Telegram Web Link
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³-¹⁴ ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ።
¹⁵ የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን?
¹⁶ በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው።
¹⁷ ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤
¹⁸ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም።
¹⁹ እንግዲህ፦ እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ ትል ይሆናል።
²⁰ መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ።
²¹ እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና።
²² እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ።
²³ እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና።
²⁴ አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ራእይ 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።
¹⁴ ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት።
¹⁵ እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ።
¹⁶ ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው።
¹⁷ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤
¹⁸ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ።
² ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው፦
³ ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት።
⁴ ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ፦
⁵ እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤
⁶ ይህንም ትኵር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ።
⁷ ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ።
⁸ እኔም፦ ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ ርኵስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና አልሁ።
⁹ ሁለተኛም፦ እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ።
¹⁰ ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ እንደ ገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ።
¹¹ እነሆም፥ ያን ጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ።
¹² መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_24_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ዓጸደ ወይን አፍለስከ እምግብፅ። ሰደድከ አሕዛበ ወተከልከ ኪያሃ። ወፄሕከ ፍኖተ ቅድሜሃ"። መዝ 79፥8-9።
"ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ። በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች"። መዝ 79፥8-9።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_24_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 21
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³³ ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
³⁴ የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ።
³⁵ ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት።
³⁶ ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው።
³⁷ በኋላ ግን፦ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው።
³⁸ ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ።
³⁹ ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።
⁴⁰ እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?
⁴¹ እነርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት።
⁴² ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን?
⁴³ ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።
⁴⁴ በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።
⁴⁵ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤
⁴⁶ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
 የሚቀደሰው የ #እመቤታችን_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የፀበለ ማርያምና የአባ ዘግሩም የመታሰቢያ በዓልና ዕለተ ሰንበትና የጽጌ ጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን #ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ) አረፈ፣ የመላእክት አምሳል የሆነ #አባ_እብሎይ አረፈ፣ የከበረ #ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው፣ የደብረ ሊባኖሱ #አባ_ሕፃን_ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቡነ_አቢብ (አባ ቡላ)

ጥቅምት ሃያ አምስት በዚህች ቀን ታላቅና ክብር የሆነ አቢብ የተባለ መስተጋድል አባ ቡላ አረፈ።

የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አብርሃም የእናቱም ስም ሐሪክ ነው እነርሱም ከሮሜ አገር ሉፊ ከሚባል አውራጃ ናቸው በዘመናቸውም ከሀዲው ንጉሥ መክስምያኖስ በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራ ስለ አመጣ ስደት ሁኖ ነበርና እነርሱም በስደት ብዙ ዘመን ኖሩ።

ልጅንም በአጡ ጊዜ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ በጾም በጸሎት ተወስነው ወደ #እግዚአብሔር ለመኑ የ #እግዚአብሔርም መልአክ በሕልም ተገለጠላቸውና ፍሬ የመላበትን ዘለላ ሰጣቸው።

ይህም ቅዱስ በተፀነሰ ጊዜ በቤታቸው አጠገብ ታላቅ ዛፍ በቀለ በቅጠሉም ላይ በሮማይስጥ ቋንቋ ቡላ የ #እግዚአብሔር አገልጋይ በጽዮንም አድሮ የሚኖር የያዕቆብ ፈጣሪ ያከበረው የሚል ጽሑፍ ነበረበት።

በተወለደም ጊዜ ክርስትና ሳያስነሡ ዓመት ሙሉ አኖሩት እመቤታችን #ማርያምም ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለሰለባስትርዮስ ተገልጣ ወደ አብርሃም ቤት ሒዶ ሕፃኑን እንዲአጠምቀው አዘዘችው እርሱም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው ስሙንም ቡላ ብሎ ሰየመው እናትና አባቱም ሳይነግሩት ቡላ ስለ ሰየመው አደነቁ ዕፁብ ዕፁብ አሉ።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ በጸለየ ጊዜ የቊርባን ኅብስትና ወይን የተመላ ጽዋ ከሰማይ ወረደ እርሱም ቀድሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ከሕፃኑ ጋር አቀበላቸው በዚያንም ጊዜ ሕፃኑ የአንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከ #ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ #አብ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት ከ #አብ#መንፈስ_ቅዱስ ጋር አንድ የሆነ #ወልድ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው በባሕርይ በህልውና በመለኮት በ #አብ#ወልድ ጋር አንድ የሆነ #መንፈስ_ቅዱስ በግብር በአካል በስም ልዩ ነው ብሎ ተናገረ።

ከጥቂት ዘመንም በኋላ አባትና እናቱ ኅዳር ሰባት ቀን ሙተው ሕፃኑ ብቻውን ቀረ።

ሕፃኑም ዐሥር ዓመት በሆነው ጊዜ ለጣዖት መስገድን የሚያዝ ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ቡላም በሰማ ጊዜ ወደ መኰንኑ ሒዶ የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ መኰንኑም በአካል ታናሽነቱን አይቶ እጅግ አደነቀ በዚያንም ጊዜ በችንካር እንዲቸነክሩት ሥጋውንም እንዲሠነጣጥቁት ቆዳውንም ከዐጥንቱ እንዲገፉ እጆቹንና እግሮቹንም በመጋዝ እንዲቆርጡ ጀርባውንም እንዲገርፉ በሾተሎችና በጦሮች መካከል አድርገው ከመንኰርኵር ውስጥ እንዲጨምሩት ዳግመኛም በመንገድ ላይ እንዲጐትቱት አዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳነው ያለ ጉዳትም ጤነኛ አደረገው።

ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ መኰንን ሒዶ እርሱንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገመ መኰንኑም ተቆጥቶ በሚያዝያ ወር ዐሥራ ስምንት ቀን ራሱን በሰይፍ ቆረጠው ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው ወደ አንድ ገዳምም ወስዶ የምንኲስና ልብስንና አስኬማን በ #መስቀልም ምልክት አለበሰው። እንዲህም አለው ከቅዱሳን ጻድቃን አንድነት ትሆን ዘንድ #እግዚአብሔር አዝዞሃል።

ያን ጊዜም ቅዱስ አባ ቡላ ከደረቅ ተራራ ላይ ወጣ ያለ ማቋረጥም በውስጧ እየተጋደለ ኖረ። የ #ጌታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስን መከራውንና ስቅለቱን በአሰበ ጊዜ ከረጅም ዕንጨት ላይ በመውጣት ራሱን ወደታች ሁል ጊዜ ይወረውር ነበር።

በአንዲትም ቀን ከዛፍ ላይ በተወረወረ ጊዜ ሰይጣን ሊገድለው ስለ በረታበት ሞተ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #መድኃኒታችን ከሞት አነሣውና እንዲህ አለው ከእንግዲህ ስምህ ቡላ አይሁን አቢብ ይባል እንጂ የብዙዎች አባት ትሆናለህና።

እርሱም የ #ክርስቶስን ፍቅር እጅግ ጨመረ ፊቱንም እየጸፋ ሥጋውን በየጥቂቱ እየቆረጠ ጀርባውንም ሰባት መቶ ጊዜ እየገረፈ ኖረ #ጌታችንም ይፈውሰው ነበር በየእሑድም ቀን ከቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያም እንደተወለደ በሌሎች ቀኖችም እንደተያዘና ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበለ ሁኖ ይገለጽለት ነበር።

ስለዚህም ሳይበላ ሳይጠጣ አርባ ሁለት ዓመት ኖረ ዳግመኛም ናላው ፈስሶ እስቲአልቅ ዐሥራ ሁለት ወር በራሱ ተተክሎ ኖረ። በአንዲትም ቀን የ #ጌታችንን መከራ በአሰበ ጊዜ ሰይፉን በአንጻሩ ተከለ ከዕንጨት ላይም ወጥቶ በላዩ ወድቆ ሞተ ቅድስት ድንግል እመቤታችን #ማርያምም ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥታ የእኔና የልጄ ወዳጅ ሰላምታ ይድረስህ አለችው ። ከበድኑም ቃል ወጥቶ የሰማይና የምድር ንግሥት #እመቤቴ ሰላምታ ይገባሻል አላት እርሷም በከበሩ እጆቿ ዳሥሣ ከሞት አስነሣቸው።

ዕድሜውንም ፈጽሞ ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእጁ ልዩ የሆኑ አክሊሎችን የሚያበሩ ልብሶችንም ይዞ ተገለጠለት ወዳጄ አቢብ ሆይ በማያልቅ ተድላ ደስታ ደስ አሰኝህ ዘንድ ወደእኔ ና ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ እኔ ኃጢአቱን አስተሠርይለት ዘንደ በራሴ ማልኩልህ ወይም ለተራቆተ የሚያለብሰውን ለተራበም የሚያጠግበውን ለተጠማ የሚያጠጣውን የገድልህን መጽሐፍም የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውንና የሚሰማውን በጸሎትህም የሚታመኑትን ሁሉ እስከ ዐሥር ትውልድ እምራቸዋለሁ ይህንም ብሎ አፉን ሳመው በደረቱም ላይ አድርጎ ወደአየር አወጣው የመላእክትንም ምስጋና በሰማች ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ገባች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አቡነ አቢብ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_እብሎይ

ዳግመኛም በዚህችም ቀን ደግሞ አክሚም ከሚባል አገር የመላእክት አምሳል የሆነ አባ እብሎይ አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አሞኒ የእናቱ ስም ሙስያ ነው ሁለቱም በ #እግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሆኑ በሕጉ ጸንተው የሚኖሩ ድኆችንና መጻተኞችን የሚወዱ የሚረዱ ናቸው።

ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም ሙስያም ዕንጨት የያዘ ብርሃናዊ ሰው በቤቷ ውስጥ ሲተክለውና ወዲያውኑ ለምልሞ አብቦ ሲያፈራ ያ ብርሃናዊው ሰውም ከዚህ ፍሬ የሚበላ ሁሉ ለዘላለም ይኖራል ሲላት እርሷም ከፍሬው ወስዳ ስትበላና በአፏ ውስጥ ጣፋጭ ሲሆንላት በልቧም ፍሬ ይሆንልኝ ይሆን ስትል ራእይን አየች።

ከእንቅልፏም በነቃች ጊዜ ራእይን እንዳየች ለባሏ ነገረችው እርሱም እርሷ እንዳየችው ያለ ማየቱን ነገራት #እግዚአብሔርንም አብዝተው አመሰገኑት ትሩፋትንና ተጋድሎን በመጨመር በየሁለት ቀን የሚጾሙ ሆኑ ምግባቸውም እንጀራና ጨው ነው።

ይህን ቅዱስ እብሎይን በፀነሰችው ጊዜ እናቱ በገድል ወንዶችን እስከምታሸንፍ ድረስ በየሌሊቱ ሁሉ አንድ ሽህ ስግደትን ትሰግዳለች ሕፃኑን እስከ ወለደችው ድረስ ዘጠኝ ወር ያህል እንዲህ ስትጋደል ኖረች።

በወለዱትም ጊዜ እብሎይ ብለው ሰየሙት በጐለመሰም ጊዜ የምንኩስናን ልብስ ሊለብስ ወደደ ምክንያትም እስቲያገኝ እንዲህ ኖረ አቢብ የሚባል ወዳጅ ነበረውና እርሱ በሌሊት ወሰደው ከላዕላይ ግብጽ በሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ መነኰሰ በገድልም በመጠመድ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
ከጥቂት ወራትም በኋላ በጥቅምት ወር ሃያ አምስት ቀን አባ አቢብ አረፈ ያን ጊዜ አባ እብሎይ አብሎግ ወደሚባል ገዳም ሔደ ወደርሱም ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እርሱም በበጎ አምልኮ #እግዚአብሔርን መፍራትን የሚያስተምራቸው ሆነ።

ቅዱስ አቢብም በአረፈበት ቀን መታሰቢያውን ሲያደርጉ ይህ ቅዱስ አባ አብሎይ ወንድሞች ሆይ በአባ አቢብ ስም ዛሬ ጸሎትን የሚጸልየውን ኃጢአቱን #እግዚአብሔር ያስተሰርይለታል በዕረፍትህ መታሰቢያ ቀን የአባ አቢብ ፈጣሪ ሆይ ኃጢአቴን ሁሉ ተውልኝ ብሎ አንዲት ጸሎትን የሚጸልየውን ሁሉ እኔ ኃጢአቱን እተውለታለሁ ሲል ቃል ኪዳን ሰጥቶታልና አላቸው።

በዚያችም ሰዓት ከመነኰሳት አንዱ አረፈ እነርሱም ሊገንዙት በዚያ ቁመው ሳሉ አባ እብሎይ ስለ ተናገረው ቃል ከመነኰሳት አንዱ ተጠራጠረ በዚያንም ጊዜ ያ የሞተው ተነሥቶ ይናገር ዘንድ ጀመረ አባ እብሎይ ስለተናገረው ቃል ለምን ትጠራጠራላችሁ ለአባታችን አቢብ በመታሰቢያው ቀን በዚህ ቃል ኪዳን #እግዚአብሔር ሰጥቶናልና አላቸው ። ይህንንም ብሎ ተመልሶ አረፈ መነኰሳቱም አደነቁ ምስጉን #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ይህ አባ እብሎይም ብዙ ዘመናት ኖረ ልጆቹ መነኰሳትም በዙ ብዙ ገዳማትም ተሠሩለት። የኖረበትም ዘመኑ በታላቁ አባ መቃርስ ዘመን ነው የአባ እብሎይንም የትሩፋቱን ዜና አባ መቃርስ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ተሰኘበት እርሱን እያጽናና እያረጋጋ መነኰሳት ልጆቹንም #እግዚአብሔር የሚወደውን በመሥራት ያጸናቸው ዘንድ መልእክትን ጻፈለት።

ይህንንም በአስቄጥስ ገዳም ሁኖ አባ መቃርስ ሲጽፍ አባ እብሎይ በላዕላይ ግብጽ ሳለ በ #መንፈስ_ቅዱስ አውቆ በዙሪያው ያሉትን መነኰሳት እንዲህ አላቸው። እነሆ ማጽናናትን የተመላች መልእክትን አባ መቃርስ ጻፈልን። ከዚህም በኋላ ከአባ መቃርስ ዘንድ የተላኩትን መነኰሳት ሁሉ ወጥተው በደስታ ተቀብለው አስገቧቸው መልእክቱንም በመነኮሳቱ ሁሉ ፊት አነበቡ በታላቅ ደስታም ደስ አላቸው።

ይህም አባ እብሎይ ወደ አባ አሞንዮስ የሔደ ከእርሱ ዘንድም የምትኖረውን ስሟ የዋሂት የተባለችውን የተቀደሰች ሴት ያየ ነው። ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወዶ በየካቲት ወር በአምስተኛው ቀን አረፈ እኛ ግን የአባ እብሎይን ዜና ከወዳጁ ከአባ አቢብ ጋር ጻፍን።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አባ እብሎይ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮልዮስ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ዳግመኛ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ሰማዕት ለሆነ ለቅዱስ ዮልዮስ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ነው።

ይህም ቅዱስ ዮልዮስ በሀገረ ጥዋ በሰማዕትነት በአረፈ ጊዜ በገድሉ እንደተጻፈ ዲዮቅልጥያኖስ ከጠፋ በኋላ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ሳይጠመቅ ነገሠላቸው በጥቂት ወራትም የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንም ሥልጣን ከፍ ከፍ አለ ከሀድያን ነገሥታት ለገደሏቸው ንጹሐን ሰማዕታት በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት ታነፁ።

ስለ ቅዱሳን ሰማዕታትም ስለ ሥጋቸው እንዲአስብ ገንዞ በመሸከም ወደ አገራቸው እንዲአደርሳቸው ከአገልጋዮቹም ጋር ገድላቸውን እንዲጽፍ #እግዚአብሔር እንደአቆመውና እንደጠበቀው ከዚህም እርሱ ራሱ በሰማዕትነት እንዴት እንደ ሞተ የቅዱስ ዮልዮስን ዜና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በሰማ ጊዜ ስለበጎ ተጋድሎው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ቅዱስ ዮልዮስን አመሰገነው ።

ስለዚህም ለቅዱስ ዮልዮስ ያማረች ቤተ ክርስቲያን በግብጽ አገር ሠርተው ሥጋውን በውስጧ ያኖሩ ዘንድ ንጉሡ ወደ ግብጽ አገር ብዙ ገንዘብ ላከ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ እንዳዘዘ አነፁለት ። የቅዱስ ዮልዮስንም ሥጋ አፍልሰው በውስጧ አኖሩት ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስም ከኤጲስቆጶሳቱ ጋር አከበራት እንደዛሬዪቱም ቀን በዓል አከበረባት ከሥጋውም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ዮልዮስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሕጻን_ሞዐ_ዘደብረ_ሊባኖስ

በዚህችም ቀን የደብረ ሊባኖሱ አባ ሕፃን ሞዐ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ነው። በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡

እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜናማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡

ከ47ቱ የሀገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸው በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወሰ ነው፡፡

ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የ2 ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ 25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_25 እና #ከገደላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ጥቅምት_25_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ኤፌሶን 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴-¹⁵ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤
¹⁶ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤
¹⁷ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
¹⁸ በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤
¹⁹ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤
²⁰ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ።
²¹ ነገር ግን እናንተ ደግሞ እንዴት እንዳለሁ ኑሮዬን እንድታውቁ የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ያስታውቃችኋል፤
²² ወሬአችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው።
²³ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን።
²⁴ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 3
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁰ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤
¹¹ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤
¹² የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
¹³ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?
¹⁴ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥
¹⁵ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
¹⁶ በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ።
¹⁷ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና።
¹⁸ ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 11
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤
²⁴ ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ።
²⁵ በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ መጣ፤
²⁶ ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፥ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_25_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇🌹

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ። ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ። ትኩላን እምንቱ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር"። መዝ.91፥12-13።
"ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ"። መዝ.91፥12-13።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ጥቅምት_25_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤
² አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦
³ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
⁴ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።
⁵ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
⁶ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
⁷ የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
⁸ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
⁹ የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
¹⁰ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
¹¹ ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
¹² ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
¹³ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
¹⁴ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
¹⁵ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።
¹⁶ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️ 🌹
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ሠለስቱ_ምዕት_ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ቡላ አቢቡ የዕረፍት በዓልና የጽጌ ጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ነገ በ25 የሚጸለይ


☞ከመዝ በሉ፦

. . . ይቤ . . .
በስምየ ወበስመ አቢብ ገብርየ፤
አኃድግ ሎቱ ዘገብረ ጌጋየ

!https://www.tg-me.com/zikirekdusn
🌹እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን🌹

‹‹ #በእንተ_አቡነ_አቢብ !››

እነሆ ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ምእመናን በሚቀምሱት የዕለት ምግብ አማካኝነት በነፍስም በሥጋም እንዲድኑ አስገራሚ የምሕረት ቃልኪዳን እንደተቀበሉ የሚናገር የገድል ተአምራታቸው ይህ ነው፡- ብዙዎች ስማቸውን ጠርተው በሚቀምሱት ምግብ አማካኝነት ከተለያዩ በሽታዎች የተፈወሱ አሉ፡፡ ይህ ቃልኪዳናቸው ለኹላችን ይደረግን ዘንድ ከመመገባችን አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም እንጥራ (አቡነ ዘበሰማያትን ማለቱ ነው፡፡) ከተመገብን በኋላም የዕለት ምግባችንን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እናመስግን፡፡ ዘወትር ከተመገብን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹ስለ ወዳጅህ ስለ አቡነ አቢብ›› እያልን ሦስት ጊዜ እንቅመስ፡፡ አስቀድሞ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ አቢብ ተገልጦላቸው ‹‹…ወዳጄ አቢብ ሆይ! የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበልኩትን ሕማማተ መስቀል እያሰብህ ይህንን ሁሉ ገድል ፈጽመሃልና ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ ንዑድ ክቡር ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብም ‹‹ጌታዬ አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መቼም ሰው ሁሉ ሳይመገብ አይውልም አያድርምና በተመገበ ጊዜ ስሜን ጠርቶ የተማጸነውን ማርልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አባታችን አቡነ አቢብ ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅር ካደነቀ በኋላ ‹‹…ከማዕድ በኋላ ስብሃት ተብሎ የተረፈውን ‹በእንተ አቢብ› ብሎ ሦስት ጊዜ የተመሰገበውን ሰው ሁሉ እምርልሃለሁ›› በማለት ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ያልተጠመቀ አረማዊ አሕዛብም እንኳን ቢሆኖ "ስለ አቡነ አቢብ" ብሎ ከተማጸነ ጌታችንን ያንን ሰው ወደቀናች የእምነት መንገድ ሳይመራወና በንስሓ ሳይጠራው በሞት እንደማይወስደው ለአባታችን ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ለማዳን ትንሽ ምክንያትን የሚፈልግ ያለ ምክንያትም የማያድን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ እስከዘላለም ድረስ ይክበር ይመስገን!
ሰው ተመግቦ እንኳን መዳን እንዲችል ይህን ድንቅ ቃልኪዳን ለአባታችን ሰጥቷቸዋልና በየቀኑ በዚህ ቃልኪዳን እንጠቀምበት፡፡ ተመግበን ከጨረስንና ስብሃት ካልን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹በእንተ አቡነ አቢብ›› ብለን እንቅመስ፡፡

በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 25 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው የሚውሉት ጻድቁና ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ከቃልኪዳናቸው ረድኤት በረከት ይክፈሉን!

‹‹ #በእንተ_አቡነ_አቢብ !››

(ደብረ ሰላም ቃጭልቃ አቡነ አቢብ ገዳም ያሳተመው ገድለ አቡነ አቢብ፣ ገጽ 105)
2024/12/25 08:01:38
Back to Top
HTML Embed Code: