Telegram Web Link
    የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት    

መ ጻ ጉ ዕ   

አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹መጻጒዕ› ይባላል፡፡

ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩ ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል የተወሰደ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን በቤተ ሳይዳ ሕሙማንን እንደ ፈወሰ ተነግሮአል፡፡ ብዙ ሕሙማን ፈውስ ሽተው አንዲት የመጠመቂያ ሥፍራን ከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚያች ሥፍራ ቀድሞ የወረደ እና የተጠመቀ አንድ በሽተኛ ብቻ ይፈወስ ነበር፡፡

ጌታችን በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ በሽተኞችን ጐብኝቷል፡፡ በዚያም ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸው አምስት ዓይነት ሕሙማን እንደ ነበሩ ተገልጧል ፤ እነዚህም ፦ ሰውነታቸው የደረቀ ፣ የሰለለና ያበጠ ፤ እንደዚሁም ዕውራን እና ሐንካሳን ነበሩ፡፡ ከዚህ አምስት የተለያየ ዓይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል ደዌው የጸናበት ፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ ፣ ባልጋ ቍራኛ ተይዞ የኖረው ፤ ከደዌው ጽናት የተነሣ ‹መጻጒዕ› ተብሎ የተጠራው በሽተኛ አንዱ ነበር፡፡

መጻጒዕ ስም አይደለም፡፡ ደዌ የጸናበት በሽተኛ ሕመምተኛ ማለት ነው እንጂ፡፡ ሰውየው ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ ጠፍቶ በበሽታው ሲጠራ የነበረ ነው፡፡ አምላካችን ይህን ሰው "አልጋህን ተሸክመህ ሒድ" ብሎ ሠላሳ ስምንት ዘመን የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረጉ የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ሳምንቱ ‹መጻጒዕ› ተብሎ በተፈወሰው በሽተኛ ስም ተሰይሟል፡፡ [ሙሉ ታሪኩን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፩-፲፯ ይመልከቱ]፡፡

ዛሬም ቢኾን በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ ፤ የሥጋውን ደዌ ሐኪሞች ያውቁታል፡፡ ከዚህ የከፉ የነፍስ ደዌያት እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀና ያበጠ ፤ ሰውነታቸው የሰለለ ፤ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ ፤ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን አሁንም አሉ፡፡ ፈውስን ይሻሉ ፤ ድኅነትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደ መጻጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ፡፡

[ በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ ]

@ortodoxtewahedo
“ችግሮች ቢኖሩም ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፈው የሚሰጡ ልጀች እንዳሉ አይተናል፤ ቤተ ክርስቲያን መሻገሯ አይቀርም”

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

+++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++

የማኅበረ ቅዱሳን የ2016 ዓ.ም የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤ በመጨረሻ ቀን ውሎው ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተው ነበር።

የማኅበሩ ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ለብፁዕነታቸው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በዚህ የሥራ አመራር ጉባኤ በሀገር ውስጥ ካሉን 55 ማእከላት ውስጥ ጦርነት ውስጥ ካሉ አካባቢዎች ሳይቀር ከ48 ማእከላት ሰብሳቢዎች እና ተወካዮች እንዲሁም ከውጭ 9 ማእከላት ተሳትፈዋል ብለዋል።

ሰብሳቢው አክለውም ጉባኤው በሁለት ቀን ውሎው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አሁናዊ ችግሮችና መፍትሔዎች እንዲሁም የማኅበረ ቅዳሳን የአገልግሎት ድርሻ ላይ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

“ጽና፤ እጅግም በርታ” በሚል ኃይለ ቃል ቃለ ምእዳን የሰጡት
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

“የኛ የሆነውን አሳልፎ ላለመስጠትና በክብር የተቀበልነውን በክብር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ጥንካሬ ያስፈልጋል፤ እናንተም ጽናት ባይኖራችሁ በዚህ ሁሉ መከራ መሀል አትገኙም።ችግሮች ቢኖሩም ራሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፈው የሚሰጡ ልጀች እንዳሉ አይተናል” ብለዋል።

ትውልዱ ጽናት ያለው የሚመስል ነገር ግን በጉዞ መሐል የሚንቀጠቀጥ የሚንገዳገድ ትውልድ መሆን የለበትም ሲሉም አብራርተዋል ።

“ከምእመን እስከአባቶች ከበረታን ቤተ ክርስቲያን ከእነሙሉ ክብሯ ትተላለፋለች፤ መሻገሯም አይቀርም” ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም “ ሌላ ጉልበት የለንም ጉልበታችንም ጽናታችንም እግዚአብሔር ነው፤ አቅጣጫ የሚሰጠንም ቃሉ ነው፤ እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚያስተካክል እናምናለን የእኛ ድርሻ ግን እንወጣ ” ብለዋል።

ብፁዕነታቸው ማኅበሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር የበለጠ በመናበብና ግብዓት በመስጠት በፍቃደ እግዚአብሔርና በጥበብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እናሻገር ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም ከውጭ ሀገራት የተሳተፉ አባላትን መነሻ በማድረግም “ጽኑ፤ በምትሠሩት መንፈሳዊ አገልግሎትም ቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ስለሆናችሁ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስም አመሰግናለሁ” ብለዋል።

@ortodoxtewahedo
2024/09/28 21:35:27
Back to Top
HTML Embed Code: