Telegram Web Link
³⁴ ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?
³⁵ መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥
³⁶ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን?
³⁷ እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤
³⁸ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ።
³⁹ እንግዲህ ደግመው ሊይዙት ፈለጉ፤ ከእጃቸውም ወጣ።
⁴⁰ ዮሐንስም በመጀመሪያ ያጠምቅበት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ እንደ ገና ሄደ በዚያም ኖረ።
⁴¹ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፦ ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ።
⁴² በዚያም ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ #ቅዳሴ_እግዚእነ ነው። መልካም የቅዱስ ዕፀ መስቀል የደመራ በዓል ለሁላችንንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_17

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ ሰባት በዚህች ቀን #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የተሰቀለበት የከበረ #መስቀል በዓሉ ነው፣ #የቅድስት_ድንግል_ታኦግንስጣ እና የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ዲዮናስዮስ እረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በዓለ_ቅዱስ_መስቀል

መስከረም ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን ክብር ይግባውና #ጌታችን_አምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የተሰቀለበት ለከበረ #መስቀል በዓሉ ነው። ይህም የጻድቁ ንጉሥ የቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ከተሠወረበት የገለጠችው ነው።

የጎልጎታን ኮረብታ በአስጠረገች ጊዜ የከበረ #መስቀልን አገኘችው ታላቅ ኮረብታም የሆነበት ምክንያት እንዲህ ነው። ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ክብር ይግባውና ከ #ጌታችን_ከመድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመቃብሩና ከከበረ #መስቀሉ የሚገለጡ ሁነው ሙታን ይነሡ ነበርና የጎበጡና በሽተኞች ሁሉ ይፈወሱ ነበር።

ስለዚህም አይሁድ ተቆጡ እንዲህም ሥርዓትን ሠርተው አዘዙ በይሁዳ አገር ሁሉና በኢየሩሳሌም ቤቱን የሚጠርግ ሁሉ ወይም አፈር ወይም ጉድፍ የሚጠርግ በናዝሬቱ #ኢየሱስ መቃብር ላይ ይጥል ዘንድ እንዲህም እያደረጉ ዕሌኒ ንግሥት እስከ መጣች ድረስ ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ኖሩ።

እርሷም በመጣች ጊዜ ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መቃብርን እስከ አሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሠቃየቻቸው ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው የከበረ #መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ።

ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራች በዚች ቀንም አከበሩዋት ለ ቅዱስ #መስቀሉም በዓልን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን አከበሩለት። የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም ከሀገሮቻቸው በመምጣት ክብር ይግባውና ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ የትንሣኤውን በዓል እንደሚያከብሩ ለ ቅዱስ #መስቀልም ታላቅ በዓልን የሚያክብሩ ሆኑ።

ክርስቲያኖችም በጎዳና እየተጓዙ ሳሉ ስሙ ይስሐቅ የሚባል አንድ ሳምራዊ ሰው ከእርሳቸው ጋር ነበር ከእርሱም ጋር ብዙዎች ሳምራውያን ነበሩ ይህ ይስሐቅም የክርስቲያን ወገኖችን ለምን በከንቱ ትደክማላችሁ ለዕንጨትስ ልትሰግዱ እንዴት ትሔዳላችሁ እያለ ይሣለቅባቸው ነበር። ከክርስቲያን ወገኖችም ስሙ አውዶኪስ የሚባል አንድ ቄስ አለ ሕዝቡም በጎዳና ሲጓዙ የሚጠጡት ውኃ አላገኙም ነበርና ተጠሙ።

ወደ አንድ ጉድጓድም ሔዱ በውስጡም መሪር የሆነና የገማ ውኃ አገኙ እጅግም በውኃ ጥማት ተሠቃዩ። ይስሐቅም እጅግ ይሣለቅባቸው ጀመረ የቀናች ሃይማኖት ካለቻችሁ ይህ የገማና የመረረ ውኃ ተለውጦ እስቲ ጣፋጭ ይሁን ይላቸው ነበር።

ቀሲስ አውዶኪስም በሰማ ጊዜ መንፈሳዊ ቅናትን ቀንቶ ከዚያ ሳምራዊ ይስሐቅ ጋር ተከራከረ ያ ሳምራዊም በ #መስቀል ስም የተአምራት ኃይልን ከአየሁ እኔ በ #ክርስቶስ አምናለሁ አለ። ያን ጊዜም ቀሲስ አውዶኪስ በዚያ በገማ ውኃ ላይ ጸለየ ውኃውም ወዲያውኑ ጣፋጭ ሆነ ከእርሱም ሕዝቡ ሁሉ እንስሶቻቸውም ጠጡ።

ሳምራዊ ይስሐቅ ግን በተጠማ ጊዜ በረዋት ከያዘው ውኃ ሊጠጣ ፈለገ ግን ገምቶ ተልቶ አገኘውና መሪር ለቅሶን አለቀሰ። ወደ ከበረ ቄስ አውዶኪስም መጥቶ ከእግሩ በታች ሰገደ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_በአምላካችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመነ በከበረ ቄስ በአውዶኪስ ጸሎት ጣፋጭ ከሆነው ከዚያ ውኃም ጠጣ።

በዚያም ውኃ ውስጥ ታላቅ ኃይል የሚሠራ ሆነ እርሱ ለአማንያን የሚጣፍጥ ሲሆን ለከሀዲያንና ለአረማውያን የሚመር ሆነ በውስጡም የብርሃን #መስቀል ታየ በአጠገቡም ውብ የሆነች ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ።

ሳምራዊ ይስሐቅም ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በደረሰ ጊዜ ወደ ኤጴስቆጶሱ ሒዶ ከቤተሰቡ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። የከበረ #መስቀልም ዳግመኛ የተገለጠበት መጋቢት ዐሥር ቀን ነው ዜናውንም በዚሁ ቀን ጽፈናል።

ምእመናንም በታላቁ ጾም መካከል በዓሉን ማክበር ስለአልተቻላቸው በዓሉን ቤተ ክርስቲያኑ በከበረችበት ቀን አደረጉ ይህም መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው በዚህም ቀን አስቀድሞ ከከበረ መቃብር በንግሥት ዕሌኒ እጅ የተገለጠበት ነው።

#መስቀሉ ላዳነን #ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ክብር ምስጋና ገንዘቡ ነውና ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ታኦግንስጣ

በዚችም ቀን የከበረች ሮማዊት ታኦግንስጣ አረፈች ። ይቺም ቅድስት በደጋጎች ነገሥታት በአኖሬዎስና በአርቃዴዎስ ዘመን የነበረች ናት። በዚያም ወራት የህንድ ንጉሥ መልእክተኞች እጅ መንሻ ይዘው ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ መጡ በሚመለሱም ጊዜ ይችን ድንግል ታኦግንስጣን አገኟት የምታነበውም መጽሐፍ በእጅዋ ውስጥ ነበር ወደ አገራቸውም ነጥቀው ወሰዷት ለህንድ ንጉሥም ሚስቶቹንና ቤተሰቦቹን የምትጠብቅ ሆነች።

በአንዲት ዕለትም የንጉሡ ልጅ አስጨናቂ በሆነ ደዌ ታመመ የከበረች ታኦግንስጣም ወስዳ በብብቷ ታቅፋ በ #መስቀል ምልክት አማተበችበት በዚያንም ጊዜ ዳነ ከእርሷም ስለ ተደረገው ተአምር የዚች የከበረች ድንግል ታኦግንስጣ ዜናዋ በሀገሩ ሁሉ ተሰማ ከዚያችም ቀን ወዲህ በእነርሱ ዘንድ እንደ እመቤት እንጂ እንደ አገልጋይ አልሆነችም።

ከዚህም በኋላ የህንድ ንጉሥ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ ጉም ጭጋግ ዐውሎ ነፋስና ጨለማ በላዩ መጣ ንጉሡ ግን የከበረች ታኦግንስጣ ስታማትብ ስለአየ በ #መስቀል ምልክት ማማተብን ያውቅ ነበርና ያን ጊዜ በጭጋጉ በጉሙ በጨለማውና በጥቅሉ ነፋስ ላይ በ #መስቀል ምልክት አማተበ። ወዲያውኑ ፀሐይ ወጣ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ጠላቶቹንም በዚሁ የ #መስቀል ምልክት ድል አደረጋቸው እጅግም ደስ አለው።

ንጉሡም ከጦርነት በተመለሰ ጊዜ ለከበረች ታኦግንስጣ። ከእግርዋ በታች ሰገደ እርሱንና ቤተሰቦቹን ሁሉ የሀገሩንም ሰዎች የከበረች የክርስትና ጥምቀትን ታጠምቀው ዘንድ ለመናት ቅድስት ታኦግንስጣም እንዲህ አለችው ይህን አደርግ ዘንድ ለእኔ አይገባኝም የሚያጠምቃችሁን ካህን ይልክላችሁ ዘንድ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ ላኩ።

ያን ጊዜም ከወገኖቹ ጋር የሚያጠምቀውን ካህን እንዲልክለት የህንድ ንጉሥ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ መልእክተኞችን ላከ ንጉሥ አኖሬዎስም ልመናውን ተቀብሎ የሚያጠምቃቸውን ቄስ ላከ ቄሱም አጠመቃቸው መሥዋዕትንም ቀድሶ ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን አቀበላቸው #እግዚአብሔርንም የምትወድ የከበረች ድንግል ታኦግንስጣ እጅግ ደስ አላት ያንንም ቄስ መንፈሳዊ ሰላምታ ሰጠችውና ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለች እርሱም ከእርሷ በረከትን ተቀበለ።

ከዚህም በኋላ ለራስዋ ገዳም ሠራች ብዙዎች ደናግልም ተሰበሰቡ የምንኩስና ልብስንም በመልበስ እንደርሷ መሆንን ወደዱ እርሷም እመ ምኔት ሆነች። ያም ባሕታዊ ቄስ የክርስትና ጥምቀትን ከአጠመቃቸው በኋላ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ ተመልሶ የህንድን ሰዎች እንዳጠመቃቸውና ክብር ይግባውና ወደ #ክርስቶስ ሃይማኖት እንደገቡ ነገረው። ንጉሥ አኖሬዎስም እጅግ ደስ አለው የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳትንም ይህን ባሕታዊ ኤጲስቆጶስ አድርጎ እንዲሾምላቸው አዘዘው እርሱም ኤጲስቆጶስነት ሹሞ ከህንድ ሰዎች ላከላቸው እጅግም ደስ አላቸው።
ከዚህም በኋላ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩ ጀመሩ ምሰሶዎችንም በፈለጉ ጊዜ አላገኙም በዚያም አከባቢ ታላቅ የጣዖት ቤት ነበረ በውስጡም ያማሩ ምሰሶዎች አሉ። ድንግሊቱ ታኦግንስጣም ክብር ይግባውና #ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ብዙ በማልቀስ ለመነች ያን ጊዜም እሊያ ምሰሶዎች ከጣዖት ቤት ፈልሰው ሐናፂዎች ከሚሹት ቦታ በቤተ ክርስቲያን መካከል ተተከሉ አማንያን ሁሉ ክብር ይግባውና #ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አመሰገኑት ጣዖትን ሲያመልኩ የነበሩም ጣዖቶቻቸውን ሰብረው ክብር ይግባውና ወደ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት ተመልሰው ገቡ በዚያችም አገር ታላቅ ደስታ ሆነ።

ቅድስት ድንግል ታኦግንስጣም ተጋድሎዋን ከፈጸመች በኋላ #እግዚአብሔርንም አገልግላ ደስ አሰኝታ በዚያ ገዳም በደናግሉ መካከል በሰላም በፍቅር አረፈች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_ዲዮናስዮስ

በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዲዮናስዮስ አረፈ። ይህንንም ቅዱስ ንጉሥ ዳኬዎስ ሊገድለው ፈልጎት ነበር ግን #እግዚአብሔር ሠወረው ይህም አባት ብልህ አዋቂ ስለነበረ ብዙዎች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ተረጎመ።

በዘመኑም በሮም ንጉሥ በከሀዲ ዳኬዎስ እጅ ቅዱስ መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፈ። ሁለተኛም ሰባቱ ደቂቅ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት አንቀላፍተው ነቁ እሊህም ለጣዖታት ሊአሰግዳቸው በፈለጋቸው ጊዜ ከዳኬዎስ ፊት የሸሹ ከኤፌሶን አገር ከታላላቆች ተወላጆች ወገን የሆኑ ናቸው።

ዳግመኛም በዘመኑ የመነኰሳት አለቃ ገዳማትን የሠራ ግብጻዊው ታላቁ እንጦንዮስ ለመጀመሪያ ጊዜ መነኰስን ሆነ። ይህም ቅዱስ ዲዮናስዮስ በሊቀ ጵጵስናው ሹመት ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ። መንጋዎቹንም በትክክል በፍቅር አንድነት ጠበቃቸው #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#መስቀሉ ላዳነን ለ #እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_17)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤
¹⁰ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።
¹¹ ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል፤ በክርስቶስ ላይ ተነሥተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና፤
¹² የፊተኛውንም እምነታቸውን ስለ ናቁ ይፈረድባቸዋል፤
¹³ ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም።
¹⁴ እንግዲህ ቆነጃጅት ሊያገቡ፥ ልጆችንም ሊወልዱ፥ ቤቶቻቸውንም ሊያስተዳድሩ፥ ተቃዋሚውም የሚሳደብበትን አንድን ምክንያት ስንኳ እንዳይሰጡ እፈቅዳለሁ፤
¹⁵ ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን እንዲከተሉ ፈቀቅ ብለዋልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውኃ ያመነጫልን?
¹² ወንድሞቼ ሆይ፥ በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውኃም ጣፋጭ ውኃ አይወጣም።
¹³ ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።
¹⁴ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ።
¹⁵ ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤
¹⁶ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና።
¹⁷ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
¹⁸ የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና።
²⁷ አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው።
²⁸ ሊቀ ካህናቱም፦ በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው።
²⁹ ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ፦ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።
³⁰ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤
³¹ ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።
³² እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_17_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወረከብናሁ ውስተ ኦመ ገዳም። ንበውዕ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር። ወንሰግድ ውስተ መካን በኃ ቆመ እግረ እግዚእነ"። መዝ 131፥6-7።
"እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን"። መዝ 131፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_17_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ፦ ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።
²⁶ ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን፦ አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት።
²⁷ ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን፦ እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
ወይም👇
ማቴዎስ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶-¹⁷ በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ፦ እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
¹⁸ ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ።
¹⁹ አንድ ጻፊም ቀርቦ፦ መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።
²⁰ ኢየሱስም፦ ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።
²¹ ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው፦ ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው።
²² ኢየሱስም፦ ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው።
²³ ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።
²⁴ እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር።
²⁵ ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።
²⁶ እርሱም፦ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።
²⁷ ሰዎቹም፦ ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈ_ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ዕፀ #መስቀል በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም አስራ ስምንት በዚህች ቀን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ #አቡነ_ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር፣ የደብረ ጽጋጉ #አቡነ_አኖሬዎስ፣ ሰማዕቱ #ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ካልዕ#የአቡነ_ያዕቆብ_ግብፃዊ ዕረፍታቸው ነው። ዳግመኛም ይህች ዕለት ሐዋርያው #ቅዱስ_ቶማስ በሕንድ አገር ድንቅ ተአምር ያደረገባት ዕለት ናት፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ_ከፋሌ_ባህር

መስከረም ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ወንጌልን የሚሰብክ የሃይማኖት መምህር አባታችን ኤዎስጣቴዎስ አረፈ ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ክርስቶስ ሞዓ የእናቱ ስም ስነ ሕይወት ይባላል ሁለቱም ደጋጎች #እግዙአብሔርን የሚፈሩና በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ነበሩ።

ከዘህም በኋላ በከበረ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት ይህን ቅዱስ ወለዱት ስሙን የጌታ ጥብቅ ብለው ሰየሙት ። በአደገም ጊዜ የዳዊትን መዝሙርና የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍትን አስተማሩት ።

ከዚህም በኋላ የእናቱ ወንድም አባ ዘካርያስ ወደአለበት የመነኰሳት ገዳም ወሰዱት ። አባ ዘካርያስም የ #እግዚአብሔርን ጸጋ እንዳደረችበት አውቆ የምንኩስናን ሥርዓት አስተምሮ የመላእክትን አስኬማ አለበሰው ። ከገድሉ ጽናት የተነሣ በገዳም ያሉ አረጋውያን እስኪያደንቁ ድረስ በጾም በጸሎት የተጠመደ ሆነ እርሱ በጥበብና በዕውቀት የጸና ነውና ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ዲቁና ተሾመ የዲያቆናት አለቃ እንደሆነ እስጢፋኖስም ለቤተ ክርስቲያን አገለገለ ።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር ተገለጠለትና ሰላምታ ሰጠው በንፍሐትም #መንፈስ_ቅዱስን አሳደበረት እንዲህም አለው ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ሆይ እኔ ከእናትህ ማሕፀን መረጥኩህ ያለ ፍርሀትና ድንጋፄ ወንጌልን ለብዙዎች ሕዝቦች ትሰብክ ዘንድ ከኢትዮጵያ እስከ አርማንያ ድረስ መምህር አደረግሁህ አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን ያልሰማ እኔን አልሰማም #ጌታችንም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ ።

ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስም ወደ ጳጳስ ሒዶ ቅስና ተሾመ የወንጌልንም ሃይማኖት ይሰብክ ዘንድ ጀመረ ብዙ ሰዎች ወደ ርሱ እስቲሰበሰቡ ድረስ በእርሱም እጅ መንኩሰው ደቀ መዛሙርትን ሆኑት ከእርሳቸውም ታላቁ አባ አብሳዲ ነው ።

ብዙዎችንም የከፋች ሥራቸውን አስትቶ ከክህደታቸው መለሳቸው ትምህርቱም በሀገሩ ሁሉ ደረሰ በመላ ዘመኑም የሰንበታትና የበዓላት አከባበር የጸና ሁኖ ተሠራ ከሐዋርያትም ሕግና ሥርዓት ወደቀኝም ሆነ ወደ ግራ ሁሉም ፈቀቅ አላሉም ።

ወደ ኢየሩሳሌምም ሁለት ጊዜ ሔደ #እግዚአብሔርም በእጆቹ የዕውራንን ዐይኖች በማብራት አንካሶችንና ጎባጦችን በማቅናት አጋንንትን በማስወጣት ቁጥር የሌላቸው ተአምራትን አደረገ ።

ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ለመሔድ በአሰበ ጊዜ ልጆቹን ሰብስቦ የመነኰሳትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ከመናፍቃንም ጋር እንዳይቀላቀሉ አማፀናቸው ። ልጁ አብሳዲንም በእነርሱ ላይ ሾመውና ወደ ኢየሩሳሌም ሰንበትን እያከበረና የ #ክርስቶስን ሃይማኖት እያስተማረ ሔደ ። ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚንም ደርሶ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለ የሃይማኖትንም ነገር ተነጋገሩ ዳግመኛም ከከበሩ ቦታዎች በመሳለም በረከትን ተቀበለ በዮርዳኖስም ተጠመቀ ።

ከዚያም ወደ አርማንያ ሔደ ወደ ኢያሪኮ ባሕርም ሲደርስ በመርከባቸው ያሳፍሩት ዘንድ መርከበኞችን ለመናቸው በከለከሉትም ጊዜ ዓጽፉን በባሕሩ ላይ ዘረጋ በ #ቅድስት_ሥላሴ ስም በላዩ ባረከ ራሱንም በ #መስቀል ምልክት አማተበ እንደ መርከብም ሁኖለት በላዩ ተጫነ ሁለት መላእክትም ቀዛፊዎች #ጌታችንም እንደ ሊቀ ሐመር ሆኑለት ። ከባሕሩም ግርማ የተነሣ እንዳይፈሩ ልጆቹን አጽናናቸው ። ግን እንዲህ አላቸው ልጆቼ በልባችሁ ቂምንና ሽንገላን እንዳታኖሩ ተጠበቁ ለኔ ግን ከእናንተ አንዱ አንደ ሚጠፋ ይመስለኛል ይህን ሲናገር ልቡ የቂም የበቀል ማከማቻ ስለሆነ ወዲያውኑ አንዱ ከእነርሱ መካከል ሠጠመ ።

#እግዚአብሔርም ፈቃድ ባሕሩን ተሻግሮ ወደ አርማንያ ከተማ ደርሶ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ተገናኘ ሰገደለትም ከእርሱም ቡራኬን ተቀበለ ሊቀ ጳጳሱም በአየው ጊዜ ታላቅ ደስታን ደስ አለው በፍቅርም ተቀበለው ።

አባታችን ኤዎስጣቴዎስም ሁሉም በትመህርቱ አንድ እስከሆኑ ድረስ የአርማንያን ሰዎች ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው የሠሩትን ሥርዓት እያስተማራቸው ኖረ ።

ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲደርስ ክብር ይግባውና #ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ቃል ኪዳንን ሰጠው ። በአረፈም ጊዜ ጳጳሳትና ካህናት በታላቅ ክብር ገንዘው በሰማዕቱ በቅዱስ መርምህናም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀበሩት ። ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገለጡ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አኖሬዎስ_ትልቁ

በዚችም ቀን የደብረ ጽጋግ መምህር አባ አኖሬዎስ አረፈ።

"አኖሬዎስ ትልቁ" መባላቸው "ትንሹ አኖሬዎስ" በሚል ስያሜ የተጠሩ ሌላ ጻድቅ አሉና ነው፡፡ ይኸውም ታላቁ አቡነ አኖሬዎስ አባታቸው ዘርዐ ሃይማኖት ወይም ዘርዐ አብርሃም እናታቸው ደግሞ ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ አቡነ አኖሬዎስ ታላቁ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር እነዚህ ሁሉም የወንድማማቾች ልጆች ናቸው፡፡

እነኚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናትም የእኅትማማቾች ልጆች ናቸው፡፡ ማለትም የአኖሬዎስ ታላቁ እናት ክርስቶስ ዘመዳ፣ የሕፃን ሞዐ እናት ትቤ ጽዮን፣ የንጉሡ የዐፄ ይኮኖ አምላክና የማርያም ዘመዳ እናት እምነ ጽዮን እኅትማማቾች ናቸው፡፡ እነዚህም ሦስቱ እኅትማማቾች (እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ) መድኃኒነ እግዚእ የሚባል አንድ ወንድም አላቸው፡፡ እርሱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት እናት የቅድስት እግዚእ ኀረያ አባት ነው፡፡ ማርያም ዘመዳም አቡነ ዜና ማርቆስንና ማርያም ክብራን ወልዳለች፡፡ ማርያም ክብራም ትንሹን አኖሬዎስን ወልዳለች፡፡ ታላቁ አቡነ አኖሬዎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ ወደ ትግራይ በመሄድ ፀዓዳ ዓንባ ከተባለ ቦታ ገዳም መሥርተዋል፡፡

ግብፃዊው አቡነ ያዕቆብ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደብረ ሊባኖሱን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን አስጠርተው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለት አበው መርጠን ክርስትና ይስፋፋ” ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያን መርጠው ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሠማሩ፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ሲሠማሩ ለአቡነ አኖሬዎስ እንደ ግብጦን የተባለ ቦታ ደረሳቸው፡፡ ይህም ቦታ ከግንደ በረት እስከ ባሌ ያለውን አገር ያካትታል፡፡ እርሳቸውም ሰባት ታቦታት ይዘው በመሄድ አብያተ ክርስቲያናት ተክለው ክርስትናን አስፋፍተዋል፡፡ በአካባቢው ስብከተ ወንጌልን ካስፋፉ በኋላ ባርጋባን የተባለ የአካባቢው ሰው ተአምራታቸውንና ትምህርታቸውን ተመልክቶ በጽጋጋ
ገዳም እንዲመሠርቱ ስለነገራቸው አቡነ አኖሬዎስ በጽጋጋ ገዳም መሥርተዋል፡፡

ይህ የአቡነ አኖሬዎስ ገዳም ደሴ ዙሪያ በጽጋጋ የሚገኝ ሲሆን ከደሴ ወደ መካነ ሰላም በሚወስደው መንገድ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ገዳሙ የተመሠረተው በ1317 ዓ.ም በንጉሥ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ አቡነ አኖሬዎስ በጽጋጋ ገዳማቸው እያሉ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በክፉዎች ምክር ተታሎ የአባቱን ሚስት በማግባቱ ጻድቁ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ ንጉሡን ስለገሠጹት ታስረው ወደ ወለቃ ተጋዙ፡፡ ንጉሡ ሲሞት ሠይፈ አርዕድ ነግሦ የተጋዙት በሙሉ እንዲመለሱ ስላወጀ አቡነ አኖሬዎስም ወደ በዓታቸው ጽጋጋ ተመለሱ፡፡ አቡነ አኖሪዎስ በነገሥታቱ ፊት ቆመው የወንጌልን ሕግ በመመስከራቸው እየታሰሩ ምድረ ጸወን ወደምትባል አገር (ይህውም ደቡብ ወሎ ቦረና የምትገኝ ናት) እንዲሁም ዝዋይ ደሴ ገማስቄ ግድሞ (ባሌ አካባቢ) ወደ ተባለው አገር ተጋዙ፡፡ ለብዙ ዓመታት ገዳም መሥርተው ቆይተው ወደ ጥንት በዓታቸው ተመልሰው ጽጋጋ መጥተው በገዳማቸው ብዙ ተጋድለው በ1471ዓ.ም በዚሁ በጽጋጋ ገዳማቸው ነው ያረፉት፡፡

በኋላም ወደ አሩሲ በመሄድ ኢስላሞችን አስተምረዋል፡፡ ብዙ ተአምራት ያደረጉላቸው ሲሆን መንደራቸውንም ያማረ መንደር ብለው ሰይመውላቸዋል፡፡ የአሩሲ ኢስላሞች እጅግ ያከብሯቸውና ይወዷቸው ነበር። ከአክብሮታቸውም የተነሣ አቡነ አኖሬዎስን ‹‹ኑር ሁሴን›› እያሉ ይጠሯቸው ነበር፡፡ ጻድቁ በአሩሲ ቆመው የጸለዩበት ቦታ ዛሬም ድረስ ተከብሮ ይኖራል፣ ሶፍ ዑመር ዋሻ ተብሎ የሚጠራው ታሪካዊ ዋሻ የአቡነ አኖርዮስ በዓት መሆኑ በታሪክ የሚታወቅ ሐቅ ነው፣ ይህም በገድለ ተክለ ሃይማኖትና በድርሳነ ቅዱስ ዑራኤል ላይ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ ጻድቁ በኢቲሳ 21 ዓመት ቆመው ሲጸልዩ ብርሃን ተተክሎ ይታይ ነበር፡፡ ከጌታችን ከ #መድኃኒታችን_ከኢየሱስ_ክርስቶስ ትልቅ ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ መስከረም 18 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አኖሬዎስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መርቆሬዎስ_ካልዕ(ሰማዕት)

በዚች ቀን በከሀዲው ዮልያኖስ እጅ ሌላው ቅዱስ መርቆሬዎስ በሰማዕትነት አረፈ እርሱም አስቀድሞ ክርስቲያን የነበረ ነው ። የታላቁ ቈስጠንጢኖስ ልጅ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ በሞተ ጊዜ የቈስጠንጢኖስ እኅት ልጅ ዩልያኖስ ነገሠ እርሱ ግን ጣዖታትን አመለከ ሰገደላቸውም የክርስቲያን ወገኖችንም አሠቃያቸው ብዙዎችም በእርሱ እጅ በሰማዕትነት አረፉ ።

የንጉሡም የልደቱ ቀን በሆነች ጊዜ የሳቅ የሥላቅ የሆኑ ተጫዋቾችን ሰበሰባቸው ይህ ቅዱስ መርቆሬዎስም ቁጥሩ ከእሳቸው ጋር ነበር ካህናት በቤተክርስቲያን እንደሚያደርጉት በክርስትና ሥርዓት እንዲጫወት ይህን መርቆሬዎስን ከሀዲው ንጉሥ አዘዘው እንዳዘዘውም በክርስትና ሥርዓት ሁሉ ተጫወተ ታላቅም ሳቅና ሥላቅ ሆነ።

ሁለተኛም በክርስትና ጥምቀት ሥርዓት ሊጫወት ጀመረ በ #መስቀል ምልክት አንድ አምላክ በሚሆን በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም እያለ በውኃው ላይ አማተበ ። ያን ጊዜም መለኮታዊ ብርሃን በውኃው ውስጥ ወረደ #እግዚአብሔርም የልቡናውን ዐይን ገልጦለት ያንን ብርሃን አየው ልብሱን ጥሎ ራቁቱን ወደ ውኃው ወርዶ በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያለ ተጠመቀ ።

ከዚህም በኋላ ወጥቶ ልብሱን ለበሰ በንጉሡም ፊት ቆሞ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ታመነ ንጉሡም በርሱ ላይ ተቆጣ እንዲህም ብሎ አስፈራራው ለእኔ በመታዘዝ ለአማልክት ዕጣንን ካላሳረግህ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ ትእዛዜን ከተቀበልክ ግን እኔ ብዙ ገንዘብ ሰጥቼህ እጅግ አከብርሃለሁ ።

ቅዱስ መርቆሬዎስም የዚህን ዓለም ገንዘብ ሁሉና መንግሥትንም ብትሰጠኝ #ጌታዬ_እግዚአብሔር_ኢየሱስ_ክርስቶስን አልክደውም ብሎ መለሰለት ። ያን ጊዜም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ንጉሡ አዘዘና ቆረጡት በሰማያዊት መንግሥትም የማይጠፋ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አማን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ግብጻዊ_ሊቅ_ቅዱስ_ያዕቆብ

በዚችም ቀን መስተጋድል የሆነ ግብጻዊ ሊቅ ያዕቆብ አረፈ። ወላጆቹም ደጎች ምእመናን ነበሩ ይህንንም ቅዱስ አገልጋይ ሊሆን ለ #እግዚአብሔር ሰጡት ። ትምህርቱንም በአደረሰ ጊዜ በእስክንድርያ ወደ አለ ገዳም ወላጆቹ ወሰዱት ለአበ ምኔት አባ ገብርኤልም ሰጡት ። እርሱም ተቀብሎ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሁኖ ሳለ አመነኰሰው ።

ከዚህም በኋላ ሃያ ዓመት ሲሆነው ለተጋድሎ ከመምህሩ ጋር ወደ በረሃ ወጡ ከፍታ ያላት ግንብንም አግኝተው አባ ገብርኤልና አባ ያዕቆብ ከላይዋ ላይ ወጡ ። ከዚያም የውኃ ጉድጓድ አለ ከዚያም ጉድጓድ ውኃ እየቀዱ በገንዳዎች ላይ ያፈሳሉ የዱር እንስሶችም ሁል ጊዜ እየመጡ ከገንዳው ውኃ ይጠጣሉ አባ ያዕቆብም ያልባቸዋል ወተታቸውንም አይብ አድርጎ ከመምህሩ ጋር ይመገባሉ ።

አባ ገብርኤልም በአረፈ ጊዜ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ዐሥራ ሁለት ገዳማውያን መጡ በጾምና በጸሎትም በመትጋት የእንስሶቹን ወተት በመመገብ ከእርሱ ጋር ተቀመጡ ለገዳሙ የሚያስፈልገውን ግን ነጋዴዎች ሥንዴን ከሩቅ ያመጣሉ ።

ከዕለታትም በአንዲቱ ዕለት እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ አባ ሙሴ ጸሊምን ብናየው ከእርሱም ብንባረክ እንወድ ነበር። ሰይጣንም በሰማ ጊዜ በመፋቀራቸው ቀንቶ በሙሴ ጸሊም አምሳል በክንፍ እየበረረ መጣ ሽማግሌ ስሆን ከቦታዬ ለምን አናወጻችሁኝ አላቸው ። እነርሱም የሕይወትን ቃል ከአፍህ ልንሰማ ከአንተም በረከትን ልንቀበል እንወዳለን አሉት ደግሞ ኑሮአችሁ እንዴት ነው አላቸው ። እነርሱም ለዱር እንስሶች በገንዳ ላይ ውኃን እንደሚቀዱ ውኃውንም ሊጠጡ ሲመጡ እንደሚአልቧቸውና ሁል ጊዜ በየማታው ከወተታቸው እንደሚመገቡ ነገሩት ።

ሰይጣንም እንዲህ አላቸው የአዘዝኳችሁን ትሰማላችሁን አላቸው አዎን እንሰማሃለን አሉት ። ዳግመኛ እንዲህ አላቸው የእንስሶቹን ወተት አትጠጡ እናንተ መነኰሳት ስትሆኑ አታምጡአቸው ጾምን ግን በየአርባ ቀን ጹሙ የዳዊትንም መዝሙር አትጸልዩ እርሱ በዐመፅ የኦርዮን ሚስት ነጥቋልና። እርሱንም ገድሎታልና ጥቅም የሌለው ብዙ ነገርንም መከራቸው እነርሱም እርሱ እንደ አባ ሙሴ መስሏቸው ይመልሱለት ነበር ።

ከዚህም በኋላ ሰይጣን እንደሆነ ለሊቅ ያዕቆብ #መንፈስ_ቅዱስ አስገነዘበው ደቀ መዛሙርቱንም የቁርባን ቅዳሴ እንዲቀድሱ አዘዛቸውና ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ ሰይጣን መሆኑን ለልጆቹ መነኰሳት ነገራቸው ።

ሁለተኛም በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አምሳል ወደርሳቸው መጣ ከእርሱም ጋር በኤጲስቆጶሳት አምሳል አሉ ። በደረሰም ጊዜ በላያቸው ተኰሳተረ ከዚህ ልትኖሩ ማን ፈቀደላችሁ ብሎ አወገዛቸው ሊቅ ያዕቆብም አይቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እጆቹን ዘርግቶ ጸሎትን አደረገ ። ወዲያውኑ ሰይጣን ተበተነ ግን መፈታተኑን አሁንም አልተወም በሚአስፈራ ዘንዶ አምሳልም ወደ አባ ያዕቆብ የሚመጣበት ጊዜ አለ ። በንጉሥ አምሳልም ደም ግባታቸው በሚያምር ደናግል አምሳልም በአሞራዎችና በቁራዎች አምሳልም ሁኖ በጥፍሮቻቸው ፊቱን እየነጩ በእንዲህ ያለ ፈተና ሰባት ዓመት ተፈተነ ከዚህም በኋላ ትዕግሥቱንና ድካሙን #እግዚአብሔር አይቶ መብረቅን ልኮ ሰይጣንን ቀጥቅጦ በተነው ያዕቆብ ሆይ ከአንተ የተነሣ ወዮልኝ በጸሎትህ አቃጠልከኝ እያለ ሸሸ ።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና #እግዚአብሔር አብዲን ወደሚባል ገዳም እንዲሔድ ሊቅ ያዕቆብን አዘዘው ። እርሱም ለልጆቹ መነኰሳት ይህን ነገራቸው ከዚያም ግንብ ውስጥ እንዲኖሩ አማፀናቸው ።

እርሱ ግን ብቻውን ወደ ኢያሪኮ ባሕር ዳርቻ ሔደ መርከብንም በአጣ ጊዜ በባሕሩ ሞገድ ላይ ባረከ ገብቶም ወደ ተርሴስ አገር እስከ ገባ ድረስ በባሕሩ ላይ እንደ ደረቅ ምድር ሔደበት ።

በሀገሩ ጥጋጥግ አልፎ ሲሔድ በትል የተከበበ ቁስለኛ ሰው አገኘና ሊቅ ያዕቆብ ስምህ ማነው ብሎ ጠየቀው እርሱም ስሜ እንጦኒ ነው አባቴም ለባለ መድኃኒቶች ብዙ ገንዘብ ሰጠልኝ ሊፈውሱኝ አልቻሉም ። መምህር ያዕቆብም ስለ ደዌው ተከዘ ጸሎትንም አድርጎ ሁለመናውን በመዳሰስ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ጤነኛ ሁን አለው ወዲያውኑ ዳነ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው ።

ከዚህም በኋላ ከረድኡ ጋር ሲጓዝ ሀገረ ዐምድ ደረሱ የንጉሥ አንስጦስን ልጅ እያሳበደ ራሱን በደንጊያ ሲደበድብ አገኙት እርሱን መያዝም የሚችል አልነበረም። ሊቅ ያዕቆብም ይዞ ያመጣለት ዘንድ ረድኡን አዘዘው በአቀረበለትም ጊዜ በከበረ #መስቀል ምልክት አማተበበትና ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ከሰውዬው ወጥቶ እንዲሔድ ሰይጣንን አዘዘው ። ያን ጊዜም በጥቁር ባርያ አምሳል ወጣ የንጉሡም ልጅ በከበረ ሊቅ ያዕቆብ ጸሎት ዳነ አባቱና ወገኖቹ ሁሉ በታላቅ ደስታ ደስ አላቸው ንጉሡም ለከበረ ሊቅ ያዕቆብ ብዙ ገንዘብ ሊሰጠው ወደደ እርሱ ግን አይሆንም አለ ምንም ምን አልተቀበለም ።

ክብር ይግባውና በ #እግዚአብሔርም ትእዛዝ አብዲን በሚባል አገር የገዳም አበ ምኔት ከሆነ ከአባ በርሳቦ ጋር ተገናኝተው በአንድነት ተጓዙ በጒዞ ላይም እያሉ እንጦኒ በሆድ ተቅማጥ በሽታ ታመመና በሦስተኛው ቀን አረፈ ቀበሩትም።

ስሟ አውርሳ ከሚባል አገር በደረሱ ጊዜ የአገረ ገዥውን ልጅ ታሞ አገኙት በሊቅ ያዕቆብም ጸሎት ዳነ መኰንኑም ልጁ እንደ ዳነ አይቶ በታላቅ ደስታ ደስ አለው እስከ ዕለተ ሞቱ ረድዕ ይሆነው ዘንድ ለከበረ ያዕቆብ ልጁን ሰጠው የልጁም ስም ፍቁር ነው ።

ወደ ሊቅ በርሳቦ ገዳምም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ተቀበሏቸው በብዙ ምስጋናም እየዘመሩ አስገቧቸው በዚያችም አገር ጎን የታነፀ የጣዖት ቤት አለ ስሙ ሰሚር የሚባል የፋርስ ንጉሥ በየዓመቱ እየመጣ ለጣዖታት በዓልን ያከብራል የከበረ ሊቅ ያዕቆብም መነኰሳቱን እንዲህ አላቸው እነሆ የፋርስ ንጉሥ እንደመጣ ሰምታችኋል የክብር ባለቤት ስለ ሆነ ክርስቶስ ስለ ስሙ ኑ ደማችንን እናፍስስ ።

መነኰሳቱም በዚህ ምክር እየተስማሙ ሳሉ የንጉሡ ጭፍሮች ወደዚያ ገዳም ደረሱ መነኰሳቱንም ጥቁር ልብስን ለብሰው አዩአቸውና እናንተ ምንድን ናችሁ ከአምልክትስ ማንን ታመልካለችሁ አሏቸው ። ቅዱሳን መነኰሳትም እንዲህ አሏቸው እኛ ከሰማያት የወረደውን በ #መንፈስ_ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል #ማርያም ሰው የሆነ የሕያው #እግዚአብሔርን ልጅ ክብር ይግባውና #ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እናመልከዋለን ጭፍሮችም ወደ ንጉሥ አቀረቧቸው ።

በደረሱም ጊዜ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ክርስቶስ ስም በንጉሡ ፊት ታመኑ ንጉሡም ሀገራቸውን መረመረ አባ በርሳቦም የእኔና የወንድሞቼ መነኰሳት አገራችንም ሮም ነው አለ ። አባ ያዕቆብም የእኔ አገር ግብጽ ነው አለ ንጉሡም የአባ ያዕቆብን ቃል ሰምቶ ሊገድለው አልፈለገምና ብቻውን ገለል እንዲያደርጉት አዘዘ ። ከግብጽ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ስላለው መነኰሳቱን ግን ደማቸው እስቲፈስ ገርፈው ከእሥር ቤት እንዲጥሏቸው አዘዘ የ #እግዚአብሔርም መልአክ ፈወሳቸው ።

በማግሥቱም ጤነኞች ሁነው በአገኛቸው ጊዜ ብዙ ሀብት እንደሚሰጣቸው ተስፋ ሰጣቸው እነርሱ ግን ቃሉን አቃለሉ ። ንጉሡም በወይን መርገጫ ውስጥ በማስረገጥ በግርፋት ጥርሶችን የእጆችንና የእግሮች ጥፍሮችን በማውለቅ ሰባት ቀኖችም ያህል አፍንጫን፣ ከንፈርን፣ ጆሮዎችን በመቆረጥ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ።

በስምንተኛውም ቀን ራሶቻቸውን ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ መምህራቸው ሊቅ በርሳቦም እየአንዳንዱን ለሰያፊ ከሰጣቸው በኋላ ዐሥሩ መነኰሳት ተቆረጡ የንጉሡ የፈረሶች ባልደራስ ያን ጊዜ ለቅዱሳኑ የወረዱትን አክሊሎች አየ ትጥቁንም ፈትቶ ጥሎ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ እርሱንም አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት መምህር በርሳቦም ልጆቹ ከተቆረጡ በኋላ አንገቱን ዘርግቶ ሰያፊውን የታዘዝከውን ፈጽም አለው ያን ጊዜም ሰያፊው ቆረጠው ምስክርነታቸውንም ነሐሴ ሃያ ስምንት ቀን ፈጸሙ።

ንጉሡም ሥጋቸውን በእሳት እንዲአቃጥሉ አዘዘ ምድርም ተከፍታ ሥጋቸውን ሠወረች ንጉሡም አፍሮ ወደ አገሩ ሊሔድ ወደደ ። ያን ጊዜም አባ ያዕቆብ ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ከሰማይም ከጠቆረ ደመና ጋርና ከሚከረፋ በረድ ጋር እሳት በንጉሡ ላይ ዘነመ ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ተቃጥሎ ጠፋ ከእነርሱ አንድ እንኳ አልቀረም ።

የዚያች አገር ሰዎችም በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወጥተው ፈረሶቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን ገንዘባቸውንም ወሰዱ ወደ ሊቅ ያዕቆብም አምጥተው እሊህን ገንዘቦች ለምትሻው ሥራ ውሰድ አሉት ። እርሱም አልተቀበላቸውም ግን በሰማዕታት መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ አዘዛቸው ቤተ ክርስቲያኒቱም እስከ ዛሬ አለች ።

ከዘመናትም በአንዲቱ አገር ቸነፈር ሆነ ወደ ሊቅ ያዕቆብ እንዲጸለይላቸው ላኩ እርሱም ሰምቶ እጅግ አዘነ ማዕጠንትም ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ረጅም ጸሎት ጸለየ ዕጣንንም አሳረገ ። ከዚያም ወጥቶ መልእክተኞችን አትፍሩ አትጨነቁ በሰላም ሒዱ አላቸው ። በደረሱም ጊዜ አገሪቱን ጤነኛ ሁና አገኟት ደስ ብሏቸው የሊቅ ያዕቆብን አምላክ አመሰገኑት ።

ዳግመኛም ለከበረ ሊቅ ያዕቆብ ዳንኤል የሚባል ረድእ ነበረው ደግሞ ለቅዱስ ያዕቆብ ወዳጁ የሆነ አገር ገዥ አለ ለአገረ ገዥውም ወደ ቅዱስ ያዕቆብ ከአባቷ ጋር የምትመጣ ብላቴና አለችው ረዱን ዳንኤልን በኃጢአት ልትጥለው ፈለገችው እምቢ ባላትም ጊዜ ከአባቷ አገልጋይ ፀነሰችና በሊቅ ያዕቆብ ረድእ አመካኘችበት አባቷም ሰምቶ መምህር ያዕቆብንና ደቀ መዝሙሩን ሊገድል ሔደ በጒዞ ላይም ሳለ በላዩ ከሰማይ መብረቅ ወርዶ ዐይኖቹን አሳወረው ።

የመኰንኑም ልጅ ከወለደች በኋላ ወደ ከበረ መምህር ያዕቆብ በጉባኤ መካከል ሕፃኑን አባትህ ማን እንደሆነ ትናገር ዘንድ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም አዝዝሃለሁ አለው ። ሕፃኑም አባቴ የእናቴ የአባቷ አገልጋይ እገሌ ነው አለ የተሰበሰቡትም ሕዝብ ሰምተው አደነቁ የተመሰገነ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ።

ከዚህም በኋላ ዕረፍቱ ሲቀርብ ደቀ መዝሙሩን እንዲህ ብሎ አዘዘው ከዚህ ዓለም የምለይበት ጊዜ ደርሷል በምሞትም ጊዜ ከአባ በርሳቦና ከልጀቹ ጋራ ቅበረኝ ይህንንም ብሎ በሦስተኛው ቀን አረፈ መላእክትም ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ነፍሱን በክብር አሳረጉ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቶማስ_ሰማዕት

በዚችም ቀን የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ በሕንደኬ አገር ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ ። ቶማስም በሕንድ አገር ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ለመሔድ በተነሣ ጊዜ ወደዚያች አገር መግባትን እንዴት እችላለሁ ብሎ አሰበ ። ይህንንም ሲያስብ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠለትና አትፍራ ቸርነቴ ከአንተ ጋር ትኖራለችና አለው።
ወዲያውኑ ከሕንደኬ የጎና ነጋዴ አቤኔስ መጣ #ጌታችንም ምን ትሻለህ አለው ነጋዴውም ሐናፂ የሆነ ባሪያ እሻለሁ አለ። ጌታም ይህን ባሪያዬን ገዝተህ ውሰድ እርሱ አናፂ ነውና አለው ከዚህም በኋላ በሦስት ወቄት ወርቅ ሸጠው እንዲህም ብሎ ጻፈለት የጠራቢ ዮሴፍ ልጅ የሆነ ባሪያዬን ለጎና ነጋዴ ለአቤኔስ ሸጨዋለሁ።

ከዚህም በኋላ አቤኔስ ቅዱስ ቶማስን ተረክቦ ወደ አገሩ ወሰደው ወደ ከተማውም በቀረቡና በደረሱ ጊዜ የእንዚራና፣ የመሰንቆ፣ የዛጉፍ፣ የእምቢልታ ድምፅ ሰምተው ይህ ምንድን ነው አሉ።

ሰዎችም ንጉሥ ለሴት ልጁ ሠርግ አዘጋጅቷል ወደ ንጉሡ ሠርግ ያልሔደውን እንዲቀጡት ንጉሥ አዟል አሏቸው። ይህንን ሰምተው አቤኔስና ቅዱስ ቶማስ ወደ ሠርጉ ሔዱ ሁሉም ሲበሉና ሲጠጡ ሐዋርያ ቶማስ ምንም አልቀመሰም በዚያም ዕብራዊት የሆነች አዝማሪ አለች ። በሠርጉ ምሳ ላይ ከሚያገለግሉ ውስጥ አንድ ሰው ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስን በጥፊ ፊቱን ጸፋው ሐዋርያውም በዕብራይስጥ ቋንቋ ይቺን እጅ ውሾች ሲጎትቷት አያታለሁ አለ አዝማሪዋም ብቻዋን ሰማችው።

ይህም በጥፊ የመታው ውኃ ሊቀዳ ወደ ውኃ ጉድጓድ ወረደ አንበሳም መጥቶ ገደለውና በታትኖ ተወው አንድ ውሻም የቀኝ እጁን ይዞ ወደ ምሳ መካከል ወሰዳት ከዚያ ያሉትም ማን ነው የሞተ አሉ ሰዎችም ይህን እንግዳውን በጥፊ የመታው ያ አሳላፊ ነው አሏቸው። አዝማሪዋም በሰማች ጊዜ ወደ ሐዋርያው ሒዳ በአጠገቡ ቁማ በጥፊ የመታችኝን እጅ ውሾች ሲጎትቷት አያታለሁ ሲል እኔ ስምቼዋለሁ አለች በዚያ ያሉትም ሁሉ ይህን ሰምተው አደነቁ።

ይህም ነገር በንጉሡ ዘንድ በተሰማ ጊዜ ንጉሡ ወደ ሐዋርያው መጥቶ ዛሬ አጋብቻታለሁና ና በልጄ ላይ ጸሎት አድርግ አለው። ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ወደ ጫጒላ ቤት ገብቶ ስለ ሙሽሮቹ ወደ #ጌታችን ጸለየ የሃይማኖትንም ቃል አስተምሮ ባረካቸው በሐዋርያውም ቃል አመኑ ። #ጌታችንም ደግሞ በቶማስ አምሳል ተገልጦላቸው እርሱም ሃይማኖትን አስተማራቸው እነርሱም አመኑበት ጽምረታቸውንም ትተው ድንግልናቸውን ጠበቁ ንጉሥም ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

#መስከረም_18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
5.ቅድስት እሌኒ ንግሠት
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ መርቆሬዎስ ካልዕ (ሰማዕት)
8.ቅዱስ ቶማስ ሰማዕት
9.ቅዱስ ኤፍሬም ሰማዕት
10.አባ ፊልሞስ
11.ቅዱስ ሰልሖን ሰማዕት
12.ቅዱስ አክሳኤልስ ሰማዕት
13.ቅዱስ ይስሐቅ ሰማዕት
14.ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀሲስ
15.ቅዱስ ነኪጣ ሰማዕት
16.አባ ፊላታውዎስ መንክራዊ
17.አባ ኖብ ባሕታዊ
18.አባ አትናቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
19."60" ሰማዕታት (ማሕበረ ቅዱስ አቦሊ)
20.ሊቁ አባ ዳንኤል (ኢትዮጵያዊ)

#ወርሐዊ_በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

" እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም #ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: " (ማቴ. 5:13-16)

#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር


(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_18)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 10
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና።
¹² በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤
¹³ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።
¹⁴ እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?
¹⁵ መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?
¹⁶ ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና።
¹⁷ እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።
¹⁸ ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦ ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።
¹⁹ ነገር ግን፦ እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ፦ እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ብሎአል።
²⁰ ኢሳይያስም ደፍሮ፦ ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ።
²¹ ስለ እስራኤል ግን፦ ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥
¹⁵ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ።
¹⁶ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
¹⁷ እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤
¹⁸ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 14
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ ከዚያም ስለ ፈጸሙት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ።
²⁷ በደረሱም ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ሰብስበው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ ለአሕዛብም የሃይማኖትን ደጅ እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ።
²⁸ ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_18_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አንተ ትኴንን ኃይለ ባሕር። ወአንተ ታረምሞ ለድምፀ ማዕበላ። አንተ አኅሠርኮ ለዕቡይ ከመ ቅቱል"። መዝ 88፥9-10።
"የባሕርን ኃይል አንተ ትገዛለህ፥ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ። አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው፥ በኃይልህም ክንድ ጠላቶችህን በተንሃቸው"። መዝ 88፥9-10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_18_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት?
⁹ ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ፦ የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች።
¹⁰ እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ዕፀ መስቀል፣ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ የአቡነ አኖሬዎስ፣ የቅዱስ መርቆሬዎስ የቅዱስ ሊቅ ያዕቆብና የቅድስት ጸበለ ማርያም የዕረፍት፣ የቅዱስ ቶማስ የተዓምር በዓልና የሁሉም ቅዱሳን በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2024/09/28 03:43:08
Back to Top
HTML Embed Code: