Telegram Web Link
'' ለክርስቶስ ከሚኖር ሰው በቀር ነፃ ሰው የለም ! ''

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://www.tg-me.com/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️

#ለሌሎች_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ🤗
መስቀል ዕፀ ሕይወት ነው። መስቀል ዕፀ መድኃኒት ነው። መስቀል ዕፀ ትንቢት ነው። መስቀል ዕፀ ዕረፍት ነው።

መስቀል ሰይጣንን የሚያጠፋ ምሳር ነው። የአጋንንትንም ራሶች የሚቆርጥ ሰይፍ ነው።

መስቀል ርኵሳን መናፍስትን የሚወጋቸው የእሳት ዘገር ነው። የአመስቴማውያንንም ሠራዊት የሚመታ የመብረቅ ጦር ነው።

መስቀል ማኅተመ ሥላሴየሌለው ሰው ወደእርሱ ሊቀር በው የማይቻለው አምባ መጠጊያ ነው። መስቀል ከግራም ከቀኝም ለሚመጣ ጠላት የጽድቅ ጋሻ ነው። ጳውሎስ ውጊያችሁ ከሥጋና ከደም ጋር አይደለምን እንዳለው መስቀል የጦር መሣርያ ነው።

መስቀል የጦር ውጋት ሊቀድደው፣ የቀስትና የዘንግም ጫፍ ሊበላው የማይችል የሃይማኖት ጥሩር ነው። መስቀል አማሌቃውያንን ለመዋጋት በራፊድ በረሐ በተዘረጋው ስሙሴ እጅ አምሳል የተሠራ ነው።

መስቀል ሰሙሴ እጅ ወደ ውስጥ በተጨመረ ጊዜ መራውን ውኃ በቀር በረሐ ያጣፈጠ ነው። መስቀል የቅድስናና የንጽሕና ማኅተም ነው።

መስቀል ለሚጋደሉ የድል አክሊል፤ ወደ በጉ ሰርግ ለተጠሩትም የሰርግ ልብሳቸው ነው። መስቀል የማይነጥፍ ምንጭ፣ በቁዔትም ጥቅምም የሞላበት የክብር ጉድጓድ ነው።

(ውዳሴ መስቀል - በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ)

#ለሌሎች_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇🤗
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://www.tg-me.com/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
+ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር +

☞ ተወዳጆች ሆይ ጊዜ ሳለልን ድኅነታችንን እንፈጽም፡፡ ጊዜ ሳለልን ለመብራታችን ዘይት የተባለ ምጽዋትን እንያዝ፡፡ ጊዜ ሳለልን መክሊታችንን ለማብዛት እንፍጨርጨር፡፡ በዚህ ዓለም ሳለን ይህን ለማከናወን ልል ዘሊል እና ሐኬተኞች ከኾንን በወዲያኛው ዓለም እልፍ ወትእልፊት ጊዜ ወዮ ብለን ብናለቅስ ብንጮህም እንኳን የሚረዳን የለምና፡፡ ያ ባለ አንድ መክሊት ሠራተኛ አንዲቷን መክሊት ሳይቀንስ ለጌታው ቢያስረክብም ከኩነኔ አላመለጠምና፡፡ አምስቱ ሰነፎች ደናግልም ጌታችንን ለምነውት ነበር፤ በሩን አንኳኩተው ነበር፡፡ ነገር ግን ልመናቸውም ማንኳኳታቸውም ከንቱ ነበር፥ ጥቅም አልባ ነበር፡፡

☞ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ዐውቀን በሀብታችንም፣ በትጋታችንም፣ ለወንድማችን በምናደርገው ማናቸውም ጠቃሚ ነገርም የዓቅማችንን ያህል እንጣር፡፡ መክሊት የተባለው የእያንዳንዱ ሰው በእጁ ያለውና ማድረግ የሚችለው ነገር ማለት ነውና፡፡ ለአንዱ ወንድሙን መጠበቅ ሊኾን ይችላል፥ ለአንዱ በገንዘቡ ደግ ነገር ማድረግ ሊኾን ይችላል፥ ለሌላው ማስተማር ሊኾን ይችላል፥ ለሌላው ደግሞ ይህን በመሰለ ሌላ ነገር ሊኾን ይችላልና ጊዜ ሳለልን በሞተ ሥጋም ሳንወሰድ መክሊታችንን እናብዛ፡፡ አንድ ሰውስ እንኳን መክሊቴ አንዲት ናት አይበል፡፡ የተሰጠችህ መክሊት አንዲት ብትኾንም አንተ ንቁ ከኾንህ ንዑድ ክቡር ከመባል አትከለከልምና፡፡ ምንም ያህል ድኻ ብትኾንም ከዚያች ኹለት ሳንቲም ከሰጠችው ሴት በላይ ድኻ ልትኾን አትችልምና የተሰጠቺኝ ትንሽ ናት አትበለኝ፡፡ ከቅዱስ ጴጥሮስና ከቅዱስ ዮሐንስ በላይ ያልተማርክ ልትኾን አትችልምና እኔኮ አልተማርኩም አትበለኝ፡፡ እነርሱ ምንም ያልተማሩ ቢኾኑም ባሳዩት ትጋት ርስት መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ተችሎዋቸዋልና እኔ አይቻለኝም አትበለኝ፡፡

☞ እግዚአብሔር አንደበትን የሰጠን ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር እግርን የሰጠን ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር ብርታትን፣ አእምሮን፣ ማሰብን የለገሰን ለዚህ ነው፡፡ እነዚህን ኹሉ የሰጠን ለራሳችን እንድናተርፍባቸውና ለባልጀሮቻችንም እንድንጠቅምባቸው ነውና ኹለት ወይም አምስት መክሊት አልተሰጠኝም አትበለኝ፡፡'

ተርጓሚ፦ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ

#ለሌሎች_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇🤗
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://www.tg-me.com/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
በመስቀል ጉዳይ ከትውፊታውያን አብያተ ክርስቲያናት የምንጋራቸው ምንባባትና ሥርዓታት

ደብተራ በአማን ነጸረ

--
1.ውዳሴና ክብረ መስቀል
ውዳሴ መስቀል የሚባል የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድርሰት አለ፡፡ በእንግሊዝኛ ከምናገኘው Exaltation of the Holy Cross የሚል የምሥራቃውያን ትውፊት ተዛምዶ ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡ የነገረ መስቀል ታሪክና ድርሰቶች በምሥራቁም በምዕራቡም ተቀራራቢነት አላቸው፡፡ ከመስቀል ጋራ የተገናኙ ተዛማጅ ምንባባት አሉን፡፡ እንጥቀስ፡- “ለመስቀልከ ንሰግድ ኦ ሊቅነ፣ ወለትንሣኤከ ቅድስት ንሴብሕ ኵልነ፣ ይዕዜኒ፡፡ ወዘልፈኒ - መምህራችን ሆይ! ለመስቀልህ እንሰግዳለን፣ ቅድስት ትንሣኤህን እናወድሳለን፣ ዛሬም ዘወትርም - Before thy Cross, we bow down in worship, O Master, and thy holy resurrection we glorify” ቅዱስ ቴዎፍሎስ ዘእስክንድርያ ‹‹The cross is the helper of the wretched, assisting all the oppressed.›› ሲል የደረሰው ድርሰት በቅ/ያሬድና አባ ጊዮርጊስ ቃል በቃል ‹‹ለአግብርት፡ ግዕዛን፣ ጽንዕ፡ ለድኩማን፡ መስቀል፡፡ - መስቀል ለባሮች ነጻነት፣ ለደካሞችም ረዳት ነው›› በሚል ሰፍሯል፡፡

በበረከት አዝመራው ( Bereket Azmeraw አነጋገር መስቀልን እንደ ግዑዝ ሳይሆን እንደ ሕያውና ሰማኢ ባለግዕዛን አካል አድርጎ መናገር (Personification) በእኛም በሌሎችም አለ፡፡ በፕ/ር ጌታች የተሰባሰበ የነገረ መስቀል ድርሳን፡- ‹‹ወሶበ ተቀኖከ መስቀል ምስለ እደ ክርስቶስ ክቡር፡፡ ሞተ መልአከ ሞት መኰንነ ኵሉ ፍጡር፡፡ ወሙታንሂ ተንሥኡ እምዝህር - መስቀል ሆይ! ከከበረ የክርስቶስ እጅ ጋራ ብትቸነከር፣ የፍጥረታት ሁሉ ገዢ የሆነ የሞት መልአክ ሞተ፣ ሙታንም ከመቃብር ተነሡ›› ይላል፡፡ መስቀልን እንደ ሰው ያናግረዋል፡፡ ግባጻውያን በውዳሴያቸው (Doxology) መስቀልን ግዕዛን ሰጥተው እንዲህ ያናግሩታል፡- ‹‹ We carry you, O Cross, the strength of the Christians, powerfully around our necks, and we proclaim openly. - የክርስቲያኖች ብርታት የምትሆን መስቀል ሆይ! በአንገታችን ዙሪያ አጽንተን እንይዝሃለን፤ በይፋም እንሰብክሃለን፡፡›› እንደ ሰው ያናግሩታል፡፡ ‹‹Hail to you, Praise to You, We bow down - ስብሐት ለከ፣ ንሰግድ ለከ - እናመሰግንሃለን፣ እንሰግድልሃለን›› የሚል መነሻ ያላቸው ድርሰቶች በሁላችንም ዘንድ አሉ፡፡ መስቀል ይከበራል፣ የጸጋ ስግደት ይሰገድለታል! የመስቀል ድርሰቶች ቢነጻጸሩ ዝምድናቸው ሰፊ ነው፡፡

---
2.መታሰቢያ
የመስቀል ከተዳፈነበት በንግሥት ዕሌኒ መውጣት ከሞላ ጎደል ዓለም አቀፋዊ ታሪክ ነው፡፡ አከባበሩና የሚከበርበት ቀን በመጠኑ ሊለያይ ይችል ይሆናል፡፡ መስቀል ሁለት ጊዜ ይታሰባል፡፡ መጋቢት 10 እና መስከረም 17፡፡ የመጋቢቱ ዐቢይ ጾም ወይም የኢየሱስ ጾም (ጾመ ኢየሱስ) ላይ ይውላል፡፡ (አሁን አሁን በንግሥ ዙሪያ ትውፊቱ ቢሸረሸርም) በኢየሱስ ስም በተሠየው ጾም በዓልን ያውም የአደባባይ በዓል ማክበርን ቀኖናችን አይፈቅድም፡፡ (መስቀሉንና የመስቀሉን ጌታ ልዩነት አበጥረን እናውቃለን! ብንል አጉል ትምክሕት አለመሆኑን እዚህ ላይ አስተውል!) በዓሉ የጌታን ጾም ክብር እንዳይጋፋ ተጠቃሎ መስከረም ላይ ይከበራል፡፡ መስቀል በዝክር ብቻ አይቀርም፡፡ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል፡፡ ‹‹መስቀለ ኢየሱስ›› የሚባል ቤተ ክርስቲያን አለን፡፡ በወላጆቼ አካባቢ ‹‹ወር/ዕ/ያ መስቀል›› የሚባል ደብር አለ፡፡ በግብፆች፣ በምሥራቆችና በካቶሊኮች ‹‹Holy Cross Church of Coptic Orthodox Church, Holy Cross Greek Orthodox Church, Holy Cross Catholic Church›› በሚል ስም አብያተ ክርስቲያናት መትከል የተለመደ ነው፡፡
---
3.የመከበሩ ፋይዳ
መስቀል ለክርስቲያኖች የስቃይ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ከስቃይ በኋላ የሚገኝ ድል አድራጊነት ይዘከርበታል፡፡ ተዘክሮውን Contemplation ሲሉት ሰምቻለሁ፡፡ ነገረ ድኅነት ይታሰብበታል፡፡ የድኅነት መሣሪያ (Instrument of Redemption) ይሉታል፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንለው መስቀል የክርስትና አርማ ነው፡፡ ባንዲራ ነው፡፡ ባንዲራውን ስታይ አገርህ ትታሰብሃለች (ከፈለግህ ክልልህም ትዝ ትበልህ! ምሳሌ ነውና)፡፡ ባንዲራው ጨርቅ መሆኑ አይጠፋህም፣ አይጠፋንም፡፡ ውክልናው ግን ከፍ ይላል፡፡ የሚመጣልህ ሐሳብ ጨርቁ ከምን ተሠራ አይደለም፡፡ ለክብሩ የተከፈለው ዋጋ ነው፡፡ መስቀል ክቡር ደም ፈስሶበታል! የሌላ ደም አይደለም፡፡ የፈጣሪ ደም ነው! ‹‹አኮ ደመ ካልዕ፡ አላ ደመ ወልድ ክቡር!›› እንዲል መስተብቊዕ ዘመስቀል፡፡
---
4.ማማተብ
ማማተብን ዕድሜ ለብሔራውያንና ዓለም አቀፍ ስፖርተኞች የክርስትና ቋንቋ አድርገውታል፡፡ ስናማተብ ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ›› እያልን ከግንባራችን ጀምረን ወደታች፣ ከዚያም ወደግራና ቀኝ እናማትባለን፡፡ ጸሎትና የእምነት አዋጅ ነው! ‹‹በሥላሴ ሦስትነትና አንድነት አምናለሁ!›› ብሎ እምነትን ማወጅ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ሠይጣንን እንገሥጻለን፡፡ ይህም ድንበር ተሸጋሪ ትውፊት ነው፡፡
--
5.ሥርዓቱና ደመራው
በእኛ ታሪኩ በቃል ብቻ ተነግሮ አይቆምም፡፡ መስቀሉ የወጣበት ሒደት በአደባባይ በተምሳሌት ይገለጻል፡፡ የክርስትናው የአምልኮ ጠባይ ነው፡፡ ከምዕራቡ ለየት ያደርገናል፡፡ የእኛ ከዊንን/ ክዋኔን (Performance) ሲከተል የምዕራቡ ቃላዊ ገለጻን (description) ያዘወትራል፡፡ በመስቀል ዙሪያ ጥቅሶችን እየነካኩ ‹መስቀል የተባለው እንደዚህ ነው፣ እንደዚያ ነው እንጅ ዕንጨት ማለት አይደለም› የሚል ተቃዋሚ ቢነሣ አይገርምም፡፡ ማለፍ ነው! የአምልኮ መንገዳችን ስለሚለያይ፡፡ የተግባሩን ገለጻ ጥሬ ቃልና ጥቅስ በመፍተል ለመዳኘት የሚደረግ የሚዛን መለያየት ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ እንለፈው! ላደለው ምልጣኑ ላይ ያለቺው ንሺ (የቅብብሎሽ ዜማ) ‹‹እመኑ ብየ፡ ወእመኑ በአቡየ፡ አበርህ በመስቀልየ - በእኔ እመኑ፣ በአባቴም እመኑ፣ በመስቀሌ አበራለሁ / ጨለማውን እገፋለሁ/›› የሚል ነው፡፡
በመስቀሉ ያብራልን!


#ለሌሎች_ሼር_ማድረግ_አትዘንጉ👇🤗
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
https://www.tg-me.com/orthodoxzelalemawit
⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️⛪️
2024/09/27 19:19:38
Back to Top
HTML Embed Code: