Telegram Web Link
በማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል 30ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

ማእከሉ ከ1,500 በላይ አባላት፣ 26 ግቢ ጉባኤያት፣ 3 የንዋየ ቅድሳት መሸጫ ሱቅ እና አንድ የዜማ መሣሪያዎች ማሠልጠኛ ተቋም፣ 2 ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች እንዳሉት በዕለቱ በቀረበው ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡

በዓመቱም 553 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን የአብነት ትምህርት በማስተማር 9 ዲያቆናት ክህነት እንዲቀበሉ ያደረገ ሲሆን 334 በደረጃ 1 እና 64 በደረጃ 2 አዳዲስ አመራሮችን ማሠልጠኑም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም 5 ተማሪዎችን ማስጠመቅ መቻሉን፣ ለ18 ሰንበት ትምህርት ቤቶችና 86 መምህራነ ወንጌል እንዲሁም በ4 አጥቢያዎች ለሚገኙ ካህናትና ለቅድመ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሥልጠናዎች መሰጠታቸው ተነግሯል፡፡

በክልሉ ባለው ጦርነት ምክንያት በምእመናን እና ካህናት ላይ የደረሰውን ጥቃት መረጃ መሰብሰብ መቻሉንና በጦርነት ውስጥ የሚገኙ የወረዳ ማእከላት ሥራ አስፈጻሚዎችን ባሕር ዳር እንዲመጡ በማድረግ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች እንዲሰጣቸው ተደርጓልም ተብሏል፡፡

በሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍም ማእከሉ በደብረ ሰላም ወረዳ ማእከል በችግር ዉስጥ የሚገኙ የሀቢታት ነዋሪዎች ከ900,000 ብር በላይ፤ በጣና ወረዳ ማእከል ዝግባ የአረጋዉያንና የሕጻናት ማእከልና በጊዮን ወረዳ ማእከል ለጎልማሶች ማገገሚያ የትንሳኤ በዓልን ለማክበር ከ200,000 ብር በላይ ወጭ በማድረግ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የዋና ማእከል የብሮድካስት አገልግሎትን የሚያግዝ የሚድያ ክፍል ግብዓት አሟልቶ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በጉባኤው የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊና ተወካይ ሥራ አስኪያጅ  መልአከ ብርሃን ፍሥሐ ጥላሁን፣ የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኀላፊ መልአከ ምሕረት ግሩም አለነ፣ የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኀላፊ መልአከ ገነት መጽሐፈ ሕይወት ዐይናለም፣የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሀገረ ስብከቱ የልዩ ልዩ የክፍል ኀላፊዎች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ጽ/ቤት ኀላፊ አቶ ንጉሤ መብራቱ  ፤የማኅበረ ቅዱሳን ሰሜን ምእራብ ማእከላት ማስተባበሪያ ም/ሰብሳቢ ዶ/ር በሪሁን ተፈራና የጉባኤው ልዑክ ፤ የወረዳ ቤተ ክህነት ተወካዮች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፤ የወረዳ ማእከላት ፣ የግቢ ጉባኤያት ተወካዮችና የማእከሉ አባላት ተገኝተዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙርና ኪነ ጥበባት አገልግሎት ማስተባበሪያ ከአሜሪካ ማእከል ሚዲያ፣ መዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል ጋር በመተባበር ፍኖተ ያሬድ ልዩ መጽሔት አሳተመ

መጽሔቱ በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎቹ እንዲሁም መዝሙርና ሥነ ጥበባት አገልግሎት ለስብከተ ወንጌል ያለውን ድርሻ በዝርዝር የሚተነትን ሲሆን በዚህም ስለ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፣ የዜማ መሳሪያዎችና ሥነ ጥበባት አገልግሎት ወቅታዊ ሁኔታዎችን (በጎ እድሎችና ተግዳሮቶች) እንዲሁም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በተለያየ ምዕራፍ አቅርቧል፤

ልዩ መጽሔቱ በየዓመቱ ዝክረ ቅዱስ ያሬድ መርሐ ግብራትን በማከናወን ለምእመናን ይቀርቡ ከነበሩት የዐውደ ርእይና ሌሎችም ጽሑፎች በመነሳት በምእመናን አስተያየት መሠረት ለተሻለ ተደራሽነት በሁለት ቋንቋ ማለትም በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ ሊታተም ችሏል።

ማስተባበሪያው በ2016 ዓ.ም አኮቴተ ያሬድ በሚል ርእስ የመዝሙር መጽሐፍ አሳትሞ እያሰረጨ ያለ ሲሆን ይህ ከአሜሪካ ማእከል የሚገኝ ሲሆን በጋራ የታተመው መጽሔት ደግሞ በጽሑፍ ኅትመት ደረጃ የዓመቱ ሁለተኛ ሥራው ነው። 

መጽሔቱ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል 5ኛ ፎቅ በመዝሙርና ኪነ ጥበባት ቢሮ እንዲሁም በአሜሪካ ማእከል ማግኘት እንደሚቻል ተገልጽዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በምሥራቅ ወለጋ  4 ቦታዎች ላይ ለሚገኙ 145 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ 

የማኅበረ ቅዱሳን ሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ፣ በሀገራችን እያጋጠሙ ያሉ መጠነ ሰፊ ማኅበራዊ ቀውሶች በልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚያስከትሉትን ችግር ለማቃለል ልዩ ልዩ የማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ማኅበራዊና ሰብአዊ ሚናውን እየተወጣ እንዳለ ይታወቃል።

ማስተባበሪያው በማኅበራዊ ዘርፍ ከሚያደርጋቸው ድጋፎች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን በተገቢ ሁኔታ ለመከታተል የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሕጻናትና ታዳጊዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ አንዱ ነው። በዚህ መሠረት በየዓመቱ እንደሚደረገው ከመስከረም11-12 ቀን 2017 ዓ.ም ከማኅበረ ቅዱሳን #ነቀምቴ ማእከል ጋር በመተባበር፣ በምሥራቅ ወለጋ 4 ቦታዎች ማለትም በሲቡ ስሬ፣ ጉደቱ አርጆ ፣ ነቀምቴ ከተማ እና ጅማ አርጆ በድምሩ ለ145 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ድጋፎችን በፍጥነት ለማድረስ ማስተባበሪያው እየሰራ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ስለሆነም የነገ ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ተስፋ ለማስቀጠል በሚደረገው የሰብአዊነት ሥራ ምእመናን፣ ማኅበራት፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና በጎ አድራጊ ድርጅቶች የተለመደ ድጋፍ እንድታደርጉልን ሲል ጥሪውን ያቀርባል።
#በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሒሳብ ቁጥሮች፡-
1. በአሐዱ ባንክ - 0025393810901
2. በአቢሲንያ ባንክ - 37235458
3. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - 1000309803648
4. በወጋገን ባንክ - 0837331610101
5. በአዋሽ ባንክ 01329817420400
6. በወገን ፈንድ ፡- https://Www.wegenfund.com/mknu መጠቀም የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።
በማኅበረ ቅዱሳን የደሴ ማእከል ለወሎ ዩንቨርሲቲ ዋናው ግቢ እና ለልዕለ ሕክምና ካምፖስ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የአቀባበል መርሐ ግብር ማካሄዱን ገለጸ።

በመርሐ ግብሩ ላይ የደሴ ማእከል ምክትል ሰብሳቢ ፣የደብረ ዕንቁ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ወልደ ጊዮርጊስ ፣የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላትና የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ዋና ክፍል አባላት ተገኝተዋል።

በዕለቱ ለተማሪዎች መልእክት ያስተላለፉት የደብረ ዕንቁ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ወልደ ጊዮርጊስ እኛ ወጥተን ወርደን አምጠተን ማስተማር ሲኖርብን እናንተ መጥታችሁ አስተምሩን በማለታችሁ እጅግ እድለኞች ነን ብለዋል፡፡

አስተዳዳሪው አክለውም ወጀብ በበዛበት ዘመን ማኅበረ ቅዱሳን ባይኖር እናንተ ዓለም ትውጣችሁ ነበርና የተመቻቸላችሁን ዕድል ተጠቅማችሁ በሁለቱም የተሳለ ሰይፍ ሁናችሁ መውጣት አለባችሁ በማለት አሳስበዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል

የመስቀል ነገር በመጀመሪያ የተገለጸው በመላእክት ዓለም ነበር፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥነ ፍጥረትን በጻፈበት አክሲማሮስ በተባለ መጽሐፉ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ አለ፡፡ ያን ጊዜ በመላእክት ዓለም ረብሻ ሆነ፤ ከፊሉ ዲያብሎስን አምኖ ከእርሱ ጋር ሆነ፤ ቅዱስ ገብርኤል ግን የፈጠረንን እስክናገኝ በያለንበት ጸንተን እንቆይ አለ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ሌሎች መላእክትም አብረው ጸንተው ቆዩ፤ ተጠራጥውም ከሁለቱም ጎን ሳይሆኑ የቀሩ ነበሩ፡፡

ከዚያም በመላእክትና በዲያብሎስ መካከል ጦርነት ተጀመረ፤ በተዋጉ ጊዜ ዲያብሎስ ሁለት ጊዜ አሸነፋቸው፤ ሆኖም መላእክት አምላካቸውን ‹‹ፈቃድህ ነውን?›› ብለው ቢጠይቁት፤ ‹‹ፈቃዴስ አይደለም፤ ድል የምታደርጉበትን ኃይል እንድታውቁት ብዬ ነው እንጂ›› ብሎ በክንፋቸው ላይ የብርሃን መስቀል ቀረጸላቸው፤ በእጃቸው ደግሞ የብርሃን መስቀል አስያዛቸው፤ ሄደውም ዲያብሎስን ቢገጥሙት በመስቀሉ ኃይል ድል ነሥተውታል፡፡ መላእክት ሳጥናኤልን ድል ያደረጉት በመስቀል ኃይል ነው (ራዕ. ፲፪፥፯፣ መዝ. ፶፱፥፬)፡፡
በዘመነ አበው መስቀል የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፤ ዘፍጥረት ላይ ፤ ‹‹ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው›› ‹‹ወአስተሐለፈ እዴሁ ላዕለ ርዕሰ ኤፍሬም ወምናሴ፤ እጆቹን በኤፍሬምና በምናሴ ላይ በመስቀል ምልክት አድርጎ ጭኖ ባረካቸው›› ይላል፡፡ (ዘፍ. ፵፰፥፲፩)፤ ዕብ. ፲፩፥፳፪)

ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህኑ ቀድሶ በሚወጣበት ጊዜ በእጆቹ ይባርካል፤ ይህም የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያን መሠረቷ ከላይ በዓለመ መላእክት ከታች ደግሞ በዘመነ አበው ያየነው መስቀል መሆኑን ነው፡፡

መስቀል በብሉይ ኪዳን እንደየሀገሩ ሁኔታ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲፈጸምበት ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፡- ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል፤ ለአርማም ይጠቀሙበት ነበር፡፡

መስቀል በሐዲስ ኪዳን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) አስታርቋል፡፡

ደመራ
ደመራ ማለት መጨመር፣መሰብሰብ፣መከመር ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸው የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ የጌታችን መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች፡፡

በኋላ ግን አንድ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ አካባቢውን ነግሯት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ብትማፀን የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከታት፡፡

እርሷም በምልክቱ መሠረት ብታስቆፍር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኘች፤ ከእርሱ መስቀል ጋር ሁለት ወንበዴዎች የተሰቀሉበትን መስቀል አብራ አግኝታው ስለነበር የጌታችን መስቀል ለይታ ያወቀችበት መንገድ ግን ድውያንን በመፈወሱ፣ አንካሳ በማበርታቱ፣ ጎባጣን በማቅናቱ የዕውራንንም ዐይን በማብራቱ ነው፡፡ ስለዚህም በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው፡፡

እርስዋም መስከረም ፲፯ ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉን አግኝታ አስወጥታ የቤተ ክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች፡፡

የጌታ መስቀል ለብዙ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት መስቀሉን ለመውሰድ ጠብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት::

ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ለዐራት ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት:: የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት የግብፅ ክርስቲያኖች በአማሌቃውያን ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ በማድረጋቸው የግብፅ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው:: ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ወርቅ ሳይሆን ጌታ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንደሆነ ገለጹላቸው::

በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች:: ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ከሐዋርያት በተማረችው መሠረት የወርና የዓመት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
2024/09/28 08:20:51
Back to Top
HTML Embed Code: