Telegram Web Link
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

❇️አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) መደራ❇️

=>አቡነ ገሪማ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሮም
ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸው መስፍንያኖስና ሰፍንግያ
እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት
ነበሩ:: ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ፡፡

+እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን ይስሐቅ
ብለው አሳደጉት:: ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ
ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ:: ለ7 ዓመታት ሕዝቡን
በፍትሕ
እያስተዳደረ: መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል::

+አንድ ቀን ግን ከግብፅ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው::
ላኪው አባ_ዸንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ
ንግሥና ምን ያደርግልሃል?
ይልቁኑስ በሰማይ ለዘለዓለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና"
የሚል ነበር::

+ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው
ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ:: ድንገት
ግን ቅዱስ_ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብፅ አባ
ዸንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው::

+እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው
አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮዽያ
መጡ:: ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና
ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው:: ሰውነታቸውን በገድል
ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር::

+አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው
አባ ዸንጠሌዎን አዘኑ:: ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ
የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ" አሉ:: አባ ይስሐቅ ግን
"ሰዎች ብቻ አይደሉም: ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል"
ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (800 ሜትር)
ተጠራርጎ ሸሸ::

+ይሕንን የተመለከቱት አባ ዸንጠሌዎን
"ወልድየ_ይስሐቅ_ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)
አሏቸው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮም
"አቡነ_ገሪማ" ተብለው ቀሩ፡፡

+አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና
ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም
ግሩም ነህ" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል::

+ጻድቁ ወንጌልን: ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ
ተአምራትን ሰርተዋል:-

1.ስንዴ ጠዋት ዘርተውት በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር "በጽባሕ
ይዘርዕ: ወበሠርክ የአርር" እንዲል::
2.ጧት የተከሉት ወይን በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር::
3.አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጸበል ሆኖ ዛሬም አለ::
4.ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች::
5.አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን
አቁመዋታል::

+ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን
ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው::
"ስምሕን የጠራ: መታሰቢያህን ያደረገ: እስከ 12 ትውልድ
እምርልሃለሁ:: አንተ ግን ሞትን አትቀምስም" ብሏቸው
ተሰወረ:: ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ
ብሔረ_ሕያዋን አድርሰዋቸዋል፡፡

✞ አባ ለትጹን የዋህ ✞

=>ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን
በግብጽ የተወለዱ:
¤በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ:
¤ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ:
¤አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ:
¤ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ:
¤በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን
የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው::

+ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው
ንስሃ ይገቡ ነበር:: አንዴ ግን እናቱን 10 ጊዜ በዝሙት
ያረከሰ: ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማሕጸኗ
የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል
ደረሱ::

+አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ:: ኃጢአቱ
ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሃ ሊቀበሉ ጀመሩ: ከንስሃቸው
ጽናት
የተነሳ ሞቱ:: ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ:
አልምረውም" አላቸው::

+ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ:: ለ2ኛ ጊዜ ሞቱ::
አሁንም ቀጠሉ: 3ኛ: 4ኛ: 5ኛ ጊዜም ሞቱ:: በ6ኛው ግን
መፍትሔ መጣ:: ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ:
ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ:: "ፍርዴ አይታጠፍምና
ወደ ገነት
አላስገባትም:: ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል
አልጥላትም:: ስለዚሕም እንዳልተፈጠረች ትሁን" ብሎ
እፍ
አለባት:: ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች::

+ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ:: ከብዙ
ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ::

✞ አባ_ዸላሞን_ፈላሲ ✞

=>ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ
አባ ዸላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር:: ይሕ ቅዱስ
ከአጋንንት
ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል:: ከ60
ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው
አላየም::

+በነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል::
በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል::
እርሱ ግን
በእግዚአብሔር ቸርነት: በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና
በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል::

=>ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት
ይክፈለን:: በምልጃቸውም ይቅር ይበለን::

=>ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
2.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
3.አባ ዸላሞን ፈላሲ
4.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
5.ሰማዕታት እለ አኮራን
6፡ ፯፼ ፹፻ ሰማዕታት ማኅበረ ቅዱስ ተክለሃ ይማኖት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት
2፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
3፡ ቅዱሳን መክሲሞስ ወደማቴዎስ
4፡ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::ቅዱሳኑንም
አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . . ጻድቃን ምድርን
ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::የጻድቅ አፍ ጥበብን
ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::የአምላኩ ሕግ በልቡ
ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://www.tg-me.com/zikirekdusn
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 20-በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ያለ ዕንጨት ያለጭቃና ውኃ በሦስት ድንጋዮች ብቻ በተወደደ ልጇ እጅ የታነፀችበት ዕለት ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤልሳዕ ዐረፈ፡፡ ኤልሳዕ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጠባቂ ነው›› ማለት ነው፡፡ ዐፅሙ የሞውተን ሰው ያስነሣ ታላቅ ነቢይ ሲሆን ኢዮራም፣ አካዝያስ፣ ኢዩና እንዲሁም ዮአስ በተባሉ በአራት ነገሥታት ዘመን ትንቢት የተናገረ ሲሆን የትንቢቱም ዘመን ከ50 ዓመት በላይ ነው፡፡ ታላቁ ነቢይ ኤልያስ በመንገድ ሲሄድ የሳፋጥ ልጅ አልሳዕን በ12 ጥማድ በሬ ሲያርስ አገኘው፡፡ ኤልያስም ሄዶ መጎናጸፊያውን በላዩ ጣለበት፡፡ ኤልሳዕም እርሻውን ትቶ ተከተለው፡፡ ተመልሶም በመምጣት በሬዎቹን አርዶ ሕዝቡን መግቦ በፍጹም ልቡ ኤልያስን ተከትሎ ብዙ ዓመት ሲያገለግለው ኖረ፡፡
ኤልያስ በሚያርግበት ጊዜ ኤልሳዕን ‹‹ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ሳልወጣ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምነኝ›› አለው፡፡ ኤልሳዕም ‹‹በአንተ ያደረ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ሆኖ ይድርብኝ›› አለው፡፡ መምህሩም ‹‹…ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወጣ ብታየኝ ይደርብህ›› አለው፡፡ ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሄዱ በመሀል የእሳት ፈረስና የእሳት ሠረገላ መጥቶ ኤልያስን ነጥቆ ወሰደው፡፡ ኤልሳዕም ይህን በተመለከተ ጊዜ ‹‹የእስራኤል ኃይላቸውና ጽናታቸው አባ አባ…›› ብሎ ጮኸ፡፡ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ አላየውም፡፡ መጠምጠሚያውንም ጣለለትና በራሱ ላይ ወረደች፡፡ በእርሷም የዮርዳኖን ወንዝ ለሁለት ከፍሎ ተሻግሮባታል፡፡ 2ኛ ነገ 2፡1-14፡፡ ኤልሳዕም እንደምኞቱ በመምህሩ በኤልያስ ላይ ያደረሰውን የመንፈስ ቅዱስን ሀብት በእጥፍ ስለተቀበለ ኤልያስ የዮርዳኖስን ወንዝ አንድ ጊዜ ሲከፍል ኤልሳዕ ግን ሁለት ጊዜ ከፈለ፡፡ ኤልያስ አንድ ሞት ሲያስነሣ ኤልሳዕ ግን ሁለት ሞታንን አስነሥቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ወደ ኢያሪኮ ሲገባ የሀገሪቱ ሰዎች ውኃቸውን ሲጠጡት ሴቶቹ እንደሚመክኑ ነገሩት፡፡ እርሱም ‹‹ጨው ጨምራችሁ አዲስ ሸክላ አምጡልኝ›› ብሎ ወደ ምንጩ ውሃ ሄዶ ጨውን ጨመረው፡፡ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ፣ እርሱን ሲጠጡ የሚመክኑትም ሴቶች ወላዶች ሆኑ፡፡ ወደ ቤቴልም በወጣ ጊዜ ከከተማው ሲወጡ ታናናሽ ልጆችን አገኘ፡፡ እነርሱም ‹‹አንተ ራሰ በራ ውጣ›› እያሉ ሲዘባበቱበት የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ቢረግማቸው ወዲያው ሁለት ድቦች ከዱር ወጥተው 42 ልጆችን ገደሉ፡፡
ኤልሳዕ ሌላው የሚታወቅበት ነገር የመበለቲቷን ቤት በበረከት በመሙላቱ ነው፡፡ ሴቲቱ ወደ ኤልሳዕ መጥታ ‹‹የምታውቀው የእግዚአብሔር ሰው የሆነው ባሌ ስለሞተ አሁን ባለዕዳ ሁለቱን ልጆቼን ወስዶ በባርነት ሊገዛቸው›› አለችው፡፡ እርሱም በቤቷ ምን እንዳለ ጠየቃት፡፡ ‹‹ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም›› አለችው፡፡ እርሱም ከጐረቤቶቿ ባዶ ማድጋዎችን ተውሳ እንድታመጣ ነግሯት ማድጋዎቹን ሁሉ በጸሎቱ በተአምራት በዘይት ሞልቶላታል፡፡ እርሷም ዘይቱን ሸጣ ለባለ ዕዳው ከፈለች፡፡ የተረፈውንም ከልጆቿ ጋር ተመገበች፡፡
ነቢዩ ኤልሳዕ መካን ስለነበረችው ስለሱነማዊቷ ሴት ግያዝ ነግሮት ኤልሳዕ ካስጠራት በኋላ ‹‹በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ›› ብለ ከነገራት በኋላ በዓመቱ ፀንሳ ወልዳለች፡፡ ልጁም ካደገ በኋላ ከአባቱ ጋር ወደ አዝመራ ወጥቶ ሳለ ታመመና በእናቱ እቅፍ እያለ ሞተ፡፡ በሞተም ጊዜ በእግዚአብሔር ሰው በነቢዩ አልጋ ላይ አስተኝታው በሩንም ዘግታበት ወጣች፡፡ ሎሌዋን ይዛ አህያዋን ጭና የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ ወዳለበት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣችና የልጇን መሞት ነገረችው፡፡ ኤልሳዕም ሄዶ የሞተውን ልጇን ከሞት አስነሣላትና ‹‹ልጅሽን አንሥተሽ ውሰጂ›› አላት፡፡ እርሷም ለኤልሳዕ ከሰገደችለት በኋላ ልጇን ወሰደች፡፡
ነቢዩ ኤልሳዕ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንን በዮርዳኖስ ውኃ እንዲጠመቅ ካደረገው በኋላ ከለምጹ ፈውሶታል፡፡ ንዕማንም ከለምጹ ከዳነ በኋላ ለኤልሳዕ ወርቅና ብር ልብስም ሊሰጠው ሲል አልሳዕ በሕያው እግዚአብሔር ስም ምሎ አልቀበልም አለው፡፡ ንዕማንም ‹‹እነሆ ከእስራኤል ዘንድ በቀር በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ አወቅሁ›› ብሎ ከመሰከረ በኋላ ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር ወስዶ ወደ ሀገሩ ሶርያ ሄደ፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግያዝ ግን ንዕማንን በመንገድ ተከትሎ ‹‹ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋልና አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ›› በማለት በኤልሳዕ ስም ዋሽቶ ተቀበለ፡፡ ኤልሳዕም ግያዝ በሥውር ያደረገውን ዐውቆ አዘነ፡፡ ወደ እርሱም ተመልሶ በመጣ ጊዜ ‹‹ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም›› አለ፡፡ ኤልሳዕም ‹‹ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ›› ብሎ ያደረገውን እንዳወቀበት ከነገረው በኋላ ‹‹እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ ለዘላለምም በዘርህ ላይ ይጣበቃል›› አለው፡፡ ግያዝም እንደ በረዶ ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ፡፡ ከዚህም ሌላ ኤልሳዕ ውኃ ውስጥ የወደቀውን የብረቱን ምሳር በውኃው ላይ ዕንጨቱን ጥሎ የሰመጠውን ብረት ተንሳፎ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡
የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት በዱር ሰፍሮና ተደብቆ ሳለ የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ ‹‹ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ፡፡ የእስራኤልም ንጉሥ በዚያ ባለመሄድ ራሱን አዳነ፡፡ የሶርያም ንጉሥ ባሪያዎቹን ጠርቶ ‹‹ከእኛ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ ንገሩኝ?›› አላቸው፡፡ ከባሪያዎቹም አንዱ ‹‹ጌታዬ ሆይ በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል›› አለው፡፡ የሶርያ ንጉሥ ኤልሳዕ ያለው በዶታይን እንደሆነ ሲነግሩት የዶታይንን ከተማ ከበባት፡፡ የኤልሳዕ ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ የከበባቸውን ጭፍራና ፈረሶቻቸውን ሲመለከት እጅግ ፈራ፡፡ ኤልሳዕም ‹‹ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ›› አለው፡፡ ‹‹አቤቱ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን እባክህ ግለጥ›› ብሎ በመጸለይ የብላቴናውን ዐይኖች ገለጠ፡፡ ኤልሳዕም በጸሎቱ ሁሉንም ዕውር አደረጋቸው፡፡ ወደ ሰማርያም እየመራቸው ከወሰዳቸው በኋላ ዳግመኛ ያዩ ዘንድ ጸለየና ሁሉም ማየት ቻሉ፡፡ የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ አልሳዕን ‹‹አባቴ ሆይ?›› ባለው ሰዓት እንዳይገድላቸው ይልቁንም አብልቶ አጠጥቶ እንዲልካቸው ነገረው፡፡ እነርሱም በልተው ጠጥተው ሲያበቁ ወደ ጌታቸው ሄዱ፡፡
ከዚያም በኋላ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበና ወጥቶ ሰማርያን ከበባት፡፡ በሰማርያም ታላቅ ራብ ሆኖ ነበር፤ እነሆም፥ የአህያ ራስ በአምሳ ብር፥ የርግብም ኩስ የጎሞር ስምንተኛ የሚሆን በአምስት ብር እስኪሸጥ ድረስ በሀገራቸው የሶርያ ሰዎች ሰፍረው ተቀመጡ፡፡ በዚህም ጊዜ እናት ልጇን ቀቅላ እስክትበላ ድረስ እጅግ አሠቃቂ ታላቅ ርሃብ ሆነ፡፡ ይህም ክፉ የርሃብ ዘመን በነቢዩ ኤልሳዕ ጸሎት በአንዲት ቀን ተለውጦ የጥጋብ ዘመን ሆኗል፡፡ 2ኛ ነገ 6፡8-33፣ 7፡1-20፡፡ ኤልሳዕም በዘመኑ ትንቢትን እየተናገረ እጅግ ታላላቅ ተአምራን እያደረገ እግዚአብሔርንም ሕዝቡንም ሲያገለግል ከኖረ በኋላ ሰኔ 20 ቀን ዐርፏል፡፡ ከሞተም በኋላ ዐፅሙ የሞተን ሰው
አስነሥቷል፡፡ 2ኛ ነገ 13፡21፡፡ ይኸውም የሞአብ ሰዎች አገራቸውን ከበው ሳለ አንድ ሰው ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት አደጋ ጣዮች አዩአቸው፡፡ እነርሱም ደንግጠው ሬሳውን በአልሳዕ መቃብር ላይ ጣሉት፡፡ በዚህም ጊዜ ሬሳው የአልሳዕ ዐፅም በነካው ጊዜ አፈፍ ብሎ ከሞት ተነሥቶ በእግሮቹ ቆሟል፡፡ የነቢዩ የቅዱስ ኤሌሳዕ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + ዳግመኛም በዚኽች ዕለት በኬልቄዶን አውራጃ በቂሣርያ አገር የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ያለ ዕንጨት ያለጭቃና ውኃ በሦስት ድንጋዮች ብቻ በተወደደ ልጇ እጅ የታነፀችበት ዕለት ነው፡፡ የዚኽም ቤ/ክ የቅዳሴ በዓል ነገ በ21 ስለሚከበር ነገ ላይ አብረን እናየዋለን፡፡
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሰኔ 21-ለአዳም ዘር ሁሉ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች ንግሥተ ሰማይ ወምድር ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓሏና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ መታሰቢያ ታላቅ በዓል ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚሀች ዕለት እመቤታችን ለቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ከተገለጠችለትና ሥዕሏን እንዲያሠራላት ከነገረችው በኋላ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አደረገች፡፡
+ አስቀድሞ ከከሃዲውና ከጨካኑ መኮንን ከአርያኖስ ጭፍሮች ውስጥ አንዱ የነበረው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ጢሞቴዎስ ተጋድሎውን በድል ፈጸመ፡፡
+ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በመሸታ ቤት ባረዷት ሴት ላይ ላደረገው ታላቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ፡፡
+ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ያጠመቀውና በኋላም ዲቁናና ቅስና የሾመው አባ ከላድያኖስ ዕረፍቱ ነው፡፡ እርሱም አባ ሜልዮስ ባረፈ ጊዜ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 4ኛ የሆነ ነው፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ጢሞቴዎስ፡- ይህም ቅዱስ ጢሞቴዎስ ከምስር የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ እርሱም አስቀድሞ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራዎች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ ሰው ሁሉ ጣዖትን እንዲያመልክ የሚያዝ የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ትእዛዝ በግዛቱ ሁሉ በተነበበ ጊዜ ይህ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ከሕዝቡ መካከል ተነሥቶ የንጉሡን የአዋጅ ደብዳቤ ቀደደው፡፡ ደብዳቤውን ከቀደደው በኋላ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ‹‹ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም›› ብሎ መሰከረ፡፡
የንጉሡ የዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል የሆነው መኰንን ይህንን የቅዱስ ጢሞቲዎስን ድፍረት በተመለከተ ጊዜ ይዞ ክፉኛ አስደበደበው፡፡ ዳግመኛም ሰውነቱ ሁሉ እስኪደቅ ድረስ እንዲደበድቡት አዘዘ ነገር ግን ጌታችን መልአኩን ልኮ ፈውሰው፡፡ ከሥቃዩም ድኑ ፍጹም ጤነኛ ሆኖ አደረና በቀጣዩ ቀን ወደ መኰንኑ ቀርቦ አሁንም በድጋሚ ‹‹ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም አንተ ከሃዲ እፈር›› ብሎ መሰከረ፡፡ መኰንኑም ይዞ እጅግ አሠቃየው፡፡ ሰውነቱንም በመጋዝ ቆራርጦና ሰነጣጥቆ ሰቀለው፡፡ በብረት ምጣድም አድርጎ ሥጋው እንደ ሰም እስኪቀልጥ ድረስ በእሳት አበሰለው፡፡ ከከተማ ውጪም አውጥቶ ጣለው፡፡ አሁንም ጌታችን ፍጹም ጤነኛ አድርጎ ፈወሰውና ወደ መኰንኑ ተመልሶ ሄዶ ‹‹ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም አንተ ከሃዲ እፈር›› ብሎ ድጋሚ መሰከረ፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው በዙያው የነበሩ በጣም ብዙ አሕዛብ በጌታችን አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡ መኰንኑም ቅዱስ ጢሞቴዎስን ማሠቃየቱ በሰለቸው ጊዜ ሰኔ 21 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና የሰማዕትነት አክሊልን እንዲቀዳጅ አደረገው፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + ++ + ++ + ++ + ++ + +
የእመቤታችን ዓመታዊ በዓልና በዓለም ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ስለመታነጻቸው፡- ይኽም በዓል ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ‹‹ህንጸተ ቤተ ክርስቲያን›› ይባላል፡፡ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በሰኔ 20 ቀን ነው፡፡ አናጺውም እራሱ ባለቤቱ መድኀኔዓለም ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው፡፡
እመቤታችን ካረገች በ4ኛ ዓመት ጳውሎስና ባርናባስ በፊሊጲስዮስ ገብተው አስተምረው ሕዝቡን አሳምነው ካጠመቁ በኋላ ‹‹እንግዲህ ወደ ቤተ ጣዖት አትሂዱ›› አሏቸው፡፡ አሕዛብ የነበሩትና አምነው የተጠመቁትም ‹‹የለመድነውን ከከለከላችሁን መካነ ጸሎት ስጡን›› አሏቸው፡፡ የከበሩ ሐዋርያትም ወደ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልእክት ላኩባቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም ‹‹ያለ ጌታችን ፈቃድ አንዳች ልታደርጉ አይገባምና ጸልዩ እኛም እንጸልያለን›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ሁሉም ሱባኤ ይዘው በጸሎት ተጉ፡፡ ጸሎትና ሱባኤያቸውን ከጨረሱ በኋላ ጌታችን በሞት ያረፉትን አስነሥቶ በሕይወት ያሉትንም ደቀመዛሙርቱን በደመና ጠቅሶ ፊልጵስዩስ ሰበሰባቸው፡፡ ጌታችን በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጌታዬ ለምን ሰበሰብከን?›› ብሎ ጠየቀ፡፡
ጌታችንም ‹‹በእናቴ ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ ፈቃዴ ነውና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሳያችሁ ሥርዓት ላስተምራችሁ ነው›› አለው፡፡ ይህንን ብሎ ወደ ምሥራቅ ወሰዳቸው፡፡ በዚያም ተራርቀው የነበሩ 3 ደንጊያዎች ነበሩ፡፡ ጌታችንም ሦስቱን ድንጋዮችን በተአምራት አቀራርቦ አንሥቶ ጎተታቸው፡፡ ድንጋዮቹም እንደ ሰም ተለጠጡ፣ እንደ ግድግዳም ሆኑ፡፡ ቁመቱን ወርዱን መጥኖ ለሐዋርያቱ ሠጣቸው፡፡ እነርሱም እሳት እንዳየው ሰም ከእጃቸው እየለመለሙ (እየተሳቡ) ቁመቱን 24 ወርዱን 12 ክንድ አድርገው ሠርተውታል፡፡ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ አድርጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ለሐዋርያቱ ‹‹እንግዲህ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ›› ብሏቸው ዐረገ፡፡
ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴን ሦስትነት ወደ አንድ ሆነው አንድ ሕንፃ መታጹ የሥላሴን አንድነት ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ ለኛ ለክርስቲያኖች እጅግ ታላቅ በዓልና ደስታ ነው፡፡ ስለዚች ቤተ ክርስቲያን አባቶች ደማቸውን አፍሰውላታል፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተውላታል፣ አጥንታቸውን ከስክሰውላታል፣ ቆዳቸው ተገፏል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በአውሬ ተበልተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳዋ ውኃ መሠረቷ ደም ነው፡፡ የማትታደስ ነገር ግን ከኃጢአት ከበደል የሚታደሱባት ርትዕት ናት፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ‹‹የክርስቶስ አካሉና ሙላቱ ናት፡፡›› ኤፌ 1፡13፣ ቆላይ 1፡18፣14፡፡ እናም የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጣስና ትምህርቷን መቆነጻጸል የክርስቶስን አካል ማድማት ነው፡፡ ዳግመኛም በማግሥቱ ሰኔ 21 ቀን ጌታችን ድንግል እናቱን እመቤታችንንና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ወረደ፡፡ እመቤታችንን መንበር፣ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቁርቧቸዋልና ፍጹም ደስታም ሆነ፡፡ ዳግመኛም ጴጥሮስን እጁን ጭኖ ፓትርያርክ አድርጎ ሾሞታል፡፡ በዚህም ጊዜ ሰማያውያን መላእክት ምድራውያን ሐዋርያት አንድ ሆነው አመስግነዋል፡፡
ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታችን እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተ ክርስቲያን አንጸዋል፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው የእነ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ፣ የአይሁድ ምኩራብ፣ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ሥርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፡፡ እንኪያስ ‹‹ሐዋርያት የት ነበር ሕዝቡን የሚያጠምቁትና የሚያቆርቡት?›› ከተባለ እንደ ማርቆስ እናት ቤታቸው ለሐዋርያት በሰጡ ‹‹በየአማኞቹ ቤት›› ይከናወን ነበር፡፡
ሰኔ 20 ቀን ህንጸተ ቤተክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን መታነጽ) ታላቅ በዓል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሻሽ የመጣችና ሩቅ ብእሲ የመሠረታት ሳትሆን እራሱ ጌታችን አምላካችን በገዛ ደሙ የመሠረታት ናት፡፡ ሐዋ 20፡28፡፡ በዕለተ ዐርብ በዕፀ መስቀል ላይ ከጌታችን የፈሰሰውን ቅዱስ ደም ቅዱሳን መላእክት በብርሃን ፅዋ ቀድተው በዓለም ሁሉ ረጭተውታል፡፡ ስለሆነም የጌታችን ወርቀ ደም በነጠበባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይሠራባቸዋል፡፡
ዳግመኛም በዚህች ዕለት በቂሣርያው በቅዱስ ባስልዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ፡- ቅዱስ ባስልዮስ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ከሠራ በኋላ በውስጧ የሚያኖረውን የእመቤታችንን ሥዕል ሊያሠራ መሳያ ሠሌዳ ፈለገ፡፡ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ቤት ጥሩ ሠሌዳ እንዳለ ነገሩትና ሄዶ ባለጸጋውን ሠሌዳውን እንዲሰጠው ለመነው፡፡ ባለጸጋውም ‹‹የልጆቼ ነው አልሰጥም›› አለው፡፡ በትዕቢትም ሆኖ በታነጸቸው ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብን ነገር ተናገረ፡፡ ወዲያውም ወድቆ ክፉ አሟሟት ሞተና ልጆቹ ፈርተው ሠሌዳውን አምጥተው ለባስልዮስ ሰጡት፡፡ እርሱም ያንን ሠሌዳ የእመቤታችንን ሥዕል አሳምሮ ይስልበት ዘንድ ለሰዓሊ ወስዶ ሰጠው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን በራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጠችለትና ከአመፀኛ ሰው የተገኘ ነውና በዚያ ሰው ሠሌዳ ሥዕሏን እንዳያስል ከለከለችው፡፡
የእመቤታችን ሥዕሏ የተሳለበትን ሠሌዳም የት እንደሚገኝ ነገረችውና ባስልዮስ ሄዶ በታላቅ ክብር አምጥቶ በቤተ ክርስቲያኑ አስቀመጠው፡፡ ከሥዕሏም ሥር ድውያንን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት መፍሰስ ጀመረ፡፡ በዚህም ብዙዎች ድንቅ የሆነ ፈውስን አገኙ፡፡ የከበረች ሥዕሏ ከተቀመጠበት ምሰሶ ሥር ጸበል ፈለቀና በዚኽም ብዙዎች ተፈወሱ፡፡ ይህም የተፈጸመው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት ዕለት በሰኔ 21 ቀን ነው፡፡ የብርሃን እናቱ የእመቤታችን ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡
#ሰኔ_23

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሰኔ ሃያ ሦስት በዚች ቀን በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠ የዳዊት ልጅ #የጠቢቡ_ሰሎሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ በክብር ባለቤት ክርስቶስ የታመነ #አባ_ኖብ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢየ_ጽድቅ_ቅዱስ_ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)

ሰኔ ሃያ ሦስት በዚህች ቀን በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

የዚህ የሰሎሞንም የእናቱ ስም ቤርሳቤህ ነው ዳዊትም ሕግ ተላልፎ ከእሷ ጋራ ስለ መበደሉ ባሏንም ስለ ማስገደሉ ጌታ በገሠጸው ጊዜ ንስሓ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ ጌታም ንጹሕ ስለሆነ ንስሓው ይቅር አለው። ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ እርሷን አገባትና ሰሎሞንን ወለደችው ንጉሥ ዳዊትም ከእርሱ በኋላ ልጅዋ ሰሎሞን እንዲነግሥና በዙፋኑ ላይ እንዲቀመጥ ቃል ገባላት።

እንዲህም ሆነ ሰሎሞን ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ አዶንያስ እነግሣለሁ ብሎ ተነሣ ምክሩም ሁሉ ከሶርህያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ አብያታር ጋር ሆነ። እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ረዱት። አዶንያስም በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ባለ በኤልቲ ዘዘኤልቲ ላይ ፍየሎችን በጎችንና ላሞችን አርዶ የንጉሥ አሽከሮች የሆኑ የይሁዳ አርበኞችን ሁሉና የንጉሡን ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ ጠራ።

ከዚህም በኋላ አዶንያስ ይህን እንዳደረገ ለቤርሳቤህ በነገሩዋት ጊዜ ወደ ንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ገብታ ለንጉሡ ሰገደች ንጉሥ ዳዊትም ምን ሆንሽ አላት። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለህ ለእኔ ለባርያህ በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ስም አንተ ማልክልኝ እነሆ ዛሬ አዶንያስ ነገሠ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ አንተ ግን አላወቅህም አለችው።

ከንጉሥም ጋራ ገና ስትነጋገር ነቢዩ ናታን መጣ ለንጉሡም ናታን መጣ ብለው ነገሩት። ወደ ንጉሡም ገባ በምድር ላይም በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ነቢዩ ናታንም ከእኔ ቀጥሎ አዶንያስ ይንገሥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጥ ያልክ አንተ ነህን ዛሬ ወርዶ በጎችንና ብዙ ፍየሎችን አርዶ የሠራዊቱ አለቆችንና የንጉሥ አሽክሮችን ሁሉ ካህኑ አብያታርንም ጠርቷልና በፊቱም ይበላሉ ይጠጣሉ አንዶንያስ ሽህ ዓመት ያንግሥህ ይሉታል አለው።

ዳዊትም መልሶ ቤርሳቤህን ጥርዋት አለና ጠሩዋት ገብታም በንጉሡ ፊት ቆመች። በእግዚአብሔር ፊት እንደማልኩልሽ አሁንም በዚች ቀን እንደዚሁ እንዳደርግ ሰውነቴን ከመከራዬ ሁሉ ያዳናት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕያው ነው ብሎ ማለ። ቤርሳቤህም አንገቷን ደፍታ በግምባርዋ በመሬት ወድቃ ለንጉሡ ሰገደች ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ኑር አለች።

ንጉሥ ዳዊትም የዮዳሄ ልጅ ብንያስንና ካህኑ ሳዶቅን ነቢዩ ናታንንም ግራዝማቹንና ቀኝ አዝማቹን ጥሩልኝ አለ። ንጉሡም ከእናንተ ጋራ የጌታችሁ አሽከሮችን ይዛችሁ ልጄ ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጣችሁ ወደ ግዮን አውርዱት። በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅ ቀብታችሁ በእስራኤል ላይ አንግሡት አላቸው።

ቀንደ መለከት ንፉ ሰሎሞን ሺህ ዓመት ያንግሥህ በሉ። ተከትላችሁትም ውጡ ገብቶም በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ እርሱም ስለ እኔ ፈንታ ይንገሥ በሁለቱ ነገድና በዐሥሩ ነገድ ይነግሥ ዘንድ እኔ አዝዣለሁ። ካህኑ ሳዶቅም ከድንኳኑ ቀርነ ቅብዑን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው ቀንደ መለከትንም ነፉ ሕዝቡም ሁሉ ሰሎሞን ሺህ ዓመት ያንግሥህ አሉ ሕዝቡም ሁሉ ተከትለውት ወጡ ከበሮም መቱ ታላቅ ደስታም አደረጉ ከድምፃቸውም የተነሣ ምድሪቱ ተናወጸች።

ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋን ተቀመጠ። የንጉሡም አሽከሮች ጌታቸው ንጉሡ ዳዊትን ሊአመሰግኑ ገቡ። እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርገው ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ የበለጠ ያድርገው አሉት። ንጉሡም በዐልጋው ሆኖ ሰገደ። እንዲህም አለ ዐይኖቼ ሲያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅን ለኔ ለባርያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን አለ። ዳዊትም የሚሞትበት ወራት በደረሰ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው። እኔ ሰው ሁሉ በሚሔድበት በሞት ጐዳና እሔዳለሁ አንተ ግን ጽና ብልህ ሰውም ሁን።

በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ትእዛዙን ጠብቅ እኔ እንዳዘዝሁህ እንዴት እንደምታደርግ ታውቅ ዘንድ በሙሴ ሕግ የተጻፈውን ትእዛዙንና ሕጉን ፍርዱንም ጠብቅ ልጆችህ ሕጌን ቢጠብቁ በፊቴም በፍጹም ልቡናቸው በፍጹም ሰውነታቸው በዕውነት ጸንተው ቢኖሩ ከእስራኤል ዙፋን ላይ ሰው አይጠፋብህም ብሎ እግዚአብሔር ለእኔ የነገረኝ ቃሉን ያጸና ዘንድ ጠብቅ ብሎ አዘዘው።

ዳግመኛም በኢዮአብና በሳሚ ወልደ ጌራ ላይ በቀል እንዲአደርግ አዘዘው እነርሱ እጅግ የከፉና ብዙ ክፋት የሠሩ ነበሩና። ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ሰሎሞን በዚያ መሥዋዕትን ይሠዋ ዘንድ ተነሥቶ ወደ ገባዖን ሔደ ገባዖን ፈጽማ ትሰፋ ነበርና ሰሎሞንም በገባዖን በዚያው መሠዊያ ውስጥ ሽህ መሥዋዕትን ሠዋ። እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት ለአንተ እሰጥህ ዘንድ ልብህ ያሰበውን ልመናን ለምን አለው።

ሰሎሞንም በቅንነትና በእውነት በንጹሕ ልቡናም ከአንተ ጋራ በፊትህ ጸንቶ እንደኖረ ከአባቴ ከዳዊት ጋራ ታላቅ ቸርነትን አድርገሃል በዚችም ቀን ልጁን በዙፋኑ ላይ ታስቀምጠው ዘንድ ይህን ታላቁን ቸርነት አጽንተህለታል አለው። አሁንም አቤቱ አንተ ፈጣሪዬ ስለ አባቴ ስለ ዳዊት ፈንታ እኔን ባሪያህን አነገሥኸኝ እኔም መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ።

እኔ ባሪያህ ግን የማይቈጠር ብዙ ሕዝብ በሆነ በመረጥከው ወገንህ መካከል አለሁ። ለዚህ ለብዙ ወገንህ መፍረድ የሚችል የለምና ሰምቶ ለወገኖችህ በእውነት ፍርድን ይፈርድ ዘንድ ከክፉ ነገርም ለይቶ በጎውን ነገር ያውቅ ዘንድ ለባሪያህ ዕውቀትን ስጠው። ሰሎሞን ይህንን ነገር ለምኖታልና ይህ ነገር እግዚአብሔርን በፊቱ ደስ አሰኘው። እግዚአብሔርም ይህንን ነገር ከእኔ ለምነሃልና ለአንተም ብዙ ዘመንንና ባለጸግነትን አልለመንህምና ጠላቶችህንም አጥፋልኝ ብለህ አልለመንህምና ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እነሆ እንዳልህ አደረግሁልህ።

እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስተዋይ ልቡናን ሰጠሁህ። ሰው በመንግሥቱ እንዳንተ እንዳልሆነ አድርጌ ያልለመንኸኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።

ሰሎሞንም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንደ ሆነ ዐወቀ ተነሥቶም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ በጽዮንም በእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ አንጻር ባለ በመሠዊያው ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀረበ ለሰዎቹና ለሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ።

በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ አንዲቱም ሴት ጌታዬ ስማኝ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን በአንድ ቦታም ወለድን እኔ በወለድሁ በሦስተኛው ቀን ይህች ሴት ወለደች በአንድነትም እንኖራለን በዚያም ቤት ከሁለታችን በቀር ከኛ ጋራ ማንም አልነበረም። በላዩ ላይ ተጭናዋለችና የዚያች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ።

በሌሊት እኩሌታም ተነሥታ ተኝቼ ሳለሁ ልጄን ከአጠገቤ ወስዳ በብብቷ አስተኛችው። የሞተውን ልጅዋንም በአጠገቤ አስተኛችው። ልጄን አጠባ ዘንድ በጧት በነቃሁ ጊዜም ያንን የሞተ ልጅ አገኘሁ በነጋም ጊዜ አየሁት እነሆ የወለድሁት ልጄ አይደለም አለች።

ያቺ ሁለተኛዋ ሴትም አይደለም ይህ ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው እንጂ ያንቺ ልጅ አይደለም ያንቺስ የሞተው ነው አለች። በንጉሡም ፊት እንዲህ ተባባሉ።
ንጉሡም ሰይፍን አምጡ ደኅነኛውንም ልጅ ከሁለት ቆርጣችሁ እኵሌታውን ለዚች እኵሌታውን ለዚያች ስጡ አለ። ስለ ልጅዋ ማሕፀኗ ታውኳልና ልጅዋ ደኅና የሆነ ያቺ ሴት መልሳ ንጉሡን ጌታዬ አይደለም መግደልስ አትግደሉት ደኅነኛውን ልጅ ለሷ ስጧት አለችው ያቺ ሴት ግን አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእሷም አይሁን አለች።

ንጉሡም መግደልስ አትግደሉት እሱን ለእሷ ስጧት ላለችው ለዚች ሴት ደኅነኛውን ሕፃን ስጧት እርስዋ እናቱ ናትና አለ። እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ የፈረደውን ይህን ፍርድ ሰምተው ቅን ፍርድን ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና በንጉሡ ፊት ፈሩ።

ከዚህም በኋላ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት ዘመን በሆነ ጊዜ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሊያንፅ ጀመረ።

በዐሥራ አንደኛውም ዘመነ መንግሥቱ ወሩ ባዕድ በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱንና ሥርዓቱን ሁሉ ፈጸመ በሰባት ዓመትም ውስጥ ሠራው የራሱንም ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠርቶ ጨረሰ። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት በሃያ ዘመን ሠርቶ በጨረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያመጣት ዘንድ ያን ጊዜ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች የአባቶቻቸውንም ቤት አለቆች ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው።

የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን በሰባተኛው ወር በጥቅምት ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ ካህናቱም ታቦትዋንና የምስክሩን ድንኳን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ያለ ንዋየ ቅድሳቱንም ሁሉ ተሸከሙ። ንጉሡና እስራኤል ሁሉ በታቦትዋ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸው በጎችና ላሞችን ይሠዉ ነበር። ካህናቱም ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ቦታዋ አገቧት።

ኪሩቤል በታቦትዋ ቦታ ላይ ክንፋቸውን ጋርደዋልና ኪሩቤልም በስተላይ በኩል በቅድስተ ቅዱሳን ላይ ታቦትዋን ጋርደዋት ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳንም ጋራ የተያያዙ ነበሩ። ቅዱሳን ኪሩቤል ከፍ ብለው ከቅድስተ ቅዱሳኑ አንጻር ላይ ሁነው ያያሉ በውጭ ግን አይታይም ነበር። ከግብጽ አገር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ጋራ ቃል ኪዳን ከገባባቸው ሙሴም በዚያ በኮሬብ ከአኖራቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ሌላ አልነበረም።

ከዚህ በኋላ ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ሁሉ ብርሃን መላው። የእግዚአብሔር ብርሃን በማደሪያው ቤተ መቅደስ መልቷልና ከብርሃኑ መገለጥ የተነሣ ካህናቱ ሥራቸውን መሥራትና ከፊቱ መቆም ተሳናቸው።

ያን ጊዜ ሰሎሞን እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁ ብሏል። እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደስን በእውነት ሠራሁልህ አለ። ንጉሡም ፊቱን መልሶ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቃቸው ወደ እግዚአብሔርም ረዥም ጸሎትን ጸለየ። ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ልመና ወደ እግዚአብሔር ለምኖ በጨረሰ ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ከሰገደበት እጆቹንም ከዘረጋበት ከመሠዊያው ፊት ተነሣ።

ቆሞም የእስራኤልን ማኅበር እንደተናገረው ሁሉ ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጣቸው እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ብሎ በታላቅ ቃል መረቃቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሡና የእስራኤል ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕትን ሠዉ።

ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስለ ሰላም መሥዋዕት የሠዋቸው ሃያ ሁለት ሽህ ላሞችና አንድ መቶ ሃያ ሽህ በጎች ናቸው ንጉሡ ሰሎሞንና የእስራኤል ልጆች ሁሉ ያንጊዜ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ለቤተ መቅደስ ቅዳሴ ቤት አደረጉ።

ቀድሞ በገባዖን እንደታየው ዳግመኛ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ታየው በፊቴ የለመንኸኝ ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ። እንደ ልመናህም ሁሉ አደረግሁልህ ስሜ በዚያ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ አከበርሁት ልቡናዬም ዐይኖቼም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ አለው። ሰሎሞንም አርባ ዘመን ነገሠ ከመንገሡም በፊት ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ መላ ዕድሜውም ሃምሳ ሁለት ዓመት ነበር በሰላም አረፈ።

ይህም ጥበብ የተሰጠው ንጉሥ ሰሎሞን ጥቅም ያላቸው ብዙዎች መጻሕፍትን ደርሶአል። እሊህም ትንቢትና ትምህርት ያለባቸው ምሳሌዎችና መኃልዮች ናቸው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ኖብ

በዚህችም ቀን ደግሞ በክብር ባለቤት ክርስቶስ የታመነ አባ ኖብ አረፈ። ይህም ቅዱስ መነኰስ በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ የሚጋደል ጽሙድ ነበር።

ዲዮቅልጥያኖስም ብዙዎች ሰማዕታትን ሊአሠቃይና ደማቸውን ሊያፈስስ በጀመረ ጊዜ በአንዲት ቀን ሰማንያ ሰማዕታትን አቅርቦ ደማቸውን አፈሰሰ። በዚያን ጊዜ አባ ኖብን አስታወሱት የእንዴናው ገዥ ወደሆነው ወደ አርያኖስ አቀረቡት። እርሱም ለአማልክት ዕጠን ሠዋ ይህንንም የምንኵስና ልብስ ከላይህ አውጥተህ ጣል አለው።

አባ ኖብም ይህ ሥራ ከቶ ከእኔ ዘንድ አይደረግም የክብር ባለቤት ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስንም አልተውም የረከሱ ጣዖታትንም አላመልክም አለ። መኰንኑም በየራሱ በሆነ ሥቃይ እጅግ አሠቃየው ያም አባ ኖብ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ኃይል ታግሦ ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ወደ አምስቱ አህጉር ሰደደው በዚያም በጉድጓድ ውስጥ ጣሉት በውስጡም ጌታችን ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስን አጥፍቶ ደግ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስን እስከሾመው ድረስ ሰባት ዓመት ኖረ።

ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ የታሠሩትን ሁሉ ፈትተው ወደርሱ እንዲአቀርቧቸውና ከእርሳቸው እንዲባረክ ወደ አገሮች ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። ለመልእክተኞችም እንዲህ አላቸው ሁሉንም ወደ እኔ ማድረስ ካልተቻላችሁ እጆቻቸውን በራሴ ላይ ጭነው ይባርኩኝ ዘንድ ክብር ያላቸውን ታላላቆችንና መምህራኑን አምጡአቸው።

ከእነርሱም ውስጥ የታወቁ አህናህ ከተባለ አገር አባ ዘካርያስ ከፍዩም መክሲሞስ ከሀገረ ድኂን አጋብዮስ ከሀገረ በላኦስ አባ ኖብ ናቸው የንጉሥ መልእክተኞችም በየአገሮች ሁሉ እየዞሩ የታሠሩ ቅዱሳንን ከእሥር ያወጡአቸው ነበር እነርሱም ደስ ይላቸው ነበር የተመሰገነ እግዚአብሔርንም ያመሰግኑት ነበር ይዘምሩለትም ነበር።

የንጉሥ መልእክተኛም አባ ኖብን ከአምስቱ አገሮች ፈልጎ የአገሩ አንጻር ወደ ሆነች ወደ ሀገረ በሰላ ወሰደው። በዚያም የብረት ልብስ ለብሶ ተቀምጦ ነበር የንጉሡ መልእከተኛም አገኘውና ከእርሱ ጋራ ወሰደው ወደ እንዴናውም እስከ ደረሱ በመርከብ ተሳፈሩ ክርስቲያኖችም ተሰበሰቡ ከውስጣቸውም አራት ኤጲስቆጶሳት ነበሩ አባ ኖብንም ያለ ውዴታው ቅስና ሾሙትና የቊርባን ቅዳሴን ቀደሰ።

በቅዳሴውም ፍጻሜ ቅድሳት ለቅዱሳን ብሎ ጮኸ ይህም ማለት ንጹሕና ቅዱስ የሆነ ከሥጋው ከደሙ ይቀበል ማለት ነው በዚያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ ንስሐ የገቡትን ኃጢአታቸውን ይቅር ሲላቸው አየው ሥጋውንና ደሙንም ከአቀበላቸው በኋላ ወደ ንጉሡ ለመሔድ ተዘጋጁ ቍጥራቸውም ሰባ ሁለት ነበር ሠላሳ ሰባት ሠረገላም አዘጋጅተውላቸው እየአንዳንዳቸው በሠረገላው ተቀመጡ።

በአለፉም ጊዜ የደናግል ገዳማት ካሉበት ደረሱ ደናግሉም ወጥተው ተቀበሏቸው ቍጥራቸው ሰባት መቶ ነበር ከእነርሱ ጋራም እስከሚሰበሰቡ በቅዱሳን ፊት ይዘምሩ ነበር።

ወደ ንጉሡ ከተማም በደረሱ ጊዜ ወደ ንጉሡ ከመግባታቸው በፊት በውኃ ያጥቧቸውና አዳዲስ ልብሶችን ያለብሷቸው ጀመሩ እንዲሁም ለሁሉ አደረጉ ቅዱስ አባ ኖብ ግን አልታጠበም ልብሱንም አልለወጠም ።
ወደ ንጉሡም በገቡ ጊዜ ከእነርሱ ቡራኬ ተቀበለ ቁስላቸውንም ሳመ እጅግም አከበራቸው ብዙ ገንዘብም ሰጣቸው እነርሱ ግን ለቤተ ክርስቲያን ከሚሆን ንዋየ ቅድሳት በቀር ምንም ምን አልተቀበሉም ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥቶ ወደየሀገራቸው በሰላም አሰናበታቸው። አባ ኖብም ወደ ቦታው ተመልሶ አረፈና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሰኔ_23)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ሰኔ_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ኤፌሶን 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤
² በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤
³ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።
⁴ በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤
⁵ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
⁶ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።
⁷ ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።
⁸ ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።
⁹ ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው?
¹⁰ ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው።
¹¹ እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤
¹²-¹³ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።
¹⁴ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥
¹⁵ ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤
¹⁶ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
² እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።
³ ትእዛዛቱንም ብንጠብቅ በዚህ እንዳወቅነው እናውቃለን።
⁴ አውቄዋለሁ የሚል ትእዛዛቱንም የማይጠብቅ ውሸተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
⁵ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤
⁶ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል።
⁷ ወንድሞች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረቻችሁ አሮጌ ትእዛዝ እንጂ የምጽፍላችሁ አዲስ ትእዛዝ አይደለችም፤ አሮጌይቱ ትእዛዝ የሰማችኋት ቃል ናት።
⁸ ዳግመኛ አዲስ ትእዛዝን እጽፍላችኋለሁ፥ ይህም ነገር በእርሱ በእናንተም እውነተኛ ነው፤ ጨለማው ያልፋልና እውነተኛውም ብርሃን አሁን ይበራል።
⁹ በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ።
¹⁰ ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤
¹¹ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና።
¹² ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹³ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፥ አብን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ።
¹⁴ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።
¹⁷ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥
² ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው።
³ እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።
⁴ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።
⁵ ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤
⁶ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ።
⁷ ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?
⁸ እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?
⁹ የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥
¹⁰ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥
¹¹ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።
¹² ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው፦ እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ።
¹³ ሌሎች ግን እያፌዙባቸው፦ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሰኔ_23_ቀን_የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዐርገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ። ወወሀብከ ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው። እስመ ይክሕዱ ከመ ይኅድሩ"። መዝ 67፥18-19።
"ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፥ ደግሞም ለዓመፀኞች በዚያ ያድሩ ዘንድ።
እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው የመድኃኒታችን አምላክ ይረዳናል"። መዝ. 67፥18-19።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ሰኔ_23_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።
² በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤
³ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።
⁴ ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።
⁵ ቶማስም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው።
⁶ ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።
⁷ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።
⁸ ፊልጶስ- ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።
⁹ ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ?
¹⁰ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።
¹¹ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።
¹² እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥
¹³ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።
¹⁴ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤
¹⁷ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።
¹⁸ ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።
¹⁹ ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ።
²⁰ እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።
²¹ ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም ዕለት ሰንበትና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/07/01 03:04:00
Back to Top
HTML Embed Code: