Telegram Web Link
ርሳቸውን ሳስብ በሃገሬ ላይ ተስፋ አደርጋለሁ! !!!


ሽማግሌ የለም ሁሉም አሽቃባጭ ነው ። ትልቅ ህንጻ
እንጅ ትልቅ ሰው ጠፍቷል ። የሃይማኖት መሪ እንጅ
መንፈሳዊ መሪ አጥተናል ። አድር ባይ እንጅ ቆራጥነት
ጥሎን ሸሽቷል ። በዚህ መሃል ተስፋ ልንቆርጥ ስንባጅ
እነደ መጋቢ ሃዲስ እሸቱ ያለ የነፍስያ ምግብ እየፈተፈተ
የሚያጎርሰን ጎበዝ ባገኘን ጊዜ የነተበው አጥንታችን እንደ
ውሃ ዳር ቄጤማ ይለመልማል ። ተአምር ባጀበው
አንደበታቸው የደነዘውንና የሞተውን ኢትዮጲያዊነት
ከመቃብሩ ፈንቅለው ህያው ባደረጉት ጊዜ እንደገና
በሃገሬ ተስፋ ማድረግ እጀምራለሁ ። የሁልጊዜም
ንግግራቸው ከገዛ እውነታችን የተቀዳ ነውና ድምጻቸውን
በሰማሁ ጊዜ ራሴን ህዝቤንና ሃገሬን እየታዘብኩ
እቆጫለሁ ፤ እደመማለሁ እንደገናም አስባለሁ ። ከጥልቅ
ንግግራቸው ጀርባ ለእኔና ለኔ ዘመን የሚሆን ትልቅ የቤት
ስራ ቢሰጠንም ልብ ያልነው አልመሰለኝም ። ሁሌም
ከጣእመ ንግግራቸው ጀርባ ለኛ የሚተርፈውን የቤት ስራ
በደንብ እየሰራን ለመሆኑ እጠራጠራለሁ ። እንዲህም ሆኖ
ግን ሰውየው እንደ ተወርዋሪ ኮከብ በጨለመው
እሳቤያችን ላይ የዘሩትን ወገግታ ባሰብኩ ጊዜ ዛሬም
ባገሬ ሰው ተስፋ እንዳልቆርጥ ሆኛለሁ ። በዚህ ዘመን
በስስትና በጉጉት አይኔ የማስባቸው የዘመን ጌጥና
የትውልዱ ሀኪም ናቸውና አምላኬ ረጅም እድሜ ከጤና
ጋር ይሰጣቸው ዘንድ ከልቤ ተመኝቻለሁ! !!!


አረ እንደው ያሉበትን የሚያውቅ እንደው ቢጠቁመኝ......?


ሸጋ ምሽት ይሁንላቹ!!!!

@balmbaras
@wegoch
@wegoch
. የኢትኖግራፊ ጉዞ ወደ ጎጃም
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
ያ በእውቀቱ ስዩም የሚሉት ጎጃሜ ብላቴና አምናና ዘንድሮ የኛዋን ኦሮሚያን በብዕር
መነካካቱን አብዝቷል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ “ይሄ ልጅ ለምን አያርፍልንም? እኛም እርሱን
ስላፈራችው ጎጃም መጻፍ የማንችል መሰለው እንዴ” እያልን ከራሳችን ጋር ስንነጋገር
ቆይተናል (“እኛ” ወልደ-ገለምሶ ዘብሔረ ሀረርጌ በመሆናችን ባሰኘኝ ጊዜ እንደ ጃንሆይ
“እኛ” የማለት ሊቼንሳ ያለን ባለመብት መሆናችንን እያስታወሳችሁ!)፡፡ በዛሬዋ ሌሊት ግን
ነገሩ ይለይለት አልኩኝና ስለጎጃም መጻፍ ጀመርኩ፡፡ “አነ ወጠንኩ እጽሕፈ መጣጥፈ
ሕሩይ ለምድረ ጎጃም ዘነገደ ግዮን” እንዲል ግዕዙ!
አንቺዬ ጎጃም ነን ያላችሁ
ውረዱ እንያችሁ!
አዎን!! ዛሬ ወደ ጎጃም ልንጓዝ ነው! ደጀን ላይ ምሳ ልንበላ ነው! ዲማ ጊዮርጊስ ላይ ቅኔ
ልንዘርፍ ነው፡፡ ደብረ ወርቅ ላይ “ድጓ” ልንማር ነወ፡፡ ደብረ ኤሊያስ ላይ “ታሪከ አበው”
ልናነብ ነው፡፡ ማንኩሳ ላይ “ታሪከ ሀገር” ልንመረምር ነው፡፡ መርጡለ ማሪያም ላይ “ታሪከ
ነገሥት” ልንበረብር ነው፡፡ ቢቸና ላይ የበላይ ዘለቀን ጀግንነት ልናደንቅ ነው፡፡ መራዊ ላይ
በ“ድርሳነ እጽ” ልንፈወስ ነው፡፡ ባሕር ዳር ላይ ዓሳ ለብለብ ልንበላ ነው፡፡ የዛሬው
የኢትኖግራፊ ጉዞአችን ወደ ጎጃም ነው፡፡ ዳይ! ዳይ! ዳይ!
--------
ጎጃምን በቀዳሚው ዕድሜአችን (ከ1983 በፊት) በሚዲያና በትምህርት ቤት ባወቅናቸው
የጣና ሐይቅና የጢስ ዐባይ ፏፏቴ ውበት፣ የበላይ ዘለቀ የጀግንነት ገድል፣ የየትኖራ
ገበሬዎች ማህበር ብልጽግና እና የግሽ አባይ ኪነት ቡድን ሀገር አቀፍ ዝና አማካኝነት
ተዋውቀናት ነበር፡፡ ጉርስምና መጥቶብን ለአቅመ አዳም ካበቃን በኋላ በተጠናወተን የንባብ
ባህል ልደታቸው በጎጃም የተበሰረውን እነ አራት ዐይና ጎሹን፣ እነ ተድላ ጓሉን፣ እነ ራስ
አዳልን (ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን)፣ እነ ቆምጬ አምባውን፣ እነ ሙሉጌታን ሉሌን፣ እነ
ብርሃነ መዋንና ሌሎችንም ሀገር-አቀፍ አድባሮችን ስናውቅና ዝክረ ታሪካቸውን
ስንመረምርማ ጎጃምን ስለማየት ማለም ጀመርን፡፡ እያደር የህልማችን ጡዘት እንደ አባይ
ወንዝ እየተጥመለመለ ሲያራውጠን ደግሞ እኛም የወንዙ ልማድ ተጋብቶብን ህልማችንን
እንደ ግንድ ይዘን ስንዞር ባጀን፡፡ ይኸው እንግዲህ ብሩህ ህልም አልመን፣ ብሩህ ምኞት
አርግዘን፣ በአምሮት እየተጠለዝንና በፍላጎት እየተንጠራወዝን ከህልማችን ጋር እዚህ
ደርሰናል፡፡
ዋናው ተስፋ አለመቁረጥ ነው ጓዶች!! “ተስፋ…የደሃ ወዚፋ” እንዲሉ የሱፊ ከቢሮቻችን
(የ“ደሃ ሀብት” ማለታቸው ነው)፡፡ በርግጥም ጎጃምን ባናየውም “እናየዋለን” ማለታችንን
አላቆምንም፡፡ ወደፊትም በዚሁ እንቀጥላለን፡፡ ጀሊሉ አንድ ቀን ህልማችንን ያሳካልናል
ብለንም እናምናለን! ያ ቀን መጥቶ ምኞታችን እውን እንዲሆንልን በብርቱ እየተመኘን
የህልማችን ማስቀጠያ ትሆን ዘንድ ጎጃምን በዐይነ ህሊናችን ያየንባትን ጽሑፍ ለጀማው
እንዲህ እናበረክታለን፡፡
--------
አዎን! ዛሬ ፍኖተ ሰላም ነን! ዛሬ ጎዛምን ነን! ዛሬ ዳንግላ ነን! ዛሬ ሞጣ ነን! ዛሬ ዱርቤቴ ነን!
በምናባችን እንደ ኢስከንደር (እስክንድር) ባለ ክንፉን ሐሳብ-ወለድ ፈረሳችንን እየጋለብን
ወደ ተናፋቂው የጎጃም ምድር ገባን!
ከሁሉም ከሁሉም ከሁሉም በላይ
የጀግና አገር ጎጃም መጣሁ አንተን ላይ፡፡
የአገሬ የወንዜ ሸበላ
ቡሬ ዳሞት ነው ዳንግላ
ቆየኝ መጣሁልህ አንተን ብዬ
ጎጃሜ ነህ ሲሉኝ ተከትዬህ፡፡
ፍቅረ አዲስ ነቅዐ-ጥበብ የዛሬ 20 ገደማ ባወጣችው ካሴት ስለጎጃም ያዜመችውን ነው
በራሴ መንገድ እንዲህ የጻፍኩት (ዓመታቱ በጣም ስለሄዱ ከግጥሙ ስንኞች ግማሾቹን
ረስቼአቸዋለሁ)፡፡ እርሷ ጎንደሬ ስለሆነች በደጃፏ ላይ ያለውን የጎጃም ምድር መዘየርን
የውሃ መንገድ አድርጋው እንደኖረችው አንጠራጠርም፡፡ ከዓመታት በኋላ ደግሞ ነዋይ ደበበ
ተነሳና እንዲህ ብሎ አዜመ፡፡
ልቤ ፍቅር ሠራ አባይ ወዲያ ማዶ
የበላይዬን ዘር ጎጃሜዋን ወዶ፡፡
ሁለቱ ከያኒያን ለሸበላውና ለጉብሏ ነበር ያቀነቀኑት፡፡ እኛ የኢትኖግራፊ ወግ መሞካከር
እንደ ቁራኛ የተለጠፈብን ለማጅ ጸሐፊ ግን እገሌ እገሌ ሳንል ስለጎጃም ህዝብ በሙሉ
ብንዘምር ነው የሚያምርብን! የጎጃምን ምድር በሙሉ ብንዞር ነው የሚብስብን!
ጎጃም የነገረ መለኮት ሀገር! የጾመ-ድጓ ሀገር! የስንክሳር ሀገር! የቅኔ ማህሌት ሀገር!
የወረብ ሀገር! የሽብሸባ ሀገር! ቱባ የእምነት ርእዮቶችና አስተምህሮዎች የፈለቁበት
የሃይማኖት ምድር!
ጎጃም የቅኔ ሀገር! የግጥም ሀገር! የመዲና ሀገር! የዘለሰኛ ሀገር! የክራር ሀገር! የመሰንቆ
ሀገር! እጅግ ውብ የሆነ የኪነት ሀብት የሞላበት የጥበብ መንበር!
ጎጃም የሰዋስው ሀገር! የጽሕፈት ሀገር! የሥርዓት ሀገር! የዘይቤ ሀገር! የፈሊጥ ሀገር!
የውረፋ ሀገር! የነቆራ ሀገር! የስላቅ ሀገር! የአሽሙር ሀገር! የአንክሮ ሀገር! የኩሸት ሀገር!
የአግቦ ሀገር! አስገራሚ የአነጋገር ብሂሎችና የቋንቋ ዐውዶች የፈለቁበት ደብር!
ጎጃም የድግምት ሀገር! የመስተፋቅር ሀገር! የመስተዋድድ ሀገር! የአሸን ክታብ ሀገር!
የጥላ ወጊ ሀገር! አነጋጋሪ የሆኑ የመተትና የአስማት ስነ-ቃሎች የገነኑበት መንደር!
----
ስለጎጃም ልጽፍ ስነሳ “እኔም ትረካዬን እንደ በእውቀቱ ስዩም፣ እንደ ደመቀ ከበደ እና እንደ
ኑረዲን ዒሳ በግጥም ላስኪደው እንዴ?” አሰኝቶኝ ነበር፡፡ ምክንያቱ ምን መሰላችሁ?…
በጎጃሜዎች ዘንድ እንደ ልዕላይ ንግግር (elite speech) የሚወሰደው የመግባቢያ እና
የመናበቢያ መንገድ ቅኔ መዝረፍና የግጥም ስንኞችን መቋጠር ስለሆነ ነው፡፡ በርግጥም
የጎጃምን ሰው ረብጣ ብር አስታቅፈኸው ስድ-ንባብ ከምታነበንብለት ይልቅ የሀረሩን
“ሁልበት ብላሽ” በልተህ፣ የብላሽ ብዕርእን ጨብጠህ፣ ሁለት ስንኞችን ብቻ በመወርወር
ጆሮውን ብትኮረኩረው ይመርጣል ነው የሚባለው፡፡ ጎጃሜው ስለራሱ እንዲናገርና
ስለሀገሩ እንዲገልጽ በተፈቀደለት ጊዜም ግጥምና ቅኔውን ቢያስቀድም ነው የሚሻለው፡፡
ሌላው ነገር ይቅርና በርካታ የጎጃም ተወላጅ ስሙ ከአባቱ ስም ጋር ተቀናጅቶ ሲጻፍ አንድ
መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ትገነዘባላችሁ፡፡
እያደር አዲስ
ፍቅር ይልቃል
አዱኛው ሲፈራው
እስከ-አድማስ ማን-በግሮት
ስንሻው ተገኘ
ወዘተ….ወዘተ….
በእርግጥም የጎጃም ምድር ከቅኔና ከግጥም ጋር መርፌና ክር መሆኑ ዘወትር
የሚያስገርመኝ ጉዳይ ነው፡፡ እስቲ እንደ ዋዛ ተቋጥረው የሁላችንም ሀብት ለመሆን የበቁ
ህዝባዊ ግጥሞቻችንን ተመልከቷቸው፡፡ በጣም ልብ ከሚሰረስሩት መካከል ቀላል
የማይባል ቁጥር ያላቸው ከጎጃም የፈለቁ፣ አሊያም በጎጃሜዎች የተገጠሙ፣ ወይ ደግሞ
ስለጎጃም ስም የሚያወሱ ሆነው ነው የምታገኟቸው፡፡ ለአብነቱም ይህንን ግጥም ውሰዱ!!
ሞጣ ቀራንዮ ምነው አይታረስ
በሬ ሳላይ መጣሁ ከዚያ እዚህ ድረስ፡፡
“ክፉ ቀን” እየተባለ በሚጠራው የረሀብና የጠኔ ዘመን ህዝብ እንደ ቅጠል መርገፉን ያየ
ተመልካች ነው ይህንን የተቀኘው፡፡ በዘመኑ የረሀቡን ጽልመታዊ ገጽታና የጠኔውን አሰቃቂ
ድባብ የሚያሳዩ ብዙ ግጥሞችና ቅኔዎች ከየአቅጣጫው የተወረወሩ ቢሆንም ከሁሉም
በላይ ገንኖ የወጣው ይህ ጎጃም-በቀል ግጥም ነው፡፡ ገጣሚው “ቀራንዮ” እና ሞጣ
በሚባሉት አካባቢዎች ያየው የሬሳ መአት ናላውን ቢያዞረው ነው አሉ እንዲህ ብሎ
የተቀኘው፡፡
ጀግናው በላይ ዘለቀ “ስዩመ እግዚአብሄር የሆኑትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከስልጣን
ለመገልበጥ አሲረሃል” በሚል ያለ ጥፋቱ ተወንጅሎ በስሙኒ ገመድ በተሰቀለበትና
ጣሊያንን
በባንዳነት ያለገለገሉ ሰላቶዎች በየአጥቢያው በተሾሙበት ወቅት ደግሞ እንዲህ
ተብሎ ተገጥሞአል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡
ጎጃም በአንድ ክፍለ ሀገር ብቻ በተማከለበት ዘመን ዋና ከተማው ደብረ ማርቆስ ነበረች፡፡
ለዚህች ከተማ መቆርቆር ምክንያት የሆነው ሰው ሳሊሕ ጠይብ የተባለ ነጋዴ ነው አሉ፡፡
ይህ ነጋዴ ለአካባቢው የመጀመሪያ የሆነውን ቆርቆሮ ቤት በአሁኗ የደብረ ማርቆስ ከተማ
የሠራው 20ኛው ክፍለ ዘመን እንደባተ ነው፡፡ ታዲያ የጎጃም ሕዝብ የርሱን ቤት በጥንቱ
ዘመን ተወዳጅ ከነበረው “ደንገላሳ” የተባለ የፈረስ ግልቢያ ስልት ጋር በማቆራኘት እንዲህ
የሚል ግጥም ቋጥሯል ይባላል፡፡
ፈረሴን ኮርኩሬ ብለው ደንገላሳ
የሳሊሕ ጠይብ ቤት ቆርቆሮው ተነሳ፡፡
እንደዚህ ግጥም አዋቂ የሆነውን ጎጃሜ በአክብሮት ከቀረባችሁት በእጥፍ ያከብራችኋል፡፡
በነገር ወጋ ካደረጋችሁት ግን አለቀላችሁ!! ለትንኮሳችሁ ምላሹን ሲሰጥ ለጊዜው እንጀራ
ፍርፍር የመሰለ ቅኔ ቋጥሮ በሳቅ ያንፈራፍራችኋል፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ “ወስዋስ” ቢጤ
ይጀማምራችሁና “ይህ ጎጃሜ የወረወረብኝ ቅኔ የመስተፋቅር ፍላጻ ይሆን እንዴ?” በማለት
ህብሩን ለመመርመር ትነሳሳላችሁ፡፡ በምሽት ሰዓት የቅኔው ሚስጢር ሲገባችሁ ደግሞ ቀን
ከሳቃችሁት በላይ ንዴቱ አንጀታችሁን ንፍር ያደርጋችኋል፡፡
በቃ እመኑኝ ነው የምላችሁ!! ጎጃሜውን በፍቅር ብትቀርቡት ነው የሚያዋጣችሁ!!
በመውደድና በመደድ ከቀረባችሁት በሐሴት ፌሽታ ያንበሸብሻችኋል፡፡ በሙሐባ ድር
ተብትቦአችሁ ወደ ፍስሐ አፀድ ያስገባችኋል፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አርቲስቱ እንዲህ
በማለት የዘፈነው፡፡
የበላይን ጸባይ ይዘዋል ሰዎቹም
ለፍቅር ነው እንጂ ለጸብ አይመቹም፡፡
-------
ታዲያ ጎጃሜ ገጣሚ ብቻ አለመሆኑን እያስታወሳችሁ ጓዶች!! በዝርው ጽሑፍም ቢሆን
አደገኛ የሆነ ህዝብ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የአማርኛ የልበ ወለድ ድርሰት የጻፈው አፈወርቅ
ገብረ ኢየሱስ እና “አልወለድም” በተሰኘው አነጋጋሪ መጽሐፍ የሚታወቀው አመጸኛና ልበ
ደንዳና ደራሲ አቤ ጉበኛ የተወለዱት በጎጃም ምድር ነው፡፡ ከሁሉም ጸሐፊዎቻችን ብዙ
የተነገረለትና ልደቱ በጎጃም የተበሰረው የልብ ወለድ ደራሲ ግን ሌላ ነው፡፡
“ፍቅር እስከ መቃብር”ን የማያውቅ አለን?…የአማርኛ ልብ-ወለድ ድርሰቶች ጉልላት ተደርጎ
የሚታየው እርሱ ነው፡፡ በመጽሐፉ የተወሱት እነ በዛብህ፣ እነ ሰብለ ወንጌል፣ እነ ጉዱ ካሳ፣
እነ ፊታውራሪ መሸሻ ከቤተሰቦቻችን አባላት አንዱ እስኪመስሉን ድረስ በብዙዎቻችን ልብ
ኖረዋል፡፡ የወጣት አንባቢዎችን ልብ ሰቅሎ የሚወዘውዘው የመጽሐፉ አጸቅ በበዛብህና
በሰብለ-ወንጌል መካከል የነበረው ጥልቅ ፍቅር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቴዲ አፍሮ በለቀቀው
አዲስ አልበምም በጥንዶቹ መካከል የነበረውን ፍቅር እጅግ ልብ በሚነካ ግጥምና
በተዋበ ዜማ ዘክሮታል፡፡ የመጽሐፉን ይዘት በዘመኑ ከነበረው የተዘበራረቀ የማኅበረሰብ
አወቃቀር እና የደራሲው ተራማጅ አስተሳሰብ ጋር በማነጻጸር የገመገሙ ምሁራን ግን
“መጽሐፉ የተጻፈበት ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተጭኖ የነበረውን የፊውዳል
ስልተ-ምርት አስከፊነት በተዋዛ ቋንቋ ማስተማርና የስርዓት ለውጥ እንዲደረግ በስልታዊ
ዘዴ መጎትጎት ነው” ይላሉ፡፡
በርግጥም ደራሲው ለህዝብ የነበረውን ተቆርቋሪነት ያስተዋለ ሰው ከምሁራኑ አባባል ጋር
ይስማማል፡፡ ለምሳሌ በደራሲው ብዕር የተቀረጸው ካሳ ዳምጤ (ጉዱ ካሳ) የተሰኘ ገጸ-
ባሕሪ የፊውዳሉን ሥርዓት በመረሩ ቃላት ሲሸረድደው ከመጽሐፉ እናነባለን፡፡ ይህ ገጸ-
ባሕሪ “በአጥር ካብ ከስር ሆኖ ከላዩ ሌላ ግዑዝ የተጫነው ድንጋይ ለዘልዓለም እንዲሁ
አይኖርም፣ ካቡ ሲያረጅ ከላይ ያለው ድንጋይ ተንዶ መንከባለሉ የማይቀር ነው” እያለም
የሥርዓቱን መውደቅ ሲተነብይ እናያለን (ዐረፍተ-ነገሩ ቃል በቃል አልተጻፈም)፡፡ በሌላ
በኩል በዘመኑ ቱባ የመንግሥት ባለስልጣን የነበሩት የመጽሐፉ ደራሲና እንደርሳቸው
ተራማጅ የነበሩት አስር የዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በቢሾፍቱ ሐይቅ
ዳር ተሰባስበው ከተነጋገሩ በኋላ በቃለ-ጉባኤ መልክ የጻፉት ደብዳቤ ከጥቂት ዓመታት
በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ታትሞ አንብበነው ነበር፡፡ ያ ደብዳቤ ንጉሠ ነገሥቱ በሀገሪቱ
ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በማካሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ ነፃነት እንዲሰጡ ይጠይቃል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ግን ጥያቄአቸውን በጄ አላሉትም፡፡ ሁሉንም ሹማምንት ጥርግርግ አድርገው
ከስልጣን አባረዋቸዋል፡፡
እንግዲህ በዚያ ታላቅና ዘመን ተሻጋሪ (classic) ድርሰት የተነገረው ታሪክ በአብዛኛው
የተፈጸመው በጎጃም ነው፡፡ ከዘመኑ ቀድሞ ማየት የቻለውን ያንን አስተዋይ ደራሲ
ያፈራውም የጎጃም ምድር ነው፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁ ይባላል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ለአማርኛ ስነ-ጽሑፍ እድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ በ1991 የክብር የዶክትሬት ዲግሪ
ሰጥቶታል (አንቱታውን የተውኩት ወደዚህ ላቀርበው ብዬ ነው)፡፡
-------
ስለጎጃም ሳስብ ዘወትር የሚደንቀኝ ሌላኛው ነገር ስሙ በታሪክ ድርሳናት የተጻፈበት አኳኋን
ነው፡፡ ያ ምድር በጽሑፍ ምንጮች “ጎጃም”፣ “ጎዣም”፣ “ጐጃም” እና “ጐዣም” እየተባለ
ተወስቷል፡፡ ከዐፄ ዓምደ ጽዮን ዘመን ጀምሮ በተጻፉ ድርሳናት ውስጥ አራቱንም ስሞች
ለማየት ይቻላል፡፡ ስሞቹ የተለያዩ ፍቺዎች እንዳሏቸው ሰምቼ አላውቅም፡፡ በስሞቹ
መጀመሪያ ላይ የሚጻፉት “ጎ” እና “ጐ” ተመሳሳይ ድምጽን እንደሚወክሉ ማንበቤን
አስታውሳለሁ፡፡ ይሁንና በስሞቹ መሀል ያሉት “ጃ” እና “ዣ” የተለያዩ ድምጾችን
እንደሚወክሉ እየታወቀ ክፍለ ሀገሩ “ጎጃም” እና “ጎዣም” ተብሎ መጠራቱ ሁል ጊዜም
ሲገርመኝ ኖሯል፡፡ ለዚህ ማብራሪያ የሚሰጠን አካል ይኖር ይሆን? በከፍተኛ በጉጉት
እንጠብቃለን፡፡
(ይቀጥላል)
----
አፈንዲ ሙተቂ
ሀምሌ 21/ 2009
በአዳማ ከተማ ተጻፈ፡፡
-----
ይህ ጽሑፍ ተስፋፍቶና ዳብሮ "የኤርትራ ህልም" በተሰኘው መጽሐፌ ውስጥ ቀርቧል።

@balmbaras
@wegoch
@wegoch
. ==የሩሚ ወግ==
ከአፈንዲ ሙተቂ
---------
አራት ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚያም ሰዎች ግሪክ፣ ፋርሲ (ኢራናዊ)፣ ዐረብ እና ቱርክ ነበሩ፡፡ የሚፈልጉትን ነገር ይገዙበትም ዘንድ የተወሰነ ገንዘብ ተሰጣቸው፡፡ ግሪኩ “እኔ ስታፊል አምሮኛል፤ ስታፊል ግዙልንና እንበላው” አለ፡፡ ፋርሲው “የምን ስታፊል? ኡዙም ግዙልን እንጂ ሰዎች” አለ፡፡ ሶስተኛው “አረ ወደዚያ! ኢነብ ነው የምንገዛው፤ ኢነብ መግዛት አለብን” በማለት ተናገረ፡፡ ቱርኩ “እንዴ! አንጉር ነው መግዛት ያለብን፤ አንጉር እንጂ ሌላ ነገር አትግዙብን” አለ፡፡ አራቱ ሰዎች ተከራከሩ፡፡ ተነታረኩ፡፡ በጭራሽ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ እንዲህ እየተወዛገቡ ሳለም አንድ መንገደኛ መጣ፡፡ “ምንድነው የሚያጨቃጭቃችሁ?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ ጉዳዩን ነገሩት፡፡ ሰውየውም “በዚህ ፍራንክ የሁላችሁንም ፍላጎት ማሟላት ይቻላል” አላቸው፡፡ ሰዎቹም “እንዴት?” በማለት ጠየቁት፡፡ ሰውዬም ገንዘቡን እንዲሰጡት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም እንደተባለው አደረጉ፡፡
መንገደኛው ሰውዬ በአካባቢው ከነበረ የፍራፍሬ መሸጫ ገብቶ አንዱን የፍራፍሬ ዓይነት ገዝቶ ሲወጣ አራቱ ሰዎች ተያዩ፡፡ በዚያው በሳቅ ፈረሱ፡፡ ለካስ አራቱም የአንዱን ፈራፍሬ ስም በየቋንቋቸው እየጠሩት ነበር? አራቱም “ወይን እፈልጋለሁ” እያሉ ነበር የሚከራከሩት፡፡
(ጀላሉዲን ሩሚ፤ መሥነቪ፣ Trasnslated by UNESCO as “Tales from Masnavi”፣ የገጽ ቁጥሩንና ዓመቱን ረስቼዋለሁ)
* * * ሩሚ ከዛሬ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የጻፉት ወግ ዛሬም ድረስ እውነት ሆኖ ይሰራል፡፡ ዛሬም አንድ ዓይነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ፍላጎታቸውን በሚገልጹበት መንገድ ብቻ ይነታረካሉ፡፡ ዛሬም ሰዎች ተመሳሳይ ግብ ኖሯቸው በስልት /ታክቲክ/ ብቻ ይወዛገባሉ፡፡ከዚህ እልፍ ሲልፍም አንድ ዓይነት ግብ የሚያልሙ ነገር ግን በስልት የሚለያዩ ሰዎች፣ ቡድኖች፣ ክበቦች፣ ማህበራት፣ ፓርቲዎች ወዘተ… እስከ መገዳደል የሚደርሱበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ከሁሉም ዘንድ የጠፋው በሩሚ ወግ የተጠቀሰው የአስታራቂው መንገደኛ ቢጤ ነው። አሁን ባለንበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንደ መንገደኛው አስታራቂ ያለ አርቆ
አስተዋይ ሰው በእጅጉ ያስፈልገናል። አላህ ለእኛም አርቆ አስተዋለ አስታራቂዎችን ይላክልን።


@balmbaras
@wegoch
@wegoch
(በላይ በቀለ ወያ)

ክርስቶስ ዘረኛ ቢሆን (መቼም አይሆንም እንጂ!!!)
"እኔ ፡ታግዬ፡ ታስሬ፡ተገርፌ፡ተሸክሜ ፡ተሰቅዬ ፡ሞቼ፡ ባመጣሁት፡ መስቀል፡እናንተ፡ ችቦ፡ታበራላችሁ።" ይለን ፡ ነበር ።
መልካም በዓል።🌼
@wegoch
@yeyhudaanbesa
🌻🌻
ይትቀደስ ስምከ
በሀይለ መሥቀልከ
በዕፀ መሥቀልከ ክቡር
ዘ አእበዮከ ለ ስምከ(2×
ስብሀት ለከ ለባዕቲትከ ልዑል(2×



" የመሥቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለ እኛ ለምንድን ግን የ እግዚአብሔር ሀይል ነው"


🌻🌻እንኳን ለ ብርሀነ መስቀሉ አደረሰን አደረሣችሁ🌻🌻

ከ-🌻 ግጥም ብቻ

@wegoch
@getem
፡፡፡፡፡እሱባለው አበራ፡፡፡፡

ከሚነደው የእሳት ግምጃ ተጠግተን በያዝነው የፍቅር ዘንግ፤ ነዲደ እሳቱን እየቆሰቆስን በእሸታማ ገላችን ሐሴት የተባለ ልጅ እንፈለፍላለን። የነበልባለ ብልጭታ ፍንጥርጣሪዎቹ ክንፍ አውጥተው ሰማዩ ላይ ይበራሉ። አንዷ የእሳት ነቁጥ ተሰንጥራ አየር ላይ ሁለት ትሆናለች። ፍቅሬ. . . ሁለቱን በራሪ የእሳት ቀያይ ኳሶች ሰርቃ በግርምት እያየች “ ፍቅር. . . እያትማ አንዷ እሳት ሁለት ስትሆን ! ” አለቺኝ። ቀና ብዬ በውኃ ሰማያዊው ሰማይ ላይ የሚሰርጉትን ፈዛዛ የእሳት ብናኞች ተመለከትኳቸው። ብናኞቹ ጠፍተው ከአይኖቻችን ሲሰወሩ፤ ፊቷን ወደ እኔ እንድትመልስ በጣቶቼ ጋበዝኳት። ማራኪ ጨረቃማ ፊቷን አዙራ፤ በስልምልም ዜማማ አይኖቿ የአይኖቼን በዐፍአ ተሳለመች። እኔም “ ይኸው አሁን ደግሞ የማይጠፋፉ ሁለት የእሳት ፍንጥርጣሪዎች አንድ ሲሆኑ ተመልከቺ ” ብዬ ከናፍረ — ጨረቃዋ ላይ በከናፍሬ ተነክሬ ቀረሁ።

እንዲህ እሳት ነበረችና። እኔም እንዲህ እሳት ነበርኩና።

@tekuye17
@wegoch
ለፈገግታ 😁😁😁


አንዱ ነው አሉ ሺሻ ቤት ገብቶ ..ለረጅም ሰዐት ሳያስቀይር ይስበዋል ..
...
አስተናጋጇ ተናዳ "ወንድሜ ተቃጥሏል እኮ በቃ ለምን አተወውም ....ወይስ እንደ ዳመራ
እስኪወድቅ እየጠበቅከው ነው ?"


@balmbaras
@wegoch
@wegoch
ይድረስ ለዘር ፖለቲከኞች !!!

በመሻኢኮቹ ሃገር ወሎ ዛሬም እንደ ተወርዋሪ ኮከብ የሚንቦገቦግ ሃሳብና ኢልም ያላቸው
እነ ሸህ መሃመድ ሃምዲንን የመሰሉ አሊሞች እየተገለጡልን ነውና አልሃምዱሊላህ
እንላለን!!!!!!
የወሎው አልሃዛር ወሎ ማር ዘነቡ ፤
አያወላውልም ሃቅ ነው ኪታቡ ።
ማለታችን ሃቅ እኮ ነው !!!!!
ዛሬም ነገም ዘራችንን ፈልገን በምርጫችን አላገኘነውም ። ስለሆነም በዘራችን አናፍርም
አንኮራም ። የሚያሳፍርም የሚያኮራም ስራችን ብቻ ነው!!!!!
እኛም እንደነሸህ ዘርና ዘርዛሬ አላህ ያንሳህ!!!!!! በዘርና በዘር ማንዘር የተሰራን ዘማማ ጎጆ
አፍርስ !!!!! አርከባስ ብለናል!!!!#


@balmbaras
@wegoch
@wegoch
. የኤርትራ ህልም!
---------
ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
---------
ኤርትራ ድሮ ከእኛ ጋር ነበረች፡፡ አጼ ኃይለ ሥላሤ ለሁላችንም አስፈላጊ የነበረውን
የፌዴሬሽን ፎርሙላ ሰረዙትና ህዝቡን አስቀየሙት፡፡ ደርግ ደግሞ የራሳችንን ህዝብ እንደ
ባዕድ እየቆጠረ በመትረየስ አጨደው፡፡ በታንክ ደመሰሰው፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣቱ “አደይ
ኤሪቲሪያ”ን እየዘመረ ወደ ባርካና ሳህል ነጎደ፡፡ ራሱን አደራጅቶ ጀብሃና ሻዕቢያ ሆኖ መጣ፡፡
ውጤቱም 1983 ላይ ታየ፡፡
የደርግና የኃይለ ሥላሤ መንግሥታት ያደረጓቸው ነገሮች ሲገርሙን በጣም ግራ
የሚያጋባው ሶስተኛው መንግሥታችን መጣ፡፡ ይህ የኛ መንግሥት በጅምሩ ላይ ሰላም
ፈላጊ መስሎ ቀረበ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን መንግሥቱ ከሚከተለው ግልጽነት
የጎደለው አሰራር የተነሳ በ1990 ሺዎችን ያረገፈ ግዙፍ ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ከአንድ ምንጭ
የተቀዱ ህዝቦች ተጋደሉ፡፡ እነሆ ዛሬም ድረስ ነገሩ ሳይለይለት በጨለማ ውስጥ ነው
ያለነው፡፡
እኛ ግን ተስፋ አንቆርጥም! በአያያዝ ጉድለት የተለየንን ወገናችንን መመለስ እንፈልጋለን፡፡
ህዝቡ ለጊዜው ሪፈረንደም አድርጎ ነጻነቱን ማወጁን እናደግፋለን፡፡ ቢሆንም ህልም
አይከለከለምና አንድ ቀን ተቀራርበን በጋራ ስለመስራት እንወያይ ይሆናል ብለን
እናልማለን፡፡ የኛ ልጆች ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ስለመስራት ያስቡ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜም
አሁን የምንመኘው በአንድነት ውብ የመሆን ሚስጢራችን ይመለስልናል ብለን እንመኛለን፡፡
ምን ይታወቃል? ለፈጣሪ የሚሳነው ነገር የለም፡፡
ወገኖቼ ደጉን ነው የተመኘሁት፡፡ በቅን ልቦና በርትተን ከጸለይንና ከኛ የሚጠበቀውን
ካደረግን ሁሉንም የሚችለው ፈጣሪ ህልማችንን እውን ያደርግልናል ብለን ተስፋ
እናደርጋለን፡፡
-------
ምን እንደጣለብኝ እንጃ! ያንን ምድር እጅግ ሲበዛ እወደዋለሁ፡፡ እኔ ለተወለድኩበትና
አብዛኛውን ዕድሜዬን ለጨረስኩበት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልል ጎረቤት ከሆነችው ሶማሊያ
ይልቅ በ1600 ኪ.ሜ. የምትርቀው አስመራ ናት የምትናፍቀኝ፡፡ ስለሶማሊያ የተጻፈ መጽሐፍ
ማንበብ ብዙም አይማርከኝም፡፡ ስለ ኤርትራ የተጻፈ መጽሐፍ ካጋጠመኝ ግን ሳላየው
አላልፍም (ይህ ግን ሶማሊያን ከመጥላት እንደማይቆጠርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ)፡፡
ታዲያ በርካቶቻችሁም እንደኔው ትመስሉኛላችሁ፡፡ ለምሳሌ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲታተም
የቆየው የበኒ አምሩን ወጣት የሚያሳየው ፖስተር ዛሬም ድረስ ከኛ ጋር ተሳስሮ ነው ያለው፡፡
አሁንም ድረስ በበርካታ ስፍራዎች ተለጥፎ አይቼዋለሁ፡፡ በፌስቡክም እርሱን እንደ
ፕሮፋይል ፒክቸር የሚጠቀም ኢትዮጵያዊ ሞልቷል፡፡ በሌላ በኩል የኤርትራን ሙዚቃ
የሚያዳምጡ ሰዎች በሽ ናቸው፡፡ ደራሲ መሐመድ ሳልማን መቐለ ሄዶ ያየው ነገር
ቢያስገርመው “በኤርትራ ሙዚቃ የምትጨፍር ከተማ” የሚል አስደናቂ ወግ ጽፎ እውነቱን
አስረድቶናል፡፡ መንግሥታት ቢጣሉ እንኳ ህዝቦች ምንጊዜም እንደሚነፋፈቁ ከዚህ በላይ
የሚያስረዳ ዋቢ ያለ አይመስለኝም፡፡
--------
ማርታ ሀይሉን አስታወሳችኋት? አዎን! ማርታን “ብራ… ነው… ብራ ነው”፤ “አዘዞ”፤ “ሎጋ
..ና እናውጋ” በተሰኙት ዘፈኖቿ እናውቃታለን፡፡ ከማርታ ዘፈኖች ዘወትር ቀልቤን ይገዛ
የነበረው ግን የትግርኛ ዜማዋ ነው፡፡ አዝማቹ እንዲህ ይመስለኛል፡፡
ካብ አስመራ ድንገት ርእዮ
ምጽዋ ገባሁ ልበይ ሕብዮ፡፡
እንተርጉመው እንዴ?… ግድ የለም ማርታ ራሷ እንዲህ እያለች በአማርኛ ተርጉማዋለች፡፡
“ከአስመራ ድንገት አይቼው
ምጽዋ ገባሁ ልቤን ሰጥቼው”፡፡
አዎን! ትናንት የኛ ናት ስንላት ለነበረችው ኤርትራ ነው እንዲህ የዘመርንላት፡፡ ዛሬም
ብንዘምርላት እንከበራለን እንጂ አንወቀስም፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት ደረጃ ነው
የተለያየነው፡፡ ሁለት ፓስፖርት እንዲኖረን ነው የተደረግነው፡፡ ሁለታችንም ግን አንድ
ህዝቦች ነን፡፡ በደምም ሆነ በባህል በጣም የተዋሃድን የአንድ መሬት ብቃዮች ነን፡፡
ሁለታችንም የተዋብን የሴምና የኩሽ ህዝቦች ውቅር ነን፡፡ እንደኛ የሚያምር ህዝብ
በትኛውም ዓለም የለም፡፡ የጀበና ቡና፣ ዶሮ ወጥ፣ ድፎ ዳቦ፣ የስጋ ፍትፍት፣ አምባሻ፣
ወዘተ…. ሁለታችን ዘንድ ብቻ ነው ያለው፡፡
-----
በርግጥ እላችኋለሁ፡፡ በምንባብና በወሬ እንጂ በአካል የማላውቃት ኤርትራ ትናፍቀኛለች!
ያ በታሪክ ምዕራፎች “ምድሪ ባህረ ነጋሽ” እየተባለ ሲጠራ የኖረው ጀግና መሬትና ህዝብ
ይናፍቀኛል፡፡ ያ የሰሜኑ በረኛ እያልን ስንመካበት የነበረው ህዝባችን ይናፍቃል፡፡
እውነትም ኤርትራ ! የዳማት ታሪክ ውቅር! የመጠራ አብያተ መንግሥታት ከርስ! የሀውልቲ
ፍርስራሾች ቀብር! የአዱሊስና የዙላ ወደቦች መዘክር! የሱዋኪምና የዳህላክ ሱልጣኖች
ደብር!
ኤርትራ የአብረሃ ደቦጭ ሀገር! የሞገሥ አስገዶም ሀገር! የዘርዓይ ደረስ ሀገር! የሎሬንዞ
ታዕዛዝ ሀገር! የደጃች ሀረጎት ሀገር! በአይበገሬ ጀግንነታቸው ድፍን አፍሪቃን ያኮሩ
አርበኞች የበቀሉበት ምድር!
ኤርትራ የበረከት መንግሥተ አብ ሀገር! የአብረሃም አፈወርቂ ሀገር! የአሕመድ ሼኽ ሀገር!
የሄለን መለስ ሀገር! የየማነ ባሪያው ሀገር! የሄለን ጳውሎስ ሀገር! በስርቅርቅ ድምጻቸው
የሰውን ልብ እየሰረሰሩ የመግባት ሀይል ያላቸው የጥበብ ከዋክብት የወጡበት መንደር!
ኤርትራ የፊያሜታ ጊላይ ሀገር! የስዕላይ በራኺ ሀገር! የኦቦይ ተኽሌ ሀገር! የተክላይ
ዘድንግል ሀገር! የሆቴል ፓራዲዞ ሀገር! የዕቁባይ ሲላ ሀገር! የምንወደው ደራሲያችን በዓሉ
ግርማ በ“ኦሮማይ” መጽሐፉ እንደ ፊልም ግልጥልጥ አድርጎ እየተረከልን ዝንተ-ዓለም
እንድንወዳት ያደረገን የቀይ ኮከብ ትዝታ ወመዘክር!
ኤርትራ የፊዮሪ ሀገር! የሳባ ሀገር! የማርቲና ሀገር! የብርኽቲ ሀገር! ፊያሜታ ጊላይን
የመሳሰሉ “ሽኮሪናዎች”ን ያበቀለች ውብ የውቦች እመቤት!
-----
ኤርትራን ስንጠራ በቅድሚያ ወደ አዕምሮአችን የምትመጣው አስመራ ናት፡፡ የአስመራ
ናፍቆት ይገድላል፡፡ አስመሪና፣ አስመሪቲ፣ አቲ ጽብቕቲ!…
ውይ ስታምር! “ቀሽቲ” እኮ ናት፡፡ ያኔ በልጅ አዕምሮአችን በዘምባባ ጥላዋ ተሸክፋ
በፖስትካርድ ስትቀርብልን “የኛ ውቢት” እያልን እንመጻደቅባት ነበር፡፡ እንቆቅልሽ
ስንጫወትና መልሱ ጠፍቶን “ሀገር ስጠኝ” ስንባል እርሷን ለመስጠት እንሰስት ነበር፡፡
ጠያቂውም የዋዘ ስላልሆነ “አስመራ” ካላልነው ለጠየቀን ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ
አይነግረንም ነበር፡፡ ከማናውቃቸው “ዋሽንግተን” እና ሮማ ይልቅ አስመራ ነበር
የምትበልጥብን፡፡ በትምህርት ቤት መዝሙራችንም እንዲህ እንል ነበር፡፡
ኦኬ ኦኬ ኦኬ ስራ
ሰላም ሰላም ወደ አስመራ
አዲስ አስተማሪ ከጃፓን የመጣ
ማስተማሩን ትቶ በቦክስ የሚማታ
አናግረኝና አናግርሃለሁ
በአሜሪካ ሽጉጥ አዳፍንሃለሁ፡፡
አማርኛም አልችል ትግርኛም አልሰማ
ሰተት ብዬ ልግባ አስመራ ከተማ፡፡
ግጥሙ “አንታራም” የሚሉት የህጻናት ጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን አስመራ ከልባችን
እንዳትጠፋ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ዛሬም በልባችን ነግሳለች አስመሪና!
----
አስመሪና! እቲ ሽኮሪና! ሰሜናይት ጽብቕቲ! በዓሉ ግርማ ላንቺ ክብር የጻፈው ትዝ ይልሻል?
እስቲ እናስታውሰው!
አስመሪና አስመራዬ
ካብ ሐንቲ ንግሥቲ ይበልፅ መልክእኪ
አማአድዬ ክርእየኪ ከሎኹ ኽአ
አብ ኢደይ ዘሎ ነገር ይወድቕ፡፡
(አስመራ አስመራዬ)
(ከአንድ ንግሥት ይበልጣል መልክሽ)
(በሩቅ ሲያይሽ በውበቷ ስለተማረከ
በእጄ ያለ ነገር ሳይታወቀኝ ይወድቃል)
------
ጸጸራት፤ ፎርቶ፣ ሐዝሐዝ፣ አርበእተ አስመራ፣ እምባጋሊያኖ፣ ኮምቢሽታቶ፣ አዲ ጓእዳድ፣
ቃኘው፣ ማይተመናይ፣ ሰምበላይ፣ ጎዳይፍ፣ ገጀረ
ት፣ ወዘተ… በጽሑፍ የማውቃቸው
የአስመራ ሰፈሮች ናቸው፡፡ አንድ ቀን በሆነልኝና ባየኋቸው እያልኩ አልማሁ፡፡ እነዚህ
አስገራሚ የአስመሪና ሰፈሮች ብዙ ባለታሪኮችን አብቅለዋል፡፡ ብዙዎች ገድላቸው
እየተደጋገመ ሲነገርላቸው እሰማለሁ፤ አነባለሁ፡፡ ለኛ ቅርብ የነበረ አንድ ውድ ልጅ እየተረሳ
በመሆኑ ግን አዝኛለሁ፡፡
አማኑኤል እያሱ ይባላል! አስታወሳችሁት አይደል? አዎን! አማኑኤል በኛ ዕድሜ ዘመን
ኢትዮጵያ ዋንጫ መብላት እንደምትችል ያስመሰከረው የታላቁ የ1980 የእግር ኳስ
ቡድናችን ቋሚ ተሰላፊ ነበረ፡፡ የማሊያ ቁጥሩ 2 ይመስለኛል፡፡ አማኑኤል የያኔው ቡድናችን
ባደረጋቸው ሁሉም ጨዋታዎች ተሰልፏል፡፡ ቡድኑ ዋንጫውን ሲበላም ከጓደኞቹ ጋር
ቤተመንግሥት ድረስ ተጋብዞ ተሸልሟል፡፡ አማኑኤልን ያስገኘው ከዚያ ዘመን ዝነኛ
ቡድኖቻችን መካከል አንዱ የነበረው የኤርትራ ጫማ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን የኤርትራ
አንደኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን በተደጋጋሚ ያሸነፈ ነው፡፡
አማኑኤል እያሱ በኢትዮጵያ ትቅደም አንደኛ ደረጃ ዋንጫም ለኤርትራ ክፍለ ሀገር ምርጥ
ቡድንም ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ባልሳሳት የ1981 የኢትዮጵያ ዋንጫን ያሸነፈው እነ
አማኑኤል የነበሩበት የኤርትራ ክፍለ ሀገር ቡድን ነው፡፡ የአማኑኤል እያሱን ወሬ ለመጨረሻ
ጊዜ ያነበብኩት በ1988 ለወዳጅነት ጨዋታ አዲስ አበባ መምጣቱን በማስመልከት
በርካታ የግል ጋዜጦች ቃለ-መጠይቅ ባደረጉለት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ በምን ሁኔታ ላይ
እንዳለ መረጃው የለኝም፡፡ እስቲ የአስመራ ልጆች ወሬው ካላችሁ ስለአማኑኤል እያሱ አንድ
ነገር በሉን፡፡
-----
(በመጽሐፉ ውስጥ "የኤርትራ ህልም" በሚል ርእስ ለቀረበው ረጅም የኢትኖግራፊ ወግ
የመነሻ መሠረት የሆነው ይህ አጭር ጽሑፍ ነው። ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ መጽሐፉን
ይግዙ)።


@balmbaras
@wegoch
@wegoch


ሽብርቅርቅ ያለች ቅዳሜ ትሁንላቹ!!!!!!!
የሚስቴ ሰርግ ማስታወሻ
(ልዑል ሀይሌ)
......................................................
ውዴ! ምንም እንኳ ቁመቴ አጥሮ ለሌላ ሲድሩሽ አማትሬ ማየት ቢሳነኝም በቤታችሁ አጥር ተንጠላጥዬ ናፍቆቴን ልገልፅልሽ እንደምንም የደረሰውን እጄን አወዛውዤ ነበር።ነገር ግን የአባትሽ ከዘራ
ከአንቺ የናፍቆት ምላሽ ቀድሞ እጄን ስለሰበረኝ ካንቺ በፊት ስለ አባትሽ
ከዘራ ልፅፍ ቀሪዋን ግራ እጄን አለማምጃለሁ!(ለካ አሁን ሲገባኝ የቀኝ
እጅ የቀለም ቀንድ የግራ እጅ መሃይም ኖሪያለሁ)...እውነት ውዴ!..አባትሽ አባትሽ
ባይሆኑ እንዲህ እላቸው ነበር።

"ምነው እጄን ነሱኝ
ልጆን ሰላም ልላት አንድ እጄን ሳነሳ፤
ከዘራዎት ነው ወይ
ለልጆ የተዳረ ያ ጎበዝ ጎልማሳ።"
.
እውነት ውዴ አባትሽ አባትሽ ባይሆኑ እንዲህ እላቸው ነበር
"ይኸው ዕድሜ ለእርሶ ዱላዎት ሰብሮኛል፤
ለድብደባ ሱሶ ነገ ልምጣሎት ወይ አንድ እግሬ ቀርቶኛል።"

ነገር ግን የአባትሽን አባት መሆን ልሽር አይቻለኝምና።ወደ ከዘራው ተሸጋግሬ ልወቅሰው ተነሳሁ። ውዴ! ያ ከዘራ የአባትሽ ሆነ እንጂ ሌላ ከዘራ ቢሆን እንዲህ ብዬ ቅስሙን ልሰብረው ተነስቼ ነበር(አይጣል የከዘራ ቅስም!)

"ምን አይተህ ነው ከ`ጄ አጥንት የሰበርከው
ሲቀር ተከፋህ ወይ አምና የለመድከው"

ዳሩ ምን ያደርጋል ከዘራው የአባትሽ ስለሆነ ትቼዋለሁ...ለነገሩ ምን አለፋኝ አጥር ዘልዬ እጄን እንዳነሳ፤ አባትሽም ከዘራቸውን እንዲያነሱ ምክንያት የሆንሺው አንቺ አለሽ አይደል?! ብዬ ወዳንቺ ልዞር አሰብኩኝ። እውነት ውዴ!...አንቺ አንቺን ባትሆኚ እንዲህ ብዬ ባለማመድኳት ግራ እጄ ልፅፍልሽ አስቤ ነበር

"ናፍቆት አንገብግቦኝ እጄን ባነሳልሽ፤
የአምናው ክህደት ዳዴ
በአባትሽ ከዘራ እግ፡ር አወጣልሽ፤
ክህደትሽስ ይሁን ይቁም እግር ያውጣ፤
ልብ ይሰበራል ወይ
ፍቅሩን ሊገልፅልሽ ለሰርግሽ ለመጣ።"

ምን ዋጋ አለው?! አንቺ አንቺ ሆነሻል...
ምን ያደርጋል!?..ከዘራውን መንካት አባትሽን፤ አባትሽን መንካት አንቺን፤
አንቺን መንካት የገዛ ራሴን ህመም መቀስቀስ ስለሚሆንብኝ ልተወው
ተገድጄአለሁ! ...ምክንያቱም አፈቅርሻለሁ !..የፍቅሬ ልክ ክደሽኝ ሄደሽ
እንኳ በሰርግሽ ዕለት በአጥራችሁ ተንጠልጥዬ የአባትሽ ከዘራ ሲሳይ
ሆኜ በመመለስ ገልጫለሁ። ያወዛወዝኩትን እጄን በቅፅበት አይተሽው
ከሆነ ለስንብት እንዳነሳሁት ታውቂልኝ ዘንድ አሳውቅሻለሁ...(ትዝታ
ሲቀሰቅስ የሚቀጥል...)
፲፰-፩-፳፻፲፩
ከለሊቱ ፭ ሰዓት ከ ፲፭

@lula_al_greeko
@getem
@getem
...............አምባገነንነት በዚ ቤት
አምባገነንነት ሚሠራው ጭንቅላት ውስጥ ነው። ከዛ ወደ ቃታ ያድጋል።
በተለይ ተማርን በምንል ሠወች ሲሆን አምባ ገነንነት የበለጠ አጥፊ ይሆናል።
ይሄን ስነ-ልቦና የሚሠራው በማህበረሠቡ ነው (ህዝብ መሪውን ይሠራል እንዲሉ)።
ሂትለር ስልጣን ሲይዝ ለፍፁምነት በቀረበ ነፃ ምርጫ አሸንፎ ነው። ከዛም ማህበረሠቡ ያሣደጋቸውን ሚቶች (አፈ ታሪኮች)በተለይም 13ቱን ነቅሶ አዎጥቶ ይሁዲና ሴሞች ላይ ዘመት። ህዝብም ስለሡ ሞገስ በደስታ ወጣ እንዲሁም ህዝብ በስራው አለቀ።
እኛም የዛ ውጤት እየሆንን ነው።
ቻናሉ ላይ "እንዴት ይሄን አልክ? ለምን ይሄንን አሰብክ" ብሎ እሱ የበላውን አንተ እንድታቀረሽለት የሚሻ ; እቤቱ ከወንድሙ ጋ መቻቻልና በሀሳብ መጣስ ሲያቅተው በንዴት መአዱን ድፍቶ ይወጣና እዚ ቻናል ገብቶ ያንተን ሀሣብ በውስጥ ገብቶ በመስደብ ይወጣለታል። ቱ!
ይቺን ጢንጥየ ሃሳብ በሀሣብ መሞገት ያቃተው ነገ ቀበሌ ገብቶ የሠራውን ማህበረሰብ እየተነፈሠ የህይወት አዙሪቱን ይቀጥላል።
ሰው ቻናሉ ላይ የፈለገውን ካላሰበ ነገ እሡ በሚመራው ድርጅትማ አስቡት። እምነት በሀሣብ መተቸት መብት ነው እኔ ባልሳደብም። ግን ደላቹን እምነቱን ብሠድብበት ቀጥታ መርዝ ይበጠብጣል።
ኧረ ሼም ነው! የማይመቸኝ ነገር ካለ አልተመቸኝም እላለሁ እንጅ እንዴት "እኔን ካልሆንክ " ብየ አስባለሁ።
አንድ ድፍረት ልጨምር እዚ የእኔን ሀሣብ መዋጥ ያቃተው ነገ አይደለም ከመሰረተው ቤተሠብ ከራሡም ሀሣብ ጋ ይጣላል ከዛ ገመድ ይሠቅላል። ም/ቱም ሠው ከራሡም ጋ አንዳንዴ በሀሣብ ተቃርኖ ውስጥ መግባት አለበት ከዛም አንዱን ሃሳብ ማስተናገድ አለበታ።
ብቻየን የጠራሁት የተቃውሞ ሰልፍ።
በነገራችሁ ላይ እዚ ቤት እጅግ የሚገርሙ smart ሠወችን አጊቸበታለሁ!!


ሸጋ ሸጊቱ ምሽት!!!!

@balmbaras
@wegoch
@wegoch
የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ወጣቶች – (ቄሮ ፡- ተስፋና ስጋቱ፣ ፈውስና ሕመሙ) –
/እንዳለጌታ ከበደ/
...................................ክፍል አንድ ................
እንደ መንደርደርያ
ወጣትነት የልማትና የጥፋት ፍሬ የሚበቅልበት ዛፍ ነው፡፡ ለፍሬው መምረርና መጣፈጥ ዛፉ
የተተከለበት ቦታ፣ ዛፉን የሚንከባከቡት ግለሰቦች ችሎታና ፍሬው የሚለቀምበት ጊዜ
ይወስነዋል፡፡ፍሬውን ለመልቀም ማኅበረሰቡ ድንጋዩን ሽቅብ ሊወረውር ወይም ወቅቱ ደርሶ
እስኪረግፍ ሊጠብቅ ወይም ዛፉ ላይ ወጥቶ ፍሬውን የራሱ ሊያደርግ ወይም ሌላ መላ
ሊዘይድ ይችላል፡፡ ይህ የትም ያለ ነው፡፡ ዛሬ አልተጀመረም፡፡ ዛሬም አይቋጭም፡፡
ወጣትነት ለማዘዝ እንጂ ለመታዘዝ ዝግጁ የማይኮንበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡ እንደ ፍም
መጋል፣ መንበልበል፣ ጉልበተኛነት፣ አለመንበርከክ፣ ተራማጅነት፣ ለራስ ህልውና ቀናዒ
መሆንና የለውጥን ፍሬ ለማጣጣም መቸኮል የዕድሜ ክልሉ መገለጫ ነው፡፡
ለዚህም ነው፣ በወጣትነት ዕድሜ የተለኮሰ እሳት ፍሙ በቀላሉ የማይበርደው፡፡ ተስፋና
ስጋቱ፣ ሕመሙና ፈውሱ ተላላፊ ነው፡፡ ደስታውም ሀዘኑም በቀላሉ ይዛመታል፤ ይጋባልም፡፡
(‹THE ROOTS OF AFRIICAN CONFLICTS› የተሰኘው በ Alfred Nhema እና በ
Paul Tiyambe Zeleza የተሰናዳው መጽሐፍ፤ ይህንኑ ድምዳሜ አጽንዖት ሰጥቶ
ይተነትነዋል፡፡)

ወጣት አማጺዎች በኢትዮጵያ
..
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የወጣትነት አኗኗር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከሰመ፣ እየዳመነና
እየተቀየጠ መጣ እንጂ በአብዛኛው ‹ተቋማዊ› የሚመስል ነገር ነበረው ብዬ አምናለሁ፡፡
አሁንም አብዛኛው የገጠር ማኅበረሰብ ትውልዱን የሚኮተኩትበት፣ የሚያንጽበትና
የሚያድንበት መንገድ አለው፡፡
የሴቶቹን ለጊዜው እናቆየውና፣ ወንዱ ቤተሰብ ከመመስረቱ በፊት የሚጠበቅበት፣
የሚፈተንበት፣ ሙሉ ሰው ለመሆን መቃረቡን የሚያሳውጅበትና ሊሻገረው የሚገባ ድልድይ
(Rites of passage እንዲሉ ፎክሎሪስቶች) አለው፡፡ ድልድዩ ተወደደም ተጠላ
መመዘኛው ነው፡፡
በሀገራችን፣ ወጣቱን ጋሻ አድርጎ፣ በተናጠልም ሆነ በቡድን፣ ባህላዊ በሆነ መልኩ፣ የራስን
መብት ማስከበርና ሕዝባዊ ተቃውሞ ማሰማት የተለመደ ነው፡፡
እንደ ብርሃንና ጨለማ፣ እየተፈራረቁ፣ በገዢነት ስሜት ሌላውን ማፈናቀል፣ እየተፈራረቁ
በዘርና በሃይማኖት እየወገኑ የማይመስላቸውን መበደል፣ እየተፈራረቁ ሌላውን እንደ ወገን
አልባ ቆጥሮ ማስቆጠር፣ ትናንትም ዛሬም ያለ ልማድ ነው፡፡
ከሰማንያ ዘጠና ዓመት በፊት በተደረገው ‹የአማጺዎች› መንገድና አሁን እየተደረገ ባለው
ተቃውሞ መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ ነው። ልዩነቱ የትናንቶቹ ማኅበራዊ ሚዲያውን
ለቅስቀሳና መገናኛ አይጠቀሙበትም፡፡
መቀጣጠርያቸው፣ መፎከርያና መሸፈቻ ሜዳቸው ጫካው፣ ዱርና ገደሉ ነበር፡፡
ልጃገረዶችም፣ ለጎበዝ አራሽ ከዘፈኑት ይልቅ አውሬ አድኖ፣ጠላት ገድሎ፣ ንብረቱን አደርጅቶ
ለተመለሰው ጉብል አሞካሽተው የዘፈኑት ይበዛል፡፡
ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ፣ ‹ካየሁት ከማስታውሰው› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ፣
በየጊዜው ይነሳ ስለነበረ አመጽና ሁከት እና ሁከቱን ለማስወገድ ስለተሄደባቸው መንገዶች
በብዛት ጽፈዋል፡፡
ለአብነት ያህል አንዱን ብናነሳ፣ ‹‹በዚያም ወራት ባዲስ አበባ ሰሜን ያለ አገር ራያ፣ አዘቦ፣
ዋጅራት የራስ ጉግሳ አርአያ የክፍል ግዛት አገር እራሱ አለቃ እያበጀ፣ አንድነት እየሆነ
እየዘመተ፣ የወሎን ክፍል የአፋሩን አገር ግዛትና ከደጋውም ወረባቦ የሚባለውን የኦሮሞውን
አገር ጭምር እየወረረ፣ ሰውን እየገደለና እየሰለበ፣ ከብቱን እየዘረፈ ይወስድ ነበር፡፡ (ገጽ
143)›› ይላሉ፡፡
በ1919 ዓ.ም ደግሞ፣ ‹ወያኔ› ተብለው የሚጠሩ ወጣቶች ደሴን አምሰዋት እንደነበር
‹ብርሃንና ሰላም› ጋዜጣ ጽፎ ነበር፡፡ እነዚህ ወያኔዎች ‹ያባቶቻችን ልማድ ነው!› እያሉ በረባ
ባልረባ ነገር ንብረታቸውን የሚያጡ፣ በጦር የሚገዳደሉ ነበሩ፡፡ ይህን የታዘበ የጋዜጣው
ወዳጅ፣ ቅሬታውን ጽፎ ሲጨርስ፣ ‹‹እኝህን የመሰሉ ለደህና ቀን የሚሆኑ ልጆች ባልረባ
በትንሽ ነገር እየተበላሹ መቅረታቸውን ተረዳሁት፡፡
ይህ ሁሉ መደረጉ የትምሕርት ማነስና መንግሥት አገሩን እየሰጣቸው የሚገዙ ሰዎች
ለዕለቱ ከማሰባቸው በተቀር ለተወለዱባት አገራቸው ለመልካሚቱ ኢትዮጵያ ከሕይወታቸው
የተረፈውን ባያስቡላት ይመስላል››
ወጣትነት ያኔም አሁንም ለለውጥ ብቻ ሳይሆን ለነውጥም የቀረበ ትጋት የሚስተዋልበት
የዕድሜ ክልል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ወጣት፣ በወጣትነት ዕድሜው እንደ ጭልፊት ነጥቆ
የሚበላበት፣ እንደ አንበሳ ጉልበቱን በሌሎች ብቻ ሳይሆን በራሱ ጎሳ ላይም ጭምር
እንዲያሳይ የሚጋበዝበት፣(የሮናልድ ሌቪን Greater Ethiopia የተሠኘውን መጽሐፍ ልብ
ይሏል)፣ ኅብረተሰቡን የሚፈትን መከራ ሲመጣ ቀዳሚ ሆኖ እንዲጋፈጥ የሚጠበቅበትና
ይህን በመሰለ ተጋድሎ ራሱን ለማስተዋወቅ አሻራውን እንዲያሳይ የሚበረታታበት ነው፡፡
አንዳንዴ ወጣቶቹ ከሚጠበቅባቸው በላይ ሲጓዙ፣ አንዳንዴ ደግሞ የሚፈትናቸው ነገር
ጠፍቶ፣ የሌለ ጦርነት ያውጃሉ። ‹ጦር አውርድ› ብለው ይማጸናሉ፡፡በአብዛኛው ኢትዮጵያ
ባሕል ውስጥ፣ወጣቱ ‹እራሱ አለቃ እያበጀ፣ አንድነት እየሆነ፣ እየዘመተ… ሰው እየገደለ፣
ከብት እየዘረፈ› ሕይወቱን ይመራል፡፡

ቄሮ/Qeerroo እና መሰሎቻቸው
.....
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ፣ የምስጋናው የበኩር
ተቋዳሽ ወጣቱ ብቻ (ብቻ የሚለው ቃል ይሰመርበት) እየሆነ ነው።የለውጡ ጀማሪዎችም
ፈጻሚዎችም ቄሮዎች፣ ፋኖዎችና ዘርማዎች ናቸው እየተባለ ነው፡፡ይህ አገላለጽ፣ በሌሎች
ሕዝቦች መሐል ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ክፉኛ ‹መገለልና መድልዎ› እየደረሰባቸውና
አንዳችም ዋጋ እንዳልከፈሉ የሚያስቆጥር ነው፡፡
ቄሮ፣ ፋኖና ዘርማ – ሦስቱም – ዘራቸውን/ ብሔራቸውን ከሚደርስበት ጥቃት ለመከላከል፣
ከመከላከልም ወደ ማጥቃት ለመሸጋጋር ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ ወይም ውክልናውን
ለራሳቸው የሰጡ የመብት ተሟጋቾች ናቸው፡፡ ሲሆን እንዳየነው፣ ጥብቅናቸው ለወጡበት
ብሔር ብቻ ነው፡፡አልፎ አልፎ፣ እጅግ በጣም አልፎ አልፎ፣ የሌላውን ብሔር ስም
እየጠቀሱ አጋርነታቸውን ለማሳየት ሲሞክሩ እንጂ፣ ተከታታይነት ያለው ሕብረት ሲፈጥሩ፣
በአንድ ቃል ሲናገሩ በአንድ ልብ ሲመክሩ አይታዩም።በጩኸታቸው ውስጥ ‹የጋራ ቤታችን›
የሆነችው ኢትዮጵያን የማያት በጨረፍታ ነው፡፡ በ1960ዎቹ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ፣
‹ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ፣ እንደነሆቺሚኒ እንደቼጎቬራ› ተብሎ ይዘመር ነበረ፡፡መዝሙሩ
ብሔራዊ ስሜትን እንዲቀሰቅስ የጥሪ ደወላቸውን የሚያስደምጡ ወጣቶች ተሳትፎ
ያደርጉበት ነበር እንጂ፣ ‹አማራነትን› መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ አልነበረም፡፡
እርግጥ ስለ ቄሮም ሆነ ስለ ለፋኖ እንዲሁም ስለ ዘርማ በቂ ዕውቀት – ማለትም
ሃሳባቸውንና አደረጃጀታቸውን ለማቀፍም ሆነ ለመንቀፍ የሚያስችል፣ ለመውደድም ሆነ
ለመጥላት የሚያበቃ በቂ ዕውቀት – የለኝም፡፡ አንድ ነገር ግን መመስከር እችላለሁ፡፡
ሦስቱም ሕብረት አፍቃሪዎች ናቸው።መሰረታቸው ባሕላቸው ነው፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ አንድ
አባባል አለ – ‹ትናናሽ ናቸው ተብለው የሚናቁት ጉንዳኖች እንኳን በሰልፍ ሆነው ተቧድነው
ሲመጡ አንበሳ ይፈራቸዋል፡፡› የሚል፡፡‹ድር ቢያብር አንበሳን ያስር› እንደ ማለት፡፡ የወጣቶቹ
ድምጽና ጩኸት የኢያሪኮን ግንብ ማፍረስ የሚችል ይመስላል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ቄሮ ማለት ወጣት ነው። ያላገባ፣ ሌጣውን የሆነ፡፡ ቄሮ ቤተሰቡን
ተጠግቶ የሚኖር
፣ የሚፈነቅለው ድንጋይ እንዲበዛ የሚኳትን፣ ቢያንስ ቢያንስ በአካባቢው
ዘንድ ተከባሪና ተፈሪ ለመሆን ከመሰሎቹ ልቆ ለመታየት ዝግጁ የሚሆን ነው፡፡ማደጉን፣
ለለውጥ መዘጋጀቱን፣ ለትዳር መድረሱን፣ በራሱ እግር ለመቆም መወሰኑን
የሚያስታውቅበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡(ይቀጥላል)
….
(አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ መስከረም 12/2011 ታትሞ የወጣ)

@balmbaras
@wegoch
@wegoch
የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ወጣቶች – (ቄሮ ፡- ተስፋና ስጋቱ፣ ፈውስና ሕመሙ) –
/እንዳለጌታ ከበደ/
እንደ መንደርደርያ
…..ክፍል ሁለት….
እንደሚታወቀው፣ ቄሮ ማለት ወጣት ነው። ያላገባ፣ ሌጣውን የሆነ፡፡ ቄሮ ቤተሰቡን
ተጠግቶ የሚኖር፣ የሚፈነቅለው ድንጋይ እንዲበዛ የሚኳትን፣ ቢያንስ ቢያንስ በአካባቢው
ዘንድ ተከባሪና ተፈሪ ለመሆን ከመሰሎቹ ልቆ ለመታየት ዝግጁ የሚሆን ነው፡፡ማደጉን፣
ለለውጥ መዘጋጀቱን፣ ለትዳር መድረሱን፣ በራሱ እግር ለመቆም መወሰኑን
የሚያስታውቅበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡
እንዳነበብኩት፤ በአርአያነቱ ሊጠቀስ ይገባዋል በሚባለው፣ በገዳ ሥርዓት ውስጥ፣
በዕድሜ ተገድበው የተቀመጡ አስር እርከኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ እርከኖች መካከል አንዱ –
ሶስተኛው -‹ደበሌ› ይባላል፡፡ደበሌ ዕድሜያቸው ከ17-24 ዓመት ያሉ ወጣቶች ሲሆኑ፣
በኦሮሞ ባህል፣በዚህ እርከን ውስጥ ያለ ወጣት፣ ስለ ባህሉ፣ ስለ አንድነቱ፣ ስለ ነጻነትና
ስለ መብቱ ሲቆረቆር ይታያል፡፡ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ላይም ጉዳት እንዳይደርስ
የሚሟገትበት ዕድሜ ነው፡፡
በሕዝቡ ላይ ችግር ሲደርስ ቀድሞ ቅሬታውን ማሰማት፣ ደስታ ሲሆንለትም በእልልታና
ጭብጨባ ስሜቱን ማስተናገድ ይጠበቅበታል፡፡ የሕዝቡ የልብ ትርታ የሚደመጠውም
በደበሌ አንደበት ነው ይባላል፡፡በእኔ መረዳት፣ ደበሌና ቄሮ የሚመሳሰል ነገር አላቸው፡፡
በእርግጥ ቄሮ ወንዶችን እንጂ ሴቶችን አያካትትም፡፡
ስለ ቄሮ ሳስብ ቅርም ግርምም የሚለኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካው
መድረክ ላይ የምናያቸው ስመ-ጥር አክቲቪስቶች፣ ቄሮን አወድሰው አይጠግቡም፡፡የእኔ
ጥያቄ፣ ቄሮ የማን ነው? ራሱን የቻለ ነው? ወይስ በአንድ ግለሰብ ወይም ፓርቲ የሚመራ
ቡድን? በኦሮሞ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ሁሉም ማለት ይቻላል፤
‹ቄሮ የእኛ ነው!› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ኦህዴድም፣ ኦፌኮም፣ ኦነግም፣ ጃዋር መሃመድም፣ ሌላ
ሌላውም የእኔ ናቸው ይላሉ። ‹እኛ ነን ለነውጥ ያሰማራናቸው፤ ላመጡት ለውጥ ሹመቱም
ሽልማቱም ይገባናል› ይላሉ፡፡እነ ዶክተር መራራ ጉዲናም፤ ‹ቄሮን አንቅተን መንገዱን
አሳይተን፣ እዚህ ያደረስነው እኛ ነን› ብለዋል፡፡በዚህች በ‹አዲስ አድማስ› ጋዜጣ እንኳን
ስንቶቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ፖለቲከኞች ናቸው፣ ለቃለ መጠይቅ ተጋብዘው፣ (በዓላማም
ሆነ በሌላ ሌላው ፈጽሞ የማይገናኙ) ቄሮን የልብ ወዳጃቸውና የቁርጥ ቀን ልጃቸው
አድርገው በስሙ ያጌጡት? በስሙ የማሉት? ይሄ ግርታዬ ነው፡፡
እንደኔ እምነት ቄሮ ፈረስ አይደለም፣ ሁሉም እየመጣ የሚጋልብበት፡፡ የራሱ አደረጃጀት
ያለው፣ ፍትህ ግድ ከሚሰጠው ሕዝብ አብራክ የተከፈለ ነው።የሚታገለው፣ የወጣትነት
ዕድሜውን የሚገብረው፣ የራሱን ብሔር ነጻነት ለማስከበር ብቻ ነው የሚል እምነትም
የለኝም፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ አቃፊ ነው፤ ከአብራኩ ያልተከፈለውን ልጅ እንደ ራሱ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣
የሌላውን ማኅበረሰብ ሃሳብ መቀበል የሚችል፣ ሕመሙንም ለመታመምና ጩኸቱን
ለማሰማት ዝግጁ የሆነ ነው፡፡የፖለቲካ ድርጅቶቹና አክቲቪስቶቹ ግን ሃሳባቸውን በብርሃን
ፍጥነት መለዋወጥና ለአንድ ብሄር ብቻ ማጋደል፣ እንደ ‹ፖለቲካ ስትራቴጂ› የሚቆጥሩ
ናቸው፡፡
ቄሮና መሰሎቻቸው አስተዋጽኦ ያደረጉበትን ስለ ወቅታዊው ለውጥ ስናነሳ፣ወጣቶቹ
የመብት ተሟጋቾች አድርገውታል፤ እያደረጉትም ነው ከሚለው እንቅስቃሴ ጋር በቀጥታም
ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ ግንኙነት ያለው አንድ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ጉዳዩ ቅድም መጠቀሚያ
የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ ብዬ ካስነበብኩት ጋር ግንኙነት አለው፡፡ የቅሬታዬም መነሻ ነው፡፡
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ፣ ‹ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 1922-1927› በሚለው
መጽሐፋቸው (ገጽ 134-136)፤ ራስ ኃይሉ በመንግስት ላይ አሲረዋል ተብለው ተሽረው፣
ራስ እምሩ የጎጃም አስተዳዳሪ ተደርገው በተሾሙበት ዘመን ስለተፈጸመ ሽብር
የሚተርኩልን አላቸው፡፡
ራስ እምሩ የጎጃም አገረ ገዥ ከሆኑ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወደ አውሮጳ አቀኑ፡፡ ከንቲባ
ማተቤ ተጠባባቂ ሆነውም ጎጃምን ማስተዳደር ሲጀምሩም የሚከተለው ሁነት ተፈጸመ
ይላል መጽሐፉ፡፡‹…በዚህ ጊዜም የራስ እምሩ እንደራሴ ቀኛዝማች ወልደየስና የጦር
አለቃው ቀኛዝማች ደምሴ በዛብህ የቤት አሽከሮችንና የቁጥር ወታደሮችን ይዘው
በዳውንት ላይ ተጓዙና ወደ ጎጃም ተሻግረው በሐምሌ ወር ደብረ ማርቆስ ገቡ፡፡
የራስ ኃይሉ ልጅ ፊታውራሪ አድማሱም ከአቸፈር መጥቶ በሐምሌ ወር ደብረማርቆስ ገባ፡፡
ይህ ሰው በአባቱ መታሰር የተከፋ መሆኑን ለመግለጽ ከል የገባ የሀዘን ልብስ ለብሶ ይታይ
ነበር፡፡ በከንቲባ ማተቤም ላይ አምባጓሮ ለማንሳትና የአባቱን ግምጃ ቤት ለማስዘረፍ፣
ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ተመካክሮ ሲሰናዳ ከረመ፡፡ ከተዘጋጀም በኋላም፣ በመስከረም 20
ቀን 1925 ዓ.ም ዓርብ ጧት ከንቲባ ማተቤ ወዳሉበት ግቢ በስተጀርባ መጥቶ ተኩስ ከፍቶ
ውጊያ ጀመሩ፡፡
ሕዝቡም ለዘረፋው ተባባሪ ሆኖ አብሮት ተሰለፈ፡፡… ከእኩለ ቀን በኋላ ፊታውራሪ አድማሱ
በአንድ ወገን ጥሶ ወደ ግቢው ገባና ከፎቅ ላይ ወጥቶ የመትረየስ ተኩስ ከፈተ፡፡በዚህ ጊዜ
ለዘረፋ የተሰበሰበው ሕዝብ ግምጃ ቤቱን ሰብሮ ገንዘቡንና ልብሱን፣ ዕቃውንና መሳርያውን
ይዘርፍ ጀመረ፡፡ ይህ ዘረፋ የብዙዎቹን ሕይወት ለማስጠፋት ምክንያት ሆነ።አንዱ ዘርፎ
ተሸክሞ ሲሄድ፣ ሌላው ጠብቆ እየገደለ ይወስድበት ነበርና፣ በአንድ ዕቃ እስከ አስር ወይም
እስከ አስራ አምስት ሰው የተገደለበት ብዙ ሰው ነበር። ዕቃውን የሚወስደውም
የመጨረሻው ዘራፊ ብቻ ነበር፡፡በግምጃ ቤት ተከማችቶ የነበረውንም አረቄ ዘራፊው ያለ
ግምት ስለጠጣው ሁሉም ደፋርና ጨካኝ ሆኖ ዋለ፡፡… በዚያ አምቧጓሮና በዘረፋው
ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 300 ሲሆን፣ የቆሰሉትም ከሺህ በላይ መሆናቸው ተነገረ››
በዚህ ተረክ ውስጥ አጋጣሚውን ይጠባበቁ የነበሩ፣ ላንዳፍታ ‹ወሳኙ ሰው› ገለል
እስኪልላቸው ሲያደቡ የነበሩ፣ ሌሎች የጫሩትን እሳት መሰረት አድርገው ደግሞ “አባቴ/
አባት ፓርቲዬ ተበድሏል” በሚል ሰበብ፣ በመንግሥት ላይ ሁከት ለማስነሳት ከፍተኛ ምኞት
ያደረባቸው ነበሩ፡፡
በተፈጠረው ግርግር ጣልቃ ገብተው፣ በዘረፋው ራሳቸውን ለማበልጸግ የሚቋምጡ
ወመኔዎችም ነበሩ፡፡ እልቂቱን ከፍ ያደረገውም ይሄ ነው፡፡ ዛሬም ያለው ሁኔታ ይኸው ነው፡፡
ተሸናፊው ‹ባልበላውም ጭሬ ልበትነው!› ማለቱ አይቀሬ ነው። የራስ ኃይሉ ልጅ፣ አባቱ
ከስልጣን ተሽሮ በመታሰሩ አዝኖ አመጽ በመቀስቀስ፣ ለአማጺዎች ስንቅ በመስፈር፣ ጥይት
በማቀበል እንደተጠመደው ሁሉ፣ አሁንም ‹የበፊቱን› ኢሕአዴግ የሚመርጡ፣ በራሳቸው
ቋንቋ ልጠቀምና፣ ‹ያለፈው ሥርዓት ናፋቂዎች› አሉ፡፡ወጣቱ የራሱን መዝሙር ለማሰማት
ወደ አደባባይ ሲወጣ ‹ያለፈው ሥርዓት ናፋቂዎች› ሰልፉን ተቀላቅለው፣ የራሳቸውን
አዝማች ደበላልቀው ሲያሰሙ መስማት አይቀሬ ነው፡፡
….
አሁን ምን መደረግ አለበት?
ለውጡም፣ ለውጡን ተከትሎ የመጣው ነውጥም በደስታና ሀዘን ካፊያ ብቻ ሳይሆን
በወጀብና ውሽንፍር የተሞላ ነው፡፡
‹ለውጥ መጣ እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ይህን ልኖረው ምኞቴ ነበረ› ብሎ የዘፈነውም፣ ‹እረኛ
አልባ ሆነን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ልንጠፋ ነው!› ብሎ አንጎራጓሪውም አየሩንና
ሚዲያውን ተቆጣጥሮታል፡፡የምሥራቹም መርዶውም በፍጥነት እየተደመጡ ነው፡፡ እንዲህ
ባለ ‹የሽግግር ጊዜ› የሚጠበቅ ሁከት ቢኖርም፣ አሁን እየሆነ ያለውና እየሆነ ባለው ነገር
ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም።በምክር ብዛት፣ በመፈክር
ብዛት፣ በማባበል ብዛት
ሕግ አይጸናም፡፡ የመንግሥት ጥንካሬ የሚለካው አንዱ አካል
እንዲናገር ብቻ ሳይሆን ከሚመለከተው አካል ጋር እንዲነጋገር በማድረጉ፣በጽኑ አቋሙና
በፈጥኖ ደራሽነቱም ጭምር ነው፡፡
የሆነው ሆኖ፣‹መግደል መሸነፍ ነው› ስለተባለ ለውጥ አይመጣም፡፡ ‹መግደል መሸነፍ
ነው!› የሚለው አባባል፣ ‹እዚህ አካባቢ መሽናት በሕግ ያስቀጣል› ከሚለውና በየግንቡ
ላይ ከሚጻፈው ማስጠንቀቂያ እኩል እየሆነ ነው፡፡ መግደሉም በየግንቡ ስር መሽናቱም
እየቀጠለ ነው፡፡
ግንብ ስር ሲሸና ተገኝቶ ለሕግ የቀረበ ሰው አላውቅም፡፡ የማስጠንቀቂያው መጻፍ ቦታውን
ጽዱ አላደረገውም፡፡ ልክ ‹መግደል መሸነፍ ነው!› የሚለው አባባል፣ ገዳዮቹን፣ ‹እውነት እኮ
ነው!› አሰኝቶ አደብ እንዳላስገዛቸው ሁሉ።እርምጃ መወሰድ አለበት። ከእርምጃው በፊት
ግን፣ ወጣቶቹ ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ እንዲናገሩ፣ ከመንግሥት ሹማምንት ጋር
እንዲወያዩበት፣ ወደ መፍትሄ በሚወስደው መንገድ በጋራ ሲጓዙ ማየት ቢቀድም ይበጃል፡፡
አለመነጋገር ነው ችግራችን፡፡
እንደኔ እምነት፣ ለወጣቱ እየተሰጠው ያለው ክብር አለቅጥ በዝቷል፡፡ አሁን ያለው ለውጥ፣
በባለፉት ሦስት አራት ዓመታት ጊዜያት በተነሳ ተቃውሞ ብቻ የመጣ ለውጥ ተደርጎ
መቆጠሩ ተገቢ አይደለም።የብዙ ንብርብር፣ የብዙ ድምር ውጤት ነው፡፡ የሃያ ሰባት
ዓመታት ልቅሶ፣ ሙግት፣ እንግልትም ጭምር እንጂ፡፡ ለውጡ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ነው፡፡
ስንቱ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ታስሮአል? ተሰዷል? ስንቱ ተንከራቷል? ስንቱ ሀገሬን
ኢትዮጵያን ብሎ በመዝፈኑ ነቀፌታን አስተናግዷል? አሁን ያለው ወጣት በመጨረሻው ሰዓት
ዱላው እጁ ላይ ተይዞ ስለተገኘ፣ በዚህም የተነሳ ዋጋ በመክፈሉ ብቻ፣ በፍጥነት ሮጦም
ሪቫኑን ስለበጠሰው፣ ‹ብቸኛ አሸናፊ እሱ ነው› ማለት አይደለም፡፡
እነ ቄሮን በየሕዝባዊ ሰልፉ፣ በየዘፈኑ፣ በየጋዜጣዊ መግለጫው መሃል ማመስገን፣ ረዘም
ያለ ጭብጨባ እንዲጎርፍለት ማድረግ፣ ፖለቲከኞቹ ካለፉት አምስት ስድስት ወራት ጀምሮ
የተጠመዱበት ሆኗል፡፡መመስገናቸው ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ
ተደርገው መቆጠራቸው ደግሞ አግባብ አይደለም፡፡ለምሳሌ፣ አክቲቪስቱ ጃዋር በአንድ
ቃለ መጠይቁ ውስጥ ሁለት ዓይነት መንግሥት አለ ብሎ፣ አንደኛውን መንግሥት ቄሮ
አድርጎ ሲቆጥረው መስማት ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ ቄሮ አዲስ አበባን መቆጣጠር
እንደሚችል የተናገረውን መስማትና የተነገረበት ድምጸት ፈጽሞ ሊያሳምነኝና ልወድለት
አልቻልኩም፡፡ጃዋር፣ በሻሸመኔ ከተማ በግፍ ስለተገደለው ወጣት ሲጠየቅ፣ ድርጊቱን
የፈጸሙት ቄሮዎች እንዳልሆኑና ማን እንዳደረገው እንደሚያውቅም ጭምር ተናግሯል፡፡ ግን
በወቅቱ እስፍራው የነበሩ፣ በእሱ አቀባበል ላይ ተሳታፊ የነበሩ ቄሮዎች፣ ግድያውን በዝምታ
– የቃና ቴሌቪዥን ድራማዎችን እንደምትመለከት ሴት በተመስጦ – ለመከታተል
መፍቀዳቸው፣ የኦሮሞ ባህል እንዳልሆነ ተናግሮ፣ ድርጊቱን ሲኮንነው ብሰማ አክብሮቴ ከፍ
ይል ነበረ፡፡
ሲባል እንደምንሰማው፣የቄሮ መነሻና መድረሻ ግድ ሳይሰጣቸው የተቀላቀሏቸው አሉ፡፡
‹አንዲት የሞተች ዝንብ ባጥሩ መዓዛውን ሽቶውን ሁሉ ታገማዋለች› እንዲሉ፣ ሽቶው
እንዳይከረፋ፣ዝንቦችን ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ሽቶው ለገዛ ውብ ጠረኑ ሲል፣ ራሱን ከሟች
ዝንቦች ይጠብቅ፡፡ አንድ አለቦታው ትግሉን የተቀላቀለ ወጣት፣በገንዘብ ተደልሎም ይሁን
በራሱ ተነሳሽነት ተቀላቅሎ ገብቶ፣ እንቅስቃሴውን ሊያዳምነው ይችላል፡፡ታናናሾቻቸውም
እያዩአቸው ነው፡፡ እናም ሊኮረጅ የሚገባቸው ሰናያት ተግባራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሳጠቃልለው፣ የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ለመብታቸው ያላቸውን ቀናኢ ስሜት
እያደነቅሁ፣ ይህ ቀናኢ ስሜታቸው በብሔራዊ ደረጃ እንዲያድግ እየተመኘሁ፣ አንዳንዶቹ
ደግሞ ከከንቱ ሆይ ሆይታ፣ ወይም ከባዶ ድንፋታ፣ ወይም ከአጉል ጀብደኝነት ተላቅቀው፣
በዕውቀት ለመጎልመስ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው መጠቆምም እፈልጋለሁ፡፡
ወጣቶቹ ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ባለ ሥራ እንዲሆኑ፣ ‹በትምህርት ማነስ› ምክንያት ከላይ
እንዳነሳናቸው ‹ወያኔዎች› ሀገራቸውን እንዳያጨልሙ፣ የወጡበትን ማኅበረሰብ አንገት
እንዳያስደፉ፣ ከማን ጋር ምን መምከር እንዳለባቸው መንገድ መጠቆም የታላላቆቻቸው
ፈንታም ጭምር ነው፡፡ይህ የመቧደን እንቅስቃሴ፣ አፍርቶና ጎምርቶ ለተጠቃ ሲደርሱ፣
የጎበጠውን ሲያቀኑ፣በዳዩን ወደ ፍርድ ተቋማት ሲያስረክቡ መታየት
አለባቸው፡፡‹ለመልካሚቱ ኢትዮጵያ› አርአያ መሆን የሚገባውን ሥራ በሚሰሩበት ዕድሜ፣
የአንድ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሠራተኛ ከመሆን እንዲታቀቡ ምክርም ተግሳጽም
ሊለገሳቸው ይገባል፡፡
....
(አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ መስከረም 12/2011 ታትሞ የወጣ)


@balmbaras
@wegoch
@wegoch
2024/09/29 19:27:55
Back to Top
HTML Embed Code: