Telegram Web Link
ልጆቼ! የእግዚአብሔር ትእዛዝ እንዴት ቀላል እንደሆነ የምታስተውሉ ሁኑ፡፡ ምክንያቱም ታስሬ አስፈትታችሁኛልና ሳይሆን ጠይቃችሁኛልና፤ ታምሜ አድናችሁኛልና ሳይሆን ጠይቃችሁኛልና፤ ተርቤ በየዓይነቱና ውድ የሆነ መዓድ ሳይሆን አንዲት ዳቦ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ በየዓይነቱና ውድ የሆነ መጠጥ ሳይሆን አንዲት ቀዝቃዛ ኩባያ ውኃ አጠጥታችሁኛልና ነው የሚለን፡፡

በጣም የሚያቀለው ደግሞ እነዚህን ቀላል ትእዛዛት በራሳችን ጥረት የምናደርጋቸው አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በቃሉ "ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም" ስለሚለን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን አጋዥ አድርገን ነው፡፡ እንግዲያውስ ድሀ ስለሆንኩ እነዚህን ማድረግ አልችልም ብለን ራሳችን ሰነፎች የምናደርግ አንሁን፡፡ ሺህ ጊዜ ደሀ ብንሆን ሁለት ሳንቲም ከሰጠችው መበለት በላይ ድሀ ልንሆን አንችልምና፡፡ ስለዚህ ስንፍናን ከእኛ እናርቅ፡፡

ልጆቼ! እነዚህን በእርሱ እርዳታ ስላደርግንስ ምን እንደምንባል ትገነዘባላችሁን? “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን!” ካላደረግንስ? “እናንተ ርጉማን ከእኔ ዘንድ ሂዱ!” እንግዲያውስ ለእኛ ሳይሆን ለሰይጣንና ለመላእክቱ የተዘጋጀውን እሳት ከሚያገኘን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለእኛ የተዘጋጀውን መንግሥት እንወርስ ዘንድ ዛሬ አብዝተን ዘይት የምንገዛ እንሁን፡፡ እንደነዚያ ሰነፍ ደናግላን እዚያ መግዛት በማይቻልበት ቦታ ሄደን ከምንጠይቅ ዛሬ ሳይመሽብን የሚበቃንን ያህል ዘይት እንግዛ፡፡ ዘይቱ የሚገዛውስ የት ነው? የታመሙት ጋር፤ እስረኞች ጋር፤ ቁርና ሀሩር በሚፈራረቅባቸው ወንድሞቻችናነ እኅቶቻችን ጋር፡፡

ልጆቼ! እንደ ነዌ እዚህ ምድር ባለጸጎች ሆነን ያኔ ከምንለምን ዛሬ አልዓዛርን ልናስበው ይገባል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ማየት ለተሳናቸው ምእመናን የጸሎት መጽሐፍትን አዘጋጅቶ አስመረቀ።

በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ የስብከተ ወንጌልና የርቀት ትምህርት አገልግሎት ዋና ክፍል ማየት ለተሳናቸው ምእመናን አገልግሎት የሚውል የብሬል የጸሎት መጽሐፍትን እና የድምጽ ትምህርቶችን በማዘጋጀት አስመርቋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ማየት የተሳናቸው ት/ቤት ግቢ ጉባኤ ሥር መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የብሬል መጽሐፍቱ በነጻ የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ ማስተባበሪያው በሌሎች አገራችን ክፍሎች እያስተማራቸው ለሚገኙ ማየት የተሳናቸው ምእመናን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ተገልጿል።

በዕለቱ ማኅበረ ቅዱሳን መሰል ሥራዎችን በትኩረት በማከናወን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን በተለይ የብሬል መጽሐፍት እና የድምጽ ትምህርቶቹን በሚገባ ለማዳረስ የአጋር አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል።
የማኅበረ ቅዱሳን ኬንያ ማእከል ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ በኬንያ ናይሮቢ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተከናወነ።

የማኅበረ ቅዱሳን ኬንያ ማእከል "“ቤተክርስቲያንን እንያት፣ እንወቃት፣ እንውደዳት፤ ድርሻችንን እንወጣ" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ዐውደ ርእይ ናይሮቢ በሚገኘው በደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ለዕይታ ቀርቧል።

ምእመናን የቤተክርስቲያንን መሠረተ እምነትና ዓለማቀፋዊነት ተረድተው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው የቤተክርስቲያን ትውፊት እና ተቋማዊ አንድነት ለማስጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማስገንዘብን ዓላማ ያደረገው ዐውደ ርእይ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት ሄኖክ ይገዙን ጨምሮ ጥሪ ተደረገላቸው እንግዶች እና ምእመናን ተገኝተው እንደጎበኙት ለማወቅ ተችሏል።
የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋዮች " ንጹሕ ምንጭ ኢትዮጵያ " የተሰኘውን ዐውደ ርእይ ጎበኙ

በሐመረ ብርሃን የብራና ሥራ ድርጅት  አማካኝነት " ንጹሕ ምንጭ ኢትዮጵያ " በሚል መሪ ቃል ግዮን ሆቴል እየተዘጋጀ የሚገኘውን ዐውደ ርእይ የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋዮች በዛሬው ዕለት ጎብኝተውታል። አገልጋዮቹ የብራና ሥራ ድርጅቱ እያከናወነ ያለው ተግባር እጅግ ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ገልጸዋል።

ዐውደ ርእዩ የቤተ ክርስቲያንን ቀደምት ታሪክ ፣ አስተምህሮ እና ሥርዓት ከማሳየት አንጻር ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን በተለይም የብራና ሥራን አሁን ላለው ትውልድ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው።

ድርጅቱ  በዘርፉ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ምእመናን በቀሩት ሁለት ቀናት በቦታው በመገኘት ዐውደ ርእዩን እንደከታተሉ ጥሪ ቀርቧል።
2024/09/29 14:23:42
Back to Top
HTML Embed Code: