Telegram Web Link
#ኪዳነ ምህረት

ቢዘገይም… ብዙዎች ድንግል እናቱን ኪዳነ ምህረት ስንል ግራ ሲጋቡ አስተውላለሁ። በእርግጥም ግራ ቢጋቡ አይደንቅም ምክንያቱም ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቆ መረዳትና የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ይፈልጋልና።

በብሉይ አማናዊው መሥዋት ከመሰዋቱ በፊት “የሥርየት መክደኛ”በእንግሊዘኛው ደግሞ “mercy seat` እንዲህም ሲባል “የምህረት ዙፋን" የሚባል ክፍል ያለው የቃል ኪዳኑ ታቦት ነበር። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን በማድረጉ በታቦቱ ላይ ተገልጦ ሙሴን ያነጋገረው ካህናቱን መሥዋዕታቸውን ይቀበል ነበር።

ይህ መገለጥ ግን ከሰዎች ልጆች ጋር ፍጹም እርቅ መፈጸሙን የሚያሳይ አልነበረም። ነገር ግን በዚህ ሕዝቡ ይጽናና ራሱንም ለበለጠ የትንሣኤ ሕይወት ያዘጋጀው ነበር። ምክንያቱም ለአባታቸው ለአብርሃም የገባውን ቃል ኪዳን እንደማያጥፍ ያምኑ ነበርና።

በሠውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የወረደው ግን ድንግል እናቱን የቃል ኪዳኑ ታቦት አድርጎ ሥጋና ደም ተካፍሎ ሰው ሲሆን ነው። ያኔ በሰውና በእግዚአብሔር በሰውና በመላእክት በሰውና በሰው መካከል የነበረው ጠብ ፍጻሜ አገኘ። እርቅን ከሰው ጋር በተዋሕዶ ከፈጸመ በኋላ በሰው ልጆች ላይ ሰልጥኖ የነበረውን ዲያብሎስ ከድንግል እናቱ በተካፈለው ሰውነት በመስቀሉ ድል ነሳው። ድል መንሳትንም ለእኛ ሰጠን።

ስለዚህ እርቅ የወረደልን ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተሰጠን እርሷንና ሥጋዋን ለራሱ የቃልኪዳን ታቦቱ በማደረግ ስለሆነ ድንግል እናቱን ኪዳነ ምህረት እንላታለን። ምክንያቱም ምህረትና እርቅ ለሰው ልጆች ሁሉ ሆኖአልና።

እርሱ እግዚአብሔር ቃል ከእርሷ ከድንግል እናቱ ሥጋና ነፍስ ነስቶ ባሕርያችንን ለብሶ በእርሱም ለፍጥረቱ ተገልጦ በእኛ ላይ የተፈረደውን ፍርድ በራሱ ተቀብሎ ዲያብሎስን ድል ነስቶ በእርሱ ያመኑትን እርሱን ተስፋ የሚያደርጉትን ከቅዱሳን
መላእክት ጉባኤ ደመራቸው፡፡ ያመኑትንም በጥምቀት እርሱን ለብሰን እንድንነሣ በማድረግ ከቅዱሳን ጉባኤ እንድንደመር አደረገን፡፡

ሰውነታችንን መቅደሱ በማድረግ ሕጉንም በመንፈስ ቅዱስ በልቡናችን ሰሌዳ ላይ ጻፈልን፡፡ እነዚህንና ሌሎች
በረከቶችን ሊሰጠን የወደደው ከድንግል እናቱ በነሣው ሥጋና ነፍስ ነበር፡፡

ስለዚህም ድንግል እናቱ መንፈስ ቅዱስ አናግሩዋት “በእኔ ታላቅ ሥራን አድርጎአልና እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ብላ ከፍ አድርጋ ተናገረች፡፡ ስለዚህ ነው ኪዳነ ምሕረት መባልዋ፤ በእርሷ እርቅ ወርዶአልና።
በነቢዩም “ ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔ አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፡፡

”(ዕብ.8፡10) የሚለው ቃል በእኛ የተፈጸመው በድንግል ማርያም ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ ጳውሎስ
“እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው”ብሎ ጽፎልናል፡፡

(2ቆሮ.3፡3)ይህን በማን አገኘነው ብንባል በክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ የድንግል እናቱን ሥጋና ደም ሳይካፈል ባይወለድ ኖሮ ይህ የምህረት ቃል ኪዳን በእኛና በክርስቶስ መካከል ባልተፈጸመ ነበር፡፡

እናም አጥርቶ ለመረደት የሚፈለግ ቅድስት እናቱን ኪዳነ ምህረት የማለታችን ዋናው ምክንያት ሰውነቷን የምህረት ቃል ኪዳን ታቦት በማደረግ ከርሷ በነሣው ሥጋ ዓለሙ መዳኑ ነው።...

@ortodoxtewahedo
#ኪዳነ ምህረት #16

ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡

ከ33ቱ በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡ እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን አላቋረጠችን እመቤታችንም እንዲህ ብላ ስትጸልይ ልጄ ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መጥተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለች በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት ተሰነጣጠቀ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡

እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡

ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ በራሴ በአባቴና በመንፈስ ቅዱስ ስም ቀል እገባልሻለው ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል።

በዚህም የተነሳ እመቤታችን እኛን በምልጃዋ የምታስምርበተ ፣ ጥያቄያችንን የምታስመልስበት ፣ እንቆቅልሻችንን የምታስፈታበት የምህረት ኪዳን የካቲት 16 ተቀብላለች እና ኪዳነ ምህረት እንላታለን ።

@ortodoxtewahedo
ጥያቄ : ሰባቱ ኪዳናትን ስማቸውን ጥቀሱ ።
መልሳችሁን 👇 ኮመንት ላይ ፃፉ
✝️7ቱ ኪዳናት✝️

ሰባቱ ኪዳናት "ተካየደ" ማለት "ተስማማ : ተማማለ" እንደ ማለት ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል : ስምምነት" እንደ ማለት ነው:: ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር: ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል:: ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው:: እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጓል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ 7 እንደ ሆኑ ታስተምራለች:: :: "ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ" "ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ" (መዝ. 88:3)

#1 ኪዳነ አዳም አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት: የፍጡራን አስተዳዳሪ: ነቢይ: ካህንና ንጉሥ ነው:: እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው:: ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ:: (ዘፍ. 3:1) አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ: "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ:: (ቀሌምንጦስ: ገላ. 4:4)

#2ኪዳነ ኖኅ ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት 10 ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች:: ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች:: ከመርከቡ ከወጣ በኋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ:: "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል:: (ዘፍ. 9:12) 

#3 ኪዳነ መልከ ጼዴቅ መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ: የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ15 ዓመቱ መንኖ: አጽመ አዳምን ይዞ: በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር:: እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ: በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል:: በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም:: ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: (ዘፍ. 14:17, ዕብ. 7:1)

#4 ኪዳነ አብርሃም ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት: ሥርወ ሃይማኖት: የጽድቅም አበጋዝ ነው:: ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ" አለው:: (ዘፍ. 12:1) የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው:: (ዘፍ. 17:1-14)

#5 ኪዳነ ሙሴ ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ: የእሥራኤል እረኛ: የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው:: በፈጣሪው ትዕዛዝ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለ40 ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል:: (ዘጸ. 20:1, 31:18)

#6 ኪዳነ ዳዊት ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት: ጻድቅ: የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው:: እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ" (መዝ. 131:11) ሲል ምሎለታል:: አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን:: (መዝ. 88:35)

#7 ኪዳነ ምሕረት በብሉይ ኪዳን የነበሩ ስድስቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲዖል ማዳን ግን አልቻሉም:: ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር:: ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማኅጸን አደረ:: በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ: አድጎ: ተጠምቆ: አስተምሮ ለአለም ቤዛ የሆነበት ነው ።

@ortodoxtewahedo
"ሕጻናት ሀገር ያሳጡን ክፉዎች ብለው ሳይረግሙን ቶሎ እንመለስ።" #ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጾመ ነነዌን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል።

የመልእክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

ስለሀገራችን ነነዌ እንጸልይ!

ለተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ በሙሉ፣ ይህን መልእክት ስጽፍ በእንባ እየታጠብኩ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጎዳል ብዬ በማሰብ መልካም ነገርን እንኳ ለመናገር ወስኜ ነበር። ነገር ግን፣ የወገኖቼ መቸገር፣ ምግብ ሳይጠፋ መራብ፣ ወንዝ ዳር ተቀምጦ መጠማት፣ በትርጉም የለሽ ግጭቶች መሠቃየት የኅሊና እረፍት ሊሰጠኝ አልቻለም። መንፈሴ አሁንም “ኢትዮጵያ ለምን መፍትሔ አጣች? ኢትዮጵያ ለምን መፍትሔዋን እግዚአብሔርን እና መንገዱን ተወች? መቼስ ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት ትመለሳለች?" በሚሉ ጥያቄዎች ይረበሻል። ብቻዬን ባለቅስም አልወጣልህ ስላለኝ የአምናው እንባና ጩኸታችሁን፣ ለእኛ የነበራችሁን እምነትና ሐዘኔታ እያሰብኩ ቢያንስ አብራችሁኝ ታለቅሱ ዘንድ ይህን ጻፍኩ።

ከሁሉ አስቀድሞ ምሕረቱ ብዙ የሆነው አምላክ ባለፈው ዓመት ቤተ ክርስቲያን መከራ ደርሶባት በጾመ ነነዌ ከፊቱ ቀርባ ስታዝን ምሕረቱን ከእኛ ያላራቀብን እግዚአብሔር ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ ለዓመቱ አድርሶናልና ክብር ምሥጋና ይሁንለት!

እንደምናስታውሰው አምና ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ብዙ ምእመናን ወገኖቻችን ተገድለዋል፤ ታሥረዋል፤ ቆስለዋል፤ ቀሪዎቹ እኛም የኅሊና ቁስላችንን እያስታመምን እነሆ ሌላ ጾመ ነነዌ ላይ ደርሰናል። ዘንድሮም እንደአምናው ከመንፈስ ልጆቼ ጋር በጋራ እንዳናለቅስና በእግዚእብሐር ፊት እንባችንን እንዳናፈስ ከ27 ዓመታት በኋላ እንደገና በአዲስ መልከ ለስደት ተዳርጌያለሁ።

“ነነዌ ኢትዮጵያ ናት!” ያልኩትን ጾም ቤተ ክርስቲያን የጣለችብኝን ኃላፊነት እየተወጣሁ፣ በኢትዮጵያ ካሉ ምእመናን ሆኜ ባለ መጾሜ የበለጠ ጾሙን በተሰበረ ልብ እንዳሰብ አድርጎኛል። ዛሬ ይህን በምጽፍበት ሰዓት እንኳን መነኮሳት ወንድሞቼ የሆኑት የደብረ ከዋክብት ዝቋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መነኮሳት በግፍ መገደላቸውን ሰምቼ እያነባሁ ነው።

ወገኖቼ፣
ትናንት ኃይለ እግዚአብሔርን ተማምነን በጾም በጸሎት እንዳሳለፍነው ሁሉ ዘንድሮም ከአምናው የበለጠ ማቅ የምንለብስበትና አመድ የምንነስንስበት ጊዜ ላይ ነን። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ የመበዳደሉ
መጠን፣ የድሆች ቁጥር፣ በማኅበራዊ ቀውስና ግጭት የሚሰደዱና የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ዛሬም እየጨመረ ነው። ሰዎች እንደልባቸው ወጥተው መግባት ተቸግረዋል። ጎረቤት ከጎረቤት ጋር በጥርጣሬ ይኖራል። በዚህ ጊዜ በእግዚእብሐር ፊት ቀርቦ አለማልቀስ፣ መጽናናትን ከእርሱ አለመፈለግ ይቻላልን? ዛሬም እንደ ልማዳችን በእግዚአብሔር ፊት ማቅ ለብሰን አመድ ነስንሰን የሦስት ቀን የሐዘን ጾም ውስጥ እንግባ። እንባችንንም በእግዚአብሐር ፊት እናቅርብ። መፋቀር ትተን ስለመገዳደላችን፣ ምግብ ሳይቸግረን በጠኔ ስለ መማቀቃችን፣ ስፍራ ሳይጠብበን ስለመሰደዳችን፣ ትሕትናን ትተን ትዕቢትን የኑሮ ዘይቤ ስለማድረጋችን፣ መግቦቱ ሳይጎድልብን ስግብግብነትን ሙጥኝ ስለማለታችን ኑ እናልቅስ። በኃጢኣታችን ምክንያት ስለሚሠቃዩት ዐቅመ ደካሞች፣ ስለወላጅ አልባዎች፣ ስለጧሪ አጦች ኑ እናንባ። በልባችን የሞላው እልኸኝነት ያዋረዳቸውን ወንድም እኅቶቻችንን፣ እንደስንቅ በጉያችንን የሸሸግነው ጠበኝነት ጧሪ ያሳጣቸው ወላጆቻችንን፣ አእምሯችንን የያዘው ቂመኝነት ሰላም የነሣቸውን ሕጻናት እያሰብን ኑ በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ እንግባ። ከእልኸኝነታችን ቁስል እንፈወስ። የወላጆቻችን እንባ ጎርፍ ሆኖ ሳያሰጥመን እንትረፍ። ሕጻናት ሀገር ያሳጡን ክፉዎች ብለው ሳይረግሙን ቶሎ እንመለስ፡፡

እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ
"ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ የምነግርህንም ስብከት ስበክላት አለው። ዮናስም ተነሥቶ እንደ እግዚአብሔር ቃል ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌም የሦስት ቀን መንገድ ያህል እጅግ ታላቅ ከተማ ነበረች። ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኸም። በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ። የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾምም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ። ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም ይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም” (ትን. ዮናስ 3:2-10)።

የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ሆይ፣
ዛሬም እግዚአብሔር የምሕረት እጁ እንደተዘረጋ ነው። ዛሬም የእናንተ የቡሩካን ምእመናን ጸሎት ልባቸው የደነደነውን ያለዝባል። ለመሪዎች የእግዚአብሔርን መንገድ ያሳያል። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ከርስቲያን በኢትዮጵያ ምድር በዚህ ሁሉ ወጀብ ውስጥ ዛሬም ጸንታ ያለችው አሁን ባለነው መሪዎቿ ብቃትና የመሪነት ችሎታ ሳይሆን እናንተ ለቤተ ክርስቲያናችሁ ባላችሁ ታማኝነት፣ ልባችሁ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ የፈሰሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ዘወትር በክርስቶስ በሆነ ተስፋ ለበጎ ነገር ሁሉ ስለሚያተጋችሁ ነው (ሮሜ 5፣ 5)።

ስለሆነም ኑ አብረን በእግዚብሔር ፊት እነዚህን ሦሰት ቀኖች በእንባ እናሳልፋቸው። እንባን ሁሉ ከዓይን የሚያብስ አምላካችን ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ምሕረቱም የበዛ ስለሆነ እንባችንን ያብሳል። ጸሎታችንንም ይቀበላል። እኛ የክርስቶስ አካል ነንና በወደደን በአምላካችን ተስፋ አንቆርጥም። ነገር ግን በእርሱ ፊት ኃጢኣታችንን እንናዘዛለን፤ ይቅርታውንም እንማጸናለን፤ እንባችንንም እንደነነዌ ሰዎች እንዲህ እያልን በፊቱ እናፈስሳለን፦ ጌታ ሆይ! “ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና። ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ አምላካችንንም ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል። ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና። እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል” (ኢሳ 59:12-15)። ይህን ስናደርግ ጆሮው ትሰማናለች፤ ከማዳንም የማታጥረው ክንዱ የኃጢኣታችንን ግድግዳ ደምስሳ ሰላሙን ትሰጠናለች። የተሠወረብንንም ውብ ፊቱን ትገልጽልናለች (ኢሳ 59:1-2 )።
ስለዚህም ወንድም እኅቶቼ፣
እነዚህን ሦስት ቀናት በእግዚአብሔር ፊት እናለቅስ ዘንድ በሀገረ ስብከታችን ስም ጥሪዬን አቀርባለሁ። የቻለ በቤተ ክርስቲያን ከወንድም እኅቶቹ ጋር ተሰብስቦ፣ ያልቻለም ባለበት ቦታ ሆኖ ልቡን ከወንድም ከእኅቶቹ ጋር እንድ አድርጎ በንስሐ ይጸልይ። እግዚአብሔር አምላከ ጸሎታችንን ይስማ! ልባችንን፣ ቤተ ከርስቲያናችንንና ሀገራችንን ከክፉ ሁሉ ያድንልን። አሜን።

አባ ጴጥሮስ (የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ)
የካቲት ፲፬ ፪ሺ፲፮ ዓ.ም

@ortodoxtewahedo
በአክሱም ጽዮን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተነሳው የእሳት አደጋ ጉዳት ሳያደርስ በምዕመናንን ርብርብ በቁጥጥር ውስጥ ውሏል
***

እናታችን ጽዮን ....ይህ ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ ክፉ አይድረስሽ።ከእነ ሠላምሽ ምህረት ከልጅሽ አሰጭን

@ortodoxtewahedo
"በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኅዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆነናል "

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

@ortodoxtewahedo
" በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር ተፈርዶብናል "
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

" እንጀራና ሰላም የተራቡ ወገኖችን እናፅናናቸው "

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይህንን ያሉት ዛሬ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጾመ ነነዌን አስመልክቶ ባስተላለፉት አባታዊ ቃለ በረከት ነው።

" የነነዌን ጾም ስንጾም በአንድ በኩል እንጀራን የተራቡ፣ በሌላ በኩል ሰላም የተራቡ ወገኖች ስለአሉን ወደ እነዚህ ወገኖች የንስሐን ስብከት የማጽናናትን መልእክት ይዘን መሄድ አለብን"
ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

" ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን፣ በረሃብ፣ በመታረዝ፣ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን የመከራ ማቅ በሕሊናችን ተሸክመን ስለጾሙ የተውነው የዕለት ቊርሳችንን ለእነርሱ ሞትን ማባረሪያ እንዲሆን ልንፈቅድ ያስፈልጋል " ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚሁ መልዕክታቸው " በፈረሰ ልብ የሚገነቡ ከተሞች የቀን ጉዳይ እንጂ ፍርስራሽ መሆናቸው አይቀርም " ብለዋል።

ነነዌ ከተማዋ አድጎ ልማቷ ቢሰለጥንም እግዚአብሔር ግን የተመለከታት ፈርሳና ተበላሽታ ነበር ... ያሉት አቡነ ማትያስ "በፈረሰ ልብ የሚገነቡ ከተሞች የቀን ጉዳይ እንጂ ፍርስራሽ መሆናቸው አይቀሬ ስለሆነ ዛሬ ነነዌ ከታሪክ መዝገብ ላይ ብትሰፍርም በዓይን ግን የምትታይ አይደለችም " ሲሉ አመሳክረው አስገንዝበዋል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነነዌን ጾም ያወጀችው " ዓመት ሙሉ የተጣላ በነዚህ ሦስት ቀናት እንዲታረቅ፣ ሲካሰስ የሚኖር ሕዝብም ወደ ፈጣሪው በንስሐ እንዲመለስ ነው " ሲሉ አውስተዋል።

ፓትርያርኩ በቃለ በረከታቸው ከሰሞኑ በጥንታዊው ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስለ ተገደሉት መነኮሳትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

" ዓለሙን ትተው በፈቃዳቸው ረሀብተኛ እና ጥማተኛ ሆነው ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ መነኮሳት ጫካው መኖሪያችሁ፣ ዳዋው ልብሳችሁ፣ ቅጠሉ ምግባችሁ መሆን አይችልም ተብለው የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎንጭተዋል " ብለዋል።

አክለውም " እነርሱ በሥጋ እየሞቱ እኛም በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆነናል " በማለት አስፍረዋል።

የፓትርያርኩ መልዕክት ሲቀጥልም " ይህ ለእነርሱ ክብር ቢሆንም ለቤተክርስቲያን ግን ታላቅ ደወል ያሰማ ክስተት ነውና ውሉደ ክህነት ቤተክርስቲያናችሁን የምትጠብቁበት፣ የመከራውን ማዕበል ለማለፍ በመንፈሳዊ ፍቅር አንድነትን ማጽናት የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን እናሳስባለን " ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በመልዕክታቸው መጨረሻ " ታላቅ ሀገር ይዘን፣ ምድሩ ሳይጠበን አመል እያጋፋን ነው " ሲሉ ሀዘንና ቁጭት ያዘለ ቃለ በረከታቸውን አስተላልፈዋል።

" ጾማችን፣ጸሎታችን ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ለሀገር ደኅንነት፣ ለሕዝብ ድኅነት እንዲያመጣልን
እግዚአብሔር ይቅር ብሎን ዘመኑን በምሕረት ያሻግረን ዘንድ በታላቅ ንስሐ፣ በጸሎትና በአስተብቍዖት ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ አባታዊ መልእክታችንን በመሐሪው አምላክ ስም እናስተላልፋለን " በማለት የነነዌ ጾም በማስመልከት ያስተላለፉትን ቃለ በረከት ቋጭተዋል።

በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላዓለሙ አሜን !

@ortodoxtewahedo
2024/09/29 23:32:54
Back to Top
HTML Embed Code: