Telegram Web Link
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብዙኃን መገናኛ ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የበላይ ኃላፊ በዩጋንዳ ኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑትን ክብርት አምባሳደር እጸገነት በዛብኅ ጋር ተወያዩ፡፡

ብፁዕነታቸው ዩጋንዳ ሲያቀኑ በኢንቴቤ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተቀብለዋቸው የመድኃኔዓለምን ክብረ በዓል በካምፓላ መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አክብረዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በዩጋንዳ ቆይታቸው የሀገረ ስብከቱን የሥራ ኃላፊዎች በማነጋገር የሥራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤምባሲን በመጎብኘት በዩጋንዳ ኢፌዴሪ አምባሳደር ከሆኑት እጸገነት በዛብኅ ጋር ተወይይተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ የተጻፈላቸውን የምደባ ደብዳቤ ቅጂ ለክብርት አምባሳደሯ የሰጡ ሲሆን፤ አምባሳደር እጸገነት በዛብኅ የብፁዕነታቸውን ደብዳቤ በክብር ተቀብለው ብፁዕነታቸው በኤምባሲው ተገኝተው ስለጎበኟቸውና ስለባረኳቸው ምስጋናቸውን በመግለጽ ከቤተክርስቲያኗ ጋር አብሮ ለመሥራት ያላቸውን ተነሳሽነት ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በቀጣይ በካምፓላ መንፈሳዊ ትምሕርታቸውን በመከታተል የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነት በመከተል ሥርዓተ ጥምቀት የሚፈጸምላቸው ዩጋንዳውያንን የሚያጠምቁ ሲሆን መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ለተከታተሉ ታዳጊዎችም ማዕረገ ዲቁና ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል EOTC TV ዘግቧል።
የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን መርሐ ግብር ተከናወነ።

በማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት እና ትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ በኩል በየ 3 ወሩ የሚዘጋጀው ዓለም አቅፈ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን መርሐ ግብር በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ ተከናውኗል።

ዝማሬ፣ ትምህርተ ወንጌል እና የልምድ ልውውጥን ያካተተው መርሐ ግብር በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን በሌሎች የክልል ከተሞች የሚገኙ የማኅበሩ አባላት በማእከላት አስተባባሪነት በቀጥታ ስርጭት እንዲከታተሉት ተደርጓል።

የማኅበረ ቅዱሳን ሕዝብ ግንኙነት እና ትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ ም/ኃላፊ የሆኑት መጋቤ ብርሃናት ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት አባላት ከግቢ ጉባኤ ተመርቀው ከወጡ በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጠነክሩ እና እርስ በእርስ በመገናኘት በኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲጎለብቱ ማድረግን ዓላማ አድርጎ በሚዘጋጀው በዚህ መርሐ ግብር በ2015 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በተጨማሪም ማኅበሩ ጉባኤ ከማዘጋጀት ባለፈ ለምሩቃኑ የሀገር ውስጥ እና ውጭ የትምህርት ዕድል ድጋፍ እንዲሁም የሥራ ዕድል የማመቻቸት ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህንን አገልግሎት የሚፈልጉ አባላት "ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን ኅብረት" በሚል የተከፈተውን የቴሌግራም ቻናል መቀላቀል እንዲሚችሉም አሳውቀዋል።
በተጨማሪም ማኅበሩ የሥራ ፈጠረ ሐሳብ ያላቸው የግቢ ጉባኤ ምሩቃንን በማወዳደር የተሻለ ውጤት ለሚያመጡ አባላት ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ኃላፊው አባላት ከ ኅዳር 1 እስከ ኅዳር 30 2016 ዓ.ም ድረስ የፈጠራ ሐሳባቸውን ማስገባት ይችላሉ ብለዋል። አባላት በተጠቀሱት ቀናት በማእከላት ወይም በዋና ማእከል በመገኘት የፈጠራ ሐሳባቸውን ማስገባት እንደሚችሉም ጠቅሰዋል።

ይህንን አገልግሎት የሚፈልጉ አባላት "ዓለም አቀፍ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን ኅብረት" በሚል የተከፈተውን የቴሌግራም ቻናል መቀላቀል እንዲሚችሉም አሳውቀዋል።

https://www.tg-me.com/gibigubayat_mirukan_hibret
"ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽሽ ተመለሽ" (መሓ.፯፥፩)

ክፍል አምስት (የመጨረሻ ክፍል)

‹‹ወጎየ እግዚእ ኢየሱስ ውስተ ደብረ ሊባኖስ ወውስተ ምድረ ግብጽ ወብሔረ አግዓዚ ምስለ ማርያም እሙ፤ ጌታችን ከእናቱ ማርያም ጋር ወደ ሊባኖስ ተራራ ወደ ግብጽና ወደ ኢትዮጵያ መልአኩ እንደነገረው ሳያመነታ ተሰደደ፡፡›› (ትርጓሜ ማቴ. ፪፥፲፫)

እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያም ጭምር እንደ ተሰደደች፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በተለያዩ ስፍራዎች እንደ ተመላለሰች፣ ሀገራችንንም፣ ሕዝባችንንም እንደ ባረከች፣ ተወዳጅ ልጇ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብዙ እንደ ነገራት፣ በቃል ኪዳኗ እንድትጠብቃቸው፣ በምልጃዋ እንድታስምራቸው፣ ዐሥራት አድርጎ እንደ ሰጣት፣ በዚህም የእመቤታችንና የኢትዮጵያውያን ጥልቅ ፍቅር የጸና መሆኑን ሊቃውንትም መዛግብትም ያስረዳሉ፡፡ (ድርሳነ ዑራኤል መቅድም)

ይህን የሚያረጋግጥልን ‹‹ወጎየ እግዚእ ኢየሱስ ውስተ ደብረ ሊባኖስ ወውስተ ምድረ ግብጽ ወብሔረ አግዓዚ ምስለ ማርያም እሙ፤ ጌታ ከእናቱ ከማርያም ጋር ወደ ሊባኖስ ተራራ ወደ ግብጽና ወደ ኢትዮጵያ መልአኩ እንደ ነገረው ሳያመነታ ተሰደደ›› የሚለው ነው፡፡ (ትርጓሜ ማቴ. ፪፥፲፫)

መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም ዕንባቆም ‹‹የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ የምድያም አገር መጋረጃዎች ተንቀጠቀጡ›› ሲል የተናገረውን ጌታችን እና ከእናቱ ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ጋር አገናኝተው ይተረጉሙታል፡፡ (ዕንባ. ፫፥፮)
በድርሳነ ዑራኤል ተጽፎ እንደምናገኘው እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው በሀገረ ናግራን በኩል አልፋ በደብረ ዳሞ፥ በአክሱም፣ በደብረ ዓባይ ከዚያም በታላቁ ገዳም ዋልድባ አድርጋ መላው ኢትዮጵያን በደመና ተጭና በመልአኩ ዑራኤል መሪነት ሲሆን በብዙ ቦታዎች በኪደተ እግሯ ተመላልሳ ጎብኝታታለች፤ ባርካታለች፡፡ ‹‹ሰላም ለምጽአትክሙ ጥንተ ዜና ነገር አእመነ፤ በዓለ ደመና ዑራኤል ወድንግለ ሲና እምነ፡፡ ሰሎሜ ወዮሴፍ በኢትዮጵያ ምድርነ፡፡..፤ ከጥንት ጀምሮ የተነገረውን ዜና ለማሳመን የደመናው ባለቤት ዑራኤል ዮሴፍና ሰሎሜ፤ የሲናዋ ድንግል እናታችን ሰላምታ ይገባችኋል፤ ለአደረጋችሁት አመጣጥ በኢትዮጵያ ምድራችን›› እንዲል፡፡

እመቤታችን ለተወዳጁ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ነገረችው ጌታችን በተወዳጅ እናቱ ጀርባ ላይ ሆኖ አብዝቶ ወደ ምዕራብ ይባርክ ስለ ነበረ እንዲህ ስትል ጠይቃው ነበር፡፡ ‹‹ለምንት ኩለሄ ትባርክ ነቢረከ ኅዙለከ ዲበ ዘባን ምድረ አዜብ…፤በጀርባዬ ላይ ሆነህ ሁል ጊዜ ወደ ምዕራብ የምትባርከው ስለምን ነው ብዬ ጠየቅሁት፡፡›› (የኅዳር ድርሳን) ልጇም እንዲህ ሲል መለሰላት፤ ‹‹ኦ እምየ ይእተ ሀገረ ዘእባርክ ወሀብኩኪ ዐሥራተ ወይኩኑ ለኪ ሰብአ ኢትዮጵያ ክፍለ ለርስትኪ እስከ ኅልቀተ ዓለም….፤ እናቴ ሆይ በዚች በምባርካት አገር በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ዐሥራት አድርጌ ሰጥቸሻለሁ፤ እናቴ ሆይ አሁንም ወደዚያች ሀገር እንሄድ ዘንደ ተነሽ..›› ይላታል፡፡ እናቱን እንዲህ ባለ ቃል ከነገራት በኋላ ብሩህ ደመና ጭናቸው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡

በዚህም በሃማሴን በኩል አድርገው በደብረ ዳሞ፣ በአክሱም ጽዮን፣ በደብረ ዓባይ በተለይም በዋልድባ ወደ ጣና ደሴት ከመግባታቸው በፊት ቆይታ አድርገዋል፤ በአክሱም ጽዮን ገብታ ሕዝቡንም ካህናቱንም ንጉሡንም ባርካቸዋለች፡፡ ደራሲው ይህንንም በውብ ቃል እንዲህ ሲል ይገጸዋል፤ ‹‹…ተፈስሐት ዓውደ ጽዮን ወተሰርገወት ብርሃነ፡፡ እስመ ጽዮን እንዘ ጽዮን አብዓለት ጽዮነ፤ እርሷ ጽዮን ስትሆን የጽዮንን በዓል አከበረች ጽዮን፡፡ የጽዮንንም አደባባይ ደስ እያላት አከበረች በብርሃን›› ይላል፡፡ እመቤታችን በገዳመ ዋሊ (ዋልድባ) በዋሻዎቿ ሁሉ ተቀምጣ፣ የሚበላ ሳይኖር ልጇ መራራ የዕፅዋት ሥሮችን ቆፍሮ ሰጥቷት ቀምሳ ስለ እርሷ ፍቅር መራራውን ቀምሰው፣ መከራውን ታግሠው፣ በስሟ ተማጽነው፣ በውዳሴዋና በቅዳሴዋ ተጽናንተው፣ ሥጋን እስከ ክፉ መሻቱ አሸንፈው ሰማያዊ ሰው ምድራዊ መልአክ ሆነው የሚኖሩ መነኮሳት መናንያን የሚኖሩበት ታላቅ የቅድስና ስፍራ እንዲሆን ያደረገችው በዚሁ በስደቷ ወቅት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ደጎች እንደ ነበሩ፤ እንግዳ ተቀባይነታቸውም በቃላት የማይገለጽ እንደ ሆነ እመቤታችን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡ ከዋልድባ ተነሥታ ጣናንና አካባቢውን በጎበኘችበት ጊዜ በደስታ እንደ ተቀበሏት እንዲህ ትላለች፤ ‹‹በብርሃን ሠረገላ ተጭነን ተነሣንና ከጣና ባሕር ወደብ ደረስን በዚያች የባሕር ደሴት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እነዚህ የነገሥታት ልጆች የሚመስሉ እንግዶች ከወዴት መጡ እያሉ በመደነቅ በደስታ ተቀበሉን፤….እነዚያ ደጋግ ሰዎች መምጣታችንን ለጌታቸው ነገሩት፡፡ እርሱም ፈጥኖ ተነሣና ወደ እኛ መጥቶ በሰላም፣ በደስታ ተቀበለን፤ ማረፊያ ቦታም ሰጠን›› በማለት ለቅዱስ ዮሐንስ ስትተርክለት ጽፎታል፡፡

እመቤታችን በጣና ውስጥ ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ተቀምጣለች፡፡ በዚህም ምክንያት የጣናን ባሕር የብርሃን መላእክት መጥተው በእሳት ሰይፍ ስለ ከበቧት አጋንንት እንደ ሸሹ፣ መባርቅትም ሊያጠፏቸው እንደ ተከታተሏቸው፣ በዚያም በባሕር እንዳሰጠሟቸውና ወደ ሲኦልም እንደ ጣሏቸው በድርሳነ ዑራኤል ላይ ተጽፏል፡፡ (ደርሳን ዘታኅሣሥ)

እመቤታችን እና ተወዳጅ ልጇ በስደት የቆዩበት ዘመን የተፈጸመውም በኢትዮጵያ ነው፡፡ ‹‹ወመዊቶ ሄሮድስ፤ ናሁ መልአከ እግዚአብሔር አስተርዮ በሕልም ለዮሴፍ በምድረ ግብጽ እንዘ ይብል ተንሥእ ወንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወሑር ውስተ ምድረ እስራኤል፤ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ በግብጽና በኢትዮጵያ ሳለ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ነገረው፤ ብላቴናውንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ እስራኤል ተመለስ፤ ሕፃኑን የሚፈልጉት ሞተዋልና›› እንዲል፡፡ (ማቴ.፪፥፲፱) የሄሮድስ መሞት የምሥራቹን የሰሙት በጣና ደሴት ለሦስት ወር ከዐሥር ቀን ያክል ከተቀመጡ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ መልአኩ እንዲህ አላት፤ ‹‹ተንሥኢ እግዝእትየ ከመ ንሁር ሀገረኪ ናዝሬተ ወተጸዓኒ ዲበ ሠረገላ ብርሃን መልዕልተ ደመና ዘሀሎ፤ ተነሽ ወደ ሀገርሽ ናዝሬት እንሂድ አላትና ሊሄዱ ተነሡ፡፡ ያ ደግ እንግዳ ተቀባይ ሀገረ ገዥ ምነው ምን በደልኩ ለምን ትሔዳላችሁ›› እያለ እያለቀሰ ለመናቸው፡፡

በዚህ ጊዜ መልአኩ ‹‹ምንም አልበደልክም፤ አንዳችም ክፉ ሥራ አልሠራህባቸውም፤ ሄሮድስ ስለ ሞተ ወደ ገሊላ ስለሚመለሱ ነው›› አለው፡፡ ያ መኮንንም ይህን በሰማ ጊዜ ጮሆ አለቀሰ፤ የደሴቱና አካባቢው ሰዎችም እስኪሰበሰቡ ድረስ ጮኸ፡፡ ከዚህ በኋላ ከደመናው በላይ ባለው የብርሃን ሠረገላ ላይ ወጥታ ቆመችና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ተራሮችን ሁሉ እያሳየ ‹‹ለስምሽ መታሰቢያ ይሁኑሽ›› አላት፤ ባረከቻቸውም፡፡

በዚህ የተደሰቱ የመላእክት ማኅበር በሙሉ ተሰብስበው ‹‹በእንቲአኪ ተራከባ ሣህል ወርትዕ ጽድቅ ወሰላም ተሰዓማ ለዛቲ ሀገረ ኢትዮጵያ ምሕረትኒ ወጽድቅ ይነብር ላእሌሃ..፤ በአንቺም ይቅርታና ቅንነት እውነትና ሰላም ተገናኙ፤ በዚችም በኢትየጵያ ምድር ላይ ምሕረትና እውነት ይኖራሉ›› ሲሉ አመስግነዋታል፡፡ ይህን ሁሉ ከስደቷ መልስ ለዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ የተረከችለት ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ! እመቤታችንና ኢትዮጵያውያንን ያቆራኛቸው ቃል ኪዳን እስከ ዓለም መጨረሻ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የማንዘልቀውን ጀምረናልና በዚሁ ይበቃናል፤ ብቻ ዝም ብለን በጠቢቡ ቃል እኛም ‹‹ተመየጢ፥ ተመየጢ፥ ሰላመ ሰጣዊት ወንርአይ ብኪ ሰላመ›› አንቺ የሰላም መፍሰሻ፣ አንቺ የደስታ መገኛ ሆይ፥ ተመለሽ!›› እንበላት፡፡ (መቅድመ ኪዳን)

አሁን ኢትዮጵያውያ ስደተኛ መቀበል አትችልም ስደተኛ ሆናለችና፤ ሱላማጢስ ሆይ አሁን እነዚያ ደጋግ ሰዎች ለእንግዳ ማረፊያ አይሰጡም፤ እነርሱም ማረፊያ መጠለያ አጥተዋልና፤ አሁን የተራበን ለማብላት አቅም የላቸውም፤ እነርሱም ረኃብተኞች ናቸውና፡፡ እናታችን ሆይ ተመለሽ! ሰላማችን ሆይ ነይ! ወደ ዐሥራት ሀገርሽ ተመለሽ! ቃል ኪዳንሽንም አድሽ! የአዲስ ኪዳን ስደተኞች በኩር ሆይ ተመለሽ! መከራችን ያበቃ ዘንድ፣ እንባችን ይታበስ ዘንድ ተመለሽ!

ጨለማው ይገፈፍ ዘንድ፥ ብርሃናችን ሆይ ተገጭ! መላእክት እንደ ተናገሩት ለኢትዮጵያ ምድር ምሕረትና እውነት ይኖሩ ዘንድ ተመለሽ! ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ! ተመለሽ! እናይሽ ዘንድ ተመለሽ! እንበላት፤ ሰላማችን ሆይ ተመለሽ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ገነት የሕጻናት መርጃ ማዕከል በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን ተቀብሎ ሥራ ጀመረ።

ሕጻናትን በአካልና በአእምሮ ለማሳደግ በ1972 ዓ.ም የተቋቋመው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ገነት የሕጻናት መርጃ ማዕከል ትልልቅ ደረጃ የደረሱ በርካታ ዜጎችን በማፍራት ለቁም ነገር ማብቃቱን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ሕፃናቱን ለመጎብኘት በተገኙበት ዕለት ተናግረዋል።

በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ተቀብሎ በመንከባከብ ግማሽ ምዕተ ዓመት የሚጠጋ አገልግሎት የሰጠው ይህ ማዕከል ከታኅሳስ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የግሪክ ምዕመናን በተለያየ ምክንያት በማቋረጣቸው አገልግሎት መስጠት አቁሞ እንደነበር ብፁዕነታቸው ገልፀዋል።
አካባቢው በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ድጋፍ የሚፈልጉ ሕፃናት በበዙበት ዓመት ማዕከሉ ሥራ በማቋረጡ እረፍት የነሳቸው ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ደጋፊ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማፈላለግ ከመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ዳግም ሥራ አስጀምረውታል።

ሀገረ ስብከቱ ከሀና ፋውንዴሽን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በጦርነቱና በተለያዩ ምክንያቶች ሁለቱንም ወላጆቻቸውን ያጡ ከዞኑ አስር ወረዳዎች የተውጣጡ 20 ሕጻናትን በመቀበል ነው ሥራ የጀመረው።

ብፁዕነታቸው ሕጻናቱ ትምህርታቸውን በግል ት/ቤት መጀመራቸውን አስታውሰዋል።
ሀገረ ስብከቱ ከሀና ፋውንዴሽን ጋር ስምምነት ሲፈራረም ለሠራተኛ ደመወዝ፣ ለምግብ፣  ለአልባሳት፣ ለትምህርትና ሌሎች ወጭዎች የአንድ ልጅ ወርሀዊ በጀት 50 ዶላር ቢሆንም በገበያ ዋጋ ንረት ምክንያት በቂ ባለመሆኑ ሀገረ ስብከቱ ተጨማሪ በጀት መመደቡንም ተናግረዋል።

ማዕከሉ የቦታ ስፋቱ 15 ሽህ ካሬ ሜትር የሆነና ለሕጻናት መንከባከቢያ የተመቸ ግቢ ያለው በመሆኑ ተጨማሪ የሙት ልጆችን ተቀብለን መንከባከብ እንዲንችል ኢትዮጵያውያን በግል እና በቡድን እየሆኑ  ድጋፍ እንዲያደርጉ ብፁዕነታቸው አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።

መረጃው  የሰሜን ወሎ ሀገረስብከት ሚዲያ ነው
2024/10/01 05:03:57
Back to Top
HTML Embed Code: