Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ †  እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።  † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊   †  ቅዱስ ናትናኤል  †   🕊

† በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ዘግይቶ ሰማዕትነትን የተቀበለ ይህ ቅዱስ ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ የተወለደው ከእሥራኤላውያን ወላጆቹ ጌታችን በተወለደበት ዘመን አካባቢ ነው:: ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ እርሱ ሕፃን እያለ ሔሮድስ 144,000 ሕፃናትን ሲፈጅ እርሱ ግን በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፏል:: እናቱ በቅርጫት ውስጥ አድርጋ የበለስ ዛፍ ላይ አስቀምጣው ተደብቃ ታጠባው ነበር::

ለሐዋርያው ወላጆቹ ያወጡለት ስም ስምዖን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ናትናኤል ብሎታል:: በባልንጀሮቹ ሐዋርያት ደግሞ የቃናው ስምዖን [ገሊላ ቃና አካባቢ ስላደገ] አንዳንዴም ቀናተኛው ስምዖን ይሉት ነበር::

ምሑረ ኦሪት ነበርና ዘወትር ለሕግ ይቀና ነበር:: በገሊላ ቃና ሰርግ የደገሰው ዶኪማስ የቅዱስ ናትናኤል የአጎት ልጅ ነው:: ጌታና ደቀ መዛሙርቱን ዶኪማስ የጠራበት አንዱ ምክንያትም ይሔው ነው::

ቅዱስ ናትናኤል ኦሪትን ከገማልያል ተምሮ: ከበለስ ቁጭ ብሎ ይተክዝ ነበር:: "መሲሕ ምነው ቀረህ?" እያለም ይተክዝ ነበር:: ማዕምረ ኅቡዓት አምላካችን ክርስቶስ ይህንን አውቆ በፊልጶስ አማካኝነት ጠርቶታል::

ናትናኤል ለጊዜው ተከራክሮ ነበር:: በኋላ ግን የጌታችንን ማንነት በደቂቃዎች ተረድቶ አምኗል:: ጌታችንም "ክዳት ሽንገላ በልቡ ውስጥ የሌለበት ንጹሕ እሥራኤላዊ" ሲል አመስግኖታል::

ሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል ከጌታችን እግር ሥር ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን ተምሮ: በጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሰክሮ: ብዙ አሕዛብን ከጨለማ [ጣኦት አምልኮ] ወደ ብርሃን [አሚነ ክርስቶስ] መልሷል:: እጅግ ብዙ መከራንም ተቀብሏል::

የጌታችን ወንድም የተባለ ቅዱስ ያዕቆብ በአይሁድ ከተገደለ በኋላም ቅዱስ ናትናኤል የኢየሩሳሌም ሁለተኛ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አገልግሏል:: ከአይሁድም ዘንድ ብዙ መከራ ደርሶበታል:: በመጨረሻም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት አልፏል:: በገድለ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ቅዱሱ ሰማዕት የሆነው በመቶ ሃምሳ ዓመቱ ነው:: ያ ማለት ደግሞ ከሐዋርያት አባቶች በመጨረሻ ያረፈው እርሱ ነው ያሰኛል::


🕊   †   አባ ብስንዳ   †     🕊

† ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ አባ ብስንዳ ይታሠባል:: አባ ብስንዳ በዘመነ ጻድቃን ምድረ ግብጽ ውስጥ ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ነው:: ቅዱሱን ከገድሉ ጽናት የተነሳ መላእክት በእጅጉ ይወዱት ነበር:: "እኔ ልሸከምህ - እኔ ልሸከምህ" እያሉ ይሻሙበት: በተራ በተራም ተሸክመውት ይውሉ ነበር:: እርሱም ለበርካታ ዓመታት ውኃ የሞላበት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ይጸልይ ነበር::

እንደ እሳት በሚባላው በረዶ ውስጥ ገብቶ መጸለዩ የፈጣሪውን ሕማማት ለመሳተፍ እና ለኃጥአን ምሕረትን ይለምን ዘንድ ነው:: ሁሌም በዘጠኝ ሰዓት መላእክት ተሠብስበው ይመጡና በብርሃን ሠረገላ ይሸከሙታል:: ከመሬትም ዘጠኝ ክንድ ከፍ ያደርጉት ነበር:: ከብዙ ዓመታት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሒዷል::

† እግዚአብሔር በቅዱስ ናትናኤል ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿንም ከመቅሰፍት ይሰውርልን:: ከሐዋርያው እና ከጻድቁ አባ ብስንዳ በረከትም አይለየን::

🕊

[  †  ሐምሌ ፲ [ 10 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ [ቀናተኛው ስምዖን]
፪. ታላቁ አባ ብስንዳ ጻድቅ
፫. አባ ከላድያኖስ ሊቀ ጳጳሳት

[   †  ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
፪. ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
፫. አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ወልደ እልፍዮስ]
፭. ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
፮. ቅዱስ ዕፀ መስቀል

" ጌታ ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ 'ተንኰል የሌለበት በእውነት የእሥራኤል ሰው እነሆ' አለ:: ናትናኤልም 'ከወዴት ታውቀኛለህ?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም መልሶ 'ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ በታች ሳለህ አየሁህ' አለው:: ናትናኤልም መልሶ 'መምሕር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ:: አንተ የእሥራኤል ንጉሥ ነህ' አለው::" † [ዮሐ. ፩፥፵፰-፶፩]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ †  እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።  † ]


† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊 † ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ ወሰማዕት †  🕊

† ቅዱስ ዮሐንስ በቀደመው ዘመን ከነበሩ ታላላቅ አበው አንዱ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ መርባስ ትባላለች:: ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚወዱ: ምጽዋትን የሚያዘወትሩና በበጐው ጐዳና የሚኖሩ ነበሩ:: ነገር ግን ልጅ በማጣታቸው ምክንያት ፈጽመው ያዝኑ: ይጸልዩም ነበር:: በተለይ ለመጥምቁ ዮሐንስ ልዩ ፍቅር ስለ ነበራቸው ዝክሩን ይዘክሩ: በስሙም ይማጸኑ ነበርና መጥምቁ ሰማቸው::

ወደ ፈጣሪውም ልመናቸውን በማድረሱ መልክ ከደም ግባት የተባበረለት ደግ ልጅን ወለዱ:: እጅጉን ደስ ስላላቸው በአካባቢያቸው የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስን ቤተ ክርስቲያን በገንዘባቸው አነጹ:: ሕፃኑንም በመጥምቁ ስም "ዮሐንስ" አሉት:: ጻድቁ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር አድሮበታልና ሕይወቱ ግሩም ነበር::

በሕፃን ገላው ይጾምና ይሰግድ: በልጅ አንደበቱም ተግቶ ይጸልይ ነበር:: ወላጆቹ ወደ እረኝነት ባሰማሩት ጊዜም መፍቀሬ ነዳያን ነውና ቁርስና ምሳውን ለነዳያን እያበላ እርሱ ጾሙን ይውል ነበር:: አባቱ የሚያደርገውን ሰምቶ ለማረጋገጥ ተከተለው:: እንዳሉትም እናቱ ጋግራ የሰጠችውን ትኩስ ዳቦ ለነዳያን ሲሰጥ አየው::

ሊቆጣው ፈልጐ "ዳቦህ የታለ?" ቢለው ሕፃኑ ቅዱስ ዮሐንስ "በአገልግሉ ውስጥ አለ" ሲል መለሰለት:: አባት ለመቆጣት እንዲመቸው አገልግሉን ሲከፍተው ግን ያየውን ማመን አልቻለም:: በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ዳቦዎቹ ትኩስ እንደሆኑ ተገኙ::

አባትም ወደ ቤቱ ወስዶ "ልጄ! አንተ የእግዚአብሔር ሰው ስለሆንክ እኛን ሳይሆን እርሱን አገልግል" ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላከው::

በዚህ ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ወደ ትምህርት ገባ:: በስድስት ዓመታትም ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቀ:: አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ደግነቱን ወደዋልና በግድ ቅስና ሾሙት:: እርሱ ግን ለተወሰነ ጊዜ አስተምሮ ዘመዱ የሆነውንና ዲያቆኑን ቅዱስ ስምዖንን አስከትሎ መነነ:: በዚያም በፍጹም ገድል ሲኖር ብዙ ተአምራትን ሰርቷል::

¤ አንድ ወታደር [አንድ ዐይና ነው] ሊባረክ ብሎ ሲጐነበስ የታወረች ዐይኑን የቅዱስ ዮሐንስ ልብስ ቢነካት በርታለታለች:: ከዚህ አልፎም ቅዱሱ ብዙ ድውያንን ፈውሷል: ለምጻሞችን አድኗል: አጋንንትን ከማደሪያቸው [ከሰው ላይ] አሳድዷል::

ታዲያ አንድ ቀን የወቅቱ የአንጾኪያ ንጉሥ የቅዱስ ዮሐንስን ዜና ይሰማል:: የእርሱ ልጅ ደግሞ አጋንንት አድረውባት ስቃይ ላይ ነበረችና የሚያድናት አልተገኘም:: ንጉሡ "ጻድቁን አምጡልኝ" ብሎ መልዕክተኛ ሲልክ ቅዱስ ዮሐንስ ደመና ጠቅሶ: በዚያውም ላይ ተጭኖ ከተፍ አለ:: ንጉሡ አይቶት ደነገጠ:: አባ ዮሐንስ ግን "እኔ ኃጢአተኛ የሆንኩ ሰው ለምን እንዲህ ትፈልገኛለህ?" ብሎ ታማሚዋን አስጠራ::

ጻድቁ እጆቹን አንስቶ ወደ ፈጣሪው ሲጸልይ በወጣቷ ላይ ያደረው ሰይጣን ሕዝቡ እያዩት ከሆዷ በዘንዶ አምሳል ወጥቶ ሔደ:: ንጉሡ ስለተደረገለት ውለታ ለቅዱስ ዮሐንስ ወርቅና ብር ብዙ ሽልማትም አቀረበ:: አባቶቻችን እንዲህ ዓይነት ነገር አይወዱምና ቅዱሱ "እንቢ አልወስድም" አለ::

ቅዱስ ዮሐንስ "ልሒድ" ብሎ ሲነሳ ንጉሡ "አባቴ ወድጄሃለሁና አትሒድ" ብሎ የልብሱን ዘርፍ [ጫፍ] ያዘው:: በቅጽበት ግን ደመና መጥታ ነጥቃ ወሰደችው:: የቀሚሱ ቁራጭም በንጉሡ እጅ ላይ ቀረች:: እርሱም ቤተ ክርስቲያን አሳንጾ ያችን የተባረከች ጨርቅ በክብር አኑሯታል::

ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ስምዖን [ደቀ መዝሙሩ] ግን ከብዙ የተጋድሎ ዓመታት በኋላ ሌላ ክብር መጣላቸው:: "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" የሚል ንጉሥ በመነሳቱም ሒደው በጌታችን ስም መሰከሩ:: በገድል በተቀጠቀጠ ገላቸው ላይ ግርፋትን: እሳትን ታገሱ:: በዚህች ቀንም አንገታቸውን ተቆርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታችቸውም ያድለን::

🕊

[  † ሐምሌ ፲፩ [ 11 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ አባ ዮሐንስ [ሰማዕት ወጻድቅ]
፪. ቅዱስ ስምዖን [ደቀ መዝሙሩ]
፫. አባ ኢሳይያስ ዘገዳመ አስቄጥስ
፬. አባ ገብርኤል ሊቀ ጳጳሳት

[    †  ወርኀዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ያሬድ ካህን
፪. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
፫. ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
፬. አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
፭. ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት

" ሒዳችሁም መንግስተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ:: ድውዮችን ፈውሱ: ሙታንን አንሱ: ለምጻሞችን አንጹ: አጋንንትን አውጡ:: በከንቱ ተቀብላችሁ በከንቱ ስጡ:: ወርቅ: ወይም ብር: ወይም ናስ በመቀነታችሁ: ወይም ለመንገድ ከረጢት: ወይም ሁለት እጀ ጠባብ: ወይም ጫማ: ወይም በትር: አታግኙ:: ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና:: " † [ማቴ. ፲፥፯]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊                        💖                       🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን፡፡ †

[          ሐምሌ ፲፪          ]

                         🕊                       

✞ እንኩዋን ለቅዱስ " ሚካኤል ሊቀ መላእክት " የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ " አባ ሖር " ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞

†  🕊  ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል  🕊

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት ሁሉ አለቃቸው : የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም በሆነ ተአምር ከከተማው ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል::

                        🕊                       

❝ በቅዱስ ፡ ሚካኤልም ፡ ጸሎትና ፡ ልመና ፡ ሀገር ፡ ከጥፋት ፡ ትድናለች።

ይልቁንም ፡ የቅዱስ ፡ ሚካኤል ፡ በዓሉ ፡ በሚከበርበት ፡ ዕለት ፡ ወይንና ፡ ስንዴ ፡ ጧፍ ፡ ዕጣን ፡ ለቤተ ፡ ክርስቲያኑ ፡ መባ ፡ የሰጠ : እስከ ፡ ግማሽ ፡ እንጀራም ፡ ቢሆን ፡ ለተራበ ፡ ያበላ ፡ እንዲሁም ፡ ቀዝቃዛ ፡ ውሀ : ለተጠማ ፡ ያጠጣ ፡ በክብር ፡ በምስጋና ፡ ዕድል ፡ ፈንታው ፡ ከቅዱሳንና ፡ ከሰማዕታት ፡ ጋር ፡ ይሆናል ፡ እስከ ፡ ዘላለሙ ፡ አሜን። ❞

[ ድርሳነ ሚካኤል  ]


🕊                        💖                       🕊
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"

              #ሐምሌ ፲፪ (12) ቀን።

እንኳን ለከበረ መልአክ ለመላእክት አለቃ #ለቅዱስ_ሚካኤል_የፋርስ_ንጉሥ ወደ ሆነ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት እግዚአብሔር ለላከበት ቀን #ንጉሥ_ሕዝቅያስን ረድቶ በአንድ ሌሊት ከሰናክሬም ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞች ለገደለበት ለወራዊ መታሰቢያ በዓልና ስርያቆስ ከሚባል አገር ለሆነ #ለአባ_ሖር ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #የአባ_ሖር_ማኅበር_ከመቶ_ሰባት_ወንዶችና_ከሃያ_ሴቶች_ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፡፡

                              
በዚች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል_የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ ወደ ሆነ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት እግዚአብሔር ላከው ከሰናክሬም ሠራዊት ከሰናክሬም ሠራዊትም መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞች ገደለ።

ይህም እንዲህ ነው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን በከበባት ጊዜ ሕዝቅያስንና ፈጣሪው እግዚአብሔርን እየዘለፈ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ እንዲህም አለ "እግዚአብሔር ያድናችኋል እያለ ሕዝቅያስ አያስታችሁ ከእጄ የሚያድናችሁ ማን ነው"።

የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እጅግ አዘነ ወገኖቹንና አገሩ ኢየሩሳሌምንም ያድን ዘንድ ማቅ ለብሶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀበሎ ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላከለት። ድንቅ ሥራንም ሠርቶ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አዳናቸው።

ስለዚህም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል መታሰቢያ በዚች ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ረድኤቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                             
✝️ #አባ_ሖር፦ ይህም አባት ስርያቆስ ከሚባል አገሩ ነው። አባቱም አንጠረኛ ነበር አንዲት እኅቱም ነበረችው። ጎልማሳም በሆነ ጊዜ ሰማዕት ይሆን ዘንድ ወደ አገረ ፈርማ ሔደ በመኰንኑም ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ከሥቃዩም ድኖ ተነሣ። መኰንኑም በእጁ ላይ ጌታችን ያደረገውን ይህን ተአምር አይቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ አመነ። በሌላ መኰንን እጅም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ በሰማዕትነት ሞተ።

✝️ ቅዱስ አባ ሖርን ግን ወደ እንዴናው ላከው በዚያም በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ አሠቃዩት በመንኰራኵሮችም አበራዩት ዘቅዝቀውም ሰቅለው በእሳት በአጋሉት የብረት በትር ደበደቡት። መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነትን አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 12 ስንክሳር።

                          ✝️ ✝️ ✝️
✝️ "#ሰላም_ለሖር_በኀበ_እግዚኡ_ዘተመዝገነ። አመ ጽዕለተ ተወክፈ ወበትረ ኀፂን ርሱነ። ወሶበ እምኔሁ ነጸረ ዕበየ ተአምር ዘኮነ። ምስለ ብእሲቱ ወደቂቁ ከዊኖ ፍልጣነ። በእደዊሁ መኰንን አምነ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_12

                           ✝️ ✝️ ✝️
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦"ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዓውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታምእሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ 33፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 24፥30-36።

                          ✝️ ✝️ ✝️
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኀ ሠራዊቱ። ወያርብህኒ ኢድኅነ በብዝኃ ኃይሉ። ወፈረስኒ ሐሰት ኢያድኅን"። መዝ 32፥16-17። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 9፥17-30፣ ይሁ 1፥7-14 እና የሐዋ ሥራ 10፥3-9። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥1-9። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል የወራዊ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።


@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=10006389661688     

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw  
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

🕊  †  ሐምሌ ፲፪   †     🕊

[ †   እንኩዋን ለቅዱስ "ሚካኤል ሊቀ መላእክት"
የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ "አባ ሖር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ  † ]



🕊 †  ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል  †   🕊

ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም በሆነ ተአምር ከከተማው ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደት ፯ መቶ [700] ዓመታት በፊት ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር:: ደጋጉ ዳዊትና ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም ነበር::

ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሕዛብ [የአሦር] ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት:: ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ ከ፻፹፭ ሺህ [185,000] በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ ማነው? ሕዝቡንም እግዚአብሔር ያድናል ብለህ አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ አንደበት እንዲሕ አለ :- "ስለ ባሪያየ ስለ ዳዊት ከተማዋን አድናታለሁ::"

በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ ቅዱስ_ሚካኤል ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው ከአሕዛብ ሠራዊት ፻፹፭ ሺህ [185] ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ:: በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

በድንጋጤ ወደ ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ ልጆች [አድራማሌክና ሳራሳር] ገደሉት:: ትዕቢተኛው ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: [፩ነገ.፲፰፥፲፫] [፲፱፥፩] (18:13, 19:1)

🕊 †  ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት  †   🕊

ዳግመኛ በዚህ ቀን አባ_ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል::

ቅዱሱ :-

¤ ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ:
¤ ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ:
¤ ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ:
¤ ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት:
¤ ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው::

እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል:: በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው ፻፳፯ [127] ወንዶችና ፳ [20] ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል::

እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን:: ከሰማዕቱም በረከት ያሳትፈን::

🕊 

[  †  ሐምሌ ፲፪ [ 12 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
፪. ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
፫. ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
፬. ፻፵፯ "147" ሰማዕታት [የአባ ሖር ማሕበር]

[   †  ወርሐዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
፪. ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ [ ንጉሠ ኢትዮዽያ ]
፫. ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ድሜጥሮስ
፭. ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
፮. ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ [ ሰማዕት ]
፯. ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
፰. አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

" እግዚአብሔር ይላል :- ስለ እኔም ስለ ባሪያየም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ:: በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ:: ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ:: ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: +" [፩ነገ.፲፱፥፴፬] (19:34)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ብስንድዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።  † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  † ቅዱስ ብስንድዮስ ጻድቅ †  🕊

† ቅዱስ ብስንድዮስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ድንቅ ሥራ ከሠሩት እንደ አንዱ ሆኖ ይዘከራል:: ቅዱሱ ግብጻዊ ሲሆን በልጅነቱ ወደ ትምሕርት ቤት ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: የሚገርመው የብሉይም ሆነ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ያጠናቸው በቃሉ ነበር::

በእርግጥ ይሕንን ማድረግ የቻሉ በርካታ የሃገራችን ሊቃውንት ዘንድሮም አሉ:: ልዩነቱ ግን ወዲህ ነው:: ቅዱስ ብስንድዮስ መጻሕፍቱን ያጠናቸው ለሕይወት እንጂ ለእውቀት አልነበረምና ሁሌም ነግቶ እስከ ሚመሽ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እያጣጣመ ይጸልይ ነበር:: ይሕንን ሲያደርግ ደግሞ
ባጭር ታጥቆ ጫማውን አውልቆ: በባዶ ሆዱ ቁሞ ነው::

ታዲያ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ክፍል ሲጸልይ ነቢይ ቢሆን ሐዋርያ ወደ እርሱ ይወርድለት ነበር:: ለምሳሌ ዘፍጥረትን ሲጸልይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ይመጣና ከፊቱ ተቀምጦ ይሰማዋል:: ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ሲደርስ ኢሳይያስ: ወንጌለ ማቴዎስ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ማቴዎስ ይመጡና ደስ እያላቸው ያደምጡት ነበር::

አንዱ ነቢይ: ወይ ሐዋርያ ሲወጣ ቅዱስ ብስንድዮስን ባርኮ ሌላኛውን ተክቶ ነው:: በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሕይወት በምድር እያለ ሰማያዊ ሆነ: ሰማንያ አንዱን አሥራው መጻሕፍት የጻፉ ቅዱሳንን ለማየት በቃ: በእጆቻቸውም ተባረከ::

የቅዱስ ብስንድዮስ ቀጣይ የሕይወቱ ተግባር ብሕትውና ሆነ:: ዓለምንና ግሳንግሷን ትቶም ወደ በርሃ መነነ:: በአጽንዖ በዓት: በጾምና በጸሎት: በትሕርምትም ተጋደለ:: በየደረሰበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር በእጆቹ ድንቅ ተአምር ይሠራ ነበር:: ብዙ ድውያንን ፈወሰ: አጋንንትንም ከአካባቢው አሳደደ::

በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ግን ስዕለት ስላለበት ሴቶችን ላለማየት ይጠነቀቅ ነበር:: በሆድ ሕመም ትሰቃይ የነበረችና ጥሪቷን በመድኃኒት የጨረሰች አንዲት ሴት ስለ ቅዱሱ ዝና ትሰማለች:: ችግሩ ግን እርሱ ከውዳሴ ከንቱና ከሴት የሚርቅ ነውና እንዴት ብላ ታግኘው? አንድ ቀን ከበዓቱ አካባቢ ተደብቃ ውላ ሲመጣ የልብሶቹን ዘርፍ ለመንካት በእምነት አሰበች::

ልክ ከበዓቱ ሲዘልቅ ስሉጥ [ፈጣን] ነበርና ገና እንዳያት ሩጦ አመለጣት:: እንዳትከተለው ድውይ ናትና አልቻለችም:: አዝና ዝቅ ስትል ግን የረገጠውን ኮቲ ተመለከተች:: በፍጹም ልቧ: በእምነት "የጻድቁ አምላክ ማረኝ" ብላ ከአፈሩ ቆንጥራ በላች:: ደቂቃ አልቆየችም:: ፈጥና ከደዌዋ ዳነች:: እንደ እንቦሳ እየዘለለች ወደ ከተማ ሔዳ ተአምሩን ተናገረች::

ከእነዚህ ዘመናት በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅፍጥ [Qift] በምትባል ሃገር ጵጵስናን [እረኝነትን] ተሹሟል:: ወደ ከተማ ሲገባ የቀደመ ተጋድሎውን ቸል አላለም:: ይልቁኑ ይተጋ ነበር እንጂ:: ከብቃት መዓርግ ደርሷልና ሲቀድስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገሃድ ያየው: ሠራዊተ መላእክትም ይከቡት ነበር::

ሕዝቡ ሊቆርቡ ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይታየው ነበር:: የበቁትን እያቀበለ: ያልበቁትን እየመከረና ንስሐ እየሰጠ ይመልሳቸዋል:: እንዲሕ በጽድቅ: በሐዋርያዊ አገልግሎትና በንጽሕና ተመላልሶ ቅዱስ ብስንድዮስ በዚህች ቀን ዐርፏል::

ቅዱስ ብስንድዮስ ካረፈ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ከመግነዙ ጥቂት ቆርጦ አስቀርቶ ብዙ ድውያንን ፈውሶበታል::

† ቸር አምላክ ለአባቶቻችን የሰጠውን ጸጋ ለእኛ ለባሮቹም አይንሳን:: ከቅዱሱ በረከትም ያድለን::

🕊

[  † ሐምሌ ፲፫ [ 13 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ ብስንድዮስ ሊቅ ወጻድቅ
፪. ቅዱስ አሞን ሰማዕት [ዘሃገረ ጡህ]

[   † ወርኀዊ በዓላት    ]

፩. እግዚአብሔር አብ
፪. ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
፫. ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
፬. ቅዱስ አስከናፍር
፭. አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
፮. ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
፯. አቡነ ዘርዐ ቡሩክ


" አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር:: ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና:: ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል:: የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጐ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምሕርትና ለተግሣጽ: ልብንም ለማቅናት: በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል:: " † [፪ጢሞ. ፫፥፲፬]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"

              #ሐምሌ ፲፬ (14) ቀን።

እንኳን ልክ እንደ #ቅዱስ_ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሊሰቃይ ሲሔድ #ጌታችን_ለኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጾ ለመለሰው #ለቅዱስ_አብሮኮሮንዮስ_ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ለመነኰሳት አለቃ #ለታላቁ_አባት_አባ_መቃርስ_ለመታሰቢያ_በዓሉ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከሰማዕቱ_አሞንዮስ_ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                            
#ሰማዕቱ_ቅዱስ_አብሮኮሮንዮስ፦ የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ከኢየሩሳሌም ነው የአባቱ ስም ክርስቶፎሮስ ነው ትርጓሜውም ክርስቶስን የለበሰ ማለት ነው ክርስቲያንም ነበረ የእናቱም ስም ቴዎዶስያ ነው እርሷ ግን ጣዖትን ታመልክ ነበረች።

አባቱም በዐረፈ ጊዜ እናቱ ወሰደችው ከእርሱም ጋራ ብዙ ገንዘብ ይዛ ወደ አንጾኪያ ከተማ ሔደች ልጅዋንም በእስክንድርያ ከተማ ገዥ አድርጎ ይሾመው ዘንድ ለዲዮቅልጥያኖስ እጅ መንሻ ሰጠችው እርሱም ሾመው የሹመት ደብዳቤውንም ጽፎ ክርስቲያኖችን እንዲአሠቃዩ አዘዘው።

ከአንጾኪያም ከተማ ወጥቶ ጥቂት እንደ ተጓዘ ወደእርሱ የሚያስፈራ ቃል ከሰማይ መጣ በስሙ ጠርቶ እንዲህ አለው "ከሀዲው ዲዮቅልጥየኖስ እንዳዘዘህ ብታደርግ አንተ በክፉ አሟሟት ትሞታለህ። እርሱም "ራስህን ትገልጥልኝ ዘንድ ጌታዬ ሆይ እለምህሃለሁ" አለው ወዲያውኑም የብርሃን መስቀል ታየው ዳግመኛም "በኢየሩሳሌም የተሰቀልኩ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ" የሚለውን ቃል ሰማ።

ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ተመልሶም ከአንጥረኛ ዘንድ የወርቅ መስቀል አሠራ ከዚያም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ተጓዘ በጒዞውም ውስጥ ሊገድሉት ዐመፀኞች አረማውያን ተነሡበት እርሱም በእነርሱ ላይ በርትቶ ክብር ይግባውና በጌታ ክርስቶስ መስቀል ድል አደረጋቸው። እናቱም "በጦርነት ላይ ለረዱህና ላዳኑህ አማልክት መሥዋዕትን ሠዋ" አለችው እርሱም እንዲህ አላት "እኔስ አዳኝ በሆነ በመስቀሉ ኃይል ላዳነኝ ክብር ይግባውና ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ"። ይህንንም በሰማች ጊዜ ልጅዋ አብሮኮሮንዮስ ክርስቲያን እንደሆነ ወደ ዐመፀኛው ዲዮቅልጥያኖስ ልካ ነገረችው። ዲዮቅልጥያኖስም ጭፍራ ልኮ ወደ ቂሣርያ ከተማ አስወሰደው የቂሣርያውንም ገዥ ስለ ርሱ እንዲመረምርና እንዲአሠቃየው አዘዘው።

ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ በአቀረቡት ጊዜ በፊቱ ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ለመሞት እስቲደርስም ጽኑዕ ግርፋትን ገረፈው ከዚህም በኋላ አሠረው። በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ብርሃን ውስጥ ታየው ከእርሱም ጋራ ብርሃናውያን መላእክት ነበሩ ከማሠሪያውም ፈታውና በመለኮታዊ እጁ ዳሰሰው ከቍስሎቹም ሁሉ አዳነው።

በማግሥቱም መኰንኑ ስለ ቅዱሱ ዜና ሙቶ እንደሆነ ወይም አልሞተ እንደሆነ ጠየቀ ለእርሱ የሞተ መስሎት ነበረና። ቅዱሱም በመጣ ጊዜ ጤነኛ ሁኖ አየውና መኰንኑ አደነቀ በዚያ የነበሩ ሕዝቡም አይተው እጅግ አደነቁ እንዲህም እያሉ ጮኹ "እኛ በግልጥ ክርስቲያን ነን በቅዱስ አብሮኮሮንዮስ አምላክ እናምናለን"። ከእነርሱም ጋራ ሁለት መኳንንትና ዐሥራ ሁለት ሴቶች እናቱ ቴዎዶስያም ነበሩ መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ። እነርሱም ቆረጡአቸው። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ሐምሌ ስድስት ቀን ተቀበሉ።

ቅዱስ አብሮኮሮንዩስን ግን ምን እንደሚያደርግበት እስቲአስብ ድረስ ሦስት ቀን አሠረው ከዚህም በኋላ አውጥቶ እንዲህ አለው "ልብህ እንዲመለስ ነፍስህንም እንድታድን ለአማልክትም እንድትሠዋ እነሆ በአንተ ላይ ሦስት ቀናት ታገሥኩ"። ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት "መኰንን ሆይ የለም ልቤ ወደ ስሕተት አይመለስም ክብር ይግባውና ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ አውቄ ተረድቼአለሁ ጣዖታቱም ሁሉ ከዕንጨትና ከደንጊያ በሰው እጅ የተሠሩ ፍጡራን ናቸው እንጂ አማልክት አይደሉም አይጐዱም አይጠቅሙም"።

መኰንኑም ሰምቶ እጅግ ተቆጣ ጐኖቹንም በሰይፍ እንዲሰነጣጥቁ አዘዘ አርኬላዎስ የሚባል ባለ ሰይፍም የቅዱሱን ጐኖቹን ሊሠነጥቅ እጁን ዘረጋ ያን ጊዜም እጁ ደረቀች ወድቆም ሞተ። መኰንኑም ተቆጥቶ በምድር ጥለው ይገርፉት ዘንድ አዘዘ እንደ አዘዘም ገረፉት በሰይፍም ጐኖቹን ሠንጥቀው በቍስሉ ውስጥ መጻጻ ጨመሩ እስከ ወህኒ ቤትም ድረስ በእግሩ ጐተቱት በዚያም ሁለት ቀኖች ኖረ ከዚህም በኋላ አውጥቶ እሳትን በተመላች ጕድጓድ ውስጥ ጣለው ክብር ይግባውና ጌታችንም አዳነው ምንም ምን አልነካውም።

ብዙ ከማሠቃየቱም የተነሣ መኰንኑ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                          
"#ሰላም_ለአብሮኮሮንዮስ_በኢየሩሳሌም ዘተወልደ። እምለባሴ ክርስቶስ አቡሁ በአርዑተ ወንጌል ዘተጸምደ። በትእዛዘ ንጉሥ ሠዊዐ ሶበ ለጣዖት ፈቀደ። ቃል ዘይከልኦ እምሰማይ ወረደ ወበቊስላቲሁ አንበረ መለኮት እደ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_14

                          

@sigewe

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA

https://www.facebook.com/profile.php?id=10006389661688

https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKw
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (ተአምኆ ቅዱሳን)
2024/10/01 19:32:25
Back to Top
HTML Embed Code: