Telegram Web Link
ማኅበረ ቅዱሳን በ8 ማእከላት ለሚገኙ ከ1,700 በላይ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አገልግሎት ከአንድ ቤተሰብ ለአንድ ተማሪ በሚል መሪ ቃል ፕሮጀክት ቀርጾ ወላጆቻቸውን ላጡና መማር ላልቻሉ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን ከማስተባበሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የማኅበረ ቅዱሳን ሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የፕሮጀክት ገቢ አሰባሰብ ባለሙያ ወይዘሮ ጣይቱ ማስረሻ እንደገለጹት በአቅም ማነስ: ሃይማኖታቸውና በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለው መማር ላልቻሉ እንዲሁም በጠረፋማ አካባቢ ለሚገኙ አዲስ ተጠማቂ ተማሪዎችን ተደራሽ ያደረገ ድጋፍ ነው የተደረገው ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ያነሱት የፕሮጀክት ገቢ አሰባሰብ ባለሙያዋ ወይዘሮ ጣይቱ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ሕዝብ ግንኙነትና ትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ ለመሐል ማእከላት ሕዝብ ግንኙነትና ትብብር አገልግሎት ዋና ክፍል አባላት የልምድ ልውውጥ እና የሥልጠና መርሐ ግብር አካሄደ።

በዋና ማእከል ሕዝብ ግንኙነት እና ትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ የተዘጋጀው ሥልጠና ከደብረ ብርሃን፣አዳማ ፣አሰላ፣ወልቂጤ፣ወሊሶ ፣አምቦ እና አዲስ አበባ ማእከላት የተወጣጡ ከ 50 በላይ አባላት የተሳተፉበትና ለሁለት ቀናት የቆየ ሲሆን  ስለ አገልግሎት እና መሰል ጉዳዮች ውይይቶች እና የልምድ ልውውጥ ያካተተ ነበር።

ሥልጠናው ማኅበረ ቅዱሳንን እና አገልግሎቱን ከማስተዋወቅ አንጻር የሚዲያ አገልግሎት ጥቅም እና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ያለው አስተዋጽኦ  ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ 5ተኛውን ሐዊረ ሕይወት አካሄደ::

የግንኙነት ጣቢያው ጽ/ቤት እንደገለጸው መነሻውን ከኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በማድረግ ቺካጎ ወደሚገኘው የደብረ ጽዮን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሜ ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ. ም በኢንዲያና ዙሪያ የሚገኙ ከ185 በላይ ምእመናንን ያሳተፈ መንፈሳዊ ጉዞ አካሂዷል።

በዕለቱ ምክረ አበውና በርካታ መርሐ ግብራት መከናወናቸው የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ምን መምሰል እንዳለበት የሕይወት ልምድና ትምህርት ተሰጥቷል ተብሏል፡፡

በመርሐ ግብሩ የአሜሪካ ማእከል ሥራ አስፈጻሚ አባልና አቅም ማጎልበቻና የሰው ሀብት ዋና ክፍል ኀላፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ፍስሐ እሸቱ፣ የኢንዲያና ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ ንጉሤ ገብሬ፣ ሰባኬ ወንጌል ብርሃኑ አድማስ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ኢንዲያና ግንኙነት ጣቢያ አባላት እንዲሁም ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
በማኀበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ኤስድሮስ ሥነ መለኮት ሰሚናሪ በሥነ መለኮትና ግእዝ ቋንቋ ለሦስት ዓመታት ያስተማራቸውን 33 ደቀመዛሙርት አስመረቀ፡፡

ኤስድሮስ ሴሚናሪ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም በሚዙሪ ግዛት ሴንት ሉዊስ ከተማ 21 ወንዶችና 12 ሴቶችን በድምሩ 33 ደቀ መዛሙርትን ማስመረቁ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተስፋቸው መሆኗን የገለጹት ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ወደፊትም ብዙ አገልግሎት እንደሚያበረክቱና በሰሚናሪው ቆይታቸው ያገኙት ትምህርት ለአገልግሎታቸው ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ጠቅሰው ኤስድሮስ ሴሚናሪ ላደረገላቸውም ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

ከምርቃት ሥነ ሥርዓቱ አስቀድሞም ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት ተጨማሪ የሕይወትና የአገልግሎት ስንቅ የሚያገኙበት ሥልጠና መሰጠቱ ተጠቅሷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የኦሃዮና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለተመራቂዎች ዲፕሎማና የምስክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንን ከምሥረታ ጀምሮይ እንደሚያውቁትና አገልግሎቱን እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

የኤስድሮስ ሥነ መለኮት ሰሚናሪ በ2011 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከቶች እውቅና አግኝቶ ማስተማር የጀመረ ሲሆን ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ያስመረቀ ሲሆን ሴሚናሪው በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች የግእዝ ቋንቋንና ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ እንዲያውቋት ጠንካራ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል።
የማኅበረ ቅዱሳን የሀገር ውስጥ እና የውጭ ማእከላት የጽ/ቤት ኀላፊዎች የምክክር መድረክ ተከናወነ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በሚገኙ ማእከላቱ ውስጥ በመደበኛነት አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የጽ/ቤት ኀላፊዎች ጋር የውይይት እና የምክክር መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ከጥቅምት 22 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በቆየው በዚህ መርሐ ግብር ላይ የማኅበሩን ሥልታዊ ዕቅድ ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ሰፊ ውይይቶች እና ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል።

መርሐ ግብሩ የማኅበሩን ተቋማዊ የመፈጸም አቅም በማሳደግ እና ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
2024/11/06 00:36:56
Back to Top
HTML Embed Code: