Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ገላትያ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤
² እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው።
³ ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤
⁴ ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።
⁵ የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።
⁶ አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥
⁷ ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤
⁸ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና።
⁹ ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤
¹⁰ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።
¹¹ ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።
¹² አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ።
¹³ የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቆላስይስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ጌቶች ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና ለባሪያዎቻችሁ በጽድቅና በቅንነት አድርጉላቸው።
² ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ፤
³ በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤
⁴ ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ።
⁵ ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ።
⁶ ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን።
⁷ የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ ቲኪቆስ ኑሮዬን ሁሉ ያስታውቃችኋል፤
⁸-⁹ ወሬያችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና፥ ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም ከአናሲሞስ ጋር ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው፤ የዚህን ስፍራ ወሬ ሁሉ ያስታውቁአችኋል።
¹⁰-¹¹ ከተገረዙት ወገን ያሉት፥ አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ ስለ ማርቆስ፦ ወደ እናንተ ቢመጣ፥ ተቀበሉት የሚል ትእዛዝ ተቀበላችሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከእኔ ጋር አብረው የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፥ እኔንም አጽናንተውኛል።
¹² ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል።
¹³ ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና።
¹⁴ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁵ በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን።
¹⁶ ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ፤ ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ።
¹⁷ ለአክሪጳም፦ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ።
¹⁸ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤
²⁴ ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ።
²⁵ በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ፤
²⁶ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።
²⁷ በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤
²⁸ ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ።
²⁹ ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤
³⁰ እንዲህም ደግሞ አደረጉ፥ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ 44፥9-10።
"የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች። ልጄ ሆይ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ"፤ መዝ 44፥9-10።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።
¹⁸ ዘካርያስም መልአኩን፦ እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው።
¹⁹ መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤
²⁰ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው።
²¹ ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር።
²² በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ።
²³ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ።
²⁴-²⁵ ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፦ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች።
²⁶ በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥
²⁷ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።
²⁸ መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።
²⁹ እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች።
³⁰ መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።
³¹ እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።
³² እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤
³³ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።
³⁴ ማርያምም መልአኩን፦ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ በርናባስ የዕረፍት በዓልና የነቢያት የገና (ጾም) ጊዜ  ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_22

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
#ቅዱስ_ገብርኤል_እመቤታችንን ያበሰረበት መታሰቢያ ነው፣ የመላእክት አለቃ #የቅዱስ_ገብርኤል ዳህና በሚባል አገር ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራችበት ነው፣ #የብርሃን_እናቱ_ድንግል_ወላዲተ_አምላክ ለወዳጇ #ለቅዱስ_ደቅስዮስ ሰማያዊ ወንበርና ልብስ የሰጠችበት እና የዕረፍቱ ዕለት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ብሥራተ_ቅዱስ_ገብርኤል

ታኅሣሥ ሃያ ሁለት በዚህች ዕለት ብርሃናዊው መልአክ #ቅዱስ_ገብርኤል#እመቤታችን አምላክን እንደምትወልድ ያበሰረበት መታሰቢያ ነው፡፡ ይኸውም ‹‹ልዑል #እግዚአብሔር ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ‹ሂድና ለጽዮን ልጅ ለ #ድንግል#እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ወደ አንቺ መጥቶ ኃይለ ልዑል #ወልድ ሥጋሽን ለብሶ ሰው ይሆናል፤ ይኸውም ካንቺ የሚወለደው ጽኑዕ ነው ብለህ ንገራት› አለው፡፡ ‹ደንቆሮዎች የሚሰሙበት፣ ድዳዎቸ የሚናገሩበት፣ ዕውራንም የሚያዩበት፣ ሙታን የሚነሡበት፣ ለምጻሞች የሚነጹበት፣ ሐንካሳዎች የሚሄዱበት፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ብርሃን የሚያዩበት ጊዜ እነሆ ደረሰ ብለህ ንገራት› አለው፡፡

ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ በግንባሩ ተደፍቶ ልዑል #እግዚአብሔርን ‹ጌታ ሆይ! የምትነግረኝ ይደረግ ዘንድ እንደምን ይሆናል?› አለው፡፡ #ጌታም ‹የጀመርኩትን ቸርነት ፈጸምኩ፣ የወይን ግንድ ይቆረጣል (ወልደ #እግዚአብሔር ይሞታል)፣ ወይራም ከበለስ ጋር ይተከላል ( #መስቀል ይተከላል)፣ ቅጽሮችም ይቀጸራሉ (ምግባር ከሃይማኖት ጋር ይሠራል)፣ የኤልፍና የሌሚ ወገን ይነሣል፡፡ ገብርኤል ሆይ! ሄደህ ለዳዊት ልጅ ‹ #እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ› ብለህ አብሥራት› አለው፡፡ ‹ለዘለዓለም ነግሦ የሚኖረውን እነሆ ትፀንሳለሽ በላት› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ሰገደ፡፡ ልብሱንም በላዩ ይዞ በ #መስቀል ቀኝ ይወርድ ዘንድ ወደደ፡፡ ጌታም ‹መግባትህና መውጣትህ በፍቅር አንድነት ይሁን› አለው፡፡ ‹ዘካርያስን ረግመህ አንደበቱን እንዳሰርህ እርሷን እንዳታሳዝናት ይልቁንም አብዝተህ ደስ አሰኛት አንጂ› አለው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ይህን ሰምቶ ፈጽሞ ደስ እያለው ሊባኖስ ከሚባል ተራራ እስኪሰማ ድረስ ክንፉን እያማታ ወረደ፡፡ በዚህም ጊዜ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ‹ይህ የምንሰማው ምንድነው?› ይሉ ነበር፡፡ የተደረገበትንም ቦታ አላወቁትም ነበር፡፡››
#እመቤታችንን በ3 ዓመቷ እናትና አባቷ ብፅዓት አድርገው ለ #እግዚአብሔር ሰጥተዋታልና ካህናትም በቤተ መቅደስ ከመካነ ደናግል አስገብተዋት በመልአኩ በቅዱስ ፋኑኤል አማካኝነት ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመጣላት ያንን እየተመገበች ቅዱሳን መላእክት እየጎበኟት 12 ዓመት ኖራለች፡፡ በ15 ዓመቷ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ለ #እመቤታችን #ጌታችንን እንደምትወልድ በዚህች ዕለት አብሥሯታል፡፡ በመጀመሪያ #እመቤታችን ውኃ ቀድታ ስትመለስ የጠተማ ውሻ እያለከለከ ሲመጣ ብታየው ለፍጥረት ሁሉ የምትራራ ናትና በወርቅ ጫማዋ ለዛ ለተጠማው ውሻ ውኃ ስታጠጣ አብሯት የነበሩ ሴቶች ‹‹ማድጋሽን አጎደልሺው፣ ቀድቼ እሞለዋለሁ እንዳትይ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው መቅጃም የለሽም›› አሏት፡፡ ክብርት #እመቤታችንም ‹‹ውሃ የሚገኘው ከወደላይ ነው እንጂ ከወደታች ነውን? ፍጥረቱን ያጠጣ #ጌታ ይሞላልኛል›› አለቻቸው፡፡ ማድጋዋም በተአምራት ሞልቶ ተገኘ፡፡ ሴቶቹም ዳግመኛ ‹‹በዚህ ዘመን አምላክ ከድንግል ይወለዳል ይላሉ ካንቺ ይሆን?›› እያሉ ሲዘብቱባት ወዲያው ከወደኋላዋ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› አላት፡፡ #እመቤታችንም ዞር ብትል የተናገራትን አጣችው፡፡ በዚህም ጊዜ ‹‹አባቴን አዳምን እናቴን ሔዋንን ያሳተ ጠላት ይሆናል›› ብላ ሄደች፡፡
ዳግመኛም #እመቤታችን ከቤት ደርሳ ማድጋዋን ስታስቀምጥ መልአኩ አሁንም በድምፅ ‹‹እነሆ ትጸንሻለሽ›› አላት፡፡ #እመቤታችንም ይህን ጊዜ ‹‹ምነው ይህስ ነገር ደጋገመኝ እንዲህ ያለውን ነገር ቤተ መቅደስ ሄደው ሊረዱት ይገባል›› ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዳ ወርቅና ሐር እያስማማች ስትፈት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እሁድ ቀን በ3 ሰዓት በገሃድ ተገለጸላትና እጅ እየነሳ እየሰገደ አበሠራት፡፡ ‹‹የዕውነተኛ ንጉሥ እናቱ #እመቤታችን ላንቺ ፍቅር አንድነት ይባል›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹አንቺ ከሴቶች ይልቅ ተለይተሸ ንዕድ ክብርት ነሽ›› አላት፡፡ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት #እመቤታችንም የብርሃናዊውን መአልክ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል በሰማች ጊዜ ‹‹እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን ይቀበሏል! እንዴትስ መቀበል ይቻላል? እንጃ›› አለችው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ #ማርያም_ሆይ! መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፣ ኃይለ ልዑል #ወልድም ሥጋሽን ይለብሳልና አይዞሽ አትፍሪ›› አላት፡፡ ዳግመኛም ‹‹ይህ ካንቺ የሚወለደው ጽኑ ከሃሊ ነው፡፡ ስሙንም #ኢየሱስ ትዪዋለሽ፣ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፣ #ጌታ_አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም›› አላት፡፡ #እመቤታችንም መልአኩን ‹‹ምድር ያለ ዘር ፍሬን አትሰጥምና እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?›› አለችው፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹ #መንፈስ_ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የ #እግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እርሷ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፡፡ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፣ ለ #እግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› አላት፡፡ ክብርት #እመቤታችንም ይህን ጊዜ ‹‹እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› አለችው፡፡ መልአኩም ከእርሷ ዘንድ ሄዶ ተሠወረ፡፡ አካላዊ ቃልም በማኅፀኗ አደረ፡፡ በዚያችም ቅጽበት የ #እመቤታችን የፊቷ መልክ ተለወጠ፣ እንደፀሐይም አሸበረቀ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ድንግል #ማርያም አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ገብርኤል

በዚች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የ #ቅዱስ_ገብርኤል የበዓሉ መታሰቢያ ዳህና በሚባል አገርም ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራችበት ተአምራትም ያሳየበትና በዚች ቀን ቤተ ክርስቲያኒቱ የከበረችበት ነው የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ አርኬላዎስ ምስክር የሆነበት ነው።

ይህም መልአክ ስለ ወልደ #እግዚአብሔር ሰው መሆን ምሥጢር የታመነ ሆኖ ወደ እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም የተላከ "የደስታ መገኛ ደስ ይበልሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ #እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው አንቺም ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ" አላት።

ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መወለድም ካህኑን ዘካርያስን ያበሠረው እርሱ ነው ይህ መልአክ እጅግ የከበረ የተመረጠ ገናና የሆነ ነውና ስለ እኛ ወደ #እግዚአብሔር ይማልድ ዘንድ ልባችንን አንጽተን ወደዚህ የከበረ መልአክ እየለመንን መታሰቢያውን ልናደርግ ይገባል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ መልአክ አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ደቅስዮስ
በዚህችም ዕለት ዳግመኛ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት #እመቤታችንን የከበረ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ባበሠራት መሠረት ቅዱስ ደቅስዮስ በዓልን ያደረገበት እና ቅዱስ ደቅስዮስ ያረፈበት ዕለት ነው፡፡ በዓልን የማክበሩ ምክንያትም እንዲህ ሆነ፡- መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል #እመቤታችንን ያበሠራትና የ #ጌታችንም ፅንሰት የተከናወነው በመጋቢት ወር በ29ኛው ቀን በዕለተ እሁድ በ3 ሰዓት ነው፡፡ ታዲያ ምነው በታኅሣሥ 22 ብሥራቱና ፅንሰቱ ተከበረ? ቢሉ መጋቢት 29 ቀን ሰሙነ ሕማማት ላይ ይውላልና በዚህ ወቅት ደግሞ ፍጹም ሐዘን ልቅሶ ጾም ጸሎት ይያዛል እንጂ ደስታ ፌሽታ እልልታ ጭብጨባ የለም፡፡ ዓቢይ ጾም ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፡፡ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበር ስህተት ነው፤ የአባቶችንም ሥርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ምስጋና ይድርሳቸውና ቅዱሳን አባቶቻችን ሁሉንም ነገር በሥርዓት በሥርዓቱ አድርገው ሰፍረው ቆጥረው አስቀምጠውልናል፡፡ ከዓቢይ ጾም በኋላ ያሉትን 50 ቀናት ረቡዕና ዓርብንም ጭምር ሥጋ እንኳን እንድንበላ ነው ሥርዓት የሠሩልን፡፡ አባቶቻችን የሠሯት ሕግ ፍጽምት ናት፡፡ በዚህም መሠረት አባቶቻችን ሥርዓትን ሠሩልንና የመጋቢት 27 የ #ጌታችንን የስቅለቱን በዓል ወደ ጥቅምት 27 ቀን አምጥተው እንዲሁም የመጋቢት 5 የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን የዕረፍት በዓል ወደ ጥቅምት 5 ቀን አዙረው እንዲከበር አድርገዋል፡፡ የመጋቢት 29 የብሥራቱን በዓል ደግሞ ወደ ታኅሣሥ 22 ቀን አዙረውት በዚህ ዕለት እንዲከበር አድርገውታል፡፡ አንድም ነገረ ልደቱን ከማክበር አስቀድሞ ነገረ ፅንሰቱን ማዘከር ማክበር ተገቢና መሆንም ያለበት ነውና ነው፡፡ ይህንንም ያደረገው ታላቁ አባት ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ በ #እመቤታችን ፍቅር ልቡ የነደደው ይህ ታላቅ አባት የ #እመቤታችንን ተአምራቶቿን የጻፈላትም እርሱ ነው፡፡ እርሱም ከፍቅሩ ጽናት የተነሣ የ #እመቤታችንን የተአምራቷን መጽሐፍ ሰብስቦ አዘጋጀ፡፡

አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት #እመቤታችንም ተገለጸችለትና መጽሐፉን በእጇ አንሥታ ይዛ ‹‹ወዳጄ ደቅስዮስ ሆይ! ይህን መጽሐፍ ስለጻፍክልኝ ባንተ ደስ አለኝ፣ አመሰገንኩህ፣ እንዳከበርከኝ እኔም አከብርሃለው›› አለችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሱ ተሠወረች፡፡ ደቅስዮስም #እመቤታችንን ከመውደዱ የተነሣ ፈጽሞ ደስ አለው፡፡ ፍቅሯም እንደ እሳት አቃጠለው፡፡ የእርሷን ክብር አብዝቶ ይጨምር ዘንድ ምን እንደሚያደርግ የሚሠራውን ያስብ ጀመር፡፡

ከዚህም በኋላ በዚያን ጊዜ ጾም ስለነበር ሰዎች አስቀድመው ሊያከብሩት ያልተቻላቸውን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ባበሠራት ቀን በዓሏን አከበረ፡፡ እርሱም የከበረ የሚሆን የልደትን በዓል ከማክበር አስቀድሞ በ8 ቀን አደረገ፡፡ ይኸውም ታኅሣሥ በባተ በ22ኛው ቀን ነው፡፡ ይኽችውም ሥርዓቱ እስካሁን ጸንታ ኖራለች፡፡ ሰዎቹም በዓሉን ባከበሩ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናቸ ክብርት #እመቤታችን በእጇ የከበረ ልብስ ይዛ ዳግመኛ ለቅዱስ ደቅስዮስ ተገለጸቸለትና ‹‹አገልጋዬ የሆንክ ወዳጄ ደቅስዮስ ሆይ! በዕውነት አመሰገንኩህ፣ በአንተ ደስ አለኝ፣ ሥራህንም ወደድኩ፡፡ በእኔም ደስ እንዳለህና የከበረ መልአክ ገብርኤል እኔን በአበሠረበት ቀን በዓሌን ስላከበርክ ሰውንም ሁሉ ስለእኔ ደስ ስላሰኘህ እኔም ዋጋህን ልሰጥህ መጥቻለሁ፤ አንተ በዚህ ዓለም እንዳከበርከኝ እኔም በሰው ሁሉ ፊት አከብርህ ዘንድ እወዳለሁ›› አለችው፡፡ ይህንንም ካለችው በኋላ ‹‹እርሷን ትለብስ ዘንድ ይህችን ልብስ እነሆ አመጣሁልህ፤ በላዩም ትቀመጥ ዘንድ ይህን ወንበር አመጣሁልህ ፡፡ ከሰው ወገን አንድ ስንኳ ይህችን ልብስ ሊለብሳት በዚህችም ወንበር ላይ ሊቀመጥ የሚቻለው የለም፡፡ ይህንን ነገሬን የሚተላለፍ ቢኖር እኔ እበቀለዋለሁ›› አለችውና ሰማያዊ ልብስና ሰማያዊ ወንበር ሰጠችው፡፡ #እመቤታችንም ይህንን ተናግራ ከባረከችው በኋላ ከእርሱ ተሠወረች፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ደቅስዮስ በዚሁ በዓለ ብሥራትን ባከበረበት ዕለት ታኅሣሥ 22 ቀን ካረፈ በኋላ አንድ ሌላ ኤጲስቆጶስ በተሾመ ጊዜ #እመቤታችን ለቅዱስ ደቅስዮስ የሰጠችውን ልብስ ለበሰ፣ በወንበሩም ላይ ተቀመጠ፡፡ ሰዎችም ይህን አይተው ‹‹እባክህ ይቅርብህ #እመቤታችን እንዲህ ብላ ተናግራለችና›› ቢሉት በመታጀር ‹‹እርሱም (ደቅስዮስም) ሰው እኔም ሰው፣ እርሱም ኤጲስቆጶስ እኔም ኤጲስቆጶስ›› ብሎ በትዕቢት ተናገረ፡፡ በወንበሩም ላይ እንደተቀመጠ ወድቆ ሞተ፡፡ ይህንንም ያዩ ሁሉ ከ #እመቤታችን ተአምር የተነሣ አደነቁ፡፡ እጅግም ፈርተው #እመቤታችንን አከበሯት፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ ለቅዱስ ደቅስዮስ የተለመነች ክብርን የተመላች ድንግል ወላዲተ አምላክ ለእኛም ትለመነን! አምላካችን ልጇ በምልጃዋ ይማረን!

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_22 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጢሞቴዎስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤
⁹ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥
¹⁰-¹¹ አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።
¹² ስለዚህም ምክንያት ይህን መከራ ደግሞ ተቀብዬአለሁ፥ ነገር ግን አላፍርበትም፤ ያመንሁትን አውቃለሁና፥ የሰጠሁትንም አደራ እስከዚያ ቀን ድረስ ሊጠብቅ እንዲችል ተረድቼአለሁ።
¹³ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ፤
¹⁴ መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።
¹⁵ በእስያ ያሉቱ ሁሉ ከእኔ ፈቀቅ እንዳሉ ታውቃለህ፥ ከእነርሱም ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ናቸው።
¹⁶ ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤
¹⁷ በሰንሰለቴም አላፈረበትም፥ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ፤
¹⁸ በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደኅና ታውቃለህ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።
¹⁰ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።
¹¹ ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።
¹² እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።
¹³ ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን።
¹⁴ እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።
¹⁵ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።
¹⁶ እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።
¹⁷ በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።
¹⁸ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር።
⁷ እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና፦ ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ።
⁸ መልአኩም፦ ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ።
⁹ ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም።
¹⁰ የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ።
¹¹ ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ።
¹² ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ።
¹³ ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤
¹⁴ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች።
¹⁵ እነርሱም፦ አብደሻል አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ መልአኩ ነው አሉ።
¹⁶ ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ።
¹⁷ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና፦ ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሩ አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ። ወትሠይም(ሚ)ዮሙ መላእክተ በኵሉ ምድር። ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ"። መዝ. 44፥16-17።
"በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ። ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፤ ስለዚህ ለዓለምና ለዘላለም። አሕዛብ ይገዙልሃል"። መዝ. 44፥16-17።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁹ ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥
⁴⁰ ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት።
⁴¹ ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥
⁴² በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።
⁴³ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?
⁴⁴ እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።
⁴⁵ ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።
⁴⁶ ማርያምም እንዲህ አለች፦
⁴⁷ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
⁴⁸ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
⁴⁹ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።
⁵⁰ ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
⁵¹ በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤
⁵² ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
⁵³ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
⁵⁴-⁵⁵ ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።
⁵⁶ ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች።
⁵⁷ የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የብስራት ቅዱስ ገብርኤል በዓል፣ የቅዱስ ደስቅዮስ የዕረፍት በዓልና የነቢያት (የገና) የጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_23

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት #ልበ_አምላክ_ቅዱስ_ዳዊት ዐረፈ፣ ቅዱሳን አባቶቻችን #አባ_ሳሙኤል#አባ_ስምዖንና #አባ_ገብርኤል ዕረፍታቸው ነው፣ የከበረ #አባ_ጢሞቴዎስ_ገዳማዊ ዕረፍቱ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ልበ_አምላክ_ቅዱስ_ዳዊት

ታኅሣሥ ሃያ ሦስት በዚህች ዕለት ልበ አምላክ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ዐረፈ፡፡ ይህም ንጉሥ ዳዊት በ #እግዚአብሔር ፊት መልካም ጒዞን የተጓዘ ከእራኤልም ነገሥታት ሁሉ እውነተኛ ፍርድን ያደረገ ነው እርሱም አገሩ ቤተልሔም የሆነች ከይሁዳ ነገድ ነው ሳኦልም የ #እግዚአብሔር ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ለእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ መረጠው ነቢይ ሳሙኤልንም ቅብዐ መንግሥትን የእሴይን ልጅ ይቀባ ዘንድ ላከው። ሳሙኤልም ታላቁን ኤልያብን ተመለከተ መልኩ ያማረ አካሉም የጸና ነበርና #እግዚአብሔር ግን አልመረጠውም። "የኤልያብ ፊቱን አትይ የመልኩንም ማማር አትመልከት #እግዚአብሔር ሰው እንደሚያይ የሚያይ አይደለምና" አለው እንጂ "ሰው መልክ ያያል #እግዚአብሔር ግን ልብን" ያያል።

ከእሴይ ከሰባቱ ልጆች በኋላ ነቢይ ሳሙኤል ዳዊትን በእስራኤል ልጆች ላይ ይነግሥ ዘንድ ቀባው #እግዚአብሔርም በሥራው ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆነ። ከልቡናው ንጽሕና ከየዋህነቱም ብዛት የተነሣ ጠላቱን ሳኦልን ብዙ ጊዜ ሲያገኘው በላዩ ምንም ምን ክፉ ነገር አላደረገበትም። በአንዲትም ዕለት ሳኦል ከእስራኤል ሁሉ የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ዳዊትን ከሰዎቹ ጋር ይፈልገው ዘንድ ዋሊያዎች ወደሚታደኑበት ሔዶ በጐዳና አጠገብ ያሉ ዘላኖችም ወደሚሠማሩበት ደረሰ በዚያም ዋሻ ነበር ሳኦልም ይናፈስ ዘንድ ወደዚያች ዋሻ ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ዳዊትም ተነሥቶ ቀስ ብሎ ከልብሱ ጫፍ ቆረጠ። በሁለተኛም ጊዜ በድንክ አልጋ ላይ ተኝቶ ወዳለበት ከአቢሳ ጋር ገብቶ ከራስጌው ጦሩንና ውኃ ያለበትን ረዋቱን ይዞ ተመልሶ ሔደ ክፉ ነገርንም አላደረገበትም ሰዎቹም ጠላትህ ሳኦልን ግደለው በአሉት ጊዜ #እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ልዘረጋ አይገባኝም ብሎ መለሰላቸው።

ስለ ሳኦልም መገደል አንድ ሰው በነገረው ጊዜ ዳዊትም "ያንን ሰው ማን ገደለው" አለው ሰውዬውም "እኔ ገደልሁት" አለው ዳዊትም እጅግ አዘነ ልብሱንም ቀደደ ያንንም ሳኦልን እኔ ገደልሁት ያለውን ሰው ገደለው። #እግዚአብሔር በዚህ በጻድቅ ዳዊት ልብ ብዙ ትሩፋትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ቅንነትን፣ ትዕግሥትን ፍቅርን አከማቸ ክብር ያለው ንጉሥ ሲሆን ራሱን ውሻ ትል እንስሳም አድርጎ ይጠራል ስለዚህም ከምድር ነገሥታት ሁሉ ከፍ ከፍ አደረገው እንዲህም ብሎ አመሰገነው "የእሴይን ልጅ ዳዊትን እንደ ልቤ ሆኖ አገኘሁት ፈቃዴን ሁሉ የሚያደርግ ታማኝ ሰው ነው"።

#እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች ኢየሩሳሌምንም ስለ ዳዊት ደግነት ብዙ ጊዜ ጠበቃቸው እርሱ ካለፈ በኋላም በነቢያቶቹ አንደበት አከበረው ነገሥታትንም ከእርሱ ዘር አደረገ። እርሱም በሁሉ ዓለም የታወቀ የመዝሙሩን መጽሐፍ ደረሰ ይኸውም በሰይጣናት ላይ ጋሻና ጦር የሆነ መልካም ቃልንም የተመላ በሰማይና በምድርም ያሉ በእርሱ #እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ነው።

ቅዱስ ዳዊትም ፊቱ እንደ ሮማን ቀይ ነው ቁመቱም መካከለኛ የሆነ አካሉም የጸና ብርቱ ነበር ታናሽ ብላቴናም ሁኖ ሳለ እርሱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ አንበሳ ወይም ተኵላ መጥቶ ከመንጋው ውስጥ በግ ነጥቆ በሚወስድ ጊዜ ተከትሎ ገድሎ ከአፉ ያስጥለው ነበር ሊጣላውም ቢነሣበት ጒረሮውን ይዞ ይሠነጥቅዋል። ከፍልስጥዔማውያንም ጋራ ሰልፍ በሆነ ጊዜ ብርቱ ሰው ስሙ ጎልያድ የሚባል ከጌት ሰዎች የተወለደ ቁመቱ ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ ከኢሎፍላውያን ሰፈር ወጣ። በራሱ ላይ የነሐስ በርቦርቴ ደፍቷል የነሐስ ጽሩርም ለብሷል በርሱ ላይ ያለ የብረቱና የነሐሱ ሁሉ ሚዛኑ አምስት ሽህ ወቄት ነበር። በእግሮቹ ባቶችም ላይ የነሐስ ሰናፊል ታጥቆ ነበር በጫንቃውም መካከል የነሐስ እባቦች ነበሩ። የጦሩም ዛቢያ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ሁኖ በላዩ ሽቦ ነበረበት የጦሩም ብረት መጠን ስድስት መቶ ወቄት ነበር ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሔድ ነበር።

ቁሞም ወደ እስራኤል ሰፈር ይጮህ ነበር "ከእኛ ጋር ትዋጉ ለምን ወጣችሁ እኔ የኤሎፍላውያን ወገን ነኝ ከእናንተ የሳኦል ባሮች አይደላችሁምን ከእናንተ አንድ ሰው መርጣችሁ ወእኔ ይውረድ ከእኔ ጋር መዋጋት ችሎ ቢገድለኝ ባሮች እንሆናችኋለን እኔ ከርሱ ጋራ ችዬ ብገድለው እናንተ ባሮች ሁናችሁ ትገዙልናላችሁ" አላቸው። ያም ኢሎፍላዊ ለወገኖቹ "ዛሬ በዚች ቀን አንድ ሰው ስጡኝና ሁለታችን ለብቻችን እንደዋጋ ብሎ የእስራኤልን አርበኞች እነሆ ተገዳደርኳቸው" አላቸው። እስራኤል ሁሉና ሳኦልም ይህን የኢሎፍላዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ ደነገጡ እጅግም ፈሩ የእራኤልንም ወገኖች እንዲህ እየተገዳደራቸውና እየተመካባቸው አርባ ቀኖች ያህል ኖረ ከእስራኤልም ወገን ወደርሱ ይወጣ ዘንድ የደፈረ የለም።

በዚያም ወራት ቅዱስ ዳዊት ወንድሞቹን ሊጐበኝ ወጣ ያንንም የኢሎፍሊ ወገን የሆነ ሰው የ #እግዚአብሔር ወገኖችን ሲገዳደራቸው በአየው ጊዜ አምላካዊ ቅናትን ቀና ሳኦልንም እንዲህ አለው "እኔ ሔጄ ይህን ያልተገረዘ ቈላፍ ገድዬ ዛሬ ከእስራኤል ሽሙጥን አርቃለሁ። ሕያው የሚሆን የ #እግዚአብሔርን አርበኞች ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ቁም ነገር ነው ከድብ አፍና ከአንበሳ አፍ ያዳነኝ እርሱ #እግዚአብሔር ከዚህ ካልተገረዘ ኢሎፍላዊ እጅ ያድነኛል"። ሳኦል "ሒድ #እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው። ዳዊትም ወንጭፋን በእጁ ያዘ ከወንዝ መካከልም ሦስት ደንጊያዎችን መረጠና ወደዚያ ኢሎፍላዊ ሔደ። ጎልያድም ዳዊትን በአየው ጊዜ ናቀው እንዲህም አለው "ደንጊያና በትር ይዘህ ወደኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ውሻ ነኝን" ዳዊትም "ከውሻ የምትሻል አይደለህም ከውሻ ትብሳለህ እንጂ" ቈላፍ ጎልያድም ዳዊትን በጣዖቶቹ ስም ረገመው።

ያም ኢሎፍላዊ ዳዊትን "ወደ እኔ ና ሥጋህን ለሰማይ ወፎችና ለዱር አራዊት እሰጣሁ" አለው ዳዊትም ያንኑ ኢሎፍላዊ "አንተ ጦር ሰይፍና ጋሻ ይዘህ ወደኔ ትመጣለህ እኔ ግን አሸናፊ በሚሆን በ #እግዚአብሔር ስም ወዳንተ እመጣለሁ። ዛሬ የእስራኤልን አርበኞች የተገዳደርክ አንተን ዛሬ #እግዚአብሔር በእጄ ይጥልሃል እገድልህምአለሁ ራስህንም እቆርጣለሁ የኢሎፍላውያን ሠራዊት ሬሳና ያንተን ሬሳ ዛሬ ለዱር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እሰጣለሁ ሰዎችም ሁሉ #እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ ሠራዊትም ሁሉ #እግዚአብሔር በጦርና በሰይፍ የሚያድን እንዳይደለ ያውቃሉ ድል የ #እግዚአብሔር ገንዘብ ነውና"።

ቅዱስ ዳዊትም እጁን ወደ ድጉ ሰዶ አንዲት ደንጊያ አውጥቶ ወነጨፋት ያንንም ኢሎፍላዊ ግንባሩን ገመሰው ያቺም ደንጊያ ከግንባሩ ገብታ ናላውን በጠበጠችው በምድር ላይም በግንባሩ ተደፋ። ዳዊትም ሩጦ የገዛ ሰይፉን አንሥቶ ራሱን ቆረጠው ከእስራኤልም ልጀጆች ስድብን አራቀ። ቅዱስ ዳዊትም መላው ዕድሜው ሰባ ነው መንግሥትን ሳይዝ ሠላሳ ዓመት ኖረ ከያዘ በኋላ አርባ ዓመት ኖረ። የክብር ባለቤት #ኢየሱስ_ክርስቶስ በሥጋ ከመምጣቱ በፊት በሽህ አንድ መቶ ሃያ ዓመት ውስጥ ትንቢት የተናገረበት ዘመን ነው በሰላምም ዐረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነብዩ ቅዱስ ዳዊት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ሳሙኤል_አባ_ስምዖንና_አባ_ገብርኤል
በዚህች ዕለት የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን አባ ሳሙኤል፣ አባ ስምዖንና አባ ገብርኤል ዕረፍታቸው ነው፡፡
አባ ሳሙኤል የተባለው ይኽም ቅዱስ ባሕታዊ ሆኖ ቀርጣሚን በምትባል አገር የሚኖር ነው፡፡ በዚያም አቅራፎስ የሚባል ሰማዕት ዐፅም ስለነበር ከእርሱ በረከትን እየተቀበለ እየተሳለመ ይኖር ነበር፡፡ ሰሊባ የሚባል አንድ መኮንን ነበር፡፡ እርሱም ስምዖን የሚባል ልጅ አለው፡፡ ልጁም ለሞት በሚያበቃ ጽኑ ሕማም ታመመ፡፡ መኮንኑ በልጁ ላይ ይጸልይ ዘንድ ወደ አባ ሳሙኤል ላከ፡፡ ነገር ግን አባ ሳሙኤል ሲደርስ ልጁ ሞቶ አገኘው፡፡ አባ ሳሙኤልም በጸሎቱ ከሞት አስነሣው፡፡ ልጁ ስምዖንም ከሞት ከተነሣ በኋላ የአባ ሳሙኤል ደቀመዝሙሩ ሆነ፡፡ ሁለቱም በጋራ በተጋድሎ አብረው ኖሩ፡፡

ቅዱስ ስምዖን ውኃ ሊቀዳ ሲሄድ ሰይጣን እንስራውን ሰበረበት፡፡ አባቱም ሌላ መቅጃ ቢሰጠው እርሱንም ሰበረበት፡፡ የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ አዘዛቸው፡፡ ንጉሥ አንስጣስዮስም ቤተ ክርስቲያኑን ሠራላቸው፡፡ እነርሱም ለመነኮሳትና ለነዳያን መኖሪያ 500 መኖሪያ ቤቶችን ሠሩ፡፡ አባ ሳሙኤልም ባረፈ ጊዜ መነኮሳት ልጆቹን ለአባ ስምዖን አስረክቦ በሰላም ዐረፈ፡፡ መነኮሳቱም 12 ሺህ እስኪሆኑ ድረስ በዙ፡፡ አባ ስምዖንም በሚገባ ይመራቸው ነበር፡፡ በዘመኑም "ትንሣኤ ሙታን የለም" የሚል ሰይጣን በልቡ ያደረ አንድ መናፍቅ ተነሣ፡፡ አባ ስምዖንም ቢመክረውና ቢያስተምረው የማይለስ ሆነ፡፡ አባ ስምዖንም በሞተ ሰው ላይ ጸልዮ ያንን ሙት አስነሥቶ እንዲመሰክርለት ቢያደርገው አላምን አለው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ስምዖን ወደ #እግዚአብሔር ቢጸልይ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያንን መናፍቅ አቃጠለውና ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ አባ ስምዖንም አገልግሎቱን ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡

ከአባ ስምዖንም በኋላ አባ ገብርኤል ተሹሞ መለኮሳቱን የሚጠብቅ እረኛ ሆነ፡፡ እርሱም ምግባሩ ያማረ ሃይማኖቱ የሰመረ በትሩፋት በተጋደሎ ያጌጠ ነው፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም የሚያደርግ ሆነ፡፡ ከዕለታም በአንደኛው ቀን መነኮሳቱ ለእንጀራ ማቡኪያ የሚሆን እጅግ ትልቅ የሆነ የድንጋይ ገንዳ ወደ ገዳሙ ሊያስገቡ ቢሉ ከክብደቱ የተነሣ እምቢ አላቸው፡፡ አባ ገብርኤልም በዚህ ጊዜ በገዳሙ ያሉት ሁሉ ወጥተው እንዲራዱ በቃላቸው ባዘዙ ጊዜ 10 ሺህ ሰዎች ከሙታን ተነሡ፡፡ አባ ገብርኤልም ይህን አይቶ "እናንተን ያልኩ አይደለም በሕይወት ያሉትን ነው እንጂ" አሏቸውና ወዲያው ወደ መቃብራቸው ተመለሱ፡፡

ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ሰው ብዙ የሆነ ወርቁን ከአንዱ መነኩሴ ዘንድ በአደራ አስቀምጦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፡፡ ሰውየውም በተመለሰ ጊዜ መነኩሴው ለማንም ሳይናገር በሞት ዐርፎ አገኘው፡፡ የመነኩሴውም ረድእ አባቱ ያስቀመጠበትን ቦታ እንዳልነገረው አስረዳ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ገብርኤል ወደሟቹ መነኩሴ መቃብር ሄዶ መቃብሩን ስለዚያ ወርቅ ጠየቀው፡፡ ሟቹም መነኮሴ ወርቁን ያኖረበትን ቦታ ለአባ ገብርኤል ነገረውና ወስዶ ለባለቤቱ ሰጠው፡፡ ባለወርቁም እጅግ እያደነቀ ወርቁን ተቀብሎ በሰላም ሄደ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጢሞቴዎስ_ገዳማዊ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ ዐረፈ፡፡ ይኸውም ደጋግ የሆኑ ወላጆቹ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ ባደገም ጊዜ ዓለምን ንቆ መንኩሶ ገዳም በመግባት በተጋድሎ መኖር ጀመረ፡፡ መጻተኞችንና ጦም አዳሪዎችን ይመግባቸው ዘንድ ከገዳሙ አቅራቢያ መኖሪያን አበጀ፡፡ ነዳያንንም እየመገበ በመንፈሳዊ ተጋድሎው እያጸና 5 ዓመት ያህል ከኖረ በኋላ የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ሰይጣን በቅናት ተነሣበትና የእጅ ሥራውን ትገዛ ዘንድ አንዲት ጋለሞታን ወደ እርሱ አመጣበት፡፡

እርሷም ወደ አባ ጢሞቴዎስ ከመመላለሷ የተነሣ የኃጢአት ፍቅር አድሮባቸው በመብል ጊዜ አብረው የሚመገቡ ሆኑ፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሷ ጋር በኃጢአት ወደቀና በኃጢአት ሥራ ውስጥ 7 ወር ያህል ኖረ፡፡ #እግዚአብሔር ሁለቱንም አልጣላቸውምና በዕለተ ምፅዓት በፊቱ የሚቆሙ መሆናቸውን አሳሰባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጢሞቴዎስ ተነሥቶ ጥቅጥቅ ወዳለ ጫካ ገብቶ በዚያ እየታደለ ብዙ ዘመን ኖረ፡፡ #እግዚአብሔርም ጣፋጭ የሆነች የውኃ ምንጭንና ቴምርን አዘጋጀለት፡፡ እርሷን እየተመገበ በተጋድሎ ሲኖር ሰይጣን ዳግመኛ በቅናት ተነሣበትና አስጨናቂ የሆድ ሕማም አመጣበት፡፡ አባ ጢሞቴዎስ ከሕማሙ ጽናት የተነሣ በግንባሩ ምድር ላይ የወደቀ ሆኖ ቀረ፡፡ በዚህም ጊዜ ነፍሱን ‹‹ነፍሴ ሆይ ይህ የሠራሽው የኃጢአትሽ ፍሬ ነውና በዚህ ደዌሽ ታገሺ›› ይላት ነበር፡፡ በዚህም አስጨናቂ ሕማም ውስጥ ሆኖ 4 ዓመት ኖረ፡፡

ከ4 ዓመትም በኋላ መሐሪና ይቅር ባይ የሆነ #እግዚአብሔር ለአባ ጢሞቴዎስ መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም የአባ ጢሞቴዎስን ሆድ በእጁ አሸው፡፡ ጎኑንም በጣቱ ሰነጠቀና ጨንጓራውንና አንጀቱን አፀዳለት፡፡ በኋላም ወደቦታው መልሶ እንደቀድሞው አያይዞ አዳነውና "እነሆ እንግዲህ ጤነኛ ሆንክ፣ ዳግመኛ አትበድል ከዚህ የከፋ እንዳይደርስብህ" አለው፡፡ አባ ጢሞቴዎስም በበረሃ እየተጋደለ 40 ዓመት ኖረ፡፡ ከዚያ በፊት በገዳም 17 ዓመት በዋሻ 10 ዓመት ኖሯል፡፡ በእነዚህም ዘመናቱ ከልብስ ተራቁቶ ኖረ፡፡ የራሱም ፀጉር ከፊትና ከኋላ ሸፍኖት ነበር፡፡ ስለ አገልግሎቱ፣ ስለ ተጋድሎውና ስለ አምልኮቱ የዱር አራዊት እስኪ ሰግዱለትና የእግሩን ትቢያ እስኪልሱለት ድረስ #እግዚአብሔር ትልቅ ጸጋን ሰጠው፡፡ አገልግሎቱንም ፈጽሞ ታኅሣሥ 23 በሰላም ዐረፈ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_23)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ጢሞቴዎስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ፤
⁹ ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።
¹⁰ ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን መዳን ከዘላለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስለ ተመረጡት በነገር ሁሉ እጸናለሁ።
¹¹ ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው፦ ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤
¹² ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤
¹³ ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።
¹⁴ ይህን አሳስባቸው፥ በቃልም እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፥ ይህ ምንም የማይረባ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና።
¹⁵ የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፥ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።
¹⁶ ነገር ግን ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍ ራቅ፤ ኃጢአተኝነታቸውን ከፊት ይልቅ ይጨምራሉና፥ ቃላቸውም እንደ ጭንቁር ይባላል፤
¹⁷ ከእነርሱም ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ናቸው፤
¹⁸ እነዚህም፦ ትንሣኤ ከአሁን በፊት ሆኖአል እያሉ፥ ስለ እውነት ስተው፥ የአንዳንዶችን እምነት ይገለብጣሉ።
¹⁹ ሆኖም፦ ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም፦ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሞአል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
² በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤
³ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤
⁴ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ።
⁵ እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።
⁶ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
⁷ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤
³¹ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው።
³² እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤
³³ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና።
³⁴ እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ፦ የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል።
³⁵ ደግሞ በሌላ ስፍራ፦ ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና።
³⁶ ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤
³⁷ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም።
³⁸-³⁹ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን።
⁴⁰-⁴¹ እንግዲህ፦ እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።
⁴² በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው።
⁴³ ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው።
⁴⁴ በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_23_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ለስሒት መኑ ይብልዋ። እምኅቡአትየ አንጽሐኒ። ወእምነኪር መሀኮ ለገብርከ"። መዝ.18፥12-13
"ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ"። መዝ.18፥12-13
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_23_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 22
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹-³² ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፦ እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
³³ ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ።
³⁴ ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ።
³⁵ ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፦
³⁶ መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው።
³⁷ ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።
³⁸ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
³⁹ ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።
⁴⁰ በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።
⁴¹-⁴² ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ፦ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት።
⁴³-⁴⁴ እርሱም፦ እንኪያስ ዳዊት፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል?
⁴⁵ ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው።
⁴⁶ አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_24

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ሃያ አራት በዚህች ዕለት ጌታ ሐዲስ ሐዋርያ ብሎ የሾማቸው የኢትዮጵያ ብርሃኗ የሆኑ የደብረ ሊባኖሱ #አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት ልደታቸው ነው፣ የከበረና የተመሰገነ #ቅዱስ_አግናጥዮስ_ምጥው_ለአንበሳ ዕረፍቱ ነው፣ #አባ_ጳውሊ_ዘሰሎንቅያ ዕረፍታቸው ነው፣ የአሚናዳብ ልጅ #ቅድስት_አስቴር ዕረፍቷ ነው፣ የአንጾኪያው #አባ_ፊሎንጎስ ዕረፍቱ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት

ታኅሣሥ ሃያ አራት በዚህች ዕለት #ጌታችን በቃሉ ''ሐዲስ ሐዋርያ'' ብሎ የሾማቸው የኢትዮጵያ ብርሃኗ የሆኑ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ልደታቸው ነው፡፡

#እግዚአብሔር አምላካችን ለኢትዮጵያ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ የመረጣቸው ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ 24 ቀን 1197 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጻድቁ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ #አብ ቅዱስ አሐዱ #ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ #መንፈስ_ቅዱስ ›› ማለትም ‹‹አንዱ #አብ ቅዱስ ነው አንዱ #ወልድ ቅዱስ ነው አንዱ #መንፈስ_ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት የፈጠራቸውን አምላክ አመስግነውታል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ይኸውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡ የወላጆቻቸው የቀድሞ ስማቸው ዘርዐ ዮሐንስና ሣራ ይባል ነበር፡፡

ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና እነ አቡነ ዜና ማርቆስ ሌሎቹም እነ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ ሕፃን ሞዐ፣ አቡነ አኖሪዮስ(ትልቁ)፣ አቡነ ገላውዲዮስ፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋርና አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል የትውልዳቸው መሠረት ኢያሱ ለሌዋውያን ክፍል ትሆን ዘንድ ከለያት ከኢየሩሳሌም ነው፡፡ ስማቸውን የጠቀስኳቸው እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን የወንድማማቾች ልጆች ሲሆኑ ከአዳም ጀምሮ 61ኛ ትውልድ ናቸው፡፡ ይኸውም እንዴት ነው ቢሉ ትውልዱ ከአዳም ጀምሮ በካህኑ አሮን በኩል የሆነውና የሌዋዊያን ሊቀ ካህን የነበረው የሳዶቅ ልጅ አዛርያስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ከታቦተ ጽዮንና ከብዙ ሌዋዊያን ካህናት ጋር ሊቀ ካህን ሆኖ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አክሱም ተቀምጦ ኖረ፡፡ የኦሪትንም ሕግ እየዞረ ለኢትዮጵያ ሰዎች አስተማረ፡፡ ትውልዱም በአብርሃ ወአጽብሓና በአባ ሰላማ ዘመን እስከነበረው እንበረም የሚባለው ጻድቅ ድረስ ደረሰ፡፡ የእንበረምም ትውልድ ደገኛው ሕይወት ብነ በጽዮን ድረስ ደረሰ፡፡ ሕይወት ብነ በጽዮንም የደማስቆ ምድር ከሚሏት ከወለቃ ሀገር የመኮንን ልጅ የሆነችውን ወለተ ሳውልን አግብቶ አበይድላን ወለደ፡፡ አበ ይድላም በንጉሡ ድልዓዥን ዘመነ መንግሥት ለ150 ካህናት አለቃ ሆኖ በወለቃ ሀገር የ #ክርስቶስን የወንጌል ሕግ እያስተማረ ብዙዎችን አጠመቀ፡፡ እስከ ሸዋ ምድር ድረስ እያስተማረ መጥቶ በሸዋ ምድር ተቀመጠ፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳነጸ፡፡ እጅግ አስደናቂ ተአምራትንም ያደርግ ነበር፡፡ ‹‹በሸዋ ጽላልሽ ተቀምጦ ሲያስተምርም በአንዲት ቀን እስከ ሁለት መቶ ሺህ ሕዝብ ያጠምቅ ነበር›› በማለት ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይመሰክርለታል፡፡

አበይድላ በመጨረሻ በፈቃደ #እግዚአብሔር ከሸዋ ጽላልሽ ምድረ ዞረሬ ሚስት አግቶ ሀበነ እግዚእን ወለደ፤ ሀበነ እግዚእም በኩረ ጽዮንን ወለደ፤ በኩረ ጽዮንም ሕዝበ ቀድስን ወለደ፤ እርሱም ነገደ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ሕዝበ ቀድስም ብርሃነ መስቀልን ወለደ፤ እርሱም ዐቃቢነ እግዚእ የተባለ ነው፡፡ ብርሃነ መስቀልም ሕይወት ብነን ወለደ፤ እርሱም ሴትን ወለደ፡፡ ሴትም ወረደ ምሕረትን ወለደ፡፡ ወረደ ምሕረትም ዘካርያስን ወለደ፡፡ ዘካርያስም የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የሆኑ 6 ወንድማማች ልጆችን ወለደ፡፡ እነርሱም እንድርያስ፣ አርከሌድስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብ፣ ቀሲስ ዮሐንስና ቀሲስ ዮናስ ናቸው፡፡ እንድርያስም ሳሙኤል ዘወገግን ወለደ፤ አርከሌድስም ሕፃን ሞዐን ወለደ፤ ዘርዐ አብርሃምም ታላቁን አኖርዮስን ወለደ፤ ዘርዐ ዮሐንስ ወይም ጸጋ ዘአብም ተክለ ሃይማኖትን ወለደ፤ ቀሲስ ዮሐንስም ዜና ማርቆስን ወለደ፣ ቀሲስ ዮናስ ደግሞ የፈጠጋሩን ማትያስንና ገላውዲዮስን ወለዳቸው፡፡ ገላውዲዮስም የመሐግሉ ቀውስጦስን ወለደ፡፡ እነዚህ ደጋግ ቅዱሳን በእናታቸውም በኩል እንዲሁ በዝምድና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ማቴዎስ የተባለው ደገኛ ክርስቲያን የሸዋ ገዥ የነበረ ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ መድኃኒነ እግዚእንና ሦስት ሴቶች ልጆችን ወለደ፡፡ ሶስቱ ሴቶች ልጆችም እምነ ጽዮን፣ ትቤ ጽዮንና ክርስቶስ ዘመዳ ይባላሉ፡፡ ሦስቱ እኅትማማቾችም ደጋጎቹን አባቶቻችንን ወለዱልን፡፡ እምነ ጽዮን የእነ ዜና ማርቆስን እናት ማርያም ዘመዳንና ወለደች፡፡ ትቤ ጽዮንም ሕፃን ሞዐን ወለደች፡፡ ክርስቶስ ዘመዳ ደግሞ ታላቁን አኖሬዎስን ወለደች፡፡ የፈጠጋሩ ገዥ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ የተክለ ሃይማኖትን እናት እግዚእ ኀረያን ወይም በሌላ ስሟ ሣራን ወለደ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከልጅነታቸው ጀምሮ በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በ15 እና በ22 ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ (ጌርሎስ) ዲቁናንና ቅስናን ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ያገለግሉ እንደነበር በዚህ ይታወቀል፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን አባታችን ከጓደኞቻቸው ጋር ለአደን ወደ ዱር ሄደው ሳለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ታያቸው፡፡ ቅዱስ አባታችንም ‹‹እንደዚህ ባለ ገናንነት የማይህ ጌታዬ ማነህ?›› ባሉት ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ዘወትር የምጠብቅህ ካንተ የማልለይ እናትህንና አባትህንም ስላንተ ከውኃ ስጥመትና ከምርኮ ያዳንኳቸው እኔ ሚካኤል ነኝ፡፡ ከእንግዲህ አውሬ አዳኝ አትሁን፤ ሰውን ወደ #እግዚአብሔር ለመመለስ ሰውን በትምህርት የምታድን ሁን እንጂ፡፡ እነሆ #እግዚአብሔር ጽኑዕ ሥልጣን ሰጥቶሃልና፤ ሙት ታስነሣለህ፤ ድውያንን ትፈውሳለህ፤ አጋንንትም አንተን በመፍራት ይሸሻሉ፡፡ ስምህ ፍሥሐ ጽዮን አይሁን፤ ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንጂ፡፡ ትርጓሜውም ተክለ #አብ፥ ተክለ #ወልድ፥ ተክለ #መንፈስ_ቅዱስ ማለት ነው›› አላቸው፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ይህን ሲነግራቸው #ጌታችን በሥጋ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበር ሆኖ መልከ መልካም ጎልማሳ መስሎ ታያቸው፡፡ #ጌታችንም ‹‹ወዳጄ እንዴት ሰነበትክ? ቸር አለህን?›› አላቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ‹‹ጌታዬ ሆይ አንተ ማነህ?›› ብለው ሲጠይቁት #ጌታችንም ‹‹እኔ የዓለም መድኃኒት #ኢየሱስ ነኝ፤ በናትህ ማኅፀን ፈጥሬህ ያከበርኩህ እኔ ነኝ፡፡ በተወለድክ በሦስተኛው ቀን አሐዱ #አብ ቅዱስ አሐዱ #ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ #መንፈስ_ቅዱስ ብለህ ታመሰግነኝ ዘንድ የምስጋና ሀብት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ በርሃብ ዘመን በቤት የሚያሻው ምግብ ሁሉ ቅቤው፣ የስንዴው ዱቄት በእናት በአባትህ ቤት ይመላ ዘንድ በእጅህ ሀብተ በረከት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ ያንን ሰው አንተን በተጣላ ጊዜ በነፋስ አውታር የሰቀለኩት በመዓት ጨንገር የገረፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ውኃ ጠምቶህ በለመንከኝ ጊዜ ከደረቅ መሬት የጣፈጠ ውኃ ያመነጨሁልህ እኔ ነኝ፡፡ ከልጅነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ተአምራት እያደረግሁ በአንተ እጅ የታመሙትን
ያዳንኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ወደፊትም አደርግልሃለሁ›› አላቸው፡፡ ይህንን ብሎ በእጆቹ ባረካቸውና ‹‹ንሣእ #መንፈስ_ቅዱስ›› ብሎ የሹመትን ሀብት አሳደረባቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሁን፤ በምድርም የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሁን፤ አንተን የሰማ እኔን መስማቱ ነው፤ የላከኝ አባቴንም መስማቱ ነው፡፡ አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ ማለቱ ነው፡፡ የላከኝ አባቴንም እንቢ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ቀድሞ ለሐዋርያት ሰጥቻቸው ነበር፡፡ ከሐዋርያትም ሹመትን የተቀበለ ጳጳሱ ትሾምና ትሽር፣ ትተክልና ትነቅል ዘንድ ሥልጣንን ሰጠህ፡፡ ይህንንም ያደረኩልህ የጳጳሱን ቃል በመናቅ አይደለም፡፡ የፍቅሬን ጽናት ባንተ እገልጽ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ሐዋርያት ወዳልደረሱበት ሕዝብ በመምህርነት እልክህ ዘንድ በሚካኤል ቃል አዲስ ስም አወጣሁልህ፡፡ አንተም በማናቸውም ሥራ ከእነርሱ አታንስም፣ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጌሃለሁና፡፡ ሰውን ሁሉ በእኔ ስም እያስተማርክ ታሳምን ዘንድ፣ ቅዱስ ሚካኤልም ባሰብከው ሥራ ሁሉ ረዳት ይሁንህ፣ ሁል ጊዜ ካንተ አይለይም፤ በምትሄድበትም ጎዳና ሁሉ እርሱ መሪ ይሁንህ፤ እኔም ባለ ዘመንህ ሁሉ አልለይህም›› ካላቸው በኋላ ሰላምታ ሰጥቷቸው ዐረገ፡፡

ብፁዕ አባታችንም እጅ ነሥተው ‹‹ለእኔ ለኀጥኡ የማይገባኝ ሲሆን ይህን ሁሉ ጸጋ የጠኸኝ ስምህ በሰማይ በምድር የተመሰገነ ይሁን›› አሉ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሀብተ ኃይልን የተመሉ ሆኑ፡፡ ወደቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ሀብት ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጥተው ጨረሱ፡፡ ከዚያም ‹‹አቤቱ ጌታዬ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ›› ብለው ቤታቸውን እንደተከፈተ ትተው ወንጌልን ለማስተማር ወጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት ስለመለሱት በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ተብለዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ተክለሐይማኖተ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አግናጥዮስ_ምጥው_ለአንበሳ

ይህም ቅዱስ የወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሩ ነው በስብከተ ወንጌልም በማገልገል ከእርሱ ጋር ብዙ አገሮችን ዙሮ አስተምሮአል ከዚህም በኋላ በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾመው በውስጥዋ መሰረተ ሕይወት የሆነ የወንጌልን ትምህርት አስተማረ ብዙዎችንም #እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው በትምህርቱም ልቡናቸውን አበራላቸው።

ከዚህም በኋላ ጣዖትን ለሚያመልኩ ስሕተቻተውን በገለጠላቸው ጊዜ ተቆጡ። ወደ ከሀዲው ንጉሥ ወደ ጠራብዮስ ሔደው ከሰሱት እንዲህም አሉት "አግናጥዮስ የአማልክቶችህን አምልክ ይሽራል እኮን ሰዎችንም እያስተማረ #ክርስቶስን ወደ ማመን ያስገባቸዋል"። በዚያንም ጊዜ ወታደሮች ልኮ ወደርሱ አስመጣውና "አግናጥዮስ ሆይ ለምን ይህን አደረግህ የአማልክቶቼን አምልኮስ ለምን ሻርክ ሰዎችን ሁሉ #እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ አስገብተሃቸዋልና" አለው። አግናጥዮስም "ንጉሥ ሆይ ቢቻለኝስ የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ #ክርስቶስ አምልኮት ባስገባሁህ ነበር" አለው ንጉሡም "ይህን ነገር ትተህ ለአማልክቶቼ ሠዋ አለዚያ በታላቅ ሥቃይ አሠቃይሃለሁ" አለው። "በእኔ ላይ የምትሻውን አድርግ እኔ ግን ለረከሱ አማልክቶችህ አልሠዋም ሥቃይህንም እሳትም ቢሆን አንበሳንም ቢሆን አልፈራም ከሕያው ንጉሥ ከ #ክርስቶስ ፍቅር ልትለየኝ አትችልም" አለው። ይህንንም ሲሰማ ንጉሡ ተቆጣ ያሠቃዩትም ዘንድ አዘዘ በተለያዩ በብዙ ሥቃዮችም አሠቀሠዩት በእጆቹም ውስጥ እሳት አድርገው ከእጆቹ ጋር በጉጠት ይዘው አቃጠሉት።

ከዚህም በኋላ በዲንና በቅባት እያነደዱ ጎኖቹን አቃጠሉ በሾተሎችም ሥጋውን ሠነጠቁ። ከማሠቃየትም በደከሙ ጊዜ የሚያደርጉበትን እስከመክሩ ድረስ ከወህኒ ቤት ጨመሩት ብዙ ቀኖችም በዚያ ኖረ።

ከዚህም በኋላ አስታውሱት ከወህኒቤትም አውጥተው በንጉሡ ፊት አቆሙት ንጉሡም "አግናጥዮስ ሆይ አማልክቶቼን ብታያቸው ውበታቸው ባማረህ ነበር" አለው። ቅዱሱም "ንጉሥ ሆይ አንተ በክብር ባለቤት #ክርስቶስ ብታምን ሙታኖችን የምታሥነሣቸው በሽተኞችንም የምትፈውሳቸው ባደረገህ ነበር"። ንጉሡም "ለፀሐይ ከመስገድ የተሻለ የለም" አለ የከበረ አግናጥዮስም "መንግሥቱ የማያልቀውን ፈጣሪ ትተህ ለተፈጠረ ፀሐይ ትሰግዳለህን?" ብሎ መለሰ ንጉሡም "ለራስህ መልካም አልክ ግን በመተላለፍ የአንጾኪያና የሶርያን ሰዎች ስበሕ ወደ #ክርስቶስ አምልኮት አስገባሃቸው እንጂ" አለው። የከበረ አግናጥዮስም ተቆጥቶ "ንጉሥ ሆይ ከንቱ የሆነ ጣዖትን ከማምለክ ሰዎችን ስለሳብኳቸውና ሰማይና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ #ክርስቶስ አምልኮት ስለአስገባኋቸው በእኔ ላይ ትቆጣለህን ለረከሱ ጣዖቶችህስ እንድሠዋ ታዘኛለህን እኔ ግን ቃልህን ተቀብዬ ለሰይጣናት አልሠዋም ለእውነተኛ አምላክ ለ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ እሠዋለሁ እንጂ" አለው።

በዚያንም ጊዜ ንጉሥ ተቆጣ ከሥጋው ምንም ምን ሳያስቀሩ ይበሉት ዘንድ ሁለት የተራቡ አንበሶችን በላዩ እንዲሰዱ አዘዘ። የከበረ አግናጥዮስም አንበሶች ወደርሱ ሲቀርቡ በአያቸው ጊዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሕዝብን እንዲህ አላቸው "ከዚህ የተሰበሰባችሁ እናንተ የሮሜ ሰዎች ቃሌን ስሙ እወቁም እኔ ይህን ሥቃይ የታገሥኩት በትዕቢትና በትምክህት አይደለም የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታዬና_በፈጣሪዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ፍቅር እንጂ። አሁንም እኒህ አንበሶች እንደ ሥንዴ ይፈጩኝ ዘንድ ነፍሴ ወደደች የክብር ባለቤት ወደ ሆነ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ልትሔድ ነፍሴ ሽታለችና"።

ንጉሡም ቃሉን ሰምቶ አደነቀ ድንጋጤም አድሮበት እንዲህ አለ "የክርስቲያኖች ትዕግሥታቸው ምን ይብዛ ስለ አምልኮት ከአረማውያን በእንዲህ ያለ ሥቃይ ላይ የሚታገሥ ማን ነው" አለ። እነዚያ አንበሶችም ወደ ቅዱሱ ቀረብ ብለው ደንግጠው ቆሙ። ከዚህም በኋላ አንዱ አንበሳ እጁን ዘርግቶ አንገቱን ያዘው በዚያንም ጊዜ ደስ ብሎት ነፍሱን በፈጣሪው #ክርስቶስ እጅ ሰጠ ልመናውንም ፈጸመለት።

ለእነዚያ አንበሶችም ሥጋውን ይዳስሡት ዘንድ አልተቻላቸውም የክብር ባለቤት #ክርስቶስ ዳግመኛ እስከ ሚመጣ የተጠበቀ ሆነ እንጂ ከዚህም በኋላ በክብር በምስጋና ከከተማ ውጭ ቀበሩት እንደዚህም በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም በመልካም ተጋድሎ ምስክርነቱን ፈጸመ ለምእመናንም ጠቃሚ ይሆን ዘንድ ገድሉን ጻፉ የበዓሉንም መታሰቢያ አደረጉለት።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አግናጤዎስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጳውሊ_ዘሰሎንቅያ

በዚህች ዕለት አባ ጳውሊ ዘሰሎንቅያ ዐረፈ፡፡ ሰሎንቅያ በምትባል በምስር አገር ሰይጣንን ገዝተው በግልጽ ያነጋገሩትና ብዙ ምሥጢርን እንዲናገር ያደረጉት ታላቅ አባት ናቸው፡፡ የሰሎንቅያ አገር ሰዎች የሄሮድስ ወገን የሆኑ ክፉዎች ናቸው፡፡ ከዱሮ ጀምረው ሴቶችና ወንዶች ሆነው በጋራ በአንድነት ወደ አንድ ክፍል ገብተው እንስሳዊ ግብራቸውን ይፈጽማሉ፡፡ ብዙ ሆነው ገብተው በሩን ዘግተው መብራት አጥፍተው በእጃቸው የገባውን ይዘው ያድራሉ፡፡ እኅቱም ትሁን ልጁ ወደዚያ ቤት የገባ ሰው ሌላውን አይለየውም፡፡ ይህም ሰይጣናዊ ተግባራቸው ባሕላቸው ሆኖ በወር አንድ ጊዜ ያደርጉታል፡፡
አባ ጳውሊም ይህን ባየ ጊዜ ስለ ኃጢአታቸው በጣም አዝኖ "ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ?" ቢላቸው እነርሱም "አባቶቻችን ያዘዙን ትእዛዝና ባሕላችን ነው" አሉት፡፡ አባ ጳውሊም ወደዚያ ቤት ሲገቡ አይቶ እጅግ በማዘን ወደ #ጌታችን ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም እንደፈጸመ አንድ ጥቁር ሰው ከዝሙት ቤቱ ዕራቁቱን ሆኖ የእሳት ሰይፍ ተሸክሞ መጣ፡፡ አባ ጳውሊም ካማተበበት በኋላ "አንተ ማነህ? ማንንስ ትሻለህ?" አሉት፡፡ ጥቁሩም ሰው "እኔ ሰይጣን ነኝ፣ አንተ ወደ #ጌታህ በለመንህ ጊዜ ላከኝ" አለው፡፡ አባ ጳውሊም "የምታስትበትን ነገር ሁሉ ትነግረኝ ዘንድ እጠይቅሃለሁ" አለው፡፡ ሰይጣንም "የምትሻውን ጠይቀኝ" አለው፡፡ አባም "ያለ #እግዚአብሔር ፈቃድ በሰው ላይ ታድር ዘንድ ምክንያት እንዴት ታገኛለህ?" አለው፡፡ ሰይጣንም "ሰው በእግዚአብሔር ሕግ ጸንቶ ሳለ የ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም በጠራ ጊዜና በንጽሕና ሆኖ የ #ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ከቡር ደምን በሚቀበል ሰው ላይ ለማደር ሥልጣን የለኝም" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ የሚያስትበትን ሁሉ በዝርዝር ነገረው፡፡ ሊቀ ጳጳሳትን፣ ጳጳሳትን፣ መነኮሳትን፣ መእመናንን፣ ባለትዳሮችን፣ አዛውንቶችን፣ ወጣቶችና ሕፃናትን…ሁሉንም ነገር እያንዳንዱን በምን በምን እንደሚያስት ሁሉንም ነገር በዝርዝር ነገረው፡፡ ወዲያውም የሰይጣን መልኩ ተለውጦ እንደ እሳት ነበልባል ሲሆን አባ ጳውሊ ተመልክቶ እጅግ ደነገጠ፡፡ በዚያም ቅጽበት የታዘዘ መልአክ መጥቶ አባ ጳውሊን አበረታው፡፡

በዚያችም ሌሊት መቅሰፍት ወርዶ በዝሙት ቤት ያሉትን አጠፋቸው፡፡ ከ5 ወንዶችና ከ5 ሴቶች በቀር የተረፈ የለም፡፡ አባ ጳውሊም "ይህን ለምን ታደርጋላችሁ?" ቢላቸው "በየወሩ አንዲት ቀን ወደ ውሽባ ቤት እየገባን በሩን ዘግተን መብራት አጥፍተን ከእጃችን የገባችዋን ሴት ይዘን አንተኛለን" አሉት፡፡ "ከእናንተ ውስጥ እኅቱን ወይም ልጁን እንዴት ያውቃል?" አላቸው፡፡ "እንደ እንስሳ በመሆን እንጃ ማወቅ የለም" አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን የ #ክርስቶስን ወንጌል ሰበከላቸውና አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ ቅዱስ ሥጋ ክቡር ወደሙንም አቀበላቸው፡፡ በሃይማኖት ካጸናቸው በኋላ ወደ በዓቱ ተመልሶ ገድሉን ፈጽሞ ታኅሣሥ 24 ቀን በሰላም ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አስቴር

የአይሁድ ወገን የሚሆን ስሙ መርዶክዮስ የሚባል የኢያኤሩ ልጅ ከብንያም ወገን የተወለደ የቄስዩ ልጅ አንድ ሰው በሱሳ አገር ነበረ፡፡ ከኢሩሳሌምም በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነጾር እጅ የተማረከ ነው፡፡ ያሳደጋት ልጅ ነበረችው፡፡ እርሷም የአባቱ ወንድም የአሚናዳብ ልጅ አስቴር ናት፡፡ ከዘመዶቿ ተለይታ በወጣች ጊዜ ልጅ ትሆነው ዘንድ አሳደጋት፡፡ እርሷም እጅግ መልከ መልካም ነበረች፡፡ በአንዲትም ዕለት ንጉሥ አርጢክስስ ብዙ ተድላ ደስታ አድርጎ መኳንንቶቹን ሁሉ ጠራ፡፡ የመኳንንቶቹንም አለቃ አማሌቃዊውን ሐማንንም ጠራው፡፡ እርሱ ከሁሉም መኳንንት የከበረ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ 7ቱን ባለሟሎቹን ጠርቶ ንግሥቲቱን አስጢንን አምጥተው የእቴጌነት ዘውድ ያቀዳጇት ዘንድ እርሷ መልከ መልካም ናትና ለአሕዛብም አለቆች ሁሉ መልኳንና ውበቷን ያሳዩ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ ንግሥቲቱ አስጢን ግን የንጉሡን ትእዛዝ ባለመቀበል እምቢ አለች፡፡ ከባለሟሎቿም ጋር ትመጣ ዘንድ ባለወደደች ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተናዶ ከንግሥትነቷ ሻራት፡፡ ከዚህም በኋላ 127 ከሚሆኑ ከሚገዘቸው አገሮች አንድ ሺህ ቆነጃጅቶችን ይመርጡለት ዘንድ ንጉሡ አዘዘ፡፡ ከሺህ መቶ፣ ከመቶ ዓሥር፣ ከዓሥር ሦስት መረጡ፡፡ ከሁሉም በመልክ፣ በውበት፣ በደም ግባትም አንደኛ ሆና አስቴር ተመረጠች፡፡ ንጉሡም አስቴርን አነገሣት፡፡

ንጉሡም አስቴርን እጅግ አድርጎ ወደዳት፣ በሴቶቹም ሁሉ ላይ የበላይ አድርጎ ሾማት፡፡ ከዚህም አስቀድሞ መርዶክዮስ አገሩንና አደባባዩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ ባለሟሎች ጋር በአደባባይ ኖረ፡፡ እነርሱም ስማቸው ታራ እና ገቦታ ይባላል፡፡ እርሱም እነዚህ ሁለቱ በንጉሡ ላይ ያሰቡትን ተንኮላቸውን ሰማ፡፡ ንጉሥ አርጤክስስን ይገድሉት ዘንድ ወንጀልን እንዳዘጋጁ ባወቀ ጊዜ መርዶክዮስ ሄዶ ለንጉሡ ነገረው፡፡ ንጉሡም ነገራቸውን መርምሮ ቀጣቸውና ይህን ነገር ታሪክና ወግ በሚጻፍበት ላይ ጻፈው፡፡ ሐማ ግን አማሌቃዊ ነበረና መርዶክዮስንና እስራኤላውያንን ይጠላቸው እጅግ ነበርና የአይሁድን ወገን ሁሉ ለማጥፋት ተነሣ፡፡ መርዶክዮስም ይህንን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀዶ ማቅ ለበሰ፡፡ መርዶክዮስም የሀዘኑን መርዶ ለአስቴር እንዲደርሳት አደረገ፡፡ አስቴርም "እስከ ሦስት ቀን ጹሙ ጸልዩ እኔም ደንገጡሮቼም እንጾማለን" ብላ ላከችለት፡፡ ሱባኤዋንም እንደጨረሰች የማቅ ልብሷን አውልቃ ጥላ ወደ ንጉሡ አዳራሽ በገባች ጊዜ "እስከ መንግሥቴም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁና የሆንሽውን ንገሪኝ" አላት፡፡ በዓልንም አደረገና ሐማንና መኳንንቱን ሁሉ ጠራ፡፡ በበዓሉም ላይ ድጋሚ "ላደርግልሽ ፈቅጂውን ንገሪኝ" አላት፡፡

ንጉሡም ለመርዶክዮስ ውለታ ያደረገለትን ሲያስብ ምንም እንዳላደረገለት ዐወቀ፡፡ ወዲያውም ሐማ መርዶክዮስን በመስቀል ላይ ሰቅሎ ሊገድለው እንደሆነ ተነገረ፡፡ ንጉሡም ሐማን "ንጉሥ የወደደውን ሰው ምን ያደርግለት ዘንድ ይገባል?" አለው፡፡ ሐማም "ይህስ ለእኔ ነው" ብሎ "በክብር ይሾም ዘንድ ሹመቱም አዋጅ ይነገርለት ዘንድ ይገባዋል" አለ፡፡ ንጉሡም ለሐማ ይህን ጊዜ "መልካም ተናግረሃል፣ ለመርዶክዮስ እንዲሁ ይደረግለታል" አለው፡፡ ሐማም የንጉሡን ትእዛዝ ተቀብሎ መርዶክዮስን በፈረስ አስቀምጦ በከተማው በማዞር በክብር መሾሙን በአዋጅ አስነገረለት፡፡

ከዚህም በኋላ ንጉሡና አስቴር ለማዕድ አብረው በተቀመጡ ጊዜ ንጉሡ "ጉዳይሽን የማትነግሪኝ ለምንድነው?" አላት፡፡ እሷም ይህን ጊዜ "ንጉሥ ሆይ ዝም ባልኩ በወደድኩ ነበር ነገር ግን ወገኖቼና እኔ ለሞት ተላልፈን ተሰጥተናል" በማለት ሐማ እስራኤላውያንን በአዋጅ ሊያጠፋ መሆኑን ነገረችው፡፡ ንጉሡም "ማነው ይህን በማድረግ የደፈረኝ?" አላት፡፡ እሷም ሐማ መሆኑን ነገረችው፡፡ ንጉሡም ሐማ መርዶክዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው መስቀል ላይ ራሱ ሐማን እንዲሰቅሉት አዘዘ፡፡ ሐማም ተሰቅሎ ሞተ፡፡ የእስራኤል ወገኖችም ሁሉ በጻድቂቱ አስቴር መዳናቸው በእርሷ ተደርጓልና ሁሉም አመሰገኗት፡፡ ምስጉን የሆነ #እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ ድኅነታቸው በእርሷ ተደርጓል።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አስቴር ጸሎት ይማረን በረከቷም ይደርብን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ፊሎንጎስ

በዚህች ዕለት አባ ፊሎንጎስ ዐረፈ፡፡ ይኽም ቅዱስ አስቀድሞ ሚስት አግብቶ አንዲት ልጅ ወለደ፡፡ ከዚህም በኋላ ሚስቱ ሞተች፡፡ እርሱም ከዚህ በኋላ የምንኩስና ልብስ ለብሶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ኖረ፡፡ ስለ መልካም ተጋድሎውትና ስለ ትሩፋቱ በአገልግሎትም ስለመጠመዱ በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት እንዲሆን #እግዚአብሔር መረጠው፡፡ በተሾመም ጊዜ የ #ክርስቶስን መንጋዮች ምእመናንን በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው፡፡ ከአርዮሳውያን ከመቅዶንዮስና ከሰባልዮስ ነጣቂ ተኩላዎች በሚገባ ጠበቃቸው፡፡ በሊቀ ጵጵስናውም የሹመት ወቅት አኗኗሩን እንደ መላእክት አደረገ፡፡ መልካም የሆነ ገድሉንም ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡
2025/01/08 16:46:43
Back to Top
HTML Embed Code: