Telegram Web Link
ሰምቶ እጅግ አደነቀ አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትላለች እንዲህ ትሠራለች ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነው።

በዚህም አባት ጴጥሮስ ዘመን ከሀዲ አርዮስ ተነሣ ከክህደቱም ይመለስ ዘንድ ይህ አባት ብዙ ጊዜ መከረው ገሠጸው ቃሉንም ባልሰማው ጊዜ ረግሞ አወገዘው።

ከዚህም በኋላ የንጉሥን አማልክት እንዳያመልኩ በሁሉ ቦታ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚያስተምር ዜናውን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ስለዚህ ይዘው እብዲአሥሩት መልእክተኞችን ላከ። የሀገር ሰዎችም በአወቁ ጊዜ የንጉሥ መልእክተኞችን ይወጓቸው ዘንድ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ተሰበሰቡ።

ቅዱስ አባት ጴጥሮስም ስለርሱ ታላቅ ሁከት እንደሚሆን በአየ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሊሰጥ ወደደ ሕዝቡንም ሁሉ ወደርሱ አቅርቦ በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አዘዛቸው አጽናንቶ አረጋግቶ ወደ ቤቶቻቸው እንዲገቡ አሰናበታቸው።

አርዮስም ቅዱስ አባት ጴጥሮስ ከዓለም በሞት እንደሚለይ በአወቀ ጊዜ ይህ አባት ጴጥሮስ ከውግዘቱ እንዲፈታው ያማልዱት ዘንድ አኪላስንና እለእስክንድሮስን ለመናቸው እነርሱም እንዲፈታው በለመኑት ጊዜ በውግዘት ላይ ውግዘትን ጨመረ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀደደ ልብስ ለብሶ እንዳየው ልብስህን ማን ቀደዳት ባለውም ጊዜ ልብሴን አርዮስ ቀደዳት እንዳለው አስረዳቸው። ይህም ማለት ከአባቴ ለየኝ ማለት ነው ሁለተኛም ከእርሱ ተጠበቁ በክህነት ሥራም አትሳተፉት እርሱ ለክብር ባለቤት ክርስቶስ ጠላቱ ነውና አላቸው ። አንተም አኪላስ ከእኔ በኋላ ሊቀ ጵጵስና ትሾም ዘንድ አለህ አንተም አርዮስን ትቀበለዋለህ ፈጥነህም ትሞታለህ አለው።

ከዚህም ነገር በኋላ ቅዱሳ አባት ጴጥሮስ ከንጉሥ መልክተኞች ጋር በሥውር ተማከረ በእሥር ቤት ከውስጥ ሲያንኳኳላቸው እነርሱ ወደ መስኮት እንዲቀርቡ እርሱም ራሱን ሊሰጣቸው ንጉሡ እንዳዘዛቸው ይፈጽሙ ዘንድ በዚያንም ጊዜ የወንጌላዊ ማርቆስ መቃብር ወዳለበት ከከተማው ውጭ ይዘው ወሰዱት በዚያም ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደሜ መፍሰስ ለጣዖታት አምልኮ መጨረሻ ይሁን ከሁሉ ዓለምም ይጥፋ ብሎ ጸለየ። ከሰማይም አሜን ይሁን ይደረግ የሚል ቃል መጣ።

ለዚያ ቦታም በአቅራቢያው የነበረች አንዲት ብላቴና ድንግል ይህን ቃል ሰምታ ተናገረች።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባት ጴጥሮስ ወታደሮችን የታዘዛችሁትን ፈጽሙ አላቸው በዚያንም ጊዜ የከበረች ራሱን ቆረጡ በድኑም ሁለት ሰዓት ያህል ቆመ ሕዝቡም ከከተማ ፈጥነው በመውጣት ወደ እሥር ቤት መጡ እስከ ነገሩአቸውም ድረስ የሆነውንም አላወቁም ነበር ከዚህም በኋላ የቸር ጠባቂያቸውን ሥጋ አንሥተው ወደ ከተማ አመጡ አክብረውም ገነዙትና ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አግብተው በወንበሩ ላይ አስቀመጡት።

ከዚህ አስቀድሞ በወንበሩ ላይ ሲቀመጥ ከቶ ማንም አላየውም በወንበርህ ላይ የማትቀመጥ ለምንድን ነው ብለው በጠየቁት ጊዜ እኔ የእግዚአብሔር ኃይል በወንበር ላይ ተቀምጦ አያለሁና ስለዚህ በዚህ ወንበር ላይ መቀመጥን እፈራለሁ ብሎ መለሰላቸው።

ግንዘቱንም አከናውነው ከተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት ከሥጋቸው ጋር ሥጋውን አኖሩ እርሱም በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር በሹመት የኖረው ዐሥራ አራት ዓመት ነው የተሾመውም ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ በሃያ ስድስት ዓመት ነው ከሥጋውም ብዙ ድንቅ ተአምር ተገለጠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ቀሌምንጦስ_ሐዋርያ

በዚህች ቀን ለሮሜ ሀገር ሊቀ ጳጳሳት የሆነ የሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ደቀ መዝሙሩ ቀሌምንጦስ በሰማዕትነት አረፈ።

ይህም ቅዱስ ከመንግሥት ልጆች ወገን የሆነ ለሮም ንጉሥ የጭፍራ አለቃ ለሆነ ለቀውስጦስ ልጁ ነው ደጎች የሆኑ አባትና እናቱም ቅዱስ ጴጥሮስ የወንጌልን ትምህርት በሰበከ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋት አድርገው ሰጡ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ቀውስጦስ ወደ ንጉሥ ሒዶ በዚያው በዘገየ ጊዜ ወንድሙ የመኰንኑን የቀውስጦስን ሚስት ሊአገባት አሰበ እርሷም በአወቀች ጊዜ አባታቸው እስቲመለስ ወደ አቴና ሔዳ ጥበብን ታስተምራቸው ዘንድ ቀሌምንጦስንና ታናሽ ወንድሙን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች።

በዚያንም ጊዜ ብርቱ ነፋስ በመንፈሱ ማዕበል ተነሥቶ መርከቡ ተሰበረ ቀሌምንጦስም በመርከቡ ስባሪ ተንጠለጠለ የባሕሩም ሞገድ ወደ እስክንድርያ አገር አደረሰውና በዚያ ጥቂት ቀኖች ኖረ። በዚያንም ወቅት የከበረ ሐዋርያ ጴጥሮስ ቃል ጠራውና ወደ እስክንድርያ ሀገር እንዲሔድ አዘዘው በሔደም ጊዜ በውስጥዋ የወንጌልን ቃል ሰበከ ከዚህ ከቅዱስ ቀሌምንጦስ በቀር ከሀገር ሰው አንድ እንኳን ያመነ የለም እርሱ የቅዱስ ሐዋርያ ጴጥሮስን ትምህርት በሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የክርስቶስን ጥምቀትን ተጠመቀ።

ሐዋርያ ጴጥሮስም የጌታችንን የመለኮቱን ምሥጢር ለሚያመልኩትም የሚሰጣቸውን ብልጽግናውንና ክብሩን በስሙም ኃይል ድንቅ ተአምራትም እንደሚደረግ ገለጠለት። ከዚችም ዕለት ጀምሮ ቀሌምንጦስ ቅዱስ ጴጥሮስን ተከተለው ደቀ መዝሙሩም ሆነ እርሱም የሐዋርያትን ገድላቸውን ከዐላውያን ነገሥታትና መኳንንት የደረሰባቸውን ሥቃይ ሁሉ ጻፉ።

ከዚህም በኋላ በብዙ አገሮች ውስጥ አስተማረ ሐዋርያትም በጉባኤ ተነጋግረው የሠሩአቸውን የሥርዓት መጻሕፍትን ለርሱ ሰጡት። ከዚህም በኋላ በሮሜ አገር ሊቀ ጵጵስና ተሾመ በትምህርቱም ከሰዎቿ ብዙዎችን እግዚአብሔርን ወደማወቅ መለሳቸው።

ስለርሱም ከሀዲ ንጉሥ ጠራብሎስ ሰምቶ ጭፍራ ልኮ ወደርሱ አስመጥቶ ክርስቶስን ክደህ ለአማልክት ስገድ አለው ትእዛዙንም ባልሰማ ጊዜ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ ወደ አንዲት አገር ሰደደው እርሱ በላዩ እንዳይነሡበት ከሀገር ሰዎችና ከዘመዶቹ የተነሣ ፈርቷልና መኰንኑንም ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃየው አዘዘው።

የዚያችም አገር መኰንን በመርከቦች ውስጥ የሚኖር እግሮች ያሉት ከባድ ብረት በአንገቱ ውስጥ አንጠልጥሎ ከባሕር ውስጥ አሠጠመው ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ ወንጌልን እንደ ሰበኩ ሐዋርያትም በመንግሥተ ሰማያት የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ።

እንዲህም ሆነ አንዲት ዓመትም ስትፈጸም ባሕሩ ተገልጦ እንደተኛ ሁኖ የቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ታየ። እርሱም ሕይወት ያለው ይመስል ነበር ሰዎችም ገብተው ከእርሱ ተባረኩ የከበረ የደንጊያ ሣጥንም አምጥተው ሥጋውን በውስጡ አድርገው አንሥተው ከባሕር ውስጥ ሊአወጡት ፈለጉ ግን ከቦታው ሊአንቀሳቅሱት አልቻሉም ከባሕር ውስጥ መውጣትን እንዳልፈለገ አወቁ በዚያም ትተውት ወደ ቤቶቻቸው ሔዱ። ከዚህም በኋላ በመታሰቢያው ቀን በየዓመቱ ያቺ ባሕር ከቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋ ላይ የምትገለጥ ሆነች ምእመናንም ሁሉ ገብተው ከእርሱ ይባረካሉ መታሰቢያውንም በማድረግ በዓሉን ያከብራሉ ከዚያም በኋላ ወጥተው ወደቤታቸው ይገባሉ።

ከአስደናቂዎች ተአምራቶቹም ከተጻፉት ያዩ ይህን ተናገሩ በአንዲት ዓመት ከሥጋው ሊባረኩ በገቡ ጊዜ የቅዱስ ቀሌምንጦስ ሥጋው ካለበት ሣጥን ዘንድ ሲወጡ ታናሽ ሕፃን እንደረሱ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚወዱት ቅዱሳኑ ክብራቸውን ከርሱ የተቀበሉትንም ጸጋ ይገልጥ ዘንድ ወዷልና ። ወላጆቹም ከወጡ በኋላ ሕፃኑን ፈለጉት ግን አላገኙትም ባሕሩም በላዩ ተከድኖ ነበር ሙቶ በባሕር ውስጥ ያሉ አራዊት የበሉት መስሏቸው አለቀሱለት እንደ ሥርዓቱም በማዕጠንትና በቁርባን ቅዳሴ መታሰቢያውን አደረጉ።
በዳግመኛውም ዓመት ያቺ ባሕር ተገልጣ እንደ ልማዳቸው ገቡ ሕፃኑንም በሕይወት ሁኖ በቅዱስ ቀሌምንጦስ የሥጋ ሣጥን ዘንድ ቁሞ አገኙት በዚህ ባሕር ውስጥ አኗኗርህ እንዴት ነበር ምን ትበላ ነበር የባሕር አራዊትስ እንዴት አልበሉህም ብለው ጠየቁት። እርሱም ቅዱስ ቀሌምንጦስ ያበላኝ ነበር እግዚአብሔርም በባሕር ካሉ አራዊት ይጠብቀኝ ነበር ብሎ መለሰ ሰምተውም እጅግ አደነቁ በቅዱሳኑና ስለ ከበረ ስሙ ደማቸውን በአፈሰሱ ሰማዕታት የሚመሰገን ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_29 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ))
#ኅዳር_30

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ሠላሳ በዚህች ቀን ጻድቁ #ንጉሥ_አፄ_ገብረ_መስቀል ዕረፍቱ ነው፣ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_አካክዮስ አረፈ፣ #የቅዱሳን_ቆዝሞስና_ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አፄ_ገብረ_መስቀል_ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)

ኅዳር ሠላሳ በዚህች ቀን ጻድቁ ንጉሥ አፄ ገብረ መስቀል ዕረፍቱ ነው።

ዐፄ ካሌብ የናግራንን ሰማዕታት ደም ተበቅሎ በድል ከተመለሰ በኋላ በአቡነ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ ገዳም ከገባ በኋላ ልጁ ገብረ መስቀል ነገሠ፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በእውነትና በቅንነት ከነገሠ በኋላ አመራሩ ከአህጉሪቷ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ደረሰ፡፡ በዘመኑም ሁሉ መንግሥቱን የሚቃወም አልተነሣም፤ እርሱም ቤተ ክርስቲያንን ከመሥራት በቀር ወደ ጦርነት የሄደበት ጊዜ የለም፡፡ መንግሥቱንም ይባርክለት ዘንድ ሠራዊቱን ይዞ ወደ አባታችን ወደ አቡነ አረጋዊ ዘንድ ደብረ ዳሞ ሄደና በፊቱ ሰግዶ ‹‹አባቴ ሆይ! እኔን ባሪያህን፣ መንግሥቴንና ሕዝቤን ሠራዊቴንም ሁሉ ባርክ›› እያለ አጥብቆ ማለደው፡፡ አባታችን አረጋዊም ‹‹የአባቶችህን የዳዊትንና የሰሎሞንን መንግሥት የባረከ፣ የአባትህን የካሌብንም መንግሥት የባረከ #እግዚአብሔር የአንተንም መንግሥት ይባርክ…›› ብለው ባረኩት፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል አቡነ አረጋዊን የት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን እንደሚሠራ ጠይቋቸው ካሳዩት በኋላ ሲሠራ ሁለት ዓመት የፈጀበት ግሩም ቤተክርስቲያን ሠራላቸውና 12 የወርቅና የብር መስቀሎችን ጨምሮ ብዙ ንዋያተ ቅድሳቶችንና ሥጦታዎችን ሰጣቸው፡፡ ጳጳስም አስመጥቶ አስባረካትና ከማኅበረ በኩር ያመጣውን በወርቅ በብር የተለበጠች የ #እመቤታችንን ታቦት በውስጧ አስገባ፡፡ ጳጳሱና ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀልም አቡነ አረጋዊን ‹‹ቀድሰህ አቁርበን›› ብለውት ይቀድስ ዘንድ በገባ ጊዜ መላእክት ሙቀት ያልተለየው ኅብስትና ወይኑን በጽዋ ለቅዳሴው የሚያስፈልገውንም ሁሉ ከሰማይ አወረዱለትና ቀድሶ ሲያበቃ ሁሉንም አቆረባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዐፄ ገብረ መስቀል ከተራራው ጫፍ በሚወርድበት ጊዜ አባታችንን ‹‹ይህን የተራራውን መውጫ መሰላል ላፍርሰው ወይስ ልተወው?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ለልጅ ልጅ መታሰቢያ እንዲሆን ይህን ድንቅ ሥራ እያየ በፍጥረቱ ሁሉ አንደበት #እግዚአብሔር ይመሰገን ዘንድ የደረጃውን መሰላል አፍርሰው፣ ነገር ግን ስለዘንዶው ጅራት ፋንታ ገመድ አብጅ›› አለው፡፡ ንጉሡም እንደታዘዘው የደረጃውን መሰላል አፈረሰውና ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፡፡ ጻድቁ ንጉሥ በዐፄ ገብረ መስቀል ካበረከተልን ትልቅ ውለታው ውስጥ አንዱ ዛሬ በዩኔስኮ የተመዘገበውን የ #መስቀል በዓልን በአደባባይ እንዲከበር ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ በዘመኑም ካህናቱ ሕዝቡ ሁሉ አደይ አበባ ይዘው ወደ አደባባይ በመውጣት በያሬዳዊ ዝማሬ የ #መስቀልን በዓል ያከብሩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ብርሃኗ የሆነ ነገር ግን እርሷ እንደሚገባው መጠን ያላከበረችው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ጻድቅ ንጉሥ በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት የነበረ ነው፡፡ አብረውም ብዙ ታሪኮችን ፈጽመዋል፡፡ ገዳማትን ላይ በመዟዟር ቅዱስ ያሬድ ዜማን ሲያስተምር ንጉሡ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ያስፋፉና ቋሚ መተዳደሪያ ይሰጡ ገዳማቱን ያጠናክሩ ነበር፡፡ አቡነ አረጋዊ ደግሞ አብረው ምኩስናን ያስፋፉ ነበር፡፡ ሦስቱም ይህን ተግባራዊ እንዳደረጉ ለማሳያ ይሆን ይሆን ዘንድ ቅዱስ ያሬድ 3 ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት ያስተማረባትንና ዛሬም ድረስ ማስመስከሪያ የሆነችውን እጅግ ጥንታዊቷን ዙር አባ ጽርዓ አርያም አቡነ አረጋዊ ገዳምን እንደምሳሌ ማየት እንችላለን፡፡ አቡነ አረጋዊና ቅዱስ ያሬድ በዘንዶ ታዝለው ዓምባው ላይ ከወጡ በኋላ ለንጉሡ ለዐፄ ገብረ መስቀል ደግሞ ተራራውን ባርከው ከፍለው መንገድ አበጅተውላቸው ወደ ዓምባው ወጥተው ሦስቱም በዚያ በጋራ ኖረው ብዙ መንፈሳዊ ሥራን ሠርተዋል፡፡

ጻድቁ ንጉሥ ዐፄ ገብረ መስቀል ከተስዓቱ ቅዱሳን ጋር ሆኖ ብዙ መንፈሳዊ ሥራን ሠርቷል፡፡ ሌላው በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ከነበሩት ቅዱሳት አንስት ውስጥ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ዋነኛዋ ናት፡፡ ይኽችውም ቅድስት ከልጅነቷ ጀምራ በምግባር በሃይማኖት፣ በተጋድሎ በትሩፋት ያጌጠች ናትና ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ገብረ መስቀል በሁለመናዋ የተመሰገነች መሆኗንና ዝናዋን ስለሰማ ‹‹በጸሎትሽ አስቢኝ›› በማለት ከአገልጋዮቹ ውስጥ እርሷን እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮችን ልኮላታል፡፡ ለነገሥታት ሚስቶች የሚደረገውን በሐርና በወርቅ የተሠሩ ልብሶችና ጫማ ልኮላታል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል በጽድቅ ሕይወት እየተመላለሱ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የዋሉት ውለታ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ገርዓልታ አካባቢ ከዱጉም #ሥላሴ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ የቅዱስ ዐፄ ገብረ መስቀል አስደናቂ ፍልፍል ቤተ መቅደስ ይገኛል፡፡

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_አካክዮስ

በዚህች ቀን የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት አካክዮስ አረፈ።

ይህም ቅዱስ ቸር የሆነ ምሁር ነው አምላክ ያጻፋቸውንም መጻሕፍት ቃላቸውን አሳምሮ የሚተረጉም አዋቂ ነው በቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያንም ቅስና ተሹሞ ነበር ። በኬልቄዶንም ስብሰባ በሆነ ጊዜ ይህ አባት በጉባኤው ውስጥ በሆነው ሁሉ ደስ አላለውም ስለ እውቀቱም እንዲመጣ በፈለጉት ጊዜ እርሱ አሞኛል ብሎ ስለራሱ ምክንያት ሰጠ።

በእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ ስለ ደረሰበት ሥቃይ በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ሃይማኖታቸው የቀና እንደሆነ በሚያውቃቸው ባልንጀሮቹ በሆኑ በወዳጆቹ በወታደር አለቆችና በመኰንኖች ፊት የአንድነት ጉባኤያቸውን ረገመ ከእሊህም ክፉዎች ከጉባኤያቸው አንድ ያላደረገኝ #እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ አለ ።

የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት እንጣልዮስም በአረፈ ጊዜ ሃይማኖቱ የቀና እንደ ሆነ ስለ አወቁ የአገሩ ሊቃውንትና መኳንንት ይህን አባት አካክዮስን መረጡት። እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሆነው መጣላትና መለያየትን ያስወግዳል በማለት ተስፋ አድርገው በቁስጥንጥንያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

በተሾመ ጊዜም ከብቻው #እግዚአብሔር በቀር ማንም ሊአስወግደው የማይችል የጥልና የመለያየት የማይድን በሽታ አገኘ በልቡም አስቦ መጀመሪያ ራሴን አድን ዘንድ አይሻለኝምን አለ የቅዱሳን አባቶችን የቄርሎስንና የዲዮስቆሮስን የቀናች ሃይማኖት የተማረና በእርሷ የጸና መሆኑን እየታመነለት ከዚህም በማስከተል በክህነት ሥራ በመሳተፍ ይቀበለው ዘንድ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ሦስተኛው ጴጥሮስ መልእክትን ላከ።

አባ ጴጥሮስም መልእክቱን በአነበበ ጊዜ ደስ ብሎት ታላቅ ክብርን አከበረው ያቺንም መልእክት በጉባኤ ፊት አስነባባት ከዚህም በኋላ አባ ጴጥሮስ ለመልእክቱ መልስ ጽፎ ከሦስት ኤጲስቆጶሳት ጋር ወደ አካክዮስ ላከ እነርሱም ወደ ቁስጥንጥንያ ከአባ አካክዮስ ዘንድ በደረሱ ጊዜ የአባ ጴጥሮስን ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ሃይማኖታቸው በቀና በወዳጆቹና በሀገሩ መኳንንት ፊት አነበባት።
ሁሉም ደስ አላቸው አባ አካክዮስም እሊህን ኤጲስቆጶሳት ታላቅ ክብርን አከበራቸው ወደ አንድ ገዳምም ወሰዳቸው መሥዋዕትንም አዘጋጅቶ የቁርባን ቅዳሴ በመቅደስ ከእሳቸው ጋር አንድ ሆነ ከእሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ።

ዳግመኛም ከአባ አትናቴዎስ፣ ከአባ ጢሞቴዎስ፣ ከአባ ቄርሎስ፣ ከአባ ዲዮስቆሮስ ከሃይማኖታቸው የሚተላለፈውን እያወገዘ ጻፈ ያቺንም የመልእክት ደብዳቤ ሰጣቸውና በፍቅር በሰላም አስናበታቸው።

ወደ አባ ጴጥሮስም በደረሱ ጊዜ አባ አካክዮስ ያደረገውን ሁሉ ነገሩት የመልእክቱንም ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ደስ አለው ስሙንም በማዕጠንትና በቁርባን ጊዜ እንዲጠሩ አዘዘ።

ዜናውም በሮማውያን ኤጲስቆጶሳት ዘንድ በተሰማ ጊዜ አባ አካክዮስን ከቁስጥንጥንያ መንበር አሳደዱት በቀናች ሃይማኖት እንደ ፀና በደሴት ውስጥ አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ቆዝሞስ_ወድምያኖስ

በዚችም ቀን የቅዱሳን ቆዝሞስና ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያናቸው የከበረችበት ነው። እሊህም ቆዝሞስ፣ ድምያኖስ ወንድሞቻቸውም አንቲቆስ፣ ዮንዲኖስ፣ አብራንዮስ ድዮማ ከምትባል ከተማ ስለ #እግዚአብሔር ልጅ የታነፀች ግምብ ከአለችበት አረምያ ከምትባል አገር ናቸው።

እናታቸውም ቴዎዳዳ #እግዚአብሔርን የምትፈራና የምትራራ መጻተኞችንና ዶኆችን የምትወዳቸው የምትረዳቸው ናት አባታቸውም ከሞተ በኋላ ልጆቿን እያስተማረች አሳደገቻቸው ። እሊህም ሁለቱ ቆዝሞስና ድምያኖስ የሕክምና ጥበብን ተምረው በሽተኞችን ያለ ዋጋ የሚፈውሱአቸው ይልቁንም ድኆችን አብዝተው የሚረዷቸው ሆኑ።

ወንድሞቻቸው ሦስቱ ግን ወደ ገዳም ሒደው መነኰሱ በጾምና በጸሎትም ተጠመዱ ። ከአባ አጋግዮስ አደራ በአስጠበቀው በንጉሠ ቊዝ ልጅ ምክንያት ዲዮቅልጥያኖስ ክዶ የረከሱ ጣዖታትን በአመለከ ጊዜ በምእመናን ላይ መከራ ሆነ ገንዘብ ወዳጅ አጋግዮስ ብዙ ወርቅን ተቀብሎ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ወደ አባቱ ልኮታልና ከዚህም በኋላ የንጉሠ ቊዝን ልጅ ዲዮቅልጥያኖስ ዳግመኛ ከጦር ሜዳ አግኝቶ ማረከው እርሱንም የንጉሡን ልጅ ሠውሮ አባ አጋግዮስን ጠራው ያንንም አደራ የሰጠውን የንጉሠ ቊዝን ልጅ እንዲአመጣ አዘዘው አጋግዩስም ሙቶ ተቀብሮአል ብሎ በሐሰት ተናገረ በዚያንም ጊዜ በመሠዊያው ፊት አማለው እሳትም ከሰማይ ወርዳ እንደምታቃጥለው ጠበቀ የእሳትም መውረድዋ በዘገየ ጊዜ ወርቅን በእሳት አቅልጦ አጠጣውና አቃጠለው ስለዚህም ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጣዖታትን አመለከ ።

ቆዝሞስና ድምያኖስ በሀገሩ ሁሉ ስለ #ክርስቶስ እነርሱ እንደሚያስተምሩ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ወደርሱ እንዲአቀርቧቸው አዘዘ በደርሱም ጊዜ ለአገረ ገዢው ለሉልዮስ እንዲአሠቃያቸው ሰጠው ። እርሱም በብዙ ሥቃዮች ማሠቃየትን ጀመረ በእሳት የሚያቃጥልበት ጊዜ አለ በግርፋት የሚገርፍበትም ጊዜ አለ ሦስት ወንድሞችም እንዳሏቸው ሰምቶ እነርሱንም ወደርሱ አስመጣቸውና አምስቱንም በመኰራኲር ውስጥ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ። ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨመሩዋቸው በውስጡም ሦስት ቀኖችና ሌሊቶች ኖሩ ያለ ጥፋትም በጤንነት ወጡ ዳግመኛም ከብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቻቸው እሳትን አነደዱ #እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት ጠበቃቸው።

መኰንኑም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ወደ ንጉሥ መለሳቸው ንጉሡም ዳግመኛ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ቴዎዳዳ እናታቸውም የምታስታግሣቸው ንጉሡንና የረከሱ ጣዖቶቹን የምትረግም ሆነች።

በዚያንም ጊዜ አንገቷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትንት አክሊልንም ተቀበለች ሥጋዋ ግን በምድር ላይ ወድቆ ነበር ቆዝሞስም እንዲህ ብሎ ጮኸ የዚች አገር ሰዎች ሆይ ይችን አሮጊት መበለት ሥጋዋን አፈር አልብሶ ይሠውራት ዘንድ ከውስጣችሁ ርኅራኄ በልቡ ያደረበት የለምን የህርማኖስ ልጅ ቅዱስ ፊቅጦርም በሰማ ጊዜ ተደፋፍሮ ሥጋዋን ገንዞ ቀበራት።

ንጉሡም እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ከመከራውም ዘመን በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_30 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጢሞቴዎስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤
⁶-⁷ ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል።
⁸ ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤
⁹-¹¹ ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሰራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሰራ ሲያውቅ ነው።
¹² ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤
¹³ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፥
¹⁴ የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ።
¹⁵ ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤
¹⁴ ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ።
¹⁵ በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤
¹⁶ አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ።
¹⁷ ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ።
¹⁸ ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ።
¹⁹ በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና።
²⁰ ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል።
²¹ የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።
¹¹ በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፦ ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው።
¹² በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ።
¹³ ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤
¹⁴ እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው፦ ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል።
¹⁵ እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን አሉአቸው።
¹⁶ የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው።
¹⁷ ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ፦ ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፥ የሚያወራለት ነገር አለውና አለው።
¹⁸ እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና፦ ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ አለው።
¹⁹ የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ፦ የምታወራልኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው።
²⁰ እርሱም፦ አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል።
²¹ እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው።
²² የሻለቃውም፦ ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው።
²³ ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ፦ ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው።
²⁴ ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው።
²⁵ ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል፦
²⁶ ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን።
²⁷ ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና።
²⁸ የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤
²⁹ በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_30_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ክብር ንጉሥ ፍትሐ ያፈቅር። አንተ አፅናዕካ ለጽድቅ በኃይልከ። ፍትሕ ወጽድቀ ለያዕቆብ አንተ ገበርከ"። መዝ 98፥4-5 ወይም መዝ 25፥5።
“የንጉሥ ክብር ፍርድን ይወድዳል፤ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ ለያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ አደረግህ።” መዝ.98፥4
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_30_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዮሐንስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ኢየሱስም ይህን ብሎ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ።
² ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ጊዜ ወደዚያ ስለ ተሰበሰቡ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ደግሞ ስፍራውን ያውቅ ነበር።
³ ስለዚህ ይሁዳ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻ ጦርም ወደዚያ መጣ።
⁴ ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣና፦ ማንን ትፈልጋላችሁ አላቸው።
⁵ የናዝሬቱን ኢየሱስን ብለው መለሱለት። ኢየሱስ፦ እኔ ነኝ አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር።
⁶ እንግዲህ፦ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ።
⁷ ደግሞም፦ ማንን ትፈልጋላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፦ የናዝሬቱን ኢየሱስን አሉት።
⁸ ኢየሱስ መልሶ፦ እኔ ነኝ አልኋችሁ፤ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው አለ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️#ሚቀደሰው_ቅዳሴ#እመቤታችን#ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የጻድቁ ንጉሥ የቅዱስ ገብረ መስቀል የዕረፍት በዓልና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ። ሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ታኅሣሥ_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ታኅሣሥ አንድ በዚህች ቀን በእስራኤል ፊት #ነቢይ_ቅዱስ_ኤልያስ የተገለጠበት ነው፣ የእስራኤላዊ #ቅዱስ_ናቡቴ ዕርፍቱ ነው፣ ቅዱስ አባት የጋዛ #ኤጲስቆጶስ_ጴጥሮስ አረፈ፣ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ዮሐንስ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኤልያስ_ርዕሰ_ነቢያት

በዚህችም በታኅሣሥ አንድ ቀን በእስራኤል ፊት ነቢይ ኤልያስ የተገለጠበት ነው። ይህ ቀናኢ ኤልያስ ከሌዊ ወገን የሆነ የአባቱ ስም ኢያስኑዩ የእናቱም ስሟ ቶና ነው።

ስለርሱም እንዲህ ተነገረ በተወለደ ጊዜ ብርሃንን የለበሱ አራት ሰዎች ሲሰግዱለትና ሕፃናት በሚጠቀለሉበት ጨርቅ ፈንታ በእሳት ሲጠቀልሉት አባቱ አየ። እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ይህን ለካህናቱ ነገራቸው እነርሱም ማደሪያው በብርሃን ውስጥ ይሆን፣ በቃሉም የሚቆርጥ ይሆን፣ ወይም እስራኤልን በሰይፍና በእሳት እየቀጣ ይገዛቸው ይሆን ተባባሉ።

በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብና በሚስቱ በኤልዛቤል በልጁም በአካዝያስም ዘመን ያደረገው የተአምራቱ ዜና በመጽሐፈ ነገሥት ተጽፎአል ። ወደ ሰማይ ያረገበት ዜናው ግን በጥር ወር በስድስት ቀን ተጽፎአል።

በኋላ ጊዜም ስለሚሆነው ሞቱ ራእይን በሕይወቱ ያየ ዮሐንስ ከኄኖክ ጋር እንደሚመጣና ሐሳዊ መሲሕን እንደሚቃወሙት ተአምራትንም እንደሚያደርጉ ተናግሮአል። ሁለቱ የዘይት ዕንጨቶች በምድር ላይም የተሾሙ በ #እግዚአብሔር ፊት የሚያበሩ ሁለት መብራቶች ናቸው አለ።

ከጠላቶቻቸውም ወገን ሊጣላቸው የወደደውን እሳት ከአፋቸው ወጥታ ታጠፋቸዋለች የሚጠሏቸው እንዲህ ይጠፋሉ። ትንቢት በሚናገሩበት ወራት በምድር ላይ ዝናም እንዳይዘንም ይዘጓት ዘንድ በሰማይ ላይ ሥልጣን አላቸውና ዳግመኛም ደምን ያደርጉት ዘንድ በውኃው ላይ ሥልጣን አላቸው የፈለጉትን ያህል በመቅሠፍቱ ሁሉ ምድርን ያስጨንቋታል።

ምስክርነታቸውንና ትንቢታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከባህር የወጣው አውሬ ከእሳቸው ጋር ይጣላል ድል ነስቶም ይገድላቸዋል ። አስከሬናቸውንም ፍጥሞ በምትባል በታላቂቱ አገር ያስጥለዋል ይችውም በምሥጢር ሰዶም ግብጽ የተባለች #ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።

አስከሬናቸውንም ሕዝብና አሕዛብ በሀገርም ያሉ ነገዶች ሦስት ቀን ተኩል ያዩታል አስከሬናቸውንም በመቃብር ይቀብሩት ዘንድ አያሰናብቱም። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በእነርሱ ሞት ደስ ይላቸዋል እርስበርሳቸውም በደስታ እጅ መንሻ ይሰጣጣሉ እሊህ ሁለቱ ነቢያት በምድር በሚኖሩ ሰዎች መከራ አጽንተውባቸዋልና ይላሉ።

ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከ #እግዚአብሔር ዘንድ የሕይወት መንፈስ መጥታ ታድርባቸዋለች ተነሥተውም በእግራቸው ይቆማሉ በሚያዩዋቸው ላይም ጽኑ ፍርሀት ይሆናል።

ከወደ ሰማይ ቃል መጥቶ ወደዚህ ውጡ ይላቸዋል ከዚህ በኋላ ጠላቶቻቸው እያዩአቸው በደመና ያርጋሉ። በዚያችም ሰዓት ጽኑ መነዋወጥ ይሆናል የዚያችም አገር ዐሥረኛ እጅዋ ይጠፋል በዚያም መነዋወጥ ሰባት ሽህ ሰዎች ይሞታሉ የቀሩት ግን ደንግጠው የሰማይ አምላክን ፈጽመው ያመሰግናሉ።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ነብይ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ናቡቴ_ኢይዝራኤላዊ

በዚህችም ዕለት የእስራኤላዊ ናቡቴ ዕርፍቱ ነው ይህ ናቡቴ በሰማርያው ንጉሥ በአክዓብ ቤት አጠገብ የወይን አትክልት ቦታ ነበረው። አክዓብም ናቡቴን ለቤቴ ቅርብ ነውና የተክል ቦታ ይሆነኝ ዘንድ ይህን የወይን ቦታህን ስጠኝ ከሱ የሚሻል ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ ዋጋውንም ትሻ እንደሆነ የዚህን የወይን ቦታህን ሽያጭ ወርቅ እሰጥሃለሁ የተክል ቦታ ይሁነኝ አለው።

ናቡቴም አክዓብን የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እንዲህ ያለ ነገር #እግዚአብሔር አያምጣብኝ አለው። አክዓብም አዝኖ ሔደ ፊቱንም ተከናንቦ በመኝታው ተኛ እህልንም አልበላም። ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደርሱ ገብታ እህል የማትበላ ምን ሆንክ የሚያሳዝንህስ ምንድን ነው አለችው። የኢይዝራኤል ሰው ናቡቴን የውይንህን ቦታ በዋጋ ሽጥልኝ ትወድም እንደሆነ ስለርሱ ፈንታ ሌላ ቦታ እሰጥሃለሁ ብዬ ብናገረው የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎኛልና ስለዚህ ነው ያዘንሁት አላት።

ሚስቱ ኤልዛቤልም ዛሬ እንዲህ የምታደርግ አንተ የእስራኤል ንጉሣቸው ነህን አሁንም ተነሥተህ እህል ብላ ራስህንም አፅና ልቡናህም ደስ ይበለው የኢይዝራኤል ሰው የናቡቴን ቦታ እኔ እሰጥሃለሁ አለቸው።

በአክዓብ ስም ደብዳቤ ጽፋ በማኅተሙም አትማ ያቺን ደብዳቤ ከናቡቴ ጋር ወደሚኖሩ ወደዚያ አገር አለቆችና ወደዚያች አገር ሽማግሌዎች ላከቻት።

የዚያችም ደብዳቤ ቃል እንዲህ የሚል ነው ጾምን ጹሙ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት የሐሰት ምስክሮችንም ሁለት ሰዎችን አስነሡበት #እግዚአብሔርን ሰደብከው ንጉሥንም ረገምከው ብለው ይመስክሩበት ከከተማም ወደ ውጭ አውጥታችሁ በደንጊያ ውገሩትና ይሙት የሚል ነው። እንዲህም በግፍ ኤልዛቤል አስገደለችው።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጴጥሮስ_ዘጋዛ

በዚህችም ቀን ቅዱስ አባት የጋዛ ኤጲስቆጶስ ጴጥሮስ አረፈ። ይህም ሮሀ ከሚባል አገር ክብር ካላቸው ወገን ነው ይሾመውም ዘንድ ወላጆቹ ለንጉሥ ቴዎዶስዮስ ሰጡት እርሱ ግን ሹመትንና ክብርን ይጠላ ነበር በንጉሡም አዳራሽ ውስጥ በጾም በጸሎት በሰጊድ ተጠምዶ ኖረ ከርሱም ጋር የፋርስ አገር ሰማዕታት ሥጋ አብሮት አለ በዚያንም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነው።

ከዚህም በኋላ ከገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ሔዶ መነኰሰና ጽኑ ተጋድሎንም ተጋደለ የቅድስናውና የተጋድሎው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ፈቃድ ወስደው ጋዛ በምትባል አገር በአውራጃዋም ሁሉ ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። ስለርሱም የቊርባንን ቅዳሴ በሚቀድስ ጊዜ ኅብስቱን ሲፈትት ጻሕሉን እስቲ መላው ድረስ ብዙ ደም እንደሚፈስ ተነገረ።

የቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን ሥጋ ወደርሱ ወስዶ ከኢየሩሳሌም ገዳማት በአንዱ ገዳም ኖረ በከሀዲው መርቅያን ዘመንም ወደ ግብጽ አገር ሸሸ የቅዱስ ያዕቆብም ሥጋ ከእርሱ ጋር አብሮ ነበር በዚያም ጥቂት ጊዜ ኖረ።

በአንዲትም ዕለት መሥዋዕት አዘጋጅቶ እርሱ ሲቀድስ ቁመው የነበሩ ሕዝብ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር በቅዳሴ ቊርባን ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስም አልገሠጻቸውም የ #እግዚአብሔርም መልአክ አይቶ ወደታች ሊወረውረው ወዶ ከመካከላቸው አንሥቶ ያዘው ግን ታግሦ ተወው እርሱ እነርሱን መገሠጽ አፍሮ አክብሮአቸዋልና።

የከሀዲው መርቅያን ዘመን በተፈጸመ ጊዜ ወደ ፍልስጥዔም ምድር ተመልሶ አብያተ ክርስቲያናትን አጠናከረ ከግብጻዊ አባ ኢሳይያስም ጋር ተገናኘ ዜናውም በንጉሥ ዘይኑን ዘንድ በተሰማ ጊዜ ንጉሡም ሊያየው ወደደ እርሱ ግን አልወደደም ከዚህ ከኃላፊው ክብር እጅግ ይሸሽ ነበርና።

ከዚህም በኋላ ጋውር ከሚባል አገር ዳርቻ ደርሶ በዚያ ተቀመጠ የተመሰገነ የሰማዕታት ፍጻሜ የሆነ የሊቀ ጳጳሳት ጴጥሮስ በዓሉ በደረሰ ጊዜ የቊርባንን ቅዳሴ ሠራ ቅዱስ ጴጥሮስም ተገለጸለትና ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደርሱ ትመጣ ዘንድ ይጠራሃል አለው። ከዚያችም ቀን ወዲህ የዕረፍቱ ጊዜ እንደ ደረሰ አውቆ ሕዝቡን ጠራቸውና በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አዘዛቸው ከዚህም በኋላ እጆቹን ዘርግቶ ነፍሱን በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_ዮሐንስ_ሊቀ_ጳጳሳት

በዚህችም ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዮሐንስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳኛ ነው።

ይህም የከበረ ቀሲስ የሆነ የገምኑዲ አገር ሰው ነው በዘመኑም የቅዱሳን ሰማዕታት የሰርጊስና የባኮስ ቤተ ክርስቲያናቸው ተሠራች ዳግመኛም የአቡቂርና የዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በምስር መሰብሰቢያ ቅጽር አጠገብ ተሠራች ያነፃቸውም ስሙ እንድርያስ የሚባል #እግዚአብሔርን የሚፈራ ያዕቆባዊ አንድ የግብጽ ሰው ነው። እርሱም ለመርዋን ልጅ ለገዢው ለንጉሥ አብደል ጸሐፊው ነው።

ይህም አባ ዮሐንስ የወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስን ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ አገር በታወቀ ቃምስ በሚባል ቦታ የሠራ ነው።

በዚህ በንጉሥ አብደል ዘመንም ሦስት ዓመት ያህል ጽኑ ረኃብ ሆነ ይህም አባት ለድኆች ለጦም አዳሪዎችና ለችግረኞች የሚያስብ ሆነ በየሳምንቱም አራት ጊዜ ወርቅና ብር እንጀራም ይሰጣቸዋል አብዝቶ የሚራራ መመጽወትን የሚወድ በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ነውና።

በዘመኑም ንጉሥ ይዜድ ሙቶ በርሱ ፈንታ መርዋን ነገሠ ይህም አባት በማርቆስ ወንበር ዘጠኝ ዓመት ኖረ በሰላምም አረፈ።

#እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ_1)
2024/12/28 01:51:46
Back to Top
HTML Embed Code: