Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
³ በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።
⁴ ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤
⁵-⁶ እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር፦ ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።
⁷ ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
⁸ ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
⁹ ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን?
¹⁰ እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።
¹¹ ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።
² ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
³ እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን።
⁴ እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ።
⁵ እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።
⁶ አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።
⁷ የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤
⁸ ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው።
⁹ በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤
¹⁰ ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።
¹¹ ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?
¹² ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
² እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ።
³ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው።
⁴ እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ፦ ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው፦ ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ።
⁵ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ።
⁶ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።
⁷ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ፥ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፥
⁸ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ። በቀለ ደሞሙ፡ለአግብርቲከ፡ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ 78፥10-11።
"አሕዛብ፦ አምላካቸው ወዴት ነው? እንዳይሉ፥ የፈሰሰውን የባሪያዎችህን ደም በቀል በዓይኖቻችን ፊት አሕዛብ ይወቁ።
የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ፤ እንደ ክንድህም ታላቅነት ሊገደሉ የተፈረደባቸውን አድን"። መዝ 78፥10-11።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤
¹³ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል።
¹⁴ ስለዚህ እንዴት እንድትመልሱ አስቀድማችሁ እንዳታስቡ በልባችሁ አኑሩት፤
¹⁵ ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና።
¹⁶ ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤
¹⁷ በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
¹⁸ ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤
¹⁹ በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታገኛላችሁ።
²⁰ ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ፋሲለደስ የዕረፍት በዓል፣ የቅድስት ታዖድራ፣ የቅዱስ ቀርኔሌዎስ፣ የቅድስት በነፍዘዝ ሰማዕትና የቅዱሳን ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሁለት መላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ጉባኤ_ኤፌሶን የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላእክት

መስከረም ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና #እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ #እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ለንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገለት ተአምር፡-

ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ዳዊት በኋላ በእስራኤል እንደ ሕዝቅያስ ያለ ሌላ ጻድቅ ንጉሥ አልተነሣም፡፡ ከሕዝቅያስ በኋላ የተነሡት ሁሉም ጣዖትን አምልከዋል፣ ለጣዖታቱም የሚሆን መሠዊያ ሠርተዋል፡፡ ንጉሡ ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ግን ጣዖታትን ሰባብሯቸዋል፣ የእስራኤል ልጆች ያመልኩት የነበረውን የነሐስ እባብ ቆራርጦታል፡፡ #እግዚአብሔርንም በማመኑ መንግሥቱ እጅግ ሰምሮለታል፡፡ #እግዚአብሔርም ያሳጣው በጎ ነገርም የለም፡፡

ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዘመን የፋርሱ ነጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት፡፡ ይህም ሰናክሬም በወቅቱ እንደ እርሱ ያለ ኃይለኛ የለም ነበርና ሁሉም የምድር ነገሥታት ይፈሩትና ይገዙለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም ግርማና የጦሩ ብዛት የተነሣ ፈርቶ ኢየሩሳሌምን እንዳያጠፋት ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ቢልክለትም ሰናክሬም ግን እጅ መንሻውን አልቀበልም ብሎ ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ዘንድ ተነሣ፡፡ ለሕዝቅያስም ‹‹አምላካችሁ #እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያደናችሁ ከቶ አይችልም›› የሚል የስድብን ቃል ላከለት፡፡

ሁለተኛም በልዑል #እግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ጽፎ ደብዳቤ ላከለት፡፡ ሕዝቅያስም ይህን ሲሰማ ወደ #እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ፡፡ ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ የሰናክሬምን ድፍረትና በኢየሩሳሌምና በሕዝቧ ላይ ሊያደርስ ያሰበውንም ጥፋት ወደ #እግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ቀጥሎም ሕዝቅያስ ሰናክሬም የተናገረውን ይነግሩት ዘንድ ስለ ሕዝቡም እንዲጸልይ ለነቢዩ ኢሳይያስ መልእክት ላከበት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ #እግዚአብሔር አመለከተ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ስለ ንጉሡ ለነቢዩ መልእክትን አመጣለት፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም የመጣለትን መልስ እንዲህ ብሎ ለሕዝቅያስ ላከለት፡- ‹‹ልብህን አጽና፣ አትፍራ፡፡ በዓለሙ ሁሉ እንደ እርሱ ያለ ያልተሰማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ #እግዚአብሔር ይሠራል›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከ #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) የፋርስ ሠራዊቶችን በአንድ ሌሊት ገደላቸው፡፡ 2ኛ ነገ 17፣19፡፡ የለኪሶ ሰዎችም ሲነጋ በተነሡ ጊዜ ምድሪቱን በእሬሳ ተሞልታ ስላገኟት በድንጋጤና በፍርሃት ከንጉሣ ጋር ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ፡፡

ንጉሡ ሰናክሬምም ወደ አምላኩ ወደ ጣዖቱ ቤት ገብቶ ሲጸልይ የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉትና ወደ አራራት ኩበለሉ፡፡2ኛ ነገ ምዕራፍ 19፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ያዳነውን #እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡

ከዚህም በኋላ ሕዝቅያስ ታሞ ለሞት በደረሰ ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹ #እግዚአብሔር ‹ትሞታለህ እንጂ አትድንም› ብሎሃል›› አለው፡፡ ነገር ግን ሕዝቅያስ አሁንም ልብሱንም ቀዶ ማቅ በመልበስ ጸሎቱን ወደ #እግዚአብሔር አቀረበ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ቅዱስ ሚካኤል #እግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ መጥቶ ነቢዩ ኢሳይያስን ወደ ንጉሡ ሕዝቅያስ ሄዶ በዕድሜው ላይ 15 ዓመት እንደተጨመረለት እንዲነግረው ያዘዘው፡፡

መልአኩ እንዳዘዘው ነቢዩ ኢሳይያስ ንጉሥ ሕዝቅያስን " #እግዚአብሔር የአባትህ የዳዊት አምላክ ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፣ እነሆ እኔ አድንሃለሁ፡፡ በዘመኖችህም 15 ዓመት ጨምሬልሃለሁ፡፡ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ፡፡ ይህችን አገር ስለ እኔና ስለ ባለሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ›› ብሎሃል ብሎ የተላከውን ነገረው፡፡ ከዚህም በኃላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የ #እግዚአብሔር ኃይል ስላደረበት የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈርተውት እየተገዙለት እጅ መንሻን ያገቡለት ጀመር፡፡ ንጉሡም ዕድሜው ከተጨመረለት በኃላ ሚስት አግብቶ ምናሴን እስኪወልድ ድረስ ቆየ፡፡ በመንበረ መንግሥቱም 29 ዓመት ነግሦ ከኖረ በኋላ #እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ጉባኤ_ኤፌሶን

በዚችም ቀን ደግሞ በኤፌሶን ከተማ የቅዱሳን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው።

ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጥሮስ ነው። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና እመቤታችን #ድንግል_ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የ #እግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት የተረገመ የከ*ሐዲ ንስጥሮስ የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት።

ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት #ድንግል_ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ። እንዲህ የሚል #እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል #እግዚአብሔር ልጅም ይባላል ።

ዳግመኛም እነሆ #ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል።

ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ #እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን።

ከ*ሀዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግ*መው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደ*ዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ።

እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የ #እግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው።

ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አርቅቀው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ #እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
በተጨማሪ በዚች ሰማዕት #ቅዱስ_አፍላሆስ መታሰቢያውና የሥጋው ፍልሰት ነው። የእስክድርያ አገር የሆኑ ባልንጀሮቹ ሰማዕታትም መታሰቢያቸው ነው። #የሰማዕታት_ቅዱሳን_ሉዩራስና_ባሌኒኮስ#ቅዱስ_ኢያቄምና_ቅድስት_ሐናም መታሰቢያቸው ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_12 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤
² በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም፦ አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል።
³ ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤
⁴ ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን።
⁵ እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ።
⁶ ይህንም እላለሁ፦ በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።
⁷ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።
⁸-⁹ በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።
¹⁰ ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤
¹¹ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ።
¹² የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤
¹³ በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥
¹⁴ ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል።
¹⁵ ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ።
² ሀብታችሁ ተበላሽቶአል፥ ልብሳችሁም በብል ተበልቶአል።
³ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጎአል፥ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል። ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል።
⁴ እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል።
⁵ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚያወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል።
⁶ ጻድቁን ኰንናችሁታል ገድላችሁትማል፤ እናንተን አይቃወምም።
⁷ እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፥ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል።
⁸ እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።
⁹ ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²¹ ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ፦ ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ።
²² ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ።
²³ በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ።
²⁴ ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤
²⁵ እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ።
²⁶ ይህም ጳውሎስ፦ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል።
²⁷ ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል።
²⁸ ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ።
²⁹ ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ።
³⁰ ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት።
³¹ ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት።
³² ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና።
³³ አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ።
³⁴ አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።
³⁵ የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው?
³⁶ ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል።
³⁷ የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና።
³⁸ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ።
³⁹ ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል።
⁴⁰ ዛሬ ስለ ተደረገው፦ ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ምድርኒ ትሁብ ፍሬሃ። ወይባርከነ እግዚአብሔር አምላክነ ወይባርከነ እግዚአብሔር"። መዝ.66÷6-7
"ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል። እግዚአብሔር ይባርከናል፥ የምድርም ዳርቻ ሁሉ ይፈሩታል"።
መዝ.66÷6-7
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_12_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁴ አላቸውም፦ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል።
²⁵ ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
²⁶ እርሱም አለ፦ በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥
²⁷ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል።
²⁸ ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች።
²⁹ ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሶአልና ወዲያው ማጭድ ይልካል።
³⁰ እርሱም አለ፦ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን?
³¹ እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፥ እርስዋም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፥
³² የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታደርጋለች።
³³ መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፥
³⁴ ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀ መዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።
³⁵ በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፦ ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው።
³⁶ ሕዝቡንም ትተው በታንኳ እንዲያው ወሰዱት፥ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ።
³⁷ ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውኃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር።
³⁸ እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ አንቅተውም፦ መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን? አሉት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ወይም የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል ወራዊ በዓልና የኤፌሶን ጉባኤ የተሰበሰቡ የ200 ኤጲስቆጶሳት በዓልና ዕለተ ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_13

#ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሣርያ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን ታላቅና ቅዱስ የሆነ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ባስልዮስ ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው አንድ ጐልማሳ አገልጋይ የጌታውን ልጅ ስለወደዳት ልቡ እርሷን ወዶ እንደ እሳት እስከ ነደደ ድረስ እርሷንም ከመውደዱ ብዛት የተነሣ ወደ አንድ ከሀዲ ሥራየኛ ሔደ። ሥራየኛውም የክህደት ደብዳቤ ጽፎ ሰጠው። ወደ አረሚ መቃብርም ሒዶ በመንፈቀ ሌሊት ደብዳቤዋን ይዞ ወደላይ እጁን አንሥቶ በዚያ እንዲቆም አዘዘው።

ይህም አገልጋይ ይህን ነገር ተቀብሎ ያ መሠርይ እንዳዘዘው አደረገ። በዚያንም ጊዜ ከሰይጣናት አንዱ መጥቶ ወደ አለቃቸው ወስዶ አደረሰው ያቺንም የክህደት ደብዳቤ ከእጁ ወሰደ። እንዲህም ብሎ ጠየቀው "ንጉሥህ #ክርስቶስን ትክደ*ዋለህን? ፈቃድህን ከፈጸምኩልህ በኋላ ወደ እርሱ አትመለስምን?" ይህም ጐስቋላ ባሪያ "አዎን ጌታዬ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ" አለው። መስሐቲ ዲያብሎስም ይህን ልታደርግ በእጅህ ደብዳቤ ጻፍልኝ አለው። እርሱም በከበረ ደሙ የዋጀውን የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክዶ በደብዳቤ ውስጥ የክህደቱን ቃል ጻፈለት።

በዚያንም ጊዜ ሰይጣን በጌታው ልጅ ልብ ውስጥ የፍትወት እሳትን አነደደ ይህንንም ባሪያ እጅግ ወደደችው ከእርሱም መታገሥ አልተቻላትም። ወደ አባቷ በመጮህ በግልጥ ከዕገሌ ባሪያህ ጋር ካላጋባኸኝ አለዚያ ራሴን እገድላለሁ ትለዋለች እንጂ መታገሥ አልተቻላትም። አባትና እናቷም ፈጽሞ አዘኑ በምንም በምን ሊያስታግሥዋት አልቻሉም። የዚያም አገልጋይ ፍቅሩ በየዕለቱ በልቧ ይጨመር ነበር እንጂ። ስለዚህም ራሷን እንዳትገድል አባቷ ፈራ ለዚያ ባሪያ ሰጠው። እርሱም የጌታውን ልጅ ተቀብሎ ወደቤቱ አስገባት። ከርሷ ጋር ያለውን ፍላጎቱንም ፈጸመ። ከእርሱም ጋር ረጅም ጊዜ ከኖረች በኋላ አባትና እናቷም ይቅር ብሎ ኀዘናቸውን ከላያቸው ያርቅላቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ኀዘንንና ልቅሶን አብዝተው ነበር።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ጩኸታቸውን ሰማ ልመናቸውንም ተቀብሎ ይህ የወደደችው አገልጋይ ጐልማሳ ክርስቲያን እንዳልሆነ አስገነዘባት ከእርሷ ጋር በነበረበት በዚህ በረጅም ዘመን አንዲት ቀን እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔድ ሥጋውንና ደሙንም ሲቀበል ወይም አዳኝ በሆነ በ #መስቀል ምልክት ራሱን ሲአማትብ እርሷ አላየችውም።

ስለእምነቱም ጠየቀችው ግን አልገለጠላትም እርሷም እንዲህ አለችው "አንተ ክርስቲያን ከሆንክ ና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሒድና በፊቴ ቅዱስ ቊርባንን ተቀበል።" እንዲህም በአስገደደችው ጊዜ ስለርሷ ያደረገውን ሁሉ ወደ ሥራየኛ እንደሔደም በሰይጣንም አምኖ እምነቱንም በክርታስ ጽፎ ያንን ክርታስ ለሰይጣን እንደ ሰጠው ነገራት።

ይህንንም ነገር ከእርሱ በሰማች ጊዜ ደነገጠች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች ራሷንም በማወዛወዝ እጅግ ተጸጽታ አዘነች። ያን ጊዜም ፈጥና ተነሣች የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ወደሆነው ወደ ሀገርዋ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደች ከእግሩ በታችም ወድቃ ሰገደችለት በላይዋ የደረሰውን ሁሉ አስረዳችው ለሰው ልጆች ጠላት ከሆነ ከሠይጣን እጅ ፈጽሞ ያድናት ዘንድ ብዙ በማልቀስ ለመነችው።

ቅዱስ ባስልዮስም ባሏ የሆነውን ባርያ ወደርሱ ልኮ አስመጣውና ጠየቀው እርሱም የሠራውን ሁሉ አስረዳው ቅዱስ ባስልዮስም "ተመልሰህ ክርስቲያን ልትሆን ከሰይጣንም እጅ ልትድን ትወዳለህን?" አለው ያም ባርያ "ጌታዬ ይሆንልኛልን?" አለ ይህ ቅዱስ አባትም የፈጣሪህን ስም እየጠራህ ልብህን አጽና አለው።

ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ በአንድ ቦታ ዘጋበት በ #መስቀል ምልከትም አማተበበት እንዲጸልይም አዘዘው ራሱ ቅዱስ ባስልዮስም ስለርሱ ጸለየ። ከሦስት ቀኖች በኋላም ጎበኘው እንዲህም አለው በእሊህ በሦስት ቀኖች የደረሰብህ ምንድን ነው እርሱም በላዩ በመጮህ ሠይጣናት ሲያስፈራሩት ያንንም ደብዳቤ ሲአሳዩትና በእርሱ ላይ ሲቆጡ በመከራ ውስጥ እንደኖረ ነገረው ቅዱስ ባስልዮስም ከእሳቸው ቁጣ የተነሣ አትፍራ እግዚአብሔር ይረዳሃልና አጽንቶም ይጠብቅሃል አለው።

ከዚህም በኋላ ጥቂት እንጀራና ውኃ ሰጥቶ ወደ ቦታው መለሰው ቅዱስ ባስልዮስም ስለዚያ አገልጋይ ሒዶ ይጸልይ ጀመረ። ዳግመኛም ከሦስት ቀኖች በኋላ ጐበኘውና በእርሱ ላይ ምን እንደ ደረሰበት ጠየቀው ያ አገልጋይም ጩኸታቸውን እሰማለሁ ግን አላያቸውም ብሎ መለሰለት። እንጀራና ውኃም ሰጠውና መከረው ወደ ቦታውም መለሰውና ስለርሱ ሊጸልይ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደ። እስከ አርባ ቀኖች ፍጻሜ ድረስ እንዲህ አደረገ። በአርባውም ቀን ፍጻሜ ከእርሱ ስለ ሆነው ጠየቀው ያ አገልጋይም እንዲህ አለው ቅዱስ አባቴ ሆይ ስለ እኔ ሰይጣንን ስትጣላውና ድል አድርገህ ጥለህ ስትረግጠው በዛሬዋ ሌሊት አየሁ አለው።

ቅዱስ ባስልዮስም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው የገዳማቱን መነኰሳትና ካህናቱንም ጠርቶ ስለዚያ ሰው ያቺን ሌሊት መላዋን እንዲጸልዩባት አዘዛቸ። በነጋ ጊዜም ያንን አገልጋይ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲአመጡት የዚያችንም አገር ሕዝብ ሁሉንም ሰብስቦ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንሥተው አቤቱ #ክርስቶስ ማረን ይቅር በለን እያሉ ወደ #እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዲማልዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ።

እንዲህም እያሉ ሲማልዱ ያ ሰው ጽፎ ለሰይጣን የሰጠው የክህደት ደብዳቤ ከሰይጣን እጅ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደቀ ሁሉም ደስ ብሏቸው ምስጉን #እግዚአብሔርን አመሰገኑት የከበረ አባት ባስልዮስም ባረካቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀብሎ ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በፍቅር አሰናበታቸው ። እነርሱም ስለ ኃጢአታቸው ስርየትና ስለ ድኅነታቸው ፈጽሞ ደስ እያላቸው #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይህንን ቅዱስ አባት ባስልዮስን እያከበሩ ወደ ቤታቸው ገቡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ሌሎችንም እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፥ አይተዋት፤
¹³ ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርስዋ ጋር ሊቀመጥ ቢስማማ፥ አትተወው።
¹⁴ ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፥ ያላመነችም ሚስት በባልዋ ተቀድሳለች፤ አለዚያ ልጆቻችሁ ርኵሳን ናቸው፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው።
¹⁵ የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።
¹⁶ አንቺ ሴት፥ ባልሽን ታድኚ እንደ ሆንሽ ምን ታውቂአለሽ? ወይስ አንተ ሰው፥ ሚስትህን ታድን እንደ ሆንህ ምን ታውቃለህ?
¹⁷ ብቻ ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ከፈለለት እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይመላለስ። እንዲሁም በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እደነግጋለሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።
¹⁵ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል።
¹⁶ እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤
¹⁸ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር።
¹⁹ ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።
²⁰ እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ብፁዓን እለ ተኀድገሎሙ ኃጢአቶሙ። ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኵሎ ጌጋዮሙ። ብፁዕ ብእሲ ዘኢኈለቈ ሎቱ እግዚአብሔር ኃጢአቶ"። መዝ 31፥1-2።
"መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው"። መዝ 31፥1-2።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_13_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
  ሉቃስ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ እንዲህም አላቸው፦ ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥
⁶ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን?
⁷ ያም ከውስጥ መልሶ፦ አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን?
⁸ እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል።
⁹ እኔም እላችኋለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
¹⁰ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል።
¹¹ አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን?
¹² ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን?
¹³ እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_14

መስከረም ዐሥራ አራት በዚህች ቀን #አባ_አጋቶን_ዘዓምድ አረፈ፣ #የአቡነ_ያሳይ_ዘመንዳባ እና #የቅዱስ_አባ_ጴጥሮስ የእረፍታቸው መታሰቢያ ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_አጋቶን_ዘዓምድ

መስከረም ዐሥራ አራት በዚች ቀን ቅዱስ አባት አባ አጋቶን ዘዓምድ አረፈ። ይህም ቅዱስ ለግብጽ አገር ደቡብ ከሆነ ተንሳ ከሚባል መንደር የሆነ ነው ወላጆቹም #እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለድኆችና ለችግረኞች መመጽወትን የሚወዱ ደጎችና ቸሮች ነበሩ። የአባቱም ስም መጥራ የእናቱም ማርያ ነው የምንኲስና ልብስን ይለብስ ዘንድ የሚተጋና በልቡም ሁል ጊዜ የሚያስብና የሚታወክ ሆነ።

ዕድሜውም ሠላሳ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ቅስና ተሾመ ከዚህ ዓለምም የሚወጣበትን መንገድ ይጠርግለት ዘንድ ወደ ገዳም ሒዶ በዚያ እንዲመነኲስ #እግዚአብሔርን እየለመነው የከበረች ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል የተጠመደ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ምክንያት ሰጥቶት ከሀገሩ ወጣ መርዩጥ ወደሚባልም አገር ገባ ከዚያም ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ በመነኰስ አምሳል ከእርሱ ጋር በመጓዝ ወደ ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳም እስከ አደረሰው ድረስ እየመራው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ። ለከበሩ አረጋውያንም ለአባ አብርሃምና ለአባ ገዐርጊ ደቀ መዝሙር ሁኖ ከእሳቸው ጋር ሦስት ዓመት ያህል ኖረ።

ከዚህም በኋላ በአባ ዮሐንስ ቤተ መቅደስ ፊት አቆሙት በምንኵስናው ልብስና በአስኪማው ላይ ሦስት ቀኖች ያህል ጸልየው አለበሱት ከዚያችም ቀን ወዲህ ተጋድሎውንና የ #እግዚአብሔርን አገልግሎት እጥፍ ድርብ አደረገ። ተጋድሎውም ሁል ጊዜ በቀንና በሌሊት በመጾም፣ በመጸለይ የሥጋው ቆዳ ከዐጥንቱ እስቲጣበቅ ያለ ምንጣፍም በምድር ላይ በመተኛት ሆነ።

ሁል ጊዜም የአባ ስምዖን ዘዓምድን ገድል ያነብ ነበረ መንፈሳዊ ቅናትንም ቀንቶ ራሱን በገድል እሥረኛ ሊያደርግ በልቡ አስቦ ለከበሩ አባቶች አማከራቸው እነርሱም ይህ ሀሳብ መልካም ነው አሉት በላዩም ጸለዩ ከእርሳቸውም በረከትን ተቀብሎ ከገዳም ወጣ ለዓለም ቅርብ ወደ ሆነ ስካ ወደሚባል አገር ሒዶ በአንዲት ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀመጠ ምእመናንም ዓምድ ሠሩለት። በዚያ ላይም ወጥቶ እየተጋደለና እያገለገለ ሃምሳ ዓመት ያህል ቆመ።

በዘመኑም ሰይጣን ያደረበት ሰው ተገለጠ ብዙ ወገኖችንም አሳታቸው እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀመጥ ሁኖ ትምህርቱን የሚሰሙ ሕዝቦች የዕንጨት ቅርንጫፎችን በመያዝ በዙሪያው ይቀመጣሉ አባ አጋቶንም ልኮ ወደርሱ አስመጣው በላዩም ጸለየና በሰውዬው ላይ አድሮ ለሰዎች በመናገር የሚያስተውን ሰይጣን ከእርሱ አስወጣው።

እንዲሁም ሰማዕት ሚናስ ያነጋግረኛል የምትል ሴት ተነሥታ በቅዱስ ሚናስ ስም የውኃ ጒድጓድ እንዲቆፍሩ በጠበሉ ውኃ ተጠምቀው ከደዌያቸው እንዲፈወሱ የአገርዋን ሰዎች አዘዘቻቸው ያቺንም ሴት ወደርሱ አስመጥቶ በላይዋ ጸለየ ርኵስ መንፈስንም ከእርሷ አስወጣው የዚያችንም የአገርዋን ሰዎች አዘዘቻቸው ያችንም ሴት አዘዛቸው።

ዳግመኛም ሌላ ሰው ተነሣ እርሱም ጋኔን ይዞ ያሳበዳቸውን ሰበሰባቸው ሲደበድባቸውም ለጥቂት ጊዜ ጋኔኑን ያስተዋቸዋል ብዙዎችም ጋኔን የያዛቸው ወደርሱ ተሰበሰቡ ቅዱስ አባ አጋቶንም ወደርሱ እንዲመጣ ወደ ሰውዬው ላከ ሰውዬውም ትእዛዙን ሰምቶ አልመጣም የስሕተት ሥራውንም አልተወም። የዚያችም አገር ገዥ ሲያልፍ የሰበሰባቸው እብዶች ሰደቡት ረገሙትም ስለዚህ ያን ሰው መኰንኑ ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየውና በሥቃዩ ውስጥ ሞተ።

ሌላው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ቄስ ነበረ እርሱም ከአንዲት ሴት ጋር በዝሙት ወደቀ የአካሉም እኩሌታ በደዌ ተበላሸ ተሸክመውም ወደ አባ አጋቶን አደረሱት እርሱም ጸልዮለት በ #እግዚአብሔር ስም አዳነው ያንንም ቄስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እንዲጠነቀቅና በክህነቱም እንዳያገለግል አዘዘው።

ይህም ቅዱስ አባ አጋቶን ብዙ ተአምራትን አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው። ከዚህም በኋላ በመላእክት አምሳል በመልካም ዝማሬ በመዘመር እያመሰገኑት ሰይጣናት ተገለጡለት እርሱ ግን የክብር ባለቤት #ክርስቶስ በሰጠው ጸጋ ሽንገላቸውን አውቆ አዳኝ በሆነ በ #መስቀል ምልክት አማተበባቸው ፈጥነውም ከፊቱ ተበተኑ።

ክብር ይግባውና #እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ ጥቂት ታሞ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ አስረከበ። ከዚህም በፊት ሕዝቡ ወደርሱ ይሰበሰቡና የ #እግዚአብሔርን መንገድ ያስተምራቸውና በጸሎቱም ከበሽታቸው ይፈውሳቸው ስለነበር አሁን በአረፈበት ላይ በአገኙት ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሱ እነርሱ የሚያጽናናቸውን አባታቸውን በማጣት ከእርሱ ከቅዱስ አባት በመለየት የሙት ልጆች ሁነዋልና።

መላው የሕይወቱ ዘመንም መቶ ዓመት ሆነ ከርሱም ሠላሳ አምስቱን በዓለም ውስጥ ኖረ። ዐሥራ አምስቱን ዓመት በገዳም ኖረ ኃምሳውን በዓምድ ላይ ቁሞ ኖረ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ሰው ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_ያሳይ_ዘመንዳባ

እኒህ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ በ14ኛው መቶ ክ/ዘ በጣና ገዳማትውስጥ ያበሩ ኮከብ ናቸው:: ከ7ቱ ከዋክብት (አባ ዮሐንስ፣ አባ ታዴዎስ፣ አባ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አባ ሳሙኤል ዘቆየጻና አባ ሳሙኤል ዘጣሬጣ ) እርሳቸው አንዱ ናቸው:: እነዚህ አበው ከገዳማዊ ሕይወታቸው ባሻገር በምስጉን የወንጌል አገልግሎታቸው የሚታወቁ ናቸው::

ገድላቸው እንደሚለው አቡነ ያሳይ የዐፄ ዐምደ ጽዮን ቀዳማዊ ልጅ ሲሆኑ የተወለዱትም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ሽዋ ተጉለት ውስጥ ነው:: ገና በልጅነታቸው ወደ አባታቸው ቤተ መንግስት የሚመጡ መነኮሳትን እግር እያጠቡ ሥርዓተ ምንኩስናን በድብቅ ያጠኑ ነበር::

ብሉይ ከሐዲስ የጠነቀቁ ናቸውና የአባታቸውን ዙፋን (ልዑልነት) ስለ ፍቅረ #ክርስቶስ ንቀውት እየዘመሩ ጠፍተው ወደ ትግራይ ተጓዙ:: በዚህም ምክንያት 'መናኔ መንግስት' ይባላሉ:: በዚያም ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ውስጥ ገብተው የታላቁ አባት የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደቀ መዝሙር ሆኑ::

ቀደም ሲል የጠቀስናቸው 7ቱ አበው በዚያ ነበሩና 7ቱም በአንድ ቀን ሲመነኩሱ ገዳሙ የተቃጠለ እስኪመስል ድረስ ብርሃን ወርዶ ነበር:: አቡነ ያሳይ በረድእነት በቆዩበት ዘመን ዛፎችን መትከል ይወዱ ነበር:: ከትሩፋት መልስም በልብሳቸው ውሃ እየቀዱ ያጠጡ ነበር:: በተለይ "ምዕራገ ጸሎት" የሚባለው ተአምረኛ ዛፍ ዛሬ ድረስ አለ ይባላል::

አቡነ ያሳይ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተባርከው: ከ2ቱ ባልንጀሮቻቸው (አቡነ ሳሙኤል ዘዋሊና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ) ጋር ወደ ጣና ሐይቅ መጡ:: በዚያም አካባቢ ተአምራትን እየሠሩ ሕዝቡንም እያስተማሩ ከቆዩ በኋላ ጌታ ወደየፈቀደላቸው ቦታ ተለያዩ::

አቡነ ሳሙኤል ወደ ዋልድባ: አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ወደ ገሊላ: ከዚያ ወደ ጉጉቤ ሲሔዱ አቡነ ያሳይ መንዳባ ውስጥ ገቡ:: ጻድቁ ወደ አርባ ምንጭ ሒደው ታቦተ #መድኃኔ_ዓለምን ይዘው ሲመጡ ጣናን የሚሻገሩበት አጡ:: #ጌታን ቢማጸኑት:- "ምነው እሷን ድንጋይ ባርከህ አትቀመጥባትም?" አላቸው:: እሳቸውም በእምነት: ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጣናን ተሻገሩት:: ይህንን ከርቀት ያዩ የዘመኑ ሰዎች "ብዙ ተአምር አይተናል: ነገር ግን ማን እንደ አባ! ጣናን በድንጋይ የተሻገረ" ሲሉ አድንቀዋቸዋል::
ጻድቁ ጣናን ተሻግረው: ገዳም መሥርተው: ብዙ አርድእትን አፍርተው: በተጋድሎ ሕይወታቸው ቀጥለዋል:: በተለይ ዛሬ ድረስ የሚተረከው የ'አትማረኝ' ታሪክም የሚገኘው እዚሁ ገዳም ውስጥ ነው:: ታሪኩም በየዋህነት "አትማረኝ" ብለው ጸልየው ጣናን ያለ ታንኳ በእግራቸው የረገጡ አባትን የሚመለከት ሲሆን ከአቡነ ያሳይ ጋርም ወዳጅ ነበሩ::

አባታችን አቡነ ያሳይ ለዘመናት በቅድስና ኑረው: ቅዱሳንንም ወልደው መስከረም 14 ቀን ታመሙ:: "ጌታ ሆይ!" ብለው ቢጠሩት #መድኃኔ ዓለም መጣላቸው:: ጣና በብርሃን ተከበበች:: #ጌታም "ወዳጄ! ስለ ድካምህ: ደጅህን የረገጠውን: መታሰቢያህን ያደረገውን: በስምህ የተማጸነውን ሁሉ ከነትውልዱ እምርልሃለሁ" ብሏቸው ነፍሳቸውን አሳረገ:: አበውም ሥጋቸውን ገንዘው እዚያው መንዳባ መድኃኔ ዓለም ውስጥ ቀበሩት:: ዐጽማቸው ዛሬም ድረስ ይገኛል::

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ያሳይ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ጴጥሮስ_መምህረ_ፃና (ጣና)

በዚችም ቀን ደግሞ የፃና (የጣና) መምህራን ለሆኑ አባቶች ዐሥራ አንደኛ የሆኑ የፃና (የጣና) መምህር ቅዱስ አባት አባ ጴጥሮስ አረፉ።

ትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ቡልጋ ልዩ ስሙ ደብረ ጽላልሽ ነው፡፡

ጻድቁ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በሥራቸው ሁሉ እውነተኛና ንጹሕ በቀንና በሌሊትም በጾምና በጸሎት የተጠመዱ ስለነበረ ሕዝቡም በጎ ሥራቸውንና ቅድስናቸውን በአዩ ጊዜ ለመምህርነት መርጠው ሾሙአቸውና በሹመቱ ወንበር አርባ ስምንት ዓመት በሰማዕት ገላውዴዎስ መቅደስ እያጠኑ ኖረዋል።

ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ ሊቃኖስ እጆቻቸው እያበሩ ለገዳሙ መብራትነት ይጠቀሙባቸው እንደነበረው ሁሉ የአቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊም እጆቻቸው እንደፋና እያበራ ለጣና ሐይቅ ገዳማት በመብራትነት ያገለግል ነበር፡፡ ጻድቁ ለ31 ዓመታት ከመላእክት ጋር እየተነጋገሩ የኖሩ ሲሆን መናም ከሰማይ እያወረዱ መነኮሳቱን ይመግቡ ነበር፡፡ ድውያንን በመፈወስ፣ ሙታንን በመንሣት ብዙ አስተደናቂ ተአምራት እያደረጉ ወንጌልን በሀገራችን ዞረው በማስተማር #እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ኖረው በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፈው ቅድስት ነፍሳቸውን ቅዱሳን መላእክት በክብር ተቀብለዋታል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘላለሙ ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

#መስከረም_14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የ #ቅዱሳን በዓላት
1.አባ አጋቶን ዘዓምድ
2.አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ
3.አባ ጴጥሮስ መምሕረ ጻና (ጣና)
4.ቅዱስ ዴግና ቀሲስ

#ወርሐዊ_በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

†"ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላቹሃለሁ ዋጋው አይጠፋበትም::" †
(ማቴ. ፲፥፵፩)

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_14 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁴ ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና።
³⁵ ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ።
³⁶ ምን ነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን?
³⁷ ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ፤
³⁸ ማንም የማያውቅ ቢኖር ግን አይወቅ።
³⁹ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ፤
⁴⁰ ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።
¹⁹ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።
²⁰ እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።
¹² በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ።
¹³ ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥
¹⁴ ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።
¹⁵ ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።
¹⁶ ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ። ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት። ወይድኀኑ ፍቁራኒከ"። መዝ 59፥4-5።
"ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው። ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም"። መዝ 59፥4-5።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_14_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።
²³ ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።
²⁴ ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር።
²⁵ ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።
²⁶ ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፦ ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ።
²⁷ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።
²⁸ ጴጥሮስም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው።
²⁹ እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።
³⁰ ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ።
³¹ ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።
³² ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ።
³³ በታንኳይቱም የነበሩት፦ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት።
³⁴ ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ።
³⁵ የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤
³⁶ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ነው። መልካም የቅዱስ አጋቶን፣ የአቡነ ያሳይና የአቡነ ጴጥሮስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/24 00:18:19
Back to Top
HTML Embed Code: