Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 9
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁷ መጽሐፍ ፈርዖንን፦ ኃይሌን በአንተ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይነገር ዘንድ ለዚህ አስነሣሁህ ይላልና።
¹⁸ እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም እልከኛ ያደርገዋል።
¹⁹ እንግዲህ ስለ ምን እስከ አሁን ድረስ ይነቅፋል? ፈቃዱንስ የሚቃወም ማን ነው? ትለኝ ይሆናል።
²⁰ ነገር ግን፥ አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን?
²¹ ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን?
²²-²³ ነገር ግን እግዚአብሔር ቍጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ፥ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ፥ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ፥ እንዴት ነው?
²⁴ የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
¹⁰ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።
¹¹ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።
¹² እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥
¹³ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 20
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁸ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።
²⁹-³⁰ ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።
³¹ ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_12_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዘነፈቃ ለባሕረ ኤርትራ ወከፈላ። እስመ ለዓለም ምሕረቱ። ወአውፆኦሙ ለእስራኤል እንተ ማዕከላ"። መዝ 135፥14-15
"እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና"፤ መዝ 135፥14-15
ወይም👇
"ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ ለዕለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጣዐሙ ወታእመሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ.33÷7-8
"የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።
እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው"። መዝ.33÷7-8
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኀዳር_12_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁵ ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤
¹⁶ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤
¹⁷ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።
¹⁸ እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።
¹⁹ ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል።
²⁰ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️✝️✝️  የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ_ቅዳሴ ነው። መልካም የ #ቅዱስ_ሚካኤል በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_13

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን #ቅዱሳን_አእላፍ_መላእክት (፺፱ኙ ነገደ መላእክት) መታሰቢያ ነው፣ የከበረ ባለጸጋ #ቅዱስ_አስከናፍር እረፍቱ፣ የከበረ አባት #ቅዱስ_ጢሞቴዎስ_ዘእንጽና እረፍቱ፣ ሊቀጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ዘካርያስ እረፍቱ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አእላፍ_መላእክት (፺፱ኙ ነገደ መላእክት)

ኅዳር ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን የአእላፍ መላእክትን የበዓላቸውን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን ። እሊህም ሥጋ የሌላቸው ረቂቃን የሆኑ ለዓለሙ ሁሉ የሚማልዱ ናቸው ።

ቅዱስ ኄኖክም ስለእርሳቸው እንዲህ አለ በሰማይ እያለሁ ነፋሳት በደመና ውስጥ አወጡኝ በእሳት ላንቃም ወደታነፀ ቤት አደረሱኝ በዚያም አእላፋት መላእክትን አየሁ እነርሱም በእሳት ላቦት ላይ የቆሙ ልብሳቸውም እንደ በረድ ነጭ ነው አለ።

ቅዱስ ያዕቆብም እንዲህ አለ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርስ መሰላልን አየሁ የ #እግዚአብሔርም መላእክት በውስጥዋ ይወጡ ይወርዱ ነበር። ሁለተኛም ከሶርያ መመለሻው በሆነ ጊዜ የመላእክት ሠራዊትን አየሁ አለ ።

ቅዱስ ሙሴም እንዲህ አለ #እግዚአብሔር አሕዛብን በቦታ እንደለያቸው የአዳምን ልጆች እንደበተናቸው #እግዚአብሔርን በሚያገለግሉ መላእክት ቁጥር የአሕዛብን አውራጃዎች እንደ ወሰናቸው። ሁለተኛም #እግዚአብሔር ከሲና ተራራ መጥቶ በሴይር ታየኝ ረቂቃን መላእክቶቹም ከእርሱ ጋር ነበሩ አለ ።

ቅዱስ ዳዊትም እንዲህ አለ መላእክቱን መንፈስ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ እርሱ ነው ። ሁለተኛም የ #እግዚአብሔር ሠረገላዎች የብዙ ብዙ ሽህ ናቸው አለ ። ቅዱስ ኤልሳዕም የእሳት ሠረገሎችና የእሳት ፈረሶች በዙሪያው ቁመው ሲጠብቁት አየ ።

ቅዱስ ዳንኤልም እንዲህ አለ ዙፋኖችን እስቲዘረጉለት ድረስ ደርሶ አየሁ ብሉየ መዋዕል #እግዚአብሔር በላያቸው ተቀመጠ ልብሱም እንደ በረድ ነጭ ነው የራሱም ጠጉር እንደ ብዝት ነጭ ነው ዙፋኑም የሚነድ እሳት ነው ሠረገላውም የሚንቦገቦግ ፍም ነው ። የእሳትም ጐርፍ በፊቱ ይፈሳል የብዙ ብዙ የሆኑ መላእክትም ያገለግሉታል የእልፍ እልፍ መላእክትም በፊቱ ይቆማሉ በአደባባይም ተቀምጦ መጻሕፍትን ገለጠ ።

ቅዱስ ሉቃስም እንዲህ አለ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት መጡ #እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ በሰማይ ለ #እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰው ልጅ በጎ ፈቃድ እያሉ ።

ቅዱስ ማቴዎስም እነሆ መላእክትም ሊአገለግሉት መጡ አለ ። ሁለተኛም የሰው ልጅ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በጌትነቱ በሚመጣበት ጊዜ ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ላይ ይቀመጣል ። ቅዱስ ዮሐንስም #ጌታችን ከተናገረው ቃል እንዲህ አለ እውነት እውነት እላችኋለሁ ከእንግዲህ ወዲህ ሰማዮች ሲከፈቱ የ #እግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወርዱና ሲወጡ ታያላችሁ አላቸው የሚል ነው ።

ሐዋርያው ይሁዳም እነሆ #እግዚአብሔር ይፈርድ ዘንድ አእላፋት የሆኑ ቅዱሳን መላእክቶቹን አስከትሎ ይመጣል አለ። የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም የመዓርጋቸውን ደረጃ ወይም አይነት እንዲህ ብለው ተናገሩ መላእክት አጋዕዝት ሥልጣናት ኃይላት መናብርት መኳንንት ሊቃናት አርባብ ኪሩቤል ሱራፌል ብለው ተናገሩ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በቅዱሳን መላእክቶቹ አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አስከናፍር_ሮማዊ

በዚህችም ቀን ዐሥራ ሦስት ወንበዴዎች ስለርሱ በእርሱ ሃይማኖት ከዓለም የተለዩ የከበረ ባለጸጋ አስከናፍር አረፈ ። ይህም ቅዱስ አስከናፍር ከሮሜ መኳንንት አንዱ ነው እርሱም ለድኆችና ለምስኪኖች ምጽዋትን የሚሰጥ እንግዶችንና መጻተኞችን የሚቀበል ነው ።

በዚያም ወራት ያገኙትን ሰው ሁሉ የሚነጥቁና የሚያጠፉ ዐሥራ ሦስት ሽፍቶች ነበሩ እንግዳ እንደሚቀበል ይልቁንም መነኰሳትን እንደሚወድ የ ቅዱስ አስከናፍርን ዜና በሰሙ ጊዜ ወደርሱ ሒደው በተንኮል ይገድሉት ዘንድ ገንዘቡንም ሁሉ ሊወስዱ ተማከሩ ። ከዚህም በኋላ የምንኲስና ልብስ ለብሰው ከደጁ ቆሙ በአያቸውም ጊዜ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንደሆኑ አንዱ ጌታ #ክርስቶስ እንደሆነ አሰበ ሰገደላቸውም ወደ ቤቱም አስገብቶ ማዕድ አቀረበላቸው እግራቸውንም አጠበ ሠላሳ አምስት ዓመት ሽባ ሆኖ በኖረ ልጁ ላይ ያንን እግራቸውን የታጠቡበትን ውኃ ረጨ ወዲያውኑ ልጁ ዳነ ።

እነዚያ ሽፍቶችም የሆነውን በአዩ ጊዜ እጅግ ደነገጡ እርሱ ቅዱስ አስከናፍር ግን አባቶቼ ሆይ #ጌታ_ክርስቶስ ከእናንተ መካከል የቱ እንደሆነ ንገሩኝ እሰግድለት ዘንድ አላቸው የአገር ሰዎችም የመኰንኑ ልጅ እንደዳነ በሰሙ ጊዜ ወደርሳቸው መጥተው ሰገዱላቸው እንዲህም አሏቸው የ #እግዚአብሔር ቅዱሳኖች ሆይ ባርኩን በሽተኞቻችንን አድኑልን ። ከዚህም በኋላ እሊያ ወንበዴዎች ሾተሎቻቸውን አውጥተው በእርሳቸው ልንገድልህ በወደድንበት እኛን ይገድሉን ዘንድ እሊህን ሾተሎች ውሰድ አሉት #እግዚአብሔር በአንተ ጽድቅ የራራልን ባይሆን በአጠፋን ነበር ።

ይህንንም ከአሉት በኋላ ተሰናበቱት ከእርሱም አንድ አንድ መስፈሪያ ምስር ለየአንዳንዳቸው ተቀብለው ሃያ አምስት ቀን ያህል የሚያስጉዝ ጉዳና ወደ ምድረ በዳ ተጓዙ ያንንም ምስር ከአሸዋ ውስጥ በተኑት ፀሐይ በሚገባም ጊዜ ከአሸዋው ውስጥ ሦስት ሦስት ምስር ፈልገው ይቀምሳሉ እንደዚህም ሠላሳ ዓመት ኖሩ ። ከዚህም በኋላ ከሀዲ መኰንን በመጣ ጊዜ እርሱ ወዳለበት ሒደው በ #ጌታችን ታመኑ እርሱም ገደላቸውና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በ ቅዱስ አስከናፍርና በእሊህ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ጢሞቴዎስ_ዘእንጽና

በዚህችም ቀን የሀገረ እንጽና ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት ጢሞቴዎስ አረፈ ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ ልቡ ንጹሕ የሆነ ጻድቅ ሰው ነው ታላቅ ተጋድሎንም የተጋደለ ነው። የእንጽና አገር መኰንንም ለሰዎች የቀናች ሃይማኖትን በማስተማሩና በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስለ አመነ ይዞ ጽኑዕ ሥቃይን ብዙ ዘመናት አሠቃየው ። ከእሥር ቤትም አውጥቶ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃይቶ ወደ እሥር ቤት ይመልሰው ነበር ከእርሱም ጋር ስለ ሃይማኖት የታሠሩ ብዙዎች ቅዱሳን ሰማዕታት ነበሩ ከእሳቸውም በወህኒ ቤት ጥቂቶች እስከቀሩ ድረስ ያ ከሀዲ መኰንን ብዙዎቹን አውጥቶ አሠቃይቶ ንጹሕ ደማቸውን በማፍሰስ ፈጃቸው ።

ከዚህም በኋላ ከሀዲውን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን #እግዚአብሔር በአጠፋው ጊዜ #እግዚአብሔርን የሚወድ ጻድቅ ሰው ቅዱስ ቈስጠንጢኖስ ነገሠ በዚያንም ጊዜ #ክርስቶስን በመታመን የታሠሩትን ሁሉ ይፈቱአቸው ዘንድ መልእክቱ በሀገሮች ሁሉ ደረሰች ።

ይህ ቅዱስ አባት ጢሞቴዎስም ከእሥር ቤት በወጣ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ ያሉትን መነኰሳቱንና ካህናቱን ሁሉ ሰበሰባቸው ስለዚያ ስለአሠቃየው መኰንን ነፍስ ድኅነትም #እግዚአብሔርን እየለመነ ከማታ እስከ ጥዋት ድረስ ፍጹም የሆነ ጸሎትን በማድረግ አደረ ።
እንዲህም ብሎ ጸለየለት አቤቱ ይህን መኰንን ማረው እርሱ ለእኔ ታላላቆች የሆኑ በጎ ነገሮችን አድርጎልኛልና ወደ አንተም ለመድረሴ ምክንያት ሁኖኛልና አቤቱ እንዲሁ በአንተ አምኖ ወዳንተ ይደርስ ዘንድ ምክንያት አድርግለት ። የዚህ አባትም ልብ ከቂም ከበቀል የነጻ በመሆኑ ሰዎች አደነቁ ።

ይምረው ዘንድ ነፍሱንም ያድንለት ዘንድ አባ ጢሞቴዎስ ስለርሱ ወደ #እግዚአብሔር እንደሚለምን ለመኰንኑ ነገሩት መኰንኑም ሰምቶ እጅግ አደነቀ እንዲህም አለ እኔ ግን ጽኑ ሥቃይን ስለአሠቃየሁት እንደሚረግመኝ አስብ ነበር አሁን እርሱ ግን ስለ እኔ ምሕረትን ይለምናል የእሊህ ክርስቲያን ሃይማኖታቸው በውስጡ የተሠወረ ሰማያዊ የሆነ ምሥጢር አለ። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ልኮ ይህን አባት ጢሞቴዎስን አስመጣውና ስለ ክርስትና ሕግ ያስረዳው ዘንድ ለመነው እርሱም ከዓለም መፈጠር ጀምሮ ያለውን ገለጠለት ዳግመኛም የ #ወልደ_እግዚአብሔርን ሰው የሆነበትን ምክንያት ከብዙ ዓመታትም አስቀድሞ ነቢያት ስለርሱ ትንቢት እንደተናገሩ ከእመቤታችን ከቅድስት #ድንግል_ማርያም#እግዚአብሔር ልጅ ሰው በመሆኑ ትንቢታቸው እንደተፈጸመ ስለእኛ መከራ ተቀብሎ ተሰቅሎ ስለመሞቱ ስለትንሣኤውና ስለ ዕርገቱ ዳግመኛም ለፍርድ ስለመምጣቱ አስረዳው ።

መኰንኑም በክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምኖ በዚህ አባት እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ሹመቱንም ትቶ መነኰሰ በገድልም ተጠመደ ከዚህም አባት ጢሞቴዎስ መንጋዎች ውስጥ የተቈጠረ ሆነ ። ይህም አባት ጢሞቴዎስ የቀረ ዘመኑን መንጋዎቹን ሁልጊዜ እያስተማረ በቀናች ሃይማኖትም ላይ እያጸናቸው ኑሮ በሰላም በፍቅር አንድነት አረፈ ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባት ጢሞቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባት_ዘካርያስ

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዘካርያስ አረፈ ። ይህም አባት ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ነው በቤተ ክርስቲያንም ንብረት ሁሉ ላይ መጋቢነትና ቅስና ተሾመ እርሱም በተጋድሎ የጸና ንጹሕ ድንግል ነው በጠባዩም የዋህ ቅን የሆነ በዕድሜውም የሸመገለ ነው ።

ሊቀ ጳጰሳት አባ ፊላታዎስም በአረፈ ጊዜ ለዚች ሹመት የሚገባ ሰው ይመርጡ ዘንድ በ #እግዚአብሔር ምክር ኤጲስቆጶሳት ተሰበሰቡ እነርሱም ለዚች ሹመት ስለሚሻል ሰው በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው እየተነጋገሩ ሳሉ እነሆ አንድ ሰው መማለጃ በመስጠት ያለ ኤጲስቆጶሳት ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ከንጉሥ የመልእክት ደብዳቤ ይዞ እንደሚመጣ ከእርሱም ጋር ከንጉሥ የተቀበላቸው ጭፍሮች እንዳሉ ሰሙ ። ኤጲስቆጶሳቱም የአባቶቻችንን የሐዋርያትን ሥርዓት በመተላለፍ መማለጃ በመስጠት ስለሚደረገው የሊቀ ጵጵስና ሹመት አዘኑ ። ስለዚህም እርሱ ራሱ የመረጠውን ይሾምላቸው ዘንድ ወደ #እግዚአብሔር ተግተው በማዘውተር የሚጸልዩና የሚማልዱ ሆኑ ።

እነርሱም #እግዚአብሔርን እየለመኑ ሳሉ እነሆ ይህ አባት ዘካርያስ ከቤተ ክርስቲያን ጫፍ በመሰላል ሲወርድ ሆምጣጤ የተመላ እንስራ በእጁ ይዞ ነበር እግሩንም አድጦት ከመሰላሉ ጫፍ እስከታች ወደቀ እንስራውንም እንደያዘ ፈጥኖ ተነሣ እንስራውም አልተሰበረም ሆምጣጤውም አልፈሰሰም ።

ኤጲስቆጶሳቱም ይህን ምልክት በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ የአገሩንም ሰዎች ትንሹንም ትልቁንም ስለርሱ ጠየቋቸው እነርሱም ጽድቁንና ትሩፋቱን ተናገሩ ስለርሱም መሾም ሁሉም ተስማምተው ይህን አባ ዘካርያስን በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ።

ከዚህም በኋላ ብዙ መከራና ኀዘን በላዩ ከግብጽ ንጉሥ እልሐክም ዘንድ ደረሰበት ይህም ገዢ ማለት ነው ። በዚያም ወራት ከአባ መቃርስ ገዳም አንድ መነኲሴ ወደርሱ መጥቶ ኤጲስቆጶስነት ሹመኝ አለው አባ ዘካርያስም ልጄ ሆይ ታገሥ አባቶቻችን ሐዋርያትም ያዘዙትን ሥርዓት አትተላለፍ ግን ወደ ገዳምህ ተመልሰህ ስለ ነፍስህ ድኅነት ተጋደል #እግዚአብሔርም የፈቀደው ይሁን አለው ።

ይህንንም በጎ ምክር በሰማ ጊዜ ያ መነኵሴ ተቆጣ በልቡም ሰይጣን አደረበትና ወደ ግብጽ ንጉሥ ሒዶ በሐሰት ነገር አባ ዘካርያስን ወነጀለው ንጉሡም የከበረ አባት ዘካርያስን ይዞ አሠረው ። ከዚህም በኋላ ተነጣጥቀው ይበሉት ዘንድ ለአንበሶች ጣለው አንበሶችም ከቶ አልቀረቡትም ንጉሡም የአንበሶቹን ጠባቂ ተቆጣ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጉቦ የተቀበለ መስሎት ነበርና ። ከዚህም በኋላ አንበሶቹን አስራባቸውና ሊቀ ጳጳሳቱን የላም ደም ቀብቶ በድጋሜ ለአንበሶች ጣለው እነርሱም ከቶ አልቀረቡትም ንጉሡም አደነቀ ከአንበሶች መካከልም እንዲአወጡት አዘዘ።

ከዚህም በኋላ ሦስት ወር አሠረው ሁል ጊዜም እንዲህ የሚለው ሆነ የክርስቲያንን ሃይማኖት ትተህ ወደእኛ ሃይማኖት ካልገባህ አለበለዚያ እኔ አሠቃይቼ በሰይፍ እገድልሃለሁ ። ዳግመኛ ለአንበሶች እጥልሃለሁ ወይም ከእሳት ውስጥ እጨምርሃለሁ የከበረ አባ ዘካርያስ ግን በሃይማኖቱ በመጽናት ምንም ምን አልፈራም ።

ሁለተኛም ብዙ ቃል ኪዳኖችን ገባለት እንዲህም አለው ትእዛዜን ተቀብለህ ወደ ሃይማኖቴ ብትገባ እኔ ብዙ ሀብት እስጥሃለሁ በሁሉ መሳፍንትም ላይ መስፍን አድርጌ እሾምሃለሁ ቅዱስ አባት ዘካርያስም በዓለም ያለ መንግሥትን ሁሉ ብትሰጠኝም የቀናች ሃይማኖቴን አልተውም ብሎ መለሰለት ።

ከዚህም በኋላ ጥቂት ቀን አሥሮ ለቀቀው ከእሥር ቤትም ወጥቶ አባ ዘካርያስ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ። ንጉሡንም ስለ መፍራት ከእርሱ ጋር የሔዱ ብዙ ኤጲስቆጶሳት ነበሩ በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉንም እንዲአፈርሱአቸው ንጉሥ አዞ ነበርና ። ታላቅ ሥቃይንም እያሠቃየ ብዙዎች ክርስቲያኖችን ከሃይማኖታቸው አወጣቸው የክርስቲያንም ወገኖች በዚህ መከራ ውስጥ ዘጠኝ ዓመት ኖሩ ።

ከዘጠኝ ዓመትም በኋላ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሕዝቡን ይቅር አለ ቊጣውንም መለሰ መከራውንም ሁሉ ከላያቸው አስወገደ ንጉሡ በሚገዛቸው አገሮች በሁሉ ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ ከእነርሱም የወሰዱትን ገንዘባቸውን ሁሉ የምድራቸውን ጒልት እንዲመልሱላቸው ንጉሡ አዘዘ ።

ከዚህም በኋላ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ ከፊተኛውም እጅግ የተሻሻሉ ሁነው ዳግመኛ ታደሱ ይህም አባት ዘካርያስ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ ክርስቲያኖችም በአብያተ ክርስቲያኖቻቸው በሚጸልዩና በሚቀድሱ ጊዜ ያለ ሥጋት ደወሎቻቸውን እንዲደውሉ ንጉሥ አዘዘ ።

ክርስቲያኖችም በታላቅ ደስታ የሚኖሩ ሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ሁሉ የቀና ሁኗልና ይህም አባት አብያተ ክርስቲያናትን እያሠራ የሚያሻቸውንም እያሰበ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ ።

በአንዲት ዕለትም በሥጋው ለምጽ ያለበት ስሙ መርቆሬዎስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ወደርሱ መጣ አባ ዘካርያስም በትሕትና በቅን ልቡና እንዲህ አለው ። ወንድሜ አባ መርቆሬዎስ ሆይ በአንተ ላይ ስለደረሰ ስለዚህ ደዌ እኔም በጸሎቴ ረዳሃለሁ #እግዚአብሔር ሙሴን በፍርድ ውስጥ ለማንም አታድላ ያለውን አንተ ታውቃለህ ስለዚህ ይህ የለምጽ ደዌ በላይህ እያለ ክህነት አይገባህም መጽሐፍ ርኲስ ነው ብሎታልና አለው ኤጲስቆጶሱ አባ መርቆሬዎስም አለቀሰና አባቴ በጸሎትህ ርዳኝ አለው ።
ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ ሔደ በሀገረ ስብከቱ ወዳለች የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ ከዚህም ደዌ ታነጻው ዘንድ ወደርሷ በመጸለይና በመማለድ እያለቀሰ በ #እመቤታችን_ማርያም ሥዕል ፊት ቆመ ከሰኞ ጥዋት ጀምሮ እንዲህ እያደረገ ቀንና ሌሊት እየጸለየና አየጾመ ኖረ ።

በረቡዕ ዕለትም በዘጠኝ ሰዓት ደክሞት የእመቤታችን የቅድስት #ድንግል_ማርያም ሥዕል ከበላዩ ካለችበት ግድግዳ ላይ ራሱን አስጠግቶ አንቀላፋ ። በእንቅልፉም ውስጥ ሳለ የሥዕሊቱ እጅ ሥጋውን ሲዳሥሥ አየ በዚያንም ጊዜ ነቅቶ ሥጋው ከለምጹ ነጽቶ አገኘው ታላቅ ደስታም አደረገ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስንም አመሰገነው እመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምንም አመሰገናት ረድኡም ሲመጣ ና ልጄ ሆይ ሥጋዬን እይ #እመቤቴ_ማርያም ከደዌ አንጽታኛለችና አለው በዚያችም ቤተክርስቲያን ውስጥ #እግዚአብሔርን እያመሰገነ እስከ ቀዳሚት ሰንበት ድረስ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ተነሥቶ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዘካርያስ ሔደ በዕለተ እሑድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለ በእርሱ ላይ የሆነውን አስረዳው እንዲህም አለው ይህ ሁሉ የተደረገልኝ በከበረች ጸሎትህ ነው ። የከበረ አባ ዘካርያስም እንዲህ ብሎ መለሰለት #እግዚአብሔር ንጹሕና ቅን የሆነ ልቡናህን ተመልክቶ ልመናህንና ዕንባህንም ተቀብሎ ከደዌህ አነጻህ አሁንም ከተቀበልከው ጸጋ እንባረክ ዘንድ ቀድሰህ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ልታቀብለን ይገባሃል ። ያን ጊዜም መሥዋዕትን ሠርቶ ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን አቀበላቸው በቤተ ክርስቲያን ያሉትም ሁሉ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበሉ ስለዚች ምልክትም አደነቁ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ።

ሁለተኛም አንድ ዲያቆን ወደ አባ ዘካርያስ መጥቶ ሰገደለት በፊቱም አለቀሰ እግሮቹንም እየሳመ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ራራልኝ እኔ ተሳስቼ በኃጢአት ወድቄአለሁና ወዲያውኑ ሥጋዬ ሁሉ ለምጽ ሆነ ። አባ ዘካርያስም ልጄ ሆይ በ #እግዚአብሔር ፊት በድካም ላይ መጽናት ይቻልሃልን አለው አዎን አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ።

በዚያንም ጊዜ በእርሱ ዘንድ በጨለማ ቤት ዘጋበትና እንዲህ ብሎ አዘዘው ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ በመቆም በቀንም በሌሊትም ስለ ኃጢአቱ እየተጸጸተ ወደ #እግዚአብሔር በጸሎት እንዲማልድ አባ ዘካርያስም ከሦስት ቀኖች በኋላ ጥቂት እንጀራ በሚዛን መዝኖ ጥቂት ውኃም ሰጠው ሦስት ሱባዔዎችም እንዲህ አድርጎ ሥጋውን ጐበኘ ለምጹንም አገኘው በወር መጨረሻም ጐበኘው ለምጹን በሥጋው ላይ አገኘ።

ልጄ ሆይ በርታ አትፍራ አለው አርባ ቀኖችም ከተፈጸሙ በኋላ ጐበኘው ሥጋው ከለምጹ ነጽቶ አገኘው ዘይትንም ቀባው ልጄ ሆይ እነሆ ድነሃል ነፍስህን ጠብቅ ከእንግዲህም ዳግመኛ ወደ ኃጢአት ሥራ እንዳትመለስ ተጠበቅ አሁንም በሰላም ወደ ቤትህ ግባ አለው እርሱም የተመሰገነ #እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ገባ ።

#እግዚአብሔርም በዚህ አባት እጆች ድንቆች ተአምራትን አደረገ በሹመቱም ወንበር ሃያ ስምንት ዓመት ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ ይኸውም ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በሰባት መቶ ስልሳ ነው ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_13)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ዕብራውያን 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²² ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥
²³ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥
²⁴ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።
²⁵ ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ይሁዳ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴-¹⁵ ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።
¹⁶ እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል።
¹⁷ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር።
⁷ እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና፦ ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ።
⁸ መልአኩም፦ ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ።
⁹ ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም።
¹⁰ የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ።
¹¹ ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_13_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ባርክዎ ለእግዚአብሔር ኵልክሙ መላእክቲሁ። ፅኑዓን ወኃያላን እለ ትገብሩ ቃሎ። ወእለ ትሰምዑ ቃለ ነገሩ"። መዝ 102፥20።
“ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ።” መዝ 102፥20።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_13_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³¹ የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤
³² አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥
³³ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።
³⁴ ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።
³⁵ ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥
³⁶ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።
³⁷ ጻድቃንም መልሰው ይሉታል፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ?
³⁸ እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ?
³⁹ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?
⁴⁰ ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።
⁴¹ በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።
⁴² ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥
⁴³ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና።
⁴⁴ እነርሱ ደግሞ ይመልሱና፦ ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል።
⁴⁵ ያን ጊዜ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል።
⁴⁶ እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ ወይም  የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ እግዚአብሔር አብ በዓል፣ የ99ኙ ነገደ መላእክት በዓል፣ የቅዱስ አስከናፍር፣ የቅዱስ ጢሞቴዎስና የሊቀጳጳስ የአባ ዘካርያስ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ዐሥራ አራት በዚህች ቀን #ቅዱስ_መርትያኖስ_ዘጠራክያ አረፈ፣ #የአባ_ዳንኤል_ገዳማዊ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መርትያኖስ_ዘጠራክያ

ኅዳር ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የሀገረ ጠራክያ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አባት አባ መርትያኖስ አረፈ።

ይህም ቅዱስ ሶርያ ከምትባል አገር ነው ወላጆቹም ክርስቲያን ናቸው እርሱም በገድል የተጠመደ ተጋዳይ ነው አርዮሳውያንንም የሚቃወማቸው ከሀድያን የሚላቸው አውግዞም የሚያሳድዳቸው ሆነ። ስለዚህም በእርሱ ላይ ታላቅ መከራ ደረሰበት። በሚያልፍባትም ጎዳና ጠብቀው ይይዙታል አብዝተውም ገርፈው እግሩን ይዘው በሜዳ ውስጥ ይጎትቱታል እንዲህም ብዙ ጊዜ አደረጉበት። ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው ሸሽቶ ወደ ሩቅ አገር ተጉዞ ከኤርትራ ባሕር ዳር ደረሰ ከምድር የሚበቅሉ ቅጠሎችን እየተመገበ በዚያ በዋሻ ውስጥ ብዙ ዓመታትን ኖረ።

ኤጲስቆጶስም ይሆን ዘንድ #እግዚአብሔር መረጠው እነሆ የተጋድሎውና የትሩፋቱ ዜና በተሰማ ጊዜ ከዚያ ወስደው ጠራክያ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት እንደ ሐዋርያት ሥርዓት በሹመቱ በጎ አካሔድን ተጓዘ በዘመኑም በብዙዎች ላይ ሰላም ፍቅር ቸርነት ሆነ።

#እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ተአምራትን አደረገ በጎዳናም አልፎ ሲሔድ የሞተ ሰው አየ ሌላም ዓመፀኛ ልቡ የደነደነ በሐሰት ከእርሱ ላይ አራት መቶ የወርቅ ዲናር አለኝ ያንን ካልሰጡኝ አላስቀብርም ብሎ ዘመዶቹን ሲከለክል ነበር። ይህም ቅዱስ የሞተውን ይቅበሩት ተዋቸው ብሎ ብዙ ለመነው እርሱ ግን አልሰማውም። በዚያንም ጉዜ ይህ ቅዱስ ወደ #እግዚአብሔር እየጸለየ ማለደ ያን ጊዜ የሞተው ሰው ተነሥቶ ምንም ምን ዕዳ እንደሌለበት ተናገረ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርትያኖስ ያንን ዓመፀኛ በሰው ፊት እንዲህ አለው ለምን በሐሰት ተናገርክ የተሠወረውን የሚያውቅ #እግዚአብሔርን አትፈራውምን በዚያንም ጊዜ ያ ዓመፀኛ ሞተ ከሞት የተነሣው ግን በሰላም ወደ ቤቱ ገባ።

ከዚህም በኋላ ይህ ቅዱስ መርትያኖስ ብዙ ዘመናትን ኖረ መልካም አገልግሎቱንም ፈጽሞ #እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ዳንኤል_ገዳማዊ

በዚህችም ቀን ለፋርስ ንጉሥ ተአምራት ያደረገና ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ያሳመነው የአባ ዳንኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።

የእምነቱም ምክንያት እንዲህ ነው ይህ ንጉሥ ጽኑዕ የሆነ የሆድ በሽታ ታሞ ነበር፤ ባለ መድኃኒቶችም ሊአድኑት አልቻሉም። ንጉሡም ከማዕዱ የሚመግበው አብሮት የሚኖር ሥራየኛ ሰው ነበረው። ንጉሡም እንዲህ አለው "ያንተ ከእኔ ጋር መኖር ጥቅሙ ምንድንነው? ከዚህ በሽታ ካልፈወስከኝ እገድልሃለሁ።"

ሥራየኛውም ንጉሡን በተንኮል እንዲህ ብሎ ተናገረው "ንጉሥ ሆይ የምነግርህን ካደረግህ ከደዌህ ትድናለህ። አሁንም ለአባትና እናቱ አንድ ብቻ የሆነ ልጅ ይፈልጉልህ እናቱ አሥራ ትያዘው አባቱም ይረደው በእርሱም ደም ትድናለህ።" መሠርዩ ይህን ማለቱ ግን እንዲህ ያለ ሥራ መሥራትን ንጉሥ ይፈራል ወይም ልጁን የሚሰጥ አይገኝም ብሎ አስቦ ነው።

ንጉሥም በሚገዛው አገር ውስጥ ፈልገው በአንድ ሺህ የወርቅ ዲናር ሕፃን ልጅ ይገዙለት ዘንድ አሽከሮቹን አዘዘ። በዚያችም አገር አንድ ልጅ ያላቸው ድኆች የሆኑ ባልና ሚስት ነበሩ እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ልጃቸውን ወደ ንጉሥ ወሰዱ ልጁም በማልቀስ እኔ በፈጠረኝ #እግዚአብሔር ላይ ተማምኛለሁና እርሱም ያድነኛል ይል ነበረ።

እናቱም አጥብቃ አሠረችው አባቱም ሊያርደው በንጉሡ ፊት ሾተሉን መዘዘ፤ በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ አይኖቹን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ ወደ #እግዚአብሔር በልቡ ሲጸልይ ከንፈሮቹን አንቀሳቀሰ። #እግዚአብሔርም በንጉሡ ልብ ርኅራኄን አሳደረ ፈትታችሁ ልቀቁት ብሎ አዘዘ። ወደርሱም አቅርቦ "ዐይኖችህን ወደ ሰማይ በአቀናህ ጊዜ ምን አልክ?" አለው። "ጌታዬ ሆይ ልጅን የሚገፋው ቢኖር አባትና እናቱ ያድኑታል ከዚያም የጸና ሥራ ቢኖር ንጉሥ ዳኛ ያድነዋል እኔ ግን ከሁላችሁም ርዳታ በአጣሁ ጊዜ ወደ #እግዚአብሔር ለመንኩ" አለው። ንጉሡም ሰምቶ ራራለት አንድ ሽህ የወርቅ ዲናርንም ሰጠው።

ስለዚህም #እግዚአብሔር ይቅር ሊለው ወዶ መነኰስ ዳንኤልን ላከለት። እርሱም ወደ ንጉሡ በደረሰ ጊዜ በፊቱ ተአምራትን አድርጎ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አሳመነው ከበሽታውም ፈወሰው። ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋርም አጠመቀው። ከዚህም በኋላ ወደ በዓቱ ተመልሶ እየተጋደለ ኖረ። #እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_14)
"በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

           #ኅዳር ፲፫ (13) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ ኤርትራ ውስጥ በሚገኘው ታላቁ ገዳም ደብረ ቢዘን #ከአቡነ_ፊሊጶስ በኋላ አበምኔት ለነበሩት ልክ እንደ #ነቢዩ_ቅዱስ_ኤልያስ ዝናብ እንዳዘንብ ሦስት ዓመት ሰማይን ለለጎሙት ለታላቁ አባት ለሃይማኖት መምህር #ለአቡነ_ዮሐንስ ለዕረፍት በዓል መታሰቢያና  በሰላም አደረሰን።

#ስለ_አቡነ_ዮሐንስ_ዘደብረ_ቢዘን_ዕረፍት፦ "...ሁለተኛም ከሞቴ በኋላ ባገኛችሁት ጊዜ በሁላችሁ አንደበት ላይ መታሰቢያየ ይበዛሉ ስሜን ሳታስቡ አንዲት ቀን እንኳን አታልፋችሁም" አላቸው። ይህንንም ብሎ አባ ሠረቀ ብርሃን ጠራውና መምህርነት ሾሞ በጽድቅ ሥርዓት ባረከውና "አባቴ ፊሊጶስና እኔ በሠራነው በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወንድሞቼን ጠብቃቸው በጽድቅ ሥርዓትም ጠብቅ" አለው። "ከሁለታችን ጋር ስላለው ነገር አንተ ታውቃለህና" ይህንን ሁሉ ካለው በኋላ በከበረች በረከት ገዳሞችን ሁሉ ባረከ።

ሁለተኛም "ይህች ቀን ምን ናት" አላቸው "ኅዳር ዐሥራ ሁለት ቀን የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን ናት" አሉት "በዚች ቀን ተወለድኩ በዚች ቀን መጨረሻየ ቢሆን በወደድኩ ነበር" አላቸው። "እግዚአብሔር ቢወድ በዚች ቀን ይጐበኘኝ ዘንድ በሁለተኛው ቀን ዕረፍቴ ለእኔ ይሆን ዘንድ ለመንኩት። በብዙ ትጋት መታሰቢያየ ለሚያደርጉ ወንድሞች ዕረፍትና ደስታ ትሆናቸው ዘንድ ጸሎቴን ስማኝ" አለ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ መለሰና ወደ ውስጣቸው ገብቼ እግዚአብሔርን እጅ እነሳ ዘንድ የጽድቅ ደጅን ለእኔ ክፈቱልኝ "ያ ደጅ የእግዚአብሔር ነው ጻድቃን ወደ ውስጡ ይገቡበታል" አለ። ከእርሱ ጋር ያሉ ወንድሞችም "አባ ምን ትላለህ" አሉት። ቅዱስ ዮሐንስም "ሰባቱ የሰማይ ደጆች ለእኔ ተከፈቱልኝ የእኔን ነፍስ ይቀበሉ ዘንድ የሰማይ መላእክት እና ሁሉም የነቢያትና የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት ማኅበርተኞች ወደ እኔ መጡ" አላቸው። "አባቶቼ አቡነ ኤዎስጣቴዎስና ፊሊጶስ የቅዱሳን ማኅበርተኞች እና ሁሉም ገዳማውያን መነኰሳት ከአምላካቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እና ከጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ እኔ መጡ" አላቸው።

ይህንንም ከተናገራቸው በኋላ ከሽቶዎች ሁሉ ሽታው ፈጽሞ ውስጥ መዓዛ ያለው ሽታ ተመላ በእሑድ ቀን የሌሊቱ ሰዓት ሰባት ሰዓት በሆነ ጊዜ በመስቀል ምልክት ፊቱን አማተበና የከበረች ንጽሕት የሆነች ነፍሱ ከሥጋ ያን ጊዜ ወጣች መላእክትም በተወደደ ምስጋና "የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል" እያሉ አሳረጓት።

ተጋዳዮች ባሕታውያን ይህን በሰሙ ጊዜ ፈጽመው አደነቁ የዕረፍቱ ቀንም ኅዳር ዐሥራ ሦስት (13) ሆነ ልጆቹም ጥሩ አገናነዝን ገነዙት በሩቅና በቅርብ በየገዳማቱ ያሉ ወንድሞች መነኰሳትም ተሰበሰቡና ጓደኞቻቸው እስከሚረግጡ ድረስ ብዙ ጭንቅ ሆነ። ከአባታችን ከአቡነ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ከአቡነ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን።
                           
                           + + +
"#ሰላም_ለዮሐንስ_ገሣጼ_ሕዝብ አብዳን። በከሊአ ዝናም ወጠል መጠነ ሠለስቱ አዝማን። እንበይነ ዝንቱ ኃይልከ ኃይለ አንጥናን። #ትትሜሰል_በኤልያስ_ወበዮሐንስ ካህን። ወበቴስባን ትትሜሰል ቢዘን"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር_14።    
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ኅዳር_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 15
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ፦ ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?
¹³ ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤
¹⁴ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤
¹⁵ ደግሞም፦ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።
¹⁶ ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤
¹⁷ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።
¹⁸ እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ።
¹⁹ በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።
²⁰ አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።
²¹ ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና።
²² ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።
²³ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤
²⁴ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
⁷ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።
⁸ በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤
⁹ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
¹⁰ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።
¹¹ ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
¹² እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።
¹³ ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
¹⁴ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 23
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁶ ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ፦ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ።
⁷ ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ።
⁸ ሰዱቃውያን፦ ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ።
⁹ ታላቅ ጩኸትም ሆነ፥ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው፦ በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን? ብለው ተከራከሩ።
¹⁰ ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኅዳር_14_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ አቡየ ወእምየ ገደፋኒ። ወእግዚአብሔር ተወክፈኒ። ምርሀኒ እግዚኦ ፍኖተከ"። መዝ.26÷10-11
"አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ። አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ"። መዝ.26÷10-11
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ኀዳር_14_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ዮሐንስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁴⁷ እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደ መጣ ሰምቶ ልጁ ሊሞት ስላለው ወደ እርሱ ሄደ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው።
⁴⁸ ስለዚህም ኢየሱስ፦ ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም አለው።
⁴⁹ ሹሙም፦ ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ አለው።
⁵⁰ ኢየሱስም፦ ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ።
⁵¹ እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና፦ ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት።
⁵² እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እርሱም፦ ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት።
⁵³ አባቱም ኢየሱስ፦ ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ።
⁵⁴ ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው።

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
✝️የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ዳንኤል ገዳማዊ፣ የአባ መርትያኖስ ካልዕ፣ የአባ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን የዕረፍት በዓልና ቀዳሚት ሰንበት ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2025/01/04 03:46:07
Back to Top
HTML Embed Code: