Telegram Web Link
የሰላም መንፈስ በመካከሏ ሆኖ ከስሕተት የሚጠብቃት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም አመለካከቱ ስሕተት ንግግሩ ሐሰት በሆነው ዓለም የጽድቅና የሰላም ባሕርይ መገለጫ ነው፡፡ ልጆቿ በሰላም በፍቅር በታነጸ ዕለታዊ ሕይወት እንዲኖሩ በማድረግ ሰላም የደግነት ሁሉ አክሊል የመንፈሳዊ ምግባራት ዘውድ መሆኑን ስታውጅ መኖሯን የታሪክ መዛግብት፣ ዕውነትን ለመግለጥ የሚተጉ ጸሐፍት ከመቅድም እስከ ህዳግ ይመሰክሩላታል። መሪዋና አጽናኟ ከሆነው መንፈስ ቅዱስ በተገኘው የሰላም እሴት በእምነታቸው ጸንተው በምግባር በትሩፋት አጊጠው የሚኖሩት ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናንም የረጅም ዘመናት የቅድስና ታሪክ ጉዞዋ ማሳያዎች ናቸው። የእውነትና የሰላም አምድ እንደመሆኗም በሀገራችን እየተከሰቱ ያሉ አለመግባባቶችንና የእርስ በእርስ ደም መፋሰሶች እንዲቆሙ የሰላም ጥሪ ከማድረግ ጀምሮ ምህላ፣ ጾምና ጸሎት በማወጅ እግዚአብሔር ለሀገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን እንዲሰጥ ስትማጸን ቆይታለች። የየዕለት አገልግሎቷም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላም መንፈስ በመካከሏ እንዲሆን አድርጎ ወኃቤ ሰላም መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት ስለሆነ

በዓለም ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የክብር ስፍራውን ይዞ የሚቀጥል ቀዳሚና ዐቢይ ተልእኮዋ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን ።

በመጨረሻም ሰላም የሚጸናው ማንኛውም ማኅበረሰብ እርስ በእርሱ በመተሳሰብና በፍቅር በእውነተኛ መግባባትና በፍትሕ በርኅራሄና በመከባበር አብሮ መኖር ሲቻል ነውና በወንድማማችነት መካከል ጠብን ከሚዘሩ ጥላቻንና መራራቅን ከሚያሰፉ ንግግሮችና ድርጊቶች በመቆጠብ ሁሉም የማኅበረ ሰብእ ክፍል እግዚአብሔር ለሀገራችን ፍጹም ሰላምን ይሰጣት ዘንድ በጸሎት እንዲተጋ ቋሚ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

ከምን ጊዜውም በላይ ሰላምና ፍቅር በሀገራችን እንዲሰፍን በአንድነት ሆነን የምንሠራበት ወቅት ላይ በመሆናችን በመጪዎቹ ዐበይት በዓላት፣ በዘወትሩ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉም በየደረጃው ያላችሁ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና አገልጋዮች "ወፍሬሃኒ ዘጽድቅ በሰላም ይዘራዕ ለእለ ይገብርዋ ለሰላም ... የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ ሰዎች በሰላም ይዘራል" በሚለው ሐዋርያዊ ቃል መሠረት በየዐውደ ምሕረቱ ሰላምንና እርቅን በመስበክ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ችግር እንዲወገድ፣ ማኅበራዊ ሰላም እውን እንዲሆን የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ቋሚ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል። ያዕ 3÷18

እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላምን ጽድቅን፣ፍቅርንና ፍትሕን ይስጥልን

ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም
"የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን”

"ጠቡ መለያየቱ መጨካከኑ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተናዊ ውድመት ብቻ ነው"

"ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል"

"በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅና የሰው ሰራሽ ምክንያት በችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው። "

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
• በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡-

በፍጹም ፍቅሩ እኛን ወደ ሰላም ለማምጣት በእኛ ሰውነት በዚህ ዓለም የተወለደው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በደኅና አደረሳችሁ!
“ትእምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)
ዓለም ሁሉ በተለይም የክርስቲያኑ ዓለም በትክክል እንደሚያውቀው ቅዱስ መጽሐፍ በሰዎች የቋንቋ ዘይቤ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ርእዮት ቋንቋ የመልእክት ማስተላለፊያና መግባቢያ መሳሪያ እንደሆነ ይታወቃል እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ መልእክቱን በዚህ መንገድ ለሰዎች ሲያስተላልፍ ኖሮአል የሚያስተላልፈውም መልእክት እንዲሁ ተሰምቶ እንዲቀር ሳይሆን እንዲታወቅ፣ እንዲታመን፣ እንዲተገበርና ሰዎች እንዲጠቀሙበት ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነውከሚፈለገው ጥቅም ለመድረስም ሰዎች መልእክቱን በሚገባ መረዳት የግድ ይሆናል ሰዎች እንዲረዱት ደግሞ በቋንቋቸውና በባህላቸው ዘይቤ ሊነገራቸው ይገባል።

በመሆኑም እግዚአብሔር ቃሉን በሰዎች ቋንቋ ባህላዊ ዘይቤ መልእክቱን ለዓለም ሲያስተላልፍ ኖሮአል፤ ቤተክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ የእግዚአብሔርን ቃል በሰው ቋንቋ ዘይቤ ታስተምራለች፤ ከዚህ አንጻር በሰው ልማዳዊ የዘይቤ ቋንቋ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የሰላም ሰንደቅ ዓላማ” የሚል ቅፅል ተሰጥቶታል፤ ምክንያቱም ንጉሥም ወታደርም ተራው ሕዝብም የሀገሩ ነጻነትና ክብር፣ አንድነትና ሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ተከትሎ ስራ ይሰራል ክብሩንም ይገልፃልና ነው።ተከተል አለቃህን ተመልከት ዓላማህን የሚለው ብሂልም ይህንን ያንፀባርቃል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን 
ምእመናንና ምእመናት!


ጌታችን በመድኅንነቱ የሁላችን የሰላም ሰንደቅ ዓላማ በመሆኑ መምህራችን ቅዱስ ያሬድ “የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነ ልጅ ተወለደልን” ብሎ ይገልፀዋል፤ ጌታችን በዛሬው ዕለት በቤተ ልሔም ሰውነታችንን ሰውነት አድርጎ መወለዱ ራሱ የሰላም ማሳያ ምልክት ነው።ምክንያቱም ሳይወደን አይቀርበንም፤ አይዋሐደንምና ነው። በልደቱ ዕለት “ለዕጓለ እመሕያው ሠምሮ የሰው ልጅን ወደደው” ተብሎ በቅዱሳን መላእክት የተዘመረበትም ምክንያት ይኸው ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነውእንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነው። በዚህ ዓለም የኖረውም ከሚያሳድዱት፣ ከሚከሱት፣ ስሙን ከሚያጠፉና ሊገዱሉት ከሚከጅሉ ጋር እንጂ ከወዳጆቹ ጋር ብቻ አልነበረም፤እሱ ግን ሁሉንም በፍቅር ይቀበል ነበረ፣ ይፈውስና ያድን ነበረ፣ ያስተምርም ነበረ፤ ለሁሉም ስርየተ ኃጢአትን ሰጠ፤ ለጠላቶቹም ጸለየ፤ ጌታችን በዚህ ሁሉ ለኛ አርአያና የተግባር መምህር በመሆኑ የሰላም ሰንደቅ ዓላማችን ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን 
ምእመናንና ምእመናት!


ዓለም በጌታችን ዕለተ ልደት የተዘመረውን ሰማያዊውን የሰላም መዝሙር መዘመር ከጀመረች  እነሆ ዛሬ ድፍን ሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመት ሆነ፤የሰላሙ መዝሙር ዛሬም በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ይዘመራል፤ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ሰላም ሰፍኖ እየታየ አይደለም፤ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ደምበኛ መልስ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔርን አለማመንና አለመፍራት ያመጣው ችግር ነው የሚል ነው።

ምክንያቱም ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ፍትሕ ይጐድላል፣ ፍትሕ ከጐደለ ብሶት ይፈጠራል፣ ብሶት ካለ ሰላም ሊኖር አይችልም፤ በሁሉም የዓለማችን ክፍል ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚብሔር እየተዘነጋ በመሄዱ ቀውሱ ተባብሶ ይታያል፤ የሰው ልጅ ኑሮ በየትም ይሁን በየት በስጋት የተሞላ ሆኖአል፤የሚወራው ሁሉ ስለ ግጭት ስለአየር ብክለት ስለ ረኃብና እልቂት ሆኖአል፤ ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል፤ የዝቅተኛው ማኅበረ ሰብ ሰብአዊ መብት ተዘንግቶአል፤ከዚህ አኳያ ዓለም በዚህ እስከ ቀጠለች ድረስ ሰላም የማግኘቷ ዕድል በጣም አጠራጣሪ ነው። የክርስቶስ ልደት ያስተማረን ግን እንደዚህ አልነበረም፤ ጌታችን የተወለደው በተዋበና ምቹ በሆነ የሀብታም ቤት ሳይሆን በከብቶች በረት ነበረ፤ የተገለጠውም ለባለሥልጣኖች ሳይሆን ዝቅተኞች ለሚባሉ እረኞች ነበረ፤ ልዑላኑ ሰማያውያንና ትሑታኑ ምድራውያን በአንድነት አገናኝቶ ስለ ሰላም በጋራ እንዲዘምሩ አደረገ፤ አሳዳጅ ሳይሆን ተሳዳጅ ሆኖ በግብጽ አገር በመንከራተት አደገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛ እሱን እያየን እንደ ሰንደቅ ዓላማ እንድንከተለው ነበር፤ ጌታችን ከባለሥልጣናቱና ከባለሀብቶቹ ይልቅ በድሆቹ ደረጃ የተወለደው ለድሆቹና ለዝቅተኞቹ ትኩረት እንድንሰጥ ለማስተማር ነው።የእኛ ድርጊት ግን ግልባጩ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ክርስቲያን ነኝ ብሎ፣ በስመ እግዚአብሔር ተሰይሞ፣ መስቀልን በአንገቱ ተሸክሞ የእሱ መሰል በሆነው ወይም መስቀል በተሸከመው ወንድሙ እና እኅቱ እንዲሁም በመሰል ፍጡር ላይ ያለ ርኅራኄ ሲጨክን መታየቱ ነው፤ እንዲህ እየሆነ እንዴት ሰላም ይምጣ? እግዚአብሔርስ እንዴት በረከቱ ይሰጣል? ይህ እጅግ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን 
ምእመናንና ምእመናት!


እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለብን፤ ጠቡ፣ መለያየቱ፣ መጨካከኑ፣ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተና ውድመት ብቻ ነው። ያስገኘልን ትርፍ ይህ መሆኑ እያወቅን በዚሁ ልንቀጥል አይገባም፤ ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን?  ሦስት ሺሕ ዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች እንዴት ችግራቸውን በጠባይና በብልሐት ማስወገድ አቃታቸው? ይህ ከቶ ሊሆን አይገባም፤ ሁላችንም ሰከን ብለን እናስብ፤ ለሁሉም የማሰቢያና የመመካከሪያ ጊዜ ፈጥረን ችግሩን በስፍሐ አእምሮ እንፍታው፤ ችግርን በምክክርና በይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ጥበብ ነው። የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ልኂቃን በዚህ ተግተን ልንሰራ ይገባል፤ መንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ፤ በዚህም ሰላማችንን እንመልስ፡፡

በመጨረሻም

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅና የሰው ሰራሽ ምክንያት በችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው። በመሆኑም የወገን ደራሽ ወገን ነውና ሁሉም ካለው ብቻ ሳይሆን የቀን ቊርሱን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲለግስና በመተጋገዝ ረኃቡን እንድንከላከለው ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ መልካም
የልደት በዓል ያድርግልን!!

  እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!

       ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።

              አባ ማትያስ ቀዳማዊ
  ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 

                  ታኅሣሥ ፳፰ቀን ፲ወ፮ ዓ.ም.
                   አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
የ2016 ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የቅዱስ ፓትርያርኩ የእንኳን አደረስዎ መርሐ ግብር በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ተከናወነ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትን እንኳን ለ2016 ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረስዎ ለማለት በተዘጋጀው መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ; ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ;ብፁዓን  አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡር ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ፣ ክቡር  ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያውና የድርጅት  ኃላፊዎች፣  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ጸሎተ ወንጌል የደረሰ ሲሆን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ደቀ መዛሙርት ያሬዳዊ ዜማ አሰምተዋል።
በማስከተልም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና የጋሞ ብሔረሰብ ዘማርያን መዝሙር አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ለ2016 ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ቅዱስ ፓትርያርኩን የእንኳን አደረስዎ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም  በዚህች ዕለት ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳሉት ‹‹በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፤ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፤ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋሕዷልና ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፡፡ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ›› እያልን ሐሴት በፍስሐ የጌታችን የልደት በዓል እያከበርን እንገኛን ያሉ ሲሆን፡፡ ስለ ሀገራችን ሰላምና ስለ ቤተክርስቲያናችን አንድነት ቅዱስነታቸው እና ቅዱስ ሲኖዶስ በሚወስናቸው ማናቸውም ውሳኔዎች ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ ቅዱስነታቸውን ለብርሃነ ልደቱ በዓል በሰላም አደረስዎ ብለዋል፡፡

በዝግጅቱ በሊቃውንት ቅኔ የቀረበ ሲሆን ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅዱስነታቸውን እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አደረስዎ በማለት የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም "ሰላም በምድር ለሰው ልጅ በጎ ፈቃድ " በሚል ቅዱስ ቃል መነሻነት ሰብአሰገል ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ እንዳቀረቡ አስታውሰው በዓሉ ለምድር ሰላም የታወጀበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል። እያንዳንዳችን በተሰለፍንበት ዘርፍ ቤተክርስቲያንን ማገልገል እንድንችል የቅዱስነትዎ ቡራኬና ጸሎት አይለየን ብለዋል። ብፁዕነታቸው በቦሌ ደብረ ሣሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል በልደት በዓል ዋዜማ የተከበረውን በኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ ትውልድ የተሰናዳውን "የአእላፋት ዝማሬ" ልዩና ቤተ ክርስቲያንን የሚመጥን ነው ይህም በቅዱስነትዎ በዘመነ ፕትርክናዎ የተከናወነ በመሆኑ በሚሰጡን መመሪያ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በክብረ በዓሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት መልዕክት እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉን ለማክበር በሥፍራው ለተገኙ ትምህርት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው   አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን በመብላታቸው ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነመ እሳት ተፈርዶባቸው 55ዐዐ ዘመን በመከራ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን ዕፀ በለሱን ከበሉ በኋላ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን በመረዳት ንስሐ ገብተው ንስሐቸውን ሲጨርሱ እግዚአብሐር ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ተስፋቸውም "በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ " 55ዐዐ ዘመን ሲፈፀም ከልጅ ልጀህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋ ስለሰጣቸው ይሄን ተስፋ ለመፈፀም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም በመወለዱ ምክንያት አድርገን በዓሉን በታላቅ ድምቀት እያከብርን እንገኛለን ብለዋል።

ነጻ ፈቃድ ቢኖረንም በምርጫችን ልንጠነቀቅ ይገባል ለሀገር ሰላም እና አንድነት ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ቅዱስነታቸው እርሳቸው የተገኙበት በቦሌ ደብረ ሣሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል በልደት በዓል ዋዜማ የተከበረውንና በኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ ትውልድ የተሰናዳውን "የአእላፋት ዝማሬ" በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተሰናዳ ነው ያሉ ሲሆን የሰላም መዝሙር የተዘመረበት ነው ብለዋል።

በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው በጸሎት መርሐ ግብሩ ፍጻሜ አግኝቷል።

ምንጭ ፦ የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት
የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ ጉዞ በቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ሥርዓት መሠረት የተፈቀደ ነው።

ብፁእ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኔዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወደ ሀገረ ስብከታቸው የጥምቀትን በዓል ለማክበር መጓዛቸው ይታወቃል። ጉዟቸውን በተመለከተ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተናፈሰ ያለው ወሬ እጅግ የተሳሳተ ሲሆን የብፁእነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ በቤተ ክርስቲያን ሕግ እና ሥርዓት መሠረት በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነ እና በቅዱስ ፓትርያርኩ የተፈቀደ መሆኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስታውቋል።

ጽ/ቤቱ እንደገለጸው ብፁእነታቸው ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ እና መደበኛ የጽ/ቤት ሥራቸውን እንደሚመሩ አሳውቋል።

ምንጭ፦ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ሕ/ግ/መ
የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓል ጥንታዊ ሃይማኖታዊ
ሥርዓቱን በጠበቀ ሁኔታ ሰላማዊና ደማቅ በሆነ መልኩ
እንዲከበር ሁሉም ወገን በኃላፊነት መንፈስ እንዲሠራ
ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጥሪ አስተላለፉ።


ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት "ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም" (መዝሙር ፴፬፥፲፫) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኀይለ ቃል መነሻ በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት የጥምቀት በዓል ጥንታዊና ሃይማኖታዊ መሠረቱን በጠበቀ መልኩ ሰላማዊ በሆነና በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው ገልጸዋል።

በዓሉ የቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የአገራችን ብሎም የዓለማችን ታላቅ በዓል መሆኑን የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓሉን በምናከብርበት ጊዜ ሕግን ባከበረ፣ ፍጹም ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በጠበቀ፣ በኦርቶዶክሳዊ አለባበስ በተዋበ ሥርዓት በዓለ ጥምቀትን በማክበር መንፈሳዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በዓለ ጥምቀቱ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የተሰጠው በመሆኑን አበክረው የገለጹት ብፁዕነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ብቻ ሳትሆኑ በሰው ልጆች እኩልነት የምታምኑ የተለያዩ እምነት ተከታዮች የሆናችሁ ኢትዮጵያን ወገኖች እንደ ሁል ጊዜው እምነታችሁ ባይሆንም "በዓሉ በዓላችን ነው።" እያላችሁ በተለያዩ ጊዜያት አብራችሁን የምታከብሩ፣ ድጋፍ የምታደርጉ ወገኖች በዓሉን ራሳችሁ አክባሪዎች፣ ራሳችሁ የጸጥታው አስተናጋጆች የሰላም መሪዎች ናችሁ ቅድስት ቤተክርስቲያን በምታስተላልፈው መልዕክት መሠረት በዓሉ በሞቀና በደመቀ መልኩ እንዲከበር የተለመደውን ጥረት ታደርጉ ዘንድ በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም ጥሬዬን አስተላልፋለሁ ብለዋል።

የጸጥታ አካላትን በተመለከተ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልዕክት የጸጥታው አካላት የአገራችንን ሰላም ባስጠበቀ መንገድ በዓሉን በማክበር የሀገራችንን መልካም ገጽታ ማሳየት ይቻል ዘንድ ከማንኛውም ቅሬታ ነፃ በሆነ መልኩ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል። ይህን ካላደረጋችሁ ይህን አናደርግም ከሚል አስተሳሰብ በመራቅ ሕግን የማስከበር ሥራውንም ያከናውን ዘንድ ቤተክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች ብለዋል።

በሌላ በኩል ጸብ አጫሪዎችን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት አሁን አሁን ቅድስት ቤተክርስቲያን እየተጎዳች ያለችው አማኞች ሳይሆኑ ነጠላ የሚለብሱ፣ አማኞች ሳይሆኑ ማተም የሚያደርጉ፣ የቤተክርስቲያን ልጆች መስለው በመካከል ገብተው ችግር ፈጥረው ቤተክርስቲያን ችግር እንደፈጠረች የሚያስመስሉ ስላሉ ተናባችሁ፣ ተዋውቃችሁ፣ በሥነ ሥርዓቱ በዓሉን በልዩ መንገድ እንድናስከብር ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም የጥምቀት በዓልን እንዲመራ በጠቅላይ ቤተክህነት የተሰየመው ዓቢይ ኮሚቴ ከከተማችን አስተዳደርና ከሚመለከታቸው የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር በትላንትናው ዕለት ውይይት ያደረገ መሆኑን ገልፀው በውይይቱ በአንዳንድ አባቶች የተነገሩ ንግግሮችን ቤተክርስቲያኗ ማውገዝ ይኖርባታል። ይህ ካልሆነ ግን እኛም በትብብር ለመሥራት እንቸገራለን በማለት የገለጹት ሀሳብ ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ መነሣቱ አግባብነት የለውም ካሉ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች በአባቶች የሚሰጡትን አስተያየቶች ቤተ ክርስቲያን ለምን በዝምታ አለፈችው የሚል ቅሬታ ቀደም ሲልም እንዳለ አስታውሰው ቋሚ ሲኖዶስ በጉዳዩ ዙሪያ በስፋት ተወያይቶና የሚለውን ብሎ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ እንዲታይ ወደዚያው አስተላልፎታል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ሞትን አታውጅም ትንሣኤን ነው የምታውጀው። ወደ ንስሐ ትጣራለች እንጂ ሞትን አታውጅም ያሉት ብፁዕነታቸው ጉዳዩን በሰማሁ ጊዜ በጣም ነው ያዘንኩት መግለጫ በግሌ ለመስጠትም ተዘጋጅቼ ነበር ካሉ በኋላ መንገዱን ስናየው ግን መጠላለፊያ እንጂ የጽድቅ ስላልሆነ ነው ዝም ያልነው ብለዋል።

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን የአሜሪካ ጉዞን በተመለከተም በሀገረ ስብከታቸው የጥምቀት በዓልን ለማክበር በሀገረ ስብከታቸው ቅዳሴ ቤቱ የሚከበረውን ቤተክርስቲያን ለመባረክ ታቦት ይዘው ሕጋዊ ደብዳቤ ተጽፎላቸው በህጋዊ መንገድ የተጓዙ መሆኑን ገልጸው የሄዱበትን ሐዋርያዊ ጉዞ አጠናቀው ወደ አገር ቤት በመመለስ መደበኛ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል።ብፁዕነታቸው በልዩልዩ ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ገለዳዮች ዙሪያ ግልጽና ጥልቀት ያለው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣የደስታ፣የጤናና የበረከት እንዲሆንልን በመመኘት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

ምንጭ፡- የ/ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
2024/09/30 04:18:47
Back to Top
HTML Embed Code: