Telegram Web Link
Daniel:
:
እንኩዋን ለነቢየ እግዚአብሔር "ቅዱስ ሐጌ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ቅዱስ ሐጌ ነቢይ "*+

=>ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር) : መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

+"ዘመነ ነቢያት" ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

+ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

+የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

+ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

+ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው : ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

+ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት "15ቱ አበው ነቢያት" : "4ቱ ዐበይት ነቢያት" : "12ቱ ደቂቀ ነቢያት" ና "ካልአን ነቢያት" ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

=>"15ቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

=>"4ቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ *ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

=>"12ቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

=>"ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::

=>ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ:: በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-

*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

+ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

+ቅዱስ ሐጌ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ450 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸው::

=>"ሐጌ" ማለት መልአከ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መልእክተኛ) ማለት ነው:: አንዳንዴም "በዓል" ተብሎ ይተረጐማል:: ትውልዱ ከነገደ ጋድ ሲሆን አባቱ አግታ: እናቱ ሲን ይባላሉ::

+በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከደኃርት (ከሁዋለኛው ዘመን ነቢያት) አንዱ ነው ይባላል:: ቁጥሩም ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+እሥራኤል ከተከፈለችበት ከመንግስተ ሮብዓም (ከክርስቶስ ልደት 931 ዓመታት በፊት) በሁዋላ 10ሩ ነገድ "እሥራኤል": 2ቱ ነገድ "ይሁዳ" ተብለው በሰሜንና በደቡብ አቅጣጫ ተለያዩ:: መናገሻቸውም ኢየሩሳሌምና ሰማርያ ሆኑ::

+ከዕለት ዕለት ግን የሁሉም ኃጢአት እየበዛ በመሔዱ እግዚአብሔር አዘነባቸው:: ለአሕዛብም አሳልፎ ሰጣቸው:: አስቀድሞ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ722 ዓመት የአሦሩ ንጉሥ ስልምናሶር መጥቶ ሰማርያን አጠፋት:: 10ሩን ነገድም በባርነት አሦር አወረዳቸው::

+ከዚህ ትምሕርት መውሰድ የተሳናቸው 2ቱ ነገድም ሊገሰጹ አልቻሉምና ተመሳሳይ ዕጣ ደረሰባቸው:: የእግዚአብሔርንና የነቢያቱን ድምጽ: ይልቁኑ የኤርምያስን ምክር አልሰሙምና ከክርስቶስ ልደት 586 ዓመታት በፊት ኃይለኛው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር መጣ::

+የሚገድለውን ገድሎ: ሕዝቡንም ማርኮ ወደ ፋርስ ባቢሎን ሲያወርዳቸው ኢየሩሳሌምን ምድረ በዳ አደረጋት:: (2ነገ. )

+እግዚአብሔርን የማይሰማ ሕዝብ ምን ጊዜም እጣ ፈንታው ይሔው ነው:: በተለይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቸርነት የበዛለት ሕዝብ እንዲህ አንገተ ደንዳና ሲሆን ይገርማል:: በእርግጥ ዛሬ እስራኤል ያይደለ ሃገረ እግዚአብሔር ኢትዮዽያ ናትና ከመሰል መከራ ለመራቅ ድምጹን መስማት ያስፈልጋል::

+ሕዝቡ ግን ፋርስ : ባቢሎን ወርደው መከራን ሲቀበሉ : ነቢያት ያሉት ሁሉ ሲፈጸምባቸው ተጸጸቱ:: ፈጣሪም ተስፋ እንዳይቆርጡ በዚያው ዳንኤልን የመሰሉ ነቢያትን አስነሳላቸው:: እነ ኤርምያስንም ከግብጽ ላከላቸው::

+ሕዝቡም (በተለይ "ትሩፋን" የተባሉት) "እግዚአብሔር ሆይ! 'ወሰብዓ ዓም ኃሊቆ' ባልከው ቃልህ : 70ው ዘመን ሲፈጸም ወደ አባቶቻችን ርስት ብትመልሰን መቅደስህን እናንጻለን:: በጐ ምግባርን እንይዛለን" ሲሉ ተሳሉ::

+ልመናን የሚሰማ ቸሩ ፈጣሪም እንደ ቃሉ 70ው ዘመን ሲፈጸም እሥራኤል በነ ኤርምያስ ባሮክና እና ሌሎችም አማካኝነት በኃይል: በድንቅና በተአምራት ከፋርስ ባቢሎን ወጡ:: በድል ተጉዘውም ወደ ርስታቸው ገቡ::

+የሰው ነገር አስቸጋሪ ነውና ከርስታቸው ከገቡ በሁዋላ ግን ስዕለታቸውን ሳይፈጽሙ ቀሩ:: በዚህ ጊዜም እንደ ዘወትሩ ይገሥጻቸው ዘንድ እግዚአብሔር ነቢያቱን ሐጌን : ዘካርያስንና ሚልክያስን አስነሳቸው::

+ሕዝቡ "እስመ ኢኮነ ጊዜሁ ለሐኒጽ - ለማነጽ ወቅቱ አልረዳንም" እያሉ ቤተ መቅደሱ ሳይታነጽ ዘመናት አለፉ:: የሚገርመው ግን ቤተ መቅደሱ ምድረ በዳ ሆኖ የራሳቸውን ቤት አሳምረው ያንጹ ነበር::

+በዚህ ጊዜ በመካከላቸው የነበረው ቅዱስ ሐጌ ዘለፋቸው::
"እምጊዜሁ ለክሙ ከመ አንትሙ ትንበሩ ውስተ ቤት ጥፉር: ወቤትየሰ ምዝቡር? - ቤቴ ፈርሶ ሳለ እናንተ ባማሩ ቤቶቻችሁ ልትኖሩ ጊዜው ነውን?" (ሐጌ. 1:4) አላቸው::

+አክሎም "ቃላችሁን አልፈጸማችሁምና በረከቴን ከእናንተ አርቃለሁ" አላቸው:: ተግሣጹን ከልብ የሰሙት ሕዝቡም በዘሩባቤል መሪነት 46 ዓመታት የፈጀውን ቤተ መቅደስን አንጸዋል::

+ቅዱስ ሐጌም በሕጉ እየኖረ: ትንቢትን እየተናገረ ዘመኑን ፈጽሟል:: በትውፊት ትምሕርትም ቅዱሱ የተወለደው በ500 ዓ/ዓ ሲሆን ያረፈው በ70 ዓመቱ በ5,070 ዓ/ዓ ነው:: ከክርስቶስ ልደት 430 ዓመታት በፊት ማለት ነው::
=>አምላከ ሐጌ ለቤቱ የምናስብበትን ዘመን ያምጣልን:: ከቅዱሱ ነቢይ በረከትም ይክፈለን::

=>ታሕሳስ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሐጌ ነቢይ
2.አባ አውጋንዮስ
3.ታውፊና ንግሥት

=>ወርኀዊ በዓላት
1..ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
6.ማር ቴዎድሮስ ኃያል ሰማዕት

=>+"+ 'ብሩ የእኔ ነው:: ወርቁም የእኔ ነው' ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር:: 'ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል' ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር:: በዚህም ሥፍራ ሰላምን እሰጣለሁ:: +"+ (ሐጌ. 2:9)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ውሉደ ቤተክርስቲያን ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ:
እንኩዋን "ለኖላዊ ሔር ክርስቶስ" : ለቅዱሳን "በርናባስ ሐዋርያ" እና "አባ ይስሐቅ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ኖላዊ ሔር "*+

=>እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ:: በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ: በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ: በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት:: በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው::

+ከዚህ በሁዋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር:: ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር: ሱባኤ ይቆጠር: ምሳሌም ይመሰል ገባ::

+ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ:: ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል:: ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት / ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል::

+ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል:: እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል::

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህችን ዕለት "ኖላዊ ሔር" ብላ ታከብራለች:: ይሕንንም ለሳምንት ያህል ታዘክራለች:: መሠረታዊ መነሻዋም (ዮሐ. 10:1) ነው:: "ኖላዊ" ማለት በቁሙ "እረኛ" ማለት ሲሆን "ሔር" ደግሞ "ቸር-ርሕሩሕ-አዛኝ" እንደ ማለት ነው::

+ገጥመን ብንተረጉመው ደግሞ "ቸር እረኛ" የሚል ትርጉምን ይሰጠናል:: ከአባታችን አዳም ስህተት በሁዋላ ተፈጥረው ከነበሩ ችግሮች አንዱ ቸር እረኛ ማጣት ነው:: እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ: ቸር እረኛ ሆኖ በገነት አሰማርቶት ነበር::

+ኤዶም ገነት የለመለመች: ፈሳሾች የሞሉባት መልካም መስክ ናትና:: አባታችን ቅዱስ አዳም ደግሞ እንደ አቅሙ የጸጋ እረኝነት ተሰጥቶት ነበር:: ድቀት ካገኘው በሁዋላ ግን ከነፍስ እረኛው ጋር ተጣልቶ ከመልካሟ መስክ ገነት ወጣ::

+እርሷንና የነፍሱን እረኛ ሲሻም አለቀሰ:: ተስፋ ድኅነት ሲሰጠውም ለልጆቹ ነገራቸው:: ከዚያም በመንጋው ላይ በአዳም ሴት ተተካ:: ከሴት ኄኖስ: ከኄኖስ: ቃይናን . . . እያለ ከኖኅ ደረሰ::

+ከኖኅም በሴም ከአብርሃም: ከአብርሃምም በይስሐቅና በያዕቆብ ወርዶ ከሙሴ ደረሰ:: ከሙሴም በኢያሱ አልፎ ከነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ደረሰ:: እነዚህ ሁሉ እረኞች ምንም እንኩዋ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በትጋት ቢሠሩም ሕዝቡን ከሲዖል ማዳን አልቻሉም::

+ከሲዖል የሚያድን የነፍስ እረኛ ነውና ያን ጊዜ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የራሱን: የአባቶቹንና የልጆቹን ጩኸት ባንድ አድርጐ ጮኸላቸው:: "ኖላዊሆሙ ለእሥራኤል አጽምዕ - የእሥራኤል እረኛ ሆይ ስማን!" አለ:: (መዝ. 79:1)

+ጩኸቱም ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ይህንን የሰማ ጌታም በጊዜው ከድንግል ማርያም ተወለደ:: በየጥቂቱ አድጐ ቸር እረኝነቱን ገለጠ:: መድኃኒታችን እንዳስተማረን እርሱ ቸር እረኛ ነው::

+ከእርሱ በፊት የተነሱት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ (ሐዋ. 5:36, ዮሐ. 10:8) ሐሰተኛ እረኞች ነበሩ:: እርሱ ግን እውነተኛው የበጐች በር ነውና (ዮሐ. 10:7) በእርሱ የሚገቡ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛሉ::

+እርሱ እውነተኛ እረኛ ነውና (ዮሐ. 10:11) ለመንጋው ራሱን አሳልፎ ይሰጣል:: በእሥራኤል ባሕል እረኞች ከፊት: መንጋው (በጐቹ) ከሁዋላ ሆነው ይሔዳሉና ገዳይ ቢመጣ መጀመሪያ የሚገድለው እረኛውን ነው::

+መድኃኒታችን ክርስቶስ በሞቱ ሕይወትን: በመራቆቱ የጸጋ ልብስን: በውርደቱ ክብርን: በድካሙ ኃይልን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ:: የማይሞት ንጉሥ ስለ መንጋው ሞተ:: ሰማይን ከነግሡ ምድርንም ከነልብሱ የፈጠረ ጌታ (ዘፍ. 1:1, ዮሐ. 1:2) ስለ በጐቹ ይህንን ሁሉ ታግሦ ከሲዖል አዳነን::

+በሚያርግ ጊዜም በእርሱ ፈንታ ባለ ሙሉ ስልጣን እረኞችን: ሐዋርያትን (ዮሐ. 21:15) ሊቃነ ዻዻሳትን (ሐዋ. 20:28) ካህናትን (ማቴ. 18:18) ሾመልን:: እነርሱን እረኞች አሰኝቶ እርሱ "ሊቀ ኖሎት-የእረኞች አለቃ" ተባለ:: እነርሱም እስከ ዓለም ፍጻም የክርስቶስን መንጋ ሊጠብቁ ስልጣኑም: ኃላፊነቱም አለባቸው:: (ማቴ. 28:19)

+*" ቅዱስ በርናባስ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱሱ ሐዋርያ ስሙ ሲጠራ ሞገስ አለው:: የቅዱሱ ሰው የመጀመሪያ ስሙ ዮሴፍ ሲሆን በርናባስ ያለው መድኃኒታችን ክርስቶስ ነው:: ትርጉሙም "ወልደ ኑዛዜ-የመጽናናት ልጅ" እንደ ማለት ነው::

+በምሥጢሩ ግን "ማሕደረ መንፈስ ቅዱስ-የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ" እንደ ማለት ያስተረጉማል:: ቅዱስ በርናባስ ምንም በትውልዱ እሥራኤላዊ ቢሆን ተወልዶ ያደገው በቆዽሮስ ነው:: እስከ ወጣትነት ጊዜውም የቆየው እዚያው ነው::

+የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆኑ ዜና ሲሰማ ግን ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ መድኅን ክርስቶስን ተመለከተ:: ጌታውንም ሊከተል በልቡ ቆረጠ:: የፈጠረን ክርስቶስም እንዲረባ (እንዲጠቅም) አውቆ: ስሙን ቀይሮ አስከተለው:: ከ72ቱ አርድእትም ደመረው::

+ቅዱስ በርናባስ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ለ3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ቁጭ ብሎ ተማረ:: ተአምራቱንም ሁሉ ተመለከተ:: ከጌታ ዕርገት በሁዋላ 120ው ቤተሰብ በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩም አብሮ ይተጋ ነበር::

+በጊዜውም አበው ሐዋርያት በይሁዳ ፈንታ ከ12ቱ የሚቆጠረውን ሰው ለመምረጥ 2 ሰዎችን አቅርበው ነበርና አንዱ ይኸው ቅዱስ ነው:: እዚያውም ላይ ጌታችንን ከመጀመሪያው ጀምሮ ማገልገሉ ተመስክሮለታል:: (ሐዋ. 1:22)

+ስሙንም ኢዮስጦስ ብለውታል:: ባለ 3 ስም ነበርና:: በወቅቱም ዕጣ በቅዱስ ማትያስ ላይ ስለ ወደቀ በርናባስ ከ72ቱ አርድእት: ማትያስ ከ12ቱ ሐዋርያት ሆነው ቀጠሉ::

+ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ በርናባስ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ በኃይል ያገለግል ጀመር:: የሐዋርያትን ዜና በሚናገር መጽሐፍ ላይ የተጻፉና ስለ ቅዱሱ ማንነት የሚናገሩ ክፍሎችን እንመልከት::

1.ቅዱሳን ሐዋርያት የእኔ የሚሉት ንብረት ሳይኖራቸው: ያላቸውን በጋራ እየተጠቀሙ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ነበር:: ያለውን ሁሉ ሸጦ በሐዋርያት እግር ላይ በማኖር ደግሞ ቀዳሚውን ሥፍራ ቅዱስ በርናባስ ይይዛል:: (ሐዋ. 4:36) በዚህም የዘመነ ሐዋርያት የመጀመሪያው መናኝ ተብሏል::

2.ልሳነ እፍረት (ብርሃነ ዓለም) ቅዱስ ዻውሎስ ባመነ ጊዜ ሐዋርያት ለማመን ተቸግረው ነበር:: የሆነውን ሁሉ አስረድቶ ቅዱስ ዻውሎስን ከሐዋርያት ጋር የቀላቀለው ይህ ቅዱስ ነው:: (ሐዋ. 9:26)

3.አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ "ፍልጥዎሙ ሊተ ለሳውል ወለበርናባስ - በርናባስና ሳውልን (ዻውሎስን) ለዩልኝ" በማለቱ ሐዋርያት ጾመው: ጸልየው: እጃቸው ከጫኑባቸው በሁዋላ ላአኩአቸው:: (ሐዋ. 13:1)

+እነርሱም ወንጌልን እየሰበኩ በየሃገሩ ዞሩ:: በሃገረ ልስጥራን መጻጉዕን ስለ ፈወሱ ሕዝቡ "እናምልካችሁ" ብለው የአማልክትን ስም አወጡላቸው:: 2ቱ ቅዱሳን ግን ይህንን ሲሰሙ ልብሳቸውን ቀደው በጭንቅ አስተዋቸው:: መመለክ የብቻው የፈጣሪ ገንዘብ ነውና:: (ሐዋ. 14:8-18, ዘጸ. 20:1)

4.በአንጾኪያ የነበሩ አሕዛብ ክርስትናን በተቀበሉ ጊዜ ከሐዋርያት ተልኮ ሒዶ በጐ ጐዳናን መራቸው:: (ሐዋ. 11:22)
+ቅዱስ በርናባስ በአገልግሎት ዘመኑ መጀመሪያ ከቅዱስ ዻውሎስጋር: ቀጥሎ ደግሞ ቅዱስ ማርቆስን አስከትሎ ብዙ አሕጉራትን አስተምሯል:: ቆዽሮስም ሃገረ ስብከቱ ናት::

+ቅዱሱ ከብዙ ትጋት በሁዋላ በዚህች ቀን አረማውያንና አይሁድ ገድለውታል:: ቅዱስ ማርቆስም ገንዞ ቀብሮታል::
<< ስለርሱ መጽሐፍ "ደግ: መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ነው" ይላልና ክብር ይገባዋል !! >> (ሐዋ. 11:24)

+"+ አባ ይስሐቅ ጻድቅ +"+

=>ይህ ቅዱስ በመካከለኛው ዘመን በምድረ ግብጽ የነበረ ገዳማዊ ነው:: መንኖ ለብዙ ዘመናት በገዳም ሲኖር ምኞቱ አንዲት ብቻ ነበረች:: እመቤታችንን በአካል መመልከትን ይፈልግ ነበር::

+የገዳሙ ጠባቂ በመሆኑ መነኮሳት ሲተኙ መቅደሱን ከፍቶ በድንግል ማርያም ስዕል ፊት ይጸልይ: ይሰግድ: ያነባ ነበር:: እንዲህ ለ7 ዓመታት ስለ ተጋ ድንግል እመ ብርሃን ልመናውን ሰማች::

+በዚህ ዕለትም ከፀሐይ 7 እጅ ደምቃ ወደ እርሱ መጣች:: ደንግጦ ሲወድቅ አነሳችው:: "ከ3 ቀናት በሁዋላ እመለሳለሁ" ብላም ተሠወረችው:: በ23ም ዐረፈ::
"በዛቲ ዕለት ሶበ ጸለየ ጥቡዐ::
ለይስሐቅ አስተርዓየቶ እም አይቆናሃ ወጺአ::
እምጸዳለ መብረቅ ጥቀ እንዘ ትጸድል ስብአ::" እንዳለ ደራሲ:: (አርኬ)

=>የእሥራኤል እረኛ ሥጋችንን ከመቅሰፍት: ነፍሳችንን ከገሃነመ እሳት ይጠብቅልን:: ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን::

=>ታሕሳስ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ኖላዊ ሔር
2.ቅዱስ በርናባስ ሐዋርያ
3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

=>+"+ መልካም እረኛ እኔ ነኝ:: አብም እንደሚያውቀኝ: እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጐች አውቃለሁ:: የራሴም በጐች ያውቁኛል:: ነፍሴንም ስለ በጐች አኖራለሁ:: ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጐች አሉኝ:: እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል:: ድምጼን ይሰማሉ:: አንድም መንጋ ይሆናሉ:: +"+ (ዮሐ. 10:14)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Daniel:
=>+"+ እንኩዋን "ለተአምረ እግዝእትነ ማርያም": "ቅዱስ ደቅስዮስ": "ቅዱስ አንሰጣስዮስ" እና "ቅዱስ ገብርኤል" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ተአምረ ማርያም "*+

=>"ተአምር" የሚለውን ቃል በቁሙ "ምልክት" ብሎ መተርጐም ይቻላል:: መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው:: ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ): ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል::

+ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው:: ስለዚህም ነው "ኤልሻዳይ - ከሐሌ ኩሉ - ሁሉን ቻይ" እያልን የምንጠራው::

+እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል:: በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ (1 ነገሥት) እንደ ነበር ይታወቃል::

+እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል:: በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል:: (ማቴ. 10:8, 17:20, ማር. 16:17, ሉቃ. 10:17, ዮሐ. 14:12)

+እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: (ሐዋ. 3:6, 5:1, 5:12, 8:6, 9:33-43, 14:8, 19:11)
+በተአምራት ብዛት ደግሞ ከጌታ ቀጥላ ድንግል እመ ብርሃን ትጠቀሳለች:: ዛሬም የምናስበው የእርሷን ተአምራት ነው::

+የእግዝእትነ ማርያም ሙሉ ሕይወቷ ተአምር ነው:: አበው:- "ድንግል ተአምራት ማድረግ የጀመረችው ገና ሳትወለድ ነው" ሲሉ የሚጸንባቸው ሰዎች አሉ:: ከአዳም ውድቀት በሁዋላ በእርሷ እንደሚድን "ሴቲቱ" (ዘፍ. 3:15) በሚል ከተነገረው በሁዋላ ድንግል በብዙ ተአምራት (በምሳሌ) ተገልጣለች::

+ለአብነት ያህልም እግዚአብሔር ኖኅን ከጥፋት ውሃ እንዲሁ ማዳን ሲችል ተአምራቱን በመርከብ ገለጠ:: (ዘፍ. 7:1) ለሚያስተውለው ያቺ መርከብ ናት ድንግል::

+አብርሃም ይስሐቅን ሊሰዋ ሲል በተአምራት በግ በእፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል:: (ዘፍ. 22:13) ያዕቆብ በቤቴል ድንቅ መሰላልን ተመልክቷል:: (ዘፍ. 28:12) ሙሴ በጽላቱ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል:: (ዘጸ. 34:29, ዘሌ.10:1)

+የአሮን በትር ስትለመልም ድንቅ ተአምራቱ እመቤታችንን ያሳያል:: ኢሳይያስ የድንግልን መጽነስ "ምልክት (ተአምር) ይሰጣቹሃል" ሲል ገልጾታል:: (ኢሳ. 7:14)

+በሐዲስ ኪዳንም የድንግል:-
*ያለ በደል መጸነሷ:
*ንጽሕት ሆና መወለዷ:
*በቤተ መቅደስ ለ12 ዓመታት ምድራዊ ምግብን አለመመገቧ:
*ያለ ወንድ ዘር መጸነሷ (ሉቃ. 1:26):
*ያለ ምጥ መውለዷና
*በልደት ዕለት የታዩ ተአምራት (ሉቃ. 2:1):
*እናትም: ድንግልም መሆኗ (ሕዝ. 44:1) ሁሉ በራሱ ድንቅ ተአምር ነው::

+ከዚህ ባለፈም በቃና ዘገሊላ ያደረገችውን ዐይነ ልቡናው ከታወረበት ሰው ውጪ ዓለም ያውቃል:: (ዮሐ. 2:1) ባለ ራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ:-

"ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ:: ፀሐይን ተጐናጽፋ: ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያላት: በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች" ብሎ የእመቤታችን መገለጥ (መታየት) በራሱ ተአምር መሆኑን ነግሮናል:: (ራዕይ. 12:1)

+ድንግል እመቤታችን በሕይወተ ሥጋ ከሠራችው ተአምራት በበዛ መንገድ ላለፉት 2ሺ ዓመታት ስትሠራ ኑራለች:: እየሠራች ነው:: ገናም ትቀጥላለች:: ለሚያምናት ተአምራትን መሥራት ብቻ አይደለም: ነፍሱንም ከሲዖል ታድነዋለች::

+ሁሉን ቻይ ልጅ አላትና እርሷም ሁሉን ትችላለች:: እንኩዋን የፈጣሪ እናት ድንግል ማርያም የክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያቱም "የሚሳናችሁ የለም" ተብለዋል:: (ማቴ. 17:20)

+*" ቅዱስ ደቅስዮስ "*+

=>ይህ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ በዘመነ ጻድቃን አካባቢ እንደ ነበረ ይታመናል:: ከምናኔ ሕይወቱ ባሻገር በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ የጥልጥልያ ሃገር ዻዻስም ነበር:: ይሕ ቅዱስ ሰው በእውነቱ ያስቀናል::

+እመቤታችንን ሲወዳት መንጋትና መምሸቱ እንኩዋ አይታወቀውም ነበር:: ፍቅሯ በደም ሥሮቹ ገብቶ በደስታ ያቃጥለው ነበርና ዘወትር እያመሰገናት አልጠግብ አለ:: የሚያስደስትበትን ነገር ሲያስብ ደግሞ የተአምሯ ነገር ትዝ አለው::

+ከዚያ በፊት የእመቤታችን ተአምሯ በየቦታው ይነገራል: ይጻፋል: ይሰበካል:: ግን በአንድ ጥራዝ አልተያዘም ነበርና በሱባኤ: በፈጣሪው እርዳታ: በፍጹም ድካም የእመ ብርሃንን ተአምራት ሰብስቦ በአንድ ጠረዘውና ለአገልግሎት ቀረበ::

+እርሷን ከመውደዱ የተነሳ ይህንን አድርጉዋልና እመ ብርሃን ወደ እርሱ ወረደች:: "ወዳጄ ደቅስዮስ ደስ አሰኘኸኝ" አለችው:: መጽሐፉንም ተቀብላው ባረከችው:: "አመሰግንሃለሁ" ብላውም ተሰወረችው::

+በዚህ ጊዜ ቅዱሱ ሐሴትን አደረገ:: (እመቤታችን ማየት እንዴት ያለ ሞገስ ይሆን!)
ቅዱስ ደቅስዮስ ግን ፍቅሯ እንደ እሳት ልቡን አቃጠለው:: አሁንም ደስ ሊያሰኛት ምክንያትን ይሻ ነበር::

+እመቤታችን ጌታን የጸነሰችበት በዓል (መጋቢት 29) ሁሌም ዐቢይ ጦም ላይ እየዋለ ለማክበር አይመችም ነበርና ቅዱሱ ታሕሳስ 22 ቀን ሊያከብረው ወሰነ:: በሃገሩ ያሉ ክርስቲያኖችን ጠርቶ ታላቅ በዓልን ለድንግል አከበረ::

+ሕዝቡም ጸጋ በዝቶላቸው ስለ እመቤታችን ታላቅ ሐሴትን አደረጉ:: በዚያች ሌሊትም እመ ብርሃን በሞገስ ወረደች:: "ወዳጄ ደቅስዮስ! ዛሬም ፍጹም ደስ አሰኘኸኝ! እኔም ስለ ክብርህ ይህንን አመጣሁልህ" ብላ ሰማያዊ ልብስና ዙፋን ሰጠችው::

+ማንም እንዳይቀመጥበት ነግራው: ባርካው ዐረገች:: ከዚህች ዕለት በሁዋላ ቅዱስ ደቅስዮስ ፈጣሪውንና ድንግል እናቱን ሲያገለግል: ተአምሯን ሲሰበስብ: ምዕመናንን ሲመራ ኑሮ በዚህች ዕለት ዐርፏል:: ከእርሱ በሁዋላ የተሾመው ዻዻስም በድፍረት በእርሱ ዙፋን ላይ በመቀመጡ መልአክ ቀስፎ ገሎታል::

+የእመቤታችንን ተአምር መስማትና ማንበብ ያለውን ዋጋ የሚያውቅ ጠላት ሰይጣን ግን ዛሬም ድረስ ባሳታቸው ሰዎች አድሮ ተአምሯን ይቃወማል:: <እኛ ግን ለእመቤታችን እንሰግዳለን!! ተአምሯንም እንሰማለን!! ጥቅማችን እናውቃለንና!!>

+ለመረጃ ያህልም:-
*የእመቤታችን ተአምር የሰበሰበ (ቅዱስ ደቅስዮስ)
*የተአምሯን ሥርዓት ያዘጋጁ (ቅዱሳን አበው ማቴዎስ: ማርቆስና አብርሃም ሶርያዊ)
*እሰግድ ለኪን የደረሰው (ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ)
*የተአምሯን ሃሌታ (ቅዱስ ያሬድ)
*የዘወትሩን መቅድም (ቅዱሳን ሊቃውንት) ናቸው::

<< ልመናዋ ክብሯ በእውነት ለዘለዓለሙ ይደርብን !! >>

+"+ ቅዱስ አንስጣስዮስ +"+

=>የግብጽ 36ኛ ፓትርያርክ የሆነው ይህ አባት በ6ኛው ክ/ዘ የተወለደ ሲሆን በትጋቱ: በትምሕርቱና በድርሰቱ ይታወቃል:: ምዕመናንን ለማስተማርም ከ12,000 በላይ ድርሰቶችን ደርሷል:: ብዙ መከራዎችን አሳል በ7ኛው መቶ ክ/ዘ ዐርፏል::

+*" ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል "*+
=>ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከ7ቱ ሊቃናት አንዱ: በራማ አርባብ በሚባሉ 10 ነገደ መላእክት ላይ የተሾመ: በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን መላእክትን ያጸና: ቅዱሳንን ሁሉ የሚረዳ: ሠለስቱ ደቂቅን: ዳንኤልን: ሶስናን ከሞት የታደገ ታላቅ መልዐክ ነው::+ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያን "መጋቤ-ሐዲስ" ብላ ታከብረዋለች:: የስሙ ትርጏሜ "አምላክ ወሰብእ-እግዚእ ወገብር" ነውና ለሥነ ፍጥረት ሁሉ የሚሆን ሐዲስ ዜናን ወደ እመቤታችን ድንግል ማርያም አምጥቷል::
መልዐኩ እመቤታችንን ከመጸነሷ ጀምሮ ባይለያትም ከእግዚአብሔር ተልኮ አብስሯታል::

+ቅዱስ ገብርኤል ዛሬ የብሥራቱ መታሰቢያና ዳናህ በተባለ ሃገር ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ነው::
"ገብርኤል ዜናዊ ምጽዓተ ክርስቶስ አንበሳ::
ለዛቲ በዓልከ በዘይትሌዓል ሞገሳ::
በዓለ ማርያም አንበረ ደቅስዮስ በርዕሳ::" እንዲል:: (አርኬ)

=>ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን : ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አዕምሮውን: ጥበቡን በልቡናችን አሳድሪብን::

=>ታሕሳስ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ተአምረ ማርያም
2.ቅዱስ ደቅስዮስ ጻድቅ
3.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
4.ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ
5.አባ አርኬላዎስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.አባ እንጦንስ
3.አባ ዻውሊ የዋህ
4.ቅዱስ ዮልዮስ
5.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ

=>+"+ የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው:: መንፈስ ግን አንድ ነው:: አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው:: ጌታም አንድ ነው. . . ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል:: ለአንዱ ጥበብን መናገር . . . ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ: ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ . . . ይሰጠዋል:: +"+ (1ቆሮ. 12:4)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2024/09/30 18:26:28
Back to Top
HTML Embed Code: