Telegram Web Link
ልንጋባ ሁለት ሳምንት ሲቀረን እጮኛዬ ጤነኛ እንዳልሆነ አወቅኩ (ክፍል አራት)

"አባትህን እንዴት አድርገህ ነው የገደልከው?" እንዲህ ተብሎ አይጠየቅም! "ቅድም አባቴን ገደልኩት ነው ያልከኝ?" ይሄም ያው ነውኮ! "ቅድምኮ እንዴት መጀመሪያ እንዳወቅክ እየነገርከኝ ...." ኤጭ ምንድነው የምቀባጥረው?

ወደ መኝታ ከመሄዴ በፊት ሽንት ቤት ሆኜ ጥርሴን እየፋቅኩ ነው ፊልም ላይ እንደሚያወሩት ብቻዬን የማወራው። የራሱ ጉዳይ በቃ "አባትህ ምን ሆነው ነው የሞቱት?" እለዋለሁ። እሱ አፉን ሞልቶ አባቴን ገድዬ ሲል ያልተሳቀቀ እኔ ምን ያሳቅቀኛል? ውይ እሱ ወሰድ ያደርገዋል ለካ!

"ስለአባታችን እባክሽ እንዳታነሺበት!" ትለኛለች ይህቺ ደግሞ ከሽንት ቤቱ ስወጣ ጠብቃ

"ለምን?" ያልኳት እንደመጣልኝ ነው

"ለእሱ እጅግ በጣም መጥፎ ትዝታው ነው። ሰላም እደሪ!" ብላኝ እብስ ልትል .... አባቴን ገድዬ ካለኝ ሰውዬ ጋር ደግሞ እንዳታነሺበት ብላኝ ደህና እደሪ ? ቀልድ ነው?

"እሺ አንቺ ንገሪኛ? አባቴን እንደገደልኩት ሳስብ እኮ ነው ያለኝ!"

"ኦ ኖ ኖ እንደሱ አይደለም! (ዘገነናት) ፔር ማንም ላይ እጁን የሚያነሳ ሰው አይደለም! ኦህ ማይ ጋድ ጭራሽ አታውቂውም አይደል? (ቆይ እዚህ ቤት ታዲያ ምን ትሰሪያለሽ? በውል እንኳን የማታውቂውን ሰው ነው አገባዋለሁ ብለሽ ቀን የቀጠርሽው? የሚል ለዛ ነው ድምፅዋ ያለው።) በጥቂቱ አፈርኩ። የምርም አላውቀውም!

"ስለዛ ቀን ለማንም አውርቶ አያውቅም በትክክል በቦታው የተፈጠረውን ከግምት ውጪ ማናችንም አናውቅም። ፔር በ20 ዓመቱ የዩንቨርስቲ ተማሪ እያለ ነበር። አባታችን ከጓደኞቹጋ አሳ ሊያጠምዱ ሲወጡ አብሬ ካልሄድኩ ብሎ ወጣ ስምንት ሆነው ነው የሄዱት። መጥፎ ወጀብ ነበር። መርከባቸው ከዓለት ጋር ተጋጭታ ተሰባበረች። እኛ የምናውቀው የእርዳታ ሰጪ ሰራተኞቹ ሌሎቹን ማትረፍ ሲችሉ አባቴን ማትረፍ አለመቻላቸውን ነው። 'ላድነው እችል ነበር ገደልኩት' እያለ ይቃዥ ነበር። ከዛ ውጪ ለማንም ቃል ተንፍሶ አያውቅም።" አለችኝ

ዝም አልኩ። መተንፈሴን የሚያስጠረጥር ዝምታ ዝም አልኩ። የሆነ ነገር የተጫነብኝ ቁመቴ ሁሉ ያጠረ መሰለኝ።

"እንደማታፈቅሪው አውቃለሁ። እውነት ለማውራት እኔም አልወድሽም! ግን እባክሽ ወንድሜ በቂ ስቃይ በህይወቱ የተሰቃየ ሰው ነው። አትጨምሪበት! ደህና እደሪ!!" ብላኝ በቆምኩበት ጥላኝ ወደ ክፍሏ ሄደች። እግሬን እየጎተትኩ መኝታ ቤታችን ገባሁ። በጎኑ ተኝቶ ኩርምት ብሏል። ቶሎ አልጋው ላይ አልወጣሁም።

"እባክሽ እንደሱ አትዪኝ" አለኝ በዛ እንባ ሳይወጣው ለቅሶ ባለው ድምፁ

"እንዴት አድርጌ አየሁህ?" አልኩት ቅስስ እያልኩ አንሶላውን ገልጬ እየገባሁ

"ልክ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ .... ከጥፋት ውጪ ምንም ፍፃሜ እንደሌለው።"

"እንደሱ አልነበረም ያየሁህ!" አልኩት ልክ እንደሱ በጎኔ ፊቴን ወደሱ አዙሬ እየተጋደምኩ።

"እኔ እስከማውቀው ከራስህ አልፈህ ለሀገርህ የምትተርፍ ጂኒየስ ነህ! አንተ በሰራሃቸው ሶፍትዌሮች ምክንያት ብዙ ስርአጥ ስራ አጊንቷል። ብዙ ድርጅት አትርፏል። የብዙ ሰዎችን ህይወት አቅልለሃል አንተን ከጥፋት ውጪ ሌላ ፍፃሜ እንደሌለው ሰው ማየት እንዴት ይቻላል?"

(በሙያው IT ኢንጂነር ነው። የምሬን ነው ያልኩት ከIT ቴክኖሎጂጋ ተያይዞ ያለው እውቀትና ፈጠራ የምርም ለሀገር የተረፈ ነው።)

"ውሃው ቀዝቃዛ ነበር። ጨለማ ነበር። ሁላችንም የእርዳታ ሰራተኞቹ እስኪደርሱልን ነፍሳችንን ለማትረፍ እየታገልን ነበር። እንደምንም በህይወት ለመቆየት ጭንቅላቴን ከውሃው በላይ አድርጌ እየዋኘሁ ነበር። እሱም ነፍስ ይዞት ለመትረፍ ሲፍጨረጨር እግሬን ይዞኝ ለመትረፍ መታገል ጀመረ። እግሬን በጎተተኝ ቁጥር እኔም እየዘቀጥኩ ለመሞት መሽቀዳደም ሆነ። እግሬን አስለቅቄው ነፍሴን ለማዳን መዋኘት ጀመርኩ። በሰዓቱ ራሴን ከማዳን ውጪ ስላለው ነገር አላሰብኩም። በኋላ ላይ እግሬን ያስለቀቅኩት አባቴ መሆኑን አወቅኩ።"

ይሄን እያወራኝ ይበልጥ ኩምትር አለ። እንባው ትራሱ ላይ ተከታተለ። አቀፍኩት። ድምፅ ሳያሰማ ህቅ ሳይል ሰው ይሄ ሁሉ እንባ እንዴት ይወጣዋል? አብሬው አለቀስኩ።.... ለምን እንዳለቀስኩ እንኳን ሳይገባኝ ፍቅፍቅ ብዬ አቅፌው አለቀስኩ .....

አሁንም በድግምጋሚ አልጨረስንም

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ልናጋባ ሁለት ሳምንት ሲቀረን እጮኛዬ ጤነኛ እንዳልሆነ አውቅኩ (ክፍል አምስት)

አንድ ህቅታ ሳያሰማ እቅፌ ውስጥ ሆኖ ትኩስ እንባው ክንዴን ያርሰኛል። ለምን እንዲህ ሆድ እንደባሰኝ አላውቅም። የሚያስለቅሰኝ የሱ ለቅሶ ይሁን የራሴ ውጥንቅጥ ሁላ አላውቅም። ግን መቼ እንዳለቀስኩ የማላስታውሰውን ለቅሶ ከሱ የባሰ ተንፈቀፈቅኩ።

ምን አለ ሀላፊነት ባይኖርብኝ? ምናለ ጠዋት ተነስቼ ጨርቄን ማቄን ሳልል መጥፋት ብችል? ምናለ ድሀ ባልሆን? ምንለ የሆንኩትን ሁላ ባልሆን? ምናለ ከነጭራሹኑ እኔን ባልሆን?

“የቱ ይብሳል? " አልኩት ሁለታችንም ከለቅሷችን ጋብ እንዳልን

"ከምኑና ከምኑ?"

"ከሜኒያው እና ከዲፕረሽኑ?" (የበሽታው ሁለቱ የስሜት ፅንፍ ኢፒሶዶች ናቸው)

"ሁለቱም ያው ናቸው። አንደኛው አይንሽን የሚያጠፋ ብርሃን ሌላኛው የሚያደናብር ድቅድቅ ጨለማ ናቸው። ሁለቱንም ጊዜ ራሴን አይደለሁም። የማታዢበት ጭንቅላትና ሰውነት መያዝ ምን ያህል ዋጋ ቢስነት ነው?" አለኝ ከእቅፌ ሸሽቶ በጀርባው እየተኛ ፊቱን ወደኔ መልሶ አይን አይኔን እያየ።

ለደቂቃዎች ዝም አልኩ። እንባውን ለመዋጥ ሲታገል የሚንቀጠቀጥ ከንፈሩን ልስመው ፈለግኩ ግን ደግሞ የባሰ የሚታዘንለት ፍጥረት እንደሆነ እንዲሰማው አልፈለግኩም።

"ግንኮ በብርሃንህ ወቅት ብዙ ነገር ትሰራለህ። እራሱን እንደማይቆጣጠር ሰው አይደለህም።" አልኩት ከልቤ

"አ..ዎ...ን (ዝቅ ባለ አቅመ ቢስ በሆነ ስሜት አይኑን ቡዝዝ አድርጎ) ችግሩ የቱጋና መቼ ከልክ በላይ እንደሚሆን አታውቂውም። የሆነኛው ቀንና ቦታ ላይ የልኩን መስመር አልፋለሁ።" አለኝ

በማንባት ያበጡ አይኖቹን ተራ በተራ ሳምኩለት። ከንፈሩን ልስመው ከንፈሬን ሳንቀሳቅስ የእንባው ጨው ጨው የሚል ጣዕም ምላሴ ላይ ደረሰ። እንባውን ነው የቀመስኩት .....ሀዘኑን ነው በምላሴ ያጣጣምኩት ..... የዘመናት ሰቀቀኑን ነው ከምራቄ አዋህጄ ምላሴ ላይ ያጣጣምኩት .... .....እናም የዋጥኩት .... እናም የተዋሃድኩት ....... ሆዴ እርብትብት አለብኝ።

ከንፈሩን በስሱ ስሜው ደረቱ ላይ ጋደም አልኩ። የቀመስኩት ሀዘን ..... የዋጥኩት ሰቀቀን ..... ያጣጣምኩት እንባ ....... ድጋሚ ያነፋርቀኝ ጀመር። በተራው እሱ ደግሞ ደረቱ ላይ በሁለቱም እጆቹ አቅፎኝ ለኔ ይሁን ለራሱ እንባውን አብሮኝ አፈሰሰው። ደክሞን እንቅልፍ በዛው ይዞን ሄደ።

እንዲህ እንደሚሆን ባውቅ ላገባው እወስን ነበር? እንዲህ እንደሚሆን ባውቅ ወደ ኖርዌይ እመጣ ነበር? እንዲህ እንደሚሆን ባውቅ የግብዣ ወረቀቱን ልላክልሽ ሲለኝ እሺ እለው ነበር? እንዲህ እንደሚሆን ባውቅ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሊያየኝ ሲመጣ ቤተሰቤን አስተዋውቀው ነበር? ልጄን አሳየው ነበር? እንዲህ እንደሚሆን ባውቅ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያየኝ ሲመጣ ለጓደኞቼ አስተዋውቀዋለሁ? ኸረ ቀድሞውኑ እንዲህ እንደሚሆን ባውቅ ስልኬን እሰጠው ነበር?

ዱባይ ነው የተዋወቅነው። እሱ ከሆነ ሶፍትዌር ካምፓኒ ጋር የስራ ውል ኖሮት። እኔስ? እቁብ ጥዬ ተጣጥዬ በአንዲት ጓደኛዬ ምክር እና ምሪት ከዱባይ እቃ አምጥቶ ለመሸጥ ተከትያት ሄጄ!

ስንሸማምት ውለን የሆነኛው ቦታ ቡና ልንጠጣ ባረፍንበት። ቡናውን ከምትቀዳው ሴትዮ ተቀብዬ በቁሜ ስኳር ስጨምር

"ኦውውው .." የሚል ድምፅ ሰምቼ ዘወር አልኩ።

"ይሄ ሁሉ ስኳር ለአንድ ብርጭቆ ቡና ገርሞኝ ነው ይቅርታ" አለኝ። ፈገግ ብዬ ዝም አልኩት።

በሚቀጥለው ቀን አንደኛው ሞል ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር ክልው ክልው ስል ድጋሚ ተገናኘኝ።

"Ohh hey Sugar lady" አለኝ

አለ አይደል ጓደኛህን አጊንተህ "አንተ ከንቱ አለህ በናትህ ?" ምናምን እንደምትለው አይነት ምን የሚሉት አጠራር ነው አሁን ይሄ

"ሄይ" አልኩት ቆም ብዬ ... በእጄ አንድ ሀገር እቃ ተሸክሚያለሁ። 'ላግዛችሁ?' ብሎ የተወሰነ እቃ ተቀበለን። ማታ እራት ሊጋብዘኝ ሲጠይቀኝ እንደሀበሻ ሴት መግደርደር አልነበረብኝም? ቢያንስ ላስብበት አይባልም?

አይባልም! የፈረንጅ ቆንጆ ነው .... በዛ ላይ ሰውነቱ.... በዛ ላይ ..... ምንም ምክንያት አያስፈልገውም። በቃ አብሬው እራት መብላቱን ፈልጌዋለሁ!!

እራት ስንበላ ስለብዙ ነገር አወራን። ስለስራው .... ስለሀገሩ .... ሀገሩ ስለሚያመርተው brown cheese ሳይቀር አወራልኝ። (የትኛውም ኖርወጅያን ይሄን ካልጠቀሰላችሁ የተወጋ ኖርዌጅያን ነው)።

ጨዋነቱ ደስ ሲል ..... በረራው የዛኑ እለት እኩለ ለሊት ነበር።

"እንዴት ላግኝሽ?" ሲለኝ ስልኬንም ... ሜሴንጀሬንም ... ዋትስአፔንም .... የሰይጣን ነገር አይታወቅም እሱም ባይሰራ የቤት ስልክ ... ድንገት ሰይጣን እጅግ ሲከፋና ይሄም ካልሰራ ፖስታ ሳጥን ቁጥሬም ሳይቀር ሰጠሁት።

ለወራት በርቀት ስናወራ ፎቶ ስንለዋወጥ ከቆየን በኋላ ሊያየኝ መጣ።

የአዲስ አበባ አስፓልቶች ላይ ተመናቀርኩ። ድህነት ላይ ዘበጥኩበት። ብቸኝነት ላይ ተቁላላሁበት ::

አስቡት ፈረንጅ ሆኖ ቆንጆ .... ቆንጆ ሆኖ ሀብታም ... ሀብታም ሆኖ ውጪ የሚወስድ ያውም ከነ ልጅሽ ልንከባከብሽ የሚል ..... ዋናው ነጥብ የአልጋው ልፋት ላይ ሌላ የማያስመኝ ለፊ ... በምንም የማይገኝ ስብጥርኮ ነው።

ህም .......

ስብጥሩ እብደት እንደሚቀላቀልበት ባውቅ ኖሮ ይሄን ሁሉ እርቀትስ እሄድ ነበር?

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ልንጋባ ሁለት ሳምንት ሲቀረን እጮኛዬ ጤነኛ እንዳልሆነ አወቅኩ (ክፍል ስድስት)

"በፍፁም እኔ አይኔ እያየ የሀብትህ ተካፋይ አታደርጋትም!" ብላ ያዙኝ ልቀቁኝ አለች እህትየው።

"ለምን?" አላት ኮስተር ብሎ

"ይሄን እንዴት ማየት ያቅትሃል? አትወድህም!" ብላ ተንጨረጨረች። ቀና ብሎ ትርጉሙ ያልገባኝ አስተያየት አይቶኝ

"ንብረቱ የኔ አይደል? እኔ ልወስንበት! አይሻልም እህቴ? " ብሏት

ምንም የሚቆረፍድ ነገር እንዳልተወራ እኔም እንዳልሰማሁ አስመስሎ የበረዶ ሸርተቴ ልንጫወት እኔና እሱ ልብሳችንን ደራርበን እቃዎቹን መጫን ጀመርን።

ልንጋባ ቀን ቀጥረን ነው። የጋብቻ ውህደቱ ላይ እኔን ከማግባቱ በፊት ያፈራው ንብረት ተካፋይ እንዳልሆን እህትየው ወጥራ የምትሟገተው።

እውነት ለማውራት ይሄን ጉዳይ አላሰብኩትም ነበር። ከሀገሬ ስመጣም የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ከዛ ልጄን ማምጣት ከዛም ለዓመታት ስቋምጥ የነበረውን ትምህርት መማር ከዛ ቤተሰቤን መርዳት በእርሱ ሀብት ከእርሱና ከልጄ ጋር በድሎት ስለመኖር እንጂ ብፋታው ወይ እሱ የሆነ ነገር ቢሆን ስለሚለው አስቤ አላውቅም። ቢሞትስ ብዬም ያሰብኩ ጊዜ ስለ መኖሪያ ፈቃዴ እንጂ ስለሀብቱ ሽውም አላለኝ:: ሳልዋሽ ግን የእህትየው መንገብገብ እልህ አስያዘኝ።

"እህትህ አትወደኝም!" አልኩት የበረዶ መናሸራተቻውን ጫማው ላይ እየሰካን። መናሸራተቱን ከዚህ በፊት ሁለቴ ሞክሬው ሁለቴም ወድቄ እግሬን ተጎድቻለሁ። ዛሬ ለኔ ብዬ ሳይሆን እርሱን ደስ እንዲለው ነው አብሬው የወጣሁት። ሰሞኑን ብዙ ነገር ለእርሱ ብዬ እያደረግኩ ነበር:: አላውቅም:: ብቻ ደህና እንዲሆን እፈልጋለሁ::

"አንቺን ስለማትወድሽ አይደለም እኔን ካንቺ በላይ ስለምትወደኝ የተጠነቀቀችልኝ መስሏት ነው!" አለኝና አወሳሰበብኝ።

"እኔ ስለንብረትህ አስቤ አላውቅም ታምነኛለህ? እሷ እንዳለችው ብታደርግም ቅር አይለኝም" አልኩት።

"አምንሻለሁ። እውነቱን ሳወራሽ እሷ ጉዳዩን እስካነሳችበት ሰዓት ድረስ እኔም ብንለያይ ወይም ብሞት የሚለውን አስቤው አላውቅም!" አለኝ

መንሻራተቱን ጀምረነው ስለነበር መደነቃቀፌን ጀመርኩ። ቁልቁላቱ ላይ ልንደርስ ስንቃረብ ከነመንሸራተቻዬ አዝሎኝ ቁልቁለቱን ተምዘገዘገ። እጮሃለሁ .....ይስቃል ...... እስቃለሁ ደግሞ እጮሃለሁ። የሚያየን ሰው ፈገግ እያለ .... የሚያውቁት ደግሞ ሰላም እያሉት እንተላለፋለን። ቁልቁለቱን ስንጨርስ ተያይዘን በረዶው ላይ ወደቅን።

ከብዙ ቀናት በኋላ ጥርሱ እየታየ ሳቀ:: ክፉ ደግ እንደማያውቅ ህፃን ፍልቅልቅ ብሎ ሳቀ!! ኩርምት ብሎ አራት ሳምንት ጉልበቱን አቅፎ እንዳልተኛ ሰው ሳቀ ........ ከአራት ሳምንት በፊት ራሱን ሊያጠፋ እንዳልነበረ ሰው ሳቀ .........

ድንገት ሳቁን አቁሞ ደንግጦ እያየኝ "ምነው ምንሆነሻል?" ሲለኝ ነው ሳቁን እያየሁ እንባዬ ሳያስፈቅደኝ ጉንጬ ላይ እየተንከባለለ እንደሆነ ያወቅኩት

"ምንም አልሆንኩም ደስ ብሎኝ ነው። የደስታ እንባ ነው አልኩት::" እንባዬን እየጠረግኩ።

ገብቶታል። ፈገግ እያለ እጄን ተቀብሎኝ ውስጥ እጄን ሳመልኝ።

"አፈቅርሻለሁ!" አለኝ እጄን ደጋግሞ እየሳመ። ዝም አልኩት። ከዚህ በፊትም እንዲህ ሲለኝ ምንም መልሼለት አላውቅም። እንድመልስለትም ጠብቆ አያውቅም። ዛሬ ታዲያ ለምን ጨነቀኝ? ለምን የበደለኝነት ስሜት ይሰማኛል? ልቤ ላይ አየር ያጠረኝ አይነት የማፈን ስሜት .... ልነግረው ነበር .... ምን እንደሚሰማኝ አላውቅም ልለው ..... እህትህ ያለችው እውነቷን ነው ልለው ..... አላፈቅርህም ነበር አሁን ግን ላፍቅርህ አላፍቅርህ አላውቅም ልለው ነበር ....... አፌን ስከፍት ቶሎ ብሎ በሌባ ጣቱ ከንፈሬን ከደነው

"ተይ እንዳትይኝ!" አለኝ ዝም አልኩትና ከንፈሬ ላይ የጫነውን ጣቱን ስሜው

"እሺ እንነሳ!" አልኩት። ተመልሰን መኪናችንጋ እስክንደርስ ምንም ሳናወራ እሱ በመንሸራተቻው እኔ በጫማዬ ተጓዝን። እቤት ደርሰን ሻወር ሊወስድ ሲገባ እህቱ ሳሎን ተቀምጣ መፅሃፍ እያነበበች ነበር። አጠገቧ ተቀመጥኩ። ምን እንደምላት አስቀድሜ ያሰብኩት ነገር አልነበረም።

"ቃል እገባልሻለሁ እሱን የሚጎዳ ምንም ነገር አላደርግም!" አልኳት። የሆነ ከአፌ እስኪወጣ እየጠበቀችው ያለ ነገር ይመስል ስግብግብ ብላ ተጠመጠመችብኝ።

"አመሰግናለሁ። አመሰግናለሁ ። አመሰግናለሁ" ብዙ ጊዜ አለችኝ ጭምቅ አድርጋ ይዛኝ።

ቤተክርስቲያን ፀሎት አድርሶ አንደሚመለስ ሰው ያለ ስሜት ...... ለካህን ሀጢያቱን ተናዞ እንደሚመለስ ሰው ያለ ስሜት ..... ተቀበለኝ። ወደ መኝታ ቤት እየሄድኩ ለእሷ ያልኳትን ለራሴ ደጋግሜ እያልኩ ነበር

"ምንም ቢሆን የሚጎዳው ነገር አላደርግም!!" ከኋላዬ ገብቶ የመኝታ ቤቱን በር ሲዘጋው ወደርሱ ዞርኩ። ፎጣውን ወገቡ ላይ አሸርጦ የረጠበ ፀጉሩን ወደ ኋላ እየላገ በስድ አይን እያየኝ ነበር። እንዲህ ካየኝ መቼ ነበር? ወር? ስድስት ሳምንት? እኔንጃ ..... ዘልዬ እጄን አንገቱ ላይ ጠምጥሜ በእግሬ ወገቡን ዞርኩት። "

ምንም ቢሆን የሚጎዳህ ነገር አላደርግም እሺ!" እያልኩት አንገቱን .... ትከሻውን .... ጸጉሩን ... ጆሮውን ያገኘሁትን ቦታ እስመዋለሁ! ያልኩበት ስሜት ገብቶት ይሁን አላውቅም እየደጋገመ

"አውቃለሁ! አውቃለሁኮ" ይለኛል። መልሼ ነግረዋለሁ መልሶ "አውቃለሁ" ይለኛል።
ያሸረጠው ፎጣ ተፈታ (አይበቃችሁም እንዴ ምንድነው?) ለፍተን በጀርባችን እንደተጋደምን።

"ፔሬድሽ መምጣት አልነበረበትም?" አለኝ:: ቆጠርኩ .....ከተጋደምኩበት ብንን እንዳለ ሰው ተስፈንጥሬ ተነሳሁ

"ኦህ ኖ !" አልኩኝ። ተስፈንጥሮ ተነሳ

"በፍፁም! በፍፁም አይሆንም! በፍፁም እንደእኔ አይነት ልጅ እንዲወለድ አልፈልግም።" እንዲህ ጮሆብኝ አያውቅም። ሁኔታው አስደነገጠኝ!!

ህመሙ በዘር እንደሚተላለፍ ያነበብኩት ትዝ አለኝ።

እህእ አልጨረስንማ ታዲያ

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ታክሲዋ ከታክሲነት ወደ ክለብነት ተቀየረች ።
በጃቦኒ ሆኖ መሪውን የሚዘውረው ሹፌር ድራፍት ማዘዝ እስኪቀረው ድረስ ቧረቀ።
ጭራሽ አንድ ሞቅ ያለው ተሳፋሪ ተነስቶ እንደመደነስ ሁሉ ቃጣው ።
ይህን ጊዜ አንድ እድሜያቸው የቆጠረ.. .በጉልምስና እና እርጅና መሀል የተጣዱ አባት ... "ሹፌር ኸረ ሙዚቃውን ቀንስልን በመድሀኒያለም " አሉት ጮክ ብለው።
ሹፌሩ እቴ!
እንኳን ሰው የጮኸበት ዝንብ ያረፈበት እንኳ ሳይመስለው ሸመጠጠ። ባልሰማ ላሽ አላቸው /ሰምቶዋቸውም ሊሆን ይችላል :) /
ሽማግሌው "ሹፌር ሰማኸኝ? " አሉ ቀጥለው ።
ዝም!
በዚህ ቅፅበት ታድያ አንዲት እናት ቱግ ብለው "ደግሞ ደህና ብብት እንዳለው ሰው በካኒቴራ ይዝናናል " ብለው አንጓጠጡ ።
እውነትም የሹፌሩ ብብት ያሳቅቃል ። ወደ ቡኒ መልክ ያጋደሉ ጠጉሮች ብብቱን ሞልተውታል ።
"ሰውዬ የእንጦጦ ጫካን በብብትህ ይዘህ ነው እንዴ የምትዞረው? ... ፓርኩ ግን አይታየኝም " አለች አንዲት ዘመናይ ሴት ለጥቃ ።
ለሽማሌና አሮጊቷ ሀፍረት ይሁን ንቀት አድሮበት ዝም ብሎ የነበረው ወያላ ...
"ዝም በይ አንቺ ፔሬድ የላሰች ውሻ " ብሎ ሞሸለቃት ።
እግዚኦ ሀበሻ ይሄ ሁሉ የስድብ ማህደር ተሸክሞ ነው የሚዞረው ? እስክል ድረስ ታክሲዋ ወደ 7ተኛ ሰፈር ተቀየረች።
የቡና ቤት ሴቶች ራሱ ይሄን ያህል ሲሰዳደቡ አይቼ አላውስም።
በመሀል ሽማግሌው.. .የመኪናዋን መስኮት ከፈት አድርገው
"ፎሊስ ይሄ ዋልጌ ሹፌር አስቸገረን" ብለው አንባረቁ። ሹፌሩ ወታደር ፖሊሱን ባላየ ሸልቅቆ ሊያልፍ ሲል አስቆመው ።
"ችግርህ ምንድነው? " ብሎ ሹፌሩን ተቆጣው።
"አብርሮ ሊደፋን ነው ልጄ! ይሄ ሰው ፓይለት ነው ወይስ የታክሲ ሾፌር ?" ብለው ጠየቁ አሮጊቷ።
"ምን ይሄ ብቻ ይሄ የጁንታ ርዝራዥ የሆነ የቀን ጅብ አልደመርም ብሎ ሲፎክርና ሲያሽላላ ነበር " ብሎ ቀጠለ አንዱ ስጋው በላዩ ላይ አልቆ የሞገገ ነፍሰ ቀጭን ሰውዬ :)
የሌዘር ጃኬቱ ላዩ ላይ ነትቦ በኗል።ይሄን ጭማሪ ወሬ ከየት አምጥቶ እንደሰካው እንጃ!
ይህን ጊዜ ወታደር ፖሊሱ ሹፌርና ረዳቱን እንደኳስ አንጠባጠባቸው ።
"ፎሊስ!" ብለው የተጣሩት ሽማግሌ የወታደሩ ርግጫ ጠንከር ማለቱን ሲረዱ ...
"አይ ፎሊሱም አበዛው ቆለጣቸውን ሊያበረው ነው እንዴ? " አሉ በለሆሳስ ።
"ሰውዬ ዝም በሉ ...አለበለዚያ ዱላው ወደ እርሶም ይዞራል " ሲላቸው ቀጭኑ ሰውዬ ሁላችንም ኩምሽሽ ብለን ተኮማተርን።
ወታደሩ ረግጦ ካስገባቸው በኋላ...
"ችግር ካለ ቁጥሬን ያዙ " ብሎ ሳናገር አቃጣሪው ሰውዬ ስልኩን አውጥቶ መጠቅጠቅ ጀመረ ።
በራፕ ሙዚቃ ሲያደናቁረን የነበረው ሹፌር ከባምቢስ እስከ ሜክሲኮ ድረስ በበዛወርቅ ትዝታ ሙዚቃ አጅቦን ደረሰ።
እኔ በመሀል ወታደሩን ሰውዬ የት እንደማውቀው ስብሰለሰል ቆይቼ የልጅነት ጓዴ ቦቄ ስለሆነ ሰላምታ ሳልሰጠው ማለፌ ቆጨኝ።
ቦቄ ከመዋዕለ ህፃናት ጀምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ አብሮኝ የተማረ ልጅ ነበር ።
ሜክሲኮ እስክንደርስ ድረስ ሹፌሩ ባጉረመረመ ቁጥር ቀጭኑ ሰውዬ ስልኩን እያወጣ ሲያስፈራራውም ነበር።
መዳረሻ ቦታችን ደርሰን ሁሉም ተሳፋሪ ከወረደ በኋላ ሹፌሩ ጮክ ብሎ.. .
"አንተ አቃጣሪ ያደረከው ቆዳ ሌዘር አንተ ላይ የቆየውን ያህል በሬው ላይ አልቆየም። ሾክሿካ " ብሎ ተሳደበና አቅጣጫውን አዙሮ ተፈተለከ ።
እኔ ቀጭኑን ሰውዬ ተከተልኩት ። ልክ ከስሩ ስደርስ.. .
"ወንድም " ብዬ ተጣራሁ.. .
"አቤት "
"እባክህን የቅድሙን ወታደር ስልክ ቁጥር ስጠኝ። የልጅነት ጓደኛዬ ነበር " አልኩት ...
ነፍሰ ቀጭኑ ሰውዬ ለረዥም ደቂቃዎች ከትከት ብሎ ሲስቅ ከቆየ በኋላ.. .
"ሹፌሩን ላስፈራራ እንጅ ስልክ ቁጥር መመዝገብ አልችልም " ብሎ ኩም አደረገኝ :)

...ሚካኤል አስጨናቂ ....

@wegoch
@wegoch
@paappii
ልንጋባ ሁለት ሳምንት ሲቀረን እጮኛዬ ጤነኛ እንዳልሆነ አውቅኩ
(የመጨረሻ ክፍል)

ልጄን ወይ እወልደዋለሁ ወይ አስወርደዋለሁ። ምርጫ ነው። ህይወት ራሱ የምርጫችን ውጤት አይደል? ልክ እሱን ማግባት አለማግባት ራሱ ምርጫዬ እንደሚሆነው?

"ተገላገልሽ!" ትለኛለች ያቺ ታይላንዳዊቱ ወዳጄ ጠርታኝ። ሁለታችንም የምናውቀው አንድ ምግብ ቤት ባለቤት የሆነ ሰውዬ ያለሁበትን ሁኔታ ነግራው ሊያገባኝ እና ሊረዳኝ እንደሚፈልግ እየነገረችኝ።

"ለምን ሊረዳኝ ፈለገ?"

"ምክንያቱ ምን ያደርግልሻል? የመኖርያ ፈቃድሽን አይደል የምትፈልጊው? ደሞ አሪፍ እድል ነው። ካልፈለገች አብራኝ አለመኖር ትችላለች ብሏል። ቅረቢውና ከወደድሽው አብረሽ ትሆኛለሽ። ካለበለዚያ በቃ ለመኖርያ ፈቃድሽ ሲባል የውሸት ጋብቻ ይሆናል ማለት ነው።"

(እዩት እድሌን ግን ... ይሄ እድል ስፈልገው የት ነበር? ዛሬ ስለፔር ማሰብ ስጀምር .... ራሴን የማልመልሰው ርቀት ያህል ከሄድኩ በኃላ ነው የሚረዳኝ ሰው የሚገኘው? የት ነበር? )

"አልፈልግም" አልኳት ሳስብ ቆይቼ

"እና ከእብድ እጮኛሽ ጋር መጋባቱ ይሻልሻል?"

"ሁለተኛ እብድ እንዳትዪው!" ብዬ ዘልዬ ተነሳሁ

"ኦ ማይ ጋድ ፍቅር ይዞሻል" አለችኝ በጣም የተገረመች መስላ

አልመለስኩላትም። ትቻት እየሄድኩ የወሰንኩት ውሳኔ ይቆጨኝ እንደሆነ አስባለሁ። ህይወት ራሱ የምርጫችን ውጤት አይደል? እሱን መረጥኩ። ምርጫዬ የሚያፈራው ፍሬ መራራም ይሁን ጣፋጭ ..... እሱን መረጥኩ::

"ማውራት አለብን!" አልኩት እቤት እንደገባን

"እሺ" አለኝ።

"ልጃችን የባይፖላር ተጠቂ ላይሆን የሚችልበት እድልምኮ አለው" አልኩት::

"ሊሆን የሚችልበት እድልም ሰፊ ነው።"

"እሺ ባይሆንስ?"

"ዜሮ ምናምን ነጥብ ቢሆን እንኳን የመሆን እድሉ በፍፁም በፍፁም ልጄን እኔ የማልፈውን ስቃይ እንዲያልፍ አልፈቅድም።"

"እሺ እኔ ልጄን ማስወረድ ባልፈልግስ?"

"እባክሽ እዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አትክተቺኝ። እባክሽ?" አለኝ

ዝም አልኩ። ወሬውን ከዛ በላይ መቀጠል አልፈለግኩም። ተጨማሪ ጥያቄ ብጠይቀው የሚመልሰውን መልስ ፈራሁት። ወይ ልጄን ወይ እሱን መምረጥ አለብኝ:: ልጄን መውለድ እፈልጋለሁ ብለው መጋባቱ ይቅርብኝ እንደሚል እንኳን ልቤ እያወቀው .... እሱ የምርጫው አጣብቂኝ ውስጥ ላለመግባት እኔን እንድመርጥ እያስገደደኝ እንደሆነ እንኳን እያወቅኩ እሱን መረጥኩ!! .... ደግሞም ልጄስ እሱ እንደፈራው አባቱ የሚያልፈውን ሰቀቀን የሚደግም ቢሆንብኝስ? ከአንድ ልጄ ውጪ ሌላ ልጅ መውለድ ብፈልግም አልወልድም።

እሱን ማግባት የሚያስከፍለኝን በሙሉ አሰብኩት። አለማግባቱም የሚያስከፍለኝን አሰላሁት። ከእርሱ ጋር መሆን ብዙ ያስከፍለኛል። እንደዛም ሆኖ ማድረግ የምፈልገው ከእርሱ ጋር መሆኑን ነው።

"እሺ!" አልኩት በመጨረሻ

"እሺ ምን?" አለኝ ከአፌ የሚወጣውን ለመስማት እየጓጓ

"እሺ ልጅ አይኖረንም ግን አንድ ነገር ቃል እንድትገባልኝ እፈልጋለሁ!"

"ምንም ይሁን ምንም!.... ምንም ነገር!!" አለኝ በደስታ እያቀፈኝ

"መድሃኒትህን መቼም ቢሆን ሳታቋርጥ እንደምትወስድ ቃል ግባልኝ።"

"ቃሌ ነው።"

ሰርጋችን በቤተክርስቲያን እንዲሆን የመረጥኩት እኔ ነኝ። ቄሱ ፊት ቆሜ አይን አይኑን እያየሁት

"በህመሙም በጤናውም በድህነቱም በሃብቱም ........" ብዬ እየማልኩ እህቱን አያታለሁ ለሚያያት ሰው ግድ ሳይላት እንባዋን ትነዳዋለች።

ጨርሰናል!!!!!

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
መሳቅ ሽቼያለሁ። መንከትከት ፈልጌያለሁ። ነገር ግን ለሐሴት፣ ለተድላ፣
ለፍስሓ፣ ለፈገግታ ምክንያት አጥቼያለሁ። ከንፈሬን መግለጥ ከብዶኛል።
ሰውነቴ በጭንቀት፤ አእምሮዬ በሐሳብ እንደበገና አውታር ተወጥሯል።
ከብፌ ላይ በተርታ እንደሚወድቁ የሸክላ ሳህኖች ከወለል ላይ ልጋጭ
ተዘጋጅቼያለሁ። እንዲህ ማን እንዳስቀመጠኝ አላወቅሁም።
ደግሞ





ት ነው።
ደግሞ

ት ሊለኝ ነው።
ደግሞ እንደ ቅል




ጥ ነው።
ደግሞ እንደ ገል




ር ነው።
ደግሞ ሕመም እንዳዘለ፤ በቤት ውስጥ እንግዳ ሲመጣ ውኃ
እንደሚጠጣበት ያማረ ብርጭቆ ከእጅ ወድቄ


ቅ ልል ነው።
ከክርስቶስና ከገብርኤል ጋር በዕንባ ተራመድሁ። ሰው ነኝና የመለኮት ቋንቋ
አይገባኝም። ልሳናቸው ሐምራዊ ቀለም ይዞ እንደዥረት ይፈስሳል።
“ምናለበት የሚያወሩት ቢገባኝ?!” እላለሁ። ደጋግሜ የማልደርስበት ቦታ
ላይ ስለበላኝ ቁስል እነግራቸዋለሁ። “ክርስቶስ ሆይ በላኝ እኮ!”
“ገብርኤልዬ አሳከከኝ እኮ!” በዕንባ እንደጨርቅ የራሱ ዓይኖቼ
ይንከላወሳሉ። ሸንበቆ አንገቴ ሊሰበር ደርሷል። ሕፃን ነኝና የትልቅ ሰው
ጨዋታ አይያዝልኝም። የሚሰሙኝም የማይሰሙኝም ይመስለኛል። ጮክ
ልበል ይሆን? ልንጠራራ ይሆን? ዓይኔ እስኪጠፋ ላልቅስ ይሆን? ወይስ
እምነት ማን ያበድረኛል? የቱ ደገኛ ነው የሚጨምርልኝ? አለማመኔንስ
የሚረዳው?
የፈሰሰን ውኃ በጸሎት ማፈስ ይቻላል? ወደ ሕዋ አንጋጥጬ የማጣትንና
የማግኘትን በር አየሁ። አንዱ ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቶ፤ አንዱ ወለል ብሎ
ተከፍቷል። እየበረርኩ “አንኳኩ ይከፈትላችኋል…” እንደተባለ እንዲሁ በሩን
ዘበዘብሁ። ለእኔ ጸሎት ሄጄ የሰው ለቅሶ አየሁ። ሰዉ ያለቅስ የለ እንዴ? …
አለቃቀስ አይቼ የዚህ ሰውስ በእምነት የሚደረግ ታላቅ ልመና ነው
አልኩኝ። በቀትር የቤተክርስቲያን ደጅ ላይ ተንበርክኮ በዓይኖቹ ክረምትን
የሚያውጅ ሰው ምንጭ ዕንባዬን አሳፈራት። ሰው ከለቀስተኛ ጋር ያለፈቃዱ
ተነክቶ እንዲያለቅስ እንዲሁ ከጸሎተኛ ሰው ጋር ዳር ይዤ አለቀስሁ።
መጠለያ ፈለግኩ። የስቃዬ ቀን ረዘመ። መቅኔው እንደተመጠጠለት
አጥንት ባዶ ሆንኩኝ። በዋጋ ቀለልሁኝ፤ በሕመም ከበድኩኝ። ሰው ፈልጌ
ሰው አጣሁ። ማን ጋር ልደውል? ከማን አንደበት አጽናኝ ቃል ልስማ?
በምሄድበት መንገድ ዕንባዬ ከቁጥጥሬ ውጪ ፈሰሰ። ረዥም መንገድ
ለብቻዬ ሄድኩኝ። በጣም ረዥምምም ጎዳና በሌጣ እግሬ ተጓዝሁ። ቤት
ስደርስ ደክሞኝ ብተኛ… ፎጣ ብሆን ብዬ። መንገዱ አጥሮ ዕለቱ ረዘመ።
እንደሰከረ ሰው ተንገዳገድሁኝ። በደረቅ ሌሊት እንደ ልጅ ባነንሁኝ። ወደ
ግድግዳዬ ዞሬ እስከሚነጋ በደካማ ቃላት ልመናዬን ያዝኩኝ። እየጸለይኩ
እንቅልፍ ወሰደኝ። ማለዳ በሕመም ተቀበለኝ። አዲስ ልብስ ገዛሁኝ።
ገላዬን ታጥቤ አንድ በአንድ ለበስኩኝ። መስታወት ፊት ቆምኩኝ።
እንዳማረብኝ ግን እንደከፋኝ አየሁ። መንገደኛ ይላል “ዛሬ አምሮብሃል” ።
ሁሉም ሰው ከውጪዬ እንጂ ከውስጤ አይደለም። እና ሌላውስ ሰው
እንዴት አድሮ ይሆን? ጎዳና ላይ ሽር ብትን ከሚለው፤ ቂቅ ብሎ ከለበሰው
መሃል ስንቱን ሰው ከፍቶታል?
መንገዱን ተሻግሮ ነጭ ግርማው የሚያስፈራ መልአክ የሚመስል የቀትር
ሠይጣን ይደንሳል። ከሁኔታው ያለለት፤ አንዳችን ነገር የሰመረለት
ይመስላል። ጠጋ ብዬ እጠይቃለሁ።
“ምን አግኝተህ ነው?”
“ሕልምህን ታውቃለህ!” ይለኛል።
“ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ እንዲል እንኳን ደስ አለህ!” እለዋለሁ።
ደስ እንደማይለኝ እያወቀ፤ ለይስሙላ ያልኩትን ይዞ “እንኳን አብሮ ደስ
አለን!” ይለኛል።
“ብቻ ግን…”
ዳንሱን አቁሞ “ ብቻ ግን ምን??? ” ሲል ይጠይቃል።
“ብቻ ግን ደስታህ እንደሚቀጥል ርግጠኛ ሁን!” ብዬው አልፋለሁ።
ይስቃል። ሠይጣንስ ማን አለው? ሥራው ምንድነው? ማነው የቀጠረው?
ምናገባኝ!
የጭንቅ ወዳጆቼ “ተሥዬልሃለሁ! ” “እጸልይልሃለሁ እና ደግሞ ቅዳሜና
እሁድ አገኝሃለሁ” “በታመምኩበት ወቅት ስለሆነ የጸለይኩልህ የምሰማ
ይመስለኛል” “እጸልይልሃለሁ ... እና ደግሞ ሁሉም ያልፋል። በምድር
እንዳያልፍ ሆኖ የተፈጠረ ኅዘንና ችግር የለም።” ይሉኛል።
ከራሴ ጋር እነጋገራለሁ።
“እስኪያልፍ እንዴት እሆናለሁ?”
“ሕፃን ነህ እንዴ? እደግ እንጂ! ”
የምር መሳቅቅቅቅ በጣም ፈልጌያለሁ። ግን አልቻልኩም። እንዴት ብዬ?
የጠፋብኝን ፍለጋ ብዙ በር ያለማቋረጥ አንኳኳሁ። ደበደብሁ። እና
ያጠያይቃል። ማለት ጠፋብን ያልነው ነገር ባንኳኳነው የበር ብዛትና
የድምፅ ኃያልነት በኩል ምን ያህል እንደፈለግነው ይረዳል? ወይስ እርሱን
ፍለጋ ባንኳኳነው የበር ብዛትና ድምፅ ይረበሻል? እና እያንኳኳሁ እጄ ዝሎ፤
ድምፄ ሰልሎ፤ እንዲያው መሳቅ እንዳማረኝ እ'ደጁ ላይ ተኛሁ።
በእንተ ኅዙናን ወትኩዛን ናስተበቁዕ ከመ እግዚአብሔር ይናዝዞሙ ፍጹመ።
(እግዚአብሔር ፈጽሞ ያረጋጋቸው ዘንድ ስላዘኑና ስለተከዙ ሰዎች
እንማልዳለን።)


©እሱባለው አበራ

@wegoch
@wegoch
@Mahletzerihun
"ጳውሎስ ሆስፒታል እንሂድ" አልኩ፡፡ ስልኩ ከመዘጋቱ በፊት የሀኪም ቤቱን ስም ከርቀት ሰምቼው ነበር፡፡ " ግን እኮ አለርት ሆስፒታል ይቀረበናል" አለኝ አንድ ጎረቤታችን " ወንድሜ እዛ ነው ያለው እዛ ውሰዱን" አስካሁን እንባዬ ማቆሚያ አላገኘም፡፡ ' እንዴት ግን ወንድሜ እንደሆነ አሰብኩ? አባቴም ቢሆን ሹፌር ነው፡፡ እንዴ! ሌላ ዘመድስ ቢሆን?' የማይፈታ እነቆቅልሽ ለራሴ እየጠየኩ ሆስፒታሉ በር ላይ ደረስን፡፡ 'የድንገተኛ አደጋ ' ወደሚለው ክፍል ገሰገስኩ፡፡ እናቴን የት እንደወሰዷት አላውቅም፡፡የክፍሉን በር ልከፍትስታገል አንዲት ነርስ የተራመደች ወደኔ መጣች፡፡
"የልጁ ቤተሰብ ነህ ?" አለችኝ፡፡ መልስ አልሰጠዋትም፡፡ "በቃ እሱ ነው ፤ወንድሜ ፤ አንድ ቀን እንኳን ወጉ ደርሶኝ ወንድሜ ብዬ ያልጠራሁት ምስኪኑ ወንድሜ " ብቻዬን እንደ እብድ ማውራት ጀመርኩ፡፡ ነርሷ በየደቂቃው እየመጣች " ተረጋጋ የኔ ወንድም" ትለኛለች፡፡ ተረጋጋ ባለችኝ ቁጥር ህመሜ እንደሚብስ አልገባትም፡፡ ፊቴን ወደግድግዳው እንዳዞርኩ የክልሉ በር ሲከፈት ተሰማኝ፡፡ ፊቴን መለስ አደረኩ ዶክተሩ ጓንቱን እያወላለቀ ወደኔ መጣ፡፡ "ዶክተር የልጁ ቤተሰብ ነው" አለች ነርሷ ወደኔ እያየች ፡፡እኔ ለሰከንዶች ዶክተሩን እንደ እግዜር ቆጥሬ መልካም ነገር እንዲነግረኝ ተመኘው፡፡ "አንተ ምኑ ነህ የኔ ወንድም?" አለኝ፡፡ የሀዘን ስሜት ፊቱ ላይ ይነበባል፡፡
" ወንድሙ " አልኩ ባጭሩ፡፡
" ይኸዉልህ .....ምን መሰለህ...... ወንድምህ በደረሰበት አደገኛና አሰቃቂ አደጋ ........ሂወቱ አልፋለች፡፡ ይቅርታ በጣም አዝናለው" የቺን ቃል እንደቀላል ተናግሮ ወንድሜ ወዳለበት ክፍል እንድገባ ጋበዘኝ ፡፡ የእግሬ ኮቴ ከተኛበት እንዳይቀሰቅሰው ይመስል ቀስ ብዬ ገባሁ፡፡ ነጩን ጨርቅ ከፊቱ ላይ አነሳውት፡፡

ኬት መቶ ነው 32 አመት ያልታየኝ ቁንጅና ዛሬ የታየኝ፡፡ "የኔ ውድ ወንድም ቆንጅዬ ኮ ነህ" እንባዬ ፊቱ ላይ ይንጠባጠባል ፤ ፀጉሩን አሻሻለው "አይ አንተ አሁን እስኪ ምን አስቸኮለህ ፤ እኔ የማልጠቅመው ፤ ለአንድ ወንድሜ የማልሆን ከንቱ ሰው እያለሁ አንተ ምን አስቸኮለህ " የህመምን መጨረሻ በዚያች ቅፅበት ታመምኩ "ወንድሜ ግን ታውቃለህ ? በጣም ነውኮ ምወድህ ፤ ማርያምን በጣም ነው ምወድህ "
የ'ናቴ ድምፅ ከሩቅ ይሰማኛል
" የታል ልጄ ? ልጄ የታል ? ልጄን አምጡልኝ እህህህህህህ"
ልጇ ወዳለበት ይዘዋት ገቡ
" እሜ ልጅሽ እኮ ..........." ትንፋሼ የቆራረጣል " እሜ ልጅሽ እኮ ሸወደን ፤ ስራ ነው ምሄደው ብሎ ሸወደን ፤ ማርያምን ሸወደን እሜ " እናቴ ደም ታነባለች፡፡ አሷስ ቀን በቀን ቁርሱን አብልታ ፤ ምሳውን ቋጥራ ፤ ግንባሩን ስማ ለምትሸኘው ለጇ ደም አለቀሰች፡፡ እኔ ግን አንድ ቀን እንኳን ሰላም ዋል ሳልለው ላመለጠኝ ወንድሜ ምን ላልቅስ? ምን ላንባ? ፡፡

ዛሬ ሁለተኛ ቀኑ ነው የኔ ውድ ወንድም ከተሰናበተን፡፡ እናቴ 'እኔ አፈር ሳለብስ የኔ ልጅ አፈር አይለብስም' ብላ አላስቀብርም ብላ ነበር፡፡ ዛሬ እንደመንም ሽማግሌዎች መክረዋት እሺ አለች፡፡
የቀብር ሰአት ሲደርስ ልብሴን ለመቀየር ወደ ክፍሌ ገባው፡፡ ክፍሌ ገብቼ ከዛሬ ስምንት አመት በፊት ገና ስራ እንደያዘ በመጀመሪያው ደሞዙ በሌለው ገንዘብ የገዛልኝን ጅንስ አወጣውት፡፡

አይገርምም ደሞዙ 400 ብር ነበር፡፡ 'የመጀመሪያ ደሞዜ ነው ለራሴ አንድ ነገር ላድርግበት' ሳይል 200 ብር ተበድሮ ለኔ ሰማያዊ ጅንስ ገዛልኝ፡፡ ከዚህ በፊት የልብስ ቀለም አማርጬ አላውቅም፡፡
ያን ቀን ግን ለዘላለም የማይጠገን ስብራት ወንድሜን ሰበርኩት፡፡

ከስራ ደክሞት ነበር የመጣው፡፡ ወደቤት ሲገባ ግን ሙሉ ፈገግታን ተላብሷል፡፡ ብረት ሲያቀልጥና ሲቀጠቅጥ የዋለ አይመስልም ነበር፡፡ ፊቱ ግን እሳት የለበለበው
ለብቻው ቅርፅ ይዞ ያስታውቃል፡፡
እናቴ ፤ አባቴና እኔ ክብ ሰርተን ተቀምጠናል፡፡ ወንድሜ ነጫጭ ጥርሶቹን እያሳየ ገባ፡፡
"ሰላም አመሻችሁ" ፈገግታው አልተለየውም ነበር፡፡
"እግዚሀር ይመስገን እንዴት አመሸኽ" አባቴም እናቴም እኩል መለሱለት እኔ ግን ፊቱን እንኳን ቀና ብዬ አላየውትም፡፡
" እሜ......... ዛሬ የመጀመሪያ ደሞዜን ተቀበልኩ ፤ በመጀመሪያ ደሞዜ ደሞ......... ከሚቀጥለው ወር ደሞዜ ላይ 200 ብር ተበድሬ ለወንድሜ ጅንስ ሱሪ ገዛውለት" አላት የደስታ እንባ እየተነናነቀው፡፡
ሱሪውን ከፌስታሉ እስኪያወጣው ቸኩሎ ነበር፡፡ እናቴ የምርቃት ናዳ ታወርድበታለች፡፡ እኔ ግን አሁንም አልዞርኩም፡፡ ፌስታሉ አልፈታም ሲለው ቀዶ አወጣው፡፡ የሱሪውን ወገብና ወገብ ይዞ "ወንድሜ እየውማ አያምረም? ብታይ እኮ 600 ብር አልሸጥም ብሎኝ ጉልበቱ ላይ መውደቅ ነው የቀረኝ
ላለቅስ ሁላ ነበር" አሁንም አይኑ እንባ አቅርሯል፡፡ "ሰማያዊ ጅንስ ከመቼ ጀምሮ ነው ሳደርግ አይተኸኝ ምታቀው?" መለስኩ፡፡
ፊቱ ከብርሀን በቅፅበት ወደ ጨለማነት ተቀየረ፡፡ ማንም ሰው ምንም አልተናገረም፡፡ በቆመበት ጥዬው ወደ ክፍሌ ገባሁ፡፡
ታዲያ በምድር እንደኔ አረመኔ ሰው ይገኛል? በፍፁም አይገኝም፡፡
የትኛው ወንድም ነው ወንደሙ ላይ የዚን ያህል የሚጨክን? ፤ የትኛው ወንድም ነው ወንድሙ እጁ እስኪላጥ ብረት ቀጥቅጦ ያመጣለትን ስጦታ የሚንቅ? ኸረ እኔ ሰው አደለውም፡፡ ሰው ብሎ ሚጠራኝም ካለ ሰውነት ምን እንደሆነ አልገባውም ማለት ነው፡፡

ጥቁሩን አውለቄ ሰማዊውን ጅንስ መልበሴ ሰውን ሁሉ አስገርሞታል፡
የመጣው ሰው ሁሉ "አሁን ይሄ ወንድም ነው? እንዴት በቀብር ቀን ሰመያዊ ይለብሳል?" እያሉ በሹክሹክታ ያሙኛል፡፡ በማንም ግን አለፈረድኩም ምክንያቱም የምፈርድበት አንደበት የለኝማ፡፡

የወንድሜ እሬሳ በሰው ለቅሶ ታጅቦ ፤ በእናቴ የደም እንባ እየተመራ ቤተ ክርስቲያን ደረሰ፡፡ ስርአቱ ከተፈፀመ ቡኃላ ወንድሜ አፈር ለበሰ፡፡እኔም አረመኔው ወንድሜን በእንባ ሸኘውት፡፡

ይሄ ሁሉ ከሆነ እንሆ ስምንት አመት ሆነ፡፡ ከዛ ሁሉ ህመም ቡኃላ በወንድሜ ሱፍ ተመርቄ በምርቃቴ ቀን በወንድሜ ሱፍ አገባሁ፡፡ እናም ከስምንት አመት በፊት የጣልኩትን ጥቅስ በድጋሚ በፍሬም አሰርቼ ከግርግዳችን መሀል ለመሀል ሰቀልኩት፡፡

""""""""""'""""
""""""!! ሁሉም ያልፋል!!""""''''"
""'''"''"""""""""

፡ የጌትነት ልጅ ፃፈ

@wegoch
@wegoch
@paappii
ድሮ አስረኛ ክፍል ተማሪ ሳለን ነፍሰ ቀጭኑ ኬሚስትሪ መምህራችን እንዲህ ሲሉ ጠየቁን ።
ውሀ ከምን እና ከምን ንጥረ ነገሮች ነው የተፈጠረው ?🙂
ብዙ ተማሪዎች ይህችን ቀላል ጥያቄ ለመመለስ ተቅለበለብን ። መምህሩ ግን ከሁሉም ተማሪ ይልቅ ትኩረታቸውን ስንሻው ላይ አድርገው እንዲመልስ አስገደዱት ።
ስንሻው ከእንቅልፉ የተነሳ ይመስል አይኑን አሻሽቶ ትንሽ ቆየና መምህሩ ጥያቄውን እንዲደግሙለት ጠየቃቸው። /በነገራችን ላይ የስንሻው አባት ልጃቸው ትምህርት እንዳይገባው ተደግሞበታል ብለው ስለሚያስቡ እሱን ይዘው ያልተንከራተቱበት ፀበል አልነበረም ። ኋላ ላይ ቢታክታቸው ጊዜ እርግፍ አድርገው ተውት ! እርሱም ትምህርት አይንህን ላፈር ብሎ ማንበብ እና ማጥናቱን እርግፍ አድርጎ ተወው /
"እኛ የምን ጠጣው ውሀ ከምንና ከምን ውህደት ተፈጠረ ? " ብለው ጥያቄውን ደገሙለት ።
ውሀ ልማት እና ቀበሌ ተዋህደው በገጠሙት የቧንቧ መስመር ነው የተፈጠረው ! ብሎ ሲመልስ ያልደነገጠ ተማሪ አልነበረም ። ሁላችንም እያሾፈ ነው ብለን በትኩረት አየነው ።
እሱ እቴ !
ልቡ ደጭ እንኳ አላለም !
“ስ ! ውይ ይቅርታ” አለን መልሶ .... በቃ ኦክሲጂንና ሀይድሮጂን ታውሰውት ነው ማለት ነው ብለን ማስተካከያውን በጉጉት መጠባበቅ ያዝን !
“ውሀ ልማት እና ሰሜን ሸዋ ዞን በመተባበር ነው “ ብሎ እርፍ አለው ።
ነፍሰ ቀጭኑ መምህራችን በንዴት ተነፋፍተው ነብር አከሉ ! አለ አይደል የቤት ውስጥ ድመት ስትቆጣ እንዴት ነው ኩፍ የምትለው ?
መምህራችን ኩፍ አሉ ።
በስመአብ !
አስተማሪ ሲናደድ ለካ እንደዚህ ያስፈራል ?
ከአስተማሪም ሁሉ ደግሞ ኬሚስትሪ አስተማሪ ሲናደድ በጣም ያስፈራል ። የሆነ ሰልፈሪክ አሲድ ከላብራቶሪ አንስተው ፊቱ ላይ የሚከለብሱበት ሁሉ መሰለን ።
“ተነስ !”
ስንሻው ተነሳ ።
“እነ ሚካኤል ፣ እነ እዮብ እነ አቤል ኢንጅነር ወይ ዶክተር ሲሆኑ ሻንጣ ተሸካሚያቸው እንደምትሆን አልጠራጠርም “ ብለው ሞራሉ ላይ ቀዝቃዛ ውሀቸውን ከለበሱበት ።
እንደፈራነው ከወራት በኋላ ስንሻው ማትሪክን ወደቀ ። እኛ ፈተናውን በጥሰን አለፍን ።
እኛ አስራ ሁለተኛ ክፍል አልፈን ለዩንቨርሲቲ ስንዘጋጅ ስንሻው የሆነ ትምህርት እንደከረሜላ አሽጎ የሚሸጥ ኮሌጅ ዲፕሎማ መማር እንደጀመረ ሰማን ።
ግቢ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስንሆን ስንሻው ቀበሌ ስራ አጊንቶ መግባቱ ተነገረን ። ያኔ በሱ ሙድ ያልያዘ አልነበረም ።
እንደውም አንድ ቀን በድሉ የሚባል ቸካይ የነበረ ተማሪ ወደኔ ጠጋ ብሎ "ስንሻው በዚህ ድድብናው ቀበሌ ስራ ማግኘቱም ተመስገን ነው ብሎ ገለፈጠ ። "ስንሻው እኮ ቀን ስራ እንኳ ይበዛበታል ። እንደ ህንዶች ሰባቴ ቢፈጠር ሰባት ጊዜም ትምህርት አይገባውም" አለኝ ቀጥሎ ።
ስንመረቅ ግን የነፍሰ ቀጭኑ ሰውዬ እርግማን ለስንሻው ምርቃት ሆኖ እርፍ አለው ።
የከተማችን አስተዳደር ተመራቂ ተማሪዎች ተደራጅታችሁ ኮብልስቶን አንጥፉ ምናምን ብሎ በስብሰባ ሰበብ ሲጀናጀነን ስንሻው ተከብሮ የከተማችን ከንቲባ ሆኖ ነበር ።
ጭራሽ እዛ አመዳችን ቡን ባለ ተመራቂ ተማሪዎች ፊት ቀርቦ ስለ ስራ ፈጠራ ሰፊ ማብራሪያ ሰጠን ። ኢንጅነር ነን ዶክተር ነን ብላችሁ አትኮፈሱ የጀበና ቡና ብታፈሉ ትችላላችሁ ። ለምሳሌ ሚካኤል እዮብ አቤል በኢንጅነሪንግ እና ዶክትሬት ተመርቃችሁ ሰፈር ለሰፈር ከምታውደለድሉ የጀበና ቡና ብታፈሉ ምን ችግር አለው ? ብሎ በምሳሌነት ጠቀሰን ። እኔ እንዳስተማረን ሳይሆን እንደ ሰደበን ቆጥሬው እሳት እንደነካው ላስቲክ ተኮራመትሁኝ ።
ከስብሰባው በሁላ ስንሻውን ለማናገር ከተቀመጥሁበት ተነስቼ ተራመድኩኝ ። የልጅነት ጓደኛዬ ስለሆነ ሰላምታ ልሰጠው አስቤ ነው የቀረብሁት ። በሰዓቱ ከየት መጣ ያልተባለ ጠባቂው በመዳፉ ጭብጦ አሽቀነጠረኝ ።
ቀና ብዬ አየሁት !
“ምን አጠፋሁ አለቃ?”
ፈርጣማው ጠባቂ በቁጣ ቱግ ብሎ እንዲህ አለኝ
“አንተ ምን አይነት ደፋር ነህ ባክህ ? ክቡር ከንቲባችንን ለመቅረብ አይደለም ሻንጣቸውን ለመሸከም ብትመጣ እንኳ ማስፈቀድ ነበረብህ “ 🙂

@wegoch
@wegoch
@paappii

#ሚካኤል አስጨናቂ
ወግ ( የቀን ማህደር )

ከሶላ


<< አለወትሮዬ ... >>

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨ ገፅ ፩ ፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨


አለወትሮዬ ነበር በጠዋት የነቃሁት ... አለወትሮዬ ስነቃ አለወትሮዬ ያለምኩት ህልም ትዝ አለኝ ... አለወትሮዬ በህልሜ ሊያውም በተመረኩበት ስራ ሳገኝ ይታየኝና ስነቃ የፍርድ ቤት ዳኛ ያስመሰለኝ የምርቃት ፎቶዬ ትኩር ብሎ ሲያየኝ አገኘዋለሁ ... ( መንቃቴ ህልም ቢሆን ምን ነበር ) የፎቶው ፍሬም ወይም ጋወኑ ተሰቅሎ ከመቆየቱ ብዛት አቧራ ለብሷል ... በፎቶው ላይ መመረቄን ከሚያውቁ ሰዎች ውጭ የሚያመሳክር ኮፍያም ይሁን ሪቫን የለውም ... እንዴት ? ... ከምርቃቴ 5 ቀን በፊት ሙሉ ጋወኔን ወሰጄ እቤት አስቀመጥኩ ፤ የምታስርበት ስታጣ እናቴ < ለራሱ አይደል እንዴ > ብላ በሪቫኑ የጠመቀችውን ጠላ ሸብ አረገችበት ... በርግጥ ጠላው ለምርቃቴ ለተጠሩት እንግዶች ነው ትበል እንጂ በክፍያ ነበር ስትሸጥላቸው የነበረው ... እርሱም ቢጎል ምን ችግር ብዬ ሳለ በሞንታርቦው በኩል << እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ >> የሚለው ዘፈን ሲንቆረቆር የጠዋቱ ድባብ ታውሶኝ ኮፍያዬን ከአናቴ አንስቼ ወደ ላይ ለመልቀቅ ወደ ጎን ስወረውር ከግቢው ውጭ አረፈች ... ሰው እንዳልፈነከትኩ ተስፋ እያረኩ ከግቢው ስወጣ እንኳን ሌባ ልትጠብቅ ትቅርና በረሮ ገና ስታይ የምትገባበት የሚጠፋት << ክፉን ችላ >> የምትባለው ውሻ በጥርሷ ዘነጣጥለው ስጨርስ ደረስኩ ... ከመቅጠኗ እና ከመናደዴ የተነሳ ልበላት ወስኜ ነበር ፤ እርጉዝ ስለሆነች ተውኳት እንጂ ... ጥቂት ከተጨፈረ በኋላ ፎቶግራፈሩ መጣ ... እናቴ በነፃ እንድትሰጠው ያረኩትን ጠላ እና < ብፌው ከሱ ነው እንዴ የሚነሳው > እስኪባል ድረስ ተራራ አሳህሎ ካነሳው ማዕድ ጋር እያጣጣመ ያጋጠመኝን አወራውት ...

<< ብሮ ዛሬ ምርቃቴ ነው ታውቃለህ አ ? >>

<< አውቃለሁ >> ( አጎራረሱን ለአንባቢዎቼ ስል ውጬዋለሁ. )

<< ግን ኮፍያው እና ሪቫኑ የለኝም ብሮ ... >>



<< አደለም እርሱ COC ስ መች አለሽ >> ( በጉርሻው መሀል የተብላላ ድምፅ ነው )

<< ምን አልሽኝ ብሮ ? >>

<< ጣጣ የለውም በ Photoshop ይመጣል >> አለኝ

በበሳምንቱ...

<< ብሮ ሰራሽው እንዴ ? >>

<< አይ አልሰራውትም >> ( ሲያገሳ የድግሱን ወጥ ይሸታል )

<< እንዴ ለምን ? >>

<< ንሰሀ ስለገባሁ ልሰራልህ አልችልም ... ባይሆን >>

<< ባይሆን ምን ... >>

<< ባይሆን ንሰሀውን ስጨርስ >> ሲለኝ ተናድጄ

<< እንደውም Soft copyውን ስጠኝ >> ብዬ ከተቀበልኩ በኋላ << ከቻልክ ንሰሀውን ስጨርስ ንሰሀ ግባ >> ብዬው ሄድኩ


፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨ ገፅ ፪ ፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

በአንድ ቀን መምህሩ 3+1=4 ነው ብሎ ሲያስተምር < አንተ ውሽንታም ትናንትና 2+2=4 ነው አላልክም > ብሎ ትምህርት በአፍንጫዬ ያለው ጓደኛዬ ...

<< ታውቃለህ ? >>

<< ምኑን ነው ማውቀው ... >>

<< የምርቃትህ ፎቶ አሁን ሶስተኛውን ምርጫ ሊያይ ነው >>

ዝም ...

ለጠቀና

<< አንዳንዴም እጠበው >>

<< ደሞ አሁን ምኑን ነው? >>

<< የተመረክበትን ጋወን ነዋ >> ብሎኝ ወደስራ ይሄዳል ... ( አሽሙር መሆኑ እኮ ነው ) ... አለወትሮዬ ፎቶውን ደጋግሜ አየሁት ... ስራ አግኝቼ ፤ ፍቅረኛ ይዤ ፤ ልጆች ወልጄ ፤ የልጆቼን ምርቃት ሳይሆን ስራ ማግኘት አይቼ ፤ ከደሞዛቻቸው ስበላ እያየሁ .... ለወትሮ እንኳን አልሜ የማላውቀውን አለወትሮዬ በሀሳብ እኖራለሁ ... ከምናበ አሳቤ እንደመጣው ያኔ ስንመረቅ መልስ ለመመለስ አውጥቶ የሚፈልገው ተማሪ እስኪያወጣ ድረስ ባላየ እንደሚሆን መምህር እጆቻችንን አስነስተው ያስገቡን ቃል ትዝ አለኝ ... በወቅቱ የመድረኩ መሪ የነበረው ወጣት << በተማራችሁት ስራ አምናችሁ ህዝባችሁን በታማኝነት እያገለገላችሁ ልትፈውሱት ይገባል ስለዚህም ቃል ግቡ >> ( አሁን ፓስተር ሳይሆን አይቀርም ) እያለ ሲያጨናንቀን ነገረኛው ተመራቂው አይምሮዬ << እኛ ቃሉ መች አስጨነቀን ስራ ማግኘቱ እንጂ >> ያለው መልስ በጊዜው ቢያስቀኝም ነገሩ ትንቢት መሆኑ የገባኝ አሁን አለወትሮዬ ሳስታውሰው ነው ... ከጥቂት አለወትሮ የመጣ ዝምታ በኋላ የግቢው በር ተንኳኳ ... እመቤቴ ማርያም ሆይ ብቻ < እቴዬ ወይዘሮ > ባልሆኑ ብዬ ዝም አልኩ ... በድጋሚ ኳ .. ኳ .. ኳ .. አለ ፤ በሩን እስከክፍተው ድረስ አይምሮዬን ስራኝ ቀጥሬው እትዬ ወይዘሮ ባለፈው ያሉኝን ማስታወስ ጀመርኩ.

<< ደህና ዋልህ ልጄ ? >>

<< እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ዋሉ ? >>

<< ይመስገነው... እኔ ምለው እናትህ አለች ? >>

<< አይ የለችም ስራ ሄዳለች >> ( አድጌም እየሰራች የምታኖረኝ እናቴ ነች ውዷ እናቴ )

<< አይ የኔ ነገር ረስቼው እኮ ነው ... አንተስ ስራ አለህ እንዴ ? >>

<< ለጊዜው የለኝም >>

<< እሱንስ ተወው ...ለጊዜው እያልክ ይሄው 3 የምርጫ ዘመን አየህ እኮ >> ( በነገራችን ላይ ከላይ ለነገርኳችሁ ጓደኛዬ እናቱ ናቸው ) ለጥቀውም ...

<< እንግዲህ ስራም የለኝም ካልክ ና ቡና አጣጣኝ >>

በሩን ከፈትኩ ... የ< እገሌ > ፓርቲ ቀስቃሾች ነበሩ ... ወጣት እና ፈርጣማ ከመሆናቸው የተነሳ እየደበደቡ በፍቅር ምረጥ የሚሉ ይመስሉ ነበር ... እንዳልገባው ሆኜ...

<< ምን ነበር >>

<< ከእገሌ ፓርቲ ነው የመጣነው የይምረጡን ቅስቀሳ እያደረግን ነበር >> ( እውነት በሉ እስኪ... ይልቅ የምናውቀን ትታችሁ የማናውቀውን ብትነግሩንስ አላልኩም )

<< እሺ ቀጥሉ >> ( እኔ ሂዱ ማለቴ ነበር )

ከብዙ ቀደዳዎች በኋላ << ፓርቲያችን ከፍተኛ የስራ ዕድልን ይሰጣል >>

<< ጥሩ ነው ግን ልጠይቃችሁና በዚህ ፓርቲ ስንት አመት ሰርታችኋል ? >>( ወጣትነታቸውን ታሳቢ አድርጌ )

ተያዩና << እኛ እንኳን አሁን በተጠባባቂነት ነው ያለነው ያው ግን ወደፊት... >>

.
.
.

እነሆ ከዚህም በኋላ ጥሁፌም በጥሁፌ ውስጥም ያለው የግቢዬ በር ተከርችሞ አለ !

@wegoch
@wegoch
@paappii

#በሶላ
የታናሽ ወንድሜ ክፍል ገባሁ ።
እንደ አጋጣሚ ሱቅ ተልኮ ስለወጣ እንጂ የቤተሰቡን አባል ቤቱ ውስጥ የማስገባት ፍላጎት አልነበረውም።
እማዬ ብዙ ጊዜ በሩን ስትቆረቁር እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ያንባርቃል።
"ይሄ የድመት ሙጭሊት የመሰለ ልጅ ቤቱ ውስጥ ፎርጂድ ዶክመንት ይሰራል እንዴ? " ይላል አባዬ አንዳንዴ ሲበሳጭ ።
እኔም ምክንያቱ የገባኝ ዛሬ ገና ነው :)
የቤቱ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የሚታዩት ፖስተሮች ከ አምስተኛ ክፍል ተማሪ የሚጠበቅ አይደለም። ጭራሽ በቀኝ በኩል በፒኪኒ ሙታንታ የተበለቃቀተች የፈረንጅ ሴት ፎቶ አየሁ ።
እግዚኦ!
አሁን ይሄ ልጅ እንብርትና የሴት ልጅ ብልትን እንኳ በቅጡ የሚለይበት እድሜ ላይ ነው ወይ ?
ፍራሹን ከፍ ሳደርገው የባህል መድሀኒት የሚሰራ ደብተራ ይመስል የደረቁ ቅጠሎች ተበታትነዋል።
ሀሽሽ ????
አቤት ይህቺ ምድር የተሸከመችው ጉድ !!
አሀ !
ከዚ ቀደም ለካ ከክፍሉ ሲወጣ እንባ የምታክል ውሀ መሬት ላይ አይቶ እንደ ሚዳቆ ዘሎ የተሻገራት ለዚህ ነዋ !
ብዙ ጊዜ ... የሬጌ ሙዚቃ እንደሚሰማ አውቃለሁ። ግን...ግን እንዲህ እንደ ትልቅ ወጣት ሀሽሽ ያጨሳል ብዬ እንዴት ልመን?
ጌታ ሆይ ወዴት ነህ? ! መምጫህስ መቼ ነው?
በጣም ደንፍቼ ስልኩ ላይ ስደውል ስልኩ ጠረጴዛ ላይ አቃጨለች። ይዟት አልወጣም ማለት ነው !
አንስቼ መጎርጎር ጀመርኩ ። እጄን ምን እንደመራኝ ባላውቅም ቴሌግራሙ ውስጥ ገባሁ ።
Mal love u! ብሏል ፀዲ ጭሷ ለምትባል ህፃን ወጠጤ።
የታችኛው መልዕክት ውስጥ ዘው አልኩኝ።
ማማዬ ዛሬ ያደረግነው Sex አቅሌን አሳተኝ ይላል mal Lila ***×+~ ምናምን የሚል ስም ላላት ሌላ ህፃን ሴት !
እስክስ ማተራመስ !
ሶስተኛው መልዕክት ሄድኩኝ የድብቅ ወሲብ አገናኝ የሚል ግሩፕ ውስጥ ቀንደኛ ተሳታፊ ወንድም ነው ያለኝ።
አበስኩ ገበርኩ !
ወደ ኋላ ልወድቅ ተንገዳገድኩ ። አራተኛው መልዕክት ውስጥ ገባሁ ።
አንዲት የሚመጠጠውን ከረሜላ እግር የምታክል ልጅ የእርቃን ፎቶ ልካለታለች ።
አሁን ይህቺ እቃቃ ተጫውታ ያልጠገበች ልጅ የእርቃን ፎቶ ለመላክ ምን አነሳሳት ?
ወንድ ልጅ ፀጉሩን በአጭሩ ከመቆረጥ ሌላ ምን አይነት ባህሪ እንዳለው ከምኔው ለየች ?
ደግሞ እኮ ነጥብ የምታክል ትንሽዬ ጡት አላት ።
Mal ያበደ ገላ ነው ብሎ መልሶላታል ወንድሜ ።
እኔ በሱ መልዕክት አበድኩ !
ወድያው Sami ላላ የሚባል ልጅ ፎቶ ሰደደለት ። ክለብ ተቀምጦ ሺሻ የሚያጨስ ህፃን ልጅ! ... እኔ በሱ እድሜ ትምህርት ቤት ውስጥ የስነ ፅሁፍ ክለብ ምናምን ነበር የምሳተፈው ።
እሺ ክለብ መግባቱንስ ይግባ!
እዚህ ውድ ክለብ ገንዘብ ከየት አምጥቶ ገባ ?
እሺ መግባቱንስ ይግባ የክለቡ ተጠቃሚዎች እንዴት ኮርኩመው አላበረሩትም ?
ስምንተኛው ሺህ ነው ወይስ አስራ ስምንተኛው ሺህ ላይ ነው ያለነው ጎበዝ? :)
....
ከዚህ በላይ የመቀጠል አቅሙ አልነበረኝም።
በንዴት ጨስኩ !
በብስጭት በገንኩ !
ይሄ ልጅ ይምጣ እንጂ እንደ ቴኒስ ኳስ ነው የማነጥረው ስል ዛትኩኝ።
....ብቻዬን ቁጭ ብዬ ተብሰለሰልኩ ...
አላስችል ብሎኝ ላፕቶፑ ላይ ደግሞ ማሰስ ጀመርኩ። የወሲብ ቪድዮ መዓት! የሬጌና ራፕ ሙዚቃ መዓት !
ገና መቀመጫውን በቅጡ ያልጠረገ ፈላ ይሄ ሁሉ የዝሙት ፊልም ምን ያደርግለታል ?
ትዝ የሚለኝ እኮ ከቤተሰብ ጋር ተሰብስበን ህንድ ፊልም ስናይ እማዬ ይሄ ለልጅ የሚሆን ፊልም አይደለም ብላ አባራዋለች።
እማዬ ጉድሽን ባወቅሽ ?
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ህፃኑ ጋኔን መጣ።
ተንደርድሬ አንገቱ ላይ ተሳፈርኩ ። መቀጥቀጥ ብቻ ሳይሆን ሚጥሚጣ ባጥነውም አልጠላም። አንድ ሁለቴ ሳቀምሰው እንደ ሚግ ተወንጭፎ እናታችን ጋር ደረሰ። የእማዬን ቀሚስ ይዞ ከጀርባዋ ተሸሸገ !
"ልቀቂኝ እገለዋለሁ!"...አንባረኩኝ።
"አንተ ምን ያርግህ ይሄ ህፃን ልጅ! " እናቴም በተራዋ ጮኸችብኝ።
"ምን አልሽ ?"
"ይሄ ህፃን ምን ያርግህ ?" እማዬ ደገመችው።
ምፅ!
ህፃን ልጅ አሳድጋ ሞታለች።
ተንደርድሬ ወደ ጓዳ ገባሁ ። የሚጥሚጣውን መያዣ ክዳን ስከፍት አንድ ድምፅ ከውጭ ሰማሁ።
"ምን አርገኸው ነው ወንድምህን አንተ ?"
"ምንም እማዬ! ... ከፍቅረኛው ጋር ተያይዞ ቤርጎ ሲገባ ስላየሁት እሱን እንዳልናገርበት ነው የሚደነፋው " ብሎ ፈላው መለሰ።
ጭራሽ እንደ ሀገራችን ፖለቲከኞች ሴራም ተምሮልኛልና !
እማዬ ፊቷን ኮስኩሳ ወደኔ ተንደረደረች :) ....

ሚካኤል አስጨናቂ

@wegoch
@wegoch
@paappi

ለተጨማሪ https://www.tg-me.com/MichaelAschenakipoems
ክትባት እንዴት እንዳመለጠኝ

(በእውቀቱ ስዩም)

አበሻ ገራሚ ህብረተሰብ ነው! ማስክ ገድግደህ ሲያይህ” ይሄን ያህል ትንቦቀቦቃለህ እንዴ” እያለ ያሸማቅቅሀል ፤ ከዚያ አጅሬው አስተኝቶ ለሳምንታት ያክል አበራይቶ ትቶት ይሄዳል፤ ከዚያ እንዴት ነህ? ስትለው” በዝሆን እግሩ ረግጦ አድቅቆ ለቀቀኝ በማለት ፈንታ” ይዞ ለቀቀኝ “ በማለት አቃሎ ይነግርሃል፤ ከህመሙ በረከት እንዲደርስህ ወጥሮ ያበረታታሀል፤ ስለክትባት ስታነሳበት “ ቺፕስ ሊያስገቡብን” ነው ይልሀል፤ ባለፈው አንዱ “ ፈረንጆች ቺፕስ ክንዴ ላይ ቀረቀሩብኝ “ እያለ የዝግባ ፍልጥ የመሰለ ክንዱን ለታዳሚው ሲያስጎበኝ በሆነ ዩቲውብ ቻናል ላይ አየሁት ፤ ዙም አድርጌ ስሾፈው ክንዱ ላይ ያለው ኮረሪማ እሚያክል ኪንታሮት ነው፤

እኔ ያለሁበት ከተማ ውስጥ የክትባት እደላ ቢጀመርም ምዝገባውና ወረፋው አይቀመስም ፤ አንድ ቀን ግን ዝም ብየ በድንኩዋን ሰበራ ጎራ አልሁ፤
“ ምን ፈልገህ ነው?” ሲሉኝ

“ የማትፈልጉት ክትባት ይኖራችሁዋል? ” አልኩ ራሴን እያከክሁ’

“ እድሜህ ስንት ነው?” አለቺኝ ነርሲቱ

“ ኦፊሻል እድሜየ አርባ ይገመታል ፤”

“ አዝናለሁ! አሁን እየከተብን ያለነው ካምሳ አመት በላይ የሆኑትን ነው “ አለችኝ::

“ የሰባ አመት አዛውንት አተነፋፈስ ነው ያለኝ ፤ እንደምንም አጠጋግተሽ አስገቢኝ ”ብየ ተማፀንኩዋት፤

“ ኦኬ፤ ተመዝግቦ የቀረ ሰው ካለ፤ በምትኩ ትከተባለህ”

“ እጅሽን ከቁርጥማት ይሰውርልኝ” በማለት መርቂያት ቁጭ አልኩ
ጥበቃው እንዳይታክተኝ አጠገቤ ከተቀመጠው ሰውየ ጋ ላውጋ ብየ ዞር አልሁ፤ በሁለት ከዘራ መሀል ጎብጦ የሚንቀጠቀጥ አዛዛዛዛውንት አይቼ
“ስንት አመትዎ ነው?’ በማለት ጠየኩት፤
“ ምን አልከኝ ? ” አለኝ፤
ከኪሴ ማይክ አውጥቼ
“ ቼክ ማይክ! ዋን ፥ቱ ፥ ትሪ ! ስንት አመት ሆነዎት? “

“ ባለፈው ሳምንት መቶ አመት ሞላኝ “

“ እና ርስዎም ክትባቱን ይፈልጉታል?”

“ አይ ለኔ አይደለም! አባቴን ላስከትብ መጥቼ ነው”

በመጨረሻ ተጠራሁ፤

ነርሲቱ ፥ ክንዴን አፈፍ አድርጋ ይዛ እንደ ጥጥ ስታባዝተው ከቆየች በሁዋላ፤
“የደም ስርህ ላገኘው አልቻልኩም” አለቺኝ ፤

“ የደምስሬ wireless ነው፤ በቀላሉ አይገኝም “ አልኩዋት

“ አትቀልድ ፤ በዚህ ሁኔታ መርፌ ለመጠቀም ያስቸግረኛል”

“ እንደ ልጅነት ልምሻ ክትባት ለምን አፌ ላይ ጠብ አታረጊልኝም?”

“ ብዙ ጊዜ የምትመገበው ምግብ ምንድነው ?” ስትል ጠየቀችኝ፤

“ ሩዝ ! ይገርምሻል ሩዝ አብዝቼ ከመውደዴ የተነሳ ወዳጆቼ ' ሩዝቤልት' የሚል ቅፅል ስም አውጥተውልኛል”

“ በል አሁን ወደ ቤትህ ተመልሰህ፤ ገንቢ ምግብ ብላ፤ ዳምፔል አንሳ! ፑሽ አፕ ስራ ፤ ከዚያ ከሁለት ወር በሁዋላ ተመለስ”

ይህን ስትለኝ ይሄን ልላት ብየ ተውኩት፤
“ ሴት!Yo! ልትከትቢኝ ነው ወይስ ቦዲጋርድ ልትቀጥሪኝ ነው የምትፈልጊኝ ? ”

በዕውቀቱ ሥዩም

@wegoch
@wegoch
@beckyalexander
ሽልማቱ

(በእውቀቱ ስዩም)

በቀደም ሰይፉ ላይ የሰማሁት ዜና እንዲህ ይላል” የናይጀርያ ዜግነት ያላቸው ሌቦች አዲሳባ ገብተዋል” 🙂ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋራ ልምድ ልውውጥ ለማድረግ መሆን አለበት!

ሌብነት ሲነሳ የሚከተሉት አስተካዥ ገጠመኞች ትዝ ይሉኛል፤
ሰውየው የበግ ነጋዴ ናቸው፤ ወደ ገበያ ሲሄዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ እንደተለመደው አንድ ማለዳ ገንዘባቸውን ከፍየል የቆለጥ ማቀፍያ ቆዳ የተሰራች ትንሽየ ቦርሳ ውስጥ ጠቀጠቁት፤ ከዚያ ቦርሳውን እንደ ቡዳ መዳኒት አንገታቸው ላይ አንጠለጠሉት ፤ በላዩ ላይ ግድንግድ የድሮ ቢትልስ ለበሱበት፤ በዚያ ላይ ካሽሚር ጃኬት በጃኬቱ ላይ ጋቢ፥ በጋቢው ላይ ደግሞ መለስተኛ ቤተሰብ ማስጠለል እሚችል ካፖርት ደረቡበት፤ ከዚህ ሁሉ ጥንቃቄ በሁዋላ ገበያ ውለው ሲወጡ እጃቸውን ወደ አንገታቸው ሲሰዱ ቦርሳው አምልጡዋል ፤

ቤታቸው ገብተው የደንቡን ያክል አልቅሰው ሲያበቁ ወደ ሚስታቸው ዞረው
“ ጉድ እኮ ነው! ይሄን ሁሉ አለባብሼው፥ ሌባው እንዴት አርጎ ወሰደው?” አሉዋቸው’?’

ሚስትዮም እንዲህ መለሱ ፥

“ አንተ ደሞ! ላት ያላት በግ አትሰረርም ያለህ ማነው?”

2

ሸገር ውስጥ "የሌባ ሰፈር " ነው እየተባለ የሚታማ ሰፈር አለ! እስከ ሰባ አመት ፥በዚህ አለም መቆየት ስለምፈልግ ስሙን አልጠቅሰውም! አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ በሬድዮ ፕሮግራሙ ላይ ስለዚህ ሰፈር ለየት ያለ ቆንጆ ፕሮግራም ሰራ፤ የሰፈሩ ልጆች ሰምተው ፈነጠዙ! “ በስርቆት ብቻ ሲነሳ የነበረ ሰፈራችንን ገፅታ ስለገነባህልን የምስጋና ድግስ አዘጋጅተንልሀል ፤ ሽልማትም ተሰናድቶልሀል” ብለው ጋበዙት፤ እሱም ልቡ በጣም ተነክቶ በዝግጅታቸው ላይ ታደመ፤ መኪናውን ዝግጅቱ ከሚዘጋጅበት አዳራሽ ጀርባ አቆመና ወደ ውስጥ ዘለቀ፤ ድብልቅልቅ ባለ ጭብጨባ ተቀበሉት::

የተለያየ የኪነጥበብ ድግስ ተከታትሎ መቅረብ ጀመረ፤ አንድ ወጣት “ ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ” የሚል ግጥም አነበበና በቅርቡ ከሚታተመው መድብሌ የተወሰደ ነው ብሎ ከመድረክ ወረደ::

የስነፅሁፍ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ ምሳ አበሉት፤ ምን ምሳ ብቻ፤ በሹርቤ ብርሌ ጠጅ አቀረቡለት፤ ብርሌውን ሾፍ ሲያደርገው “ ብሄራዊ ሙዝየም “ የሚል ማህተም ተለጥፎበታል፤ በመጨረሻወደ መኪናው ሄደ፤ ባየው ነገር ክው ብሎ ቀረ፤ የመኪናው ሁለት ስፖኪዮ በቦታው የለም፤

የደረሰበትን የነገረኝ ቀን በምን ቃል እንዳፅናናሁት አልረሳም

” ጎማውን ስለማሩልህ እንደ ሽልማት ቁጠረው”

@wegoch
@wegoch
@beckyalexander
ኢትዮዽያ መኪና ነድቼ አላውቅማ ... ራሴ ነዳለሁ ብዬ መኪናውን ልከራይ የቀጠርኩት ሰውዬ ...

"አይከብድሽም? እርግጠኛ ነሽ? ረዥም አመት እንኳን ውጪ የነዱትኮ እዚህ ይፈራሉ .... (ሲያስፈራራኝ ከቆየ በኃላ ) ለማንኛውም እስኪ አብረን ሆነን ልይሽ" ብሎ ከኃላ ተቀምጦ ስንዳ ... ሲኖትራክ ሲንቀለቀል መጣ ...

"ውይይ ይለፍ ቆይ ያስፈራል" አልኩት ...

"ገና እሩቅ ነውኮ .."

"አይ ቢሆንም አመጣጡን እየው ያስፈራል::" እለዋለሁ:: ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?

"በዚህ አያያዝሽ ሹፌሩ ወርዶ ሁላ እለፊ ቢልሽ...'በማርያም ሞተሩንም አጥፋውና ነው የማልፈው' ትያለሽ::" 😊

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Meri feleke
ፍተላ ነች አበበና አቤል፣ ሁለቱ ጓደኛሞች በረሃ አቋርጠው ሲጓዙ በጣም ራባቸው። በዚሁ ከቀጠሉ በረሃብ እና በውሀ ጥም ሊሞቱ እንደሆነ እየተነጋገሩ ጥቂት እንዳዘገሙ አንድ መስጊድ አዩ። አበበም "ስማችንን ቀይረን እዚህ መስጊድ እንግባ ምግብ ይሰጡናል - እኔ አህመድ ሆናለሁ" አለ።

አቤል "እኔ ስሜን አልቀይርም" አለና ወሰነ። ተያይዘው ወደ መስጊዱ ገቡ።
የመስጊዱ ኢማምም "አሰላሙአለይኩም፤ ሀጂ አሊ እባላለሁ" ሲሉ መንገደኞቹን በሰላምታ ተቀበሏቸው። አበበ "አህመድ እባላለሁ" ብሎ ራሱን አስተዋወቀ። አቤልም "አቤል እባላለሁ" አለና ስሙን ተናገረ። ሀጂም እንግዶቻቸውን ካስቀመጡ በኋላ "ልጆች፡ ለአቤል ምግብ እና የሚጠጣው ነገር አምጡለት። አህመድ ያው ጾም ነው . . . ረመዳን ከሪም!"

@wegoch
@wegoch
@paappii

#Gemechu merara fana
ብ.ል.ግ.ና ፓርቲ

" ጣፋጯን ሲጋራ እናጭስ በጋራ"

በጠዋት ከተነሳው ዛሬ አምስት አመቴ ሆነኝ ማለት ነው፡፡ በዚ ለሊት 'ምሄድበት አለኝ አደራ እንዳላረፍድ ቀስቅሱኝ' ያላቸው ሰው ያለ ይመስል በሁለት ትላልቅ ማደንቆሪያ ሬድዮ ከመቀስቀስ አልፎ ልትፈርስ አንድ ሀሙስ የቀራትን ጎጆአችንን ሊያፈርሱት ሲሞክሩ አንዲት አዛውንት አሮጊት ቀድሞውኑም የተከፈተ በራቸውን ከፍተው ወጡ፡፡

"ኧረ ስለፈጠራቹ ፤ ኧረ በጉልበታችሁ አምላክ ፤ ቆይ እስኪ ንገሩኝ እኛ ምርጫ በመጣ ቁጥር ጭቃ ማዘጋጀት አለብን እንዴ?" ወገባቸውን ይዘው ሹፌሩን ይገላምጡት ጀመር፡፡

" እንዴ ማዘርዬ የምርጫ ካርዶን ነው እንጂ የምን ጭቃ ነው ሚያዘጋጁት?" ሹፌሩ መለሰ፡፡

" እናንተ የቦረቦራቹትን ጆሮዬንም ግርግዳዬንም ልደፍንበት ነዋ" አሉት የንዴት ፊት እያሳዩት፡፡

ሹፌሩም ምንም ሳይመስለው ፈገግ ብሎ የሬድዮኑን ድምፅ ከፍ አደረገው፡፡

"ሰላም ሰላም ሰላም ፤ ስዶች ነን ብ.ል.ግ.ናን ይምረጡ ፤ ፓርቲአችን በብዙዎች ዘንድ የሚወደደውን 'ሲጋራን' ምልክት አድርጓል፡፡
ብ.ል.ግ.ናን ቢመርጡ ሲጋራን የማናደርስበት ክልል አይኖርም፡፡ ምን እሱን ብቻ ከሲጋራ ጋር እጅና ጓንት የሆኑትን አሽሽ ፤ ጋንጃና ጫትን እንደ እድሜአችሁ ተደራሽ እናደርጋለን፡፡ አሮጊቶች ያለከልካይ ሰው እንዲዘለዝሉ ወይንም እንዲያሙ ተግተን እንደምንሰራ
በ ስድ ስም ቃል እንገባለን፡፡ እኛን አምነው ስልጣን ላይ ቢሾሙን ከበፊቱ በተሻለ መልኩ አምስት አመት ሙሉ ያለስራ ተኝቶ የሚቅም ትውልድ እናፈራለን፡፡
አላማችን ሳንባ የሌለው ትውልድ ማፍራት ነው ፡፡
ብ.ል.ግ.ናዎች ነን !! "

በሂወቴ እንደዛሬ ምርጫ እንደ ነፃነት የናፈቀኝ ጊዜ የለም፡፡ እኔም የዜግነት ግዴታዬን ለወጣ ብዬ አሰብኩና ከሱቅ ሲጋራ ገዛውና ወደ ሹፌሩ ጠጋ ብዬ "ተመርጣችሁ በነፃ አብረን እስከምንጨስና እስከምናጨስ
አሁን እኔ የገዛውልህን አጭስ" ብዬው መርሀቸውን ጮክ ብዬ እየተናገርኩ ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡

#Beki

@wegoch
@wegoch
@MahletZerihun
"ጣፋጯን ሲጋራ እናጭስ በጋራ"

ቤካ ስም አይጠቅስም😜
"መዳፍና ዓይን"
(ያሬድ ሹመቴ)
ለፊልም ስራ አባይ ማዶ ተሻግሬ በነበረበት ጊዜ እንዲህም ሆነ! ፊልሙ - የገጠር ያውም የሽፍታ ታሪክ ነበረና "አብራራው" የተባለው የድሮ ጠመንጃ አስፈለገ። "አብራራው" ስሙን ያገኘው ለማቀባበል ከሚወስደው ጊዜ ተነስቶ ይመስላል። አንድ ሰው ነገር ስያረዝም "አብራራው" እንደሚባለው ማለት ነው።... የምንሰራው ፊልም ርዕሱ "ገዳይ ሲያረፋፍድ" ይሰኛል። እኔ በፕሮዲዩሰርነት እና በኤዲተርነት ተሳትፌበታለሁ። ዝግጅቱ የናኦድ ለማ ነው። የቀረጻ ቦታውም የጣና ሐይቅ ደቡብ ምዕራባዊ አቅጣጫ ላይ የምትገኘው ቆራጣ ላይ ነው።....ይህን ጠመንጃ ፈልጎ ማግኘት ቀላል ቢሆንም ፈቃጅ ማግኘቱ ግን እጅጉን ያለፋል። ምክንያቱም የጦር መሣሪያ ነዋ። ከፖሊስ ሊገኙ የሚችሉት መሣሪያዎች ዘመናዊ በመሆናቸው አንዱን የየአካባቢው ሰው ማሳመን ግድ ሆነ። "አብራራው"ን አስፈቅደን ቀረጻ ላይ ለማዋል "አብራራው" ከሆኑ [አቶ አዝመራው ከተባሉ] የአካባቢው ነዋሪ ጋር ስንለማመጥ ስንነታረክ አረፈድን። በኋላ በቀን 50 ብር ክፍያ ተስማምተን ያለ ጥይት አብራራውን ተከራየነው።
"አብራራው" ፀሐይ ስትወጣ ስራ ይጀምርና ፀሀይ ስትጠልቅ "በሞክሼው" (የጠመንጃው ባለቤት) ወደ ቤቱ ይወሰዳል። እንዲህ እንዲህ
እያለ ጥይት አልባው ጠመንጃ የፊልም ባለሙያ ሆነ። ብዙውን ጊዜ በቀረጻ ወቅት ደጋግሞ ማቀባበልና ቃታ መሳብ የተለመደ ስለሆነ ከዚህ ቀደም ሰርቶ የማያውቀውን ከባድ እንቅስቃሴ ለመደ። ለካንስ ይህ አሮጌ መሳሪያ ዕለት በዕለት በሚገጥመው ከባድ ስራ የቃታው ማስፈንጠሪያ እየላሸቀ ሄዷል። ከተቀባበለ በኋለ ቃታውን ለመሳብ በማሰብ ብቻ ተወንጭፎ መርፌውን
ይመታል። ጠመንጃ በባህሪው ልክ እንደ ውሀ እያሳሳቀ ነው የሚወስደው። "ወይ ወደ መሬት፥ አልያም ወደ ሰማይ ተደርጎ ነው የሚነጣጠረውም፥ የሚተኮሰውም።"
የሚለውን መርህ ለመሻር ጥይት አልባውን አብራራው ለሁለት ቀናት ብቻ
ሲያቀባብሉ እና ቃታ ሲስቡ መዋል በቂ ነው። ከዛ በኋላ ማቀባበሉም ሆነ መተኮሱ በወዳጅ ላይ ልክ እንደ ቀልድ ነው የሚቆጠረው። ጥይት የጎረሰለት
መጉረሱ ይዘነጋና የዕለት ቀልድ ሊቀጥል ይችላል። አንድ ቀን ታዲያ ጠመንጃው ጥይት ሲጎርስ መቀረጽ ስለነበረበት ባለ ንብረቱ ጥይቶች ይዞልን መጣ። ጥይቱን ተከትሎ ዝናብ መጣ። ቀረጻው ተስተጓጎለ። ጠበቅን ጠበቅን አያባራም። "ለበጎ ነው" የሚለውን ጥቅስ ያስታወሰ ማንም አልነበረም። ተበሳጭተን ተስፋ ቆርጠን እቃችንን ጠቅለን የገጠሩን መንደር ለቀን ወደ ባህር ዳር ተመለስን።
የአብራራው ባለቤት እዛችው መንደር ባለች "አንጓች አረቄ ቤት" ውስጥ የላሸቀውን ጠመንጃ ጥይቱን አጉርሶ፥ እንደነገሩ ነቅነቅ ሲያደርገው ተፈትልኮ መርፌና እርሳስ ተገናኝተው ባረቀ። በተአምር ማለት ይቻላል አንድም ሰው
ሳይጎዳ አካባቢውን አሸብሮ የአንጓችን የተደረደሩ 6 ትላልቅ ጋኖችን በታትኖ
ቤቱን በጠላ ጎርፍ ሞላው። የተፈጠረውን ድንጋጤና ረብሻ ለመረዳት ቦታው ላይ መድረስ አላስፈለገንም ወሬው 42 ኪ.ሜትሮችን አቆራርጦ ባህርዳር ሳለን ሰማን። የነበረን ምርጫ
ከቦታው መሰወር ብቻ እስኪመስለን ድረስ ተደናገጥን። እየመነታን እያማተብን በማግስቱ ማልደን ቆራጣ ገባን። የአብራራው ባለቤት አቶ አዝመራው ግን "የምወዳትን ጠመንጃዬን አሰሩልኝ እንጂ እግዚአብሔር ባዘዘው ገብቼ እናንተን አልወቅስም" አለ። ያስጠነቀቀው ግን ታዲያ "ጠመንጃዬ ያልተሰራች እንደው ይቅርታም አላደርግ" ብሎ ነው። በአካባቢው አሉ የተባሉ የመሳሪያ አዋቂዎች ዘንድ ተንከራተትን።
የመሳሪያው አሮጌነትና በአይን ለማየት አስቸጋሪ የሆነውን የውስጡን ክፍል ለይቶ ማን ይወቀው። እንግዲህ ፀባችን እርግጥ ሆነ ስንልም ሁላችንም ሰጋን።
በዚህ ግዜ ነበር አንድ ወዳጄ ባህር ዳር ሆስፒታል አካባቢ አንድ ባለሙያ መኖራቸውን የጠቆመኝ። ወደተባሉት ሰው የመጨረሻ እድል ለመሞከር ሄድኩ። አሮጌ ጠመንጃ ታጥቄ ባህርዳር ከተማ ውስጥ መታየት ችግር እና ትኩረት መሳብ ሊፈጥርብኝ ይችላል ብዬ ስላሰብኩ ጋቢ ጣል አድርጌ አብራራውን
ታጠቅኩት። መኪና መግባት እስከሚችልበት ቦታ ድረስ በመኪና ሔጄ ጠመንጃውን አንግቼ ከመኪና በመውረድ እየተንጎራደድኩ የባለሙያውን ቤት ፍለጋ የሰፈሩን ሰዎች
ማጠያየቅ ጀመርኩ። አንድም አተኩሮ ያየኝ ሰው የለም። ቤቱን ጠቆሙኝ። እኚህ ሰው ጋሽ ጥላሁን ይባላሉ። በአካባቢው ስመጥር ናቸው። ግን ሸምግለዋል። ሽማግሌ መሆናቸውን ስሰማ አይሳካም ስልም አመነታው። ነገር
ግን "ለካስ የባሰም አለ" አልኩ ቤታቸው ደርሼ ሳያቸው። በእርጅና ምክንያትም
አንደኛው ዓይናቸው ከናካቴው ሲጠፋ ሁለተኛው ደግሞ ከጥላ ውጪ ማየት
አይችልም ነበር። "አሰላሳይ አገናዛቢ" ነኝ ብሎ ለሚታበይ ሰው በሙሉ የሚመጣለት፥ "ጊዜ መግደል ጥሩ አይደለም" የሚል ሀሳብ ነው። እኔም ቢሆን እንዲያ ማለቴ አልቀረም።
ነገር ግን ሰውየው። አብራራውን ተቀበሉኝና ከመቅፅበት በእጃቸው ዳብሰው በስሙ ጠሩት። "አብራራው" አሉ። ትንሽም ቢሆን ላምናቸው ሞከርኩ። እሳቸው ለዘመናት የሚያውቁትን መሳሪያ እኔ ያን ሰሞን ስላወኩት የምበልጣቸው መስሎኝ ነበር። የስህተቴ ብዛት። እኚህ ሰው ፊታቸውን ወደ ጣራው መልሰው ጥቂት ዳብሰውት "ሰው አገኘባችሁ ታዲያ?" አሉ። "ሰምተው ነበር እንዴ?" አልኳቸው። "ኣረ የለ! ምላጭ ማስወንጨፊያው ከጥቅም ውጪ መሆኑን እያየሁት?" አሉኝ ቆጣ ብለው። ዋጋ ነግረውኝ በኋላ ተመለስ ብለው ቀጠሩኝ። ከቀጠሩኝ ሰዓት ትንሽ ረፈድ አድርጌ ደረስኩ። ጊዜ ልስጣቸው ብዬ ነበር። ቤታቸው ደርሼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ከድምፄ ቀድመው በጥላዬ አውቀውኛል። ተቆጡኝ። "ምነ ቆየህ? አንተን ጥበቃ በር በር ልይ እንዴ? ሽማግሌ እኮ ማረፍ አለበት" አሉኝ። ማስረዳት ስላቃተኝ ይቅርታ ጠየቅኳቸው። ልቅም አድርገው
ስራቸውን አጠናቀው ነገረኛውን አብራራው ጤነኛ አድርገው ጠበቁኝ ነበር። በጣም ገረመኝ። ለሙከራም አንገላታሁት። ወይ ፍንክች። እንደ ጠላት የታየንበት መንደር በኩራት ተመልሰን የፊልማችንም ቀረጻ ቀጠለ። አብራራውም አደብ ገዛ (ከነ ሞክሼው) ጤነኛውን ጠመንጃም ለባለንብረቱ አቶ
አዝመራው ሳስረክበው አንድ ጥያቄ ደጋግሞ ጠየቀኝ። "ማነው የሰራው?" የሰውየውን ማንነት "አብራራሁለት"። ዐይናቸው እንደማያይላቸው ስነግረው
ትልቅ ቁም ተናገረ፦ "እጃቸው ላይ ሸምግለው ነዋ" አለኝ። በአንድ ሙያ ውስጥ ማርጀት፥ አይን እንኳ ጠፍቶ ጠቢብነትን አይነጥቅም" ወደ ፊልም ሙያ አንድ አፍታ ልመለስ። በሆሊውድ እና በሌሎቹም ግዙፍ የፊልም ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ታዋቂና ስኬታማ የተባሉት የፊልም ዳይሬክተሮች በሙሉ (99%) ሽማግሌዎች ናቸው። ምክንያቱም በፊልም ሙያ ውስጥ የተራቀቀ ጥበበ የሚወለደው በሙያው ሲያረጁበት ነውና። በየሙያቸው፣ ሙያቸው ላይ ያረጁ ሰዎችን እናክብር!! እውቀት ከዚያ አለች!! አመሰግናለሁ።

@wegoch
@wegoch
@paappii
"ወዜን አልሸጥም"
(ያሬድ ሹመቴ)
ከአመታት በፊት በካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ይፋዊ የዕይታ ተሳትፎ በማድረግ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ፊልም ሆኖ የተመረጠው እኔ በረዳት ዳይሬክተርነት የተሳተፍኩበት፤ የያሬድ ዘለቀ ዳንግሌ (Lumb) ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ የነበረኝን የሥራ ቆይታ አስታውሼ፣ ከቀረፃው በፊት ስለነበረው የአልባሳት ግዢ ቆይታ ላጫውታችሁ። ህሊና ደሳለኝ የፊልም ሥራ ውስጥ በአልባሳት ዲዛይነርነት እየታወቀች የመጣች ወጣት ባለሙያ ነች። አሁን በቃና ቲቪ ውስጥ በዳይሬክተርነት ትሰራለች። በዚህ ፊልም ደግሞ የዋናዋ ፈረንሣዊት ዲዛይነር የሳንድራ በርቢ ረዳት ናት። ከእሷ ረዳት መስከረም ወንድማገኝ (ነፍስ ሔር!) ጋር ሆነን ሦስታችንም በመኪና አዲስ አበባን ለቀን በክረምቱ ወራት ጉዞ ወደ ጎጃም
አደረግን። ለፊልሙ የሚያስፈልጉ አልባሳትን ንድፍና ናሙናቸውን በፎቶ የተደገፈ ማብራሪያ ስለያዝን ፣ የሚቀራረብ ልብስ ባየን ቁጥር በየመንገዱ እየቆምን ለመግዛት
ጥረት ማድረግ ጀመርን። ልብሶቹ ከተሰበሰቡ በኋላ በዲዛይነሮቹ አማካኝነት ወደ'ሚፈለገው የልብስ አይነት ስለሚቀየሩ በአብዛኛው በዲዛይነሯ የተነደፉ አልባሳት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው የተለበሱ፣ ያገለገሉ የገጠር አልባሳት ላይ ትኩረት እናደርግ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር "ወዜን አልሸጥም" የሚል ፈተና የገጠመን።
ወዝ መሸጥ ምንድነው? ወዝ ማለት - ላብ ያረፈበት ልብስ ልክ እንደ አንድ የአካል ክፍል የሚቆጠር ማለት ነው - ቆይቶ እንደገባኝ። እኛ የምንፈልገው የተለበሰ፣ በመጠኑ ያረጀ ወይም ደግሞ ለእድሳት የተለጣጠፉ የአዘቦት የሥራና የክት የገጠር አልባሳትን ነው። በአጭሩ ወዝ የተነከሩ። ብዙ ተለብሰው መነሻ ባህሪያቸውን የቀየሩ። የገጠሩን ነዋሪ ኑሮውን ሚመለከት የሚመስሉት። ከአፈር ጋር ያላቸውን ትግል የሚያሳዩ ማለት ይቻላል። "አንዱ 'አዋቂ' ቤት ሄዶ ለባልንጀራው ክፉ ሲመኝ ‘ወዙን አምጣልኝና እሠራልሀለው' ተብሎ የልብሱን ቁራጭ አዋቂው ጋር ወስዶ አፍዞ አደንዝዞ አስቀረው። እና በምን አምኛችሁ ነው ወዜን የምሸጥላችሁ?" ሲል አንዱ ቆፍጣና ገበሬ አወጋኝ። ጉድ እኮ ነው። አንዱ ምስኪን የለበሰውን ያለ ቅያሪ አውልቆ ግዙኝ ያለበት መንደር ደግሞ፣ በካህን አስወግዘው ሰው ያለ ጨርቅ የሚያስቀሩ ጉዶች መጡ ተብለናል። በጢስ ዓባይ መንደር ልጆች ዕርዳታ ቅዳሜ ገበያ አሮጌ ልብስ ለብሶ የመጣውን ገበሬ በአዲስ ልብስ እየቀየርነው የተወሰነ ግዢ አደረግን። ትንሽ ቆይቶ ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቅና ለአሮጌ ጉርድ ቁምጣ ሙሉ ጋቢ በድርቡ መጠየቅ መጣ። ከጢስ ዓባይ ደግሞ ተሰደድን። እንዲህ እንዲህ እያልን ፈተናውን እያጣጣምን እግረ መንገዳችንንም እየተገረምን ፍለጋችንን ቀጠልን። ከዚህ ቀደም "ገዳይ ሲያረፋፍድ" የተሰኘውን ፊልም ፕሮዲዩስ ለማድረግ ሄጄ የተዋወቅኳቸው ሰዎች ያሉባትና ከባህር ዳር 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው የአለቃ ገብረ ሐና የትውልድ መንደር "ቆራጣ" በመባል
የምትታወቀው ቀዬ ትልቅ ተስፋ ይዘን አመራን። የፊልም ሥራን ባህሪ የተረዱ
ነዋሪዎች ያሉበት ቦታ በመሆኑ ብዙ ልብሶች ገዛን። "ወዜን አልሸጥም" የሚል ቃል ያልሰማንበት ብቸኛውን መንደር እያደናነቅን፣ በማግሥቱ ስለሚኖሩን በርካታ ግዢዎች ዕቅድ እያወጣን ወደ ባህር ዳር ዘለቅን። በማግሥቱ ጠዋት የገዛናቸውን ልብሶች ባህር ዳር ላገኘናት አመለ ሸጋ ልብስ አጣቢ፣ አሮጌዎቹ ልብሶች በመጠኑ ብቻ እንዲፀዱ አስረድተናት ወደ ቆራጣ
አመራን። ቆራጣ ስንደርስ የመንደሩ ሰው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ልብሱንም አዘጋጅቶ ጠበቀን። በደስታ እየመረጥን ዋጋም እየተስማማን ከሰዓት በኋላውን በሙሉ ስንገበያይ ዋልን። ወዙን አምኖ የሰጠንን የመንደሩ ነዋሪ ከፈቃደኝነቱ
በላይ ግፊያው መከራ ቢሆንም፣ የምንፈልገውን ያህል ገዝተን በደስታ፣
በጥቋቁር ረጃጅም ላስቲኮች ሰባት ከረጢት ሙሉ "ወዞችን" የራሳችን አደረግን። ዲዛይነር ህሊና ደሳለኝ አንድ ቀለሙ ለየት ያለ "ጎጃም አዘነ" (ፎጣ) ከርቀት አየች። በጣም ተመኘችው። መኪናችንን አስነስተን ሰውየው ወደሄደበት አቅጣጫ እንደተጠጋን ጠመንጃ የያዘ ሰው አፈ ሙዙን ደግኖ "ቁሙ!" ብሎ አስቆመን። ሰውየው የመንደሩ አዲስ ሹም ነው። የተፈጠረው ግርግር በምን ምክንያት እንደሆነ ጠየቀን። አስረዳነው። ሊገባው አልቻለም። ከዚህ ቀደም እዚህ መንደር ፊልም እንደሠራሁ በትህትና ነገርኩት "አይመለከተኝም" አለ። መንገዱን
ዘግቶብን ከመኪናው ፊት እንደቆመ ስልኩን አውጥቶ ለወረዳው ኃላፊ እያጋነነ ሪፖርት ማድረግ ጀመረ። ከውስጥ የሚያወራው ሰው ድምፅ አይሰማኝም። ሰውየው ግን "እሺ ጌታዬ"፣ "እሺ ጌታዬ" ይላል። ስልኩን እንደዘጋው ይቅርታ ጠይቆን መንገዱን ለቀቀልን። እኔ ስደሰት ህሊና ግን ተናዳለች። ዐይታ የወደደችው "ጎጃም አዘነ" የለበሰው ገበሬ ተሰውሯል።
ወደ ቆራጣ መንደር የሚያሳጥፈው ብቸኛውን የፒስታ መንገድ እየተውን
አስፋልቱን ለማግኘት ወደ ሐሙሲት አቅጣጫ ልንወጣ አስፋልቱ ዳር ስንደርስ
ሰባት ታጣቂ ፖሊሶችና ሁለት ሚሊሻዎች መሣሪያቸውን እንደታጠቁ መንገዱን
ዘግተው አስቆሙን። ልብሱም እኛም በቁጥጥር ሥር ዋልን። ሁሉም መኪናው
ላይ ተጣበው ተጭነው ወደ ሐሙሲት ከተማ አመራን። የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ በሌሎች ታጣቂዎች ታጅበው ጠበቁን። አስረዱ ተባልን ትንታኔ ሰጠሁ። ምክትል አስተዳዳሪው "የአካባቢው ሕዝብ አስተዳደርና የፀጥታ አካላት እንዲህ ዓይነቱን የወረዳችንን ‘ኢሜጅ’ የሚያጠፋ ድርጊት በቀላሉ አንመለከተውም?" በማለት ፖለቲካዊ አንድምታ ሰጡት። ቀጠል አድርገውም፣ "መጪው ዓመት የምርጫ በመሆኑ ‘ሕዝቡ ኑሮው አልተቀየረም' የሚል መልዕክት የማስተላለፍ አዝማሚያ ያለው ድርጊት በመሆኑ፣ ጉዳዩን ላይ ድረስ የምናጣራው ይሆናል። ልብሶቹን በሙሉ አስረክቡ፤" አሉ። "ወዜን አላስረክብም" ዓይነት ወኔ መጣብኝ። በስንትና ስንት ልፋት እና ውድ ዋጋ የተገኙ ልብሶች ዕጣ ፈንታ መቃጠል እንደሆነ አንዱ አጃቢያቸው "ከነተባዩ እሳት መልቀቅ ነው" በማለት ሲናገር ሰምቼ ተረዳሁ። "ከነልብሱ እዚህ እቆያለሁ እንጂ ብቻውን አልሰጣችሁም፤" አልኳቸው። ምክትል አስተዳዳሪው ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተው ሄዱ፡፡ ‘‘ቀበቶህን ፍታ’’ ተባልኩ። ሲመሻሽ ከሰባቱ ላስቲክ ልብሶች ጋር
ወደ ወህኒ ወረድኩ። በሕይወቴ የመጀመሪያዬ የሆነውን የእስር ጊዜ ከ11 ታሳሪዎች ጋር ለማሳለፍ ወደ እስር ቤቱ ስገባ በእጅጉ ተገረምኩ። አሥራ አንዱም እስረኞች ያለፍራሽ ወለሉ ላይ የተነጠፈው ላስቲክ ላይ ተኝተዋል። ሰባቱን ላስቲኮቼን ግጥም አድርጌ አስሬ ደርድሬ ምቹ ፍራሽ አደረግኳቸው። የላስቲኩን ድምፅ የሰሙት እስረኞች በየተራ እየነቁ ከኔ ጋር ማውራት ጀመሩ።
የታሰርኩበትን ምክንያት ስነግራቸው መሳቅ ጀመሩ። አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች
የገጠር ሰዎች ስለነበሩ "የኔን ወዝ የማትገዛኝ" እያሉ አሳሳቁኝ። አንዳንዶቹም ልሽጥልህ እያሉ ሲያስጎመጁኝ አደሩ። በሕይወቴ የማውቀው ረጅሙ ሌሊት በእስረኞቹ አጫዋችነት በመጠኑም ቢሆን አጥሮልኛል። ሊነጋ ሲል ሸለብ
አደረገኝ። ጠዋት በሩ ተከፍቶ የሚጣፍጥ አምባሻ በሻይ መጣልን። እስር ቤቱ በራፍ ላይ ካለው ፍርግርግ አጥር ውስጥ ፀሐይ ለመሞቅ ስንወጣ ስልክ ተፈቅዶልኝ መደወል ጀመርኩ።
በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ሰኢድን አናገርኳቸው። ሊረዱኝ የሚችሉ ሌላ ባህርዳር ከተማ የሚገኙ ኃላፊ ጋር
ደውለው ጉዳዬን እንደራሳቸው ጉዳይ ነገረው በአስቸኳይ እንድፈታ ትብብር
ጠየቁልኝ። ኃላፊዎች ተባብረውኝ፣ ስለሥራችን አስረድተውና ደብዳቤ ጽፈው እኔም ልብሶቹም ከእስር ነፃ ወጣን

የወረዳው አስተዳደር ወዙ ደርቆ "ወዜን" አሳልፌ አልሰጥም ቢልም በስንት ውጣ
ውረድ ከቃጠሎ የተረፉ ልብሶችን አስለቅቀን ወደ መንደሩ ላለመመለስ ወስነን ወጣን። አዲስ አበባ ለመመለስ ጉዞ ጀምረን ጥቂት እንደተጓዝን የህሊና ዓይኖች ብርሃን ለበሱ። ቆራጣ የወደደችውና ያመለጣትን "ጎጃም አዘነ" ተመሳሳይ ልብስ አንድ የቆሎ ተማሪ ለብሶ አየች። መኪናውን አስቁመን መንደር ውስጥ ተሯሩጠን ደረስንበት። የእግዜር ሰላምታ ተለዋውጠን የሮጥንበትን ምክንያት አስረዳነው። የቆሎ ተማሪው በጥያቄ ሲያጣድፈን ቆይቶ "ወዜን አልሸጥም" ብሎን እብስ አለ።
ወዝ ያለው!!

@wegoch
@wegoch
@paappii
ስልክ አውርቶ ካበቃ በኋላ ጓደኛዬ ላሎ ፊቱ ጨው ሆኖ ከሰመ።
"ምን ሆንክ ላሎ ?"
"ተወኝ እስቲ !" ወገቡን ይዞ ተንጎራደደ ።
ወድያው እጁን ከወገቡ ላይ አንስቶ ጠረጴዛውን ደቃው ።
"እንዴት አባቷ እንደዚህ ታደርጋለች? :) ...እኔ ላይ ? ቤቴ ላይ ? አይደረግም !"
"ማናት ምን ሆንክ ?"
በረዥሙ ተነፈሰ። እሳት ከአፉ ውስጥ ተፋ ብል ይቀለኛል። ላሎ ቫምፓየር ሆነ ...
"ማናት ?" ጥያቄውን ደገምኩለት !
"ሚስት ተብየዋ ናታ !"
ጠረጴዛውን መነረቱን ለቀቅ አድርጎ ወደኔ አቅጣጫ ተመለሰ። መሀል ወለሉ ላይ ያገኘውን የወረቀት መያዣ ካርቶን ጠለዘው።
ባዶው ካርቶን ግንባሬን ቀምሶ ተንሸራቶ ወደቀ።
"ይቅርታ ሚኪ !"
"አይ ምንም አይደለም። "
"አትፍረድብኝ የሆነውን ነገር ብታውቅ ሽጉጥ ባርቆብኝ ብመታህም አትፈርድብኝም።" ለደቂቃዎች ዝም አለ።
"ደግሞ እኮ አልጋችን ላይ። ሌላ ቦታ አጣች ይህቺ አለሌ !" ...የድምፁ ንዝረት እየጎላ መጥቶ መንግስቱ ሀይለማርያምን የሆነ መሰለኝ።
በቃ ሚስቱ ቺት አድርጋበት ይሆናል አልኩኝ ካርቶኑ የቀመሰኝን ግንባሬን እያሻሸሁ።
"ተኗኗርናታ! ...ተዛለቅናታ !" ... ላሎ ለይቶለት ወፈፈ።
ሚስቱ ከሱ ሰርቃ ሌላ ወንድ ጋር ሄዳ ከሆነ ይሄም ሲያንሰው ነው። ... ምሽት ቤቱ ሲገባ ካገኛት እንደ ማስቲካ ያላምጣታል...እንደ ቲማቲም ይከትፋታል ...እንደ እንቁላል ይጠብሳታል።
ዛሬ ያቺ ሴት ያከትምላታል በቃ !
ቀጣዩ የተዘጋው ዶሴ ታሪክ የነ ላሎ ታሪክ ነው።
ተራኪው ፖሊስ ተጠርጣሪው ግለሰብ ከቢሮ ወጥቶ ቤቱ በደረሰ ወቅት መጥረቢያ ይዞ ገባ። ... በያዘው መጥረቢያ የባለቤቱን አናት ፈርክሶ እዛው ልጆቻቸው ፊት ገደላት ። ምናምን እያለ ድምፁን እየጎተተ ሲናገር አስቤ አንፃረ ገፄን ሶስት ጊዜ አማተብኩኝ።
"ማንነቴን ታየዋለች!
ላሎ ማን እንደሆነ ታየዋለች ይህቺ ዋልጌ !"
ድምፁ ከመጮህ ወደ መንቀጥቀጥ ወረደ።
ሰው ሲናደድ ለካ ድምፁ የጎዣምን እንቅጥቅጥ ይደክራል። ሰማኸኝ በለው በሌለበት የላሎ ድምፅ እንደ ዝናብ ወረደ። ጉሮሮው ... አንደበቱ አብዮት ጨፋሪውን ሆነ። እንዝርት ሆኖ ሾረ።
ይሄ ሚስቱ ቺት ያደረገችበት ወዳጄን ምን ብዬ ላፅናናውና ላረጋጋው እችላለሁ ብዬ ተብሰለሰልኩ።
"እገድላታለሁ! " አለኝ ፈርጠም ብሎ።
"ተረጋጋ ላሎ! "
"አልረጋጋም " አንባረቀ። ጩኸቱ የደረሰች ሴት ማህፀን ከፍቶ ፅንስ ያስወርዳል።
እየፈራሁ እየተቸርኩ...
"ባለቤትህ ምን አደረገች ?" አልኩት።
"እሷ? "
"አዎ እሷ"
"እሷማ ከዚህ በላይ ምን ታደርግ? ...ኑሮ የሚያቃጥለኝና ቤቴን ሙሉ የማደርገው አንሶ ጭራሽ አልጋችን ላይ ?"
ዝም አልኩ።
መልሼ የጅል ጥያቄዬን ወረወርኩ።
"አልጋችሁ ላይ ምን? "
ላሎ ሲያስብ ቆየነ አንደበቱን ከፈተ...
"ትናንት የገዛሁላትን አምስት ሊትር ዘይት ስትደናበር አልጋችን ላይ ደፋችው "😃

ሚካኤል አስጨናቂ

@wegoch
@wegoch
@paappii
ሰላም እንዴት ሰነበታቹ ፥ በሸክላ ስራ ሙያ ላይ (የሚሸጡ አይደለም) እና በመምህርነት ሙያ ላይ የተሰማራችኹ ወይንም በዚኹ ሙያ ላይ ያለ የምታዉቁት ሰው ካለ በዚህ ሊንክ @Mykeyliyew አናግሩን።

@Wegoch
@Wegoch
@Wegoch
2024/09/23 13:24:02
Back to Top
HTML Embed Code: