Telegram Web Link
ለቅዳሚታችሁ
💚💚💚💚

በፈጣሪ ብርሀን ፍቅር አገኜሁ


☞ ሱፊዝም
የሰው ልጅ በመውደቁ ምክንያት ተስፋ መቁረጥ የሚገጥመው አስቀድሞ በእምነቱ ሳይሆን
በሥራው በመመካቱ ነው እናም ለአእምሮህ ማስተዋልን ለልብህ ደግሞ ፅናትንና ርኅራኄን
መግበው።
ሕይወትን አቅልለህ ስትመለከታት የምትሰጥህ ትርጉም እጅግ ሙሉ ይሆናል፣ ከዓለም
የምትሻው እንዲሁ ጥቂት ሲሆን ከፈጣሪህ የምትካፈለው ደግሞ እጅግ ብዙ መሆን
ይጀምራል። ይሉናል ሱፊዎች ሱፊዝም እስልምና ሀይማኖት የወለደው መንፈሳዊ ተመስጥኦ
ነው።


የእምነቱ አራማጆችም እስላማዊ ተሰጥኦ ነው ይሉታል።
ምንም እንኳን ሱፊዝም መሰረቱ እስልምና ይሁን እንጂ የእምነቱ መሪዎች ወደ ህንድ ሂደው
የሂንዱዝም እምነት በስፋት የወሰዱትና የተቀበሉት እንዳለ ይታመናል


ሱፊዎች ስለ እምነት ሲናገሩ "እምነት ሲናገሩት ቀላል ለማድረግ ግን እጅግ የከበደ ነው "
ይላሉ አንዳንዴ እምነታችን ከእግዚአብሄር በቀር በቀረው ነገር ላይ ሁሉ የምናደርግበት ጊዜ
አለ። በፍርድቤት ስንከሰስ ወይም ስንከስ እምነታችን ሁሉ በጠበቃችን ላይ ይሆናል፤
እንዲሁም ስንታመም ደግሞ የእምነታችንን ታላቅነት በዶክተሮቻችን ላይ ይገለጣል፤
ገንዘባችን እንደሚያድነንና እንደሚጠብቀንም እንታመናለን፤ ዕውቀትና ጥበባችንን ደግሞ
ከችግር እንደምናወጣበት አምነን እንመካለን። እናም እምነታችን ሲመረመር የተመሰረተው
በተፈጠረው ነገር እንጂ በፈጣሪ ላይ አይደለም።


ሱፊዎች እምነትን፣ ፍቅርን ፣ ትዕግስትን፣ ደስታን፣ ተስፋን…አስመልክተው በተለያዩ ጣፋጭ
ወጎችና ትረካዎች ከሚማርኩኝ እንዱ ሩሚ ነው።


#ሩሚ

"መምህር ሆይ! ፍቅርን ፈልጎ ለማግኜት መንገዱን ይምሩኝ ይላቸዋል። ሩሚም "የአንተ
ድርሻ ፍቅርን መፈለግ አይደለም ነገር ግን ከእሱ ጋር እንዳትገናኝ ያገደህንና በልብህ
የገነባኸውን የጥላቻ ግንብ ማፍረስ ነው " ። ለሩሚ ፍቅር ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ
በመሆኑም ይህንን ስጦታ የምናገኝበት ቀላሉ መንገድ ሰጭውን አጥብቆ መፈለግ ነው።


ለዚህም ሩሚ ሲናገሩ፦ በፈጣሪ ብርሀን ፍቅር አገኜሁ፤ ከእሱም ውበት ቅኔን ተቀኜሁ፤
የሰው ልጅ ዓይኖች ሊያዩህ በማይቸሉት ልቤ ውስጥ ሆነህም ዘወትር አሸበሽባለሁ፤ እናም
አንዳንዴ በአንተ ታጅቤ ስወዛወዝ ሰዎች ይመለከታሉ ይህንን ደግሞ ጥበብ በማለት
ይጠሩታል


ሩሚ አንድ ወዳጃቸው ቤት ተጋብዘው እጅግ ደስ የሚል የፍቅር ታሪክ ሰምተው ሲጨርሱ
ጋባዣቸው፦ "ፍቅር በእርግጥም እውር ነው፤ ሰዎችን ባልጠበቁት ስፍራ ወስዶ
ያገናኛቸዋል" አለ።


ሱፊው ሩሚ አንድ ወዳጃቸው ቤት ተጋብዘው እጅግ ደስ የሚል የፍቅር ታሪክ ሰምተው
ሲጨርሱ ጋባዣቸው፦ "ፍቅር በእርግጥም እውር ነው፤ ሰዎችን ባልጠበቁት ስፍራ ወስዶ
ያገናኛቸዋል" አለ።


ሩሚ ግን እንዲህ በማለት አስተካከሉት፦ "ፍቅረኞች በመጨረሻ የሚገናኙበት ስፍራ
የሚባል ነገር የለም፤ አስቀድሞ አንዳቸው በሌላው ውስጥ ነበሩና "።


በመጨረሻም የምትገርመኝን አባባል ልጨምር


""የሰው ልጅ ሰይጣን ያስተማረዉን ያህል የትኛውም መልአክ አላስተማረዉም"

ሸጋ ሸጊቱ ቅዳሜ!!💚

@wegoch
@wegoch
@balmbaras
ለሰንበታችን
💚💚💚

ከነገሥታት አንዱ “ዘመን እንደምን አለች?” ብሎ ጠየቀና፥ ዘመን ማለት አንተ ነህ፥ አንተ
ሰላማዊ ስትሆን እሷም ሰላማዊ ትሆናለች፤ አንተ የከፋህ እንደሆነ ትከፋለች ብለው
መለሱለት፡፡


አንገረ ፈላስፋ

መልካም ሰንበት!💚

@wegoch
@wegoch
ለውብ ቀን
💚


አራት ዓይኖች አሉህ


እነርሱም...ግራ ዓይንህ..ቀኝ ዓይንህ..አዕምሮህና ልብህ ናቸው


አምስት እንዲሆኑልህ በሕሊና ሥራበት


ማህተመ ጋንዲ

ሸጋ ቀን!💚💚💚

@wegoch
@wegoch
_የማቼቴ መልዕክት ወደ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች_
(ኤልያስ ታረቀኝ)

ለጉረቤቱ ከፍተኛ ጥላቻ ያለው አንድ ገበሬ ነበር፡፡ ይሄ ገበሬ ዘወትር በጎረቤቱ እንደቀና ነው፡፡ ጎረቤቱ ሲደሰት፣ እሱ ያዝናል፤ ጎረቤቱ ሲያዝን፣ እሱ ይደሰታል!
እና ከእለታት አንድ ዕለት እግዚአብሔር/አላህ ከሰማይ ወርዶ እዚህ ቀናተኛ ስውዬ ቤት ይገባና እንዲህ ይለዋል "አንተ ገበሬ እንደምን አለህ!? እኔ የአለማት ሁሉ ፈጣሪ ጌታ ነኝ! ዛሬ ላንተ አንድ ነገር ላደርግልህ አስቢያለሁና የፈለከውን ጠይቀኝ ወዲያው እሰጥሃለሁ! ነገር ግን ላንተ ያደረኩልህን እጥፍ ደግሞ ለጎረቤትህ አደርጋለሁ" አለው፣ የመብረቅ ብልጭታ በሚመስል ጎርናና ድምጥ፡፡
...
ሰውዬው ታዲያ ማሰላሰል ያዘ! ብዙ አሰበ! አንድ ስልቻ ወርቅ ስጠኝ ቢል ያ ጎረቤቱ ደሞ ሁለት ስልቻ ወርቅ ሊያገኝ ነው፤ ይሄ ደሞ ለጎረቤቱ ካላው ጥላቻ የተነሳ የማይሆን ነገር ሆነበት፡፡ ይልቅስ ጎረቤቱን በምን አይነት መንገድ መጉዳት እንደሚችል አወጣ አወረደና በሚብረቅረቅ ብርሃን ዙሪያውን ተከቦ ፊቱ ለቆመው ፈጣሪ እንዲህ አለው፡
"አንድ ዓይኔን አጥፋልኝ"
ፈጣሪም ቃሉን ተቀብሎ አንድ ዓይኑን ሲያጠፋለት፣ የጎረቤትዮን ደግሞ ሁለቱንም ዓይኖቹን እውር አደረጋቸው፡፡
ይህ ቀናተኛ ገበሬም ባንድ ዓይኑ ሁለቱንም ዓይኖቹን ያጣውን ጎረቤቱን ባየ ጊዜ በጣም ተደሰተ፡፡

በየአከባቢያችን በጎረቤቶቻቸው ላይ ሸር የሚሸርቡ፣ ተንኮል የሚጠነስሱ፣ መተት የሚያሰሩ፣ በሌላው ሀዘን የሚደሰቱ፣ ሰውን ከመጉዳት ሌላ ጭንቅላታቸው የተሻለ ሀሳብ አስቦ የማያውቅ ክፉ ሰዎች ሞልቷል፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ደካማዎች ናቸው፡፡ አለምንም አስቀያሚና አደገኛ ስፍራ ያደረጓት እንደነዚህ አይነት ከይሲ ሰዎች ናቸው፡፡ በሰው ቁስል የሚደሰት አዕምሮ ያለው ሰው ከእንስሳ በምን ይሻላል? ይልቅ ከእንደዚህ አይነት ሰው መቶ እጅ እንስሳት ይሻላሉ! ምክኒያቱም አንድ እንስሳ የራሱ ወገን የሆነ ሌላ እንስሳ አይጎዳማ! ጅብ አስፈሪ እንስሳ ነው፡፡ ጨካኝም ነው፡፡ ነገር ግን ጅብ ጅብን አይገልም! ጎረምሳ ዝንጀሮ ታዳጊ ዝንጀሮቲን አይደፍርም! ሰው ነው የራሱን ዘር የሆነውን ሰው የሚገድል! ሰው ነው የ9 አመት ታዳጊ ህፃን አስገድዶ የሚደፍር! እባብ በጣም ትፈራላችሁ! እኔ ደግሞ ልንገራችሁ፤ አንዳንድ ሰው ግን ከእባብ የበለጠ መርዘኛ ነው! እባብ እባብን አይነድፍም፤ እባብ ካልነካኸው አይነካኽም! ሰው ግን ከእባብ የከፋ እንስሳ ነው! ማን ነበር 'የሰውን ልጅ ይበልጥ ባውቅኸው ቁጥር ውሻህን እየወደድከው ትመጣለህ' ያለው? ማንም ይበል፤ ብቻ ይሄ ሰው አልተሳሳትም!

ፈጣሪ ሰለሚወድህ/ሽ በጥበቡ ሰው አድርጎ አበጀህ/ሽ! ውሻ አድርጎ ሊፈጥርሽ ይችል ነበር፤ ዝንብ አድርጎ ሊፈጥርህ ይችል ነበር፤ አይጥ አድርጎ ሊሰራኝ ይችል ነበር፤ እሱን ግን ለኛ የተሻለውን ሰጠን፡ ሰው መሆን! ሰው መሆን ክቡር ነገር ነው! አብዛኛዎቻችን ግን ሰው መሆን የከበደን ይመስላል! ወይም ሰው የመሆን ትርጉሙ በቅጡ አልገባንም! ሰው መሆን አልተመቸንም መሰል እንስሳ ከመሆን አልፈን ምንነቱ ወዳልታወቀ ፍጡርነት እየተቀየርን ነው! (ኢቮልሽን

እናንተ ቆንጆዎች፣ በሚዲያ ዜና አዳምጣችሁ ታውቃላችሁ? ስንት ሰው ተፈናቀለ ሲባል ሰማችሁ? ህፃናቱ አያሳዝኑም ወይ ቤት አልባ ሆነው ሲቀሩ? አዛውንቱስ? ስንት ሰው ሞተ ሲባል አዳመጣችሁ? ስንት ቤተክርስቲያን፣ ስንት መስጅድ ተቃጠለ ሲባል ሰማችሁ? አደባባይ ላይ ምስኪን ሰርቶ አዳሪ ተዘቅዝቆ እንደ አረፋ በግ በቢላው ሲታረድ አላያችሁም ወይ? ሀናን ረሳቿት? ከአመታት በፊት ከትምህርት ቤት ስትወጣ ደደብ ጎረምሶች አስገድደው ደፍሯት ለሞት የበቃችው ያቺ ጨቅላ ልጅ እንኳ? የሀና እናት እንዴት ስቅስቅ ብለው እንዳለቀሱ እነዚያ ደፋሪዎች ያውቁ ይሆን? ባሏ ፊት ሰለደፈሯት ነፍሰጡር ሴትዮስ? ሰምታቿል አይደል? የባሏን መሸማቀቅና ሃፍረት ማን ነበር የተረዳለት? ይህን ሁሉ ግፍ ማን የፈፀመ ይመስላቿል? እባብ? ጅብ? ሼይጣን? በፍፁም አይደለም፤ እኔ ልንገራችሁ፤ ይሄ ሁሉ የሚፈፅመው በሰው ነው! እባብ ነፍሰጡር ሴትን ባሏ ፊት አየደፍርም! ጅብ ደካማ አዛውንት፣ ህፃናትን ከክልሌ ውጡ ብሎ አያባርርም! ሀናን ደፍሮ ለሞት ያበቃት ሴይጣን አይደለም! ማርያምን አይደለም! ይሄን ሁሉ የሚያደርገው ሰው ብቻ ነው! ልታፍሩ ይገባል! Shame on you!

እኔምላችሁ፣
ለሰው መልካም ማሰብ እየቻላችሁ ለምን ክፉ ትመኛላችሁ?
ለጎረቤቶቻችሁ ጥሩ አሳቢ መሆን እየቻላችሁ ለምንስ የጎን ውጋት ትሆንባቿላችሁ?
በፍቅር አብሮ መኖር እየቻላችሁ ለምን በጥላቻ ትገዳደላላችሁ?

በአፋችሁ ፣ በአለባበሳችሁ ሃይማኖት አለን ትላላችሁ፤ ነገር ግን በድርጊቶቻችሁ ከሃማኖቶቻችሁ አስተምዕሮት ተቃራኒ ስትሆኑ ትታያላችሁ!

እኔ ግን ዛሬ ልምከራችሁ:
ክፉ አታስቡ! ሸር አትሸርቡ! ተንኮል አትቀምሙ! መልካም ስሩ! እውነት አውሩ! ጥሩ አስቡ! በጎ በጎውን ተመኙ! በቃ ሰው መሆን እኮ እንዲህ መሆን ነው! ሌላ የለውም! ቀላል ነው!

በሉ አሁን ሰው እንሁን
ፈጣሪም በእኛ ደስ ይበለው

@wegoch
@wegoch
ለውብ ቀን
💚


እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት፡ አለው። ማታም ሆነ
ጥዋትም ሆነ፥ ማክሰኞም ሆነ ለውብም ማክሰኚት እንዲሆን እንዲህ አልን💓


👉🍂ሲታሰብ ከባድ ቢመስልም በአንድ ወቅት ውስጥህን ያቆሰሉትን ያቆሸሹትን
የጎዱህን የጣሉህን ሁሉ ተዋቸው።
አንተ ደስታህን ሊሰጥህ ስለሚችል ነገር ብቻ ላይ ትኩረትህን አድርግ።


ባሳዘኑህ ነገሮች ላይ ባተኮርክ ቁጥር አሁን ያለህን የደስታህን ጊዜ ታጣዋለህ። በቻልከው
መጠን አስተሳሰብህን ቋጥሮ ከያዘክ የሀሳብ እስር ቤት ራስህን በራስህ አውጣ።


ስለ ህመምህ ብቻ ካሰብክ ከፊትለፊትህ ያለውንንና እንዳትንቀሳቀስ ያደረገህን ግርግዳ
ራስህ በራስህ ታጠነክረዋለህ።


ከፊትህ ያለውን ግርግዳ ናቀውና እለፈው ትልቅነቱን ሳይሆን
የአንተን የአሁን የደስታህን ትልቅነት ብቻ አስብ።


ስላለፈው ሳይሆን ስለአሁኑ ስለቀረው ሳይሆን ስለመጪው የምታስብ ሁንና ደስታህን
በእጅህ አድርግ።

ውብ ቀን!💚

@wegoch
@wegoch
ዘመቻ 'X' ን ፍለጋ! ዳይ!
~~~~~~~~~~~~~
ወደ ፈተና አታግባን ብለን ብንፀልይም ይኸው ዘላለም አለማችንን 'X' ን እንፈልጋለን፡፡ 'X' ሁል ግዜ እንደ ጎረቤታችን አሰለፍ ቀዥቃዣ ልጅ እንደጠፋች ነው፡፡ የጎረቤታችን ልጅ መጥፋት ልማዱ ነው፡፡ በቀን እንኳን አንድ አራቴ ይጠፋል... እናቱ ትጮሀለች... "ኡኡኡኡኡ ልጄን መኪና በላው! እኔ አሁን እናት ነኝ ወይይይይይ" (ወይይይይይ የምትለዋ የመጨረሻዋ ቃል ረዘም ያለች ነች እንደ ቅጥቅጥ መኪና ሞተር፡፡) የሰፈሩ ሰው እንደ ቆዳ ፋብሪካ ጩኸታም ደወል እሷ ስትጮህ ጠብቆ ቁርሱን ይበላል... ወንድ የቀጠረች ኮረዳ እየተጣደፈች ትወጣለች... ባለ ዲግሪው ወጣት ስራ ሊፈልግ ወጣ... ደወል ነች አሰለፍ (በበጎ ፈቃደኝነት ሰፈሩን ታነቃለች፡፡ "ኡኡኡኡኡኡ ልጄን መኪና በላው! አሁን እኔ እናት ነኝ ወይይይይይይይይ... ልጁም ሰዓቱን ጠብቆ ይመጣል፡፡ አይደንቃትም... አመል ሆኖባት ነው የምትጮኸው... ትንሽ ይቆይና ጩኸት እንሰማለን... "ኡኡኡኡኡኡኡ... አሁን እኔ እናት ነኝ ወይይይይይይይ" ሰፈሩ ምሳውን ይበላል... ያ ከይሲ ልጅ ነው ይባላል...ማንም አይፈልገውም ያንን እንደ አዲሱ አንድ ብር በየደቂቃው የሚጠፋ ልጅ... አንዳንዴ ልጁ አርፎ እቤት ከተቀመጠ የሰፈሩ ኑሮ እና ህይወት ፍፁም ይስተጓጎላል፡፡ ሰራተኞች ያረፍዳሉ (ደሞዛቸው ይቆረጣል፡፡) የቀጠረ ይቀራል... የተነፋፈቀ ይጣላል... "እድሜ ለአሰለፍ ልጅ!" ይባላል... የታመመ የሚመስላቸው ራሱ ብዙ ናቸው፡፡ በቀጣይ ቀን ኑሮ ይቀጥላል... አሰለፍ በጠዋቱ ቶጮሀለች!
'X' ራሱ እንደ አሰለፍ ልጅ ትመስለኛለች፡፡ አሰተማሪው የትም ይንዘላዘልና ማጣፊያው ሲያጥረው ጩኸት ይጀምራል "ኡኡኡኡኡኡ Xን ወረቀት በላው! አሁን እኔ ቲቸር ዘውዴ ነኝ ወይይይይይይ?!"
X ዘመዴ ምናምን ትመስለኛለች... ያለ X ኑሮ ኑሮ አይሆንም! ለዛ ይመስለኛል ዘላለም አለማችንን የምንፈልጋት... በህይወታችን ከእግዜር... ከሚስት እና ከገንዘብ ቀጥሎ እንደ X የፈለግነው ነገር የለም፡፡ X እንደ አሰለፍ ልጅ ነች... ልክ "ፈልጋት" ስትባል የፈተና ሰዓት መድረሱን ትገነዘባለህ፡፡ ራስህን ይዘህ ትጮሀለህ... አሁን እኔ ተማሪ ነኝ ወይይይይይይይ?!
X ሆይ ወዴት ነሽ?
ዘመቻ Xን ፍለጋ ቀጥሏል...
ምን ለማለት እንደፈለግሁ በግልፅ ባይገባኝም ለመግለፅ ልሞክር በግልፅ... (ኸረ ገለፃ! :) )
የወደፊት ሚስቴ ሆይ የመፈለግ አቅሜ 'X'ን በመፈለግ ስለተዳከመ ግማሽ መንገድ ወደ እኔ በመምጣት ካልተባበርሺኝ ዘላለም አለማችንን በብቸኝነት በረንዳ ላይ ተቀምጠን ነጠላ እና ጋቢ እየቋጨን በብቸኝነት መሞታችን ነው!... አስተውይ! :)
እንደዛ መሰለኝ...
(በረከት ታደሰ)
(በረከት ታደሰ)

@Wegoch
@wegoch
ስለ መገለማመጥ... (ይሄ ውስጣዊ ብሶት ስለሆነ መሀረብና ሙሉ ስኒ አጥሚት ይዘህ አንብበው)
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ገላመጠችኝ!
ልክ ደረጃውን ስንወርድ ደረጃው በሰው ተሞልቷል! የአንበሳ ባስ ተሳፋሪ እንኳን በእስታይል መገፋፋት በጀመረበት ሰዓት አገጭ ለአገጭ እየተሻሸን እንወርዳለን፡፡ ልጅቷ ቀይ ነች ሰው በሞላበት ደረጃ እንዴት አይን ለአይን እንደተያየን እንጃ! አየችኝ አየኀት... ብዙ ነገር በሀሳቤ ሳልኩ (ይሄ ሁሉ ሲሆን ዙሪያዬ በሰው ተጥለቅልቆ እታች ወተት የሚታደል ነው የሚመስለው) ደስ ትላለች! ተዋውቀን ተሳስቀን መለያየት ትልቅ ትርጉም ያለው መሰለኝ... ዞሮ ዞሮ የህይወት ትርጉም ነጭ ፂም ካበቀለ ሽማግሌ አንደበት ውስጥ የምትፈልግ ከሆነ ፍፁም ተሳስተሀል፡፡ የህይወት ትርጉም በመተዋወቅ ይጀምራል... ከዛ ምንም ይፈጠር! በቀኑ እና በእድሜያችን መጨረሻ ግን የምናተርፈው ቁርጥራጭ ትዝታ መሆኑን እንዳንረሳ!
ልጅቷ ጋር ነበርን... ልክ እንዳየችኝ እንደ አባቷ ገዳይ ፣ እንደ እህቷ ልጅ አባት (አስረግዞ የጠፋ...)፣ እንደ የሆነ ነገር አይታ መብረቅ ቀረሽ ግልምጫ ገላመጠችኝ፡፡ እርግጠኛ ነበርኩ ከዚህ በፊት አይቻት እንደማላውቅ...
ጥያቄ!
ቆይ ግን ምን አመጣው መገለማመጡን?
እንደተያየን ዝም ብሎ መተላለፍ ሲቻል... ትንሽ ሲሻሻል "አንተ እለፍ፣ አንቺ እለፊ" እየተባባልን አርባ ደቂቃ ጥሩ ሰው መሆን ሲቻል... በጣም ስናሻሽለው ሰፈሯ ድረስ በበጎ ፈቃደኝነት አዝዬ ላደርሳት ስችል... ግልምጫውን ምን አመጣው?
ይኸውልሽ... ነገ ተያይተን የማይሰፈር ሳቅ መሳቅ ስንችል ይሄ ጉርድ በርሜል የሚገለብጥ ግልምጫሽን ባትለጥፊብኝ ምን ነበረበት?
ብቻ ዋና ሀሳቡ positiveness ይባላል፡፡
የሆነ ሰው በአንቺ ፈገግታ ቀኑ እንደ ስጋ ቤት አምፖል ሲበራ አየሸታይሽም?
የሆነ የተስፋ ውሉ የጠፋው ሰው በፈገግታሽና ጥሩ ፊትሽ የተወዳጅነት ስሜት ሲሰማው... ሲያልፍም ወዳጅሽ ሲሆን አይታይሽም?
ፀሀይ ብርሀን አይደለችም! ሰው ነው ሙሉ ብርሀን! ፀሀይ ፊት እንጂ ስሜት አታበራም!
ብቻ... ፈገግታሽ ልብ እና ነፍስ እንደሚያሞቅ ካልገባሽ... ትልቁ ስህተትሽ እሱ ይሆናል፡፡
በመጨረሻም...
ስትስቂ ሲያምርብሽ ብታዪ... ሳቅሽን እያየ ስንት ሰው እንቅፋት እንደመታው ብታዪ... እንቅፋቱ የአውራ ጣት ጥፍሩን እንደነቀለው ብታዪ... አውራ ጣቱ ላይ ያስጠመጠመውን ክቡን የቁስል ፋሻ አይተሽ "ማንኪያ ይመስላል" ብለሽ ስትስቂ... ያ ደግሞ ለሌላ ሰው ትርፍ ይሆናል ብለሽ አስቢ!
እንደዛ መሰለኝ...
(በረከት ታደሰ)


@wegoch
@wegoch
ለውብ ቀን
💚

የእናቶች ፀሎት እና ልመና ጠብ የምትል አይደለችም!! ያደለው ቅዱሳንን ተማፅኖ እንዲህ
ቤቱ በተአምራት ይሞላል! ይባረካል ይፈወሳል


እግዚአብሔር ሁላችንም ወደ ልቦናችን ይመልሰን እና በእጃችን የያዝነውን እንቁ
እንድናስተውል ይርዳን።



መልካም የፍልሰታ ጾም ይሁንላችሁ። የጾሙ ጊዜ በጸሎት፣ በፍቅር፣ በእርቅ፣ በተስፋ፣
በትብብርና በመልካም ስራ እንዲያፍልን የሚቻለንን ሁሉ እናደርግ

ውብ ቀን💚

@wegoch
@wegoch
የሚቀጥለው ፋሲካ
(በእውቀቱ ስዩም)
(የሚያስተክዝ ትዝታ)

ያኔ ልጅ እያለሁ ፤ የፍልሰታ ጦምን እስከዘጠኝ ሰአት እፆም ነበር:: የፆም አላማ ፤ወደ እግዚያብሄር ለመቅረብ፤ በረከት ለማግኘት እና ሀጢአትን ለማስተረይ እንደሆነ ይታወቃል :: እኔ ግን የምጦመው በፆም ወቅት ቤት ውስጥ ምግብ ስለማይሰራ ነው፤ ጦሙ ሊገባ ሁለት ቀን ሲቀረው እናታችን፤ ያንን ትልቁን ብረትድስት ፤ ለሁለት ወራት ስለማትፈልገው፤ ለእትየ ፋጤ ታከራያቸዋለች፤ እትየ ፋጤ በመላው ዳሞት ብቸኛ የሙስሊም ምግብ ቤት ያላቸው ሴትዮ ነበሩ፤
በፍስክ ወቅት፤ትምርት ቤት ከምንዘምራቸው መዝሙሮች ውስጥ፤
"ሳይንስ ሳይንስ መዳኒቴ
አስታወሰኝ ጤንነቴ ( ምን ለማለት ተፈልጎ ነው ግን?)
ፊቴን ታጥቤ ፤ቁርሴን ስበላ
ሳይንስ ትዝ አለኝ፤ ከጤና ጋራ"
የሚለው አይዘነጋኝም፤በፆም ወቅት ግን ፤መዝሙሩን ትንሽ አስተካክለን እንደሚከተለው እንዘምረዋለን፤
ሳይንስ ሳይንስ መዳኒቴ
……
ፊቴን ታጥቤ ቁርሴን ባልበላም
እናት አገሬ ሁኝልኝ ሰላም
በፆም ወቅት፤ አያሌ ምእመናን ጊዝያቸውን፤ በፆሎትና በስግደት ያሳልፉታል:: እኔ ግን በፆም ወቅት ቀኑን የማሳልፈው ፤ አላፊ አግዳሚውን እያስቆምኩ ፤ ሰአት በመጠየቅ ነው:: (ዘጠኝ ሰአት ካልሞላ እህል ወደኛቤት አይደርስም፤)
ለምሳሌ ጋሽ በለው በቤታችን በር በኩል ሲያልፉ ጠብቄ፤
"ጋሼ ስንት ሰአት ነው?"
ጋሽ በለው ፤ የእጅ ሰአት ለማሰር ከታደሉት ጥቂት የማንኩሳ ነዋሪዎች አንዱ ነበሩ:: ከሴኮ ሰአታቸው የሚመነጨው ኩራታቸው ወሰን አልነበረውም፤ ሰአትን የፈለሰፈው ሰውየ እንኩዋ የሳቸውን ያህል አይንጠባረርም !! የእጅ ሰአቱን ፤የዳሞትን አውራጃ በመወከል ፤በውሃ ዋና ውድድር አሸንፈው፤ ከጃንሆይ የተሸለሙት ነው ይባላል:: የዋና ችሎታቸውን ለማጋነን በየጠላ ቤቱ እሚወራው ብዙ ነው፤ አንዳንዴ ጋሽ በለው፤ ሲደብራቸው፤ ጣና ላይ ዳይቭ ገብተው ፤ ቀይ ባህር ላይ ብቅ ይሉና የባህር ሃይላችንን ሰራተኞች “ጉዋዶች በርቱ!” ብለው፤ ይመለሳሉ ይባላል::
በነገራችን ላይ "አሳ በለው በለው" የተባለው ዘፈን ለሳቸው ነው የተዘፈነው ለእሳቸው መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን?፤ እና ሰአት ስጠይቃቸው፤ በኩራት ፈገግግግ ብለው፤ እስክስታ እንደሚመታ ሰው ግራ እጃቸውን ትንሽ ርግፍ ርግፍ አድርገው፤ በክርናቸው ነፋሱን ጎስመው፤ አይበሉባቸውን ወደ ፊታቸው ያመጡና ግንባራቸውን ቁዋጠር ፈታ ሲያረጉ ቆይተው፤
" ሰባት ሰአት ነው" ይሉኛል::
“ትንሽ አጠገባቸው ቆሜ ኦና ሆዴን ሳክ ከቆየሁ በሁዋላ “አሁንስ?"
“ሰባት ካምስት”
“አሁንስ?”
"ወግድ ከዚ"
እኔም ከዚ እወግድና ሌላ ሰአት አስሮ የሚያልፍ ሰው እጠብቃለሁ:: ዘጠኝ ሰአት የሚባለው ነገር እየተንቀራፈፈ፤ እሪህ ያለበት ኤሊ እየጋለበ ፤ እስኪመጣ ድረስ እጠብቃለሁ፤
ጦም ሲታሰብ ፍስክ ትዝ ይለኛል፤ ፍስክን ሳስብ ትንሽ ወንድሜ ሞሴ ይመጣብኛል ፤ ሞሴ እንቁላል አጥብቆ ይወዳል ፤ ሞሴ እንቁላል ከመውደዱ የተነሳ የሰጎን እንቁላል ከቤተክስያን ጉልላት ላይ አውርዶ ቢቀቅል አይጠላም፤ ያኔ እንቁላል የሚባል ነገር መኖሩ ትዝ የሚለን በሁለት አጋጣሚዎች ነው፤ በሳይንስ ክፍለጊዜ ስለገንቢ ምግብ ስንማር እና የፋሲካ ሌሊት ፤ የፋሲካ ሌሊት እናታችን በትልቁ ሰታቴ ብስል ያጋም ፍሬ የመሰ ዶሮ ወጥ ሰርታ አስራሁለት ቅቅል እንቁላል ትጥልበታለች ፤
ያገራችን ዶሮዎች፤ ከላይ ጆፌ አሞራ እያንጃበባቸው፤ ከታች ጎረቤት በቅዝምዝም እያባረራቸው ፤ ተሳቀው ጭረው፤ የሚጥሉት እንቁላል ከውሃ ብይ አይበልጥም፤ እንድያውም አንዳንዳንዴ ፤ከዶሮይቱ እንቁላል ፤የዶሮይቱ አይን ይተልቃል፤
ባንዱ ፋሲካ ዶሮ ወጥ ከብበን ስንበላ፤ እናታችን በየፊታችን እንቁላሎችን አስቀመጠችልን፤ ሞሴ ድርሻውን አንስቶ፤ በትንሽ በትንሹ እየቆረሰ፤እየቆጠበ በልቶ ጨረሰ፤በጉንጩ ገበር ላይ ተለክኮ የቀረውን የንቁላል ቅሪት በምላሱ ጠርጎ አጣጣመ፤ከዚያ ፤
“እማየ”
“አቤት ልጄ ”
“የሚቀጥለው ፋሲካ ስንት ቀን ቀረው?”

@WEGOCH
@WEGOCH
ከውልብታ ገፅ ላይ ስንቆነጥር
(ለመዝገን ፈልጋቹ አንብቡት)

ሥም ያለው
(ገፅ 22)
ታክሲ ውስጥ ገብታ ልትቀመጥ ከወደኋላዋ ድምፅ ሰማወሁ "ጡ...ጥ"

ከሷ ፊት ስለተቀመጥኩ በመገረም ዞር ስል በሀፍረት ጥሬ አክላ አገኛታለሁ ያልኳት ባለድምፅ እኔ ላይ አፍጣ:-

"ምነው? ስምህ ነው እንዴ?"አለችኝ።

"ስም ያለው ሞኝ ነው" ደገመችኝ።
***

መምጣትና መሄድ
(ገፅ 21)
ተገናኙ
"በምን አፈቀርከኝ?"
"በውስጣዊ ውበትሽ"
"ውበት ከፈለግክ ሌላ ቦታ ሂድ÷ ውስጣዊ ውበት ሳይሆን ሥነምግባር ነው ሚባለው።"

....ተለያዩ።

***
ግብይት
(ገፅ 49)
"ቅቤ፣ ቅቤ።……ቅቤ!"

"ባለ ቅቤ"

"አቤት"

"ሁለት ኪሎ ቅቤ ለቅዳሜ አምጣልኝ"

"እሺ"

"አደራህን"

"እረ ግዴለም፣ደንበኝነት ለመቼ ነው?"

"አደራህን፣ አደራህን"

"ምን ሆነዋል? ግዴለም እያልኮት"

"አደራ ያልኩህ ለምን እንደሆነ አላወከውማ"

"ለምንድንነው?"

"ሙዙን ጠቃጠቆ አድርገው"
--------------
"ውልብታ"
ደራሲ- አለማየሁ ገላጋይ
ዋጋ -71.50
ገጽ ብዛት - 160

@WEGOCH
@WEGOCH
Forwarded from ግጥም ብቻ 📘 (👋ገብርዬ)
Forwarded from ግጥም ብቻ 📘 (👋ገብርዬ)
🇪🇹🇪🇹🇪ዘጠነኛው የብርሃን ዕለት የመጀመሪያው ማክሠኞ ነሀሴ 7። ይምጡና አብዝተው ያትርፉ እንድቅትዮን በ አዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ(ፒያሳ) ።
ልዩ እና እውቅ የጥበብ ሰዎች ግጥም እና ወግ በባህላዊ ሙዚቃ ታጅበው ያቀርባሉ።

እማይቀርበት ልዩ የጥበብ ምሽት!


@getem
@wegoch
@tebeb_mereja
ህይወት እንዲሁናት መሰለኝ.. ..።


ከእለታት አንድ ቀን ድንገት ከእንቅልፍህ ስትነቃ .....ሁሉም ነገር የሌለህ መስሎህ
በሚሰማህ ግዜ ሁሉን ነገርህን የምትሆንልህን እናትህን አጥተህ እራስህን
ታገኘዋለህ.....ትኖራለህ።


ደሞ ሌላ ግዜ ድንገት ሁልግዜ የምትኮራበትን ይምትመጻደቅበትን አባትህን እራስህን
ታገኘዋለህ.....ትኖራለህ።
ደሞ እንደገና በመኖርህ ውስጥ ድንገት ስትነቃ ፍልቅልቅ ጨቅላ ልጆችህን አጥተህ
እራስህን ታገኘዋለህ......አሁንም እየኖርክ ነው።
ኑሮ እየቀጠለ ነው።


አሁንም በምንቃትህ ውስጥ ደሞ ድንገት በህይወት መንሸራተት ወንድሞችህ ርቀውህ
አጥተሃቸው እራስህን ታገኘዋለህ ........መኖር ቀጥሏል።
......ደሞ ድንገት ስትነቃ እንዲሁ የወደድከውን ያፈቀርከውን አጥተህ እንደተለመደው
እራስህን ታገኘዋለህ......ህይወት እንደቀጠለች ነው።
የማጣቱ ምክንያቱ....ተፅእኖው.....አይነቱ ይለያያል።
.....ግን ግን ሁሉም ማጣትን መለየትን ያሸክሙሃል።
ሌላ ግዜ ደሞ ድንገት ዝሸክምን ችሎ ለመኖር በልምምድ ውስጥ ሆነህ እራስህን
ታገኘዋለህ .... ከተስፋ መቁረጥ ጋር ትንቅንቅ ገጥመህ። አንዳንዴ ለመኖር የምትፈተነውን
ያክል መኖር ለማቆምም ከባድ ፈተና መሆኑን ትረዳለህ። .
.
.
.
.ድንገት ደሞ ሌላ ግዜ ስትነቃ የትዕግስትህ መጠን አድጎ ....ቻይነትህ
ጎልብቶ.......ማስተዋልህ በዝቶ በህይወትህ ያገኘሃቸው...የተደረጉልህ......ያሉህ ነገሮች
በህይወትህ ካጣሃቸው....ካልተደረጉልህ....ከሌሉህ ነገሮች እጅግ በጣም የበዙ
መሆናቸውን ተገንዝበህ ፈጣሪን ስታመሰግን እራስህን ታገኘዋለህ ። .......
.
.
.
.
ለጊዜው ድንገት በመንቃቴ ውስጥ
በዚህ ስሜት ውስጥ ሁኜ እራሴን አገኘሁት። ""ተመስገን ፈጣሪዬ!!!!!! እባክህ ትዕግስቱን
ስጣኝ "" ስል ሙሉ ለሙሉ ነቃሁ።


ውብ ቀን!💚

@wegoch
@wegoch
@balmbaras
ኑሮ ግን ሲጢጢጢጢም!
፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠፠
ወደ ክላስ እየሄድኩ ነው፡፡ ሁሌ ታክሲ የምይዝበትቦታ ቆሜያለሁ፡፡ ፀሀይዋ በጋለ ጣቷ አናቴን ስትነካኝ ይሰማኛል... ፊቴን አጨፍግጌ ቆሜያለሁ፡፡ የሜክሲኮ ታክሲ እየጠራ ሰማሁ፡፡ መኪናው ጋር ስደርስ ከኀላ ካሉት ወንበሮች ውጭ ሞልቷል፡፡ ከኀላ የተቀመጡት ሰዎች ተጠጋጉልኝ... የኀላ ወንበር አልወድም! ከርዝመቴ ጋር ተደምሮ እንደ እኛ ቤት ሳሎን በጣምምም መጥበቡ አይመቸኝም! የሆነ በህገወጥ መንገድ ወደ የመን እየተሰደድኩ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ ትልቅ ቂጥ ያላት ሴት ካለች ሲኦል ነው፡፡ በሩ ስር ያለው ትርፍ ቦታ ተቀመጥኩ፡፡ የሆነ እጅ ነካኝ! ስዞር ሀይማኖት ነበረች... ሀይማኖት ማለት በአካል ብዙ አንተዋወቅም፡፡ የሰፈር ልጅ ነች... ሰሞኑን በፌስቡክ ማውራት ጀምረናል፡፡ ዘፋኝ መሆን ስለምትፈልግ ግጥም እንድሰጣት ጠይቃኝ ነበር፡፡ ሲጀመር የዘፈን ግጥም አልፅፍም! ሲቀጥል ደግሞ ሀይማኖቴ ዘፈንን ይቃወማል! ስላት ግጥሙ ቀረና ትንሽ ወዳጅነት ጀመርን፡፡ በአካል አሁን ገና ስትነካኝ ማለት ነው... "ሀይሚ እንዴት ነሽ?" አልኳት (ነች ብዬ ያሰብኳት ልጅ የምር እንዳሰብኳት ነች? ብዬ እየገመገምኩ...)
ፈገግ አለች፡፡ ጓደኛዋ አጠገቧ ነበረች... ሳታየኝ እጇን ዘረጋች፡፡ "ተጠጊለት እንጂ? ና እዚህ ጋ!" አለችኝ፡፡ አጠገባቸው ተቀመጥኩ፡፡ "ወዴት ነው?" አልኳት አይን አይኔን እያየች የሆነ አይነት ወሬ እንደጠበቀች ስለገባኝ፡፡ "ክላስ" ብላ ወሬውን አንገቱን ቆረጠችው፡፡ "በአካል ታስታውሺኛለሽ ብዬ አላሰብኩም ነበር..." ሀሳቤ ላይ የመጣው ወሬ ይሄ ነበር... "አዎ..." ብላ ዝም አለች...
ቀጣይ ወሬ አልነበረኝም! የማታውቀውን ሰው ለማዋራት ከመጣር የበለጠ ስቃይ የለም! ጓደኛዋ ሌላ ወሬ ጀመረች... እኔን አያሳትፍም፡፡ አጠገባቸው ተቀምጬ አጠገባቸው አልነበርኩም፡፡
አሁን ከራሴ ጋር አወራሁ
1) በስሷ ኪሴ የሶስት ሰው ሂሳብ ልከፍል ነው፡፡ ያውም እስከ ሜክሲኮ ድረስ የማያገባኝን እና መስማት የማልፈልገውን ወሬ እየሰማሁ፡፡
2) የባዳነት ስሜት እየተሰማኝ... የማውቃት ግን ፍፁም የማላውቃትን ሀይሚን የጓደኛዋን ፊት አልፌ ሳያት... እያዋራቺኝ ደግሞ አይደለም፡፡ እነንደ ጎረቤት ጨዋ ልጅ ዝምምምምምም ብዬ!
3) የሆነ ያልተጠራሁበት ድግስ ላይ የተቀመጥኩ መሰለኝ!
ያስጠሉኝ ነገሮች በዙ! ይሄንን ሁሉ ጣጣ ያመጣብኝ የኀላ ወንበር ስለሆነ ጠላሁት ፣ ኀላ ወንበር ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ አስጠሉኝ ፣ ኀላ ወንበር ላይ የሶስት ሰው ወንበር ይዛ የምታጣብብበዋ ቂጣም አስጠላቺኝ ፣ ቂጥ አስጠላኝ ፣ ታክሲ ሲያስጠላ ፣ ፌስቡክ ሲያስጠላ ፣ ማርክ ዙከርበርግ ከነ ወፍራም ባለ ኮፍያ ሹራቡ ሲያስጠላ ፣ ትርፍ መጫን ሲያስጠላ ፣ ትርፍ ስጋ ሲያስጠላ ፣ ሜክሲኮ ሜክሲኮ እያለ የሚጣራው ረዳት ድምፅ ሲያስጠላ ፣ ሜክሲኮ መሄድ ሲያስጠላ... በተለይ የምታውቀው ከሚመስልህ ግን ከማታውቀው ሰው አጠገብ መሄድ ሲ-ያ-ስ-ጠ-ላ!!!!!

ይሄንን እንዳሰብኩ ሀይማኖትን ስልክ በያዘው እጄ ጠራሁዋት፡፡ ወሬዋን አቋርጣ ዞረች... ወሬው ሲቋረጥባት ጓደኛዋም ዞረች፡፡ 'ጨርሻለሁ' አልኳት፡፡ ምን ለማለት እንደፈለግሁ እንጃ! ብቻ ሀሳቤ እሱ ነበር፡፡ ጨርሼ ነበር፡፡ ወረድኩ እና እየተጣራ የነበረውን ረዳት ተረኛ ታክሲ የትኛው እንደሆነ ጠየቅሁት፡፡ እነ ሀይሚ ግራ ገብቷቸው ያዩኛል፡፡ ግልግል የሆነ ስሜት ተሰማኝ! አርባ ኩንታል ሸክም የወረደልኝ ያህል ረጅም ኡፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍፍ አልኩ!
ምን ገባኝ መሰለህ...
አንዳንዴ ዝም ብለህ ወስን፡፡ እየተጨነክ ያለኸው በትንሽ ነገር ነው፡፡ ወስን ወዳጄ! የኑሮህ መንገድ በእጅህ እንዳለ ይሰማሀል፡፡ የማንም ባለ እዳ አይደለህም! በየትኛውም መንገድ ራስህን አትሰር... ራስህን ፍታ ወዳጄ! ራስህን ነፃ አውጣ!

ከዛ... ከዛማ... በኩራት ተራመድ
(በረከት ታደሰ)


@wegoch
@wegoch
@wegoch
🇪🇹🇪🇹🇪ዘጠነኛው የብርሃን ዕለት የመጀመሪያው ማክሠኞ ነሀሴ 7። ይምጡና አብዝተው ያትርፉ እንድቅትዮን በ አዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ(ፒያሳ) ።
ልዩ እና እውቅ የጥበብ ሰዎች ግጥም እና ወግ በባህላዊ ሙዚቃ ታጅበው ያቀርባሉ።

እማይቀርበት ልዩ የጥበብ ምሽት!


@tebeb_mereja
@tebeb_mereja
@tebeb_mereja
2024/09/27 19:22:10
Back to Top
HTML Embed Code: