Telegram Web Link
በደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ አዘጋጅነት በወላይታ ሀገረስብከት በሚገኘው ካህናት ማሠልጠኛ  ለስድስት  ተከታታይ ቀናት  ሲሰጥ የቆየው የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራር ሥልጠና  መጠናቀቁ ተገለጸ።

ሰኔ ፲፬/፳፻፲፯ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ አዘጋጅነት ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ለተዉጣጡ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ለስድስት  ተከታታይ ቀናት  እየተሰጠ የቆየው የደረጃ ሁለት ተተኪ አመራር   ሥልጠናና ውይይት በዛሬው ዕለት ብፁዕ  አቡነ ይስሐቅ የወላይታ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ በተገኙበት  የማጠቃለያ መርሐ ግብር በርእሰ አድባራት ወገዳማት ደብረ መንክራት አቡነ ተክለሃይማኖት አንድነት  ገዳም መከናወኑ ተገልጿል ።

ሠልጣኞች  ከአርባ ምንጭ ፣ ከወላይታ ፣ ከጂንካ  ፣ከሆሳዕና ማእከላት የተወጣጡ ቁጥራቸው ከ50  በላይ እንደሆኑ ተጠቁሟል ።

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የመሪነት ሚና ትላንት፣ ዛሬና ነገ ፣ ኦርቶዶክሳዊነት ሕይወቱና ክህሎቱ ፣የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ፣ ሴኩላሪዝም ከኦርቶዶክስ እሳቤና ኑሮ አንጻርና ሌሎች ሥልጠናዎች እንደሰጠም ተመላክቷል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው  በማጠቃለያ መርሐግብር የወላይታ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ  " የተካሄደው ሥልጠና እጅግ ጠቃሚ የሆነና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው   " የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በማለት ሠልጣኞች በተሰጠው ሥልጠና  እግዚአብሔርን በመፍራት፣ ሕይወታቸውን በመምራት፣   መክሊታቸውን በማትረፍ በሚሄዱበት ሁሉ ቅድስት  ቤተ ክርስቲያንን፣ ወላጆቻቸውንና አገራቸውን እንዲያገለግሉ የአደራ መልእክትና አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል።
የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ግቢ_ጉባኤ ያስተማራቸዉን ተማሪዎች ብፁዕ አቡነ እንጦንስ  በተገኙበት አስመረቀ

ሰኔ ፲፮/፳፻፲፯ ዓ.ም

የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ለአራትና አምስት አመታት  ያስተማራቸዉን 225 ተማሪዎችን የምዕራብ ሐረርጌ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ  በተገኙበት አስመርቋል።


ብፁዕ አቡነ እንጦንስ   ቃለ እግዚአብሔርን መሰረት በማድረግ ፣  ህገ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ  ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን ማገልገል ይጠበቅባችኋል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።

አክለውም አገልግሎታችሁም ሁሉ  በፍቅር መሆን አለበት  ያሉ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት  በሚገኙ ወጣቶች ላይ ሥራ እየሠራ በመገኘቱም  አመስግነዋል።

የጭሮ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ዳንኤል ሞገስ እንደገለጹት  ማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ተማሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እደሚገኝ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ እንጦንስ  ለተመራቂ ተማሪዎች የአደራ መስቀል የሰጡ ሲሆን ከተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት  በሜዳሊያ ለተመረቁ አራት ተማሪዎች ዕዉቅናና ሽልማት ተበርክቷል።
ደብረ ማርቆስ ማእከል በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

ሰኔ ፲፮/፳፻፲፯ ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን ደብረ ማርቆስ ማእከል በመደበኛውና በማታው መርሐ ግብር በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።

የማእከሉ ሰብሳቢ ድረስ እንዳላማው  ተመራቂ ተማሪዎችን “የድካማችሁን ፍሬ ለማየት ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ”  ያሉ ሲሆን  የማኅበሩ ርእይ ቤተ ክርስቲያን የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት እንደመሆኑ መጠን  እናንተም የሚጠበቅባችሁን በማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር በመግባት፣ በጉልበታችሁ፣ በገንዘባችሁና በዕውቀታችሁ ማገልገል እንዲሁም  ከማኅበሩ ጋር በጋራ መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

በመርሐ  ግብሩ ተማሪዎች በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆነው ለመውጣት በግቢ ቆይታቸው የተሻለ ትጋት ለነበራቸውና በዓለማዊ ትምህርታቸው የሜዳሊያ ተሸላሚ ለሆኑ የግቢ ጉባኤ ፍሬዎች በምሥራቅ ጎጃም ሃገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ ምሕረት መ/ር ይትባረክ ክንዴና በሃገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ፍቅረሥላሴ አማካኝነት ከግቢ ጉባኤው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም ተመራቂ ተማሪዎች "ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋየ ጋር ትጣበቅ" ብለው ቃል በመግባት የአደራ መስቀል ተቀብለዋል።
2025/07/06 18:37:58
Back to Top
HTML Embed Code: