Telegram Web Link
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
🕊

[ † እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ እና ለመነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

†  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊 † ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት †  🕊

† ቅዱሱ ተወልዶ ያደገው በአንጾኪያ [ሶርያ] በ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: አባቱ ደግ ክርስቲያን የነበረ ሲሆን ስሙ ክርስቶፎሮስ ይባላል:: "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ ማለት ነው:: እናቱ ግን ቴዎዳስያ የምትባል አረማዊት ነበረች:: ምንም እንኩዋ አባቱ ክርስቲያን ቢሆን እናቱ ኃይለኛ የቤተ መንግስት ሰው ስለነበረች በልጅነቱ አብሮኮሮንዮስ ክርስትናን ሊማር አልቻለም::

የልጁን አረማዊ መሆን ያልወደደ አባት አማራጩ አንድ ብቻ ነበር:: እሱም ወደ ጌታ መለመን ነበር:: በእንዲሕ ያለ ግብር ዘመናት ጐርፈው አብሮኮሮንዮስ ክርስቶስን ሳያውቅ ፳ [20] ዓመት ሆነው:: እናቱ ወስዳ: አሰልጥና ለጣዖት አምላኪ ንጉሥ ሰጠችው:: ንጉሡም የጦር አለቃ አድርጐ ሾመውና አንድ ትዕዛዝ ሰጠው:: "ክርስቲያኖችን ሁሉ ባገኘህበት ቦታ ጨፍጭፍ:: ቤታቸውንም አቃጥል::"

አብሮኮሮንዮስ የታዘዘውን ሊፈጽም ሠራዊት አስከትሎ ሲወጣ ግን የአባቱ የ፳ [20] ዘመናት ለቅሶና ጸሎት ፍሬ አፈራ:: ገና መንገድ ላይ ሳለ ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ_ክርስቶስ ድምጹን ከሰማይ ላከለት:: "ወደ እውነተኛ መንገድ ተመለስ:: ካልሆነ ግን ሾተሉን ብትረግጥ ላንተ ይብስብሃል" አለው::

አብሮኮሮንዮስም እየተንቀጠቀጠ "አቤቱ አንተ ማነህ?" አለው:: ጌታም "ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ" ሲል መለሰለት:: ዳግመኛም "ምልክት ስጠኝ" ቢለው የብርሃን መስቀል በሰማይ ላይ ገለጠለት:: ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ጊዜ አላጠፋም::

ሠራዊቱን ይዞ ወደ ንጉሡ ከተማ ተመልሶ ንጉሡን በድፍረት አለው :- "እኔ ክርስቲያን ነኝ:: ክርስቶስንም አመልካለሁ::" ካነጋገሩ የተነሳ አባቱን ደስ ሲለው ንጉሡና እናቱ ግን ደነገጡ:: ንጉሡ ሊያስፈራራው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: ከዚያማ ያሰቃየው ገባ::

አንድ ቀን አካሉ እስኪቆራረጥ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: ሞተ ብለው አስበው ነበር:: ወደ እርሱ ሲመለሱ ግን ጌታችን አድኖታልና የሰንበር ምልክት እንኩዋ በአካሉ ላይ አልተገኘም:: እናቱ ቴዎዳስያ ከዚህ በላይ ምልክትን አልፈለገችም:: በደቂቃዎች ልዩነት እርሷም ወደ ክርስትና ተመለሰች:: ልጇንም ቀድማ ሐምሌ ፮ [6] ቀን ሰማዕት ሆነች::

ቅዱስ አብሮኮርዮስን ግን ለበርካታ ጊዜያት አሰቃይተው ከክርስቶስ ፍቅር ሊለዩት ባለመቻላቸው በዚህች ቀን ገድለውታል:: አባት: እናትና ልጅ [ክርስቶፎሮስ: ቴዎዳስያና አብሮኮሮንዮስ] ለሰማያዊ ርስት በቅተዋል:: አባት ይሏቹሃል እንዲህ ነው!


🕊 †  ታላቁ ቅዱስ መቃርስ  †   🕊

† በገዳማዊ ሕይወቱ እንደ ዘንባባ ያፈራው: የመነኮሳት ሁሉም አለቃቸው ቅዱስ መቃርስ አንድ ቀን እንዲህ አደረገ :-

አንድ በከተማ የሚኖር ባለ ጸጋ ስለ ቅዱስ መቃርስ ዝና ሰምቶ ሊባረክ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ይመጣል:: አባ መቃርስ ባለ ጠጋው ወደ እርሱ እየመጣ መሆኑን ሲያውቅ በወንድሞች መነኮሳት መካከል ልብሱን ጥሎ እንደ አበደ ሰው አለል-ዘለል እያለ ይጫወት ጀመረ::

ያ ከተሜ ባለ ጠጋ እንደ ደረሰ ወደ መነኮሳቱ ጠጋ ብሎ "የታላቁን መቃርስ ዝና ሰምቼ ልባረክ ነበር የመጣሁት:: ከእናንተ መካከል ማንኛው ነው?" ቢላቸው "ያውልህ" ብለው አሳዩት:: ሲያየው እንደ እብድና ሕጻን እየዘለለ ይጫወታል:: ባለጠጋውም "ወይኔ! እኔኮ ደኅና ሰው መስሎኝ ነው:: በከንቱ ደከምኩ" ብሎ እያዘነ ሔደ:: ወዲያው መነኮሳት ተሰብስበው ቅዱስ መቃርስን "ለምን እንደዚህ አደረግህ?" ቢሉት "መጀመሪያ እንደ ሰውነቴ ሊያከብረኝ ይገባል" በሚል መልሷል:: በርግጥም ከምንም ነገር በፊት ሰውን በሰውነቱ [በእግዚአብሔር አርአያ በመፈጠሩ] ብቻ ልናከብር ይገባል::

† ታላቁ ቅዱስ መቃርስ በቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዓሉ ይከበራል::

† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታችቸውም ያድለን::

🕊

[  †  ሐምሌ ፲፬ [ 14 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት  ]

፩. ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ ሰማዕት
፪. ቅዱሳን ክርስቶፎሮስና ቴዎዳስያ [ወላጆቹ]
፫. ታላቁ ቅዱስ መቃርስ [የመነኮሳት አለቃ]
፬. ቅዱስ አሞንዮስ

[    †  ወርሐዊ በዓላት     ]

፩. አቡነ አረጋዊ [ዘሚካኤል]
፪. ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ሙሴ [የእግዚአብሔር ሰው]
፭. አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮. አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯. እናታችን ቅድስት ነሣሒት

" ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጐ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ:: አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ: አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ:: ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ:: የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ_ኢየሱስ ካሉ: ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ::" †††  [፩ጢሞ.፩፥፲፪]  (1:12)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
Audio
Forwarded from ገድለ ቅዱሳን (♱ ባሕራን ♱)
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ †††

††† እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው ንጽቢን በምትባል የሶርያ ግዛት ውስጥ በ298 / 306 ዓ/ም ነው:: ወላጆቹ በክርስቶስ የማያምኑ አላውያን ነበሩ:: (ምንም አንዳንድ ምንጮች ክርስቲያኖች ነበሩ ቢሉም)

ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ንጽቢን ጵጵስናን የተሾመ ቅዱስ ያዕቆብ የሚባል ታላቅ ሰው ነበር:: የሰማዕትነት: የሐዋርያነት: የጻድቅነትና የሊቅነት ግብር ያለው አባት ነው:: ታዲያ ቅዱስ ኤፍሬም ይሔ አባት ሁሌ ሲያስተምር ይሰማው ነበርና በስብከቱ ተማርኮ ደቀ መዝሙሩ ለመሆን በቃ::

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱስ ያዕቆብ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ሙሉ የወጣትነት ጊዜውን ያሳለፈው በትምሕርት ነው:: የሚገርመው መምሕሩ ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍጹም ልቡ የሚወድና ጠርቷት የማይጠግብ አባት ነውና ለልጁ ለቅዱስ ኤፍሬም ይሕንኑ አጥብቆ አስተምሮታል::

ቅዱስ ኤፍሬም ክርስትናን ሲመረምር የእመቤታችን ፍቅር ይበዛለት ጀመር:: ምክንያቱም እመ ብርሃንን ሳይወዱ ክርስትና የለምና:: እንደ እርሱ የሚወዳት የለም እስኪባል ድረስ ያገለግላት: ይገዛላትም ገባ::

እንዲህ እንደ ዛሬ የድንግል ማርያም ምስጋና በአንደበት እንጂ በመጽሐፍ አይገኝም ነበር:: እርሱ ግን ከወንጌለ ሉቃስ በስድስተኛው ወርን (ይዌድስዋን) እና ጸሎተ ማርያምን(ታዐብዮን) አውጥቶ በየዕለቱ በዕድሜዋ ልክ ስልሳ አራት ስልሳ አራት ጊዜ ያመሰግናት ነበር::

በእንዲህ ያለ ግብር እያለ አርዮስ በመካዱ እርሱን ለማውገዝና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማጽናት በ317 (325) ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በኒቅያ ሲሰበሰቡ አንዱ መምሕረ ኤፍሬም ቅዱስ ያዕቆብ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ኤፍሬም ከሊቃውንቱ ትምሕርትና በረከትን አግኝቷል::

ከጉባዔ መልስ መንገድ ላይ በራዕይ የብርሃን ምሰሶ አይቶ "ጌታ ሆይ! ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ "ይሕማ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ነው::" አለው:: እርሱም መምሕሩን ቅዱስ ያዕቆብን ተሰናብቶ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ (ቂሣርያ) ወረደ:: ተገናኝተውም በአንድ ሌሊት ቋንቋ ተገልጦላቸው ሲጨዋወቱ አድረዋል::

በቦታው ብዙ ተአምራት ተደርጓል:: ቅዱስ ኤፍሬም ከታላቁ ባስልዮስ ከተማረ በኋላ ሃገረ ስብከት ተሰጥቶት ያስተምር ጀመር:: ሁል ጊዜ ታዲያ ጸሎቱ ይሔው ነበር:: "እመቤቴ ሆይ! ምስጋናሽ እንደ ሰማይ ከዋክብት: እንደ ባሕር አሽዋ በዝቶልኝ: እንደ እንጀራ ተመግቤው: እንደ ውኃ ጠጥቼው: እንደ ልብስም ተጐናጽፌው" እያለ ይመኝ ነበር::

አፍጣኒተ ረድኤት: ፈጻሚተ ፈቃድ እመ ብርሃንም በገሃድ ተገልጻ የልቡን ፈቃድ ፈጸመችለት:: ዛሬ ጸጋ በረከት የምናገኝበትን ውዳሴ ማርያምን ደረሰላት:: ሲደርስላትም እርሷ አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላ ወርዳ: በፊቱም ተቀምጣ ሲሆን እርሱ ደግሞ ባጭር ታጥቆ: በፊቷ ቆሞ: በመንፈስ ቅዱስም ተቃኝቶ ነው::

ውዳሴዋን በሰባት ቀናት ከደረሰላት በኋላ በብርሃን መስቀል ባርካው: ሊቀ ሊቃውንትም እንዲሆን ምሥጢር ገልጣለት ዐረገች:: ከዚህ በኋላ በምሥጢር ባሕር ውስጥ ዋኝቶ አሥራ አራት ሺህ ድርሰቶችንም ደርሷል:: ዛሬ ሶርያ ውስጥ የምንሰማውን ዜማም የደረሰው ይህ ቅዱስ ነው::

እንዲያውም አንድ ቀን የምሥጢር ማዕበል ቢያማታው "አሃዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ" ብሎ ጸልዩዋል:: (የጸጋህን ማዕበል ያዝልኝ) እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በመጨረሻ ሕይወቱ ተክሪት በምትባል ሃገር ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሹሟል::

በጣፋጭ ስብከቱ ብዙዎችን ካለማመን መልሷል:: የምዕመናንንም ሕይወት አጣፍጧል:: ለመናፍቃንና ለአርዮሳውያን ግን የማይጋፉት ግድግዳ ሆኖባቸው ኑሯል:: በዘመኑም ብዙ ተጋድሎ አፍርቷል:: ተአምራትንም ሠርቷል:: በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ በ365 (373) ዓ.ም ዐርፎ ተቀብሯል::

††† ቅዱሱ ለሶርያ ብቻ ሳይሆን እመቤታችንን ለምንወድ የዓለም ክርስቲያኖች ሁሉ ሞገሳችን ሆኗል:: ስለዚህም እንዲህ እያልን እንጠራዋለን:-
1.ቅዱስ ኤፍሬም
2.ማሪ ኤፍሬም
3.አፈ በረከት ኤፍሬም
4.ሊቀ ሊቃውንት ኤፍሬም
5.ጥዑመ ልሳን ኤፍሬም
6.አበ ምዕመናን ኤፍሬም
7.ርቱዐ ሃይማኖት ኤፍሬም . . . አባታችን አንተ ነህ::

††† ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ለቅዱስ ኤፍሬም የሰጠሽውን ጸጋውን: ክብሩን: አእምሮውን: ለብዎውን በልቡናችን ሳይብን: አሳድሪብን . . . አሜን::

††† ጴጥሮስ ወጳውሎስ †††

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ይታሠባሉ::

ቅዱሳኑ ሶርያ አካባቢ ውስጥ ወደምትገኝ አንዲት ሃገር ገብተው ሕዝቡን ከንጉሣቸው ጰራግሞስ ጋር አሳምነው አጥምቀዋል:: ነገር ግን እነርሱ ሲወጡ ሰይጣን አስቶት አጥፊ ሰው ወደ መሆን ተመልሶ ንጉሡ ሐዋርያትን አሰቃይቷቸዋል::

ስለ ቅዱሳኑ ግን ፈረሶቹ ሰግደው: በሰው አንደበት ቅድስናቸውን መስክረዋል:: በመጨረሻም ንጉሡን ከነ ሕዝቡና ሠራዊቱ በዓየር ላይ ሰቅለው ንስሐ ሰጥተውታል:: በእነዚህ ተአምራትም ሁሉም አምነው ለከተማዋና ለሕዝቡ ድኅነት ተደርጓል::

††† ከአባቶቻችን አበው ሐዋርያት በረከት ይክፈለን::

††† ሐምሌ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ብርሃናተ ዓለም ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስ ወጳውሎስ
3.አባ ሓርዮንና ደቀ መዛሙርቱ (ሰማዕታት)
4.አባ ፍሬምናጦስ መስተጋድል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

††† "ለምኑ ይሰጣችሁማል:: ፈልጉ ታገኙማላችሁ:: መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል:: የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና:: የሚፈልገውም ያገኛል:: መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል::" †††
(ማቴ. ፯፥፯)

††† "የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም::" †††
(መዝ. ፴፯፥፴)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
õ Eñ5 B-F5 ÈEõ5u ¢è # ØÈ-
ASR by NLL APPS
ገድለ ቅዱስ ቂርቆስ ወቅድስት ኢየሉጣ ዘወርሃ ሐምሌ. https://www.tg-me.com/SinkisarZekidusan2
††† እንኳን ለቅዱስ አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ) †††

††† ቅዱሱ "ወንጌሉ ዘወርቅ" እየተባለ የሚጠራው ከሌሎች ዮሐንስ ከሚባሉ ቅዱሳን ለመለየት ቢሆንም ዋናው ምክንያት ግን እድሜ ልኩን የሚያነበው: ከእጁ የማይለየውና አቅፎት የሚተኛ በወርቅ የተለበጠ ወንጌል ስለ ነበረው ነው::

የቅዱስ ዮሐንስ ታሪኩ ከመርዓዊ (ሙሽራው) ገብረ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ሙሴ ሮማዊ ጋር ተመሳሳይነት አለው::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በሮም ግዛት ሥር የሚኖሩ አጥራብዮስና ብዱራ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ነበሩ:: እግዚአብሔር በቀደሰው ትዳር የሚኖሩና ነዳያንን የሚዘከሩ ነበሩና ይህንን ቅዱስ ወለዱ:: ስሙን ዮሐንስ ብለው: እንደሚገባም አሳድገው: ምሥጢረ መንግስተ ሰማያትን እንዲረዳ ለመምህር ሰጡት:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመምህሩ ዘንድ ቁጭ ብሎ መጻሕፍተ ቤተ ክርስቲያንን ተማረ::

ለወላጆቹ ቅንና ታዛዥ ነበርና አባቱ "ልጄ! የምትፈልገውን ጠይቀኝ:: ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" አለው:: ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድሮ እኛን የሚያምረን ሁሉ አላሰኘውም:: አባቱን "ቅዱስ ወንጌልን ግዛልኝ: በወርቅም አስለብጠው" አለው:: አባትም የተባለውን ፈጸመ::

ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ከዚህ ዓለም ተለይቶ እስካረፈባት ቀን ድረስ ቅዱስ ዮሐንስና የወርቅ ወንጌሉ ተለያይተው አያውቁም:: ሁሌም ያለመታከት ያነበዋል:: ሲቀመጥም ሲነሳም: ሲሔድም ሲተኛም አብሮት ነበር::

ቅዱስ ዮሐንስ ወጣት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይድሩት ዘንድ ተዘጋጁ:: ልብሰ መርዐም (የሙሽራ ልብስ) አዘጋጁ:: በዚያው ሰሞን ግን አንድ እንግዳ መነኮስ ወደ ቤታቸው መጥቶ ያድራል:: በዚያች ሌሊት መነኮሱ በጨዋታ መካከል ስለ ቅዱሳን መነኮሳት ተጋድሎና ክብር ነገረው:: የሰማው ነገር ልቡናውን የማረከው ቅዱስ ዮሐንስ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደ ፈጣሪው ይለምን ነበር::

አንድ ቀን ግን ያ መነኮስ በድጋሚ መጥቶ አደረ:: ቅዱስ ዮሐንስ መነኮሱን ወደ ገዳም እንዲወስደው ቢጠይቀው "አይሆንም: አባትህ ያዝንብኛል" አለው:: ቅዱሱ ግን "በእግዚአብሔር ስም አማጽኜሃለሁ" ስላለው ሁለቱም በሌሊት ወጥተው ወደ ገዳም ሔዱ::

አበ ምኔቱ "ልጄ! የበርሃውን መከራ አትችለውም: ይቅርብህ" ቢለውም "አባቴ! አይድከሙ:: ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር አይለየኝም::'' ስላላቸው እንደሚገባ ፈትነው አመንኩሰውታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከመነኮሰ በኋላ በጾም: በጸሎት: በስግደትና በትሕርምት ያሳየው ተጋድሎ በርካቶችን አስደነቀ::

ለሥጋው ቦታ አልሰጣትምና በወጣትነቱ አካሉ ረገፈ:: ቆዳውና አካሉም ተገናኘ:: ሥጋውን አድርቆ ነፍሱን አለመለማት:: በእንዲሕ ያለ ሕይወት ለሰባት ዓመታት ከተጋደለ በኋላ በራዕይ "ወደ ወላጆችህ ተመለስ" እያለ ሦስት ጊዜ አናገረው::
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ አበ ምኔቱ ሒዶ ቢጠይቀው "ራዕዩ ከእግዚአብሔር ነው" ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ አሰናበተው::

ቅዱስ ዮሐንስ በላዩ ላይ የነበረችውን ልብስ በመንገድ ለነዳይ ሰጥቶ: በፈንታው ቆሻሻ ጨርቅ ለብሶ ከወላጆቹ በር ላይ ለመነ:: "እባካችሁ አስጠጉኝ" አላቸው:: ወላጆቹ በጭራሽ ሊለዩት አልቻሉም:: ነገር ግን አሳዝኗቸዋልና በበራቸው አካባቢ ትንሽ ቤት ሠሩለት::

በዚያች በዓት ውስጥ እንዳስለመደ በትጋት ለሰባት ዓመታት ተጋደለ:: በእነዚህ ዓመታት እንኳን ሌላው ሰው ወላጆቹም ቢሆኑ ፍርፋሪ ከመስጠት በቀር አይቀርቡትም ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ "ይሸተናል" የሚል ነበር:: በመጨረሻም መልአከ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ "ከሰባት ቀናት በኋላ ታርፋለህ" አለው::

እናቱን ጠርቶ "አንድ ነገር ልለምንሽ" አላት:: "እሺ" አለችው:: "ከሞትኩ በኋላ በለበስኳት ጨርቅ እንድትገንዙኝ: በበዓቴ ውስጥም እንድትቀብሩኝ" አላትና የወርቅ ወንጌሉን አውጥቶ ሰጣት:: ያን ጊዜ አባቱም ደርሶ ነበርና ደነገጡ::

የወርቅ ወንጌሉን ለዩት:: ልጃቸውን ግን መለየት አልቻሉምና እያለቀሱ ስለ ልጃቸው የሚያውቀው ካለ እንዲነግራቸው ለመኑት:: እርሱም "ልጃችሁ ዮሐንስ እኔ ነኝ" አላቸው::

በዚያ ቅጽበት ወላጆቹ የሰሙትን ማመን አልቻሉም:: በፍጹም ዋይታ እየጮሁ አለቀሱ:: ለቅሷቸውን የሰሙ ሁሉ ተሰበሰቡ:: ለሰባት ቀናት እኩሉ እያለቀሰ: እኩሉ እየተባረከ በዓቱን ከበው ሰነበቱ:: በሰባተኛው ቀን መልአኩ መጥቶ በክብር ነፍሱን ተቀበለ::

እናቱ የልጇን አደራ ረስታ (እሷስ መልካም አደረግሁ ብላ ነው) ለሠርጉ ባዘጋጀችው የወርቅ ልብስ ገነዘችው:: ወዲያው ግን በጽኑ ታመመች:: አባት ግን ፈጠን ብሎ በዚያች ጨርቅ ገንዞ በበዓቱ ውስጥ ቀበረው:: ያን ጊዜ እናት ፈጥና ዳነች:: ከቅዱሱ መቃብርም ብዙ ተአምራትና ፈውስ ተደርጓል::

††† ቸሩ አምላካችን ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

††† ሐምሌ 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮጵያ (የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዳንኤል ጻድቅ

††† "እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ: የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ: በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ:: በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሱ:: የመዳንንም ራስ ቁር: የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ:: እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው:: በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ:: በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ::" †††
(ኤፌ. ፮፥፲፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለነቢዩ #ቅዱስ_ዮናስ እና ለእናታችን #ቅድስት_አውፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ ቅዱስ ዮናስ ነቢይ ✞✞✞

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: #ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ #ቅዱስ_ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) #አብድዩና #ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን #እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ለቀን ቆይቷል::
ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው #ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ #በሐዲስ_ኪዳን ለሚደረገው ምስጢረ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+"+ ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት +"+

=>እናታችን #ቅድስት_አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው::
"አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው #ጌታ_ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን #ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር
Audio
††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ †††

††† ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል ትልቅ ሞገስ የነበረውና "የጌታችን ወንድም" ተብሎ የተጠራ ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ (የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ የሞተችው እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ የምትባል እህትም ነበረችው::

እናቱ ማርያም ከሞተች በኋላ ዕጓለ-ማውታ (ደሃ አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው::

እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም:: ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውኃ አምጥታ የሕፃኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል::)

እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለዘጠኝ ወራት: ከተወለደ በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ሕፃኑን ያዕቆብን ተንከባከበችው:: ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ግን ድንግል ማርያም አምላክ ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለሃያ አምስት ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና::

ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና ወተትን) ብቻ ነው:: ስለዚህም:-
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል)

††† ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ
1.ለሰላሳ ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው
2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ በመሆኑ
3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች በመሆናቸው
4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን "ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ ተገኝቷልና::)

ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር ተከተለው::
¤ከሰባ ሁለቱ አርድእት ተቆጠረ
¤ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ተማረ
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም" ብሎ ማክፈልን አስተማረ
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ አገለገለ
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ
¤ሙታንን አስንስቶ
¤ድውያንን ፈውሶ
¤የመካኖችን ማኅጸን ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተዓምራትን ሠራ:: እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ መልካሙን ገድል ተጋደለ::

በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው" እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት)

††† በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ:-
አምላክ:
ወልደ አምላክ:
ወልደ አብ:
ወልደ ማርያም:
ሥግው ቃል:
እግዚአብሔር ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው::

ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ::

ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ : ጸጉሩን ተላጭቶ : ገላውን ታጥቦና ልብሱን ቀይሮ አያውቅም::
"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ::
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ::
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ" እንዲል::

††† ከጾም : ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ (ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል::

††† ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም ምሕረትን ይላክልን::

††† ሐምሌ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት-የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት)
2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ እንድራኒቆስ ሰማዕት
4.ዘጠኝ ሺህ ሰማዕታት (የቅዱስ ኤስድሮስ ማኅበር)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

††† "የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም::" †††
(ያዕ. ፩፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰዉ ድንገተኛ የመሬት ናዳ ምክንያት የወገኖቻችን ሕይወት በማለፉ የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን፤ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ሰላማዊ እረፍትን፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን።
††† እንኳን ለቅዱሳኑ ገብርኤል ሊቀ መላእክት: ቂርቆስ ወኢየሉጣ: በጥላን ጠቢብ እና ሰማዕታተ እስና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት †††

††† ቅድስት ኢየሉጣ እናታችን በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩና በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳት አንዷ ናት:: በወቅቱ ቅዱስ ቂርቆስ የሚባል ደግ ልጅ ወልዳ ባሏ ባለመኖሩ በመበለትነት ትኖር ነበር:: የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር ከመነገር በላይ ነው:: በዛው ልክ ደግሞ መከራው በጸጉራቸው ቁጥር ልክ ነበር::

ከሮም ግዛት በአንዱ ከቅዱስ ልጇ ጋር የምትኖረው ቅድስት ኢየሉጣ የስደቱ ዘመን ሲመጣ እርሷም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ተሰደደች:: እስክንድሮስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ ግን ያለችበት ድረስ ተከትሎ እንድትያዝና እንድትቀርብ አደረገ::

ወዲያውም "ስምሽ ማን ይባላል?" ቢላት "ክርስቲያን እባላለሁ" አለችው:: ንጉሡ ተቆጣ:: "መዋቲ ስሜን ከፈለክ ኢየሉጣ ይባላል" አለችው:: ንጉሡ መልሶ "አሁን ለጣዖት ካልሠዋሽ ሲጀመር ስቃይ: ቀጥሎም ሞት ይጠብቅሻል" ቢላት ቅድስቲቱ መልሳ "በከተማ ውስጥ የሦስት ዓመት ሕፃን አለና እርሱን አምጣው:: ማንን ማምለክ እንዳለብን ይነግረናል" አለችው::

አስፈልጐ ቅዱስ ቂርቆስን አስመጣው:: "ስምህ ማን ይባላል?" አለ ንጉሡ:: "ከማይደፈርስ ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ ክርስቲያን ይባላል:: መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ቂርቆስ ይባላል" አለው::

ንጉሡ ሊያታልለው "ደስ የተሰኘህ ሕፃን" ቢለው ቅዱሱ ሕፃን "ትክክል ተናገርክ: ለእኔ በሰማያት ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን እውነተኛው አምላክ ይፈርድብሃል" አለው:: በሦስት ዓመት ሕፃን አንደበት ዘለፋ የገጠመው ከሃዲ ተቆጣ::
እናትና ልጅን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃያቸው::

ሰውነታቸውን ቸነከረ: አካላቸውን ቆራረጠ: ዓይናቸውን አወጣ:: ሌላም ሊናገሩት የሚጨንቅ ስቃይን አሰቃያቸው:: በዚህች ቀን ግን ትልቅ ድስት አሰርቶ ባሩድ: አረር: ስብና የመሳሰሉትን ጨምረውበት በእሳት አፈሉት::

የእሳቱ ወላፈን አካባቢውን በላው:: በድስቱ ውስጥ ያለው ነገር እየፈላ ሲገላበጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይጮህ ነበር:: የስድስት ሰዓት የእግር መንገድ ድረስም ተሰምቷል:: ቅድስት ኢየሉጣ ይሔኔ ነበር ልቧ ድንግጥ ያለው:: ሕፃኑ ቂርቆስ የእናቱን ፍርሃት ሲመለከት ጸለየ::

"ፈጣሪዬ! ፍሬው ያለ ግንዱ አይቆምምና እኔን እንዳጸናሕ እናቴንም አጽናት" ሲል ለመነ::
"እግዚኦ ትፈቅድኑ ለፍሬሁ ተአልዶ:
እንዘ በእሳት ታውኢ ጉንዶ" እንዲል::
በዚያች ሰዓት ቅድስት ኢየሉጣ ዓይኖቿ ተከፍተው ሰማያዊ ክብርን ተመለከቱና ልቧ ወደ ድፍረቱ ተመለሰ::

ልጇንም "አንተ አባቴ ነህ: አንተን የተሸከመች ማኅጸኔ የተባረከች ናት" አለችው:: ከዚያም ሁለቱንም ወደ ፈላው ድስት ውስጥ ቢጨምሯቸው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደላቸው:: በበትረ መስቀሉ ባርኮ የፈላውን አቀዘቀዘው:: የነደደውን ውኃ አደረገው:: ቅዱሳኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ከብዙ መከራ በኋላ በሰማዕትነት አልፈዋል::

††† ቅዱስ በጥላን ጠቢብ †††

††† ቅዱሱ ከአሕዛብ ወላጆቹ ተወልዶ: ያደገውም በጣዖት አምልኮ ነው:: በሙያው እጅግ የተመሠከረለት ሐኪም ነበር:: የሃገሩ ሰዎች "ጠቢብ" እያሉም ይጠሩታል:: በጥላን ምንም ጣዖት አምላኪ ቢሆን በተፈጥሮው ተመራማሪና ቅን ነበር::

አንድ ካህንም በጐረቤቱ ነበርና ዘወትር ስለ ሃይማኖት ይከራከሩ ነበር:: ካህኑ ሌሊት ሌሊት ስለ በጥላን ተግቶ ይጸልይ ነበርና ተሳክቶለት አሳመነው::

አንድ ቀን በጥላን መንገድ ሲሔድ እባብ ሰው ነድፎ ለሞት ደርሶ አየውና ጸሎት አድርሶ ስመ ክርስቶስን ቢጠራ የተነደፈው ድኖ እባቡ ሞተ::

በዚህ ተዓምር ደስ ብሎት ወደ ካህኑ ሒዶ ተጠመቀ:: ከዚያም ጾም ጸሎትን ጀመረ:: በየቦታው እየዞረ ሕሙማንን እንደ ቀድሞው በመድኃኒት ሳይሆን በጸሎት ያድናቸው ነበር:: ስላዳናቸውም በርካቶቹ ወደ ክርስትና መጡ::

የአካባቢው ሰው: ወላጆቹን ጨምሮ ክርስቲያኖች ሆኑ:: በመጨረሻም ቅዱስ በጥላን: ቤተሰቦቹ: ካህኑና ከደዌ የዳኑት ወገኖቹ በአካባቢው ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ሰብከው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

††† ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና †††

††† እስና ማለት ግብጽ ውስጥ የምትገኝ የቀድሞ አውራጃ ናት:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በከተማዋ በርካታ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር:: የእንዴናው መኮንን መጥቶ "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: ሕዝቡ በአንድ ድምጽ መለሱ:- "ይሕማ ፈጽሞ ሊደረግ አይችልም::" መኮንኑ ተቆጥቶ "ሁሉንም ግደሉ" አለ::

ወታደሮቹ ሰው አልመረጡም:: ከታዘለ ሕፃን አልጋ ላይ እስካለ ሽማግሌ: ከጤነኛ እስከ ሕመምተኛ: ሁሉንም ጨፈጨፏቸው:: ከተማዋ በደም ተነከረች:: ከከተማዋ ክርስቲያኖች ወሬ ለመንገር አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም:: ሁሉም ስለ ክርስትና ደማቸውን አፈሰሱ::

††† ጌታችን ስለ ሰማዕታቱ ብሎ: ደማቸውንም አስቦ በሃይማኖታችን ያጽናን:: ከመከራም ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያድለን::

††† ሐምሌ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ቂርቆስ ወእሙ ኢየሉጣ
3.ቅዱስ በጥላን ጠቢብ ሰማዕት እና ማኅበሩ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
2.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
3.አቡነ ስነ ኢየሱስ
4.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ መራቆት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቆጠርን::' ተብሎ እንደተጻፈው ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::" †††
(ሮሜ. ፰፥፴፭-፴፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
2024/10/01 22:39:36
Back to Top
HTML Embed Code: