Telegram Web Link
iPhone ባይኖርህ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

  "መልክ ይስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ" ትላለች እናቴ።

"Snapchat ይኑር እንጂ ሙያ ከጎረቤት እማራለሁ" ዘመን ላይ ሳንደርስ በፊት።ዕድሜ ለካሜራ ጥራትና ለSnapchat እኔና መሰል መልከጥፉአውያን መልክን ትተን ስለሙያ መጨነቅ ከጀመርን ቆየን!በቀደም አንዷ የሰፈሬ ልጅ ቴሌግራሟ ላይ የለጠፈችውን ፎቶዋን አይቼ ጉድ ብዬ አልበቃኝ አለ!ሳውቃትኮ ትል ያላመጠው ቲማቲም ነው ምትመስለው!እንዲያውም የአፍንጫዋን ትልቅነት በተመለከተ እናቷ ወ/ሮ አበሩ ሲቀልዱባት

  "ዝንጀር እስቲ ወጡን አሽትችና ጨውን ንገሪኝ" ይሏታል።ሰፈር ውስጥ ሁሉም "ዝንጀር" ነው የሚላት...ዕውነተኛ ስሟ "ጤና"እስኪረሳ ድረስ!ታዲያ ዝንጀር ዩኒቨርስቲ ስትገባ አጎቷ ከካናዳ IPhone ላከላት።በሄደች በሳምንቷ "ለእታባ አሳይልኝ"ብላ ጊቢ የተነሳቻቸውን ፎቶዎቿን በቴሌግራም ላከችልኝ።

  ወ/ሮ አበሩ ስልኬን እያገላበጡ ፎቶውን አዩትና

  "ሚጡ...የዝንጀርን ፎቶ አምጭው እንጅ"
  "ይኸው ዝንጀር ናትኮ"
   "ክይ!ቅማላም!...መሀይም ነኝ እንጅ መቀለጃ ነኝ?"
   "ኧረ ማርያምን አበርዬ!ይኸ ባለፈው የገዙላት ቲሸርት አይደል እንዴ?"
   "የት ገብቶ ነው ያ ለምቦጭ?ያ ሁላ ቡግር ምን ዋጠው?"
   "አገሩ ተመችቷት ይሆናላ"
   "በሳምንት?እኔ መልኳ መለስ ቢል ብየ በየሳምንቱ የቅቤ ስቀፈቅፍ ኖሬ እዛ ኸዳ በሳምንት ይኸን ያህል ወዝ?ይች በልቶ ካጅ!""

ዝንጀር ለእረፍት ስትመጣ በስልኳ የተወሰኑ ፎቶዎች አስቀረሁና ፌስቡኬ ላይ ለጠፍኩ።ከዚህ ቀደም ለፎቶዎቼ የተሰጡኝን አስተያየቶች መለስ ብዬ ቃኘሁ።

  ጥሎብኝ አንድ መፅሀፍ ባነበብኩ ቁጥር ከመፅሃፉ ጋር ፎቶ ተነስቶ የመለጠፍ ልምድ አለኝ።''የኢትዮጵያ ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢህአዴግ"ከሚለው መፅሐፍ ጋር ፀጉሬን አጎፍሬ ለተነሳሁት ፎቶ አንዱ ተንከሲስ እንዲህ የሚል አስተያየት አስቀምጦልኛል።

  "የ77ቱ ድርቅ መልክ ቢኖረው አንቺን ይመስላል።ዘቅዝቄ እንደ መጥረጊያ ብጠቀምሽ ጉራንጉሩ ሁላ አይቀርሽም ስታፀጅው።"

ዝቅ ብሎ ደግሞ ሌላኛው

   "አንቀፅ 39 ፊት!ፊትሽ የመገንጠል ስሜቴን ቀሰቀሰው!ከኢትዮጵያ ውጣ ውጣ የሚለኝ መጣ!" ብሎኛል።ወረድ ስል ደግሞ

  "ፀሀዩ ከሮ ጥላ ተወዶ ፊት!ፊትሽ ህልም ይመስላል...አይቼው ልጮህም አማረኝ ልሮጥም አማረኝ ግን አልቻልኩም...ፍቺና ወይ አስፈቺና ገላግይን አቦ!" ሌላው ደግሞ

"ይኸን ግንባር ይዘሽ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብትሄጂ የራስሽ ክልል ይኖርሽ ነበር!"

  ከኔ ፎቶ በላይ 'ኮመንቶቹ' ናቸው ላይክ ያገኙት።በዝንጀር iPhone ታሪክ ሳይቀየር በፊት...ከአሁኖቹ "ኮመንቶች" በጥቂቱ

   "ፍንጭትሽ ደስ ስትል...ካንቺ ፍንጭት ከኔ ዲምፕል 'ሼር' አርገን ለምን አንዲት ቆንጅዬ ልጅ አንወልድም?"

  "ዓይኖችሽ  አንድነት ፓርክን ያክላሉ።ፍቀጂልኝና ሰልፊ ልነሳባቸው"
   
  

ወይ iPhone ወይ iPhone ያለው ጓደኛ ይኑርህ!

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(
@gize_yayeh)

15/09/2015 ዓ.ም.


@wegoch
@wegoch
@paappii
ከቤት ስወጣ የሚያጋጥመኝ ሶስት አይነት ሰው ነው። ሙሉ በሙሉ የነቃ (ሞቲቬሽናል ስፒች ሚሰማ መሰለኝ) ሙሉ በሙሉ ያልነቃ (ከምኔው ታክሲ ውስጠሰ ገብቼ ያቋረጥኩትን እንቅልፍ በቀጠልኩ የሚል) እና በከፊል የነቃ ሰው ይገኙበታል። በከፊል የነቃውን ኢዜማ ልትሉት ትችላላችሁ🙂

ቅም አያቴ እስልምናን ከመቀበሉ በፊት መዳፍ ያነብ ነበር የሚል ታሪክ ሰምቻለሁ። እኔም የርሱ የልጅ ልጅ ልጅ ልጅ የሰው ፊት ማንበብ ቀኔን እጀምራለሁ።

ለታክሲ ከተሰለፉት ቁርሱን ቂንጬ የበላ ፣ ያደረ ሽሮ የበላና አሳር የበላን አብጠርጥሬ የመለየት ልዩ ተስጥኦ አለኝ። ከቤታቸው ፓንኬክ በልተው ሚወጡ ይኖሩ ይሆናል። የታክሲ ሰልፍ ላይ ግን አጋጥመውኝ አያውቁም።
ለአንድ ብጣሽ ቁርስ ወተት እንቁላል ዱቄት የሚያባክን ሰው ወይ መኪና አለው ወይ በራይድ ነው ሚንቀሳቀሰው። ድንገት ታክሲ ከተሰለፈ ይህንን ፅሁፍ እየፃፈ ነው😀

ጥሩ ቁርስ የጥሩ ቀን ማስጀመርያ ነው ይላል ኒቼ🙂 ኒቼ እንዲህ ያለ ነገር ይበል አይበል አላውቅም። ዮናስ ዘውዴ ይህንን ፖስት ካየው ግን ቀጣይ ብሔራዊ ቴአትር የሚዘጋጅ መድረክ ላይ ኒቼ እንዳለው ብሎ እንደሚጠቅሰው እርግጠኛ ነኝ🙂

ሰው የሆዱን በዝምታ ቢሸሽግ ግንባሩን ግን በፍፁም መሸሸግ አይቻለውም። ለሊቱን አለሙን ሲቀጭ ያደረና በትራስ እጦት አንገቱ የተቀጨ መለየት ለኔ በጣም ቀላል ነው።
አንዲት ቆንጆ በአጠገባችን ስታልፍ ዞሮ ካላየ ወይ ባለቤቱ አጠገቡ አለች ወይም አንገቱ ተቀጭቷል። አለዚያ ሌላ ነገር እንድንጠረጥር እንገደዳለን።

መጠርጠር ስል ሰሞኑን ሀገር እንደሚበጠብጡ የተጠረጠሩ ሰዎች እየታሰሩ ነው ተብሏል። አሁንም ግን የዘራ በረሮ ሚሸጡ ሰዎችና ጌታ መጣልህ እያሉ ሚያስደነግጡን ሰዎች ከተማው ላይ በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ነው።ከቴም ሰላም ማስከበር¡

ትላንት ስራ ውዬ በድካም ተርከም ተርከም እያልኩ አስፋልት ስሻገር በግብዳ ስፒከር "ጌታ እየመጣ ነው" ብሎ አንባረቁብኝ። በድንጋጤ መኪና ውስጥ ተወርውሬ ነበር። ጌታ ሳይመጣ እኔ ወደርሱ ሄጄ ነበር😑

የሆነው ሆኖ "ቡና ጠጥቶ ከቤት መውጣት የብልሆች መገለጫ ነው ይላል ኒቼ"🙂

@wegoch
@wegoch
@paappii

By #Muaz jemal
Forwarded from ግጥም ብቻ 📘 (Leul M.)
ሥዕል ለማሳል በ+251984740577
ወይም @gebriel_19 ላይ  ፎቶ  በመላክ በ ተመጣጣኝ ዋጋ  ማዘዝ ይችላሉ!


@seiloch
@seiloch
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°
   ዘርሽ ቢቆጠር ጉድፍ የለበትም።የጀግና ዘር ነሽ!በአባትሽ በኩል ቢኬድ ቅድመ አያትሽ የሚኒሊክ ዘብ ጠባቂ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ።በእናትሽም በኩል ቢኬድ ምንጅላትሽ የሽምብራ ቆሬ ጦርነት ላይ የግራኝ አህመድን አሽከር በቀይ ጥይት ግራ ቂጡን ነድለውት ሲቅመደመድ ኖሮ መሞቱን አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሆነ ጊዜ ላይ አስነብቧል።

  በማን እንደወጣሽ ባይታወቅም፣ዕድልሽ ይሁን ተፈጥሮሽ ግልጽ ባይሆንም፣ከአንድ ወንድ አትረጊም።ተረግመሽ ነው መሰል ከሚያጋጥሙሽ ወንዶች 25 % የሚሆኑት የጥሪ ማሳመሪያ ተጠቃሚዎች ናቸው። ልክ ስትደውይ
  "ወይ ሞልቶ ላይሞላ
   ለዚች ዓለም ኑሮ
   እኔ አልጨነቅም
   ከዛሬ ጀምሮ" የሚል መፈክር ይሁን ዘፈን ያልለየለት ብሶት ትሰሚያለሽ።(ሳትረገሚማ አትቀሪም!) ሌሎቹ 25 % የሚሆኑት ደግሞ የትንሽ ጣታቸውን ጥፍር የሚያሳድጉ ናቸው።ደህና መትረየስ እንዳነገበ ጀግና በጥፍራቸው አይን አ*ቸውን እየመነገሉ፣የከናፍራቸው ጫፍ ላይ የወጣችን ቡግር እየፈነቀሉ ቀንሽን ለሰማይ ለምድር የከበደ 'ትራጀዲ'ያደርጉብሻል።(በእርግጠኝነት ምንጅላትሽ የመቱት አሽከር ነው የረገመሽ!)

'እፎፎፎይ'ብለሽ ወደ ሌላኛው 25% ስትሮጪ መፈናፈኛ እስኪያጣ ሱሪውን የሚያስጠብብ፣ቀሪው 25% ደግሞ የሞተ ፍየል በብብቱ የያዘ እስኪመስል ድረስ አስጨናቂ ጠረን ያለው፣ላቡ ከብብቱ ስር እንደቀበና የሚወርድ ክልል-ዘለል የሆነ ፌደራላዊ ግማት ላይ ትወድቂያለሽ ።

"እና እንዴት ነው ኑሮው?"ይልሻል አፉ እንደተቀየደ ፈረስ ድዱን እያሰጣ።

  "ደህና ነው መቸም" ትያለሽ ሰው ያገኘሽ መስሎሽ።

"እናስ ተማሪ ነሽ ሰራተኛ?"ይልሻል  እንዳገጠጠ አንዴ ከላይ ወደታች፣አንዴ ደግሞ ከታች ወደ ላይ scan እያደረገሽ።

  አንድ ቀን አልፎልሽ በፀሃፊነት ወደምትሰሪበት ድርጅት ለጉዳይ የመጣ ነጋዴ ነኝ ባይ ትተዋወቂያለሽ...ቀጠሮ ትይዣለሽ።ደሞዝሽ በፈቀደው መጠን ለመዘነጥ ትሞክሪያለሽ።ከታች እናትሽ መሰረተ-ትምህርት ሲማሩ ለብሰውት ይሄዱ የነበረውን ቀሚስ ከወገቡ አስቆርጠሽ በሰውነትሽ ልክ አሰፍተሽ ለብሰሻል።ከላይ ከሰልቫጅ ተራ በ80 ብር የገዛሻትን ቲሸርት ጣል አድርገሻል።ባለፈው ወር እቁብ ሲደርስሽ የገዛሻትን የ 200 ብር ሽቶ "ምናባቱ!ሺህ ዓመት አይኖር!"ብለሽ የግራ ብብትሽ ስር አንዴ ረጭተሻታል። የቀኙንም'ኮ ልትረጭው ነበር ግን አሰብ አረግሽና "መቸስ ከጎኑ ስሄድ አንድ ጎኔ ነው በሱ በኩል የሚሆን"ብለሽ ተውሽው።ኤታባቱ!ሺህ ዓመት አይኖር!

  ፀጉርሽን በ 50 ብር ካስክ አፍሪካዊ ለዛውን ታሳጭዋለሽ።ተመስገን ነው!ሰሞኑን ማበጠሪያ አይሰበርብሽም!በፈቃደኝነት የሚያፈናቅል ሽታ ያለውን ሎሽንሽን መላ ሰውነትሽን ተቀብተሻል...ለእግርሽ ግጣም ከቆራሌው የተረፈች አንዲት ክፍት ጫማሽን ግጥም ታደርጊና ትሄጃለሽ !ወደ 'ዴትሽ'

ሰውዬሽም ከሞላ ጎደል ዘንጧል።

  "ምን ይምጣ የሚበላ?"
  "አንተ የተመቸህ ይሁን"
ጥብስ ይታዘዝና ጠበሳው ይቀጥላል ። ጥብሱ እስኪደርስ...

"እና...ደሞዜ 3000 ብር ነው አልሺኝ?"
"3200"
"ያው ነው...አሁን እኔ ወደዚህ ስመጣ የኮንትራት ታክሲ 200 ብር ነው የከፈልኩት" ብሎ ኩም ያረግሻል።ጥብሱ ደርሶ ከተበላ በሁዋላ
  "እና የቤት ኪራይ 600 ብር ነው የምከፍለው አልሽኝ?"
  "550"
  "ያው ነው 50 ብር ማለትኮ ለአስተናጋጅ የሚሰጥ 'ቲፕ' ነው"
  "እሱሰ ልክ ነህ"ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ
"ተጫወች እንጂ ምነው?እኔ ዝም የሚል ሰው አልወድም...የምሬን ነው!የሚያስጨንቅሽ ነገር ካለ ንገሪኝ"
"ኧረ የለም!አመሰግናለሁ"
  "ምስጋና ስንቅ አይሆንም ...ባይሆን..."
  "ባይሆን ምን?"
  "ባይሆን ሌላ ጊዜ በደንብ ታጫውችኛለሽ እ?ሃሃሃሃሃ"
በኮንትሮባንድ የገባ ሳቅ ይለቅብሻል።
"እንሂድ እየመሸ ነው"ትያለሽ ሰዓትሽን አየት ታደርጊና።
"ኧረ ገና ምኑን ያዝነውና!አይዞሽ እኔ ራሴ ነኝ በኮንትራት ታክሲ ቤትሽ የማደርስሽ"ብሎ ሳይሰማሽ መጠጥ ያዛል ።'አልኮል አልጠጣም' ብለሽ ለመገገም ትሞክሪያለሽ።
"ምናይነቷ ናት ባካችሁ?ልንዝናና አይደል ወይ የመጣነው?እንደ ህፃን ፋንታ ልትጠጪ ነው?"ብሎ እንደምንም ቀበጣጥሮ አንድ ቢራ ያስከፍትልሻል።እየተሽኮረመምሽ መቀማመስ ትጀምሪያለሽ።ሞቅ ሲልሽ ፍርሀት ቢጤ ይሰማሽና

"እየመሸ ነው ብሄድ ሳይሻል አይቀርም"ስትይ ሰዓቱን አየት ያደርግና 
"ሆሆሆሆ እንዴት ያለችው ላይ ጣለኝ ባካችሁ?ገናኮ 3 ሰዓት ነው...ምን የሚያስቸኩል ነገር አለ?ገብተሽ አታበስይ ምናለሽ?"

"እሱስ አላበስልም...አከራዬ ደስ አይላቸውም እንጂ..."
"አአአአይ ...ለዛሬ የኪራይ ቤትሽን እርሻት...እዚሁ ቆንጆ room እይዝልሻለሁ" ሲልሽ መፍራት ትጀምሪያለሽ።

"ኧረረረረ አያስፈልግም ቤት እገባለሁ"ስትይ
"ለማንኛውም እየጠጣሽ "ይልሽና በተቀመጥሽበት ትቶሽ ወደ እንግዳ ተቀባዪአ ይሄዳል።ከቆይታ በሁዋላ አንድ ቁልፍ ይዞ ይመጣል።

"ምን...ባክሽ...' 'ሩሞቹ' ተይዘው አልቀዋል' አለችኝኮ...አይዞሽ double bed ነው የያዝኩት...መቼም የመሸበት አላሳድርም አትይም ሃሃሃሃሃ"
አሁን የምር...የምር...የምር ትፈሪያለሽ።ያቺ ተቆንጥጣ ያደገችዋ...ያቺ በዘመን ግሳንግስ ቀለሟን ያደበዘዝሽው አንቺነትሽ እየተፍገመገመች
"አምልጪ!...ተበላሽ! ትልሻለች።
"አአአአይ....ኧረ አትቸገር እዚሁ አካባቢ አንድ ጓደኛ አለችኝ እሷ ጋር እደውላለሁ..."
"ቆይ አላመንሽኝም ማለት ነው?ስታስቢው በጥብስና በቢራ የሴትን ገላ የምገዛ ርካሽ እመስላለሁ?I really feel sorry እንደዛ ካሰብሽኝ"
"ኧረ...እንደዛ ማለቴኮ አይደለም...አስቸገርኩህ ብዬ ነው እንጂ!እሺ በቃ" ትይውና

"እሳትና ጭድ አንድ ክፍል ውስጥ ያድሩ ዘንድ ደግ አይደለም...አንዳቸው የሌላቸው መጥፊያ ይሆናሉና " የሚለውን ቃል ጥሳችሁ አንድ ጣራ ስር ታድራላችሁ።

ጧት ለሰዓታት የተቃጠልሽበት ፀጉርሽ ፈርሶ...ጋኔል ያደረባት ጃርት መስለሽ ወደሰፈርሽ ትመለሻለሽ።ወደ መዳረሻሽ ገደማ ፋርማሲ ታይና ጎራ ትያለሽ።ሰው የተባለ ፍጡር ገና ከእናታቸው ማህፀን ሳሉ ጀምሮ የማያምኑት አከራይሽን ፋርማሲ ውስጥ ስታያቸው ልብሽ በአፍሽ ልትወጣ ትደርሳለች።በተጠራጣሪ አይኖቻቸው ከእግር እስከራስሽ አብጠርጥረው ያዩሽና
"አንች የኔ ዓለም የት ጠፍተሽ ነው ስታሸብሪን ያመሸሽ?"ይሉሻል።

"እንዴት አደሩ እትዬ?ማታ...ኮ አምሽቼ የምጨርሰው ስራ ኖሮኝ ሰዓት ስለሄደብኝ እንዳልረብሻችሁ ብዬ እዛው አድሬ ነው"

"ኧሯሯሯሯሯ!እና ስልኩ ቢከፈት ምን ይላል አደራሽ?...በዚህ በከፋ ዘመን እንደው ሰውስ ያስባል አይባልም?ጅብ በመውጫው አንችን ፍለጋ እንጉለሌ ልህድ?"

"ይቅርታ በጣም"

"የሆነው ሁኖ...ምን ልትገዥ ነው?"
ብለው እጅ ከፉ እንደተያዘ ሌባ ያፋጥጡሻል።

"እ...እንቅልፉ ነው መሰል ትንሽ ራሴን አሞኛል ማስታገሻ ልግዛ ብዬ"

"እህህህህም ነው?በይ...ደህና ዋይ"ብለውሽ ከፋርማሲው ሲወጡ የዘመናት ሀጥያትሽ የተፋቀልሽ ያህል ይቀልሽና "እፎፎፎፎፎፎይ!"ትያለሽ በሆድሽ።የምትገዥውን ገዝተሽ ስትወጪ አከራይሽ ፋርማሲው በር ላይ ቆመዋል።ስታያቸው ስቅቅ ብለሽ ታልፊያቸዋለሽ።ከማለፍሽ ወደ ፋርማሲው ድጋሚ ሲገቡ ታይና ጠጋ ብለሽ ለማየት ትሞክሪያለሽ።

"የኔ ዓለም...እንደው አሁን የወጣችቱ ልጅ የገዛችው ክኒና የምንድነው?" ይሉታል መድሀኒት ሻጩን።
"ምነው ማዘር ችግር አለ?"
"ኧረ የለም ዓለሜነህ!...አምና ቁርጥማት ያመኝ የነበር ግዜ ይኸን መሳይ ክኒና ነበር እምውጥ እንደው ሲያገረሽብኝ ግዜ ድጋምኛ ልዋጠው ይሆን ብየ ነው ...ሌላም አይደል"

"ኧረ...ተመሳስሎብዎት ነው 'ሚሆን ማዘር ይሄኮ post pill ነው"
"ምን pill?"
"postpill....postpill ማለት..."ብሎ ማብራሪያ ሲጀምርላቸው አንቺ እቃሽን እንዲያሻክፉሽ ወደ ጓደኞችሽ እየደወልሽ ነው።

ማዕዶት ያየህ(ዘማርቆስ)
(@gize_yayeh)
25/09/2015 ዓ.ም.

@wegoch
@wegoch
@paappii
"የሙሉቀን መለሰ ትዝታዎች"
(በዕውቀቱ ሥዩም)

ከብላቴናነቴ ጀምሮ ሙሉቀን መለሰን ስወደው ኑርያለሁ። አስቴር አወቀ፣ ኤፍሬም፣ ሙሉቀን እና አበበ ተካ በዜማ ባያጣፍጡት ኖሮ የጉብዝና ወራቴ ምንኛ እጅ እጅ ይል ነበር...!
"ስለምትመኘው ነገር ተጠንቀቅ አንድ ቀን ልታገኘው ትችላለህና" ይላል ጠቢብ...!
ታድያ አንድ ቀን ራሴን ሙሉቀን መለሰ ቤት አገኘሁት። በርግጥ ያገኘሁት በልጅነቴ የማልመውን ሙሉቀንን አልነበረም፤ ሙሉቀን የወጣትነት ሥራውን ሲኮንን ነበር የደረስኩበት። "የዘፈን ምንጭ ሰይጣን ነው" ይላል፡፡(ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ባህል ሚኒስትር ሰይጣን ላገራችን ኪነጥበብ ያደረገውን አስተዋጽኦ አስታውሶ ቢሸልመው ደስ ይለኛል...ሰይጣን አይሸለምም ያለው ማነው?)🙄
ሙሌ የተራኪነት ተሰጥኦ አለው፡፡ ስለአማርኛ ዘፈን ታሪክ ሲነሣ ጠንከር ያለ ትንታኔ ያቀርባል፣ ለጊዜውም ቢሆን ዘፈን የሰይጣን መሆኑን ይረሳና በግሉ ስላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይተርካል።
በርግጥ የታዋቂ ዘፋኞችን ችሎታ ያጣጥላል። አንዱን ስሙን የማልጠቀሰውን ዘፋኝ ሣነሳበት...
“እሱ እንዲያውም መዝፈን አይደለም ዘፈን እንዲያዳምጥ እንኳ ሊፈቀድለት አይገባም” አለኝ🤭 በተለይ ጥላሁን ገሠሠን ተችቶ አያባራም...
”እሱ እኮ የጉልበት ዘፋኝ ነው” ይለዋል።
ነገሩን ማስ ማስ ሳደርገው ከጥላሁን ገሠሠ ጋር ያለው
ግኑኝነት የፉክክር ብጤ ይመስላል። አልፈርድበት
“ሁለት አንበሶች ባንድ ዋሻ ውስጥ አይኖሩም ” ይላል ጎርኪ። በቅርቡ ሙሌ፤ “ናፍቆት ኢትዮጵያ” ከተባለ መጽሄት ጋር ዘለግ ያለ ቃለ-መጠይቅ አድርጓል።
ከምልልሱ ውስጥ ይቺን በፈገግታ ቀንጭቤ ልሰናበት...
ናፍቆት:- ለመሆኑ እስከ ስንተኛ ክፍል ተምረሃል?
ሙሉቀን፡- ረሳሁት እስከ ሦስተኛ ክፍል የተማርኩ ይመስለኛል።
ናፍቆት፡- ድምፃዊው ጥላሁን ገሠሠ በሁለት ክፍል ይበልጥሃላ!
ሙሉቀን፡- እሱ እዚያ ደርሷል እንዴ?
ናፍቆት:– አዎ፣ የምናውቀው እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ መማሩን ነው ….
ሙሉቀን፡- እንዲያውም አሁን ትዝ አለኝ አምስተኛ ክፍል ድረስ ነው የተማርኩት...🤭🤣🤣

(ቀንጭቤው ነው እንጂ ረጅም ነበር)

@wegoch
@wegoch
@paappii
ድሮ ድሮ ብሶት በወለደው በዘመነ ኢህአዴግ

¤¤¤¤

ድሮ ድሮ ከአድማስ ዩኒቨርሲቲ በዲፕሎማ ለተመረቀ ልጃቸው በሬ አርደው የሚደግሱ ቤተሰቦች ነበሩ

¤

ድሮ ድሮ ኑሮ ጥሩ ስለነበረ ህዝቡ ደረጄና ሀብቴ "ሙያሽ ይዘርዘርልሽ" እያሉ ሲዘፍኑ ሆዱን ይዞ ይስቅ ነበር

¤

ድሮ ድሮ ወደደብረ ማርቆስ የሚጓዝ አውቶቡስ ውስጥ የታደለ ገመቹን የነቀምት አውቶቡስ ውስጥ የሰማኸኝ በለውን ዘፈን መስማት ኖርማል ነበር

¤

ድሮ ድሮ ታመን ጤና ጣቢያ ስንሄድ ከመድኃኒቱ በፊት ወተትና ስጋ መመገብ እንዳትረሱ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠን ነበር

¤

ድሮ ድሮ አንድ ሱፍ ለመስፋት 30 ሜትር ጨርቅ እንጠቀም ነበር

¤

ድሮ ድሮ አዜብ መስፍን የተባሉ የቤት እመቤት ባለቤታቸው በሚከፈላቸው 7500 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ድልቅቅ ብለው እንደሚኖሩ ከታይላንድ ጉብኛታቸው በዃላ ነግረውናል

¤

ድሮ ድሮ የመንግስት ሰራተኛው በወርሃዊ ቁጠባ ኮንዶሚኒየም ይደርሰው ነበር

¤

ድሮ ድሮ አርከበ እቁባይ የተባለ የብዙ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ህይወት የቀየረ ከንቲባ ነበረ

¤

ድሮ ድሮ አበበ ተካ የሚባል ዘፋኝ የሆነች ቀሽት ዲያስፖራ አፍቀሮ "አለቅሳለሁ" የሚል ዘፈን አውጥቶ ሲያለቃቅስ ህዝቡ በጣም ስለተሰማው ገንዘብ ተሰብስቦ በአላሙዲን ድጋፍ አሜሪካ ሄዶ ልጅቷን እንዲያገኛት ተደርጓል

¤

ድሮ ድሮ ኃይሌ ገብረስላሴ 5 ኪሜ ውድድር ሲያሸንፍ ህዝቡ ከኮተቤ ፒያሳ ድረስ 10 ኪሜ እየሮጠ ደስታውን ይገልፅ ነበር

¤

ድሮ ድሮ ሰው ቤት ገብቶ መዘፍዘፊያ የሰረቀ ሌባ ፖሊስና ህብረተሰብ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ ይወገዝ ነበር

¤

ድሮ ድሮ ከሰል ለማያያዝ አንድ ሌትር ጋዝ የሚጠቀሙ እናቶች ነበሩ

¤

ድሮ ድሮ ሀገሪቱ ውስጥ ከነበረው ህዝብ መካከል ስጋ በደንብ አያገኝም ተብሎ በፍለጋ የተገኘ አንድ አዛውንት አለቤ ሾው ላይ ቀርቦ ለ3 ዓመት ስጋ በነፃ እንዲወስድ ስሙን የረሳሁት ስጋ ቤት ቃል ገብቶላቸው ነበረ

¤

ድሮ ድሮ ተኽላይ ደምቢዶሎ ውስጥ አራርሳ ባህርዳር ላይ ሆቴል ነበራቸው

¤

ድሮ ድሮ ባለስልጣናትና አርቲስቶች የእግር ኳስ ግጥሚያ በህዝብ ፊት ያካሂዱ ነበር

¤

ድሮ ድሮ "ምግብማ ሞልቷል አምላክ መች ነሳኝ" የሚል ዘፈን ነበር

¤

ድሮ ድሮ ምግብ በተትረፈረፈበት ዘመን ከመመገባችን በፊት እጃችንን መታጠብ አንርሳ የሚል ተደጋጋሚ ማስታወቂያ ነበረ

¤

ድሮ ድሮ የ4ኛ ክፍል መምህር ካዛንቺስ ተከራይቶ ይኖር ነበር

¤

ድሮ ድሮ ማር ሲበዛ ይመራል የሚሉ ማር ያላቸው ወላጆች ነበሩን

¤

ድሮ ድሮ የቀበሌያችን ሊቀመንበር ልጆች አብረውን ደጃዝማች ወንድይራድ ት/ቤት ይማሩ ነበር

¤

ድሮ ድሮ መክሰስ የሚባል 10 ሰዓት ላይ የሚበላ ምግብ ነበረ

@wegoch
@wegoch
@paappii

By yihune ephrem
Audio
ፀሀፊና አንባቢ : ማዕዶት ያየህ (ዘማርቆስ)
@gize_yayeh

@wegoch
@wegoch
@wegoch
አነቃቂው መድረኩ ላይ እየተንጎራደደ "በህይወቴ ምርጡ ጊዜ ሚስቴ ያልሆነች ሴት እቅፍ ውስጥ ያሳለፍኩት ጊዜ ነው!" ሲል ተነገረ።

ለመነቃቃት አዳራሹ ውስጥ የተሰበሰበው ሰው በድንጋጤ ክውታ ተዋጠ።

አነቃቂው ንግግሩን በመቀጠል "እናም ያቺ ምርጥ ሴት፣ ዘጠኝ ወር በሆዷ፣ ከእዛም በጀርባዋ፣ ከእዛም በእቅፏ ያሞላቀቀችኝ ምርጥ ሴት፣ ያቺ ስጦታ ሳልሰጣት ያቀፈችኝ ምርጥ ሴት እናቴ ናት?!" ሲል ተናገረ።

አዳራሹ በሳቅ እና በጭብጨባ ተሞላ።

**
ከሳምንት በኋላ በእዚህ የአነቃቂ ንግግር ላይ የተገኘ ሥራ አስኪያጅ ድግስ ብጤ አዘጋጅቶ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ ቤቱ ጠራ። ዝግጅቱ ላይ ወዲህ ወዲያ እያለ ሰው ሲያስተናግድ፣ ሲጎርስ ከመጠጡ ሲጎነጭ ሞቅ ከማለት አልፎ ሰከረ።

ይሄኔ ነው እንግዳው ምግብ በልቶ፣ ጠጥቶ ሳይዝናና መሄድ የለበትም ሲል በአነቃቂ ንግግር ስልጠና ላይ ተገኝቶ የሰማውን ቀልድ ለታዳሚው ለመጋበዝ በመወሰን ድምጹን ጠራርጎ ንግግር የጀመረው።

"በህይወቴ ምርጡ ጊዜ፣ ሚስቴ ያልሆነች ሴት እቅፍ ውስጥ ያሳለፍኩት ጊዜ ነው!" ሲል ተነገረ።

ይሄኔ የሚስቱ ፊት፣ እንደመቅላት፣ አመድ እንደ መንዛት፣ አሸቦ እንደመምሰል ከእዛም ወደ ጥቀርሻነት ተለወጠ። ንግግሩን የሰማው የድግሱ ታዳሚ በድንጋጤ የጨው አምድ መሰለ።

ይሄኔ ባልየው በአነቃቂ ንግግሩ ወቅት የተነገረው የቀልዱ ሁለተኛ ክፍል ምን እንደሆነ ስለዘነጋ ለማስታወስ ለሀያ ሰከንዶች ያህል በዝምታ ከቆየ በኋላ ትዝ ሊለው ስላልቻለ ጎሮሮውን ጠራርጎ...

"...እናም ያቺ ሴት ማን እንደሆነች አላስታውስም!" ሲል ንግግሩን ደመደመ።
**
ማስታወሻ፣

ሰውየው ንግግሩን እንደጨረሰ ከሚስቱ በተሰነዘረበት የውስኪ ጠርሙስ ፍንከታ ምክንያት ኮማ ውስጥ ስለገባ አሁን ላይ ሆስፒታል ተኝቶ እስኪነቃ እየታከመ ይገኛል።

@wegoch
@wegoch
@paappii

By #Tilahun ango Girma
ኩርፊያህን ለምን እንደምናፍቀው ይገባህ ይሁን…… የምልህ አለአይደል ስትነጫነጭ ጊዜ …… ወይ ስትቆጣ ንዴትህን ግልፅ ስታደርግልኝ…… ትኩረቴን ፈልገህ ልክ እንደህፃን ሲያደርግህ በሆነው ባልሆነው ስታኮርፍ ኩርፊያህ ታስፈልጊኛለሽ የሚል መልዕክት ያለው ይመስለኛል እንክብካቤ ፈልገህ ትኩረቴን ሽተህ ይመስለኛል …… ሰዎች ፊት የነበረህን ኩራት አሽቀንጥረህ እኔ ዘንድ ብሶትህን ስትነፋረቅ…… ከጉያዬ ሽሽግ ስትል ፀጉርህን በጣቶቼ ዳበሳ ስበታትናቸው ጭንቀትህም አብሮ ቢበተን ……ትኩስ እንባህን በፈገግታዬ ባብስልህ…… እኚህን ሁሉ ሁነቶች እወዳቸዋለሁና ኩራትህን አሽቀንጥረህ መሸሸግን ፈልገህ ናልኝ…… በዚህች በጠበበችህ አለም ሳይታክትህ ትሸጎጥበት ዘንዳ እቅፌ ላንተ ሰፊ ነውና መሰልቸትን እኔ ጋር አታስበው…… የነፍስህ ጭንቀት ሲራገፍ የስስት አይኖችህ በፈገግታ ሲያበሩ እኔነቴን አንተው ውስጥ አየዋለሁ እናም አለም ሁሉ ብትጠብህ እቅፌ ላንተ ሰፊ ነው

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Fereha nuraddis
✍️ ሀገር ሰላም ብዬ የተቀመጥኩበት ታክሲ ውስጥ ጎኔ ያለችው ልጅ በሹክሹክታ ድምጽ ምን አለችኝ አባቱ ትወርድልኛለህ? ደሞ የአይኖቿ መስለምለምስ ትውልዱ አይን አውጥቷል ስትሉኝ አለማመኔ my dirty mind😏

✍️ባለፈው አዳነች አቤቤ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሀይል ለመናድ ከአንድ ክልል ብቻ የሚደረግ ከፍተኛ ፍልሰት አለ ስትል ዲቻ ምንም እንዳልመሰለው ሳስብ ብቻዬን ሳቄ ያመልጠኛል ጦሶ🤦‍♂️

✍️ትናንት ምሳ የበላሁበት ስጋ ቤት ቆራጩ" የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ" እያለ እየዘፈነ ነፍ ስጋ የሰጠኝ በደህና ነው ትላላችሁ😳 አሁን በጠዋት ችክክም ችክክም ችከክም በል በል እያለኝ እኮ ነው 🐎

✍️አርባ አመት ሙሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ለመሆን የታገለው ቀጨላ መርዳሳ የኦነግን የምስረታ በአል አብሮ ያከብራል ማለት ነው🤷‍♂️

✍️ በየ ለቅሶ ቤቱ ግን ከቀብር በኋላ የሚዘጋጅ የምሳ ግብአት ቀይ ምስር እና አልጫ አተር እንዲሆን ያወጁት ቀደምት እናቶች በማ ዘመነ መንግስት እንደነበሩ ዶክተር ሮዳስ ሲያብራራ ሰምቼው አላውቅም ወይስ አምልጦኝ ነው🤪

✍️ከአባታቸው ባገኙት አስር ሚሊየን ብር እና አምስት ተሽርካሪ ደሞ የሆነ የሆነ ሱቅ ተነስተው የሀብት ማማ ላይ የተቀመጡ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብለው ንግግር የሚጀምሩ  ቱጃሮች በወንጀል እንዲከሰሱልን ስል በትህትና አመለክታለሁ📯

✍️በቀደም እለት ዶፍ ዝናብ እየዘነበ ጣራችንን እንደ አታሞ ሲደልቅ ከዛ የዝናብ ኳኳታ ጋር በሚታገል ጮክ ባለ ድምጽ እናቴ
"እስቲ አንድ ልጅ ወልደህ አምጣልኝ" ብላ ያሳቀቺኝ ሳቅ አመቱን ሙሉ ከሳቅኩት ይበልጣል😂😂😂 እኔ እኮ እድሜዬን መቁጠር የረሳች መስሎኛል ለካ እስከዛሬ እየቆጠረች ነው Shame on you Mom እኔ ላንቺ ጊዜ ምን ብዬሽ አውቃለሁ🙄

✍️ያቺ በጣም ቆንጆ ሂጃቢ ያስሚን ወንድ አትጨብጥም 2 አመት እኮ አንድ መስሪያ ቤት አብረን ሰርተናል ሁሌም ስንገናኝ በርቀት እንደታቦት ብቻ ጎንበስ ቀና ብዬ ተሳልሜ ነበር ሰላም የምላት ምናል አንድ ቀን ከሀር የሚለዝብ የሚመስለኝ ለስላሷ እጇን ብታስነካኝ መዳፌ ላይ ያረፈ ጠረኗን ከሷ ተደብቄ አንድ ቀን ባሸተው ምነበረ😍😍😍

✍️በቀደም መንገድ ላይ እየሄድኩ በሀሳብ ጭልጥ ከማለቴ የተነሳ የማስበው ጠፍቶኝ ወደራሴ ስመለስ 801, 802, 803, 804 እያልኩ አገኘሁት ራሴን ምን ለምን እየቆጠርኩ እንደነበረ ግን ስካሁን ትዝ አላለኝም። እየጨለልኩ ነው እንዴ🧐

ከላይ ያልኩት ሁሉ አይረባም አውቃለሁ
አንዳንዴ እንዲ ነኝ
ወፈፍ ያደርገኛል እዘባርቃለሁ

By Binyam behaylu

@wegoch
@wegoch
@paappii
ውድ አልማዞች!
•••••••
የግመል ነጋዴው በገበያው ለሽያጭ ከቀረቡት ግመሎች መካከል በአንዱ እጅግ ስለተሳበ ከሻጩ ጋር ድርድር ጀመረ። በገዢና በሻጭ መካከል ብዙ ደቂቃዎችን የፈጀ የቀንስልኝ፣ አልቀንስም ክርክር ከተደረገ በኋላ ገዢው በዋጋ ተስማምቶ ግመሉን ገዝቶ ወደ ቤቱ ሄደ።

የግመል ነጋዴው ቤቱ እንደደረሰ አገልጋዩን ጠርቶ የግመሉን ኮርቻ እንዲያወርድ ይነግረዋል። አገልጋዩ የግመሉን ኮርቻ ሲፈታ ከኮርቻው ስር አነስተኛ መጠን ያላት የተቋጠረች ከረጢት ያገኛል። ከረጢቷን ሲፈታ በውድ የአልማዝ ማእድን ተሞልታለች።

አገልጋዩም "አለቃ የገዟት ግመል በነጻ ጭና ያመጣችውን በረከት ይመልከቱ!" ሲል በደስታ ተሞልቶ ጮኸ። ነጋዴውም በአገልጋዩ መዳፍ ላይ በጸሐይ ብርሀን የሚንቦጎቦጉ የአልማዝ እንክብሎች ሲመለከት እጅግ ተደነቀ።

ይሁንና "ግመሏን እንጂ አልማዞቹን አልገዛኋቸውም። አሁኑኑ ለባለቤቱ መመለስ አለብኝ" አለ - ነጋዴው።

አገልጋዩም "ምን የማይረባ አለቃ ነው ያለኝ?!" ሲል በሆዱ ካወራ በኋላ "ማንም ሰው የአልማዞቹን ትክክለኛ ባለቤት ሊያውቅ አይችልም! ሲል ተናገረ።

ይሁንና ነጋዴው ምክሩን ችላ ብሎ ጊዜ ሳይወስድ ባለቤቱን ፍለጋ ወደ ገበያው ተመለሰ። ብዙም ሳይለፋ የተቀሩ ግመሎችን ለመሸጥ ገዢ ሲጠብቅ የነበረውን የግመል ሻጭ አግኝቶ ትንሿን ከረጢት መለሰለት።

የግመል ሻጩም እጅግ ተደስቶ " እጅግ የከበሩ ማእድናቴን በኮርቻው ስር መደበቄን ዘንግቼ ነበር። አሁን ሽልማት እንዲሆንህ በከረጢቱ ውስጥ ካሉት አልማዞች ውስጥ ለዐይንህ ደስ ያሰኘህን ውሰድ!' አለ።

"ለከፈልኩት ገንዘብ ጥሩ ግመል ሽጠህልኛል። ተጨማሪ ሽልማትም ስጦታም አልቀበልም።" አለ - ነጋዴው። ነጋዴው ስጦታውን አልቀበልም ቢልም ግመል ሻጩ እንዲቀበለው ይወተውተው ጀመር።

በመጨረሻም ነጋዴው በፈገግታ ተሞልቶ "ከረጢቱን ልመልስልህ ስወስን ሁለት እጅግ የከበሩ አልማዞችን እራሴ ዘንድ አስቀርቻለሁ! ከእነርሱ የሚልቅ ሽልማት የለም!" አለው።

የግመል ሻጩ የነጋዴው የእምነት ቃል ሲሰማ እጅግ ተበሳጭቶ በከረጢቱ ውስጥ ያሉትን ውድ አልማዞች የጨርቅ እራፊ ላይ ደፍቶ ይቆጥራቸው ጀመረ። ይሁንና ቆጠራውን እንደጨረሰ በእፎይታ ተሞልቶ "በከረጢቱ ውስጥ ከነበሩት አልማዞቼ መካከል አንድም አልጎደለም። የትኞቹን ውድ አልማዞች ነው ለራሴ አስቀርቻለሁ ያልከኝ?"

ነጋዴውም በኩራት ተሞልቶ "እኔ ዘንድ ያስቀረኋቸው ውድ አልማዞች ታማኝነቴና ለእራሴ ያለኝ ክብር ናቸው!" ሲል መለሰለት።

ሻጩ የሰማውን ነገር ባለማመን ዐይኖቹን አፍጥጦ ነጋዴውን ከመመልከት ውጪ መልስ ሊሰጠው አልቻለም።

**
ሁላችንም ወደ እራሳችን መመልከትና እነዚያ ውድ አልማዞች እንዳሉን እንፈትሽ። ሁለቱ ውድ አልማዞች ያለው ማንኛውም ሰው የዓለማችን ባለጸጋው ሰው ነው።

@wegoch
@wegoch
@paappii
በአንድ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ሲሰሩ ነበር የተዋወቁት ፡ እና ተቀራረቡና ፡ አንድ ቀን እራት ልጋብዝሽ አላት ።

ጥሩ ቦታ ወሰዳት ፡ አሪፍ እራት በሉ ፡ እና ወደቤት ሊሄዱ ተነሱ ፡ ዴንዝል ዋሽንግተን የተጠቀሙበትን ሂሳብ ከፈለና ፡ ኪሱ ውስጥ የቀረውን ገንዘብ ሲያይ ደነገጠ ። በወቅቱ ሁለቱም መኪና የላቸውም ። ኪሱ ውስጥ የቀረው ገንዘብ ለታክሲ ላይበቃ ይችላል ። እና በባቡር እንሂድ ልበላት ? ወይስ ፡ ለምን ወክ አናደርግም ብዬ እስከቤት ልሸኛት ? የሚለውን እያሰበ እያለ ፡ ከሆቴሉ ወጥተው በሩ ላይ የተደረደሩት የሜትር ታክሲዎች ጋር ደረሱ ።

ፓውሌታ የአንዱን ታክሲ በር ከፍታ ገባች ። ዴንዝል ተከተላትና ፡ ወደቤቷ አቅጣጫ መጓዝ ጀመሩ ፡ እና እያወራት ፡ በመሀል ስንት እንደቆጠረ የታክሲውን ሜትር ያያል ።
ኬሎሜትሩ በጨመረ ቁጥር ፡ ብሩም እያደገ ሄደ ። ዴንዝል ዋሽንግተን ፡ ሀሳብ ገባው ፡ በመጀመሪያ ቀን ዴቲንግ ፡ የታክሲ መክፈል ያልቻለ ሰው ሆኗል ።
በመጨረሻም ቤቷ ደረሰች ። ዴንዝል ነገራት ።
ብር ጨርሻለሁ
ታዲያ ምን ችግር አለ ብላ የመጣችበትን እና እሱን ቤቱ ሊያደርሰው የሚችለውን ጨምራ ከፍላ ወረደች ።
......
ግንኙነታቸው እያደገ ሄዶ ፡ አንድ ቀን ቀለበት ገዝቶ ተንበረከከ
ፓውሌታ ፡ አብረን እንድንኖር እፈልጋለሁ ። ታገቢኛለሽ ? ሲል ጠየቃት
አላገባህም አለችው
ቀለበቱን ኪሱ ከቶ ተለያዩ ።
.....
ትንሽ ቆይቶ አንድ ቀን ይህንኑ ጥያቄ ደገመው ።
እኔና አንቺ ባልና ሚስት መሆን ያለብን ሰወች ነን ፡ አብረን እንድንኖር እፈልጋለሁ ፡ አለና ያንኑ ቀለበት አውጥቶ ለጋብቻ ጠየቃት ።
አዝናለሁ ዴንዝል አላገባህም ብላው ሄደች ።
እሱም ሄደ ።
....

ከወራት በኋላ አንድ ቀን ያችኑ የፈረደባት ቀለበት አውጥቶ ፡ ለሶስተኛ ጊዜ አግቢኝ ሲል ጠየቃት ።
ፓውሌታ ይህን ተስፋ የማይቆርጥ ሰው ፡ አትኩራ አየችው እና የቀለበት ጣቷን ዘረጋችለት ።
እሽ አገባሀለሁ ።
..........
ቆየት ብለው ሰርግ ደገሱ ፡ ትንሽ ሰርግ ነበር ። እና የሚበላ ነገር በጠሯቸው ሰወች ልክ ተዘጋጀ ።

እንግዶች እየተመገቡ እያለም ፡ ሙሽሮቹ ዴንዝል ዋሽንግተንና ፡ ፓውሌታ ፒርሰን ፡ በሰርጋቸው ላይ የተገኙትን እንግዶች ፡ እየዞሩ ሰላም ሲሉና አብረው ፎቶ ሲነሱ ቆይተው. . ምግብ ሊያነሱ ወደ ጠረጴዛው ሲሄዱ ፡ ባዶ ነው ።
ምግቡ አልቋል ።
......
እንግዶቻቸውን ሸኝተው በሰርጋቸው ቀን ሬስቶራንት ሄደው ተመገቡ ።

ይህ ከሆነ አሁን አርባ አመታት አለፈ ። በዚህ መልኩ የተገናኙት ጥንዶች አራት ልጆች ወልደው ፡ ሶስት መቶ ሚሊየን ዶላር በባንክ አጭቀው ፡ ሆሊውድን የሚያምሰው የመፋታት አባዜ ሳያገኛቸው ፡ እስካሁን አሉ ።
....
በዩቲዩብ ቻናላችን የሚቀርቡ ስቶሪዎችን መስማት ለፈለገ ፡ ከስር ያለው ሊንክ መገኛችን ነው ።

@wegoch
@wegoch
@paappii

By wasyihun
«ጉድ ሆንኩኝ ዛሬ...!» ይላል ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ጭብጥ... ልቅቅ... ውርጭት እያደረገ... የእልህና የሀዘን ዲቃላ እንባውን ..ከዐይኑ እየጠረገ... አስፓልቱ ያቆራቸውን የውሀ ኩሬዎች በቆዳ ጫማው ጠርዝ በእልህ እየረጫጨ... በላዩ ላይ የሚወርደውን ካፊያ ከምንም ሳይቆጥር በቀስታ ይጓዛል። መሀል ላይ «ወይኔ ተዋረድኩ ዛሬ!» ይላል።

በዚህ ወር ብቻ ሰባተኛ ሥራ ከእጁ ወጥቷል። ከዚያ በፊት በነበሩት ስድስት ወራት የቀድሞ ደንበኞቹ በተለያየ ምክንያት ትተውት... አዳዲስ ደንበኞች ማጥመድ ተስኖት... ሥራ በጨረታም... በልመናም... በልምምጥም እየሞከረ አልተሳካለትም። መጨረሻ የተገኘችው ስራ ሁለት ወይ ሶስት ወር ያልፋታል... የዛሬዋ ግን ከሁሉም አንገብግባዋለች። ተስፋውን ሁሉ ጥሎባት ነበርና ማጣቱ ወፈፍ ሊያደርገው ደረሰ። «ወይኔ ተዋረድኩ... በተከበርኩበት ሀገር!» ይላል እየተንተባተበ።

አስራ ሶስት ሰራተኞች ቀጥሮ ያሰራል። የሰራተኞች ደሞዝ፡ የቢሮ ኪራይ አለበት። የመጋዘን ኪራይ... የመኪና ኪራይ የጥሬ እቃ... የመብራት ፡ የውሃ ...የስልክ... የኢንተርኔት... የነዳጅ....የግብር የፍቃድ ማደሻ... ስም ያለው ስም የሌለው መዓት ወጪ አለበት። በዚያ ላይ ስራ ባጣባቸው ወራት ወጪዎቹን ለማስታገስ ብሎ ከስንት ተቋም...ከስንት ሰው ብር ተበድሯል። በዚያ ላይ የሱ ኑሮ ደሞ አለ። የመኖሪያ ቤት ኪራይ...ልጆቹ ትምህርት ቤት... የቤት አስቤዛ ወጪ... የእናቱ ሕክምና እና ሌላ የወጪ ክምር ደግሞ በገዛ ኑሮው በኩል ይጠብቀዋል።

እሱ ግን መንቀሳቀሻ ሳንቲም እንኳ ከኪሱ ከጠፋ ከራርሟል... ኮትና ሱሪውን ለብሶ ለትራንስፖርትና ለምሳ መክፈል እያቃተው ባዶ ሆዱን በእግሩ ስንት ቦታ እንደተንከራተተ የሚያውቀው የሰማዩ ጌታ ብቻ ነው። ግን ከሁሉም የዛሬዋ ቁስሉ ባሰች። ተስፋውን ሁሉ አሟጥጦ አሸክሟት ነበርና... ስትወድቅ አብሮ ሁሉ ነገሩ ወደቀበት... ተስፋ ቆረጠ።

የገዛ መስሪያቤቱ የሰራተኞቹን ዐይን ላለማየት ብሎ ከሄደ ሰነባብቷል። ስልክ ማንሳት እንደጦር ይፈራል። መንገድ ላይ ከአበዳሪዎቹ አንዱ እንዳያዩት ኮፍያና መነፅር ማድረግና ውስጥ ለውስጥ መንገድ ማቋረጥ ልማዱ ሆኗል። ዛሬ ግን እየተንተባተበ... ዝናብ እያረጠበው በተከበረበት በዋናው ጎዳና ላይ... ያለኮፍያና መነፅር ጭንብል... እንደእብድ ጮክ ብሎ እያወራ እንደልጅነቱ ውሃ እያንቦራጨቀ... ወደገዛ መስሪያ ቤቱ ደመነፍሱን እየሄደ ነው።

ሰዓቱ ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ጥቂት አልፏል። የሰራተኞች መውጫ ሰዓት ማለፉን እንኳ ሳያገናዝብ እየተወራጨ መስሪያ ቤቱ ደረሰ። ምን ሊያደርግ እንዳሰበ አላወቀም። ግን ምንም ብርሃን አይታየውም። ጨለማ ነው። ከዚህ አይነት ውርደት ሞት የተሻለ እንደሆነ አንዳች መንፈስ ሹክ ይለዋል። የእልህ እንባ እና ሳግ እያደናቀፈው አሁንም አሁንም... «ኧረ መቅለል...! » እያለ የመስሪያቤቱን ደረጃ በፍጥነት ወጥቶ መግቢያው መጋዝን ጋ ሲደርስ ቆመ።

ለቢሮነት የተከራያቸው ክፍሎችና የስፌቱ መጋዝን በሕንፃው አንደኛ ፎቅ ላይ የሚገኙ ናቸው። ሕንፃው ላይ የሚሰሩት ሁሉም ሰራተኞች ባለመኖራቸው ከውጭ ምንም የሰው እንቅስቃሴ አይታይም። የሱ ቢሮዎችና መጋዘኑ ያለበት አንደኛው ፎቅ ግን በብርሃን ደምቆ ነበርና ገና እንዳየው ተናደደ። «እኔ ለራሴ የእዳ ማእበል ሊወስደኝ አሰፍስፏል...ጭራሽ መብራት አብርተው እየሄዱ ውዝፍ እዳ ሊከምሩብኝ ነው? a bunch of stupid people» ብሎ ሰራተኞቹን ተራግሞ ሰዓቱን ጎንበስ ብሎ አየ... ለአንድ ሰዓት አስር ጉዳይ። « ወይኔ የማንም መሀይም መቀለጃ ሆንኩ!» ብሎ መጋዝኑን ለመክፈት ቁልፍ ከኪሱ አውጥቶ ሊያስገባ ሲል የመጋዝኑ በር አልተዘጋም ነበርና... ወለል ብሎ ተከፈተ።

በንዴት ጦፎ ወደ ውስጥ ሲገባ ... ሁሉም ሰራተኞች በፍጥነትና በትጋት ስራቸውን እየሰሩ አየና በድንጋጤ ፀጥ አለ። መምጣቱን ስላላዩ ወደርሱ አልዞሩም ያለአንዳች መናጠብና ግዜ ማባከን በጥራትና በብቃት ስራቸውን እየሰሩ ነው። ቀስ ብሎ አንገቱን እያሽከረከረ ሁሉንም ሰራተኞቹን ቃኘ... የሚያወራ እና ስራ የፈታ አንድም የለም። ቀስ ብሎ የኋሊት ተራምዶ ወደሌሎቹም ቢሮዎች ሄደ። ሁሉም ሰራተኞች በትጋት እየሰሩ ነው። የቀረ .... ያልመጣ ... የእረፍት ጊዜዬ ደርሷል ብሎ አቋርጦ የወጣ የለም። ሁሉም አለቃቸው ሳይሰልላቸውና ሳይቆጣጠራቸው... እስከዚህ ሰዓት አምሽተው ሊያውም በእረፍት ቀን እየሰሩ ነው።

ቀሰስ ብሎ ወደገዛ ቢሮው ሄደና ወንበሩ ላይ ተቀመጠ። ተስፋ የመቁረጡ ስሜት ለራሱ አናደደው። «እንዴት ያለእረፍት ... ሳልቆጣጠራቸው... ሀያአራት ሰዓት... ሰባት ቀናት... ወሩን አመቱን ሙሉ የሚለፉልኝ የሚተጉልኝ ባለሞያ ሰራተኞች ይዤ ተስፋ እቆርጣለሁ? ተሳካለት? ወይስ አልተሳካለት ሳይሉ... ቢሮ ገባ አልገባም ሳይሉ... ደሞዝ ዘገየብን ቆየብን ሳይሉ... ሰራተኞቼ እየለፉ እኔ ምን ነክቶኝ... ምን ገጥሞኝ.. ምን ከብዶኝ... ተስፋ እቆርጣለሁ? አለ። ብቸኛው... ስራ ፈት እኔ ነኝ። እንጂ በስሬ የማይሰራ የለም። ብቸኛው ሰነፍ እኔ ነኝ ... እንጂ በስሬ ያልበረታ የለም አለ... አለና ልብሱን አስተካክሎ በግለት እየሮጠ ወጣ ...

እሱ ሲወጣ አንተ የት ጋ ነህ ወንድሜ?
ሰራተኞችህን እያቸው እስኪ አይንህን ጨፍንና። ልብህን እያት አንተን ጌታዋን ታምና ...ብታያትም ባታያትም ከማሕፀን ከመመስረትህ ጀምሮ ያለማቋረጥ እየተንደቀደቀች እየሰራች ነው። ኩላሊትህ ፈሳሽ ከማጣራት አልቦዘነም። ሳንባዎችህ ንፁህ አየር ከማስገባት የተበከለውን ከማስወጣት ተዘናግተው አያውቁም። ጉበትህ አንጀትህ ጨጓራህ... እግሮችህ... እጆችህ... ጆሮዎችህ አይኖችህ ምላስና ከንፈርህ... የደም ስሮችህ ...የነርቭ ጅማቶችህ... እጢዎችህ... የምታውቃቸውም የማታውቃቸውም እልፍ ሰራተኞችህ አንተ እንደአንተ እንድትቆም እንድትራመድ እንድታስብ እንድትኖር... የእድሜ ዘመንህን ያክል ያለእረፍት እየተጉ እየለፉ ነው። አለቃቸውን አንተን ሕያው ለማድረግ ስትቆጣጠራቸውም ሳትቆጣጠራቸውም የሞያቸውን ያክል የባህሪያቸውን ያክል ይለፋሉ። እንዴት ብትጨክንባቸው? እንዴት ብትንቃቸው? እንዴት ብታቃልላቸው? እንዴት ከመጤፍ ባትቆጥራቸው ነው ተስፋ የቆረጥከው ወንድሜ?

ምን ችግር ምን መከራ ቢገጥምህ... ምን ብትዝል ምን ብትንገሸገሽ... ቅን ሰራተኞችህስ? ልፋታቸውስ? እነሱ ቆመው እያደሩ ወድቀህ ልትቀር? እነሱ እየተራወጡ እየዋሉ አንተ ፈዝዘህ ልትመክን? ትጉህ ሰራተኞች የነበሩት ወዳቂ... ባለሞያዎች የሚለፉለት ብኩን ልትሆን? ይሄን ሁሉ በብርሃን በጨለማ ቢታሰስ ቢፈለግ የማይገኝ የኤክስፐርት መዓት ሰብስበህ መስሪያቤቱን ልትዘጋው? ልትተወው? ልትዘነጋው? ልትጥለው? ተስፋ ልትቆርጥ?

እህቴ...እንዴት ያለእረፍት ... ሳትቆጣጠሪያቸው... ሀያአራት ሰዓት... ሰባት ቀናት... ወሩን አመቱን ሙሉ የሚለፉልሽን የሚተጉልሽን ባለሞያ ሰራተኞችሽን ይዘሽ ተስፋ ትቆርጫለሽ? ተሳካላት? ወይስ አልተሳካላት ሳይሉ... ተኛች አልተኛችም ሳይሉ... ምግብ ...ዘገየብን መድሃኒት ቆየብን ሳይሉ... ወደውስጥሽ የምትዶያቸው የመርዝና የኬሚካል መአት ሳይበግራቸው... ሰራተኞችሽ...እየለፉ አንቺ ምን ነክቶሽ... ምን ገጥሞሽ.. ምን ከብዶሽ.. ለውጫዊ ሰው... ለውጫዊ ነገር... ለውጫዊ ሁኔታ ብለሽ...ተስፋ ትቆርጫለሽ? ። ብቸኛው...
ስራ ፈት አንቺ ነሽ። እንጂ በስርሽ የማይሰራ የለም። ብቸኛው ሰነፍ አንቺ ነሽ ... እንጂ በስርሽ ያልበረታ የለም።... ተነሺ... ልብስሽን አስተካክይ... ልብሽን አስተካክይ...
ከሱ አስቀያሚ ጥግ... ውጪ...
ከትጉሕ ሰራተኞችሽ ብለጪ...

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Rediet aseffa
ሥዕል ለማሳል በ+251984740577
ወይም @gebriel_19 ላይ  ፎቶ  በመላክ በ ተመጣጣኝ ዋጋ  ማዘዝ ይችላሉ!


@seiloch
@seiloch
Fifty shades of him
'
'
አለሜ የምለው እርሱ "የኔ ጨረቃ " ብሎ ያለኝ ለታ ስሸሻት የኖርኳት የምጠላት ጨረቃ ፊት እስክቆም ድረስ የአምስተኛ ክፍል ሳይንስ መምህራችን "ፀሃይ ትልቋ ኮከብ ናት .... ጨረቃ ደግሞ ከእርሷ ብርሃን ትሰበስባለች "ካሉን ቀን ጀምሮ ብርሃን መስረቋ አናዶኝ ጨረቃን ጠምጄ ያዝኳት።

ስንቴቴ "የዛሬው ብርሃንስ ጤፍ ያስለቅማል" በተባለለት ምሽት ሰማይ ኮርኒስ ላይ የተንጠለጠለች የብርሃን ኳስ ፅልመቱ ላይ የተንሰራፋች ለታ፣ እርሷን ለመሸሽ ስሮጥ አምጪ የተባልኩትን የታናሽ እህቴን ወተት ንጬ ቅቤ ወጣለት።
እናቴም የተቀበለችኝን የወተት እቃ ከፍታ እያየች "ብራ ጨረቃ እየጠበቀማ የሚያበር ጋኔል ሰፍሮብሻል" ስትል የምሮጠው ጨረቃ ወለል ስላለች መሰላት እንጂ ከእርሷ እየሸሸሁ እንደሆነ አታውቅም ነበር።

የኋላ ኋላ የጠመድኳት ጨረቃ መልሳ ጠምዳኝ ነው መሠል የሃምሌ ጭጋግ በጋረደው ምሽት መሃል አግኝቶኝ "ቤት ሄደን ጃኬት ደርቤ ልሸኝሽ " ያለኝን የሰፈሬን ጎረምሳ ተከትዬ ቤቱ ደርሰን ጃኬት ይደርባል ብዬ ስጠብቅ ልብሱን ሁሉ አውልቆ ርቃኑን ወደ ቆምኩበት መጥቶ ወተቴን ተቀብሎኝ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ ልብሴን ሲያወላልቅ እንደበግ እየተነዳሁለት የሆነው ሁሉ ሆኖ " አይዞሽ" እያለኝ አስሬ እንደምንም ለባብሼ ከቤቱ ስንወጣ ቀና ብዬ ሳይ፣ ቅድም የጋረዳትን ጭጋግ ገፍፋ የወጣች ሙሉ ጨረቃ ቁልቁል ስታየኝ አየኋት። የያዘኝን እጁን መንጭቄ በጉያዬ መኻል ያለውን ህመም ችዬ እየተደነቃቀፍኩ ለመሮጥ ስንቧቸር በብሩህ ጨረቃ ቀናት የማይነሳሳ ሴትነቴን በደመና ተከልላ ያታለለችኝ ሙሉ ጨረቃ ላስታውሰው እንኳ ለማልሻው ደብዛዛ ሰው ድንግሌን እንደሸለመች፣ ከእኔ እንዳስነጠቀችብኝም እያሰብኩ ነበር።

እና "የኔ ጨረቃ " ያለኝ ቀን ዘመናት በመሃላችን በኩርፊያ ያለፉት እኔና እርሷ ማዶ ለማዶ ፊት ለፊት ተፋጠጥን። አልጠላኋትም የዛን ቀን አልሸሸኋትም ያን ማታ ብቻ ግን እርሷን ሆንኩላት፤ እኔንም የሆነች መሰለኝ።

በእኔና በእርሱ መካከል የነበረው የቦታ ርቀት በዘመን ሁሉ የሚሰፈር ይመስለኝ ነበር። በቃ እርሱን የማቀርብበት ከእርሱ የምገናኝበት ምንም መንገድ የለም ብዬ ተስፋ ከቆረጥኩ ብሰነብትም አለሜ አፍ አውጥቶ "አንተያይም ተስፋ ቁረጪ" ሲለኝ ቅስሜ ደቅቆ ተሰበረ።

ገላዬ የናፍቆት ብርድ ያቆራመተው ነው። በእርሱ መታቀፍ በእርሱ መነካት ብቻ ይፈልግ ነበር። ጭኔ ላይ ያቆጠቆጡ ጥቃቅን ፀጉራት ሲቆሙ ይታወቀኛል፣የጡቴ ጫፎች ሲሾሉ ይታወቀኛል ፣ ብሽሽቴን ሲሞቀኝ ይታወቀኛል፣ ገላዬን የኔ ያልሆነ ያህል ልመቆጣጠር ሲያቅተኝ።

እየሩስዓለሜ ነበር። ሰርክ ዕለት ልሳለመው የማልመው ነክቼው ልፈወስ ዳብሼው ካለ እና ከሚመጣው ነገር ሁሉ ልነፃበት የምፈልገው።

ዳስሼው ከቅዱስነቱ ቅንጣት ቆንጥሬ ዘመኔን ሁሉ በደጄ የሚፈስ የቅባ መውደዱን ዘይት ነፍሴን እንዲያረሰርስ፤ ከአላፊ አግዳሚው መሃል ጨርቁን ጨብጬ ልፈወስ ....

"ካለሽበት የምመጣበት መንገድ ጠቧል" ሲለኝ ለመዓከ ገብሬል አባቴ በእለተ ቀኑ ነግሬው፣ "በግራም በቀኝም የለኝ ካላንተ የማስቸግረው" ብዬ ከቅፅሩ ተንበርክኬ የደጁን ጠጠር ዘግኜ ነጠላዬ ጫፍ የቋጠርኩት፣ ቤቴ ስመለስ ጎረቤቴ ለሣምንቱ ሰባት ቀናት ሁለት ጡት ያላቸው ሶስት ጀበናዎች አፈራርቃ የምትካድም፣ የፋጤና ከድጃን ቀናት የምታከብር፣ በአርሲዋ እመቤት ምትምል ባለውቃቢ ደግ ሴት የገብሬል ቡና ካልጠጣሽ ብላ ስትበቅተኝ፣ እንደታቦት ቀን እየቆጠረች ከምታወጣቸው ፍንጀሎቿ በአንዱ ያፈላችውን ቡና አቀብላኝ ...ምን አስተከዘሽ ብትለኝ "የምወደው ሰው የሰው ሃገር ቀረብኝ " ብያት እጆቿን ወደ ላይ ዘርግታ መአት አይነት መለዓክ፣ መአት አይነት መላይካ እየጠራች በአማርኛ በኦሮምኛ ተማፅኖዋን ስታንበለብል
"በየአፍ መፍቻቸው ይሆን የምትፀልይላቸው?" እያልኩ እየሰማዃት.....

የማግሁትን ቡና ሲኒውን ላቀብላት ከተቀመጥኩበት ስነሳ ነጠላዬ ጫፍ ከተቋጠሩ የገብሬል ጊቢ ጠጠሮች መሃል አንዲቷ ጊርጊራዋ ላይ ድንገት ተፈትታ ብትወድቅ ከእጣን ማጨሻዋ ላይ ሃምራዊ ጢስ ሲንቦለቦል አየሁ ...በሰፈሩ ቀድሞ ያልነበረ ጣዕመ አልባስጥሮስ ጠረን ሸተተኝ። ይህም ለመምጣቱ ምልክት ሆኖኝ መላዕክት መላይካዎቹ ጭላንጭል ተስፋ ቢያሳዩኝ ታላቁ ፀገመ እንዳለው ተስፋ መቀነት ሆነኝ።

አመታት እንደቀናት አልፈው "ካለሽበት የምመጣበት መንገዱ ሁሉ ቁልፍ ነው" ያለኝ አለሜ ሃገር ቤት ድረስ መጣ። ግን የሌላ ሰው ሆኖ ከሌላ ሰው በፍቅር ከንፎ ያለሁበት ከተማ ውስጥ ተገኘ።

ይህን ሳውቅ "ምን ከከፍታ ሆነው ወደ ታች ቢወረውሩት እርሱ እንደሁ እንደ ላባ ነው ተችሏቸውም አይሰብሩት" ብዬ የታባልኩለት ልቤ እንክት ብሎ ወደ እልፍ ቅንጣቶች ደቀቀ። እንባዬ በጉንጬ መም ነድሎ እንደ ጤግሮስ ዥረት ሆነ።

ደውሎ "ላግኝሽ" አለኝ
ግን ላገኘው አቅም አነሰኝ .... ናፍቆቴ ዘመን ተሻግሮ መጥቶልኝ ከኔ ከተማ ላገኘው ጉልበቴ ከዳኝ ላገኘው ወኔዬ ጠፋ የሰው መሆኑን ስሰማ።

የሚሰሙኝን ስሜቶች ስም ልሰጥ ስጥር ከረምኩኝ ቅናት ነው? ፍቅር ነው? በእርሷና በእርሱ የሚሰማኝ ይህ ነገር ምቀኝነት ነው? እያልኩኝ.... ሌት ተቀን ስብከነከን እህህ ብዬ ከረምኩኝ።

አንድ ቀን መልክት ደረሰኝ
"በዚህ ፀባይሽ ሳላገኝሽ ልሄድ ነው።"
"መች?" አልኩት መለስኩና "ዛሬ" አለኝ......ይሄኔ አንጀቴ ተላወሰ ጥፋተኝነት ተሰማኝ "ከማንስ ጋር ቢሆን ምን አለ አንዴ እንኳ ባየው ?" እያልኩኝ ፀፀት እንደጦስ ዶሮ አርባ ዘጠኝ ጊዜ ሲዞረኝ ቤት ገባሁ። በረንዳ ወጣሁ። ምጥ እንደያዛት ድርስ እርጉዝ ስንቆራጠጥ ቆይቼ ድንገት ወደ ላይ ቀና ብል ጨረቃ ከአናቴ ቆማ እኔን በአንክሮ ስትሰልል .....

ልጅነት እንደ ጧት ጤዛ አላፊ ነው ረጋፊ ወጣትነትም እጢ ነው ክው ያሉ ለታ ጠፊ ... እሱን በጠበኩባቸው ዘመናት መኻል የታዘብኩት ፍቅርን ከኖሩት በላይ የናፈቁት ናቸው የሚያውቁት።ጊዜ አቃጣሪ ነውና ጉርምስናዬን አስጥሎ ምን ለእርጅና ቢድረኝም እንደ አዲስ "ቀን አንድ" ብዬ ዳግም ብጠብቀው ቅር አይለኝም።

የስልኬ ሰሌዳ ላይ ሚሴንጀሬን ከፍቼ መፃፍ ጀመርኩ ።
"አለሜ በሰላም ግባ ... የሆነ ቀን ግን ናልኝ ለእኔ ብቻ ብለህ እኔ ጋር ብቻ ናልኝ"

Note :- ናፍቆት ከፍቅር ይበልጣል።

@getem
@getem
@paappii

By Elsa mulgeta
[ማነቂያ]

የሰኔ ጢንፍ የሚያበሰብሰው፣ አቋምና ማገሩ መጋለጥ የጀመረ የጭቃ ግድግዳቸውን ተደግፎ ከካፊያው ጋር የሚመጣውን ቅዝቃዜ ሽሽት ከእድሜ ብዛት መነሾ የሳሳ ኮሌታው የተበዘበዘ ሸሚዙን ከአንገቱ አጣብቆ ኩርምት ብሏል። እናቱን ጥበቃ!

እሷ እንደሁልጊዜው ሁሉ "የትልቅ ሰው ወሬ ልናወራ ስለሆነ ውጭ ቆይ! ጎሽ የ'ኔ ልጅ!" በማለት ነበር በሩን ከውስጥ የቀረቀረችበት።

እናቱ በየዕለቱ ከተለያዩ ወንዶች ጋር ምን እንደምታወራ አያውቅም። ቢያውቅም አይገባውም። ብቻ ወሬአቸው ቶሎ እንዲያልቅ ከደጃፍ ተቀምጦ እላዩ ላይ የሚፈረፈረውን ወደ መፍረሱ የተጠጋውን የግድግዳ አፈር እያራገፈ በተቻለው ሁሉ በእንቅልፍ ላለመውደቅ እየታገለ ይጠብቃታል።

በርግጥ የሆነ ቀን ግን ብርዱ በጣም ሲብስበት የፒያሳ ጎዳና ተዳዳሪ ውሾች ዛቻ ሲፀናበት "እማ ጨለማውን ፈራሁት ወሬአችሁን አልሰማባችሁም አስገቢኝ” ብሏት ያውቃል።

ለዚህ እሮሮው ከእናቱ ያገኘው መልስ ግን "ወንድ ልጅ አይደለህ ለምን ትፈራለህ…" የሚል ነበር። አንዳንዴ ሳስበው ወንድ መሆን መረገም ይመስለኛል!! ወንድ መሆን በራሱ ጫንቃ የሚያደነድን የሚመስላቸው ብዙ አውቃለሁ። ወንድነት ፍዳን ከመቀበል ጋር ያለውን አወንታዊ ቁርኝት የሚያሳስበው ማግኘት እምብዛም ነው!

በርግጥ በእሷም ፍርድ የለ! ምን ታድርገው! ገላዋን ለጎረምሳ የስካር ማብረጃ መስዋዕት ካላቀረበች እሷንም ልጇንም አድፍጦ የሚጠብቃቸው ከርሳም ርሃብ ይበላቸዋል።

እዚህ መሸት ሲል አዳኝና ታዳኝ፣ ገጸባህርይ እና ድርሰት፣ ንጋትና ምሽት፣ ገሃነምና ገነት፣ ገዥና ሻጭ የሚገዙበትን ገንዘብ የሚሸጡትን እቃ ይዘው በድንግዝግዙ ይገናኛሉ።

የገዢው መድረሻ ከደቂቃዎች ሀሴት የሻጭም ዋጋ ወስፋትን ገሎ ከማደር አልፎ አያውቅም። እዚህ ህይወት ዛሬን ተንፈስ ስለማለት ጠግቦ ስለማደር እንጂ ነገን ስለመድረስ አይደለችም።

እዚህ እናትነት በአደባባይ ለሽያጭ ይቀርባል፣ እህትነት ይሸቀጣል። አባትነት ይረክሳል፣ ወንድምነትም እንዲሁ። ሁሉም ለስሜቱና ለሆዱ ብቻ፤ ትግሉ፣ መፍጨርጨሩ፣ ሳንጃ መሞሻለቁ፣ ቡጢ መሰናዘሩ፣ ይሉኝታን መጣሉ… ዛሬን ይተርፉ ዘንድ ብቻ ነው። እዚህ ሁሉም የሚሰዋለት የየግል ጥም አለው። ይህ ዶሮ ማነቂያ ነው!

በረድፍ ተደጋግፈው የተሰደሩት ጠባብ ገላ መሸቀጫ ቤቶች የእነሱን ቤት ጨምሮ መጋረጃቸውን ከውጭ አድርገው በውሽንፍር እያውለበለቡ ከውስጥ ተቀርቅረዋል። የአልጋዎች መንሰጣሰጥና በወሲብ የሚቃትቱ ድምፆች ሰፈዋል።

እንግዲህ
የመጋረጃቸው ከውጭ ሆኖ በሩ ከውስጥ መቀርቀር ቤቱ በወሲብ ፈረስ እየተጋለበ ስለመሆኑ ምልክት መሆኑ ነው። ማንም አንቀጽና ገጽ ጠቅሶ ያላወጀው ግና ሁሉም የሚያወቀው ምልክት። ገዥና ሻጭ፣ ኢላማና ፍላፃ የሚግባቡበት እጅግ የረቀቀ ምልክት።

ቀስ እያለ
ካፊያን ውሽንፍር አመሻሽን ወድቅት ተስፋን ሀዘን ተካቸው። አልፎ አልፎ እየተሯሯጡ ከሚያልፉ የውሻ መንጋ በቀር በሰፈሩ ብቅ የሚል አይታይም። የሰፈሩን ሰርጣሰርጥ ቅያሱንም ሁሉ እንደ መቃብር ቤት ያለ ጭርታ ከበበው። ከላይ ጎርፉ እያንከባለለ የሚያመጣቸው የለስላሳ ጠርሙሶች እየተንገጫገጩ አረፋ እየደፈቁ ከቤታቸው ፊት በሚገኝ ቦይ ስር ያልፉ ጀመር። የህይወቱ ማለዳ ልጅነቱ እየተንገጫገጨ ያለፈ መሰለው…

“አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣አራት…”

@wegoch
@wegoch
@paappii

By Tamiru temesgen
ሥዕል ለማሳል በ+251984740577
ወይም @gebriel_19 ላይ  ፎቶ  በመላክ በ ተመጣጣኝ ዋጋ  ማዘዝ ይችላሉ!


@seiloch
@seiloch
2024/09/21 22:54:55
Back to Top
HTML Embed Code: