Telegram Web Link
መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን

ክፍል አንድ


ውድ የዚህ ጽሑፍ አንባብያን! እንዴት ሰነበታችሁ? እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ‹‹መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ ተከታታይ ጽሑፍ እናደርሳችኋለንና ተከታተሉን፡፡

መልካም አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚሠራ ሳይሆን ተሠርቶ የተጠናቀቀ መዋቅር ባለቤት ናት፡፡ የመንግሥት መዋቅር በሌለበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ ከአጥቢያ እስከ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ድረስ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሊቃውንትን፣ ካህናትን፣ መነኮሳትን፣ ዲያቆናትን፣ መዘምራንን፣ ምእመናንንና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የምታስተዳድር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ብዙ የሰው ኃይል በማስተዳደር የሀገር ሸክምን ያቃለለች፣ የብዙ ሰዎችን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት የቀየረች፣ ለተራቡ ሁሉ ምግበ ሥጋ፥ ምግበ ነፍስ የምትመግብ ናት፡፡ የታመሙ የሚፈወሱባት፣ ያዘኑ የሚጽናኑባት፣ የተሰበሩ የሚጠገኑባት፣ የፈውስ፣ የድኅነት መገኛ መሆኗን ዓለም ያወቀው እውነት ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት ይህን ጽኑ ተግባር ስትፈጽም ከዚህ የደረሰችው ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብ በተሞሉ መሪዎችና አገልጋዮች ከፍተኛ አስተዳደራዊ ጥበብና መሥዋዕትነት ነው፡፡ ሥርዓተ መንግሥት አንድ ሺህ አንድ ጊዜ ፈርሶ ተሠርቷል፡፡ ምክንያቱም የሚመሩት ሥጋዊ ጥበብ ቢኖራቸው መንፈሳዊ ጥበብ የሚድጎላቸው ናቸውና፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ጥበብ የጎደላቸው እና ፍቅረ ንዋይ የሚገዳደራቸው አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ በመኖራቸው እየተፈተነች በከፋ የአስተዳደር ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡
መልካም አስተዳደር ማለት ምን ማለት ነው?

ዓለም በአሁኑ ጊዜ ትልቅ አጀንዳ ከሚያደርጋቸው ጉዳዮች ዋናው መልካም አስተዳደር ነው፡፡ መልካም አስተዳደር መገለጫው ብዙ ነው፤ እንደ የተቋማቱ ባሕርይ፣ የሥራ ሁኔታ በልዩ ልዩ ሁኔታ ሊገለጽ የሚችል ቢሆንም የጋራ ባሕርያት ይኖሩታል፡፡

ይሁን እንጂ መልካም አስተዳደር ውጤታማነት፣ ጥራት፣ የተገልጋዮችን ነጻነት የሚያከብር፣ አድልዎ የሌለባት፣ የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ግልጸኝነት፣ ያለው አገልግሎት መስጠትን፣ መልስ ሰጭነትን፣ ኃላፊነት መውሰድን፣ አሳታፊነት፣ ፍትሐዊነትና ስልታዊ የሆነ ርእይ መያዝን የሚያካትት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ መልካም አስተዳደር ካለ ሥልጣን ለያዙ ሰዎች ላይ ሕጋዊ ገደብ የሚያስቀጥ እና ሥልጣን በተወሰኑ በተጨማሪም መልካም አስተዳደር ግለሰቦች ሥር እንዳይሆን የሚያደርግ ነው፡፡

መልካም አስተዳደርን ከቤተ ክርስቲያን አኳያ ብፁዕ አቡነ አስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለሥራ ኃላፊዎች በሐምሌ ፳፻፭ ዓ.ም በተሰጠ ሥልጠና ላይ ተገኝተው እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡

‹‹መልካም አስተዳደር ማለት ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት በሁሉም መስክ በጎ አርአያነት ያለው መልካም እረኛ መሆን ነው፡፡›› የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በድረ ገጹ በለቀቀው አንድ ጽሑፍ ላይ ደግሞ ‹‹መልካም አስተዳደር ማለት በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር›› ማለት እንደሆነ ያትታል፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲገለጽ መልካም አስተዳደር የሚባለው ሐሳብ ከውሳኔ አሰጣጥ ሂደትና የተወሰነውን ውሳኔ ከማስፈጸም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም ለተገልጋዮች ፍላጎት ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ፣ መብታቸውን የሚያስጠብቅ፣ አገልግሎት የሚያቀርብ እና ሕጎችን ተግባራዊ የሚያደርግ የአስተዳደር ሥርዓት ሁሉ መልካም አስተዳደር ሊባል እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የምንለው ምኑን ነው?

በዓለም ያሉ ተቋማት ቢያስተዳድሩ የተወሰነ ጉዳይን ነው፤ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ግን ሥጋውንም፣ መንፈሳዊውንም ያቀፍ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ ይህም ከሰው ሀብት አስተዳደር፣ ከፋይናንስ አስተዳደር እና የንብረት አስተዳደር በተጨማሪ መንፈሳዊ አስተምህሮውም ያካተተ በመሆኑ ነው፡፡

ሀ. የሰው ሀብት አስተዳደር

የአንድ ተቋም ህልውናው የሚረጋገጠው ዋናውና የመጀመሪያው የሰው ሀብት አስተዳደሩ ነው፤ ተቋም ውጤታማ ለመሆን በጠንካራ፣ በብቁና በሥነ ምግባሩ ምስጉን የሆነ የሰው ኃይል መዋቀር አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራንና ሌሎችም በልዩ ልዩ ሙያ የሚያገለግሎ ምእመናንን በርካታ የሰው ኃይል ታስተዳድራለች፡፡ እነዚህ አገልጋዮች ብዙኃኑ ጠንካሮችና በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመሩ፣ የሥጋዊና መንፈሳዊ ዕውቀት ባለቤቶች ስለ ነበሩ ቤተ ክርስቲያኗ በማዕበልና በወጀብ ውስጥ አልፋ ለእኛ ልትደርስ ችላለች፡፡

ለ. የንብረት አስተዳደር

ቤተ ክርስቲያን እጅግ ግዙፍ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ቁጥራቸው ከአርባ ሺህ በላይ አድባራትና ገዳማትን፣ በርካታ የመሬት ይዞታዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ኮሌጆችን፣ ልማት ተቋማትን፣ ሕንፃዎችን፣ የጸበል ቦታዎችን እና ተሽከሪካረዎችን የአገልግሎት መስጫዎችን፣ መኪኖችን ከመንበረ ፓትርያሪክ እስከ አጥቢያ ድረስ ታስተዳድራለች፡፡

ሐ. የፋይናንስ አስተዳደር

በገንዘብ አስተዳደር በኩልም በስእለት፣ በዐሥራት በኩራት፣ በልማት፣ በኪራይ፣ በርዳታ፣ በስጦታ፣ በጸበል እና በልዩ ልዩ አገልግሎት ምክንያት የሚሰበሰብ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታስተዳድራለች፤ ታንቀሳቅሳለች፡፡

መ. የምእመናን አስተዳደር

መንግሥትም ሕዝብን ቢያስተዳድር በኃይል ታግዞ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ምእመናንን ታስተዳድራለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድ ተቋም እንደሚያደርገው በሥሯ የሚያገለግሉትን ብቻ ሳይሆን ምእመናንን በሥጋዊና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ትልቅ ኃላፊነት ወስዳ በኃይል ሳይሆን በሰላም በጠብ ያይደለ በፍቅር ታሰተዳድራለች፤ ትጠብቃለች፡፡

ሠ. የመንፈሳዊ ሀብት አሰተዳደር

ቤተ ክርስቲያን ሌላም ድርብ አስተዳደራዊ ኃላፊነት አለባት፡፡ እርሱም የማይዳሰሰውንና በቁሳዊ ዋጋ የማይተመነውን መንፈሳዊ ሀብት ማስተዳደር ነው፡፡ ይህም ዜማውን፣ ቅኔውን፣ ሥነ ጥበባዊ ዕውቀቱን፣ ሥነ ጽሑፋዊ ሀብቱ፣ ሥነ ሥዕሉን ሁሉ መንፈሳዊ ዋጋ ያለውን፣ መለያዋ የሆነውን ትጠብቃለች፤ ታስተዳድራለች፡፡ ከምንም በላይ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮውን፣ ትውፊቱን፣ ዶግማውን ከቀኖና አስተባብራ ትጠብቃለች፤ እንዳይቀሰጥና እንዳይሸራረፍ ታሰተዳድራለች፡፡

የተወዳጆችሁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! ለዛሬ በዚህ አበቃን! ‹‹የመልካም አስተዳደር እጦት በቤተ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ ሁለተኛውን ክፍል ይዘንላችሁ እስክንቀርብ ቸር እንሰንብት! አሜን!
የስብከተ ወንጌልን ተደራሽነት ለማስፋት 36 ሰባኪያነ ወንጌል ተመረቁ ፡፡

በጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ ፣ ቦረና ፣ ምሥራቅ ቦረና እና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከትና በማኅበረ ቅዱሳን ትብብር  የአገልጋይ እጥረት ካለባቸው ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ  36 ሠልጣኞች ለ 3 ወራት  የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲከታተሉ  ቆይተው  ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም  ሊቀ ማዕምራን ጌታሁን ሞርኪ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና የተለያዩ የሀ/ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ምእመናን በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡

     በሀገረ ስብከቱ የሚታየውን የሰባኪያነ ወንጌል እጥረት መቅረፍና ስብከተ ወንጌልን ማስፋት ዓላማውን ያደረገው ሥልጠና  ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ ሠልጣኞቹ የኦሮምኛ፣ጌድዮኛ፣ ኮንሶኛ፣ ሶማልኛና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ  በመሆናቸው የቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ከማስፈጸም አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል።  

በሥልጠናውም ነገረ ሃይማኖት ፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ፣ የስብከት ዘዴ ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ነገረ ድኅነት እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱ ሲሆን  ሥልጠናው በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት ከ 6 ዓመታት በፊት በነገሌ ቦረና ለሀ/ስብከቱ በተሠራው  አዳሪ አብነት ት/ቤት የተሰጠ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የጾም ቁርሳችን ለወገናችን
በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅና ማኅበራዊ ቀውስ ወገኖቻችን ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል።
ስለዚህ እርስዎ ከታኅሣሥ 1 -27 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የጾም ቁርስዎን በመስጠት የሰው ሕይወትን ያትርፉ።
በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሒሳብ ቁጥሮች፡-
1. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - 1000309803648
2. በአሐዱ ባንክ - 0025393810901
3. በወጋገን ባንክ - 0837331610101
4. በአቢሲንያ ባንክ - 37235458
5. በአዋሽ ባንክ - 01329817420400 በወገን ፈንድ ለመለገስ የተያያዘውን ሊንክ ይጫኑ።
https://www.wegenfund.com/causes/nu-badereqe-yatagodu-waganocaacenene-hheyete-eneta/
ማኅበረ ቅዱሳን
09 84 18 15 44
09 43 00 04 03
«ለአብያተ ክርስቲያናት ማሰሪያ በሚል መንገድ ላይ የሚለምኑ ከእውቅናዬ ውጪ ናቸው» የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን

በመንገድ ላይ ለአብያተ ክርስቲያናት ማሰሪያ ብለው የሚለምኑ አካላት ከእውቅናዬ ውጪ ናቸው ስትል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የቅዱሳን ስዕለ አድሕኖዎችን የያዙ ሰዎች በልመና ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በተመሳሳይ የቤተክርስቲያን ህንጻ ማሰሪያ ነው በሚል በስፒከር እያስነገሩ የልመና ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎችንም ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡

ታዲያ አሐዱ ሬዲዮ እነዚህን የልመና ተግባራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታቃቸዋለች ወይ ፤ ለምንስ ለሚገነቡት አቢያተ ክርስቲያናት የገንዘብ እርዳታ አታደርግም ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ጠይቋል፡፡

አዲስ ለማነጽም ሆነ ያገለገሉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስ ጠቅላይ ቤተክህነት ፈቃድ የሚሰጥበት አግባብ አለ ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት እቅድ እና ልማት መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቤ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በሀገሪቱ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናትን ለመገንባትም ሆነ ለማደስ መሰረታዊ የኪነ ህንፃ መስፈርቶችን አሟልቶ አስፈላጊውን እቅድ ወጥቶ የየሀገረ ስብከቱ ጳጳሳት ካወቁት እና ጠቅላይ ቤተ ክህነት ፈቃድ ከሰጠ በኋላ ነው ወደ ግንባታ የሚገቡት ብለዋል::

አብያተ ክርስቲያናቱን ለማሰራት ከአካባቢው ተወላጆች : ከበጎ አድራጊዎች እና ማህበራት : ከምእመናን እንዲሁም አባቶች ከንስሃ ልጆቻቸው በሚያገኙት ገንዘብ ካልሆነ መንገድ ላይ ወጥቶ መለመን አይቻልም ሕጋዊም አይደለም ሲሉ ነው ኃላፊው ያሳሰቡት፡፡

በመሆኑም ቤተክርስቲያኗ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሕጋዊ አይደሉም ምእመኑም ከመስጠት እንዲቆጠብ ነው የገለፁት::  

ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየሀገረ ስብከቱ ለሚገነቡ እና ለሚታደሱ አብያተ ክርስቲያናት በዓመት በጀት እንድሚመድብም ገልፀዋል:: ይሁን እንጂ በየመንገዱ የሚታዩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተገን አድርገው የሚለምኑት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ቤተክርስቲያኒቱ ብታሳስብም ችግሩ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም ሲል አጋዱ ሬዲዮ ዘግበዋል።
መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን
ክፍል ሁለት

፪. የመልካም አስተዳደር እጦት በቤተ ክርስቲያን፡-

መልካም አስተዳደር ምን ማለት እንደ ሆነ ከዚህ በፊት ባቀረብነው ክፍለ ትምህርት ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ መሆኑ እንደማያጠያይቅም ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችንን ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከመመሪያ እስከ አጥቢያ የመልካም አስተዳደር እጦት በእጅጉ እየፈተናት መሆኑን በርካታ አካላት ይገልጻሉ፡፡ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መጋቢት ፳፻፯ ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የወደ ፊት ሥጋቶች›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት ላይ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ለመውደቅ መፍገምገም ጀምራለች›› ሲሉ የጉዳዩን ክብደት አመልክተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለሥራ ኃላፊዎች ሐምሌ ፱ ቀን፣ ፳፻፭ ዓ.ም በተሰጠ ሥልጠና ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እየከፋ ስለመሄዱ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡

አቡነ ሳሙኤል ባቀረቡት ጥናት የታደሙ አካላትም በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗ በዕቅድና በሕግ እየተመራች አለመሆኑን፣ እንዲሁም በጥራዝ ነጠቆች እየተደፈረች፣ ደካማ አመራርና አንዱ ከሌላው የሚጣረስ የሥራ ኃላፊነት መኖር፣ መስመር የለቀቀ ዘረኝነት፣ ልቅ ሙስናና ዝርፊያ መስፈኑንና ዘመናዊ አስተዳደር እንዳይኖር የሚቃወሙ አካላት ጭምር መብዛታችውን አንሥተው ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ጥናት አቅራቢው አባት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በወቅቱ ዋና ዋና ያሏቸውን ግኝቶች ሲያስረዱ፡-
• ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የመዋቅራዊ አደረጃጀት ክፍተት መኖሩን፤
• ተጠያቂነት የሌለበት ኃላፊነት መስጠት እየተለመደ መምጣቱን ፤
• በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ የሰው ኃይል ምደባ መለመዱን
• የሥራና ሠራተኛ አለመገናኘት (የሥራ ድርሻን ለተገቢው ሰው ያለመስጠት)
• በመንደርተኝነት መሳሳብና ሀብት ለማፍራት መሯሯጥ መብዛቱን፣
• ኋላ ቀር የፋይናንስ ሥርዓትና የንብረት አያያዝ መኖሩ እና መሰል በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቤተ ክርስቲያንን ገፍተው ሊጥሏት እንደሆነ በጥናታቸው ገልጸዋል፡፡

ቀሲስ ወንድም ስሻ አየለ የተባሉ አባት በበኩላቸው ‹‹የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሻሻል ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት የጥናት ሰነድ ‹‹ቀኖናዊነትን አጽንቶ የዛሬውን ትውልድ ለመምራት ጥብቅና ዘመናዊ አስተዳደር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ይህን እንደ ሽፋን ሊጠቀምበት የሚፈልግ የእምነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ፍላጎት ያለው ሁሉ ለራሱ ጥቅም እየገባ ያሻውን እንዲያደርግ ምቹ ሆኖ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግር ደረጃው ይለያያል እንጂ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የሚታይ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አህጉረ ስብከት በተለይም ከፍተኛ ሀብት ባላቸው አድባራትና ገዳማት ችግሩ ከፍተኛ ነው፡፡

፪.፩. የቤተ ክርስቲያን መልካም አስተዳደር እጦት መንሥኤዎች፡-

ቤተ ክርስቲያንን እግር ከወርች ይዞ አላራምድ ያላት የመልካም አስተዳደር ችግር ብዙ መንሥኤዎች ይኖሩታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩ኛ. የመዋቅር ችግር

ይህም ማለት መዋቅራዊ አደረጃጀቱ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱንና በየደረጃው ያሉ የመምሪያና የአድባራት ኃላፊዎችን ሚና ቁልጭ አድርጎ የሚያመለክት አለመሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ዕውቀት አይኖረውም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን እንዲያስተዳደሩ፣ ሌላው ደግሞ የፋይናንስ፣ የንብረት፣ የሰው ኃይል አስተዳድሩን እንዲሁም ልማቱን ወቅቱ በሚፈልገው ዕውቀትና የሰው ኃይል እንዲመራ አለመደረጉ በዕለት ዕለት እንቅስቃሴያችን የምንታዘበውና ከላይ የጠቀስናቸው ጥናት አቅራቢዎችም የጠቆሙት ሐሳብ ነው፡፡ አሁናዊውን የቤተ ክርስቲያን የተወሳሰበ አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት ከመንፈሳዊ ዕውቀትና መንፈሳዊነት ባሻገር ጊዜው በሚጠይቀው የአስተዳደር ጥበብና ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

፪ኛ.የምእመናን ተሳትፎ አናሳ መሆን

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማኅበረ ካህናትንና ማኅበረ ምእመናንን ያቀፈ ነው፡፡ ስለሆነም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ መተኪያ የሌለው ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አባቶቻችን ሥጋዊውንም፥ መንፈሳዊውንም አስተዳደር ስለሚመሩ ከአስተዳደሩ ስፋትና ወቅቱ ከወለደው የአስተዳደር ጥበብ የተነሣ ክፍተቶች ስለሚፈጠሩ ይህን ክፈተት ለመሙላት ምእመናን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የሥራ ክፍፍልን ያስተማረች ቤተ ክርስቲያን አሁን ላይ አስተዳደራዊ ፈተናዎች የበዙበት በመሆኑ ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የማስፈጸም እና ሕግ የመተርጎም ሥራ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ሙያው ያላቸውንና የተመሰከረላቸው ምእመናን ማሳተፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ይሞላል፡፡ ይህን በተመለከተ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልም በጥናታቸው ‹‹ለምእመናን የተሰጠ ሥልጣን ስለሌለ ይህም ተጠያቂነት የሌለበት አሠራር እንዲሰፍን አድርጓል›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊው ካህን የሙሴ አማት ዮቶር ሙሴ ሕዝቡን በመዳኘትና በመምራት በደከመና ሕዝቡ በተጉላላ ጊዜ ማድረግ ያለበትን እንደሚከተለው መክሮታል፡፡

‹‹……አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም፡፡ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም፡፡……አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፤ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፤ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው፡፡….ከሕዝቡ ሁሉ ዐዋቂዎችን፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ…..በሕዝቡ ላይ ሁል ጊዜ ይፍረዱ፤…እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፤ ለአንተም ይቀልልሃል፡፡….መቆም ይቻልሃል፤ ሕዝቡም በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል…›› ሲል መፍትሔውን ነግሮታል፡፡ (ዘፀ.፲፰፥፲፯-፳፫)

ችግሩን ለመቅረፍ አባቶቻችን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሕግ አውጪም፣ ሕግ አስፈጻሚም፣ ሕግ ተርጓሚም ሆነው፣ ሃይማኖታዊውንም ሥጋዊውንም ጉዳይ ሊያስተዳድሩና ሊመሩ አይገባም፡፡ የአብያተ ክርስቲያን አስተዳደዳሪዎችም ሙያ የሚጠይቀውን ሥራ ለባለሙያው አይተውም፡፡ ከልማት ኮሚቴ፣ ከሰበካ ጉባኤ፣ እንዲሁም በየደረጃው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ መንፈሳዊ ማኅበራት ጋር የሚፈጠረው ግጭት ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ይህ ማለት ለምእመናን ምንም ሥልጣን አልተሰጠም ማለት ሳይሆን በቂ አለመሆኑንና ተግባራዊነቱም ችግር የሚስተዋልበት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡

፫ኛ. የመንግሥት ጣልቃ ገብነት

በቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከቀድሞ ጀምሮ ችግር ሆኖባት የዘለቀ ጉዳይ ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት እንዳይለያዩ በማድረግ ብዙ የሃይማኖት መሪዎች በንጉሡ ይሾሙ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ የደርግ መንግሥት ሲገባ ቤተ ክርስቲያንን ከንጉሡ ጋር በመፈረጅ ሀብት፣ ንብረቷን ወርሷል፡፡ ኢሕአዴግ መንግሥትም በከፍተኛ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መዳከምና ለመልካም አስተዳደር ችግር እንድትጋለጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን አሁንም የተላቀቀችው ችግር ባለመሆኑ ዘረኞች፣ ሙሰኞች፣ ተሐድሶ መናፍቃን እንዲሁም ፖለቲከኞች በመንግሥት ትከሻ ተጭነው ቤተ ክርስቲያን በመግባታቸው፣ ሕዝብ በፖሊስ የሚያስደበድቡ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ቢሮዎችን፣ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከላትን የሚያሳሽጉ፣ የሰበካ ጉባኤ እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችን የሚያሳስሩ ሰው የሚያስፈራሩ የግል ፖሊስ ጥበቃ ያላቸው አማሳኝ ቡድኖች ከዚህም ከዚያም የሚታዩ መሆናቸው የአደባባይ እውነት ነው፡፡

፬ኛ. ዕውቅና ያለው የራሷ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አለመኖር

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፈንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን?...በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው፡፡ ብትበደሉ አይሻልምን?ብትታለሉስ አይሻልምን?›› ይላል፡፡ (፩ኛቆሮ.፮፥፩-፯)

ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋና ሥርዓቷ በሚፈቅደው አግባብ አገልጋዮቿንና ምእመኖቿን የምትዳኝበት ፍርድ ቤት የላትም፡፡ የአገልጋዮች ጉዳይ ጭምር የሚዳኘው በመንግሥት ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀኖና ጥሰትና በእምነት ችግርና በሌሎችም ጉዳዮች ቤተ ክርስቲያን ያገደቻቸው አካላት ተመልሰው እንዲገቡና የብልሹ አስተዳደር ምክንያት ሆነው እንዲዘልቁ ከማድረጉም በላይ ቤተ ክርስቲያናንን ለትችት ዳርጓታል፡፡

፭ኛ.ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ድልድል አለመኖር
ይህ መሠረታዊ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየደረጃው የሚሾሙና የሚቀጠሩ ሰዎች ማንነት፣ ብቃት፣ መንፈሳዊነት ሁልጊዜ ጥያቄ ይነሣበታል፡፡ ምደባው፣ ዝውውሩና ቅጥሩ በጣም ግልጸኝነት የጎደለው፣ ከወንዜነትና ከጥቅም ጋር የተሳሰረ፣ “ምን ያህል ተምረሃል? ሳይሆን ምን ያህል ትከፍላለህ?” የሚባልበት፣ እምነቱ፣ ሥነ ምግባሩ፣ እውቀቱ ግምት ውስጥ የማይገባበት፣ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነት የጠፋበት ቅጥር፣ ዝውውር፣ ሹመት የሚሰጥበት መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ ‹‹በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል›› እንዳለ ሐዋርያው ብዙ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሳይቀር በየመድረኩ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ብልሹ አሠራር እያነሡ ምእመናንን አንገት ሲያስደፉ የነበረው የሚረሳ አይደለም፡፡ (ሮሜ ፪፥፳፬)

በየጊዜው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባነር አሠርተው ሰልፍ የሚወጡ አገልጋዮችና ምእመናን ሁሉ ስናስታውስ የሚያመለከቱት ይህንኑ እውነት ነው፡፡ የሀብት ክፍፍሉም ፍትሐዊ አለመሆኑ ምንም አጠያያቂ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሀብት ቢኖራትም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ግን ማስቀደሻ አጥተው ተዘግተዋል፡፡ ነጠላ ለብሰው የሚቀድሱ ካህናት እንዳሉ የሰማ ጆሮ አዲስ አበባ ያለውን ማስቀመጫ ያጡ አልባሳትና ንዋያተ ብዛት ማሰብ ያማል፡፡

ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ቀዳሽ አጥተው፣ ብዙ ተማሪዎች መምህር አጥተው ብዙ መምህራን ምግብ አጥተው ጉባኤ ታጥፏል፡፡ ወንጌል ተሰብኮበት የማያውቅ ዐውደ ምሕረት ብዙ ነው፤ ብዙ ገዳማት ተፈተዋል፡፡ ሀብቷ ለገዳሞቿ፣ ለምእመናን፣ ለአብነት ትምህርት ቤቶቿ አልደረሰም፡፡ ሁሉም ከተማ ገብተዋል፤ ሁሉም አንድ ቦታ ላይ ተከማችተዋል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ እና አንዳንድ ትልልቅ ከተሞች ላይ በወር አንድ ጊዜ እንኳን የአገልግሎት ተራ የማይደርሳቸው አገልጋዮች ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ችግረኛ ገዳማትና አድባራት፣ ጥቂት የተትረፈረፈ ሀብት ያላቸው ባለጸጋ ገዳማትና አድባራት፣ ሊቀምሱት፣ ሊለብሱት ያጡ ብዙ መነኮሳትና ካህናት እንዲሁም በቅንጡ መኪና የሚንሸራሸሩ ጥቂት መነኮሳትና ካህናት፣ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር ለመቅረፍ፣ ክብሯን ለማስጠበቅ፣ ገዳማቷ፣ አብነት ትምህርት ቤቶቿ እንዳይፈቱ ቆላ ደጋ የሚሉ፣ ከኪሳቸው ችግሯን ለመቅረፍ የሚተጉ ምእመናን ያሏት ቤተ ክርስቲያን ገንዘቧን መዝብረው፣ ቅርሷን ሸጠው በዓለም ጌጥና ምቾት የሚዘባነኑ ጥቂት ግለሰቦች ያሏት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የብልሹ አስተዳደር መገለጫው ይህ ነው፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች! የመልካም አስተዳደር መንሥኤዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ እንመለስበታለን፡፡ እስከዚያው መልካም ሳምንት!
ከሐዲያ ስልጤ ሀገረ ስብከት የተወጣጡ ተተኪ መምህራን ተመረቁ።

የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያምና  ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ  ካቴድራል ዕውቀት ብርሃን ሰ/ት/ቤት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር  ከሐዲያና ስልጤ  ሀገረ ስብከት ለተወጣጡ ተተኪ መምህራን ለተከታታይ 15 ቀናት የሰጡት ሥልጠና  ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቆ ሠልጣኞች ተመርቀዋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁእ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎች የአገልግሎት መመሪያ እና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኮት ይኄይስ እንደገለጹት ሠልጣኞቹ በሚሄዱበት ቦታ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዕውቀተ ብርሃን ሰ/ት/ቤት ሰብሳቢ የሆኑት ዲ/ን ፋሲል ጳውሎስ ሰ/ት/ቤቱ ለሠልጣኞች የትራንስፖርት፣ የምግብ እና የሥልጠና ግብአቶች ሙሉ ወጪን በመሸፈን ሠልጣኞች በቆይታቸው ለአገልግሎት የሚጠቅማቸውን ዕውቀት እንዲገበዩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

የማኅበረ ቅዱሳን የትምህርት እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ማንደፍሮ ስንታየሁ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት በዛሬው ዕለት የተመረቁት መምህራን የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስቀጠል ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ማኅበረ ቅዱሳን ሌሎች ሰ/ት/ቤቶችም ይህንን ልምድ በመውሰድ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመለመሉ ተተኪ መምህራንን በማሠልጠን የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ እንዲደግፉ ጥሪውን እያስተላለፈ በማኅበሩ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻል።
ማኅበረ ቅዱሳን በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች 1 ሚሊዮን ብር ወጭ የሆነበት ድጋፍ አደረገ
+++

ባለፉት ዓመታት በሀገራችን እያጋጠመ ባለው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት፣ ጦርነትና መፈናቀል ኦርቶዶክሳዊያንን ጨምሮ ብዙ ወገኖቻችን ለከፋ ማኅበራዊ ቀውስ ተጋላጭ ሁነዋል። ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት 5 ዓመታት በአርሲ፣ በሐረር ፣በባሌ፣ በወሊሶ፣ በሻሸመኔ፣ በምዕራብ ሸዋ ባኮ ትቤ፣ በመተከል፣ በቤንሻጉል ጉምዝ ድባጤና ቡለን፣በሽሬ፣ በአክሱም፣ በአዲግራት፣ በመቐለ እንዲሁም በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ በወልዲያ፣ በላሊበላ፣ በሐይቅ እስጢፋኖስ፣ በቻግኒና በሌሎች የሀገራችን ክፍል ያጋጠሙ ማኅበራዊ ቀውስና ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ድጋፍ አድራጊ ምእመናንና ተቋማትን እያስተባበረ የአልባሳት፣ የምግብ እና መሠል አስቸኳይ ድጋፎችን በስፋት ሲያደርግ ቆይቷል። አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል።

በአሁኑ ወቅት ሰፊ ተፈናቃይ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ደብረ ብርሃን ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። በከተማዋና በዙሪያው ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የተሰደዱ ከ25,000 በላይ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። የባቄሎ መጠለያ ጣቢያ ከ4,500 በላይ ተፈናቃዮችን ይዟል።
የማኅበረ ቅዱሳን ሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ በዚህ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች መጭው በዓለ ልደት ምክንያት በማድረግ ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በቦታው በመገኘት 105 ኩንታል የምግብ ግብዓት ድጋፍ አድርጓል። ለድጋፉ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) ብር ወጭ ተደርጓል። በድጋፍ ርክክብ ወቅትም የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ እኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ አባቡ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ልዑካንና የደብረ ብርሃን ማእከል ተወካዮች በተገኙበት የእጅ በእጅ ተደርጓል።

ከወለጋና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተፈናቃሉ እነዚህ ተጎጅዎች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ከኖሩበት ቀያቸው ተፈናቅለው የተሰደዱና ባለፉት 3 ዓመታት አሰቃቂ የተባለ ሕይዎት እየመሩ መሆናቸውን ገልጸው የሚመለከታቸው አካላት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።

ድጋፉ ከሜሪላንድ ኆኅተ ምሥራቅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ከአሜሪካ ደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ክርስቶስ ሠምራ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፣ከደቡብ አፍሪካ ላይ ድንበርግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽዋ ማኅበር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተከናወነ ነው።

በተመሳሳይ መረጃ በቅርብ ጊዜያት ብቻ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅና ጃን አሞራ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች፣ በሰቆጣና አካባቢው ለሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በደቡብ ኦሞ በናጸማይ ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች፣ በሃይማኖት ተኮር ጥቃት ከቅበት ተፈናቅለው ቡታጅራ ይገኙ ለነበሩ ተጎጅዎች ተመሳሳይ ድጋፎች ተደርገዋል።

ማኅበረ ቅዱሳን በቀጣይ ጊዜያትም በድርቅና ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ቀውሶች ለተጎዱ አካባቢዎች ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረስ “የጾም ቁርሳችን ለወገኖቻችን” በሚል ሰፊ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ እያደረገ ይገኛል። ስለሆነም ማኅበሩ የሚያከናውናቸው የማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮጀክት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አጋርና ባለድርሻ አካላት የተለመደ ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪችንን እናቀርባለን።

ድጋፍ ለማድረግም፡-
በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሒሳብ ቁጥሮች፡-
1. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000309803648
2. በአሐዱ ባንክ 0025393810901
3. በአቢሲንያ ባንክ 37235458
4. በወጋገን ባንክ 0837331610101
5. በአዋሽ ባንክ 01329817420400
6. በወገን ፈንድ፡- https://www.wegenfund.com/causes/nu-badereqe-yatagodu-waganocaacenene-hheyete-eneta/ መጠቀም የምትሉ መሆኑን እንገልጻለን።

ለበለጠ መረጃ
• 09 84 18 15 44
• 09 43 00 04 03

ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 1ኛ ወለል

የማኅበረ ቅዱሳን ሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስተባበሪ
2024/09/30 18:23:14
Back to Top
HTML Embed Code: