Telegram Web Link
አታምጣ ስለው አምጥቶ ቆለለው #8
«ስትነቃ ውሳኔሽን ባትቀበልስ” አለኝ ማት። የግሩምን ጉዳይ በሽምግልና እንዲያልቅ መወሰኔን ስነግረው።
"አስቤዋለሁ ማትዬ ... ይህቺ ሴት ሱቅ ውስጥ ተቀጥራ ነበር የምትሰራው። የቤት ኪራይ ከፍላ ...ልጇን አሳድጋ ... የትምህርት ቤት ከፍላ .... ምን ዓይነት ህይወት የነበራት ይመስልሃል? ይህቺ ሴት አንድ ቀን የምትጎርሰው ብታጣ ሄዳ የምትጠጋበት ዘመድ እንኳን የላትም። ታዲያ ለዝህች ሴት የገጫትን ሰው በእስር ከማስቀጣት እና ለልጇ የወደፊት ህይወት ዋስትና የሚሆናት ተቀማጭ ገንዘብ ከማግኘት የቱ ይበልጥባታል?"
"እሺ ካሳው ምን ያህል ብር እንዲሆን ነው ያሰብሽው?"
"ለዛ ነው እኮ የፈለግኩህ! ጉዳዩን በቁም ነገር እንዲይዙት እፈልጋለሁ። የሽምግልና ሂደቱ በትክክል ይደረጋል። ሰዎቹ ሀብታም ነገር ናቸው። ጥሩ ሰዎችም ይመስላሉ! እናትየው ልጇ አይታሰርባት እንጂ ምንም ያህል ብንላት አታመነታም! ብቻ ለባባ የወደፊት ዋስትና የሚሆን ገንዘብ መጠን መሆን አለበት። ሽምግልናውን የሚይዙልን ሰዎች አዘጋጅልኝ! "
"እንደገባኝ ከሆነ ያሰብሽው ገንዘብ ትንሽ አይደለም። ባይስማሙስ? "
"ምንም ቢሆን በልጄ ጉዳይ እንደማልቀልድ ማወቅ አለባቸው።" ባባን 'ልጄ!' ብዬ መጥራቴን ያስተዋልኩት ማት ያንን የስስት ፈገግታውን ፈገግ ሲል ነው።
"እሺ መች እንዲሆን ነው ያሰብሽው?"
"ነገሩን እያሰነዳዳን ትንሽ እንቆይ። ማትዬ ትንሽ ልጠብቃት። ምንም እንኳን አሸናፊ ሃላፊነቱን ቢሰጠኝም፣ እሷም ስሜን ስትፅፍ አምናብኝ ቢሆንም ህይወቱ የሷ ነው። የሷ የወደፊት ነው። ምንም የሚያስቸኩለን ነገር የለም! ልጠብቃት!"
"እሺ አያድርገውና ብትሞትስ?"
"ውሳኔዬን የፈራሁት እሱን ሳስብ ነው። ያሰብኩት ገንዘቡ ለባባዬ እንዲቀመጥለት ነው። ራሱን ሲችል የሆነ ነገር ለመጀመር ይረዳዋል። እናቱን አይመልስለት ይሆናል። ቢያንስ ግን ለሆነ ነገር ይጠቅመዋል። ግሩም ቢታሰርም እናቱን አይመልስለትም። ግን ትልቅ ሆኖ ከገንዘቡ ይልቅ እናቴን ያሳጣኝ ሰው ቢቀጣልኝ ነበር የምፈልገው ቢለኝስ? ይቅር ባይለኝስ? ቢጠላኝስ?"
"እህቴ ያንቺ ልጅ ሆኖ አድጎ እንደሱ ይላል ብዬ አላስብም! ካንቺ ጋር አይደለም አድጎ አንድ ቀን አድሮ ያንቺ ልብ የማይጋባበትኮ አይኖርም! ትልቅ ሲሆን እንዳንቺ ይቅር ባይ፣ እንዳንቺ ጠቢብ፣ እንዳንቺ መልካም ነው የሚሆነው።"
"ሁሉም ልጆችኮ በእናታቸው አይወጡም!"
"ሁሉም ልጆች ግን እንዳንቺ ፍቅሯ የዓለምን ክፋት ሁሉ የሚያስረሳ እናት የላቸውም።"
"ባክህ እናት ሁሉ ለልጇ እንደዛ ናት።"
"ለልጇ አዎ! በዙሪያዋ ላሉ በሙሉ ግን አይደለችም። ልጆችሽ ለእነርሱ የምታደርጊውንና የምትሆኚውን ብቻ እያዩኮ አይደለም የሚያድጉት። በእያንዳንዷ ቀንሽ ለሌሎች የምታደርጊውን እና የምትሰጪውን ፍቅር ያያሉ። እነርሱም ሲያድጉ በደም ለተጋመዳቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ ቅንና ፍቅር ሰጪ መሆን ትክክለኛው መንገድ መሆኑን ያውቃሉ። በልጅሽ ውስጥ ራስሽን አታዪም? "
"እኔእንጃ ማት አንዳንዴ እኔ እንደምትሏት ዓይነት ቅን ሰው ከሆንኩ፣ ሁሌ እንደምትለኝ ገራሚ ልብ ካለኝ ለምንድነው አምላክ ደስተኛ ሆኜ እንድኖር ያልፈቀደው?" አልኩት
ማለት የፈለግኩት የነበረው ግን ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የወደድኩት ሰው ትቶኝ ሲሄድ ጥፋቴ ምን ነበር? ሙሉ ልቤን ሰጥቼ ፍርክስክስ ያለ ልብ መቀበል ፍራቻ ወንድ መልመድ ሸሽቼ ልጄን ብቻዬን ሳሳድግ የየትኛው ጥፋቴ መከር ነበር?
"የምትፈልጊውን አምላክሽን ለምነሽው ታውቂያለሽ?"
"አምላክ እኮ ነው። የሚያስፈልገኝን ከእኔ በላይ የሚያውቅ፣"
"እራሱ አምላክ ነው 'ጠይቁ ይሰጣችኋል አንኳኩ ይከፈትላችኋል' ያለው። ሳንጠይቀው በፊት የምንጠይቀውን ስለማያውቅ አይደለም። አምላክ የነፃነት አምላክ ስለሆነ በፈቃዳችን ነው የሚያደርግልን። ፈቃዳችንን ይፈልጋል። ባይሆን ኖሮ ስንቱን ልበ ድንጋይ እያጋጨ አይመልሰውም ነበር? ምክንያቱም ልኩና የሚያስፈልገው መልካም መሆን ስለሆነ! ግን ለምርጫችን ይተወናል። አምባገነን አይደለማ!"
"እንዴ? የምንፈልገውና የምንጠይቀው ሁሉኮ ልክ አይደለም። አንዳንዴ የማይበጀንን እንጠይቃለን። እርሱ ግን የቱ እንደሚበጀን ያውቃል።"
"እኔ የማምነው ለምሳሌ 'አምላኬ ሆይ ደስተኛ አድርገኝ!' ብለሽ ስትለምኚ ምናልባት ያንቺ ልመና ገንዘብ ሊሆን ቢችል እርሱ ደስታሽ ልጅጋ ከሆነ ያለው ልጅ ይሰጥሻል። የለመንሽው ደስታን ነውና ደስታሽን ታገኛለሽ። እኔ እንደዛ ነው የማስበው!"
"እና ስላልጠየቅሽ ነው ያልተሰጠሽ ነው የምትለኝ?"
"ያንቺ ከዛም ያልፋል እህቴ!" ሳቅ እያለ "አምጥቶ አልጋሽ ላይ ቢያስተኛልሽም ራሱ 'የእግዜር እንግዳ' ነው ብለሽ አልጋሽን ለቀሽለት ትሄጃለሽ! ቢሰጥሽም ለመቀበል ዝግጁ አይደለሽም።"
"ባል ነው የምፈልገው ወጣኝ?" አልኩት ፈገግ ብዬ። ሁሌም ሳልናገር በፊት ያሰብኩት እንዴት እንደሚገባው ግርም ይለኛል።
"እኔስ እንግዳ ተቀባይ ነሽ አልኩ እንጂ ባል ትፈልጊያለሽ ወጣኝ? እኔ የምለው እማዬ ባባን እንዳላመጣሽው ነገረችኝ ለማን ትተሽው ነው ስራ የገባሽው?" አለኝ። ስራ ስገባ እነእማዬጋ እየተውኩት ነበር የምሄደው።
"የምታይልን ልጅ ቀጠርኩ" ስለው የሆነ የምስራች የነገርኩት ነበር የሚመስለው። ደስ አለው።
"ምነው? ምንድነው የሚያስፈነድቅህ?"
"እህቴ ሰራተኛ ኖራት!" ብሎ አሁንም ይፍነከነካል።
"ታዲያ ምኑ ነው የሚገርመው?"
"እስከዛሬ ሰው ሳያስፈልግሽ ቀርቶ ነበር ሰው ያልኖረሽ? 'እኔ የማንን ጎፈሬ ሳበጥር ነው ሰራተኛ የምቀጥረው?' ያልሽንን አምነንሽ ዝም ያልን ነው የሚመስልሽ? አዲስ ሰው ወደ ህይወትሽ በምንም መልኩ እንዲገባ ስለማትፈልጊ ነው። ይሄንንማ ለእማዬ እስክነግራት...."
"ኸረ አይደለም! ደግሞ እማዬም እንደዛ ነው የምታስበው?" የምርም በዚህ መንገድ አስቤው አላውቅም!!
"አንቺ ብቻ ነሽ እንደዛ የማታስቢው" አለኝ አሁንም ፈገግታው ፊቱ ላይ እየተርመሰመሰ። ቀጠል አድርጎ "ግሩም ምን አለ?"
"ስለምኑ?" ድንብር አልኩ።
"ስለሽምግልናው ነዋ!"
"ደስ ነው ያለው!! ቅጣቱን አይደል በገንዘብ የቀየርንለት? ለምን ካሳውን እንደመረጥኩ ስነግረው 'እንኳን በሞትና በህይወት መሃከል ለመሆኗ ምክንያት ሆኜ፣ እንዲሁም ልንረዳት የሚገባት ሴት ናት!' አለኝ"
"ቆይ ቆይ ከዚህ ሌላ ምን አወራችሁ?"
"ምንም!" አልኩኝ ፍርጥም ብዬ
"አላውቅሽም እና ነው? ሌላ ነገርማ አለ! ምን አለ ስልሽ እንደፌንጣ አትዘዪም ነበር።"
"እራት ልጋብዝሽ!" አለኝ።
"እና?"
" ለምን? ስለው ላመሰግንሽ አለኝ! እስከአሁን ያመሰገንከኝ በቂ ነው እራቱ አስፈላጊ አይደለም አልኩት ..." ተናግሬ ሳልጨርስ ማት በሳቅ ይንፈቀፈቅ ጀመር።
"እንዴት ያለሽው ገልቱ ነሽ?" እያለ በሳቅ ይፈርሳል ። የማይሆን ነገር ስናደርግ ገልቱ ብቸኛዋ የአባዬ ስድብ ናት። እራት ልጋብዝሽ ማለት 'ላውቅሽ እፈልጋለሁ!' ማለት እንደሆነ ጠፍቶኝ አልነበረም። አፌ ላይ የመጣልኝ ለምን? የሚል ጥያቄ ነበር። እሱም እንደማቲ 'ምኗ ገልቱ ናት?' ብሎ መሰለኝ ላመሰግንሽ! ያለኝ!! ማት መሳቁን አላቆመም!!
"ማቲዬ በእማዬ ሞት እረፍ!"
"እሺ ይቅርታ!" ለመኮሳተር ይሞክርና ደግሞ ይስቃል። "እህቴ ይቅርታ አለመሳቅ ከባድ ነው። ለምን? ምን የሚሉት ጥያቄ ነው?" ይደክማል። "ቆይ አንቺ ከአሼ በኃላ ጭራሽ ዴት አድርገሽ አታውቂም? እንዴ (እንደማስታወስ እያለ) ማነው ይሄ ቢጫ መኪና የሚነዳው ቢጫው ሰውዬ ..." ይስቃል
"ድንገት ከመሬት ተነስቶ እራት ልጋብዝሽ ብሎኝ ግን አይደለም ዴት የተደራረግነው?"
"ደብዳቤ ይፃፍ? የልብ ስዕልስ ይጨምርበት? መንገድ ላይ እየጠበቀ ሳታዪው ከጀርባሽ እየተከተለ ለአንድ ዓመት ይሸኝሽ? አንቺን ለማየት ደሞዙን 30 ቦታ ከፍሎ በየቀኑ ባንክ እየመጣ አስር አስር ብር በየቀኑ ሴቭ ያድርግ? "
(ቢጫ ሰውዬ ያለው 'አዲስ' እንደዛ ነበር ያደረገው። በመጨረሻ እሺ ብዬው ሁለት እራት እንኳን በስርዓቱ ሳንበላ ነው የተለያየነው።)
"For God sake ዴት ለማድረግ እየደረሰች ያለች ልጅ ባደረሽበት እድሜ እንደኮረዳ መሽኮርመም? እህቴ! ትልልቅ ሰዎች እንደዚህ ነው የሚያደርጉት በአዋቂ ደንብ ተገናኝተው ይነጋገራሉ። ይተዋወቃሉ። አብሮ የሚያስኬድ ነገር ካላቸው ይቀጥላሉ ካልሆነ ተነጋግረው መንገዳቸውን ይለያሉ!"
"እኔ ይሄ ጠፍቶኝ ነው? "
"ጠፍቶሽማ ነው!" ይንፈቀፈቃል። "ትልልቅ ሰዎች ሌላ የሚያደርጉት ምን መሰለሽ? አንደኛው እስኪደውል አይጠባበቁም! ደውዪና እራቱን መች እናድርገው ?በይው።"
"አላደርገውም! በፍፁም!"
"እህቴ? " አለኝ ሳቁን ጨርሶ እየተኮሳተረ አንድ አንዴ አንዳንዴ ሲያዝንልኝ በሚያወራበት ፊቱ «ብቻሽን ዘመንሽን ሁሉ ትኖሪያለሽ? የሰው ልጅ ደግሞ ቀርበሽ ሳታውቂው ወጥ ውስጥ ያለጨው እንደሚቀመሰው ቅምስ አድርገሽ አታውቂውም! እድሉን ስጪውና ሞክሪው!"
"ብወደውና ልቤን ቢሰብረውስ?"
"የፍቅር ቀመሩኮ ያ ነው እህቴ! ስትወጂ ሊሰብረው እንደሚችል እያወቅሽ አምነሽ ልብሽን ትሰጫለሽ! አንዳንዱ ይጠብቅልሻል። አንዳንዱ ደግሞ እንደፈራሽው ሰብሮ ይመልስልሻል። ደፍረሽ ካልሞከርሽው ግን ልብሽን እንደእንቁ ሊጠብቅልሽ የሚችለውንም ገፋሽው ማለት አይደል?"
"እሺ ይሁን እንበልና ብወደውኮ የባባን እናት የገጫትን ሰው ማለት ነው። አይበለውና ባትተርፍ እናቱን የቀማውን ሰው ዴት ማድረጌን ሲያውቅ ባባ ምን ይለኛል? "
"ታወሳስቢው የለ እንዴ?" አለኝ ግርም ብሎት እያፈጠጠ። ......
ይቀጥላል.....

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
የአብዮት ፍሬ ነኝ 2

ዱርዬ ነው ፊቱ !

ብዙ አይነት ፈተና አውቃለሁ። የአምስተኛ ክፍል የሁለተኛዋ ክፍለ ጊዜ ፈተና ግን እንዴት ይገለፃል?

ሁለተኛ ክፍለ ጊዜ የእረፍት መንደርደሪያ ናት። የየሺ ጮርናቄ የሚጠበሰው በሁለተኛዋ ክፍለ ጊዜ ነው።

የጮርናቄ ሽታ ከሸክላ ጥብስ ሽታ በላይ ያማልላል...ከጭቅና ጥብስ በላይ ያነሆልላል። ምድረ ውሪ ነፍሳችን ዝቅ የምትልለት ውብ መዓዛ! በዛ ሰዓት ከገነት ፍሬ በላይ ለጮርናቄ ሽታ እንንበረከካለን። ከፈጣሪ አልቀን ለፓስቲ እንሰግዳለን። 

ወንድማችን ፓስቲ ሆይ

በሰማይ የምትኖር ብለን ለመፀለይ አይሸመቅቀንም 😋 እንደውም ማንም ሰባኪ መጥቶ ገነት ምን ትመስላለች ቢለን...ሰማዩም ...ምድሩም...ዛፉም...ድንጋዩም.. .ሳሩም ጮርናቄ የሆነ ቦታ ብለን የምንመልስ ይመስለኛል። 

ያቺ ሰዓት የቤት ልጆች ከፍንዳታ ልጆች ተለይተን የምንቁለጨለጭባት ክፉ ትውስታችን ናት።

አንድ ብር ከስሙኒ ማግኘት ተዓምር ነው...ምትሀት ነው...ድግምት መተት ነው ለኛ !

እነ ፍንዴክሶቹ እስጢፎና ቦጌ ለዚህ የታደሉ ናቸው ። በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ አስፈሪው ሂሳብ መምህራችን ቢከሰቱ እንኳ እነ እስጢፎ በመስኮት ከመዝለል አይመለሱም። 

እኛ ሆዳችን እየተላወሰ ጂኦሜትሪ ምናምን እንማራለን ። የሌላውን ባላውቅም እኔ ግን በዛች ፔሬድ ትምህርት አይገባኝም።

እንኳን ጂኦሜትሪ ቀላሉ አማርኛ እንኳ ለኔ ፊዚክስ ይሆንብኛል። በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ አንድ የአማርኛ መምህር የቆጡን አወርድ ብላ ቢጀምሩ የብብቷን ፓስቲ ጣለች ከማለት አልመለስም 😄

የሆነውም ሆኖ ግን ዱርዬ ነው ፊቱ የዋህ ነው ልቡ ይሉት ዘፈን የገባኝ ያን ጊዜ ነው። 

ቸካዮቹ እነ አቤኒ (የሀብታም ልጅ ነው እኮ)

ጮርናቄ ገዝተው አካፍሉን ስንላቸው ፓስቲውን በርገድ ያደርጉና ምራቃቸውን እንትፍ ይሉበታል። ወሽመጥህ አብሮ ቁርጥ ይላል ።

እስጢፎ ግን የዋህ ነው...ከገዛት ፓስቲ ውስጥ አርባ አራቱንም ታቦት ጠርተን ቢሆን ያካፍለናል። ያቺን አንድ ጉርሻ ማን ወንድ አላምጦ ይውጣታል? እንደ ጫት ተርዚና ወጥረን ደቂቃዎችን እንቆያለን ። 

እንደውም ከኔ ጋር ከሚለምነው ቢኒያም ጋር አንድ ቀን ተጣልተናል።

ቢና ፓስቲዋን አንዴ ቆርሶ ውጧታል። እረፍት ጨርሰን ስንገባም ያላምጣል። ከኛ ተደብቆ ኪሱ ውስጥ ይዞ ይሆናል ብዬ በረበርኩት ወፍ የለም። 

ቀስ ብዬ ስሾፍ እጁን የትም ሳይሰድ አፉ ግን ያላምጣል። ከቆይታ በኋላ አንድ ነገር ገባኝ።

ቢኒ ጮርናቄዋን በእረፍት ሰዓት ቢውጣትም...መልሶ መላልሶ እያጋሳ እንደ ፈረስ መኖ እያመነዠካት ነበር።

ስነቃበት ደነገጠም ...አፈረም...እኔና ጓደኞቼ ደግሞ ዜብራው እያልን ሙድ ያዝንበት.. .እንደ ፈረስ አሽካካንበት.. .

ከዛች ቅፅበት በኋላ ቢኒ እኔን ሲያየኝ ብዙ አልመቸውም 😂

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Mikael Aschenaki
በር ላይ እንደመግቢያ የሚያገለግለው ፓስታ ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ ... ደረቅ ምግብ ፣ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ፣ አልባስ ይሆናል ! ቀን 23/4/2014 በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይቀርባል ! በለቱ ከጠዋት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር በር ላይ ደም የሚሰጥ ይሆናል ። ቴአትሩ የሚቀርብበት ሰዓት 11:30 ይጀምራል

@wegoch
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #9

“በቅርብ ጊዜ …. ማለቴ አናቴ በነጭ ፀጉር ከመከደኑ በፊት ዝግጁ የምትሆኚ ይመስልሻል?”አለኝ ግሩም ፈገግ እያለ።

ማት እንዳለኝ ራሴው ነኝ የደወልኩለት። አዋቂዎች ያደርጉታል እንደተባልኩት የእራቱን ሀሳብ ተቀብያለሁ አልኩት። ስለብዙ ነገሮች ስናወራ ቆይተን።

"ግሩም አሁን ባለሁበት ሁኔታ ካንተጋ ለመሆን ዝግጁ አይደለሁም!" ብዬው ነው

"አናቴ በነጭ ፀጉር ከመከደኑ በፊት ዝግጁ የምትሆኚ ይመስልሻል?" የሚለኝ

"እንደማየው ከሆነ ካሁኑ ነጭ ፀጉር ጀምሮሃል! ሙሉ አናትህን እስኪከድነው ያለው ጊዜ ዝግጁ ለመሆን ያንሰኛል!" አልኩት እሱ በጀመረው ጨዋታ

"የእውነት ዝግጁ ስላልሆንሽ ነው ወይስ እንደአንዳንድ ሴቶች ደጅ በማስጠናት ምን ያህል ርቀት እንደምሄድ ልትፈትኚኝ ነው?"

"አይ እኔስ የእውነቴን ነው። ግን እንዳልካቸው ሴቶች ቢሆንስ?" አልኩት

"አታስዋሺኝ እኔ ትዕግስቱ የለኝም። ቀጥተኛ ሰው ነኝ! የተሰማኝን ፊትለፊት እናገራለሁ። ይሄ የልጅ አባሮሽ ጨዋታ እድሜዬም ባህሪዬም ነው ብዬ አላስብም። ለአባባል ነው እንጂ ጠብቀኝም ብትዪኝ ፀጉሬ ነጭ እስኪሆን አልጠብቅሽም አልዋሽሽም!" አለኝ እየሳቀ

"ሀቀኝነትህ ደስ ይላል"

"እኔ ስለሆንኩ ነው ወይስ ባጠቃላይ ማንንም ቢሆን ለመቀበል ዝግጁ አይደለሽም?"

"ለማንም ቢሆን ዝግጁ አይደለሁም! አንተ መሆንህ ደግሞ ይባስ ፈታኝ ይሆንብኛል።"

ለማውራት የሚከብድ ሰው ስላልሆነ ወይም ምክንያቴን ማወቅ ይገባዋል ብዬ እኔእንጃ ጥቃቅን ነገሮች ሲቀሩ ብዙውን ነገር ስለአሸናፊ አወራሁት። በዝምታ ሲሰማኝ ከቆየ በኋላ

"የሆነ ሰው በጥይት ተመቶ ቢቆስል ቁስሉ እያንገበገበው መጀመሪያ የሚያደርገው ሀኪምጋ መሄድ አይደል? ቁስሌ ሲነካ ስለሚያመኝ ብሎ የሚደማ ቁስሉን አቅፎ እቤቱ አይቀመጥም! ሀኪሙ ቀዶም ይስፋው፣ ምንም ያድርገው ግን አምኖ ቁስሉን ይሰጠዋል። ያኔ የሚፈጀውን ጊዜ ፈጅቶ ቁስሉን ያድንለታል። ያው ጠባሳው ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም!" አለ ትከሻውን እየሰበቀ።

"አይገናኝም! ሀኪሙ እንደሚያድነው ቀድሞ ነገር ያውቃል። ከርሱ ቁስል ሌላ ብዙ ቁስሎች እንዳዳነ ስለሚያውቅ ነው አምኖ የሚሰጠው!" አልኩት

"ያን ለማወቅ የሀኪሙን ፋይል ያገላብጣል? ያለፈ ታሪኩን ያጠናል? በፍፁም! የለበሰውን ነጭ ጋውንና ማዕረጉን አይቶ ያምነዋል። ምናልባት ሀኪሙምኮ የሆነ ቀን ተሳስቶ በሙያው ህይወት የሚቀጥፍ ስህተት ሰርቶ ያውቅ ይሆናል።"

"እና ሀኪሙን ነኝ እያልከኝ ነው?"

"አቁሳይ እንዳለ ሁላ ሀኪምም አለ እያልኩሽ ነው!"

ኑሮዬ ያለፉትን 15 ዓመታት (ከሆስፒታል ስልክ እስከተደወለልኝ ቀን ድረስ) ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ምን እንደሚመስል የማውቀው ፣ የታቀደ ቀን ያለኝ ፣ ተመሳሳይ እና በአብዛኛው ተደጋጋሚ ነበር።

ያልተለመደ፣ አዲስ፣ አድቬንቸር ያለበት ቀን አልወድም። አልሞክርም። አዲስ ነገር ስለምጠላ አይደለም። የምሞክረው አዲስ ነገር ያለኝንም ረጭ ያለ ቀን ይዞብኝ ሄዶ የተሻለ ፍለጋ ያለኝን እንዳላጣ ስለምፈራ እንጂ። ስለዚህ ባለኝ ቀን አርፌ እውላለሁ። አዲስን ነገር በመሞከር ውስጥ የተሻለ ነገር ሊኖር እንደሚችልም ጠፍቶኝ አይደለም። የመሆን አጋጣሚው 0.00002 % ቢሆንም የባሰውን የምጋፈጥበት ዝግጁነት የለኝም! ስለዚህ ጨው የሌለበት አልጫ አልጫ የሚል ቀኔን እያመሰገንኩ እሰለቅጣለሁ።

"እንደውም ሀሳቤን ቀይሬያለሁ! ፀጉሬ እስኪሸብት እጠብቅሻለሁ" ብሎኝ ነበር ግሩም እየሳቀ የዛን ማታ ወደቤቴ ሲሸኘኝ። ራይድ ጠርቶ ነበር የሸኘኝ።

"እስከመቼ ነው መኪና የማትይዘው?" ስለው

"እሷ እስክትነቃ! ነቅታ ጥፋትህ አይደለም ካለችኝ የዛኑ ቀን ካለሽበት መጥቼ ወደምትፈልጊበት እሸኝሻለሁ።"

"ካልነቃችስ?"

"አላውቅም! ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድብኝ አላውቅም! ጊዜ እፈልጋለሁ" ነበር ያለኝ።

ከግሩም ጋር እራት መብላቴ ስለግሩም ያለኝን ነገር አይደለም የቀየረው። ባልገባኝ ምክንያት በዙሪያዬ ያሉትን ነገሮች የማይበትን መነፅር እንደቀየረው ገባኝ። እና ለማድረግ የማልደፍረውን ነገር ደፈርኩ። አቢጋ ደወልኩ! እስከዛሬ ያልነገርኳትን ቻው እንኳን ሳትለኝ መሄዷ እንዴት እንዳስከፋኝ፣ በህይወቷ እንዳልነበርኩ ስትረሳኝ የተሰማኝን መታመም ልነግራት እንጂ ልወቅሳት አይደለም።

'ህይወት የቅፅበቶች ጥርቅም ናት' ትላለች እማዬ። ቤተሰቦቼ በጣም ለጥቃቅን ነገሮች ትኩረት የሚሰጡ፣ ትንንሽ ለውጦችን ትኩረት ሰጥተው የሚከታተኩ ዓይነት ናቸው። ደስታም ይሁን ሀዘን። ለምሳሌ እማዬ ሰራተኛ መቅጠሬን ከዩንቨርስቲ የመመረቄን ያህል እኩል እንደትልቅ ክስተት እንደምትደሰትበት ፣ ከግሩም ጋር እራት መብላቴን ስነግረው ማት ስራ ቦታ መጥቶ የተሰማኝን ስሜት እንደሚያረጋግጠው ፣ 'ባባ ፖፖ ላይ ተቀምጦ ነው የሚሸናው' ስላቸው አባዬ እቤት ድረስ መጥቶ 'ወንዶቹ እንዴት እንደሚሸኑ ላሳይልሽ' እንዳለኝ አይነት .....ህይወት የትልቅ ክስተቶች ጥርቅም አይደለችም! ልክ ስለሰው ያለንን ነገር በጥሩም ይሁን በመጥፎ ለመቀየር አንድ ሰው እንጂ የሰው ልጅ ሁሉ እንደማያስፈልገው ....... በአንድ ሰው ምክንያት መላ የሰው ዘርን እንቀየማለን፣ እንፈራለን፣ እንጠላለን እንጠራጠራለን እንደዛው በአንድ ሰው ምክንያት ደግሞ መላ ህይወትን እንወዳለን ለመኖር እንጓጓለን ፍጥረትን ሁሉ እንወዳለን እንደዛ .....
የሚገርመው ያ አንድ ሰው ባደረጋት አንዲት ስህተት ወይም አንዲት መልካምነት ይሆናል እንደዛ ዓለማችን የሚገለባበጠው

"ይቅርታ አድርጊልኝ ፌቪዬ እንደዛ እንዲሰማሽ እንዳደረግኩ በጭራሽ አላውቅም! ልጆች ነበርንኮ!" አለችኝ አቢ ፀጥ ብላ ከሰማችኝ በኃላ .... ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ዛሬ የሆነ ያህል እያንዳንዱን ነገር ማስታወሴ የገረማት ትመስላለች። እንዳሰብኩትም የሆነ ሸክም ከላዬ ላይ የቀለለኝ ስሜት ተሰማኝ።

እንዲህ ነውኮ አይደል? የተቀየማችሁት ሰው፣ በእሱ ምክንያት እንቅልፍ ያጣችሁለት ሰው፣ ህመማችሁን ለዓመታት ያስታመማችሁበትን ቁስል የሰጣችሁ ሰው ጭራሽ መከፋታችሁንም ላያውቀው ሲችል? ልክ እሱ ከእናንተ ህይወት ሲወጣ ረስቷችሁ ህይወቱን እንደኖረው እናንተም ረስታችሁት የኖራችሁ ሲመስለው? ለልጄ የመከርኳትን ምክር ለራሴ መተግበር ነበረብኝ።

"አቢዬ ቂም አልያዝኩብሽም። ካልነገርኩሽ አይወጣልኝም ብዬ ስላሰብኩ ነው የነገርኩሽ። ከሰሞኑ የገባኝ እኔ ያለስስት እንደእህቴ ሊወድሽ የሚችል ትልቅ ልብ ስለነበረኝ እንጂ የወደድኩሽ አንቺ ስለሚገባሽ አልነበረም። ያኔ ቢገባኝ ደስ ይለኝ የነበረው ልቤ ፍቅሩን የተሳሳተ ቦታ ማፍሰሱ እንጂ መውደዱ ስህተት እንዳልነበር ባውቅ ነበር።" አልኳት። ስልኩን ዘግቼው አስብ የነበረውም ያንን ነው። በህይወቴ ውስጥ በብዙ ወድጃቸው በተመሳሳይ ሁኔታ በአካል አጊንተው እንኳን ሊሰናበቱኝ ላልፈለጉ ሁለት ሰዎች መውደዴ ስህተት ይመስል ራሴን ስቀጣ የኖርኩርኩት እኔ! ረስተውኝ ስለኖሩ መታመሜን እንደመሸነፍ ቆጥሬው በራሴ የምበሳጨው እኔው!

ደስ የሚል ስሜት ሲሰማኝ ከረምኩ። ቀኖቼ የተለመዱት ቢሆንም ስሜቴ ግን ይለይ ነበር:: (እንደዋዛ ቀናት ወራትን ተክተው በአንዱ ጠዋት ከሆስፒታል ተደውሎ ሄለን መንቃቷ እስከተነገረኝ ሰዓት።) የሚሰማኝን ስሜት መለየት ቸገረኝ። የሆነ ደስ የሚል ስሜት ከዛ ደግሞ የሆነ የተወናበደ ልቤን ክብድ የሚለው ስሜት ከዛ ደግሞ የመከፋትም ስሜት በአንድ ጉዳይ ሁሉም ስሜት። ለደቂቃዎች ስልኬን እንኳን ከጆሮዬ ሳላወርደው ቆየሁ። ድንዝዝ ያለ ስሜት .........
ከተቀመጥኩበት ሳልነሳ ማት እና ግሩምጋ ደወልኩ።
"እግዚአብሄር ይመስገን!" ካለኝ በኋላ ወዲያው "መጣሁ!" አለኝ ማት ሳልነግረው ይገባው የለ? ግሩም ፈነጠዘ። ሆስፒታል ስደርስ ነቅታ ሰውነቷ ላይ ተሰካክተው የነበሩት ማሽኖች ተቀንሰው ቅልል ብሏታል።

"ልጄስ?" ነው ያለችኝ ገና ስታየኝ መልኬን ታውቀዋለች ማለት ነው? ወይስ ገምታ ነው ብዬ እያሰብኩ

"ትምህርት ቤት ነው!" አልኳት ባባ ትምህርት ከጀመረ ሁለት ሳምንቱ ነበር። ዶክተሩ 'ከዚህ በኃላ ልትነቃ የምትችልበት እድል እየጠበበ ነው።'ያለኝ ጊዜ ነው ትምህርት ቤት ግማሽ ሴሚስተር ላይ ያስመዘገብኩት። ዝም አለች። ከዛ ደጋግሜ "እንዴት ነሽ አሁን?" የምላት እኔ ሆንኩ። ማት እና ግሩም ሲገቡ ማናቸው በሚል ስታያቸው ማንነታቸውን ነገርኳት።

"ቤተክርስቲያን እየሄድኩ ነበር።" አለች ለግሩም በሚመስል አነጋገር።

"ይቅርታ በፍፁም አላየሁሽም ነበር!" አላት ቀጥሎ ከአፏ የሚወጣውን ለመስማት መጓጓቱ እያስታወቀበት።

"ከእጄ ላይ ሳንቲም ወድቆ እሱን ላነሳ ነበር!የመኪና መንገዱ መሃል መድረሴንም አላስተዋልኩትም ነበር።" አለች አሁንም ግሩምን እያየች .......ያቺ ያነሳኋት የአንድ ብር ሳንቲም ትዝ አለችኝ የዛን ቀን የቦርሳዬ ትንሽዬ ኪስ ውስጥ እንደከተትኩት ነው።

"የምሰራበት የነበረበት ሱቅ ባለቤት ስራ ልቀይር ነው ብሎ ሱቁን ዘግቶት ነበር። ስራ እየፈለግኩ እጄ ላይ የቀረው አንድ ብር ብቻ ነበር።" እንደነገሩ ቀለል አድርጋ እያወራችው ግን የሚጋባ መከፋት ነበረው ድምፅዋ

"በአንድ ብር ምን አደርግበታለሁ? ልጆች ሆነን ማሳደጊያ እማሆይ ወይኗ የምንላቸው እናት ነበሩ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያነቡልን ስለአንዲት ሴት ያነበቡልንን ሁሌ የማስታውሰው ነበር:: በሀገሩ የሚበላ ጠፍቶ ድርቅ በነበረበት ዘመን የቀራትን ትንሽዬ ዱቄት በውሃ ለውሳ ጋግራ ለነብዩ ስላበላች ሴት ..... ቃል በቃል አላስታውሰውም!ያላትን ለእግዚአብሔር አገልጋይ ሰጥታ እጇን አጣጥፋ ሞቷን ስለጠበቀች ሴት ........ ያለሽን የመጨረሻ እንጥፍጣፊ አልሰሰትሽምና ብሎ አምላክ ስለባረካት ሴት ....." ብላ ዝም አለች። የሁላችንንም ፊት ተራ በተራ ካየች በኃላ

"አላዋቂ ናት ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። የማደርገውን ሳጣ ያስታወስኩት ይሄን ታሪክ ነበር። በዛ ለሊት ተነስቼ ቤተክርስቲያን የምሄደው ያቺን የቀረችኝን አንድ ብር ለቤተክርስቲያን ሰጥቼ ልጄንም እኔንም እንደፈለግክ አድርገን ልለው ነበር። ከዛ ውጪ ምን ማድረግ እንደነበረብኝ አላውቅም ነበር። የማውቀው፣ ቸገረኝ የምለው ዘመድም ጓደኛም የለኝም ነበር።" ብላ አሁንም ዝም አለች። ማንም ምንም ለማለት አቅሙም ቃሉም አልነበረውም። ጉንጭሽ ላይ ካልተደፋሁ ብሎ መጣሁ መጣሁ የሚል እንባዬን መታገል ጀመርኩ። "አይዞሽ፣ እኔን!" ልላት እፈልጋለሁኮ ግን ቃል ከአፌ ከመውጣቱ በፊት እንባዬ እንደሚቀድም ስለገባኝ የባሰ ሆድ ላስብሳት አልፈለግኩም። ከሆነ ደቂቃ በኋላ

"አይዞሽ! ከአሁን በኋላ ቤተሰብ አለሽ! " አላት ማት እሷ ወደ እኔ አየች። ያን እንዳረጋግጥላት ይሁን አልገባኝም። የምለው ግራ ገባኝ እና እጇን ያዝኳት

"ከፈለግሽ ባባን በኋላ ከትምህርት ቤት ሲወጣ ላመጣው እችላለሁ!" ስላት ሳግ እያነቃት

"እሺ!" አለችኝ። ባባን እንደምትወስድብኝ ሳስብ የሆነ አንጀት የሚቆርጥ ህመም አለው ግን የመተው ዓይነት ህመም አይደለም...... ይከፋኛል ብዬ ያሰብኩትን ያህል አይደለም:: ልክ የሆነ ስሜት ሳይሆነው ልክ የሆነ ነገር ....... የሆነ በህመም ውስጥ ፈውስ ያለበት ነገር......

ይቀጥላል.......

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ደጋግመን በጣም ብዙ ጊዜ ተያይተናል።
'የሆነ ቦታ የማውቅህ መሠለኝ ፡ መልክህ አዲስ አይደለም' ብዬ ራሴው ወሬ ጀመርኩኝ።
ሙሉ መልኩን ሳላይ ፡ ማስክ አድርጓል ኮ
ይጠብቅ የነበረው አጋጣሚ ይመስል ፡
"አይገርምም? እኔም እያልኩኝ ነበር በውስጤ ፡ የት ነው የማውቃት? እያልኩ" አለኝ።
እዚህ አከባቢ ነህ?
አይ ፡ አይደለሁም።
እሺ እዚህ አከባቢ ነሽ? ምናልባት መንገድ ላይ ተያይተን ከሆነ?
ኧረ አይደለሁም።
(መንገድ ላይስ ብንተያይ አሁን ማን ይሙት እንዲህ አስታውሰው ያስታውሰኝ ይመስል ?
አልኩኝ በሆዴ።)
እዚህ ሀገር ነበርክ?
ኧረ በጭራሽ።
እዚህ ሀገር ሄደሽ ታውቂያለሽ?
አላውቅም ኧረ።
እዚህ አከባቢ ይሆን የማውቅሽ?
ወደዛም ሄጄ አላውቅም።
ok ፡ እከሌ የሚባል ወንድም አለህ?
ወንድም የለኝም ፡ እም ፡ ለቤተሰቤ ከሦስት ሴቶች በኋላ የተገኘሁ ብቸኛ ወንድ ልጅ ነኝ።
ምናልባት የሆነች የማውቃት እከሌ የምትባል ልጅ አለች፡ እሷን መስለሽኝ ይሆን ?
እኔ እንጃ ፡ እንደዛ የምትባል ሴት በእርግጥ አላውቅም። ምናልባት መልኬን እሷን መስሎህ
ይሆን?።
እንደዚህ የሚባል መስሪያቤት ትመጣ ነበር? ምናልባት እዛ ብዙ ሰው ስለሚመጣ እዛ
አይቼህ ከሆነ።
ኧረ እኔ የተሰማራሁት በዚህ ስራ መስክ ነው፡ ወደዛ አከባቢ መጥቼ እንኳን አላውቅም።
.
.
.
.
በመሀል ሰው መጣ እና ፡ እሱም ወደ ውጭ ወጣ ፡ ጥያቄዎቻችንን በእንጥልጥል ተውነው
፡ ምናምን።
ከነበርኩበት ለመሄድ ተነስቼ ወጣሁ ። ከርቀት ለየሁት ፡ የጊቢው በር አከባቢ ከሰዎች ጋር
ቆሞ ሲያወራ ተመለከትኩት። እሱም አይቶኝ እንደነበር የገባኝ፡ አይኖቻችን ሲገጣጠሙ
ፈገግ ብሎ ሲመለከተኝ ማስተዋሌ ነው። እያወራሁ የነበረውን ስልክ ዘግቼ ወደሱ አመራሁ
"ልትሄጂ ነው እንዴ?" ሲለኝ አዎን ፡ግን ነገ እመለሳለሁ አልኩት። ወደእኔ ቀረብ ብሎ
እንደሚተዋወቅ ሰው እቅፍ አድርጎኝ ፡ እከሌ እባላለሁ ሲለኝ ስሜን ብቻ ነግሬው ነገ
እመለሳለሁ ብዬው ተለየሁት። ትንሽ ተደነባብሬ ፣ ተንተባትቤ ስሜንም በአግባቡ
አልነገርኩትም መሠለኝ።
ቆይ ነገ ታምሜ ባልሄድስ?
እሱ አሞት ነገ ባይመጣስ?
ድንገተኛ ለቅሶ ያጋጥመው ይሆን?
በተለየ ነገር መንገድ ይዘጋ እና መምጣት አይችል ይሆን?
የምሄድበት ምክንያት ሌሊቱን አልቆ ብቀርስ?
ምናምን ምናምን እያልኩ ሀሳብ ገብቶኝ አደርኩኝ።
ሰው እንዴት ስልክ አይለዋወጥም? መች ነው ፋራ የሆንኩት?

መልካም ቀን ቤተሰብ

@wegoch
@wegoch
@paappii

#ጠርሲደ ከበደ
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #10

(የመጨረሻው ክፍል)

«ጥፋቱ የልጄ አይደለም። እራሷ ተንቀልቅላ ነው የገባችበት። ያን ሁሉ ብር መክፈላችን ልክ አይደለም! በዛ ላይ የዚህን ሁሉ ጊዜ የህክምና ወጪ ሸፍነናል።” ብለው የግሩም እናት ሀገር ይያዝልኝ ብለው ነበር መንቃቷን የሰሙ ጊዜ። ብዙ ጊዜ ነገር “ሁሉ ለበጎ ነው” የሚለው ቃል ያናድደኛል። የምወደው ሰው ሞቶ ወይ ታሞ ወይ የምሰራው ስራ ተበላሽቶብኝ ለበጎነቱ አይታየኝም። በእንዲህ ያለ ጊዜ ግን በጣም ፈገግ ብዬ ነገር "ሁሉ ለበጎ ነው!" እላለሁ።
ዶክተሩ 'ከዚህ በኋላ የመንቃት እድሏ ጠባብ ነው!' ያለን ጊዜ ነበር የሽምግልናውን ሂደት ያከናወነው። በሰዓቱ የሄለንን በህይወት ያለመኖር ታሳቢ አድርገን ባባ ትምህርቱን እስኪጨርስ ያለውን ወጪ ተምነው.... እናቱን ስለነጠቁት ካሳ እንዲሆን ተብሎ 500 ሺህ ብር ካሳ ስንጠይቅ የሄለን ያለመትረፍ አስደንግጧቸው ስለነበር በተለይ የግሩም እናት ሁለቴን አላሰቡትም ነበር። አባትየው የዛኔም 'ኡኡኡ ' ብለው ነበር። እቤት ሄደው ተማክረው (ቀልቤ እንደነገረኝ የግሩም ተፅዕኖ አለበት።) ብሩን ሊከፍሉ ተስማሙ። በባባ ስም በተከፈተ አካውንት ገንዘቡ በገባ በሳምንቱ ሄለን ስትነቃ ነው እንደአዲስ እሪሪሪሪ የሚሉት። እፊታቸው ፈገግታዬ ሲያመልጠኝ
"ሳቅሽ? ቱ! እንተያያለን! ገንዘቤን ትመልሷታላችሁ!" ብለው ተቀነጣጠሱ። ትልቅ ሰው ናቸውና መባለግ አልፈለግኩም ነበር ግን አበሳጩኝ። መጥተው 'ልጄ ከሚታሰር ቅበሪኝ!' ብለው እግሬ ላይ የወደቁ ሴትዮ የጭንቅ ቀናቸው ሲያልፍ ገንዘቤን ይላሉ?
"አስገድደን አላስፈረምኖትምኮ ፈቅደውና ጊዜ ወስደው አስበው የወሰኑት ውሳኔ ነው። በሽማግሌ በምስክር ፊት ተስማምቻለሁ ብለው ያደረጉት ነው። አይ ካሉ ይክሰሱኝ!" አልኳቸው ትቻቸው እየሄድኩ።
"ፀሎቴን ሰምቶኛላ! እግዚአብሔር ፀሎቴን ሰምቶኛላ? ጥሎ አልጣለኝም!" ነበር ያለችው ሄለን ከእንባ ጋር የምትይዘው አጥታ እየተቅበጠበጠች ምን ያህል ገንዘብ እንደተካሰች ስነግራት።
ከሆስፒታል የወጣች ቀን ቅዳሜ ቀጥታ እነእማዬጋ ነበር የመጣችው። ምሳ ተዘጋጅቶ። አባዬና እማዬ 'ጥሩ ሃሳብ አይደለም!' ብለው ነበር። እቤት ከገባችም በኋላ አሁንም አሁንም የእኔን ስሜት ይፈትሻሉ። ሄለን የሆነ ቀን ሆስፒታል ልጠይቃት ባባን ይዤ በሄድኩበት ባባ ስለእህቱ እየደጋገመ ሲያወራ ልጄ እንደሆነች እና የባባ እህት እንደሆነች ከነገርኳት በኋላ ብዙም አላወራችም። እነአባዬ ጥሩ ሀሳብ አይደለም ያሉት የገባኝ የልጄን ሁኔታ ሳይ ነው። ቃል አውጥታ ምንም ባትናገርም። ነገረ ስራዋ ሄለንን እንዳልወደደቻት ያስታውቅባታል። እንድትነነግረኝ ብወተውታትም 'ምንም' ከማለት ውጪ አትመልስም። ምናልባት አባቴን የወሰደችብኝ ሴት ናት ብላ ፣አሁን ደግሞ ተላምዳው ቀኗን በፍካት የሞላላትን ሁሌ እንዲኖራት ትመኘው የነበረውን ወንድሟን ልትወስድባት መሆኑ፣ ልታስበው ትችላለች ብዬ የማስበውን አስባለሁ።
"መጀመሪያ ላይ ማግባቱን አላውቅም ነበር።" አለችኝ ሄለን የምሳው ግርግር አልቆ እኔና እሷ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ልጆቹ ጊቢ ውስጥ ሲተረማመሱ እያየን።
"አረብ ሀገር ከሄድኩ በኋላ በህይወት ለመኖር ፣ ለመስራት የምጓጓ የነበረው ተመልሼ መጥቼ ከእርሱ ጋር ለመሆን ነበር። ሌላ ምንም የምጓጓለት ነገር አልነበረኝም። ሰርቼ ብር አጠራቅሜ ከእርሱ ጋር ህይወት መጀመርን ሳስብ ነበር ማታ ተኝቼ ጠዋት ለመንቃት የምጓጓው። ህይወቱ የተበለሻሸው ለእኔ ብሎ ነው። ለእኔ ብሎ ባይሆን ይሄኔ የት በደረሰ። ታውቂያለሽ ሁሌም እድለ ቢስ ነበርኩ! ሁሌም መኖር ጀመርኩ ስል የሚገድለኝ አጋጣሚ ይፈጠራል። ታመምኩ። ህመሜ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ያጠራቀምኩትን ገንዘብ በህክምና ጨርሼ። ከነህመሜ ተጠርዤ ወደሃገሬ ስመለስ በመከራ ነበር አስፈልጌ ያገኘሁት።" ብላኝ ዝም አለች።
ጊዜውን አስታውሰዋለሁ። በህይወቱ ውስጥ አንድ የፍቅር ታሪክ ብቻ ያለው ሰው እንዴት የዚያን ታሪኩን ገፅ እያንዳንዱን ቀኑን ሊረሳ ይችላል? ተጋብተን በሰባተኛ ወራችን አካባቢ ነው።
ከስራ ስመጣ የእንጨት ብናኝ የለበሰውን የስራ ልብሱን ሳያወልቅ ሳሎን መመገቢያ ጠረጴዛው ጋር የእናቱን ሞት የተረዳ መስሎ ቅስስ ብሎ ተቀምጦ ነበር። ሁኔታው አስደንግጦኝ ኮቴን አውልቄ እየወረወርኩ
"ምን ሆነሃል? ምን ተፈጠረ? ንገረኝ ምን ሆነሃል?" እያልኩ ስወተውተው ቆይቼ
"ሄለን ብዬ የነገርኩሽን ልጅ ታስታውሻታለሽ? ማሳደጊያ ..... " ብሎ ሳይጨርስ አስታወስኳት።
ስለማሳደጊያው ሲያወራ ፊቱ በፈገግታ የሚፈካው ስለእሷ እና ስለእማሆይ ሲያወራ ብቻ ነበር። ያለችበትን ለማወቅ ፈልጎ ሊያገኛት ያልሞከረው ሙከራ አልነበረም። ከአረብ ሀገር መጣሁ ያለች ሴት ባገኘ ቁጥር እንደቂል ያውቋት እንደሆነ ይጠይቅ እንደነበር አስታውሳለሁ። በኋላ ላይ ተስፋ ቆርጦ ፍለጋውን ተወው። 'የሆነ ነገር ሆና ቢሆንስ?' ብሎኝ ያውቃል። እሷ ላይ በሆነው ነገር ሁሌ ራሱን ይወቅስ ነበር። 'ልጠብቃት ቃል ገብቼላት ነበር። ብቸኛ ቤተሰቤ እሷ ነበረች። እኔ በህይወት እያለሁ ማንም እንደማይጎዳት ቃል ገብቼላት ነበር። የማንም ባለጌ ሲደፍራት እንኳን ልጠብቃት አይዞሽ ብዬ ላባብላት እንኳን አጠገቧ አልነበርኩም' ነው ያለኝ ታሪኩን የነገረኝ ጊዜ
"ታማ ከአረብ ሀገር ተመልሳለች። ሆስፒታል ናት!" አለኝ።
"በእማዬ ሞት! ደህና ናት? ማለቴ ምንድነው ህመሟ? ትድናለቻ?" አልኩት አተካከዙ መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነች ለመገመት አይከብድም ነበር።
"አትድንም! ህክምናው ያለው አንድ የግል ሆስፒታል ነው። እሱም በትንሹ 430 ሺህ ብር ያስከፍላል። ድጋሚ ስትሞት ዝም ብዬ ላያት ነው።" ብሎ ሲሆን አይቼ እንደማላውቀው ደም ስሩ ተገታትሮ ነፍሱ ጣር ላይ ያለች ሰው መሰለ።
"መላ እንፈልጋለን! ከቢሮም ቢሆን እበደራለሁ! ወይም ከአባዬ እበደራለሁ! የሆነ መላ አይጠፋም! ብቻ ትዳን እንጂ የሆነ ነገር አይጠፋም!" ብዬ አባበልኩት። አባቴን ዋሸሁት! ቤት ልንገዛ ብር አንሶን ነው ብዬ አባቴን ዋሸሁት። እማዬን የምታልመው እስራኤል ሊወስዳት ብሎ ለዓመታት ያጠረቃመውን ገንዘብ አንስቶ ሰጠኝ። ብሩን ሰጥቼው ሳውዝ አፍሪካ ለስድስት ሳምንት ስልጠና በቢሮ ተልኬ ሄድኩ። ደስተኛ ነበር። 'የእህቴን ህይወት ነው መልሰሽ የሰጠሽኝ' ነበር ያለኝ። ከስልጠና ስመለስ ህክምናዋን ጨርሳ ወደቤት መግባቷን ሲነግረኝ ልጠይቃት በተደጋጋሚ እቅድ አውጥቼ አውቅ ነበር። አሁን ሳስበው ምናልባት እንዳገኛት እሱ ስላልፈለገ ይሆናል ብቻ ተሳክቶልኝ አያውቅም ነበር።
"ብሩን ከየት አምጥቶ እንዳሳከመኝ ያወቅኩት ቆይቶ ነው። እኔጋ ያለው ስሜት እሱጋም ያለ ይመስለኝ ነበር። ተሽሎኝ ከሀኪም ቤት የወጣሁ ጊዜ ለእኔና ለእሱ ብዬ ብር አጠራቅሜ እንደነበር ስነግረው ከታናሽ እህትነት ውጪ እንደሌላ እንደምንም እንደማያየኝ ነገረኝ። ማግባቱንና የታከምኩበትን ብር አንቺ እንደሰጠሽው ነገረኝ። አላመንኩትም ነበር። ምንም ስሜት ባይኖረው ማግባቱን ለቀናት አይደብቀኝም ነበር ብዬ አሰብኩ።" ብላ ስሜቴን ለማጣራት በሚመስል አየት አድርጋኝ ቀጠለች::
"....ወደላይ ወደታች ብታዪ ወደግራም ወደቀኝም ብትዞሪ አይንሽን የምታሳርፊበት አንድ ነገር ብቻ ኖሮሽ ያውቃል? ሊያውቅ አይችልም!" አለችኝ ዙሪያ ገባችንን እየቃኘች። ማት ባባን እና የሱን ልጆች ጨምሮ ሳሩ ላይ እየተንከባለለ እያጫወታቸው ፣ የማት ሚስት የእማዬን ፀጉር እያበጠረችላት፣ እቤት ውስጥ አባዬና የኔ ልጅ በሆነ ነገር እየተከራከሩ ድምፃቸው ይሰማል። ቀጠለችና
"ልጅነቴ፣ እድገቴ፣ ተስፋዬ፣ ፍቅሬ፣ ቤተሰቤ፣ የወደፊት ትዳሬ ብዬ በልቤ የተሸከምኩት እሱን ብቻ ነበር። ማግባቱን የነገረኝ ቀን ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ። እሱ ጭራሽ ከዛ በኋላ ለሳምንት አይኔንም ማየት አልፈለገም። የምኖርበት ምክንያትም ተስፋም አልታይሽ አለኝ። የሆነ ቀን ማታ ራሴን ላጠፋ ሞከርኩ። እድለ ቢስ ነኝ አላልኩሽም? ሞት እንኳን እንደደህና ነገር ራሱን አዋደደብኝ! ለመሞት ይታይሽ? ሰው እንዴት ሞት እንኳን አይሳካለትም? ተረፍኩ!! ተደውሎለት መጣ! "
እሷ እየነገረችኝ ቀኑን በእርግጠኝነት አስታወስኩት። ማታ 3 ሰዓት አካባቢ ስልክ ሲደወልለት ደንግጦ ከተቀመጠበት ሲስፈነጠር። "አብሮኝ የሚሰራው ልጅ ራሱን ሊያጠፋ ሞክሮ ሆስፒታል ነው!" ነበር ያለኝ።
የዛን ቀን ባልደረባዬ የስራ እድገት አጊንቶ እራት ተጋብዘን ሄደን "ስራህ ምንድነው?" ብለውት በዛ ሳቢያ ተጨቃጭቀን ነበር። 'ሁልጊዜ ላንቺ ትንሽ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ .... ሱፍ ለብሰው ለሚውሉ የስራ ባልደረቦችሽ እንጨት ስፈቀፍቅ ነው የምለው ብዬ አንቺን ላሳፍርሽ አልፈልግም!' ብሎኝ ተናድጃለሁ። ሱፍ ለበሰ የስራ ቱታ ለእኔ ለውጥ እንዳልነበረው ያውቅ ነበር። ሱፍ ለባሽ ከሚላቸው ማናቸውም ለደቂቃ ሀሳቤን ሰርቀውት እንደማያውቁ ያውቃል። ብቸኛ ምርጫዬ እንደሆነ ያውቃል። ብቸኛ በፍቅር የማውቀው ወንድ መሆኑንም ያውቃል።
እስከዛ ቀን ድረስ ሙያውን እንደሚወደው ነበር የማውቀው። የራሱን ፈርኒቸር ቤት ሊከፍት የሚያስፈልጉትን ማሽኖችና ጥቃቅን ወጪዎች መዝግበን አስቀምጠናልኮ! ትምህርቱን ቢጨርስ ደስ ይለው እንደነበር የነገረኝ ቀን እኔ አሁን እየሰራሁ አንተ ተማር እና አንተ ስትጨርስ ደግሞ በተራህ ማስተርሴን ታስተምረኛለህ ብዬው ነበር። ምንም መከፋት ባልነበረው ስሜት ነበር የሚፈልገው ፈርኒቸር ቤቱ ላይ መስራት እንደሆነ የነገረኝ። በእንዲህ ጭንቅላቴ በተሰፋበት ሰዓት ነበር ስልኩ የተደወለው። ሆስፒታል ሊያድር እንደሚችልም ሲነግረኝ ምናልባት እሱም እንደእኔ መጨቃጨቃችን ረብሾት ጊዜውን በዛውም ፈልጎት ይሆናል ብዬ ከማሰብ አልዘለልኩም። አብጠርጥሬ የምጠይቅበት ጥርጣሬ አልነበረኝም።
"እርሱ የሌለበት ህይወት መኖር እንደማልፈልግ ስነግረው 'እሷስ?' ነበር ያለኝ አንቺን 'በህይወቴ ማንም ሰው ያልሰጠኝን ክብርና ፍቅር ነው የሰጠችኝ። በምን ጥፋቷ ልቅጣት?' ነበር ያለኝ። የእውነቴን ነበር። እርሱ ከሌለበት የመኖር እንጥፍጣፊ ፍላጎት አልነበረኝም። ለሊቱን ሙሉ ያደረግሽለትን የሆንሽለትን እየነረኝ ነበር ያደረው። በየቀኑ እንደምንገኛኝ ነግሮኝ ድጋሚ ራስ ማጥፋቱን እንዳልሞክረው ቃል አስገብቶኝ ጠዋት ሄደ።
ያኔ ያላስተዋልኳቸውን እና ባስተውላቸውም ከዛን ቀን እራት ጋር እያያዝኩ ምክንያት የሰጠኋቸውን ለውጦቹ ምክንያታቸው ተገጣጠመልኝ። ከዛ ቀን በኋላ ተነጋግረን የተስማማን የመሰለኝን ልጅ የመውለድ ጉዳይ አንስቶ አላስፈላጊ ብስጭት እየተበሳጨ 'እኔ የሚሰማኝ ስሜት አይገባሽም!' ብሎኛል። 'አንቺ በፍፁም አትረጂኝም' የዛን ሰሞን ዜማው ሆኖ ነበር:: በትንሽ በትልቁ ይነጫነጭ የነበረው ጥሎኝ ለመሄድ ምክንያት እንድሰጠው የሚሰማውን ፀፀት ሊቀንስ መሆኑ ሳይገባኝ ልጅ ስላልሰጠሁት ነው ብዬ አምኜ ነበር ለማርገዝ የወሰንኩት።
በአንድ ጊዜ ቅናትም ጥላቻም ቁጣም እልህም ቁጭትም ..... አንድ ላይ የሚሄዱ ስሜቶች መሆናቸውንም እንጃ ብቻ ውስጤን ሞልተው ፊቴ ላይ ሲንቀለቀሉ እሷ እንኳን አይታዋለች። መበለጥ .....መታለል .....መከዳት ....መሸነፍ...
"ውደጂኝ አልልሽም ግን አትጥዪኝ። እኔ ህይወት ራሷ የቀጣችኝ ሰው ነኝ። እኔን ስለመረጠ እንደበለጥኩሽ ታስቢያለሽ? ያውም እኔ ከምሞትበትና አንቺ ከምታዝኚበት ምርጫ ሰጥቼው? በጥሩነትሽ በልጠሽኛል። ጊዜ አምጥቶ ከነልጄ እጅሽ ላይ ጣለኝ አይደል? ይበልጥ ቅጣቱ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? አሁንም ማን እንደሆንኩ እያወቅሽ ደግ መሆንሽ? እሱ ይበልጥ ያማል።" ብላኝ ዝም አለች::
"አንዳንዴ የክፋቴ ውጤት ነው ብዬ አስቤ አውቃለሁ:: በመጨረሻ ተደላድዬ እግዜር ታርቆኛል ብዬ መኖር ስጀምር ያ ከይሲ መጣ!! የእግዚአብሄር ቁጣ ካልሆነ በከተማው ከሞላው ሱቅ እኔ ሱቅ ምን ያደርጋል? እድሌ ሲከፋ እንጂ ካልጠፋ ሰዓት አሹ ሊወስደኝ እዛው በቆመበት? .... በአንድ ቦክስ ከግድግዳ ጠርዝ ተጋጭቶ ሰው ሞቶ ያውቃል?? ለኔ ሲሆን የማይገጣጠም ነገር የለም!....... ከዛሬ በኋላ አይኔን ማየት ካልፈለግሽ ከነልጄ ከህይወትሽ እወጣለሁ እመኚኝ አደርገዋለሁ። " ብላኝ እንባዋን እንዳላይባት ዞረች::
"በልብሽ ትንሽዬ ርህራሄ ከተረፈሽ ግን እባክሽ ባባ ከእህቱ ጋር ይጠያየቅ። ለእኔ ብለሽ አልልሽም ለባባ እንዴት እንደምትሳሱለት አይቻለሁ። ይሄን ተስፋውን ይሄን ፍቅር አታሳጪው" ብላኝ መልሴን ሳትጠብቅ ወደውስጥ ገባች።

ከዛ ሁሉ እንደእሳት ከሚንቀለቀል ስሜትጋር ሀዘኔታስ ሲደባለቅ የጤነኛ ሰው ስሜት ነው? ባባ ትምህርቱ እንዳይስተጓጎል በሚል ለትምህርት ቤቱ የሚቀርብ ቦታ ቤት ተፈልጎ እቃዎቿ ተጭነዋል። ሲመሽ ተሰናብታን እና አመስግናን ልትሄድ ስትነሳ ባባ ሁላችንንም ለጤንነት ያልቀረበ ስሜት ውስጥ ከተተን። አንዴ የእህቱን እጅ ይዞ አብራው እንድትሄድ ያለቅሳል። ደግሞ መለስ ብሎ የእናቱን እጅ ይይዝና እንድትቀር ይወተውታል። እላዬ ላይ ተንጠልጥሎ 'መላ በዪኝ!' አይነት ተቁለጨለጨ። እናቱንም እኔንም እህቱንም ማንንም መምረጥ ቸገረው። አባዬ ላለማየት ሳሎኑን ለቆ ወጣ። የነበረኝ ቅጥ አንባሩ የጠፋ ስሜት ላይ ባባ ሊሄድብኝ መሆኑ አተረማመሰኝ:: ማት ሁሉንም ተቆጥቶ
"ምንድነው የማንገናኝ ነገር አደረጋችሁት። የአንድ ታክሲ ርቀት ላይ ናቸውኮ!" ብሎ ሁሉንም አረጋጋ። ለባባ 'ነገ እንገናኛለን! ብለን አባብለነው ሄዱ።
"እውነትሽን ነው? ነገ እንገናኛለን ያልሽው?" አለችኝ ልጄ
"ወንድምሽ አይደል? ልታገኚው በፈለግሽ ሰዓት መሄድ ትችያለሽ! እሱም መምጣት ይችላል።" ስላት ራሴን ሰማሁት። መጥታ አቀፈችኝ። የሚሰማኝን ስሜት ለይቼ እንኳን ሳልረግብ
"አባቴጋ መሄድ እፈልጋለሁ" ብላ ድንጋጤ አከለችልኝ። ድጋሚ አሸናፊን ላየው መዘጋጀቴን እርግጠኛ አልነበርኩም!! የዛን ቀን የማስበው ምን እንደሆነ እንኳን አላውቅም አንዱን ሀሳብ ሳነሳ ሌላውን ስጥል ነጋ! ከቀናት በኋላ ግሩምጋ ደውዬ ሸዋ ሮቢት ሊያደርሰኝ ይችል እንደሆነ ስጠይቀው
"ድሮም ከአማትሽ ጋር ንትርክ ስትጀምሪ ልትጀነጅኚኝ እንዳሰብሽ ገብቶኛል" ብሎ ቀለደብኝ። ከእናቱ ጋር በገንዘቡ ዙሪያ መነጋገራችንን ነግረውታል ማለት ነው።
ሳየው የምናደድ ፣ የምተክን ፣ እንባ የሚያንቀኝ፣ ብዙ ነገር የምለው ነበር የመሰለኝ። እንደዛ አይደለም የተሰማኝ። ዝም ያለ ስሜት! ምንም!ከልጁ ጋር ብቻውን እንዲሆን ትቼው ከግሩም ጋር ርቀን ቆምን።
"አንቺን እስካገኘሁበት ቀን ድረስ እንዳንቺ አይነት ቅን ሰዎች እንደዳይኖሰር ከምድር የጠፉ ነበር የሚመስለኝ። ክፋት፣ ፉክክር፣ ጥሎ ማለፍ ዓለምን በዝቶ እንደልክ ተቆጥሯል። መልካምነት ፣ ለሌላው ቅድሚያ መስጠት፣ መከባበር .....ቂልነት እየመሰለ መጥቷል። ፌቨን የምሬን ነው አንቺ እጅግ መልካምና ቅን ሰው ነሽ። በዚህ ደስ ልትሰኚ ይገባል። ግን ሰውን ከምትወጂው ከፍ አድርገሽ ራስሽን ውደጂ፣ ሌላውን ከምታከብሪው ከፍ አድርገሽ ራስሽን አክብሪው፣ ያኔ አልፎ ሂያጅ የሚሰብረው ልብ አይኖርሽም!" አለኝ ዓይኖቹ ርቀው እነአሸናፊን እያዩ
"አንተም ብትሆን ማለት ነው?"
"ዝግጁ ነኝ እያልሽኝ ነው?"
"አምነሽ ካልሰጠሽ ያክምሽ ያቁስልሽ በምን ታውቂያለሽ?" አላልከኝም? በስሱ ፈገግ አለ። ያልቸኮለ ፈገግታ .......
የምላችሁ ........ጨርሰናል።

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ቁንጅናዋ ብዙ ሰው የሚስማማበት አይነት ነው ። ቆንጆ እንደሆነች ታውቃለች ፤ ግን ቆንጆ
ስትባል ደስ ይላታል።
ሴት ልጅ በየትኛውም እድሜ ቆንጆ መባልን አትጠላም ። ሴት ልጅ መደነቅ ድክመቷ ነው
መሰለኝ። በእርግጥ መደነቅ እና ትክክል መባል የሰው ሁሉ ድክመት ይመስለኛል።
ምንም እንኳን የገላዋ አሰራርም ለአድናቆት እንዲመች አድርጎ ያበጃጃት ቢሆንም
ሴቶች በሚወዷቸው እንደማይጨክኑ ፤ ኤልዳና እኔን እንዳላገኛት መንገድ አለመዝጋቷ
ምስክር ነው ።
እኔ ሞኝ የምባል አይነት ሰው ነኝ መሰለኝ። ለቀልድ እንኳን ሞኝ ስባል አራስ ነብር
የምሆነው ፤ በቃ ክፍ....ት ነው የሚለኝ ።
ሞኝነት ድክመቴ ባይሆን ሞኝ ስባል እስቅ አልነበር ? አሁን ቀጫጫ አይደለሁም ፤ ቀጫጫ
ብባል ግን እስቃለሁ እንጂ አልናደድም ስለዚህ ሞኝ ነኝ ማለት ነው እላለሁ ፤ አንዳንዴ
ደግሞ እንደዚህ ከተመራመርኩ እኮ ሞኝ አይደለሁም እላለሁ
ዘይገርም
አንዳንዴ ሰዎች ጭንቅላቴ ስል ሲሆንባቸው ትኩር ብለው ያዩኛል ። በቂላቂልነቴ save
አድርገውኝ ባይሆን ኖሮ እንዴት እንደዚህ አሰበ ብለው ሲገረሙብኝ አይናቸው ላይ መች
አስተውል ነበር !?
ሰው ድክመቱን ባያሻሽለው እንኳን ጥንጥም ይገባዋል ማለት ነው ፤ ያ ማለት ደግሞ he
might be denying the hard fact deliberately ።
ኤልዳና ጋ ብዙ ቀን እደውላለሁ ፤ ኤልዳና ሲሻት ብቻ ስልኬን ታነሳለች ። ከደወለችልኝ የሆነ
ነገር ፈልጋ ነው ።
ቢሆንም ደስስ ይለኛል
ኤልዳና ከእኔ ጋ ስታወራ አወራሯ ፆታዊ ነገር የለውም ፤ መሽኮርመም ሆነ ደርባባነት
አይታይባትም ፤ ምንም ፆታዊ ፍላጎት ስለሌላት ይሆን ?
አላውቅም !
አግኚኝ ስላት ሀገር እንደምታስተዳድር አይነት ነው ባተሌ መሆኗን የምትነገርኝ። የግል
university እያስተማርኩ ፤ ትልቅ ፕሮጀክት እየመራሁ እኔ እንኳ እንደእሷ ስለመባተል
አላወራም ።
ተሳክቶልኝ ኦር ፈልጋኝ ያገኘችኝ ጊዜ...
ነፃ መሆን አልችልም ፤ አክብጄ ስለማያት ጨዋታ አይመጣልኝም ።
ባገኘውት አጋጣሚ ቀልቧን ለመሳብ እባዝናለሁ ።
በቃ እዛው ከእኔ ጋ እያለች ከሌላ ሰው ጋ ስልክ ታወራለች ። ፊቴ ለምታወራው ወንድ ሲሆን
ደግሞ ደርበብ እሽኩርምም ስትል አስተውላለሁ ፤ሞኝ ስለምመስላት ይሄን የምረዳ
አይመስላትም ወይም ሳይታወቃት በደመ-ነብስ ነው ሁኔታዋ እና አነጋገሯ የሚቀየርባት ።
አንዳንዴ 'ለምንፈልገው ነገር አድራጎታችን ከእውቅናችን ውጪ ይሆን የለ' ።
ትንሽ ለመጫወት እሞክራለሁ ፤ ቀላል ወሬ ታወራልኛለች
ከዛ
የማይመለስ ብር ትበደረኛለች ፤ ከዛ እንቅ አድርጋ ትስመኛለች ደስስስስስ ይለኛል።
ጓደኞቿ ጋ ሆና ካገኘኋት በጣም እንደምወዳት እሷ ደግሞ ከምንም እንደማትቆጥረኝ ፤
ለብቻቸው የነገረቻቸውን በማስረጃ እያጣቀሰች እና እየቀለደችብኝ ታሳየቸዋለች ፤ እነሱ
ደግሞ አምነንሻል ፤ ገብቶናል ለማለት ያሽካካሉ።
አሁን እንደው የሚወደን ሰው ላይ እማኝ አስቀምጦ ማልመጥ ምን የሚሉት ስልጣኔ
ነው?? !!
ኮትህን የት ገዛኸው አለቺኝ አንድ ጓደኛዋ ሽሙጥ እንዳልሆነ እንዳያሳብቅ ፊቷን
እየተቆጣጠረችው
አይን አይዋሽ አይኗ ያስታውቃል ፤ ለበኋላ
የሚሆን ቧልት እያድቦለቦለች ነው
ዝም አልኳት
አሁን ሰው መርጦ እና ወዶ በለበሰው ኮት የለበሰው ሰው ፊት ማላገጥ ትክክል ነው??
ጓደኞቿ እኔ ላይ ያላቸውን ንቀት ወላጇ
የምወዳት ኤልዳና መሆኗን ነጋሪም መስካሪም አያስፈለገኝም
ተሰብስበው ሳገኛቸው ከሚጨንቀኝ ነገሮች አንዱ እጄን የት እንማደርገው ነው ። ኪሴ
ውስጥ እከተዋለሁ ወይ አጣምራለሁ ፤ አልያም የግራ አና የቀኝ ጣቶቼን አቆላልፋለሁ ፤
በእሱ ራሱ ይቀልዳሉ ።
ፍቅር ተአምራዊ መሆኑ ማሳያዬ
ይሄ ሁላ እየገባኝ አለመሸሼ
እኔ ለእሷ ክፉ አይደለሁ ። ከሁሉም ሰው በላይ ስለምወዳት አይደል የተበደረችኝን
እንደረሳሁ ሆኜ ሌላ ቀን እንደገና የማትመልስልኝን ገንዘብ የማበድራት ፤ ለዛውም ላይ ታች
ብዬ የማመጣውን ገንዘቤን !!
መውደዱ የእውነት እንደሆነ የሚታወቅ ሰው ላይ ይሾፋል???
ሰው ላይ መቀለድ አራድነት ነው ???
ስለማታውቀኝ ነው እኮ
ማጣጣል እንደማይጥለኝ ፤ ስንቴ በትግሎቼ እንደወደቅኩ ፤ ወድቄ ሳለሁ ቆሜ
ስለምታገለው እንደማሰላስል !
ለዚህ ነው ይሄ ሁላ ነገሯ እየገባኝ
ጊዜ ሃያል ነው ፤ አይኗ ሲከፈት ሞኝነቴ ጥበብ እንዳለው ትረዳለች ብዬ መጠበቄ።
የድንቁርናዋ ምንጩ አለማስተዋል እንደሆነ የምረዳላት።
ከብልግናዎቿ መሃል መልካምነቷን ለራሴ እንደምነግር አልገባትም ።
ክፉ ቀን ቢመጣባት አብራ ከምታላግጥብኝ ጓደኞቿ የበለጠ እንደምረዳት ፤ ከአጠገቧ
እንደማልጠፋስ አልገባትም ።
ሰው በረከቱ ላይ እንዴት ያላግጣል ? መወደድ በረከት አይደለምን?
ፍቅር የሚወዱንን ብቻ መውደድ አይደለም ።
ለዛ ነው የምወዳት። የቀን ጉዳይ ነው እንጂ ፍቅሬ አንድ ቀን ይጋባባታል ።
ያ አንድ ቀን እንዲመጣ
ትላንት ባልሞከርኩት መንገድ መምጣት አለብኝ ። ለተመሳሳይ አወዳዳቅ ተመሳሳይ
የአተጋገል ስልቶች ምክንያት ናቸው ። ጥበብ ማለት የሚፋለመንን መረዳት ብቻ ሳይሆን
መቅደምም ጭምር ነው። ከትላንት የተሻለ ውጤት መጠበቅ ያለብኝ ትላንት በሄድኩበት
መንገድ ካልመጣሁ ብቻ ነው ።
ማስታወሻ ፦
እጅ መስጠት ውስጥም ደማቅ ድል አለ!!!

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Adhanom Mitiku
(ፋራ ነኝ)

በመሊኩ [ MAJNUN ]

ከወሎ ኮምቦልቻ 23 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የምትገኘው ደሴ ከተማ ከኢትዮጲያ ቀደምት ከተማዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ነች፡፡ ኮምቦልቻም ያው ስሟ እንደ ደሴ ባይገንም ቀደምትነቷ እና ድሙቅነቷ እሙን ነው፡፡ ከጂኦግራፊ ቀረቤታዊ አቀማመጣቸው እና ከማህበራዊ ስሪታቸው ፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚ ትስስራቸው አንፃር መንትዮቹ የሚል ቅፅል ስምም ተችሯቸዋል፡፡ ባንድም በሌላም መልኩ ግን የደሴ ስም ከኮምቦልቻ ይልቅ መናኘትን ተጎናፅፏል፡፡ አንዳንዶች ለደሴ ድምቀት እኛ ወሎዬዎች "የወሎ ሀፍረት"!! ብለን ስሙን ልንጠራው የማንሻውን የልጅ ሚካኤል(ራስ አልይ/መሀመድ አልይ) መንበር መቀመጫ መሆኗን እንደ አንድ አመክንዮ ያነሱታል፡፡

ብቻ ከድሮ ጀምሮ ደሴ የወሎ መዲና ነበረች፡፡ ባሁነኛውም የፌደራሊዝም ስረዐት ከወሎ መዲናነቷ ዝንፍ ሳትል እንደ ደመቀች ፣ ተጀብና ተከሽና ፣ አለች፡፡ ወደ ወሬዬ ልመልሳችሁ... ጁመዐ ማለዳ ከኮምቦልቻ ወደ ደሴ መንገድ ትራንስፖርት የሞተር ሳይክል ታርጋ ለማውጣት ማልጄ ወጥቻለሁ፡፡ ያው የደቡብ ወሎ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ገዘፍ ያሉ መንግስታዊ እና ግለ-ሰባዊ ድርጅቶች መገኛም ነች፡፡ ከተለያዩ የወሎ ክፍለ ሀገሮች ግልጋሎት ለማግኘት ብዙ ሰዎች ስለሚመጡ ጉራው (ወረፋው) እንደ አንቻሮ ገበያ ደመቅቅቅቅቅ ይላል፡፡ በዛ ላይ መመላለስ ከያዝኩኝ ሳምንት ሆኖኛል፡፡ ለዛም ነው የደሴን ብርድ ሳልፈራ ማልጄ የወጣሁት፡፡ ብዙ ሰዉ ከሩቅ ሀገር ስለሚመጣ ላለመቆየት እና ላለመስተጓጎል ሲል ሙስና እየሰጠ ጉዳዩን ያስፈፅማል፡፡ እንደ እኔ አይነቱ ደረቅ አራዳ ደግሞ ሳምንት ታሽቶ ይሸኛል፡፡ ያም ገዱ ካማረ ነው፡፡

አቤት በየመስሪያ ቤቱ ያለ ሙስና እና ዘረፋ!! አሁን አሁንማ የምግቤት ስጋ ቆራጮችም ሳይቀር ሙስና ለምደው ደምበኛ ለይተዋል፡፡ ስጋ መብላትን በረጅም የእቅድ ፕላት ፎርሙ አካቶ በወር አልያም በአመት አንዴ የሚበላን ገሚስ ሀበሻ ሙስና ያልከፈለ እንደሁ አንጆ እና ጣንፊያ ያቀርቡለትና ከአንጆና ጣንፊያው ጋር የስጋ ቆራጩን ስጋ በልቶ ይወጣል፡፡ ብቻ በኛ ሀገር ውስጥ የሙስና እና የዶላር እድገት እንደ ፈረንጅ ልጅ ሆኗል፡፡ ኧረረረ የደሴ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ግን ይለያል፡፡ ደግሞ እኮ የሚገርመው ካንዱ የግድግዳ ጥጋት ከመስሪያ ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ዝርዝር ዝቅ ብሎ "በግርግር ውስጥ ኪስዎን ከሌባ ይጠብቁ" ፣ "ሙስናን በጋራ እንከላከል" ብለው ለጥፈዋል፡፡ ህህህ ቀልዳቸው እኮ አይጠገብም፡፡

አንዱ ሰራተኛ ከሰኞ ጀምሮ ጥርሱን ስሎ ሊበላ ሲያሰባኝ...ሲያሰባኝ ነገ ዛሬ እያለ ይሄው ሳምንቴ መጣ፡፡ በመጨረሻም ምርር ብሎኝ ወደ አለቃው ይግባኝ ብዬ ሄድኩኝ፡፡ አለቃውም ከኔ ሀልጋ ከፍ ከክላሴ ዝቅ ያለ ተሽከርካሪ ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ "ምን ልርዳህ"? አለኝ የነፍሰጡር ሆድ የመሰለ ቀፈቱን እያሻሸ፡፡ ካነጋገሩ የወደላይ ሀገር ሰው (ጎጃሜ) ይመስላል፡፡ ኧረ እንደው ጌታዬ እባክዎትን ቢሮ ቁጥር 8 ካሰሩት ጅብ ያድኑኝ፡፡ እእእ ... ማለቴ ቢሮ ቁጥር ስምንት ያለው ባለ ሙያ ከስራ ዲስፕሊን ውጭ የሆነ አላግባብ ክፍያ ካላመጣህ ብሎ እያስተጓጎለኝ ነው አንድ ይበሉልኝ፡፡ አልኩኝ ሙስና ማለት ፈርቼ፡፡ "እህ እህህህ" ብሎ ጉሮሮውን ጠራርጎ ከተገደፈበት ወንበር ቀና አለና እሺ እንግዲህ ችግር የለውም፡፡ ወደዚህ መምጣትህ ጥሩ አድርገሀለል፡፡ አሁኑኑ ባስቸኳይ ቶሎ እንዲሰራለህ አደርጋለሁ፡፡ እንደውም ልደውልለት ብሎ ስልኩን አንስቶ መታ "ለካ ከጅቦች መንጋም እንደዚህ አይነትም ቀና ሰው አለ" ብዬ በእዝነ ህሊናዬ ስብሰለሰል "እህእህህህእ" ብሎ በዳግማዊ ጉሮሮ ጥርጊያ ከሀሳቤ መለሰኝ፡፡ እሺ ይሄው ደውዬለታለሁ፡፡ በቶሎ ይሰራልሀል አለኝ፡፡ ከተቀመጥኩበት ወንበር ተነስቼ ለቀናነቱ አላህ ይስጥልኝ ብዬ አመስግኜ ልወጣ ስል ሰልሶ ጉሮሮውን ጠራረገና ታዳ የደንቡን ውረድ እንጂ አለኝ፡፡ የደንብ? የደንብ? የደንብ ምን ነበር? አቤት??? አልኩኝ ግራ እየተጋባሁ፡፡ ቶሎ እንዲሰራልህ ላደረኩበት የሻሂ አምጣ ብሎ የደንብን ትርጓሜ ፈሰረልኝ፡፡ እህህህ??? የደምብ ማለት ሙስና ነው እንዴ? እዚህም ሙስና??? አልኩኝ ከፊቴ የተቀመጠው መልአክ በቅፅበት ወደ ትልቅ ጅብነት ሲቀየርብኝ ደንግጬ፡፡ ጉድ እኮ ነው!! በር ላይ ያነበብኩት የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሙስና የሚል ደንብ አላየሁም፡፡ ወይስ ሙስናም ህገ መንግስቱ ውስጥ ካለተፃፉት ህጎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ኖሯል??? ከተኛበት አልጋ ላይ ማለቴ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ ተነስቶ "ዉጣ!! የማነው ፋራ" ብሎ አምባረቀብኝ፡፡ ለካ አስር ግዜ ጉሮሮውን ሲጠራርግ የነበረው ይሄ ትልቅ ጅብ ጠቦት አገኘሁ ብሎ ሊበላኝ አስቦ ኖሯል፡፡ ሆሆሆ ሳይመታኝ ተነስቼ ልውጣ ብዬ ሾከክ እያልኩ በገባሁበት በር ወጣሁኝ፡፡ ከግቢ ውጭ ላንድ አፍታ ቆም ብዬ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ሳስብ ከመንገድ ትራንስፖርት ጀርባ ካለው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሄጄ ማመልከትን ሁነኛ መፍትሄ ብዬ ዘየድኩኝ፡፡ ወደ... ፀረ ሙስና ኮሚሽን፡፡

ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደርሼ ወደውስጥ ዘልቄ ገባሁ፡፡ ግቢው በር ላይ የፖሊስ ፓትሮል ቁሟል ፣ አልፎ አልፎ ክላሽ የያዙ ፖሊሶች ተገትረዋል፡፡ እነሱን አልፌ ወደ ህንፃው ሳንቃ ስጠጋ ሰራተኞቹ ውጭ ላይ ይተራመሳሉ፡፡ ግራ ገብቶኝ እንደኔ ፋይል ይዞ ግራ የገባውን አንዱን ባለ ጉዳይ ምን እንደተፈጠረ ጠየኩት፡፡ የመስሪያ ቤቱ ሀላፊ በሙስና ወንጀል እጅ ከፍንጅ ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዱት እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እርፍፍፍፍፍፍ አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው አለ!! የፀረ ሙስና ኮሚሽን ስራ አስኪያጅ የሙስና ልማት አስኪያጅ ሆኖ ተገኘ፡፡ ጉድ አትሉም!! ሰዐቱ 10:30 ገደማ ደርሷል የደጋማዋ ደሴ ብርድ ከንፋስ ጋር እያፉጫጨ ነው፡፡ ከዛ በኀላ መቆየት አንደ ታይታኒኩ ጄያክ የብርድ ሲሳይ መሆን ነው ብዬ ወደ ወደ ኮምቦልቻ መሄድ ወሰንኩኝ፡፡

የምሽቱ ግር ግር ደሴ ላይ ደርቷል የደሴ ውብ ቀዘባዎች ወ ሸበላዎች ባስፓልቱ ላይ ይገማሸራሉ፡፡ የሸርፍ ተራ ወዝ አደሮች ጥፍንግ ቦንዳ ተሸክመው መንገድድድድድድ እያሉ እየጮሁ ይሮጣሉ፡፡ ወያላው ይጮሀል ፣ የመኪናው ጡሩንባ ያናፋል.... እኔ የሳምንት ልፋት ፣ ብክነት ፣ ቁጭት ፣ ብስጭት አዝሎኝ ወደ መናሀሪያ እራመዳለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የታክሲውን ሻተር ከፍቶ አንዱ ረዳት ኧኧኧ ቧንቧ ውሀ ነህ? ያለኝ፡፡ አይደለሁም ብዬው አለፍኩ፡፡ ሌላኛው እረዳት ፀጉሩን እየገመደ ኧኧኧ አባት አራዳ ነህ አለኝ፡፡ ዝም ብዬው አለፍኩ፡፡ እኔ ለራሴ ደክሞኛል ምን ይጨቀጭቁኛል ጃል!! ኧኧኧ አራዳ ነህ ብሎ ደግሞ ጠየቀኝ፡፡ " አሁንም ዝም" ሰውዬ ጆሮ የለህም እንዴ? አራዳ ነህ ወይይይይይ??? ያ...ረቢ ኑባሲ!! ሰውዬው የሚፋታኝ ነገር አይደለም፡፡

መለስኩለት............አይ ፋራ ነኝ፡፡


ህህህ አበቃ፡፡


@wegoch
@wegoch
@wegoch
Forwarded from ❀ርብቂ Ribki Photography (Ribka Sisay)
ያ ደግ ከመወለዱም በፊት በፅልመት ነበርን።

ሲወለድም የእልልታችን ድምፅ ሻክሮ ነበር።

ፍንደቃችንም ተቀዛቅዞ። ንጉሳችንም ደነበረ።

ጨቅላዎቻችንን ደጉን ለመጉዳት ሲል ቀጠፈ።

ከግዜያት በኋላ ግን ከደጉ የተሻለ ደስታ አልነበረንም።

ባለፈበት ሁሉ ሳር ቅጠሉ ይቦርቅ ጀመር።

እኛም ስለክብሩ ዳንኪራ ባንረግጥም ስናየው የውስጥ አካላችን ይዘል እና እልልልልልልልል ይል ነበር።

ከተማይቱ በደስታ አቅሏን ስታ ነበር።

ምክንያቱም ደጉን የመሰለ ንጉስ አብሮን ነበርና።

ማንም ሰውም ብቻውን አልነበረም። የሚስቅ እንጂ ከንፈሩን የሚነክስ ሰው አልተገኘብንም።

ፅልመቱም ተገፎልናል።

ስንራመድ እኛን የሚመስል በሄድንበት የሚሄድ በብርሃን የተበጀ የደጉ መልዕክተኛ ይጠብቀናል።

ኦ ደጉ ሆይ ስለተወለድክ አመሰግንሃሁ!

ኦ የደጉ እናት ሆይ እወድሻለሁ !

ኦ የደጉ ተንከባካቢ ሆይ አከብርሃለው!!

.........
የደጉ ጌታችን ልደት መልካም ልብ የምናተርፍበት ይሁንልን!
🤍🤍🤍
......
@ribkiphoto
(ዘመነ ጁንታ በወሎ)

ክፍል 1

ጆሮ የተኩስ እሩምታን ለምዷል ፣ አይን ሬሳ እና ደምን ከቁብ አይቆጥርም ፣ አፍንጫም በየጊዜው የሚሰነፍጠው የባሩድ ሽታ ጋር ተስማምቷል፡፡ከግለሰብ ኪዎስኮች ጀምሮ እስከ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ሁሉም በየፈርጁ ተበርብረዋል፡፡ ፋብሪካዎች ወድመዋል፡፡ ብቻ ያቺ የወይና ደጋዋ ውብ ኮምቦልቻ እንደ ግንቦት ዛፍ ተራቁታለች፡፡

የወያኔ ጦር (ጁንታ) ወሎን ከተቆጣጠረ በኀላ ከኮሞቦልቻ EDDC (Ethiopia Domestic Distribution Corporation) ዘርፎ የተረፈውን ስንዴና ዘይት ለኮምቦልቻ አቅመ ደካሞች በማከፋፈል ህዝባዊነቱን እያሳየ ነው፡፡ ህህህ አይ ጁንታ!! እርዳታውም ተጠቃሚ የሚያደርገው ሴቶችን እና አቅመ ደካሞችን ብቻ ነው፡፡

በህጉ መሰረት ተረጅ አቅመ ደካማ ሴቶች ከካሜራ እና ከክላሽ ፊት መደዳውን ተኮልኩለዋሉ፡፡ የርዳታው አስተባባሪ ታጋይ ኪሮስ አብረሀ መዝገብ ይዞ ትግረኛ ይሁን አማረኛ በማያስታውቅ ቋንቋ ስማቸውን እየጠራ እርዳታውን እያጋፈረ ነው፡፡ በመሀል አንዳንድ የሙስሊም ስሞችን ሲጠራ ጓያ እንደሰበረው ሰው ይወላከፋል፡፡

ልክ እንደ አብዱ ዛራቅ😜

ከዚህ በታች ስማችሁን የሙጠራችሁ ሰዎች ቶሎ ቶሎ አቤት እያላችሁ ወደዛ እለፉ፡፡ ብሎ ወደ ስንዴ እና ዘይቱ ክምችት ሌባ ጣቱን ቀሰረ፡፡
ወይዞሮ ዘይነባ???
"አቤት"
እለፊ፡፡
ወይዘሮ የዝናሽ???
"አቤት ጌታዬ"
እለፊ፡፡
ቀጠለ.....ወይዞሮ ነፊሳ???
"አቤት" ቀጠን ያለ የወጣት ሴት ድምፅ ነው፡፡ ካቀረቀረበት መዝገብ ቀና ብሎ አያት፡፡ ዋይ!! አንቺ ዎጣት አይደለሽ እንዴ? ምነው ሂደሽ ካንዱ ሱቅ የማትዘርፊ??? በይ አሁን ሳልቶክስብሽ ከዚ ጥፊ!! አለ በ11 ቁጥር ምልክት የተቀነደበ ቅንድቡን ከፍ ዝቅ እያደረገ፡፡
ከዛም ወደ መዝገቡ ተመለሶ..... መጥራቱን ቀጠለ፡፡
ወይዞሮ ፍሬ ወይኒ???
"ዝምምምም" መልስ የለም፡፡ ከንደገና ፊደል እየቆጠረ በሎህሳስ ድምፅ "ፈ...ር...ሒ...ን" ብሎ አስተካክሎ አንብቦ "ዋይ ፈርሂን ነው እንዴ የሚል"..... ወይዞሮ ፈርሂን? ብሎ ተጣራ፡፡
"አቤት አለሁ...አለሁ" ብላ ወደ ዘይት እና ስኳሩ ስታልፍ...ቆይ ቆይ ሙን ያስቾኩልሻል? ቆስ ቦይ እስኪ፡፡
እእእ ስሙሽ እንደ ኮንክሪት ሙሽግ አስቾጋሪ ነው፡፡ ፍሬ ወይኒ ብለሽ የማትቀይሪ ለምድን ነው??? ብሎ ትዕዛዛዊ ምክሩን ሰጠ፡፡ እሺ ጌታዬ እርሰዎ እንዳሉት ይሆናል ብላ መንገዷን ቀጠለች፡፡
እሱም ስም ጥሪውን ቀጠለ...እሺ ወይዞሮ ፏጥማ? ወይዞሮ ፏጥማ?
እድሜያቸው የገፋው እማማ ፋጡማ በሰለለ ድምፃቸው "ለበይክ ጁንታው" አሉ፡፡ የተሰበሰበው ጀማ ግማሹ በድንጋጤ ነፍሱ ባፉ ሹልክ ልትል ደርሳለች፡፡ ከፊሉ ደግሞ በማማ ፋጤ የድንገቴ ቃል የሳቅ ሳግ ተናንቆታል፡፡
ዋይ!! ......ቀና ብሎ አይኑን እያጉረጠረጠ ከፍ ዝቅ አድርጎ አያቸው፡፡ እርሶ ሊረዱ መተው ጁንታ ይላሉ እንዴ???
እንግዲያ ምንዲን ነው የሚባለው እንቶ?? ብለው ጥያቄያዊ መልስ መለሱ፡፡ ዋይ ጁንታ ማለት እኮ ስድብ ነው፡፡ አሁን ብቶኩሱብሁ የማን ያለህ ሊሉ ነው? አለ፡፡ ተግሳፃዊ ቁጣ ጋር፡፡
መገን የኔ ነገር!! በቴሌቢጅን ጁንታ ቲሉ ብሰማ እኮ ነው ጁንታ ማለቴ፡፡ ሲ...ቆይ ታዳ ጁንታ እሚባሉት ማንኞቹ ናቸው አሉ፡፡ አጭር ምርኩዛቸው ላይ አገጫቸውን አስደግፈው ግራ በመጋባት፡፡ ጁንታ ማለትማ እኛ ነን፡፡ ግን እኛ አይደለንም፡፡ እኛ ለነፃነት የምንፋለም ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ነው የምንባል፡፡ በሉ ካሁን በኃላ ጁንታ እንዳይሉ ወደዛ ይለፉ አለ ወደ ስንዴው ድርድር ቀኝ እጁን እያወናጨፈ፡፡ እሺ አፉ በለኝ ጋሽ ጁንታ ብለው ጁንታነትን ጋሼ የሚል ማዕረግ ጨምረው በድጋሜ ጠሩት፡፡ ያኔ እንደ ምጥ ሳቅ እያማጠ የቆየው ጀማ አሽካካ "ሀሀሀሀሀሀሀሀ" ታጋይ ኪሮስም ሳይቀር በእማማ ፋጤ የዋህነት አብሮ ሳቀ፡፡ ሳቁ ጋፕ ሲል መልሶ ፊቱን ቋጠረና መጥራት ጀመረ፡፡
እሺ እንግዲህ...ፀጥታ ይከበር፡፡ እእእ ወይዞሮ ካሚል ሲራጅ??? ወይዞሮ ካሚል ሲራጅ?? "አቤት" ከሰልፈኞቹ መሀል ጎርነን ያለ የወንድ ድምፅ ተሰማ፡፡ ዋይ....እኖዚ ሰዎች ምን ኖክቷቾዋል፡፡ አንተ ዶግሞ እዚህ ሙንድን ነው ሙትሰራ? እኛ ዎንድ ሞች ጠራን? የሴቶች መረሀ ግብር አይደል እንዴ??? አለ እንደ ሀምሌ ደምና ፊቱን አጨፍግጎ፡፡

አቶ ካሚል መለሰ.....ኧረ ጌታዬ እናንተ ከመጣችሁ በኀላ ምን ወንድ አለ??? ጨርሰን ሴት ሁነናል እኮ፡፡

"ሀሀሀሀሀሀሀ" የእድምተኛው ሳቅ ድጋሚ አስተጋባ፡፡

@wegoch
@wegoch
@paappii

#በመሊኩ [ MAJNUN ]
Forwarded from ❀ርብቂ Ribki Photography (Ribka Sisay)
ልጄ ሆይ የእውነት ከምወድህ በላይ አስበልጬ ራሴን የውሸት እወደዋለው።
አሰፍስፈው ለሚጠብቁኝ መካን ጥንዶች በገንዘብ እቀይራቸዋለው። ጥሩ ስለሚንከባከቡክ እና ልብህም ስስ ስለሆነ ቶሎ ችላ ትለኛለህ።
አታስብ መሃል አናትህን መሳም እንደምትወድና ሲደባብሱህ እንቅልፍ እንደሚጥልህ ነግሬልሀለው።
ከእኔ የሆነልህ ይሄው ነው። ይሄንንና ጥሩ ምግብ ንፁህ ልብስ ቆንጆ መኝታም ታገኛለህ።

አደራ ልጄ እንዳየሀቸው ተቀበላቸው። እኔንም እንደ እሩቅ ዘመድ ዘንጋኝ!!
.....
©Ribka Sisay
....
@ribkiphoto
Forwarded from ❀ርብቂ Ribki Photography (Ribka Sisay)
አደራዬን ከበላው ቆየው! አማቼ ሲያርፉ ልጃቸውን ከእነ ልጇ ተንከባከብ ብለውኝ ነበር።

ሞከርኩ። ግን ከልጆቼ ላስበልጠው አልቻልኩም። እሷንስ እንደሚስት ሾሜያታለው።

አሁን ብበድለውም ብክሰውም ለውጥ አይኖረውም!

የአብራክ ክፋዬ ስላልሆነ ርህራሄ የለኝም!
ወዝ በፊቱ ግጥም ሲል ያንገበግበኝ ጀመር።

እናቱ እሱን እሱን ስትል የእኔን ልጆች ዘንግታለች!

በእጄ ሰበብ ሳይሆን መላ ላበጅለት።
ከተማ እንደደረስን ገብያ መሃል ወስጄ እሰወርበታለው!

ለሳምንት ድምፄን አጠፋና ደውዬ ልጅሽ ጠፋብኝ እርምሽን አውጪ እላታለው!

ትንሽ የሚያሳስበኝ ያን ስትሰማ መነጫነጯ ነው። ለነገሩ ስታኮርፍም ታምራለች!!
......
© Ribka Sisay
.....
@ribkiphoto
ሶፊያ ትባላለች የቀድሞ ፍቅረኛዬ ነበረች። ከተለያየን በጣም ብዙ ጊዜ ሆኖናል። እጅግ ከብዙ ጊዜ በኋላ ተደዋውለን ሻይ እየጠጣን ነው። በጨዋታችን መሃል ድንገት ለምን ግን ያኔ ተውሺኝ አልኳት ። ሳቀች ፤ ስትስቅ አይኗ ይጨፈናል ። ሰላማዊ በሆነ አስተያየት ካለምንም ወቀሳ መልሷን እየጠበኩ እንደነበር የተረዳች መሰለኝ ከሳቋ መልስ "እውነቱን ለመናገር ያኔ መተው ነበረብኝ ፤ ያን ውሳኔ የወሰነችው የድሮዋ ሶፊያ ናት"። አብራሪልኝ አልኳት ከስስ ፈገግታ ጋር ፊቴን አኮስኩሼ "ጭንቅላትህ ምክንያታዊ ሃሳብ አያፈልቅም ነበር ። የማይጥምህን ሃሳብ ፤ ያልወደድከውን አቋም ነፍስህ ተረጋግታ አትሰማም ። አንተ ያልፈለከው ካልሆነ ፤ ነፍስህ ትቅበዘበዛለች ሁሌ ከአንተ የፈለቀ ሃሳብ ትክክለኛ እና አዳኝ ይመስልሃል። Soft dictator ነህ ። አምባገነንነትህ በፍቅር ስለምትሸፋፍነው እና
ያፈጠጠ ስላልሆነ በቀላሉ አይገለጥም ።
ፍቅርህ እጅ መንሻህ ነበር መከራከርያ፤መደራደርያህ፤ማፅናኛህ ፤መፅናኛህ ፍቅር ነበር ። ፍቅር ከእውነት የሚበልጥ ይመስልሃል። አንዳንዴ ፍቅር ፤ አንዳንዴ እውነት እንደየሁኔታው እንደሚበላለጡ አልገባህም ።
በበነነው በተነነው ትቀናለህ ፤ እንዳላየህ የምታልፈው ነገር የለም። ሰው ደሞ ብስለቱ
የሚለካው እንዳላየህ በሚያልፈው እና እያወቀ በሚተወው ልክ ጭምር ነው። ስሜትህን ሆነ አስተውሎትህን አሁንም አሁንም ታንፀባርቃለህ። ከፍተኛ የሆነ Emotional intelligence ይጎልህ ነበር ። በዚህ ሁሉ መሃል አንደ አሁን ብስለት መገለጫ ባይሆን ራሱ በአሁን ማስተዋሌ በጭራሽ አልተውክም ነበር። አየህ ያኔ ሙሉ ሰው ፍለጋ ላይ ነበርኩ። ሙሉ የሚባል ሰው አለመኖሩን ለመረዳት ከብዙ ነፍስ ጋር ተዋሃድኩ ፤ ጉድለት ፤ እንከን ፤ ድክመት መልክ እና ይዘቱን እየቀያየረ ሁሉም ጋር እንዳለ ብዙ ቆይቶ ነው የገባኝ ። ጉድለት ይዞ ምሉዕ ፍለጋ መባተል ያለመብሰል ምልክት ነበር። አለመብሰል ነበር ያዳከረኝ ። ትላንት የገፋሁትን አይነት ማግኘት ቀላል አይደለም ። ሶፊያ እንዲህ አልነበረችም ፤ ጭንቅላቷ ሰልቷል ። እድሜ ይሆን ፤ንባብ ይሆን ፤ ከነፍስ ነፍስ መባተሏ ይሆን ብቻ ሃሳቦቿን የምትገልፅበት መንገድ ጭምር ተቀይሯል ።
ዋነኛ የመለያየት ምክንያት ፍፁም ነፍስ ፍለጋ መባተል ነው። ለድክመቶቻችን ሁሉ ጣት
ቅሰራ እና ማላከክ ፈይዳ የለውም ! አለመብሰል ስንቱን በረከታችንን አሳጣን ።

ቸር ሰንብቱልኝ

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Adhanom Mitiku
በጣም "ነበር" ምወዳት


ሰው እንዴት በበአለ ልደቱ በጠዋት ተነስቶ ማልቀስ ይቃጣዋል ። ያውም ወንድ ልጅ ሆኖ ፤ በቃ እንባ እንባ ይለኛል ፤ ልክ አንድ ልጇን እንዳጣች እናት ወገብህ ላይ ነጠላህን አስረህ ፣ ቃላት እንደጉድ እያዥጎደጎድክ እሪሪሪሪሪሪሪሪሪ በል ይለኛል ። ግን ማልቀስ እንዴት ነው? ፣ እንባስ አይንን ከሚያክል ግድብ እንዴት ነው አምልጦ ሚወጣው? ፣

ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ይባላል ፤ ከልቤ ያለቀስኩበት ጊዜ አስታውሳለው ፣ ከአይኔ እንባ የፈሰሰበትን ጊዜ ግን አላስታውስም ፤ታዲያ እኔ በጨጓራ ነው እንዴ ምኖረው? (ምናልባት ለመጨረሻ ጊዜ ያለቀስኩት ይቺን አለም ስቀላቀላት ሳይሆን አይቀርም)


ያዘንኩባቸው ጊዜያት ግን አሁን ድረስ ሳስታውሳቸው እንዳዲስ ያሳዝኑኛል ፤ ማልቀስ ግን አልችልም ፣ በቃ አልችልም ፤ ውሀው እንደ ደረቀ ዥረት ፣ የኔም የእምባ ቧምቧ ደርቋል ፣ ልቤ በቢላ እንደተወጋ እየደማ እንኳን አይኔ ቅርር እንኳን አይልበትም ፣ ምን አለመታደል ነው ፣ ከአበቦች መሀል አበባ ሆነህ ሳለ እንደ እሾህ መታየት።

ሰው በሙሉ የሀዘኑ መግለጫን እንባ እያደረገ የኔ አይነቱ በነሱ ፊት አረመኔ ድንጋይ ተደርጎ ይወሰዳል። ስንት አዞ ባለበት ያንተ እንባህ ስላሎረደ ብቻ አውሬ ተደርገህ ትቆጠራለህ።

በጣም ነበር ምወዳት ፣


ስለምታምነኝና ስለማምናት ሌሎች ከሚወዷት በላይ እወዳት ነበር። ጓደኝነት በመተማመን ላይ ሲመሰረት ከምድር ከፍ ይላል ፤ መተማመኑ ሲቋረጥ ደግሞ ጓደኝነቱ እንዳይተርፍ ሆኖ ከተሰቀለበት ይከሰከሳል።

የአንድን ሰው እምነት ሰብረህ ከምትጎዳው በላይ ፣ እምነቱን እየጠበክለት ያ ሰው እምነቱን እንደሰበርክበት ሲያስብ የምትጎዳው ጉዳት ይበልጥ ያቆስላል። ከዛ የሚከፋው ደግሞ ዳግመኛ ሌላ ሰው እንዳያምንብህም ፣ እንዲያምንብህም ማድረግ እንዳትችል ያደርግሀል።

በጣም ነበር ምወዳት ፣


"ከልቤ አምንህ ነበር " ነበር ያለችኝ ። የቱ ጋር እንደዋሸዋት አልገባኝም ። እኔን ግን ምን ያክል እንደጎዳችኝ አልገባትም። በ"ነበር " ውስጥ "ከዚ ቡኋላ አይኖርም" የሚል ቃል በውስጡ እንዳለ አልገባትም።
በእርግጥ ላይኖርም ይችላል ምክንያቱም እኔ አሁንም እወዳታለው ግን.....


በጣም ነበር እኮ ምወዳት


"የእውነትህን ስትምል በማነው ምትምለው?" ብላ ጠየቀችኝ
"የማያምነኝ አይመነኝ እንጂ በማንም አልምልም ፣ ግን ላንቺ በእናቴ ሞት እምልልሻለው" ነበር ያልኳት

ለማንም እኮ በእናቴ ምዬ አላውቅም ። ደስ የማይላትን ነገር ላላደርግ 'እናቴ ትሙት' ብዬ ነበር የማልኩላት። እና የትኛው ቃል ከብዶኝ ነው እናቴ እንድትሞት ምፈቅደው?

በፍፁም ቃሌን አላጠፍኩም ፣ ከዛም ብሶ ውሸታም ቀጣፊ እስከሚያስብለኝ ድረስ መካዴን አደለም ሰው ሆኜ እሬሳ ብሆን እንኳን እንዴት አይገባኝም።

በጣም ነበር ምወዳት

"እንዴትም ብንጣላ አኮርፍሽ ይሆናል እንጂ አልለይሽም" ብዬ ቃል ገብቼ ነበር።
ግን ይሄን ቃሌን እንዳልጠብቅ ቃሉን የማይፈፅም ከንቱ ሰው አደረገችኝ ፣ ማነው አላምንህም እየተባለ እታመናለው የሚል?

በሁለት ባላ እንደተወጠረ ገመድ ሆኛለው ፣ አንደኛው ቃሌ አንዱን እንዳፈርስ ይገፋፋኛል ፣ አንደኛው ደሞ ቃሌን እንድጠብቅ ያስገድደኛል ።

መተውም አለመተውም ግዴታ ሲሆን ከምጥ የከፋ ምጥ ይሆናል። ልክ መውለድም አለመውለድም የመጨረሻ ምርጫ ሲሆን ፣ ልክ ጥፍርህን በፒንሳ እየጎተቱ ' ድምፅህን እንዳታሰማ' እንደመባል አይነት ስሜት ላይ ገብቻለው።

በጣም ነበር ምወዳት

ከዚ ቡኋላ አምንሀለው ብላ በእናቷ ብትምልልኝ እንኳን እንደምታምነኝ አላምናትም ፤ መፅሀፍ ቅዱስ ብትመታልኝ እንኳን በፍፁም አላምናትም ፤ ልክ ሳይተማመኑ እንደሚኖሩ ሁለት ሌቦች መኖርን እመርጣለው ፤ ግን በማንም የማይተካ ልቤን ከሷ ውጪ ለማንም አልሰጥም ፣ ይሄን ደሞ ማንም እንዲያምነኝ አልሻም ፤ ብቻ ግን......


በጣም እወዳት ነበር ..........................

ወደፊትም መውደዴን ሳታምነኝ እወዳታለው።

ነገ ሁሉ ዛሬ መሆኑ አይቀርም ፣
ዛሬ ሁሉ ደሞ ትናንት መሆኑ የማይቀር ነገር ነው።

(ቤካ)
@wegoch
@wegoch
@wegoch
Forwarded from ❀ርብቂ Ribki Photography (Ribka Sisay)
የመንፈስ ጭሰት ታውቃለህ? ጨሻለው!

ብዥዥዥ እሽክርክርክር ቅብዥርዥርዥር ቅብጥርጥርጥር ያደርገኛል!

አሁን አንተ ራሱ ታወዛግበኛለህ ስታወራ አትሰማኝም!!
ዝም ስትል ግን ትጮኽብኛለህ!!
....
©Ribka Sisay
....
@ribkiphoto
-ፅልመት-

ክፍል 1

እንደው ለበደለኩት ሲቀጣኝ እንጂ ካልጠፋ መንገድ በኮሮኮንች ምን ወሰደኝ? እንደው በድፍረት ለሰራሁት ጥፋት ቅምሻ ቅጣት ብሎ እንጂ ለምን በኮብልስቶኑ ታጠፍኩኝ ቀጥታ
መሄድ ስችል ? ድንገት መተጣጠፌ የድካሜ ሰበብ ሆኖኝ ጉሮሮዬን የሚያረሰርስ መጠጥ ፈለኩ በአንዱ እጥፋቴ ቅጽበት ሰዋራ ስፍራ ላይ ያለች ሆቴል አየሁ ወደ ሰዋራዋ ሆቴል ገባሁ
አንዱ ጥግ ቁጭ ከማለቴ ቅፅበት አስተናገጁ ሲወረወር መጣ ቀዝቃዛ በደሌ አዘዝኩ ድንገት የሆቴሉን ድባብ እና ስፋት በዓይኔ ስቃኝ ፤ ስመትር የማቀውን ባለኮፍያ ብራቡሬ ሹራብ የለበሰ ጀርባ አየሁ ሹራቡንም ጀርባውንም አውቀዋለሁ ። ግንባሬን ቁጥር ፤ አይኔን
ትኩር አድርጌ ተመለከትኩ ። ሹራቡን የለበሰችው ልጅ ስታሽካካ ከመስማቴ በፊት ነበር ሚስቴ እንደሆነች ያወኩት ። የሚስቴን ሹራብ ለብሶ እዚህ ሰዋራ ስፍራ የመጣው ማነው ? የሚስቴን ጀርባ የለበሰው ማነው? የሚስቴን ሳቅ አይነትስ የሚያሽካካውስ? አብሯት ያለው ጎረማሳ እያሳቃት ፤ አንገቱ ስር እየወሸቃት ነው ። ሁሉ ነገራቸው ሌላ ነገር እንዳዘለ ያስታውቃል።
አለም ሚዛኗ ተዛባባኝ ፤ ወበቀኝ ፤ ጥሜ ጠፋ ። ግንባሬ ሲወረዛ ታውቆኛል ።ሰውነቴ
ልፍስፍስ አለብኝ ። ሰው ለካ ዱብ'ዳ ሲገጥመው ይሰበራል እንጂ ያዙኝ ልቀቁኝ አይልም ። ወንበሬ ላይ እንዳለሁ እንስ አልኩ ፤ እንደው ኩርምት
የሚስቴን እኔ ራሴ የገዛሁላትን ሹራብ አይቼ ። ስንት ቀን ያሸውትን ፤ የተደገፍኩበትን ፤ከሰውነቴ ጋ የተፋተገውን ጀርባ በቅፅበት ብለየውም አላመንኩም ። ሳቋን የሰማው ጆሮዬን ማመን አልተቻለኝም ። የሆነ ሰው ሹራቧን ፤ ጀርባዋን ሳቋን ተውሷት መሆን አለበት! ስልኬን አውጥቼ "ቤቱሻዬ " ብዬ ሞባይሌ ላይ save ያደረኩትን የሚስቴን ቁጥር ደወልኩበት የሚስቴን ሳቅ፤ ጀርባ ፤ሹራብ የያዘችው ሴት ስልኳ ጠራ ፤ ከቦርሳዋ ስታወጣው እንቅስቃሴዋ ነገረኝ ወይ ገመትኩ ፤ ግን አልተነሳም ። ድብዝዝ አለብኝ ። መላቅጡ የጠፋ ውጅንብር ውስጥ ሰመጥኩ ፤ ተምታታብኝ ፤ እሪሪ ማለት መጮኽ ፈለኩ ግን ደግሞ አቅም አጣሁ እኔ ስልኳ ላይ ከደወልኩላት እሷ እኔ እንደደወልኩ ካወቀች እና ካላነሳች ቀጥሎ ለአስተናጋጁ ምልክት የሰጡት ይመስለኛል ቀልጠፍ እያለ እነሱ ጋ ሲሄድ አየሁት
ገባኝ ካለወትሮዬ በዚህ ሰዓት መደወሌ ቢፈልገኝ ነው ብላ ተለይታው ልትደውልልኝ ነው ። በቃ አስቻኩላው ነው አልኩ ። አስተናጋጁ ተመልሶ መጣ ፤ መልስ ይዞላቸው የመጣ ይመስለኛል።
ተነሱ ፤ ሲነሱ እንዳያዩኝ ፌቴን ወደ ሌላ ቦታ አዞርኩ አላስችል ብሎኝ ስዞር ፤ ይመጣሉ ብዬ በጠበኩት ተቃራኒ ፤ በጀርባ በኩል ገቡ ። ላመል
ያክል ከጎረምሳው ጋ አብራዋ ያለችው ወደ ጀርባውን በአይኖ ገልመጥ አድርጋ ሄደች።
ሌባ ደምቡ ነው ከመኖርያ ስፍራ ርቆ ሰዋራ ስፍራ ይገባል፤ ሹርብ ይለብሳል ጥግ ላይ ጀርባውን ሰጥቶ ይቀማጣል ሲንቀሳቀስ ጀርባውን አያምንም ገልምጥ ያደርጋል ። አዞዞሯ ደመነፍሳዊ ስለነበር አላየቺኝም
አስተናጋጁን ጠራሁት ። አንድ ያልጠጣሁት በደሌ ፊቴ እያለ ሌላ አንድ አምጣልኝ አልኩት ፤ ሊሄድ ሲል በዚህ ጋ መውጫ አለ እንዴ አልኩት ፤ ተያይዘው በገቡበት እጄን እያመላከትኩ ፤ የለም አልጋ ክፍል ብቻ ነው በዚህ ጋ ያለው አለኝ።
ደረቴ ስር ሲሸቀሸቀኝ ተሰማኝ ፤ አጥወለወለኝ ። ብዙ ጥያቄ መጠየቅ ፈልጌ ነበር ። አዘውትረው ይመጣሉ ወይ? ታቃቸዋለህ?? በየ ስንት ግዜ ፤ ስንት ሰዓት ላይ?? ማለት ፈልጌ ነበር አቃተኝ ።
ዝም ብዬ ትኩር ፍዝዝ ብዬ ሳየው ከአፉ እንቅስቃሴ በቀር የሚለውን አልሰማ ስለው ሄደ ።
አለም የምናስበውን እና የሆነብንን ትመስላለች ። አሁን ከሰዓት በፊት የነበረችው አለም ሰላም ነበረች ከመቼው አዘቀዘቀች ። ከመቼው ጤናዬ ታወከ ። ሁሉን ማመን አቃተኝ ፤ የመጨረሻ ብዬ ለአስተናጋጁ በምልክቴ ሂሳብ አልኩት
ሂሳብ ይዞ መጣ እና ድፍን ሁለት መቶ ብር ሰጠሁት ፤ በቶሎ ዘጠና አምስት ብር ይዞ
ተመለሰ ። መልሱን ያዘው አልኩት ። እጅግ አመሰግኗኝ ሊሄድ ሲል ። እንደምንም ራሴን አረጋግቼ ፤ እዛ ከልጅቷ ጋ የተቀመጠው ልጅ ቀጥሮኝ ነበር ፤ እመጣለሁ ብሎኝ ቀረ አልኩት ፤ ዝም ብሎ አየኝ ፤ አዳር ነው እንዴ አልጋ የያዘው አልኩት ፤ አይ አረ ጊዜያዊ ነው አለኝ!!
ፊቴን አዞርኩ ። በዘጠና አምስት ብር ጉርሻ ሚስቴ እንደምትማግጥብኝ አረጋገጠልኝ። በስተመጨረሻ አለማመኔ ድል ተነሳ !
አይኔ የሆነውን ሁሉ ክስተት ሲያስተውል ቆይቶ አለቀሰ። እምባዬን በጉንጬ በኩል
ወረወረው እስከዛሬ ከሷ ጋ እያበረ ከስሜቴ ጋ እየተማከረ የሚወዳት የሚሳሳላት የማይዋሻት አይኔ አለቀሰባት ። ነገዬ ፤ ኑሮዬ ፤እምነቴ ፤ ትዳሬ እጣፈንታዬ ገብቶት አይኔ ብዙ እምባ አመነጨ ።
ባልተከፈተው ቢራ አጠገብ የተከፋ ልቤን አቅፌ ኩርምት እንዳልኩ አንገቴን አቀርቅሬ ድምፅ ሳላወጣ እየተንሰቀሰቅኩ አለቀስኩ ።

ይቀጥላል

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Adhanom Mitiku
2024/09/22 23:26:34
Back to Top
HTML Embed Code: