Telegram Web Link
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
'' በፍጥረት አለም ባለመስጠቱ የሚመሰገን ባለመስጠት ቸርነትን የሚያደርግ አለመስጠት ስጦታ የሆነለት ፍጥረት የለም ! እግዚአብሔር ግን ባለመስጠቱ የሚመሰገን አለመስጠቱ ቸር የሚያስብለው አለመስጠት ስጦታ የሆነለት ቅዱስ አምላክ ነው🥰🥰''

ዲ/ን ኤርሚ
"ክርስቶስሃ መድኅነ ንሰብክ"
***
"በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።
እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥
ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥
በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።
በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤
ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥
መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።"
(ፊል. 2፥5-11)
***
ጥንተ ስቅለቱ ለመድኃኔዓለም!
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
Do not ask from priests more than you are, be understanding and tolerant with them, and instead of judging them, better pray!

Father Dometie Manolache
እንደ ሙሽራ እንጠብቀው ወይስ እንደ ሌባ ይምጣብን?!
***
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
***
ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ምጽአቱ ሲናገር ሁለት የሚቃረኑ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል፦ ሙሽራ እና ሌባ። ሙሽራ በደስታ እና በእልልታ የሚጠበቅ ነው። ሌባ ደግሞ ሳያስቡት መጥቶ የሰውን ሕይወት የሚያመሰቃቅል እና ንብረቱን የሚያጠፋ ነው። ታዲያ ጌታችን በአሥሩ ደናግል ምሳሌ ነቅተን በእልልታ መብራት ይዘን፣ ነጭ ለብሰን ልንጠብቀው የሚገባን ሙሽራ እንደሆነ ነግሮናል። "እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ፤" እንዲል። (ማቴ. 25፥6-10) በሌላ ቦታ ደግሞ "ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፤" ይላል። (ማቴ. 24፥42-44) ቅዱስ ጳውሎስም ይህን የጌታችን ትምህርት ይዞ "የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና፤" ይላል። (1ኛ ተሰ. 5፥2)
ወዳጄ፥ አምላካችን ክርስቶስ ስለ ምጽአቱ ሁለት ምስሎችን ስሎልናል፦ የሙሽራ እና የሌባ። እርሱ 'መጣብን' የሚባል ሌባ ሳይሆን 'መጣልን' የሚባል የሚወደድ ሙሽራ ሆኖ እንጠብቀው ዘንድ ነው በጎ ፍላጎቱ። እኛ በፍቅር ሆነን ነቅተን ካልጠበቅነው ግን እርሱ የሚፈልገው ያ ባይሆንም እንኳ በእኛ ችግር ምክንያት እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል። የእርሱ ጽኑ መሻት ግን እልል እያልን እንደ ተወዳጅ ሙሽራችን በጉጉት እንድንቀበለው ነው። ንጉሣችን እንደ አእዛብ ነገሥታት በፍርሃት የሚገዛን ሳይሆን እንደ ሙሽራ መወደድን የሚመርጥ ነውና። ክብሩ በማዳኑ የሆነ ድንቅ ነውና። እኛ ግን እንደ ምን ልንቀበለው እየተዘጋጀን ነው? እንደ ሙሽራ ወይስ እንደ ሌባ?
ክርስቶስ የሚመጣው በታላቅ ክብር ነው። "መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤" እንዲል። (ማቴ. 24፥27) ነገር ግን ይህ ክብር ተዘጋጅተው ለሚጠብቁ ምዕመናን ለመደነቅ እና እልል ብሎ ለማመስገን የሚያነሣሣ እንጂ የሚያሸብር አይደለም። የሚወደድ እንጂ ባልመጣብን የሚባል አይደለም። እነ ቅዱስ ጴጥሮስ በታቦር ተራራ ላይ ክብሩን ሲያዩ ከግርማው የተነሣ ቢፈሩም ነገር ግን የሚወደድ ስለሆነ በዚህ መሆን መልካም ነው ብለዋል። የእግዚአብሔር ክብር ሲገለጥ ቅዱሳንን በፍቅር ይስባል፤ ከፍርሃታቸው አጽንቶ በዚህ እንሁን ያስብላል። ለዓመጸኞች ግን የሚገቡበት ቀዳዳ እስኪያጡ የሚያስጨንቅ ይሆናል። ሌባ ሲመጣ እንደሚያሸብረው እንደዚያ ይሆናል። ጸሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት እና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የጌታችን መምጣት አብረው ያከብራሉ። ይህ ሁሉ ለቅዱሳን ሙሽራውን የመቀበል ሥርዓት አካል (cosmic celebration) ነው፤ ደስታና እልልታን የተሞላ ትእይንት ነው። የክርስቶስን ማዳን ችላ ላሉ ግን የፍጥረታት እንግዳ እንቅስቃሴ ከሽብር ላይ ሽብር የሚፈጥር ዱብ እዳ ነው።
አምላካችን እንደ ሙሽራ እልል እያልን በፍቅር እንቀበለው ዘንድ እንጂ እንደ ሌባ መምጣት አይፈልግም። ለአንዳንዶቻችን ግን በንስሐ ካልተመለስን ይህ መሆኑ አይቀርም። የእርሱ ፍላጎት ሁላችንም በደስታ እንቀበለው ዘንድ ስለሆነ "ንቁ!" "አስተውሉ!" "ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ!" እያለ በፍቅር ቃል ቀድሞ በተደጋጋሚ ተናግሮናል። ምን እያደረግን ነው? ለሙሽራው እንዘጋጃለን ወይስ ሌባ በድንገት እንደሚመጣ አስጨናቂው ቀን በድንገት ይደርስብን ዘንድ ተዘልለን ተቀምጠናል? ይልቁንም የመጨረሻው ዘመን እየደረሰ እንደሆነ እያሰብን ራሳችን እንመርምር። "መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ።" (ራእይ 22፥17)
***
Bereket Azmeraw
"ስለ እኛ የሚማልደው…"
***
ይህ ጉዳይ ደጋግሞ የሚነሣባቸውን ሦስት የቅዱሳት ጥቅሶች እንጥቀስ እና ድንቅ የሆነ ውስጣዊ ትርጉማቸውን እንይ፦
***
"እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?
ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል?
የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኰንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?
ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥
ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።" (ሮሜ. 8፥31-39)
***
"እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥
እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።
እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤
እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤
ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።
ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤
እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።
ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።
ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን።" (ዕብ. 7፥20-8፥1)
***
"ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።" (1ኛ ዮሐ. 2፥1-2)
***
እነዚህ ጥቅሶች የጋራ መነሻቸው ቅዱስ ጳውሎስ ደጋግሞ እዚህም ላይ የጠቀሰው መዝሙር 109/110 ነው። ይህ መዝሙር በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብዙ ቦታዎች የተጠቀሰ እና ጌታችን ራሱ ስለራሱ የጠቀሰው ነው። በሐዋርያት በብዛት ከተጠቀሱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንደዚህ መዝሙር የሚበዛ የለም። ይህ አጭር ግን እምቅ የሆነ የመዝሙር ትንቢት እንዲህ ይላል፦
***
"እግዚአብሔር ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።
እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ።
ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ።
እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም።
እግዚአብሔር በቀኝህ ነገሥታትን በቍጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል።
በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ያበዛል፤ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል።
በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፤ ስለዚህ ራስ ከፍ ከፍ ይላል።" (መዝ. 109/110፥1-7)
***
በዚህ ትንቢት ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ የሚቀመጥ ነገር ግን ደግሞ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ዘላለማዊ የሆነ ካህን መሆኑ ተነግሯል። ለወትሮው ካህን በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል እንጂ በእግዚአብሔር ቀኝ በመለኮታዊ ዙፋን ላይ አይቀመጥም! ለዚህ እንግዳ ሥርዓት አንክሮ ይገባል። ይህ ምንድር ነው? በመለኮቱ ተቀምጦ በሰውነቱ ቆመ (ማለደ) እንዳንል ይህ ክርስቶስን ከሁለት መክፈል ነው። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ያዛባል፤ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የሆነው በሰውነቱ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑም ነውና! መልከ ጼዴቅ ምሳሌው የሆነው በዘላለማዊነቱ (መነሻው ባለመታወቁ) እንደሆነ አንርሳ። እንዲህ ያለው ዘላለማዊነት ደግሞ የሰው ባሕርይ አይደለም። በሌላም ቦታ "ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል፤" ሲልም ክህነቱ ልዩ የሆነ ሰውነቱን ብቻ ሳይሆን አምላክነቱንም የሚገልጽ እንደሆነ እየነገረን ነው። አምላክ ሆኖ እንዴት ካህን ይሆናል ብለህ ብትጠይቅ ግን ካህን ሆኖስ እንዴት በእግዚአብሔር ዙፋን ይቀመጣል? ብለን እንጠይቃለን። ይህ ንጉሥም ካህንም ከሆነው ከመልከ ጼዴቅ የተሻለ ምሳሌ የሌለው እንግዳ ሥርዓት ነው።
ታዲያ ሊቀ ካህናት ሆኖ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ ማለት ምን ማለት ነው? ክርስቶስ በሞቱ እና በትንሣኤው አንጽቶ እና ቀድሶ የእግዚአብሔር ልጆች አድርጎ ለአባቱ ላቀረባቸው ምእመናን የእግዚአብሔር ዙፋን "የጸጋ ዙፋን" መሆኑን እና ከስህተት የሚያነሣቸው እና ከመከራ የሚጠብቃቸው ጸጋው እና ረድኤቱ ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር መሆኑን ለመሳየት ነው። (ዕብ. 4፥16) እነዚህን ምእመናን የሚቸገሩባቸውን እና ድል ያደርጉ ዘንድ ከእግዚአብሔር ጸጋ እና ረድኤት የሚለምኑባቸውን ነገሮች መዝሙሩ የክርስቶስ ጠላቶች ይላቸዋል። "ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ" እንዲል። ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሮሜ 8 ላይ "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? … ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል?" እያለ እየጠየቀ ይዘረዝራቸዋል። ቅዱስ እስጢፋኖስም መከራ ሲጸናበት ክርስቶስ "በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ" ታይቶታል። (የሐዋ. 7፥59) ("ቆመ" የተባለው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው፤ ሊቃውንት እንደሚሉት መቆሙ የመጀመሪያውን ሰማዕቱን ነፍስ በክብር ለመቀበል ነው። ለመማለድ እንዳይባል እስጢፋኖስ "ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል" ብሎ አምላክነቱን በሚመሰክር ቃል ተናገረ እንጂ "ማልድልኝ" አላለም። ነፍስን የሚቀበል እግዚአብሔር ነውና። እሱም ቆሞ ነፍሱን ሊቀበል እንጂ ምንም ሲያደርግ አልታየም።)
ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ እና በዕብራውያን ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡን ተናግሮ ነው ቀጥሎ "ስለኛ የሚማልደው" የሚለው። ይህም መዝሙሩ ቀድሞ በትንቢት "በቀኜ ተቀመጥ" ካለ በኋላ "ለዘላለም ካህን ነህ" ስለሚል ነው። በመሆኑም የክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥ እና ዘላለማዊ ክህነቱ በመዝሙሩ፣ በሮሜ እና በዕብራውያን አብረው በጥምረት የተነገሩ ናቸው። ቀድሞ በምድር የክህነት አገልግሎት እያደረጉ በሰማይ ካለው ዙፋን ምሕረቱን እና ረድኤቱን ይጠብቁ ነበር። አሁን ግን የክህነት መቅደሱ እና የረድኤት ዙፋኑ አንድ ሆነ። ዙፋኑ ራሱ በዘላለማዊት መሥዋዕት መዳንን ያስገኘ ሰማያዊ ካህን ያለበት ቅድስተ ቅዱሳን ሆነ። ቀድሞ
ሊቀ ካህናቱ በትህትና ቆሞ የሚያገለግልባት ቅድስተ ቅዱሳንም ሰማያዊው እና መለኮታዊው ሊቀ ካህናት ቆሞ ሳይሆን ተቀምጦ ምሕረትን የሚያስገኝባት "የጸጋ ዙፋን" ሆነች። (ዕብ. 4፥16)
እንግዲህ ቀድሞ በምድር ላይ ኃጢኣት ስንሠራ የሚያስታርቁን፣ ጠላት ሲያይልብን ከእግዚአብሔር ረድኤት የሚያሰጡን የሚማልዱልን ነቢያትና ካህናት ነበሩን፤ አሁን ግን ያ ሁሉ ካለፈ ምን እንሆናለን? እግዚአብሔር ያለ አማላጅ እና መካከለኛ ትቶናል? ከእግዚአብሔር ጋር ማን ያገናኘናል? እንደ ነቢያቱ (ምሳሌ ሙሴ) እና እንደ ሊቃነ ካህነቱ መካከለኛ ማን ይሆነናል? ብሎ የሚጨነቅ እንዳይኖር በመዝሙሩ "ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ" ተብሎ የእግዚአብሔር አዳኝነት ተነገረ። በዚህም የክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጥ ጠላቶቹ (የምዕመናን ጠላቶች) ድል የሚሆኑበት፣ በመስቀሉ የተገለጠ ፍቅሩ እና ኃይሉ ያለማቋረጥ የሚሠራበት የረድኤት እና የጸጋ ዘመን እንጂ እግዚአብሔር ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ (passively) የሚያይበት እንዳልሆነ ያመለክታል። በምዕመናን ላይ መከራ የሚያጸኑት ለክርስቶስ "ጠላቶቹ" መባላቸው እግዚአብሔር ምዕመናንን የሚጠብቀው ስለ ክርስቶስ (አካሉ ስለሆንን) እንደሆነ ያሳያል። "ይማልዳል" መባሉ ጸጋውን እና ረድኤቱን ሁሉ በእርሱ ምክንያት የምናገኘው በመሆኑ ነው። አብ በልጁ ፍቅር ይጠብቀናል፤ አካሉ ያደረገን የወልድ ፍቅርም የመለኮታዊ ረድኤት ምንጭ ነው። (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
በዮሐንስ መልእክትም "በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን" የሚለው በሌላ መንገድ ቢነገርም ያው ነው። "በአብ ዘንድ" ማለት "በአብ ቀኝ የተቀመጠ" ማለት ነው።
ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ "ምልጃ" ሲናገሩ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡን ሁሌ የሚነግሩን እንደ ቅዱሳን ምልጃ ያለ ልመና አለመሆኑን፣ ይልቁንም አዳኛችን ክርስቶስ የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ በዙፋኑ ላይ መቀመጡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የጸጋ እና ረድኤት ምንጭ መሆኑን ጥልቅ በሆነ ዘይቤ (metaphor) የሚገልጽ ምስጢር ነው። ከፍቅሩ የተነሣ አካሉ ያደረገን እርሱ መድኃኒታችን ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ መቀመጡ ምልጃ ሁሉ ሊያስገኘው የሚችለውን ጸጋ እና ረድኤት አስገኝቶአል፤ ያለማቋረጥም ያስገኛል።
ታዲያ ቅዱሳን ለምን ይማልዳሉ? የሚል ይኖራል። ይህ ከመነሻው የተሳሳተ ጥያቄ ነው። ቅዱሳን የሚማልዱት የክርስቶስ ተከታዮች ስለሆኑ ነው። በዙፋኑ ላይ ሆኖ ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ የሚሻው እና የጸጋ ሁሉ ምንጭ የሆነው የእርሱ መንፈስ ጰራቅሊጦስ ስላደረባቸው ነው። (መንፈስ ራሱ "ይማልዳል" እንደተባለ አንርሳ) እሱ ሁሉን ስለሚወድ እና ሁሉን ስለሚሰጥ እኛ ለምን ሰውን እንወድዳለን? ለምንስ መልካም እናደርጋለን? ብሎ እንደመጠየቅ ነው። የክርስቶስ መካከለኝነት እና የቅዱሳን ምልጃ ለአንዳንዶች ቢጣላባቸውም ለታላቁ ሐዋርያ ለቅዱስ ጳውሎስ አልተጣላበትም፤ "በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለው 'መካከለኛ' አንድ ነው፤ እርሱም ሰው የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤" ባለበት ቦታ "ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ፤" ብሎ አስተምሮአልና። (1ኛ ጢሞ. 2፥1-2)
***
ለማጠቃለል ያህል በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተነገረው ይህ ጉዳይ ከፊደል የሚያልፈው ድንቅ ምስጢሩን መረዳት ይገባል። ቀድሞ እነ አርዮስ ክርስቶስን ፍጡር ለማለት እነዚህን ጥቅሶች ይጠቅሷቸው ነበር። (St. Athanasius, Against the Arians, Discourse IV) ሌሎችም ሰውነቱን ነጥሎ ለማየት እና ሁለት ባሕርይ ለማለት ይጠቅሷቸዋል። የቅርቦቹ ደግሞ የቅዱሳንን ምልጃ እና ክህነትን ለመቃወም እንዲሁም ሌሎች ድብቅ የሆኑ ነገረ-ክርስቶሳዊ እሳቤዎችን (latent Arianism and Subordinationism) ለማንጸባረቅ ይጠቅሷቸዋል። ይህ ሁሉ ስለሆነ ግን ጤነኛ መልእክታቸውን አንጥልም። ከሐዋርያዊ ትምህርትም አንቀንስም። በትክክለኛ ዓውዳቸው መረዳት ይገባናል እንጂ። ሥጋ ባለበት አሞራዎች ይሰበሰባሉ እንደተባለው ብዙ ውዝግብ የሚበዛባቸው ጥቅሶች ጠለቅ ብለን ስናያቸው ድንቅ መልእክት ያላቸው ናቸው።
(እነዚህን ጥቅሶች መና*ፍ*ቃ*ን አብዝተው ስለሚጠቅሳቸው እንዳንጥላቸው እና እንዳንጠላቸው ይልቁንም ከፊደላቸው አልፈን መንፈሳቸውን በመረዳት እንድንጠቀምባቸው ይህ ተጻፈ።)

Dn Bereket Azmeraw
"ስለ አንተ ድክመት የሚነግርህን ጥሩ #ባልንጀራ አድርገህ ያዘው።"

•• ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
👆👆👆👆👆
ሃይማኖት እና እምነት
* ሃይማኖት ምንድን ነው?
* እምነት ምንድን ነው?
* የእምነት አይነቶች በመጽሀፍ ቅዱስ
ሃይማኖት አያስፈልግምን ?
* ክርስትና ሃይማኖት አይደለምን?
* ድህነት በሃይማኖት አይደለምን?
* በሞተልን ጌታ የምንገኘው እንዴት ነው?
* ወንጌል በየትኛውም ሃይማኖት ቢሰበክ ችግር የለውምን?
* ዶግማ ማለት ምን ማለት ነው?
* ኦርቶዶክስ ተዋህዶበሰው የተመሰረተች ነችን?
* የሃይማኖት ክፍልፋይ ስም ነው ችግራችን? ወይስ የመጽሀፍ ቅዱስ አረዳድ?
* የመጽሀፍ ቅዱስ ክርስትና እንደምን ያለ ነው?
* በሃይማኖቶች መካከል ያለው የአስተምህሮ ልዩነት ችግር የለውምን?

#መድሎተ_ጽድቅ

#ዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ
"God so loved you; for this reason He brought you into being. God so loved you, for this reason He created you in the best image; He created you in His image. He gave you understanding, wisdom, spirit, immortality, beauty in all things"

+ Pope Shenouda +

"እግዚአብሔር እንዲሁ ወዶሃልና፤ ስለዚህም ወደ መኖር አመጣህ። እግዚአብሔር እንዲሁ ወዶሃልና፤ ስለዚህም በመልካሙ መልክ (ምስል) ፈጠረህ፤ በመልኩ በአምሳሉ ፈጠረህ። ማስተዋልን፣ ጥበብን፣ መንፈስን፣ ዘላለማዊነትን፣ በሁሉም ነገር ውበትን ሰጠህ።"

+ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሺኖዳ +
2024/11/15 09:26:09
Back to Top
HTML Embed Code: