Telegram Web Link
"+" በትረ ሙሴ ( አርዌ በትር ) "+"

ጌታችን ኢየሱስ ሆይ በትረ ሙሴያችን ነህ!

ከ666 እና ከኢሊዩሚቲ ጋር ተያይዞ በበትሩና በእባቡ
ዙሪያ ጥያቄ ለተፈጠረባቸው መልስ እነሆ። ቅዱስ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉ በእጃቸው በሚይዙት በትር ላይ የለውእባብ ምንድ ነው ? ብለው ለሚጠይቁ ሁሉ መልስ እነሆ ። ጥያቄው የቆየ ቢሆንም ሰሞኑን እንደ አዲስ እያገረሸ ነውና፤በዚህም ተያይዞ አንዳንድ ወገኖች በበትሩ ላይ የሚታዩት አራዊት ዘንዶ ናቸው በማለት ነገርየውን # ከ666 ጋር ለማያያዝ ሲሞክሩ ይታያሉ ። ነገር ግን በፎቶው ላይ እንደሚታየው ዘንዶ ሳይሆን የእባብ ምስል ነው። እባቡም ደግሞ እንደምትመለከቱት ከመስቀሉ
ስርነው የሚታየው። ምክንያቱም መስቀል የሁሉም የበላይና እባብ የተሰኘው ዲያብሎስም አናት አናቱን የተቀጠቀጠበት ነውና ።
[ መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና
ትስታላችሁ ] ማቴ 22፣29 ። የኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናትን የሚመሩ ቅዱሳን ፓትርያርኮችና ሊቃነ
ጳጳሳት ፣ ኤጲስ ቆጶሳትም በእጃቸው የሚይዙት አርዌ ብርት/መስቀልና የእባብ ምልክት ያሉበት/ በትር ምሳሌነቱ
ከመስቀሉ ስር ያለው ሙሴ ለሕዝቡ መዳኛ ያደረገው የናስ እባብ ምሳሌ ነው፡፡ @ “ሙሴም የናሱን እባብ
ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ” ።( ዘኍ 2፣ 19 )። ይኼ
ምሳሌ መሆኑን ክርስቶስ ሲያስተምር....“ሙሴም በምድረ
በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው
ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” ። ዮሐ 3 ፣ 14 በማለት ምሳሌና ጥላ የነበረውን አማናዊ ለማድረግ፣ ጌታችን አምላካችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ያዩት ሁሉ እንደሚድኑ አመሳስሎ አስተማረበት፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የናሱን እባብ
ከራሱ ስቅለት ጋራ ሲያነጻጽረው ያላፈረበትን፤ የእኛ አባቶች የናሱን እባብ ምሳሌ “በትረ ሙሴ” የሚባለውን
በግራ እጃቸው፣ የተሰቀለበትን መስቀል በቀኝ እጃቸው ቢይዙ የሚያሳፍር አይሆንም፡፡ በብሉይ እግዚአብሔር ሕዝቡ ሲበድሉት “እባቦችን ሰደደ፥
ሕዝቡንም ነደፉ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ” ። (ዘኍ 21፡6 ) በእባብ መርዝ ተነድፈው የታመሙ ሁሉ መርዝ በሌለው የናሱን እባብ በማየት እንዲድኑ አድርጓል። ይህም ምሳሌው ለእኛ ነው፡፡የበደሉት እስራኤላውያን የእኛ የሰዎች ምሳሌ ሲሆኑ፤ መርዝ ያለው እባብ የዲያብሎስ ምሳሌ ነው፤ የናስ እባብ መርዝ እንደሌለው ሁሉ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ በደሉ ተሰቅሎ ስለ እኛ ኃጢአት እርሱ የመሞቱ ምሳሌ ነው፤ “እባብን ሠርተህ
በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል” ዘኍ 21፣8 መባሉ፣ የናሱን እባብ ሲያዩ የዳኑ፣ ጌታ ተሰቅሎ አይተው የዳኑ ሰዎች ምሳሌ ሲሆን፣ ከሩቅ ያሉት ሰዎች ምሳሌነት ወንጌልን ከመምህራን በመስማት ሳያዩ ቃሉን ብቻ ሰምተውና አምነው የዳኑ
ክርስቲያኖች ምሳሌ ነው፡፡ ምክንያቱም በስብከታቸው “በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር” ገላ 3፣1 እንዳሉት ማለት ነው፡፡
በፓትርያርኩ እጅ የምናየው “በትረ ሙሴ” ትምህርት ነው የሚሰጠው፤ ምክንያቱም የሚታይ ሥዕልና ቅርጽ ትምህርት እንደሚሆን ሁሉ በቤተ ክርስቲያናችን አማኝ ሁሉ ጠባቂ
መልአክ እንዳለው እንዲያውቅ እንዲረዳ “ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ” ዘጸ 25፣18 ባለው አምላካዊ
ቃል መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን ግንቦች ላይ ሁሉ ሥዕል ይሳላል፤ የሚመለከት ጠባቂ መልአክ ይባላሉ ብሎ እንዲያስታውስ ማለት ነው፡፡
ለዚህም ነው ንጉሥ ሰሎሞን “በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት
ሁለት ኪሩቤል ሠራ በወርቅም ለበጣቸው" ተብሎ በዚሁ
እንድንቀጥል የተሠራው የተጻፈልን 1ኛ ነገሥ 6 ፣23-35፣ 2ኛ ዜና 3፣7-13 የብሉይ ኪዳን ምሳሌ የሆነውን የናሱን እባብ ስናይ እስራኤላውያን የዳኑት በዚህ
በፓትርያርኩ በግራ እጃቸው ባለው የናስ እባብ ነው ብለን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈልንን እንድናስታውስና፣ እኛ
ግን የዳንነው በቀኝ እጃቸው ባለው መስቀል ላይ በተሰቀለው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት ለመመስከር
ሁለቱንም ማለትም ብሉዩንም አዲሱንም፤ የናሱን ምስልና የክርስቶስን መስቀልን ይዘው ይታያሉ፡፡
ሌላው መሪው ሙሴ የናሱን እባብ ይዞ በዓላማ ላይ ሲሰቅለው እንዳዳናቸው፤ እግዚአብሔር አብ ልጁን በመስቀል ላይ ሰቅሎ ዓለሙን ለማዳኑ መስካሪዎች
ስለሆንን “በትረ ሙሴ” የሚል ስያሜ ያለውን በትር የኤጲስ ቆጶሳቱ አለቃ በእጃቸው ይዘው ይታያሉ፡፡ ሙሴ
የእስራኤላውያን መሪ ነው፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ ደግሞ የሃይማኖት መሪ ናቸውና ይህን በትር ይይዛሉ፡፡
<<ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>
"+" እንኳን ለንጽህተ ንጹሀን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ግሸን ደብረ ከርቤ ታላቅ ክብረ በዓል አደረሳችሁ"+"

"+"ብዙኃን ማርያም"+"

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል ‹ብዙኃን ማርያም› በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤
በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጠረ፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡
በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ አበው ይገኙበታል፡፡
ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡
፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎች ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ‹ብዙኃን ማርያም› እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡ እነዚህ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬)፡፡
በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤
ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው ‹‹የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል›› አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር ‹‹የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ›› የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው አሳውጀው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡
ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡
መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፡፡ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ አስነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የክርስቶስ የመስቀሉ ኃይል፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡– መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ ፫፻፶፬–፫፻፶፮፡፡
Forwarded from ርቱዓ ሃይማኖት via @like
የጸሎት ሥርዓቶች
------------------------
ጸሎት በማንኛም ጊዜ በየትኛውም ቦታ ሊጸለይ ይችላል አይነቱንና መጠኑን
ለመወሰን በንቃትና በትጋት ለመከታተል እንዲያመች ሲባል መጠንና ግዜ
ተወስኖለታል፡፡ የአፈጻጸም ሥርዓትም አለው፡፡ በዘፈቀደ የሚደረግ አይደለም፡፡
በዚህ መሰረትም የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ሀ. ቀዊም፡- ለጸሎት በተነሳን ግዜ ውስጣዊና አፍአዊ ሁለንተናን አዘጋጅቶ
አለባበስን አስተካክሎ መቆም ነው፡፡ ዳዊት ‹‹ማለዳ በፊትህ እቆማለሁ ለአንተም እታያለሁ›› እንዳለ መዝ 5÷3፣ ዘፍ 24÷12-14

ለ. ቀኒተ ኅቋ፡- ወገብን ታጥቆ ፊትን ወደ ምስራቅ መልሶ መቆም ነው፡፡ ጌታችን
‹‹ወገባችሁ የታጠቀ ይሁን›› ብሎ እንዳስተማረ (ሉቃ 12÷35)
የግል ጸሎትን የሚጸልይ ሰው ፊቱን ወደ ምስራቅ መልሶ እንዲጸልይ ታዟል
ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡-
ክርስቶስ በዳግመኛ ምፅአቱ ግዜ በምስራቅ በኩል ይገለጥ ዘንድ የተነገረበት፤ ቃሉ የተሰማበት፤ ምፅአቱን የሚያደርግበት ስለሆነ ነው፡፡ ራሳችንን በዚህ መልክ ካዘጋጀንና በፈጣሪያችን ዙፋን ፊት ቆመን ለመጸለይ ከተዘጋጀን በኋላ ህሊናችንን መሰብሰብ፣ ዐይኖቻችንን ወደ ግራ ወደ ቀኝ ከማየትና አካባቢን ከመቃኘት እንዲቆጠቡ የውስጥ አይኖቻችን ጋር ተዋህደው ወደ ሰማይ እንዲመለከቱ መገለጥ አለባቸው፡፡ የልመና፣ የምስጋና፣ የአንክሮ፣ የተዘክሮ ጊዜ ነውና በፍጹም ንቃትና ጥንቃቄ መቆም ይኖርብናል ከክርስቶስም የምንማረው ይህንኑ ነውና፡፡
ኢየሱስም አይኖቹን ወደላይ አንስቶ፡- ‹‹አባት ሆይ ስለሰማኸኝ አመሰግንሀለሁ
ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ …..›› አለ ‹‹ዮሐ 16÷41)

ሐ. አቲብ (ማማተብ)፡- የቀኝ እጅ ጣቶችን በመስቀል ቅርጽ (አምሳል) አዘጋጅቶ
ወይም በመስቀል ከላይ ወደታች ከግራ ወደ ቀኝ ማንቀሳቀስ (ማማተብ) ነው፡፡

የጸሎት ጊዜያት ለእግዚአብሔር የምስጋና ጊዜና አመስጋኝ አይወሰንበትም በማናቸውም ጊዜ
በፍጥረቱ ሁሉ ይመሰገናል፡፡ ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ ስለሆነ ቅዱሳን
መላዕክትም የሚያመሰግኑትም ያለማቋረጥ በመአልትም በሌሊትም ነው፡፡ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ምሳጋናቸው እረፍታቸው ነው፡፡
ይሁን እንጂ በአለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሰርቶ መኖር ግዴታቸው በመሆኑና
ከተግባረ ነፍሱ በተጨማሪ የሚያከናውኑት ተግባረ ስጋ ስላለ ግዜውን ማካፈልና ማደላደል ስለሚገባ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ጊዜያት ወስና በዚሁ መሰረት እንዲፈፀም ስርአት ሰርታለች፡፡ እነዚህም ሰባት የጸሎት ጊዜያት ልበ አምላክ ዳዊት ‹‹ለኔ ብለህ በሰራህልኝ ቀን ሰባት ግዜ አመሰግንሀለሁ›› ብሎ በተናገረው ላይ የተመሰረቱ ናቸው እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ. ጸሎተ ነግህ
ፀሎተ ነግህ (የጠዋት ፀሎት) ከመኝታ በነቁ ግዜ ፀሀይ ከመውጣቷ በፊት
ማለዳ የሚቀርብ ፀሎት ነው የዚህም ምክንያት፡-
የሌሊቱን ጨለማና የዕረፍቱን ጊዜ አሳልፎ ቀኑን ስላበራልንና የስራውን ጊዜ
ስለተካልን ለማመስገን ቀኑንም እንዲባርክልን ለመለመን ነው፡፡
ነብዩ ዳዊት ‹‹አምላኬ፣ አምላኬ በማለዳ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ ብሎአል‹‹ (መዝ 62÷1)
የማለዳው ጊዜ በጥናተ ፍጥረት የመጀመሪያው ሠው አዳም የተፈጠረበት
ስለሆነ በሱ ዘር ሁላችንም የተገኘንበት በመሆኑ ለማመስገን በስህተቱ ከተድላ ገነት የተባረረበት ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ በደል በመካሰሱ ጲላጦስ ፊት የቆመበት

ለ. ጸሎተ ሠለስት (3 ስዓት)
ይህ ክፍለ ጊዜ፡- ሔዋን የተፈጠረችበት ነው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብስራተ መልዐክን የሠማችበት፤
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት ስለ እኛ
የተገረፈበት፤
ለአበው ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ስለሆነ።

ሐ. ቀትር ( 6 ሰዓት)
ሰይጣን አዳምን ያሳተበት፤
በራሱ ስህተትና ጥፋት በሀጢያት የወደቀውን ሰው ለማዳን የዓለም መድኅን
ኢየሱስ ክርስቶ በቀራኒዮ ኮረብታ የተሰቀለበት፤
ርዕሰ ነቢያት ሄኖክ ገነትን ያጠነበት ስለሆነ ከነቢዩ በረከት እንዲያካፍለን
የአጋንንት ኃይል እንዲያበረታን የጌታን መከራ መስቀሉን እያሰብን በሀጹረ
መስቀሉ እንዲጠብቀን እንጸልያለን፡፡

መ. ተሠዓት (9 ሰዓት)
ጌታችንና አምላካችን በመስቀል ላይ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ስጋው በራሱ
ስልጣንና ፈቃድ የለየበት ስለሆነ የእኛን ሞት ተቀብሎ ሕይወቱን እንደሰጠልን፣
ፍቅሩን ቸርነቱን በማሰብ አለምን ያዳነበትን ጥበቡን በማድነቅ መፀለይ ማዘን ይገባል፡፡
ቅዱሳን መላዕክት የሠውን ስራ (በጎም ይሁን ክፉ) ወደ ልዑል ፈጣሪ የሚያቀርቡበት

ሠ. ጸሎተ ሠርክ (11 ሰዓት)
ይህ ሠዓት ሳይበድል እንደበደለኛ ተቆጥሮ በደለኞችን ለማዳን በመብዕልተ
መስቀል የተሰቀለው የአለመ ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ስጋ ወደ መቃብር፤
በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ በሞት ጥላ ሥር በጨለማ የነበሩትን ነፍሳት ነጻ
ያደረገበት ስለሆነ የቸርነቱን ስራ እያሰብን እንፀልያለን፡፡

ረ. ጸሎተ ንዋም (የመኝታ ግዜ ጸሎት)
የጊዜ ባለቤት እግዚአብሔር ቀኑን ስንደክምበት የዋልንበትን የተግባር ግዜ
አስፈጽሞ የምናርፍበት፣ የሌሊቱን ግዜ ስላመጣልን ለማመስገን፤ ሌሊቱን
የሰላምና የዕረፍት እንዲሆንልን ለመለመን እንጸልያለን፡፡
ቅዱስ ዳዊት ‹‹በመኝታዬም አስብሀለሁ፡፡›› እንዳለ እንቅልፍ ትንሹ ሞት
መኝታውም የመካነ መቃብር ምሳሌ ነውና ስንተኛ ሞትን ስንነቃ ትንሳኤን
አስተውለን ሕይወታችንን ለባለቤቱ ለጠባቂው እግዚአብሔር አደራ መስጠት
ይገባል፡፡
በዚህ ክፍለ ሠዓት ጌታችን ለሐዋርያት ሥርዓት ፀሎትን ያስተማረበት መሆኑንና
ስለ እኛ በጭፍሮች መያዙን እናስባለን፡፡
ሰ. መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት)
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በእንስሳት በረት በሌሊት
መወለዱን በማሰብ
ኃጢአትን፣ ሞት፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሞት
ከመቃብር በመንፈቀ ሌሊት መነሳቱን በማሰብ፤
በመጨረሻውም የቁርጥ የፍርድ ጊዜ በጎ ለሰሩ ዋጋ ክፉ ለሰሩ ፍዳን ለመስጠት
በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት፣ በይባቤ መላዕክት የሚመጣበት የፍጻሜ
ዘመን ማሰቢያ ሰአት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ
እነሳለሁ›› እንዳለ ከእንቅልፍ ከፍሎ ለእግዚአብሔር የምስጋና ጊዜ ማበርከት
ነው፡፡ (መዝ ---÷62)
ጸሎታችንን ይቀበልልን!!!
❤️ወስብሐት ለእግዚአብሔር❤️
----------------------------
👇👇👇👇👇👇👇👇
👉 @rituaH @rituaH 👈
👉 @rituaH @rituaH 👈
👉 @rituaH @rituaH 👈
👆👆👆👆👆👆👆👆
"+" ለመዳን ምን ያስፈልገናል?"+"

እባክዎን ለሌሎችም ያጋሩት

1.እምነትና ሥራ በምድር ላይ ጊዜ ላለው ሰው ለመዳን እኩል ያስፈልጉታል፤ ምክንያቱም መዳናችን በእርግጠኝነት እጃችን የሚገባው በመጨረሻው የፍርድ ቀን መሆኑን መረዳት ( 1ጴጥ1፡5)
2. መዳናችን ዕለት ዕለት በጎ ፈቃዱን በመፈለግና በማድረግ የምንፈጽመው (ፊሊጵ . 2፡ 12 -15) ፣ በመከራ በመጽናት በቆምን ቁጥር የምንቀበለው መሆኑን መረዳት ( 1ጴጥ. 1፡ 7 -9) ፣
3. እምነት ያለ ሥራ እንደ ሰርዴስ ቤተክርስቲያን ሥም ያለን ሙቶች እንደሚያደርገን መገንዘብ ( ራዕ . 3፡1-2) ፣
4. የመጨረሻቀው ፍርድ ለአማኞች በሥራ ( 1ጴጥ. 1፡ 17 ፤ 2ቆሮ . 5፡ 10 ፤ ማቴ. 25፡ 31- 46፤ ዮሐ 5፡ 28 -29) ላላመኑ ደግሞ በእምነትና በሥራ ማለትም የሕይወት መጽሐፍንና የሥራ መጽሐፍትን በመግለጥ እንደሚሆን መረዳት( ራዕ . 20 ፡11-15 ) ፣ አንደበትና ሀሳብ ለገሀነም ሊዳረጉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል( ማቴ. 12፡ 35- 37፤ ያዕ . 3፡ 6፤ ሮሜ. 2፡ 1-6)፡፡
5.ስለዚህ፣ ሕይወትን
የሚወድ፣ መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ ምላሱን ከክፉ፣ ከንፈሮቹንም ተንኮል ከመናገር ይከልክል፡፡ ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይፈልግ ይከተላትም ( 1ጴጥ 3፡10-11) ፡፡ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶአልና፡፡ እንግዲህ ፍርድ የሚጀምረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን ? እንግዲህ፣ ጻድቅ የሚድነው በጭንቅ ከሆነ፣ ዐመፀኛውና ኃጢአተኛው እንዴት ሊሆን ይሆን ? ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ነፍሳቸውን ለታነመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ ( 1ጴጥ 4፡ 17 -19 ) ፡፡
6. እምነትነታችን መታተም አለበት ይህን ማለት እምታችንን የምናረጋግጥባቸውና ከእግዚአብሔር ጋር አንድ
የሚያደርገንን ነገር መፈጸም አለብን፡ እነዚህም  ጥመቀትና መንፈስ ቅዱስን መቀበል ናቸው ፤ከውሃና ከመንፈስ መወለድ ማለት ነው ። ዮሐ 3፤5 እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና
ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ
አይችልም።  ቲቶ 3፡5 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት
በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን  ማር 16፤16 ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል እንዳለ ያለ ጥምቀት ድህነት የለም።  በቤተ ክርስቲያን
መንፈስ ቅዱስን መቀበል በሜሮን ይፈጸማል። ሜሮን ቃሉ የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም ቅብእ ማለት ነው።  ቤተ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን በሜሮን አማካኝነት መስጠት የጀመረችው
በሐዋርያት ዘመን ነው። 1ኛ ዮሐ 2፤20 እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እንዲሁም 1ኛ
2፤27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።
 ዘጸ 30፡22-25 ምስጢረ ሜሮን ምሳሌው በብሉይ ኪዳን
ነበረ፡ የብሉይ ኪዳን ንዋያተ ቅዱሳት ይቀቡ ነበር
7. ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን አለብን፡ ሰው ለመዳን ከክርስቶስ ጋር ህብረት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በዮሐ 6፤56 ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ዮሐ 6፡54 ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥
8. ላለመሰናከል፣ ፍሬ ቢስ እንዳንሆን፣ መመረጣችንን እና መጠራታችንን በማጽናት በሙላት ወደ መንግሥቱ ለመግባት ከፈለግን ትጋትን፣ በጎነትን ፣ ዕውቀትን፣ ራስን መግዛትን፣
መጽናትን ፣ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ ወንድማዊ መተሳሰብን እና ፍቅርን በእምነታችን ላይ መጨመር ግድ የሚል መሆኑን መረዳት ይገባል ( 2ጴጥ. 1፡ 511 ) ፡፡

👉 ማብራሪያ:-ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም ማንም እንዳይመካ ከስራ አይደለም ›› ኤፌ2፡8 ይህን ማለቱ በቸርነቱ በእምነት ድነናል ፡፡ያዳነንም እግዚአብሔር በቸርነቱ ነው ፡፡ይህ
ድኅነት ለሰዎች ሁሉ በመስቀል ላይ የተፈፀመው በእግዚአብሔር
ቸርነት እንጂ በማንም ስራ አለመሆኑን ይገልጻል ኤፌ 2፡ 4፤ሮሜ4፡4-5 ይህንንም ጸጋ ቸል ልንለው አይገባም ይሁ4 በዚህ በቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ክፍል ውስጥ ሰው የዳነው
በራሱ ስራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስጦታ /ጸጋ/እና ቸርነት በኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ቤዛነት ነው ፡፡ይህ ማለት ግን ለመዳን ስራ አያስፈልግም ማለት ሳይሆን አዳም ካመጣብን በደል እና ኃጢአትየምንድነው ነጻ የምንወጣው በስራችን አይደለም ይህም በእምነት መዳንን የሚያሳይ ሲሆን ‹‹በእምነት
ብቻ መዳን›› ከሚለው ሀሳብ እና አስተምህሮ ይለያል፡፡ አንድ ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ አምኖ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው የማዳን ጸጋ በምስጥራቱ አማካኝነት/በምስጢረ ቁርባን እና በምስጢረ ሜሮን እንዲሁም በምስጢረ ጥምቀት/
ይደርሰዋል ይህም ለመዳን የሚያደርገውን ጉዞ ጸጋው ያግዘዋል
ለመዳናችን ከእግዚአብሔር የሚጠበቀው ነገር ሁሉ የተፈጸመ
ሲሆን ከእኛ የሚጠበቅ ነገር እንዳለ ሳያል ፡፡ ማቴ 25:14-46 በዚህ ምዕራፍ ክርስቶስ በ 2 ምሳሌዎች ለሚያምን ሰው መዳን በስራ እንደሆነ ያስረዳበት አንቀጽ ነው!
እነዚህም ምሳሌዎች
1ኛ)ለመዳን በዚህ ምድር ምን ማድረግ እንዳለበን በ3ቱ መክሊት ተቀባይ አገልጋዮች ሲናገር (25:14-30)...
2ኛ)ጌታ በሰማይ ምን ብሎ እንደሚጠይቀንና መንግስቱን ለመውረስ ምን እንደሚጠበቅብን ይናገራል
(25:31-46):: ብዙ ሰዎች እንዴት ነው የዳነው? እና እንዴት ነው የምንድነው?የሚሉትን ጥያቄዎች ባለመረዳት የአንዱ መልስ ከሌላው ጋር ሲደባልቁ እናያለን! ከዚህ አልፈውም መዳን በእምነት ብቻ ነው;፣ ሰው በስራ አይድንም በማለት የሚባክኑም
አልጠፉምና እውነቱን እንገልጥ ዘንድ ወደድን!
1)እንዴት ነው የዳነው? ይሄ ጥያቄ ክርስቶስ ከሰማያት ወርዶ እንዴት እንዳዳነን የሚያጠይቅ ነው:: ክርስቶስ ወደኛ የመጣው እኛ ወደርሱ መሄድ ስላቃተን ነው! ሊያድነን የመጣው በራሳችን መዳን ስላልቻልን ነው! ስለዚህም እንደ ጸጋው ስጦታ አዳነን! ያዳነውም በርሱ ያምኑ የነበሩትን 120 ሰዎች ብቻ አልነበረም! ዓለሙን ሁሉ እንጂ! ...

👉 ታድያ ከምን አዳነን?
1)ከአዳም መርገም
2)ከዲያብሎስ ባርነት
3)የተዘጋችውን ገነት በመክፈት

👉 .... አሁን ክርስቲያን ቢሆን አሕዛብ ጥንተ አብሶ ይዞ የሚወለድ የለም! የዳንነው በእምነታችን አይደለም! እንዲያ ቢሆንስ ኖሮ የእምነት አባታችን አብርሃም በዳነ ነበር! በምግባራችንም አይደለም! ነቢያት ሁሉ መዳን ይችሉ ነበረና! ሁሉም እምነታቸውና ምግባራቸው ከንቱ ሆነ! ያድናቸውም ዘንድ ልዑል ክንዱን ላከ! ስለዚህም የዳንነው በጸጋው ብቻ ነው!! በቸርነቱ ብቻ!! ግን አሁን ድነናል በማለት መቀመጥ አለብን? አይደለም!
የሞተልንን ጌታ በማመን፣ ያደረገልንም ውለታ እያሰብን፣ በእምነት ተመስርተን በምግባርም ጸንተን ፊልጵ 2:12 ....
ታድያ አሁን በክርስቶስ ጸጋ ከዳንን አሁን ለመዳን ምን እናድርግ?...

👉 2)እንዴት ነው የምንድነው?... ይህ፣ አሁን ሁላችንም መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ነው! ለመዳን ከኛ ምን ይጠበቃል? ምን ብናደርግስ ነው መንግስቱን የምንወርሰው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማም የዚህን ጥያቄ መልስ ማብራራት ነው! ሰው ለመዳን ወይም መንግስቱን ለመውረስ 2 ነገሮች
ያስፈልጉታል!
1)ማመን:- ይሄም ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ፣ ስለ ዓለም ኃጢአት እንደሞተና እንደተነሳ፣ አሁንም በመንበሩ
ተቀምጦ እንደሚፈርድና ሊያድነንም የታመነ እንደሆነ አምኖ መቀበል ማለት ነው! 1ዮሐ5:12 በክርስቶስ ያላመነ ሁሉ አሁን ተፈርዶበታል! ይፈረድበታልም!.

👉 2)መልካም ምግባር:-የሚያምን
ሰው የሚያምነውን በስራ እስካልገለጠ ድረስ እምነቱ የሞተ ነው! (ያዕ2:17)... መልካም ስራ የማያደርጉ ሰዎች ደግሞ
የእግዚአብሔር መንግስት አይወርሱም (ገላ5:21) ወዳጄ ሆይ በጎና ታማኝ አገልጋይ ተብሎ የተሸለመው በእምነቱ ነው ወይስ በምግባሩ? የዳነውስ ስላመነ ነው ወይስ ስለታመነ? በጥቂቱ
ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ የተባለ አይደለምን? (ማቴ25:23)
ደግሞስ ክፉና ሃሰተኛ ባርያ ተብሎ ወደ እሳት(ሲኦል) የተጣለው ሰው እምነት ስለጎደለው ነው ወይስ ምግባር
ስላልነበረው?....

👉 ጌታ በሰማይ ምን ብሎ እንደሚጠይቅህ ታውቃለህን? በእኔ ስላመንክ ደስ ይበልህ ይለሃል? ወይስ
ምግባር ስላለህ ደስ ይበልህ የሚልህ ይመስለሃል? መንግስቱን የሚወርሱትስ ሰዎች እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ
አጠጥታችሁኛልና... የሚላቸው አይደለምን? ወደ እሳቱ የሚጣሉት ሰውችን ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና... አላልቸውምን?
ማቴ 25 :31.... በዚህም እምነት ያላቸው ክርስቲያኖች በስራ
እንደሚድኑ አረጋገጠ!
ይቆየን
ምንጭ ዲ/ን ሸዋፈራው አለነ
"+" እምድርሳነ ርቱዓ ሃይማኖት በእንተ ሞቱ ለእግዚእነ"+"

በብዕር ስሙ “ርቱዓ ሃይማኖት” በመባል የሚታወቀውና በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ኢትዮጵያዊ ሊቅ የጌታችንን ሞት አስመልክቶ በደረሰው ድርሳኑ እንዲህ አለ፡
- ጌታዬ ሆይ፡ በመስቀል ላይ ተሰቅለህ መሞትህን ሳስብ አለቅሳለሁ፤ የመስቀልህ ጥላ ሙታንን እንዳስነሳ ሳስብ ደግሞ አደንቃለሁ።
- መስቀሉ ላይ ራስህን ዘንበል ማድረግህን አስባለሁ፤ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሄደህ፡ የብረት ሰንሰለቶችን ፈትተህ፡ አዳምንና ልጆቹን ወደ ርስታቸው ወደ ገነት በመመለስህ እደሰታለሁ።
- ነፍስህ ከሥጋህ መለየቷን አስቤ አለቅሳለሁ፤ በቀኝህ ለተሰቀለው ወንበዴ ለ5533 ዓመታት ተዘግታ የነበረች ገንትን በመክፈትህ ደግሞ እደሰታለሁ።
- በመስቀል ላይ በችንካር መችንከርህን ሳስብ አለቅሳለሁ፤ ፀሐይ በመጨለሟ ደግሞ እደነግጣለሁ።
- መስቀል ላይ ዕርቃንህን ሳይህ አለቅሳለሁ፤ ቀኑ ጨልሞ ሌሊት መሆኑን ሳስብ ደግሞ አደንቃለሁ።
- ራስህን እየመቱ “ክርስቶስ ሆይ ትንቢት ተናገር” ማለታቸውን ሳስብ አለቅሳለሁ፤ እልፍ አዕላፍ የሚሆኑ ቅዱሳን መላዕክት፡ “ቅዱስ እግዚአብሔር፡ ቅዱስ ኃያል፡ ቅዱስ ሕያው የማይሞት፤ በዕፀ መስቀል ላይ የተሰቀለ” እያሉ በመስቀልህ ዙሪያ ተነጥፈው ማመስገናቸውን ሳሰላስል ደግሞ ሐሴት አደርጋለሁ።
- በሰፍነግ ሐሞት እንዳጠጡህ አስቤ አለቅሳለሁ፤ ከጎንህ ደምና ንጹህ ውሃ ወጥቶ፡ መስቀልህ ሥር ያለውን ዓለት ሰንጥቆ የአዳም መቃብር መድረሱን ሳስብ ደግሞ እገረማለሁ።
- ፊትህ ላይ ምራቃቸውን በመትፋታቸው አለቅሳለሁ፤ ዕውር ሆኖ የተወለደውን፡ በምራቅህ መፈወስህን አስቤ ደግሞ እደሰታለሁ።
- የብረት ሰንሰለት በአንገትህ ከትተው መጎተታቸውን አስቤ አለቅሳለሁ፤ ሰይጣን ያሰራቸውን በቃልህ መፍታትህን ሳስብ ደግሞ አደንቃለሁ።
- በጲላጦስ ፊት ታስረህ መቆምህን አስቤ አለቅሳለሁ፤ በባህር ላይ እንደ ደረቅ መሬት መሄድህንና ነፍሳትን መገሰጽህን ሳስብ ደግሞ በእጅጉ እደነቃለሁ፡፡
- ሊቃነ ካህናቱ እና ሕዝቡ “ስቀለው፡ ስቀለው” እያሉ በመጮሀቸው አለቅሳለሁ፤ ነቢያት ያዩህ ዘንድ እንደተመኙ ሳስብ ደግሞ እገረማለሁ።
- በሁለት ወንበዴዎች መሃል መሰቀልህን አስቤ አለቅሳለሁ፤ በደብረ ታቦር በሙሴና በኤልያስ ፊት የመለኮትህ ብርሃን ማንጸባረቁንና የመንግሥትህ ግርማ መገለጡን ሳስብ ደግሞ እደሰታለሁ።
- መስቀልህን እስከ ቀራንዮ ድረስ በመሸከምህ አለቅሳለሁ፤ መጻጕዕን “ኃጢአትህ ተትቶልሀል፡ ተነስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ያልከውን አስቤ ደግሞ እደሰታለሁ።
- ሊቃነ ካህናቱ ሐና እና ቀያፋ “ደሙ በእኛና በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን” ማለታቸውን ሳስብ አዝናለሁ፤ ለ12 ዓመታት ደም ይፈስሳት የነበረችይቱን ሴት መፈወስህን ሳስብ ግን እደሰታለሁ።
- ይሁዳ በ30 ብር እንደሸጠህ ሳስብ አለቅሳለሁ፤ ጴጥሮስን ከዓሣ ሆድ ዲናር አውጥቶ ለሄሮድስ መልዕክተኞች ግብር እንዲከፍል ማዘዝህን ሳስብ ደግሞ አደንቃለሁ።
- መስቀል ላይ ሆነህ “ተጠማሁ” በማለትህ አለቅሳለሁ፤ በቃና ዘገሊላ ውሃን ወደ ወይን ጠጅ መለወጥህን አስቤ አደንቃለሁ።
- እናትህ ድንግል ማርያም ከዮሐንስ ጋር ሆና የመስቀል ስቃይህንና ሞትህን በማየቷ አለቅሳለሁ፤ መልአኩ ገብርኤል “ካንቺ በመንፈስ ቅዱስ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም” ያላትን አስቤ ደግሞ እደሰታለሁ።
- ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ለመግነዝህ የሚሆን በፍታ መግዛታቸውን አስቤ አለቅሳለሁ፤ በታቦር ተራራ ላይ ልብስህ በሚያንጸባርቅ መልኩ ነጭ እንደነበር ሳስብ ደግሞ እደሰታለሁ።
- ሥጋህን ለመቅበር አዲስ መቃብር መፈለጋቸውን ሳስብ አለቅሳለሁ፤ አልአዛርን ከ4 ቀናት በኋላ ከመቃብር አውጥተህ በማስነሳትህ ደግሞ እደሰታለሁ።
- መራራ ሐሞት እንዳጠጡህ አስቤ አለቅሳለሁ፤ በ5 እንጀራ 5000 ሕዝብ ማጥገብህን ሳስብ ደግሞ እደነቃለሁ።
- መቃብርህን በታላቅ ድንጋይ መዝጋታቸውን አስቤ አለቅሳለሁ፤ በመሰቀልህ ምክንያት መላዋ ምድር በመናወጿ ደግሞ እገረማለሁ።
- ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንደገነዙህ አስቤ አለቅሳለሁ፤ በልደትህ አህያና ላም በትንፋሻቸው እንዳሟሟቁህ አስታውሼ ደግሞ እደነቃለሁ።
- በከርሠ መቃብር ማደርህን አስቤ አለቅሳለሁ፤ መስቀል ላይ ሳለህ ጎንህን በጦር የወጋውን ወታደር፡ የታወረችውን አንድ ዓይኑን ከጎንህ በፈሰሰው ደም መፈወስህን እያሰብኩ አደነቃለሁ።
- ባጠቃላይ፡ የመስቀል ስቃይህን አስቤ በእጅጉ አለቅሳለሁ፤ በቀኝህ የተሰቀለውን ወንበዴ፡ “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” በማለትህ ደግሞ እደሰታለሁ።
†††
ክርስቶስ ፍቅሩን በልቦናችን ይሳልብን

"+"ወስብሐት ለእግዚአብሔር"+"
@rituaH @rituaH
"+" የማለዳ ጸሎት "+"

የጊዜያት ባለቤት እግዚአብሔር አምላክ ሆይ የጨለማውን ግርማ ገፈህ ብርሃንህን እንድመለከት ስላደረከኝ አመሰግንሃለሁ ። በመኝታዬም ሰለጠበከኝ ከሞት ስለሰውርከኝ እጅ መንሳቴን አቀርባለሁ።
ቸር እረኛዬ ትጉህ የማታንቀላፋ ነህና ሌሊቱን ከእኔ ጋር ሆነህ እንደጠበከኝ ይህንን ማለዳ ባርከህ ቀድሰህ የሰላም ውሎ እንድውል ቀኝህ ትርዳኝ መንገዴን ሁሉ ከፊቴ እየሆንክ ምራኝ ከደካማ ፍጡርነቴ የተነሳ በአላማዬም ምን እንዳለ አላውቅምና አንተ ጠብቀኝ በዙሪያዬ ሁሉ ጠላት ያስቀመጠብኝን እንቅፋትና መሰናክል አስወግድልኝ በመልካም እሴቶች አስጊጠኝ ከፈተና የተነሳ እንኳን ብወድቅ አንሳኝ እንጂ አትተወኝ አንተ ያልከው ይሆን ዘንድ የግድ ነውና በከንቱ ከመጨነቅና ከመተከዝ ተስፋም ከመቁረጥ ሰውረኝ ለዘለዓለሙ አሜን ወአሜን፡፡
..አቡነ ዘበሰማያት፡፡
"+" ስለ ጽድቅ የሚስደዱ ብጽዓን ናቸው፡፡ ሜቴ 5፥10 "+"
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በክርስቶስ ክረስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊያን የተሰችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የድንግል ማርያም የአሥራት የበረከት ልጆች በወደደንና በመረጠን በአምላካችን በልዑል እግዚአብሔር ሰላምታ እንደምን ሰነበታችሁ አመላካችን ቢወድና ቢፈቅድ ወቅቱን በተመለከተ ስብከት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ የምናስተውሉበትን ልቦና ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ መንፈሱን ለሁላችን ያድለን፡፡
ቃሉን የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንቀጸ ብፁዓን ተብሎ በሚጠራው በተራራው ስብከቱ ነው፡፡ የቃሉን ፍቺ ስንመለከት ስለ ጽድቅ የሚስደዱ ብፁዓን ናቸው ማለት ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣መንግሥት፣ በረከት፣ ረድኤት ብለው ከትውልድ ሀገራቸው ተለይተው ከከተማ ከሕዝብ ርቀው በምድር የላመ የጣመ ምግብ ሳይመገቡና ሣይጠጡ ለቁመተ ስጋ ብቻ ያገኙትን ቅጠል የሚመገቡ ይህችን ዓለም የጠሉ አባቶች እናቶች እነሱ የተመስገኑ ቅዱሳን፣ የተመረጡ ቡሩካን፣ የተለዩ ምስጉኖች ማለት ነው፡፡
1.1 ስደት መቼ ተጀመረ ?
በዓለመ መላዕክት ነው፡፡ እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ ከፈጠራቸው ከሰባቱ ሥነ-ፍጥረታት ውስጥ መላዕክት ናቸው፡፡ ከፈጠራቸው በኋላ የተሰወረባቸውም የእርሱን አምላክነት ምሀሪነት ሁሉን ቻይነቱን ይረዱ ያውቁ ዘንድ ተሰወረባቸው፡፡ የመላእከት አለቃ የነበረ ሳጥናኤል እኔ ፈጠርኳችሁ በማለት ብዙዎችን አሳተ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሚካኤል ሃይማኖታችንን እስከ ምናውቀው ባለንበት እንቁም(ንቁም በበህላዊነ እሰከ ንረክቦ ለአምላክነ) ብለው መላዕክትን አጽናኑ፡፡ ሳጥናኤልና ከሰማይ ወደዚህ ዓለም(ምድር) ተሰደዱ ስደትም በእዚያን ጊዜ ተጅመረ፡፡
1.2 ሰዎች የሚሰደዱበት ምክንያት
ሀ/የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላለፍ፡- የሁላችን አባት አዳም አትበላ ተብሎ ከተከለክለው ከዕፀ በለስ በመበላቱ ገነት ከሚያህል ቦታ እግዚአብሔርን ከመሰለ አምላክ ተሰደደ፡፡ ዘፍ 3፥8
ለ/ረሀብ ቸነፈር ሲመጣ ፡- አንደ አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ በሀገሩ ለአመስት ዓመት ረሀብ ሆነ እግዚአሔርም ያዕቆብን በሕልም አነጋገረው ወደ ግብፅ ሀገር ሂድ ብሎ ነገረው እርሱም ተሰደደ ዘፍ 46፥11
ሐ/የሰውን ነፍስ በማጥፋት የሚሰደዱ ፡- ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ አደገ ወደ ወንድሞቹም ወጣ መከራቸውንም ተመለከተ የግብፅ እና አንድ ዕብራዊ ሲጣሉ አገኛቸው ለዕብራዊውም በማገዝ ግብፃዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ ቀበረው፡፡ በሁለተኛ ቀንም ወጣ ሁለት ዕብራዊያን ሲጣሉ አየ ሙሴም በዳዩን ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ አለው፡፡ ወንደሙን ሚበድለውን ያም ሰው በእኛ ላይ አንተን አለቃ ዋስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብጻዊውን ትናንት እንደገደለኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው፡፡ሙሴም በእውነት ይህ ነገር ታውቆአልን ብሎ ፈራ፡፡ ፈርዖንም ይህን ነገር ሰማ ሙሴንም ሊገለው ፈለገ ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ በምድያም ምድር ተቀመጠ፡፡ ዘጸ 2፥11-16
መ/ለሰው ልጆች ሰላም አብነት ለመሆን የሚሰደዱት ስደት ነው፡፡ ይህ ስደት የጌታችን እና የእመቤታችን ሰደት ነው፡፡ ሰለ ጌታችን እና ሰለ እመቤታችን ሰደት ከመነጋገራችን በፊት ስለ ጌታ ልደት ትንሽ ልበል ጌታችን በቤተልሔም ሲወለድ ቤተልሔም በእሳት አጥር ታጠረች አጋንንትም ሄደን እናያለን ብለው ቢቀርቡ የብርሃን መላዕክት በእሳት ፍላጻ እያቃጠሉ ሊያስቀርቧቸው አልቻሉም፡፡ አጋንንትም ለአለቃቸው ለዲያብሎስ ነገሩት ዳያብሎስም በትዕቢት በኪሩቤል አምሳል 4 ተሸካሚዎችን አዘጋጅቶ ተሸክመውት ቤተልሔም ደረሱ ወደ ጌታም መቅረብ አልቻሉም፡፡ ከዚች ሰዓት ጀምሮ ዲያብሎስ በስልጣኔ ላይ ችግር የፈጠረብኝ ማነው? ብሎ ፈርቶ እየተንቀጠቀጠ ለአጋንንት ከእኔ የሚሰወር የለም ዓለምን ዙሬ ነገሩን መርምሬ ውጤቱን እስክነገራችሁ ታገሱኝ አላቸው፡፡ ሁሉን ቦታ አሰሰ ግን አልቻለም፡፡ መጨረሻ ላይ እነድህ በማለት ተናገረ አስከ ዛሬ ድረስ ከተሰራው ታአምር የሚበልጥ ታላቅ ተአምር ነው አለ ፡፡ ነቢያት ስለ እርሱ ትንቢት የተናገሩለት በቤተልሔም ተወልዶ ከሆነ መንግሥቴን እነደሚቀማኝ አልጠራጠርም እያለ ተጨነቀ አሁንም ኑ ሄደን ጠይቀን እንረዳ ብሎ ሠራዊቱን ይዞ ወደ ቤተለሔም መጣ እረኞች እና መላዕክት በአነድነት ‹‹በሰማይ ለእግዚአበሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ለሰው የሰላም መሠረት ተጣለ›› እያሉ ሲያመሰግኑ ሰምቶ ደነገጠ ፡፡ ሉቃ 2፥12-16
ጌታ ሰለመወለዱ ይነግሩት ዘንድ የእስራኤል የኦሪት ምሁራንን አነሳስቶ ጌታ ከድንግል እስኪ ወለድ ድረስ አትሞትም በአልጋ ላይ ተጣብቀህ ትኖራለህ ተብሎ ከእግዚአብሔር መላዕክት ትንቢት ወደ ተነገረለት ወደ ካህኑ ስምዖን ሄደው ስምዖን ሆይ አንተ ተስፋ የምታደርገው የዓለም መድኃኒት የሆነው ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጫው ደርሷን? በማለት ጠየቁት፡፡ ስምዖንም አዎን መምጫው ደርሷልን አላቸው እርነሱም ጊዜው መድረሱን በምን አወቀህ? አሉት ሰምዖንም ቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ 7፥14‹‹ ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች በድንግልናም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች›› ፡፡ ተብሎ የተነገረውን ትንቢት ተጠራጥሬ ነበር እና ታስሮ የነበረው እጁ ሰለተፈታ መወለዱን በዚህ አውቃለሁ አላቸው፡፡
ሰይጣንም የእስራኤልን የኦሪት ምሁራንን ቆሞ ይሰማ ነበርና ፈጽሞ ታወከ የተንኮል ባሌቤት የሆነው ዲያብሎስም በሄሮድስ ልቡና አድሮ ሄሮድስ! የእኔንና የአንተን ስልጣን የሚቀማን ንጉሥ ተወልዷልና ከተወለዱ 2 ዓመት እና ከእዚያም በታች እደሜ ያላቸውን ሕፃናትን አስገድላቸው አለው፡፡ ሉቃ 2፥25-27 ጌታችን፣ አመቤታችን ፣ሰሎሜ እና ቅዱስ ዮሴፍ ወደ ግብፅ ተሰደዱ፡፡ ‹‹የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሳ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እሰክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ›› ማቴ2፥13 የሰላም ባሌቤት አምላካችን ለእኛ ሲል የግብፅን በረሃ እንደ ጋለ ብረት የሚያቃጥለውን አሸዋ እየረገጠ አሳቹን ዲያብሎስን ረጋግጦ ከእግራችን በታች ጣለልን፡፡ በእርሱ ስደት የእኛ ስደት ተባረከልን ተቀደሰልን፡፡ ፍጥረታት ሁሉ በመንቀጥቀጥ የሚሰግዱለት እነግሣለው አይል ንጉሥ በሄሮድስ ተሰደደ፡፡
1.3 የጌታችንና የእመቤታችን መሰደድ ምክንያቶች(ነጥቦች)
1/ የአዳምን የ5500 ዓመት ስደት ለመሰደድና ለመባረክ ነው ፡፡
2/ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደግጽ ይመጣል ፣የግብጽ የእጆቻቸውን ስራውች በፊቱ ይዋረዳሉ ››፡፡ ኢሳ 19፥1 ከግብጽ መመለሱን አስመልክቶ የተነገረውም ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው ፡፡ ‹‹ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት ›› ፡፡ሆሴ 11፥2 አንሁም ከግብጽ ወደ ናዝሬት ሄደ ናዝራዊ ይባል ዘንድ ወደ ናዝሬት ሄደ፡፡ ‹‹በኒቢያት ልጄ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ናዝሬት ወደ ምትባል ከተማ
3/ ጌታ ባይሰደድ ሕፃናቱ ሲገደሉ እሱ ከሞት ቢተርፍ ትስብእቱ (ጌታ ሰው መሆኑ) ምትአት ነው ብለው እንዳይሰናከሉ ነው ፡፡
4/ አበነት ለመሆን ለጻድቃን ለሰማዕታት ሰደት ለመጀመር እና የእነሱንን ሰደት ለመባረክ ለመቀደስ ነው፡፡ ሰማዕትነት በሰይፍ መቀላት በእሳት መቃጠለ በመጋዝ መተርተር ብቻ አይደለም ዓለምን ንቆ ወደ ምድረ በዳ መሰደድም ሰማዕትነት ነው፡፡
ዕብ 11፥37-38 በመጋዝ የሰነጠቁአቸው በድንጋይ የወገሯቸውን በሰይፍም ስለት የገደሉአቸው አሉ ማቅ፣ ምንጣፍና ሌጦ ለብሰው ዞሩ፣ ተጨነቁ፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናችው፡፡ ዱር ለዱር ተራራ ለተራራ
፣ ዋሻ ለዋሻ ፈርኩታ ለፍርኩታ ዞሩ፡፡
5/ የጌታችን የእመቤታችን መሰደድ የቅዱሳን ሰደት ተባርኮላቸዋል የሕይወት እርካታን አገኝተዋል፡፡ጌታችን በስጣ በምትባል ሀገር እመቤታችን ውኃ እና ቁራሽ እንጀራ ለመነች የሚሰጣት አንድም ሰውም አላገኘችም ሁሉም አባረሯት፡፡ ጌታችን በዓለት ላይ በመስቀል አምሳል ባርኮ ውኃን አፈለቀ ይችም ውኃ ሁለት ጠባይ ሆነች በእዚያች ሀገር ለሚኖሩ ሰዎች መራራ ከሩቅ ለሚመጡ ነጋደውች ከማር የበለጠች ጣፋጭ ሆነችላቸው፡፡ የሕይወትን ውኃና ምግብን ዳግመኛ የማያስርበውን የሚሰጠውን ጌታችን ከለሉት እነዚህ ሰዎችም 2 ጠባይ ካላት ጠጥተው መረራቸው፡፡ራዕ 21፥6-7 ‹‹ባለማውቅ ጠጥተው ዳግመኛ የሚያስጠማውን ውኃ የዚች ሀገር ሰዎች ከለከሉት››
እርስ በእረሳችን እንከባበር እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ እንሠራ ርኅራኄን በጎነትነን ሀበቶቻችን እናድርጋቸው በረከትን ለማገኘት እግዚአብሔርን እንፈልገው ት.ሶፎ 2፥3 እግዚአብሔርን ፈልጉ ፍርድንም አድርጉ ጽድቅንም ፈልጉ፡፡ ዕብ 12፥4 ‹‹ኃጢአትን ተጋደሏት አሸንፏትም ፣ተስፋችሁንም የምታሰጣችሁን ትምህርት ውደዷት››፡፡
- ‹‹ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች ››ት..ሕዝ 18፥4
<<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>>
@rituaH @rituaH @rituaH
"+" ጥቅምት 27 - እንኳን ለቸሩ መድሀኒዓለም አመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ፡፡"+"

"እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም፡ ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር"
እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የነበረ የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ኢየሩሳሌም ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ መድኃኒትን አደረገ ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት /መዝ. 73፡12/

ይህ በመጋቢትና በጥቅምት 27 ቀን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት የምናከብረው በዓላችን ዓመተ ፍዳው፤ ዓመተ ኲነኔው አክትሞ የሰው ዘር የሆነው ሁሉ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት፣ ከሲኦል ወደገነት፣ የተመለሰበትና የተሸጋገረበት ዕለት መሆኑን ለማዘከር ነው፡፡ አዳም በሥላሴ አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተጎናጽፎ ነጻ የኅሊና ፈቃድ ያለው ሰው ሁሉ ገነትን ያህል ቦታ ይዞ ሥዩመ እግዚአብሔር፡ ነቢየ እግዚአብሔር፣ ካህነ እግዚአብሔር ሁኖ ለሰባት ዓመታት በስነ ሥርዓት በገነት ይኖር ነበር፣ ይሁንና እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ሆነ /ዘፍ. 1፡31/ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደምንረዳው እግዚአብሔር አምላካችን በስድስቱ ቀናት የፈጠረው ሁሉ መልካም ሲሆን በተለይም በሥላሴ አርአያና አምሳል ለተፈጠረው ሰው የሕይወት እስትንፋስን ሰጥቶ በገነት በሕያውነት እንዲኖር ያስቀመጠው የከበረ ክቡር ፍጡር ነበር፡፡ "ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፡፡

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ አድርጎ ቢፈጥረውና የጸጋ ገዥ ቢያደርገው ያልተሰጠውን የባህርይ አምላክነትን በመፈለጉ የገዥና የተገዥ፣ የፈጣሪና የፍጡር መለያ የሆነውን ትእዛዘ እግዚአብሔርን በመጣሱ በዚህ ምክንያት ሞተሥጋ፣ ሞተ ነፍስ ተፈረደበት፡፡ ከክብሩ ተዋርዶ ከገነት እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ተመልሶ ወደገነት ገብቶ ተጨማሪ ኃጢአትን እንዳይሠራም ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ሜሎስን በእጃቸው የያዙ ኪሩቤልን በኤደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ ይላል የሙሴ መጽሐፍ፡፡ /ዘፍ. 3፡22-24/

አዳም ሳይቸገር በጠላት ከንቱ ስብከት እንደእግዚአብሔር ለመሆን ክፉውንና ደጉንም ፈጥኖ ለማወቅ ቸኩሎ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱ ወደቀ፣ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡ በሰው ሕይወት ላይ አሳፋሪ፣ አስፈሪና አስነዋሪ ታሪክ ፈጸመ፡፡ አዳም እግዚአብሔር አታድርግ ያለውን የአምላኩን ትእዛዝ በማፍረስ የሞተ ሞት ተፈረደበት፡፡ ከዚህ አሳፋሪና አስፈሪ ታሪክ በመነሣት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለሞት ማሰብ ለማንም ሰው ቢሆን ቀላል ነገር አልሆነም፡፡ ያ ሰው የኖረው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ የሁሉ እድል ፈንታ በሆነበት ጊዜ ነበርና ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞተ ከእርሱ በኋላ ፍርድ ተመደበባቸው ይላል፡፡ ዕብ. 9፡27

ነቢዩ ሕዝቅኤልም እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፣ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች፣ ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፣ ኃጢአትየምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች፡፡ /ሕዝ. 18፡4/ በማለት የዚህን ማስጠንቀቂያ፣ ኃይለኛነትና ጥብቅነት ያሳያል፡፡ በቀል የእኔ ነው እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና ደግሞም ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል፣ በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅም የሚያስፈራ ነው ያላል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ /ዕብ. 10፡30-31/፡፡

ስለዚህ፣ ሞት፣ የኃጢአት ዋጋ ሆኖ በኃጢአት ምክንያት የመጣ ቢሆንም በኃጢአት ላይ የተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ /ቅጣት/ ባለመሆኑ ከሞት በኋላ ሌላ ፍርድ የሚጠበቀን መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ይሁንና ቀዳማዊ አዳም በስህተቱ ተጸጽቶ በማዘኑ፣ በማልቀሱና ንስሐ በመግባቱ ለቸርነቱ ወሰን የሌለው አምላክ ንስሐውን ተቀብሎ የተስፋ ቃል ሰጠው፡፡ የተሰጠውም የተስፋ ቃል አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋዬን ቆርሼ ደሜን አፍስሼ አድንኅለሁ የሚል ነበር፡፡ ይህ የተስፋ ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ፣ ትንቢት ሲነገር ሱባኤ ሲቆጠር ኖሮ አምስት ሺህ አምስት መቶ የተስፋው ዘመን ሲፈጸም የተናገረውን የማይረሳ፣ የሰጠውን ተስፋ የማይነሣ እግዚአብሔር "ክርስቶስኒ መጽአ በዕድሜሁ ይሙት በእንተ ኃጢአትነ እንዘ ኅጥአን ንሕነ" /ሮሜ. 5፡6/ ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ጊዜው ሲደርስ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ኃጢአት ሊሞትመጣ፣ ሰው ሆነ በሥጋም ተወለደ፣ በተወለደ በ30 ዘመኑ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ጾመ፣ በሰይጣን ተፈተነ፣ ፈታኙ ሰይጣንም ባቀረበው ፈተና ድል ተመታ፣፣

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን የጀመረው በጥምቀት፣ በጾም በጸሎት በትምህርት በተአምራት ሲሆን ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት በይሁዳ፣ በሰማርያና በገሊላ አውራጃዎች በቅድስት ሀገር እየተዘዋወረ ወንጌልን አስተማረ፡፡ ትምህርቱ እየሰፋና እየተዳረሰ ሲሔድ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ለሕማም፣ ለሞት፣ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ተሰቀለ፣ በሥጋ ሞተ፣ ተቀበረ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ውሎና አድሮ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ሞትን ድል አደረገ፡፡

ስለሞተ ነፍስና ሞተ ሥጋ ብዙ ተብሏል፣ እየተባለም ነው፣ እነዚህ ሁለቱም በመጀመሪያው ሰው፣ ሕግ ተላላፊነት በአንድ ወቅት በሰው ሕይወት ላይ የደረሱ አሳዛኝ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ለማለት እንደሞከርነው በመጀመሪያው ሰው ሕግ ተላላፊነት ሞተ ነፍስና ሞተ ሥጋ በዚህ አጋጣሚ ሁለቱም በዚያን ጊዜተያየዘው የመጡ ሲሆን ሞተ ነፍስ በ34 ዓ.ም በማዕከለ ምድር ቀራንዮ በስግው ቃል ሞተ ሥጋ አክትሞለት ሁሉም የአዳም ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት፣ ከሲኦል ወደ ገነት ተመልሷል፣ ይሁንና ሞተ ሥጋው የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ትንሣኤ ዘጉባኤን በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በዚያን ጊዜ ሞተ ሥጋውም ያከትምለታል፡፡ በዚያን ጊዜ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ፣ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል አናት ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ የሚል በእብራይስጥ በፅርዕና የሮማይስጥ ተጽፎና ተለጥፎ ይነበብ ነበር፡፡ የእነዚህ የሦስቱ መንግሥታት የሥልጣን፣ የሥልጣኔና የጥበብ ኃይል በአንድነት ቢተባበሩም የክርስቶስን ኃይል ሊቋቋሙት አለመቻላቸው በግልፅ ታይቷል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት መደምሰሻ፣ የሰይጣን ድል መንሻ፣ የድኅነት ጋሻ ያደረገው መስቀል በክርስትና ሕይወት የላቀ ክብርና ቦታ ያለው ሆነ፡፡ሰውን በስቅላት መቅጣት የተጀመረው የፋርስ ባቢሎን እንደነበረ በታሪክ የሚታወቅ ሲሆን መስቀል ከዘመነ ሥጋዌ በፊት የወንጀለኞች፣ የኃጢአተኞችና የበደለኞች መቅጫ መሣሪያ መሆኑ የታወቀ ነበር፡፡ ጌታ በዚህ ዓለም በተገለጠበት ጊዜ በዓለም ግዛቱን አስፍቶና አስፋፍቶ የነበረው የሮሜው የቴሣሩ መንግሥት ይህን የስቅላት አሠራር ልምድ ከፋርስ ባቢሎን ወርሶ ምንም ዓይነት ኃጢአት ሳይኖርበት በኃጢአተኞች ይሙት በቃ የተፈረደበት ጌታችን፣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሰቀልላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ፍርድን ሰጠ፡፡
👇👇👇👇
👆👆#የቀጠለ..

ቅድስት ድንግል ማርያምን ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ የወሰዳት የሮማዊው የአውግስጦስ ቄሣር የሕዝብ ቆጠራ ትእዛዝ ሲሆን /ሉቃ. 2፡1-3/ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለውም የክርስቶስ ስቅላት የተካተተውም ሮማዊው እንደራሴ ጲላጦስ በሰጠው ትእዛዝና ፍርድ ነበር፡፡

እስከዚህ የተገለፀው መታቢያነቱን የምናከብረው በዓላችን የሰው ልጆች አባት የሆነው ቀዳማዊ አዳም በዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ፍርድ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የተመለሰበት፤ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዳዊት ከተማ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ልደቱ ጀምሮ እስከ ቀራንዮ ጎልጎታ ድረስ ለሰው ልጅ ያደረገውን ቸርነት የምናዘክርበት፤ ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኃኒችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የተሰጠ የደኅነት ጸጋ የተረጋገጠበት፤በዓለም ሁሉ ሰላም የወረደበትና ፍጡር ከፈጣሪው ፍጹም ሕይወትን ያገኘበት ዕለት ነው ብለን ነው፡፡

ስለዚህ ይህ ዕለት የሰላማችን፣ የደስታችንና የድል በዓላችን ስለሆነ በየዓመቱ በዝማሬ፣ በውዳሴና በቅዳሴ እናከብረዋለን፡፡ከዚህ ዕለት አድርሶ በዓላችንን ለማክበር እንዳበቃን ለሚመጣውም 2012 ዓ.ም አድርሶ ለማክበር እንዲያበቃን የእግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን፣ ድካማችንን ተቀብሎ ምሕረቱን፣ ቸርነቱን ያድርግልን፡፡እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከን ይቀድሰን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
+---+---+---+---+---+---+---+---+---+
@rituaH @rituaH @rituaH
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ለተሀድሶ መናፍቃን ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀው ጉባኤ በትናንትናው ዕለት በደ/መ/ቅ/ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተካሄደ:-

መምህር ምህረተአብ አሰፋ ተሀድሶ ማነው በሚል ርዕስ ያስተማሩ ሲሆን ትምህርታቸውን እንዲህ በማለት ነበር የጀመሩት:-
"+ጥሩ የሰበከ፣ ጥሩ የዘመረ ኢየሱስ ክርስቶስን በደንብ አድርጎ የሰበከ ሰው ተሀድሶ ነው አይደለም፤
+ጥሩ የዘመረ ሰው፣ በህዝብ ተቀባይነት ያለው ሰው ተሀድሶ ነው አይደለም፤
+ጥሩ ተናግሮ ማሳመን የሚችል ሰው፣ ህዝብ የተከተለው ሰው ተሀድሶ ነው አይደለም፡፡
በመጀመሪያ ተሀድሶ ማለት በራሱ ቤት ሳይሆን በሰው ቤት ውስጥ ገብቶ የሌላን እምነት ምንፍቅናን የሚያራምድ ማለት ነው እግዚአብሔር ለሰዎች የእምነት ነጻነትን ሰጥቷል አንድ ሰው የፈለገውን እምነት መከተል ይችላል መጨረሻ ላይ ነው እግዚአብሔር የሚፈርደው፤ ዛፍ አምላኬ ነው ካለ ድንጋይ አምላኬ ነው ካለ መብቱ ነው እግዚአብሔር አምላክ ሁሉንም ሰው ወደ ቤቱ የሚጠራው በፍቅር ወዶ እንዲከተለው ነው እንጂ አስገድዶ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እንኳን በግድ ይህን እመን ሊል ሲያድን እንኳን ልትድን ትወዳለህን ብሎ የሰውየውን ፈቃድ ጠይቆ ነው፡፡
የሰው ልጅ የእምነት ነጻነት አለው የፈለገውን እምነት መከተል ይችላል ነገር ግን ተሀድሶ የሚለየው እዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብተው በውጪ መዋጋት ያቃታቸው መናፍቃን ህዝቡን የመቀየር ስራ የሚሰሩ ናቸው ልዩነታቸው ምንድነው ሲባል፡-
ተሀድሶ ሙሉ ለሙሉ ከኦርቶዶክስ እምነት ጋራ አይስማማም ከፕሮቴስታንት ጋር ግን ይስማማል፡-
1. ኦርቶዶክስ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅና አምላክ ስትል እነሱ አማላጅ ነው ይላሉ
2. ድንግል ማርያም ወለዲተ አምላክ ብለን ስናምን ተሀድሶዎች ግን ይህን አያምኑም
3. ለካህን ኃጢያትን መናዘዝ አይቀበሉም ቀጥታ ለጌታ ብቻ ይላሉ
ተሀድሶ ማለት መናፍቅ ነው ታቦትን አይቀበሉም፤ በጸበል አያምኑም፤ በስጋ ወደሙ አማናዊነት አያምኑም፤ በስዕል በመስቀል አያምኑም፤ ለቅዱሳን ስግደት እንደሚገባ አያምኑም ስለዚህ በአጠቃላይ ምንድነው ሲባል እኛ ውስጥ ያሉ ነገር ግን ስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ሆነው የበቀሉ ናቸው፡፡
(((መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም፦ ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን፦ እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። ማቴ. 13፡28 )))
ተሀድሶዎችን በአለባበሳቸው መለየት አይቻልም፡-
ዘፍ. 27፡1-33- ያዕቆብና ኤሳው
ያዕቆብ የኤሳውን በረከት የወሰደው አባታቸው ይስሀቅ በዳሰሰው ጊዜ ሰውነቱ ኤሳውን እንዲመስል የበግ ጸጉር ለብሶ ነው ይስሀቅም ማነህ አለው ያዕቆብ ነኝ አባቴ አለ በዳሰሰው ጊዜ ሰውነቱ እንደ ወንድሙ ኤሳው ጸጉር ነበርና ሰውነትህ ኤሳውን ይመስላል ድምጽህ ግን የያዕቆብ ነው አለው፡፡
ልብስና መስቀሉ መርካቶ ሞልቷል ቆቡም እንደዛው፤ ቤተክርስቲያን ውስጥም መግባት ይቻላል፤ በመዋቅር ውስጥም መስራት ይቻላል፤ ተሀድሶዎች በየኮሌጆቹ ውስጥም አሉ፡፡ ተሀድሶዎችን በልብሳቸው መለየት አይቻልም አለባበሳቸው የኦርቶዶክስ ነው ድምጻቸው(ንግግራቸው፤ ትምህርታቸው) ግን የምንፍቅና ነው:፡ ስለዚህም አለባበሳቸው የኦርቶዶክስ ሆኖ ንግግራቸው የመናፍቃን ከሆነ እነዚህ ሰዎች ተሀድሶዎች ናቸው፡፡
በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆኖ ይህን ስራ መስራት ለምን አስፈለገ???
ጠላት ይህችን ቤተክርስቲያን ለማጥፋት የሚቀለው ከውጪ ሆነ ከመዋጋት ይልቅ ከውስጥ ሆኖ በማጥቃት ስለሆነ ነው:-
2ኛ ሳሙ. 15፡33- አርካዊው ኩሲ
እነሆ አቤሴሎም አባቱ ዳዊትን መንግስት በቀማ ጊዜ ንግስናውንም በተቆጣጠረ ሰዓት ንጉስ ዳዊት ከአቤሴሎም ፊት ሸሸ የዳዊት አገልጋይ የሆነ አርካዊው ኩሲም ትቢያ ነስንሶ ንጉሱን ሊገናኘው በመጣ ጊዜ ንጉስ ዳዊት ከእኔ ጋር ከምትሆን ይልቅ አቤሴሎም ጋር ሄደህ አስቀድሞ ለአባትህ ባሪያ እንደ ነበርሁ እንዲሁ አሁን ለአንተ ባሪያ እሆንሃለሁ በለው ከንጉሡ ቤትም የምትሰማውን ነገር ሁሉ መልዕክተኞች ላክልኝ አለው፡፡ ኩሲም ዳዊት እንዳለው ወደ አቤሴሎም ተመልሶ ባሪያ እንደሚሆንለት ነገረው እርሱም ተቀበለው፡፡ ክፉ መካሪው አኪጦፌል ዳዊትን በዚህች ለሊት ሄደን እናሳደው ብሎ አቤሴሎምን በመከረው ጊዜ ኩሲ ግን ይህን በዚህች ሌሊት ማድረግ የለብንም ብሎ አቤሴሎምን ካሳመነው በኋላ ሳትዘገይ ተሻገር እንጂ በዚህች ሌሊት በምድረ በዳ መሻገሪያ አትደር ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት ብሎ ለዳዊት መልዕክት ልኮ ዳዊትን አስመልጦታል፡፡
እንግዲህ ኩሲ የሚበላው የሚጠጣው የሚኖረው በአቤሴሎም ቤት ውስጥ ሆኖ ሳለ የሚሰራው ግን ውጪ ላለው ለዳዊት ነበር፡፡ ዛሬም ኦርቶዶክስ ውስጥ ሆነው፤ ከእኛው ጋር እየዋሉ፤ ከእኛው ጋር እየበሉ እየጠጡ ለመናፍቃን የሚሰሩ እነሱ ተሀድሶዎች ናቸው፡፡
ማንም ሰው እንግዳ ት/ት ቢያስተምራችሁ እንዳትቀበሉ፤ እኔም ብሆን ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ የተለየ፤ ከዶግማዋና ቀኖናዋ ውጪ የሆነ ት/ት ብሰብክላችሁ ከየት ነው ያመጣኽው ብላችሁ ልትጠይቁ ይገባችኋል፡፡
ቤተክርስቲያን ማንም ሰው እንዲጠፋባት አትፈልግም፤ እንኳን ብዙ ሰው የሚያስተምሩ መምህራንና ዘማሪያን ቀርቶ አንድም ክርስቲያን እንዲጠፋባት አትፈልግም፡፡ ስለዚህም ትመክራለች ታስተምራለች ትገስጻለች ተሳስተሀል ተመለስ ትላለች አይ አልመለስም ካለ አውግዛ ትለያለች፡፡
ከብርቱካኖች መሀል አንዱ ከበሰበሰ ሌሎቹን እንዳያበሰብስ ይጣላል፤ ጣት ቢቆስል ህክምና ይደረግለታል ፈውስ ባይመጣና ወደ ሌላ ሰውነት ሊዛመትም ቢሆን ግን ጣታችንን ማጣት ባንፈልግም ስለ ሌሎቹ የሰውነት አካላችን ስንል እንቆርጠዋለን፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የመናፍቃንን ዘር ቢዘራ ተው ይባላል እምቢ ካለ ግን ውስጥ ሆኖ ቤተክርስቲያንን ሳይበክላት አደጋ ሳያደርስ ይወገዛል፡፡
ስለ ጥላቻ ሳይሆን ሌሎችን ስለማዳን ነው አባቶቻችንም አርዮስ ሆይ አንተን እንወድሀለን ት/ትህን ግን እንጠላለን ብለው ነው አርዮስን ያወገዙት፡፡"

እንግዲህ ጉባኤው ከብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስል ነበር.....ቀረ የምትሉትን ደግሞ በጉባኤው ላይ የነበራችሁ ጨምሩበት፡፡
በነገራችን ላይ ጉባኤው በቀጣዩ ረቡዕ ጥቅምት 3 ይቀጥላል መምህር ምህረተአብ በመረጃ የተደገፈ ት/ት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፤ ከዚያም ጥቅምት12 የመጨረሻው ጉባኤ ይሆናል ምክንያቱም ጥቅምት 14 መምህራችን ለአገልግሎት ወደ አሜሪካ ይሄዳሉና ነው ፡፡ በቀጣዩ ጉባኤ ማህተባችሁን ያልበጠሳችሁ ሁሉ እንዳትቀሩ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
እግዚአብሔር ለመምህራችን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፤ የአገልግሎት ዘመናቸውን ያርዝምልን፡፡ አሜን!!!
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው፣ የማትለወጠው፣ የማትታደሰው፣ ጸንታ የምትኖረው እውነተኛ መንገድ!!!
ሁላችንንም በተዋህዶ ያጽናን፡፡ አሜን!!!
@rituaH. @rituaH @rituaH
"+" ተፈፀመ ማህሌተ ጽጌ "+"
"""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
" አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ፤እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ።በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ?እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት። "

" አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ከአንቺ ጋር እንፈልገው ዘንድ ውድሽ ወዴት ሄደ?ውድሽስ ወዴት ፈቀቅ አለ? "

" በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት።"

" ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ጠጕርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድእንደ ፍየል መንጋ ነው። "

" እንብርትሽ የወይን ጠጅ እንደማይጐድልበትእንደ ተነጠጠ ጽዋ ነው፤ሆድሽ እንደ ስንዴ ክምር፥ በአበባም እንደ ታጠረ ነው። "

"የብር ዥንጉርጉር የነጭና የቀይ ድብልቅ መልክ ያለው ንፁህ ተዓምርሽ በወርቅ አምሳል የተዘጋጀ ነው"
እነሆ ያማረ የተወደደ ማኅሌተ ጽጌ የተባለ ምሥጋና መላ ተፈፀመ::
የሰማይና የምድር ንግሥት ማርያም ሆይ ልጅሽ ወዳጅሽ በእቅፍሽ ውስጥ እንዳለ ይህንን የማኅሌተ ጽጌ ምሥጋናን ተቀበይ ወደ ሰማይ አሳርጊ::
ምንጭ ፦መኃልዬ ዘ ሰለሞን
የተወደዳችሁ ህዝበክርስቲያን በስደት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰርተችሁ ተለውጣችሁ ከስደታችሁ እመአምላክ ወላዲተ አምላክ በሰላም ለሀገራቹ ታብቃቹ፤ በውስጥ ያለነውንም ጥላቻን ታርቅልን፤ ሀገራችንን ትጠብቅልን ሰላም ፍቅር አንድነት ትስጥልን፤ አረጋውያንን ህጻናትን ትጠብቅልን። የዓመት ሰው ይበለን፡፡

መልካም እለተ ሰንበት፡፡
@rituaH @rituaH @rituaH
" አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን"

+ ኅዳር 12-ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚበር ንሥረ አርያም የሚባል ውዳሴው እንደ ማር የጣፈጠ ንዑድ ክቡር የሆነ ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የተሾመበት ዕለት ነው፡፡

+ ጻዲቁ ንጉሥ በእደ ማርያም ዕረፍታቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡

+ የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በደብረ ማህው የታየችበት ዕለት መሆኑን ስንክሳሩ ይጠቅሳል፡፡

"+" የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል"+"

ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ' ካ-ከመ' ኤል-አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ ‹‹መኑ ከመ አምላክ-እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው›› ማለት ነው፡፡ አንድም ለእግዚአብሔር አሸናፊ ድል አድራጊ የቸርነትና የርህራሄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው፡፡
ገናናው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስን ወደ ጥልቁ ጥሎት በእርሱ ምትክ ከሁሉ የበላይ ሆኖ በተሾመበት በዚህ ዕለት በበዓሉ መታሰቢያ በኅዳር 12 ቀን የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔር ፈቃድ ክንፎቹን ወደ ሲኦል ያወርዳል፣ ኃጥአንንም ወደ አዲሲቱ ምድር ያወጣቸዋል ይኸውም የመላእክት አለቃ የሚካኤል ሠራዊት ይሆናሉ፡፡ ይቅርታ የተደረገላቸውና ምሕረት አግኝተው በአንድ ጊዜ በክንፉ ያወጣቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በየዓመቱ በኅዳር 12 ቀን እንዲህ እያደረገ እልፍ ነፍሳትን ያወጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ወገኖች የሆኑትን ሁሉ እንደሥራቸው ወደ ምሕረት ቤት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አብ መጋረጃ ውስጥ ይገባል፣ በዚህች ዕለት ምድራዊትና ሰማያዊት ስለሆነች ምሕረቱም ከመንበሩ በታች ይሰግዳል፡፡ ስለውኃ ምንጮች፣ ስለ ወይን ቦታዎች፣ ስለ ምድር ፍሬዎች በምድርም ላይ ስለሚኖሩ ስለ ሰው ልጆች ነፍስ ሁሉ፣ ስለ እንስሳትም፣ ስለ ሰማይ ወፎችም፣ ስለ ባሕር ዓሣዎችም፣ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የምሕረት ባለቤት ከሆነ ከአብ ዙፋን በታች ሁልጊዜ በማመስገን ይሰግዳል፤ ልመናውንም እስኪሰማውና የምሕረትንም ቃል እስኪያስተላልፍለት ድረስ ከእግረ መንበሩ ሥር አይነሣም፡፡
ለዚህ ዓለም ምሕረትን የሚለምኑ ቅዱሳን መላእክትም በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀንበእግዚአብሔር የዙፋኑ ዓውደ ምሕረት ዙሪያ ተሰብስበው ስለ ሰውና ስለ እንስሳትም ሁሉ ምሕረትን የሚለምን ቅዱስ ሚካኤል ከአብ መጋረጃ ውስጥ በወጣ ጊዜ ቸርና መሐሪ አብ ለቅዱስ ሚካኤል የሰጠው ልብሱን እነዚያ መላእክት ይመለከታሉ፣ ይቅርታን የማግኘት ምልክታቸው ነውና፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት በምድር ላይ ምሕረት እንደተደረገ ሰውንም እንስሳትንም ይቅር እንዳለ በዚህ ዓለምም የሚሆነውን ሁሉ አይተው ቅዱስ ሚካኤል በለበሰው ልብስ አምሳል ያውቁታል፡፡
ስንክሳሩ እንደሚለው ይህ እጅግ የከበረ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋራ በመሆን ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ የሚያጽናናቸውና የዘወትር ጠባቂአቸው ሆኖ የሚራዳቸው እርሱ ነው፡፡›› የብዙዎቹንም ቅዱሳን ገድል ስንመለከት የዘወትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
ቅዱሳን በሕይወት ሳሉ ይህ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ረዳትና የዘወትር ጠባቂ፣ እንደጓደኛም አማካሪ ሆኖ የተበቃቸውን ስንቱን ቅዱሳን ዘርዝረን እንቸላለን፡፡ እርሱ ያልረዳው ቅዱስ የለም፡፡ መከራውን ያላስታገሰው ሰማዕት የለም፡፡ ለቅዱሳኑ እንዲህ እንደጓደኛቸው ሆኖ ሲጠብቃቸው ይኖራል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ሚካኤል ለኃጥአንና አምላካቸውን ለካዱ ሰዎች ደግሞ በቁጣ ለመቅሰፍት ይመጣባቸዋል፡፡ ሰናክሬም በእግዚብሔር ላይ ክፉ በመናገሩ በአንዲት ሌሊት ብቻ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) ሠራዊቱን ቅዱስ ሚካኤል በብርሃን ሰይፉ ፍጅቷቸው አድሯል፡፡ 2ኛ ነገ 19፡35፣ ኢሳ 37፡36፡፡
እግዚአብሔርን ለሚወዱና እርሱንም ለሚያከብሩት መታሰቢያውንም ለሚያደርጉለት ግን ከሚፈልጉት ነገር ከቶ አያሳጣቸውም፣ ዘወትርም ይጠብቃቸዋል፣ በኋላም በአማላጅነቱም ከሲኦል እሳት ያድናለቸዋል፡፡ እነሆ ይህ ገናና ክቡር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- ‹‹የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ነገር ግን ወደቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክበር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንድሰነጥቅ አዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ 300 የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አጀጋጀላችሁ›› አላቸው፡፡
እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፡፡ የከበረ ገናናው መልአክም ‹‹ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፡፡ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡››
የመላእክት አለቃ ቅዱስ የሚካኤል ጥበቃው አይለየን! ከበዓሉ በረከት ይክፈለን!
ምንጭ:—ከገድላት አንደበት
@rituaH @rituaH @rituaH
"ፆምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ። ትንቢተ ኢዮኤል ፩:፲፬
✞✞✞ እንኳን ለጽዮን "ማርያም ማሕደረ አምላክ" እና ለቅዱሳኑ "ጐርጐርዮስ ወዮሐንስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ ጽዮን ማርያም +"+

=>"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው:: አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው:: ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም: ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል::
+እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በሁዋላ በጊዜው ለእሥራኤላውያን ክብር: ሞገስ: አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል:: (ዘጸ. 31:18) ከዚያም ለ500 ዓመታት ከእነሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች::
+ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ: በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ-እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮዽያ መጥታለች:: እነሆ በሃገራችን የ3ሺ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው:: ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን::
+ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን:: ግን አንጨነቅም:: ምክንያቱም የመጣችውም: የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም:: በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም:: ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም::
+ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን: ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች:: "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው:: "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው::
+"ታቦት" ማለት "ማሕደር-ማደሪያ" እንደ ማለት ነው:: ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል:: ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው:: በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም 2 ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን:: (2ቆሮ. 6:16, ራዕይ. 11:19)
+በመጨረሻም ኅዳር 21 ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን:: በዚህች ቀን:-
1.ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን:: ይሕ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ 40 መዓልት: 40 ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው:: (ዘጸ. 31:18, ዘዳ. 9:19)
2.በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኩዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች:: ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች:: (1ሳሙ. 5:1)
3.በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና: ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ: አገለገለ:: ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት:: በዚህም ሜልኮል ንቃው ማሕጸኗ ተዘግቷል:: (1ዜና. 15:25) ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል" ብለውናል::
"ሰላም ለኪ ማርያም እምነ::
ዘሰመይናኪ ጸወነ::
ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ::
ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ::
ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ::" እንዲል:: (አርኬ ዘኅዳር 21)
4.በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል:: (2ዜና. 5:1, 1ነገ. 8:1)
5.በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮዽያ ገብቷል::
6.በዘመነ አፄ ባዜን (በ4 ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች:: በዚህ ጊዜም 2ቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል::
7.በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ 12 መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚሁ ቀን በጌታችን ተቀድሷል::
8.በተጨማሪም በየጊዜው: ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር:: ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር 21 ቀን ነው:: በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው::
+*" አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን "*+
=>"ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል:: እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት እምቡሩካን: ኅሪት እምኅሩያን" ናትና::
+ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች:: እርሷ እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ ናትና::
+እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት: ልዩ" ማለታችን ነው::
1."ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ: ከገቢር: ከኃልዮ ንጽሕት ናት::
"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው: ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ ማርያም)
2."ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በሁዋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::
¤"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ ያሬድ)
¤ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-ማርያም ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)
3.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው:: እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::
4.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና::
+"+ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘሮም +"+
=>በቤተ ክርስቲያን እጅግ ስመ ጥር ከሆኑት ሊቃውንት አንዱ ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚታወቀው "ገባሬ መንክራት" በሚለው ስሙ ነው:: ገባሬ መንክራት የተባለውም እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን በመሥራቱ ነው::
+በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ሥር ተወልዶ ያደገው ቅዱስ ጐርጐርዮስ ከመመነኑ በፊት ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: እርሱ በበርሃ እያለም ከሮም ዻዻሳት የአንዱ በማረፉ ተሿሚ ፍለጋ አበው ሱባኤ ገቡ:: እግዚአብሔርም "የበረሃውን ጐርጐርዮስን ፈልጉት" አላቸው::
+"እሺ!" ብለው ፍለጋ በርሃ ቢሔዱ ውዳሴ ከንቱን ይጠላልና ተሰወረባቸው:: እነርሱም እያዘኑ ተመልሰው በመንበረ ዽዽስናው ላይ ወንጌልን አኖሩና ተለያዩ:: በዚህ ጊዜ ቅዱስ መልአክ ወርዶ "ጐርጐርዮስ ሆይ! ልትሔድ ይገባሃል" አለው::
+እርሱም ወደ ከተማ ወርዶ ታላቁ ሊቅ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ባለበት በዓለ ሲመቱ ተከብሯል:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ በዘመኑ ብዙ መጻሕፍትን ደርሶ: የክርስቶስን መንጋም ጠብቆ: ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል:: ከተአምራቱም:-
+ወንድማማቾች ከአባታቸው በወረሷት አንዲት ሐይቅ እየተጣሉ ሲያስቸግሩ
በጸሎቱ ሐይቁን የብስ አድርጐ አስታርቁዋቸዋል::
+"+ ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስዩጥ +"+
=>በ4ኛውና በ5ኛው መቶ ክ/ዘመናት ከተነሱ ከዋክብት ጻድቃን አንዱ ነው:: እድሜው በጣም ረዥም በመሆኑ የብዙ ቅዱሳን ባልንጀራም ነበር:: በገድል አካሉን ቀጥቅጦ: በስብከትም የአስዩጥን (አሲዩትን) ምዕመናን አንጾ: ብዙ ተአምራትንም ሠርቶ በተወለደ በ125 ዓመቱ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::
=>አምላከ ቅዱሳን የአማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያምን ጣዕሟን ፍቅሯን: ጸጋ በረከቷን ያሳድርብን:: ከአበው በረከትም አይለየን::
=>ኅዳር 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ጽዮን ድንግል ማርያም
2.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘሮሜ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስዩጥ
4.ቅዱስ ቆዝሞስ ሊቀ ዻዻሳት
5.ቅድስት ዲቦራ ዘድልበት
6.ቅዱስ ዘኬዎስ ሐጺር
=>ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ
4.አባ አሮን ሶርያዊ
5.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
=>++"++ ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግስት ይጠፋል:: እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ . . . የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ:: የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ:: የእግዚአብሔርም ከተማ: የእሥራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል:: ++"++ (ኢሳ. 60:12)
ምንጭ - ከዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ
---+----+----+----+----+----+---
@rituaH @rituaH @rituaH
@rituaH @rituaH @rituaH
="="="="="="="="="="="="="
=" "+" የጾም ጥቅም "+" ="
="="="="="="="="="="="="="
ጾም ማለት ለተወሰኑ ሰዓታት ከእህል እና ከውሃ (ጥሉላት መባልዕትን ጾሙ እስኪፈጸም ፈጽሞ መተው) እንዲሁም ለተወሰኑ ጊዜያት ከሥጋ ፈቃዳት መከልከል ነው።። ስለዚህ መጾም ማለት በጾም ወቅት የምግብ ዓይነትን መለወጥ ብቻ ሳይሆን የምንወደውን የሥጋ ፍላጎት ስለ እግዚአብሔር ብለን መተው ነው።። የሥጋ ፍላጎት የዓለምን ምኞት መፈጸም ሲሆን ይህን ነገር የምንገታው ደግሞ ራሳችንን በጾም በመግዛት ነው። ”ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ- ነፍሴን በጾም አስመረርኋት” መዝ. 68፥10 እንዲል። ታሪካቸው በትንቢተ ዳንኤል ተጽፎ የምናገኘው ሦስቱ ወጣቶች በንጉሥ ቤት እየኖሩ የተሻለ ነገር መመገብ ሲችሉ እግዚአብሔርን ስለ መውደድ ብለው በንጉሡ ቤት ከሚዘጋጀው ማለፊያ ምግብ ይልቅ ጥራጥሬን መመገብ መረጡ። ትን ዳን. 1፥8-16። በተጨማሪም እንደ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በመፍራት ምክንያተኝነትን በመተው ከኃጢአት መጾም ነው:፡ ዮሴፍ ኃጢአቱን ለመሥራት የእመቤቱን ፈቃደኝነትና የእርሱን ወጣትነት እንደ ምክንያት አላቀረበም። ነገር ግን ፈጣሪውን ዘወትር በፊቱ በማድረጉ ከኃጢአት ለመጾም ችሏል። ዘፍ 39፥7-13;: ስለዚህ ጾም ማለት እያለንና ማድረግ እየቻልን ስለ እግዚአብሔር ብለን መተው ነው።
ለምን እንጾማለን?
ጾም ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነትና ፍቅር የምንገልጽበት የአምልኮ ሥርዓት መገለጫ ነው። እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ መጀመሪያ የሰጠው ትዕዛዝ ጾም ነው(ዘፍ 2፥16-17)። ይኸውም ዕጸበለስን እንዳይበላ ነበር። ለአዳም እና ለሔዋን ይህ ህግ መሰጠቱ የፈጣሪ እና የፍጡር፣ የአዛዥና ታዛዥ መገለጫ ነበር።
አዳም ይህን የጾም ትዕዛዝ በማፍረሱ ከፈጣሪው ጋር ተለያየ ስለዚህም በጾም ማፍረስ የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ የመጣው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ሥራውን የጀመረው በጾም ነበር (ማቴ 4፥1-11)። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሐ ባሕርይ የሆነ፣ ሁሉ በእጁ ሲሆን ምንም እንደሌለው ተራበ፤ ይህም ለእኛ አርዓያ ይሆነን ዘንድ ነው። አንድም አምላከ ነቢያት ነውና ኦሪትንና ነቢያትን ሊፈጽም እንደ ነቢያቱ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በገዳም አደረ፤ በዲያብሎስም ተፈተነ “ጾመ ሙሴ፤ ጾመ ዳንኤል፤ እግዚእነ ጾመ አርዓያ ዚአሁ ከመ የሀበነ”(ትርጉም:- ሙሴ ጾመ፤ ዳንኤል ጾመ፤ ጌታችንም አርዓያ ይሆነን ዘንድ ጾመ) ጾመ ድጓ። ሐዋርያትም አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት በጾም ነበር ፈጣሪያቸውን የጠየቁት፤ ከዚያም በአገልግሎታቸው የጸኑ ሆነዋል። እኛም ዛሬ ጌታችንን፤ ቅዱሳን ነቢያትን፤ እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያትን አብነት በማድረግ ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ለማስገዛት እንጾማለን።
እንዴት እንጾማለን?
መጾም ማለት ከእህል ውኃ መከልከል ከጡልላት ምግቦች ወደ አትክልት ምግቦች መቀየር ብቻ ሳይሆን ሰውነታችን ከሚፈልገው መጠን ያለፈ ደስታ በመታቀብ የሥጋን ምኞት መግታት መቻል ነው። ስንጾምም በምግብ ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነታችን በተለይም የስሜት ሕዋሳታችን ሁሉ ከኃጢአት መጾም ይኖርበታል። ይህንንም ቅዱስ ያሬድ “ይጹም ዓይን፤ ይጹም ልሳን፤ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ሕሡም በተፋቅሮ – ዓይን ክፉ ከማየት ይጹም አንደበት ክፉ ከመናገር ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም“ በማለት ገልጾታል። ይህም ማየት የኃጢአት መጀመሪያ ነውና ዓይናችን ክፉ ከማየት መቆጠብ ይኖርበታል። ማየት የልቡናን ፍላጎት ስለሚቀሰቅስ ኃጢአትን ወደመሥራት ይወስደናል። የያዕቆብ ልጅ ዲና ከአሕዛብ ወገን የምትሆን ጓደኛዋን ለማየት ብላ ወደማይመስሏት ሰዎች ሄደች በዚያም የአሕዛብ ወንድ አይቶ ተመኛት ከርሱም ጋር በዝሙት በመውደቅዋ ለራሷም ጥፋት እና ለወንድሞቿ የጥል መንስኤ ሆናለች ዘፍ34። ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር ሴትን አይቶ የተመኛት ሁሉ በልቡ አመነዘረ ብሏል። ማቴ.5፥28 ማየት ክፉ ምኞትን የሚያመጣ የኃጢአት መጀመሪያ ነው። ስለዚህ በምንጾምበት ወቅት ክፉ ከማየት መቆጠብ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊፈትን እና ክፉ ምኞትን ሊቀሰቅስ ወደ ሚችል ነገር ማተኮር ተገቢ አይደለም። በመሆኑም ዛሬ በቴክኖጂ አማካኝነት መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊፈትኑ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ እንደ ክርስቲያንነታችን ከነዚህ ሁሉ ልንጾም ይገባናል።
ሌላው መጾም ያለበት አንደበታችን ነው። ይህም በአንደበታችን ክፉ ከመናገር በመቆጠብ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ለጸሎት መትጋት ይኖርብናል። በጾም ወቅት አርምሞን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል። አርምሞ የሌለበት ጾም ዋጋ አይኖረውም “አርምሞ ተአግሶ ተዐቅብ ሃይማኖተ” (ትርጉም ዝምታ፣ መታገስ ሃይማኖትን ትጠብቃለች) እንዳለ ቅዱስያሬድ። እንጾማለን እያልን ወንድማችንን በማማት የምንጎዳ ከሆነ ጾማችን እርባና አይኖረውም። “ሶበ ትዜከር አበሳሁ ለእኁከ ተንሢአከ ጸሊ በጥቡዕ ልብከ አስተስሪ ሎቱ – የወንድምህን በደል ባሰብክ ጊዜ ተነሥተህ ጸልይለት በቆራጥ ልቦና ይቅር በልለት” (ጾመ ድጓ ዘወረደ)፤ ምክንያቱም ጾም አፍቅሮ ቢጽን የምናጎለብትበት ዓይነተኛው መሣሪያ ነውና። ወንድምን በክፉ ከማንሳት ይልቅ ስለ ወንድምና እህታችን ብለን መጸለይ እና ይቅር ማለት ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ በር እንዲከፈትልን ያደርግልናል።
ሌላኛው መጾም ያለበት የስሜት ህዋስ ደግሞ ጆሮ ሲሆን ይኸውም ክፉ ከመስማት መቆጠብ ነው። ሕዝበ እስራኤልን በባርነት ከነበሩበት ከግብፅ ምድር አውጥቶ፣ ባህር አሻግሮ በምድረ በዳ መና ከሰማይ እየመገበ፣ ውኃ ከአለት እያፈለቀ፣ መዓልቱን በደመና ሌሊቱን በፋና እየመራ ያደረሳቸውን አምላክ ከሀሰተኛ ሰዎች በሰሙት ክፉ ወሬ ብቻ ተሰናክለው የእግዚአብሔርን ኃይልና ረድኤት ዘንግተው እንደገና ወደ ግብጽ መመለስ በመመኘታቸው የተስፋዋን ምድር እንዳያዩ ሆነዋል (ዘዳ 13-14)። አበው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል እንዲሉ፣ እንደ እስራኤላውያን ለክፉ ወሬ ጆሯችንን መስጠት አገልግሎታችንን ሊጎዳ ብሎም በሃይማኖታችን ላይ ኑፋቄን ሊያመጣብን ስለሚችል፣ ጆሯችን ከክፉ ወሬ እንዲጾም ማድረግ ይገባል:፡ እንዲያውም በጾም ወቅት ከምንጊዜውም በበለጠ ገድለ ቅዱሳንን ልንሰማ፣ ልናሰማ ይገባናል፤ ምክንያቱም የቅዱሳን ጽናትና ተጋድሎ የእኛን ሕይወት የምንመዝንበት፣ ተጋድሏቸውን በማሰብ የምንጸናበት ሕይወትን እናገኝ ዘንድ ይረዳናል።
ባጠቃላይም በጾም ወቅት ከሌላው ጊዜ በበለጠ አብዝተን መስገድ፣ መጸለይ እና መመጽወት እንዲሁም የስሜት ህዋሳታችንን በመግታትና አርምሞን ገንዘብ በማድረግ በተመስጦ ወደ አምላካችን መቅረብ ይጠበቅብናል።

"ወስብሐት ለእግዚአብሔር"
+---+---+---+---+---+---+---+---+
@rituaH @rituaH @rituaH
2024/06/29 18:46:43
Back to Top
HTML Embed Code: