Telegram Web Link
+ መጥምቁ ዮሐንስን ማን አጠመቀው? +

ታላቁ ነቢይ ካህን ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታ ጥምቀት በዓል በደረሰ ቁጥር የሚታሰብ የጥምቀቱ ዋነኛ ተሳታፊ ነው፡፡ የጌታን መጠመቅ ስናስብ ሁሌም በተፈጸሙት ታላላቅ ድንቅ ነገሮች ተማርከን የምንዘነጋው ርእሰ ጉዳይ ቢኖር የአጥማቂውን መጠመቅ ጉዳይ ነው፡፡

የሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ልጅ እንደመሆኑ በሊቀ ካህናትነት የማገልገል ሙሉ መብት ቢኖረውም ወደ ሰሎሞን መቅደስ በመሔድ ፈንታ ወደ በረሃ የመነነው ይህ ባሕታዊ አገልግሎቱን የጀመረው "ንስሓ ግቡ" ብሎ እንደ ምድረ በዳ የደረቀ ልብ ባላቸው አይሁድ መካከል ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ እርሱ መጣ፡፡

ዮሐንስ ክርስቶስን ያገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም፡፡ ከሠላሳ ዓተታት በፊት ሁለቱም በእናቶቻቸው ሆድ ውስጥ ሆነው ተገናኝተዋል፡፡ ‘’በእናትህ ሆድ ሳለህ አውቄሃለሁ’’ ብሎ የተናገረውን ፈጣሪውን እኔም ‘’በእናትህ ሆድ ሳለህ አውቄሃለሁ’’ ብሎ ማነጋገር የሚችል ከመጥምቁ ዮሐንስ በቀር ማን አለ? ‘ከማኅፀን ጀምሮ ባንተ ታመንሁ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ‘’ ብሎ የዳዊትን መዝሙር ለመዘመር የሚችል እንደ መጥምቁ ያለ ማን አለ? ቅዱስ ያሬድ ‘እምከርሠ እሙ አእመረ ሰገደ ወአንፈራዓፀ’’ ‘በእናቱ ማኅፀን አወቀ ሰገደ ዘለለም’ ብሎ በድጓው የዘመረለት ዮሐንስ ለጌታው ለመስገድ ከእናቱ ማኅፀን እስኪወጣም አልታገሠም፡፡ ጉልበቱ ሳይጸና መስገድ የጀመረ ፣ በዓይኑ ማየት ሳይፈልግ አምልኮ የጀመረ ከዮሐንስ በቀር ማንም የለም፡፡

አሁን በእናቱ ማኅፀን ያገኘውን ጌታ ሁላችንን ወደምትወልደው ወደ ማኅፀነ ዮርዳኖስ ሲመጣ አየው፡፡ ዮሐንስና ጌታ ከሠላሳ ዓመት በፊት ተገናኝተዋል ግን አልተያዩም ነበር ፣ መልእክት ተለዋውጠዋል ነገር ግን አልተነጋገሩም፡፡ ለዚህ ነው ዮሐንስ ስለ ጌታ ‘’አላውቀውም ነበር‘’ ያለው፡፡ /ዮሐ 1፡31/ አሁን ግን ጌታውን አየው፡፡ ወደ እርሱ ሊጠመቅ መምጣቱን ተመለከተ፡፡

ወደ ዮሐንስ ሊጠመቁ የሚመጡ ሁሉ ኃጢአት ያለባቸው ስርየትንና በውኃው መንጻትን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አሁን ግን ሊጠመቅ የመጣው ጌታ ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው ‘ክርስቶስ ከራስዋ ከጥምቀት የበለጠ ንጹሕ ነው‘’ የእርሱ መምጣት ዮሐንስን የሚያስደንቅ ነበር፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ሲል አሰበ ይላል ሊቁ ፦

‘’ጌታ ሆይ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ አንተ ‘’ክፋትን አላደረገም ፤ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም‘’ ብሎ ሳለ [ኃጢአተኞች ተጠምቀው ወደሚነጹባት] ወደ እኔ ጥምቀት ስለምን መጣህ? ሁሉን የምታነጻ ሆይ መንጻትን ትሻለህን? በልማድ በእኔ ዘንድ የሚጠመቁ ሁሉ ኃጢአታቸውን ይናዘዛሉ፡፡ አንዳች በደል የሌለብህ ሆይ አንተ ምን ብለህ ትናዘዛለህ?’’

ዮሐንስ የጌታን ሊጠመቅ መምጣት አይተው እንደ ኃጢአተኛ እንዳይቆጥሩበት ፈርቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ጮኸ፦

‘የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ!’’ አለ፡፡ ወደ እኔ ጥምቀት ሲመጣ እርሱ በደል ያለበት እንዳይመስላችሁ! እርሱ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው ብሎ በሕዝቡ ፊት መሰከረ፡፡ ይህ አዋጅ በዙሪያው ካሉት በላይ ለሁላችን የሚሠዋውን በግ ተስፋ ላደረግን ለሁላችን ታላቅ ብሥራት ነበር፡፡ አባቱን ‘የመሥዋዕቱ በግ ወዴት አለ?’’ እያለ በጥያቄ ሲያስጨንቅ እንደነበረው እንደ ይስሐቅ በጉን ልናይ ለናፈቅን ለሁላችን ደስ የተሰኘንበት መልስ ይህ የመጥምቁ ዮሐንስ ‘የእግዚአብሔር በግ እነሆ’ የሚል አዋጅ ነበር፡፡

ጌታችን ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ ሲመጣ ዮሐንስ ተጨነቀ፡፡ እናቱ ለድንግል ማርያም አንቺ እንዴት ወደ እኔ ትመጫለሽ? እንዳለች እርሱም ለጌታው እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ መጣህ? አለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‘ወገሠሦ እንተ ኢትትገሠሥ ርእሶ’ /የማትዳሰስ ራሱን ዳሰሰው/ እንዲል ጫማውን ተጎንብሼ ልፈታና ልሸከም አይገባኝም ብሎ ሲሰብክለት የቆየው ጌታ እጅህን ከራሴ በላይ ከፍ አድርገህ አጥምቀኝ ሲለው ትሑቱ ዮሐንስ እጅግ ተጨነቀ፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል ‘ዮሐንስን በመደነቅ ተሞልቶ አየሁት ፤ በዙሪያው ያሉትም እንዲሁ፡፡ የከበረው ሙሽራ በመካኒቱ ልጅ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ አጎነበሰ፡፡ የሁሉ አጥማቂ ሊጠመቅ መጣ’’ ዮሐንስ ለጌታው አጥምቀኝ የሚል ጥያቄ እንዲህ ሲል በጭንቀት መለሰ ፦ ‘‘እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል ፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን ብሎ ይከለክለው ነበር?/ማቴ 3፡14/

ቅዱስ ያሬድ ጌታ በባሪያው መሪነት ወደ ባሕር መውረዱን ያደንቃል ፤ ‘‘ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ’’ /መሬታዊ አጥመቆ ለሰማያዊ/ እያለም ሰውን ከአፈር ያበጀው ፈጣሪ በፈጠረው አፈር እጅ ሊጠመቅ ማጎንበሱን ያደንቃል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ ስለ አምላክ መገለጥ በሰበከው ስብከት /Homily on the Theophany/ ጌታ በባሪያው እጅ ሊጠመቅ በወደደ ጊዜ የተፈጠረውን ክስተት እንዲህ ይተርከዋል ፦

‘‘ጌታ በባሪያው ፊት ቆሟል፡፡ በወታደሩ ፊት የሚያጎነብስን ንጉሥ አይቶ የሚያውቅ ማን ነው? እረኛስ በጉን መንገድ ምራኝ እያለ ሲጠይቅ የተመለከተ ሰው ማን ነው?
ዮሐንስ እንዲህ አለ ፦ የማደርገው ግራ ገብቶኛል በቀን ብርሃን ላይ የብርሃን ጭረሮችን ማብራት እንዴት ይቻላል?
የጠራ ወርቅን እንዴት በጭቃ አጥቦ ማጥራት ይቻላል? ባሕር በምንጭ ላይ ይችላልን? ወንዝስ በውኃ ጠብታ ይሞላልን? ንጽሕና ራሱ በአዳፋው እጅ እንዴት ይታጠባል? ዳኛው በተፈረደበት ሰው እጅ ነጻነትን ይቀበል ዘንድ የተለመደ አይደለም፡፡ ‘እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባኛል!’’
የሞተው ሕያዉን ሊያስነሣ ይችላልን? የታመመውስ ሐኪሙን ሊፈውስ ይችላልን? የባሕርዬን መጎስቆል አውቀዋለሁ፡፡ ደቀመዝሙር ከመምህሩ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም፡፡ /ማቴ 10/ ኪሩቤል ወደ እኔ የሚቀርቡት በፍርሃት አይደለም ፣ ሱራፌልም ለእኔ ቅዱስ ቅዱስ ብለው አይዘምሩም ፣ ሰማይ ዙፋኔ አይደለም ፣ ኮከብም ልደቴን ለጥበብ ሰዎች አላሳየም ፣ ከደመናም ስለእኔ የሚጮህ ድምፅ የለም፡፡ ወዳጅህ ሙሴ እንኳን ጀርባህን ያያል ተብሎ ነበር፡፡ እጅግ ንጹሕ የሆነውን የራስህን አክሊል እነካ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? ከእኔ ኃይል በላይ የሆነን ነገር ስለምን ትጠይቀኛለህ? ፈጣሪዬን ለማጥመቅ የምችልበት እጅ የለኝም ይልቅስ ‘እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል’ ያም ሆነ ይህ ጌታ ፈቅዷልና ‘’ጽድቅን እንፈጽም ዘንድ ይገባናል’’ ብሎ የጽድቅ /ሕገ ኦሪት/ ፍጻሜ የሆነችውን የዮሐንስን ጥምቀት ሊጠመቅ ፈቀደ፡፡

ወደ ተነሣንበት ነገር ስንመለስ ዮሐንስ ጌታ አጥምቀኝ ሲለው ‘እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል’ ብሎ ጥምቀት እንደሚያስፈልገው ተናግሮ ነበር ፡፡ ይህ ቃል ምንኛ ድንቅ ነው? መጠመቅ የሚፈልግ አጥማቂ እንዴት ያለ ነው? ሌሎች በእርሱ ለመጠመቅና ለመንጻት ተሰልፈው ሳለ እርሱ ‘መጠመቅ ያስፈልገኛል’ እያለ ሌላ ጥምቀት የሚመኝ አጥማቂ እንደምን ያለ ነው? ወደ እርሱ ሊጠመቅ የመጣን ተጠማቂ አጥምቀኝ እያለ የሚማጸን አጥማቂ ማን አይቶ ያውቃል? አዎ ዮሐንስ ግን አድርጎታል፡፡
ዮሐንስ የተመኛት ጥምቀት ልጅነትን የምታስገኘዋን በክርስቶስ አምነን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የምንጠመቃትን የክርስትና ጥምቀት ነበር፡፡ የእርሱ ጥምቀት የማያጸዳው የሰው ልጅ መርገም አለና እርሱን ሊታጠብ ሽቶ መጠመቅ ፈለገ፡፡ አፈወርቅ ‘ልጠመቅ ያስፈልገኛል’ የሚለውን ንግግር ሲያብራራ እንዲህ ማለቱ ነው ብሏል ፦ ‘ጌታ ሆይ ለዓለም ሁሉ የምትሠጠውን ጥምቀትህን ሥጠኝ፡፡ በሰው ሁሉ ላይ ያለውን የመርገም ሸክም ተሸክሜያለሁና ፣ በዕባቡም መርዝ ተመርዤአለሁና እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል’’

መጥምቁ ዮሐንስ የተመኛትን ጥምቀት ተጠምቆ ይሆን? ከተጠመቀስ መቼ በማን ተጠመቀ? በሚለው ላይ አንድ በቃኝ መልስ መሥጠት ቢከብድም በዚህም አለ በዚህ ዮሐንስ ጥምቀትን ተመኝቷት እንዳልቀረ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ብዙ ሊቃውንትና ቅዱሳን የዮሐንስ ጥምቀት የትኛው ነው በሚለው ላይ የተለያዩ ሃሳቦች አስቀምጠዋል፡፡

የመጀመሪያው የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ስለ ዮሐንስ ጥምቀት ሲናገር ‘አጥመቀ ወተጠመቀ ለሊከ’’ ይላል ፤ ‘አጠመቅህ አንተም ተጠመቅህ’ ማለት ነው፡፡ በሌላ ሥፍራ ደግሞ ‘አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ በፈለገ ዮርዳኖስ እምድኅረ አጥመቀ ለሊሁ ተጠምቀ’ ‘ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ አጠመቀው ካጠመቀ በኋላም እርሱም ተጠመቀ’’ ብሏል፡፡ በአጭሩ ቅዱስ ያሬድ የመጥምቁ ዮሐንስ የጥምቀት ቀን ጌታን ያጠመቀበት ቀን ነው ባይ ነው፡፡

በእውነትም ልብ ብለን ስናየው ለዮሐንስ ጥምቀት ከዚያች ቀን የተሻለ ቀን የሚመጣ አይመስልም፡፡ ያለበት ውኃ በጌታ በራሱ የተቀደሰው የዮርዳኖስ ወንዝ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‘‘ተቀደሰት ማይ በጥምቀቱ’’ /ውኃ በጥምቀቱ ተቀደሰች/ ብሎ የዘመረው ስለ ዮርዳኖስ ነበር ፤ በጌታና በዮሐንስ መካከል የነበረውን የአጥምቀኝ ውይይት በዘመረበት ሥፍራም ‘ዮሐንስም ኢየሱስን እንደምን አንተን ማጥመቅ እችላለሁ? ጌታ ሆይ ውኃ ይሸከምሃልን? አለው፡፡ ኢየሱስም ለዮሐንስ እኔ ካልጠመቅሁ ውኃ አትቀደስም አለው’’ /‘ወይቤሎ ዮሐንስ ለኢየሱስ እፎኑ እክል አጥምቆትከ ዓይኑ ማይ እግዚኦ ይፀውረከ ፤ ይቤሎ ኢየሱስ ለዮሐንስ ኢትትቀደስ ማይ ለእመ ኢተጠመቁ አነ’’/ ብሎአል፡፡

በጌታ መጠመቅ ከተቀደሰችው ከዚህች ቅድስት ውኃ በቀር ለዮሐንስ ጥምቀት ምን የተሻለ ውኃ ሊመጣ ነው? ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እንኳን የመንገድ ዳር ውኃ አይቶ ‘እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማን ነው?’’ ካለ መጥምቁ ዮርዳኖስ መካከል ሆኖ እንዳይጠመቅ የሚከለክለው ምንድር ነው? ከውኃውም አልፎ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ አብሮት በባሕር መካከል ቆሞ ፣ አብ በደመና ድምፁን አሰምቶት ፣ መንፈስ ቅዱስ በርግ አምሳል ወርዶ ታይቶት ከዚህ የተሻለ ቀን ለዮሐንስ ጥምቀት ከየት ሊመጣ ነው? ስለዚህ ‘አጠመቅህ አንተም ተጠመቅህ’ የሚለው የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ስለ ዮሐንስ ጥምቀት እጅግ ትርጉም ያለው ምላሽ ነው፡፡

የዮሐንስን በዮርዳኖስ መጠመቅ የበረከት እንጂ የልጅነት ጥምቀት አይደለም ፤ የልጅነት ጥምቀት ገና አልተሠጠችም የሚሉ ሊቃውንትም አሉ፡፡ በእናቱ ማኅፀን ሳለ ተጠምቋል ፤ ገብርኤልም ‘’በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል’ ብሎአል ብለው ዮሐንስን በማኅፀን ተጠመቀ የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ግን ዮሐንስ ‘ልጠመቅ ያስፈልገኛል’ ብሎ አለመጠመቁን ስለተናገረ በማኅፀን የልጅነትን ጥምቀት አለማግኘቱ ግልጽ ነው፡፡ ሌላው በሊቃውንት ዮሐንስ ተጠመቀ የሚባልበት ክስተት በሰማዕትነት መሞቱ ነው፡፡ እርሱ በክርስቶስ አምኖ እና ስለ ክርስቶስ ዞሮ አስተምሮ ተጋድሎ በግፍ ሰማዕት የሆነ ነው፡፡ በክርስቶስ አምነው ሳይጠመቁ የሚሞቱ ደግሞ በውኃ ሳይሆን በደም ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ይህንንም የዮሐንስ ጥምቀት ነው የሚሉት አሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጥምቀትን አላገኛትም የሚል ቢኖር ግን ሠላሳ ሦስት ዓመታትን በምድር የነበረው ክርስቶስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለሠላሳ ሦስት ሰዓታት ለነፍሳት ነጻነትን በሰበከበት ዕለት ‘ወመጠውኩዎሙ ዕዴየ ዘየማን ወኮነቶሙ ጥምቀተ’ /የቀኝ እጄን ሠጠኋቸው ጥምቀትም ሆነቻቸው/ የተባለላት ጥምቀት መጥምቁን ልታልፈው አትችልም፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ በአንዱ የመጥምቁ ዮሐንስ ‘በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል’ የሚል ምኞቱ ተሳክቷል፡፡

ይህ ትሑት አጥማቂ ክብሩ እንዴት ከፍ ያለ ነው? ቅዱስ ያሬድ ‘ርእዩ ዕበዮ ለዮሐንስ ዘመላእክት ይስግዱ ሎቱ’’ እንዳለ ቅዱሳን መላእክት ሳይቀሩ ለክብሩ የሚሰግዱለት ፤ የሙሽራው ክርስቶስ ሚዜ ፣ ለፀሐይ ክርስቶስ ጨረቃው ፣ ለንጉሥ ክርስቶስ አዋጅ ነጋሪው ፣ ለቃል ክርስቶስ ድምፁ ፣ ጌታ በምድር ከመስበኩ በፊት ቀድሞት የሰበከ መንገድ ጠራጊው ፣ በሲኦል ላሉ ነፍሳትም ቀድሞ ከጌታ መምጣት በፊት ያወጀ የሰማይ መንገድ ጠራጊው ፣ ክርስቶስ ሞቱን ሲሰማ በምድረ በዳ ብቻውን ያዘነለት ወዳጁ ፣ ድርሳነ አማኑኤል እንደሚል ከሞተ በኋላ በኖረባት ምድረ በዳ ተዝካሩን ዓሣና እንጀራ አበርክቶ ያወጣለት የቅርብ ዘመዱ ፣ ገብርኤል አስቀድሞ ሳይወለድ የዘመረለት ታላቅ ነቢይ ፣ የአባቱን የተዘጋ ልሳን ከተዘጋ ማኅፀን ተወልዶ የከፈተ ድምፅ ፣የጌታን መወለድ ስናስብ ወላዲተ አምላክ የተባለች የድንግልን መውለድ እንደምናደንቅ የጌታን መጠመቅ ስናስብ የሱን ማጥመቅ የምናደንቅለት መጥምቀ መለኮት እጅግ ታላቅ ነው፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥምቀት 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ

ማስታወሻ :- መጥምቁ ዮሐንስ "የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም ነበር" (ሉቃ. 1:15) ይህንን በዓል በስካር ማክበር የማይሰክረውን ዮሐንስ ማሳዘን ነው::

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
#ጌታችን_ሲጠመቅ_ሰማያት_የተከፈቱት_ለምንድን_ነው?

አንተም ብትጠመቅ ሰማያት እንደሚከፈቱልህ፣ እግዚአብሔር ወደ ሰማያዊ ሀገርህ እንደሚጠራህ፣ እንደዚሁም [ነፍስህን አጉድለህ ተጨልጠህ ተገርኝተህ] ይህን ዓለም ልትወድ እንደማይገባህ ሲያስረዳህ ነው፡፡ [አንተ ወይም ሌላ ሰው ሲጠመቅ] በግዘፍ ሰማያት ሲከፈቱ ያላየህ እንደኾነም፥ በፍጹም አትጠራጠር፡፡ ድንቆችና መንፈሳዊ ምሥጢራት ኹሉ በገሃድ የሚታዩት፣ ሰው ሊያያቸው ወይም ሊሰማቸው የሚችሉ ራእያት የሚገለጡት፣ ተአምራትም የሚከናወኑት፥ መንፈሳዊ ዕውቀት ለሌላቸው፣ ለማመን በአፍአ የሚታይ ምልክትን ለሚፈልጉ፣ መንፈሳዊውን ዓለም ለመረዳት በአእምሮ ሕፃናት ለኾኑ፣ በአፍአ የሚታይ ነገር ሲኖር ባዩት ነገር ደስ ተሰኝተው ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ለሚችሉ፣ ከዚህ በኋላ እንደዚህ ያለን ራእይ ወይም ተአምር ባይመለከቱም እንኳን መጀመሪያ ላይ አንድ ጊዜ በተመለከቱት መሠረት ኹሉንም በእምነት መቀበል ላለባቸው ሰዎች ነውና፡፡

በሐዋርያትም ዘንድ፥ “እንደ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ” እና “እንደ እሳት የተከፋፈሉ ላንቃዎች (ልሳናት)” ታይተው ነበር (ሐዋ.2፡2)፡፡ ነገር ግን እነዚህ በዚያ ለነበሩት አይሁድ ረብ እንጂ ለሐዋርያቱ ጥቅም የታዩ አልነበሩም፡፡

አሁንም እኛ በአፍአ የሚታዩና የሚሰሙ ምልክቶች ባይኖሩም እንኳን አንድ ጊዜ በሐዋርያት የተገለጡትን ነገሮች በእምነት እንቀበላቸዋለን፡፡

መንፈስ ቅዱስም ቢኾን በርግብ አምሳል በጣት እንደሚጠቁም ኾኖ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያመለከተው እርሱ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ እንደ ኾነ እዚያ ለነበሩት ሰዎችና ለዮሐንስ መጥምቅ ለማሳየት ሲል ነውና፡፡ ስለዚህ ብቻም አይደለም፤ አንተም ስትጠመቅ እንዲህ ያለ ቅዱስ መንፈስ ይወርድልሃል ለማለትም ጭምር ነው እንጂ፡፡ ነገር ግን እኛ አሁን እንደዚህ ያለ በግልፅ የሚሰማና የሚታይ ራእይን ወይም ምልክትን አንሻም፤ በእነዚህ ኹሉ ፈንታ እምነት በቂያችን ነውና፡፡ ምልክት ወይም ተአምር ለማያምኑ ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለምና (1ኛ ቆሮ.14፡22)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - የማቴ. ወንጌል፣ ድርሳን 12 ቁ.3 #በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ

@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
+ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? +

ልጅ እናቱን ‹አንቺ ሴት› ብሎ መጥራት በእኛ ሀገር ባሕልና በብዙ ቋንቋዎች ባሕል ፈጽሞ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ በተለይ በአደባባይ ሲሆን ይከብዳል:: ጌታ እናቱን ካልጠፋ ስም ለምን እንዲህ ብሎ ጠራት?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አከራካሪ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የሚዳኘው በተጻፈበት ቋንቋ (Source language) እንጂ በተተረጎመበት ቋንቋ ባሕል አይደለም፡፡ ይህ አነጋገር በአይሁድ ዘንድ እና የዮሐንስ ወንጌል ላይ በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ የሚሠጠው ትርጉም በእኛ ዘንድ ካለው ትርጉም የተለየ ነው፡፡

በግሪኩ ‹‹አንቺ ሴት›› (gune = woman") ተብሎ የሚጻፍ ሲሆን ጌታችን እመቤታችንን ‹‹አንቺ ሴት›› ብሎ በጠራበት ሥፍራ ግን በግሪኩ ‹አንቺ ሴት› የሚለው ንባብ የተጻፈው ‹አንቺ ሴት ሆይ› (gynai "Dear woman") በሚል የአክብሮት አጻጻፍ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አነጋገር ደግሞ ነገሥታት ለንግሥቶቻቸው በሚጽፉአቸው ደብዳቤዎችም ላይ ጭምር ይጻፍ የነበረ እንደሆነ የቋንቋው ባለቤቶች የሆኑት ግሪካውያን አገናዝበው ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ አውግስጦስ የተባለው ንጉሥ ለግብፃዊቷ ንግሥት ለክሊዮፓትራ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመው ቃል የግሪኩን ‹gynai› /ጋይናይ /አንቺ ሴት ሆይ/ የሚለውን የአክብሮት አጠራር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ጌታችን በቃና ሰርግ ቤት ‹አንቺ ሴት› ብሎ የተናገረው ንግግር የቁጣ አነጋገር ነው የሚሉ ሰዎችን ሃሳብ እንዳንቀበል የሚያደርገን ሌላው ምክንያት ደግሞ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር ለእናቱ የተናገረው በቃና ሰርግ ቤት ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እያለ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር ቆማ መከራውን እያየች በጽኑ ኀዘን ላይ እያለች ‹‹አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ›› በማለት ዮሐንስን ለእርስዋ እርስዋን ለዮሐንስ ሠጥቷል፡፡

በልጅና በእናት መካከል ባለው ሥነ ልቡናዊ ትስስር ምክንያት ለእናት የልጅዋን ስቃይ ቆሞ መመልከት እጅግ ከባድ ስቃይን ያስከትልባታል፡፡ እመቤታችን እያንዳንዱ ችንካር በተወደደ ልጅዋ እጅ ውስጥ ሲቸነከር ልብዋ በኀዘን ይቸነከር ነበር፡፡ ታዲያ ‹አንቺ ሴት› የሚለው አነጋገር የቁጣ አነጋገር ከሆነ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ‹በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ እያለፈባት› ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል?

በሰርግ ቤት ውስጥስ ስለጠየቀችው ተቆጣ ይባል ፤ በመስቀል ሥር የልጅዋን ስቃይ በዝምታ ስትመለከት የነበረችን እናት ልጅዋ በስቃዩ መካከል ትንፋሹን ሰብስቦ ‹‹ተቆጣት›› ብሎ ሊነገር እንዴት ይችላል? በስተግራው የተሰቀለው ወንበዴ ‹አንተስ ክርስቶስ አይደለህም› ብሎ ሲሰድበው መልስ ያልሠጠ ‹ከቁጣ የራቀ› አምላክ በእርሱ ስቃይ እየተሰቃየች ያለችውን እናቱን እንዴት ይቆጣል? (ሉቃ. ፳፫፥፴፱) ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ከእናቱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ ‹እናቴ› ብሎ በመጥራት ወይም ‹ማርያም› በማለት ፈንታ ‹አንቺ ሴት› የሚለውን አጠራር መጠቀሙ እመቤታችን በኦሪት ዘፍጥረት በተጠራችበት ስም ለመጥራት እና እርስዋ ትንቢት የተነገረላት ዳግሚት ሔዋን ፣ ጌታችንም የዕባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ዘርዋ መሆኑን የሚያስረዳን ነው፡፡

በሊቃውንት ዘንድ የወንጌል መቅድም (Protevangelium / Protogospel) ወይም ‹የመጀመሪያው የነገረ ሥጋዌ ትንቢት› በመባል የሚታወቀው ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።›› የሚለው ትንቢት በእርስዋ መፈጸሙን ከምንረዳበት መንገድ አንዱ ጌታችን ‹አንቺ ሴት› ብሎ በመጥራቱ ነው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፭)

በዕለተ አርብ በዕባብ የተመሰለው ዲያቢሎስ የጌታችንን ‹ሰኮና› በአይሁድ አድሮ ሲቀጠቅጥ ዋለ፡፡ ‹ዘርዋ› የተባለው ጌታም የዕባቡን ራስ እንዲሁ በመስቀሉ ቀጠቀጠው፡፡ በዚህ ወቅት እናቱን ደግሞ ‹አንቺ ሴት› ብሎ ጠራትና በትንቢቱ ላይ ያለችው ‹ሴቲቱ› እርስዋ መሆንዋን አስረዳን፡፡

የጻፈውን መተርጎም ልማዱ የሆነው ዮሐንስም ይህንን ጉዳይ የበለጠ ግልጽ በሚያደርግ ሁኔታ የሴቲቱን ፣ የልጅዋን እና የቀደመውን ዕባብ ማንነት በአንድ ምእራፍ ላይ አብራርቶ በራእዩ ጽፎልናል፡፡ ‹‹ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። ... ዘንዶውም (እርሱም የቀደመው ዕባብ) በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ›› በማለት የዘፍጥረቱን ትንቢት በመተርጎም ሴቲቱ በእርግጥም ‹አሕዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ የወለደችው› እመቤታችን መሆንዋን አስረድቶአል፡፡ (መዝ. ፪፥፱) ስለዚህ ጌታ ‹አንቺ ሴት› ማለቱ ጾታን ለማመልከት ብቻ ሳይሆን እመቤታችን የትንቢቱ ፍጻሜ መሆንዋን የሚያስረዳ የክብር አነጋገር ነው፡፡ (ራእ. ፲፪፥፩-፲፰)

እንዲሁም ለአዳም ሔዋን በተሠጠችው ጊዜ ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።›› ማለቱ (ዘፍ. ፪፥፳፫) ሴት የሚለውን ቃል ትርጉም ጾታን ከመግለጽ በላይ ‹ሥጋሽ ከሥጋዬ አጥንትሽም ከአጥንቴ› የሚል የእኔነት ትርጉም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ የመጀመሪያው አዳም ከጎኑ ሔዋንን ያስገኘ ሲሆን ሁለተኛው አዳም ግን ከሁለተኛዋ ሔዋን የተገኘ ነው፡፡ ሆኖም ሁለተኛው አዳምም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ የሁላችንን እናት ጥምቀትን (ቤተ ክርስቲያንን) አስገኝቷል፡፡

- ከአንቺ ጋር ምን አለኝ

‹‹ከአንተ / ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ስድስት ቦታ ፣ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በአምስት ቦታዎች ተጽፎ የምናገኘው አነጋገር ነው፡፡ ይህ ዐረፍተ ነገር በየተጻፈባቸው አገባቦች (contexts) ሁለት ዓይነት ትርጉም የሚሠጥ ሆኖ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው አገባብ አለመግባባትን የሚገልጽ አነጋገር ሲሆን ፤ ሁለተኛው አገባብ ደግሞ አክብሮትን ወይም ሰላም ጠያቂነትን የሚያሳይ አነጋገር ነው፡፡

አለመስማማትን የሚያሳይ የተግሣጽ ንግግር ሆኖ የምናገኘው በነቢዩ ኤልሳዕ ታሪክ ነው፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ መፍትሔ ለመጠየቅ መጥቶ ነበር፡፡ ኢዮራም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አድርጎ ስለነበር ኤልሳዕ ‹‹እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ›› ብሎ መልሶለት ነበር፡፡ ኢዮራም ኤልሳዕን ለማነጋገር ሲሞክርም ኤልሳዕ በቁጣው ጸንቶ ‹‹አብሮህ ያለውን የይሁዳን ንጉሥ ባላፍር ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር፡፡›› ብሎታል፡፡ (፪ነገሥ. ፫፥፲፫)

በዚህ ታሪክ ውስጥ በግልጽ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል ‹ከአንተ ጋር ምን ኅብረት አለኝ?› በሚል አገባብ ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይም እግዚአብሔር የጢሮስ ፣ የሲዶናና የፍልስጤም ግዛትን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ስላደረሱት በደል እንደሚፋረዳቸው በተናገረበት አንቀጽ ‹‹ከእናንተ ጋር ለእኔ ምን አለኝ? በውኑ ብድራትን ትመልሱልኛላችሁን? ፈጥኜ ብድራታችሁን በእናንተው ላይ እመልሳለሁ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህም ስፍራ እንዲሁ ይህ አነጋገር ከቁጣ ጋር ተነግሮ ይገኛል፡፡ (ኢዮ. ፫፥፬)
ሁለተኛው አገባብ ደግሞ ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ትርጉም የሚሠጠው አገባብ ነው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ለእርሱ የተቆረቆሩ የጽሩያ ልጆች የሰደበውን ሳሚን ‹እንምታው ፣ እንግደለው› ሲሉ ‹‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?›› ብሎ ከልክሎአቸዋል፡፡ (፪ሳሙ. ፲፮፥፲) ተሳዳቢው ሳሚ መጥቶ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ ይቅርታ ሲጠይቅም ዳግመኛ ‹‹እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት ይገባዋል›› አሉ፡፡

ይህን ጊዜ ዳዊት ‹እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን?›› (፪ሳሙ. ፲፱፥፳፪)
በእነዚህ የንጉሡ ንግግሮች ውስጥ ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው ቃል በአክብሮት የተነገረ ባይሆንም መልእክቱ ግን ‹ምን ጠብ አለኝ› ማለት መሆኑን ከአገባቡ መረዳት ይቻላል፡፡ ምናልባት የመጨረሻው አገባብ ቁጣ ያዘለ ቢመስልም እንኳን እየተናገረ ያለው ለእርሱ ከእርሱ በላይ ለተቆረቆሩት ታማኝ ወታደሮቹ ጋር መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ እርሱም ‹ከእናንተ ጋር ምን አለኝ?› ያለውን ‹ለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ?› ብሎ በማብራራት የንግግሩ ፍሬ ሃሳብ ‹ከእናንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› እንደሆነ አሳይቶአል፡፡

ሌላው ማሳያ ደግሞ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ ንግግር ነው፡፡ ኒካዑ ካልተዋጋሁህ ብሎ ለመጣበት ለኢዮስያስ ፡- ‹‹የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም እግዚአብሔርም እንድቸኵል አዝዞኛል ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን በእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ ብሎ መልእክተኞችን ላከበት።›› (፪ዜና ፴፭፥፳፩) ይህ አነጋገር በትሕትና እና ‹ሆይ› በሚል የአክብሮት አጠራር የቀረበ ነው፡፡ በግልጽ ‹ልዋጋ የተነሣሁት ከሌላ ጋር ነው ፤ ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝና ነው የምዋጋው!› ነው ያለው፡፡ በእውነቱ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ማለት ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ማለት መሆኑን ለማስረዳት ከዚህም የተሻለና ግልጽ ታሪክ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢዮስያስ የተነሣው ለጠብ ነው፡፡ ኒካዑም በአክብሮት የነገረው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ብሎ ነው፡፡

እንደተጨማሪ ማሳያ የምናገኘው ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስን በቤትዋ የተቀበለችው የሰራፕታዋ መበለት የተናገረችው ነው፡፡ ይህች ሴት ኤልያስ በቤትዋ በመገኘቱ በቤትዋ ያለው ምግብ ተባርኮ በረሃብ ዘመን እየተመገቡ ከከረሙ በኋላ ልጅዋ በጠና ታመመ፡፡ ይህን ጊዜ ሴቲቱ ወደ ኤልያስ ቀርባ ፡-

‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኃጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን? አለችው።›› (፩ነገሥ.፲፯፥፲፰)
ይህች ሴት ለነቢዩ በአክብሮት ያለችው ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› ነው፡፡ የቁጣና የተግሣፅ ንግግር ነው እንዳይባል መቼም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ...›› ብሎ የሚጀምር ቁጣ የለም፡፡ እንዲያውም በአንድ ሰው ስንቆጣ ማዕረጉን ትተን እንናገራለን እንጂ ማዕረግ ጠብቆ ቁጣ የለም፡፡

ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንመጣ ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› የሚለውን ቃል የተናገሩት ዛሬ በወዳጆቻቸው አድረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ማለት ስድብ ነው› እያሉ የሚበጠብጡን አጋንንት ናቸው፡፡ ከአዋቂ ጋር እንደ አዋቂ ፤ ካላዋቂ ጋር እንደ አላዋቂ ሆኖ ማደናቆር የአጋንንት ልማድ ነውና እነሱ በሚገባ ትርጉሙን ተረድተው እየተንቀጠቀጡ ለጌታ የተናገሩትን የአክብሮት አነጋገር ለእመቤታችን ሲሆን ትርጉሙ ሌላ ነው እያሉ ያውካሉ፡፡
‹‹እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።›› (ማቴ. ፰፥፳፱)

‹‹እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።›› (ማር. ፩፥፳፬)

‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤›› (ማር. ፭፥፯)

‹‹ ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ።›› (ሉቃ. ፬፥፴፬)
‹‹ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ›› (ሉቃ. ፰፥፳፰)

ምንም እንኳን አጋንንትን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ክብር ባንሠጣቸውም ‹የጠላት ምስክርነት የታመነ ነው› እንዲል (ትምህርተ ኅቡዓት/ትር.) የአጋንንቱ ንግግር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ› የሚለው ቃል በአክብሮት ሊነገር የሚችል ‹ምን ጠብ አለኝ› የሚል ትርጓሜ ያለው መሆኑን በግልጽ ያስረዳል፡፡

ምክንያቱም ‹ከአንተ ጋር ምን አለን› ከማለታቸው ጋር ‹ኢየሱስ ሆይ ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ ፣ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ ፣ የእግዚአብሔር ቅዱሱ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግረዋል፡፡ ከዚያም ‹እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ› የሚል ልመና ተከተለ፡፡ ልመናውም ከእግሩ ሥር እስከ መደፋት ድረስ የደረሰ ነበር፡፡ መቼም ከእግር ሥር ተደፍቶ የቁጣ ንግግር መናገር የማይታሰብ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ባየነው የአገባብ ዝርዝር ‹ከአንተ ጋር ምን አለኝ?› ለሚለው ንግግር የሚያመዝነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ‹ከአንተ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል ነው፡፡ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ጌታችን ለእናቱ የተናገረው ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?› የሚለው አነጋገርም ከአገባቡ እንደምንረዳው ሌሎች ስለ እርሱ በፍርሃት የተናገሩትን የአክብሮት የተነገረ ሲሆን ትርጉሙም ‹የጠየቅሽኝን እንዳላደርግልሽ የሚከለከለኝ ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?› የሚል ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳን መልሱ የእምቢታ ቢሆን ኖሮ አንደኛ እመቤታችን ልመናዋን ቀጥላ ‹እባክህን ልጄ ሆይ› ብላ ለማሳመን ትሞክር ይሆናል እንጂ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ ለአገልጋዮቹ በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝነት ትእዛዝ ልትሠጥ አትችልም ነበር፡፡

ሁለተኛ ደግሞ ጌታችን ከዚያ በኋላ ጋኖቹን ሙሉ ብሎ ተአምራቱን አያደርግም ነበር፡፡ እንዲያውም ጌታችን ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም› ያላት በቁጣና በእንቢታ ከሆነ ለአገልጋዮቹ ‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ› ብላ መናገርዋ የበለጠ ቁጣውን የሚያነድ ነበር የሚሆነው፡፡ ለእርስዋ እንቢ እያላት ቁጣውን ከምንም ሳትቆጥር ሌሎች ሰዎችን ማዘዝዋ የበለጠ አያስቆጣም ወይ ሊባል ይችላል? ይህ ሁሉ የሚያሳየን ጌታችን አንዳች የቁጣ ንግግር አለመናገሩን ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስም የጌታችን መልስ የጠብ ሳይሆን እንዲያውም የጥልቅ ፍቅር መሆኑን ሲገልጽ ‹‹በልቡ ውስጥ ለተከማቸ ፍቅሯ በሚሻል /በሚመጥን/ ነገር መለሰላት›› ‹‹ወአውስኣ ዘከመ ይኄይስ ለዘዝጉብ ፍቅረ ዚኣሃ ውስተ ልቡ›› ብሏል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር) ስለዚህ ‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ› የሚለውን ንግግር የቁጣ ንግግር አድርጎ መተርጎም ጥቅሱን ከአገባቡ የወጣ ጥቅስ (Text out of context) ያደርገዋል፡

+ ጌታችን እናቱን ተቆጥቷት ይሆንን? +
የቃና ሰርግ ቤት ታሪክ ለጊዜው እናቆየውና አንድ ልጅ በአደባባይ በሰዎች ፊት እናቱን በምንም ምክንያት ቢቆጣ እንኳን ከሃይማኖት አንጻር ከሥነ ምግባርም አንጻር የሚደገፍ ሥራ አይደለም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ‹እናቱን በቁጣ ተናገራት› የሚለው አስተሳሰብም እንዲሁ ብዙ የሚያመጣው ጣጣ አለ፡፡ ‹‹እናትና አባትህን አክብር›› ‹‹እናቱን የሰደበ ይሙት›› የሚለውን ሕግ የሠራ አምላክ ‹እኔን ምሰሉ› እያለ ለሰው ልጆች አርኣያ ሊሆን በመጣበት በዚህ ዓለም ራሱ እናቱን በአደባባይ በሰው ፊት ያቃልላታል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድና ለብዙ ሰዎች የኃጢአትን በር ወለል አድርጎ ከፍቶ መረን የሚለቅ ነው፡፡ (ዘጸ. ፳፥፲፪ ፣ ፳፩)

እመቤታችንን የጎዱ መስሏቸው ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለው የሚሰብኩ ሰዎችም ሳያውቁት እየተናገሩ ያሉት በእመቤታችን ላይ ሳይሆን በራሱ በጌታችን ላይ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?›› ብሎ የተናገረ ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፮) ‹የሚጤስን የጧፍ ክር የማያጠፋ ፣ የተቀጠቀጠ ሸንበቆን የማይሰብር› በአነጋገሩ ጭምት ነው፡፡ ስንክሳሩም ‹‹ወንድሜ ምእመን ሆይ ጌታችን ለንጽሕት እናቱ ለድንግል ማርያም ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለቱ የክብርት እናቱን ቃል እንዳቃለለ አታስብ›› ይላል፡፡ (ስንክ. ጥር ፲፪ ቁ. ፵)

በማስከተልም ‹‹ጌታችን የሰማያዊውና የመለኮታዊ አባቱን ክብር እንደጠበቀ ይታወቅ ዘንድ እንዲሁ ከእርስዋ ፍጹም ሥጋንና ፍጽምት ነፍስን ነሥቶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደውን የእናቱን ክብር ጠበቀ፡፡ በወንጌል ይታዘዛትና ይላላካት ነበር ተብሎ እንደተጻፈ›› ይላል፡፡ (ስንክ.ጥር ፲፪ ቁ. ፵፪)
በእርግጥም ጌታችን የባሕርይ አባቱን አብን ክብር እንደጠበቀ በራሱ አንደበት ‹‹አባቴን አከብራለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፱) ለእመቤታችንና ለአሳዳጊው ዮሴፍም እንዲሁ ‹‹ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩) እመቤታችን በቃና ዘገሊላ ስለ ወይኑ የነገረችውም የልጅዋን መታዘዝ በልብዋ ትጠብቀው ስለነበር እና እንደሚታዘዛት ታስብ ስለነበር ነው፡፡

እስቲ ነገሩን ሌሎች ከሚያዩበት ማዕዘን ለመመልከት እንሞክር፡፡ እውነት ግን ጌታችን እናቱን ሊቆጣ የሚችልበት ምን ምክንያት ነበረው? ከላይ እንደተመለከትነው የለመነችው ስለ ራስዋ ጥቅም አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ልመናዋ ከሚያስፈልግ ነገር ውጪ ይደረግ የተባለ አላስፈላጊ የቅንጦት ልመና አይደለም፡፡ በሰርግ ቤት ሙሽሮችን ለዕድሜ ልክ ውርደት ሊዳርግ የሚችል የወይን ጠጅ እጥረት በተከሰተበት ሰዓት ‹ወይን እኮ የላቸውም› ብሎ ማመልከት እንኳን በሩኅሩኁ አምላክ ፊት ይቅርና በእኛ በጨካኞቹ የሰው ልጆች ፊት እንኳን ሊያስቆጣ የሚችል ነገር አይደለም፡፡

የለመነችው እንደ አይሁድ ምልክት ለማየት ጓጉታ አይደለም፡፡ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃውያን ‹አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ትሠራለህ?› ‹ከሰማይ ምልክት ልናይ እንወዳለን› የሚል የፈተና ጥያቄ አልጠየቀችም፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፩ ፤ዮሐ. ፮፥፳) ተአምር የማየት ምኞት አድሮበት እንደጠየቀው እንደ ሄሮድስም በአጋጣሚው ልጠቀምና ተአምር ልይ ብላም አይደለም፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፰) ደግሞስ ያለ ወንድ ዘር በማኅጸንዋ አድሮ በታተመ ድንግልና ሲወለድ ያየች እናት ሌላ ምን ተአምር ሊያስደንቃት ይችላል?
የሰርጋቸው ቀን የኀዘናቸው ቀን ሊሆን ስለተቃረበ ሙሽሮች ተጨንቃ መለመንዋ እንዴት የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል? ያለጊዜው ስለለመነችውና ስለቸኮለች ተቆጣት እንዳንል ልመናዋን ትንሽ ብታዘገየው ኖሮ ነገሩ ይፋ እየሆነ ፣ ሙሽሮቹ መዋረዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ የደረሰችው በሰዓቱ ነው፡፡

የጌታችን አሠራር እንዲህ አልነበረም፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ አማት በንዳድ በታመመች ጊዜ እንዲፈውሳት ሲለምኑት እሺ ብሎ ንዳዱን ገሥፆ አላቀቃት፡፡ (ሉቃ.፬፥፴፱) የአንድ መቶ አለቃ ልጅ በታመመ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎች ሊያማልዱ በመቶ አለቃው ተልከው መጡ፡፡ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑን በማሰብም ‹‹ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።›› የመቶ አለቃውንም ልጅ በመጨረሻ ፈወሰው፡፡ (ሉቃ. ፯፥፪-፮) እነዚህ ሰዎች ተአምር እንዲያደርግ ሲጠይቁት እሺ ያለ ጌታ እናቱ ስትለምነው ይቆጣል ብለን እንዴት እንቀበል? የአይሁድን ሽማግሌዎች እንኳን ያልተቆጣውን ጌታ በምን አንደበታችን እናቱን ተቆጣ ልንለው ይቻለናል?

ከሁሉ በላይ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን›› እንዳለው በረከሰ አንደበታችን ፣ በሚወላውል ልባችን ፣ በሚባክን ሃሳባችን ወደ እርሱ የምንጸልየውን የእኛን የኃጢአተኞቹን ጸሎት ለምን ጸለያችሁ ብሎ ያልከለከለ አምላክ ንጽሕት እናቱ በፍጹም ትሕትና ለለመነችው ልመና የቁጣ ምላሽ ሠጠ ማለት እንዴት እንደፍራለን? ዳዊት ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ›› ብሏል፡፡ እርሱ በልቡ በደል ስለሌለ ጌታ ከሰማው በሃሳብዋ ድንግል የሆነች እናቱን እንዴት አልሰማትም እንላለን? (መዝ. ፷፮፥፲፱-፳)

እመቤታችን የጠየቀችው ይህን ያህል የማይጠየቅ ነገር ነው እንዴ? የመንግሥትህን እኩሌታ ፣ የሥልጣንህን ፈንታ ሥጠኝ አላለችውም፡፡ የጠየቀችው ስለ ድሆቹ ሙሽሮች ነው፡፡ እኛ በረባ ባልረባው ስንዘበዝበው የምንውለውና የምናድረው ታጋሽ አምላክ ለእናቱ ለእኛ የሠጠውን ነገር ይነሣል ማለት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ‹አብን አሳየንና ይበቃናል› ፤ ‹እሳት ከሰማይ ወርዶ ሕዝቡን ያጥፋቸው› ፤ ‹በግራ ቀኝህ አስቀምጠን› የሚሉ ደቀ መዛሙርትን ታግሶ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ያስከተለ ጌታ ቅድስት እናቱ ተገቢ ልመና በተገቢ ሰዓት ስትለምነው ሊቆጣ አይችልም፡፡
እንደ ወንጌሉ ብቻ ከሔድን ደግሞ እመቤታችን ከዚህ በፊትና በኋላ ምንም ነገር ስትለምነው አልተጻፈም፡፡ በወንጌል ለተጻፈው ለዚህ ብቸኛ ልመናዋም መልሱ ቁጣ ነው ብለን አምነን መቀመጥ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ፈጽሞ የሚዋጥልን ሃሳብ አይደለም፡፡ በልጅነትዋ ወልዳው ለተሰደደችው ፣ በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ ላለፈባት እናቱ አንዴ ብትለምነው ተቆጣ ብለን እንዴት እንናገራለን?

ጌታችን በዚህ ሰርግ ቤት እንኳንስ እንዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚተረጉመው ‹ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግሮ ቀርቶ ፤ ለእናቱ የተናገረው በቀጥታና በግልፅ የቁጣ ንግግር ቢሆን ኖሮ እንኳን ጾመን ጸልየን ፣ ወድቀን ተነሥተን ምሥጢራዊ ትርጉሙን እንፈልጋለን እንጂ ሰማይና ምድር ቢነዋወጥ ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለን አናምንም!!!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከቃና ዘገሊላ መጽሐፍ የተወሰደ@ @EotcLibilery @EotcLibilery @EotcLibilery
መረጃውን በአግባቡ ለማጋራት ሰፊ ማስረጃ ይሻል።
ለጊዜው ግን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና የነፈገው "በ፬ ብፁዓን አባቶች" በወሊሶ ዛሬ በማለዳ እየተፈጸመ ያለው የ፳፭ መነኮሳት "ሲመተ ጵጵስና” ነው።

* በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የምስካየ ኅዙናን መድኃኒአለም ገዳም የበላይ አማካኝነት 25 ኤጲስ ቆጶሳትን እየሾሙ እንደሚገኝ መረጃዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ !!!
@EotcLibilery
@EotcLibilery
@EotcLibilery
2024/09/25 16:33:43
Back to Top
HTML Embed Code: