Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_9_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ተሰሎንቄ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።
¹⁴ እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።
¹⁵ እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥
¹⁶ ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።
¹⁷ እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤
¹⁸ ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።
¹⁹ ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን?
²⁰ እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ እናንተ ደግሞ ታገሡ፥ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።
⁹ ወንድሞች ሆይ፥ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ፥ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል።
¹⁰ ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።
¹¹ እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።
¹² ከሁሉም በፊት፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በሰማይ ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² ሙሴም ለአባቶች፦ ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት።
²³ ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ።
²⁴ ሁለተኛም ከሳሙኤል ጀምሮ ከእርሱም በኋላ የተናገሩት ነቢያት ሁሉ ደግሞ ስለዚህ ወራት ተናገሩ።
²⁵ እናንተ የነቢያት ልጆችና እግዚአብሔር ለአብርሃም፦ በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ ብሎ፥ ከአባቶቻችን ጋር ያደረገው የኪዳን ልጆች ናችሁ።
²⁶ ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_9_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወቀተሉ ፈላሴ። ወይቤሉ ኢይሬኢ እግዚአብሔር። ወኢየአምር አምላከ ያዕቆብ። መዝ 93፥6-7።
"ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ። እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ"። መዝ 93፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_9_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥
²⁶ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤
²⁷ የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች።
²⁸ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና።
²⁹ ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች።
³⁰ ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ፦ ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ።
³¹ ደቀ መዛሙርቱም፦ ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ፦ ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት።
³² ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር።
³³ ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው።
³⁴ እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ በአሚን የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስር በዚህች ዕለት የአንጾኪያው ሊቅ #ቅዱስ_አባት_አቡነ_ሳዊሮስ ፍልሠተ ሥጋው ነው፣ #ቅዱስ_አባት_አባ_ኒቆላዎስ አረፈ፣ #አባ_ጥዋሽ ዕረፍቱ ነው፣ የከበረች #ቅድስት_ሱርስት ዐረፈች፣ ቅዱሳን ሰማዕታት #ቅዱስ_ተላስስና_ቅዱስ_አልዓዛር በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አቡነ_ሳዊሮስ

ታኅሣሥ ዐስር በዚህች ዕለት እጅግ የከበሩ አቡነ ሳዊሮስ የፍልሥተ ሥጋቸው ሆነ፡፡ እርሳቸውም በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ቤተ ክርስቲያንን እንደፋና አብርተውላት በዓለም መድረክ አንድ ያደረጓት ናቸው፡፡ (የዕረፍታቸውን ዕለት የካቲት ዓሥራ አራትን ይመለከቷል፡፡)
እጅግ ክቡር የሆኑት የአንጾኪያው ታላቁ አባት የአቡነ ሳዊሮስ ትውልዳቸው ከሮሜ ሀገር ሲሆን አባታቸው ሳዊሮስ የሚባሉ ኤጲስ ቆጶስ ናቸው፡፡ አባታቸው ሳዊሮስ ስለ ንስጥሮስ የከፋ ክህደት በኤፌሶን ከተማ ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ከሁለት መቶው እጅግ ከከበሩት ሊቃውንት ቅዱሳን አባቶች ጋር ተሰብስበው ሃይማኖትን አቅንተዋል፡፡ ንስጥሮስንም በቃላቸው ትምህርትና የተለያዩ ተአምራትን እያሳዩ አስተምረው ሊያሳምኑት ቢሞክሩ ሰይጣን በልቡ ስላደረ ከክህደቱ ሊመለስ አልቻለም ነበርና ቤተ ክርስቲያንን እንዳያውክ ምእመናንም በክህደት በመርዙ እንዳይበክል ብለው ቅዱሳኑ በኅብረት አውግዘው ለዩት፡፡

ታላቁ አቡነ ሳዊሮስም ለጉባኤው በኤፌሶን ከተማ እንደመጡ ‹‹ከአንተ የሚወለድ ልጅህ ስሙም እንደ ስምህ ሳዊሮስ ተብሎ የሚጠራ ልጅህ የቀናች ሃይማኖትን ያጸናታል›› የሚል ታላቅ ራእይን ተመለከቱ፡፡ ይህም ታላቁ አቡነ ሳዊሮስ ባረፉ ጊዜ ልጃቸውን ሳዊሮስ ብለው ጠሩት፡፡ እርሱም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆኑትን የጥበብና የፍልስፍና ትምህርቶቸን በሙሉ ጠንቅቆ ተማረ፡፡ በአንዲት ዕለትም ከመምህሩ ዘንድ ወጥቶ በመንገድ ሲጓዝ በዋሻ ውስጥ የሚኖርና ራሱን እስረኛ ያደረገ አንድ ታላቅ ጻድቅ ሰው አገኘ፡፡ ያም ጻድቅ ሰው ሳዊሮስን ‹‹የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን መምህራቸው የሆንክ ሳዊሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው›› አለው፡፡ ያም ጻድቅ ሰው ሳዊሮስን ከነጭራሹ ሳያውቀው በስሙ ስለጠራውና የሚደረግለትንም ከመሆኑ አስቀድሞ ትንቢት በመናገሩ በጣም ተደነቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ሳዊሮስ የትሩፋት ሥራዎችን መሥራት ጀመረ፡፡ ወደ አቡነ ሮማኖስ ገዳም ገብቶ መነኮሰና በጾም በጸሎት በእጅጉ ይተጋ ጀመር፡፡ በገዳሙም ጽኑ በሆነ በመንፈሳዊ ተጋድሎ እየበረታ ሲሄድ ዜናው በሁሉ ዘንድ መሰማት ጀመረ፡፡ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት በሞት ባረፉ ጊዜ የከበሩ ሊቃውንት ኤጲስቆጶሳት በአንድ ሀሳብ ሆነው ፈቃደ #እግዚአብሔርን ጠይቀው አቡነ ሳዊሮስን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ይሾሙት ዘንድ ወደዱ፡፡ በፈቃደ #እግዚአብሔርም ያለ ፈቃዱ በግድ ወስደው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፡፡

በአቡነ ሳዊሮስ በሹመታቸው ዘመን እስከ ዓለም ዳርቻ ያለች ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆኑላት፡፡ የመለኮት ነገር የሚናገሩት ድርሰቶቻው እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡ በየሀገሩ ወዳሚገኙ መናፍቃን ከሃድያን ትምህርታቸው በሚደርስ ጊዜ ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ ሥራቸውን ይበጥሳልና፡፡ የአቡነ ሳዊሮስን ትምህርታቸውን የሰማ መናፍቅ በውስጡ ያደረበት የጥርጥር መንፈስ መድረሻ ያጣል፡፡ አቡነ ሳዊሮስ በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ቤተ ክርስቲያንን እንደፋና አብርተውላት በዓለም መድረክ አንድ አድርገዋታል፡፡

አቡነ ሳዊሮስ በቀናው ተጋድሎአቸው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን ከመናፍቃን ተኩላዎች በመጠበቅ ሲተጉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደጉና አማኙ ንጉሥ ሞቶ በእርሱ ፈንታ ስሙ ዮስጥያኖስ የሚባል መናፍቅ ነገሠ፡፡ ይህም ከሃዲ ንጉሥ ዮስጥያኖስ ‹‹በውሾቸ ጉባኤ›› የተወሰነውን የኬልቄዶንን ሃይማኖት የሚያምን መናፍቅ ከሃዲ ነው፡፡ ንግሥቲቱ ሚስቱ ቴዎድራ ግን ሃይማኖቷ የቀና ምግባሯ ያማረ ነው፡፡ አቡነ ሳዊሮስ በጣም ትወዳቸውና ታከብራቸው ነበር፡፡ ይህም ከሃዲ ንጉሥ አቡነ ሳዊሮስን ወደ ረከሰች ሃይማኖቱ ያስገባቸው ዘንድ ግድ አላቸው፡፡ በብዙ ማስፋራራትና ቁጣ ሊያስገድዳቸው ቢሞክርም አቡነ ሳዊሮስ ግን ቁጣውንና ማስፈራራቱን አልፈሩም፡፡ ንጉሡም አስገድዶ ወደረከሰች ሃይማኖቱ ሊያስገባቸው እንዳልቻለ ባየ ጊዜ አቡነ ሳዊሮስን በስውር ሊገድላቸው ፈለገ፡፡ ንግሥቲቱም ከሃዲው ንጉሡ ባሏ አቡነ ሳዊሮስን በሥውር ሊገድላቸው እንደሆነ ስትሰማ አባን ከአንጾኪያ አገር ወጥተው በመሄድ ራሳቸውን እንዲያድኑ ነገረቻቸው፡፡ አቡነ ሳዊሮስ ግን መሸሽ አልፈለጉምና ‹‹ክብር ይግባውና ስለ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ለመሞት የተዘጋጀሁ ነኝ›› ብለው ለንግሥቲቱ መለሱላት፡፡ ነገር ግን ብዙ ምእመናንና ንግሥቲቱ አጥብቀው ስለለመኗቸው ጻደቁ ወጥተው ወደ ግብፅ አገር ተሰደዱ፡፡ ከምእመናንም አብረዋቸው የተሰደዱ አሉ፡፡

ከሃዲውም ንጉሥ አቡነ ሳዊሮስን በስውር ሊገድላቸው አስቦ ይዘው እንዲያመጧቸው ወታደሮቹን ላካቸው ነገር ግን አላገኟቸውም፡፡ አቡነ ሳዊሮስን #ጌታችን ስለሰወራቸው የንጉሡ ጭፍሮች ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ እሳቸው በጭፍሮቹ አጠገብ እየተጓዙ ጭፍሮቹ ግን አያዩአቸውም ነበር፡፡ ጭፍሮቹም በፍለጋ ሲጓዙ ከአቡነ ሳዊሮስ ጋር በአንድ ቦታ የሚያድሩበት ጊዜም አለ ነገር ፈጽሞ አላዩአቸውም፡፡ #እግዚአብሔር አቡነ ሳዊሮስን ለምእመናን ጥቅም ሲል አሁን እንዲሞቱ አልፈቀደም ነበርና ጭፍሮቹም ፈልገው ባጧቸው ጊዜ ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡

አቡነ ሳዊሮስም ግብፅ አገር ከደረሱ በኋላ ከአንደኛው ገዳም ወደ አንደኛው ገዳም አንድ ተራ መነኩሴ መስለው በስውር የሚዘዋወሩ ሆኑ፡፡ በየሄዱበትም በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ምእመናንን የሚያጠነክሩ ሆኑ፡፡ #እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ድንቅ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን አደረገ፡፡ በአንዲት ዕለት አባታችን ወደ አስቄጥስ ገዳም በደረሱ ጊዜ በመጻተኛ መነኩሴ አምሳል ወደ አቡነ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ገቡ፡፡ በዚያም ቄሱ ዕጣንንና ቁርባንን ሊያሳርግ ጀመረና እንደ ሥርዓቱ እየዞረ አጠነ፡፡ ሐዋርያት የጻፏቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትና መልዕክቶቻውን የከበረ ወንጌልንም ካነበቡ በኋላ ቄሱ እጆቹን ታጥቦ ማኅፈዱን በገለጠው ጊዜ በጻሕሉ ውስጥ የቁርባኑን ኅብስት አላገኘውም፡፡ ደንግጦም መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ ከዚያም ወደ ሕዝቡ ተመልሶ ‹‹ወንድሞቼ እነሆ የቁርባኑ ኅብስት ተሰውሮ በጻሕሉ ውስጥ አላገኘሁትምና ይህ የሆነው በእኔ ኃጢአት ወይም በእናንተ ኃጢአት እንደሆነ ዐላወቅሁም›› አላቸው፡፡ ያንጊዜም የ #እግዚአብሔር መልአክ ለቄሱ ተልጦለት ‹‹ይህ የሆነው በአንተ ኃጢአት ወይም በሕዝቡ ኃጢአት አይደለም ነገር ግን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ እያለ መሥዋዕትን ለማሳረግ በመድፈርህ ነው›› አለው፡፡

ቄሱም በጣም ደንግጦ መልአኩን ‹‹ጌታዬ ሆይ! ሊቀ ጳጳሳት መኖሩን ዐላወቅሁም›› አለው፡፡ መልአኩም ተራ የመነኩሴ ልብስ ለብሰው ወደቆሙት ወደ አባ ሳዊሮስ አመለከተው፡፡ ቄሱም ወደ አቡነ ሳዊሮስ ሄዶ ከእግራቸው በታች ሰገደና ቡራኬ ተቀበለ፡፡ አባታችንም የጀመረውን ቅዳሴውን እንዲፈጽም ቄሱን አዘዙት፡፡ እርሳቸውንም በታላቅ ክብር ወደ ቤተ መቅደሱ አስገቧቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ቄሱ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ ተሰውሮበት የነበረውን የቁርባኑን ኅብስት በጻሕሉ ውስጥ መልሶ አገኘው፡፡ በዚህም ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ ምስጉን የሆነ ልዑል #እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡
የቁርባኑም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ካህናቱና ሕዝቡ ከአቡነ ሳዊሮስ ቡራኬ ተቀበሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባታችን አቡነ ሳዊሮስ ከአንደኛው ገዳም ወደ አንደኛው ገዳም አንድ ተራ መነኩሴ መስለው በስውር እየተዘዋወሩ በየሄዱበትም ምእመናንን እያጠነከሩ በእጆቻቸውም ብዙ ተአምራትን እያደረጉ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡

በመጨረሻም ስካ ወደሚባል አገር ሄደው ስሙ ዶራታዎስ ከሚባል ደግ ምእመን ባለጸጋ ሰው ዘንድ ተቀምጠው ሳለ #ጌታችን በእጆቻቸው ብዙ አስገራሚ ተአምራትን አደረገ፡፡ በመጨረሻም በዚህች ስካ በምትባል አገር የካቲት 14 ቀን እስካረፉ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁሉንም አስተማሯቸው፡፡ በኋላም ታኅሣሥ 10 ቀን ምእመናን ቅዱስ ሥጋቸውን ዝጋግ ወደምትባል ገዳም አፍልሰውታል፡፡ ጥቅምት 2 ቀን ደግሞ አባታችን ተሰደው ወደ ግብፅ አገር የመጡበት ዕለት ነው፡፡ ከእስክንድርያ ውጭ ወደሆነቸ ደብረ ዝጋግ ገዳም ቅዱስ ሥጋቸው በፈለሰበት ወቅት እንዲህ ሆነ፡- ቅዱስ ሳዊሮስ ስሓ በምትባል አገር አምላክም በሚወድ ደገኛ ክርስቲያን ባለጸጋ ስሙ ዱራታዎስ በሚባል ሰው ዘንድ ባረፉ ጊዜ ከምእመናን ሰዎች ጋር ወደ በመርከብ አሳፍሮ ላከው፡፡ ወደ ደቡባዊ ባሕረ ቅርጣስ በደረሱ ጊዜ ግን መርከባቸውን ማንቀሳስ ፈጽሞ አልተቻላቸውም፡፡

ከዚያም ወደ ደብረ ዝጋግ አድርሰው ያ ባለጸጋ ዱራታዎስ በሠራለት ቦታ ውስጥ አኖሩት፡፡ በግብጽ አገርም ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ #እግዚአብሔርም ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራቶችን ከሥጋቸው ገለጠ፡፡ ቅዱሱ በሕይወት ሳሉ የወለቀች አንዲት ጥርሳቸውን አንዱ መነኮስ አግኝቶ በጨርቅ ጠቅልሎ በገዳሙ አስቀምጧት ነበርና እርሷም ለሕሙማን ሁሉ ፈውስን የምትሰጥ ሆነች፡፡ እነርሱም ወደ እስክንድርያ ያመጧትና በሕሙማን ላይ ሲያኖሯት ሕሙማኑ ፈጥነው ይድናሉ፡፡ #እግዚአብሔርም ቅዱስ ሳዊሮስን በሕይወታቸው ካሉበት ጊዜ ይልቅ በሞት ካረፉ በኋላ እጅግ ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ ሳዊሮስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ኒቆላዎስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት አባ ኒቆላዎስ አረፈ፡፡ አባቱ ኤጲፋንዮስ እናቱ ዮና ይባላሉ፡፡ እርሱም ሜራ በምትባል አገር እጅግ ባለጸጎች ሆነው የሚኖሩ ደጋግ ሰዎች ናቸው፡፡ እጅግ ባለጸጎች ቢሆኑም ልጅ ስላልነበራቸው እያዘኑ #እግዚአብሔርን በመለመን ብዙ ዘመን ኖሩ፡፡ የመውለጃ ጊዜአቸውም ባለፈ ጊዜ ስለ ልጅ መለመናቸውን አቆሙ፡፡ #እግዚአብሔር ግን በመጨረሻ ዘመናቸው የተባረከ ይህን ኒቆላዎስን ሰጣቸው፡፡ #እግዚአብሔርም በልጃቸው ላይ የጽቅን ሥራ ገለጠ፡፡ ልጁ ገና እንደተወለደ ተነሥቶ በእግሮቹ ቆሞ በሰዎች መካከል ለሁለት ሰዓት ያህል ቆመ፡፡ ይህም ለመንፈሳዊ ሥራ የተነሣ ቅዱስ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ በሕፃንነቱም የሐዋርያትን ትምህርት ፈጽሞ ረቡንና ዓርብን በመጾም እስከ ዘጠኝ ሰዓት የእናቱን ጡት አይጠባም ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ለመምህር ሰጥተውት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ ተማረ፡፡ ወደ ገዳምም ገብቶ ማንም እንደ እርሱ ሊሠራው የማይችለውን ጽኑ ገድል ተጋደለ፡፡ አሰራ ዘጠኝ ዓመትም በሆነው ጊዜ ቅስና ተሾመና ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ማድረግ ጀመረና ሕመምተኞችን ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ፡፡ አንድ ባለጸጋ በሀገሩ ነበር፡፡ እርሱም የዕለት እራት እስኪያጣ ድረስ ፈጽሞ ድኃ ሆነ፡፡ አራት ሴት ልጆችም ነበሩትና እነርሱን ስለድኅነቱ የሚያገባቸው ጠፋ፡፡ ባለጸጋ የነበረውም ሰው የዝሙት ሙት ሠርቶ በዚያ ልጆቹ እያመነዘሩ በዝሙት ዋጋ ይኖሩ ዘንድ ይህንን የረከሰ ሀሳብ ሰይጣን አሳሰበው፡፡

#እግዚአብሔር ግን የዚያን ባለጸጋ የነበረ ሰው ክፉ ሀሳብ ለአባ ኒቆላዎስ ገለጠለት፡፡ አባ ኒቆላዎስም ከአባቱ ገንዘብ ላይ መቶ የወርቅ ዲናር ወስዶ በሌሊት ማንም ሳያየው ወደዚያ ባለጸጋ ወደነበረው ሰው ቤት ሄዶ በበሩ ሥር አስቀምጦለት ተመለሰ፡፡ ባለጸጋ የነበረውም ሰው ወርቁን ወስዶ እጅግ ደስ ብሎት ታላቂቱን ልጁን አጋባት፡፡ አሁንም ለ2ኛ ጊዜ አባ ኒቆላዎስ መቶ የወርቅ ዲናር አስቀመጠለትና ሰውየውም ሌላኛዋን ታላቅ ልጁን ዳራት፡፡ አባ ኒቆላዎስም ለ3ኛ ጊዜ እንዲሁ አደረገ፡፡ ባለጸጋውም በስተመጨረሻ ‹‹ይህን የሚያደርግልኝ የ #እግዚአብሔርን ሰው ማየት አለብኝ›› ብሎ ቁጭ ብሎ እያደረ በሌሊት የሚመጣውን መጠበቅ ጀመረ፡፡ አባ ኒቆላዎስም ለ4ኛ ጊዜ ወርቁን ሲያኖርለት አገኘውና ወድቆ ሰገደለት፡፡ ‹‹ከገንዘብና በኃጢአት ከመውደቅ አድነኸኛልና ዋጋህ ፍጹም ነው›› ብሎ አመሰገነው፡፡ አባ ኒቆላዎስ በአካባቢው ባለው ዛፍ ላይ አድረው በሰውየው ላይ መከራ ያመጡበትን አጋንንት አባረራቸው፡፡ በዚያ የነበሩ ሕመምተኞችንም አዳናቸው፡፡ ዳግመኛም ጥቂት እንጀራን አበርክቶ ብዙ ሕዝቦችን አጠገባቸው፡፡ እጅግ የበዛ ትራፊም ተመልሶ ተነሣ፡፡

ከዚህም በኋላ አባ ኒቆላዎስ ኤጲስቆጶስነት ከመሾሙ አስቀድሞ የክህነት ልብስንና ብርሃንን የለበሰ ሰው በዙፋን ላይ ተቀምጦ በራእይ አየና ‹‹ይህንን የክህነት ልብስ ለብሰህ በዙፋኑ ተቀመጥ›› የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም #እመቤታችን ተገልጣለት የክህነትን ልብስ ስትሰጠው #ጌታችንም የከበረች ወንጌልን ሲሰጠው አየ፡፡ ከዚህም በኋላ የሜራ አገር ኤጲስቆጶስ በሞት ባረፈ ጊዜ የታዘዘ መልአክ ለሮሜው አገር ሊቀ ጳጳስ ተገለጠለትና ስለ አባ ኒቆላዎስ መልኩንና ስሙን በዝርዝር ነገረው፡፡ እርሱም ለሕዝቡ ሁሉ ነገራቸው አባ ኒቆላዎስን ወስደው በሜራ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት፡፡

ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ አምለኮ ጣዖትን በግዛቱ ሁሉ ሲያውጅና የክርስቲያኖችን ደም እንደውኃ ሲያፈስ አባ ኒቆላዎስ ደግሞ ክርስቲያኖችን ያስተምራቸውና በሃይማኖት ያጸናቸው ነበር፡፡ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አባ ኒቆላዎስን ይዞ እጅግ ብዙ አሠቃየው፡፡ ነገር ግን #ጌታችን ከመከራው ሁሉ እያዳነው ከቁስሉም ይፈውሰው ነበር፡፡ ንጉሡም እጅግ ቢያሠቃየውም ቅዱሱ ደግሞ መልሶ ጤነኛ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ በዚህም ማሠቃየት ቢሰለቸው ወደ እሥር ቤት ጨመረው፡፡ #እግዚአብሔርም ዲየቅልጥያኖስን አጥፍቶት ጻደቁን ቆስጠንጢኖስን እስካነገሰው ድረስ አባ ኒቆላዎስ በእሥር ቤት ብዙ ዓመታት ኖረ፡፡ ቆስጠንጢኖስም የታሰሩትን ቅዱሳን ሁሉ በፈታቸው ጊዜ አባ ኒቆላዎስ ከእሥር ወጥቶ ወደ መንበረ ጵጵስናው ተመለሰ፡፡ ሕዝቡንም ስለቀናች ሃይማኖት አስተማራቸው፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና እጅግ የከበሩ 318 ቅዱሳን በአርዮስ ጉዳይ በተሰበሰቡ ጊዜ ይህ ቅዱስ አባት አባ ኒቆላዎስ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እርሱም ከሌሎቹ ቅዱሳን ጋር ሆኖ አርዮስን አሳዶ የቀናች ሃይማኖትን ደነገገልን፣ ሥርዓትን ሠራልን፡፡ እርሱም ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ኒቆላዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ጥዋሽ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት አባ ጥዋሽ አረፈ፡፡ ይኽም ቅዱስ ከልጅነቱ ጀምሮ ድንግል ሆኖ በምንኩስና በታላቅ ተጋድሎ የኖረ ነው፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ወደ እስክንድርያ ሲጓዝ በመንገድ ላይ አንዲት አይሁዳዊት ሴት ስታለቅስ አገኛትና ምን እንደሆነች ጠየቃት፡፡ እርሷም ‹‹ክርስቲያን መሆን እሻ ነበር›› አለችው፡፡ አባ ጥዋሽ የነፍሱን ጥቅም አስቦ ሊተዋት ነበር ግን ሴቲቱ መዳን እየፈለገች ቢተዋት በ #እግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ በደል እንዳይሆንበት ከእርሱ ጋር ወሰዳትና የክርስትና ጥምቀትን
አጠመቃት፡፡

ከዚህም በኋላ አባ ጥዋሽ ከሴቲቱ ጋር ሆኖ በየገበያው ቦታ ሁሉ እየዞሩ ለነዳያን ይመጸውቱ ጀመር፡፡ የእስክንድርያ መነኮሳትም እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አስበው በዚህ ተሰነካከሉበት፡፡ ይዘውትም ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ዮሐንስ ዘንድ አቀረቡት፡፡ አባ ዮሐንስም ሁለቱን ተያይተው እንዲታሰሩ አዘዙ፡፡ በዚያችም ሌሊት ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ዮሐንስ በሕልማቸው አባ ጥዋሽ የቆሰለ ጀርባውን እያሳያቸው ‹‹ያለበደሌ ለምን አቆሰልከኝ?›› ሲላቸው ተመለከቱ፡፡ አባ ዮሐንስም በነቁ ጊዜ አባ ጥዋሽን አስመጥተው በግርፋት ብዛት የቆሰለ ጀመርባውንና ፍጹም ድንግል መሆኑን አይተው እጅግ አዝነው አለቀሱ፡፡ ‹‹ይቅር በለኝ›› ብለው በፊቱ ወደቁ፡፡ ከዚያም አባ ጥዋሽን ያመጡትንና የደበደቡትን ሰዎች ከማዕረጋቸው አውርደው ለ3 ዓመታት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከመቀበል ከለከሏቸው፡፡ ካሳ ይሆነውም ዘንደ ለአባ ጥዋሽ ብዙ ገንዘብ ቢሰጡት እርሱ ግን ምንም ሳይቀበል ወደ በዓቱ ተመልሶ ሄዶ ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ዕለት ዐረፈ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሱርስት

ይኽችም ቅድስት ከቁስጥንጥንያ አገር እጅግ ከከበሩ ወገኖች የአንዱ ልጅ ናት፡፡ ለአንድ ለከበረ ሰው ልጅ በታጨች ጊዜ አባቷን ‹‹አባቴ ሆይ! አስቀድሜ ወደ ቤተ መቅደስ ሄጄ እሰግድ ዘንድ ፍቀድልኝ በምመለስበት ጊዜ #እግዚአብሔር እንደፈቀደ ይሁን›› አለችው፡፡ አባቷም ‹‹አስቀድመሽ ወደ ባልሽ ግቢ፣ ሠርግሽ ከተፈጸመ በኋላ ከእርሱ ጋር ወደ ወደድሽው ሄደሽ ስዕለትሽን ትፈጽሚያለሽ›› አላት፡፡ እርሷም መልሳ ‹‹በድንግልናዬ ሳለሁ ወደዚያች የከበረች ቦታ ሄጄ ልጸልይ ለ #እግዚአብሔር ቃል ገብቻለሁና ቃሌን ብዋሽ ፈጣሪ በእኔ ላይ ይቆጣል›› ስትለው አባቷ ከሚያገለግሏት ወንዶችና ሴቶች አሽከሮች ጋር ለምጽዋትም የምትሰጠው 300 የወርቅ ዲናር ሰጥቶ ላካት፡፡

ሱርስትም እዚያ በደረሰች ጊዜ የከበሩ ቦታዎችን ሁሉ እየዞረች ተሳለመች፣ ወደ ግብጻውያን ገዳምም በደረሰች ጊዜ አንድ አረጋዊ መነኩሴ ማቅ ለብሶ አገኘችውና የልቧን ሀሳብ ሁሉ ማለትም ልትመነኩስ እንደምትፈልግ ነገረችው፡፡ እርሱም ‹‹የ #እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሊሄዱ በተዘጋጁ ጊዜ ወደ ስውር ቦታ ገብታ ለወላጆቿ ‹‹እኔ ሰውነቴን ለ #እግዚአብሔር አቅርቤያለሁ አታገኙኝምና አትፈልጉኝ›› ብላ ደብዳቤ ጻፈች፡፡ ደብዳቤውንም በልብሷ አሥራ ከዕቃ ውስጥ አኖረችው፡፡ ሰዎቹም ከእነርሱ ጋር አብራ የምትሄድ መስሏቸው ዕቃ ጭነው በቀደሟት ጊዜ አንዱን አገልጋይ ይዛ አስቀረችውና ‹‹ወደ ጎልጎታ ገብቼ ልጸልይ እሻለሁና›› ብላ ምሥጢሯን እንዲጠብቅ ነገረችው፡፡

ከዚህም በኋላ ወደዚያ ሽማግሌ መነኩሴ ዘንድ ተመልሳ የያዘችውን 300 የወርቅ ዲናር ለድኆችና ጦም አዳሪዎቸ እንዲያከፋፍለው ሰጠችውና ያመነኩሳት ዘንድ ለመነችው፡፡ እርሱም ጽናቷን አይቶ ፈቃደ #እግዚአብሔርም መሆኑን ዐውቆ ራሷን ላጭቶ የምንኩስና ልብስ አለበሳት፡፡ እርሷም #እግዚአብሔር ወደፈቀደላት ወደ አንዲት ዋሻ ሄዳ በዚያ በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመረች፡፡ በዚህም ጊዜ ዕድሜዋ ገና 12 ዓመት የነበረ ቢሆንም የሰውን ፊት ሳታይ በዚያች ዋሻ ውስጥ ለ27 ዓመታት በተጋድሎ ኖረች፡፡

ቃህራ ከሚባል አገር በገድል ሥራ የሚኖር ሲላስ የሚባል መነኮስ ነበር፡፡ በቀልሞን ዋሻ የሚኖር አንድ ጓደኛ መነኮስ አለውና ፋሲካ በደረሰ ጊዜ እርሱን ጎብኝቶ በረከት ለመቀበል ሄደ፡፡ በሄደም ጊዜ አላገኘውምና እርሱን ፍለጋ ተራራ ለተራራ ዞረ፡፡ በዚያም የእግር ዱካ አገኘና ዱካውን ተከትሎ በመሄድ መግቢያው ላይ ሲደርስ ‹‹የ #እግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ባርከኝ›› አለ፡፡ ከውስጥም ያለው ድምጽ ስሙን ጠርቶት ‹‹ሲላስ ሆይ አንተ ካህን ነህና ልትባርከኝ ይገባል›› አለው፡፡ ሲላስም ወደ ውስጥ እንደገባ ቅድስት ሱርስትን አገኛት፡፡ እርሷም ምሥጢሯን ሁሉ በዝርዝር ነገረችው፡፡ ወዲያውም በሰላም ዐረፈች፡፡ ሲላስም በዚያች ዋሻ ውስጥ በክብር ገንዞ ቀበራት፡፡ ገድሏንም ጻፈላት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ሱርስት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ሰማዕታት_ተላስስና_አልዓዛር

ቅዱስ ተላስስ ከነነዌ አውራጃ ከባቢሎን ሰዎች ወገን ነው፡፡ #ጌታችንን በማመኑ ምክንያት ከሃዲው የፋርስ ንጉሥ ሳቦር ይዞት ብዙ አሠቀየው፡፡ ለአማልከቱም እንዲሠዋ ተላስስን ባስገደደው ጊዜ ቅዱሱ ግን አማልክቱን ረገመበት፡፡ ንጉሡም በተለያዩ የማሠቃያ መሣሪያዎች አሠቃየው፡፡ መቶ ጊዜ ካስገረፈው በኋላ ‹‹ተላስስ ሆይ! ከዚህ ሥቃይ እንድታርፍ ለአማልክት ሠዋ›› አለው፡፡ ቅዱስ ተላሰስስም ‹‹ፈጣሪዬ ስለሚጠብቀኝ ሥቃይህ ለእኔ አልታወቀኝም›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ ቅዱስ ተላስስን ሁለት መቶ ጽኑ ግርፋትን ካስገረፈው በኋላ በዓይኖቹ ወስጥ የብረት ችንካሮችን ተክለው እጅግ አሠቃዩት፡፡ መናገር እስከማይችል ደረስ ምላሱንም ቆርጠው ካሠቃዩት በኋላ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት ፍጻሜው ሆኖ የክብርን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ ከዚህም በኋላ አልዓዛርን በንጉሥ ሳቦር ፊት አቀረቡት፡፡ ንጉሡ እርሱንም ‹‹ለአማልክት ሠዋ›› አለው፡፡ አልዓዛርም ‹‹ለረከሱ አማላክትህ አልሠዋም እኔስ #ጌታዬን_ፈጣሪዬን_ኢየሱስ_ክርስቶስን አመልካለሁ እንጂ›› አለው፡፡ ንጉሡም ወዲያው ተናዶ ቅዱስ አልዓዛርን ወደ እቶን እሳት ውስጥ ወረወረው፡፡ ቅዱሱም በዚያው ሰማዕትነቱን ፈጸመ፡፡

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_10 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ቲቶ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤
⁶ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው።
⁷ ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥
⁸ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤
⁹ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና።
¹⁰ የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤
¹¹ እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል።
¹² የገዛ ራሳቸው ነቢይ የሆነ ከእነርሱ አንዱ፦ የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸተኞች፥ ክፉዎች አራዊት፥ በላተኞች፥ ሥራ ፈቶች ናቸው ብሎአል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ።
²¹ እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም።
²² ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።
²³ ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።
²⁴ እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።
²⁵ እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።
²⁶ ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።
²⁷ እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።
²⁸ አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።
²⁹ ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።
¹⁷ ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው፤
¹⁸-¹⁹ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ፥ በትሕትና ሁሉና በእንባ ከአይሁድም ሴራ በደረሰብኝ ፈተና ለጌታ እየተገዛሁ ዘመኑን ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዴት እንደ ኖርሁ እናንተው ታውቃላችሁ፤
²⁰-²¹ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፥ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_10_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዘረወ ወወሀበ ለነዳይ። ወጽድቁኒ ይነብር ለዓለም። ወይትሌዓል ቀርኑ በክብር"። መዝ 109፥9።

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_10_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።
² እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
³-⁴ አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።
⁵ ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ኒቆላዎስ፣ የአባ ጥዋሽ የቅድስት ሱርስት፣ ቅዱሳን ሰማዕታት ተላስስና አልዓዛር የዕረፍታቸው በዓል፣ አቡነ ሳዊሮስ የሥጋ ፍልሰት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ አንድ በዚህች ዕለት ታላቁ አባት #ቅዱስ_አባ_በኪሞስ ዐረፈ፣ ታላቁ ሰማዕት #ቅዱስ_ገላውዲዮስ ልደቱ ነው፣ #ቅዱስ_በጥላን መታሰቢያው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_አባት_ቅዱስ_አባ_በኪሞስ

ታኅሣሥ ዐስራ አንድ በዚህች ዕለት ታላቁ አባት ቅዱስ አባ በኪሞስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ከደቡባዊ ግብጽ መጺል ከምትባል አውራጃ የተገኘ ታላቅ አባት ነው፡፡ እርሱም የአባቱን በጎች የሚጠብቅ እረኛ ነበር፡፡ ዕድሜውም 12 ዓመት በሆነው ጊዜ ከ #እግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ በሰው አምሳል ተገለጠለትና ‹‹በአንድነት ሄደን እንመነኩስ ዘንድ ትሻለህ?›› አለው፡፡ በኪሞስም በዚህ ደስ ተሰኝቶ ሁሉቱም ተስማምተው አብረው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ገቡ፡፡ በዚያም ሦስት አረጋውያን መነኮሳት አገኙና አባ በኪሞስ ከእነርሱ ጋር 24 ዓመታትን ኖረ፡፡

ከዚህም በኋላ አባ በኪሞስ ከዚያ ተነሥቶ የሦስት ቀን ጎዳና ተጓዘና ሩቅ ወደሆነ በረሃ ሄደ፡፡ በዚያም ሰይጣናት በእሪያዎችና በዘንዶዎች አምሳል ሆነው መጡበት፡፡ ሊነክሱትም አፋቸውን ከፍተው በከበቡት ጊዜ እርሱ ግን የአጋንንት ሥራ መሆኑን ዐውቆ በ #እግዚአብሔር ኃይል እፍቢልባቸው እንደትቢያ ተበተኑ፡፡ እርሱም ወንዝ አግኝቶ ሰባት ሰባት ቀን እየጾመ በዚያ ሦስት ዓመት ኖረ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ ላይ በእጁ ቴምር በተአምራት መልቶ ስለሚገኝ እርሱን ይመገባል፡፡ ቅዱሱም በሌሊት ሁለት ሺህ አራት መቶ ጊዜ በቀንም እንዲሁ ሁለት ሺህ አራት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልያል፡፡ ከዚህም በኋላ 40 40 ቀን እየጾመ 24 ዓመታትን በታላቅ ተጋድሎ ኖረ፡፡ አርባውም ቀን ሲፈጸም አንድ ጊዜ ይመገባል፡፡ ከዚህም በኋላ ቆዳው ከአንጥንቱ እስኪጣበቅ ድረስ አንድ ጊዜ እስከ ሰማንያ ቀን ጾመ፡፡ በዚህም ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ አባ በኪሞስ የሚበላውንና የሚጠጣውን ሰማያዊ የሕይወት ምግብና መጠጥ አምጥቶ መገበው፡፡ ያንንም መልአክ ያመጣለትን ምግባ መጠጥ አባ በኪሞስ እስካረፈበት ጊዜ ድረስ ብዙ ዓመታት ሲመገበው ኖረ፡፡

በአንደኛውም ቀን በሌሊት #ጌታችን ለአባ በኪሞስ ተገልጦለት ወደ አገሩ እንዲመለስ ነገረው፡፡ እርሱም ወደ ሀገሩ ተመልሶ በዚያች ትንሽ በዓት አበጅቶ መኖር ሲጅር ብዙዎች ወደ እርሱ መጥተው ፈውስን የሚያገኙ ሆኑ፡፡ እርሱም ጣዕም ባለው አንደበቱ ወንጌልን እያስተማራቸው ድውያንንም ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ፡፡ በአንዲት ዕለትም የታዘዘ መልአክ መጥቶ አባ በኪሞስን ነጥቆ ወስዶ ወደ ኤፍራጥስ ምድር አደረሰው፡፡ የዚያች አገር ሰዎች ሕግን በመተላለፍ ከእውነተኛ ሃይማኖት ወጥተው ነበርና፡፡ አባ በኪሞስም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖትና ወደ በጎ ምግባር መለሳቸውና ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡ በአንዲት ዕለትም ሸጦ የዕለት ምግቡን ያገኝ ዘንድ አገልግሎችን ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲሄድ በጎዳና ላይ ደክሞት አገልግሎቹን አስቀምጦ ያርፍ ዘንድ ተቀመጠ፡፡ ወዲያውም ከአገልግሎቹ ጋር #የእግዚአብሔር ኃይል ተሸክሞ ወስዶ ከሚሸጥበት ቦታ አደረሰው፡፡

በአንደኛውም ቀን ታላቁ አባት አባ ሲኖዳ ከፍተኛ የዕንቁ ባሕርይ ምሰሶ በራእይ አየና ‹‹ይህ ታላቅ ግሩም የሆነ ምሰሶ ምንድነው?›› ብሎ ደነገጠ፡፡ የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና ‹‹ይህ አባ በኪሞስ ነው›› አለው፡፡ አባ ሲኖዳም አባ በኪሞስን ያገኘው ዘንድ ወደ እርሱ አገር በእግሩ ተጓዘ፡፡ ከዚያም በፊት ከቶ አላየውም ነበር፡፡ ሄዶም ባገኘው ጊዜ ሁለቱ ቅዱሳን ሰላምታ ተሰጣጡና የ #እግዚአብሔርን ነገር እየተነጋገሩ አብረው እየጸለዩ ጥቂት ቀን ቆዩ፡፡ በአንዲት ዕለት አብረው ሲጓዙ አንድን የሞተ ሰው ራስ ቅል አገኙና አባ ሲኖዳ በበትሩ ነቅነቅ አደረገውና ‹‹ምውት ሆይ! ያየኸውን ትነግረን ዘንድ በ #ጌታችን ስም ተነሥ›› አለው፡፡ ወዲውም ነፍሱ ወደ ዐፅሙ ተመልሳ ሥጋ ለብሶ ተነሣና ሰገደላቸው፡፡ በሲኦል ያየውንም ሁሉ በዝርዝር ነገራቸው፡፡ በየወገናቸው በሲኦል ውስጥ የሚሠቃዩትንና እርሱም የማያምን አረማዊ መሆኑን ነገራቸው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ክብር ይግባውና በ #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ያመኑ ትእዛዙን ግን ያልጠበቁ በአሕዛብ ሥራባ በአረማውያን ርኩሰት የኖሩ በሲኦል ከእኛ በታች የሚኖሩ ክርስቲያኖች አሉ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹በል ተመልሰህ ተኛ›› አሉትና እንቀድሞው ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ሲኖዳ አባ በኪሞስን ተሰናብቶ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡

አባ በኪሞስም የዕረፍቱ ጊዜ ሲደርስ አገልጋዩን ጠርቶ የሥጋውን መቅበሪያ ቦታ አሳየው፡፡ ወዲያውም በሆድ ዝማ ሕመም ጥቂት ታመመና፡፡ ቅዱሳንም ከተለያየ ቦታ በአንድነት ወደእርሱ ሲመጡ በመንፈስ ተመለከተ፡፡ ቅዱሱ 58 ዓመት በገዳም በምንኩስና ሥራ ተጠምዶ ኖሮ በሰባ ዓመቱ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በዝማሬ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም አሳረጓት፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ በኪሞስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_ሰማዕት_ቅዱስ_ገላውዲዮስ

ዳግመኛም በዚህች ዕለት ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዲዮስ ልደቱ ነው፡፡ ገላውዴዎስ ማለት ‹‹ዕንቈ ጳዝዮን›› ማለት ነው፡፡ የመላእክት አርአያ ያለቅ ቅዱስ ገላውዴዎስ አባቱ አብጥልዎስ የሮሙ ንጉሥ የኑማርያኖስ ወንድም ነው፡፡ አባቱን የአንጾኪያ ሰዎች እጅግ ይመኩበትና ይወዱት ነበር፡፡ በሕይወት እያለም በጦርነት ድል ሲያደርግ የሚያሳይ ሥዕሉን በከተማው ላይ አሠርተው ያከብሩት ነበር፡፡ ልጁ ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተማረ አደገ፡፡ የሮሙ ንጉሥም ዜናውን ሰምቶ ሊያየው ወደደና ልጁን እንዲልክለት መልእክት ላከ፡፡ ሄዶ ሲያየውም ንጉሡ ከነሠራዊቱ ወጥቶ በክብር ተቀበለው፡፡

ጣዖት አምላኪ የሆኑ የቁዝና የሌሎችም ሀገሮችን ቅዱስ ገላውዴዎስ ድል እያደረጋቸው ጣዖቶቻቸውንም ይሰባብርባቸው ነበር፡፡ ወደ አንጾኪያም በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስ #ጌታችንን ክዶ ጣዖት ማምለክ መጀመሩን ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ከቅዱስ ፊቅጦርም ጋር ሆነው የመጻሕፍትን ቃል ዕለት ዕለት ያነቡ ነበር፡፡ ሁለቱም ስለ #ጌታችን ክብር ሰማዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ በምክር ተስማሙ፡፡ ሰይጣንም በሽማግሌ አምሳል ተገልጡ ያዘነላቸው በመምስል ‹‹ልጆቼ ሆይ መልካም ጎልማሶች ናችሁ፣ የነገሥታት ልጆችም ናችሁ፣ እኔ ስለ እናንተ አዝንላችኋለሁ ስለዚህም ከንጉሡ ጋር ተስማምታችሁ አማልክቶቹን እያጠናቸሁ ትእዛዙንም እየፈጸማችሁ ኑሩ፡፡ ነገር ግን #ክርስቶስን በቤታችሁ አምልኩት ይህ ዲዮቅልጥያኖስ ግን እጅግ ጨካኝና ኃይለኝ ነው›› እያለ መከራቸው፡፡ #እግዚአብሔርንም ይህን የሚናገራቸው ሰይጣን መሆኑን ገለጸላቸውና ‹‹አንተ የሐሰት አባት ሁልጊዜ የ #እግዚአብሔርን ሀሳብ ትቃረናለህ›› ብለው በገሠጹት ጊዜ መልኩን ለውጦ ጥቁር ባሪያ ሆነ፡፡ ‹‹እነሆ ከንጉሡ ጋር አጣልቼ ደማችሁን እንዲፈስ አደርገዋለሁ›› ብሎ ወደ ከሃዲው ንጉሥ ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ሄዶ ‹‹ፊቅጦርንና ገላውዴዎስን ካልገደልካቸው በአንተ ላይ ይነሱብሃል፣ አንተንም ገድለው መንግሥትህን ይወስዳሉ፣ እነርሱም የመንግሥት ልጆች መሆናቸውን ዕወቅ›› አለው፡፡
ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን አስጠርቶ የአባቱን ሹመት እንደሚሾመው ቃል ከገባለት በኋላ ለጣዖቱ እንዲሠዋ አዘዘው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስ ግን በድፍረት ጣዖቱንና ንጉሡን ሰደባቸው፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኅርማኖስ የተባለው ባለሟሉ ‹‹እንደ ልጄ ፊቅጦር ዐመፀኛ ነውና ወደ እስክንድርያ ልከነው በዚያ እንዲገድሉት እናድርግ›› ብሎ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን መከረው፡፡ አሠቃይተው እንዲገድሉትም ከደብዳቤ ጋር አድርገው ወደ እንዴናው ሀገር ገዥ ወደ ጨካኙ አርያኖስ ላኩት፡፡

አርያኖስም ቅዱስ ገላውዴዎስን ባየው ጊዜ ደንግጦ በክብር ተቀበለው፡፡ እጅ ነሥቶም ከሳመው በኋላ ‹‹ጌታዬ ስለምን የንጉሡን ትእዛዝ ትተላለፋለህ?›› እያለ መከረው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስም ‹‹ንጉሡ ያዘዘህን ትእዛዝ ልትፈጽም እንጂ በነገርህ ልታስተኝ አልተላኩም›› አለው፡፡ መኮንኑም እስኪቆጣ ድረስ ብዙ ጊዜ እያባበለው ተነጋገሩ፡፡ ከዚህም በኋላ አርያኖስ እጅግ ተቆጣና በያዘው ጦር ወግቶ ቅዱሱን ገደለው፡፡ ቅዱስ ገላውዴዎስም የሰማዕትነት አክሊልን ሰኔ 11 ቀን ተቀዳጀ፡፡ ምእመናንም የመከራው ዘመን እስኪፈጸም ቅዱስ ሥጋውን ወስደው ከቅዱስ ፊቅጦር ጋር በሣጥን አኖሩት፡፡ የቅዱስ ፊቅጦርም እናት ቅድስት ሶፍያ ወደ እንዴና ሀገር መጥታ የሁለቱን ቅዱሳን ሥጋቸውን ወደ አንጾኪያ ወስዳ በክብር አኖረችው፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ገላውዴዎስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_በጥላን_ጠቢብ_ሰማዕት

አባቱም አረማዊ ነበረ ስሙም አውሱጢኪዮስ ነበር እናቱ ግን አማኝ ነበረች ስሟም ኤልያና ነበር። በአደገ ጊዜም አባቱ ጥበብን ሁሉ አስተማረው እጅግም አዋቂ ሆነ።

በበጥላን ቤት አቅራቢያም አንድ ቄስ ይኖር ነበር። በጥላንም በፊቱ ሲያልፍ መልኩንና ዕውቀቱን ብልህነቱንና አሰተዋይነቱንም ይመለከት ነበር ከሀዲ ስለመሆኑም ስለርሱ ያዝን ነበር። ቄሱም በጥላንን መንገድ መርቶ ወደ ቀናች ሃይማኖት ያስገባው ዘንድ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ለመነው።

ስለ በጥላንም ልመናውን በአዘወተረ ጊዜ በጥላን በእርሱ እጅ ያምን ዘንድ እንዳለው #ጌታችን በራእይ ገለጠለት ቄሱም ደስ አለው ሁልጊዜም በፊቱ ሲያልፍ በጥላንን ያነጋግረውና ሰላምታ የሚሰጠው ነበር። ስለዚህም በመካከላቸው ፍቅር ጸና።

ከዚህም በኋላ በጥላን ወደ ቄሱ ቤት ይገባና ስለ ሃይማኖት ይነጋገር ነበር። ቄሱም ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት ምን ያህል ክብር እንዳላት ለሚያምኑበትም ሁሉ ዕውቀትና ማስተዋል እንደሚሰጣቸው ድንቆችና ታላላቅ ተአምራቶች እንደሚደረግላቸው ታላቅ ፈውስም እንደሚያደርጉ ገለጠለት።

በጥላንም ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ የሚያምኑ ተአምራትን እንደሚያደርጉ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት በዚያ ቄስ ትምህርት በ;#ጌታ አመነ ቄሱም ሁልጊዜ የሃይማኖትን ትምህርት ያስተምረው ጀመር።

በአንዲትም ዕለት ቅዱስ በጥላን በከተማው አደባባዮች ሲያልፍ እባብ የነደፈውን አንድ ሰው ሲጨነቅ አየው እባቡም በርሱ ዘንድ ቆሞ ነበር በልቡም የመምህሬን ቃል ልፈትን ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ ከአመንክ በስሙ ታምራት ታደርጋለህ ብሎኛልና አለ። እባብ ወደ ነከሰውም ሰው ቀርቦ ኃይሉን ይገልጽለት ዘንድ እባቡንም ይገድለው ዘንድ ሰውዬውን ያድነው ዘንድ ክብር ይግባውና ወደ #እግዚአብሔር ረጅም ጸሎትን ጸለየ ያን ጊዜም ሰውዬው ያለ ምንም ጉዳት ድኖ በጤና ተነሣ ከይሲውም ወደቀ ወዲያውም ሞተ። የበጥላንም ሃይማኖቱ ተጨመረለት።

ከዚህም በኋላ በጥላን ወደ ቄሱ ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ሁልጊዜም ወደ ቄሱ እየመጣ ይማር ነበር። በአንዲት ቀንም ያድነው ዘንድ አንድ ዕውር መጣ። የቅዱስ በጥላን አባትም ባየው ጊዜ ዕውሩን ከውጭ መልሶ ሰደደው በጥላንም አባቱን ማነው የፈለገኝ ብሎ ጠየቀው አባቱም ልታድነው የማትችል አንድ ዕውር ነው አለው።

እርሱም አባቱን የ #እግዚአብሔርን ክብር ታይ ዘንድ አለህ አለው ይህንንም ብሎ ዕውሩን ጠራውና ዐይኖችህ ቢገለጡ ያዳነህን ታመልከዋለህን አለው ዕውሩም አዎን አምናለሁ አለ ቅዱስ በጥላን በዕውሩ ላይ ረጅም ጸሎትን ጸለየ እጆቹንም በዕውሩ ዐይኖች ላይ አኑሮ እንድታይ በ #ጌታችን_በኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እመን አለው ወዲያውኑም ዐይኖቹ ተገለጡ።

አባቱም ይህን ድንቅ ሥራ በአየ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታ_በኢየሱስ_ክርስቶስ ከዕውሩ ጋር አመነ ቅዱስ በጥላንም ወደ ቄሱ ወሰዳቸውና የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ከዚህም በኋላ ባሮቻቸውን ነፃ አወጡ ገንዘባቸውንም ለድኆችና ለችግረኞች አከፋፈሉ።

ቅዱስ በጥላንም ጥበብን ያደርግ ነበር። ያለ ዋጋም ሰዎችን ያድናቸው ነበር። ነገር ግን ክብር ይግባውና በ #ክርስቶስ እንዲያምኑ ይሻ ነበር። ስለዚህም ጥበበኞች ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሡ ወደ ንጉሥም ሒደው ከቄሱ ጋራና ከአዳነውም ዕውር ጋራ በ #ጌታችንም ከአመኑ ከብዙዎች ጋራ ከሰሱት። ወደ ንጉሡም በቀረቡ ጊዜ ንጉሡ ተቆጥቶ ለአማልክት ሠዉ አላቸው ባልታዘዙለትም ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ በጥላንን የጸና ሥቃይን አሠቃየው። ከእርሱም ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ በእጁም ብዙ ሰዎች ክብር ይግባውና በ #ጌታችን አመኑ። በሰማዕትነትም ሞቱ። ንጉሡም አይቶ በበጥላን ላይ ተቆጣ። ለአንበሳም አስጣለው አንበሳውም እግሩን ላሰው እንጂ ክፉ አላደረገበትም። ሁለተኛም ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ በዚህም ሐምሌ 19 ቀን ምስክርነቱን ፈጽሞ በመንግሥተ ሰማያት አክሊልን ተቀበለ።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አና ጻድቃን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ_11 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤
¹⁰ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤
¹¹ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤
¹² በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤
¹³ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ።
¹⁴ የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ።
¹⁵ ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ።
¹⁶ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ።
¹⁷ ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ።
¹⁸ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።
¹⁹ ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።
²⁰ ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና።
²¹ ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ እንደ ሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና።
⁷ ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥
⁸ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።
⁹ ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤
¹⁰ ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤
¹¹ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።
²⁹ እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።
³⁰ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤
³¹ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።
³² የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።
³³ እንዲሁም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጣ።
³⁴ አንዳንዶች ወንዶች ግን ተባብረው አመኑ፤ ከእነርሱ ደግሞ በአርዮስፋጎስ ያለው የፍርድ ቤት ፈራጅ ዲዮናስዮስ ደማሪስ የሚሉአትም አንዲት ሴት ሌሎችም ከእነርሱ ጋር ነበሩ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወይነግሩኑ እለ ውስተ መቃብር ሣህለከ። ወጽድቀከኒ ውስተ ሞትኑ። ይትዐወቅኑ ውስተ ጽልመት መንክር"። መዝ. 87፥11-12።
"በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን፥ እውነትህንስ በጥፋት ስፍራ ይናገራሉን?
ተአምራትህ በጨለማ፥ ጽድቅህንም በመርሳት ምድር ትታወቃለችን"? መዝ. 87፥11-12።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ታኅሣሥ_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።
⁸ ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።
⁹ እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥
¹⁰ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤
¹¹ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤
¹² እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤
¹³ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።
¹⁴ ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤
¹⁵ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።
¹⁶ ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ በኪሞስ የዕረፍት በዓል፣ የቅዱስ ገላውዴዎስ የልደት በዓልና የነቢያት የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"የምታምሩ ሽማግሌዎች ብፁዕ ኢያቄምና ብፅዕት ሐና ሆይ እንደ ሰማይ ከፍ ያላችሁ እንደ ምድርም የረጋችሁ ናችሁ። እንደ ዕንቁ የምታበሩ እንደ ወርቅም የተፈተናችሁ። #እግዚአብሔር የእናንተን ሥጋ ይዋሐድ ዘንድ እናንተን መረጠ።

#ድርሳነ_ቅዱስ_ኢያቄም_ወቅድስት_ሐና_ዘዓርብ
#ታኅሣሥ_12

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ ዐስራ ሁለት #የመላእክት_አለቃ_የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #የአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ ዐረፉ፣ #ቅዱሳን_አንቂጦስ እና #ቅዱስ_ፎጢኖስ በሰማዕትነት ዐረፉ፣ #በዚችም_ቀን_የቅዱሳን_ኤጲስቆጶሳት_የቀሳውስትና_የዲያቆናት የአንድነት ስብሰባ በሮሜ ከተማ ሆነ፣ #ዳግማዊ_ቂርቆስ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጅ ብሔረ ብፁዓን የገባበት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሚካኤል

በዚች ቀን በዚህ ወር #እግዚአብሔር ወደባቢሎን አገር ላከው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሦስቱን ልጆች አናንያን አዛርያንና ሚሳኤልን ከእሳት ማንደጃ ውስጥ በጣላቸው ጊዜ አራተኛ ገጽ ሁኖ ታየ።

የእሳቱም ነበልባል አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል ወደላይ ከፍ ከፍ አለ የጨመሩአቸውን ሰዎችና እሳት የሚያንዱትን አቃጠላቸው ይህም የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል የእሳቱን ነበልባል በበትሩ መትቶ ከሠለስቱ ደቂቅ ላይ አጥፍቶ አዳናቸው ምንም አልነካቸውም እንደ ቀዘቀዘ እንደ ጧት ጤዛ አድርጎታልና።

በዚያንም ጊዜ የአባቶቻችን ፈጣሪ #እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን እያሉ ስድስት ቃላትን ተናገሩ በዚህም ከስድስት መቶ ዓመት በኋላ #ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናገሩ።

ከዚህም በኋላ የ #ጌታ_እግዚአብሔር ሥራዎቹ ሁሉ ያመሰግኑታል እርሱ ለዘላለሙ ምስጉን ልዑልም ነው እያሉ ሠላሳ ሦስት ጊዜ አመሰገኑት በዚህም በምድር ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት #ክርስቶስ እንደሚኖር አመለከቱ፤ ስለዚህም አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያን መምህራን የመላእክት አለቃ የሆነ የ #ቅዱስ_ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ እንድናደርግ ሠሩ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም #በቅዱስ_ሚካኤል አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አርኬ
✍️ ሰላም ለከ ዐቃቤ ቅዱሳን እምተሀውኮ። ወለፀረ ነፍሶሙ ዘሞቃኮ። አመ መጽአ ወልድ በአፈ ነቢያት ተሰቢኮ። ከመ ያስተፋኑ ሐራ መልአኮ። እስከ ምጽንዓት ኃምስ ሚካኤል ተለውኮ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ

ታኅሣሥ ዐስራ ሁለት በዚህች ዕለት ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የ #ሥሉስ_ቅዱስን መንበር ያጠኑ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ዋሊ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ የተወለዱት በአክሱም ጽዮን ነው፡፡ ነገዳቸው የአክሱም ገበዝ ከነበረው ከጌድዮን ነው፡፡ የአባታቸው ስም እስጢፋኖስና እናታቸው አመተ #ማርያም ምግባር ሃይማኖታቸው የቀና ትሩፋት ተጋድሏቸው የሰመረ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ገና በ12 ዓመቱ ማይ ሹም በተባለው ባሕር ገብቶ ሲጸልይ ባሕሩ በብርሃን ተከቦ ይታይ ነበር፡፡ ከባሕሩም ወጥቶ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ እያለቀሰና እያዘነ ሲጸልይ ካህናቱ ‹‹ይህ ሕፃን የእኛ ኃጢአት እየታየው? ወይስ ምን ኃጢአት ኖሮበት ነው እንዲህ የሚያዝነውና የሚያለቅሰው?›› እያሉ ያደንቁና ይገረሙ ነበር፡፡

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ እናቱ አመተ ማርያም ቤተሰቧንና ቤት ንብረቷን ትታ ከመነኮሰች በኋላ እርሱም ካልመነኮስኩ በማለት አባቱ እስጢፋኖስን ቢለምነውም እምቢ ስላለው በራሱ ፈቃድ ከአንድ ሽማግሌ ጋር ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ደብረ በንኰል ገብቶ መነኮሰ፡፡ በዚያም ነፍሱን ‹‹ነፍሴ ሆይ! እነሆ ለ #ክርስቶስ ታጨሽ፣ የቅዱሳንን ቀንበር እንሆ ተሸከምሽ፣ የመላእክትን ንጽሕና ትጠብቂ ዘንድ ዛሬ በ #እግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ሁሉ ፊት ቃልኪዳን ገባሽ፣ ቃልኪዳንሽን ብትጠብቂ መላእክት ይደሰቱብሻል፣ ባትጠብቂ ግን አጋንንት ይዘባበቱብሻል…›› እያለ ብዙ መከራን በራሱ ላይ በማብዛት ሰባት ዓመት በዚያች ገዳም ኖረ፡፡ እህልም አይቀምስም ነበር ይልቁንም የሚሰጡትን እንጀራ ለሕጻናትና ለውሾች እየሰጠ አሠር ይመገብ ነበር፡፡

ዳግመኛም በሌላ ጊዜ ቅጠልን እየቀቀለ እስከ አምስት ቀን ከድኖ ያስቀምጠዋል፣ እስከሚተላም ድረስ ይጠብቀውና ያን ይመገባል፡፡ ኩስይ የምትባል ከሣር ሁሉ የምትመርን ሣር ምግቡ አደረገ፡፡ በኋላም አባቱም ልጁን ሳሙኤልን ተከትሎ ወደ እርሱ መጥቶ በአባ እጅ መነኮሰ፡፡ ለአባቱም መምህር ሆኖት እያገለገለው ያስተምረው ነበር፡፡ በሌላም ጊዜ 17 ዓመት ከተቀመጠባት ወይና በምትባል ቦታ ሲኖር ከውኃ በቀር ምንም ሳይቀምስ 12 ዓመት ተቀምጧል፡፡ ለ50 ዓመትም ያህል ሣር፣ ቅጠል፣ የዛፍ ሥርና ፍሬን እነዚህንና የመሳሰሉትን እየበላ ኖረ እንጂ እህል የሚባል አልበላም፡፡

ወጥቶም ወደ ዋሻ እየገባ ብዙ ጊዜ 40 ቀንና 40 ሌሊት በጾም በጸሎት እየኖረ እንቅልፍም እንዳያሸንፈው እስከሚነጋ ድረስ ሳይቆም ሳይተኛ እንደቆመ በጽኑ ተጋድሎ ተቀመጠ፡፡ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ በውስጡ እየገባ ሳይቀመጥ ሳይተኛ ሰውነቱ እንደ እንጨት እስኪደርቅ ድረስ በጾም በጸሎት በእጅጉ ይተጋ ነበር፣ በዚህም ወቅት #ጌታችን ተገልጦለት ሰውነቱን በሙሉ ምራቁን ስለቀባለትና አውራ ጣቱን ስላጠባው ከዚህ ጊዜ በኋላ ርሀብና ጥሙ ጠፍቶለት ሰውነቱም ታድሶለታል፡፡ ዳግመኛም በአፉም ድንጋይ ጎርሶ፣ እግሩንም ታስሮና ማቅ ለብሶ ወደ ባሕር እየገባ ይጸልይ ነበር፡፡

አባታችን አባ ሳሙኤል በሕይወተ ሥጋ ሳለ እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን አድርጓል፡፡ እንደሙሴ ባሕርን የከፈለበት ጊዜ አለ፤ በልዑልም ዙፋን ፊት እየቀረበ ከቅዱሳን መላእክት ጋር የሚያመሰግንበት ጊዜ አለ፣ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ጋር ሆኖ የሚያጥንበት ጊዜ አለ፤ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ሆኖ ከእነ ቅዱስ ጴጥሮስና ከሁሉ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ጋር በአንድ ላይ ማዕድ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፤ በእጆቹ የያዛቸው መጻሕፍቶቹ ምንም ሳይርሱ ትልቅ ወንዝን በውስጡ እያቋረጠ የሚሻገርበት ጊዜ አለ፤ #እመቤታችንንም ሲያመሰግናት ከምድር ወደ ላይ አንድ ክንድ ያህል ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ፤ በቤትም ውስጥ ሆኖ ምስጋናዋን ሲጀምር የቤቱ መሠረት እየተናወጠ ዝናብ እንደያዘ ደመና ቤቱ ከምድር ከፍ ብሎ የሚቆምበት ጊዜ አለ፤ #መንፈስ_ቅዱስም በብርሃን ክንፍ እየወሰደው ወደተለያዩ ገዳማት ያደርሰውና #ቅዱስ_ሥጋ_ክቡር_ደሙን እንዲቀበል ያደርገው ነበር፡፡ መልአኩ #ቅዱስ_ሚካኤልም የሁልጊዜ ጠባቂው ነውና በሁሉ ነገር ይራዳውና እንደ ጓደኛም ያማክረው ነበር፡፡ በአንዲት ዕለትም በጎዳና ሲጓዝ ወንዝ መልቶበት አገኘው፡፡ አባታችንም መጻሕፍቶቻቸውንና እሳት በእጃቸው እንደያዙ በወንዙ ውስጥ ለውስጥ ውኃውን አቋርጠው ሲሻገሩ መጻሕፍቶቻቸው አልራሱም በእጃቸው የነበረው እሳትም አልጠፋም ነበር፡፡

አባታችን ሊያስቀድሱ ወደ በተ መቅደስ በሚገቡ ጊዜ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ ይወርድላቸው ነበር፡፡ የ #እመቤታችንንም ውዳሴዋን ሲደግሙ ክንድ ከስንዝር ያህል ከምድር ከፍ ይሉ ነበር፡፡ #እመቤታችንም እየተገለጠች ንጹሕ ዕጣንንና የሚያበራ እንቁን ሰጥታቸዋለች፡፡

ቅዱስ አባታችን ለክቡር ሥጋ ወደሙ እጅግ ትልቅ ክብር አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያን አስቀድሰው ሁሉም ሥጋ ወደሙን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲወጡ ከአራቱ መነኮሳት ውስጥ አንዱ አስታወከ፣ በቤተክርስቲያንም ዳርቻ ተፋው፡፡ ያዩትም ሁሉ ደንግጠው ቆሙ፡፡ የ #እግዚአብሔር ሰው ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ግን ሁሉንም በአፉ ተቀበለው፣ በምላሱም መሬቱን ላሰው፡፡ ይህን ጊዜ ከሰማይም ‹ሳሙኤል ሳሙኤል› የሚልን ድምጽ ሰማና ወደላይ ባንጋጠጠ ጊዜ ሰባቱ ሰማያት ተከፍተው አየ፡፡ ከላይ ያለው ያ ቃልም መለሰ፡- ‹በሰው ፊት እንዳመሰገንኸኝና ፈጽሞም እንዳከበርከኝ የባልንጀራህን ትውኪያ ትቀበል ዘንድ እንዳላፈርህ እኔም እንዲሁ
አከብርሃለሁ፤ በሰማያት ባለው በአባቴም ፊት በመላእክት ማኅበር አመሰግንሃለሁ› አለው፡፡›› ሌሎቹም ቅዱሳን እነ አቡነ ተክለሐዋርያትም እንዲሁ ለሥጋ ወደሙ ክብር ሲሉ የቆረበ ሰው ሲያስመልሰው የዚያን ሰው ትውኪያ ይጠጡት እንደነበር በቅዱስ ገድላቸው ላይ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለ #ክርስቶስ ያላቸው ክብር እስከዚህ ድረስ ነው፡፡

አንድ ቀን አባታችን በገዳም ውስጥ ሳለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ይጎበኘው ዘንድ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ከእርሱም ጋር ተቀምጦ ‹ወዳጄ ሆይ! ሰላምታ ይገባሃል፡፡ አንተ ግን ከትንሽነትህ ጀምሮ አገለገልኸኝ፣ ምን አደርግልህ ዘንድ ትወዳለህ?› አለው፡፡ ትሑት ሳሙኤልም ‹የነፍሴ ወዳጅ #ጌታዬና_አለቃዬ_ሆይ! መልካም ሀብት ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ምሕረትህንና ብሩህ ፊትህን ታሳየኝ ዘንድ እሻለሁ› አለ፡፡ #ጌታችንም ‹አገልጋዬ ወዳጄ ሆይ! የፈለግኸውን እሰጥሃለሁ፣ ዳግመኛም ያልፈለግኸውንም እጨምርልሃለሁ› አለው፡፡ አባ ሳሙኤልም ‹ #ጌታዬ_ሆይ! አንዲት ልመናን እለምንሃለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ኃጢአቴን አይ ዘንድ እወዳለሁ፡፡ የሌላውን ኃጢአት ግን አታሳየኝ› አለው፡፡

አባ ሳሙኤልን የዱር አራዊትም ሁሉ ይገዙለት ነበር፡፡ ታላቅ የሆነ ዘንዶ፣ ነብር፣ ጅብ፣ ቶራህ፣ ዝሆን፣ አንበሳና ሌሎችም የዱር አራዊት ሁሉ እየመጡ እግሩን እየላሱት ወደ ቦታቸው ይመለሱ ነበር፡፡ አንበሶቹንም እሾህም በወጋቸውና እግራቸው መግል በያዘ ጊዜ በመርፌ እያነቆረ ያድናቸው ነበር፡፡ ስንጥርም ሲወጋቸው ወደ እርሱ እየመጡ ያሳዩትና ያወጣላቸው ነበር፡፡ አንበሳም አጋዘንን ገድሎ ሲበላ ሲያየው ‹‹አንዴ ዞር በልልኝ ቆዳዋን ለልብሴ እፈልገዋለሁ›› ባለው ጊዜ ይለቅለት ነበር፡፡ እንዲሁም አንበሳው ለአባታችን ምግብም ትሆነው ዘንድ ጅግራን እየያዘ በሕይወት ሳለች ያመጣለት ነበር፡፡ አባታችንም ከገዳም ወጥቶ መሄድ በፈለገ ጊዜ አንበሶችን እንደ ፈረስና በቅሎ ይጋልባቸዋል፣ መጻሕፍቶቹንም ይጭንባቸዋል፤ መንታ የወለደች አንበሳም ብትኖር ልጆቿን እየታቀፈ በየተራ ያጠባቸው ነበር፡፡

ወደ ደብረ ዋሊም በሄደ ጊዜ #ጌታችን ተገልጦለት በዕለቱ የ #እመቤታችን በዓል ስለነበር እንዲቀድስ ነግሮት ከሰማይ ኅብስትና ጽዋ መጥቶለት #ቅዱሳን_ሐዋርያት በቀኝ በግራ እየተራዱት ሲቀድስ #መንፈስ_ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ ኅብስቱንና ጽዋውን ጋርዶታል፡፡ #ጌታችንም ቦታዋንና በዚያ ያሉትን መነኮሳት ሁሉ ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ አስራት አድርጎ ሰጠው፡፡ ዋልድባ የተመሠረተው በቀደምት ጥንታዊያን አበው ቢሆንም አባ ሳሙኤል ሲገቡበት ምድረ በዳ ሆኖ ጠፍቶ ቋያ በቅሎበት የወባ ትንኞች መፈልፈያ ሆኖ ነበር፡፡ አባታችን ግን የተበታተኑትን መነኮሳት ሰብስበው ዋልድባን እንደገና አደራጅተውና አድሰው አቀኑት፡፡ የተባሕትዎ ኑሮንም አጠናከሩበትና ገዳሙን የመናንያን አበው መሰብሰቢያ አደረጉት፡፡ አባታችን ዋልድባን እንደ ሞሰብ አንስተው አስባርከዋታል፡፡

አባ ሳሙኤል ጊዜው ደርሶ ከማረፉ በፊት #ቅዱስ_ሚካኤል ነሐሴ 16 ቀን ወደ ገነት ነጥቆ ወስዶ ከዕረፍቱ በኋላ ከልጆቹ ጋር የሚኖርበትን ሥፍራ አሳይቶታል፡፡ በገነት ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ ካሳየው በኋላ በ #እግዚአብሔርም ዙፋን ፊት ቀርቦ ምስጋናና ቃልኪዳንን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ተመልሶ ታኅሣሥ 12 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፎ ነፍሱን #ጌታችን በእጆቹ ተቀብሏታል፡፡

#መድኃኔዓለም_ክርስቶስ ለአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ወደ ገነት ነጥቆ ወስዶ በዚያ ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ መኖሪያቸውንና ክብራቸውን አሳየኝ፡፡ ‹እነሆ የተጋድሎህን ሥራ ፈጽመሃልና አንተም ወደተዘጋጀችልህ ትመጣ ዘንድ ጊዜህ ቀርቧል› ብሎ #ጌታዬ የሰጠኝን መኖሪያዬን አሳየኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ልዑል ዙፋን ወደ አርያም አደረሰኝ፡፡ በዚያም በክብሩ ዙፋን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ተወዳጅ #ወልድን አየሁት፡፡ በዚያም እመቤታችን #ማርያምን ከተወዳጅ ልጁዋ ቀኝ አየኋት፡፡ የብዙ ብዙ ቅዱሳን መላእክትና ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉ በየወገናቸው ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ፍጹም አሸናፊ #እግዚአብሔር የክብር ምስጋና ሰማያትንና ምድርን መላ› እያሉ በፊቱ ይዘምሩ ያመሰግኑ ነበር እኔም በአምላኬ ፊት ሰገድኩ፡፡ ተወዳጅ #ወልድም ተናገረኝ፣ እንዲህም አለኝ፡- ‹ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ! ሰላምታ ይገባሀል፣ ደስ ይበልህ፡፡ በጥቂቱ የታመንህ ባሪያዬ ሆይ በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ እኔን በመውደድ ብዙ ደክመሃልና የ #መስቀሌንም መከራ በመሸከም እኔን መስለሃልና እኔም በመንግሥቴ መልካም የሆነውን የድካምህን ዋጋ እሰጥሃለሁ፡፡ እነሆ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የተካከለ መቀመጫህንና አክሊልህን አዘጋጀሁልህ፣ ዕድል ዕጣህም ከአሥራ ሁለቱ ቅዱሳን ሐዋርያቶቼ ጋር ነው፡፡ አፅምህ በተቀበረበት፣ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበት፣ መታሰቢያህ በተደረገበት፣ ሥፍራ ሁሉ ምሕረትና ድኅነት ይሁን፡፡ በጸሎትህ የሚታመነውን፣ መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ ለአንተ አሥራት ሰጥቼሃለሁ፡፡ ስለ እኔ የተቀበልከውን ድካም ሁሉ ዛሬ ያገኘኸውን የአንዲት ቀን የደስታ ልክ አይሆንም፡፡››

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባት ሳሙኤል ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አርኬ
✍️ ሰላም ለከ ዘፈረይከ ሕገ። ሳሙኤል ዘኮንከ ለአስካለ ወይን ሐረገ። በረድኤትከ ክፍለኒ ወእደ ሀሎከ ዐሪገ። ረድኤትከሰ ወለተ ከለባት መዘገ። ምስለ ክቡራን ከመ ተሀሉ ደርገ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሰማዕታቱ_ቅዱስ_አንቂጦስ_እና_ቅዱ_ፎጢኖስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ወንድማማቾቹ ቅዱሳን አንቂጦስ እና ቅዱስ ፎጢኖስ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ምእመናንን የሚያሠቃይባቸውን የማሠቃያ መሣሪያዎች ለሕዝቡ እያሳየ ሲያስፈራራ የጸኑንም ሲገድል ቅዱስ አንቂጦስ በሕዝቡ መሐል ቆመና ንጉሡን ስለከንቱ እምነቱ ዘለፈው፡፡ ንጉሡም ይዞ ብዙ ካሠቃየው በኋላ በሕዝቡ ፊት ለተራበ አንበሳ ሰጠው፡፡ ነገር ግን አንበሳው ቅዱስ አንቂጦስን ፊቱን አሻስቶ ሲተወው በማየቱ ንጉሡ ሰይፉን መዞ ሊሰይፈው ሊሄድ ሲል መንቀሳቀስ ተሳነው፡፡ ከዚህም በኋላ ሰውነትን ቆራርጦ ወደሚጥል መንኮራኩር ውስጥ ከተተው ነገር ግን ሰማዕቱን #ጌታችን ፍጹም ጤነኛ አድርጎ አስነሣው፡፡

ንጉሡ ዳግመኛ ቅዱስ አንቂጦስ እርሳስ ካፈሉበት ትልቅ ጋን ውስጥ ቢጨምረውም የታዘ መልአክ ከጋኑ ውስጥ ነጥቆ አውጥቶ በንጉሡ ፊት አቆመው፡፡ ይህን ጊዜም ወንድሙ ፎጢኖስን አንጢቆስን አቅፎ ከሳመው በኋላ ንጉሡን ‹‹አንተ ከዳተኛና ጎስቋላ ንጉሥ ወንድሜን ታሸንፈው ዘንድ አይቻልህም አምላኩ ይጠብቀዋልና›› አለው፡፡ ንጉሡም የሚያደርግባቸውን ነገር እስኪያስብ ድረስ ቅዱሳኑን ወንድማማቾቹን እጅና እግራቸውን አሳሥሮ ወህኒ ቤት ጨመራቸው፡፡

በማግሥቱም አውጥቶ ሰውነታቸውን ጥፍር ባለው ብረት ሰነጣጠቃቸው፡፡ ወደ አደባባይም አውጥቶ በድንጋይ አስወገራቸው፡፡ ከብዙ ግርፋትም በኋላ በቁስላቸው ላይ ጨው ጨምሮ ካሠቃያቸው በኋላ እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም እሳቱ እንደቀዝቃዛ ጠል ሆነላቸው፡፡ ንጉሡም ይህን ባየ ጊዜ ነበልባሉ ከፍ ብሎ እስኪታይ ድረስ እሳት አስነድዶ ከዚያ ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ቅዱሳኑም ከእሳቱ ውስጥ ሆነው በ #መስቀል ምልክት አማትበው ረጅም ጸሎት ካደረጉ በኋላ ቅድስት ነፍሳቸውን ለ #እግዘኢብሔር አሳልፈው ሰጡ፡፡ የሥጋቸውም በድን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ከእሳቱ ፍሕም ላይ ነበር ነገር ግን የራሳቸው ፀጉር እንኳን
አልተቃጠለችም ነበር፡፡ ምእመናንም ቅዱስ ሥጋቸውን ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ አስደናቂ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አርኬ
✍️ ሰላም እብል እንዘ አሐሊ ሐዋዘ። ለአንቂጦስ ሰማዕት ምስለ ፎጢኖስ እኁዘ። ይውግርዎ ሎቱ ሶበ ንጉሥ አዘዘ። ፁገተ አንበሳ መንገለ የዋኃት ግዕዘ። እስከ መልታሕቶ ኃሠሠ ወጽሕሞ መዝመዘ።

✍️ ሰላም እብል ለአንቂጦስ ማኅበሮ። እለ በእሳት ፈጸሙ ረዊጸ ወተባድሮ። ያብጽሑኒ እሉ ምስለ መላእክት ድርገተ ዘምሮ። ህየ አሀሉ ወሬዛ ነዳየ ኲሉ አእምሮ ኀበ ይዘብጣ ደናግል ከበሮ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#የአንድነት_ስብሰባ_በሮሜ

በዚችም ቀን የቅዱሳን ኤጲስቆጶሳት የቀሳውስትና የዲያቆናት የአንድነት ስብሰባ በሮሜ ከተማ ሆነ፤ ይህም የሆነው ከሀዲው ዳኬዎስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት በሮሜው ሊቀ ጳጳሳት በቆርኔሌዎስ የሹመት ዘመን በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በዲዮናስዮስ ዘመን በላንድዮስም በአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ ሳለ ግርማኖስም የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ሁኖ ሳለ ነው ይህም የሆነበት ምክንያት በስደት ጊዜ የካደ ቢኖር ወይም በዝሙት የወደቀ ወይም በየአይነቱ በሆነ ኃጢአት ቢሰናከል በንሰሓ ሊቀበሉት አይገባም በማለቱ ስለ ቀሲስ ብናጥስ ነው።

አባት ቆርኔሌዎስ ስለዚህ አንድ ጊዜ ዳግመኛም ሦስተኛም ጊዜ ገሠጸው መከረውም ግን አልሰማውም ስለዚህም ስልሳ ኤጲስቆጶሳትን መጻሕፍትን የተማሩ ዐሥራ ስምንት ቀሳውስትና አርባ ዲያቆናትን በርሱ ላይ ሰበሰበ፤ እነርሱም ስለዚህ ነገር ብናጥስ ቀሲስን ተከራከሩት ቀሲስ ብናጥስም ምክንያት አድርጎ የተነሣው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በስድስተኛው ምዕራፍ ጥምቀትን ከተቀበሉ በኋላ ከሰማይ የሚሰጥ ጸጋውን ከቀመሱ በኋላ በ #መንፈስ_ቅዱስም አንድ ከሆኑ በኋላ አይቻልም። መልካሙንም የ #እግዚአብሔርን ቃልና በኋላ የሚመጣውን የዓለምን ኃይል ከዐወቁ በኋላ ንስሓቸውን ሊአድሷት የ #እግዚአብሔርን ልጅ ሊሰቅሉላቸው ሊያዋርዱላቸው ዳግመኛ ሊወድቁ አይገባም ያለውን ኃይለ ቃል ምክንያት አድርጎ ነው።

እሊህ አባቶችም እንዲህ ብለው መለሱለት ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ንስሓስ ለሚገባ ሰው ይህን አላለም በኃጢአት በወደቀ ጊዜ በየጊዜው የክርስትና ጥምቀትን ስለሚጠመቅ ነው እንጂ ስለዚህም ሐዋርያው እንዲህ የሚለውን ቃል አስከተለ ዳግመኛ የ #እግዚአብሔርን ልጅ ሊሰቀሉላቸው ሊያዋርዱላቸው ይገባልን መከራ መስቀሉ አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ እንዲሁም ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ ናትና ንስሓ ግን በሁሉ ጊዜ ትገኛለች።

አንተ እንደምትለው ከሆነ በኃጢአት የወደቀ ቅዱስ ዳዊትን፣ #ጌታችንን ክዶት የነበረ ቅዱስ ጴጥሮስን ንስሓ አልተቀበለምን አጽናኝ የሆነ የ #መንፈስ_ቅዱስን ሀብት አልሰጠውምን በምእመናንስ ላይ በከንቱ ሾመውን በእጁ የሠራው ሁሉ የተጠመቀውም የጠፋ ነውን አንተ እንደምትለው ይህ ስንፍናና ድንቁርና ነው።

ክብር ይግባውና #ጌታችን ግን ሃይማኖቱን ለካደ ወይም በኃጢአት ለወደቀ ለሁሉም ንስሓን ሠርቷል ብናጥስ ሆይ ከዚህ ከረከሰና ከከፋ ምክርህ ተመልሰህ ንስሓ ግባ ለ #እግዚአብሔርም ለራስህና ለሰው ልጅም ሁሉ ጠላት አትሁን፤ እርሱ ግን ከክፉ ሐሳቡ ተመልሶ ትምርታቸውን አልተቀበለም። አውግዘውም ከምእመናን ለዩት በትምህርቱ የሚያምኑትንም ሁሉ ለዩአቸው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

አርኬ
✍️ሰላም ለጒባኤክሙ ውስተ አሐተኒ ከኒሳ። ኤጲስቆጶሳት ስሳ። ባህለ ብናጥስ ታጽርኡ ዘተመሰለ ከመ እንስሳ። ኢይተወከፉ ንስሓ ዘይቤ እምድኅረ ገብረት አበሳ። እስመ ኢትነጽሕ ነፍስ ዳግመ እምርኲሳ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ዳግማዊ_ቂርቆስ (የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጅ)

በዚህችም ቀን ዳግማዊ ቂርቆስ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልጅ ብሔረ ብፁዓን የገባበት ነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡- ብፅዕት ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ከአገልጋዮቿ መካከል አንዷ ምግባሯ የከፋ ነበርና በጣም ስላበሳጨቻት #እግዚአብሔር ቀሰፋትና ገደላት፡፡ በዚህ ጊዜ ብጽዕት ክርስቶስ ሠምራ ደንግጣ ወደ ሌላ ክፍል ገባችና ኃጢአቷን ለ #እግዚአብሔር እየተናዘዘች እጅግ በጣም አዝና ጥፋቷ እንደ ጸጸታትና #እግዚአብሔር አምላክም በእጇ የሞተችውን አገልጋይዋን ከሥጋዋ አዋሕዶ ቢያሥነሳላት ያላትን ገንዘብና ሀብት ትታ ባላት ዘመኗ ሁሉ አገልጋዩ እንደምትሆን ብጽዓት (ስዕለት) አደረገች፡፡ #እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ አገልጋይዋን ከሞት አሥነሳለት፡፡ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ‹‹ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከእኔ ከባሪያው ያላራቀ አምላክ ይክበር ይመስገን›› ብላ በታላቅ ምስጋና #እግዚአብሔርን ካመሰገነች በኋላ አስቀድማ የገባችውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኩስናዋን አዘጋጀች፡፡ ሕፃን ልጅዋንም ይዛ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደች፡፡ ስትሄድም በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግሯ ከመንገዱ ብዛት ከእንቅፋቱም የተነሳ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሟ መሬት ለመሬት እየፈሰሰ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ደረሰችና አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብሰ ምንኩስናዋን ለብሳ ከሴቶች ገዳም ገባች፡፡

ቅድስት እናታችን ይዛው የተሰደደችውን የ3 ዓመቱ ሕፃን ግን ወንድ ስለሆነ ከደጅ ላይ አስቀምጣው ስለገባች ሕፃኑ አምርሮ አለቀሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ከመነኮሳይያቱ አንዲቷ ‹‹ሕፃኑ ሲያለቅስ ከሚያድር›› ብላ ወደ በአቷ ልታስገባው ስትል የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሕፃኑን ነጥቆ ወስዶ በገነት አስቀመጠው፡፡ እርሱም ታኅሣሥ 29 ቀን ተወልዶ በ3 ዓመቱ ታኅሣሥ 12 ቀን ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፡፡ እጅግ አሳዛኝ ገድሉ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይገኛል፡፡

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አና ጻድቃን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

በዚችም ዕለት የቅዱሳን የሰማዕት አውሲስና የእንጦንዮስ የሮሜው የአባ መሐር መታሰቢያቸው ነው በረከታቸውም ትድረሰን ለ #እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።

#ታኅሣሥ_12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
2.ቅዱሳን አንቂጦስ ወፎጢኖስ (ሰማዕታት)
3.አባ ነድራ
4.ቅዱስ ዮሐንስ ተአማኒ
5.ጉቡዓን ኤዺስ ቆዾሳት

#ወርሐዊ_በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
6.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ

✍️"የሚያሳድዷችሁን መርቁ . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ፤ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ"
📖ሮሚ 12፥14-16

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶ።


(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታህሣሥ_12 እና #ከገድላት_አንደበት)
2024/12/25 06:20:50
Back to Top
HTML Embed Code: