም ወደ አዱዋ አውራጃ ዛሬ በስማቸው ወደተጠራው ገዳም ሄደው በቦታው ላይ በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ገዳሙንም ከገደሙት በኋላ በርካታ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ ጻድቁ ያፈለቁት ጠበል በፈዋሽነቱ የታወቀ ነው፡፡ በየዓመቱ በዕረፍታቸው ዕለት ነሐሴ 6 ቀን ሶሀባ በሚባለው ቦታ ቆመው በጸለዩበት ወንዝ ላይ ዓሣ ከሰማይ ይዘንባል፡፡ ይህ አሁንም ድረስ በየዓመቱ ነሐሴ 6 ቀን በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡

አቡነ ኢዮስያስን ከሃዲያን የሆኑ አረማውያን ቢያስቸግሯቸው ጻድቁም በጸሎት ቢያመለክቱ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ነጭ የንብ መንጋ መጥቶ አረማውያኑን አንጥፍቶላቸዋል፡፡ ጻድቁ በጸሎታቸው አራት ሙታንን በአንድ ጊዜ ከሞት ያስነሡ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በገዳማቸው ውስጥ በበዓላቸው ቀን ገድላቸው ሲነበብ አጋንንት ከሰው ልቡና እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፡፡

ጻድቁን እንደ ረድእ ሆኖ የሚያገለግላቸው አንበሳ ነበራቸው፡፡ ወደ ገዳማቸው መጥቶ መካነ ዐፅማቸውን የተሳለመውን እስከ 14 ትውልድ ድረስ እንደሚምርላቸው ጌታችን ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ልጁን በስማቸው የሰየመ ቢኖር የሰይጣንን ፊት ፈጽሞ እንደማያይ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ከአቡነ ኢዮስያስ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

             #ነሐሴ ፮ (6) ቀን።

እንኳን #ጌታችን_ሰባት አጋንንትን ከእርሷ ላወጣላት #ከ36_ቅዱሳት_አንስት አንዷ ለሆነችው ለእናታች #ለቅድስት_መግደላዊት_ማርያም_ለዕረፍት በዐል መታሰቢያና #ከቂሳርያና_ከቀጰዶቅያ አገር ለሆነች ለከበረች #ለቅድስት_ኢየሉጣ ሰማዕትነት ለተቀበለችበት ለዕረፍቷ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ከሚታሰበው፦ #ከአባ_ሲኖዳ_ረድእ ከቅዱስ አባት #ከአባ_ዊፃ ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                            
                          
#ቅድስት_መግደላዊት_ማርያም፦ ይችም ቅድስት ጌታችን ሰባት አጋንንትን ከእርሷ ያወጣላት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስን ተከትላ ያገለገለችው በመከራውም ጊዜ ከባልንጀሮቿ ጋራ የነበረች እስከ ቀበሩትም ድረስ ያልተለየች እናት ነች።

በእሑድ ሰንበትም ገና ጨለማ ሳለ በማለዳ ማርያም ወደ መቃብር ገሥግሣ ሔደች ደንጊያውንም ከመቃብሩ አፍ ተገለባብጦ መልአክም በላዩ ተቀምጦ አየችው ከእርሷም ጋራ ጓደኛዋ ማርያም አለች። መልአኩም "እናንተስ አትፍሩ ጌታ ኢየሱስን እንድትሹት አውቃለሁና ግን ከዚህ የለም እነሣለሁ እንዳለ ተነሥቷል" አላቸው ። ለእርሷም ዳግመኛ ተገልጾላት "ሒደሽ ለወንድሞቼ እኔ ወደ አባቴ ወደ አባቴታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ እንደማርግ ንገሪያቸው" አላት። ወደ ሐዋርያትም መጥታ የመድኃኒታችንን መነሣቱን እንዳየችውና ንገሪ እንዳላትም አበሠረቻቸው።

ከዕርገቱም በኋላ ሐዋርያትን እያገለገለቻቸው ኖረች። በኃምሳኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ ቅዱስ መንፈሴን አሳድራለሁ አለ ብሎ ኢዩኤል ትንቢት እንደ ተናገረ ያንን አጽናኝ መንፈስ ቅዱስን ከሐዋርያት ጋር ተቀብላለች።

ከዚህም በኋላ ከሐዋርያት ጋራ ወንጌልን ሰበከች ብዙዎች ሴቶችንም የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት መልሳ አስገባቻቸው። ሴቶችን ስለ ማስተማርም ሐዋርያት ዲያቆናዊት አድርገው ሾሟት ከአይሁድም በመገረፍ በመጐሳቈል ብዙ መከራ ደረሰባት። ተጋድሎዋንም ፈጽማ ነሐሴ 6 ቀን በሰላም በፍቅር ዐረፈች። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ። እኛንም የክርስቲያን ወገኖችን ሁሉ በቅድስት መግደላዊት ማርያም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

                           ✝️ ✝️ ✝️
#ከቂሳርያና_ከቀጰዶቅያ አገር የሆነች #ቅድስት_ኢየሉጣ፦ ይቺም ቅድስት ከወላጆቿ ብዙ ገንዘብ ወረሰች ከታጋዮችንም አንዱ በግፍ ተነስቶ ጥሪቷን ሁሉ ወንዶች ሴቶች ባሮቿን ለዳኛ መማለጃ በመስጠት ነጠቃት።

ይህም ዐመፀኛ እንደምትከሰውና ሐሰቱንም እንደምትገልጥበት በአወቀ ጊዜ ወደ ቂሳርያው ገዢ ሒዶ ክርስቲያን እንደ ሆነች ወነጀላት። በልቧም እንዲህ አለች "የዚህ ዓለም ገንዘብ ኃላፊ ጠፊ አይደለምን እነሆ እርሱን ነጠቁኝ የሰማይ ድልብን ገንዘብ ካደረግሁ ማንም ከእኔ ነጥቆ ሊወስድብኝ አይችልም"።

ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ቀረበች በፊቱም ቁማ እንዲህ አለች "እኔ ክርስቲያዊት ነኝ ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ በፈጠረ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ"። መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ወደ እሳትም ውስጥ እንዲወረውሩዋት አዘዘ ነፍሷንም ነሐሴ 6 ቀን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።

ነገር ግን እሳቱ አልነካትም ምንም ምን አላቃጠላትም ከውኃ ውስጥ እንደሚወጣም ከእሳት ውስጥ አወጧት። ስለ ገንዘቧና ስለ ጥሪቷም የማያልፍ የሰማይ መንግሥትን ወረሰች። ቅዱስ ባስልዮስም ብዙ ወድሷታል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ኢየሉጣ ጸሎት ይማረን።

                           
#የአባ_ሲኖዳ_ረድእ_ቅዱስ_አባ_ዊፃ፦ እርሱም ከእግዚአብሔር ብዙ ምሥጢራትን የሰማ የአባ ሲኖዳንም ገድል እንደ አየና እደንሰማ የጻፈ ነው። መልካም አካሔዱንም እንዴት እንደፈጸመ ከእርሱ ከአባ ሲኖዳ ሰማ እግዚአብሔርም አገልግሎ ነሐሴ 6 ቀን በሰላም ዐረፈ። እግዚአብሔር በአባ ዊፃ ጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 6 ስንክሳር።

                            
"#ሰላም_ለኢየሉጣ_እንበይነ_ምግባር_ሠናይ። በውስተ እቶን ዘእብዋእ በውዴተ ብእሲ እኩይ። እንዘ ኢሀሎ ላዕሌሃ አሠረ ዋዕይ። ወጽአት እምእሳት ከመ ዘወጽአ እማይ። አምሳለ ፍቱን ወርቅ ወብሩር ጽሩይ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ_አርኬ_ነሐሴ 6።

                              + + +
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወይሰግዳ ሎቱ አዋልደ ጢሮስ በአምኃ። ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሥ ሐሴቦን"። መዝ 44፥12-13። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 3፥10-22፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 16፥13-19። የሚነበበው ወንጌል ማር 16፥9-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡  †

[ †  እንኩዋን ለቅድስት እናታችን ማርያም መግደላዊት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  † ]

†  🕊 ቅድስት ማርያም መግደላዊት  🕊  †

ይህችን ቅድስት "ማርያም" ያሏት ወላጆቿ ሲሆኑ "መግደላዊት" እያሉ የጠሯት ደግሞ ሐዋርያት [ወንጌላውያን] ናቸው:: ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ :- በዘመኑ "ማርያም" የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነሱ ለመለየት ነው:: አንድም ሃገሯ ከእሥራኤል አውራጃዎች በአንዱ [በመግደሎን] ተወልዳ ያደገች ናትና::

ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረችና ሰዎች ያደንቁዋት: ወንዶች ይከተሏት ነበር:: በዚህም ፯ [7] አጋንንት ተጠግተው ፯ [7] ዓይነት ኃጢአትን ያሠሯት ነበር:: በተለይ ደግሞ በዝሙት: በትውዝፍት [ምንዝር ጌጥ] እና ትዕቢት በእጅጉ የታወቀች ነበረች::

በእንዲህ ያለ ግብር ጸንታ ለዘመናት ኖረች:: በዚያ ወራት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን ተዋሕዶ ያስተምር ነበርና ስለ እርሱ ሰማች:: "ጌታ ኃጥአንን አይጸየፍም [ይቀበላል]: አጋንንትንም ያስወጣል" ብለውም ነገሯት:: ጥሪው የእግዚአብሔር ነውና ማርያም መግደላዊት አልዘገየችም::

ወደ እርሱ ሔዳ ጌታ ባያት ጊዜ ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና አቀረባት:: በቸርነቱም ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የሞሉትን ፯ [7] የአጋንንት ነገድ አስወጣላት:: በዚያች ሰዓት ዕለቱኑ እንደተወለደ ሕጻን ከነበረባት ችግር ሁሉ ንጹሕ ሆነች:: ጌታም ከ፴፮ [36]ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ትሆን ዘንድ መርጦ ተከታዩ አደረጋት::

ቅድስት ማርያም ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች:: እርምጃዋ ሁሉ የተባረከና የንጽሕና ሆነ:: ጌታን እስከ ዕለተ ሕማሙ ድረስ በመዓልትም: በሌሊትም በቅን አገለገለችው::

ጌታችን ስለ እኛ መከራን በተቀበለባት በዚያች ዕለተ ዐርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች::

ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች:: በእግረ መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ ነበረች:: [ዮሐ.፲፱፥፳፭] (19:25) ቅዱሳኑ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን ሲቀብሩትም ከእሕቶቿ ጋር አብራ ተከትላ አይታለች::

እሑድ በሌሊት: ገናም ሳይነጋ መቃብሩን ታይ ዘንድ: ሽቱም ልትቀባ ወደ ጐልጐታ ገሠገሠች:: ፍጹም የአምላክ ፍቅር አድሮባታልና ግርማ ሌሊቱንና የአይሁድ ጭፍሮችን አልፈራችም:: ጌታችንም ከእመቤታችን ቀጥሎ ከፍጥረት ወገን ትንሳኤውን ያየች የመጀመሪያዋ ሰው ትሆን ዘንድ አደላት::

በመቃብሩ ራስጌና ግርጌም ፪ [2] መላእክትን [ሚካኤልና ገብርኤልን] ተመለከተች:: ዘወር ስትል ደግሞ የክብርን ባለቤት አየችው:: አላወቀችውምና "ማርያም" አላት:: "ረቡኒ-ቸር መምሕር ሆይ" ብላ ሰገደችለት::

ጌታም "ሑሪ ኀበ አኀውየ ወበሊዮሙ . . . ሒደሽ ለደቀ መዛሙርቴ በያቸው . . . " ብሎ የትንሳኤው ሰባኪ አደረጋት:: "ወሖረት ወነገረቶሙ ለአርዳኢሁ . . . " እንዲል ትንሳኤውን ለደጋጉ ሐዋርያት ሰበከችላቸው::

ቅድስት ማርያም መግደላዊት ከክርስቶስ ትንሳኤ በሁዋላ ለ፵ [40] ቀን መጽሐፈ ኪዳንን ፤ ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምራለች:: በዕርገቱ ተባርካ : በበዓለ ሃምሳ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ተካፍላለች:: በአዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ልዩ አገልግሎት ነበራት::

ቅዱሱ እስጢፋኖስ ፰ [8] ሺውን ማሕበር ሲመራ ሴቶችን ታስተዳድርለት ነበር:: ከሁሉ በላይ ግን ቅድስቲቱ የቅዱሳን ሐዋርያት መጋቢ ነበረች:: በዘመኑ መንፈስ ቅዱስ የሚባርከውን አጋፔ [የፍቅር ማዕድ] የምታዘጋጀው እርሷ ነበረች::

እንዲያውም አንዴ የሚበላ ጠፍቶ ለሐዋርያት ማዕድ ፍለጋ በሔደችበት እግሯ ቆስሎና ደምቶ መመለሷ ይነገራል:: እንዲህ አድርጋ ያዘጋጀችውን ማዕድ ቅዱስ መልአክ ወርዶ ወደ ሰማይ ወስዶታል:: ለቅዱሳን ሐዋርያትም እያመጣ ይመግባቸው ነበር::

እናታችን ማርያም መግደላዊት በስብከተ ወንጌልም የተመሰከረላት ነበረች:: የመጀመሪያዋ የሐዲስ ኪዳን ዲያቆናዊት ሴት ስትሆን ክርስትናንም ተዟዙራ ሰብካለች:: ስለ ቅዱስ ስሙም ሽሙጥን: ስድብን: መንገላታትን እና ግርፋትን ታግሳለች::

በተለይ አይሁድ ብዙ አሰቃይተዋታል:: ቅድስቷ እናታችን መልካሙን ገድል ተጋድላ በበጐ እድሜ በዚህች ቀን ሔዳለች:: በዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ [ከአንዳንዶቹ በቀር] ያከብሯታል::

†  🕊 ቅድስት ኢየሉጣ ዘቂሣርያ  🕊

በቀድሞው የግሪክ ግዛት [ቂሣርያ ውስጥ] በዘመነ ሰማዕታት አካባቢ የነበረችው ቅድስት ኢየሉጣ ክርስትናን የወረሰችው ከወላጆቿ ነው:: ገና ወጣት እያለች ወላጆቿ በማረፋቸው የሃብታቸው ወራሽ ሆነች::

ነገር ግን አንድ ክፉ ሰው መጥቶ ሃብቷን ነጠቃት:: በዚህ አዝና "የዳኛ ያለህ" ልትል ወደ ፍርድ ቤት ስትሔድ የጠበቃት ግን የሚገርም ነበር:: የተገፋችው እርሷ ተከሳሽ: ገፊው ደግሞ ከሳሽ ነበር:: የክሱ ጭብጥ ደግሞ "ክርስቲያን ነሽ" የሚል ነበር::

በወቅቱ በመኯንንቱ ፊት ክርስትናዋን ብትክድ በቀጥታ ሃብቷን ማግኘት ትችል ነበር:: እርሷ ግን ለአፍታ አሰበች:: "እንዴት ዘላለማዊ ሃብቴን [ሃይማኖቴን] በኃላፊው ንብረት እለውጣለሁ" ብላ ሁሉም እየሰሙ ጮክ ብላ "ክርስቲያን ነኝ" አለች::

ወዲያውም ሞት ተፈርዶባት ተገደለች:: ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ስለ ሰማዕታት በጻፈው ድርሳን ላይ በስፋት አመስግኗታል:: ለሴቶችም ታላቅ ምሳሌ ናት ብሏታል::

ቅዱሳት እናቶቻችንን ያጸና ቸር አምላካቸው እኛንም በሃይማኖትና በምግባር ያጽናን:: ከበረከታቸውም አብዝቶ ያድለን::

🕊

[  † ነሐሴ ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅድስት ማርያም መግደላዊት [ከ፴፮ [36]ቱ ቅዱሳት አንስት]
፪. ቅድስት ኢየሉጣ ሰማዕት [ ዘቂሣርያ ]
፫. አባ ዊጻ [ የታላቁ ሲኖዳ ደቀ መዝሙር ]

[   †  ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል

" ጌታ ኢየሱስም :- "ማርያም" አላት:: እርሷ ዘወር ብላ በእብራይስጥ :- "ረቡኒ" አለችው:: ትርጉዋሜውም "መምሕር ሆይ!" ማለት ነው:: ጌታ ኢየሱስም :- "ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ:: ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሔደሽ . . . ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው" አላት:: መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይሕንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች::" [ዮሐ.፳፥፲፮] (20:16)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
😭#የአፍሪካ_ሕብረት_ደብረ_ምሕረት_ቅዱስ_ሚካኤል ግቢ ሊፈርስ ነው

😭 ፍትህ ለቅድስት ቤተክርስቲያን በኮሪደር ልማት ስም
የአፍሪካ ህብረት ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ግቢ ሊፈርስ ነው


😭 የቤተክርስቲያኒቱን ይዞታ ለሌላ ቤተ እምነት ሲሰጦ" ስንጮኽ "ነበር  ህግ ይከበር ርቀት ይጠበቅ እያልን አሁን ደግሞ ጭራሽ የቤተክርስቲያኒቱን ግቢ ሊያፈርሱ ኑው።ይህ ሕዝብን መናቅ ነው።

በአዲስ አበባ ጠባብ ግቢ ካላቸው አብያተክርስቲያናት አንዱ አፍሪካ ሕብረት ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ነው። ይህ እየታወቀ ያቺንው ያለቺውን በኮሪደር  ምክንያት ግቢው ሊፈርስ  ነው።ይሄ መረጃው የደረሳችሁ የሚመለከታችሁ አካላት መፍትሔ ይደረግበት። ግቢው ፈረሰ ማለት እንደ መንገድ ላይ ሱቅ ቤተ መቅደሱ ብቻ ነው የሚቀረው ።

#ፍትሕ_ለእናት_ቤተክርስቲያን
መልእክቱን ሼር በማድረግ ያጋሩ።
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊 ቁጽረታ [ጽንሰታ] ለማርያም 🕊

ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል::
ስለ ምን ነው ቢሉ:-
ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው:: አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ::
"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ::"
"ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው::"
[መጽሐፈ ሰዓታት, ኢሳ.፩፥፱ ፣ መኃ.፬]

ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል::
የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ [አሮን] የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ: በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ: በማኅጸኗ ስትደርስ አየ::

እርሷ ደግሞ :- የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::

በሰባተኛው ቀን [ማለትም ነሐሴ ፯] መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ"
"ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ::
[ቅዳሴ ማርያም]

🕊 ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት 🕊

ዳግመኛ ይህች ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ ናት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በዚህች ቀን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልጶስ ይዟቸው ሔደ:: በዚያም ጌታ ከእነሱ ራቅ ብሎ ተቀምጦ ነበርና የማይሰማቸው መስሏቸው እርስ በእርስ ይከራከሩ ገቡ::

የክርክራቸው መነሻ ደግሞ ጌታችን ነበር:: የዋሃን [ገና ምሥጢርን ያልተረዱ] ነበሩና አንዱ ተነስቶ "ኤልያስ ነው": ሌላኛው "ሙሴ": ሦስተኛው "ኤርምያስ ነው" በሚል ተከራከሩ:: ቅዱስ ጴጥሮስ ለብቻው ቆሞ ነበርና ጠርተው "ሃሳባችንን አስታርቅልን:: ለአንተስ ማን ይመስልሃል?" አሉት::

አረጋዊው ሐዋርያም ተቆጣቸው:: "እናንተ እንደምታስቡት እርሱ ከነቢያት አንዱ ሳይሆን "እግዚአ ነቢያት-የነቢያት ፈጣሪ ነው" አላቸው:: ወዲያውም ጌታ ጠርቷቸው ወደ እርሱ ቀረቡ::

ቸር አምላክ "ለምን ተጠራጠራችሁኝ" ብሎ መገሰጽ ሲችል እንዳይደነግጡ ጥያቄውን በፈሊጥ አደረገ:: "የሰውን ልጅ ሰዎች ማን ይሉታል?" አላቸው:: እነርሱም በልባቸው ያለውን የሌላ አስመስለው ተናገሩ::

ጌታችን "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ጸጥ አሉ:: ገና ሃይማኖታቸው አልጸናም ነበርና:: በዚያን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ተነስቶ "አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው-አንተ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ ነህ" አለው:: [ማቴ.፲፮፥፲፮]

ይህች ቃል የክርስትና ሃይማኖት መሠረት ናትና ጌታችን "አንተ ዓለት ነህ" ብሎ የቤተ ክርስቲያንን በዚህ እምነት ላይ መመስረት ተናገረ:: ለቅዱስ ጴጥሮስም "መራሑተ መንግስት-የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ቁልፍ [ሥልጣን]" ተሰጠው::

ሊቀ ሐዋርያትነትንም ደረበ:: ዛሬ ለበርካቶቹ የጸነነባቸው ይሔው እምነት ነው::
ኢየሱስ ክርስቶስን "አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ ማርያም:
አካላዊ ቃል:
ሥግው ቃል:
ገባሬ ኩሉ:
የሁሉ ፈጣሪ"ብለው ካላመኑ እንኳን ጽድቅ ክርስትናም የለም::

🕊 አፄ ናዖድ ጻድቅ 🕊

ሃገራችን ኢትዮጵያ ምስፍና ከክህነት: ንግሥናን ከጽድቅ ያጣመሩ ብዙ መሪዎች ነበሯት:: ከእነዚህ አንዱ ደግሞ አፄ ናዖድ ናቸው:: ጻድቁ ንጉሥ የነገሡት ከ1487 እስከ 1499 ዓ/ም ሲሆን ለእመቤታችን በነበራቸው ልዩ ፍቅር ይታወቃሉ:: ካህን እንደ ነበሩም ይነገራል::

ዛሬ ሁላችን የምንወዳትን ጸሎት [ሰላም ለኪ: እንዘ ንሰግድ ንብለኪ . . .] የደረሷት እርሳቸው ናቸው:: ትልቁን መልክአ ማርያምም ደርሰዋል:: ይህ መልክእ ጣዕሙ ልዩ ነው::

የጻድቁ ንጉሥ ሚስት [ማርያም ክብራ] : ልጆቻቸው [አፄ ልብነ ድንግልና ቡርክት ሮማነ ወርቅ] እጅግ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩ:: ንጉሡ አፄ ናዖድ ከባለሟልነት የተነሳ ድንግል ማርያምን "እመቤቴ ስምንተኛው ሺ መቼ ይገባል? ጊዜውስ እንዴት ያለ ነው?" አሏት::

እመ ብርሃንም በአካል ተገልጻ የዘመኑንና የሰውን ክፋት ነገረቻቸው:: ንጉሡም አዝነው "እመቤቴ! ከዛ ዘመን አታድርሺኝ" አሏት:: በዚህ ምክንያት የስምንተኛው ሺህ ዘመን መስከረም 1 በ1500 ዓ/ም ሊገባ እርሳቸው ነሐሴ 7 ቀን በ1499 ዓ/ም ዐርፈዋል::

ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የድንግል እናቱን ጣዕም: ፍቅር: የቅዱስ ጴጥሮስን ሃይማኖትና የአፄ ናዖድን በረከት ያሳድርብን::

🕊 

† ነሐሴ ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

፩.በዓለ ጽንሰታ ለእግዝእትነ ማርያም
፪.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
፫.ቅዱስ ገብርኤል መበሥር
፬.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፭.አፄ ናዖድ ጻድቅ [ንጉሠ ኢትዮጵያ]
፮.ቅዱስ ዮሴፍ ጻድቅ
፯.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት

† ወርኀዊ በዓላት

፩.ሥሉስ ቅዱስ
፪.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫.አባ ሲኖዳ [የባሕታውያን አለቃ]
፬.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭.አባ ባውላ ገዳማዊ
፮.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯.ቅዱስ አግናጥዮስ

"መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው:: ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል:: የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! በአንቺ የተደረገው ድንቅ ነው . . . ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::" † [መዝ.፹፮፥፩-፮]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
2024/11/18 17:07:43
Back to Top
HTML Embed Code: