Telegram Web Link
___ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፮___
አንቀጽ ፮ ስለ ቀሳውስት ይናገራል።
፩) ቅስና ነውር ነቀፋ የሌለበት አንዲት ሴት ያገባ ሰው ይሾም። ቂመኛ አይሁን። አብዝቶ የሚጠጣ አይሁን። እንግዳ መቀበልን የሚወድ ይሁን። ደግ ሰው፣ ቸር ይሁን።
_
፪) ነገረ ሃይማኖትን የሚያስተምር ይሁን። እውነተኛ ትምህርትን በማስተማር ሰውን ማረጋጋት የሚችል ይሁን። ምን የበቃ ቢሆን ቄስ ፴ ዓመት ሳይሞላው አይሾም። የመጻሕፍትን ነገር የማያውቅ ቅስና አይሾም። ይልቁንም አራቱን ወንጌል ያልተረጎመ አይሾም።
_
፫) አምስት ሰዎች ያልመሰከሩለት ቅስና አይሾም። ቄስ በኤጲስ ቆጶሱ በአንብሮተ እድ ይሾማል። ቀሳውስት ቁመው ይጸልዩለት። ቄስ መምህር እንደመሆኑ ያስተምር።
_
፬) የቄስ ሥልጣን ማስተማር፣ ማጥመቅ፣ ቀድሶ ማቁረብ እና ሕዝቡን መባረክ ነው። ቄስ ማንንም አይሹም። ቀሳውስት በመንበሩ ዙሪያ ከኤጲስ ቆጶስ ፊት ሊሄዱ አይገባም።
_
፭) ቄስ ሁለት እህትማማች ካገባ ሰው ሠርግ አይሂድ። ይህን ያደረገ ሰው ንስሓ የሚገባው ነውና። ቄስ ከሐዋርያት የወጣ ሥርዓት በሕዝቡ ምንም ምን አያጽናባቸው።
_
፮) የሚታከም ቢሆን ነው እንጂ ቄስ በማንም በማን ፊት አይራቆት። ቀሳውስት ከኤጶስ ቆጶሳቸው በዓመት ሦስት ጊዜ ይሰብሰቡ።
_
፯) በጉቦ፣ በማስፈራራት፣ በማድላት፣ በተንኮል የተሾመ ቄስ ይሻር። ሁለት ሴት ያገባ ቄስ ይሻር። ሕዝቡን ከማስተማር ቸል የሚል ቄስ ይሻር።
_
፰) ሐሰት በመመስከር ሰውንም በማጣላት የታወቀ፣ የሚታበይ፣ ሥርዓትን አውቆ የማይሠራት፣ ዘወትር የሚሰክር፣ አራጣ የሚቀበል፣ ከሴሰኛ ሴት የደረሰ፣ በጠንቋዮች ነገር የሚያምን፣ ኮከብ በመቁጠር የሚታመን፣ ሥር የሚምሱትን ቅጠል የሚበጥሱትን ነገር የሚያምን፣ ከከሓድያን የተጠመቀ ቁርባናቸውን የተቀበለ፣ አብሯቸው የሚጸልይ ከክህነቱ ይሻር።
_
፱) አባለዘሩን የሰለበ፣ ሲሰርቅና በሐሰት ሲምል የተገኘ፣ የጋብቻ ሥርዓትና ሥጋ መብላት እንዲሁም ወይን መጠጣት አይገባም የሚል፣ በገበያ መካከል የሚበላ፣ ከመሸታ ቤት ገብቶ የሚጠጣ፣ ሙቶ የተገኘውን የአውሬ ትራፊ የሆነውን የሚበላ፣ ከደዌ ለመዳን ከዓላውያን ቤተክርስቲያን የገባ፣ የአይሁድን ጾም የሚጾም በዓላቸውን የሚያከብር፣ ወደ ዓላውያን ቤተክርስቲያን እጅ መንሻ የሚወስድ፣ ተወግዞ ከተለየው ጋር የተነጋገረ አብሮት የሚጸልይ፣ የኤጲስ ቆጶሱን ደብዳቤ ሳይዝ ሩቅ ሀገር የሚሄድ ከክህነቱ ይሻር።
_
፲) አገለግላለሁ ብሎ ወይም እመነኩሳለሁ በማለት ሚስቱን የፈታ ቄስ ይሻር። በታወቀ ምክንያት የተሻረ ቄስ ወይም ዲያቆን ቢኖርና ከተሻረ በኋላ የክህነት ሥራ ቢሠራ ከምዕመናን ፈጽሞ ይለይ። መሻሩን እያወቀ ከእርሱ ጋር አንድ የሚሆንም ይለይ።
_
፲፩) ምእመናንን ከቁርባን የሚከለክል ቄስ ከሹመቱ ይሻር። ቄስ ከተሾመ በኋላ ሳይሾም የሠራት ኃጢአት ብትታወቅበት ከምእመናን ይለይ። ቀሳውስት ሐሜተኞች አይሁኑ።
_
፲፪) ለሴት በደሟ ወራት ሥጋውን ደሙን ያቀበለ ከሹመቱ ይሻር። ቀሳውስት ዲያቆናት ከሚያገለግሉባት ቤተክርስቲያን ወጥተው ወደ ሌላ ቢሄዱ ምእመናን ሊቀበሏቸው አይገባም።
_
፲፫) ቄስ ሚስቱ ብትወልድ ከአገልግሎት አይከልከል።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።
ክፍል ፯ ይቀጥላል።
መ/ር በትረማርያም አበባው።
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፯__
አንቀጽ ፯ ስለ ዲያቆናት ይናገራል።
፩) ዲያቆናት ጸጥ ያሉ፣ የሚታዘዙ ይሁኑ። ዲያቆናት ሁለት ሦስት ሰዎች መስክረውላቸው ይሾሙ። በአገልግሎት ሁሉ ይፈተኑ። ለሰው የሚያዝኑ የሚራሩ ይሁኑ። በቀለኞች ሳይሆን በቀልን የሚተው ይሁኑ። ቁጡ ብስጩ አይሁኑ።
_
፪) ዲያቆናት ባለጸጎችን ደስ የሚያሰኙ ነዳያንን የሚያሳዝኑ አይሁኑ። አንድነትን ሦስትነትን (ምስጢረ ሥላሴን) ለመማር ለማስተማር ይትጉ። ምዕመናንን በፍጹም ክብር ያክብሩ። ሰውን በማፈር እግዚአብሔርን በመፍራት ይኑሩ። ዲያቆን በአንብሮተ እድ ይሾማል። ቀሳውስት ዲያቆናትም ቆመው ይጸልዩለት።
_
፫) ሰው ተምሮ ከተገኘ ዲቁና በ7 ዓመት፣ በ12 ዓመት መሾም ይችላል። ሀገሪቱ ሰፊ ካልሆነች ሰባት ዲያቆናት ሊሾሙ ይገባል። ሀገሪቱ ሰፊ ከሆነች ኤጲስ ቆጶሱ እንደወደደ ይሹሙ። ዲያቆናት ከቤተክርስቲያን ገንዘብ ይመገቡ። ዲያቆናትን ያክብሯቸው። ዲያቆን ቀሳውስትን ያገልግላቸው። ከሕዝቡ ወገን ጠያቂ የሌላቸውን ድውያንንም በመጠየቅ ያገልግላቸው። ለኤጲስ ቆጶሱም ችግራቸውን ይንገረው።
_
፬) ዲያቆኑ በቤተክርስቲያን ሕዝቡ እንዳይተኙ እንዳይስቁ እንዳይዘባበቱ ይጎብኛቸው። ዲያቆን ደሙን በቄሱ ትእዛዝ ለምእመናን ያቀብል። በመዓርግ ከእርሱ ለሚበልጥ ደሙን አያቀብል። ኤጲስ ቆጶስ ቄስ ባይኖር በምሳ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት ደግሞ ባርኮ ይስጥ። ዲያቆን ያስተምት ያጠምቅ፣ ሥጋውን ደሙን ያቀብል ዘንድ፣ ሕዝብን ይባርክ ዘንድ አይገባውም። ዲያቆን ዓውዱን አይያዝ።
_
፭) ሊቀ ዲያቆን በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ከኤጲስ ቆጶስ ቀጥሎ ይቁም። ከኤጲስ ቆጶሱ ብቻ በቀር ሌላ በበላዩ አይፍረድ አይቀመጥ። እስመ ውእቱ ሊቀ ካህናት። የካህናት አለቃ ነውና።
_
፮) ዲያቆናት ሆይ የተቸገሩትን ልትጎበኟቸውና የተቸገሩበትንም ነገር ለኤጲስ ቆጶሳችሁ መንገር ይገባችኋል።
_
__አንቀጽ ፰___
ስለ ንፍቀ ዲያቆን፣ አናጉንስጢስ፣ አፃዌ ኆኅት፣ መዘምር (ዳዊት ደጋሚ) እና ዲያቆናዊት ይናገራል። ሁሉም በቃል እንጂ በአንብሮተ እድ አይሾሙም።
፩) አናጉንስጢስ (አንባቢ) በንባብ ከፈተኑት በኋላ ይሾም። ነገር የማያበዛ ይሁን። ዋዛ ፈዛዛ አይናገር። አከናውኖ የሚያናብ ይሁን። የሚያነበውን ለመሥራት የሚተጋ ይሁን። ሚስት የሌለው ይሾም። አናጉንስጢስ ቢሰርቅ ለዓመት ከአገልግሎት ይከልከል። ከዓመት በኋላ ያንብብ። እስከ ዕለተ ሞቱም በአናጉንስጢስነት መዓርግ ይኑር።
_
፪) ዲያቆናዊትነትን የምትሾም ሴት 60 ዓመት የሆናት ትሁን። በአንድ ወንድ ጸንታ የኖረች ትሁን። በበጎ ሥራ ጸንታ እንደኖረች የመሰከሩላት ትሁን። ልጆቿን በሥርዓት ያሳደገች፣ እንግዳ የምትቀበል ትሁን። ዲያቆናዊት የምትሾም ሴቶችን እንድታገለግል ነው። ተጠማቂ ሴትን ከአንገቷ በላይ ቄሱ ሜሮን ይቀባታል። የቀረውን የአካል ክፍል ዲያቆናይቱ የቄሱን እጅ ይዛ ትቀባታለች። ዲያቆናዊት ሴቶችን ትገሥፃቸው።
_
፫) ንፍቀ ዲያቆናት ረዳቶች ናቸው። በዲያቆን ቦታ ሆነው ማገልገል አይገባቸውም። ንዋየ ቅድሳትን እንዲነኩ አልተፈቀደም። ልብሰ ተክህኖ መልበስ አልተፈቀደላቸውም።
_
፬) መዘምራን ዳዊት ደጋሚ እንደመሆናቸው ዳዊት. ይድገሙ። መዘምራን እና አናጉንስጢሳውያን ሚስታቸው ሞታ ሁለተኛ እናግባ ቢሉ ማግባት ይችላሉ።
_
፭) በር ጠባቂዎች (ዐጸውተ ኀዋኅው) ወንዶች በሚገቡበት በር ቁመው ይጠብቁ። በር ጠባቆች አንድ ሰዓት እንኳ ከበር መለየት የለባቸውም።
_
፮) ከሴቶች ወገን ቅስና ዲቁና መሾም አይገባም። በቤተክርስቲያንም ጸሎት መጀመር አይገባቸውም። ቃላቸውን ከፍ አድርገው አይጸልዩ።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።
ክፍል ፰ ይቀጥላል።
መ/ር በትረማርያም አበባው።
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
__ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፰___
አንቀጽ ፱ የካህናትን ሁሉ ነገር ይናገራል። ካህናት የሚላቸው የሚከተሉት ናቸው።
፩) ሊቀ ጳጳሳት (ፓትርያርክ)
፪) ጳጳስ (መጥሮጶሊስ)
፫) ኤጲስ ቆጶስ
፬) ቆሞስ (ኮሬ ኤጲስ ቆጶስ)
፭) ቀሳውስት
፮) ዲያቆናት
፯) ንፍቀ ዲያቆናት
፰) አናጉንስጢስ
፱) መዘምራን
፲) አፃዌ ኆኅት. ናቸው።
፩) ከተጠመቀ በኋላ የገዘሩትን (የገረዙትን)፣ በግድ ሰዎች የሰለቡትን፣ ባለመድኃኒት በደዌ ምክንያት አባለ ዘሩን መድኃኒት አድርገት የተቆረጠውን ለክህነት በቅተው ከተገኙ ይሾሙ። በፈቃዱ ራሱን የሰለበ ግን አይሾም።
_
፪) ባሮች ጌቶቻቸው ሳይፈቅዱላቸው ከክህነት ሥራ ወገን በማናቸውም አይሾሙ። ጌታው ነጻ ያወጣው ቢሆንና በራሱ ፈቃድ ያድር ዘንድ ነጻ ቢያወጣው ለክህነት የበቃ ቢሆን ይሾም።
_
፫) ምእመን በክርስቶስ ስም አምኖ መከራ ቢቀበል ዲቁና ቅስና ተሹሞ ለማገልገል በአንብሮተ እድ አይሹሙት። አምኖ በሰማዕትነት በተቀበለው መከራ መንፈስቅዱስ አክብሮታልና። መንፈስቅዱስ ሹሞታልና። የክርስቶስን ስም አልክድም ብሎ አምኖ ወደ ዓላውያን ነገሥታት ገብቶ መከራ ባይቀበል፣ እጁን በሰንሰለት እግሩን በእግር ብረት ታሥሮ መከራ ያልተቀበለ ቢሆን ከሰው የተለየ መከራ ባያገኘው ግን በአንብሮተ እድ ይሹሙት። ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾም ቢሆን ግን በአንብሮተ እድ ይሹሙት።
_
፬) ሰው በአካሉ ነውር ስለተገኘበት ከሹመት አይከልከል። አንካሳም ቢሆን፣ አንድ ዓይናም ቢሆን፣ ግራኝም ቢሆን በቅቶ ከተገኘ መቀደስ የሚችል ከሆነ ይሾም።
_
፭) ቤተክርስቲያን ሁላችንንም በጥምቀተ ክርስትና ወልዳናለች።
_
፮) ሁለተኛ ያገባ፣ ሚስት ካገባ በኋላ ገልጦ ወይም ሰውሮ ዕቁባት ያኖረ፣ አግብታ የተፈታችውን ያገባ፣ ዘማዊትን ያገባ፣ ወደዘፈን ቤት የምትሄደውን ያገባ ክህነት አይሾም።
_
፯) አዲስ አማኝ የሃይማኖቱ መረዳት ንጽሕናው እስኪመረመር ድረስ ክህነት አይሾም።
_
፰) አንዱስ እንኳ ለክህነት ይበቃል ብለው ሳይመሰክሩለት አይሾም። ካህናት ከመሾማቸው በፊት ሊቀ ዲያቆኑ አስቀድሞ በንባብ ይፈትናቸው።
_
፱) ለጸሎት ለአገልግሎት እንዳያንሱ በቤተክርስቲያን የሚኖሩ ካህናት ጥቂቶች አይሁኑ። ዳግመኛም ቤተክርስቲያን የምትሰጠው ምግብ እንዳታጣ ካህናት አይብዙ። ምግብ ልብስ መስጠት በሚቻላት መጠን ትሹም እንጂ።
_
፲) ኤጲስ ቆጶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሾመ ነፍስን ሥጋን ከጥፋት ይጠብቅ ዘንድ ነው። ክህነት በክብር ከመንግሥት ትበልጣለች።
_
፲፩) በብሉይ ኪዳን ደቂቀ ሜርያርይ ንዋየ ቅድሳትን ይሸከሙ ነበር፣ ደቂቀ ጌድሶር አዕማደ ደብተራ ኦሪትን ይሸከሙ ነበር፣ ደቂቀ ቀዓት ታቦተ ጽዮንን ይሸከሙ ነበር፣ አልዓዛር ኢታምር መሥዋዕተ ሠክር መሥዋዕተ ነግህ ይሠው ነበር፣ ናዳብ አብዩድ አርደው አወራርደው ያቀርቡ ነበር፣ አሮን ከዓመት አንድ ጊዜ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ ይሠዋ ነበር፣ ሙሴ አሮንን ከሾመ በኋላ የክህነት ሥራን አልሠራም።
_
፲፪) ወደ ቤት ስትገቡ "ሰላም ይኵን ለሰብአ ዝንቱ ቤት" በሉ። በረከት የሚገባው ሰው ከዚያ ቢኖር በረከታችሁ ይደርበት። በረከት የሚገባው ሰው ባይገኝ ግን በረከታችሁ ወደእናንተ ይመለስ።
_
፲፫) በከንቱ የሚራገም ሰው ራሱን ብቻ ረገመ። በማይገባ የሚሆን መርገም በማንም በማን አይደርስም። [ቁጥር ፪፻፺፫]።
_
፲፬) (ሐተታ) እየጸለይን ሳለ አንዱ ሊያነጋግረን ቢመጣ አረማዊ ከሆነ ውዳሴ ማርያም እየደገምን ከሆነ የዕለቱን ጨርሰን፣ ዳዊት እየደገም ከሆነ አሥሩን መዝሙር ጨርሰን በአቡነ ዘበሰማያት አሥረን እናነጋግረው። ክርስቲያን ከሆነ የያዝነውን አንቀጽ ጨርሰን በአቡነ ዘበሰማያት አስረን እናነጋግረው። ከዚያ ካረፍንበት መቀጠል ነው። አቋርጠን ከተነጋገርን ግን እንደገና ጀምረን መጸለይ ይገባናል።
_
፲፭) መዓርጋቸውን እንዳያስነቅፉ ካህናት ምጽዋት መቀበል አይገባቸውም። ከቤታቸው ይስጧቸው እንጂ ከአደባባይ ወድቀው አይለምኑ።
_
፲፮) ካህናት ከሠርግ አዳራሽ ሄደው ዘፈን መስማት አይገባቸውም። የሚፈክሩት የሚዘፍኑት ሳይመጡ በልተው ጠጥተው መርቀው ይመለሱ እንጂ።
_
፲፯) ካህን ከሰው ወገን ለአንዱስንኳ አይገዛ። ካህናት የሰው ተገዦች ሊሆኑ አይገባም። ክፉ ሥራ በመሥራት ለሰው አብነት አይሁኑ። ካህን ከሥጋዊ ሹማምንት ለአንዱስንኳ ሹም አይሁን። [ቁጥር ፫፻፯]
_
፲፰) ካህናት ፈጽመው አይነግዱ። እደ ጥበብ ይማሩ እንጂ። ጽፈው ደጉሰው ራሳቸውን ያኖሩ ዘንድ።
_
፲፱) በካህናት የሚፈረደውን ፍርድ ወደ መኳንንት አይውሰዱት። የዚህ ዓለም ነገሥታት መኳንንት በካህናት ላይ አይፈርዱምና። እያንዳንዱ ካህናት በመኳንንት ይፈርዳሉ እንጂ።
_
፳) በኤጲስ ቆጶስ ክፉ ቃል የሚናገር ሰው እነሆ እግዚአብሔርን በደለ።
_
፳፩) ልጄ ሆይ ቃለ እግዚአብሔር ወንጌልን ያስተማረህን ልጅነትን ለማግኘት ምክንያት የሆነኽን እንደ እግዚአብሔር አክብረው።
_
፳፪) ካህናት በጨዋ ዳኛ መዋስ አይገባቸውም። ራሱን የሰለበ ካህን ከሹመቱ ይሻር።
_
፳፫) ገበጣ የሚጫወት ካህንን ተው ይበሉት። ባይተው ከክህነቱ ይሻር። ሕዝባውያንም ካሉ ከምእመናን ይለዩ።
_
፳፬) በአንድ ዓይና፣ በአንካሳ፣ በዕውር የዘበተ ካህን ቢኖር ከምእመናን ይለይ።
_
፳፭) በሐሰት የማለ ካህን ከሹመቱ ይሻር። ሥጋዊ በሽታ ሳይከለክለው ዐቢይ ጾምንና ረቡዕ እና ዓርብን የማይጾም ካህን ከሹመቱ ይሻር።
_
፳፮) የቅስና መዓርግ ከተቀበለ በኋላ ሚስት ያገባ ለሹመቱ ይሻር።
_
፳፯) ቄስ ጠጥቶ ቢሰክር፣ ቢራቆት ከሰው ተለይቶ ሰባት ሱባዔ ይጹም። ከቅስና በታች ባለ መዓርግ በዲቁና እያገለገለ አንድ ዓመት ይኑር። ዲያቆን ቢሆን አምስት ሱባዔ ይጹም። በንፍቀ ዲያቆናት አራት ወር ያኑር።
_
፳፰) ጨዋው ጨዋውን ቢሰድብ እንደ ሕፃን ተቆጥተው ይተውት። ካህን ካህኑን ቢሰድብ ይለይ። ቀኖናውን እስኪፈጸም ድረስ ከምእመናን ይለይ።
_
፳፱) ነገር እያሠራ ዘወትር የሚያጣላ ሰው ቢኖር አንድ ጊዜ ሁልጊዜ ይተው። ዘወትር ነገር መሥራቱን ባይተው ከሹመቱ ይሻር።
_
፴) የወታደር ልብስ የለበሰ ቄስ ቢኖር አራት ወር ከቤተመቅደስ በአፍአ ይቁም። ዲያቆን ቢሆን በአፍኣ ሁለት ወር ይቁም። @EotcLibilery @EotcLibilery @EotcLibilery
_
፴፩) ቄሱ ዲያቆኑን ቢጣላው፣ ዲያቆኑም ቄሱን ቢጣላው ቅጣታቸው በኤጲስ ቆጶሱ ሰባት ሱባዔ ይሁን። አንባቢ ቄሱን ቢጣላው ቄሱ ይቅጣው።
_
፴፪) ካህን ከካህን ጋር ቢጣላ ታርቀው እስኪመለሱ ድረስ ሁለቱም ከአገልግሎት ይለዩ።
_
፴፫) ደዌ ሥጋ የታመመ ሰው እና ለምጻም ሰው ቤተመቅደስ ገብቶ ማገልገል አይገባውም። ነውር ሆኖ አይደለም። ካህናትን እንዳያሰድብ ነው እንጂ።
_
፴፬) ካህን ኤጲስ ቆጶሱ የሰጠውን የክህነት ወረቀት ሩቅ ሀገር ሲሄድ ካልያዘው የዚያ ሀገር ሰዎች ወረቀቱን ሳያዩ አይቀበሉት።
_
፴፭) ከተወገዘ ሰው ጋር አብሮ የጸለየ ከምእመናን ይለይ።
_
፴፮) {ቁጥር ፫፻፴፱} ካህን በአነዋወሩ ደግ ቢሆን ተስማምተው ሊያከብሩትና ሊታዘዙት ይገባል። በአኗኗሩ ክፉ ቢሆን ግን፣ በደሉ ቢታወቅ፣ በበደሉ ጸንቶ ቢኖር ሊቃውንት መጽሐፍ እንዳዘዘው ሊፈርዱበት ይገባል። በደሉ ባይታወቅ ግን፣ በበደሉ ጸንቶ ባይኖር ሊሽሩት አይገባም።
_
፴፯) ክህነት የአምላክ ገንዘብ ናት። በኃጥኡ ቄስና በጻድቁ ቄስ በተናዘዙ ሰዎች መካከል ሀብት ሥርየት ልጅነት በሚያገኙበት ሥልጣነ ክህነት መለያየት የለባቸውም። ኃጥእ ቄስ ራሱን ይጎዳል እንጂ ለሌላው ሀብት ልጅነት ሥርየት ይሰጣልና። [ቁጥር ፫፻፵፬ ሐተታ]።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፱ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው። @EotcLibilery @EotcLibilery @EotcLibilery
Forwarded from የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ ("የአምር አቡክሙ ሰማያዊ ዘትፈቅዱ ዘእንበለ ትስአልዎ።" ማቴ. ፮፡፰)
Share በማድረግዎ የጠፋችዉን ነፍስ ምናልባት ያተርፉ እንደሆን ማን ያውቃል?
Forwarded from የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ ("የአምር አቡክሙ ሰማያዊ ዘትፈቅዱ ዘእንበለ ትስአልዎ።" ማቴ. ፮፡፰)
➦ቅኔ እም ኀበ መምህር ያሬድ ዘርአ-ቡሩክ
መወድስ
°ቃለ ሕገ ወንጌል እግዚእ ብዕለ ጥበብከ ዘኵሎ ፈጠረ እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ፥
°ዲበ ወኢምንት ርቱዐ ከመ ያስተርኢ ጥበቦ፥
°ለሰማይ ኒቆዲሞስ ዲበ ምድር ትእዛዘ ኦሪት አቅዲሙ ረበቦ፥
°አንተሰ እግዚአ ኵሉ ለዘእም ሀብትከ ርህበ እም ሀብተ ጸጋከ ታጸግቦ፥
°ኢይሴወርሂ ቅድመ ዐይንከ መንፈቀ ሌሊት ቀሪቦ፥
°ኒቆዲሞስ ዘተሐብአ ጽልመተ ተገልቢቦ፥
°እመኒ ይሴወር መዝገበ በረከት ዘጊቦ፥
°ለለ አሐዱ ከመ ምግባሩ እስመ ፍትሐ እዴከ ትረክቦ።

ዋይ ዜማ
°ኒቆዲሞስ ወርሐ ሰማይ ዘአኰነኖ ሌሊተ እግዚአ ኵሉ ወንጌል፥
°ኀተወ መንፈቀ ሌሊት በብሩህ ፀዳል፥
°ወእስከነ አድማስ በጽሐ ፀዳለ ብርሃኑ ቀሊል፥
°እስመ ለኒቆዲሞስ ወርሕ ግብረ እደ ሐይል፥
°ተፈጥሮቱ በጽኑዕ ቃል። (ዮሐ. ፫፡፩-፲፩)

ግእዝ ክብር ይእቲ
°ወልደ ሐቌ ገሃነም ሲኦል ዘእደ ዐማኑኤል ይዳደቆ፥
°አብደኑ ጥዩቀ እስመ የሐውር ዕራቆ፥
°ወአመ ሠርቀ ወርሕ ኮነ ለእመ ቆመ ርሒቆ፥
°ሕማሙ እኩይ ኀበ ጸድፈ መስቀል ያወድቆ።

ግእዝ ዕጣነ ሞገር
°አመ ምስለ ሐይላት ዐርገ ናቡከደነፆር ንጉሥ ኒቆዲሞስ ዘአኮ እጓለ ማውታ፥
°ለኢየሩሳሌም ወንጌል ካልእተ ኦሪት ቴምናታ፥
°ምስለ እሊኣሃ ሐይላት ለዓለመ ዓለም ይንሥታ፥
°ለወንጌል ኢየሩሳሌም በሌሊት ዐገታ፥ (፪ ነገ. ፳፭፡፩-፯)

ዐሠረ ነጋሢ
°እለ እም ርሑቅ ቆምክሙ በአፍኣ ንዑ ወንሕትታ፥
°ለደብረ ምሕረት ድንግል ዘዓዲ ንጽሐ መላእክት ትርሲታ፥
°እግዚእ አምጣነ ሐደረ በውስቴታ።

➤መጋቢት ፳፬/፳፻፲፭ ዓ.ም
➤ርእሰ አድባራት ወገዳማት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል - ድሬዳዋ

https://www.facebook.com/Yared.ZeraBuruk?mibextid=ZbWKwL
Audio
በዚህ ዘመን ማንን እንከተል?
                         
Size 25.8MB
Length 1:14:01

  በርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
#የጌታ_ስቅለት_በአበው

"አደምን የፈጠሩ እጆቹ በመስቀል ቀኖች ተቸነከሩ ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖች ተቸነከሩ ወዮ የማይሞተው ሞተ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡" #ቅዳሴ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

“እጆቹን እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማሥተሥረይ መከራ ተቀበለ እንዳለ፣ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፤ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፡፡” #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ሊቀ_ጳጳስ

‹‹የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፡፡›› #ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

‹‹ታመመ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፤ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዐት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፤ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዛ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ›› #ቅዱስ_ቄርሎስ_ዘእስክንድርያ

‹‹ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፤ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ›› #ቅዱስ_አቡሊዲስ_ዘሮም

‹‹ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር በላ ጠጣ፤ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፤ እጁን እግሩን ተቸነከረ፤ ጎኑን በጦር ተወጋ፤ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/፡፡›› #ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሳሪያ

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
"ሁሉን የያዘውን ያዙት፤ ሁሉን የሚገዛውን አሠሩት፤ የህያውን አምላክ ልጅ አሠሩት፤ በቁጣ ጎተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው። በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተለ ወሰዱት፤ ሊቃነ መላእክት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤

ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፥ በመኳንንት የሚፈርደውንም በእርሱ ፈረዱበት፤ ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የሾህ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የገርማ ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት፤ ኪሩቤል በእሳት ክንፍ ተሸፍነው በፊቱ የሚሰወሩለትን እርሱን ክፉ ባሪያ አሥሮ ፊቱን ጸፋው፤ የመላእክት ሠራዊት በፍጹም መደንገጥ የሚሰግዱለት እየዘበቱበት በፊቱ ተንበረከኩ፡፡

ይህን ያህል ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? ይህን ያህል ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው? ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው በደል የሌለበትን እንደበደለኛ ሰቀሉት፡፡ ህይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ቆጠሩት፤ አዳምን የሠሩ እጆች በመስቀል ቀኖዎት ተቸነከሩ፤ ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ተቸነከሩ፡፡

ወዮ በአዳም ፊት የህይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ፤... ወዮ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምንስ አንደበት ነው? የፍቁሩ የጌታ ህማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል፤ ህሊናም ይመታል፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ ሥጋም ይደክማል የማይሞተው ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ። የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡"

/ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
_ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፬__
አንቀጽ 16 ስለ ምጽዋት ይናገራል።
፩) ምጽዋት ከርኅራኄ ወገን የሚሆን ርኅራኄ ነው። ይኽውም ሰው አበድሬ እቀበላለሁ ሳይል በገንዘቡ የሚያደርገው ርኅራኄ ነው።
_
፪) ምጽዋት የማያልፍ የማይጠፋ ሰማያዊ ድልብ ነው። የተቻለውን ያህል በመስጠት ሰው ፈጣሪውን ይመስላል። የጌታ የባሕርይ የሰው የጸጋ ነውና።
_
፫) ምጽዋት ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያኖራት የብልህ አደራ ናት።
_
፬) ለለመነህ ስጠው። ለሰው የሚያዝኑ የሚራሩ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸው። ለእነርሱም ሥላሴ ይራሩላቸዋልና። ጌታ በምጽዋት ለሰው ለሚራሩ ሰዎች ንዑ ኀቤየ ብሎ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባቸዋል።
_
፭) ለተቸገሩ፣ ለተራቡ፣ ለተጠሙ፣ ለታረዙ፣ ለእንግዶች፣ ለታመሙ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለታሠሩ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለተሰደዱ ሊመጸውቱ ይገባል። እንግዳ መቀበል ከምጽዋት ወገን ነው።
_
፮) አሥራቱን፣ በኩራቱን፣ ስለቱን እግዚአብሔርን ለሚያገለግሉ ካህናት ከፋፍለው ይስጧቸው።
_
፯) በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ታገኙ ዘንድ፣ አሥራቱን፣ ስለቱን፣ እጅ መንሻውን፣ መጀመሪያ የደረሰውን እህል (ቀዳምያቱን) ስጡ። በረከት በሚመጸውት ሰው አትጠፋምና።
_
፰) ምጽዋት መጀመሪያ ሃይማኖታችንን አንክድም ብለው ለታሠሩ ሰማዕት ትገባለች። ከዚህ ቀጥሎ ለካህናት፣ ከዚያ ቀጥሎ ለዘመድ፣ ከዚያ ቀጥሎ ለምእመናን፣ ከዚያ ቀጥሎ ላላመኑ ሰዎች ትገባለች።
_
፱) ምጽዋትን ለተቸገረ ሁሉ ሊሰጧት ትገባለች። እግዚአብሔር ለኃጥአንም ለጻድቃንም ዝናምን እንደሚያዘንብ።
_
፲) ተመጽዋቾች ምጽዋቱን ስለ ሰጧቸው ሰዎች መጸለይ ይገባቸዋል። አብዝቶ ይጸልይላቸው።
_
፲፩) ያልተቸገሩ ሰዎች ምጽዋት መቀበል አይገባቸውም። እየተቻለው ምጽዋት የማይሰጥ ሰው እንደ ከሓዲ፣ እንደ ወንበዴ፣ እንደ ሌባ ነው።
_
፲፪) ምጽዋት ከኃጢአት ታነጻለች። ከመቅሠፍትም ታድናለች። ምጽዋት መስጠት እጥፍ ድርብ ዋጋን ያስገኛል።
_
፲፫) ምጽዋትን ከሰጡ በኋላ መጸጸት አይገባም። (ጸጸትን እንዳያመጣ አስቦ መስጠት ይገባል)።
_
፲፬) ምጽዋት የሚሰጥ ሰው በሚሰጠው ሰው ላይ መታበይ የለበትም።
_
፲፭) የሚመጸወተው ገንዘብ ነውር ነቀፋ የሌለበት ይሁን። ይኽም ላለፈው የተሰረቀ የተቀማ፣ ለሚመጣው ውዳሴ ከንቱ ያለበት አይሁን።
_
፲፮) ደስ ብሎት ደስ አሰኝቶ የሚሰጠውን ሰው እግዚአብሔር ይወደዋል።
_
፲፯) ከክፉዎች ምጽዋት ትቀበሉ ዘንድ አትውደዱ። ከእነርሱ ምጽዋትን ከምትቀበሉ በረኀብ ብትሞቱ ይሻላችኋል።

__አንቀጽ ፲፯___
ይህ አንቀጽ በምጽዋትና በቤተክርስቲያን ገንዘብ እንዲሁም በመብዓው ስለሚሾሙ ሰዎች ይናገራል
፩) ኤጲስ ቆጶስ በቤተክርስቲያን ገንዘብ ሁሉ ማዘዝ ይገባዋል። ለራሱ የሚሻውን፣ ከካህናት ወገን ለተቸገሩ ሰዎች ማወጣጣት ይገባዋል።
_
፪) ኤጲስ ቆጶስ የቤተክርስቲያንን ገንዘብ ምንም ድሆች ቢሆኑ ለዘመዶቹ መስጠት አይገባውም።
_
፫) የቤተክርስቲያን ገንዘብ፣ ልብስ፣ እርሻ፣ የተክል ቦታ፣ ላም፣ በሬ፣ ፈረስ እግዚአብሔርን በሚፈሩ በታመኑ ሰዎች እጅ ይጠበቅ።
_
፬) የቤተክርስቲያንን ገንዘብ የሸጠ፣ ገዝቶም የያዘ ሰው ይመልሱ። ባይመልሱ በኤጲስ ቆጶሱ እጥፍ አድርገው ይክፈሉ።
_
፭) ከምእመናን አንዱ ገንዘቤን ለቤተክርስቲያን ስጡ ብሎ አዝዞ ቢሞት የቤተክርስቲያኑ ገበዝ ይቀበል። የሚቀበለው ገንዘብ የንጉሥ ግብር ያለበት ከሆነ አይቀበሉት። ቤተክርስቲያን ከነገሥታት ሥልጣን በታች ልትሆን አይገባምና።
_
፮) በቤተክርስቲያን በገቢው ገንዘብ የተሾመው በወጭ ገንዘብ ከተሾመው ይለይ።
_
፯) በየሀገሩ ሁሉ ለታመሙ ለድኆች ለእንግዶች የሚያድሩበት ቤት ይለዩላቸው። እነርሱን ያስተዳድርለት ዘንድ ኤጲስ ቆጶሱ መነኩሴ ይሹም። ለሹሙ ቤት ምግብ ይመቻችለት። የቤተክርስቲያኑ ገንዘብ ቢያንስ ከምእመናን ሁሉ እንደአቅማቸው በየጊዜው ምግብ ይሰብስብላቸው። ስለዚህ ነገር ብዙ ኃጢአት ይሠረያል።
_
፰) አሥራት ሁሉ ለካህናት ሊሆን ይገባል።
_
፱) በሾላ፣ በሽንኩርት፣ በዱባ፣ በቅል እና እነዚህ በሚመስሉ አትክልት ከቤተክርስቲያን አግብተው አይጸልዩባቸው። በጽጌረዳ፣ በወይን፣ በበለስ፣ በሮማን፣ በዘይት፣ በሙዝ፣ በእንኮይ ግን ይጸልዩባቸው።
_
፲) ከመሥዋዕት የተረፈውን ለኤጲስ ቆጶሱ 4 ክፍል፣ ለቀሳውስት 3 ክፍል፣ ለዲያቆናት 2 ክፍል፣ ከዚያ በታች ላሉት እስከ ዲያቆናዊት ድረስ 1፣ 1 ክፍል ይስጧቸው።

__አንቀጽ 18____
ይህ አንቀጽ ስለ አሥራት፣ ስለ በኩራት፣ ስለ ስለት፣ ስለ ጉልት ይናገራል።
፩) አሥራት፣ በኵራት፣ ስለት፣ ጉልት የምጽዋት ወገኖች ናቸው።
_
፪) በኩራት (ቀዳምያት) መጀመሪያ የተቀዳውን ዘይት፣ መጀመሪያ የተቆረጠውን ማር፣ መጀመሪያ የታለበውን ወተት፣ መጀመሪያ የተሸለተውን ጸጉር፣ ጽፈው ደጉሰው መጀመሪያ ያገኙትን ገንዘብ ለቤተክርስቲያን መስጠት ነው። ካህኑ ላመጡት ሰዎች ከመጋረጃ ውጭ ሆኖ እግዚአብሔርን ያመስግነው።
_
፫) ስለት ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ በጎ ነገርን ለማግኘት ሰው በራሱ፣ በልጆቹ፣ በገንዘቡ የተሳለውን ለመፈጸም ከፈጣሪው ጋር የተማማለው መሓላ ነው። የሚሻውን ነገር ባገኘ ጊዜ ስለቱን እንዲፈጽም ሰው ከመሳሉ በፊት በደንብ ያስብ።
_
፬) ይህ ዓለም ኃላፊ ያ ዓለም ኗሪ እንደሆነ አውቆ መሳል በጎ ነገርን ለማግኘት ነው።
_
፭) መከራ ባገኘው ጊዜ ተሳለ እንጂ የተሳለውን ስለት መፈጸም የማይቻለው ድኃ ቢሆን ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ወይም ወደ ቄሱ ይሂድ። ቄሱ ወይም ኤጲስ ቆጶሱም የሚችለውን መጠን አይተው ይወስኑለት።
_
፮) ስለትን አለመፈጸም ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍዳን ያመጣብናል።
_
፯) ሴት ልጅ በአባቷ ቤት ሳለ በራሷ ላይ ብትሳል ማለትም ንጽሕ ጠብቄ ሰውነቴን ለእግዚአብሔር ልዩ ገንዘብ አደርገዋለሁ ብላ የተሳለችውን ስለት መፈጸም ይገባታል። አባቷም ስለቷን አያፍርስባት። ስትሳል ሰምቶ ስለቷን ቢያፈርስባት ግን ስለቷ አይጸናላትም። እግዚአብሔርም በዚህ አይመራመራትም። ባል ብታገባ ግን በተሳለችው ስለት ባሏ ሊያዝበት ይገባል። ባሏ ስትሳል ቸል ብሎ ከዚህ በኋላ ቢከለክላት ኃጢአቱ በእርሱ ይሆናል።
_
፰) ጉልት ፍጽምት የሆነች ምጽዋት ናት። በዚህ ዓለምም በሚመጣው ዓለምም ዋጋን ታስገኛለች።ለቤተክርስቲያን ጉልት መጎለት መልካም ነው።
_
፱) የሚጎለተው ጉልት ለሚጎለትላቸው ሰዎች እየኖረ ጥቅም የሚገኝበት ሊሆን ይገባል። ጉልት ዘወትር የሚኖር መሆን አለበት። ይኽውም ምሳሌ የእርሻ ቦታ፣ ቤት፣ አዝርዕት አትክልት ያሉበት ቦታ ወዘተ ይሁን። ባሮችን፣ ከብቶችን፣ ንብ ወዘተ መጎለት አይገባም። እነዚህ ሁሉ ዘወትር አይኖሩምና።
_
፲) የሚጎልተው ሰው ከገንዘቡ የሚያዝበትን እንጂ የማያዝበትን መጎለት አይገባውም። የሚጎልት ሰው አካለ መጠን ያደረሰ፣ አዋቂ፣ ራሱን የቻለ፣ በልቡ በጎ ነገርን የሚያስብ ሊሆን ይገባል። የሚጎልቱለት ሰውም ሃይማኖት ከምግባር ያለው ሊሆን ይገባል።
_
፲፩) የተጎለተለት ሰው ከጉልቱ ምንም ምን አይሽጥ። ሩቅ ሀገር ለሄደ ሰው ጉልት ቢጎለትለት መታጣቱ (መሞቱ) ቢታወቅ ለእርሱ የታዘዘው ጉልት ለቤተክርስቲያን ይግባ። የተቸገሩ ሰዎች ይረዱበት ዘንድ።
_
፲፪) ጥቅም የሚገኝበት ሥርዓት ቢፈርስ መልሶ ሊያጸኑት ይገባል።
_
፲፫) ጎላቹ ቢቸገር ከጉልቱ ከርቦው ከአምሾው ሊሰጡት ይገባል።
_
፲፬) የሚጎለተው ጉልት የንጉሥ ግብር ያለበት መሆን የለበትም።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፲፭ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2024/09/24 06:22:44
Back to Top
HTML Embed Code: